በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ቅርጽ የሌላትና ባዶ ነበረች፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ “ብርሃን ይሁን” ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንደኛ ቀን። እግዚአብሔርም፦ “በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል” አለ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፥ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም፦ “ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፥ በአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ “ባሕር” አለው፥ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም፦ “ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድር ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል” አለ፥ እንዲሁም ሆነ። ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን። እግዚአብሔርም አለ፦ “ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፥ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፥ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፥” እንዲሁም ሆነ። እግዚእብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፥ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፥ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። እግዚአሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፥ በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፥ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን። እግዚአብሔርም አለ፦ “ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።” እግዚእብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውን ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፥ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚእብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፦ “ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፥ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።” ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን። እግዚአብሔርም አለ፦ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፥” እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፥ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም አለ፦ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፥ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፥ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፥ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፥ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። እግዚአብሔርም አለ፦ “እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፥” እንዲሁም ሆነ። እግዚእብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። ሰማያትና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ እነሆ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፥ ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም። ጌታ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን፥ የሰማያትና ምድር ልደት፥ በተፈጠሩበት ጊዜ፥ እንዲህ ነበር። የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ከመኖሩ በፊት፥ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ከመብቀሉ በፊት፥ ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም። ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር። ከዚህ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፥ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ጌታ እግዚአብሔርም፥ በስተ ምሥራቅ፥ በዔድን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያ አኖረው። በዚያም፥ ጌታ እግዚአብሔር ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፥ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ። ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፥ ይህም ወንዝ ከዔደን ከወጣ በኋላ በአራት ወንዞች ይከፈላል። የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፥ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የሐዊላን ምድር ይከብባል፥ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፥ ሉልና የከበረም ድንጋይ በዚያ ይገኛል። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፥ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል። የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፥ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። ጌታ እግዚአብሔርም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔደን ገነት አኖረው። ከዚያም ጌታ እግዚአብሔር ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፥ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” ጌታ እግዚእብሔርም፦ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፥ የምትሆነውን ረዳት እፈጥርለታለሁ” አለ። የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ፥ ጌታ እግዚአብሔር፥ ከምድር ፈጠረ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፥ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፥ ነገር ግን አዳም ለእርሱ ሁነኛ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። ጌታ እግዚአብሔርም አዳምን ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጎኑ አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። ከአዳም የወሰዳትንም አጥንት፥ ጌታ እግዚእብሔር፥ ሴት አድርጎ ሠራት፥ ወደ አዳምም አመጣለት። አዳምም አለ፥ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ የተገኘች ናት፥ ከሥጋዬም የተገኘች ሥጋ ናት፤ ሴት ተብላ ትጠራ፥ ከወንድ የተገኘች ስለ ሆነች ‘ሴት’ ትባል” አለ። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩምም ነበር። ጌታ እግዚአብሔርም ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ እባብ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም፦ “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ አንዳች እንዳትበሉ አዝዞአልን?” አላት። ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ “በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ ልንበላ እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፥ አትንኩትም።’” ብሏል። እባብ ግን ለሴቲቱ አላት፦ “በፍጹም አትሞቱም፥ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንደሚከፈቱ፥ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።” ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ጥበብ ለማግኘትም የሚመኙት እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፥ ስለዚህ የበለስን ቅጠሎች ሰፍተው በማገልደም እርቃናቸውን ሸፈኑ። ቀኑ በመሸ ጊዜ፥ የጌታ እግዚአብሔርን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፥ አዳምና ሚስቱ ከጌታ እግዚእብሔር ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። ጌታ እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ፦ “ወዴት ነህ?” አለው። እርሱም፥ “በገነት ድምጽህን ሰማሁ፥ ዕራቁቴንም ስለ ሆንኩ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም።” አለ። እግዚእብሔርም፦ “ዕራቁትህን እንደሆንህ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ ከእርሱ በላህን?” አለው። አዳምም፦ “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኽኝ ሴት እርሷ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። ጌታ እግዚአብሔርም ሴቲቱን፦ “ይህ ያደረግሽው ምንድነው?” አላት። ሴቲቱም፥ “እባብ አሳተኝና በላሁ” አለች። ጌታ እግዚአብሔርም እባቡን አለው፦ “ይህን በማድረግህ፥ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አፈርን ትበላለህ። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ “በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፥ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ።” ለሴቲቱም አላት፥ “በእርግዝናሽ ወራት ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፥ በጭንቅ ትወልጃለሽ፥ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍላጎትሽ ለባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” አዳምንም አለው፦ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም ከእርሱ በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፥ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ፤ “እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፥ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።” “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በግንባርህ ላብ እንጀራን ትበላለህ፥ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ።” አዳምም ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ፤ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። ጌታ እግዚአብሔርም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። ከዚያም ጌታ እግዚአብሔርም፥ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፥ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር”፥ አለ። ስለዚህ፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ፥ ጌታ እግዚአብሔር ከዔድን ገነት አስወጣው። አዳምንም ካስወጣው በኋላ፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በሁሉም አቅጣጫ የምትውለበለብ ነበልባላዊ ሰይፍን በዔድን ገነት በስተ ምሥራቅ አስቀመጠ። አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፥ እሷም ፀነሰች፥ ቃየንንም ወለደች። እርሷም፦ “ወንድ ልጅ በጌታ ርዳታ አገኘሁ” አለች። ደግሞም፥ ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፥ ቃየንም መሬትን የሚያርስ ነበረ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለጌታ መሥዋዕትን አቀረበ፥ እንዲሁም አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። ጌታም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፥ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተቈጣ፥ ፊቱም ጠቆረ። ጌታም ቃየንን አለው፦ “ስለምን ተናደድህ? ፊትህስ ለምን ጠቆረ? መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፥ ፍላጎትዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርሷ ልትሰለጥንባት ይገባል።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፥ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳም ሳሉ፥ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም። ጌታም ቃየንን፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። እርሱም፥ “አላውቅም፥ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ። ጌታም ቃየልን እንዲህ አለው፥ “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየንም ጌታን አለው፦ “ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፥ ከፊትህም እሰወራለሁ፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፥ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም ለእርሱ፥ “እንዲህስ አይሆንም! ማንም ቃየንን የሚገድል፥ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ጌታም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ከዚያም ቃየን ከጌታ ፊት ወጣ፥ ከዔድንም በስተ ምሥራቅ፥ በኖድም ምድር ተቀመጠ። ቃየንም ሚስቱን አወቀ፥ ፀነሰችም፥ ሔኖክንም ወለደች፤ ከተማም መሠረተ፤ ከተማይቱንም በልጁም ስም “ሔኖክ” ብሎ ጠራት። ሔኖክ ዒራድን ወለደ፤ ዒራድ መሑያኤልን ወለደ፤ መሑያኤል መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤልም ላሜሕን ወለደ፤ ላሜሕም ሁለት ሚስቶችን አገባ፥ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ጺላ ነበረ። ዓዳም ያባልን ወለደች፥ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፥ እርሱም በገናንና ዋሽንትን ለሚይዙ አባት ነበረ። ጺላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። ላሜሕም ለሚስቶቹ፥ “ዓዳ እና ጺላ፥ እስቲ አድምጡኝ፥ እናንት የላሜሕ ሚስቶች ሆይ፥ የምለውን ስሙኝ፤ ቢያቆስለኝ ጐልማሳውን ገደልኩ ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገደልኩ፤ “ከሆነ ቃየልን ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት፥ ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።” አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም፥ “ቃየን በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል” ስትል ሤት አለችው። ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም የጌታ ስም በሰው መጠራት ተጀመረ። የአዳም የዘር ሐረግ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረ ጊዜ በእግዚአብሔር አምሳያ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። በተፈጠሩም ጊዜ “ሰው” ብሎ ጠራቸው። አዳምም መቶ ሠላሳ ዓመት ሲኖር፥ እሱን የሚመስል፥ አምሳያው የሆነ፥ የልጅ አባት ሆነ፤ ሤት ብሎም ስም አወጣለት። ሤትንም ከወለደ በኋላ አዳም ስምንት መቶ ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። አዳምም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ሤትም አንድ መቶ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሄኖስንም ወለደ፤ ሄኖስን ከወለደ በኋላ ሤት ስምንት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ሤትም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ሄኖስም ዘጠና ዓመት ሲሆነው፥ ቃይናንንም ወለደ፥ ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ ስምንት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ሄኖስም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምስት ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ቃይናንም ሰባ ዓመት ሲሆነው፥ መላልኤልን ወለደ፥ ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ ስምንት መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ቃይናንም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ዐሥር ዓመት ሆነ፥ ሞተም። መላልኤልም ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ያሬድንም ወለደ፥ መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ ስምንት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ያሬድም መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሄኖክንም ወለደ፥ ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ ስምንት መቶ ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ያሬድም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ሄኖክም ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ማቱሳላንም ወለደ፥ ከዚህ በኋላ ሔኖክ ማቱሳለን ወለደ፥ የእግዚአብሔርንም መንገድ በመከተል 300 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤። ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ። አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ፥ እግዚአብሔር ወስዶታልና፥ ሄኖክ አልተገኘም። ማቱሳላም መቶ ሰማኒያ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ላሜሕንም ወለደ፤ ላሜሕን ከወለደ በኋላ ማቱሳላ የኖረው ሰባት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ወንድ ልጅም ወለደ። ስሙንም፥ “ጌታ በረገማት ምድር፥ ከሥራችን እና ከእጅ ድካማችን፥ ይህ ያሳርፈናል” ሲል፥ ኖኅ ብሎ ጠራው። ኖኅንም ከወለደ በኋላ ላሜሕ አምስት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንድ እና ሴት ልጆችም ወለደ። ላሜሕ የኖረበት ዘመን ሁሉ ሰባት መቶ ሰባ ሰባት ዓመት ሆነ፥ ሞተም። ኖኅም ሴምን፥ ካምን እና ያፌትን ወለደ፤ ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ። የሰው ዘር በምድር ላይ እየበዛ በሄደ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱ፥ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፥ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። ጌታም፦ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፥ እድሜውም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናል” አለ። በዚያን ዘመን ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፥ እና ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፥ እነርሱም በዱሮ ዘመን፥ ስማቸው የታወቀ፥ ኃያላን ሆኑ። ጌታም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩም ጌታ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። በዚህ ምክንያት ጌታ፥ “ከምድር ላይ የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ሰው እና አራዊትን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን እና የሰማይ አእዋፍንም፥ ስለ ፈጠርኳቸው ተጸጽቼአለሁና” አለ። ይሁን እንጂ ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንደሚከተለው ነው። ኖኅም ጻድቅ፥ በትውልዱም በደል ያልተገኘበት ሰው ነበረ፥ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። በዚያን ጊዜ ምድር በእግዚአብሔር ፊት የተበላሸች ነበረች፥ ምድርም ግፍን ተሞላች። እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በምድር ላይ መንገዳቸውን አበላሽተው ነበርና፥ ምድር የተበላሸች ነበረች። እግዚእብሔርም ኖኅን አለው፦ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፥ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፥ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ለአንተ ከጎፈር እንጨት መርከብን ሥራ፥ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፥ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ አድርግ፤ ለመርከቢቱም ጣራን አብጅለት፤ ከቁመትዋም አርባ አራት ሳንቲ ሜትር ትተህ ጨርሳት፥ መርከቡ ባለ ሦስት ፎቅ እንዲሆን አድርግ፤ በጎኑም በኩል በር አድርግለት። እነሆ፥ እኔ ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት፥ በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፥ በምድር ያለ ሁሉ ይጠፋል። ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፥ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ይዘህ ወደ መርከቡ ትገባለህ። ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታስገባለህ፥ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። እንዲሁም ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።” ኖኅም እንዲሁ አደረገ፥ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ጌታም ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ዘመን ካለው ትውልድ መካከል ጻድቅ አንተ ሆነህ አይቼሃለሁና፥ አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ። ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት፤ ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ። የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ ለማጥፋት ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ።” ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ ዓመት ነበረ። ኖኅ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥ ጥንድ ተባዕትና እንስት እየሆኑ፥ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ ገቡ። ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ ስድስት መቶ ዓመት በሆነው፥ በሁለተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ፥ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ጥልቅ መፍለቂያዎች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፥ የሰማያትም መስኮቶች ተከፈቱ፥ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ። በዚያውም ቀን ኖኅ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም፥ ካም፥ ያፌትና የኖኅ ሚስት፥ ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ወደ መርከብ ገቡ። ከእነርሱ ጋር፥ ከአራዊት፥ ከእንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበርሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ። በዚህ ዓይነት እስትንፋስ ካላቸው ፍጥረቶች ከእያንዳንዱ ዓይነት ሁለት ሁለት እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ፤ ፍጥረት ሁሉ ወንድና ሴት ሆነው ወደ መርከቡ የገቡት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ ጌታም በስተ ኋላው ዘጋበት። የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን አላቋረጠም፥ ውኃውም በዛ፥ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም በላይ ከፍ አለች። ውሃ በምድር ላይ እያደገና እየበረታ በሄደ መጠን መርከቡ በውሃው ላይ መንሳፈፍ ጀመረ። ውሃውም ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራራዎችን እንኳ እስከሚሸፍን ድረስ ጥልቅ ሆነ። ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ ሰባት ሜትር ያኽል ከፍ አለ። ወፎችና እንስሶች፥ አራዊት፥ ሰዎችም ሁሉ ሞቱ። በምድር ላይ ያሉት ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ጠፉ። በምድር ላይ የሚኖር የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ። እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን ሕያው ፍጥረት ሁሉ፥ ሰዎችንም፥ እንስሶችንም፥ ወፎችንም፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሳይቀሩ ሁሉንም አጠፋ። ከሞት የተረፉት ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ብቻ ነበሩ። ውሃውም እስከ መቶ ኀምሳ ቀን አልጐደለም ነበር። እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ። ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፥ ውኃውም ጎደለ፥ ከምድር በታች ያሉት ታላቅ የውሃ መፍለቂያዎች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈች። ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበረ፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ተገለጡ። ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ ቁራንም ወደ ውጪ ላከው፤ እርሱም ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። ርግብም ወደ ማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እነሆም፥ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው መጉደሉን አወቀ። ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ ሳትመለስለት ቀረች። የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ አንድ በሆነ ጊዜ፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፤ ምድሪቱ እንደ ደረቀች አየ። በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ፈጽማ ደረቀች። እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ አለው፦ “አንተ ከሚስትህ፥ ከልጆችህና ከልጆችህ ሚስቶች ጋር ሆነህ ከመርከቡ ውጣ፤ ተራብተውና ተባዝተው ምድርን ሁሉ እንዲሞሉ ከአንተ ጋር ያሉትን ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ወፎችን፥ እንስሶችንና ሌሎችን በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ ይዘህ ውጣ።” ከዚህ በኋላ ኖኅ ከሚስቱ፥ ከልጆቹና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ሆኖ ከመርከቡ ወጣ፤ አራዊትና እንስሶች፥ ወፎችም በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችም በየወገናቸው ሆነው ከመርከቡ ወጡ። ኖኅም ለጌታ መሠውያን ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ከየዓይነቱ አንዳንድ ወሰደ፤ መሥዋዕት እንዲሆኑም ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠላቸው። የመሥዋዕቱም መዓዛ ጌታን ደስ አሰኘው፤ ጌታም በሐሳቡ እንዲህ አለ፥ “ገና ከታናሽነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው ሐሳብ ክፉ ነውና፥ ሰው በሚፈጽመው በደል ምክንያት ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም። በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።” እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት። እንስሶች፥ ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና ዓሣዎች ሁሉ እናንተን በመፍራትና በመደንገጥ ይኑሩ፤ ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ። ከዚህ በፊት የአትክልት ዓይነቶችን ምግብ አድርጌ እንደሰጠኋችሁ እነዚህንም ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ምግብ እንዲሆኑአችሁ ሰጥቻችኋለሁ። ነገር ግን ደም ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፥ ምክንያቱም በደም ውስጥ ሕይወት አለ። ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፥ ከአራዊት እና ከሰውም ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳያ ስለ ሆነ፥ ሰውን የሚገድል ሁሉ በሰው እጅ ይሞታል። እናንተ ፍሬያማ ሆናችሁ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔርም ለኖኅ፥ ከእርሱም ጋር ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እነሆ፥ እኔም ቃል ኪዳኔን ከእናንተ ጋር፥ ከእናንተም በኋላ ከዘራችሁ ጋር እመሠርታለሁ፤ ይህም ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት አእዋፍ፥ ለእንስሳትም፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለየትኛውም የምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል። ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ እመሰርታለሁ፥ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፉም፥ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይመጣም።” እንዲህም ሲል እግዚአብሔር ተናገረ፦ “በእኔና በእናንተ፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም የማደርገው፥ የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፥ ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ፥ ይህም በእኔና በምድር መካከል የቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ምድር በደመና በምትሸፈንበት ቀስቲቱም በደመናው በምትታይበት ጊዜ፥ በእኔና በእናንተ፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ፍጥረት መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ውኃም ዳግመኛ ፍጥረትን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ የውኃ ሙላት አይመጣም። ቀስቲቱም በደመና ስትሆን፥ አያታለሁም በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ነው” አለው። ከመርከቡ የወጡት የኖኅ ልጆች ሴም፥ ካምና ያፌት ናቸው፤ ካም የከነዓን አባት ነው። በምድር ሁሉ ላይ የተበተኑ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው። ኖኅ ቀዳሚ ገበሬ ነበረ፤ የወይን ተክልንም ተከለ። ከዕለታት አንድ ቀን ከወይን ጠጁም ጠጣ፥ ሰከረም፥ በድንኳኑም ውስጥ እራቁቱን ተኛ። የከነዓን አባት፥ ካምም፥ የአባቱን ዕራቁቱን መሆን አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ልብስ በትከሻቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ፥ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ። እንዲህም አለ፦ “ከነዓን የተረገመ ይሁን! ለወንድሞቹም የባርያዎች ባርያ ይሁን።” ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የሴም ጌታ እግዚእብሔር ይባረክ! ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን! “እግዚአብሔርም ያፌትን ያደርጀው! በሴምም ድንኳን ይደር! ከነዓንም የያፌት አገልጋይ ይሁን!” ከጥፋት ውኃ በኋላም ኖኅ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ። ኖኅም የኖረበት ዘመን በአጠቃላይ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፥ ሞተም። የኖኅ ልጆች የሴም፥ የካም፥ እና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፥ ከጥፋት ውኃም በኋላ ልጆችን ወለዱ። የያፌት ልጆች፦ ጎሜር፥ ማጎግ፥ ማዳይ፥ ያዋን፥ ቱባል፥ ሜሼክ እና ቲራስ ናቸው። የጎሜር ልጆች፦ አሽከናዝ፥ ሪፋት እና ቶጋርማ ናቸው። የያዋን ልጆች፦ የኤሊሻ፥ የተርሴስ፥ የኪቲምና የሮዳኒም ሰዎች ናቸው። ከእነዚህም በባሕር ዳርቻ ሕዝቦች፥ ሁሉም በየምድራቸው፥ በየቋንቋቸው፥ በየነገዳቸው፥ በየሕዝባቸው ተከፋፍለው የሚኖሩ የያፌት ልጆች ዘር ናቸው። የካም ልጆች፦ ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ እና ከነዓን ናቸው። የኩሽ ልጆች፦ ሳባ፥ ሐዊላ፥ ሳብታ፥ ራዕማ እና ሳብተካ ናቸው። የራማ ልጆች፥ ሳባ እና ደዳን ናቸው። ኩሽም ናምሩድን ወለደ፥ እርሱም በምድር ላይ ቀዳሚው ኃያል ጦረኛ ነበረ። በጌታ ፊት ናምሩድ ኃያል አዳኝ ነበረ፥ ስለዚህም፦ “እንደ ናምሩድ በጌታ ፊት ኃያል አዳኝ” ይባላል። የእሱም ግዛት መነሻ፥ ሁሉም በሰናዖር አገር የነበሩት፥ ባቢሎን፥ ኤሬክን፥ አካድ፥ እና ካልኔ ናቸው። ከዚያም ወደ አሦር ሄደና ነነዌን፥ ረሆቦትን፥ ካላሕን መሠረተ፤ እንዲሁም በነነዌና በካላሕ መካከልም ሬሴን መሠረተ፥ እርሷም ታላቂቱ ከተማ ናት። የምጽራይም ዘሮች ሉድ፥ ዐናማውያን፥ ለሃባውያን፥ ናፍሐውያን፥ ፈትሮሳውያን፥ ከስሉሃውያን (ከእነርሱም ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው)፥ እና የካፍቶር ሕዝቦች ናቸው። የከነዓን ልጆች በኲሩ ጺዶን፥ ተከታዩ ሔት ይባሉ ነበር፤ ሌሎቹም የከነዓን ዘሮች ኢያቡሳውያን፥ አሞራውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያን፥ ዓርቃውያን፥ ሲናውያን፥ አርዋዳውያን፥ ጸማራውያን፥ ሐማታውያን ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የከነዓናውያን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤ በዚህ ዓይነት የከነዓናውያን ድንበር ከሲዶና አንሥቶ፥ በገራር አጠገብ እስካለው እስከ ጋዛ ድረስ፥ ወደ ሰዶም እና ገሞራ፥ አዳማና በላሻዕ አጠገብ እስካለው እስከ ጸቦይም ድረስ ይደርሳል። የካም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። ለሴምም ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፥ እርሱም የያፌት ታላቅ ወንድምና የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅድመ አያት ነው። የሴም ልጆች፦ ዔላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ እና አራም ናቸው። የአራም ልጆች፦ ዑፅ፥ ሑል፥ ጌተር እና ሜሼክ ናቸው። አርፋክስድ ሼላሕን ወለደ፤ ሼላሕም ዔቦርን ወለደ። ዔቦር ሁለት ልጆች ወለደ፤ አንደኛው እርሱ በተወለደበት ዘመን ሕዝቦች ስለ ተከፋፈሉ ፋሌቅ ተባለ፤ ሌላው ዮቅጣን ይባል ነበር። የዮቅጣን ልጆች፦ አልሞዳድ፥ ሼሌፍ ሐጻርማዌት፥ ዬራሕ፥ ሀዶራም፥ ኡዛል፥ ዲቅላ፥ ዖባል፥ አቢማኤል፥ ሳባ፥ ኦፊር፥ ሐዊላና ዮባብ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ዘሮች ናቸው። እነርሱ የኖሩበት ግዛት በስተ ምሥራቅ ባለው በተራራማው አገር ከሜሻ እስከ ሰፋር ይደርስ ነበር። የሴም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። ከጥፋት ውሃ በኋላ የምድር ሕዝቦች፥ እነዚህ በየነገዳቸው የተከፋፈሉ የኖኅ ዘሮች ነበሩ፤ ሁሉም የተገኙት ከእነዚህ ከኖኅ ልጆች ነበር። በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የሚናገሩበትና የሚግባቡበት ቋንቋ አንድ ብቻ ነበር። ሰዎች ከምሥራቅ ተነሥተው በተጓዙ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፥ በዚያም ተቀመጡ። እርስ በርሳቸውም፦ “ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም በደንብ እንተኩሰው” ተባባሉ። በዚህ ዓይነት የሚገነቡትን ጡብ አገኙ፤ በአንድነት የሚያጣብቁበትንም ቅጥራን አገኙ። እንዲህም፦ “ኑ ለእኛ ከተማ እንመስርት፥ በዚያም ጫፉ እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበታተንም ስማችንን እናስጠራ” አሉ። ጌታም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። ጌታም አለ፦ “እነሆ፥ እነዚህ ሕዝቦች አንድ ወገን ናቸው፥ የሁሉም መነጋገሪያ ቋንቋም አንድ ነው። አሁን ይህን ማድረግ ጀመሩ፥ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። ስለዚህ ኑ! እንውረድ፥ እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።” ከዚያ በኋላ ጌታ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፥ ከተማይቱንም መሥራት አቆሙ። ስለዚህም፥ ጌታ በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደበላልቆ እነርሱንም ጌታ በምድር ሁሉ ላይ በትኖአቸዋልና፥ ስምዋ ባቢሎን ተባለ። የሴም ትውልድ ይህ ነው። ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ሴም መቶ ዓመት በሆነው ጊዜ፥ አርፋክስድ የተባለ ልጅ ወለደ። ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ወለደ። አርፋክስድም ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሼላሕንም ወለደ፥ አርፋክስድም ሼላሕን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሦስት ዓመት ኖረ፥ ሌሎች ወንዶች እና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ቃይንምም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሳላንም ወለደ፥ ቃይንምም ሳላን ከወለደ በኋላ ሶስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ዔቦርንም ወለደ፥ ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፥ ፋሌቅንም ወለደ፥ ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ራግውንም ወለደ፥ ራግውንም ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሴሮሕንም ወለደ፥ ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ናኮርንም ወለደ፥ ናኮርንም ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ናኮርም መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ታራንም ወለደ፥ ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፥ ሞተም። ታራም መቶ ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ። የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፥ ሐራንም ሎጥን ወለደ። ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፥ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፥ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፥ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው። ሦራም መካን ነበረች፥ ልጅ አልነበራትም። ታራም ልጁን አብራምን፥ የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥንና የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሣራን ወሰደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፥ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፥ ታራም በካራን ሞተ። እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፥ ለበረከትም ትሆናለህ፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፥ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፥ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፥ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ። አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ። አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የባሉጥ ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፥ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ። እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና፦ ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ። ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ። በምድርም ራብ ሆነ፥ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብጽ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና። ወደ ግብጽም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሣራን እንዲህ አላት፦ አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ፥ የግብጽ ሰዎች ያዩሽ እንደሆነ፦ ሚስቱ ናት ይላሉ፥ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል። እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ፦ እኅቱ ነኝ በዪ። አብራምም ወደ ግብጽ በገባ ጊዜ የግብጽ ሰዎች ሴቲቱ እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፥ የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፥ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት። ለአብራምም በእርሷ ምክንያት መልካም አደረገለት፥ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችም ግመሎችም ነበሩት። እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ። ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው፦ ይህ ያደረግህብኝ ምንድነው? እርሷ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም? ለምንስ፦ እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፥ ይዘሃት ሂድ። ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው። አብራምም ከግብጽ ወጣ፥ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ። አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ። ከአዜብ ባደረገው በጉዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፥ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፥ ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፥ በዚያም አብራም የጌታን ስም ጠራ። ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው። በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም። የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ፥ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር። አብራምም ሎጥን አለው፦ እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፥ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፥ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ። ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፥ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ጾዓር ድረስ እንደ ጌታ ገነት በግብጽ ምድር አምሳል ነበረ። ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፥ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፥ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ። አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ። የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ። ሎጥ ከተለየው በኋላም ጌታ አብራምን አለው፦ “ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፥ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘለዓለም እሰጣለሁና። ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፥ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል። ተነሣ፥ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርሷን ለአንተ እሰጣለሁና።” አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የባሉጥ ዛፎች ተቀመጠ፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ። በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ። እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፥ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በዓሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። በዓሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፥ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፥ የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። ተመልሰውም ቃዴስ ወደተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፥ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴቦን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ። የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፥ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፥ የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ። በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጉድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፥ የቀሩትም ወደ ተራራ። ሸሹ። የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ። አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፥ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ይኖር ነበር፥ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። አብራምም ጠላቶቹን ለማጥቃት አገልጋዮቹን በቡድን ከፋፍሎ በሌሊት እርሱ ከባርያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ። ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፥ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። እንዲህም ሲል ባረከውም፦ አብራም ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፥ ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ፥ ልዑል እግዚአብሔርም ይባረክ፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው። የሰዶም ንጉሥም አብራምን፦ ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው። አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፥ ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል፦ አብራም ሆይ፥ አትፍራ፥ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፥ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው። አብራምም፦ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፥ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤልዔዘር ነው አለ። አብራምም፦ ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፥ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ። እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፦ ይህ አይወርስህም፥ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል። ወደ ሜዳም አወጣውና፦ “ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደሆነ ቁጠር” አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው። አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአሔር እኔ ነኝ አለው። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ። እርሱም፦ የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም ያዝልኝ አለው። እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፥ ወፎችን ግን አልከፈለም። አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው። ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፥ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፥ አብራምንም አለው፦ “ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንደሚሆኑ በእርግጥ እወቅ፥ ባርያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፥ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፥ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፥ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና።” ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፥ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ። በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ፦ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፥ ቄናውያንን ቄኔዛውያንንም ቀድሞናውያንንም ኬጢያውያንንም ፌርዛውያንንም ራፋይምንም አሞራውያንንም ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም ኢያቡሳውያንንም።” የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፥ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባርያም ነበረቻት። ሦራም አብራምን፦ እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፥ ምናልባት ከእርሷ በልጅ እታነጽ እንደሆነ ወደ እርሷ ግባ አለችው። አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባርያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፥ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። ሦራም አብራምን፦ መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፥ እኔ ባርያዬን በጉያህ ሰጠሁህ፥ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፥ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው። አብራምም ሣራን፦ እነሆ ባርያሽ በእጅሽ ናት፥ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች። የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፥ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። እርሱም፦ “የሦራ ባርያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት። እርሷም፦ “እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ” አለች። የእግዚአብሔር መልአክም፦ “ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ” አላት። የእግዚአብሔር መልአክም፦ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት። የእግዚአብሔር መልአክም አላት፦ እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና። እርሱም የሜዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፥ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፥ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል። እርሷም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፥ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ስለዚህም የዚያ ጉድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው። አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ። አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ ጌታ ለአብራም ተገለጠለትና፦ “እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፥ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፥ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ” አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፥ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፥ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፥ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘለዓለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘለዓለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፥ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፥ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፥ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያልሆነ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆናል። የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፥ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “የሚስትህን የሦራን ስም ‘ሦራ’ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፥ እባርካታለሁም፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፥ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።” አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፦ “የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ “እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር” አለው። እግዚአብሔርም አለ፦ “በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፥ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፥ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፥ ዐሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።” ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ፥ ከአብርሃም ቤተሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ፥ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፥ ልጁ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዐሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ ልጁ እስማኤልም። በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት፥ የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ። በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፥ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ፦ “አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፥ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፥ ቁራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፥ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና።” እነርሱም፦ “እንዳልህ አድርግ” አሉት። አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና፦ “ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ” አላት። አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። እርጎና ወተት፥ ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፥ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። እነርሱም፦ “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አሉት። እርሱም፦ “በድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። እርሱም፦ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፥ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለጌታ የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” ሣራም ስለ ፈራች፦ “አልሳቅሁም” ስትል ካደች። እርሱም፦ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት። ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፥ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ። እግዚአብሔርም አለ፦ “እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፥” ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው። እግዚአብሔርም አለ፦ “የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደሆነ ወርጄ አያለሁ፥ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።” ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፥ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር። አብርሃምም ቀረበ ዓለም፦ “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፉለህን? ከተማይቱንስ በእርሷ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? ይህ ከአንተ ይራቅ፥ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” እግዚአብሔርም፦ “በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ” አለ። አብርሃምም መለሰ ዓለም፦ “እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፥ ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን?” “ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም” አለ። ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ፦ “ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ?” እርሱም፦ “ለአርባው ስል አላደርገውም” አለ። እርሱም፦ “ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም” አለ። ደግሞም፦ “እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፥ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም” አለ። እርሱም፦ “እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፥ ምናልባት ከዚያ ዐሥር ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ስለ አሥሩ አላጠፋትም” አለ። እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፥ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ። ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፥ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ። ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባርያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፥ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።” እነርሱም፦ “በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም” አሉት። እጅግም ዘበዘባቸው፥ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፥ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ። ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ፥ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት። ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት፦ “በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።” ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ፥ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፥ እንዲህም አለ፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፥ እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፥ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፥ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና።” እነርሱም፦ “ወዲያ ሂድ” አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፥ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን።” ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት። በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታላቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፥ ሰዎቹም ደጃፉን ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ። ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት፦ “ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፥ እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፥ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል።” ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም፦ ተነሡ፥ ከዚህ ስፍራ ውጡ፥ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። አማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው። ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ “ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፥ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ራስህን አድን፥ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።” ሎጥም፥ አላቸው፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፥ እነሆ ባርያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፥ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፥ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርሷ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርሷም ትንሽ ናት፥ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርሷ ሸሽቼ ላምልጥ፥ እርሷ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?” እርሱም አለው፦ “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፥ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፥ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ጾዓር ተባለ። ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፥ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች። አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፥ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፥ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ። እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፥ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው። ሎጥም ከዞዓር ወጣ፥ በዞዓር ይቀመጥ ዘንድ ስለ ፈራም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፥ በዋሻም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር ተቀመጠ። ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት፦ “አባታችን ሸመገለ፥ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው ከምድር ላይ የለም፥ ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።” በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፥ ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች፥ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። በማግስቱም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት፦ “እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።” አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት፥ ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች፥ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፥ እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው። ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም፦ የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፥ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው። አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሹር መካከልም ተቀመጠ፥ በገራርም በእንግድነት በተቀመጠበት ጊዜ፥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን፦ “እኅቴ ናት” አለ፥ የገራርም ንጉሥ አቢሜሌክ በመልክተኛ ሣራን ወሰዳት። እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ “እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ትሞታለህ፤ እርሷ ባለ ባል ናትና” አለው። አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፥ እሱም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን? ‘እኅቴ ናት’ ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርሷም ደግሞ ራስዋ፥ ‘ወንድሜ ነው’ ብላኛለች፥ ይህንን በቅን ልብ እና በንጹሕ ኅሊና ነው ያደረግሁት”። እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው፦ “ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፥ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውኩህም። አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፥ እርሱ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንደምትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንደሚጠፋ በእርግጥ እወቅ።” አቢሜሌክም በነገታው ማልዶ ተነሣ፥ ባለሟሎቹንም ሁሉ ጠርቶ የሆነውን ነገር ሁሉ ነገራቸው፥ ሰዎቹም እጅግ ደነገጡ። አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው፦ “ይህ ያደረግህብን ምንድነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት ያመጣህብን ምን ብንበድልህ ነው? ፈጽሞ የማይገባ ነገር በእኔ ፈጸምክብኝ።” አቢሜሌክም አብርሃምን አለው፦ ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው? አብርሃምም አለ፦ “በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው። እርሷም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፥ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፥ ለእኔም ሚስት ሆነች። እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት፦ ‘በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው፦ ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ።’” አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። አቢሜሌክም፦ “እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፥ በወደድኸው ተቀመጥ አለ። ሣራንም አላት፦ እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፥ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዐይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፥ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና።” አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባርያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፥ ጌታ በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና። ጌታም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት። ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት። አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው። አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። ሣራም፦ “እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፥ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል” አለች። ደግሞም፦ “ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና” አለች። ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፥ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ። ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርሃምንም “ይህችን ባርያ ከነልጇ አባርራት፥ የዚህች ባርያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና” አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው “ስለ ባርያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፥ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፥ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባርያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።” አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፥ እርሷም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፥ ብላቴናውንም ከአንድ ቁጥቋጦ በታች ጣለችው፥ እርሷም ሄደች ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፥ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጉድጓድንም አየች፥ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች። እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፥ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፥ እናቱም ከምድረ ግብጽ ሚስት ወሰደችለት። በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው፦ “በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፥ አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፥ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ።” አብርሃምም፦ “እኔ እምላለሁ” አለ። አብርሃምም ባርያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጉድጓድ ምክንያት አቢሜሌክን ወቀሰው። አቢሜሌክም አለ፦ “ይህን ነገር ያደረገውን አላወቅሁም፥ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም።” አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፥ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ። አብርሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ። አቢሜሌክም አብርሃምን ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ሰባት ቄቦች በጎች ምንድን ናቸው? አለው። እርሱም፦ እኔ ይህችን የውኃ ጉድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው። ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፥ ከዚያ ሁለቱ ተማምለዋልና። በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ። አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፥ በዚያም የዘለዓለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ። ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ “አብርሃም!” ብሎ ጠራው፤ አብርሃምም፥ “እነሆ፥ አለሁኝ!” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፥ “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሕቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፥ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋልኝ” አለው። በማግስቱም ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሥቶ ለመሥዋዕት የሚሆን ዕንጨትን ቈረጠና በአህያው ላይ ጫነው፥ ከእርሱም ጋር ሁለቱን አገልጋዮቹን እና ልጁን ይስሕቅን ይዞ፥ እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ተነሥቶ ጉዞ ጀመረ። በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ቦታውን በሩቅ አየ። ከዚህ በኋላ አብርሃምም አገልጋዮቹን፥ “አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቈዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው። አብርሃምም የመሥዋዕቱን ማቃጠያ እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፥ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ከዚያም ሁለቱ አብረው ሄዱ። ይስሐቅ አብርሃምን “አባቴ ሆይ!” አለው፤ አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁ ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እነሆ፥ እሳትና እንጨት ይዘናል፤ ነገር ግን ለመሥዋዕት የሚሆነው በግ የት አለ?” በማለት ጠየቀው። አብርሃምም “ልጄ ሆይ፥ ለመሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል” አለው፤ ከዚያም ሁለቱ አብረው ሄዱ። እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሠዊያ ሠራና እንጨቱን በላዩ ላይ ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ላይ፥ ከእንጨቱ በላይ አጋደመው። እጁንም ዘርግቶ፥ ልጁን ለማረድ አብርሃም ቢላዋ አነሣ። ነገር ግን የጌታ መልአክ “አብርሃም! አብርሃም!” ሲል ከሰማይ ተጣራ። አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” አለ። እርሱም “በልጁ ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ ምንም ዓይነት ጉዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ለመስጠት እንዳልሳሳህ እነሆ አየሁ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ” አለ። አብርሃምም ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት፥ ከኋላው እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዛፍ ቊጥቋጦ ተይዞ አየ፥ አብርሃምም ሄዶ በጉን አመጣና፥ በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። ስለዚህም አብርሃም ያንን ቦታ “ጌታ ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “ጌታ በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ። የጌታ መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥ እንዲህም አለው፦ “ጌታ፥ በራሴ እምላለሁ፥ ይላል፤ ምክንያቱም ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልከኝምና፤ በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት እና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና፥ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ።” ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፥ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ። ይህም ከሆነ በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ፦ “እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤ እነርሱም የመጀመሪያው ዑፅ፥ ወንድሙም ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፤ ኬሠድ፥ ሐዞ፥ ፊልዳሽ፥ ይድላፍና በቱኤል ናቸው።” በቱኤል ርብቃን ወለደ፤ ሚልካ እነዚህን ስምንት ልጆች ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደችለት። እንዲሁም፥ ረኡማ የተባለችው የናኮር ቊባት ደግሞ ጤባሕን፥ ገሐምን፥ ተሐሽንና፥ ማዕካን ወለደችለት። የሣራም ዕድሜ መቶ ኻያ ሰባት ዓመት ሆነ፥ እነዚህ ሣራ የኖረችባቸው ዓመታት ነበሩ። በከነዓንም ምድር ባለችው ቂርያት-አርባዕ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ። ከዚያም አብርሃም የሚስቱ አስከሬን ካለበት ስፍራ ተነሥቶ ወደ ሒታውያን ሄደና እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በመካከላችሁ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፥ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ቦታ ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ አርቄ ልቅበር።” ሒታውያንም እንዲህ ብለው ለአብርሃም መለሱለት፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እስቲ ስማን፤ አንተ በመካከላችን እንደ ታላቅ መስፍን ነህ፤ ከመቃብሮቻችን ጥሩውን መርጠህ ሬሳህን እዚያ ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።” አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ በሒታውያን ፊት እጅ ነሣ። እንዲህም አላቸው፦ “ሬሳዬን ከፊቴ አርቄ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፥ በእርሻው ዳር ያለውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን ይስጠኝ፥ ይህ ስፍራ የመቃብር ቦታ እንዲሆንልኝ በእናንተ ፊት ሙሉ ዋጋ ከፍዬ እንዲሰጠኝ አድርጉልኝ።” ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፥ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፥ እርሻውን በክልሉ ውስጥ ካለው ዋሻ ጋር ሰጥቼሃለሁ፤ ሙታንህን እንድትቀብርበት በወገኖቼ በሒታውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ።” አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት እጅ ነሣ፤ የአገሩ ሰዎችም እየሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ፈቃድህ ከሆነ፥ አድምጠኝ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፥ አንተም ከእኔ ተቀበለኝና የሚስቴን አስክሬን እዚያ ወስጄ ልቅበር” አለው። ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፥ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ መሬት በእኔና በአንተ መካከል ምንድነው? እንግዲህ ሬሳህን ቅበር።” አብርሃምም ከኤፍሮን ጋር ተስማማ፥ በሒታውያንም ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል በነጋዴዎች ሚዛን ልክ መዝኖ አብርሃም ለኤፍሮን ሰጠው፥ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ። በዚህ ዓይነት ከመምሬ በስተ ምሥራቅ ማክፌላ የተባለው የዔፍሮን ቦታ የአብርሃም ርስት ሆነ፤ ይህም ቦታ እርሻውን፥ በውስጡ ያለውን ዋሻና በእርሻው ክልል ውስጥ ያለውን ዛፍ ሁሉን፤ በሒታውያን ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ መሆኑ አረጋገጡለት። ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል፥ ከመምሬ በስተ ምሥራቅ ማክፌላ፥ በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው፥ ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ። እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በሒታውያን ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና። አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፥ ጌታም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው። አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው፦ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ።” ሎሌውም፦ “ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን?” አለው። አብርሃምም አለው፦ “ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፥ ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ፦ ‘ይህችንም ምድር ለዘርህ እሰጥሃለሁ’ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፥ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው።” ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት። ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፥ ተነሥቶም ወደ መስጴጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጉድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ። እንዲህም አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፥ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃ ሊቀዱ ይመጣሉ፥ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርሷም አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርሷ ለባርያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፥ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፥ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፥ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊያናግራት ሮጠና፦ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፥ ፈጥናም እንስራዋን በእጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለች። ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጉድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። ሰውዬውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፥ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም ዐሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፥ እንዲህም አላት፦ “አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፥ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን?” አለችውም፦ “እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን።” ሰውዬውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። እንዲህም አለ፦ “ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።” ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች። ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፥ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዬው ሮጠ። ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር፦ “ያ ሰው እንዲህ አለኝ” ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፥ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። እርሱም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ ግባ፥ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ።” ሰውዬውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፥ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፥ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ። መብልንም በፊቱ አቀረበለት፥ እርሱ ግን፦ “ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም” አለ። እርሱም፦ “ተናገር” አለው። እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፥ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባርያዎችንና ሴቶች ባርያዎችን፥ ግመሎችንም፥ አህዮችንም ሰጠው። ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፥ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው። ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ፦ ‘እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት።’ ጌታዬንም፦ ‘ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ?’ አልሁት። እርሱም አለኝ፦ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል፥ ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፥ የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፥ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ።’ ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ፦ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፥ እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፥’ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ፦ ‘ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ’ ስላት፥ እርሷም፦ ‘አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርሷ ትሁን።’” “እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች እኔም፦ ‘እስኪ አጠጪኝ’ አልኋት። ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና፦ ‘አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ’ አለች፥ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች። እኔም፦ ‘አንቺ የማን ልጅ ነሽ?’ ብዬ ጠየቅኋት። እርሷም፦ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለች፥ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት። በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፥ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደሆነ ንገሩኝ፥ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ።” ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ፦ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቷል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም። ርብቃ እነኋት በፊትህ ናት፥ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን።” የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፥ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፥ ማልደውም ተነሡና፦ “ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። ወንድምዋና እናትዋም፦ “ብላቴናይቱ አንድ ዐሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች” አሉ። እርሱም፦ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፥ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ” አላቸው። እነርሱም፦ “ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ” አሉ። ርብቃንም ጠርተው፦ “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?” አሉአት። እርሷም፦ “እሄዳለሁ” አለች። እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። ርብቃንም መረቁአትና፦ “አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፥ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ” አሉአት። ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፥ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፥ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፥ ዐይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። ርብቃም ዐይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። ሎሌውንም፦ “ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው?” አለችው። ሎሌውም፦ “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት፥ እርሷም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፥ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ። እርሷም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የሽቦቅን፥ እና ሹሐን ወለደችለት። ዮቅሻንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሹራውያን፥ ለጡሻውያንና፥ ለኡማውያን ናቸው። የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፥ ነገር ግን የአብርሃም ለነበሩትም ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታ ሰጣቸው፥ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። አብርሃምም በሕይወት የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሰባ አምስት ዓመታት ናቸው። በመጨረሻዋ እስትንፋሱ አብርሃም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካምም ሽምግልና ሞተ፥ ሸምግሎ፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል፥ ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ፥ ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት። የእርሻው ቦታ አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው ነው፤ ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ ሣራ ጋር ተቀበረ። ከአብርሃም ሞት በኋላም እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤር-ላሃይ-ሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ በትውልዳቸው ቅደም ተከተል የተዘረዘሩት የእስማኤል የልጆቹ ስም እንዲህ ነው፥ የእስማኤል የበኩር ልጁ ነባዮት፥ እና ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፥ በየወገናቸውም ዐሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፥ የመጨረሻዋ እስትንፋሱን ተንፍሶም ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዘሮቹም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ሲሰፍሩ፤ የኖረውም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት በተቃርኖ ነበር። የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፥ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፥ ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፥ እርሷም በመስጴጦምያ የሚኖሩ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርሷ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ ልጆቹም በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርሷም፥ “እንዲህ እሆን ዘንድ ከሆነ፥ ስለምንድን ነው የምኖረው?” አለች። ከጌታም ምላሽ ታገኝ ዘንድ ሄደች። ጌታም እንዲህ አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንዱም ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።” የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በመጀመሪያም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር፥ ስለዚህ ዔሳው ብለው ጠሩት። ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ልጆቹን በወለደች ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ልጆቹም ባደጉ ጊዜ፥ ዔሳውም በዱር የሚውል ብልኅ አዳኝ ሆነ፥ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በቤትም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳው ካደነው ይበላ ነበርና ይወደው ነበር፥ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ ሲሠራ፥ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ እርቦኛልና!” አለው፤ (ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር።) ያዕቆብም፥ “በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም “እኔ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። ያዕቆብም፥ “እስኪ በቅድሚያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዓይነት ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት። በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ ላይ ራብ ሆነ፥ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “ወደ ግብጽ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፥ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ። ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፥ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።” ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት፥ እርሱም፦ “እኅቴ ናት” አለ፥ የዚያም ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፥ እርሷ ውብ ነበረችና። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ እንዲህም አለው፦ “እነሆ ሚስትህ ናት፥ እንዴትስ እርሷን፦ ‘እኅቴ ናት’ አልህ?” ይስሐቅም፦ “በእርሷ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም አለ፦ “ይህ ያደረግህብን ምንድነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር።” አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፦ “ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት” ብሎ አዘዘ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፥ እግዚአብሔርም ባረከው። ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፥ በግና ላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፥ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጉድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፥ አፈርንም ሞሉባቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፦ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጉድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፥ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጉድጓድ አገኙ። የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፦ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተከራከሩ፥ የዚያችንም ጉድጓድ ስም “ኤሴቅ” ብሎ ጠራት፥ ለእርሷ ሲሉ ተጣልተዋልና። ሌላ ጉድጓድም ማሱ፥ ስለ እርሷም ደግሞ ተጣሉ፥ ስምዋንም “ስጥና” ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጉድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርሷም አልተጣሉም፥ ስምዋንም “ርኆቦት” ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን።” ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፥ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ እባርክሃለሁ፥ ስለ ባርያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።” በዚያም መሠዊያን ሠራ የጌታንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፥ የይስሐቅም አገልጋዮች በዚያ ጉድጓድ ማሱ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱም አለቃ ፊኮል ከጌራራ ወደ እርሱ ሄዱ። ይስሐቅም፦ “ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? እናንተ ጠልታችሁኛል፥ ከእናንተም ለይታችሁ አሳድዳችሁኛል” አላቸው። እነርሱም፤ “ጌታ ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጥ አየን፤ ስለዚህ በእኛና በአንተ መካከል መሐላ ይኑር፤ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ፥ እኛ አንተን እንዳልነካንህ፥ በጎነትንም ብቻ እንዳሳየንህ፥ በሰላምም እንደ ሰደድንህ፥ አንተም ክፉ እንዳትሠራብን፥ አንተ አሁንም ከጌታ ዘንድ የተባረክህ ነህ።” ይስሐቅም ማዕድ አቀረበላቸው፥ በሉም ጠጡም። ማልደውም ተነሡ፥ እርስ በርሳቸውም ተማማሉ፥ ይስሐቅም አሰናበታቸው፥ ከእርሱም ወጥተው በሰላም ሄዱ። በዚያም ቀን የይስሐቅ አገልጋዮች መጡ፥ ስለ ቈፈሩአትም ጉድጓድ፦ “ውኃ አገኘን ብለው ነገሩት።” ስምዋንም “ሳቤህ” ብሎ ጠራት፥ ስለዚህም የከተማይቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ነው። ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የሒታውያዊ የብኤሪን ልጅ ዮዲትን፥ የሒታውያዊ የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ፥ እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር። እንዲህም ሆነ፥ ይስሐቅ ሸምግሎ ዐይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፥ “ልጄ ሆይ፥” አለው እርሱ፥ “እነሆ አለሁ” አለው። እርሱም አለው፥ “እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፥ ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።” ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ርብቃም ልጇን ያዕቆብን እንዲህ አለችው፥ “እነሆ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው፦ ‘አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በጌታ ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል ሥራልኝ፤’ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ። አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህ ነገር ስማኝ፥ ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካም ጠቦቶች አምጣልኝ፥ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፥ ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታስገባለታለህ።” ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት፦ “እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጉራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፥ ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፥ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም።” እናቱም አለችው፦ “ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፥ ቃሌን ብቻ ስማኝ፥ ሂድና አምጣልኝ።” ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፥ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች። ርብቃም ከእርሷ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጇን ያዕቆብንም አለበሰችው፥ የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፥ የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጇ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው። ወደ አባቱም ገብቶ፦ “አባቴ ሆይ” አለው እርሱም፦ “እነሆኝ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ?” አለ። ያዕቆብም አባቱን አለው፦ “የበኩር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፥ እንዳዘዝኸኝ አደረግሁ፥ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ።” ይስሐቅም ልጁን፦ “ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው?” አለው። እርሱም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው” አለ። ይስሐቅም ያዕቆብን፦ “ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ” አለው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሕቅ ቀረበ፥ ዳሰሰውም፥ እንዲህም፦ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፥ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለው። እርሱም አላወቀውም ነበር፥ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጉራም ነበሩና፥ ስለዚህም ባረከው። አለውም፦ “አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” እርሱም፦ “እኔ ነኝ” አለ። እርሱም፦ “ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ” አለ። አቀረበለትም፥ በላም፥ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ። አባቱ ይስሐቅም፦ “ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም” አለው። ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፥ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ፦ “የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፥ አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፥ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፥ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።” ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ። እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፥ አባቱንም፦ “አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ” አለው። አባቱ ይስሐቅም፦ “አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም፦ “እኔ የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ፦ “ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፥ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል።” ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም፦ “አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ” አለው። እርሱም፦ “ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ” አለ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፥ ብኩርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም፦ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” አለ። ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው፦ “እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፥ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ?” ዔሳውም አባቱን አለው፦ “አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ።” ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ። አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም፦ “እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፥ በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፥ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ።” ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፥ ዔሳውም በልቡ አለ፦ “ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።” ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጇ የዔሳው ቃል ደረሰላት፥ ታናሹን ልጇን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም፦ “እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል። አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፥ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፥ በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ፥ የወንድምህ ቁጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፥ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፥ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ?” ርብቃም ይስሐቅን አለችው፦ “ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፥ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?” ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፥ ባረከውም፥ እንዲህ ብሎም አዘዘው፦ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፥ ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፥ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ። ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ፥ ያፍራህ፥ ያብዛህ፥ ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃምን የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃም በረከት ለአንተ ይስጥህ፥ ለዘርህም እንዲሁ።” ይስሐቅም ያዕቆብን ላከው፥ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊ ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ። ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው ባየ ጊዜ፥ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለት ወንዞች መካካል እንደ ላከው፥ በባረከውም ጊዜ፦ ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ ብሎ እንዳዘዘው፥ ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደ ሄደ፥ የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደ ሆኑ ዔሳው ባየ ጊዜ፥ ዔሳው ወደ እስማኤል ሄደ፥ ማዕሌትንም በፊት ካሉት ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባ፥ እርሷም የአብርሃም ልጅ የሆነ የእስማኤል ልጅና የነባዮት እኅት ናት። ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፥ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። ሕልምም አለመ፥ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፥ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፥ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፥ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፦ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፥ እኔ አላወቅሁም ነበር” አለ። ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፥ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፥ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።” ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት። ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፥ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ። ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፥ ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፥ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከዐሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።” ያዕቆብም ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሰዎች አገር ሄደ። በሜዳውም እነሆ ጉድጓድን አየ፥ በዚያም ሦስት የበጎች መንጎች በላዩ ተመስገው ነበር፥ ከዚያ ጉድጓድ በጎቹን ያጠጡ ነበርና፥ በጉድጓዱም አፍ የነበረው ድንጋይ ትልቅ ነበረ። መንጎችም ሁሉ ከዚያ በተከማቹ ጊዜ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ ገለል አድርገው በጎቹን ያጠጡ ነበር፥ ድንጋዩንም ወደ ስፍራው መልሰው በጉድጓዱ አፍ እንደገና ይገጥሙት ነበር። ያዕቆብም፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንት የወዴት ናችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “እኛ የካራን ነን” አሉት። “የናኮርን ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፦ “እናውቀዋለን” አሉት። እርሱ፦ “ደኅና ነውን?” አላቸው። እነርሱም፦ “አዎን ደኅና ነው፥ አሁንም ልጁ ራሔል ከበጎች ጋር መጣች” አሉት። እርሱም፦ “ቀኑ ገና ቀትር ነው፥ ከብቶቹ የሚከማቹበት ሰዓቱም ገና አልደረሰም፥ አሁንም በጎቹን አጠጡና ሄዳችሁ አሰማሩአቸው” አላቸው። እነርሱም አሉ፦ “መንጎች ሁሉ እስኪከማቹና ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ እስኪገለብጡት ድረስ አንችልም፥ ከዚያም በኋላ በጎቹን እናጠጣለን።” እርሱም ገና ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ የላባ ልጅ ራሔል ከአባትዋ በጎች ጋር ደረሰች፥ እርሷ የአባትዋን በጎች ትጠብቅ ነበርና። ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የአጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጉድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የአጎቱን የላባን በጎችንም አጠጣ። ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ያዕቆብም የአባትዋ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፥ እርሷም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው። ላባም የእኅቱን ልጅ የያዕቆብን ወሬ በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ሮጠ፥ አቅፎም ሳመው፥ ወደ ቤቱም አገባው። ነገሩንም ሁሉ ለላባ ነገረው። ላባም፦ “በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ።” ላባም ያዕቆብን፦ “ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ደመወዝህ ምንድነው? ንገረኝ” አለው። ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፥ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፥ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፥ እንዲህም አለ፦ “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ።” ላባም፦ “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፥ ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለ። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፥ እርሷንም ይወድዳት ስለ ነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፦ “ወደ እርሷ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና” አለው። ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፥ ያዕቆብም ወደ እርሷ ገባ። ላባም ለልጁ ለልያ ባርያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፥ ላባንም፦ “ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለግልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ?” አለው። ላባም እንዲህ አለ፦ “በአገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንስጥ ዘንድ ወግ አይደለም፥ ይህችንም ሳምንት ፈጽም፥ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርሷን ደግሞ እሰጥሃለሁ።” ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፥ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፥ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው። ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፥ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት። እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፥ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፥ እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና። ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ደገመኝ አለች፥ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው። ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፥ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው። ደግሞም ፀነስች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፥ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች። ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፥ ያዕቆብንም፦ ልጆች ስጠኝ፥ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው። ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ፦ በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት። እርሷም ባርያዬ ባላ እነሆ አለች፥ ድረስባት፥ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርሷም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች። ባርያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፥ ያዕቆብም ደረሰባት። ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። ራሔልም፦ እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ አለች፥ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። የራሔልም ባርያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች። ራሔልም፦ ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፥ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው። ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባርያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆንውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው። የልያ ባርያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች። ልያም፦ ጉድ አለች፥ ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው። የልያ ባርያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች። ልያም፦ ደስታ ሆነልኝ፥ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፥ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው። ሮቤልም ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን፦ “የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። እርሷም፦ “ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን?” አለቻት። ራሔልም፦ “እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ” አለች። ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው፦ “ወደ እኔ ትገባለህ፥ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና።” በዚያችም ሌሊት ከእርሷ ጋር ተኛ። እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። ልያም፦ “ባርያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ” አለች፥ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። ልያም፦ “እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፥ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና” አለች፥ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት። እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፥ ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና፦ “እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ” አለች፥ ስሙንም፦ “እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ” ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው። ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ “ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ። ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶችንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፥ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና።” ላባም፦ “በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚህ ተቀመጥ፥ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና” አለው። “ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ” አለ። እርሱም አለው፦ “እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ። ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፥ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፥ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?” እርሱም፦ “የምሰጥህ ምንድነው?” አለ። ያዕቆብም አለው፦ “ምንም አትስጠኝ፥ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም። ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጉርጉርና ነቁጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቁጣና ዝንጉርጉር ያለበቱን እለያለሁ፥ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ። ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፥ ከፍየሎች ዝንጉርጉርና ነቁጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ።” ላባም፦ “እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን” አለ። በዚያም ቀን ከተባዕቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቁጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጉርጉርና ነቁጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው። በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፥ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር። ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለውን ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎች ፊት አኖራቸው፥ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር። በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፥ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጉርጉር ነቁጣም ያለበቱን ወለዱ። ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ሁሉ በላባ በጎች ፊት ለፊት አኖረ፥ መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም። እንዲህም ሆነ፥ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፥ በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፥ የደከሙትም ለላባ፥ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ። ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፥ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባርያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት። ያዕቆብም፥ የላባ ልጆች፦ “ያዕቆብ የአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፥ የአባታችን ከነበረውም ይህንም ሁሉ ሀብት አገኘ” ሲሉ ሰማ። እንደ ቀድሞው በላባ ተወዳጅ አለመሆኑን ያዕቆብም አየ። በዚህን ጊዜ ጌታ ያዕቆብን፥ “ወደ አባቶችህ ምድር እና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፥ ከአንተም ጋር እሆናለሁ” አለው። ያዕቆብም ላከና ራሔልንና ልያን በጎቹ ወደ ነበሩበት መስክ ጠራቸው፥ እንዲህም አላቸው፥ “አባታችሁ ከእኔ ጋር እንደ ቀድሞው እንደማይወደኝ አያለሁ፥ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። እኔ ባለኝ ጉልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልኩ እናንተም ታውቃላችሁ። አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለወጠ፥ እግዚአብሔር ግን ይጎዳኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። ‘ዝንጉርጉሮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ቢለኝ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ዝንጉርጉሮችን ወለዱ፤ ደግሞም ‘ሽመልመሌ መሳዮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ቢለኝ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ሽመልመሌ ወለዱ። እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ። በመንጋዎቹ መራቢያ ወራት ዐይኖቼን አነሳሁ፥ በሕልምም በበጎቹ ላይ የሚንጠላጠሉት አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጉርጉርና ነቊጣ እንደ ነበሩ አየሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም፦ ያዕቆብ ሆይ አለኝ፥ እኔም፦ እነሆኝ አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፥ ‘ዓይንህን አቅናና እይ፥ መንጋዎቹ ላይ የሚንጠላጠሉት ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ፥ ዝንጉርጉሮች እና ነቊጣ ናቸው፤ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። ሐውልት የቀባህበት እና ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፥ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ ምድር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።’” ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት፥ “በአባታችን ቤት ለእኛ አንዳች ድርሻ ወይም ርስት አለን? እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልኮ። ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፥ እንግዲያውስ አሁንም፥ እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ፥ አድርግ።” ከዚያም ያዕቆብ ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ መንጎቹንም ሁሉ፥ ያፈራውን ንብረት ሁሉ፥ ፓዳን-ኣራም ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። ላባም በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፥ ራሔልም የአባትዋን ቤት ጣዖቶች ሰረቀች። ያዕቆብም ለመሄድ ማቀዱን ሳይነግረው ሶርያዊውን ላባን ከድቶ ኮበለለ። እርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፥ ተነሥቶም የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ኮረብታማው አገር ገለዓድ አቀና። በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ሲነገረው፥ ከዘመዶቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ ከዚያም በገለዓድ ተራራማ አገር ላይ አገኛቸው። እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ፥ “ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። ላባም ያዕቆብን ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን ኮረብታማው አገር ተክሎ ነበር፥ ላባም ከዘመዶቹ ጋር በገለዓድ ኮረብታማው አገር ድንኳኑን ተከለ። ላባም ያዕቆብን አለው፥ “የፈጸምከው ምንድነው? እኔን አታልልከኝ፥ ልጆቼንስ እንደ ሰይፍ ምርኮኛ ለምን ወሰድካቸው? ስለምን በስውር ሸሸህ፥ እኔንም አታለልከኝ፥ በደስታና በዘፈንም በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም? ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ። ጉዳት አደርስብህ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፥ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት፥ ‘ያዕቆብን ክፉም ሆነ ደግ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ ብሎ ነገረኝ። አሁንም የአባትህን ቤት እጅጉን ናፍቆሃልና ሂድ፥ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?” ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው፥ “ልጆችህን በጉልበት ከእኔ የምትቀማኝ ስለ መሰለኝና ስለ ፈራሁ ይህን አደረግሁ። አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፥ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደሆነ በዘመዶቻችን ፊት ፈልግ፥ ውሰደውም” አለ። ያዕቆብ ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው አያውቅም ነበር። ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባርያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግን አላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም። እርሷም አባትዋን፥ “ፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፥ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና” አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም። ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፥ ያዕቆብም ላባንም እንዲህ አለው፥ “ምን በደልሁህ? ይህን ያህል ያሳደድኸኝ፥ ኃጢአቴስ ምንድነው? አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፥ የቤትህስ ሁሉ የሆነ ዕቃ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በዘመዶቼና በዘመዶችህ ፊት አቅርበው። ለሃያ ዓመታት ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፥ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፥ እኔው ራሴ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፥ በቀን ሆነ በሌሊት ቢሰረቅ፥ ያን ከእጄ ትፈልግ ነበር። እንዲህ ስሆን፥ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ። እነዚህን ሃያ ዓመታት በአንተ ቤት ነበርሁ፥ ዐሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፥ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለዋወጥኸው። የአባቴ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት፥ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ፥ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፥ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ልፋት አየ፥ ትናንትና ሌሊትም ገሠጸህ።” ላባም ለያዕቆብ መልሶ እንዲህ አለው፥ “ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው። ነገር ግን ዛሬ በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ እችላለሁ? አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፥ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን።” ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ። ያዕቆብም ዘመዶቹን “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው፥ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፥ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ። ላባም “ይጋር ሠሀዱታ” ብሎ ጠራት፥ ያዕቆብም “ገለዓድ” አላት። ላባም፥ “ይህ ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለ። ስለዚህም ገለዓድ ብሎ ሰየማት፥ ደግሞም “ምጽጳ” ፥ “እኛ አንዳችን ከሌላው በተለያየን ጊዜ ጌታ በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ” ብሏልና። “ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው፥ ማንም ሰው ከእኛ ጋር ባይኖር እንኳን፥ በእኔና በአንተ መካከል እግዚአብሔር ምስክር ነው።” ላባም ያዕቆብን አለው፥ “በእኔና በአንተ መካከል ይህ ክምር፥ ያቆምኩት ሐውልትም እነሆ፥ እኔ ወደ አንተ ይህን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህን ክምርና ይህን ሐውልት እንዳታልፍ፥ ይህ ክምር እና ይህ ሐውልት ምስክር ነው። የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ፥ የአባታቸውም አምላክ፥ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ። ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን አቀረበ፥ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጠራ፥ እነርሱም ምግብ ተመገቡ፥ በዚያም በተራራ ሌሊቱን ሙሉ አሳለፉ። ጠዋት በማለዳ ላባ ተነሥቶ የልጅ ልጆቹን እና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፥ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም አጋጠሙት። ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ፥ “እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው!” አለ። የዚያንም ስፍራ ስም ማሃናይም ብሎ ጠራው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “ለጌታዬ ለዔሳው፥ አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፥ ‘በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፥ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፥’” ብላችሁ ንገሩት “በሬዎች፥ አህዮች፥ በጎች፥ ወንድ አገልጋዮች፥ እና ሴት አገልጋዮችም አገኘሁ፥ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማሳወቅ ላኩብህ።” መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት፥ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፥ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች” አሉ። ያዕቆብም እጅግ ፈራ ተጨነቀም፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች፥ መንጎችን እና ከብቶችን ግመሎችንም፥ በሁለት ወገን ከፈላቸው፥ “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።” ብሎም አሰበ። ያዕቆብም አለ፦ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ ጌታ ሆይ፥ ለባርያህ ካሳየኸው ከጽኑ ፍቅርና ከታማኝነትህ ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፥ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበር፥ አሁን ግን ለሁለት ወገን የተከፈልኩ ሆንሁ። ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፥ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። አንተም፦ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ’ ብለህ ነበር።” በዚያችም ሌሊት ከዚያው ሰፈረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን አወጣ፥ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም እህዮችን፤ እነዚህንም መንጎቹ በየወገኑ ከፍሎ በአገልጋዮቹ እጅ አደረጋቸው፥ አገልጋዮቹንም፦ “ከእኔ ቀድማችሁ ሂዱ፥ በመንጋው እና መንጋው መካከልም እርቀት አኑሩ” አለ። የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ፥ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ በዚያን ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የባርያህ የያዕቆብ ነው፥ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው’ በለው።” እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዱሁ ብሎ አዘዘ፦ “ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት። ‘እንዲሁም ባርያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው’ እንድትሉት። እሱ ‘በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይቀበለኛል ፊቱንም አያለሁ’ ብሎ አስቧል።” ስለዚህ እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፥ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት እዚያው በሰፈሩበት አደረ። በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹን፥ እና ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። እነርሱን ወስዶ ወንዙን አሻገራቸው፥ ያለውን ሁሉ እንደዚሁ አሻገረ። ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፥ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ሲታገለው አደረ። ያ ሰው ያዕቆብን እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ፥ የጭኑን ሹልዳ ነካው፥ ያዕቆብም ሲታገለው የጭኑ ሹልዳ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤። ከዚያ ሰውየው፦ “የንጋት ጎህ ሊቀድ ነውና ልቀቀኝ” አለው። እርሱም፦ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። ሰውየውም፦ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፦ “ያዕቆብ ነኝ” አለው። ሰውየውም፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ ያዕቆብ አይባልም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና እስራኤል ይባላል” አለው። ያዕቆብም፦ “ልለምንህ፥ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ?” አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው። ስለዚህ ያዕቆብ፦ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሆኖም ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል የዚያን ቦታ ስም “ጵኒኤል” ብሎ ጠራው። ጵኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። ስለዚህም የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርቹን ሹልዳ ነክቶታልና፥ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን (በጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን) ሹልዳ አይበሉም። ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ ተመለከተም፥ እነሆም ዔሳው እየመጣ ነበር፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ። ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም አገልጋዮች አደረጋቸው። ሴት አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውንም ከፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም አስከተለ፥ ከዚያም ራሔልንና ዮሴፍን ከሁሉ በኋላ አደረገ። እርሱም ከፊታቸው ቀደመ፥ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ። ዔሳውም ሊገናኘው ሮጦ ተጠመጠመበት፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፥ ተላቀሱም። ዓይኑን አንስቶም ሴቶችንና ልጆችን ባየ ጊዜ፥ “እነዚህ ምኖችህ ናቸው?” አለ። እርሱም፦ “እግዚአብሔር ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለ። ከዚህ በኋላ ሴቶች ባርያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው እጅ ነሡ፥ ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀረበው እጅ ነሡ፥ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል ቀርበው እጅ ነሡ። እርሱም፥ “ያገኘሁት ይህ ሁሉ ጓዝ ምንህ ነው?” አለ። እርሱም፥ “በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው” አለ። ዔሳውም፥ “ለእኔ ብዙ አለኝ፥ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ።” ያዕቆብም አለ፥ “እንደዚህ አይሁን፥ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንሁ፥ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፥ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና። ይህንም ያመጣሁልህን ስጦታዬን ተቀበል፥ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ጎብኝቶኛልና፥ ለእኔም በቂ አለኝና።” በዚህም መልክ ግድ አለው፥ እርሱም ተቀበለው። እርሱም ተነሣና “እንግዲህ እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ” አለ። እርሱም አለው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፥ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ መጠንቀቅ ይኖርብኛል፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደሆነ እንሰሶቹ ሁሉ ይሞታሉ። እባክህ ጌታዬ ከአገልጋዩ ፊት ቀድሞ ይለፍ፥ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በልጆቹ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።” ዔሳውም፥ “ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን” አለ። እርሱ ግን፥ “ይህ ለምንድን ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል” አለ። ዔሳውም በዚያኑ ቀን ወደ ሴይር መንገዱ ተመለሰ። ያዕቆብ ግን ወደ “ሱኮት” ሄደ፥ ከዚያም ለራሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶቹም ዳሶችን አደረገ። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም “ሱኮት” ብሎ ጠራው። ያዕቆብም፥ ከፓዳን-ኣሪም በተመለሰ ጊዜ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው፥ ሴኬም ከተማ በሰላም መጣ፥ እናም በከተማይቱ ፊት ለፊት ሰፈረ። ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የመስክ ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው። እዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው። የልያ ልጅ ዲናም፥ የዚያን አገር ሴት ልጆችን ለማየት ወጣች። የአገሩ ገዢ የሒዋዊው ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፥ ወሰዳትም ከእርሷም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። ነፍሱም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈች፥ ልጅቱንም አፈቀራት፥ እርሷንም በአፍቅሮት አናገራት። ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፥ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፥ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በመስክ ተሰማርተው ነበር፥ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከመስክ መጡ፥ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ኀፍረትን ስላደረገ አዘኑ፥ እንዲህ አይደረግምና እጅግም ተቈጡ። ሐሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፥ “ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ነፍሱ ተወስዳለችና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርሷን ስጡት። ከእኛም ጋር በጋብቻ ተሳሰሩ፥ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም እንደፈለጋችሁ ሁኑባት፥ ኑሩባት፥ ነግዱባትም፥ ሀብትም አፍሩባት።” ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ፥ “በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። ብዙ ጥሎሽና ስጦታ አምጣ በሉኝ፥ ይህችን ልጅ እንዳገባ ስጡኝ እንጂ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ።” የያዕቆብም ልጆች፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፥ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ። እንዲህም አሉአቸው፦ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፥ ይህ ነውር ይሆንብናልና። እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፥ ሴቶች ልጆቻችንንም እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፥ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። ወጣቱም ልጅ፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፥ ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም። እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ፦ “እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፥ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፥ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፥ እርሱም እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ ነው። ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።” ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን “እሺ” አሉ፥ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው እያሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፥ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፥ በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፦ “በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፥ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፥ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፥ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።” እነርሱም፦ “በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ሊደረግ ይገባልን?” አሉ። እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፦ “ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፥ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን ሥራ።” ስለዚህ ያዕቆብ ለቤተሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ፦ “እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፥ ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፥ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን እሠራለሁ።” እነርሱም በእጃቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት ሁሉ፥ እንዲሁም በጆሮአቸውም ያሉትን ጉትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፥ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የባሉጥ ዛፍ በታች ቀበራቸው። ተነሥተውም ሄዱ፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፥ እርሷም ቤቴል ናት። በዚያም መሠዊያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም “ኤልቤቴል” ብሎ ጠራው፥ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና። የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፥ በቤቴልም ከባሉጥ ዛፍ በታች ተቀበረች፥ ስሙም “አሎንባኩት” ተብሎ ተጠራ። እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከፓዳን-ኣሪም ከተመለስ በኋላ እንደገና ተገለጠለት፥ ባረከውም። እግዚአብሔርም፦ “ስምህ ያዕቆብ ነው፥ ከእንግዲህም ወዲህ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ፥ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥” አለው። ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም አለው፦ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፥ ብዛ፥ ተባዛም፥ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጉልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጠለሁ።” እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ዐምድ አኖረ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው። ከቤቴልም ተነሡ፥ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች። ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ፦ “አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና” አለቻት። እርሷም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን “ቤንኦኒ” ብላ ጠራችው፥ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፥ እርሷም ቤተልሔም ናት። ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፥ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከዔዴር ግንብ ባሻገር ተከለ። እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፥ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፥ የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ በኩር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። የልያ ባርያ የዚልፋ ልጆችም፥ ጋድ፥ አሴር ናቸው። እነዚህ በፓዳን-ኣሪም በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ መምሬ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት፥ ወደ ቂርያት-አርባ፥ እርሷም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፥ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፥ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት። የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፥ እርሱም ኤዶም ነው። ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፥ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን፥ የሒዋዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳትን ኦሆሊባማን፥ የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ባሴማትን። ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፥ ባሴማትም ራዑኤልን ወለደች፥ ኦሆሊባማም የዑሽን፥ ያዕላምን፥ ቆሬን ወለደች። በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። ዔሳውም ሚስቶቹን፥ ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን፥ ቤተሰቡንም ሁሉ፥ እንስሶቹንም ሁሉ፥ በከነዓንም ሀገር ያገኘውን ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፥ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፥ ዔሳው ኤዶም ነው። በሴይር ተራራ የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት የዔሳው ትውልድም ይህ ነው። የዔሳው ልጆች ስም ይህ ነው፥ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝ፥ የዔሳው ሚስት የባሴማት ልጅ ረዑኤል። የኤልፋዝም ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጋታም፥ ቄናዝ። ቲምናዕም ለዔሳው ልጅ ለኤልፋዝ ቁባት ነበረች፥ አማሌቅንም ለኤልፋዝ ወለደችለት፥ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጆች እነዚህ ናቸው። የረዑኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፦ ናሐት፥ ዘራሕ፥ ሻማና ሚዛ፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት ባሴማት ልጆች ናቸው። የፅብዖን ልጅ የዓና ልጅ የኦሆሊባማ፥ የዔሳው ሚስት፥ ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ለዔሳውም የዑሽ፥ ያዕላምና፥ ቆሬን ወለደች። የዔሳው መጀመሪያ ልጅ የኤልፋዝ ልጆች፥ የዔሳው ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፥ የቴማን አለቃ፥ ኦማር አለቃ፥ ስፎ አለቃ፥ ቄናዝ አለቃ፥ ቆሬ አለቃ፥ ገዕታም አለቃ፥ አማሌቅ አለቃ፥ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ አለቆች እነዚህ ናቸው፥ እነዚህ የዓዳ ልጆች ናቸው። የዔሳው ልጅ የረዑኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ናሐት አለቃ፥ ዘራሕ አለቃ፥ ሻማ አለቃ፥ ሚዛህ አለቃ፥ በኤዶም ምድር የረዑኤል ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የባሴማት ልጆች ናቸው። የዔሳው ሚስት የኦሆሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፦ የዑሽ አለቃ፥ ያዕላም አለቃ፥ ቆሬ አለቃ፥ የዔሳው ሚስት የዓና ልጅ የኦሆሊባማ አለቆች እነዚህ ናቸው። እነዚህ ኤዶም የተባለው የዔሳው ልጆችና አለቆቻቸው ናቸው። በዚያች አገር የተቀመጡ የሖሪው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ሎጣን፥ ሾባል፥ ፅብዖን፥ ዓናና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን፥ እነዚህ በኤዶም ምድር የሖሪው የሴይር ልጆች አለቆች ናቸው። የሎጣን ልጆችም ሖሪ፥ ሄማን ናቸው፥ የሎጣንም እኅት ቲምናዕ ናት። የሾባል ልጆችም፥ ዓልዋን፥ ማናሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ ኦናም ናቸው። የፅብዖን ልጆችም፦ አያና ዓና ናቸው። ይህ ዓና የአባቱን የፅብዖንን አህዮች ሲጠብቅ በበረሓ ውስጥ የፍል ውሃ ምንጮችን ያገኘ ነው። የዓና ልጅ ዲሾን የተባለው ነው፤ ሴት ልጁም ኦሆሊባማ ትባላለች። የዲሾን ልጆች ሔምዳን፥ ኤሽባን፥ ይትራንና፥ ከራን ናቸው። የኤጽር ልጆች ቢልሃን፥ ዛዕዋንና፥ ዓቃን ናቸው። የዲሻን ልጆች ዑፅና አራን ናቸው። የሖሪ አለቆች እነዚህ ናቸው፥ ሎጣን አለቃ፥ ሾባል አለቃ፥ ፅብዖን አለቃ፥ ዓና አለቃ፥ የዲሾን አለቃ፥ ኤጽር አለቃ፥ ዲሻን አለቃ፥ በሴይር ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪ አለቆቹ እነዚህ ናቸው። በእስራኤል ልጆች ላይ ንጉሥ ከመኖሩ በፊት በኤዶም አገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። የበዖር ልጅ ቤላዕ በኤዶም ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ናት። ቤላዕ ሞተ፥ በስፍራውም የባሶራው የዛራ ልጅ ዮባብ ነገሠ። ዮባብም ሞተ፥ በስፍራውም የቴማኒው አገር ሑሻም ነገሠ። ሑሻምም ሞተ፥ በስፍራውም የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ሜዳ የመታ የቤዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፥ የከተማውም ስም ዓዊት ተባለ። ሃዳድም ሞተ፥ በስፍራውም የማሥሬቃው ሠምላ ነገሠ። ሠምላም ሞተ፥ በስፍራውም በወንዝ አጠገብ ካለችው ከርሆቦት ሻኡል ነገሠ። ሻኡልም ሞተ፥ በስፍራውም የዓክቦር ልጅ በኣል-ሐናን ነገሠ። የዓክቦር ልጅ በኣል-ሐናንም ሞተ፥ በስፍራውም ሃዳር ነገሠ፥ የከተማውም ስም ፋዑ ነው፥ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ ማጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባል ነበር። የዔሳውም የአለቆቹ ስም በወገናቸው፥ በስፍራቸውም፥ በስማቸው ይህ ነው፦ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥ ኦሆሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥ ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብጻር አለቃ፥ ማግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፤ እነዚህ በግዛታቸው ምድር በየመኖሪያቸው የኤዶም አለቆች ናቸው። የኤዶማውያን አባት ዔሳው ነው። ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ የእነርሱንም ክፋት ነገር ዮሴፍ ወደ አባታቸው አመጣ። እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፥ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ሊያናግሩትም አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እነርሱም እንደገና አብዝተው ጠሉት። እርሱም አላቸው፦ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፥ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፦ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፥ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።” ሲል ነገራቸው። ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” በማለት አባቱ ገሠጸው። ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ነገሩን ጠብቆ አኖረው። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን እየጠበቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እንድልክህ ና” አለው። እርሱም “እነሆኝ” አለው። እርሱም፦ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። በዚህ ዓይነት ከኬብሮን ሸለቆ ላከው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም በየሜዳው ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም፦ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፥ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለ። ሰውዮውም፦ “ከዚህ ተነሥተዋል፥ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ ይኸው መጣ። ኑ፥ እንግደለውና በአንዱ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሲሰማ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ” በማለት ከእጃቸው አዳነው። “ደም አታፍስሱ፥ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጉድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጉድጓዱ በተመለሰ ጊዜ፥ እነሆ ዮሴፍ በጉድጓድ የለም፥ ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ “ብላቴናው የለም፤ እኔስ ወዴት ልሂደው?” አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም ለይቶ ስላወቀው፦ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል” አለ። ያዕቆብ ልብሱንም ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፥ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም እንደዚህ ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብጽ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጶጥፋራ ሸጡት። በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ፥ ኤራስ ወደ ተባለ ዓዶሎማዊ ሰው ወረደ፤ እርሱም ዘንድ ለመኖር ቤቱ ገባ። እዚያም ሳለ፥ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ እርሷንም አግብቶ አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ዔር ተባለ። እንደገናም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙን አውናን አለችው። አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ አወጣችለት፤ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር። ይሁዳ የበኩር ልጁን ዔርን፥ ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። የይሁዳ የበኩር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር፤ ጌታም ቀሠፈው። በዚህ ጊዜ ይሁዳ አውናንን፥ “ዋርሳ እንደ መሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት” አለው። አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የእርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፥ ከወንድሙ ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ በፈጸመ ቍጥር የወንድሙንም ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወለድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስ ነበር። ይህም በጌታ ፊት ክፉ አድራጎት ሆኖ ስለ ተገኘ፥ እርሱንም ጌታ በሞት ቀሠፈው። ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፥ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፥ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፥ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጉር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር፥ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጉር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፥ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፥ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፥ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፥ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፥ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፥ “እባክሽ አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፥ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፥ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፥ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፥ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፥ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች። ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፥ መልእክተኛው ግን ሴትዮዋን ሊያገኛት አልቻለም። “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው። ሰዎቹም፥ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት። መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፥ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልኩም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። ይሁዳም፥ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፤ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ። ከሦስት ወር በኋላ፥ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው። ይሁዳም፥ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ። እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማትዋ፥ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፥ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው። ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፥ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፥ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም። የመውለጃዋ ጊዜ እንደደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ። በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፥ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤ ነገር ግን እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ። ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፥ ስሙም ዛራ ተባለ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፥ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። ጌታ ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም ጌታ ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወነለት ባየ ጊዜ፥ ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ የግብፃዊውን ቤት ባረከ፥ የጌታም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፥ ማናቸውንም ጉዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፥ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፥ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጉተውም፥ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፥ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሮአል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ ለእርዳታ መጮኼን ሲሰማም፥ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።” ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፥ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው። ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባርያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።” ጌታውም “ባርያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ፥ ተቈጣ። ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፥ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፥ ጌታ ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፥ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፥ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለማንኛውም ጉዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር። ከዚህም በኋላ የግብጽ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብጽን ንጉሥ በደሉት። ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፥ በሁለቱም ሹማምንቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው። የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር። እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደቈዩም፥ ታስረው የነበሩት የግብጽ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፥ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው። በማግስቱ ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። ስለዚህም፥ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ኀዘን ይነበባል?” በማለት አብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምንት ጠየቃቸው። እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጉምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፥ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቊጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፥ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ። እንግዲህ፥ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፥ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።” የእንጀራ ቤት አዛዡም፥ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም፥ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፥ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።” ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምንቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምንቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤ የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው። የሆነው ሆኖ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው። ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፥ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ እነሆ መልካቸው ያማረ፥ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፥ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፥ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። ፈርዖንም እንደገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፥ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብጽ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፥ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው። በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፥ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።” ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጉሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ። ፈርዖንም ዮሴፍን፥ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጉምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። ዮሴፍም ፈርዖንን፥ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። ከእነርሱም በኋላ፥ ዐቅመ ደካማ፥ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፥ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። ከዋጧቸውም በኋላ፥ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። እንደዚሁም፥ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።” ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፥ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። በመላው የግብጽ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፥ በግብጽ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፥ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፥ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፥ በመላው የግብጽ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፥ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። የሚከማቸው እህል፥ ወደ ፊት በግብጽ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።” ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። ፈርዖንም፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፥ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።” ከዚያም፥ ፈርዖን ዮሴፍን “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፥ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፥ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፥ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብጽ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው። ፈርዖንም ዮሴፍን “ጸፍናት ፐዕናህ” ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱጠ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብጽ ምድር ተዘዋወረ። ዮሴፍ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፥ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብጽን ምድር በሙሉ ዞረ። በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፥ ዮሴፍ በግብጽ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር። ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፥ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ዮሴፍም፥ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ፥ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው። እንደዚሁም፥ “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው። በግብጽ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፥ በመላው የግብጽ ምድር ግን ምግብ ነበር። ራቡ በመላው የግብጽ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፥ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፥ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው። ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለ ሄደ፥ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብጽ ጸንቶ ነበር። ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፥ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ምድር መጡ። ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን ሲሰማ፥ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ? በግብጽ እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ከመሞት መሰንበት ይሻላልና ወደዚያው ወርዳችሁ እህል ሸምቱልን” አላቸው። ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ወረዱ። ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፥ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋር አላከውም። ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፥ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፥ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት። ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፥ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቁጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፥ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም። በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፥ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤ ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።” እርሱም መልሶ፥ “አይደለም፤ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱ ግን መልሰው፥ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፥ አንዱ ግን የለም” አሉት። ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ! ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። በሉ፥ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፥ እስር ቤት ትቆያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፥ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው። ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው። በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፥ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ። እርስ በርሳቸውም፥ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፥ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። ሮቤልም መልሶ፥ “በዚህ ልጅ ላይ፥ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው። ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር። ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው። በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፥ እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፥ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፥ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ። እርሱም ወንድሞቹን፥ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፥ “እግዚአብሔር ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፥ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቁጣ ተናገረን። እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም። እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን፥ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’” “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ። ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያንም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።’” እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቾቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደ ተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፥ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ። አባታቸው ያዕቆብም፥ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ ኧረ ምን ጉድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። በዚህን ጊዜ ሮቤል አባቱን፥ “መልሼ ባላመጣው፥ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው፤ ኀላፊነቱን ለእኔ ተውልኝ፤ እኔው መልሼ አመጣዋለሁ” አለው። ያዕቆብም፥ “ልጄ አብሮአችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቷል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፥ ሽበቴን በመሪር ኀዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ” አላቸው። ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ ከግብጽ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ አባታቸው “እስቲ እንደገና ወርዳችሁ፥ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው። ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፥ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።” እስራኤልም፥ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታድያ፥ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት። ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፥ አንተም፥ እኛም፥ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘለዓለም በደለኛ እኔ ልሁን። ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፥ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።” ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፥ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውዬው በቶሎ ሂዱ። ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።” የእስራኤልም ልጆች እጅ መንሻውን፥ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብጽም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ። ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፥ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው። አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። የእስራኤልም ልጆች ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፥ “ወደዚህ የመጣነው፥ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውዬው ጥቃት ሊፈጽምብን፥ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ። ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፥ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ እንዲህም አሉት፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፥ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፥ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት። የቤቱ አዛዥም፥ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደሆንኩ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው። የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፥ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ። ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው። እነርሱም መልሰው፥ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት። ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፥ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፥ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፥ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፥ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ። ፊቱን ከታጠበ በኋላ፥ ተመልሶ፥ ስሜቱን በመቈጣጠር፥ “ማእድ ይቅረብ” አለ። ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። ወንድማማቾቹ ከበኩሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜአቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፥ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ “የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ብር በየስልቻቸው አፍ ክተተው። ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋር ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። ጎሕ ሲቀድ ሰዎቹ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። ከከተማው ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፥ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፦ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፥ ‘ለበጎ ነገር ስለምን ክፉ መለሳችሁ? ይህ ጌታዬ የሚጠጣበት፥ የተሰወረ ነገርም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? የፈጸማችሁት ድርጊት ክፉ ነው’” በላቸው። የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፥ ልክ እንደተባለው ተናገራቸው። እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባርያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ። ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፥ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በኀዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ። ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፥ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ። ዮሴፍም፥ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። ይሁዳም፥ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጦአል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ። ዮሴፍም፥ “ይህንንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባርያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው። ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖን ያህል የተከበርህ ስለሆንህ፥ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። ጌታዬ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቈ ነበር። እኛም፥ ‘አዎን፥ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር። ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፥ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፥ ‘ታናሽ ወንድማችሁ አብሮአችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገርነው። ከዚያም አባታችን ‘እስቲ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር፥ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፥ “በእርግጥ የአውሬ እራት ሆኖአል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቶአል። አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጉዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ኀዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፥ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፥ የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ኀዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። እኔ አገልጋይ፥ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፥ ለዘለዓለም በደለኛ አድርገህ ቁጠረኝ’ በማለት፥ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። ስለዚህ አሁን፥ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባርያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ። ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።” ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም፦ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፥ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ ማንም ከአጠገቡ የቆመ አልነበረም። ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፥ የግብጽ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። ዮሴፍም ለወንድሞቹ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፥ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ አለን?” አለ። ወንድሞቹም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና፥ ሊመልሱለት አልቻሉም። ዮሴፍም ወንድሞቹን “እስቲ ወደ እኔ ቅረቡ” አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፥ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። ይህ በምድር ላይ ሁለት ዓመት ራብ የሆነበት ነው፥ ገና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ይመጣል። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፥ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብጽ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፥ ከእኔም በቅርበት፥ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ። በዚያም፥ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፥ አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ።’ እነሆም የተናገረቻችሁ የእኔ አንደበት እንደ ሆነች የእናንተ ዐይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዐይኖች አይተዋል። ለአባቴም በግብጽ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፥ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፥ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፥ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ። በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፥” በሰሙትም ነገር ፈርዖንና አገልጋዮቹ ደስ ተሰኙበት። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ይህን አድርጉ፥ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከዓን ምድር ሂዱ፥ አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፥ እኔም የግብጽን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።’ አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፥ ከግብጽ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፥ ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብጽ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።” የእስራኤል ልጆችም እንደተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም አዳዲስ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። ለአባቱም እንደዚሁ፥ በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ምግብ ላከለት። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” እነርሱም ከግብጽ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ዮሴፍ ገና በሕይወቱ አለ፥ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ ሁሉ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ እስራኤልም፦ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፥ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ። እስራኤልም ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ ደረሰ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ። እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ፦ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ለእስራኤል ጠራው። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። እሱም አለው፦ “የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ወደ ግብጽ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና። እኔ ወደ ግብጽ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፥ የዮሴፍም እጅ ዓይንህን ይሸፍናል።” ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፥ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ። እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብጽ መጡ፥ ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብጽ ወሰደ። ወደ ግብጽም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፥ የያዕቆብ በኩር ሮቤል። የሮቤልም ልጆች፥ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ካርሚ። የስሞዖን ልጆች፥ ይሙኤል፥ ያሚን፥ አሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል። የሌዊም ልጆች፥ ጌድሾን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። የይሁዳም ልጆች፥ ዔር፥ ኦውናን፥ ሴላ፥ ፋሬስ፥ ዛራሕ፥ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፥ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል። የይሳኮር ልጆች፥ ቶላዕ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን። የዛብሎንም ልጆች፥ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል። ልያ በፓዳን-ኣሪም በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና፥ ሴቲቱ ልጇ ዲና እነዚህ ናቸው፥ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ናቸው። የጋድም ልጆች፥ ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤጽቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ። የአሴር ልጆች፦ ይምና፥ ይሽዋ፥ ይሽዊና በሪዓ ናቸው። እኅታቸው ሤራሕ ትባላለች። የበሪዓ ልጆች ደግሞ ሔቤርና ማልኪኤል ናቸው። እነዚህ ዐሥራ ስድስቱ ላባ ለልጁ ለልያ በሞግዚትነት ከሰጣት ከዚልፋ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤ እነርሱም ዮሴፍ በግብጽ ምድር ከኦን ከተማ ካህን ከጶጢፌራ ሴት ልጅ ከአስናት የወለዳቸው ናቸው። የብንያም ልጆች፦ ቤላዕ፥ ቤኬር፥ አሽቤል፥ ጌራ፥ ናዕማን፥ ኤሒ፥ ሮሽ፥ ሙፊም፥ ሑፊምና አረድ ናቸው። እነዚህ ዐሥራ አራቱ ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። የዳን ልጅ ሑሺም ነው። የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጼርና ሺሌም ናቸው። እነዚህ ሰባቱ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የሄዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች ሥልሳ ስድስት ናቸው፤ ይህም የልጆቹን ሚስቶች ቊጥር ሳይጨምር ነው። ለዮሴፍ በግብጽ ከተወለዱት ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር፥ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ቊጥር በአጠቃላይ ሰባ ነበር። በጌሴም ምድር እንዲቀበለው ያዕቆብ ይሁዳን ወደ ዮሴፍ አስቀድሞ ላከው፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ። ዮሴፍም ሠረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፥ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ። እስራኤልም ዮሴፍን፥ “አንተ በሕይወት መኖርህን ፊትህን አይቼ አረጋግጫለሁና፥ አሁን ልሙት አለው።” ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “እኔ መጥቼ ለፈርዖን፦ ‘እንግዲህ በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤት ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፥ እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ፥’ ብዬ እነግረዋለሁ። ፈርዖንም ቢጠራችሁ፦ ‘ሥራችሁስ ምንድነው?’ ቢላችሁ፥ በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብጽ ሰዎች ርኩስ ነውና፥ በጌሤም እንድትቀመጡ፦ ‘እኛ አገልጋዮችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን’ በሉት።” ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው። ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው። ፈርዖንም ወንድሞቹን፦ “ሥራችሁ ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን፦ “እኛ አገልጋዮችህ፥ እኝም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን” አሉት። “በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፥ የአገልጋዮችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለም፥ አሁንም አገልጋዮችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።” አሉት ፈርዖንን። ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፥ የግብጽ ምድር በፊትህ ናት፥ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፥ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱ መካከል ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።” ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፥ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። ፈርዖንም ያዕቆብን፦ “የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው?” አለው። ያዕቆብም ለፈርዖን አለው፦ “የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፥ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፋም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።” ፈርዖንን ባርኮም ያዕቆብ ከፈርዖንም ፊት ወጣ። ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብጽ ምድር በተሻለችው የራምሴ ምድር በይዞታ ሰጣቸው። ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው። ራብም እጅግ ጸንቶአልና፥ በምድር ሁሉ እህል አልነበረም፥ ከራብም የተነሣ የግብጽ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። ዮሴፍም የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች የመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። በግብጽ ምድርና በከነዓን ምድር ብሩም በሸመታ አለቀ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉም ወደ ዮሴፍ እየመጡ፦ “የምንመገበው ስጠን፥ ስለምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና” አሉት። ዮሴፍም፦ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፥ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፥ ያንንም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ልዋጭ ህልን መገባቸው። ዓመቱም ተፈጸመ፥ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ከጌታችን አንሰውርም፥ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፥ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፥ እኛ በፈትህ ስለምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባርያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፥ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።” ዮሴፍም የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፥ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። ሕዝቡንም ሁሉ ከግብጽ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባርያዎች አደረጋቸው። የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፥ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፥ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፥ በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፥ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ምግብ ይሁን።” እነርሱም፦ “አንተ ሕይወታችንን አተረፍክ፥ ጌታችንን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፥ ለፈርዖንም ባርያዎች እንሆናለን” አሉት። ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዓን እንዲሆን በግብጽ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት። እስራኤልም በግብጽ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፥ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ። ያዕቆብም በግብጽ ምድር ዐሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፥ የያዕቆብም የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው። የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፥ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብጽ ምድርም እንዳትቀብረኝ በታማኝነትና እውነት ቃል ግባልኝ፥ ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብጽ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ።” እርሱም፦ “እንደ ቃልህ አደርጋሁ” አለ። እርሱም፦ “ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፥ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ። ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ተነገረው፤ ስለዚህ ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ያዕቆብን ለማየት ሄደ። ለያዕቆብም፦ “እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል” ብለው ነገሩት፥ እስራኤልም ሰውነቱን አበረታቶ፥ በአልጋው ላይ ተቀመጠ። ያዕቆብ ዮሴፍን አለው፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም ደግሞም፦ ‘እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፥ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘለዓለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ።’” አለኝ። አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፥ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፥ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። እኔም ፓዳን በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት መንገድ ቀርቶኝ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፥ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ ቀበርኋት፥ እርሷም ቤተልሔም ናት። እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ፦ “እነዚህ እነማን ናቸው?” አለው። ዮሴፍም ለአባቱ፦ “እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው” አለ። እርሱም፦ “እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ” አለ። የእስራኤልም ዐይኖች ከሽምግልና የተነሣ ደክመው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም። እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፥ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ” አለው። ዮሴፍም ከጉልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ። ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፥ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኩር ነበርና። ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፥ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፥ በምድርም መካከል ይብዙ።” ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፥ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። ዮሴፍም አባቱን፦ “አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኩሩ ይህ ነውና፥ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ” አለው። አባቱም እንዲህ ሲል እንቢታውን ገለጸ፦ “አውቄአለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቄአለሁ፥ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፥ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።” ስለዚህ በዚያን ቀን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፥ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ።” እስራኤልም ዮሴፍን፦ “እነሆ እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፥ እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወስድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ” አለው። ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ “በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብስቡ። እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፥ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ። ሮቤል፥ አንተ በኩር ልጄና ኃይሌ፥ የጉብዝናዬም መጀመሪያ፥ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ። እንደ ውኃ የምትዋልል፥ አለቅነት ለአንተ አይሁን፥ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፥ አረከስኽውም፥ ወደ አልጋዬም ወጣ። ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፥ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፥ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፥ በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። ቁጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፥ ኩርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፥ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ። ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፥ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፥ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፥ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፥ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፥ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፥ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል። ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፥ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም። ዓይኑም ከወይን ይቀላል፥ ጥርሱም ከወተት ይነጻል። ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፥ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፥ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው። ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጉረኖም መካከል ያርፋል። ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፥ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በከባድ ጉልበት ሥራ አገልጋይ ሆነ። ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ። ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፥ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል። ጌታ ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ። ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፥ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል። የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል። ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፥ መልካም ቃልን ይሰጣል። ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፥ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፥ ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፥ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረብቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ። ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነው፥ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።” እነዚህም ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፥ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፥ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው። እንዲህ ብሎም አዘዛቸው፦ “እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፥ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፥ እርሷም በከነዓን ምድር ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በኩል በማክፌላ የሚገኘው ነው፤ አብርሃም ይህ ዋሻ የሚገኝበትን እርሻ ለመቃብር ቦታ የገዛው ከሒታዊው ከዔፍሮን ነው።” አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፥ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፥ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፥ እርሻውና በእርሷ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው። ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋ ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም። ዮሴፍም አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። መድኃኒት ቀማሚዎቹም በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው። ግብጻውያን ሰባ ቀን ሙሉ አለቀሱለት። የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደሆን ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ አባቴ፦ ‘እነሆ እኔ እሞታለሁ፥ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ’ ሲል አስምሎኛል። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።” ፈርዖንም፦ “ሂድ፥ አባትህን እንዳስማለህ ቅበረው” አለው። ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፥ የፈርዖን አገልጋዮቹም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችና የግብጽ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፥ የዮሴፍም ቤተሰቦች ሁሉ፥ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተሰቦች ወጡ፥ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ። ሰረጎሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ። በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፥ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፦ “ይህ ለግብጽ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፥” ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፥ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፥ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፥ እርሷም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብጽ ተመለሱ። የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ “ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ ‘እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፥ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባርያዎች የበደሉህን ይቅር በል።’” ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ “እነሆ እኛ ለአንተ ባርያዎችህ ነን አሉት።” ዮሴፍም አላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን ነኝ? እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ፥ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ፥ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ “እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ “እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ” አስማላቸው። ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ በሽቶም አሹት፥ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት። ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዳቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ገቡ። ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊና ይሁዳ ይሳኮር፥ ዛብሎንና ብንያም ዳንና ንፍታሌም፥ ጋድና አሴር። ከያዕቆብ ጉልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብጽ ነበር። ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም ሁሉ፥ ያም ትውልድ ሁሉ። ነገር ግን የእስራኤል ትውልዶች ፍሬያማ ነበሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ እጅግም በረቱ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ እንዳይበዙ፥ ጦርነትም በተነሣብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ ኑ በጥበብ እንምከር።” በብርቱ ሥራ እንዲያስጨንቁአቸው ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራዓምሴስን የማከማቻ ከተሞች አድርገው ሠሩ። ነገር ግን በጨቆኑአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ሰፉ፤ ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። ግብፃውያንም እስራኤላውያንን በጭካኔ እንዲሠሩ አስገደዱአቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን አስመረሩት። የግብጽም ንጉሥ የዕብራውያንን አዋላጆች አንዲቱ ሺፍራ ሁለተኛይቱም ፑአ የሚባሉትን እንዲህ አላቸው፦ “የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደ ደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብጽ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ተዋቸው። የግብጽም ንጉስ አዋላጆቹን ጠርቶ፦ “ለምን ይህን አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን በሕይወት እንዲኖሩ ፈቀዳችሁላቸው?” አላቸው። አዋላጆቹም ፈርዖንን፦ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጽ ሴቶች አይደሉም፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው” አሉት። እግዚአብሔርም ለአዋላጆቹ መልካም ነገርን አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ብርቱ ሆነ። አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤተሰብን ሰጣቸው። ፈርዖንም፦ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ዓባይ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት እንድትኖር ተዉአት” ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። ከሌዊ ወገን የሆነ አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም እዚያ ውስጥ አስገባችው፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። እኅቱም ምን እንደሚደርስበት ለማየት በሩቅ ቆማ ትከታተለው ነበር። የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥሩዋንም ልካ አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም፦ “ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንዱ ነው” አለች። እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ “ሕፃኑን እንድታጠባልሽ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት፤ የፈርዖንም ልጅ፦ “ሂጂ” አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። የፈርዖንም ልጅ፦ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ አመጣችው፥ ለእርሷም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። በነዚያም ቀኖች፥ ሙሴ ባደገ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብጽም ሰው ከወንድሞቹ አንድ የሆነውን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለው፥ በአሸዋም ውስጥ ደበቀው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለት ዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፥ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። እሱም፦ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፥ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። የምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውሀውን ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ አባታቸው ወደ ሩኤልም ሄዱ እርሱም፦ “ለምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “አንድ ግብፃዊ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ” አሉት። ልጆቹንም፦ “ሰውዬው የት ነው? ለምንስ ይህንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት ምግብም ይብላ” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ፈቀደ፤ ልጁንም ጺጶራን ለሙሴ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች፦ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን “ጌርሾም” ብሎ ጠራው። ከብዙ ቀኖች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ሕዝቦች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለባርነታቸውም የልመና ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሕዝቦች አየ፥ እግዚአብሔርም የደረሰባቸውን ነገር አወቀ። ሙሴም የምድያን ካህን የሆነውን የአማቹን የይትሮን በጎች ያሰማራ ነበር፤ በጎቹን ከምድረ በዳው ማዶ ነዳቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የጌታም መልአክ በእሳት ነበልባል በቁጥቋጦው መካከል ታየው፤ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም፦ “ልሂድና ይህን ታላቅ ራእይ ልይ ቁጥቋጦው ለምን አልተቃጠለም?” አለ። ጌታም እርሱን ሊያይ እንደመጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቁጥቋጦው መካከል፦ “ሙሴ፥ ሙሴ” ብሎ ጠራው። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። እርሱም “ወደዚህ አትቅረብ፤ ጫማህን ከእግርህ አውልቅ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ መሬት ነውና” አለው። እርሱም፦ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ማየት ፈርቶ ፊቱን ሸፈነ። ጌታም አለ፦ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ በአስገባሪዎቻቸውም ምክንያት የሚጮሁትን ጩኸት ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ። ከግብፃውያን እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወደ መልካምና ሰፊ አገር፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ከነዓናውያን፥ ሒቲያውያን፥ ኤሞራውያን፥ ፌርዛውያን፥ ሒዊያውያን፥ የቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። አሁን ደግሞ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ መጣ፤ ግብፃውያን የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። ስለዚህ ሂድ፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ እንድታወጣ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።” ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልንም ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እርሱም፦ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ይሆናል፤ ሕዝቡን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታገለግላላችሁ” አለ። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “እኔ ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ’ ባልሁ ጊዜ፦ ‘ስሙ ማን ነው?’ ቢሉኝ፥ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “የምኖር እኔ ነኝ” አለው፤ ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች፦ “‘የምኖር’ ወደ እናንተ ላከኝ በላቸው” አለው። እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘ጌታ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ፤’ ይህ ለዘለዓለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።” ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ትሰበስባለህ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ “ጌታ የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ ‘ጎበኘኋችሁ፥ በግብጽም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብጽም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ።’ እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብጽ ንጉሥ ትሄዳላችሁ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ጌታ ተገለጠልን፤ ስለዚህ ለአምላካችን ለጌታ እንድንሠዋ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ’ ትሉታላችሁ። ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር የግብጽ ንጉሥ እንድትሄዱ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብጽን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፥ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር እቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።” ሙሴም መለሰ፦ “እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ ‘ጌታ ከቶ አልተገለጠልህም’ ይሉኛል” አለ። ጌታም፦ “ይህ በእጅህ ያለው ምንድነው?” አለው። እርሱም፦ “በትር ነው” አለ። እርሱም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ እርሱም ወደ መሬት ጣለው፥ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዘው በእጁም ውስጥ በትር ሆነ። “ይህም የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ ጌታ እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው ጌታም ደግሞ፦ “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አስገባ፤ ባወጣውም ጊዜ፥ እጁ እንደ በረዶ ነጭ እንደሆነ አየ። እርሱም፦ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሰው፥ ከብብቱም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ ገላውን እንደሚመስል አየ። “እንዲህ ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ቃል ባይሰሙ፥ የኋላኛይቱን ምልክት ቃል ያምናሉ። እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዓባይ ወንዝ ጥቂት ውኃን ውሰድ፥ በደረቅ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከዓባይ ወንዝ የወሰድከውም ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም ጌታን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፌንና ምላሴን ይይዘኛል።” ጌታም እንዲህ አለው፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳ ወይም ደንቆሮ ወይም የሚያይ ወይም ዕውር ያደረገ ማን ነው? እኔ ጌታ አይደለሁምን? ስለዚህ ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ።” እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለ። የጌታም ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር አውቃለሁ፤ እርሱም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ያይሃልም፤ በልቡም ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ ቃሎቹን በአፉ ታስቀምጣለህ፤ እኔም ከአፍህ ጋርና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ለአንተ ብሎ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም እንደ እግዚአብሔር ትሆንለታለህ። ይህንንም ተአምራት የምታደርግበትን በትር በእጅህ ይዘኸው ትሄዳለህ።” ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ይትሮ ተመለሰ፥ እርሱም፦ “እባክህን በግብጽ ወዳሉ ዘመዶቼ እንድመለስ እስካሁንም በሕይወት እንዳሉ ሄጄ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። ይትሮም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። ጌታም ሙሴን በምድያን፦ “ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ ነፍስህን የሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብጽም ምድር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብጽ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ ተመልከት በፈርዖንም ፊት ታደርጋቸዋለህ፤ እኔም ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።’” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በማደሪያው ስፍራ ጌታ ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። ፂፖራም ባልጩት ወሰደች፥ የልጇንም ሸለፈት ገረዘች፥ እግሩንም ነክታ፦ “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ፦ “ለግርዛቱ የደም ሙሽራ” አለች። ጌታም አሮንን፦ “ሙሴን ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። ሙሴም ለአሮን በእርሱ ዘንድ የላከውን የጌታን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎችንም ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም ጌታ ለሙሴ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቶቹንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ጌታ የእስራኤልን ልጆች እንደተመለከተ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ ሰገዱም። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ።’” ፈርዖንም፦ “ቃሉን እንድሰማ እስራኤልንስ እንድለቅ ጌታ ማን ነው? ጌታን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም” አለ። እነርሱም፦ “የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለጌታ ለአምላካችን እንድንሠዋ እንለምንሃለን ካልሆነ ተላላፊ በሽታ ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን” አሉት። የግብጽ ንጉሥም፦ “ሙሴና አሮን፥ ለምን ሕዝቡን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ” አላቸው። ፈርዖንም፦ “እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ” አለ። ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምንቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “እንደ ቀድሞው ለጡብ ሥራ የሚሆን ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ እነርሱ ራሳቸው ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። ቀድሞ ይሠሩት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ከእርሱ አታጉድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፦ ‘ለአምላካችን እንድንሰዋ መሄድ እንፈልጋለን’ እያሉ ይጮኸሉ። ሥራውን እንዲሰሩት፥ የሃሰትን ቃላት እንዳያስቡ፥ በሰዎቹ ላይ ሥራው ይክበድባቸው።” የሕዝቡ አስገባሪዎችና ሹማምንቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም አሉት፦ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ ‘ገለባ አልሰጣችሁም። እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጉደል።’” ሕዝቡም ለገለባ የሚሆን እብቅ ሊሰበስቡ በግብጽ ምድር ሁሉ ተበተኑ። አስገባሪዎቹም፦ “ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ” እያሉ አስቸኮሉአቸው። የፈርዖንም አስገባሪዎች፦ “የተወሰነላችሁን የጡብ ሥራ ትናንትናና ዛሬ ለምን እንደ ቀድሞው አልጨረሳችሁም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ። የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ ብለው ጮሁ፦ “ለምን አገልጋዮችህን እንዲህ ታደርጋለህ? ለአገልጋዮችህ ገለባ አልተሰጠም፥ ጡብ ሥሩ ይሉናል፤ እነሆ አገልጋዮችህ ተገረፍን፤ ይህም ሕዝብህን ሐጢአተኛ ያደርጋል።” እርሱም አላቸው፦ “ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለጌታም እንሠዋ’ ትላላችሁ። ስለዚህም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጣችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ።” የእስራኤልም ልጆች አለቆች፦ “ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጉድሉ” በተባሉ ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን ቆመው አገኙአቸው። እነርሱም፦ “ጌታ እናንተ ላይ ይፍረድባችሁ፥ ሽታችንን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት አግምታችሁታልና፥ እንዲገድሉንም ሰይፍን በእጃቸው አስቀምጣችኋዋልና” አሉአቸው። ሙሴም ወደ ጌታ ተመለሰና፦ “ጌታ ሆይ፥ ለምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ለምንስ ላክኸኝ? በስምህ እንድናገር ወደ ፈርዖን ከሄድኩ ጀምሮ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም” አለ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “አሁን ፈርዖንን ምን እንደማደርገው ታያለህ በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋል፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል።” እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብም ሁሉን የሚችል አምላክ ሆኜ ተገለጥኩላቸው፤ ጌታ የሚለውን ስሜን ግን አላስታወቅኳቸውም። ደግሞም የከነዓንን ምድር፥ በእንግድነት ተቀምጠውበት የነበረውን የእንግድነታቸው ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን መሰረትኩ። ደግሞም እኔ ግብፃውያን እንዲሰሩ የሚያስገድዷቸውን የእስራኤልን ልጆች ጩኸት ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ጌታ ነኝ፥ ከግብፃውያን ጭቆና አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድ በታላቅ የፍርድ ሥራም አድናችኋለሁ፤ ለእኔ ሕዝብ አድርጌ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብጽ ጭቆና ያወጣኋችሁ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣታለሁ ብዬ እጄን ወደ አነሳሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ እርሷንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።’” ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከመንፈሳቸው መሰበር ከከባዱም ሥራ የተነሣ ሙሴን አልሰሙትም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ግባ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከምድሩ እንዲለቅ ንገረው።” ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ ታድያ እንዴት ፈርዖን ይሰማኛል? እኔ ደግሞ ከንፈሬ ያልተገረዘ ሰው ነኝ” ብሎ ተናገረ። ጌታም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የእስራኤልን ልጆችንና የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ እንዲያወጣቸው እንዲነግሩት አዘዛቸው። የአባቶቻቸው ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል ልጆች ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔፅሮንና ካርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው። የስምዖንም ልጆች ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሻኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው። እነዚህ የሌዊ ልጆች ስሞች እንደ ትውልዳቸው ጌርሾን፥ ቀሃት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። የጌርሾንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሊብኒና፥ ሽምኢ ናቸው። የቀሃትም ልጆች ዓምራም፥ ይፅሃር፥ ሔብሮን፥ ዑዚኤል ናቸው፤ የቀሃትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። የሜራሪ ልጆች ማሕሊ፥ ሙሺ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው። ዓምራምም የአባቱን እኅት ዮካቤድን አገባ፥ አሮንንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የዓምራምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። የይፅሃር ልጆች ቆራሕ፥ ኔፌግ፥ ዚክሪ ናቸው። የዑዚኤል ልጆች ሚሻኤል፥ ኤልጻፋን፥ ሢትሪ ናቸው። አሮንም የዓሚናዳብን ልጅ የናሕሾንን እኅት ኤሊሼባን አገባ፥ እርሷም ናዳብ፥ አቢሁ፥ ኤልዓዛርንና ኢታማርን ወለደችለት። የቆራሕ ልጆች አሲር፥ ኤልቃናና፥ አቢያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆራሓውያን ወገኖች ናቸው። የአሮንም ልጅ ኤልዓዛር ከፑቲኤል ልጆች አንዷን ሚስት አገባ፥ እርሷም ፒንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። እነዚህ አሮንና ሙሴ ጌታ፦ “የእስራኤልን ልጆች በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር አውጡ” ያላቸው ናቸው። እነዚህ ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ስለማውጣት የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህም ሙሴና አሮን ናቸው። ጌታ በግብጽ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን፥ እርሱም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እኔ የምነግርህን ሁሉ ንገረው።” ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ እኔ ከንፈሬ ያልተገረዘ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል?” አለ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይህ ይሆናል። አንተ ያዘዝሁህን ሁሉ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ እንዲለቅ ፈርዖንን ይነግረዋል። እኔም የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፥ ምልክቶቼንና ድንቆቼን በግብጽ ምድር ላይ አበዛለሁ። ፈርዖንም እናንተን አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብጽ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴን፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች፥ በታላቅ የፍርድ ሥራ ከግብጽ ምድር አወጣለሁ። ግብፃውያንም፥ እጄን በግብጽ ላይ ዘርግቼ የእስራኤልን ልጆች ከመካከላቸው ሳወጣ፥ እኔ ጌታ እንደሆንኩ ያውቃሉ።” ሙሴና አሮንም እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ። ፈርዖንን ባናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበር፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበር። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ፈርዖን ‘ተአምራትን በማድረግ ማንነታችሁን አሳዩኝ’ ሲላችሁ፥ አሮንን ‘በትርህን ወስደህ እባብ እንዲሆን በፈርዖን ፊት ጣለው’ በለው፥ በትሩም እባብ ይሆናል።” ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ሄዱ፥ ጌታም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነ። ፈርዖንም ጠቢባንንና አስማተኞችን ጠራ፤ የግብጽም አስማተኞች ደግሞ በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠ። ልክ ጌታ እንደ ተናገረው የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቅም አለ። ወደ ፈርዖን በጠዋት ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ አንተም እንድትገናኘው በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ ወደ እባብም የተለወጠውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። እንዲህም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ የዕብራውያን አምላክ፦ በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ፥ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆ አንተ እስከ ዛሬ አልሰማህም። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ እንደሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ በዓባይ ወንዝ ያለውን ውኃ በእጄ ባለው በትር እመታለሁ፥ ወደ ደምም ይለወጣል። በዓባይ ወንዝ ያሉትም ዓሦች ይሞታሉ፥ የዓባይ ወንዝም ይገማል፤ ግብፃውያንም የዓባይን ወንዝ ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ።’” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ውሰድ፥ በግብጽ ውኆች፥ በፈሳሾቻቸው፥ በወንዞቻቸው፥ በኩሬዎቻቸው፥ በውኃ ማጠራቀሚያዎቻቸውም ላይ ደም እንዲሆኑ እጅህን ዘርጋ፤ በግብጽም ምድር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል።’” ሙሴና አሮንም ልክ ጌታ እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በአገልጋዮቹም ፊት በዓባይ ወንዝ የነበረውን ውኃ መታ፤ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረው ውኃ ሁሉ ወደ ደም ተቀየረ። በዓባይ ወንዝ የነበሩ ዓሦችም ሞቱ፤ የዓባይም ወንዝ ገማ፥ ግብጻውያንም ከዓባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉም፤ ደሙም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ነበረ። የግብጽም አስማተኞች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ጸና፥ ጌታም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። ግብጽም ሁሉ የዓባይ ወንዝ አካባቢውን ቆፈሩ የዓባይን ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉምና። ጌታ ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ። ጌታም ሙሴን ተናገረው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በእንቁራሪቶች እመታለሁ። የዓባይ ወንዝም በእንቁራሪቶች ይሞላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ አገልጋዮችህና ሕዝብህም ቤት፥ ወደ ምድጆችህ፥ ወደ ማቡኪያ ዕቃህም ይገባሉ፤ እንቁራሪቶቹም በአንተ፥ በሕዝብህና በሁሉም አገልጋዮችህ ላይ ይወጣሉ።’” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን ‘በትርህን ይዘህ እጅህን በፈሳሾቹ በወንዞቹና በኩሬዎቹ ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብጽም ምድር ላይ እንቁራሪቶችን አውጣ’ በለው።” አሮንም በግብጽ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ እንቁራሪቶቹም ወጡ፥ የግብጽንም ምድር ሸፈኑ። አስማተኞችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብጽም ምድር ላይ እንቁራሪቶችን አወጡ። ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “እንቁራሪቶቹን ከእኔና ከሕዝቤ እንዲያርቅ ወደ ጌታ ጸልዩልኝ፤ ለጌታም እንዲሠዋ ሕዝቡን እለቅቃለሁ” አላቸው። ሙሴም ፈርዖንን፦ “እንቁራሪቶቹ ከአንተና ከቤቶችህ እንዲጠፋ፥ በዓባይ ወንዝም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ፥ ለአገልጋዮችህና ለሕዝብህ መቼ እንድጸልይ ንገረኝ” አለው። እርሱም፦ “ነገ” አለ። ሙሴም እንዲህ አለው፦ “ጌታ አምላካችንን የሚመስል እንደሌለ እንድታውቅ እንደ ቃልህ ይሁን። እንቁራሪቶቹን ከአንተ ከቤቶችህም ከአገልጋዮችህም ከሕዝብህም ያርቃል፤ በዓባይ ወንዝ ብቻ ይቀራሉ።” ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ። ሙሴም ከፈርዖን ጋር እንደተስማማው ስለ እንቁራሪቶቹ ወደ ጌታ ጮኸ። ጌታም እንደ ሙሴ ቃል አደረገ፤ እንቁራሪቶቹም በየቤቶቹ፥ በየመንደሮቹና በሜዳም ሞቱ። እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድሪቱም ገማች። ፈርዖንም እረፍት እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ጌታም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “አሮንን ‘በትርህን ዘርጋ፥ በግብጽ ምድር ሁሉ ተናካሽ ትንኝ እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው።’” እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታ፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ተናካሽ ትንኝ ሆነ፤ በግብጽ ምድር ያለ የምድር ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። አስማተኞችም በአስማታቸው ተናካሽ ትንኝ ለማውጣት እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ተናካሽ ትንኝም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። አስማተኞቹም ፈርዖንን፦ “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ጌታም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቅረብ፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ሕዝቤን ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ ላይ፥ በአገልጋዮችህ ላይ፤ በሕዝብህ ላይ፥ በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጋ እልካለሁ፤ የግብፃውያንም ቤቶች፥ የቆሙባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጋ ይሞላሉ። በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ ጌታ እንደሆንሁ እንድታውቅ፥ የዝንብ መንጋ በእርሷ ላይ እንዳይሆን፥ ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጎሼንን ምድር እለያለሁ። በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህም ምልክት ነገ ይሆናል።’” ጌታም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖን ቤት፥ በአገልጋዮቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብጽም ምድር ሁሉ ላይ፤ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ተበላሸች። ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፦ “ሂዱ፥ በምድሪቱ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው። ሙሴም፦ “እንዲህ ማድረግ ተገቢ አይደለም ለጌታ አምላካችን የግብፃውያንን ርኩሰት እንሰዋለንና፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኩሰት በፊታቸው ብንሠዋ በድንጋይ አይወግሩንምን? የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን ለጌታ ለአምላካችን እርሱ እንዳለን እንሠዋለን።” ፈርዖንም፦ “ለጌታ አምላካችሁ በምድረ በዳ እንድትሠዉ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፥ ጸልዩልኝ” አለ። ሙሴም፦ “እነሆ እኔ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፥ የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፥ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ነገ እንዲሄዱ ወደ ጌታ እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለጌታ ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን” አለ። ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፥ ወደ ጌታም ጸለየ። ጌታም እንደ ሙሴ ቃል አደረገ፤ የዝንቡንም መንጋ ከፈርዖን ከአገልጋዮቹም ከሕዝቡም ተወገደ፤ አንድ እንኳ አልቀረም። ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል፥ ብትይዛቸውም፥ እነሆ የጌታ እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶች፥ በአህዮች፥ በግመሎች፥ በበሬዎችና በበጎች ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ተላላፊ በሽታ ይወርዳል። ጌታም በእስራኤልና በግብጽ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አይሞትም።’” ጌታም፦ “ነገ ጌታ ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል” ብሎ ጊዜን ወሰነ። ጌታም ያንን ነገር በማግስቱ አደረገ፥ የግብጽም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማያት ይበትነዋል። እርሱም በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብጽም ምድር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ይሆናል።” ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማያት በተነው፥ በሰውና በእንስሳ ላይም ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ሆነ። ብጉንጅ በጠንቋዮቹና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ነበር፤ ጠንቋዮቹም ብጉንጅ ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ ጌታ ሙሴን እንደ ተናገረው ፈርዖን አልሰማቸውም። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም እንዲህም በለው፦ የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። በዚህ ጊዜ መቅሠፍቴን ለልብህ በአገልጋዮችህ በሕዝብህም በምድር ሁሉ ላይ እልካለሁ ይህም እንደ እኔ ያለ እንደሌለ እንድታውቅ ነው። አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን በተላላፊ በሽታ በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ ነገር ግን እንድትቆም ያደረግኩት ኃይሌን እንድገልጥብህና ስሜም በምድር ሁሉ ላይ እንዲታወጅ ነው። እንዳትለቅቃቸው አሁንም በሕዝቤ ላይ ትታበያለህ፤ እነሆ እኔ ነገ በዚህ ጊዜ በግብጽ፥ ከተመሠረተች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ከባድ በረዶ አዘንባለሁ። ስለዚህም ልከህ ከብቶችህንና በሜዳ ያለ የአንተ የሆነውን ሁሉ አምጣ፤ በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንሰሳ ሁሉ ላይ በረዶ ይወርዳል እነርሱም ይሞታሉ።’” ከፈርዖን አገልጋዮች የጌታን ቃል የፈራ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤ የጌታንም ቃል በልቡ ያላስቀመጠ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ በሰው፥ በከብት፥ በእርሻ ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብጽ ምድር ሁሉ በረዶ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ።” ሙሴም በትሩን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤ ጌታም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ ጌታም በግብጽ ምድር ላይ በረዶ አዘነበ። በረዶና እሳት ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እጅግ ከባድ የሚበርቅ እሳት ነበር፥ በግብጽ ምድር ሁሉ አገር ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ሆኖ አያውቅም። በረዶውም በግብጽ ምድር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ከሰው እስከ እንስሳ መታ፤ የእርሻን ቡቃያ መታ፥ በረዶውም የአገሩን ዛፍ ሁሉ ሰበረ። የእስራኤል ልጆች በነበሩባት በጎሼን ምድር ብቻ በረዶ አልነበረም። ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በዚህ ጊዜ ኃጢአትን ሰርቻለሁ፤ ጌታ ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም በደለኞች ነን። የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ ጌታ ጸልዩ፤ እለቅቃችኋለሁ፥ ከዚህ በኋላ እዚህ አትቀመጡም።” ሙሴም እንዲህ አለው፦ “ከከተማ እንደ ወጣሁ እጄን ወደ ጌታ እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ የጌታ እንደ ሆነች እንድታውቅ፥ ነጎድጓዱ ይቆማል፥ በረዶውም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። አንተና አገልጋዮችህ ጌታ አምላክን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁና።” ገብሱና ተልባው ተመታ፤ ገብሱ ገና እሸት ተልባውም እንቡጥ ስለ ነበረ ነው። ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም። ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ ጌታ ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ቆመ፥ ዝናቡም ወደ ምድር አልዘነበም። ፈርዖንም ዝናቡ፥ በረዶውና ነጎድጓዱ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ ኃጢአትን ጨመረ፥ እርሱና አገልጋዮቹም ልባቸውን አደነደኑ። የፈርዖንም ልብ ጸና፤ ጌታም በሙሴ አፍ እንደ ተናገረ የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እኔ ልቡንና የአገልጋዮቹን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው ምልክቶቼን እንዳሳይ ነው። ይህም በልጅህና በልጅ ልጅህ ጆሮ እንድትነግርና ግብፃውያንን እንዴት እንዳሞኘኋቸው፥ በመካከላቸው ያስቀመጥኩት ምልክቶቼም ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው።” ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በፊቴ እራስህን ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ እኔ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤ የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታል፥ ማንም ምድሩን ማየት አይችልም፤ ከበረዶውም ተርፎ የቀረላችሁን ሁሉ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም በሜዳ ያለ ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤ ቤቶችህም የአገልጋዮችህም ቤቶች ሁሉ የግብጽንም ቤቶች ሁሉ ይሞሉታል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ አላዩም።’” ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። የፈርዖንም አገልጋዮች፦ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? ጌታ አምላካቸውን እንዲያገለግሉት ወንዶቹን ልቀቃቸው፥ ግብጽስ እንደ ጠፋች ገና አላወቅህምን?” አሉት። ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን አመጡአቸው፦ “ሂዱ፥ ጌታ አምላካችሁን አገልግሉ፥ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። ሙሴም፦ “ወጣቶቻችን፥ ሽማግሌዎቻችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፥ በጎቻችንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ የጌታን በዓል እናደርጋለንና” አለ። እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን እናንተንና ልጆቻችሁን እለቅቃለሁ፥ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ። እንዲህ አይሆንም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱና ጌታን አገልግሉ፥ የጠየቃችሁት ይህንን ነውና።” ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው። ጌታም ሙሴን፦ “አንበጣዎቹ በግብጽ ምድር ላይ እንዲመጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም በግብጽ ምድር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ ጌታም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ በነጋም ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ። አንበጣዎችም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብጽም አገር ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፥ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ ያለ አይሆንም። የምድሩንም ፊት ሸፈኑት ምድሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር በዛፉ ላይም በቡቃያው ላይም በግብጽ ምድር ሁሉ አልቀረም። ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠራና እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ አምላካችሁንና እናንተን በደልሁ፤ አሁን እንግዲህ አንድ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንን ሞት ከእኔ እንዲያነሣልኝ ብቻ ጌታ አምላካችሁን ለምኑልኝ።” እርሱም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ ጌታም ፀለየ። ጌታም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን መለሰ፥ አንበጣዎቹንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ ስንኳ አንበጣ በግብጽ አገር አልቀረም። ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም። ጌታም ሙሴን፦ “በግብጽ ምድር ላይ ጨለማ እንዲሆን፥ ማንም ሰው የሚያውቀው ጨለማ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ሰማያት ዘረጋ፥ በግብጽም ምድር ሁሉ ላይ ሦስት ቀን ፅኑ ጨለማ ሆነ፤ ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ማንም ከስፍራው አልተነሣም፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው። ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ፦ “ሂዱ፥ ጌታን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር ይሂዱ” አለው። ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ደግሞ ለጌታ አምላካችን የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን በእጃችን ትሰጠናለህ። ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አንድ ሰኮናም አይቀርም፥ ጌታ አምላካችንን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና፤ ጌታን የምናገለግለው በምን እንደሆነ እዚያ እስክንደርስ አናውቅም።” ጌታ ግን የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም። ፈርዖንም፦ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ተጠንቀቅ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ” አለው። ሙሴም፦ “እንደ ተናገረህ ይሁን፤ ፊትህን እንደገና አላይም” አለ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በፈርዖንና በግብጽ ላይ ገና አንድ መቅሰፍት አመጣለሁ፥ ከዚያ በኋላ ከዚህ ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም ሙሉ በሙሉ ያባርራችኋል። ወንዱ ከጎረቤቱ ሴቲቱም ከጎረቤቷ የብር ዕቃና የወርቅ ዕቃ እንዲጠይቁ በሕዝቡ ጆሮ ተናገር።” ጌታም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስን ሰጠ። ሙሴም በግብጽ ምድር፥ በፈርዖን አገልጋዮች ፊትና በሕዝቡ ፊት እጅግ ታላቅ ሰው ነበረ። ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በእኩለ ሌሊት እኔ በግብጽ መካከል እወጣለሁ፤ በግብጽም ምድር ያለ በኩር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባርያይቱ በኩር ድረስ፥ የከብቱም በኩር ሁሉ ይሞታል። በግብጽ ምድር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ ኋላም ደግሞ የማይሆን ታላቅ ለቅሶ ይሆናል። በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም ይህም ጌታ በግብጽና በእስራኤል መካከል እንደለየ እንድታውቁ ነው። እነዚህም አገልጋዮችህ ሁሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፥ ለእኔም ይሰግዳሉ፥ ‘አንተ ውጣ በሥርህ ያለ ሕዝብ ሁሉ ይውጣ’ ይላሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ።” ሙሴም በጽኑ ቁጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። ጌታም ሙሴን፦ “ተአምራቴ በግብጽ ምድር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም” አለው። ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ አልለቀቀም። ጌታም በግብጽ ምድር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ ከዓመቱ ወሮችም የመጀመሪያ ይሁናችሁ። ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። የቤተሰቡ ቍጥር ም ለጠቦቱ የሚያንስ ከሆነ እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ በእያንዳንዱ ሰው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት፥ ተባዕት፥ የአንድ ዓመት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ጥቂት ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት። ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ በእሳት የተጠበሰውን ካልቦካ ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። ጥሬውን ወይም በውኃ የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ራሱ፥ ከእግሮቹና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋት የቀረውንም በእሳት አቃጥሉት። እንግዲህ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ብሉት፤ ለጌታ ፋሲካ ነው። እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር አልፋለሁ፥ በግብጽም ምድር ከሰው እስከ ከብት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ደሙም በምትኖሩባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብጽን ምድር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ በዓል አድርጋችሁ ጠብቁት፥ ለጌታ በዓል ነው፤ ለትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን ከቤቶቻችሁ እርሾ ታስወግዳላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን የቦካ የሚበላ ያቺ ነፍስ ከእስራኤል ተለይታ ትጥፋ። በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ለሁሉም ሰው የሚሆን የሚበላ ካልሆነ በቀር በእነርሱ ቀናት ምንም አትሥሩ፥ ይህንም ብቻ ታደርጋላችሁ። በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብጽ ምድር አውጥቼአለሁና የቂጣውን በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን በትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ከወሩ ሀያ አንድ ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ። ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገሩ ተወላጅ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይወገድ። እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በምትኖሩበትም ቦታ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ብሉ።” ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ በግ ውሰዱ፥ ለፋሲካም እረዱት። ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለው ደም ውስጥ ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ጉበኖችንና ሁለቱን መቃኖች ቀቡ፤ ከእናንተም ማንም ሰው እስኪ ነጋ ድረስ ከቤቱ ደጅ አይውጣ። ጌታ ግብጽን ሊመታ ያልፋል፤ ደሙንም በጉበኖቹና በሁለቱ መቃኖች ላይ ያያል፥ ጌታም በበሩ ያልፋል፥ አጥፊውም ሊመታችሁ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይፈቅድም። ይህንን ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ጠብቁት። እንዲህም ይሆናል፥ ጌታ እንደ ተናገረ ወደሚሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ይህንን አገልግሎት ጠብቁት። እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ‘ይህ አገልግሎት ለእናንተ ምንድነው?’ ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተም፦ ‘ለጌታ የፋሲካ መሥዋዕት ነው፥ በግብጽ በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነበት ነው’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጎነበሱ ሰገዱም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። እንዲህም ሆነ እኩለ ሌሊት ላይ ጌታ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ በእስር ቤት እስካሉት እስከ እስረኞች በኩር ድረስ፥ የከብቶችንም በኩር ሁሉ መታ። ፈርዖን፥ አገልጋዮቹ ሁሉና ግብጽ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብጽ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ። ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፤ እንዳላችሁትም ጌታን አገልግሉ፤ እንዳላችሁትም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ።” ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ እንዲወጡ ሕዝቡን ያስቸኩሉአቸው ነበር፥ “ሁላችንም ልንሞት ነው” አሉ። ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ማቡኪያውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት። የእስራኤልም ልጆች እንደ ሙሴ ቃል አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። ጌታም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስን ሰጣቸው እነርሱም የፈለጉትን ሰጡአቸው። እነርሱም ግብጽን በዘበዙ። የእስራኤልም ልጆች ከራዓምሴስ ወደ ሱኮት በእግር ተጓዙ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህሉ ነበሩ። ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። ከግብጽም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኮሉአቸው ይቆዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር። የእስራኤልም ልጆች በግብጽ የኖሩበት ጊዜ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር። እንዲህም ሆነ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚህ ቀን የጌታ ሠራዊት ሁሉ ከግብጽ ምድር ወጡ። ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ለጌታ የተጠበቀች ሌሊት ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ በትውልዳቸው ሁሉ ለጌታ የተጠበቀች ናት። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የፋሲካ ሥርዓት ነው፤ ማንም እንግዳ ሰው ከእርሱ አይብላ። በብር የተገዛ የማንም ባርያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ። እንግዳና ደሞዝተኛ ግን ከእርሱ አይብላ። በአንድ ቤት ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ውጭ አይውጣ፤ አጥንቱንም አትስበሩት። የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት። እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለጌታም ፋሲካን ሊያደርግ ቢፈልግ፥ እርሱና የእርሱ ወንዶች ሁሉ ይገረዙ ከዚያም ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገሩ ተወላጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። ለአገሩ ተወላጅና በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ መጻተኞች አንድ ሥርዓት ይሆናል።” የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። በዚያም ቀን ጌታ የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብጽ ምድር አወጣ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው፦ “ማሕፀንን የሚከፈት በኩርን ሁሉ፤ በእስራኤል ልጆች መካከል፥ ከሰውም፥ ከእንስሳም ለእኔ ቀድስልኝ፥ የእኔ ነው።” ሙሴም ሕዝቡን አለ፦ ከባርነት ቤት ከግብጽ የወጣችሁበትን ይህንን ቀን አስቡ፥ ጌታ ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል። ጌታም ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኬጢያውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ኤዊያውያን፥ ወደ ኢያቡሳውያንም ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አገልግሎት በዚህ ወር ታገለግላለህ። ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለጌታ በዓል ይሆናል። ሰባት ቀንም ሙሉ ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት አይታይ፥ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ። በዚያም ቀን፦ “ከግብጽ በወጣሁ ጊዜ ጌታ ስላደረገልኝ ነው” ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። በእጅህ እንደ ምልክት በዐይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ፥ የጌታ ሕግ በአፍህ እንዲሆን፥ ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶሃልና። በተወሰነለት ጊዜ ከዓመት ወደ ዓመት ይህችን ሥርዓት ጠብቃት። ጌታ ለአንተና ለአባቶችህም እንደማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ያመጣሃል ለአንተም ይሰጥሃል፤ ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለጌታ ስጥ፥ የአንተ ከሆነ ከከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለጌታ ይሆናል። የአህያውን በኩር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኩር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። እንዲህም ይሆናል በሚመጣው ጊዜ ልጅህ፦ ይህ ምንድነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ ጌታ በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብጽ አወጣን፤ ፈርዖን እንዳይለቀን ልቡን ባጸና ጊዜ ጌታ ከሰው በኩር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኩር ድረስ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለጌታ እሠዋለሁ፥ ነገር ግን የልጆቼን በኩር ሁሉ እዋጃለሁ። ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዐይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ። እንዲህም ሆነ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ምንም እንኳን ቅርብ ቢሆን በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፦ “ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብጽም እንዳይመለስ” ብሏልና። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ዞረው በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መንገድ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ምድር ለጦርነት ተሰልፈው ወጡ። ሙሴም የዮሴፍን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ “በእርግጥ እግዚአብሔር ይጎበኛችኋል፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ውሰዱት” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና። ከሱኮትም ወጡ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። በቀንና በሌሊትም እንዲጓዙ፥ ጌታ ቀን በደመና ዓምድ መንገድ ሊመራቸው፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ሊያበራላቸው ከፊታቸው ይሄድ ነበር። የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ አልተለየም። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እንዲመለሱና በሚግዶልና በባሕሩ መካከል፥ በበዓልጽፎንም ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ የእስራኤልን ልጆች ንገራቸው፤ ከእርሱም አንጻር በባህሩ ትሰፍራላችሁ።” ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ “በምድር ግራ በመጋባት ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው” ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያሳድዳቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም ማምለጣቸውን ለግብጽ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የአገልጋዮቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “ምንድነው ያደረግነው? እንዳያገለግለን እስራኤልን ለቀቅነው” አሉ። ሠረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችን፥ የግብጽንም ሰረገሎችን ሁሉ፥ የጦር አዛዦች በእያንዳንዱ ሠረገላ ላይ ነበሩ። ጌታም የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ በበዓልጽፎን ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን ከኋላቸው እየመጡ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ ጌታም ጮኹ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “በግብጽ መቃብር ስለ ሌለ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን? ከግብጽ አውጥተህ ምንድነው ያደረግህብን? በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? ተወን፥ ግብፃውያንን እናገልግል፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብናገለግላቸው ይሻላልና።” ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ ጌታ በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠፈር ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠፈር አወከ። የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኆቹም በግብፃውያን ላይ በሰረገሎቻቸው ላይ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ ጌታም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኆቹም ተመልሰው በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደኑ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተራመዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆኑላችው። ጌታም በዚያን ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሞት በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም ጌታ በግብጽ ላይ ያደረጋትን ታላቅ ኃይል አየ፥ ሕዝቡም ጌታን ፈሩ፥ በጌታና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ። በዚያን ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለጌታ ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለጌታ እዘምራለሁ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጌታ ኃይሌና መዝሙሬ ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁም፥ የአባቴ አምላክ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ጌታ ተዋጊ ነው፥ ስሙም ጌታ ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎችና ሠራዊቱን በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት መኮንኖችም በቀይ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ እንደ ድንጋይ ወደ ባሕር ጥልቀት ወረዱ። ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ በኃይል ታላቅ ነው፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ ጠላትን አደቀቀ። የግርማህ ታላቅነት አንተን በመቃወም የተነሱብህን ጣላቸው፤ ቁጣህን ሰደድህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ጥልቁም በባሕር ልብ ውስጥ ረጋ። ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ በእነርሱም ፍላጎቴ ይሞላል፥ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ትንፋሽህን እፍ አልክባቸው፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ ብረት ሰጠሙ። ከአማልክት መካከል ጌታ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስና ባለግርማ፥ በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በታማኝ ኪዳንህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራሃቸው፤ በኃይልህ ወደ ቅድስናህ ማደሪያ አስገባሃቸው። ሕዝቦች ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ፍርሃት ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞዓብ መሪዎች መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ ጌታ ሆይ የገዛኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ በኃይልህ ታላቅነት፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፥ እንደ ድንጋይ ቀጥ አሉ። አንተ ታመጣቸዋለህ፥ በርስትህም ተራራ ትተክላቸዋለህ፥ ጌታ ሆይ ለማደሪያህ በሠራኸው ስፍራ፥ ጌታ ሆይ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። ጌታ ለዘለዓለም ዓለም ይነግሣል።” የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ ጌታም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ። የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ ከበሮ በመያዝና በጭፈራ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም፦ “ለጌታ ዘምሩ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ” እያለች ዘመረችላቸው። ሙሴም እስራኤልን ከቀይ ባሕር መራ፥ ወደ ሹር ምድረ በዳም ሄዱ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም መጡ፥ የማራንም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም መራራ ነበረና፤ ስለዚህ አንድ ሰው ማራ ብሎ ጠራው። ሕዝቡም፦ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እርሱም ወደ ጌታ ጮኸ፤ ጌታም ዛፍ አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፋጭ ሆነ። ጌታም በዚያ ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እርሱም፦ “አንተ የጌታ አምላክህን ቃል ብትሰማ፥ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እኔ ጌታ ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ። ከኤሊምም ተነሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር፥ በዓሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉአቸው፦ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን ሳለን፥ ምግብ ተትረፍርፎ ስንበላ ሳለን፥ በግብጽ ምድር ሳለን በጌታ እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ ወደዚህ ምድረ በዳ አወጣችሁን።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከሰማይ እንጀራን ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡም ወጥተው ለቀኑ የሚበቃቸውን በቀኑ ይልቀሙ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ። እንዲህም ይሆናል በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ በየቀኑ ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን።” ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ አሉ፦ “ጌታ ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ በጥዋትም የጌታን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም በጌታ ላይ ያጉረመረማችሁትን ሰምቶአልና፥ በእኛም ላይ የምታጉረመርሙ እኛ ምንድን ነን?” ሙሴም፦ “ጌታ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የሚያጠግባችሁን ምግብ ሲሰጣችሁ ጌታ ያጉረመረማችሁበትን ማጉረምረም ሰምቶ ነው፤ እኛ ምንድን ነን? ማጉረምረማችሁ በጌታ ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። ሙሴም አሮንን፦ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ‘ማጉረምረማችሁን ሰምቶአልና ወደ ጌታ ፊት ቅረቡ በላቸው’” አለው። እንዲህም ሆነ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አዞሩ፤ እነሆም የጌታ ክብር በደመናው ታየ። ጌታም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረማቸውን ሰማሁ፦ እንዲህ በላቸው “ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ሸፈኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበር። ጤዛውም ከተነነ በኋላ፥ በመሬት ላይ ስስ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ መሬት ላይ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና ሁሉም ሰው ወንድሙን፦ “ይህ ምንድነው?” በማለት ተጠያየቁ። ሙሴም፦ “እንድትበሉት ጌታ የሰጣችሁ ምግብ ነው።” ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ “እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ዖሜር ይውሰድ።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ። በዖሜርም በሰፈሩት ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አላነሰውም፤ የሰበሰቡት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ነው። ሙሴም፦ “ማንም ሰው እስከ ጥዋት ከእርሱ ምንም እንዳያስቀር” አላቸው። ሙሴንም አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ጥቂት እስከ ጥዋት አስቀሩ፥ እርሱም በስብሶ ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቆጣቸው። ጥዋት ጥዋት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሐይም በሞቀ ጊዜ ቀለጠ። እንዲህም ሆነ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው ሁለት ዖሜር ምግብ ለአንድ ሰው ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም መሪዎች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ የተናገረው ይህ ነው፦ ነገ የዕረፍት ሰንበት ነው፥ ለጌታ የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ተውት ለጥዋት ለእናንተ አስቀምጡት።” ሙሴም እንዳዘዘ ለጥዋት አስቀመጡት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልነበረበትም። ሙሴም፦ “ዛሬ ብሉት፥ ዛሬ ለጌታ ሰንበት ነውና፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም። ስድስት ቀን ትሰበስባላችሁ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይኖርም።” በሰባተኛውም ቀን ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊሰበስቡ ወጡ፥ ምንም አላገኙም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እምቢ የምትሉት እስከ መቼ ነው? ጌታ ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን ምግብ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፤ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይውጣ።” ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። የእስራኤልም ቤት ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ፍሬ ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው። ሙሴም፦ “ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን ምግብ እንዲያዩ ከእርሱ አንድ ዖሜር ሙሉ በትውልዳችሁ ሁሉ ይጠበቅ” አለ። ሙሴም አሮንን አለው፦ “አንድ ማድጋ ወስደህ ዖሜር ሙሉ መና አኑርበት፥ በትውልዳችሁም ተጠበቆ እንዲኖር በጌታ ፊት አስቀምጠው።” ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ተጠብቆ እንዲኖር አሮን በምስክሩ ፊት አስቀምጠው። የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ። ዖሜርም የኢፍ አንድ አሥረኛ ነው። የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ጌታ እንዳዘዘ ሊጓዙ ከሲን ምድረ በዳ ተነሡ፥ በረፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፦ “የምንጠጣውን ውኃ ስጠን” አሉት። ሙሴም፦ “ለምን ትጣሉኛላችሁ? ጌታንስ ለምን ትፈታተናላችሁ?” አላቸው። ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ፥ ሕዝቡም በሙሴ ላይ አጉረመረሙ “እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብጽ አወጣኸን?” አሉ። ሙሴም፦ “ይህን ሕዝብ ምን ላድርገው? በድንጋይ ሊወግሩኝ ቀርበዋል” ብሎ ወደ ጌታ ጮኸ። ጌታም ሙሴን፦ በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ የዓባይን ወንዝ የመታህበትን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ። እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ከእርሱ ውኃ ይወጣል፥ ሕዝቡም ከእርሱ ይጠጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። እርሱም የዚያን ስፍራ ስም ማሳህና መሪባ ብሎ ጠራው፥ ይህም ስለ እስራኤል ልጆች ጥልና “ጌታ በመካከላችን ነው ወይስ አይደለም?” በማለት ጌታን ስለተፈታተኑት ነው። አማሌቅም መጥቶ በረፊድም ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። ሙሴም ኢያሱን፦ “ሰዎችን ምረጥልን፥ ከአማሌቅም ጋር ለመዋጋትም ውጣ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ” አለው። ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴ፥ አሮንና ሑር ወደ ኮረብታው ጫፍ ወጡ። እንዲህም ሆነ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ይበረታ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ይበረታ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ዝለው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሑርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ያዙ፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ቀጥ አሉ። ኢያሱም ዓማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። ጌታም ሙሴን፦ “ይህንን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ አኑረው፥ የአማሌቅን መታሰቢያ ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና” አለው። ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም “ጌታ ሰንደቅ ዓላማዬ ነው” ብሎ ጠራው፤ እርሱም፦ “እጅ በጌታ ዙፋን ላይ ስለጫነ የጌታ ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይሁን አለ።” የምድያን ካህን የሙሴ አማት ይትሮ እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ ጌታም እስራኤልን ከግብጽ እንዳወጣ ሰማ። የሙሴ አማት ይትሮ መልሷት የነበረችውን የሙሴን ሚስት ጺፖራን ወሰደ። እንዲሁም ሁለቱን ልጆቿን ጭምር። የአንደኛው ስም ጌርሾም ነበረ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ብሏልና፤ የሁለተኛውም ስም ኤሊዔዘር ነበረ፦ “የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ” ብሏልና። የሙሴ አማት ይትሮ፥ ከልጆቹና ሚስቱ ጋር በምድረ በዳ ሰፍሮ ወደ ነበረበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ሙሴ መጣ። ሙሴንም፦ “እኔ አማትህ ይትሮ፥ ሚስትህና ከእርሷም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ ወደ አንተ መጥተናል” አለው። ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ። ሙሴም ጌታ በፈርዖንና በግብጽ ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ ጌታም እንዳዳናቸው ለአማቱ ተረከለት። ይትሮም ጌታ ለእስራኤል ስላደረገው መልካም ነገር ሁሉ፥ ከግብጽም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው። ይትሮም እንዲህ አለ፦ “ከግብጽ እጅና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብጽም እጅ በታች ሕዝቡን ያዳነ ጌታ ይባረክ። በትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር ላይ ጌታ ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ አሁን አወቅሁ።” የሙሴ አማት ይትሮም የሚቃጠል ቊርባንና መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ አሮንና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሊመገቡ ከሙሴ አማት ጋር መጡ። በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። የሙሴ አማትም ለሕዝቡ ያደርግ የነበረውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ “ለሕዝቡ የምታደርገው ይሄ ነገር ምንድነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመዋል፥ አንተ ብቻህን ለምን ተቀምጠሃል?” አለው። ሙሴም አማቱን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በአንድ ሰውና በጎረቤቱ መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ።” የሙሴ አማትም አለው፦ “እያደረግህ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ ይህ ነገር ይከብድሃልና፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን አቅርብ፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አቅርብ፤ ሥርዓቱንና ሕጉን አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድና የሚያደርጉትን ሥራ አሳውቃቸው። አንተም ከሕዝቡ ሁሉ መስራት የሚችሉ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ የታመኑ፥ የጉቦ ትርፍን የሚጠሉ ሰዎችን ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የዐሥር አለቆችን ሹምላቸው። በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ ትልቁን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ትንሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልሃል። ይህንም ብታደርግና፥ እግዚአብሔር ቢያዝዝህ፥ መቋቋም ትችላለህ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው በሰላም ይሄዳል።” ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ መስራት የሚችሉ ሰዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የአምሳ አለቆች፥ የዐሥር አለቆች አድርጎ ሾማቸው። በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበዳቸውን ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ትንሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። ሙሴም አማቱን ሸኘው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ። የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ወጣ፤ ጌታም ከተራራው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር፦ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንዴት እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ የካህናት መንግስት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።” ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ ጌታ ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት ሆነው፦ “ጌታ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ ጌታ አደረሰ። ጌታም ሙሴን፦ “ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙና ለዘለዓለም እንዲያምኑህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣለሁ” አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለጌታ ነገረ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገን ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ እያዩ ጌታ በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና። ለሕዝቡም በዙሪያው ወሰን አድርግላቸው፥ እንዲህም በላቸው ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውን የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤ የማንም እጅ አይንካው፤ የሚነካው ግን በድንጋይ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳም ቢሆን፥ ሰውም ቢሆን አይድንም።’ ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ።” ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ። ሕዝቡንም፦ “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴትም አትቅረቡ” አላቸው። እንዲህም ሆነ በሦስተኛው ቀን ማለዳ ነጎድጓድ፥ መብረቅና ከባድ ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩ የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ በተራራው እግርጌ ቆሙ። ጌታ በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ጢሱም ከእቶን እንደሚወጣ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ተናወጠ። የቀንደ መለከቱ ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። ጌታ በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ ጌታ ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ። ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ውረድ፥ ጌታን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉና ከእነርሱም ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ሕዝቡን አስጠንቅቃቸው፤ ወደ ጌታ የሚቀርቡት ካህናትም ራሳቸውን ይቀድሱ ካልሆነ ግን ጌታ ያጠፋቸዋል።” ሙሴም ጌታን፦ “አንተ በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፥ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ሊወጡ አይችሉም” አለው። ጌታም፦ “ሂድ፥ ውረድ፤ አሮንንም ከአንተ ጋር ይዘህ ና፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እንዳያጠፋቸው ወደ ጌታ ለመውጣት አይተላለፉ” አለው። ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደና ይህንን ነገራቸው። እግዚአብሔርም እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማያት ካለው፥ በታች በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም አምሳል፥ የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም፤ እኔ ጌታ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ነኝ። “የጌታ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ ጌታ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሳይቀጣው አያልፍም። “እንድትቀድሰው የሰንበትን ቀን አስታውስ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፥ ተግባርህንም ሁሉ ፈጽም፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህ፥ ሴት ልጅህ፥ ወንድ ሠራተኛህ፥ ሴት ሠራተኛህ፥ ከብትህ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ መጻተኛ ሁሉ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ጌታ በስድስት ቀናት ሰማያትንና ምድርን፥ ባሕርን፥ እና በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ ጌታ የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም። “ጌታ አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፥ አባትህንና እናትህን አክብር። “አትግደል። “አታመንዝር። “አትስረቅ። “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት፥ ወንድ ሠራተኛውን፥ ሴት ሠራተኛውን፥ በሬውን፥ አህያውን፥ የባልንጀራህ የሆነውን ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።” ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ፈሩ ተንቀጠቀጡም፥ ርቀውም ቆሙ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር አይናገረን።” ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ሊፈትናችሁ፥ ኃጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ እንዲሆን እግዚአብሔር መጥቷልና።” ሙሴ እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ሲቀርብ ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ ‘እኔ ከሰማይ ከእናንተ ጋር እንደተነጋገርሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። ከእኔ ጋር የብር አማልክትን አትሥሩ፥ የወርቅ አማልክትንም ለእናንተ አትሥሩ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የሰላም መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ በተጠረበ ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’” “በፊታቸው የምታኖረው ሥርዓት ይህ ነው። ዕብራዊ ባርያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛው ዓመት ግን እንዲሁ ነፃ ይውጣ። ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ። ጌታው ሚስት ሰጥቶት ከሆነ እና ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታዋ ይሁኑ፥ እርሱ ብቻውን ይውጣ። ባርያውም፦ ጌታዬን፥ ሚስቴንና ልጆቼን እወድዳለሁ፥ ነፃ አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ እግዚአብሔር ያቅርበው፥ ወደ በሩ ወይም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘለዓለምም ያገልግለው። “አንድ ሰው ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ወንድ ባርያዎች እንደሚወጡ አትውጣ። ጌታዋን ደስ ባታሰኘው እንድትዋጅ ይስጣት፤ በድሎአታልና ለባዕድ ሕዝብ ሊሸጣት መብት የለውም። ለልጁም ሊድራት ቢፈልግ፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት። ሌላይቱን ቢያገባ፥ ምግብዋን፥ ልብስዋንና የጋብቻ መብቷን አይቀንስባት። እነዚህንም ሦስት ነገሮች ባያደርግላት፥ ያለ ገንዘብ ትውጣ ። “ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ ፈጽሞ ይሙት ። ሳይሸምቅበት፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አዘጋጅልሃለሁ። ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውንም በተንኮል ቢገድለው፥ እንዲገደል ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው። አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይሙት። ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ ፈጽሞ ይሙት። አባቱን ወይም እናቱን የሚያዋርድ ፈጽሞ ይሙት። “ሰዎች ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ ቢመታው፥ ባይሞት ነገር ግን በአልጋ ላይ ቢውል፥ ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ውጭ ቢወጣ፥ ሥራ ስላስፈታው ገንዘብ ከመክፈልና፥ እስኪፈወስም ድረስ ከማሳከም በቀር የመታው ሰው ከወንጀል ነጻ ነው። አንድ ሰው ወንድ ባርያውን ወይም ሴት ባርያውን በበትር ቢመታ፥ በእጁም ቢሞትበት፥ ያው ቅጣት ይቀጣ። ነገር ግን የተመታው አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቆይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ። ሰዎች ሲጣሉ፥ ያረገዘችን ሴት ቢመቱ ቢያስወርዳት ነገር ግን እርስ ባትጎዳ፥ የሴቲቱ ባል የጣለበትን ያህል ካሳ ይክፈል፤ ይህም በዳኞቹ ይሰጥ። ጉዳት ቢደርስባት ግን ሕይወት ስለ ሕይወት፥ ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ሰለ ጥርስ፥ እጅ ስለ እጅ፥ እግር ስለ እግር፥ መቃጠል ስለ መቃጠል፥ ቁስል ስለ ቁስል፥ ግርፋት ስለ ግርፋት ይክፈል። አንድ ሰው የባርያውን ወይም የባርያይቱን ዐይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ በነጻ ይልቀቀው። የባርያውን ወይም የባርያይቱን ጥርስ ቢያወልቅ፥ ስለ ጥርሱ ነጻ ይልቀቀው። “በሬ ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው። ነገር ግን በሬው አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ለባለቤቱ አስጠንቅቀውት ባይጠብቀውና ወንድን ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል። ካሳ እንዲከፍል ቢወሰንበት ግን፥ የነፍሱን ካሳ የወሰኑበትን ያህል ይስጥ። ወንድን ልጅ ቢወጋ ወይም ሴትን ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት። በሬው ወንድ ባርያ ወይም ሴት ባርያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታው ይስጥ፥ በሬው ግን ይወገር። አንድ ሰው ጉድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጉድጓድ ቢቆፍር ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ቢወድቅበት፥ የጉድጓዱ ባለቤት ዋጋውን ለባለቤቱ ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን። የአንድ ሰው በሬ የሌላውን በሬ ቢወጋ፥ ቢሞትም፥ በሕይወት ያለውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም እኩል ይካፈሉት፤ የሞተውንም ደግሞ እኩል ይካፈሉ። በሬው አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው። “አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፥ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው፥ በበሬው ፈንታ አምስት በሬዎች፥ በበጉም ፈንታ አራት በጎች ይክፈል።” “ሌባ ቤት ሲሰብር ቢገኝ፥ ቢመታና ቢሞት፥ በመታው ሰው ላይ ደሙ የለበትም። ፀሐይ ከወጣችበት ግን ደሙ በላዩ ነው፥ ዋጋውን ይክፈል፤ የሚከፍለው ከሌለው ስለ ሰረቀው ነገር ይሸጥ። የሰረቀው በሬ ወይም አህያ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት ሳለ በእጁ ቢገኝ፥ የሰረቀውን ሁለት እጥፍ አድርጎ ይክፈል። አንድ ሰው በእርሻ ወይም በወይን ስፍራ ከብቱን ቢያሰማራ፥ የሌላውንም ሰው እርሻ ቢያስበላ፥ ከተመረጠ እርሻውና መልካም ከሆንው ወይኑ ይካስ። እሳት ቢነሣ፥ እሾኽንም ቢይዝ፥ ክምሩንም ወይም ያልታጨደውን እህል ወይም እርሻውን ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያነደደው ይካስ። አንድ ሰው ብር ወይም ሌላ ነገር እንዲጠብቅለት ለባልንጀራው በአደራ ቢሰጥ፥ ከቤቱም ቢሰረቅና ሌባው ቢገኝ እጥፍ ይክፈል። ሌባው ግን ባይገኝ፥ እጁን በባልንጀራው ንብረት ላይ እንዳልዘረጋ እንዲታወቅ ባለቤቱ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለ ሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካሰሱ፥ አንዱም፦ ይህ የእኔ ነው ቢል ክርክራቸው ወደ እግዚአብሔር ይምጣ፤ እግዚአብሔርም የፈረደበት እርሱ ለባልንጀራው እጥፍ አድርጎ ይክፈል። አንድ ሰው ለባልንጀራው አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እንስሳ እንዲጠብቅለት በአደራ ቢሰጥ፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጎዳ ወይም ቢማረክ፥ በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን እንዳልዘረጋ የጌታ መሐላ በሁለታቸው መካከል ይሁን፤ የከብቱም ባለቤት መሐላውን ይቀበል፥ እርሱም ምንም አይክፈል። ከእርሱ ከተሰረቀ ግን ለባለቤቱ ይክፈል። በአውሬ ተበልቶ ከሆነ የቀረውን ለምስክርነት ያምጣው፤ በአውሬም ስለተበላ አይክፈል። አንድ ሰው ከባልንጀራው አንዳች ቢዋስ ባለቤቱም ከእርሱ ጋር ሳይኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ካሳ ይክፈለው። ባለቤቱ ግን ከእርሱ ጋር ቢኖር አይክፈል፤ አከራይቶት ከሆነም ኪራዩን ብቻ ይክፈል። “ሰው ያልታጨችውን ድንግል ቢያታልላት፥ ከእርሷም ጋር ቢተኛ፥ የማጫዋን ዋጋ ሰጥቶ ሚስት ያድርጋት። አባትዋ ለእርሱ አልሰጥም ቢል ለደናግል የሚሰጥ ማጫ ብር ይክፈል። መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት። ከእንስሳ ጋር የሚተኛ ፈጽሞ ይገደል። ከጌታ በቀር ለሌላ አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። ስደተኛውን አትበድለው፥ አትጨቁነውም፥ እናንተም በግብጽ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና። መበለቲቱንና ድሀ አደጉን አታስጨንቁአቸው። ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ ግን እኔ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ፤ ቁጣዬም ይነዳል፥ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፥ ሚስቶቻችሁ መበለት፥ ልጆቻችሁም ድሀ አደጎች ይሆናሉ። ከአንተ ጋር ላለው ለአንዱ ድሃ ወገኔ ገንዘብ ብታበድረው፥ እንደ ባለ አራጣ አትሁንበት፥ ወለድም አታስከፍለው። የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት፤ የሚለብሰው ሌላ የለውም፥ ገላውን የሚሸፍንበት እርሱ ብቻ ነውና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ መሐሪ ነኝና እሰማዋለሁ። እግዚአብሔርን አትስደብ፥ የሕዝብህንም መሪ አትርገም። ከሙላትህና ከጭማቂህ ለማቅረብ አትዘግይ፤ የልጆችህንም በኩር ትሰጠኛለህ። ከበሬህና ከበግህም እንዲሁ አድግር፤ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፥ በስምንተኛውም ቀን ለእኔ ትሰጠዋለህ። ቅዱስ ወገን ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ በሜዳ አውሬ የገደለውን ሥጋ አትብሉ፤ ለውሻ ጣሉት። “ሐሰተኛ ወሬ አታሰራጭ፥ ሐሰተኛ ምስክር ለመሆንም ከኃጢአተኛ ጋር አትተባበር። ክፉ ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። በፍርዱ ጊዜ ለድሀው አታድላ። የጠላትህን በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኘው ለእርሱ መልስለት። የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን እንዲነሳ እርዳው። በፍርዱ ጊዜ የድሀውን ፍርድ አታጥምም። ከሐሰት ነገር ራቅ፤ ንጹሑንና ጻድቁን አትግደል፥ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና። ጉቦን አትቀበል፤ ጉቦ የሚያዩ ሰዎችን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። መጻተኛውን አትጨቁን፤ እናንተ ራሳችሁ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ የመጻተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ታውቃላችሁና። “ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ምርትዋንም ሰብስብ፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህ ድሆች ይበሉታል፤ እነርሱ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። በወይንህና በወይራህም ላይ እንዲሁ አድርግ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ እንዲያርፉ የባርያህ ልጅና መጻተኛውም ዕረፍት እንዲሆንላቸው በሰባተኛው ቀን ዕረፍ። የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፍህም አይሰማ። “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታደርግልኛለህ። የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በተመደበው በአቢብ ወር ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ እንዳዘዝሁህ ትበላለህ፤ በዚህ ወር ከግብጽ ምድር ወጥታችኋልና፥ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። የመከር በዓል፥ በእርሻህ የዘራኸውን የፍሬህን በኵራት፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ በምትሰበስብበት ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ። በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ። የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ ቂጣ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቆይ። የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ ጌታ አምላክህ ቤት አምጣ፤ ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል። “በመንገድ እንዲጠብቅህ፥ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ እንዲያስገባህ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለሁ። በፊቱ ተጠንቀቅ፥ ቃሉንም አድምጥ፤ ስሜ በእርሱ ስለ ሆነ ብትተላለፉ ይቅር አይልምና አታስመርረው። አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጠላለሁ፥ የሚቃወሙህንም እቃወማለሁ። መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ኬጢያውያን፥ ወደ ፌርዛውያን፥ ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኤዊያውያንና ወደ እያቡሳውያን ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታገልግላቸውም፥ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው። ጌታ አምላካችሁን ታገለግላላችሁ፤ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ። በምድርህ የምትጨነግፍ ወይም መካን አትኖርም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ። መፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፥ የምትሄድበትን ሕዝብ ሁሉ አስደንግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ። በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ። ምድሪቱ ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፊትህ አላባርራቸውም። እስክትበዛና ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ። ድንበርህንም ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረበዳ እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፥ ከፊትህ ታባርራቸዋለህ። ከእነርሱ ጋርና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ። በምድርህ አይቀመጡ አማልክቶቻቸውን በማገልገል እኔን እንድትበድል ያደርጉሃልና፥ ይህም ለአንተ ወጥመድ ይሆንብሃል።” ሙሴንም እንዲህ አለው፦ “አንተ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ ጌታ ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ ሙሴም ብቻውን ወደ ጌታ ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፥ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ።” ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የጌታ ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ “ጌታ የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ። ሙሴም የጌታን ቃሎች ሁሉ ጻፈ፤ በማለዳ ተነሥቶ ከተራራው በታች መሠዊያንና ዐሥራ ሁለት ሐውልቶች ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለጌታም የሰላም መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤል ልጆች ወጣቶችን ላከ። ሙሴም የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጎድጓዳ ሣህኖች ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው። የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ በሕዝቡ ጆሮ ላይ አወጀ፤ እነርሱም፦ “ጌታ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም” አሉ። ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፦ “በእነዚህ ቃሎች ሁሉ ጌታ ከእናንተ ጋር ያደረገው የኪዳኑ ደም እነሆ” አለ። ሙሴ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማያት የጠራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። በእስራኤል አዛውንቶች ላይ እጁን አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም። ጌታም ሙሴን፦ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን እንድታስተምር እኔ የጻፍሁት ሕግና ትእዛዝ ያለበት የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ” አለው። ሙሴና አገልጋዩ ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። ሽማግሌዎቹንም፦ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሑርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ባለ ጉዳይም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ” አላቸው። ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። የጌታም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። በተራራው ራስ ላይ የጌታ ክብር ለእስራኤል ልጆች እንደሚባላ እሳት ሆኖ ታያቸው። ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቆየ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መባ እንዲያመጡልኝ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፤ በፈቃዱ ሊሰጠኝ ልቡ ከተነሣሣ ሰው ሁሉ መባዬን ተቀበሉ። ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፦ ወርቅ፥ ብርና ናሐስ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታና የፍየል ጠጉር፥ ቀይ የተለፋ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአስቆጣ ቁርበት፥ የግራር እንጨት፥ ለመብራት የሚሆን ዘይት፥ ለቅባት የሚሆን ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን የሚሆን ቅመም፥ መረግድ፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። በመካከላቸው እንድኖር መቅደስ ይሥሩልኝ። እኔ እንዳሳየሁህ ሁሉ፥ እንደ ድንኳኑ ምሳሌ፥ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። “ከግራር እንጨት ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። ውስጡንና ውጪውም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በላዩ ላይ ዙሪያውን ሁሉ የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። ታቦቱን በእነርሱ ለመሸከም በታቦቱ ጎን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አስገባ። መሎጊያዎቹ በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከዚያም አይውጡ። እኔ የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር። ከንጹሕ ወርቅ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። አንዱን ኪሩብ በአንድ በኩል፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው በኩል አኑር፥ በስርየት መክደኛው ላይ ኪሩቤል በሁለት በኩል ላይ ታደርጋቸዋለህ። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔ የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች እንድታዝዝ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። “ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ። በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች ላይ አድርጋቸው። ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። ገበታውን እንዲሸከሙባቸው መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። ለማፍሰሻም እንዲሆኑ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። በገበታው ላይ ኅብስተ ገጹን ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ መቅረዙ የተቀጠቀጠ ሥራ ይሁን፤ እግሩና ከአገዳው ጋር ጽዋዎቹም ጉብጉቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። በአንደኛው ቅርንጫፍ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች አድርግ፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ። በመቅረዙም እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ አራት ጽዋዎች ይኑሩት። ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ፥ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ እንቡጥ ይሁን። እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ይሁኑ፤ ሁሉም ወጥ ሆኖ ከተቀጠቀጠ ከንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊት ለፊት እንዲያበሩ መብራቶቹን ከፍ አድርገህ አስቀምጣቸው። መኮስተሪያዎችዋንና የኩስታሪ ማስቀመጫዎችዋን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ። እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። በተራራው ላይ ባሳየሁህ ምሳሌ መሠረት ለመስራት ጥንቃቄ አድርግ።” “ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተሠሩ ዐሥር መጋረጆች ያሉበትን ድንኳን ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን እኩል ይሁን። አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞም ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት እንዲሆኑ አድርግ። አምሳ የወርቅ መያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑም አንድ ወጥ እንዲሆን መጋረጃዎቹን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። ከማደሪያውም በላይ ለመሸፈኛ የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጉር ሥራ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጆች ትሠራለህ። የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ የእያንዳንዱም መጋረጃ ወርድ አራት ክንድ ይሁን፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጆች መጠን እኩል ይሁን። አምስቱን መጋረጆች ለብቻ፥ ስድስቱንም መጋረጆች ለብቻ አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛው መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። አምሳ የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎቹንም ወደ ቀለበቶቹ አስገባቸው፥ ድንኳኑንም አጋጥመው። ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአስቆጣ ቁርበት አድርግ። “ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቃዎች ከግራር እንጨት አድርግ። የሳንቃውም ሁሉ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቃዎች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቃዎችን አድርግ። ከሀያውም ሳንቃዎች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቃዎች፥ ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቃዎችን አድርግ። ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቃዎችን አድርግ። ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። ስምንት ሳንቃዎችና ዐሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቃዎች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፥ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፥ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም። “መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፤ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።” “ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱ አምስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር እንጨት ሥራ፤ መሠዊያው አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ይሁን። በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን አድርግለት፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሁኑ፤ በነሐስም ለብጠው። አመድ የሚጠራቀምባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹን፥ ድስቶቹን፥ ሜንጦቹንና ማንደጃዎቹን ታደርጋለህ፤ ዕቃዎቹ ሁሉ ከነሐስ ሥራ። እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የነሐስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የነሐስ ቀለበት በአራቱም ማዕዘን አድርግለት። መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ እንዲደርስ ከመሠዊያው እርከን በታች አድርገው። ለመሠዊያው ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሥራ፥ በነሐስም ለብጣቸው። መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ፥ መሠዊያውን ለመሸከም መሎጊያዎቹ በሁለቱ ጎኖች ይሁኑ። ከሳንቃዎች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ይሥሩት። “የማደሪያውን አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ በኩል ከጥሩ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ይሁኑ፥ የአንዱ ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤ ሀያ ምሰሶዎቹና ሀያ እግሮቹ ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ፤ የምሶሶቹ ኩላቦችና ዘንጎች ከብር የተሠሩ ይሁኑ። እንዲሁም በሰሜን በኩል መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች፥ ከነሐስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶዎች እና ሀያ እግሮች ይሁኑ፥ ለምሰሶዎቹ ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ። በምዕራብ በኩል ላለው ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች፥ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር እግሮች ይሁኑ። በምሥራቅ በኩል ያለው የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን። በአንድ በኩል ያለው የመጋረጃዎቹ ርዝመት ዐሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶዎቹ ሦስት፥ እግሮቹ ሦስት ይሁን። በሌላውም በኩል የመጋረዎቹ ርዝመት ዐሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶዎቹ ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁን። ለአደባባዩም መግቢያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ የተጠለፈ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሁን፤ ምሰሶዎቹ አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ። በአደባባዩም ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ በብር ይያያዙ፥ ኩላቦቻቸው ከብር እግሮቻቸው ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ፥ ስፋቱ አምሳ ክንድ ይሁን፥ ከፍታው አምስት ክንድ ይሁን፥ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። ለአገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹ ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የነሐስ ይሁኑ። “መብራቱ ሁልጊዜ እንዲበራ ለመብራት የሚሆን ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። ከመጋረጃው ውጭ ባለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በጌታ ፊት ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ በትውልዳቸው የዘለዓለም ሥርዓት ይሁን።” ወንድምህን አሮንንና ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት እንዲሆኑልኝ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥ አቢሁን፥ አልዓዛርንና ኢታማርን አቅርብ። ለክብርና ለውበት እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሰ ልብስ ሥራለት። ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ እንዲሆን ለአሮን ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፥ ኤፉድ፥ ቀሚስ፥ የተጠለፈ እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያና መታጠቂያ፤ ካህን እንዲሆንልኝ ለወንድምህ ለአሮንና ለልጆቹ የተቀደሰ ልብስ ይሥሩላቸው። ወርቅ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊ፥ ቀይም ግምጃና ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። “ኤፉዱንም በወርቅ፥ በሰማያዊ፥ በሐምራዊ፥ በቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በብልሃት የተሠራ ይሁን። ሁለቱ ወገን አንድ ሆኖ እንዲጋጠም በሁለቱ ትከሻ ላይ የሚጋጠም ይሁን። በላዩ ያለው በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ መታጠቂያ ከእርሱ ጋር ወጥ ሆኖ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተሠራ ይሁን። ሁለት የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ቅረጽባቸው፤ እንደ የልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ ላይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላኛው ድንጋይ ቅረጽ። በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅ ፈርጥ ሥራቸው። የእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች እንዲሆኑ ሁለቱን ዕንቁዎች በኤፉዱ ትከሻዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ትከሻዎቹ ላይ ለመታሰቢያ እንዲሆን ስማቸውን በጌታ ፊት ይሸከማል። ፈርጦችን ከወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጎነጎነ ገመድ አድርገህ ሁለት ድሪዎች ከንጹሕ ወርቅ ሥራ፤ የተጎነጎኑትንም ድሪዎች ከፈርጦቹ ጋር አያይዛቸው። “የፍርዱን የደረት ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራው ሥራው፤ እንደ ኤፉዱ አሠራር ሥራው፤ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከጥሩ በፍታ ሥራው። ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ አራት መዕዘንና ድርብ ይሁን። አራት ረድፍ የሆነ የዕንቁ ፈርጥ አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና አልማዝ፤ በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጦኖስ፤ በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፤ በወርቅ ፈርጥ ይቀመጣሉ። የዕንቁ ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ዐሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ማኅተም እንደሚቀረጽ በየስማቸው ይቀረጹ። ለደረት ኪሱም የተጎነጎኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከንጹሕ ወርቅ ሥራቸው። ለደረት ኪሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረት ኪሱ በሁለቱ ጫፎች አድርጋቸው። ሁለቱ የተጎነጎኑ የወርቅ ድሪዎችን በደረቱ ኪስ ጫፎች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታስገባቸዋለህ። የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ትከሻ በፊት ለፊት ታደርጋቸዋለህ። ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረት ኪሱ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። በተጨማሪም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ለፊት ከትከሻዎቹ በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። የደረት ኪሱም በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረት ኪሱን ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያያይዙታል። አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ ዘወትር መታሰቢያ እንዲሆን በጌታ ፊት የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ ደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፥ በጌታ ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በጌታ ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። “የኤፉዱን መደረቢያ ሙሉ ሰማያዊ አድርገው። መሃሉ ላይ ራስ ማስገቢያ አንገትጌ ይኑረው፤ እንዳይቀደድም የአንገትጌው ዙሪያ የተጠለፈ ይሁን። በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኩራዎች አድርግ፤ የወርቅ ሻኩራና ሮማን፥ የወርቅ ሻኩራና ሮማን በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። በአገልግሎት ጊዜ በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በጌታ ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። ከንጹህ ወርቅ ቅጠል ሥራ፥ በእርሱም ላይ እንደ ማኅተም ቅርጽ ‘ለጌታ የተቀደሰ’ የሚል ቅረጽበት። በመጠምጠሚያው ፊት በሰማያዊ ፈትል በመጠምጠሚያው ላይ ስፋው። በአሮን ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በጌታ ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠሉ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን። እጀ ጠባቡን ከጥሩ በፍታ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፥ በጥልፍ የተጠለፈ መታጠቂያ ትሠራለህ። ለአሮን ልጆች እጀ ጠባቦችን፥ መታጠቂያዎችንና ቆቦችን ለክብርና ለጌጥ ትሠራላቸዋለህ። ወንድምህን አሮንንና ከእርሱም ጋር ልጆቹን እነዚህን አልብሳቸው፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ እጆቻቸውንም ታነጻለህ፥ ትቀድሳቸዋለህም። ኀፍረተ ሥጋቸውን እንዲሸፍኑበት ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአት እንዳይሆንባቸውና እንዳይሞቱ፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ ወይም በመቅደሱ ሊያገለግሉ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናሉ፤ ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል። “ለእኔ ካህናት እንዲሆኑ እንድትቀድሳቸው የምታደርገው ነገር ይህ ነው፤ አንድ ወይፈንና ነውር የሌለባቸውን ሁለት አውራ በጎች ውሰድ። ያልቦካ ቂጣ፥ በዘይት የተለወሰ ያልቦካ እንጎቻ፥ በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ፥ ከመልካም ስንዴ አዘጋጅ። በአንድ መሶብ ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በመሶብ ታቀርባቸዋለህ። አሮንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን እጀ ጠባቡን፥ የኤፉዱን መደረቢያ፥ ኤፉዱንና የደረት ኪስ ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም የተጠለፈ ኤፉድ ታስታጥቀዋለህ፤ መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ። የቅባትን ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባዋለህም። ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ እጀ ጠባብንም ታለብሳቸዋለህ። አሮንንና ልጆቹን በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብን ታለብሳቸዋለህ፤ ክህነትም ለዘለዓለም ለእነርሱ የተወሰነ ይሆናል፥ እንዲሁም አሮንን እጅና የልጆቹን እጅ ትቀድሳለህ። ወይፈኑን ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ። ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በጌታ ፊት ዕረደው። ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትቀባዋለህ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ። የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱን ኩላሊቶችና በላያቸው ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ። የወይፈኑን ሥጋ፥ ቁርበቱንና ፈርሱን ግን ከሰፈር ውጭ በእሳት አቃጥለው፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና። “አንደኛውን አውራ በግ ውሰድ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ። አውራውን በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ትረጨዋለህ። አውራውን በግ በየብልቱ ትቆርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ። አውራውን በግ በሙሉ በመሠዊያው ላይ ታቃጥለዋለህ፤ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው፤ ለጌታ የቀረበ የእሳት ቁርባን ነው። ሁለተኛውን አውራ በግ ትወስደዋለህ፥ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ። አውራውን በግ አርደህ ደሙን ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ትረጨዋለህ። በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅባት ዘይት ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱና ልብሶቹ፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹና ልብሶቻቸው ይቀደሳሉ። ለክህነት ሥርዓት የቀረበ አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱን፥ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱን ኩላሊቶቹ፥ በላያቸውም ያለውን ስብና የቀኙን ወርች ትወስዳለህ። አንድ ክብ ዳቦ፥ አንድ በዘይት የተለወሰ እንጎቻ፥ አንድ ስስ ቂጣ በጌታ ፊት ካለው ያልቦካ ቂጣ ማስቀመጫ ሌማት ትወስዳለህ፤ ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ላይ ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ትወዘውዘዋለህ። ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በጌታ ፊት መልካም መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ታቃጥለዋለህ፤ ይህም ለጌታ የእሳት ቁርባን ነው። ለአሮን የክህነት ሥርዓት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ድርሻ ይሆናል። ለክህነት ሥርዓት ከቀረበው አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። የማንሣት ቁርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የሰላም መሥዋዕታቸው የማንሣት ቁርባን ይሆናል፤ ለጌታ የማንሣት ቁርባን ይሆናል። የተቀደሰው የአሮን ልብስ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን፥ ይኸውም እንዲቀቡበትና ክህነትን እንዲቀበሉበት ነው። ከልጆቹ በእርሱ ፈንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው። ለክህነት ሥርዓት የቀረበውን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። አሮንና ልጆቹ የአውራውን በግ ሥጋና በሌማት ያለውን ቂጣ በመገናኛው ድንኳን በር ሆነው ይበሉታል። በእነሱ እጃቸው ሙሉ እንዲሆንና የተቀደሱ እንዲሆኑ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ የተቀደሰ ስለሆነ ሌላ ሰው አይብላው። ከተቀደሰው ሥጋ ወይም ቂጣ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ስለሆነ አይበላም። ለአሮንና ለልጆቹ እነዚህ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግ፤ ሰባት ቀን እጆቻቸውን ትቀድሳለህ። ለማስተስረያ የሚሆን የኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን በየቀኑ ታቀርባለህ፤ በእርሱ ላይ ማስተስረያ በምታደርግበት ጊዜ መሠዊያውንም ታስተሰርይለታልህ፤ ቅዱስም እንዲሆን ትቀባዋለህ። ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰዋለህም፤ መሠዊያውም ፍጹም ቅዱስ ይሆናል፤ መሠዊያውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። “በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በየቀኑ ዘወትር ሁለት የአንድ ዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። አንዱን ጠቦት ጠዋት ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ ማታ ታቀርበዋለህ። ከአንዱ ጠቦት ጋር አሥረኛ እጅ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄት ከአራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ ተወቅጦ ከተጠለለ ዘይት ጋር የተለወሰ፥ ለመጠጥ ቁርባን የሚሆን ደግሞ አራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ጠዋቱም የእህልና የመጠጥ ቁርባን ከእርሱ ጋር ታቀርባለህ፤ ለጌታ መልካም መዓዛ የሚሆን የእሳት ቁርባን ይሆናል። ከአንተ ጋር ለመነጋገር በዚያ በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን መግቢያ፥ ይህ ዘወትር በትውልዶቻችሁ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። በዚያም ከእስራኤል ልጆች ጋር እገናኛለሁ፤ በክብሬም የተቀደሰ ይሆናል። የመገናኛውን ድንኳንና መሠዊያውን እቀድሳለሁ፤ በክህነትም እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ። በመካከላቸው እንድኖር ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ጌታ አምላካቸው እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ አምላካቸው ነኝ።” የዕጣን መሠዊያ ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው። ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ ይሁን፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ቁመቱ ሁለት ክንድ ይሁን፤ ቀንዶቹ ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሁኑ። ላዩን፥ የጎኖቹን ዙሪያ ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ ዙሪያው የወርቅ አክሊል ታደርግለታለህ። ከአክሊሉ በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን አድርግለት፤ በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ በእነርሱ እንዲሸከሙም የመሎጊያዎቹ ማስገቢያ ይሁኑ። መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። በምስክሩ ታቦት አጠገብ ካለው መጋረጃ ፊት ታኖረዋለህ፥ ለአንተ በምገለጥበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ። አሮንም መልካም መዓዛ ያለው እጣን ማለዳ ማለዳ ይጠንበት፤ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው። አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ይጠነው፥ ይህንም በትውልዳችሁ ሁሉ በጌታ ፊት ዘወትር የሚቀርብ ዕጣን ነው። በእርሱ ላይ ያልተገባ ዕጣን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል ቁርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥ ቁርባንም አታፈስስበትም። አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በዓመት አንድ ጊዜ ለትውልዳችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለጌታ እጅግ የተቀደሰ ነው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ በቆጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቆጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቁጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ። በቆጠራው የሚያልፉ ሁሉ ይህን ይስጡ፥ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት ግማሽ ሰቅል ይሰጣል፥ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው፤ ግማሽ ሰቅል ለጌታ ስጦታ ነው። በዚህ ቆጠራ የሚያልፍ፥ ሃያ ዓመት የሞላውና ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ ይህንን ስጦታ ለጌታ ይስጥ። ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የጌታን ስጦታ ስትሰጡ፥ ከግማሽ ሰቅሉ ባለ ጠጋው አይጨምር፥ ደሃውም አያጉድል። የማስተስረያውን ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስጠው፤ ለእስራኤል ልጆች ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን በጌታ ፊት መታሰቢያ ይሆናል።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የመታጠቢያ ሳሕንና መቀመጫውን ከነሐስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል ታኖረዋለህ፥ ውኃም ትጨምርበታለህ። አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በእርሱ ይታጠባሉ። ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም ለጌታ የእሳት መሥዋዕት ሊያቃጥሉ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ በውኃ ይታጠቡ። እንዳይሞቱ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ምርጥ የሆኑትን ቅመሞች ለራስህ ውሰድ፤ ፈሳሽ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል የቀረፋ ቅመም፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ ብርጉድ አምስት መቶ ሰቅል በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፥ አንድ የኢን መሥፈሪያ የወይራ ዘይት፥ በቀማሚ እንደሚቀመም ቅመም የተቀደሰ የቅባት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅባት ዘይትም ይሆናል። የመገናኛውን ድንኳንና የምስክሩን ታቦት በእርሱ ትቀባለህ፥ ገበታውንና ዕቃውን ሁሉ፥ መቅረዙንና ዕቃውን፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕኑንና ማስቀመጫውን ትቀባለህ። ቀድሳቸው ፍጹም የተቀደሱ ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ካህነት ሆነው እንዲያገለግሉኝም ቀድሳቸው። የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ይህ በትውልዳችሁ ሁሉ ለእኔ የተቀደሰ የቅባት ዘይት ነው። በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱ የተሠራ ሌላ ቅባት አትስሩ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን። እንደ እርሱ ዓይነት የሚቀምም ሰው ወይም ከእርሱ በሌላው ላይ የሚያፈስስ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።’” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መልካም መዓዛ ያለው ቅመም፥ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸት ሙጫና ንጹሕ እጣን ለራስህ ውሰድ፥ ሁሉም እኩል መጠን ይኑራቸው፤ ቀማሚ እንደሚቀምመው፥ በጨው የተቀመመ፥ ንጹሕና ቅዱስ አድርገህ ዕጣን አዘጋጅ። ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታደቀዋለህም፥ ከእርሱም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። ለእናንተም ፍጹም ቅዱስ ይሆንላችኋል። የሠራኸውን ዓይነት ዕጣን ለራሳችሁ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን። ለሽቶነት ፈልጎ እንደ እርሱ የሚሠራ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በጥበብ፥ በማስተዋል፥ በእውቀትና ሥራ ሁሉ እንዲሠራ የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፥ ልዩ ማስተዋል እንዲኖረው፥ በወርቅ፥ በብርና በነሐስ እንዲሠራ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ እንዲቀርጽ፥ እንጨት እንዲጠርብ፥ ሁሉንም ሥራ እንዲሠራ ሞላሁበት። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሆነውን የአሒሳማክን ልጅ ኤልያብን ሰጥቼዋለሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ እንዲያደርጉ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ላይ ጥበብን አኑሬአለሁ። የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩን ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑን ዕቃ በሙሉ፥ ገበታውና ዕቃው ሁሉ፥ ንጹሑን መቅረዝና ዕቃውን፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያ ሳሕንና መቀመጫውን፥ በብልሃት የተሠራውን ልብስ፥ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑ የአሮን የተቀደሱ ልብሶች የልጆቹ ልብሶች፥ የቅባቱን ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ እንዲሁ ያድርጉ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ ግን ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ፥ ይህ የምቀድሳችሁ ጌታ እኔ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ለትውልዶቻችሁ ምልክት ነውና። ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰው ፈጽሞ ይገደል፥ በእርሷ ሥራን የሚሠራ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። የእስራኤል ልጆች ሰንበትን ይጠብቁ፤ ሰንበትን መጠበቅ ለትውልዳቸው የዘለዓለም ቃል ኪዳን ያድርጉት። በእኔና በእስራኤል ልጆች መካከል የዘለዓለም ምልክት ነው፤ ጌታ ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ፈጥሮአልና፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው አርፎአልና፥ ተነቃቅቶአልና።’” በሲና ተራራ ከሙሴ ጋር ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች የሆኑ ሁለት የምስክር ጽላቶችን ሰጠው። ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፦ “ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ ተነሥና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት። አሮንም፦ “በሚስቶቻችሁ፥ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡ ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸው ተቀብሎ በቅርጽ መሥሪያ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃ አደረገው፤ እርሱም፦ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው። አሮንም አየውና መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፦ “ነገ የጌታ በዓል ነው” ሲል አወጀ። በማግስቱ ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የሰላም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ ውረድ፤ ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ለራሳቸውም ቀልጦ የተሠራ ጥጃ ሠሩ፥ ሰገዱለት፥ ሠዉለትም፦ ‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። አሁንም ቁጣዬ በእነርሱ ላይ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከአንተም ታላቅ ሕዝብ አደርጋለሁ።” ሙሴም በጌታ አምላኩ ፊት ለመነ፥ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብጽ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ቁጣህ ስለምን ነደደ? ግብፃውያን ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከገጸ ምድር ሊያጠፋቸው ለክፋት ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከቁጣህ መዓት ተመለስ፥ በሕዝብህ ጥፋት ላይ ራራ። ‘ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም ምድር ሁሉ እንደተናገርሁት ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል’ ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባርያዎችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና እስራኤልን አስብ።” ጌታም በሕዝቡ ላይ አደርጋለሁ ያለውን ክፋ ነገር መለሰ። ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቶቹ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፥ በጽላቶቹ ላይ የተቀረው ጽሑፍም የእግዚአብሔር ጽሑፍ ነበረ። ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፦ “የጦርነት ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ” አለው። እርሱም፦ “ይህ የድል ነሺዎች ድምጽ ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ” አለው። እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንና ዘፈኑን አየ፤ የሙሴ ቁጣ ነደደ፥ ጽላቶቹን ከእጁ ወርውሮ ከተራራው በታች ሰበራቸው። የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እስኪደቅም ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲጠጡት አደረገ። ሙሴም አሮንን፦ “ይህንን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ?” አለው። አሮንም እንዲህ አለ፦ “የጌታዬ ቁጣ አይንደድ፤ ይህ ሕዝብ ክፋ እንደሆነ አንተ ታውቃለህ። እነርሱም፦ ‘ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን’ አሉኝ። እኔም፦ ‘ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ሁሉ ሰብሮ ያምጣልኝ’ አልኋቸው፤ እነርሱም ሰጡኝ፥ በእሳት ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ።” ሙሴ በጠላቶቻቸው ፊት መሳለቂያ እንዲሆኑ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ ሙሴ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ፦ “የጌታ ወገን የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ!” አለ፤ የሌዊ ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዱ ሰው ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩ ውስጥ ከበር እስከ በር ወዲህ ወዲያ ተመላለሱ፥ ሰው ሁሉ ወንድሙን፥ ሰው ሁሉ ወዳጁን፥ ሰው ሁሉ ጎረቤቱን ይግደል’” የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያ ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። ሙሴም “ዛሬ በላያችሁ ላይ በረከት እንዲያወርድ እያንዳንዱ በልጁና በወንድሙ ላይ ተነሥቷልና ዛሬ ለጌታ እጃችሁን ቀደሳችሁ” አለ። በማግስቱም ሙሴ ለሕዝቡ “እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ ጌታ እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ ይሆናል” አላቸው። ሙሴም ወደ ጌታ ተመልሶ “ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁንም ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፥ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” አለ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁንም ሂድ፥ ይህንንም ሕዝብ ወደ ነገርኩህ ስፍራ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን በላያቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ።” አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ ጌታ ሕዝቡን ቀሠፈ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሂድ፥ አንተ ከግብጽ ምድር ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር ውጣ፤ በፊትህ መልአክ እልካለሁ፥ ከነዓናዊውን፥ አሞራዊውን፥ ኬጢያዊውን፥ ፌርዛዊውን፥ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን አወጣልሃለሁ። ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ውጣ፤ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንክ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ ከአንተ ጋር አልወጣም።” ሕዝቡ ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው አዘኑ፤ ከእነርሱም ማንም ጌጡን አላደረገም። ጌታም ሙሴን፦ “ለእስራኤል ልጆች ‘እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፥ አንድ ጊዜ ከእናንተ ጋር ብወጣ አጠፋችኋለሁ፤ አሁንም በእናንተ ላይ የማደርገውን እንዳውቅ ጌጣችሁን አውጡ’ በላቸው አለው።” የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወለቁ። ሙሴ ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈሩ ራቅ አድርጎ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ “የመገናኛ ድንኳን” ብሎ ጠራው። ጌታን የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚሄድበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆምና ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚገባበት ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፤ ጌታም ሙሴን ያናግረው ነበር። ሕዝቡ ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ይሰግድ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ጌታም ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲመለስ አገልጋዩ የሆነው ወጣቱ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴ ጌታን እንዲህ አለው፥ “እይ! አንተ ‘ይህን ሕዝብ አውጣ’ ብለኸኛል፥ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፦ ‘በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። አሁንም በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ እንዳውቅህና በፊትህም ሞገስን እንዳገኝ እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህንንም ሕዝብ እንደ ሕዝብህ እየው።” እርሱም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው። ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ ከዚህ አታውጣን። እኔና ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? እኔና ሕዝብህ በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ የተለየን የምንሆነው አንተ ከእኛ ጋር በመውጣትህ አይደለምን?” ጌታ ሙሴን፦ “በፊቴ ሞገስን ስላገኘህና በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። እርሱም፦ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለ። እርሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የጌታንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውን እምራለሁ።” ደግሞም “ሰው አይቶኝ መኖር አይችልምና ፊቴን ማየት አትችልም” አለ። ጌታ እንዲህ አለው፦ “እነሆ የምትቆምበት ስፍራ በአጠገቤ አለ፥ በዓለቱ ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ ሲያልፍ ዓለቱ ስንጥቅ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ በመዳፌ እጋርዳለሁ፤ መዳፌን አነሣለሁ፥ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞቹ አድርገህ ጥረብ፥ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። ለጥዋትም የተዘጋጅ፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ውጣ፥ በዚያም በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም። ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ።” ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጐ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጠረበ፤ በማግስቱም ማልዶ ጌታ እንዳዘዘው ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ። ጌታም በደመና ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የጌታንም ስም አወጀ። ጌታም በፊቱ አልፎ እንዲህ ብሎ አወጀ፦ “ጌታ፥ ጌታ፥ መሓሪ አምላክ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽ፥ ፅኑ ፍቅሩና እውነቱ የበዛ፥ ፅኑ ፍቅሩን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በደለኛውን ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆችና በልጅ ልጆች ላይ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ የሚያመጣ አምላክ ነው።” ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተደፍቶ ሰገደ፦ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ በፊትህ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና እባክህን ጌታ በመካከላችን ይሂድ፤ በደላችንንና ኃጢአታችንን ይቅር በለን፥ ርስትህ አድርገህ ተቀበለን።” እርሱም እንዲህ አለው፦ “እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉና በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገ ተአምራት ፊት አደርጋለሁ፤ እኔ በአንተ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና በመካከላቸው የምትኖርባቸው ሕዝብ ሁሉ የጌታን ሥራ ያያል። ዛሬ የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን፥ ከነዓናዊውን፥ ኬጢያዊውን፥ ፌርዛዊውን፥ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን በፊትህ አወጣለሁ። በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትገባባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውን ትሠብራላችሁ፥ አሼራንም ትቆራርጣላችሁ፤ ለሌላ አምላክ አትስገዱ፥ ስሙ ቀናተኛ የሆነ ጌታ ቀናተኛ አምላክ ነውና። አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህና ከመሥዋዕታቸው እንዳትበላ፥ በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንድ ልጆችህ ብትወስድ፥ ሴቶች ልጆቻቸው አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ልጆችህን ከአምላኮቻቸው ጋር እንዲያመነዝሩ ያደርጓቸዋል። ቀልጠው የተሠሩ የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ። “የቂጣውን በዓል ጠብቀው፤ በአቢብ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ ብላ። ማኅፀንን የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባዕት ሁሉ፥ የበሬህም፥ የበግህም በኩር የእኔ ነው። የአህያውን በኩር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ካልዋጀኸው ግን አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኩር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴ አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛው ቀን ግን ታርፋለህ፥ በምታርስበትና በምታጭድበት ጊዜ ታርፋለህ። የሰባቱን ሱባዔ በዓል ትጠብቃለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም መጨረሻ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይቅረብ። አሕዛብን ከፊትህ አስወግዳለሁ፥ ድንበርህንም አሰፋለሁ፤ በጌታ አምላክህ ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ካለው ቂጣ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካው በዓል መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይደር። የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ ጌታ አምላክህ ቤት ታስገባለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅል።” ጌታም ሙሴን፦ “በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ” አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጌታ ጋር ነበረ፤ ምግብ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም ዓሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። ሙሴ ከሲና ተራራ በሚወርድበት ጊዜ እንዲህ ሆነ፥ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች ከተራራው በሚወርድበት ጊዜ በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተነጋገረ ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። አሮንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ ፊቱ ያንጸባርቅ ነበር፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። ሙሴ ግን ጠራቸው፥ አሮንና የማኅበሩ አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም አነጋገራቸው። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ጌታ በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። ሙሴ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ ጌታ በገባ ጊዜ፥ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገራቸው። የእስራኤል ልጆች የሙሴ ፊት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ ሙሴም ከእርሱ ጋር ለመነጋገር በፊቱ እስኪገባ ድረስ እንደገና በፊቱ ላይ መሸፈኛ ያደርግ ነበር። ሙሴ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንድትፈጽሙት ያዘዘው ቃል ይህ ነው፤ ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ የዕረፍት፥ ለእናንተ የተቀደሰ ሰንበት አለለችሁ፥ በዚህ ቀን የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል። በሰንበት ቀን በመኖሪያዎቻችሁ ሁሉ እሳትን አታንድዱ።” ሙሴ ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፥ እንዲህ በማለት፥ ለጌታ ከእናንተ ዘንድ መባን አቅርቡ፤ የልብ መነሣሣት ያለው ሁሉ ለጌታ መባ ያምጣ፤ ወርቅ፥ ብር፥ ነሐስ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታ፥ የፍየል ጠጉር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት፥ የግራር እንጨት፤ ለመብራት የሚሆን ዘይት፥ ለቅባት የሚሆን ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን የሚሆን ቅመም፥ መረግድ፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። “በእናንተ መካከል ያሉ በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው ጌታ ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ። ማደሪያውን፥ ድንኳኑን፥ መደረቢያውን፥ መያዣዎቹን፥ ሳንቃዎቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹን፤ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውን፥ መሸፈኛ መጋረጃ፥ ገበታውና መሎጊያዎቹን፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹን፥ መብራት የሚያበሩበትን መቅረዝና ዕቃውን፥ ቀንዲሉን፥ የመብራቱን ዘይት፤ የዕጣኑን መሠዊያና መሎጊያዎቹን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፥ የድንኳኑን ደጃፍ መጋረጃ፤ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያና የነሐሱን መከታ፥ መሎጊያዎቹንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን፤ የአደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹንና እግሮቻቸውን፥ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፤ የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩን ካስማዎችና አውታሮቻቸውን፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት እንዲያገለግሉበት የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶችና የልጆቹን ልብሶች።” የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ። ልቡ ያነሣሣውና መንፈሱ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሁሉ ለመገናኛው ድንኳን ሥራና ለአገልግሎቱ ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ የሚሆን ለጌታ ስጦታ አመጡ። ልባቸው የተነሣሣ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ የአፍንጫ ጌጦችን፥ ሎቲዎችን፥ ቀለበቶችን፥ ድሪዎችን፥ የወርቅ ጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሰዎች ሁሉ የወርቅ ስጦታ ለጌታ አመጡ። ሰማያዊ፥ ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታ፥ የፍየል ጠጉር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። የብርና የነሐስ ስጦታ መስጠት የሚችል ሁሉ ለጌታ ስጦታ አቀረበ፤ የግራር እንጨት ያለው ሁሉ ለማንኛውም ሥራ አገልግሎት እንዲውል አመጣ። በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን፥ ሐምራዊውን፥ ቀይ ግምጃውንና ጥሩውን በፍታ አመጡ። ልባቸው በጥበብ ያነሣሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጉር ፈተሉ። አለቆችም የመረግድ ድንጋይ፥ በኤፉድና በደረት ኪስ የሚገቡ ፈርጦችን፥ ቅመማቅመም፥ ለመብራት የሚሆን ዘይት፥ ለቅባት የሚሆን ዘይት፥ ለጣፋጭ ሽታ ዕጣንን አመጡ። ከእስራኤል ልጆች ልባቸው ያነሣሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ጌታ በሙሴ እጅ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ሁሉ የሚሆን ስጦታ በፈቃዳቸው ለጌታ አመጡ። ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “ተመልከቱ፥ ጌታ ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። በእግዚአብሔር መንፈስ፥ በጥበብ፥ በማስተዋል፥ በእውቀት በሥራ ሁሉ ብልሃት ሞላው፤ በወርቅ፥ በብርና በነሐስ በጥበብ እንዲሠራ፥ ፈርጥ የሚሆንን የዕንቁ ድንጋይ በመቅረጽ፥ እንጨት በመጥረብ፥ የብልሃት ሥራ ሁሉ እንዲሠራ ችሎታ ሰጠው። እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሒሳማክ ልጅ ኤልያብ እንዲያስተምሩ በልባቸው አሳደረባቸው። በአንጥረኝነት፥ በንድፍ፥ በሰማያዊ፥ በሐምራዊ፥ በቀይ ግምጃና በጥሩ በፍታ በመጥለፍ፥ ሸማኔ በሚሠራው ሥራ፥ በማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ እንዲያደርጉ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ።” ባስልኤል፥ ኤልያብና ጥበበኞች ሁሉ፥ የመቅደሱን አገልግሎት ሥራ ሁሉ እንዲያደርጉና እንዲያውቁ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ። ሙሴም ባስልኤልን፥ ኤልያብንና ጌታ በልቡ ጥበብን ያሳደረበትን ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውን ለመሥራት ልቡ ያነሣሣውን ሁሉ ጠራቸው። የመቅደሱን ሥራ ለመሥራት የእስራኤል ልጆች ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ወሰዱ። እነዚያም በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ስጦታ አሁንም ማለዳ ማለዳ ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፥ ሙሴንም፦ “ሕዝቡ ጌታ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ አመጡ” አሉት። ሙሴም በሰፈሩ ውስጥ አዋጅ እንዲተላለፍ አዘዘ፦ “ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ስጦታ ከእንግዲህ ወዲህ አያምጣ”፤ ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። ያመጡት ነገር ሥራውን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ይተርፍ ነበር። ሥራ ሲሠሩ ከነበሩት ጥበበኞች የሆኑት ሁሉ ማደሪያውን ሠሩ፤ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ፥ ኪሩቤልም የተጠለፈባቸው ዐሥር መጋረጃዎች ሠሩ። የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የሁሉም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበር። አምስቱን መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አጋጠመ፥ ሌሎቹንም አምስት መጋረጃዎች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠመ። በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ የሰማያዊው ግምጃ ቀለበቶች አደረገ፤ ደግሞ በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ እንዲሁ አደረገ። አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው መጋረጃ አደረገ፥ አምሳ ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ መጋጠሚያ አደረገ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ። አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሠራ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠማቸው፤ ማደሪያውም አንድ ወጥ ሆነ። ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን መጋረጃዎችን ከፍየል ጠጉር ሠራ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠራ። የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሠላሳ ክንድ፥ የእያንዳንዱም መጋረጃ ወርድ አራት ክንድ ነበረ፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበረ። አምስቱን መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ፥ ስድስቱንም መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ አድርጎ አጋጠማቸው። ከተጋጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረገ፤ እንዲሁም በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በሚጋጠሙበት በኩል አምሳ ቀለበቶች አደረገ። ድንኳኑ አንድ ወጥ እንዲሆን የሚያጋጥሙበት አምሳ የነሐስ መያዣዎችን ሠራ። ለድንኳኑ መሸፈኛ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ በላዩ ላይ የሚሆን መሸፈኛ ከአቆስጣ ቁርበት ሠራስስ። ለማደሪያው የሚቆሙ ሳንቃዎችን ከግራር እንጨት ሠራ። የእያንዳንዱ ሳንቃ ርዝመት ዐሥር ክንድ፥ ወርድ አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። እያንዳንዱ ሳንቃ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያያዝበት ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩት፤ ለማደሪያው ሳንቃዎች በሙሉ እንዲሁ አደረገ። ለማደሪያው ሳንቃዎችን አደረገ፤ በደቡብ በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ ከሃያው ሳንቃዎች በታች አርባ የብር እግሮችን አደረገ፤ በአንደኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች፥ በሁለተኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች አደረገ። ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ አርባ የብር እግሮች፥ ከአንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች፥ ከአንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረገ። በማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራብ በኩል ስድስት ሳንቃዎችን አደረገ። በማደሪያው በሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቃዎችን አደረገ። ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ። ስምንት ሳንቃዎች ነበሩ፥ የብር እግሮቻቸውም ዐሥራ ስድስት እግሮች ነበሩ፥ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ነበሩ። ከግራር እንጨት መወርወሪያዎችን ሠራ፥ በማደሪያው በአንደኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት፥ በማደሪያው በሁለተኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራቡ በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎችን ሠራ። በመካከል ያለውን መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲያልፍ አደረገ። ሳንቃዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፥ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያው ማስገቢያ እንዲሆኑ ከወርቅ ሠራ፥ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው። መጋረጃውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሠራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረገ። አራት ምሰሶዎችን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች ሠራላቸው። ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ መጋረጃ አደረገ፤ አምስቱን ምሰሶዎችንና ኩላቦቻቸውን አደረገ፤ ጉልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውን በወርቅ ለበጣቸው፥ አምስቱ እግሮቻቸው የነሐስ ነበሩ። ባስልኤል ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበር። ውስጡንና ውጪውን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። በአራቱ እግሮቹ ላይ አራት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገለት፤ በአንድ በኩል ሁለት ቀለበቶችን፥ በሌላው በኩል ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። መሎጊያዎችን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አስገባ። ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበር። ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤል ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ላይ በሁለቱ ጫፎች አደረጋቸው። አንዱን ኪሩብ በዚህኛው በኩል፥ አንዱን ኪሩብ በዚያኛው በኩል አደረጋቸው፥ በሁለቱ ጫፎች ከስርየት መክደኛው ሠራቸው። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ነበሩ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ትይዩ ነበሩ፥ የኪሩቤል ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ይመለከት ነበር። ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ። በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። በዙሪያው አንድ ስንዝር የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅ አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮች ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አጠገብ ነበሩ። ገበታውን እንዲሸከሙባቸው መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎችን፥ ጽዋዎችንና ለማፍሰሻ የሚሆኑ መቅጃዎችን፥ ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጉብጉቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ። በጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ በኩል፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ በኩል። በአንደኛው ቅርንጫፍ እንቡጥ፥ ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ እንቡጥ፥ ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። በመቅረዙም ጉብጉቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጉብጉብ ነበረ። ጉብጉቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። ሰባቱን መብራቶቹን፥ መኰስተሪያዎቹንና የኩስታሪ ማድረጊያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። መቅረዙንና ዕቃዎቹን ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ሠራ። የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። ላዩን፥ የጎኑን ዙሪያ በሙሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በሁለቱም ጎን በሁለቱም ማዕዘን አደረጋቸው፥ ለመሸከምም የመሎጊያዎቹ ስፍራ ነበሩ። መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። የተቀደሰ የቅባት ዘይት፥ ንጹሕና መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን ቀማሚ እንደሚሠራው አደረገ። የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ እርሱም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱ አምስት ክንድ ነበር፥ አራት ማዕዘንም ነበረ፥ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ። በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ በነሐስም ለበጠው። የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ፥ ምንቸቶቹን፥ መጫሪያዎቹን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖቹን፥ ሜንጦቹን፥ ማንደጃዎቹን ሠራ፤ ዕቃዎቹን በሙሉ ከነሐስ ሠራ። ለመሠዊያውም መረብ የሚመስል የነሐስ መከታ ከጠርዙ በታች እስከ መሠዊያው ግማሽ ድረስ ሠራለት። ለነሐሱ መከታ አራቱ ማዕዘኖች ለመሎጊያዎቹ ማስገቢያ እንዲሆኑ አራት ቀለበቶችን አደረገ። መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠራ፥ በነሐስም ለበጣቸው። እንዲሸከሙትም መሎጊያዎቹን በመሠዊያው ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባ፤ ክፍትም አድርጎ ከሳንቃዎች ሠራው። የነሐሱ የመታጠቢያ ሳሕንና የነሐሱ ማስቀመጫውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች መስተዋት ሠራ። አደባባዩንም ሠራ፤ በደቡብ በኩል የአደባባዩ መጋረጃዎች ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ ከጥሩ በፍታ የተፈተለ ነበር። ምሰሶዎቻቸው ሃያ፥ የነሐስ እግሮቻቸውም ሃያ ነበሩ፥ የምሰሶዎቹ ኩላቦችና ዘንጎች ከብር የተሰሩ ነበሩ። በሰሜን በኩል መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቻቸው ሃያ የነሐስ እግሮቻቸውም ሃያ ነበሩ፥ የምሰሶዎቹ ኩላቦችና ዘንጎች ከብር የተሰሩ ነበሩ። በምዕራብ በኩል አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ነበሩ፤ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር የነሐስ እግሮች ነበሩት፥ የምሰሶዎቹ ኩላቦችና ዘንጎች ከብር የተሰሩ ነበሩ። በምሥራቅም በኩል አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ነበሩ። በአንድ በኩል የመጋረጃዎቹ ርዝመት ዐሥራ አምስት ክንድ ነበረ፥ ሦስት ምሰሶዎች እና ሦስት እግሮች ነበሩ። በሁለተኛው በኩል በአደባባዩ መግቢያ በዚህና በዚያ ዐሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች፥ ሦስት ምሰሶዎች እና ሦስት እግሮች ነበሩ። በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ። የምሰሶዎቹ እግሮች ከነሐስ የተሠሩ፥ የምሰሶዎቹ ኩላቦችና ዘንጎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ የምሰሶዎቹ ጉልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ያሉ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው። የአደባባዩ መግቢያ መጋረጃ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች አምስት ክንድ ነበረ፤ ምሰሶዎቹ አራት ነበሩ፤ ከነሐስ የተሠሩ እግሮች አራት፥ ኩላቦቹ ከብር የተሠሩ ነበሩ፥ ጉልላቶቻቸውና ዘንጎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር። የማደሪያውና በዙሪያው ያለ የአደባባዩ ካስማዎች ሁሉ ከነሐስ የተሠሩ ነበሩ። በሙሴ ትእዛዝ መሠረት የሌዋውያን አገልግሎት ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ የተቆጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው። ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሑር ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል ጌታ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሒሳማክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም ቀራጭ፥ ንድፍ አውጪ፥ እንዲሁም በሰማያዊ በሐምራዊ፥ በቀይ ግምጃና በጥሩ በፍታ የሚጠልፍ ነበረ። ለመቅደሱ ሥራ የተደረገው ወርቅ ሁሉ፥ የተሰጠው ወርቅ በሙሉ፥ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ። ከተቆጠረው ማኅበር የተገኘው ብር፥ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ። በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፥ የሰቅል ግማሽ ከተቆጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ይህም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያ በላይ የተቆጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ። መቶው የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶ መክሊት መቶ እግሮች ተሠሩ ይኸውም ለአንድ እግር አንድ መክሊት ማለት ነው። ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶዎቹን ኩላቦችና ዘንጎች ሠራ፥ የምሰሶዎቹንም ጉልላቶች ለበጠ። የተሰጠውም ነሐስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን መግቢያ እግሮች፥ የነሐሱን መሠዊያ፥ ለእርሱም የሚያገለግለውን የነሐሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ ሠራ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩን መግቢያ እግሮች፥ የማደሪያውን ካስማዎች ሁሉና በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ካስማዎች ሁሉ ሠራ። በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ በብልሃት የተሠራ ልብስ አደረጉ፥ ጌታም ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ። ኤፉዱንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራ። ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቆረጡት። ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራው በሰማያዊው፥ በሐምራዊው፥ በቀዩ ግምጃ፥ በተፈተለው ጥሩ በፍታ መካከል በእርሱ ጠለፉ። እንዲጋጠም በሁለቱ ትከሻዎች ላይ መጋጠሚያ ሠሩለት፥ በሁለቱ ጫፎች እንዲጋጠም አደረጉት። በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ፥ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከእርሱ ጋር ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር። በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች እንዲሆኑ በኤፉዱ በትከሻው ላይ አደረጋቸው። የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱንም ኪስ ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ አንድ ስንዝር፥ ወርዱም አንድ ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። በእርሱም ላይ በአራት ረድፍ ዕንቁዎቹን አደረጉበት፤ በመጀመሪያ ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና አልማዝ፤ በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፤ በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ። የዕንቁዎቹም ድንጋዮች እንደ ዐሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፥ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። ለደረቱ ኪስም እንደ ገመድ የተጐነጐኑ ድሪዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ። ሁለት የወርቅ ፈርጦችና ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ በኩል አደረጉት። ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ጫፎች ባሉት በሁለቱ ቀለበቶች አስገቡ። የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ። ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው። ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከትከሻዎቹ በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሰሩት። የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ሠራው። በቀሚሱ መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም አንገትጌው ዙሪያውን ተጠልፎ ነበር። በቀሚሱ ታችኛው ዘርፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ በፍታ ሮማኖችን አደረጉ። ከንጹሕ ወርቅ ሻኩራዎችን ሠሩ፥ ሻኩራዎቹንም በሮማኖቹ መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለማገልገል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኩራና ሮማን፥ ሻኩራና ሮማን አደረጉ። የሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ቀሚስ አዘጋጁ፥ ከጥሩ በፍታ መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም ቆቦች፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ፥ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተጠለፈ መታጠቂያ ሠሩ። የተቀደሰውን አክሊል አበባ ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም “ለጌታ የተቀደሰ” የሚል ጽሑፍ ቀረጹበት። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው በመጠምጠሚያው ላይ እንዲያንጠለጥሉት ሰማያዊ ፈትል አሰሩበት። የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጠናቀቀ። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ፤ እንዲሁ አደረጉ። ማደሪያውን ወደ ሙሴ አመጡት፥ ድንኳኑን፥ የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ፥ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንና እግሮቹን፥ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ መሸፈኛ መጋረጃ፥ የምስክሩን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውን፥ ገበታውንና ዕቃውን ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹን፥ ንጹሑን መቅረዝ፥ መብራቶቹን፥ የተደረደሩትን ቀንዲሎችና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ፥ የመብራቱን ዘይት፥ የወርቁን መሠዊያ፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፥ የድንኳኑን ደጃፍ መጋረጃ፥ የናሱን መሠዊያ፥ የናሱን መከታ፥ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫው፥ የአደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹን፥ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹን፥ ካስማዎቹን፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም እንዲያገለግሉበት የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶችና የልጆቹን ልብሶች አመጡ። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ። ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆ ልክ ጌታ እንዳዘዘው አድርገውት ነበር፤ እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። ገበታውን ታስገባለህ፥ በአግባቡ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አስገብተህ ቀንዲሎቹን ትለኩሳለህ። ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ መጋረጃውን ትጋርዳለህ። የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት ታኖረዋለህ። የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ መጋረጃውንም በአደባባዩ ደጃፍ ትዘረጋለህ። የቅባቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን እና በእርሱ ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱን፥ ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ትቀባለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰዋለህም። አሮንንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። አሮንን የተቀደሰውን ልብስ ታለብሰዋለህ፥ ካህን እንዲሆነኝ ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰውማለህ። ልጆቹንም አቅርበህ ቀሚስ ታለብሳቸዋለህ፤ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፥ ካህናትም ይሆኑልኛል፤ ቅባታቸውም ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ክህነት ይሆንላቸዋል።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ፥ እንዲሁም አደረገ። እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹን አኖረ፥ ሳንቆቹን አቆመ፥ መወርወሪያዎቹን አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑንም መደረቢያ በላዩ አደረገበት። ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹንም በታቦቱ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው አስገባ፥ የሚሸፍነውን መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ኅብስቱን በላዩ በጌታ ፊት አሰናዳ። መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ቀንዲሎቹን በጌታ ፊት አበራ። የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን ዐጠነበት። መጋረጃውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ሰቀለ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠልና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት። የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀመጠ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። ሙሴ፥ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በእርሱ ታጠቡ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በሚቀርቡበት ጊዜ ይታጠቡ ነበር። በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ በአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። በዚህ ዓይነት ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። ከዚህ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፥ የጌታም ክብር ማደሪያውን ሞላ። ደመናው በላዩ ስለ ነበረና የጌታ ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። ደመናው ከማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ልጆች ወደሚጓዙበት ሁሉ ይሄዱ ነበር። ደመናው ካልተነሣ ግን እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። በጉዞአቸው ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የጌታ ደመና በቀን በማደሪያው ላይ፥ በሌሊትም እሳት በዚያ ላይ ነበረ። ጌታም ሙሴን ጠርቶ ከመገናኛው ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለጌታ መባ ሲያቀርብ፥ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከሆኑ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ ታቀርባላችሁ። “መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበሬ መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በጌታ ፊት እንዲሠምርለት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የእርሱንም ኃጢአት ለማስተስረይ የሠመረ ይሆንለታል። በሬውንም በጌታ ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል። የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ብልቶቹንና ራሱን ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ በእሳትም የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ፥ በጌታ ዘንድ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ሁሉንም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። “የእርሱም ቁርባን ለሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል። በመሠዊያውም አጠገብ በስተ ሰሜን በኩል በጌታ ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። እንዲሁም ከራሱና ከስቡ ጋር አብሮ በየብልቱ ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን ያቀርበዋል፤ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም በጌታ ዘንድ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። “ለጌታም የሚቀርበው ቁርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቁርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል። ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል፤ ራሱንም ይቈለምመዋል፤ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል። ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፈጠፋል፤ የሆድ ዕቃውንም ከላባዎቹ ጋር ለይቶ በመሠዊያው አጠገብ በስተ ምሥራቅ በኩል ባለው በአመዱ ስፍራ ይጥለዋል፤ ክንፎቹንም ይዞ በመነጠል ይቀድደዋል እንጂ አይከፍለውም። ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም በጌታ ዘንድ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።” “ማናቸውም ሰው የእህል ቁርባን ለጌታ ሲያቀርብ ቁርባኑ ከመልካም ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስበታል፥ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ ወደ አሮንም ልጆች ወደ ካህናቱ ያመጣዋል። ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱ አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ከወሰደ በኋላ ካህኑ ለመታሰቢያ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ፥ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ከእህሉም ቁርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለጌታ በእሳት ከቀረበው የቁርባን ክፍል በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው። “በምድጃ የተጋገረውን የእህል ቁርባን ስታቀርብ በዘይት ተለውሶ እርሾ ያልገባበት፥ የመልካም ዱቄት የቂጣ እንጐቻ ወይም እርሾ ያልነካው በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። ቁርባንህም በምጣድ የተጋገረ የእህል ቁርባን ቢሆን፥ እርሾ ያልገባበት፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት ቂጣ ይሁን። ቈራርሰህም ዘይት ታፈስበታለህ፤ የእህል ቁርባን ነው። ቁርባንህም በመጥበሻ የተጋገረ የእህል ቁርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ዱቄት የተዘጋጀ ይሁን። ከእዚህም ነገረሮች የተዘጋጀውን የእህል ቁርባን ወደ ጌታ ታመጣለህ፤ ለካህኑም ይሰጣል፥ እርሱም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። ካህኑም ከእህሉ ቁርባን መታሰቢያውን አንሥቶ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ከእህሉም ቁርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለጌታ በእሳት ከቀረበው የቁርባን ክፍል በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው። “ማንኛውም እርሾ ያለበትን ነገርና ማርን፥ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጋችሁ አታቃጥሉትምና ለጌታ የምታቀርቡት የእህል ቁርባን ሁሉ በእርሾ የተዘጋጀ አይሁን። እነዚህንም የበኵራት ቁርባን አድርጋችሁ ለጌታ ታቀርባላችሁ፤ እንደ መዓዛው ያማረ ሽታ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠሉም። የምታቀርበውን የእህል ቁርባን ሁሉ በጨው ታጣፍጠዋለህ፤ የአምላክህንም የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቁርባንህ እንዳታጐድል፤ በቁርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ታቀርባለህ። “ከበኵራትም የእህል ቁርባን ለጌታ የምታቀርብ ከሆነ፥ በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸትን የበኵራትህ የእህል ቁርባን አድርገህ ታቀርባለህ። ዘይትም ታፈስበታለህ፥ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቁርባን ነው። ካህኑም ከተፈተገው እህል ከዘይቱም ወስዶ፥ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር መታሰቢያውን ያቃጥላል፤ ይህ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ነው።” “ቁርባኑም የአንድነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከበሬ መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በጌታ ፊት ያቅርብ። እጁንም ለቁርባን ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። ከሰላሙም መሥዋዕት ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ የሚያቀርበው፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው። የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ነው። “ለጌታም ለአንድነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቁርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። ለቁርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በጌታ ፊት ያቀርበዋል፤ እጁንም ለቁርባን ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። ከሰላሙም መሥዋዕት ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ የሚያቀርበው፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው። ካህኑም ለጌታ በእሳት ላይ የሚቀርብ ማዕድ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። “ቁርባኑም ፍየል ቢሆን በጌታ ፊት ያቀርበዋል፤ እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። ከእርሱም ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ ከቁርባኑ የሚያቀርበው፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው። ካህኑም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ማዕድ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ስቡ ሁሉ ለጌታ ነው። በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ ፈጽሞ ማንኛውንም ስብና ደም እንዳትበሉ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ባለማወቅ ጌታ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ኃጢአት ቢሠራ፥ የተቀባውም ካህን ኃጢአት ሠርቶ በሕዝቡ ላይ በደል ቢያመጣ፥ ስለ ሠራው ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለጌታ ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርባል። ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናል፥ ወይፈኑንም በጌታ ፊት ያርደዋል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ትዩዩ ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጫል። ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው መዐዛው ያማረ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር፥ ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንደሚወሰደው ከወሰደ በኋላ፥ ካህኑ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። የወይፈኑን ቆዳ፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ አመድ ወደሚፈስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዳል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ ጌታም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ሠርተው ቢበድሉ፥ የሠሩትም ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በጌታ ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በጌታ ፊት ይታረዳል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው በመሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። የኃጢአት መሥዋዕት በሆነው ወይፈን ላይ እንዳደረገው እንዲሁ በዚህ ወይፈን ላይ ደግሞ ያደርጋል፤ እርሱም እንዲህ ያደርግበታል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈሩ ውጭ ይወስዳል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። “አንድ ገዢም ኃጢአትን ቢሠራ፥ ጌታም አምላኩ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ አንዱን ባለማወቅ ሠርቶ ቢበድል፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት የታወቀ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቁርባኑ ያቀርባል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በጌታ ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ እንደ አንድነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ባለማወቅ ጌታ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ኃጢአት ቢሠራና ቢበድል፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት የታወቀ ቢሆን፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቁርባኑ ያመጣል። እጁንም የኃጢአት መሥዋዕት በሆነችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መሥዋዕት ያርዳል። ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ የተረፈውንም ደምዋን ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሳል። ከአንድነት መሥዋዕት ላይ እንደተወሰደው ስብ እንዲሁ የእርሷን ስብ ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። እጁንም የኃጢአት መሥዋዕት በሆነችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚያርድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ የተረፈውንም ደምዋን ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሳል። ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው ጠቦት ላይ ስቡ እንደሚወሰድ እንዲሁ የእርሷን ስብ ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለጌታ በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “ማንም ሰው የመሓላን ቃል ቢሰማ፥ ምስክርም ሆኖ ወይም ስለ ነገሩ አይቶ ወይም አውቆ ባይናገር፥ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል። ማንም ሰው ማንኛውንም ርኩስ ነገር ማለትም የረከሰ አውሬ በድን፥ ወይም የረከሰ ከብት በድን፥ ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚርመሰመስ የረከሰ ፍጥረት በድን ሳይታወቀው ቢነካ፥ እርሱ ርኩስ ይሆናል፤ በደለኛም ነው፤ ወይም የረከሰን ሰው በመንካት ከሚያረክስ ከማናቸውም ዓይነት ርኩሰት ሳይታወቀው ነክቶ ቢረክስ፥ ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደለኛ ይሆናል። ማናቸውም ሰው ክፉን ወይም መልካምን ለማድረግ ሳያስብ በከንፈሩ ተናግሮ ቢምል፤ ሳያስብ የማለው ስለ ማናቸውም ነገር ቢሆን፤ ይህንንም ሳይታወቀው ቢያደርግ፤ በታወቀው ጊዜ ከዚህ ነገር በአንዱ በደለኛ ይሆናል። አንድ ሰው ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ በደለኛ ቢሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። ስለ ሠራው ኃጢአት ለጌታ የበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ እርሱም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። “እርሱም ጠቦትን ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባይኖረው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ለበደል መሥዋዕት ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት ሌላውን ደግሞ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለጌታ ያመጣል። ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ እርሱም አስቀድሞ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ያቀርባል፥ ራሱንም ከአንገቱ ይቈለምመዋል፥ ነገር ግን አይቈርጠውም። ከኃጢአቱም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ግድግዳ ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈውም ደም ከመሠዊያው በታች ይንጠፈጠፋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። እንደ ሥርዓቱም ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘጋጀዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “እርሱም ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባይኖረው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት እንደ ቁርባኑ አድርጎ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካም ዱቄት ለኃጢአት መሥዋዕት ያመጣል፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና ዘይት አያፈስበትም፥ ዕጣንም አይጨምርበትም። ወደ ካህኑም ያመጣዋል፥ ካህኑም መታሰቢያው እንዲሆን ከእርሱ እፍኝ ሙሉ ይወስዳል፥ ለጌታም በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም የኃጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከእነዚያ በአንዳቸው ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። እንደ እህል ቁርባንም እንዲሁ የተረፈው ለካህኑ ይሆናል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ማናቸውም ሰው ቢተላለፍ፥ ሳያውቅም ለጌታ በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለጌታ ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያመጣል፤ ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል። በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኃጢአት ዕዳ ይከፍላል፥ በሚከፍለውም ዕዳ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበታል፥ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ፥ ጌታም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ቢተላለፍ፥ ባያውቅም፥ ያ ሰው በደለኛ ነው፥ ኃጢአቱንም ይሸከማል። ነውር የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው እንደ ግምጋሜህ መጠን ለበደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያመጣል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሠራው ስሕተት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው፤ በእውነት በጌታ ፊት በደለኛ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ በጌታም ላይ ፈጽሞ እምነትን ቢያጎድል፥ በአደራ ከእርሱ ዘንድ የተቀመጠን ነገር ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢሠራ፥ ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ኃጢአት በአንዱ ቢሠራ፥ እርሱም ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም በአደራ ከእርሱ ዘንድ የተቀመጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ ወይም በሐሰት የማለበትን ምንም ዓይነት ነገር ይመልስ፤ እርሱም የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን በሙሉ የወሰደውን ነገር ይመልስ፥ በእርሱም ላይ አምስት እጅ ጨምሮበት ለባለቤቱ ይስጠው። ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ ለበደል መሥዋዕት፥ ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ፥ ለጌታ ስለ በደሉ መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያመጣል። ካህኑም በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዝ፦ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጠባ ድረስ ይሆናል፤ የመሠዊያውም እሳት ዘወትር ይንደድበት። ካህኑም ሰውነቱን ለመሸፈን የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ውጭ ወደ ሆነ ወደ ንጹሕ ስፍራ ያወጣዋል። እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይንደድበት፥ አይጥፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥለበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ እንዲሁም የአንድነትን መሥዋዕት ስብ በዚያ ላይ ያቃጥላል። ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይንደድ፤ እርሱም አይጥፋ። “የእህሉም ቁርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ፊት ለፊት በጌታ ፊት ያቀርቡታል። ካህኑም ከእህሉ ቁርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ እንዲሁም በእህሉ ቁርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ እርሾ ያልነካው ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን በእሳት የሚቀርብ ቁርባኔ አድርጌ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ነው። ለጌታ በእሳት ከሚቀረበው ቁርባን ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ድርሻቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “እርሱ በተቀባበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኩሌታውን በጥዋት፥ እኩሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቁርባን አድርገው ለጌታ የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቁርባን ይህ ነው። ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይዘጋጃል፤ ደኅና ተደርጎ ከተለወሰ በኋላ ታመጣዋለህ፤ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የተጋገረውን የእህል ቁርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ። ከልጆቹም መካከል በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያዘጋጀዋል። ለዘለዓለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለጌታ ይቃጠላል። ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቁርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በጌታ ፊት ይታረዳል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል። ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ በልብስ ላይ ደሙ ከቶ ከተረጨ የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ። የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ ነገር ግን በናስ ዕቃ የተቀቀለ እንደሆነ ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል። ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እጅግም የተቀደሰ ነው። ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ እንዲሆን ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።” “የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል። ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል። ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። ካህኑም ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው። ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። የበደል መሥዋዕት እንደ ኃጢአት መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ አለ፤ ያም በእነርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ከእነርሱ ላይ ለራሱ ስለ ሚወስድ ነው። እንዲሁም የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን፥ ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቆዳ ለዚያው ካህን ይሆናል። በምድጃ ላይ የተጋገረው፥ በመጥበሻም ወይም በምጣድ ላይ የተዘጋጀው የእህል ቁርባን ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቁርባን በጠቅላላ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ እያንዳንዱም እንደሌላው ወንድሙ ይደርሰዋል። “ሰው ለጌታ የሚያቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። የሚያቀርውም ለምስጋና ቢሆን፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር እርሾ ያልገባበት በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ እርሾ ያልነካው በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል። ለምስጋና የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕቱን ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። ለጌታ እንደ ስጦታ አድርጎ አንድ ኅብስት ከእያንዳንዱ ቁርባን ያቀርባል። ከእርሱም የቀረው የአንድነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። “ለምስጋና የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕቱን ሥጋ በሚያቀርብበት ቀን ይበላ፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያሳድር። የቁርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ቀን ይበላ፤ ከእርሱም የቀረውን በማግስቱ ይበላ፤ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከመሥዋዕቱ የተረፈው ሥጋ በእሳት ይቃጠል። በሦስተኛው ቀን ከአንድነቱ መሥዋዕት ከቶ ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርለትም ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቁርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ሰውም ከእርሱ ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል። “ሥጋው ማናቸውንም ርኩስ ነገር ከነካ አይበላ፤ በእሳት ይቃጠል። ሌላውን ሥጋ ግን ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ከሥጋው ይብላ። ነገር ግን የረከሰ ሰው ሆኖ ሳለ፥ ለጌታ ከሆነው ከአንድነት መሥዋዕት ሥጋ የበላ እንደሆነ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። ማንም ሰው የሰውን ርኩሰት ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ምንም ዓይነት ርኩስ ሆኖ የተጠላን ማናቸውንም ርኩስ ነገር ነክቶ፥ ለጌታ ከሆነው ከአንድነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። ሞቶ የተገኘን የእንስሳ ስብ፥ እንዲሁም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ስብ ለማናቸውም ለሌላ ተግባር አድርጉት እንጂ ከእርሱ ፈጽሞ ምንም አትብሉ፤ ለጌታ በእሳት ከሚያቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሰው ሁሉ፥ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋ። በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን ፈጽሞ አትብሉ። ማንም ሰው ደም የሚበላ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ለጌታ የአንድነትን መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቁርባኑን ለጌታ ከሰላሙ መሥዋዕት ያመጣል። የእርሱ እጆች ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ያመጣሉ፤ እርሱም ፍርምባው በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘወዝ ፍርምባውን ከስቡ ጋር ያመጣዋል። ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል። ከሰላም መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን እንደ ቁርባን አድርጋችሁ ለካህኑ ትሰጡታላችሁ። ከአሮንም ልጆች መካከል የአንድነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርበው ለእርሱ ቀኝ ወርቹ ድርሻው ይሆናል። የሚወዘወዘውን ፍርምባና እንደ ቁርባን የሚቀርበውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከሰላም መሥዋዕታቸው ወስጄ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘለዓለም ድርሻ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ እነርሱን ሰጥቼአቸዋለሁ። “ጌታን በክህነት እንዲያገለግሉት እነርሱን ባቀረባቸው ቀን ለጌታ በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ይህ ነው። ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ድርሻቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን ከእስራኤል ልጆች እንዲሰጣቸው ጌታ ያዘዘው ይህ ነው። የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቁርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። ጌታ በሲና ምድረ በዳ ቁርባናቸውን ለጌታ እንዲያቀርቡ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅባቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሚቀርበውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ እርሾ ያልነካው ቂጣ የሚቀመጥበትንም መሶብ ውሰድ፤ ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ። ሙሴም ማኅበሩን፦ “ጌታ እንዲደረግ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው። ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። ልብስም አለበሰው፥ በመርገፍም በተጌጠ ዝናር አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ የኤፉድ ማንጠልጠያ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ ኤፉዱን አሰረው። የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል፥ የወርቅ ጉንጉን ሆኖ በቅጠል መልክ የተሠራውን የተቀደሰ አክሊል፥ አደረገ። ሙሴም የቅባቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ እንዲቀደሱም መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና መቀመጫውን ቀባ። ከቅባቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ እንዲቀደስም ቀባው። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመርገፍም በተጌጠ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው። የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ እንዲያስተሰርይለትም ቀደሰው። በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ከስባቸው ጋር ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቆዳውንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። ከዚያም በኋላ ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ በጌታ ፊት ካለው እርሾ ያልነካው ቂጣ ከሚቀመጥበት መሶብ አንድ እርሾ ያልገባበት የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ከዘይት ጋራ የተሰናዳ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በጌታም ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዛቸው። ከዚያም በኋላ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የቅድስና መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ ከእጃቸው ተቀብሎ በሚቃጥለው መሥዋዕት ላይ በመሠዊያው አቃጠለው። ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘው፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከሚቀርበው አውራ በግ የሆነ የሙሴ ድርሻ ነበር። ሙሴም ከቅባቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። ሙሴም አሮንንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ ከዚህም ጋር ‘አሮንና ልጆቹ ይበሉታል’ ብዬ እንዳዘዝሁ የቅድስናው መሥዋዕት እንጀራ ከሚቀመጥበት መሶብ ውስጥ ያለውን እንጀራ በዚያ ትበሉታላችሁ። ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። እናንተን በቅድስና ማዕረግ ለመሾም ሰባት ቀን ይወስዳልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። ዛሬ እንደተደረገው እንዲሁ ለእናንተ ማስተስረያም እንዲደረግ ጌታ አዝዞአል። እንዳትሞቱም የጌታን ትእዛዝ እየጠበቃችሁ፥ ለሰባት ቀን ሌሊትና ቀን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ትቀመጣላችሁ፤ እኔ እንዲህ ታዝዣለሁና።” አሮንና ልጆቹም ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዘውን ቃላት ሁሉ አደረጉ። በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ከመንጋው ነውር የሌለባቸውን ለኃጢአት መሥዋዕት እምቦሳውን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ወስደህ በጌታ ፊት አቅርብ። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ‘ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ ለአንድነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቁርባን በጌታ ፊት ለመሠዋት ውሰዱ፥ ዛሬ ጌታ ተገልጦላችኋልና።’ ” ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በጌታ ፊት ቆሙ። ሙሴም፦ “የጌታም ክብር እንዲገለጥላችሁ ጌታ እንድታደርጉት ያዘዘው ይህን ነገር ነው፤” አለ። ሙሴም አሮንን፦ “ወደ መሠዊያው ቅረብ፥ የኃጢአትህንም መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ ጌታም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቁርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም” አለው። አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኩላሊቶቹን፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። ሥጋውንና ቆዳውንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። በየብልቱም የተሸነሸነውን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከጭንቅላቱ ጋር አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም ባለው የሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። ከዚያም በኋላ የሕዝቡን ቁርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው የኃጢአት መሥዋዕት ሠዋው። እንደ ሥርዓቱም አድርጎ የሚቃጠለውን መሥዋዕትም አቀረበ። የእህሉንም ቁርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አጠገብ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው። ስለ ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት የሚቀርበውን በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ የበሬውንና የአውራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኩላሊቶቹንም፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ አመጡለት። ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ እርሱም ስቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ ሙሴም እንደ ታዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘ። አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ እርሱም የኃጢአቱንና የሚቃጠለውን የሰላሙንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ በወጡም ጊዜ ሕዝቡን ባረኩ፤ የጌታም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ሰገዱ። የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በጌታም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደውን እሳት አቀረቡ። እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጥቶ እነርሱን በላቸው፥ በጌታም ፊት ሞቱ። ሙሴም አሮንን፦ “ጌታ፦ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀደሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህ ነው” አለው፤ አሮንም ዝም አለ። ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፦ “ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ውሰዱአቸው” አላቸው። ሙሴም እንደ ተናገረው ቀርበው ቀሚሳቸውን ይዘው አነሡአቸው፥ ከሰፈሩም ውጭ ወሰዱአቸው። ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ እርሱ እንዳይቈጣ የራሳችሁን ጠጉር አታጐስቁሉ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ጌታ እሳትን ልኮ ስላደረገው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። እንዲሁም የጌታ የቅባት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትውጡ።” እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ። ጌታም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው፤ በዚህም በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል እንድትለዩ፥ ጌታም በሙሴ አንደበት የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች እንድታስተምሩ ነው።” ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እጅግ የተቀደሰ ነውና ለጌታ ከሆነው በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን የተረፈውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ እርሾም ያልገባበት ቂጣ አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤ ለጌታም ከሆነው በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ድርሻ ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤ ይህንንም እንዲህ ታዝዣለሁና። ነገር ግን የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህና ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ፤ እነዚህ ከእስራኤል ልጆች ከሰላም መሥዋዕት ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆኑ የተሰጡ ናቸውና። የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ፥ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት እንዲወዘወዝ ያመጣሉ፤ ጌታ እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ላሉት ለልጆችህ የዘለዓለም ድርሻ ይሆናል።” ሙሴም የኃጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነው ፍየል አጥብቆ ጠየቀ፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ ብሎ ተቆጣ፦ “እጅግ የተቀደሰ ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢአት እንድትሸከሙ፥ በጌታም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶአልና ለምን የኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? እነሆ፥ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንደ ታዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ይገባችሁ ነበር።” አሮንም ሙሴን፦ “እነሆ፥ ዛሬ የኃጢአታቸውን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውን በጌታ ፊት አቀረቡ፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ነገር በእኔ ላይ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢአት መሥዋዕት ብበላ ኖሮ በጌታ ፊት መልካም ይሆን ነበርን?” አለው። ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩ፦ በሕይወት ከሚኖሩ ከምድር እንስሶች ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው። ለሁለት የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸውም ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። እርያም ሰኮናው ለሁለት ተሰንጥቋል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። “በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ፤ በውኆች በባሕሮችም በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። ነገር ግን በውኆች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥም በሕይወት ከሚኖሩ ነፍሳት፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸውን ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ፤ ሥጋቸውንም አትብሉ፥ በድናቸውንም ተጸየፉ። በውኃ ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። “ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭላት፥ ጭልፊት በየወገኑ፥ ቁራ ሁሉ በየወገኑ፥ ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥ ጉጉት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። “በአራት እግሮች የሚንቀሳቀሱ፥ ጥቃቅን በራሪ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። ነገር ግን ከእግሮቻቸው በላይ በምድር ላይ የሚዘሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው፥ በአራት እግሮች ከሚሄዱ ጥቃቅን በራሪ ነፍሳት እነዚህን ትበላላችሁ። ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አንበጣዎችን በየወገናቸው፥ ደጎብያዎችን በየወገናቸው፥ ፌንጣዎችን በየወገናቸው፥ ኲብኲባዎችን በየወገናቸው። ነገር ግን ሌሎች አራት እግሮች ያሉአቸው ጥቃቅን በራሪ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። “በእነዚህም የረከሳችሁ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በድናቸውንም የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ሰኮናውም የተከፈለ ሆኖ ነገር ግን ለሁለት ያልተሰነጠቀ፥ የሚያመሰኳም እንሰሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ እርሱንም የሚነካ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ መካከል፥ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። “በምድር ላይም ከሚርመሰመሱ ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥ ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ መካከል በእናንተ ዘንድ ርኩሶች የሆኑት እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ከእነርሱም የሞተው በማናቸውም ነገር ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ይሆናል፤ የእንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቆዳ ወይም ከረጢት ቢሆን ለማናቸውም ሥራ የሚጠቅም ዕቃ ሁሉ በውኃ ውስጥ ይደረግ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ግን ይነጻል። ከእነርሱም አንዱ በማናቸውም የሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፥ በውስጡ ያለው ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እናንተም ዕቃውን ትሰብሩታላችሁ። እንዲህ ካለው ዕቃ ውኃ ፈስሶ የሚበላን ምግብ ሁሉ ከነካ ምግቡ ርኩስ ይሆናል፤ እንዲህም ካለው ዕቃ ሁሉ ማናቸውም የሚጠጣ መጠጥ በውስጡ ካለ እርሱ ርኩስ ይሆናል። ከበድናቸውም የሚወድቅበት ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰበር፤ ርኩሶች ናቸው፤ በእናንተም ዘንድ ርኩሶች ይሆናሉ። ነገር ግን ምንጭና የውኃ ማጠራቀምያ ጉድጓድ ንጹሕ ይሆናሉ፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ይሆናል። ከበድናቸውም በሚዘራ በማናቸውም ዓይነት ዘር ላይ ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ ነው። ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስበትና ከላዩም በድናቸው ቢወድቅበት፥ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። “ለምግብነት ከምታውሉት እንስሳ የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንዲሁም በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። “በምድርም ላይ የሚርመሰመስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ጸያፍ ነው፥ አይበላም። በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሄድ ወይም ብዙ እግሮች ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚርመሰመሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ጸያፍ ናቸውና አትብሉአቸው። በሚርመሰመሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የገዛ አካላችሁን አታጸይፉ፤ እንዳትረክሱም የገዛ አካላችሁን በእነርሱ አታርክሱ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና፤ ስለዚህ ራሳችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በደረታቸው እየተሳቡ በሚርመሰመሱ ሁሉ የገዛ አካላችሁን አታርክሱ። እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ ጌታ ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።” የእንስሳና የወፍ፥ በውኃም ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። በዚህም በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ በሚበላና በማይበላ ሕይወት ባለው ፍጥረት መካከል ለመለየት ነው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ሴት ፀንሳ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያኽል የረከሰች ትሆናለች፤ እንደ ወር አበባዋም ጊዜያት ትረክሳለች። በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ። ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር ሁሉ አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ። ነገር ግን ሴት ልጅ ብትወልድ እንደ ወር አበባዋ ጊዜያት ሁለት ሳምንት ያኽል የረከሰች ትሆናለች፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስልሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ። “የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣ። እርሱም በጌታ ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላታልም፤ ከሚፈስሰውም ደምዋ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው። ጠቦት ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባታገኝ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ትውሰድ፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታድርገው፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርሷም ትነጻለች።” ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ማናቸውም ሰው በሰውነቱ ቆዳ ላይ እባጭ ወይም ብጉር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሰውነቱ ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ቢሆን፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሰውነቱ ቆዳ ላይ ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ከሰውነቱ ቆዳ በታች ዘልቆ ቢታይ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ፦ ርኩስ ነው ይበለው። ነገር ግን ቋቁቻው በሰውነቱ ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ በእርሱም ላይ ያለው ጠጉር ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መገታቱን ቢያይ፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ አሁንም ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ዳግም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው። ማናቸውም ሰው በለምጽ ደዌ ቢጠቃ እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡታል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢኖር፥ በእርሱም ላይ ያለውን ጠጉር ለውጦት ቢያነጣው፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የቈየ የለምጽ ደዌ ነው፥ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይለየውም። ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ካህኑ ማየት እስከሚችልበት አካል የለምጹ ደዌ የታመመውን ሰው ቆዳ ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢሸፍነው፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ሰውነቱን ሁሉ ቢሸፍነው የታመመውን ሰው፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሰውነቱ ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ የለምጽ ደዌ ነውና ርኩስ ነው። የሚያዠው ሥጋ ግን ተለውጦ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው። በሰውነቱም ቆዳ ላይ የዳነ የብጉንጅ ቁስል ቢኖር፥ በብጉንጁም የቁስል ስፍራ ላይ ነጭ እባጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከብጉንጁ ቁስል ውስጥ ወጥቶአል። ካህኑም ቢያየው፥ እነሆም፥ በእርሱ ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖርበት፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የብጉንጅ ቁስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። “በሰውነቱም ቆዳ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣበት፥ ካህኑ ያየዋል፥ እነሆም፥ በቋቁቻው ላይ ያለው ጠጉር ተለውጦ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ነገር ግን ካህኑ ቢያየው፥ በቋቁቻውም ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖር፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የቃጠሎው እባጭ ነው፤ የቃጠሎውም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ደዌ ቢኖርባቸው፥ ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳው በታች ዘልቆ ቢታይ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጉር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ የለምጽ ደዌ ነው። ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ጥቁርም ጠጉር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጉር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ከቆዳው በታች ባይዘልቅ፥ ይላጫል፥ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ አሁንም ካህኑ ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጉር አይፈልግም፤ እርሱ ርኩስ ነው። ቈረቈሩ ግን መገታቱን ቢያይ፥ ጥቁርም ጠጉር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ድኖአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።” “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርባቸው፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ እርሱ ንጹሕ ነው። “የሰውም ጠጉር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ጠጉሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ዳሩ ግን በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ የለምጽ ደዌ ነው። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የሆነ የለምጽ ደዌ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ላይ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቢሆን፥ በለምጽ ደዌ የተያዘ ሰው ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ላይ የሚገኝ ነው። “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው የሚለብሳቸው ልብሶች የተቀደዱ ይሁኑ፥ የራሱም ጠጉር የተጐሳቈለ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ እያለ ይጩኽ። በእርሱ ደዌው እስካለበት ጊዜያት ድረስ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጪ ይሆናል። “የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢወጣ፥ ልብሱም የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ቢሆን፥ በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጉር ቢሆን፥ በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ቢሆን፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢይታ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ እዲያየው ይደረጋል። ካህኑም ደዌውን ያያል፤ ደዌውም ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል የተለፋ ቆዳ ላይ ቢሰፋ፥ ደዌው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱም ርኩስ ነው። ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ወይም ከተለፋው ቆዳ የሆነ ማናቸውም ደዌው ያለበት ነገር ላይ ቢሆን፥ እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነውና በእሳት ይቃጠል። “ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለበን ነገር እንዲያጥቡ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። ደዌው ያለበት ነገር ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ባይሰፋ ነገር ግን መልኩን ባይለውጥ፥ እርሱ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ የለምጽ ደዌው ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው። “ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢከስም፥ ምልክቱ የነበረበትን ቦታ ከልብሱ ወይም ከተለፋው ቆዳ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ዳግም ቢታይ፥ እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር በእሳት ታቃጥለዋለህ። ነገር ግን አንተ ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ ከተሠራ ከማናቸውም ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። “ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለመወሰን እንዲቻል፥ በበግ ጠጉር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ የሚወጣ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “በመንጻቱ ቀን የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ለምጽ ካለበት ሰው ላይ ቢጠፋ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሐን ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም እንዲመጣለት ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ እንዲታረድ ያዝዛል። በሕይወት ያለውን ወፍ፥ የዝግባውንም እንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ ይነክራቸዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው የወፍ ደም ውስጥ ይዘፍቀዋል። ከለምጽ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ከዚያም ንጹሕ ነህ ይለዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በተንጣለለው ሜዳ ላይ እንዲበር ይለቀዋል። የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጉሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። በሰባተኛውም ቀን ጠጉሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጉር ሁሉ ይላጫል፤ ከዚያም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። “በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ለእህሉም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ዘይትም ያለበትን አንድ የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል። የሚያነጻውም ካህን የሚነጻውን ሰውና እነዚህን ነገሮች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በጌታ ፊት ያኖራቸዋል። ካህኑም አንዱን ተባት ጠቦት ይወስዳል፤ እርሱንም ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ጎን ለጎንም ዘይቱ ያለበትን የሎግ መስፈሪያውን፤ እነርሱንም ስለ መወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል። የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርድበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ እንደ ኃጢአት መሥዋዕቱም እንዲሁ የበደል መሥዋዕቱ ለካህኑ ይሆናል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ይወስዳል፤ እርሱም የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። ካህኑም ከሎግ መስፈሪያው ውስጥ ያለውን ዘይት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሰዋል። ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ነክሮ ከዘይቱ በጌታ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ከተረፈው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት በሆነው ደም ላይ ያስነካዋል። ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ከዚያም ካህኑ በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል። ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኩሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፤ እንዲህም አድርጎ ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። “ነገር ግን ድሀ ቢሆን ይህንንም ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባይኖረው፥ እንዲያስተሰርይለት ለበደል መሥዋዕት እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት፥ ለእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያደርገዋል። በስምንተኛውም ቀን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ስለ መንጻቱ እንዲሆኑ ወደ ካህኑ ያመጣቸዋል። ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦትና ዘይትም ያለበትን የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል። የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሳል። ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በጌታ ፊት ይረጨዋል። ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት ደም ባረፈበት ስፍራ ላይ ያስነካዋል። በጌታ ፊት እንዲያስተሰርይለት ካህኑ በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል። ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል፤ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቁርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል። “ለመንጻቱ የሚቀርበውን ነገር መግዛት አቅሙ ለማይፈቅድለት የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕጉ ይህ ነው።” ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ በምትወርሱአት ምድር በአንድ ቤት ውስጥ የለምጽ ደዌ ባኖር፥ የቤቱ ባለቤት መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ የሚመስል ነገር በቤቴ ውስጥ ያለ ይመስለኛል’ ብሎ ይንገረው። ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ከግድግዳው ውጫዊ ገጽታ ዘልቆ ቢገባ፥ ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። የቤቱንም ውስጥ ዙሪያውን ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮችን አምጥተው ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። “ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው። ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በቤቱም ውስጥ የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም ውስጥ የሚበላ ልብሱን ያጥባል። “ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ጠፋ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርዳል። የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ቤቱንም በወፉ ደም፥ በምንጩም ውኃ፥ ሕይወትም ባለው ወፍ፥ በዝግባውም እንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። በሕይወትም ያለውን ወፍ ከከተማ ወጥቶ ወደ ተንጣለለው ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።” “ይህ ሕግ ለሁሉም ዓይነት የለምጽ ደዌ፥ ለቈረቈርም፥ በልብስ ላይና በቤት ውስጥ ላለ የለምጽ ደዌ፥ ለእባጭም፥ ለብጉርም፥ ለቋቁቻም የሚሆን ነው። እንዲሁም አንድ ነገር በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ ለማልከት የሚያስችል ነው። ይህ የለምጽ ደዌ ሕግ ነው።” ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩ፦ ማንም ሰው ከሰውነቱ ውስጥ ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ከእርሱ የሚወጣው ፈሳሽ ርኩስ ነው። ከእርሱ የሚፈስሰው ነገር ርኩስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሰውነቱ ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ለእርሱ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል። መኝታውንም የሚነካ ማንም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት በማናቸውም ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበትን ሰው ገላውን የሚነካ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ የተተፋበት ሰው ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። እርሱም ከተቀመጠበት በታች ያለውን ማናቸውንም ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን የሚያነሣ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ ማንንም ሰው ቢነካ፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይሰብሩታል፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠባል። “ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ፥ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል። ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባቸዋል፤ ካህኑም በጌታ ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል። “ማንም ሰው ዘሩ ከእርሱ ብልት ቢፈስስ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ዘሩ የነካው ልብስ ሁሉ ቆዳም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ወንዱ ከሴቲቱ ጋር ተኝቶ ዘሩን ቢያፈስስ፥ ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ይሆናሉ። “ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት ከሰውነቷም ውስጥ የሚፈስሰው ነገር ደም ቢሆን፥ በወር አበባዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በወር አበባዋ ጊዜ የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል። መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። በመኝታም ወይም በማናቸውም ነገር ላይ ብትቀመጥ፥ እርሱ በሚነካው ጊዜ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ማንም ሰው ከእርሷ ጋር ተኝቶ የወር አበባዋ ቢነካው፥ እርሱ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። “አንዲትም ሴት ከወር አበባዋ ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከወር አበባዋ ጊዜያት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ ፈሳሹ ነገር በሚፈስስበት ቀን ሁሉ በርኩስነትዋ ትቀጥላለች፤ በወር አበባዋ ጊዜያት እንደ ሆነች እንዲሁ እርሷ ርኩስ ትሆናለች። ፈሳሹም ነገር በሚፈስስበት ጊዜያት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በወር አበባዋ ጊዜ እንደነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ እንደ ወር አበባዋ ርኩስነት ርኩስ ይሆናል። እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች፥ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታመጣቸዋለች። ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ስለ ፈሳሽዋም ርኩስነት ካህኑ በጌታ ፊት ያስተሰርይላታል። “እንዲሁም በመካከላቸው የምትገኘውን የመገናኛዬን ድንኳን በማርከስ በርኩስነታቸው እንዳይሞቱ፥ እናንተ የእስራኤልን ልጆች ከርኩስነታቸው ለዩአቸው።” ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ዘሩም ለሚፈስስበት በእርሱም ምክንያት ለሚረክሰው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ እንዲሁም በወር አበባዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይህ ነው። በጌታ ፊት በቀረቡ ጊዜ የሞቱት ሁለቱ የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ ጌታ ሙሴን ተናገረው፤ ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና፥ እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደተቀደሰው ስፍራ፥ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። ነገር ግን አሮን ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰ ስፍራ ይግባ። የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፥ የበፍታውም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፥ በመርገፍም የተጌጠውን የበፍታው መታጠቂያ ይታጠቅ፥ የበፍታውንም መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው። ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። “አሮንም ለእርሱ የሆነውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፥ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል። ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በጌታ ፊት ያቆማቸዋል። አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፥ አንዱ ዕጣ ለጌታ ሌላው ዕጣ ለዐዛዜል ይሆናል። አሮንም ለጌታ ይሆን ዘንድ ዕጣው የወደቀበትን ፍየል ያቀርባል፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል። ለዐዛዜል ይሆን ዘንድ ዕጣው የወደቀበትን ፍየል እንዲያስተሰርይበት፥ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ለመልቀቅ በሕይወቱ እንዳለ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል። “አሮንም ለእርሱ የሆነውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል፤ ለእርሱ የሆነውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያርዳል። በጌታም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ ያለውን የእሳት ፍም በጥናው ሞልቶ ያመጣል፥ ከተወቀጠውም ከመዐዛው ያማረ ዕጣን በሁለቱ የእጁ መዳፎች ሙሉ ዘግኖ ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን የስርየት መክደኛ እንዲሸፍን በጌታ ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በምሥራቅ በኩል በጣቱ ይረጨዋል፤ እንዲሁም ከደሙ በስርየቱ መክደኛ ፊት ለፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። “ለሕዝቡም የሆነውን የኃጢአት መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ እንዲሁ በፍየሉ ደም ላይ ያደርጋል፤ በስርየቱ መክደኛም ላይና በስርየቱ መክደኛም ፊት ለፈት ይረጨዋል። ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት፥ ከመተላለፋቸውም፥ ከኃጢአታቸውም ሁሉ የተነሣ ለተቀደሰው ስፍራ ያስተሰርይለታል፤ በርኩስነታቸውም መካከል ከእነርሱ ጋር ላለው ለመገናኛው ድንኳን እንዲሁ ያደርጋል። አሮንም ለማስተስረይ ወደተቀደሰው ስፍራ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪ ወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም ሰው አይገኝ። ከዚያም በኋላ በጌታ ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያው ይወጣል፤ ለእርሱም ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰዋልም። “የተቀደሰውንም ስፍራ፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ በሕይወት ያለውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፥ መተላለፋቸውንም ሁሉ፥ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ያደርገዋል። ፍየሉም በደላቸውን ሁሉ በረሀ ወደ ሆነ ስፍራ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ እንዲሄድ ይለቅቀዋል። “አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ ተቀደሰውም ስፍራ በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤ በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ይለብሳል፤ ወጥቶም ለእርሱ የሆነውን የሚቃጠል መሥዋዕት እና ለሕዝቡ የሆነውን የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል። የኃጢአቱንም መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ወደ ዐዛዜል የሄደውን ፍየል የወሰደው ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደተቀደሰው ስፍራ የገባውን፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መሥዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቆዳቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል። “ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አዋርዱ፥ የአገሩም ተወላጅ ሆነ በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ ለእናንተ በዚህ ቀን እንድትነጹ ማስተስረያ ይደረግላችኋልና፤ በጌታም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። ለእናንተም ፈጽሞ የምታርፉበት ታላቅ ሰንበት ይሆናል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። በአባቱም ፈንታ ካህን ሆኖ ለማገልገል ተለይቶ የሚቀባው ካህን የተቀደሰውን የበፍታ ልብስ ለብሶ ያስተስርያል። ለቅድስተ ቅዱሳንም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ለማስተሰረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆንላችኋል።” ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ከእስራኤል ቤት ማናችውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል በሰፈሩ ውስጥ ቢያርድ፥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ በጌታ ማደሪያ ፊት ለፊት ለጌታ እንደ ቁርባን አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። በዚህም የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን እንዲያመጡ፥ ወደ ጌታ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ አምጥተዋቸው የአንድነት መሥዋዕት አድርገው ለጌታ እነርሱን እንዲያርዱ ለማድረግ ነው። ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በጌታ መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል። ስለዚህ ተከትለዋቸው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት ከእንግዲህ ወዲህ መሥዋዕታቸውን አይሠዉም። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሥርዓት ይሁን። “ለእነርሱም እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ ለጌታ ሊሠዋው ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። “ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቊርበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ እንዲሆን እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ አልሁ፦ ከእናንተ ማንም ሰው ደምን አይብላ፥ በመካከላችሁም ከሚኖር እንግዳ ማንም ሰው ደምን አይብላ። እንዲሁም ከእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይሸፍነዋል። “ሥጋን የለበሰ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ሕይወቱ ደሙ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ አልሁ፦ ሥጋን የለበሰ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ሕይወቱ ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ። የሞተውን ወይም አውሬ የገደለውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገሩ ተወላጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። ነገር ግን ልብሱን ባያጥብ፥ ገላውንም ባይታጠብ ኃጢአቱን ይሸከማል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። በተቀመጣችሁባት በግብጽ ምድር እንደሚያደርጉት እናንተም እንዲሁ አታድርጉ፤ እኔም ወደማመጣችሁ ስፍራ ወደ ሆነው በከነዓን ምድር ላይ እንደሚያደርጉት እናንተም እንዲሁ አታድርጉ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ። ፍርዴን ፈጽሙ፥ ሥርዓቴንም ጠብቁ፥ በእነርሱም ተመላለሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። ስለዚህ ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፥ እነርሱን የሚያደርግ ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ለመግለጥ ወደ ሥጋ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ ጌታ ነኝ። የአባትህ ኃፍረተ ሥጋ ነውና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በአገር ቤት ወይም በውጭ አገር የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ፤ የእነርሱ ኃፍረተ ሥጋ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና። እርሷ እኅትህ ነችና ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት። የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናትና። የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት፤ የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። የሴትንና የሴት ልጇን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጇን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጇን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ እርሷን አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው። እኅትዋ በሕይወት እስካለች ድረስ ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ የእርሷን እኅት እንደ ሁለተኛ ሚስት አድርገህ አታግባ። “እርሷም ርኩስ በሆነችበት የወር አበባዋ ጊዜያት ላይ ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ ወደ ሴት አትቅረብ። በእርሷም ራስህን እንዳታረክስ ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ። ከልጆችህ ማናቸውንም ለሞሌክ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ አትስጥ፥ በዚህም የአምላክህን ስም አታርክስ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነው። በእርሱም ራስህን እንዳታረክስ ከማናቸውም እንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ለመተኛት በእንስሳ ፊት አትቁም፤ ጸያፍ የሆነ ተግባር ነው። “በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ስለ በደልዋ እቀጣታለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ትተፋቸዋለች። ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩም ተወላጅ በእናንተም መካከል የሚኖር እንግዳ ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ማናቸውንም ነገር አታድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩ የምድሪቱ ሰዎች ይህን ርኩሰት ሁሉ አድርገዋልና፥ ስለዚህ ምድሪቱ ረክሳለች፤ ያለዚያ ግን ምድሪቱን ካረከሳችሁ እርሷ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ አንቅራ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች። በእርግጥ ማንም ሰው ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ነገሮች ማናቸውንም ነገር ቢያደርግ፥ ያደረጋችው ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። ስለዚህ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ላይ የተደረገውን ጸያፍ ወግ ሁሉ ፈጽሞ እንዳታደርጉ፥ በእርሱም ራሳችሁን ፈጽሞ እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። ከእናንተ እያንዳንዱ ሰው እናቱንና አባቱን ያክብር፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፥ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ለራሳችሁም ይሆኑ ዘንድ ቀልጠው የተበጁትን የአማልክት ምስሎች አትሥሩ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “የአንድነትንም መሥዋዕት ለጌታ ስትሰዉ እንዲሠምርላችሁ አድርጋችሁ ሠዉት። መሥዋዕታችሁን በሠዋችሁበት ዕለትና በማግስቱ ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ማናቸውም ነገር ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል። በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ እርሱም ተቀበባይነት አይኖረውም፤ እርሱንም የሚበላ ማናቸውም ሰው ለጌታ የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና በደሉን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጠፋል። “የምድራችሁንም መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ እስከ እርሻችሁ ድንበር ድረስ ፈጽማችሁ አትሰብስቡ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሀውና ለእንግዳው ተወው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም ማንም ሰው ወንድሙን አያታልል። በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። ተቀጥሮ የሚያገለግለውን ሰው ደመወዙን እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አታቆይበት። መስማት የተሳነውን አትስደብ፥ በዓይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ፍርድን ፈጽሞ አታጓድሉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ። በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት ወድያና ወዲህ አትመላለስ፤ በባልንጀራህም ሕይወት ላይ መሰነናክል ሆነህ አትቁም፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ በጽኑ ገሥጸው። አትበቀል፥ በሕዝብህም ልጆች ላይ ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህን ከሌላ ዓይነት ዘር ጋር አታዳቅል፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።” “ማናቸውም ሰው በባርነት ሥር ካለች ሴት ጋር ቢተኛ፥ እርሷም ለሌላ ሰው ታጭታ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ያልተዋጀች ወይም አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ይህ አድራጎት ቅጣት ይረኖረዋል፤ ሆኖም አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ ጌታ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በጌታ ፊት የበደል መሥዋዕት በሆነው በግ ለእርሱ ያስተሰርይለታል፥ የሠራውም ኃጢአት ይቅር ይባላል። “ወደ ምድሪቱም ገብታችሁ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት ለእናንተ እንዳልተገረዘ ይሆናል፤ አይበላም። የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለጌታ ምስጋና የተለየ ይሆናል። የተትረፈረፈም ፍሬ አብዝተው እንዲሰጡዋችሁ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “ከደሙ ጋር ምንም ዓይነት ነገር አትብሉ፤ ሞራ ገላጭም አትሁኑ፥ አስማትም አታድርጉ። የራስ ጠጉራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቁረጡት። ስለ ሞተውም ብላችሁ ሥጋችሁን አትተልትሉ፥ ገላችሁንም ፈጽሞ አትንቀሱት፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ምድሪቱ እንዳታመነዝር በበርኩስነትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን እንድታመነዝር አድርገሃት አታርክሳት። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ ለመቅደሴም ክብርን ስጡ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ወደ ሙታን መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ አትፈልጉአቸው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “በአዛውንት ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብጽ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገሩ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፥ እርሱንም እንደራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱት፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም አታታልሉ። ትክክለኛም ሚዛን፥ ትክክለኛም መመዘኛ፥ ትክክለኛም የኢፍ መስፈሪያ፥ ትክክለኛም የኢን መስፈሪያ ይኑሩአችሁ፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉአቸውም፤ እኔ ጌታ ነኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ደግሞ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ልጆች ወይም በእስራኤል ዘንድ ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው ልጁን ለሞሌክ ቢሰጥ ፈጽሞ ይገደል፤ የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። መቅደሴን ለማርከስ፥ የተቀደሰውንም ስሜን ለማንቋሸሽ ልጁን ለሞሌክ ሰጥቶአልና እኔ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቊርበታለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። ነገር ግን ልጁን ለሞሌክ ሲሰጥ፥ የአገሩ ሕዝብ አይቶ ያንን ሰው ፈጽሞ ቸል ቢለው ባይገድሉትም፥ እኔ በዚያ ሰውና በቤተሰቡ ላይ ፊቴን አጠቊርበታለሁ፤ እርሱንም፥ ከሞሌክም ጋር ለማመንዘር የሚከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋለሁ። “የሙታን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም በሚከተል፥ በሥራቸውም በሚያመነዝር፥ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቊራለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና፤ ስለዚህ ራሳችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ። ሥርዓቶቼን ጠብቁ፥ አድርጉአቸውም፤ እኔ የምቀድሳችሁ ጌታ ነኝ። ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና፥ ደሙ በራሱ ላይ ነው። “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ። ማናቸውም ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ የአባቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። ማናቸውም ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ደማቸውም በራሳቸው ላይ ነው። ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። ማናቸውም ሰው እናቲቱንና ልጂቱን ቢያገባ ዝሙት ነው፤ በመካከላችሁ አመንዝራ እንዳይኖር እርሱና እነርሱ በእሳት ይቃጠሉ። ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳይቱንም ግደሉአት። አንዲት ሴት ወደ ማናቸውም እንስሳ ብትቀርብ፥ ከእርሱም ጋር ብትገናኝ፥ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። “ማናቸውም ሰው የአባቱን ልጅ ወይም የእናቱን ልጅ እኅቱን ቢያገባ፥ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢያይ፥ ኃፍረተ ሥጋውንም ብታይ፥ ይህ አሳፋሪ ነገር ነው፤ ከሕዝባቸውም ልጆች ፊት ተለይተው ይጥፉ፤ የእኅቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአልና በደሉን ይሸከማል። ማናቸውም ሰው የወር አበባ ካለባት ሴት ጋር ቢተኛ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢገልጥ፥ ፈሳሽዋን ገልጦአልና፥ እርሷም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። የአባትህን ወይም የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ይህን የሚያደርግ የዘመዱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ በደላቸውን ይሸከማሉ። ሰውም ከአጎቱ ሚስት ጋር ቢተኛ፥ የአጎቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ያለ ልጅ ይሞታሉ። ሰውም የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ርኩሰት ነው፤ የወንድሙን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአልና፥ እነርሱ ልጅ አልባ ይሆናሉ። “ስለዚህ እንድትቀመጡባት ወደማመጣችሁ ስፍራ ምድሪቱ አንቅራ እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፥ አድርጉትም። እኔ ከፊታችሁ በማሳድደው ሕዝብ በሆነው ወግ አትሂዱ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አድርገዋልና ተጸየፍኋቸው። ነገር ግን እኔ እንዲህ አልኋችሁ፦ ‘ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ እንድትወርሱአትም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ።’ እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። ስለዚህ ንጹሑን እንስሳ ከርኩሱ፥ ንጹሑንም ወፍ ርኩስ ከሆነው ትለያላችሁ፤ ለእናንተ ርኩሶች ናቸው ብዬ በለየኋቸው በእንስሳና በወፍ በምድርም ላይ በሚርመሰመሱ ነፍሳት ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ። እኔ ጌታ ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም እንድትሆኑ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ሁኑ። “ወንድ ወይም ሴት የሙታን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጸመው ይገደሉ፤ በድንጋይ ይውገሩአቸው፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማንም ሰው ከሕዝቡ መካከል ስለ ሞተው ራሱን አያርክስ፤ ነገር ግን የቅርብ ዘመዱ ስለሆኑት ስለ እናቱ፥ ወይም ስለ አባቱ፥ ወይም ስለ ወንድ ልጁ፥ ወይም ስለ ሴት ልጁ፥ ወይም ስለ ወንድሙ፥ ወይም በእርሱ ዘንድ በቅርብ ስላለችው ያላገባች ድንግል እኅቱ ስለ እርሷ ራሱን ያርክስ። በሕዝቡ መካከል ያሚገኝ አለቃ የረከሰ እዳይሆን ራሱን አያርክስ። ካህናት አናታቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ገላቸውንም በመቁረጥ አይተልትሉ። ለአምላካቸው የተቀደሱ ይሆናሉ፥ የአምላካቸውንም ስም አያረክሱም፤ እነርሱም የአምላካቸው እንጀራ የሆነውን፥ ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ያቀርባሉና የተቀደሱ ይሆናሉ። ካህኑ ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና አመንዝራይቱን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም በባልዋ የተፈታችውን አያግባ። የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ ጌታ ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሆንልሃል። የካህንም ልጅ ራስዋን በዝሙት ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል። “በራሱም ላይ የቅባዓት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ እንዲለብስ የተቀደሰው፥ ከወንድሞቹ ይበልጥ ከፍ ያለው ካህን የራሱን ጠጉር አያጐስቁል ልብሱንም አይቅደድ። በድንም ወደ አለበት ስፍራ ሁሉ አይሂድ፥ ስለ አባቱም ወይም ስለ እናቱ አይርከስ። የሚቀድስውም የአምላኩ የቅባዓት ዘይት በእርሱ ላይ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ ጌታ ነኝ። እርሱም ድንግል የሆነችውን ሴት ያግባ። ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፈታችውን፥ ወይም የረከሰችውን፥ ወይም አመንዝራይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡም መካከል ከወገኑ ድንግሊቱን ያግባ። ስለዚህ በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያርክስ፤ እኔ የምቀድሰው ጌታ ነኝና።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮን እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ለማቅረብ አይቅረብ። ዓይነ ስውር፥ ወይም የሚያነክስ፥ ወይም የፊቱ ቅርጽ የተበላሸ፥ ወይም ትርፍ አካል ያለው፥ ወይም እግሩ የተሰበረ፥ ወይም እጁ የተሰበረ፥ ወይም ከወገቡ የጐበጠ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም የማየት ችግር ያለበት፥ ወይም የእከክ ደዌ ያለበት፥ ወይም ቋቁቻ የወጣበት፥ ወይም የብልቱ ፍሬ የፈረጠ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ማናቸውም ሰው ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ለማቅረብ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነውና የአምላኩን እንጀራ ለማቅረብ አይቅረብ። እጅግ ቅዱስ የሆነውን እና የተቀደሰውን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤ ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ ጌታ ነኝና።” ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ተናገረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ ለአሮንና ለልጆቹ ተናገር፤ እኔ ጌታ ነኝ። እንዲህ በላቸው፦ ‘በትውልዳችሁ ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ ሁሉ ርኩሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለጌታ ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱሳን ነገሮች ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ከአሮን ዘር ማናቸውም ሰው የለምጽ ደዌ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት፥ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሱት ነገሮች አይብላ። በበድን፥ ወይም ዘሩ በሚፈስስበት ሰው የረከሰውን ነገር የሚነካ፥ ወይም የሚያረክሰውን ማናቸውንም የሚርመሰመስ ፍጥረት፥ ወይም ርኩሰቱ ማናቸውም ዓይነት ሆኖ የሚያረክሰውን ሰው የሚነካ፥ እንዲህ ያሉትን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ። ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ነገር ይበላል። በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የገደለውን አይብላ፤ እኔ ጌታ ነኝ።’ ባረክሱት ጊዜ እንዳይሞቱ ስለ እርሱም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ትዛዝን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ ጌታ ነኝ። “ማናቸውም ምእመን ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ የሆነ እና ተቀጥሮ የሚያገለግል ከተቀደሰው አይብላ። ካህኑ ግን ባርያ በገንዘቡ ቢገዛ እርሱ ይብላ፤ በቤቱም የተወለዱት ለእርሱ ከሆነው እንጀራ ይብሉ። የካህንም ልጅ ምእመንን ብታገባ፥ እርሷ ከተቀደሰው ቁርባን አትብላ። የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ማናቸውም ምእመን ግን ከእርሱ አይብላ። ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ነገር ቢበላ በፊት በነበረው ላይ አምስት እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ነገር ለካህኑ ይስጥ። ካህናቱ የእስራኤል ልጆች ለጌታ የሚያቀርቡትን የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ፤ ከዚህም የተነሣ የምቀድሳቸው እኔ ጌታ ነኝና የእነርሱን የተቀደሰ ነገር በሚበሉበት ጊዜ ኃጢአትንና በደልን እንዳይሸከሙ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጥ እንግዳ ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ ለጌታም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በፈቃዱ የሚያቀርበውን ቁርባን ሁሉ ቢያቀርብ፥ እንዲሠምርላችሁ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ። ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ማናቸውም ነውር ያለበትን አታቅርቡ። ማናቸውም ሰው ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የአንድነትን መሥዋዕት ለጌታ ቢያቀርብ፥ እንዲሠምርለት ፍጹም የሆነ ይሁን፥ በእርሱም ነውር የሆነ ነገር አይኑርበት። ዓይነ ስውር ወይም የተሰበረ ወይም አካለ ጎዶሎ ወይም የሚመግል ቁስል ወይም የእከክ ደዌ ያለበት ወይም ቋቁቻ የወጣበት ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለጌታ አታቅርቡ፤ እነርሱንም በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጋችሁ በመሠዊያው ላይ ለጌታ አትሠዉ። የበሬው ወይም የበጉ የአካሉ ክፍል ረጅም ወይም አጭር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም። የብልቱ ፍሬ የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለጌታ አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ። ከእንግዳም ሰው እጅ የተገኙ እንደነዚህ ያሉ እንስሶችን ሁሉ ለአምላካችሁ እንጀራ እንዲሆኑ አታቅርቡ፤ ርኩሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ሆኖ ቢቀርብ የሠመረ ይሆናል። ላም ወይም በግ ብትሆን እርሷንና ልጇን በአንድ ቀን አትረዱ። የምስጋናንም መሥዋዕት ለጌታ ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ አድርጋችሁ ሠዉት። በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ስለዚህ ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉአቸውም፤ እኔ ጌታ ነኝ። እኔም በእስራኤል ልጆች መካከል እንድቀደስ የተቀደሰውን ስሜን አታርክሱ፤ የምቀድሳችሁ እኔ ጌታ ነኝ። እኔም አምላክ እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ ነኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የጌታ በዓላት፥ እነዚህ ናቸው። “ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይደረግበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለጌታ ሰንበት ነው። “እነዚህ የጌታ በዓላት፥ ለእነርሱ በተወሰነላቸው ጊዜ የምታውጁአቸው፥ የተቀደሱ ጉባኤዎች ናቸው። በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የጌታ ፋሲካ ነው። በዚህም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን ለጌታ የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን እርሾ ያልነካው የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ሰባት ቀንም ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከሩን ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ እርሱም ነዶውን በጌታ ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ ካህኑ የሚወዘውዘው በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ነው። ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ አቅርቡ። የእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ይሁን፤ ለመጠጥም ቁርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የሆነ የወይን ጠጅ ይቅረብ። የአምላካችሁን ቁርባን እስከምታመጡበት እስከዚህ ቀን ድረስ እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። “ለመወዝወዝ ቁርባን ነዶውን ካመጣችሁበት ቀን ከሰንበት በኋላ በማግስቱ ያሉትን ቀኖች ቁጠሩ። እነርሱም ሰባት ሙሉ ሳምንታት ይሁኑ። እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ ኀምሳ ቀን ቁጠሩ። ከዚያም አዲሱን የእህል ቁርባን ለጌታ አቅርቡ። ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ። ለጌታ ለበኵራት ቁርባን እንዲሆን በእርሾ ተቦክቶ ይጋገራል። ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ተባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ሆኖ ከእህል ቁርባናቸውና ከመጠጥ ቁርባናቸው ጋር ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ። እንዲሁም አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለአንድነት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ከበኩራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዛቸዋል። ለካህኑ ለጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። በዚያም ቀን ታውጃላችሁ፤ የተቀደሰ ጉባኤም ታደርጋላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። “የምድራችሁንም መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ እስከ እርሻችሁ ድንበር ድረስ ፈጽማችሁ አትሰብስቡ። የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሀውና ለእንግዳው ተዉት። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን ፈጽሞ የምታርፉበት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የምታውጁበት፥ የተቀደሰ ጉባኤ የምታደርጉበት ይሁንላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ። በአምላካችሁም በጌታ ፊት ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። በዚያም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያም ቀን ማናቸውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምሮ፥ ከማታ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለጌታ የዳስ በዓል ነው። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ሰባት ቀን ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። “የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቁርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቁርባን፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን፥ እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው ቀናቸው እንድታቀርቡባቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የጌታ በዓላት እነዚህ ናቸው። እነዚህም ከጌታ ሰንበታት ሌላ፥ ለጌታም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። “በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የምድሪቱን ምርት በሰበሰባችሁ ጊዜ የጌታን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በጌታ ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለጌታ አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ በእስራኤል ያሉት የአገሩ ተወላጆች ሁሉ በዳሶች ውስጥ ይቀመጣሉ፤ በዚህም ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳሶች ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” ሙሴም የጌታን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “መብራቱ ሁልጊዜ እንዲበራ ለመብራቱ ተወቅጦ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዝ። አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በጌታ ፊት ሁልጊዜ ያዘጋጀው፤ ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። በጌታ ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያዘጋጃል። “መልካሙንም ዱቄት ውሰድ፤ በእርሱም ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ይደረግበት። እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በጌታ ፊት በንጹሕ ወርቅ በተለበጠው ገበታ ላይ አኑራቸው። ለጌታም በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ተደርጎ፥ ለእንጀራው የመታሰቢያ ቁርባን እንዲሆን በሁለቱ ተርታ ላይ ንጹሕ የሆነ ዕጣን አድርግ። ስለ እስራኤል ልጆች የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን በጌታ ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያዘጋጀዋል። እርሱም ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ለጌታም በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ውስጥ በዘለዓለም ሥርዓት፥ ለእርሱ እጅግ ቅዱስ የሆነ ድርሻ ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።” አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ የእስራኤላዊቱም ልጅ የጌታን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። ጌታም ፍርዱን እስኪያሳውቃቸው ድረስ በእስር ቤት አኖሩት። ከዚያም ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተሳዳቢውን ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። የጌታንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገሩ ተወላጅ ቢሆን፥ የጌታን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። ማናቸውንም ሰው መትቶ የሚገድል ፈጽሞ ይገደል። እንስሳንም መትቶ የሚገድል ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይከፍላል። ሰውም ባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። በስብራት ፋንታ ስብራት፥ በዐይን ፋንታ ዐይን፥ በጥርስ ፋንታ ጥርስ ይሁን፤ በሰው ላይ ጉዳት ያደረገ ሰው እንዲሁ ይደረግበት። እንስሳንም የሚገድል በካሣ ይተካ፤ ሰውን ግን የሚገድል ይገደል። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ።” ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። ጌታም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለጌታ ሰንበት ታድርግ። ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፥ ስድስት ዓመትም የወይን ተክልህን ግረዝ ፍሬዋንም ሰብስብ። በሰባተኛው ዓመት ግን ለጌታ ሰንበት፥ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ይሁን፤ በእርሻህ ላይ አትዝራ፥ የወይን ተክልህንም አትግረዝ። በመከርህ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስብ፥ ያልተገረዘውን የወይንህን ተክል ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። የምድሪቱ ሰንበት ለእናንተ፥ ለአንተም፥ ለወንድ ባርያህም፥ ለሴት ባርያህም፥ ተቀጥሮ ለሚያገለግልህም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ትሰጣችኋለች። እንዲሁም ለእንስሶችህ፥ በምድርህም ላሉት አራዊት እርሷ የምትሰጠው ሁሉ ለመኖ ይሆናል። “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት አድርገህ በዓመታት ውስጥ ያሉትን ሰንበታት ቁጠር፤ የዓመታቱም የሰንበታት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆኑልሃል። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የቀንደ መለከትን ድምፅ ከፍ አድርገህ ታሰማለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ የቀንደ መለከትን ድምፅ ታሰማላችሁ። ኀምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእንናተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለሳል። ያ ኀምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ዓመት ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ እንዲሁም ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስቡ፥ ያልተገረዘውን የወይን ተክል ፍሬ አታከማቹ። ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ ምድሪቱ ራስዋ የምትሰጠውን ፍሬ ትበላላችሁ። “በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለሳል። ለባልንጀራህም መሬት ብትሸጥ፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ አንዱ ሌላውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። እርሱ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃልና ዓመታቱ ብዙ በሆኑ ቍጥር ዋጋውን ከፍ ታደርጋለህ፥ ዓመታቱ ግን ባነሱ ቍጥር ዋጋውን ታሳንሳለህ። እኔም ጌታ አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። “ሥርዓቶቼን አድርጉ፥ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርሷም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ዳሩ ግን እናንተ፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በእናንተ ላይ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ፤ የእርሷ ፍሬ እስከሚገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ። ምድሪቱም የእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድሪቱን ለዘለዓለም አትሽጧት። በርስት በያዛችሁት ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ ታደርጋላችሁ። “ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። የሚቤዠውም ሰው ባይኖረው፥ እርሱም ቢበለጥግ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ እርሱም እስከ ሸጠበት ጊዜ ያሉትን ዓመታት ያሰላል፥ ከዚያም የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልሳል፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል። ለማስመለስ ግን በቂ ገንዘብ ባያገኝ፥ ሽያጩ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ በገዛው ሰው እጅ ይሆናል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ ይወጣል፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል። “ማናቸውም ሰው ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት የመቤዠት መብት አለውና። አንድ ዓመትም እስከሚፈጸም ባለው ጊዜ ሁሉ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለው ቤት ለገዛው ሰው ለልጅ ልጁ ለዘለዓለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ ነፃ አይወጣም። ነገር ግን በዙሪያቸው ቅጥሮች በሌላቸው መንደሮች ያሉ ቤቶች እንደ እርሻ መሬቶች ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ነፃ ይወጣሉ። ነገር ግን ለሌዋውያን ርስታቸው በሆኑት በሌዋውያን ከተሞች ውስጥ ያሉትን ቤቶች ለዘለዓለም የመቤዠት መብት አላቸው። ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቤት ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል በሌዋውያን ከተሞች ያሉ ቤቶች ለሌዋውያን ርስቶቻቸው ናቸውና በርስታቸው ከተማ ውስጥ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል። በከተማቸውም ዙሪያ ያለው መሰማሪያ የዘለዓለም ርስታቸው ነውና አይሸጥም። “ወንድምህ ቢደኸይ፥ እርሱም በአንተ ዘንድ ራሱን መቻል ቢያቅተው፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር። ወንድምህ ከአንተ ጋር እንዲኖር ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። ብርህን በወለድ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት። የከነዓንን ምድር እንድሰጣችሁ፥ አምላክም እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “በአንተም ዘንድ ያለው ወንድምህ ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባርያ እንዲያገለግል አታድርገው። ይልቁንም እርሱ እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ እና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ። ከዚያም በኋላ እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ነፃ ይወጣል፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለሳል። ስለዚህ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸውና እንደ ባርያዎች አይሸጡ። በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። ወንድ ባርያና ሴት ባርያ እንዲኖራችሁ ብትፈልጉ ግን በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ መካከል ወንድና ሴት ባርያዎች ትገዛላችሁ። እንዲሁም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው ከእናንተ ጋር ካሉት ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ ባርያዎችን ትገዛላችሁ፤ ርስትም ይሆኑላችኋል። ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ለዘለዓለም እንዲወርሱአቸው ተዉአቸው፤ እነርሱን ባርያዎች ታደርጋላችሁ፥ ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ወንድሞቻችሁ ናቸውና አንዱ ሌላውን በጽኑ እጅ አይግዛው። “በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም በአንተ ዘንድ ለተቀመጠው እንግዳ ወይም ለመጻተኛው የቤተሰብ አባላት ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ የሥጋ ዘመዱ የሆነ ሰው ይቤዠው፤ ወይም እርሱ ቢበለጥግ ራሱን ይቤዥ። ከገዛውም ሰው ጋር ለገዢው ራሱን ከሸጠበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ያሰላል፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሆናል፤ ከባለቤቱም ጋር የነበረበት ጊዜ ተቀጣሪ አገልጋይ እንደ ነበረበት ጊዜ ተደርጎ ይተመናል። ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር በመሆን ያሰላል፤ እርሱ ማገልገል እንደሚገባው የዓመታት መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። በእርሱ ዘንድ በየዓመቱ እንደሚቀጠር አገልጋይ ይሁን እንጂ በአንተ ፊት በጽኑ እጅ አይግዛው። እርሱም በእነዚህ በማናቸውም መንገዶች ባይቤዥ፥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ነፃ ይወጣል። የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባርያዎች ናቸውና፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” “እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለራሳችሁ ይሆኑ ዘንድ ጣዖታትን አትሥሩ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ለእርሱም ለመስገድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ ለመቅደሴም ክብርን ስጡ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “በሥርዓቶቼ ብትመላለሱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉአቸውም፥ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም የተትረፈረፈ ምርትዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። ለእናተም እህሉን ማበራየቱ የወይኑን ዘለላ እስከሚቆረጥበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፥ የወይኑንም ዘለላ መቁረጥ እህል እስከ ሚዘራበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። በምድሪቱም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራራችሁ ያለ ስጋት ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በእናንተም ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም ዓሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በእናንተ ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። ወደ እናንተም ዘወር ብዬ በበጎ እመለከታችኋለሁ፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ለብዙም ጊዜ በጎተራ የተቀመጠውን ቀድሞ የነበረውን እህል ትበላላችሁ፤ ለአዲሱም ቦታ ለማስለቀቅ ቀድሞ በጎተራ የነበረውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። ባርያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁም እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።” ጌታም እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዓቴንም ባትቀበሉ፥ ነፍሳችሁም ፍርዴን በመጸየፉዋ ምክንያት ትእዛዛቴን ሳታደርጉ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፥ እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ነፍስን የሚያኮስስና ዓይንን የሚያፈዝዝ ክሳትና ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ይበሉታልና ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። ፊቴንም አጠቊርባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትሸነፋላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እነዚህም ነገሮች ተደርገውባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ ጨምሬ ዳግመኛ እቀጣችኋለሁ። የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጉልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም የተትረፈረፈውን ምርትዋን አትሰጥም፥ የምድሪቱም ዛፎች ፍሬያቸውን አይሰጡም። “እኔንም በመቃወም ብትሄዱ ልትሰሙኝም ባትፈልጉ፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ ቸነፈር እጨምርባችኋለሁ። በመካከላችሁም የዱር አራዊትን እለቅባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቁአችኋል፥ እንሰሶቻችሁንም ያጠፉባችኋል፥ እናንተንም ቁጥራችሁን ያመነምኑታል፤ መንገዶቻችሁም የተራቈቱ ይሆናሉ። “በእነዚህም ተቀጥታችሁ ወደ እኔ ባትመለሱ፥ ይልቁንም እኔን በመቃወም ብትሄዱ፥ እኔም ደግሞ እናንተን በመቃወም እሄዳለሁ፤ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። የቃል ኪዳኑንም በቀል የሚበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተሞቻችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ በመካከላችሁም ቸነፈርን እልክባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ። የእንጀራችሁንም በትር በሰበርሁ ጊዜ፥ ዐሥር ሴቶች እንጀራችሁን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው ዳግመኛ እንጀራችሁን ያመጡላችኋል፤ ትበላላችሁም ነገር ግን አትጠግቡም። “ይህም ተደርጎባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ እኔንም በመቃወም ብትሄዱ፥ እኔ ደግሞ በቁጣ እናንተን በመቃወም እሄዳለሁ፤ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። ከተሞቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትም። ምድሪቱንም የተራቈተች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባትም ጠላቶቻችሁ በእርሷ ላይ ይሣቀቃሉ። እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም ባድማ ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ይፈርሳሉ። “በዚያም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሁሉ ሰንበታትን በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበታትንም በማድረግዋ ትደሰታለች። እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ ያልነበራትን እረፈት ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሁሉ ይኖራታል። በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ መካከል በተረፉት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እልክባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታስደነብራቸዋለች፤ እነርሱም ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ። ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት የምትቆሙበት ኃይል አይኖራችሁም። በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። ከእናንተም መካከል የተረፉት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይመነምናሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ እንደ እነርሱ ይመነምናሉ። “ነገር ግን እኔን በመቃወም ሄደዋልና፥ በእኔ ላይ ፈጽሞ በከዳተኝነት ያደረጉትን በደላቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ይናዘዛሉ። እኔም ደግሞ እነርሱን በመቃወም እሄዳለሁ፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የበደላቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥ እኔም ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስታውሳለሁ፤ እንዲሁም ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትንም ቃል ኪዳኔን አስታውሳለሁ፤ ምድሪቱንም አስታውሳለሁ። ምድርሪቱም በእነርሱ ትተዋለች፤ ያለ እነርሱም ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሰንበታትን በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስላልተቀበሉ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የበደላቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። በዚህ ነገር ሁሉ ግን እኔ ጌታ አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ ፈጽሞ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። እኔ አምላክ እንድሆናቸው አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ከአባቶቻቸው ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስታውሳለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።” ጌታም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ የሰጣቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው። ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለጌታ ሊሰጥ ቢሳል፥ አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ተመጣጣኝ የሆነውን ዋጋ ይስጥ። ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስልሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምትህ ኀምሳ የብር ሰቅል ይሁን። ሴትም ብትሆን ግምትህ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምትህ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምትህ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትህ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። ዕድሜውም ስልሳ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ሰው ቢሆን ለወንድ ግምትህ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። ማናቸውም ሰው ለግምትህ ከድህነቱ የተነሣ የሚከፍለውን ቢያጣ እርሱም በካህኑ ፊት የስለቱን ሰው የምጣው፥ ካህኑም እርሱን ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው አቅሙ እንደሚፈቅደው መጠን ይገምትለት። “ለጌታም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለጌታ የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። መልካሙን በክፉ ወይም ክፉውን በመልካም ቢሆንም እንኳ እርሱን በሌላ አትተካ ወይንም አትለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው ለጌታ መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያምጣው። ካህኑም መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። እርሱም ሊቤዠው ቢወድድ ግን በተገመተው ላይ አምስት እጅ ይጨምር። “ለጌታም ቅዱስ ይሆን ዘንድ ሰው ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይጸናል። የቀደሰውም ሰው ቤቱን ሊቤዠው ቢወድድ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል። “ሰውም ከርስቱ እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ ግምትህ ለእርሻው እንደሚያስፈልገው የዘር መጠን ይሁን፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ ኀምሳ የብር ሰቅል ይገመታል። እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምትህ መጠን ይጸናል። ነገር ግን እርሻውን ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ቊጥር ገንዘቡን ያስላልህስ፤ ከዚያም ከግምትህ ላይ ይቀነሳል። እርሻውንም የቀደሰ ሰው ሊቤዠው ቢወድድ፥ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ከዚያም ለእርሱ ይጸናለታል። እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ሊቤዠው አይችልም። እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ነፃ ሲወጣ እንደ እርም ለጌታ የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ለካህኑ ርስቱ ይሆናል። ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ያሰላለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለጌታ ይሰጣል። በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደነበረው ወደሸጠው ሰው ይመለሳል። ግምትህም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል። “ዳሩ ግን ለጌታ የሆነውን የእንስሳ በኵራት ማንም ሰው ሊቀድሰው አይችልም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለጌታ ነው። የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምትህ መጠን ይቤዠዋል፤ በእርሱም ዋጋ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበታል፤ ባይቤዥም እንደ ግምትህ ይሸጣል። “ነገር ግን ሰው የእርሱ ከሆነው ነገር ሁሉ ለጌታ ለይቶ እርም ያደረገው፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለጌታ እጅግ የተቀደሰ ነው። ከሰዎችም እርም የሆነ ሰው ሁሉ አይዋጅም፤ ፈጽሞ ይገደላል። “የምድሪቱም አሥራት ሁሉ፥ ከምድሪቱ ዘር ወይም ከዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የጌታ ነው፤ ለጌታ የተቀደሰ ነው። ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ በእርሱ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበት። ከበሬም ሁሉ ከዐሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከዐሥር አንድ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል። መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዥም።” ጌታ በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው። ጌታም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እያንዳንዱን ወንድ አንድ በአንድ እንደየስማቸው ቍጥር የሕዝብ ቈጠራ አድርጉ። ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣውን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቁጠሩአቸው። ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ የሆነ ከእናንተ ጋር ይሁን። ከእናንተም ጋር ሆነው የሚረዱዋችሁ ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፥ ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥ ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥ ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥ ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ ከዮሴፍ ልጆች፥ ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፥ ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥ ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥ ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥ ከጋድ የደዑኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥ ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አሒራዕ።” ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል የወገኖቻቸው አውራዎች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ነበሩ። ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው ተጠርተው የነበሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤ በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰብሰቡአቸው፤ እነርሱም ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን አንድ በአንድ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ትውልዳቸውን መዘገቡ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው። “የእስራኤል በኩር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ አንድ በአንድ፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። “የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቍጥር፥ አንድ በአንድ የተቈጠሩት፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። “የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። “የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። “የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። “የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። “ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። “የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። “የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። “የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። “የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። “የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። “እነዚህ ተቈጥረው የነበሩ ናቸው፤ እነርሱን ሙሴና አሮን ከእስራኤል አለቆች፥ ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ቤቶች ይወክሉ ከነበሩ ጋር በመሆን ቈጠሩአቸው። ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ከእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። “ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የሌዊን ነገድ ብቻ አትቁጠረው፥ የሕዝብ ቈጠራ ስታደርግ እነርሱን ከእስራኤል ልጆች ጋር አትቁጠር፤ ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃው ሁሉ የእርሱም በሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን ሹማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ። ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሚተከል ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል። የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ። ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ።” የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። ጌታም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን ትይዩ በሁሉም አቅጣጫ ይስፈሩ። በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳን ሰፈር ዓላማ የያዙት ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ። “በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ኀምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ ኀምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ። “ከዚያም በኋላ በሰፈሮቹም መካከል የመገናኛው ድንኳን ከሌዋውያን ሰፈር ጋር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው እያንዳንዱ ሰው ስፍራቸውን ይዘው በየዓላሞቻቸው ይጓዛሉ። “በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ነበረ፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የብንያም ነገድ ነበረ፤ የብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ። “በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ነበረ፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ። ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ ኀምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ።” ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። ሌዋውያን ግን ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች እየሆኑ ተጓዙ። ጌታም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። እነዚህ የአሮን ልጆች ስሞች ናቸው፤ በኩሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። የአሮን ልጆች፥ እርሱም በክህነት አገልግሎት እንዲያገለግሉ የቀደሳቸው፥ የተቀቡ ካህናት ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው። ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በጌታ ፊት ያልተፈቀደውን እሳት ባቀረቡ ጊዜ በጌታ ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሌዊን ነገድ አምጥተህ አቅርብ እንዲያገለግሉትም በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለእርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ያለባቸውን ግዴታዎች ይፈጽሙ። የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቃሉ፥ ለእስራኤልንም ልጆች ያለባቸውን ግዴታ ይወጣሉ። ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለእርሱ ፈጽሞ የተሰጡ ናቸው። አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ማናቸውም ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኩሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ ሌዋውያንም የእኔ ናቸው፥ ምክንያቱም በኩር ሁሉ የእኔ ነውና፤ በግብጽ ምድር በኩርን ሁሉ በገደልሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኩርን ሁሉ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ያለውን ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሆናሉ። እኔ ጌታ ነኝ።” ጌታም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቁጠር፤ ወንዱን ሁሉ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውንና ከዚያም በላይ ያለውን ቁጠራቸው።” ሙሴም እንደ ጌታ ቃል፥ እንደ ታዘዘው ቈጠራቸው። በየስማቸውም የሌዊ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ። የቀዓትም ልጆች በየወገኖቻቸው፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል። የሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው። በጌድሶን ውስጥ የሎቤናውያን ወገንና የሰሜአውያን ወገን ይካተቱ ነበር፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱ የተቈጠሩት ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የወንዶች ሁሉ ቍጥር ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ይሰፍራሉ። የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያውን፥ ድንኳኑን፥ መደረቢያውን፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ የአደባባዩንም መጋረጆች፥ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፥ ገመዶቹንም መገልገያውንም ሁሉ ይሆናል። በቀዓት ውስጥም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ይካተቱ ነበር፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። ወንዶች ሁሉ እንደ ቁጥራቸው ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ የመቅደሱንም ግዴታ ለመፈጸም የተዘጋጁ ነበሩ። የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል። ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ ካህናቱም የሚገለገሉባቸውን የመቅደሱን ዕቃዎች፥ መጋረጃውንም፥ መገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ። የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም የመቅደሱን ግዴታ በሚፈጽሙት ላይ ተቆጣጣሪ ይሆናል። በሜራሪ ውስጥ የሞሖላውያን ወገንና የሙሳያውያን ወገን ይካተቱ ነበር፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቁጥራቸው ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ እነርሱም በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያውን ሳንቆች፥ መቀርቀሪያዎቹንም፥ ምሶሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ ዕቃዎቹንም ሁሉ መገልገያውንም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙትን የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ አውታሮቹንም ይሆናል። በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ በመቅደሱም ውስጥ ማናቸውንም ለእስራኤል ልጆች የሚደረገውን ሥርዓት ይጠብቃሉ፤ ማናቸውም ልዩ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል። በጌታ ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤልን ልጆች የወንድ በኩር ሁሉ ቁጠር፤ ዕድሜቸው አንድ ወር የሞላቸውንና ከዚያም በላይ ያሉትን በየስማቸው ቈጥረህ ቁጥሩን ውሰድ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኩር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ትወስዳለህ፥ እኔ ጌታ ነኝ።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኩር ሁሉ ቈጠረ። ከእነርሱም የተቈጠሩ የወንድ በኩር ሁሉ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የተቈጠሩት ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም የእኔ ናቸው፤ እኔ ጌታ ነኝ። ከሌዋውያን ወንዶች ቍጥር በላይ የሆኑትን ሁለት መቶ ሰባ ሦስት የእስራኤል ልጆች በኵራትን ለመዋጀት፥ ለእያንዳንዱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። ከቍጥር በላይ የሆኑት የተዋጁበትን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት ቍጥር በላይ ከሆኑት ዘንድ የመዋጃውን ገንዘብ ወሰደ። ከእስራኤል ልጆች በኵራት አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ገንዘቡን ወሰደ። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ጌታ ቃል፥ ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ከሌዊ ልጆች መካከል የቀዓትን ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ላይ የሕዝብ ቈጠራ አድርግ፤ ዕድሜው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያለውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገባውን ሁሉ ትቈጥራለህ። በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤ ሰፈሩ ለመጓዝ በተነሣ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይሸፍኑበት፤ በእርሱም ላይ የአስቆጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። በተቀደሰው ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ሙዳዮችንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለመጠጥ ቁርባንም መንቀሎቹን ያስቀምጡበት፤ ሁልጊዜም የሚቀርበው እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን። በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአስቆጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የመብራቱንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መቆንጠጫዎቹንም፥ መተርኮሻዎቹንም፥ ዘይቱንም የሚያቀርቡባቸውን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤ መቅረዙንና የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያኑሩት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። በመቅደስም ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡአቸው፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑአቸው፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉአቸው። አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ የሚገለገሉባቸውን የመሠውያውን ዕቃዎች ሁሉ፥ ጀሞዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ጐድጓዳ ሳሕኖቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም ላይ የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃዎች ሁሉ መሸፈናቸውን በጨረሱ ጊዜ፥ ሰፈሩም ለመጓዝ ሲነሣ፥ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ከዚያም በኋላ ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። የቀዓት ልጆች የሚሸከሙአቸው የመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች እነዚህ ናቸው። “የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት መዓዛውም በሚያምር ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቁርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይቆጣጠር።” ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤ ነገር ግን እጅግ ቅዱስ ወደ ሆኑት ነገሮች በቀረቡ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲህ አድርጉላቸው፦ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ እያንዳንዱንም ሰው በየተግባሩና በየሥራው ጫና ይመድቡት፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እንዲሁም የጌድሶንን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም የሕዝብ ቈጠራ አድርግ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቁጠራቸው። የጌድሶናውያን ወገኖች በማገልገልና በመሸከም የሚሰጡት አገልግሎት ይህ ነው፦ የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በእርሱም ላይ ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ የአደባባዩንም መጋረጆች፥ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን ደጃፍ መግብያ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ የሚገለገሉባቸውንም ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ እነርሱንም በሚመለከት ሊደረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ያድርጋሉ። የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ በየአገልግሎታቸውም የሚደርስባቸውን ሸክም ሁሉ ለእያንዳንዳቸው ትደለድላላችሁ። የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ሥራቸውንም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታማር ይቈጣጠራል። “የሜራሪንም ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቁጠራቸው። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቁጠራቸው። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ የሚሸከሙት፥ የማደሪያውን ሳንቆች፥ መቀርቀሪያዎቹንም፥ ምሶሶዎቹንም፥ እግሮቹንም፥ በዙሪያውም የሚቆሙትን የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቻቸውንም፥ ካስማዎቻቸውንም፥ አውታሮቻቸውንም፥ ዕቃዎቻቸውንና በተጓዳኝ የሚደረጉላቸውን አገልግሎቶች ሁሉ ነው፤ መሸከምም ያለባቸውን ዕቃዎች በየስሙ ትደለድላላችሁ። በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ቁጥጥር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት ይህ ነው።” ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ በየወገኖቻቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ነበሩ። ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የገቡት፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ በየወገኖቻቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። በየወገኖቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። እንደ ጌታ ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ ተደለደሉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የእስራኤል ልጆች የለምጽ ደዌ ያለበትን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ ሬሳንም በመንካት የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አወጡአቸው።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ እነርሱንም ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ ጌታ ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች ተናገር፦ ወንድ ወይም ሴት በጌታ ላይ ፈጽሞ እምነት በማጉደል ሰው የሚሠራውን ማናቸውንም ኃጢአት ቢሠሩ፥ የሠራው ያ ሰው በደለኛ ነው፥ የሠራውንም ኃጢአት ይናዘዝ፤ የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ፥ በእርሱም ላይ አምስት እጅ ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው። ነገር ግን በዳዩ ይመልስለት ዘንድ ለተበዳዩ ሰውዮ ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለጌታ የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሆናል፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተስረያ ከሚደረግበት የማስተስረያ አውራ በግ ላይ ይጨመር። የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡትን ማናቸውም የተቀደሱ ነገሮች ስጦታ ሁሉ ለእርሱ ይሆናሉ። የማናቸውም ሰው የተቀደሱ ነገረሮች ለራሱ ለሰውዬው ይሆናሉ፤ ማናቸውም ሰው ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ግን ለካህኑ ይሆናል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የማንኛውም ሰው ሚስት እርሱን ትታ ፈቀቅ ብትል፥ ለእርሱም ፍጹም ታማኝ ባትሆን፥ ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዐይን ቢሸሸግ፥ እርሷም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥ በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርሷም በመርከስዋ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርሷ ሳትረክስ በእርሱ ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ የገብስ ዱቄት የሆነውን ስለ እርሷ የሚቀርበውን ቁርባን ያምጣ፤ የቅንዓት የእህል ቁርባን ነውና፥ በደልንም የሚያስታውስ የመታሰቢያ የእህል ቁርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት። “ካህኑም ያቀርባታል በጌታም ፊት ያቆማታል፤ ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ደጃፍ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃው ውስጥ ይጨምረዋል፤ ካህኑም ሴቲቱን በጌታ ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም የተሠራ ጠጉር ይፈታል፥ በእጅዋም የመታሰቢያ የእህል ቁርባን የሆነውን የቅንዓት የእህል ቁርባን ያኖራል፤ ካህኑም እርግማንን የሚያመጣውን መራራ ውኃ በእጁ ይይዛል። ሴቲቱንም እንዲህ ብሎ ካህኑ ያምላታል፦ ‘ከአንቺ ጋር ሌላ ወንድ ካልተኛ፥ በባልሽም ሥልጣን ሥር እየነበርሽ ራስሽን ለማርከስ ዘወር ካላልሽ፥ እርግማንን ከሚያመጣው ከዚህ መራራ ውኃ የተጠበቅሽ ሁኚ፤ ነገር ግን በባልሽም ሥልጣን ሥር እያለሽ እርሱን ትተሽ ፈቀቅ በማለት ራስሽን ያረከስሽ እንደሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤’ ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን እንዲህ ይላታል፦ ‘ጌታ ጭንሽን እያመነመነ ሆድሽንም እየነፋ፥ በሕዝብሽ መካከል ጌታ ለመርገምና ለመሐላ የምትሆኚ ያድርግሽ፤ እርግማንንም የሚያመጣው ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያሰልስለው፤’ ሴቲቱም፦ ‘አሜን አሜን’ ትላለች። “ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጽፋቸዋል፥ በመራራውም ውኃ ያጠፋቸዋል፤ እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ያጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ የሆነ ሥቃይ ያመጣባታል። ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቁርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ ካህኑም ከእህሉ ቁርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ውኃውን እንድትጠጣ ያደርጋታል። ውኃውንም እንድትጠጣ ካደረጋት በኋላ እንዲህ ትሆናለች፤ የረከሰች ብትሆንና ለባልዋ ፍጹም ታማኝ ባትሆን፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያመጣባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። ይልቁንም ሴቲቱ ሳትረክስ ንጹሕ ብትሆን ከእርግማን የተጠበቀች ትሆናለች፥ ልጅንም መፀነስ ትችላች። “ሚስት በባልዋ ሥልጣን ሥር እያለች እርሱን ትታ ፈቀቅ በማለት ራስዋን በምታረክስ ጊዜ ያለው የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ወይም በባልዋ ላይ የቅንዓት መንፈስ መጥቶበት ስለ ሚስቱ በሚቀና ጊዜ ቅንዓትን በሚመለከት ሕጉ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በጌታ ፊት ያቁማት፥ ካህኑም ይህን ሕግ ሁሉ በእርሷ ላይ ይፈጽምባት። ሰውዮውም ከበደል ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም በደልዋን ትሸከማለች።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወንድ ወይም ሴት ራሳቸውን ለጌታ ለመለየት የናዝራዊነት ስእለት ቢሳሉ፥ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን ይለይ፤ ከወይን ወይም ከሚያሰክር መጠጥ የሚሠራን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ ማንኛውንም ዓይነት የወይን ዘለላ ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ዘለላ ወይም ዘቢብ አይብላ። ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ከወይን ጠጅ የሚሠራውን ሌላ ነገር ሁሉ እንዲሁም የውስጡን ፍሬ ወይም ግልፋፊውን እንኳ አይብላ። “ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ለጌታ የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጉር ያሳድግ። “ለጌታ ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። ለአምላኩ ያደረገው ቅድስና በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ራሱን ስለ እነርሱ አያርክስ። ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ነው። “ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት እርሱም የተቀደሰውን ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጫል፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨዋል። በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። ራሱን የለየበትን ወራትም ለጌታ ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። “የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ ቁርባኑንም ለጌታ ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለአንድነት መሥዋዕት፥ አንድ ሌማትም እርሾ ያልገባበት እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ እርሾ ያልገባበት ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቁርባን፥ የመጠጡንም ቁርባን ያቅርብ። ካህኑም በጌታ ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። አውራውንም በግ ለአንድነት መሥዋዕት ከሌማቱ እርሾ ካልገባበት እንጀራ ጋር ወደ ጌታ ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቁርባንና የመጠጡን ቁርባን ያቀርባል። ናዝራዊውም የተቀደሰውን የራሱን ጠጉር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጫል፥ የተቀደሰውንም ራስ ጠጉር ወስዶ ከአንድነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም እርሾ ያልገባበትን አንድ የቂጣ እንጐቻ እርሾም ያልገባበትን አንድ ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተቀደሰውንም የራስ ጠጉር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚቀርበው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ድርሻው ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ሊጠጣ ይችላል። “ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ የመግዛት አቅሙ ከሚፈቅድለት ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለጌታ የሚያቀርበው የቁርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው፦ ጌታ ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ ጌታ ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ ጌታ ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። እነርሱም ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያኖራሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።” እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ማደሪያውን ተክሎ ከጨረሰ በኋላ፥ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፤ ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙት የነገዶች አለቆች የነበሩት የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ቁርባናቸውን አቀረቡ። መባቸውንም በጌታ ፊት አመጡ፥ የተሸፈኑ ስድስት ሰረገሎች ዐሥራ ሁለትም በሬዎች፤ ለሁለትም አለቆች ለእያንዳንዳቸው አንድ ሠረገላ ለእያንዳንዱም አለቃ አንዳንድ በሬ አመጡ፤ በማደሪያው ፊት አቀረቡ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለመገናኛው ድንኳን መገልገያ እንዲሆኑ እነዚህን ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ትሰጣቸዋለህ።” ሙሴም ሰረገሎቹንና በሬዎቹን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው። በካህኑም በአሮን ልጅ በኢታምር ቁጥጥ ሥር ሆነው ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው። ለቀዓት ልጆች ግን በትከሻቸው በመሸከም ቅዱስ የሆኑትን ነገረሮች ማገልገል የእነርሱ ነበርና፥ ለእነርሱ ምንም አልሰጣቸውም። መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቁርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ በእያንዳንዱ ቀን አንድ አለቃ መባውን ያቅርብ።” በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበው ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕትም አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ። በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ። ለመባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ ጐድጓዳ ሳሕን አቀረበ፤ ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሶገር ልጅ የናትናኤ መባ ይህ ነበረ። በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ። በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሰዲዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ። በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሱሪሰዳይ ልጅ የሰለሚኤል መባ ይህ ነበረ። በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ። በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዓሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ። በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፍዳሱር ልጅ የገማልኤል መባ ይህ ነበረ። በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ። በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዳይ ልጅ የአኪዔዘር መባ ይህ ነበረ። በዓሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ። በዓሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ አቀረበ፤ መባውም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ ጐድጓዳ ሳሕን፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ሙዳይ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ ለአንድነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ። መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች መሠዊያውን ለመቀደስ ያቀረቡት መባ ይህ ነበረ፤ ዐሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ ዐሥራ ሁለት የብር ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ ዐሥራ ሁለት የወርቅ ሙዳዮች፤ እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ጐድጓዳ ሳሕን ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። ዕጣንም የተሞሉት ዐሥራ ሁለቱ የወርቅ ሙዳዮች፥ እያንዳንዳቸው በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ዐሥር ሰቅል ነበሩ፤ የሙዳዮቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሀያ ሰቅል ነበረ። የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዐሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ ዐሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ከእህሉ ቁርባን ጋር ነበሩ፤ የኃጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች ዐሥራ ሁለት ነበሩ። የአንድነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ ሀያ አራት በሬዎች፥ ስልሳም አውራ በጎች፥ ስልሳም አውራ ፍየሎች፥ ስልሳም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ መሠዊያውን ለመቀደስ የቀረበ መባ ይህ ነበረ። ሙሴም ከጌታ ጋር ለመነጋገር ወደ መገናኛው ድንኳን በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር፤ እንዲህም እርሱ ተናገረው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮን ንገረው እንዲህም በለው መብራቶቹን ስትለኩስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ።” አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ። መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ ከእግሩ እስከ አበቦቹ ድረስ ሥራው ተቀጥቅጦ የተሠራ ነበረ፤ ጌታ ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አድርጎ ሠራው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። እነርሱንም ለማንጻት እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ላይ ያለውን ጠጉር ሁሉ በምላጭ ይላጩ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ራሳቸውንም ንጹሕ ያድርጉ። ወይፈንን፥ ለእህሉም ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ። ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። ሌዋውያንንም በጌታ ፊት ባቀረብካቸው ጊዜ የእስራኤል ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። አሮንም ሌዋውያን ጌታን እንዲያገለግሉ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለመወዝወዝ ቁርባን ሌዋውያንን በጌታ ፊት ያቅርብ። ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ማስተስረያ እንዲሆኑ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ አቅርብ። ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት ታቆማቸዋለህ፥ በጌታም ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ታቀርባቸዋለህ። እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ትለያለህ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሆናሉ። “ካነጻሓቸውና ለመወዝወዝም ቁርባን ካቀረብካቸው በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ለመፈጸም ይገባሉ። እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍተው ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች እንዲያስተስርዩላቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እንዲሠሩ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ።” ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። ሌዋውያንም ከኃጢአት ራሳቸውን አነጹ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም እነርሱን ለማንጻት ማስተስረያ አደረገላቸው። ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ገቡ፤ ጌታ ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በሌዋውያን ላይ ይህ ተፈጻሚ ይሆንባቸዋል፤ ዕድሚያቸው ሀያ አምስት ዓመት የሆናቸውና ከዚያም በላይ ያሉት የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ለመፈጸም ይገባሉ። ዕድሜአቸውም ኀምሳ ዓመት ሲሞላ አገልግሎታቸውን ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤ ወንድሞቻቸው የተሰጣቸውን ግዴታ እንዲወጡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይርዱአቸው እንጂ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩ። በየአገልግሎታቸው በመደልደል በሌዋውያን ላይ እንዲሁ ታደርጋለህ።” ከግብጽም ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የእስራኤል ልጆች በተወሰነለት ጊዜ የፋሲካን በዓል ያክብሩ፤ በዚህ ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ፥ በተወሰነለት ጊዜ ታደርጉታላችሁ፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ደንቡም ሁሉ ታደርጉታላችሁ።” ሙሴም የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። የሞተ ሰው ሬሳን በመንካት የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን የፋሲካን በዓል ለማክበር አልቻሉም ነበር። በዚያም ቀን በሙሴና በአሮን ፊት ቀረቡ። እነዚያም ሰዎች እርሱን እንዲህ አሉት፦ “የሞተውን ሰው ሬሳ በመነንካት ብንረክስም እንኳ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” ሙሴም፦ “ጌታ ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ጠብቁ” አላቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው ሬሳን በመንካት ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ እንዲህም ሆኖ እንኳ ለጌታ የፋሲካን በዓል ያክብር። በዓሉንም በሁለተኛው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ ያክብሩ፤ እርሾ ካልገባበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። ከእርሱም እስከ ማግስቱ ጥዋት ድረስ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያክብሩት። ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ የፋሲካን በዓል ባያከብር፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል። በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለጌታም የፋሲካን በዓል ቢያከብር፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓትና እንደ ደንቡ እንዲሁ ያክብር፤ ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሥርዓት ይኑራችሁ።” ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው ማደሪያውን፥ የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ ነበረ፤ እርሱም እንደ እሳት ያለ አምሳል ነበረ። ሁልጊዜ በማደርያው ላይ እንዲሁ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር። ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በማናቸውም ጊዜ ሲነሣ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም ባረፈበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። በጌታ ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ ደመናው በማደሪያው ላይ ባረፈበት ጊዜያት ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። ደመናውም በማደሪያው ላይ ለብዙ ቀኖች በቈየም ጊዜ እንኳ የእስራኤል ልጆች የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደመናው ለጥቂት ቀኖች በማደሪያው ላይ ይቈይ ነበር፤ በዚያ ጊዜ እንደ ጌታ ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ ጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቈይ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዛሉ፥ ወይም ባለማቋረጥ ቀኑንም ሌሊቱንም የሚቈይ ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም ረጅም ጊዜ ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። በጌታ ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሁለት የብር መለከቶች ሥራ፤ እነርሱንም ተቀጥቅጦ በሚሠራ ሥራ ለራስህ አብጃቸው፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ተነሥተው እንዲጓዙ ለመቀስቀስ ተጠቀምባቸው። ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በአንተ ዘንድ ይሰብሰቡ። አንዱን መለከት ብቻ ቢነፉ ግን ታላላቆቹ የእስራኤል ነገድ አለቆች በአንተ ዘንድ ይሰብሰቡ። የማስጠንቀቂያውንም መለከት ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዛሉ። ሁለተኛውንም የማስጠንቀቂያ መለከት ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዛሉ፤ የማስጠንቀቅያውን መለከት እንዲጓዙ ለመቀስቀስ ይነፋሉ። ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን የማስጠንቀቂያውን መለከት ከፍ ባለ ድምፅ አታሰሙ። የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሁን። በሚቃወማችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ጦርነት ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ ማስጠንቀቂያውን በመለከቶቹ ንፉ፤ በጌታም በአምላካችሁ ፊት ትታወሳላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ። እንዲሁም በደስታችሁ ቀን፥ በተወሰኑላችሁም የበዓላታችሁ ጊዜያት፥ በወራቱም መባቻዎቻችሁ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በአንድነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት እንድትታወሱ ይሆኑላችኋል፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ። የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ ተራቸውን ጠብቀው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ዐረፈ። ጌታ በሙሴ አንደበት ባዘዘው መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጓዙ። በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ። በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ። በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ። ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙት የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ። የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ። በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ። በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ። ቀዓታውያንም የተቀደሱትን ዕቃዎች ተሸክመው ተጓዙ፤ እነርሱም ከመምጣታቸው በፊት ማደሪያው ተተክሎ ነበር። የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ። በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ። በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ። ሰፈሮቹንም ሁሉ ከኋላ ሆኖ የሚጠብቀው የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ። በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ። በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ። የእስራኤል ልጆች በተጓዙ ጊዜ ተራቸውን ጠብቀው በየሠራዊታቸው እንዲህ ተጓዙ። ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን እንዲህ አለው፦ “ጌታ፦ ‘ለእናንተ እሰጣችኋለሁ’ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ ጌታ ለእስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን።” እርሱም፦ “አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ” አለው። ሙሴም እንዲህ አለው፦ “እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዐይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤ ከእኛም ጋር ብትሄድ ጌታ ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን።” ከጌታም ተራራ ተነሥተው የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የጌታም የኪዳኑ ታቦት የሚያርፉበትን ስፍራ ለመፈለግ የሦስት ቀን መንገድ ቀድሞአቸው ተጓዘ። ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የጌታ ደመና ቀን ቀን በእነርሱ ላይ ነበረ። ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ ሁሉ እንዲህ ይል ነበር፦ “አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ።” ባረፈም ጊዜ ሁሉ እንዲህ ይል ነበር፦ “አቤቱ፥ በብዙ ሺህ ወደሚቈጠሩት ወደ እስራኤል ልጆች ተመለስ።” ሕዝቡም ስለ ደረሰባቸው መከራ በጌታ ላይ አጉረመረሙ፤ ጌታም ሰምቶ እጅግ ተቈጣ፤ የጌታም እሳት በመካከላቸው ነደደ፥ የሰፈሩንም ዳር በላ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ ጌታ ጸለየ፥ እሳቱም ጠፋ። የጌታም እሳት በመካከላቸው ስለ ነደደ የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። በእነርሱም መካከል የነበረው የተለያየ ሕዝብ እጅግ ጐመጀ፤ የእስራኤልም ልጆች ዳግመኛ ዘወር በለው አለቀሱ እንዲህም አሉ፦ “የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ሳለን እንዲያው በነጻ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ ሐብሐብውንም፥ ባሕሮውንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስታውሳለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀ፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም የሚያው ነገር የለም።” መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በሸክላም ድስት ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በእርሱ ላይ ይወርድ ነበር። ሙሴም ሕዝቡ በየወገኑ፥ ሰው ሁሉ በየድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የጌታም ቁጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም በጣም ቅር ተሰኘ። ሙሴም ጌታን እንዲህ አለው፦ “ለምን በባርያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው፦ ‘ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንደምታቅፈው እንዲሁ በብብትህ እቀፋቸው’ የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? እነርሱንስ ወልጃቸዋለሁን? እነርሱም በፊቴ እያለቀሱ እንዲህ ይላሉና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ስጠን’፤ እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት አገኛለሁ? ለእኔ እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች እንደ ሆኑ የምታውቃቸውን የእስራኤል ሽማግሌዎች የሆኑ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ እነርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር በየቦታቸው ይቁሙ። እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አኖረዋለሁ፤ አንተም ብቻህን እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም እንዲህ በላቸው፦ ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ምክንያቱም እንዲህ እያላችሁ ያለቀሳችሁት ለቅሶ ወደ ጌታ ጆሮ ደርሶአልና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ሳለን በዚያ ደኅና ነበርን፤’ ስለዚህ ጌታ ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበላላችሁም። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን ብቻ የምትበሉት አይደለም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን ጌታን ትታችሁታልና፥ በፊቱም፦ ‘ለምን ከዚያ ከግብጽ ወጣን?’ ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪ ወጣ እስኪያቅለሸልሻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” ነገር ግን ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እኔ በመካከላቸው ሆኜ በእኔ ዘንድ ያሉት ሰዎች ሲቈጠሩ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ አልህ። እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድላቸውን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ እንዲያጠግባቸው ይሰበሰብላቸውን?” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በውኑ ጌታ ለዚህ እጅ አጥሮት ነውን? አሁን ቃሌ ለአንተ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደሆነ አንተ ታያለህ።” ሙሴም ወጣ የጌታንም ቃላት ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። ጌታም በደመናው ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አኖረ፤ መንፈሱም በእነርሱ ላይ ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ ሲሆን የሁለተኛው ስም ደግሞ ሞዳድ ይባል ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን ወጥተው አልሄዱም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ ሆነው ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው” አለው። ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “የጌታ ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ ጌታም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያኖር፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። ነፋስም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ እነርሱንም የአንድ ቀን መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ አጠገብ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ያህል ቈለላቸው። በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በማግስቱም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ ዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳይታኘክ የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ጌታም ሕዝቡን እጅግ ታላቅ በሆነ መቅሠፍት መታ። እንግዲህ የጐመጀውን ሕዝብ በዚያ ቀብረውታልና የዚያ ስፍራ ስም ኬብሮን-ሐታማ ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም ከኬብሮን-ሐታማ ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ። ሙሴም ኢትዮጵያይቱን በእርግጥ አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። እነርሱም፦ “በውኑ ጌታ የተናገረው በሙሴ በኩል ብቻ ነውን? በእኛስ በኩል ደግሞ ተናገሮ የለምን?” አሉ፤ ጌታም ሰማ። ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ። በድንገትም ጌታ ሙሴንና አሮንን ማርያምንም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ፤” ሦስቱም ወጡ። ጌታም በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወደ እርሱ መጡ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “እባካችሁ፥ ቃሎቼን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ ጌታ በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ከባርያዬ ከሙሴ ጋር ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ በምሳሌ ሳይሆን እፊት ለፊት ከእርሱ ጋር በግልጥ እነጋገራለሁ፤ የጌታንም ሀልዎተ-ቅርፅ ይመለከታል፤ ታዲያ፥ በባርያዬ በሙሴ ላይ ለመናገር ለምን አልፈራችሁም?” በእርሱም ላይ የጌታ ቁጣ ነደደ፤ እርሱም ትቶአቸው ሄደ። ደመናውም ከድንኳኑ በተነሣ ጊዜ እነሆ፥ ማርያም በለምጽ ደዌ ተይዛ እንደ በረዶ ነጭ ሆና ነበር፤ አሮንም ወደ ማርያም ዘወር አለ፥ እነሆም፥ በለምጽ ደዌ ተይዛ ተመለከተ። አሮንም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ተሞኝተን ይህን አድርገናልና፥ ኃጢአትንም ሠርተናልና እባክህ፥ ኃጢአትን በእኛ ላይ አትቁጠርብን። ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ በማኅፀን እንደ ሞተ ልጅ እርሷ እባክህ፥ አትሁን።” ሙሴም እንዲህ ብሎ ወደ ጌታ ጮኸ፦ “አቤቱ፥ እባክህ፥ ፈውሳት።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት እንኳ እርሷ ሰባት ቀን ልታፍር አይገባትምን? ሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጪ ተዘግቶባት ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ።” ማርያምም ከሰፈሩ ውጪ ሰባት ቀን ተዘግቶባት ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም። ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ።” ሙሴም እንደ ጌታ ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤ ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሳፋጥ፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግዓል፤ ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ ሆሴአ፤ ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤ ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤ ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤ ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። ሙሴም የነዌን ልጅ ሆሴአን ኢያሱ ብሎ ጠራው። ሙሴም የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ላካቸው፥ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “ከዚህ በኔጌብ በኩል አድርጋችሁ ውጡ፥ ወደ ተራራማውም አገር ሂዱ፤ ምድሪቱንም ምን እንደምትመስል፥ በእርሷም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ እዩ፤ እንዲሁም የሚኖሩባት ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም የተመሸጉ አምባዎች እንደ ሆኑ፥ ምድሪቱም ለም ወይም መካን፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች ተመልከቱ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ።” በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወቅት ነበረ። ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ ለሌብ ሐማት ቅርብ እስከሆነችው እስከ ረዓብ ድረስ ሰለሉ። በደቡብም በኩል ወጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብጽ ካለችው ከጣኔዎእ ከሰባት ዓመት በፊት የተቈረቈረች ከተማ ነበረች። ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ሙሉ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት። ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። ተጉዘውም በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ መጡ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ወደ ላክኸን ምድር ገባን፥ እርሷም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው፤ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም ሰፋፊዎች ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።” ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ “ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ፥ እንውረሰው” አለ። ከእርሱ ጋር ወጥተው የነበሩት ሰዎች ግን፦ “ከእኛ ይልቅ እነርሱ ብርቱ ናቸውና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” አሉ። ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች አወሩ እንዲህም አሉ፦ “እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርሷም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን።” ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፤ በዚያም ሌሊት ሕዝቡ አለቀሰ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፦ “በግብጽ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! ጌታም በሰይፍ እንድንሞት ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ለምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብጽ መመለስ አይሻለንምን?” እርስ በርሳቸውም፦ “ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ። ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ማኅበር በሆነው ጉባኤ ሁሉ ፊት በግምባራቸው ወድቀው ሰገዱ። ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም የሆነች ናት። ጌታስ በእኛ ደስ የሚሰኝ ቢሆን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርሷንም ይሰጠናል። ብቻ፥ በጌታ ላይ አታምፁ፤ ለእኛ እንደ እንጀራ ቁራሽ ናቸውና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ ጌታም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው።” ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተማከሩ። የጌታም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በመካከላቸውም ስላደረግሁት ተአምራት ሁሉ እንኳ እስከ መቼ ድረስ በእኔ አያምኑም? ከርስታቸው እነርሱን ለማጥፋት በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” ሙሴ ግን ጌታን እንዲህ አለው፦ “ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አቤቱ፥ አንተ በዚህ ሕዝብ መካከል እንደሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ እንዲህ ይላሉ፦ ‘ጌታ ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ሊያገባቸው አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው።’ አሁንም፥ እባክህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን፤ አንተም እንዲሁ ቃል ኪዳን ያደረግከው እንዲህ ብለህ በተነናገርህ ጊዜ ነው፦ ‘ጌታ ታጋሽና ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ በደልንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን በደል እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው።’ ይህን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልከው፥ እባክህ፥ እንደ ጽኑ ፍቅርህ ብዛት የዚህን ሕዝብ በደል ይቅር በል።” ጌታም እንዲህ አለ፦ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የጌታ ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ክብሬንና ተአምራቴን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ እኔን ስለ ተፈታተኑኝ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፥ እነዚህም የናቁኝ ሰዎች ሁሉ አያይዋትም፤ ባርያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለ ተከተለኝ እርሱ ሄዶ ወደ ነበረበት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው ውስጥ ስለ ተቀመጡ ነገ ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር በኩል በሚወስደው መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።” ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የሚያጉረመርምብኝን ይህን ክፉ ማኅበር እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጉረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ሰምቻለሁ። እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ ከአጠቃላይም ቁጥራችሁ፥ በእኔ ላይ ያጉረመረሙ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያም በላይ ሆነው የተቈጠሩት ሁሉ፥ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርሷ ላስቀምጣችሁ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። ነገር ግን ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን ወደ ምድሪቱ አስገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቋታል። እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት እረኛች ይሆናሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ዝሙታችሁን ይሸከማሉ። ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ እያንዳንዱም ቀን እንደ አንድ ዓመት ሆኖ፥ በደላችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ መከፋቴንም ታውቃላችሁ።’ እኔ ጌታ፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ በእውነት እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።” ምድሪቱንም እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች፥ እነርሱም ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማውራት በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጉረመርሙ ያደረጉ፥ እነዚያ ክፉ ወሬ ስለ ምድሪቱ ያወሩ ሰዎች በጌታ ፊት በመቅሠፍት ሞቱ። ነገር ግን ምድሪቱን ለመሰለል ከሄዱት ከእነዚያ ሰዎች ውስጥ በሕይወት የቀሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ነበሩ። ሙሴም እነዚህን ቃላት ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ። በማግስቱም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ እንዲህ እያሉ ወጡ፦ እነሆ፥ እኛ በዚህ አለን፤ እኛ ኃጢአትን ሠርተናልና ጌታ ወዳለው ስፍራ እንወጣለን። ሙሴም እንዲህ አለ፦ “የጌታን ትእዛዝ ለምን አሁንም ትተላለፋላችሁ? ይህ አይሳካላችሁም። ጌታ በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትሸነፉ አትውጡ። በዚያም አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ ጌታን ከመከተል ተመልሳችኋልና ጌታ ከእናንተ ጋር አይሆንም።” የጌታ ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ ወጥተው ባይጓዙም እንኳ እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ለመውጣት ደፈሩ። በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወረዱ፥ አሸንፈወዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደምሰጣችሁ ወደምትኖሩባት ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ስእለታችሁን ለመፈጸም፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጋችሁ ለጌታ ብታቀርቡ፥ ቁርባኑን ለማቅረብ የሚያመጣ ሰው የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄትን የእህል ቁርባን አድርጎ ለጌታ ያቅርብ፤ የኢንም መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት ታዘጋጃለህ። ለአንዱም አውራ በግ የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን እንዲሆን ታዘጋጃለህ፤ ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ታቀርባለህ። ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለአንድነት መሥዋዕት ወይፈንን ለጌታ ብታዘጋጅ፥ ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን ታቀርባለህ። ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ታቀርባለህ። “ለእያንዳንዱም ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት እንዲሁ ይደረጋል። እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር መጠን፥ እንዲሁ እንደ ቁጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ። የአገሩ ተወላጅ የሆነ ሁሉ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ባቀረበ ጊዜ እነዚህን ነገሮች እንዲሁ ያደርጋል። መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ቢያቀርብ፥ እናንተ እንደምታደርጉት እርሱ እንዲሁ ያደርጋል። ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ ለጉባኤው ሁሉ አንድ ዓይነት ሥርዓት ይኑር፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁት መጻተኛውም በጌታ ፊት እንዲሁ ይሆናል። ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ዓይነት ሕግና አንድ ዓይነት ፍርድ ይኑራችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለጌታ እንደ ልዩ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ። መጀመሪያ ከምታዘጋጁት ሊጥ አንድ እንጐቻ ልዩ ስጦታ የሆነ ቁርባን አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማውም እንደ ልዩ ስጦታ አድርጋችሁ እንደምታቀርቡት ቁርባን እንዲሁ ታቀርቡታላችሁ። መጀመሪያ ከምታዘጋጁት ሊጥ እንደ ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቡትን ቁርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለጌታ ትሰጣላችሁ። “ነገር ግን ስሕተት ባለማወቅ ብትፈጽሙ፥ ጌታም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ጌታ ትዕዛዝን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ ወደፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥ ይህንንም ነገር ማኅበሩ ሳያውቀው በስሕተት የተደረገ ቢሆን፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቁርባንና ከመጠጡ ቁርባን ጋር እንደ ሕጉ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ባለማወቅ ስሕተት ፈጽመው ነበርና፥ ባለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባናቸውን አምጥተዋልና፥ ማለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው የኃጢአታቸውን መሥዋዕት በጌታ ፊት አቅርበዋልና እነርሱ ይቅር ይባላሉ። ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ ሕዝቡም ሁሉ ባለማወቅ ይህ ስሕተት ፈጽመዋልና በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል። “አንድ ሰው ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል። ባለማወቅም ኃጢአት ሠርቶ ስሕተትን ለፈጸመው ለዚያ ሰው እንዲያስተሰርይለት፥ ካህኑ በጌታ ፊት ማስተስሪያ ያደርጋል፤ እርሱም ይቅር ይባላል። ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ባለማወቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ። ነገር ግን የአገሩ ተወላጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ በትዕቢት ማናቸውንም ነገሮች የሚያደርግ ሰው ጌታን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። የጌታን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስላፈረሰ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ በደሉ በራሱ ላይ ነው።” የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። በእርሱም ላይ ምን ሊደረግበት እንደሚገባ ገና ግልጽ አልነበረምና በእስር ቤት አኖሩት። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት።” ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አውጡት፥ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉ፥ በዘርፉም ጫፍ ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል እንዲያኖሩበት እዘዛቸው። ዘርፉንም በልብሳችሁ ላይ አኑሩት እርሱንም በተመለከታችሁ ጊዜ የጌታን ትእዛዝ ሁሉ ታስታውሳላችሁ ታደርጉታላችሁም፥ ምኞታችሁንም በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዐይኖቻችሁን ፈቃድ የማትከተሉ ትሆናላችሁ። ስለዚህ ትእዛዜን ሁሉ አስታውሱት አድርጉትም፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ሁኑ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ የኤልያብ ልጆች ዳታንንና አቤሮንን ከሮቤልም ልጆች የፋሌት ልጅ ኦንን ወሰዳቸው። ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች የሆኑ ከጉባኤው የተመረጡ፥ በዝናቸውም የገነኑ የማኅበሩ አለቆች ጋር በመሆን እነርሱ በሙሴ ላይ ተነሡ። በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ ጌታም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችሁታል፤ በጌታም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወድቆ ሰገደ፤ ለቆሬም እርሱንም ለተከሉት ሁሉ እንዲህ ቡሎ ተናገረ፦ “ነገ ጠዋት ጌታ ለእርሱ የሆነውን ሰው፥ ቅዱስም ማን እንሆነ፥ ወደ እርሱም ለመቅረብ የተፈቀደለትን ሰው ያሳውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል። እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና እርሱንም የተከተሉት ሁሉ፥ ጥናዎችን ይውሰዱ፤ በማግስቱም በጌታ ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ ጌታ የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ! እጅግ አብዝታችሁታል።” ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፦ “እናንተ የሌዊ ልጆች፥ እባካችሁ ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የጌታንም ማደሪያ አገልግሎት እንድትሠሩ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት እንድትቆሙ ወደ እርሱ ለማቅረብ መፍቀዱን እንደ ቀላል ነገር ቈጠራችሁትን? አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ እንድትቀርቡ ፈቅዶላችኋል፤ ታዲያ አሁን ደግሞ ክህነትንም ትፈልጋላችሁን? ስለዚህም አንተና አንተንም የሚከተሉህ ሁሉ በጌታ ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ የምታጉረመርሙት አሮን ማን ስለ ሆነ ነው?” ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም እንዲህ አሉ፦ “አንመጣም፤ እኛን በምድረ በዳ ለመግደል ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን ቀላል እንደሆነ ነገር ቈጠርከውን? እንዲሁም በእኛ ላይ ራስህን ፈጽሞ አለቃ ታደርጋለህን? ደግሞስ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላስገባኸንም፥ እርሻና የወይንም ተክል ቦታ አላወረስከንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዐይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም።” ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ ጌታንም እንዲህ አለው፦ “ወደ ቁርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ እንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም።” ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፦ “ነገ አንተ፥ አንተንም የሚከተሉህ ሁሉ፥ አሮንም በጌታ ፊት ተገኙ፤ ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ ጌታ ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ጥናዎች፤ አንተም እንዲሁም አሮን እያንዳንዳችሁ ጥናዎቻችሁን አምጡ።” እያንዳንዳቸውም ጥናቸውን ወሰዱ፥ እሳትም አደረጉባቸው፥ ዕጣንም ጨመሩባቸው፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆሙ። ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የጌታም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ሁሉንም በአንድ ጊዜ ስለማጠፋቸው ከዚህ ማኅበር መካከል ተለዩ።” እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው በመስገድ እንዲህ አሉ፦ “አምላክ ሆይ! አንተ የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን?” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለማኅበሩ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ርቃችሁ ገለል በሉ።” ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። እርሱም ለማኅበሩ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ርቃችሁ ገለል በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ የእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ።” ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ርቀው ገለል አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሚስቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ። ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይህን ሥራ ሁሉ ለመሥራት ጌታ ልኮኛል እንጂ ከልቤ አስቤው እንዳልሆነ በዚህ ታውቃላችሁ። እነዚህ ሰዎች በተፈጥሮ ሰው እንደሚሞተው ቢሞቱ፥ ወይም ሰው ሁሉ እንደሚቀበለው የዕጣ ክፍሉ የሚቀበሉ ቢሆን እኔን ጌታ አልላከኝም። ጌታ ግን አንድ አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያንጊዜ እነዚህ ሰዎች ጌታን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።” እንዲህም ሆነ፤ እነዚህን ቃላት ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ የቆሬም የሆኑትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። እነርሱም የእነርሱም የሆነው ሁሉ በሕይወታቸው ሳሉ ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ላይ ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ። “ምድሪቱ እኛንም ደግሞ እንዳትውጠን” ብለው በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከእነርሱ ጩኸት የተነሣ ሸሹ። እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጥቶ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች በላቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የተቀደሱ ናቸውና ጥናዎቹን ከሚነድደው እሳት መከካከል ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ አርቀህ በትነው፤ በኃጢአታቸው የተነሣ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለሞት የሰጡትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፋችሁ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጓቸው፤ በጌታ ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።” ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወሰደ፤ እነርሱንም ጠፈጠፏቸው ለመሠዊያው መለበጫ አደረጓቸው። በቆሬና በእርሱም ተከታዮች ላይ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በጌታ ፊት ዕጣንን ለማጠን እንዳይቀርብ፥ ጌታ በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው። በማግስቱም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ “እናንተ የጌታን ሕዝብ ገድላችኋል” ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ብለው ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የጌታም ክብር ተገለጠ። ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ወዳለው ስፍራ መጡ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከዚህ ማኅበር መካከል ርቃችሁ ገለል በሉ፥ እኔም በአንድ ጊዜ አጠፋቸዋለሁ።” በግምባራቸውም ወድቀው ሰገዱ። ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፦ “ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከጌታ ዘንድ ቁጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል።” አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው። በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተገታ። በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። መቅሠፍቱም በተገታ ጊዜ አሮን ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች ተናገር፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ሁሉ ከየአባቶቻቸው ቤት ዐሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ። በሌዊም በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። ለእያንዳንዱ ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ አንድ በትር ይኖራቸዋልና። እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ለፊት አኑራቸው። እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፥ በእናንተም ላይ ያጉረመረሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።” ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዐሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች። ሙሴም በትሮቹን በጌታ ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው። እንዲህም ሆነ፤ በማግስቱ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነው የአሮን በትር አቈጥቁጦ፥ እምቡጥም አውጥቶ፥ አበባም አብቦ፥ የበሰለ ለውዝም አፍርቶ ነበር። ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከጌታ ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልሰህ አኑር፤ እርሱም ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆኖ ይቀመጥ፤ እነርሱም እንዳይሞቱ በእኔ ላይ ማጉረምረማቸውን ታስቆምበታለህ።” ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ እንዳዘዘው እንዲሁ እርሱ አደረገ። የእስራኤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን። ፈጽሞ ወደ ጌታ ማደሪያ የሚቀርብ ሁሉ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን?” ጌታም አሮንን እንዲህ አለው፦ “አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት ከመቅደሱ ጋር በተገናኘ የሚፈጸምን በደል ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ከክህነታችሁ ጋር በተገናኘ የሚፈጸምን በደል ትሸከማላችሁ። እንዲሁም አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ሳላችሁ ከአንተ ጋር በአንድነት እንዲሆኑ፥ እንዲያገለግሉህም፥ የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ደግሞ ከአንተ ጋር አምጣቸው። እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገልግሎት ግዴታ ይፈጽሙ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ። ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ግዴታዎች ይፈጽሙ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ። በጭራሽ ዳግመኛ በእስራኤል ልጆች ላይ ቁጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ ራሳችሁ የመቅደሱንና የመሠዊያውን ግዴታዎች ፈጽሙ። እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት እንዲሠሩ ለጌታ የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው። አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው የሚደረገውን ነገር ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን እንድታደርጉ የክህነታችሁን ግዴታዎች በትጋት ፈጽሙ፥ አገልግሉም፤ ክህነታችሁን እንደ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል።” ጌታም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባኔን ሁሉ ለአንተ እንድትጠብቀው ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተና ለልጆችህ የክህነትህ ድርሻ እንዲሆን ለአንተ የተገባህ አድርጌ ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ። በእሳት ከሚቀርበው እጅግ ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቁርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። እጅግ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ ለአንተም የተቀደሰ ይሆንልሃል። ይህም ደግሞ ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ የሚያቀርቡትን የመወዝወዝ ቁርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። ለጌታ ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ። ወደ ጌታ የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል። ለጌታ ከሚያቀርቡት ከሰው ወይም ከእንስሳ ማናቸውም ማኅፀን የሚከፍት ሥጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትዋጀዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትዋጀዋለህ። ከአንድ ወር ጀምሮ የምትዋጀውን እንደ ግምትህ ትዋጀዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው። ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትዋጅም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ እርጨው፥ ስባቸውንም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ አቃጥለው። የሚወዘወዘው ፍርምባና የቀኙ ወርች ለአንተ እንደሆነ እንዲሁ ሥጋቸው ለአንተ ይሆናል። የእስራኤል ልጆች እንደ ስጦታ ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለጌታ ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ፤ በጌታ ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ ለዘለዓለም የጨው ቃል ኪዳን ነው።” ጌታም አሮንን እንዲህ አለው፦ “በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይኖርህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ። ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ሁሉ ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ። ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ። ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግላሉ፥ እነርሱም የራሳቸውን በደል ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም። ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለሌዋውያን ተናገር እነርሱንም እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ለጌታ ለስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ። እንደ ስጦታ የምታቀርቡት ቁርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ሙላት ይቈጠርላችኋል። እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለጌታ እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ፤ ከእርሱም የጌታን የስጦታ ቁርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ። የእናንተ ከሆነው ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከእርሱም ከተቀደሰው ድርሻ ሁሉ፥ የጌታን የስጦታ ቁርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ።’ ስለዚህ እነርሱን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ከእርሱ የተመረጠውን ባቀረባችሁ ጊዜ ከአውድማው እህልና ከወይን መጭመቂያው እንደ ተገኘ ምርት ለሌዋውያን ይቈጠራል። እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገላችሁበት የድካማችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ። የተመረጠውንም ከእርሱ ባቀረባችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤልን ልጆች የተቀደሱ ነገሮች አታረክሱም።’ ” ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ጌታ ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። እርሷንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርሷም ከሰፈር ወደ ውጭ ትወሰዳለች፥ እርሷም በእርሱ ፊት ትታረዳለች። ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ይሰበስባል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኩሰትንም የሚያነጻ ውኃ ተደርጎ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። የጊደሪቱንም አመድ የሰበሰበው ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል። “የሞተውን የማናቸውንም ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን በውኃ ያነጻል፥ በዚህም ንጹሕ ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያነጻ ንጹሕ አይሆንም። የሞተውን ሰው በድን የነካ ማናቸውም ሰው ሁለመናውን ባያነጻ የጌታን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ ከርኩሰት የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኩሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። “ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። በተንጣለለው ሜዳ በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማናቸውም ሰው ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለረከሰው ሰው ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይጨመርበታል። ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ይነክረዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ ዐፅሙንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ ንጹሑም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ርኩስ በሆነው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያነጻዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በመሸም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል። “ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያነጻ፥ ያ ሰው የጌታን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። ይህም ለእነርሱ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ የሚረጨው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ከርኩሰትም የሚያነጻውን ውኃ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። የረከሰውም ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።” የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች። ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ እነርሱም በሙሴና በአሮን ላይ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት፦ “ወንድሞቻችን በጌታ ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ! እኛም ከብቶቻችንም በዚህ እንድንሞት የጌታን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ? ወደዚህ ክፉ ስፍራ ልታመጡን ከግብጽ ለምን አወጣችሁን? ለዘርና ለበለስ ለወይንም ለሮማንም የማይሆን ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም።” ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወድቀው ሰገዱ፤ የጌታም ክብር ተገለጠላቸው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በትሩን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ እነርሱም ዓይናቸው እያየ ድንጋዩ ውኃን እንዲሰጥ ተናገሩት፤ ለእነርሱም ከድንጋዩ ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ለማኅበሩና ለከብቶቻቸው የሚጠጣ ወኃ ትሰጣቸዋለህ።” ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከጌታ ፊት ወሰደ። ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰበሰቡአቸው ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናውጣላችሁን?” ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ። ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “በእስራኤል ልጆች ፊት ቅድስናዬን ለማሳየት በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም።” የእስራኤል ልጆች ከጌታ ጋር የተጣሉበት፥ እርሱም በመካከላቸው ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው። ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ የደረሰብንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ አባቶቻችን ወደ ግብጽ ወረዱ፥ በግብጽም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤ ወደ ጌታም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ልኮ ከግብጽ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፥ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጉድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ግዛትህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።” ኤዶምያስም፦ “በምድሬ ላይ አታልፍም አለበለዚያ ግን አንተን በሰይፍ ልገጥምህ እወጣለሁ” አለው። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉት፦ “በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ።” እርሱም፦ “አታልፍም” አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ። ኤዶምያስም እስራኤል በግዛቱ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ። ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ። ጌታም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ አላቸው፦ “አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በትእዛዜ ላይ ስላመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም። አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤ አሮንም የለበሰውን ልብስ አውልቅ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማቻል፥ በዚያም ይሞታል።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ። ሙሴም አሮን የለበሰውን ልብስ አወለቀ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ። ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ። በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል መምጣቱን ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ጦርነት አደረገ ከእርሱም ምርኮ ማረከ። እስራኤልም ለጌታ እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እነዚህን ሕዝቦች ፈጽሞ አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ።” ጌታም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት። ከሖርም ተራራ የኤዶምያስን ምድር በዙርያው አድርገው ለመሄድ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ ሕዝቡም በመንገድ እየተጓዙ ሳሉ ጉልበታቸው ደከመ። ሕዝቡም በጌታና በሙሴ ላይ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብጽ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃም የለም፤ ሰውነታችንም ይህን የሚያንገሸግሽ እንጀራ ተጸየፈ።” ጌታም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ላከ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “በጌታና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን ኃጢአት ሠርተናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ ጌታ ጸልይልን።” ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እባብን ሠርተህ በእንጨት ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያየው በሕይወት ይኖራል።” ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በእንጨት ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ። ከኦቦትም ተጉዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። ከዚያም ተጉዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። ከዚያም ተጉዘው ከአሞራውያን ዳርቻ ትይዩ በተዘረጋው ምድረ በዳ ውስጥ በአርኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። ስለዚህ በጌታ የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ፦ “ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥ እስከ ዔር ማደሪያ የተዘረጋው በሞዓብም ዳርቻ የሚገኘው የሸለቆች ተዳፋት መሬት።” ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም ጌታ ሙሴን፦ “ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የተናገረለት ጉድጓድ ነው። በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፦ አንተ ምንጭ ሆይ! ፍለቅ፤ እናንተም ዘምሩለት፤ በበትረ መንግሥት በከዘራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች የቈፈሩት፥ አለቆችም የማሱት ጉድጓድ። እነርሱም ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከዚያም በኋላ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት ተጓዙ፥ ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ። እስራኤልም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን ላከ፦ “በምድርህ ላይ ልለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጉድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ግዛትህን አልፈን እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን።” ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ እንዳያልፍ ከለከለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅ እስከ አሞን ልጆች ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ። እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር። ስለዚህ ባለቅኔዎች እንዲህ ብለው በምሳሌ ተቀኙ፦ “ወደ ሐሴቦን ኑ። የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረትም፤ እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤ ሞዓብ ሆይ! ወዮልህ! የካሞሽ ሕዝብ ሆይ! ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ። ቀስትን ወረወርንባቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ እሳቱ እስከ ሜድባ እስኪዛመት ድረስ ደመሰስናቸው።” እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ። ሙሴም ኢያዜርን እንዲሰልሉ ሰላዮችን ላከ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ። ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ እነርሱን ለመውጋት ወጣ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግኸው እንዲሁ ታደርግበታለህ።” ለእርሱም አንድ ሰው በሕይወት እንዳይተርፍ አድርገው እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ ገደሉ፤ ምድሩንም ወረሱ። የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ስለ ነበሩ ሞዓብ ሕዝቡን እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ “በሬ የለመለመውን የሣር መስክ ግጦ እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ አሁን ይጨርሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜም የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ የተቀመጠውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እዲጠሩት እንዲህ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፦ “እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፍኖአል፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል። አሁንም ከእኔ ይልቅ እጅግ ኃያል ናቸውና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደሆነ፥ ይህን ሕዝብ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የባረከው ቡሩክ የረገምኸውም ርጉም እንደሆነ አውቃለሁና።” የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም ለምዋርቱ የሚከፈለውን ገንዘብ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃላት ነገሩት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ ጌታም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ”፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ ላከ፦ ‘እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ ምናልባት ልወጋው ላሳድደውም እችል እንደሆነ አሁን ና እርሱን ርገምልኝ።’ ” እግዚአብሔርም በለዓምን፦ “ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን ሹማምንት፦ “ከእናንተ ጋር እንድሄድ ጌታ አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ” አላቸው። የሞዓብ ሹማምንት ተነሡ፥ ወደ ባላቅም ሄደው፦ “በለዓም ከእኛ ጋር ለመምጣት ፍቃደኛ አልሆነም” አሉት። ባላቅም ዳግመኛ ከፊተኞቹ ይልቅ እጅግ የበዙና የከበሩ ሌሎችን ሹማምንት ላከ። ወደ በለዓምም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ፥ ወደ እኔ ለመምጣት ምንም ዓይነት ነገር አያግድህ፤ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የምትነግረኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።’ ” በለዓምም መልሶ የባላቅን ባርያዎች እንዲህ አላቸው፦ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ ትንሹን ወይም ትልቁን ነገር በመፈጸም የአምላኬን የጌታን ቃል ለመተላለፍ አልችልም፤ አሁንም ጌታ ይበልጥ የሚነግረኝን ነገር እንዳውቅ፥ እባካችሁ፥ ሌሎቹ እንዳደረጉት እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ።” እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ ሊጠሩህ መጥተው እንደሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ።” በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ ሹማምንት ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የጌታም መልአክ ሊቃወመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ ሆኖ ይጓዝ ነበር፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያይቱም የጌታን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ እርሷም ከመንገዱ ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ እንድትመለስ አህያይቱን መታት። የጌታም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ዳግመኛ መታት። የጌታም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተምበርክካ ለጥ አለች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። ጌታም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። በለዓምም አህያይቱን፦ “ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያይቱም በለዓምን እንዲህ አለችው፦ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ ማድረግ ልማዴ ነበረን?” እርሱም፦ “እንዲህ አላደረግሽብኝም” አላት። ጌታም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የጌታም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፋ። የጌታም መልአክ እንዲህ አለው፦ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና ልቃወምህ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባትል ኖሮ በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርሷንም ባዳንኋት ነበር።” በለዓምም የጌታን መልአክ እንዲህ አለው፦ “ኃጢአትን ሠርቻለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ ልትቃወመኝ መቆምክን አላወቅሁም፤ እንግዲህም ይህ አሁን በፊትህ ክፉ የሆነ ነገር ቢሆን እመለሳለሁ።” የጌታም መልአክ በለዓምን፦ “ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ” አለው። በለዓምም ከባላቅ ሹማምንት ጋር ሄደ። ባላቅም በለዓም እንደመጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ድንበር በድንበሩም ጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተን ለመጥራት አላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን?” በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ እኔ አሁን አንዳችን ነገር ለመናገር እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያድርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ።” በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት ሹማምንት ላከ። በማግስቱም ጠዋት ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ ባሞት-በኣል አወጣው፤ በዚያም ሆኖ ዳር ላይ የሰፈረውን ሕዝብ አየ። በለዓምም ባላቅን፦ “ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ” አለው። ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ። በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “በሚቃጠል መሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት ጌታ ሊያገኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ።” ከዚያም እርሱ ወደ ኮረብታው ሄደ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጣ፤ እርሱም፦ “ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ” አለው። ጌታም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ፦ “ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም ተናገር” አለው። ወደ ባላቅም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ ሹማምንት ሁሉ በሚቃጠለው መሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር። በለዓምም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ‘ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን አውግዝልኝ አለኝ።’ እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? ጌታስ ያላወገዘውን እንዴት አወግዛለሁ? በተራሮች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም። የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ አራተኛውን ክፍል ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።” ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “ያደረግህብኝ ምንድነው? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው።” እርሱም መልሶ፦ “በውኑ ጌታ በአፌ ያደረገውን ለመናገር ጥንቃቄ ማድረግ የለብኝምን?” አለው። ባላቅም እንዲህ አለው፦ “በዚያ ሆነህ እንድታያቸው፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና፤ ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ።” ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ። በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “እኔ ወደዚያ ጌታን ለማግኘት ስሄድ በዚህ በሚቃጠለው መሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ።” ጌታም በለዓምን አገኘው፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ፦ “ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም ተናገር” አለው። ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ ሹማምንቶች በሚቃጠለው መሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም፦ “ጌታ የተናገረው ምንድነው?” አለው። በለዓምም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “ባላቅ ሆይ! ተነሣ፥ ስማም፤ የሴፎር ልጅ ሆይ! አድምጠኝ፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን? እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ ልመልሰው አልችልም። በያዕቆብ ላይ መከራን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጭንቀትን አላየም፤ አምላኩ ጌታ ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ። ከግብጽ ያወጣቸው እግዚአብሔር፥ ለእነርሱ እንደ ጎሽ ቀንድ ያለ ነው። በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል እንዲህ ይባላል፦ ‘እግዚአብሔር ምን አደረገ!’ እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ብድግ ይላል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን እስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አያርፍም።” ባላቅም በለዓምን፦ “ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው” አለው። በለዓምም መልሶ ባላቅን፦ “ ‘ጌታ የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ’ ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?” አለው። ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ብትረግምልኝ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝ ይሆናል።” ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ራስ ላይ በለዓምን ወሰደው። በለዓምም ባላቅን፦ “በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ” አለው። ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ። በለዓምም ጌታ እስራኤልን መባረክ ደስ እንደሚያሰኘው ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና። በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ። እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ የእግዚአብሔርን ቃላት የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ወድቆም ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ ሆይ! ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ! ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ! ወደፊትም ተዘርግቶ እንዳለው ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ ጌታ እንደ ተከለው ዓልሙን በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል። ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል። እግዚአብሔርም ከግብጽ አውጥቶታል፤ ጉልበቱ አንደ ጎሽ ቀንድ ያለ ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል። እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚባርክህ ሁሉ የተባረከ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን።” የባላቅም ቁጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ ይኸው ባረክሃቸው፤ እንግዲህ አሁን ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ እኔም እንዲህ አልሁ፦ ‘በእውነት አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤’ ጌታ ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለህ።” በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞችህ እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን? ‘ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ በራሴ ፈቃድ መልካምን ወይም ክፉን ነገር ለማድረግ የጌታን ቃል መተላለፍ አልችልም፤ ጌታ የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ።’ እነሆ፥ አሁን፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በሚመጣው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።” እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ የጌታን ቃላት የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤልም በትረ መንግሥት ይነሣል፥ የሞዓብንም ግንባር ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል። ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል። ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም በሕይወት የተረፉትን ያጠፋል።” በለዓምም አማሌቅን አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የአሕዛብ መጀመሪያ የሆነ አማሌቅ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።” ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በዐለት ላይ ተሠርቶአል፤ ቄናዊው ግን ለጥፋት የተዘጋጀ ይሆናል። አሦር የሚማርክህ እስከ መቼ ድረስ ይሆን?” ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ይህን ባደረገ ጊዜ ወዮ! ማን በሕይወት ይኖራል? ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያሠቃያሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።” በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም መንገዱን ተከትሎ ወደ ቤቱ ሄደ። እስራኤልም በሰጢም ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝር ጀመር። ሕዝቡንም ወደ አማልክቶቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ለአማልክቶቻም ሰገዱ። እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የጌታ የቁጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ላይ በጌታ ፊት ስቀላቸው።” ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፦ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው። እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ እያለቀሱ ሳሉ በእነርሱ ፊት ምድያማዊት የሆነችን አንዲት ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት። የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱንም ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። በመቅሠፍትም የሞተው ሰው ሀያ አራት ሺህ ነበረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቁጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። ስለዚህ እንዲህ በል፦ ‘እነሆ፥ የሰላም ቃል ኪዳኔን እሰጠዋለሁ። ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።’ ” ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ይባል ነበረ፤ እርሱም የስምዖናውያን ወገን የአባቱ ቤት አለቃ የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ትባል ነበረ፤ እርሷም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ምድያማውያን እንደ ጠላት ቁጠሩአቸው እነርሱንም ድል ንሱአቸው፤ በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሽንገላቸው ሸንግለዋችኋልና እነርሱን እንደ ጠላቶቻችሁ ቁጠሩአቸው።” እንዲህም ሆነ፤ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ ጌታ ሙሴንና የካህኑን የአሮን ልጅ አልዓዛርን እንዲህ አላቸው፦ “ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን፥ በእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቁጠሩ።” ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው “ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝብ ቁጠሩ።” ከግብጽም ምድር የወጡት የእስራኤል ልጆች እነዚህ ነበሩ፦ የእስራኤል በኩር ሮቤል፤ የሮቤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሄኖኅ የሄኖኀውያን ወገን፥ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን፥ ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፥ ከከርሚ የከርማውያን ወገን። እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ። የኤልያብም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን ናቸው፤ እነዚህ ዳታንና አቤሮን ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ቆሬን ከተከተሉት ሰዎች ጋር በመሆን በጌታ ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን የተገዳደሩ ነበሩ፤ ያም ወገን በሞተ ጊዜ፥ እሳቲቱም ሁለት መቶ ኀምሳውን ሰዎች ባቃጠለች ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ እነርሱን ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ። የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም። በየወገናቸው የስምዖን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከነሙኤል የነሙኤላውያን ወገን፥ ከያሚን የያሚናውያን ወገን፥ ከያኪን የያኪናውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን፥ ከሳኡል የሳኡላውያን ወገን። እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የጋድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከጽፎን የጽፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥ ከሹኒ የሹናውያን ወገን፥ ከኤስናን የኤስናናውያን ወገን፥ ከዔሪ የዔራውያን ወገን፥ ከአሮድ የአሮዳውያን ወገን፥ ከአርኤሊ የአርኤላውያን ወገን። እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። የይሁዳ ልጆች ዔርና አውናን ናቸው፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ። በየወገናቸው የይሁዳም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን። የፋሬስም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከሐሙል የሐሙላውያን ወገን። እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የይሳኮር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉዋ የፉዋውያን ወገን፥ ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሺምሮን የሺምሮናውያን ወገን። እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስልሳ አራት ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዛብሎን ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከሴሬድ የሴሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎን የኤሎናውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን። እነዚህ የዛብሎናውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስልሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም። የምናሴ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገለዓዳውያን ወገን። የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኢዔዝር የኢዔዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥ ከአሥሪኤል የአሥሪኤላውያን ወገን፥ ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ ከሸሚዳ የሸሚዳውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን። የኦፌርም ልጅ ሰለጰአድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። እነዚህ የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ኀምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን፥ ከቤኬር የቤኬራውያን ወገን፥ ከታሐን የታሐናውያን ወገን። እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን የዔዴናውያን ወገን። እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው። በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከቤላ የቤላውያን ወገን፥ ከአስቤል የአስቤላውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥ ከሑፋም የሑፋማውያን ወገን። እነዚህ የቤላም ልጆች ናቸው፤ አርድና ናዕማን፤ ከአርድ የአርዳውያን ወገን፥ ከናዕማን የናዕማናውያን ወገን። በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዔ የሰምዔያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው። የሰምዔያውያን ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስልሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የአሴር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከዪምና የዪምናውያን ወገን፥ ከየሱዋ የየሱዋውያን ወገን፥ ከበሪዓ የበሪዓውያን ወገን። እነዚህ ከበሪዓ ልጆች ናቸው፤ ከሔቤር የሔቤራውያን ወገን፥ ከመልኪኤል የመልኪኤላውያን ወገን። የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሤራሕ ነበረ። እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የንፍታሌም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከያሕጽኤል የያሕጽኤላውያን ወገን፥ ከጉኒ የጉናውያን ወገን፥ ከዬጽር የዬጽራውያን ወገን፥ ከሺሌም የሺሌማውያን ወገን። በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእነዚህ እንደየስማቸው ቍጥር መጠን ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፋፈላለች። በየወገናቸው ለብዙዎቹ እንደ ብዛታቸው፥ ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለሁሉ እንደ ቁጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፋፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ስም ይወርሳሉ። በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፋፈላለች።” ከሌዋውያንም በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን። እነዚህ የሌዊ ወገኖች ናቸው፤ የሊብናውያን ወገን፥ የኬብሮናውያን ወገን፥ የሞሖላውያን ወገን፥ የሙሳውያን ወገን፥ የቆሬያውያን ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ። የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። እርሷ በግብጽ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት። ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ተወለዱለት። በጌታም ፊት ያልተፈቀደውን እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ። ዕድሜአቸው አንድ ወር የሞላቸውና ከዚያም በላይ ያሉት ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሀያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጠሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው። ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም። ጌታ ስለ እነርሱ፦ “በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ” ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ አልቀረም። የሰለጰዓድም ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ እርሱም ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ ነበር፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦ “አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ቆሬን በመከተል በጌታ ላይ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን።” ሙሴም ነገራቸውን በጌታ ፊት አቀረበ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የሰለጰዓድ ልጆች ትክክለኛ ነገር ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ወደ እነርሱ ይተላለፍ። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘ወንድ ልጅ ሳይኖረው የሚሞት ሰው ቢኖር፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይተላለፍ፤ ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ፤ ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ፤ አባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ትሰጣላችሁ እርሱም ይውረሰው፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን።’ ” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። እናንተ በጺን ምድረ በዳ ማኅበሩ በተገዳደረኝ ጊዜ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው። ሙሴም ጌታን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነ ጌታ በማኅበሩ ላይ አንድ ሰው ይሹም። እርሱም የጌታ ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በእነርሱ ፊት የሚወጣ በእነርሱም ፊት የሚገባ እየመራቸውም የሚያስወጣቸው የሚያስገባቸው ሰው ይሁን። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በእርሱ ላይ ጫንበት፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በጌታ ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበሩም ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ ጌታም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በእርሱ ላይ ጫነበት፥ አዘዘውም። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ “‘ማዕዴን፥ ለእኔ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባኔን፥ መባዬን በተገቢው ጊዜ እንድታቀርቡልኝ በጥንቃቄ ልብ በሉ።’ እንዲህም በላቸው፦ ‘ለጌታ በእሳት የምታቀርቡት ቁርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ። አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤ የኢንም መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን ታቀርባለህ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በሲና ተራራ ላይ ተሰናድቶ በእሳት የቀረበ የዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የመጠጡ ቁርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ይሁን፤ በመቅደሱ ውስጥ ለጌታ ለመጠጥ ቁርባን መጠጥ አፍስስ። ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቁርባንና የመጠጡን ቁርባን በማለዳ እንዳቀረብህ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ።’ “በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቁርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቁርባን ታቀርባላችሁ። ዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው። “በወሩም መባቻ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ እንዲሁም ደግሞ ለእያንዳንዱም ወይፈን ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ አውራ በግም ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱም ጠቦት ለእህል ቁርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ። የመጠጥ ቁርባናቸውም ለአንድ ወይፈን የኢን ግማሽ፥ ለአውራው በግም የኢን ሢሶ፥ ለአንዱም ጠቦት የኢን አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ይሆናል፤ ይህ ለዓመቱ የወር መባቻ ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ለጌታም ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ ዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቁርባን ጎን ለጎን የሚቀርብ ይሆናል። “በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን የጌታ ፋሲካ ነው። ከዚህም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ ሰባት ቀን እርሾ ያልነካው ቂጣ ይበላል። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል፤ በእርሱም የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፤ እነርሱም ነውር የሌለባቸው መሆናቸውን ተመልከቱ። የእህል ቁርባናቸውንም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ ወይፈን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራውም በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። ማልዶ ከሚቀርበው ዘወትር ከሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ እነዚህን ታቀርባላችሁ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የቁርባኑን ማዕድ ሰባት ቀን በየዕለቱ እንዲሁ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቁርባን ጎን ለጎን የሚቀርብ ይሆናል። በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። “ደግሞ በበኵራት ቀን ከሰባቱ ሱባዔ በዓላችሁ አዲሱን የእህል ቁርባን ለጌታ ባቀረባችሁ ጊዜ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህል ቁርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱ ወይፈን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንዱም አውራ በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። ዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ሌላ እነርሱንና የመጠጥ ቁርባናቸውን ታቀርባላችሁ፤ እነርሱም ነውር የሌለባቸው መሆናቸውን ተመልከቱ።” በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ እንዲሁም ደግሞ ለእህል ቁርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ። ማስተስረያም እንዲሆንላችሁ አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። በዚህም በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ ምንም ዓይነት ሥራ አትሥሩ። ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንድ አውራ በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤ እንዲሁም ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጥ ቁርባናቸውም ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።። በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለጌታ በዓል አድርጋችሁ ታከብራላችሁ። ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለዐሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። በሁለተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባናቸው ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። በአራተኛውም ቀን ዐሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። “እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ቁርባን ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቁርባን፥ ለአንድነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለጌታ አቅርቡ። ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ጌታ እርሱን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።” ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው። ሰው ለጌታ ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱን በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አያፍርስ፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። ሴትም ደግሞ በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ለጌታ ስእለት ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና ጌታ ይቅር ይላታል። “ስእለትም ከተሳለች ወይም ራስዋን በመሐላ ያሰረችበትን ነገር ከአንደበትዋ በችኮላ ከተናገረች በኋላ ባል ብታገባ፥ ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል። ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርሷ ላይ ያለውን ስእለትዋን ከአንደበትዋም በችኮላ ተናግራ ራስዋን በመሐላ ያሰረችበትን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ ጌታም ይቅር ይላታል። “ባልዋ የሞተባት ወይም ከባልዋ የተፋታች ሴት ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸኑባታል። ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ በአንደበትዋ የተናገረችው ማናቸውም ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ ጌታም ይቅር ይላታል። “ስእለትዋን ሁሉ ራስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል። ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርሷም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። ዳሩ ግን ነገሩን ከሰማ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከንቱ ቢያደርገው በደልዋን ይሸከማል። እርሷ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል እንዲሆን ጌታ ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።” ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት የተዘጋጁ ይሁኑ፤ ስለ ጌታ በቀል ምድያምን እንዲበቀሉ በምድያም ላይ ይዝመቱ፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ላኩ።” ከብዙ ሺህ እስራኤላውያን መካከል ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተዘጋጁ ሰዎች ተመለመሉ። ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ላከ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ላካቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም የማስጠንቀቂያ መለከት በእጁ ሰጠው። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ። ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት። የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ። የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ። የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን፥ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር፥ ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር አመጡ። ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ። ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጦሩ አዛዦች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ። ሙሴም አላቸው፦ “በውኑ ሴቶችን ሁሉ በሕይወት እንዲኖሩ ፈቀዳችሁላቸውን? እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር ጌታን አታልለው ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ በዚህም ምክንያት በጌታ ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ። አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ። ወንድን በመኝታ የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ በሕይወት አቆዩዋቸው። ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ከእናንተም ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የነካ ሁሉ፥ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና እናንተ የማረካችኋቸውን አንጹ። ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጉር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ አንጹ።” ካህኑም አልዓዛር ከጦርነት የተመለሱትን ወታደሮች እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥ እርሳሱንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ። በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን ታጥባላችሁ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትገባላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቁጠሩ። ምርኮውንም ወደ ጦርት ወጥተው በተዋጉትና፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል ለሁለት ክፈል። ከእነዚያም ወደ ጦርነት ወጥተው ከተዋጉት ወታደሮች ድርሻ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከበጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለጌታ ግብር አውጣ። ከድርሻቸው ወስደህ ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን አግርህ ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጠዋለህ። ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከበጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከኀምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የጌታንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።” ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። ወታደሮቹም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስልሳ አንድ ሺህ አህዮች፥ ወንድን በመኝታ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ። በዘመቻም ለተሳተፉት ሰዎች ድርሻ የሆነ እኩሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥ ከበጎችም የጌታ ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ። በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ሰባ ሁለት ነበረ። አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ስልሳ አንድ ነበረ። ሰዎቹም ዐሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለጌታ የስጦታ ቁርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው። ለእስራኤልም ልጆች ድርሻ፥ ወደ ጦርነት ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥ የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥ ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥ ዐሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ። ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከኀምሳ አንድ ወሰደ፥ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው የጌታን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ። በብዙ ሺህ በሚቆሩት ሠራዊት ላይ የተሾሙት የጦር አዛዦች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥ ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ወደ ጦርነት የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጥረናል፥ ከእኛ አንድም ሰው አልጐደለም። ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጉትቻም፥ ከወርቁም ጌጣጌጥ ለነፍሳችን በጌታ ፊት እንዲያስተሰርይልን ለጌታ መባ አምጥተናል።” ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ከእነርሱ ወርቁንና በልዩ ልዩ ቅርፅ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ተቀበሉ። ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን አድርገው ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ ዐሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ሰቅል ነበረ። ወታደሮቹም ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ። ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በጌታ ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት። የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥ የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ አሉአቸው፦ “ዓጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ጌታ የእስራኤል ማኅበር እንዲወርሰው ያደረገው ምድር ሲሆን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባርያዎችህ እንስሶች አሉን።” እነርሱም በመቀጠል እንዲህ አሉ፦ “እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደሆነ ይህን ምድር ለባርያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።” ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? ጌታ ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ? ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ። ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ባዩ ጊዜ፥ ጌታ ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ። በዚያም ቀን የጌታ ቁጣ ነደደ እንዲህም ብሎ ማለ፦ ‘ከግብጽ የወጡት ዕድሜአቸው ሀያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ለመስጠት የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ዳሩ ግን ለዮፎኔ ልጅ ካሌብና ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በእውነት ጌታን ፈጽመው ስለ ተከተሉ ይህ እንዲህ አይሆንም።’ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በጌታም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። እነሆም፥ የጌታን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ለመጨመር እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ተነሣችሁ! እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ዳግመኛ ሕዝቡን በምድረ በዳ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።” ወደ እርሱም ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “በዚህ ለበጎቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤ እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንድሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ። የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤ ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእርሱም ወደዚያ ያለውን ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም።” ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በጌታ ፊት ወደ ጦርነት ብትሄዱ፥ እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ከእናንተ ለጦርነት የተዘጋጀው ሰው ሁሉ በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ ምድሪቱ በጌታ ፊት ድል ትሆናለች፤ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በጌታም ፊት በእስራኤል ዘንድ ከግዳጃችሁ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በጌታ ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርታችኋል፤ ኃጢአታችሁም በእውነት እንደሚያገኛችሁ እወቁ። ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአንደበታችሁም የወጣውን ቃል ፈጽሙ።” የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ ዳሩ ግን እኛ ለጦርነት የተዘጋጀነው ባርያዎችህ ሁሉ በጌታ ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት ለመዋጋት እንሻገራለን።” ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ለጦርነት የተዘገጋጁት የጋድና የሮቤል ልጆች ሁሉ ከእናንተ ጋር በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ።” የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው እንዲህ አሉት፦ “ጌታ ለእኛ ለባርያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። ለጦርነት ተዘጋጅተን በጌታ ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል።” ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና ከተሞቹን በከተሞቹም ዙሪያ ያሉትን ግዛቶች ሰጣቸው። የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን ሠሩ፤ እንዲሁም ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። የሮቤልም ልጆች የሠሩአቸው ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ ቂርያትይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ነበር፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ያዝዋትም፥ በእርሷም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ እርሱም በእርሷ ተቀመጠ። የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮቻቸውን ያዘ፥ እነርሱንም የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራቸው። ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮቻቸውንም ያዘ፥ እነርሱንም በስሙ ኖባህ ብሎ ጠራቸው። በሙሴና በአሮን ልጅ እየተመሩ በየሠራዊታቸው ሆነው ከግብጽ በወጡ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ያደረጉት ጉዞ ይህ ነበረ። ሙሴም በጌታ ትእዛዝ የጉዞአቸው መነሻ የሆኑትን ስፍራዎቻቸውን ጻፈ፤ እንደ መነሻ ስፍራዎቻቸው ጉዞአቸው እንዲህ ነበረ። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አምስተኛው ቀን ከራዓምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በማግስቱ የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ። በዚያም ጊዜ ግብፃውያን ጌታ የገደላቸውን በኩሮቻቸውን ሁሉ ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ላይ ደግሞ ጌታ ፈረደባቸው። የእስራኤልም ልጆች ከራዓምሴ ተጉዘው በሱኮት ሰፈሩ። ከሱኮትም ተጉዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ። ከኤታምም ተጉዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ። ከፊሀሒሮትም ተጉዘው ባሕሩን በመሻገር ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ። ከማራም ተጉዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ። ከኤሊምም ተጉዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ። ከኤርትራም ባሕር ተጉዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ። ከሲን ምድረ በዳም ተጉዘው በራፋቃ ሰፈሩ። ከራፋቃም ተጉዘው በኤሉስ ሰፈሩ። ከኤሉስም ተጉዘው በራፊዲም ሰፈሩ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። ከራፊዲምም ተጉዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። ከሲናም ምድረ በዳ ተጉዘው በኬብሮን-ሐታማ ሰፈሩ። ከኬብሮን-ሐታማም ተጉዘው በሐጼሮት ሰፈሩ። ከሐጼሮትም ተጉዘው በሪትማ ሰፈሩ። ከሪትማም ተጉዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ። ከሬሞን ዘፋሬስም ተጉዘው በልብና ሰፈሩ። ከልብናም ተጉዘው በሪሳ ሰፈሩ። ከሪሳም ተጉዘው በቀሄላታ ሰፈሩ። ከቀሄላታም ተጉዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ። ከሻፍር ተራራም ተጉዘው በሐራዳ ሰፈሩ። ከሐራዳም ተጉዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ። ከመቅሄሎትም ተጉዘው በታሐት ሰፈሩ። ከታሐትም ተጉዘው በታራ ሰፈሩ። ከታራም ተጉዘው በሚትቃ ሰፈሩ። ከሚትቃም ተጉዘው በሐሽሞና ሰፈሩ። ከሐሽሞናም ተጉዘው በሞሴሮት ሰፈሩ። ከሞሴሮትም ተጉዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ። ከብኔያዕቃንም ተጉዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ። ከሖርሃጊድጋድም ተጉዘው በዮጥባታ ሰፈሩ። ከዮጥባታም ተጉዘው በዔብሮና ሰፈሩ። ከዔብሮናም ተጉዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ። ከዔጽዮንጋብርም ተጉዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት። ከቃዴስም ተጉዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ። ካህኑም አሮን በጌታ ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር። በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደመጡ ሰማ። እነርሱም ከሖር ተራራ ተጉዘው በሴልሞና ሰፈሩ። ከሴልሞናም ተጉዘው በፉኖን ሰፈሩ። ከፋኖንም ተጉዘው በአቦት ሰፈሩ። ከአቦትም ተጉዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። በዒዬዓባሪም ተጉዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። ከዲቦንጋድም ተጉዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። ከዓልሞንዲብላታይምም ተጉዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። ከዓብሪምም ተራሮች ተጉዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ። ጌታም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም። ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያንዳንዱ ሁሉ ዕጣው እንደ ወጣለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ። የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ ስንጥር ለጎናችሁም እንደ እሾህ ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። እኔም በእነርሱ ላይ ለማድረግ ያሰብሁትን በእናንተ ላይ አደርግባችኋለሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት እንዲሆናችሁ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በተከለለው ድንበርዋ የከነዓን ምድር ይህች ናት፤ የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ ተነሥቶ የኤዶምያስን ዳርቻ እያዋሰነ የሚያልፈው ይሆናል፤ የደቡቡም ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤ ድንበራችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ይሻገራል፤ በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ያለው መጨረሻው ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤ ድንበሩም ከዓጽሞን ወደ ግብጽ ወንዝ ይዞራል፥ ባሕሩም ማብቂያው ይሆናል። “ለምዕራብም ድንበር ታላቁ ባሕርና ዳርቻው ድንበራችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ድንበራችሁ ይሆናል። “የሰሜንም ድንበራችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ። ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ የድንበራችሁም መጨረሻ በጽዳድ ይሆናል፤ ድንበሩም ወደ ዚፍሮን ይዘረጋል መጨረሻውም ሐጸርዔናን ይሆናል፤ ይህ የሰሜን ድንበራችሁ ይሆናል። “የምሥራቁም ድንበራችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ፤ ድንበሩም ከሴፋማ በዐይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤ ድንበሩም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መጨረሻውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ድንበርዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።” ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ጌታ ለዘጠኝ ነገድ ተኩል እንዲሰጥ ያዘዘው በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤ የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል። እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በስተ ምሥራቅ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል ወረሱ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፋፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ። ምድሪቱንም ርስት አድርገው ለመከፋፈል ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ። የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥ ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥ ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥ ከዳን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥ ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥ ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥ ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥ ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥ ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥ ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል። ጌታ በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን እንዲያከፋፍሉ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።” ጌታም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው እንዲሰጡ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰማሪያ ለሌዋውያን ስጡ። እንዲቀመጡባቸውም ከተሞቹ ለእነርሱ ይሆናሉ፤ መሰማሪያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም እነርሱም ላሏቸው ነገሮች ሁሉ ይሁን። ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰማሪያ በከተማው ዙሪያ ሁሉ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን። ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትለካላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰማሪያ ይሆንላቸዋል። ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ እንዲሸሽባቸው የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ። ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰማሪያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ። ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ለእናንተ ከተሞችን ትመርጣላችሁ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። በስሕተት ነፍስ የገደለ ሁሉ እንዲሸሽበት እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። “ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኛው ጊዜ ይግደለው። እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ገፍትሮ ቢጥለው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። “ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ገፍትሮ ቢጥለው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰውን ለሞት የሚያበቃውን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ሊያደርግበት ባይሻ፥ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን በዚህ መሠረት ይፍረድ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ቅባትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ቢወጣ፥ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ታላቁ ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። “እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። ነፍሰ ገዳይ ሁሉ ምስክሮች በሰሚጡት ቃል ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። ታላቁ ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ እንዲመለስ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው ሰው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። እኔ ጌታ በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።” ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤ እነርሱም እንዲህ አሉ፦ “ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፋፍለህ እንድትሰጣቸው ጌታ አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ ጌታም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አንተን ጌታችንን አዘዘ። ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይወሰዳል፥ እነርሱም ወደ አሉበት ወደ ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ከርስታችን ዕጣ ይወሰዳል። ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው እነርሱ ወደ አሉበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ ርስታቸውም ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይወሰዳል።” ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጌታ ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “የዮሴፍ ልጆች ነገድ እውነት የሆነን ነገር ተናግረዋል። ጌታ ስለ ሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ‘የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ወገን ከሆነ ነገድ ብቻ ያግቡ። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ የአባቶቹን ነገድ ርስት ይያዝ። ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት እንዲወርስ፥ ከማናቸውም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ። ስለዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ የራሱን ርስት ይያዝ።’ ” ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ። የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና። ጌታ በሙሴ አንደበት የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው። በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ትይዩ በሆነው ሱፍ ፊት ለፊት፥ በፋራን እና በጦፌልም፥ በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። ከኮሬብ በሴይር ተራራ መንገድ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። በአርባኛው ዓመት በዓሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን፥ ሙሴ፥ ጌታ ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ “ጌታ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ ‘በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፥ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር፥ ወደ አጎራባቾቹም በዓረባም በደጋውና በቆላው ሁሉ፥ በኔጌብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አኖራለሁ፥ ግቡ፥ ጌታ ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።’ “በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ ‘እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፥ ጌታ አምላካችሁ አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ ጌታ እንደ ተናገራችሁም፥ በዚህ ቍጥር ላይ ሺህ ጊዜ እጥፍ ይጨምር፥ ይባርካችሁም። እኔ ብቻዬን ድካምችሁን፥ ሸክማችሁንም፥ ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮች፥ አዋቂዎች የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።’ እናንተም፦ ‘እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው፥’ ብላችሁ መለሳችሁልኝ። እኔም ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች ተቀበልኩ፥ በእናንተም ላይ የሺህ አለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ የኀምሳ አለቆችም፥ የዐሥር አለቆችም ገዢዎችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። በዚያን ጊዜ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። አልኋቸውም፦ ‘የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፥ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፥ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፥ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፥ አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ፤’ በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። “ከኮሬብም ወጣን፥ ጌታ አምላካችን እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ሁሉ ባያችሁት ምድረ በዳ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፥ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም አልኋችሁ፦ ‘ጌታ አምላካችን ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፥ እነሆ፥ ጌታ አምላካችሁ ምድሪቱን በፊትህ አኑሮአል፥ የአባቶችህ አምላክ ጌታ እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፥ አትፍራ፥ አትደንግጥም።’ “እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ’ አላችሁኝ። “ነገሩ መልካም ሆኖ ታየኝ፥ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፥ ከየነገዱ ሁሉ አንዳንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ቃኙት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፥ አሉንም፦ ‘ጌታ አምላካችን የሚሰጠን ምድር መልካም ናት።’ “እናንተ ግን በጌታ በአምላካችሁ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርሷ መውጣትን አልፈቀዳችሁም፥ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ ብላችሁ አጉረመረማችሁ፦ ‘ጌታ ስለ ጠላን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ፥ ሊያጠፋን ከግብጽ ምድር አወጣን። ወዴትስ እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው፥’ ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አወኩት። “እኔም አልኋችሁ፦ ‘አትሸበሩ፥ እነርሱንም አትፍሩ፥ በዓይናችሁ ፊት በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ በፊታችሁ የሚሄደው ጌታ አምላካችሁ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ በምድረ በዳም፥ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ፥ ጌታ አምላካችሁ እንዴት እንደተንከባከባችሁ አይታችኋል።’ ይህም ሆኖ በዚህ ነገር ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም፤ እርሱ ግን የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ ለማሳየት ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም። “ጌታም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣም፤ እንዲህም ሲል ማለ፦ ‘ከዚህ ክፉ ትውልድ፥ ከእነዚህ ሰዎች አንዳቸውም፥ ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር አያይም፤ ከይፉኔ ልጅ ከካሌብ በቀር፤ እርሱ ያያታል፥ የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ፥ ምክንያቱም ጌታን ፈጽሞ ተከትሎአል።’ በእናንተው ምክንያት ጌታ በእኔም ላይ ደግሞ ተቆጥቶ እንዲህም አለኝ፤ ‘አንተም ደግሞ ወደዚያ አትገባም፤ በፊትህ የሚቆመው የነዌ ልጅ ኢያሱ ወደዚያ ይገባል፤ እርሱ ለእስራኤል ምድሪቱን ያወርሳልና አበረታታው።’ “ደግሞ፦ ‘ይማረካሉ ያላችኋቸው ሕፃናቶቻችሁ፥ ዛሬም መልካሙን ከክፉ መለየት የማይችሉ ልጆቻችሁ፥ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፥ ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ፥ ይወርሱአታልም። እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር አቅጣጫ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።’ “እናንተም፦ ‘ጌታን በድለናል፥ ጌታ አምላካችን ልክ እንዳዘዘን፥ እንወጣለን እንዋጋለንም’ ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር መውጣትን አቀለላችሁት። “ጌታም፦ ‘እኔ በእናንተ መካከል አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው’ አለኝ። እኔም ተናገርኋችሁ፥ እናንተ ግን በጌታ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ አልሰማችሁም፥ በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ። በዚያም በተራራማው አገር ይኖሩ የነበር አሞራውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፥ እንደ ንብ መንጋ አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር ድል ነሷችሁ። ተመልሳችሁም በጌታ ፊት አለቀሳችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን ሊሰማም፥ እናንተም ሊያዳምጥ አልወደደም። ስለዚህ እንደ ተቀመጣችሁበትም ዘመን መጠን፥ በቃዴስ ብዙ ቀን ተቀመጣችሁ።” “ጌታም እንዳለኝ፥ ተመልሰን በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄድን፥ የሴይርንም ተራራ ብዙ ቀን ዞርን። ጌታም እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ‘በዚህ ተራራማ አገር ለረጅም ጊዜ ተንከራታችኋልና ይብቃችሁ፥ ተመልሳችሁ ወደ ሰሜን ሂዱ። ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ በሴይር ላይ በተቀመጡት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ልጆች አገር ታልፋላችሁ፥ እነርሱም ይፈሩአችኋል፤ እንግዲህ እጅግ ተጠንቀቁ። የሴይርን ተራራ ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ እኔ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታህል እንኳ አልሰጣችሁምና አትጣሉአቸው። ከእነርሱ በገንዘብ ምግብ ገዝታችሁ ትበላላችሁ፥ ውኃም ደግሞ በገንዘብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ።’ “ጌታ አምላክህ የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና፥ በዚህ በታላቅ ምድረ በዳ መሄድህን አውቆአል፥ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ ጌታ አምላክህ ከአንተ ጋር ነበረ፥ አንዳችም አላጣህም። “እኛም ወንድሞቻችን የዔሳው ልጆች ከተቀመጡት ሴይር አልፈን፥ በዓረባ መንገድ ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር አለፍን። ተመልሰንም በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ አለፍን። ጌታም አለኝ፦ ‘እኔ ዔርን ለሎጥ ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ፥ ከእነርሱ ምድር ምንም አልሰጣችሁምና ሞዓባውያንን አትጣላ በውጊያም አትጋፈጣቸው።’” አስቀድሞ ታላቅና ብዙ ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች በቁመት የረዘሙ ኤሚማውያን በዚያ ይቀመጡ ነበር። እነርሱም ደግሞ እንደ ዔናቅ ልጆች ራፋይም ይባሉ ነበር፥ ሞዓባውያን ግን ኤሚም ይሉአቸዋል። ሖራውያንም ደግሞ አስቀድሞ በሴይር ላይ ተቀምጠው ነበር፥ የዔሳው ልጆች ግን ነጠቁአቸው፥ ጌታ የሰጣቸውን እስራኤላውያን በርስት ምድራቸው እንዳደረጉት፥ ከፊታቸው አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ። “አሁንም፥ ‘ተነሡ የዘሬድንም ፈፋ ተሻገሩ፤’ አለን። የዘሬድንም ፈፋ ተሻገርን። የዘሬድንም ፈፋ እስከ ተሻገርንበት ድረስ፥ ጌታ እንደ ማለባቸው የጦረኞች ትውልድ ሁሉ ከሰፈሩ መካከል እስከ ጠፉ ድረስ፥ ከቃዴስ በርኔ የተጓዝንበት ዘመን ሠላሳ ስምንት ዓመት ሆነ። ከሰፈሩበትም መካከል አልቀው እስኪጠፉ ድረስ የጌታ እጅ በላያቸው ነበረ። “እንዲህም ሆነ፥ ጦረኞቹ ከጠፉ ከሕዝቡም መካከል ከሞቱ በኋላ፥ ጌታ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ‘አንተ ዛሬ የሞዓብን ዳርቻ ዔርን ታልፋለህ፤ በአሞን ልጆች አቅራቢያ ስትደርስ፥ ለሎጥም ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከአሞን ልጆች ምድር ርስት አልሰጥህምና፥ አትጣላቸው አትውጋቸውም።’” ያም ደግሞ የራፋይም ምድር ተብሎ ተቆጠረ፥ ራፋይምም አስቀድሞ በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሩአቸዋል። ታላቅና ብዙም ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች ቁመታቸው የረዘመ ነበሩ፥ ጌታ ከፊታቸው አጠፋቸው፥ እነርሱንም ቀምተዋቸው በስፍራቸው ተቀመጡ። ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍቶ፥ በሴይር ለተቀመጡት ለዔሳው ልጆች እንዳደረገ፥ እንዲሁ ለእነርሱ አደረገ፥ እነርሱንም ቀምተው በስፍራቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተቀመጡ። እስከ ጋዛም ድረስ በመንደሮች ተቀምጠው የነበሩትን ኤዋውያንን ከካፍቶር የወጡ ካፍቶራውያን አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ሰፈሩ። “ደግሞም አለ፦ ‘ተነሥታችሁ ሂዱ፥ የአርኖንንም ሸለቆ ተሻገሩ፥ እነሆ፥ አሞራዊውን የሐሴቦንን ንጉሥ ሴዎንን ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፤ እርሷን በመውረስ ጀምር፥ ከእርሱም ጋር ተዋጋ። ከሰማይ በታች ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ማስደንገጥህንና ማስፈራትህን ማኖር ዛሬ እጀምራለሁ፥ ወሬህን በሰሙ ጊዜ በፊትህ ይንቀጠቀጣሉ፥ ድንጋጤም ይይዛቸዋል።’” “ከቅዴሞትም ምድረ በዳ፥ የሰላምን ቃል እንዲነገግሩት፥ ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁ፦ ‘በአገርህ ላይ ልለፍ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳልል አውራ ጎዳናውን ይዤ እሄዳለሁ። የምበላውን ምግብ በገንዘብ ሽጥልኝ፤ የምጠጣውንም ውሃ በገንዘብ ስጠኝ፤ በእግሬ እንዳልፍ ብቻ ፍድልኝ። ጌታ አምላካችን ወደሚሰጠን ምድር ዮርዳኖስን እስክሻገር ድረስ፥ በሴይር የተቀመጡ የዔሳው ልጆች በዔርም የተቀመጡ ሞዓባውያን እንዳደረጉልኝ፥ አድርግልኝ።’” “የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን ግን ያሳልፈን ዘንድ አልፈቀደም፥ እንደ ዛሬው ሁሉ በእጅህ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ፥ ጌታ አምላካችሁ መንፈሱን አደንድኖታልና ልቡንም አጽንቶታልና።” “ጌታም፦ ‘ሴዎንንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ መስጠት፥ እነሆ፥ ጀመርሁ፤ ምድሩን ትገዛት ዘንድ መውረስ ጀምር’ አለኝ።” ሴዎንም፥ እሱና ሕዝቡም ሁሉ፥ ሊጋጠሙን ወደ ያሐጽ ወጡ። ጌታ አምላካችንም እርሱን አሳልፎ ሰጠን፤ እርሱንና ልጆቹን፥ ሕዝቡንም ሁሉ መታን። በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን የተቀመጡባቸውንም ወንዶች፥ ሴቶች፥ ሕፃናቶችንም ሁሉን አጠፋን፥ አንዳችም አላስቀረንም፥ ከብቶቻቸውንና ከከተሞቻቸው ያገኘነውን ምርኮ ግን ለራሳችን ወሰድን። በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር፥ ከሸለቆውም ውስጥ ካለችው ከተማ ጀምረን እስከ ገለዓድ ድረስ፥ የትኛይቱም ከተማ አልተቋቋመችንም፤ ጌታ አምላካችን ሁሉን አሳልፎ ሰጠን። ብቻ ጌታ አምላካችን ወደ ከለከለን፥ ወደ አሞን ልጆች ምድር በያቦቅም ወንዝ አጠገብ ወዳለው ስፍራ ሁሉ በተራራማውም አገር ወዳሉት ከተሞች አልቀረብንም። “ከዚያ ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን፥ የባሳን ንጉሥ ዖግም፥ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ፥ በኤድራይ ሊዋጉን ወጡ። ጌታም፦ ‘እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፥ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሲሖን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ’ አለኝ።” ስለዚህ ጌታ አምላካችን ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዖግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፥ እኛም አንድ ሰው እንኳ ሳናስቀርለት አጠፋነው። ያን ጊዜም ከተሞቹ ሁሉ ያዝን፥ የአርጎብን ግዛቶች ሁሉ፥ ከሥልሳ ከተሞች ጋር፥ በባሳን ያለውን የዖግን መንግሥት፥ ያልወሰድነው ምንም ከተማ አልነበረም። እነዚህ ሁሉ ከተሞች፥ በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ። በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ ደመሰስናቸው፥ እያንዳንዱን ከተማ፥ ወንዶችን፥ ሴቶችና ሕፃናት ሁሉ አጠፋናቸው። ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለራሳችን ዘረፍን። በዚያን ጊዜ በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩት ሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት እጅ፥ ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ ሔርሞን ተራራ ድረስ፥ ምድሪቱን ወሰድን። የሔርሞንን ተራራ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፥ አሞራውያን “ሠኒር” ብለው ሰይመውታል። በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ ባሳንን ሁሉ፥ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ፥ በባሳንም ያሉትን የዖግን መንግሥት ከተሞች ወሰድን። ከራፋያውያን ወገን የባሳን ንጉሥ ዖግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፥ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በራባት አለ፥ ቁመቱ ዘጠኝ ክንድ የጎኑም ስፋት አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ። በዚያን ወቅት ይህችን ምድር በወረስን ጊዜ፥ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ አገር እኩሌታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገዶች ሰጠኋቸው። ከገለዓድም የቀረውን የዖግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ግዛት ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፥ ያቺ ባሳን ሁሉ የራፋይም አገር ተብላ ተጠራች። የምናሴ ልጅ ያኢር፥ ባሳንን እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ፥ የአርጎብን ግዛት ሁሉ ወሰደ፥ ይችንም የባሳን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ በሚጠራበት የያኢር መንደሮች ብሎ ጠራ። ለማኪርም ገልዓድን ሰጠሁት። ለሮቤልና ለጋድም ነገዶች ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ፥ የሸለቆውን አማካይ እንደ ወሰን፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ ሰጠሁ፤ ዓረባንም፥ ከዮርዳኖስ ጋር እንደ ወሰን፥ ከኪኔሬት እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ፥ የጨው ባሕር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን ያካትታል። በዚያም ጊዜ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፦ “ጌታ አምላካችሁ ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ የእናንተ ጦር ሰዎች ሁሉ ታጥቀው በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ። ነገር ግን፥ ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁ አውቃለሁና፥ ሚስቶቻችሁ፥ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀራሉ፤ ይኸውም ጌታ እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ ጌታ አምላካችሁ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።” ኢያሱንም ያንጊዜ አዘዝኩት፦ “ጌታ አምላካችሁ በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ያደረገውን ሁሉ ዐይኖችህ አይተዋል፥ እንዲሁ ሁሉ በምታልፍባቸው መንግሥታት ላይ ጌታ ያደርጋል። ጌታ አምላካችሁ እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና አትፍሯቸው።” “በዚያን ጊዜ ለጌታ እኔ እንዲህ ብዬ ለመንሁ፦ ‘ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለአገልጋይህ ማሳየት ጀምረሃል፥ በሰማይም ሆነ በምድርም እነዚህ ሥራዎችና ኃያል ተግባራት እንደ አንተ ማድረግ የሚችል አምላክ ማን ነው? እለምንሃለሁ፥ ልሻገር፥ በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር ያንም መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ልይ።’ “ጌታ ግን በእናንተ ምክንያት ተቆጥቶኝ ነበር፥ አልሰማኝምም፥ ጌታም አለኝ፦ ‘እንግዲህ ይበቃሃል፤ በዚህ ጉዳይ ዳግመኛ አትናገረኝ። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ፒስጋ ራስ ውጣ፥ ዓይንህንም አንሥተህ ወደ ምዕራብና ሰሜንም ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም በዓይንህ ተመልከት። ይልቅስ ኢያሱን እዘዘው፥ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና፥ አደፋፍረውም፥ አበርታውም።’ “እኛም በቤተፌዖር ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን። “አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ ጌታ ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ሕግጋት ስሙ። እኔ ያዘዝኋችሁን የጌታ አምላካችሁን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። የፌዖሩን ባዓልን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ ጌታ አምላካችሁ ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በባዓል ፌዖር ያደረገውን ዐይኖቻችሁ አይተዋል። እናንተ ግን ጌታ አምላካችሁን የተከተላችሁ ሁላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት ትኖራላችሁ። “እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ እንድታደርጉ ጌታዬ አምላኬ እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ሕግጋትን አስተማርኋችሁ። ጠብቁአት አድርጉአትም፥ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው፦ ‘በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው’ በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና። “እኛ በምንለምነው ጊዜ ሁሉ ጌታ አምላካችን ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነው፥ የየትኛው ሌላ ታላቅ ሕዝብ ነው አምላኩ ለእርሱ ቅርብ የሆነለት? በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንዳኖርኩት እንደዚህ ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ሕግጋት ያለው ታላቅ ሕዝብስ የት ይገኛል? “ብቻ አስተውል፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ዐይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይለይ፥ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አሳውቃቸው። በጌታ በአምላካችሁ ፊት በኮሬብ በቆማችሁበት ቀን፥ ጌታ፦ ‘ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት እንዲማሩ፥ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ፥ ቃሌን አሰማቸዋለሁ’ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፥ እስከ ሰማይም ድረስ እሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፥ ጨለማም ደመናና ድቅድቅ ጨለማ ነበረ። ጌታም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፥ ድምፅን ብቻ ነበር እንጂ መልክ አላያችሁም። እንድታደርጉትም ያዘዛችሁን ቃል ኪዳኑን፥ ዓሥሩን ትእዛዝ፥ ገለጸላችሁ፤ በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይም ጻፋቸው። ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉትን ሥርዓትና ሕግጋት እንዳስተምራችሁ ጌታ በዚያን ጊዜ አዘዘኝ። “ጌታ በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ ምንም መልክ አላያችሁምና፥ ለነፍሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ፤ የማናቸውንም መልክ በየትኛውም ምስል፥ በወንድ ይሁን በሴት መልክ፥ የተቀረጸውን ምስል ለራሳችሁ በማድረግ እንዳትረክሱ፥ በምድር ላይ ያለውን የማንኛውንም እንስሳ ምስል በክንፉ የሚበርና የማንኛውንም ወፍ ምስል፥ በምድርም ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን፥ ከምድር በታች በውሃ ውስጥ የሚኖሩትን የዓሣ ሁሉ ምስል አታድርጉ። ዐይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰማይ በታች ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሰጣቸውን፥ ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም፥ የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ በመሳት እንዳትሰግዱላቸውና እንዳታመልኳቸው ተጠንቀቁ። እናንተን ግን ጌታ ወስዶ፥ እንደ ዛሬው ሁሉ የርስቱ ሕዝብ እንድትሆኑለት፥ ከብረት እቶን ከግብጽ አውጥቷችኋል። በእናንተ ቃላት ምክንያት ጌታ እኔን ተቆጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገር ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። እኔ በዚህች ምድር እሞታለሁና፥ ዮርዳኖስን አልሻገርም፥ እናንተ ግን ትሻገራላችሁ፥ ያችንም መልካሚቱን ምድር ትወርሳላችሁ። ጌታ አምላካችሁ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ ጌታ አምላካችሁም የከለከለውን በማናቸውም መልክ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። ጌታ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት፥ ቀናተኛ አምላክ ነውና። “ልጆችን የልጅ ልጆችንም በወለዳችሁ ጊዜ፥ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል አድርጋችሁ ከረከሳችሁ፥ ታስቆጡትም ዘንድ በጌታ በአምላካችሁ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ከሠራችሁ፥ ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ለምስክርነት እጠራለሁ፥ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትኖሩባትም። ጌታም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ ጌታ በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። በዚያም ማየትም ሆነ መስማት፥ መብላት ሆነ ማሽተት የማይችሉትን፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። ነገር ግን ከዚያ ጌታ አምላካችሁን ትሻላችሁ፥ በሙሉ ልባችሁ በሙሉ ነፍሳችሁም የፈለጋችሁት እንደሆን ታገኙታላችሁ፤ ይህም ሁሉ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ስትጨነቁ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ትመለሳላችሁ፥ ቃሉንም ትሰማላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተዋችሁም፥ አያጠፋችሁምም፤ ለአባቶቻችሁ የገባውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም። “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጊዜ ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። እናንተን ከእሳት ውስጥ ሆኖ እንደ ተናገረው፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት መኖር የቻለ፥ ሌላ ሕዝብ ከቶ አለን? ወይስ በፈተና፥ በተአምራት፥ በድንቅ፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራም ኃይል፥ በዐይናችሁ ፊት ጌታ አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ፥ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? ጌታም አምላካችሁ እንደሆነ እንድታውቁ ይህ ለእናንተ ተገልጧል፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። ያስተምራችሁ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፥ በምድርም ላይ ታላቁን እሳቱን አሳያችሁ፥ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ።። አባቶቻችሁን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ከእናንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብጽ አወጣችሁ። ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ፥ ከእናንተ የበረቱትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊታችሁ እንዲያስወጣ፥ እናንተንም እንዲያስገባ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው። እንግዲህ፥ ጌታ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቁ፥ በልባችሁም ያዙት። ለእናንተ፥ ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም ይሆን ዘንድ፥ ጌታ አምላካችሁ ለዘለዓለም በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዛችሁን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቁ።” ከዚህ በኋላ ሙሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞች በመለየት ከለለ፤ ይህንንም ማድረጉ ትናንት ከትናንት በስቲያም ከዚህ ቀድሞ ጠላትነት ሳይኖረው፥ ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ፥ ገዳዩ ይሸሽባቸው ዘንድ፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት እንዲኖር ነው። ከተሞቹም ለሮቤል ነገድ በምድረ በዳ በደልዳላ ስፍራ ያለ ቤጼር፥ ለጋድም ነገድ በገለዓድ ያለ ራሞት፥ ለምናሴም ነገድ በባሳን ያለ ጎላን ነበሩ። ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት ያኖራት ሕግ ይህች ናት። ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ምስክርና ሥርዓት፥ ሕጎችም እነዚህ ናቸው። ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ በኋላ ድል በነሱት፥ በሐሴቦን ተቀምጦ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፥ በቤተፌዖር አንጻር ባለው ሸለቆ በዮርዳኖስ ማዶ ያወጃቸው። እነርሱም የእርሱን ምድርና እንዲሁም በዮርዳኖስ ምሥራቅ የምትገኘውን ባሳንን ይገዛ የነበረውን የሌላውን አሞራዊ ንጉሥ የዖግን ምድር ወረሱ። በአርኖን ወንዝ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ እስከ ሲሪዮን ተራራ፥ ይህም ሔርሞን ድረስ፥ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ከፒስጋ ተራራ በታች ያለውን ዓረባ ሁሉ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ወሰዱ። ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሕግና ሥርዓት ስሙ። ጌታ አምላካችን በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ጌታ ይህችን ቃል ኪዳን ከአባቶቻችን ጋር ብቻ ሳይሆን ያደረገው ዛሬ በዚህ በሕይወት ካለነው ከእኛ ከሁላችንም ጋር ነው። በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ጌታ ፊት ለፊት አናገራችሁ። እናንተ በእሳቱ ምክንያት ፈርታችሁ፥ ወደ ተራራውም አልወጣችሁምና፤ በዚያን ጊዜ፥ እኔ የጌታን ቃል ልነግራችሁ፥ በጌታና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “ ‘ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ። “ ‘ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። “ ‘በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፥ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነኝና አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም። ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን አደርጋለሁ። “ ‘የጌታን የአምላክህ ስም በከንቱ አትጥራ፥ ጌታ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሳይቀጣው አይቀርምና። “ ‘ጌታ አምላክህ እንዳዘዘህ፥ እንድትቀድሰው፥ የሰንበትን ቀን ጠብቅ። ስድስት ቀን ሥራ፥ ሥራህንም ሁሉ አከናውን፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ አምላካችሁ ሰንበት ነው፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም አገልጋይህም፥ አገልጋይትህም፥ በሬህም፥ አህያህም፥ ከብትህም ሁሉ፥ ወይም በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ፥ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፥ አንተ እንደምታርፍ ሁሉ አገልጋይህና አገልጋይትህ እንዲያርፉ። አንተም በግብጽ ባርያ እንደ ነበርህ አስታውስ፥ ጌታ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ። “ ‘ጌታ አምላክህ እንዳዘዘህ፥ ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ፥ አባትህንና እናትህን አክብር። “ ‘አትግደል። “ ‘አታመንዝር። “ ‘አትስረቅ። “ ‘በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “ ‘የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፥ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም አገልጋዩንና አገልጋይቱን፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ንብረት ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።’ “እነዚህን ቃሎች ጌታ በተራራው ላይ ለጉባኤአችሁ ሁሉ በእሳትና በደመና፥ በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ ሆኖ፥ በታላቅ ድምፅ ተናገረ፥ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጠኝ። “ተራራው በእሳት ይነድ በነበረበት ወቅት ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፥ እናንተ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች ሽማግሌዎቻችሁም ሁሉ፥ ወደ እኔ ቀረባችሁ፥ እንዲህም አላችሁ፦ ‘እነሆ፥ አምላካችን ጌታ ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፥ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔር ከሰው ተነጋግሮ ሰውም በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል። ይህች ታላቂቱ እሳት ታቃጥለናለችና፥ እንግዲያውስ አሁን ለምን እንሞታለን? እኛ የአምላካችንን የጌታን ድምፅ ደግመን ከሰማን እንሞታለን። ከሥጋ ለባሽ ሁሉ፥ እኛ እንደ ሰማን፥ በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወቱ የኖረ ማን ነው? አንተ ቅረብ፤ አምላካችን ጌታ የሚለውን ሁሉ ስማ፤ አምላካችን ጌታም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እናደርገዋለን።’ “በተናገራችሁኝም ጊዜ ጌታ የእናንተን ቃል ጽምፅ ሰማ፤ ጌታም አለኝ፦ ‘የዚህን ሕዝብ ነገር፥ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ፤ የተናገሩህ ሁሉ መልካም ነው። እኔንም ለመፍራት ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ ለመጠበቅ፥ እንዲህ ያለ ልብ ምነው ሁልግዜ በኖራቸው! ለእነርሱ ለልጆቻቸውም ለዘለዓለም መልካም በሆነላቸው ነበር! አሁንም ሂድና፦ “ወደ ድንኳናችሁ ተመለሱ” ብለህ ንገራቸው። አንተ ግን እዚህ እኔ አጠገብ ቁም፤ እኔ በምሰጣቸው ምድር እነዚህን በመጠበቅ እንዲኖሩ፥ ሕግጋቴን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቶቼን ሁሉ እነግርሃለሁ።’ “ጌታ አምላካችሁ እንዳዘዛችሁ ለማድረግ ጠንቃቃ ሁኑ፤ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። በሕይወት እንድትኖሩ፥ መልካምም እንዲሆንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ ጌታ አምላካችሁ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ። “ጌታ አምላክህ በርስትነት በሚሰጥህ ምድር እንድትጠብቃት እንዳስተምርህ ያዘዘኝ ትእዛዝ፥ ሕግና ሥርዓት ይህች ናት። አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም፥ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ፤ ጌታ አምላክህን ፈርተህ እኔ ለአንተ ያዘዝሁትን፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፥ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ፤ እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ! መልካም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ ጌታ እንደ ተናገረ፥ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር፥ እጅግ እንድትበዛ በጥንቃቄ ጠብቅ። “እስራኤል ሆይ፥ ስማ! ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኃይልህ ውደድ። ዛሬ እኔ የማዝህ እነዚህን ቃላትም በልብህ አኑር። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ሆነ፥ ስትነሣም ንገራቸው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፥ በዐይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንህ። በቤትህም መቃኖች፥ በቅጽርህም በሮች ላይ ጻፈው። “ጌታ አምላክህ ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ፥ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደ ማለላቸው ምድር ባስገባህ ጊዜ፥ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልቆፈርካቸውም የተቆፈሩ ጉድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም የወይን ተክልና የወይራ ዛፎች፥ ስትበላና ስትጠግብ፥ በዚያን ጊዜ ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን ጌታ እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። ጌታ እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፥ በስሙም ማል። በዙሪያህ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተል። በመካከልህ ያለው ጌታ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና፥ የአምላክህ የጌታ ቁጣው እንዳይነድብህ፥ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ። “ ‘በማሳህ’ እንደ ፈተናችሁት ጌታ አምላካችሁን አትፈታተኑት። ለእናንተ ያዘዘውን የጌታ የአምላካችሁን ምስክሩን፥ ሥርዓቱንም፥ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ያዙ። መልካም እንዲሆንልህ፥ ጌታም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርሷን እንድትወርስ በጌታ ፊት ትክክልና መልካሙን አድርግ። ይህም፥ ጌታ እንደሰጠህ ተስፋ፥ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ በማሳድድ ነው። “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፥ ‘አምላካችን ጌታ ያዘዛችሁ ምስክርነቶች፥ ሥርዓት፥ ፍርድስ ምንድነው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ አንተም ልጅህን እንዲህ ትለዋለህ፥ ‘በግብጽ የፈርዖን ባርያዎች ነበርን፤ ጌታም በጽኑ እጅ ከግብጽ አወጣን፥ ጌታም በግብጽና በፈርዖን በቤቱም ሁሉ ላይ፥ በዓይናችን እያየን፥ ታላቅና አሰቃቂ፥ ምልክት ተአምራትም አደረገ። ከዚያም ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር አምጥቶን ሊያስገባንና ሊሰጠን ከዚያ አወጣን። ዛሬም በሕይወት እንዳኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን ጌታን እንድንፈራ፥ እነዚህንም ሥርዓቶች ሁሉ እንድንፈጽም ጌታ አዘዘን። እርሱም እንዳዘዘን በጌታ አምላካችን ፊት እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ለመፈጸም ብንጠነቀቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።’ “ጌታ አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከአንተ የበለጡትን እና የበረቱትን ሰባቱን አሕዛብ፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን ባስወጣልህ ጊዜ፥ ጌታ አምላክህም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና ድል በምትነሣበት ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፥ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፥ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፥ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ፤ እኔን እንዳይከተል፥ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ ያኔ የጌታ ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም አድቅቁት፥ የእነርሱንም አሼራ ሰባብሩ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። “ለጌታ አምላክህ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ፥ ጌታ አምላክህ ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ እንድትሆን መረጠህ። ጌታ የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፥ ይልቁንም እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁ፤ ነገር ግን ጌታ ስለ ወደዳችሁ፥ አባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አወጣችሁ። አንተም ጌታ አምላካችሁ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ፥ ለሚወዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደሆነ እወቅ፤ የሚጠሉትን በማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፥ ለሚጠላው አይዘገይም፥ በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። እንግዲህ እንድታደርገው ዛሬ ያዘዝኩህን ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፍርድ በጥንቃቄ ጠብቅ። “እንዲህም ይሆናል፥ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ጌታ አምላካችሁ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ዘላለማዊ ፍቅር ለአንተም ይጠብቅልሃል፥ ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ እንዲሁም የምድርህንም ፍሬ፥ እህልና ወይንህን፥ ዘይትህንም፥ በከብትም ብዛት በበግም መንጋ አብዝቶ ይባርክልሃል። ከሕዝቦች ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፥ ወንድ ይሁን ወይም ሴት በሰውህና በከብትህም ዘንድ መካን አይኖርብህም። ጌታም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፥ የምታውቀውንም ክፉውን የግብጽ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ግን ያመጣባቸዋል። ጌታ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን ሕዝቦች ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፥ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። “በልብህም፦ ‘እነዚህ ሕዝቦች ከእኔ ይበልጣሉ፤ እንዴትስ አድርጌ አስወጣቸዋለሁ?’ ብለህ፥ ልትፈራቸው አይገባም፥ ነገር ግን ጌታ አምላካችሁ በፈረዖንና በግብጽ ሁሉ ያደረገውን አስብ፥ ዓይንህ ያየችውን ታላቅን መቅሠፍት፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ ጌታ አምላክህ ሲያስወጣህ የጸናችውን እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ፥ እንደዚሁ ሁሉ ጌታ አምላክህ አንተ በምትፈራቸው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደርጋል። ደግሞም ጌታ አምላካችሁ የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል። ጌታ አምላክህ፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና በእነርሱ የተነሣ ልትደናገጥ አይገባም። ጌታ አምላካችሁ እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊት እንዳይበዙብህ፥ እነርሱን በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይቻልህም። ጌታ አምላካችሁ ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ሁከት ላይ ይጥላቸዋል። ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም ተቋቁሞህ በፊት ሊቆም አይችልም። የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ አትመኝ፥ በጌታ አምላካችሁም ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። እንደ እርሱም ለጥፋት የምትሆን እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም። “በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንድትበዙም፥ ጌታም ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱአት፥ ዛሬ እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ ለማድረግ ተጠንቀቁ። ጌታ አምላክህ ሊያስጨንቅህ፥ ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ፥ በልብህ ያለውን ያውቅ ዘንድ ሊፈትንህ፥ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስታውስ። ሰው የሚኖረው በእንጀራ ብቻ ሳይሆን ከጌታ አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር ሊያሳውቅህ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን፥ አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም። እንግዲህ ሰው ልጁን እንደሚገሥፅ፥ እንዲሁም ጌታ እግዚአብሔር አንተን እንደሚገሥጽህ በልብህ አስተውል። እርሱን በመፍራትና የእርሱንም መንገድ በመከተል፥ የጌታ የአምላክህን ትእዛዞች ጠብቅ። ጌታ አምላክህ ወደ መልካም ምድር፥ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች፥ ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፥ የስንዴና ገብስ፥ የወይንና በለስ ዛፍ እንዲሁም ሮማን፥ የወይራ ዛፍና ማር ወደ ሞሉባት ምድር፥ ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት፥ አንዳችም ወደማታጣባት ምድር፥ ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፥ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር ያስገባሃል። ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ፥ ስለሰጠህም ስለመልካሚቱ ምድር ጌታን አምላክህን ትባርካለህ። “ዛሬ እኔ አንተን የማዘውን ትእዛዞቹንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ፥ ጌታ አምላክህን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። በልተህ በምትጠግብበት፥ መልካምም ቤት ሠርተህ በምትኖርበት ጊዜ፥ የከብቶችህና የበጎችህ መንጋ፥ ብርህና ወርቅህም፥ እንዲሁም ያለህ ሁሉ በበዛልህ ጊዜ፥ ልብህ እንዳይታበይና፥ ከግብጽም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ ጌታን አምላክህን እንዳትረሳ፤ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከዓለት ድንጋይም ውኃን ያፈለቀልህን፥ በመጨረሻም መልካም ነገር ሊያደርግልህ፥ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን፥ በልብህም፦ ‘ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ’ እንዳትል፥ አስብ። ባለጸጋ እንድትሆን ኃይልና ብርታት የሰጠህ ጌታ አምላክህ መሆኑን አስታውስ፤ ይህም ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ ከቀድሞ አባቶችህ ጋር በመሐላ የገባውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ ነው። ጌታ አምላክህንም ብትረሳና፥ ባዕዳን አማልክት ብትከተል ብታመልካቸውም ብትሰግድላቸውም፥ ፈጽሞ እንደምትጠፉ ዛሬውኑ አበክሬ አስጠነቅቅሃለሁ። የጌታ የአምላካችሁን ቃል ስላልሰማችሁ፥ ጌታ ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው እንደ አሕዛብ ሁሉ እንዲሁ እናንተም ትጠፋላችሁ። “እስራኤል ሆይ፥ ስማ! ከአንተ የበለጡትንና የበረቱትን አሕዛብ፥ እስከ ሰማይም ድረስ የተመሸጉትን ታላላቅ ከተሞች ለመውረስ እንድትገቡ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገረዋለህ። ስለ እነርሱም፥ ‘በዔናቅ ልጆች ፊት ማን መቆም ይችላል?’ ሲባል የሰማኸው፥ አንተም የምታውቃቸው፥ ግዙፍና ረጃጅም ሕዝቦች የዔናቅ ልጆች ናቸው። እንደሚበላ እሳት ሆኖ በፊትህ ዛሬ የሚያልፈው ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን እወቅ፥ እርሱ ያጠፋቸዋል፥ በፊትህም ያዋርዳቸዋል፤ ጌታ ተስፋ እንደሰጠህ አንተም ታሳድዳቸዋለህ፥ በፍጥነትም ታጠፋቸዋለህ። “ጌታ አምላክህ ከፊትህ ካስወጣቸው በኋላ፥ በልብህ፥ ‘እንድንወርሳት ወደዚች ምድር ጌታ ያስገባኝ በጽድቄ ምክንያት ነው’ አትበል፤ ጌታ እነዚህን ሕዝቦች ከፊትህ ያስወጣቸው ስለ ኃጢአታቸው ነው። ምድራቸውን እንድትወርስ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፥ ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ ሕዝቦች ኃጢአት ምክንያትና፥ ለአባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብ፥ ጌታ የማለላቸውን ቃል እንዲፈጸም ነው። እንግዲህ አንተ ልበ ደንዳና ሕዝብ ነህና ጌታ አምላክህ ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳልሆነ እወቅ። “ጌታ አምላክህን በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቆጣኸው፥ ከግብጽ ምድር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ እዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በጌታ ላይ እንዳመፃችሁ አስታውስ፥ አትርሳም። በኮሬብም የጌታን ቁጣ ቀሰቀሳችሁ፥ ጌታም ሊያጠፋችሁ እስኪነሳ አስቆጣችሁት። የድንጋዩን ጽላቶች፥ ጌታ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የፈጸመባቸውን ጽላቶች፥ ለመቀበል ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር፤ እህል አልቀመስኩም፥ ውኃም አልጠጣሁም። ጌታም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ፥ ተሰብስባችሁ በነበረበትም ቀን ጌታ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የነገራችሁ ቃል ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር። ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊትም በኋላ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች፥ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች፥ ጌታ ሰጠኝ። “ከዚያም ጌታ፥ ‘ተነሥ፥ ከዚህ ፈጥነህ ውረድ፥ ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ክፉ ነገር በማድረግ ረክሰዋል፤ ፈጥነው ካዘዝኋቸው መንገድ ፈቀቅ ብለዋል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስልም ለራሳቸው ሠርተዋል’ አለኝ። “ደግሞም ጌታ እንዲህ አለኝ፥ ‘ይህ ሕዝብ ልበ ደንዳና ሕዝብ እንደሆነ አይቼአለሁ፤ አጠፋቸው ዘንድ፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስስ ዘንድ ተወኝ፥ አንተንም ከእነርሱ የበረታና የበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ።’ “ስለዚህ ተመልሼ ከተራራው ወረድሁ፥ ተራራውም በእሳት ይነድድ ነበር፤ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላቶች በሁለቱ እጆቼ ነበሩ። ተመለከትሁም፥ እነሆ፥ አምላካችሁን ጌታ በድላችሁ ነበር፥ ለእናንተም ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ሠርታችሁ ነበር፤ ጌታ ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ፈቀቅ ብላችሁ ነበር። ሁለቱንም ጽላቶች ያዝሁ፥ ከሁለቱም እጆቼ ጣልኋቸው፥ በዓይናችሁ ፊት ሰበርኳቸው። ከዚህም በኋላ እንደገና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እህል ሳልቀምስና ውኃ ሳልጠጣ በጌታ ፊት በግንባሬ ተደፍቼ ቆየሁ። ይህንንም ያደረግኹት ስለ ሠራችሁት ኃጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቆጣት በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ ነበር። እግዚአብሔር ሊያጠፋችሁ በመነሳቱ ከቁጣውና ከመዓቱ የተነሣ ፈራሁ። ጌታ ግን ልመናዬን ደግሞ ሰማኝ። ጌታ አሮንንም እጅግ ተቆጥቶ ሊያጠፋው ስለ ነበር፥ በዚያን ጊዜ ስለ አሮንም ደግሞ ጸለይሁ። የሠራችሁትንም ጥጃ ምስል፥ ኃጢአት ያደረጋችሁበትንም ወሰድሁ፥ በእሳትም አቃጠልሁት፥ አደቀቅሁትም፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨሁት፥ ትቢያውንም ከተራራ በሚወርድ ወንዝ ጣልሁት። “እንደገና በታቤራ፥ በማሳህም፥ በቂብሮት ሐታዋም ጌታን አስቆጣችሁት። ጌታም፥ ‘ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ’ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በጌታ በአምላካችሁ ቃል ላይ ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ለቃሉም አልታዛችሁም። እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በጌታ ላይ ዓመፀኞች ነበራችሁ። “አጠፋችኋለሁ፥ ብሎ ጌታም ስለ ተናገረ፥ በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በጌታ ፊት ወደቅሁ። በጌታም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ ‘ጌታ አምላኬ ሆይ፥ በታላቅነትህ የተቤዠኸውን፥ በጠነከረችውም እጅ ከግብጽ ያወጣኸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። ባርያዎችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብንም አስብ፥ የዚህን ሕዝብ ደንዳንነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት፥ እኛን ከእርሷ ያወጣህባት ምድር ሰዎች፥ ጌታ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያስገባቸው ስላልቻለ፥ ስለ ጠላቸውም፥ ወደ ምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ እንዳይሉ። እነርሱም በታላቅ ኃይልህ በተዘረጋውም ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና።” በዚያን ጊዜ ጌታ እንዲህ አለኝ፥ “እንደ ቀድሞ ዓይነት ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርበህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ። በሰበርሃቸውም በቀድሞዎቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች በእነዚህ ጽላቶች እጽፋለሁ፥ በታቦቱም ውስጥ ታደርጋቸዋለህ።” “እኔም ከግራር እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደ ቀድሞዎቹም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፥ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። ዐሥርቱን ቃላት ጌታ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገራችሁ ተሰብስባችሁበት በነበረበት ቀን፥ ቀድሞ ተጽፈው እንደነበረው በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፥ እነርሱንም ጌታ ለእኔ ሰጠኝ። ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፥ ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፥ ጌታም እንዳዘዘኝ በዚያ ይገኛሉ።” እስራኤላዊያንም ከብኤሮት ብኔያዕቃን ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም እዚያ ሞቶ፥ እዚያው ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፥ ከጉድጎዳም ወደ ውኃ ፈሳሾች ምድር ወደ ዮጥባታ ተጓዙ። በዚያን ጊዜ የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከም፥ እርሱንም ለማገልገል በጌታ ፊት እንዲቆም፥ በስሙም እንዲባርክ ጌታ እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ። ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ጌታ ርስቱ ነው። “እኔም፥ ከዚህ ቀደም እንዳደረኩት፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ተቀመጥሁ፥ በዚህም ጊዜ ጌታ ደግሞ ሰማኝ፤ ጌታ ሊያጠፋህ አልወደደም። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘ተነሥ፥ ለአባቶቻቸውም ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር እንዲገቡ እንዲወርሱአትም፥ ሕዝቡን ምራ።’” “እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ ጌታ አምላክህ ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔርን እንድትፈራው፥ በመንገዱም ሁሉ እንድትሄድ፥ ጌታ አምላክህንም እንድትወደው፥ በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ እንድታመልከው፥ መልካም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የጌታን ትእዛዝና ሥርዓት እንድትጠብቅ ነው። እነሆ፥ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርሷም ያለው ሁሉ የጌታ የአምላክህ ነው። ብቻ ጌታ ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዶአል፥ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መረጠ። እንግዲህ እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ከእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፥ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ፥ ኃያልም፥ የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ ጉቦም የማይቀበል ነው። ወላጁን ላጣና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ ስደተኛውንም ስለሚወድ ምግብና ልብስ ይሰጠዋል። ስለዚህ፥ እናንተ በግብጽ አገር ስደተኞች ነበራችሁና፥ ስደተኛውን ውደዱ። ጌታ እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ፥ ከእርሱም አትነጠል፥ በስሙም ማል። ዐይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቅና የሚያስፈሩ ነገሮችን ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱ አምላክህ ነው። አባቶችህ ሰባ ሰው ሆነው ወደ ግብጽ ወረዱ፤ አሁን ግን ጌታ አምላክህ ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ።” “እንግዲህ ጌታ አምላክህን ውደድ፤ ግዴታውን፥ ሥርዓቱን፥ ሕጉንና ትእዛዙን ሁልጊዜ ጠብቅ። የጌታ አምላክህን ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፥ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደ ሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤ በግብጽ መካከል፥ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፥ በግብፃውያን ሠራዊት፥ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፥ እናንተን ባሳደዱአችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና ጌታ ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤ ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፥ ለእናንተ ያደረገላችሁን፤ የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተሰቦቻቸው፥ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም። የእናንተ ዐይኖች ግን ጌታ ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።” “ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፥ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው ጌታ ሊሰጣቸው በማለላቸው፥ በዚያች ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር ረጅም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፥ የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብጽ ምድር አይደለችም። ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፥ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፥ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። ይህች ምድር ጌታ እግዚአብሔር የሚንከባከባት፥ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የጌታ የአምላክህ ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።” “ጌታ አምላክህን በመውደድ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል፥ በታማኝነት ብትጠብቁ፥ እህልህን፥ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ። በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም። ተጠንቀቁ! ተታላችሁ ሌሎች አማልክትን እንዳታመልኩ፤ እንዳትሰግዱላቸውም። የጌታም ቁጣ በላያችሁ እንዳይነድ፤ እርሱም ዝናብ እንዳይከለክላችሁ፤ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም ጌታ ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ።” “እነዚህን ቃሎቼን፥ በልባችሁና በአእምሮአችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፥ በግምባራችሁም ላይ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ ቤት ስትቀመጥ፥ መንገድ ስትሄድ፥ ስትተኛና ስትነሣ ስለዚህ አጫውታቸው። በቤትህ መቃኖችና በግቢህ በሮች ላይ ጻፋቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ፥ ጌታ ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።” “አምላካችሁን ጌታን ትወዱ ዘንድ፥ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፥ ከዚያም ጌታ እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፥ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ። በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፥ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው ባሕር ይደርሳል። ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ ጌታ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።” “እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤ በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፥ መርገሙ ደግሞ፥ የጌታ የአምላካችሁን ትእዛዞች የማትፈጽሙ፥ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ለመከተል እኔ ከማዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው።” “ልትወርሳት ወደምትሄድባት ምድር ጌታ አምላክህ በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፥ መርገሙን ደግሞ በጌባል ተራራ ላይ ታሰማለህ። እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ ማዶ ፀሓይ በምትጠልቅበት አቅጣጫ ካለው መንገድ በስተ ምዕራብ በዓረባ በሚኖሩ የከነዓናውያን ምድር ውስጥ ከጌልገላ ፊትለፊት፥ በሞሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ አይደለምን? አምላካችሁ ጌታ በሚሰጣችሁ ምድር ትገቡባትና ትወርሷት ዘንድ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ስለሆነ፥ ምድሪቱን ወርሳችሁ በምትኖሩባት ጊዜ፥ ዛሬ በፊታችሁ እኔ ያስቀመጥኳቸውን ሥርዓቶችና ሕጎች ሁሉ ለመፈጸም ትጉ።” “የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ፥ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፥ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዓቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው። ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረጅሙ ተራሮች፥ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ አምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የ ‘አሼራ’ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቆራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።” “በዚያ ዓይነት አካሄድ ጌታ አምላካችሁን አታምልኩ። ነገር ግን ጌታ አምላካችሁ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፥ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ ትሻላችሁ፤ ወደ እዚያም ስፍራ ትሄዳላችሁ። እዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፥ አሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፥ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፥ የከብት መንጋችሁን እና የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አቅርቡ። በዚያም በጌታ በአምላካችሁ ፊት ትበላላችሁ፤ ጌታ አምላካችሁ እናንተን በባረከበት፥ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተሰቦችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።” “ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፥ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና ጌታ አምላካችሁ ወደ የሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፥ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። ጌታ አምላካችሁም ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁን ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፥ አሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፥ እንዲሁም ለጌታ የተሳላችሁትን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። እዚያም እናንተ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፥ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በጌታ በአምላካችሁ ፊት ሐሤት አድርጉ።” “የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፥ ጌታ በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝህን ሁሉ ጠብቅ።” “ሆኖም ጌታ አምላክህ በሚሰጥህ መጠን፥ በየትኛውም ከተማህ፥ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኩላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ። በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። የእህልህን፥ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን አሥራት፥ ወይም የቀንድ ከብት፥ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፥ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፥ ወይም የእጅህን ስጦታ፥ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። አምላክህ ጌታ በሚመርጠው ስፍራ አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፥ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፤ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፥ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይልሃል። በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።” “አምላክህ ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፥ ሥጋ አምሮህ፥ ‘ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ’ በምትልበት ጊዜ፥ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። ስሙን ለማኖር ጌታ እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፥ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፥ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ። ሚዳቋ ወይም ድኩላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ መብላት ይችላል። ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፥ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። በጌታ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፥ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው። ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ ጌታ ወደ የሚመርጠው ስፍራ ሂድ። የሚቃጠል መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንም ደሙንም በጌታ አምላክህ መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በጌታ አምላክህ መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። በአምላክህ በጌታ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፥ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘለዓለም መልካም እንዲሆንላችሁ፥ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።” “የምትወሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ ጌታ ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፥ ‘እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ’ ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። አምላክህን ጌታ በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ ጌታ የሚጸየፈውን ሁሉንም ዓይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳን ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።” “እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ በእርሱ ላይ ምንም አትጨምር፤ ከእርሱም አንዳች ነገር አትቀንስ።” “ከመካከልህ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ተነሥቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ፥ የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፥ ‘አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው’ ቢልህ፥ አምላካችሁን ጌታ በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወዱት እንደሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ ጌታ ሊፈትናችሁ ነውና፥ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም አላሚውን አትስሙ። አምላካችሁን ጌታን ተከተሉት፤ ፍሩት፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ታዘዙት፤ አገልግሉት፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ። ከግብጽ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በጌታ ላይ ሊያስታችሁ ተናግሮአልና፥ አምላካችሁ ጌታ እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጎአልና፥ ያ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከላችሁ አስወግዱ።” “የአባትህ፥ ወይም የእናትህ ልጅ ወንድምህ፥ ወንድ ልጅህ፥ ወይም ሴት ልጅህ ወይም የምትወዳት ሚስትህ ወይም የቅርብ ወዳጅህ አንዳቸው ቢሆኑ በምሥጢር ሊያስትህ ቢሞክር፥ አንተ ወይም አባቶችህ የማታውቁትን በቅርብም ሆነ በሩቅ፥ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላው ድረስ በዙሪያህ ያሉትን የአሕዛብ አማልክት እናምልክ ቢልህ፥ እሺ አትበለው፤ ወይም አታዳምጠው፤ አትራራለት፤ አትማረው፤ ወይም አትሸሽገው። ያለ ማመንታት ግደለው፤እርሱንም ለመግደል በመጀመሪያ የአንተ እጅ፥ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይነሣ። የባርነት ምድር ከሆነው ከግብጽ ካወጣህ ከጌታ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ፈልጎአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም በማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አይደረግም።” “አምላክህ ጌታ እንድትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፥ ክፉ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፥ ‘ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ’ በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፥ ጉዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፥ በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው፤ ከተማይቱን ከነ ሕዝቧና ከነ ቀንድ ከብቷ ፈጽሞ ደምስስ። በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፥ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ ለጌታ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘለዓለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ። ጌታ ከብርቱ ቁጣው እንዲመለስ እርም ነገሮች በእጅህ አይገኝ፤ እርሱ ምሕረቱን ያሳይሃል፤ ይራራልሃል፤ ለአባቶችህ በመሐላ ተስፋ በሰጠው መሠረት ቍጥር ህን ያበዛዋል። ይህም የሚሆነው፥ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ከጠበቅህ፥ በጌታ በአምላክህ ፊት ትክክል የሆነውን ካደረግህ፥ የጌታ የአምላክህን ቃል ከሰማህ ነው።” “እናንተ የጌታ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትቦጭቁ፤ የጭንቅላታችሁን ጠጉር አትላጩ፤ ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለጌታ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት ጌታ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል። “ርኩስ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። የምትበሏቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው፤ በሬ፥ በግ፥ ፍየል፥ አጋዘን ሚዳቋ፥ ቦራይሌ፥ የሜዳ ፍየል፥ ዋላ፥ ድኩላንና ብሖር፤ ሰኰናው ስንጥቅ የሆነውን፥ ለሁለት የተከፈለውንና የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ። ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እንስሳት መካከል ግመልን፥ ጥንቸልንና ሽኮኮን አትብሉ፤ ምክንያቱም እነርሱ ቢያመሰኩሁም፥ ሰኰናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሶች ናቸው። ዐሣማም፥ ምንም እንኳ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኩህ፥ እርሱ ለእናንተ ንጹሕ አይደለም፤ የእነዚህን ሥጋ አትብሉ፤ ጥምባቸውንም አትንኩ። “በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፥ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። ክንፍና ቅርፊትም የሌለውን ግን አትብሉ፤ ለእናንተ ርኩስ ነው። “ንጹሕ የሆነውን ወፍ ሁሉ ትበላላችሁ። የሚከተሉትን ግን አትበሉም፦ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጪ፥ ጭልፊት፥ ጭላትና መሰሎቻቸው፥ ቁራና መሰሎቹ፤ ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋልና መሰሎቹ፥ ጉጉት፥ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥንብ አንሣ አሞራ፥ እርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳና መሰሎቹ፥ ጅንጅላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው። ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው። ንጹሕ የሆነውን ማናቸውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ትበላላችሁ። “አንተ ግን ለጌታ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ እንዲበላ ልትሰጠው ትችላለህ፤ ወይም ለውጭ አገር ሰው ልትሸጠው ትችላለህ። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል። “በየዓመቱ ከእርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። ምንጊዜም ጌታ እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፥ የወይን ጠጅና የዘይትህን አሥራት፥ የቀንድ ከብትህን፥ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፥ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ። ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ቢርቅብህና ጌታ አምላክህ የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ አሥራትህን ወደ እዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልክ፥ አሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ ጌታ አምላክህ ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ ማለትም በሬና በግ፥ የወይን ወይም የብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተሰብህ በጌታህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፤ አንተና ቤተሰብህም ሐሤትም ታደርጋላችሁ። በከተሞችህ የሚኖሩ ሌዋውያን ድርሻ ወይም ርስት ስለ ሌላቸው እነርሱን ችላ አትበል። “በየሦስት ዓመቱም መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል አሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፥ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፥ አንተንም አምላክህ ጌታ በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው። “በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት ታደርጋለህ። አፈጻጸሙም የሚከተለው ነው፦ አበዳሪ ሁሉ ለባልጀራውም ያበደረውን ይተዋል፥ ጌታ የዕዳ ምሕረት አውጆአልና፥ ያበደረውን ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው። ለባዕድ ያበደርከውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማናቸውንም ዕዳ ግን ተወው። “ነገር ግን አምላክህ ጌታ ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፥ በመካከልህ ድኻ አይኖርም። ይህ የሚሆነውም ለጌታ ለእግዚአብሔር ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ብትጠነቀቅ ነው። አምላክህ ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ይባርክሃል፥ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ ከማንም ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ ማንም ግን አንተን አይገዛህም። “አምላክህ ጌታ በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፥ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አትጨክንበት፤ ወይም እጅህን አትሰብስብበት። ይልቅስ እጅህን ፍታለት፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ አበድረው። ‘ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቧል’ የሚል ክፉ ሐሳብ አድሮብህ፥ በችግረኛ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፥ እርሱም በአንተ ላይ ወደ ጌታ ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ! ይልቅስ ያለ ቅሬታ በለጋስነት በልግስና ስጠው፤ ከዚህም የተነሣ ጌታ አምላክህ በሥራህ ሁሉና እጅህ ባረፈበት በማናቸውም ነገር ይባርክሃል። መቼም ቢሆን በምድር ላይ ችግረኛና ድኻ መኖሩ ስለማይቀር፤ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞችህ፥ ለድኾችና ለችግረኖች እጅህን እንድትዘረጋ አዝሃለሁ። “ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፥ በሰባተኛው ዓመት ነጻ አውጣው። ነጻ በምታወጣው ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው። ከመንጋህ፥ ከአውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው፤ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። አንተም ራስህ በግብጽ ባርያ እንደ ነበርክና ጌታ እግዚአብሔር እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝሃለሁ። “ነገር ግን አገልጋይህ፥ አንተንና ቤተሰብህን ከመውደዱና ከአንተም ጋር ደስተኛ ከመሆኑ የተነሣ፥ ከአንተ መለየት አልፈልግም ቢልህ፥ ጆሮውን ከቤትህ መዝጊያ ላይ በማስደገፍ በወስፌ ትበሳዋለህ፤ ከዚያም ዕድሜ ልኩን አገልጋይህ ይሆናል። በሴት አገልጋይህም ላይ እንደዚሁ አድርግ። የአገልጋይህን የስድስት ዓመት አገልግሎቱ፥ አንድ የቅጥር ሠራተኛ ከሚሰጠው አገልግሎት ዕጥፍ ነውና፤ እርሱን ነጻ ማውጣቱ ከባድ መስሎ አይታይህ። ጌታ እግዚአብሔር በምታደርገው ነገር ሁሉ ይባርክሃል። “የቀንድ ከብት፥ የበግና የፍየል መንጋዎችህን ተባዕት በኩር ሁሉ ለጌታ ለእግዚአብሔር ትቀድሳለህ። የበሬህን በኩር አትሥራበት፤ የበግህንም በኩር አትሸልት፤ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ አንተና ቤተሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በጌታ ፊት ትበሉታላችሁ። አንድ እንስሳ እንከን ያለው፥ አንካሳ ወይም ዕውር፥ ወይም ደግሞ ማናቸውም ዓይነት ከባድ ጉድለት ያለበት ከሆነ ለጌታ ለእግዚአብሔር አትሠዋው፤ በየከተሞችህም ትበላዋለህ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ ይበላዋል። ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። “አምላክህ ጌታ በአቢብ ወር ከግብጽ በሌሊት ስላወጣህ፥ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የጌታ ፋሲካ አክብርበት። ጌታ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለጌታ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርገህ ሠዋ። የቦካውን ቂጣ ከእርሱ ጋር አትብላ፥ ከግብጽ አገር በችኮላ ስለ ወጣህ ከግብጽ አገር የወጣህበትን ቀን በዕድሜህ ሁሉ ታስብ ዘንድ ይህን ቂጣ፥ እርሱም የመከራን እንጀራ፥ ሰባት ቀን ከእርሱ ጋር ብላ። በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማናቸውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቆይ አታድርግ። “አምላክህ ጌታ በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤ ነገር ግን አምላክህ ጌታ ለስሙ መጠሪያ በመረጠው ስፍራ ብቻ፥ ፀሐይ ስትጠልቅ ከግብጽ በወጣህበት ቀን የወጣህበትን ሰዓት በመጠበቅ በዚያ ፋሲካን ሠዋ። ሥጋውን ቀቅለህ አምላክህ ጌታ በሚመርጠው ቦታ ብላው፤ በማግስቱ ወደ ድንኳኖችህ ተመለስ። ስድስት ቀን ያልቦካ ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛውም ቀን ለአምላክህ ለጌታ ጉባኤ ይሁን፤ በዚያ ቀን ሥራ አትሥራበት። “እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ትቆጥራለህ፤ ከዚያም በኋላ ጌታ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን፥ በፈቃድህ የምታመጣውን ስጦታ በማቅረብ የመከር በዓል አምላክህ ጌታን አክብር። አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፥ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፥ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች ጌታ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። አንተም በግብጽ ባርያ እንደ ነበርክ አስታውስ፤ ይህንንም ሥርዓት በጥንቃቄ ጠብቅ። “ከአውድማህና ከመጥመቂያህ ፍሬህን በሰበሰብህ ጊዜ የዳስ በዓል ሰባትን ቀን ትጠብቃለህ። አንተም፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባርያህና ሴት ባርያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፥ ድሀ አደግና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ። አምላክህ ጌታ በፍሬህ ሁሉ በእጅህም ሥራ ሁሉ ይባርክሃልና ጌታ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለጌታ ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፥ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል። “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንዶች ሁሉ በቂጣ በዓል፥ በመከርንና በዳስ በዓል፥ በአምላክህ በጌታ ፊት እርሱ በመረጠው ስፍራ ይታዩ፥ በጌታም ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ። አምላክህ ጌታ በረከት እንደሰጠው መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ። “አምላክህ ጌታ በሚሰጥህ ከተሞች ሁሉ ለየነገዶችህ ዳኞችንና አለቆችን ሹም፤ እነርሱም ሕዝቡን በቅን ፍርድ ይዳኙ። ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጉቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦም አትቀበል። በሕይወት እንድትኖርና ጌታ እግዚአብሔር የሚሰጥህን ምድር እንድትወርስ ትክክለኛ፥ እውነተኛውንም ፍርድ ብቻ ተከተል። “ለአንተ በምትሠራው በአምላክህ በጌታ መሠዊያ አጠገብ ከማናቸውም ዛፍ የማምለኪያ ዐፀድ አድርገህ አትትከል። ጌታ እግዚአብሔርም የሚጠላውን የማምለኪያ ሐውልት ለአንተ አታቁም። “በአምላክህ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነውና፥ ከበሬ ወይም ከበግ ነውር ወይም ጉድለት ያለበትን ለአምላክህ ለጌታ አትሠዋ። “አምላክህ ጌታ በሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ አብሮህ የሚኖር ወንድ ወይም ሴት ኪዳኑን በማፍረስ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈጽም ቢገኝ፥ ትእዛዜንም በመተላለፍ ባዕዳን አማልክትን ያመለከ፥ ለእርሱም ማለትም ለፀሓይ ወይም ለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ፥ አንተም ይህ መደረጉን ብትሰማ፥ ነገሩን በጥንቃቄ መርምር፤ የተባለውም እውነት ከሆነና እንዲህ ያለው አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ዘንድ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፥ ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸመውን ወንድ ወይም ሴት ወደ ከተማ ደጅ ወስደህ፥ ያን ሰው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። ሞት የሚገባው ሰው፥ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት ይገደል፤ ነገር ግን በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ማንም ሰው አይገደል። ሲገደልም መጀመሪያ የምስክሮቹ እጅ፥ ቀጥሎም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይረፍበት፤ እንዲሁም ክፋቱን ከመካከልህ አስወግድ። “በአንድ የነፍስ ግድያ ዓይነትና በሌላ፥ በአንድ ዓይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፥ ወይም በአንድ የክስ ዓይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጉዳይ ቢነሣ፥ ከአቅምህ በላይ የሆነ ጉዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፥ ተነሥተህ አምላክህ ጌታ ወደ መረጠው ስፍራ ውጣ፤ ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ ተሾመው ፈራጅ መጥተህ ትጠይቃለህ፥ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። አንተም ጌታ በመረጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም፤ ለመፈጸም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ። በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። ከሚነግሩህ ቀኝም ግራም አትበል። አምላክህን ጌታን ለማገልገል በዚያ የሚቆመውን ካህኑን ወይም ፈራጁን ባለመታዘዝ የሚዳፈር፥ ያ ሰው ይሙት፥ ከእስራኤልም መካከል ክፋትን አስወግድ፥ ሕዝቡም ሁሉ ሰምቶ ይፈራል፥ ከዚያም ወዲያ አይዳፈርም። “አምላክህ ጌታ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፥ በምትወርሳትና በምትቀመጥባት ምድር፥ ‘በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፥ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ’ ብትል፥ ጌታ እግዚአብሔር የሚመርጠውን ንጉሥ በላይህ ልታነግሥ ትችላለህ፤ የምታነግሠውም ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንጂ፥ እስራኤላዊ ወንድምህ ያልሆነውን ባዕድ በላይህ አታንግሥ። ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ፤ ወይም ደግሞ ፈረሰኞች ለማብዛት ሕዝቡን ወደ ግብጽ አይመልስ፤ ጌታ፥ ‘በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ’ ብሎአችኋልና። ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፤ ብዙ ብርና ወርቅም አያግበስብስ። “በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ በጥቅል መጽሐፍ ለራሱ ይጻፍ። አምላኩን ጌታን ማክበር ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዓት በጥንቃቄ እንዲከተል ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያንብበው፤ እርሱና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ረጅም ዘመን እንዲገዙ፥ ከሕጉ ቀኝም ግራም አይበል፤ ራሱን ከሌሎች ወንድሞቹ በላይ የተሻለ አድርጎ አይኩራ።” “ሌዋውያን ካህናት፥ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋር የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ድርሻቸው ነውና ለጌታ በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ። በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት ጌታ ርስታቸው ነው። “በሬ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፥ አገጩንናና ሆድ ዕቃውን ነው። የእህልህን፥ የአዲሱን ወይንህንና የዘይትህን በኵራት እንዲሁም ከበጎችህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጉር ትሰጣለህ፤ በጌታ ስም ቆሞ ለዘለዓለም ያገለግል ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጦአል። “በእስራኤል ካሉት ከተሞችህ መካከል፥ አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከየትኛውም በፍጹም ፈቃድ ጌታ ወደ መረጠው ስፍራ ቢመጣ፥ በጌታ ፊት ቆመው እንደ የሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ፥ እርሱም በአምላኩ በጌታ ስም ያገልግል። ከቤተሰቡ ንብረት ሽያጭ ላይ ገንዘብ ቢቀበል እንኳን ባልንጀሮቹ ከሚያገኙት ጥቅም እኩል ይካፈላል። “አምላክህ ጌታ ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፥ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል። በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ፥ ወይም መተተኛ፥ ሞራ ገለጭ፥ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቁል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነውና፥ ከእነዚህ አጸያፊ ልምዶች የተነሣም ጌታ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል። በአምላክህ በጌታ ፊት ነውር አልባ ሁን።” ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፥ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ ጌታ እግዚአብሔር አልፈቀደልህም። “አምላክህ ጌታ ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱን አድምጥ። በኮሬብ ጉባኤ በተደረገበት ዕለት፥ ‘እንዳልሞት የጌታ የእግዚአብሔርን ድምፅ አልስማ፤ እንዲህ ያለውንም አስፈሪ እሳት ደግሜ አልይ’ ብለህ አምላክህን ጌታን የጠየቅኸው ይህን ነውና። ጌታ እንዲህ አለኝ፤ ‘የተናገሩት መልካም ነው፤ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌን በአፉ አደርጋለሁ፤ የማዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል። ማንም ሰው ነቢዩ በስሜ የሚናገረውን ቃሌን ባይሰማ፥ እኔ ራሴ በተጠያቂነት እይዘዋለሁ። ነገር ግን እንዲናገር እኔ ያላዘዝሁትን ቃል በድፍረት በስሜ የሚናገርም ሆነ በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።’ አንተም በልብህ፥ ‘በጌታ ያልተነገረውን መልእክት እንዴት ማወቅ እንችላለን?’ ብትል፥ ነቢዩ በጌታ ስም የተናገረው ካልተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ ካልተገለጸ፥ መልእክቱ ጌታ የተናገረው አይደለም። ያ ነቢይ በድፍረት ተናግሮታልና እርሱን አትፍራው።” “አምላክህ ጌታ ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ ጌታ እግዚአብሔር በሚደመስሳቸውና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፥ አምላክህ ጌታ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፥ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ትለያለህ። ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ ጌታ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፥ በሦስት ትከፈፍላለህ። በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመግባት ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው። አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ሊቆርጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፥ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፥ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል። አለበለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፥ መንገዱ ረጅም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና፥ መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል። ሦስት ከተሞችን እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው። “ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት ጌታ እግዚአብሔር ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቷን ሁሉ ሲሰጥህ፥ ጌታን እግዚአብሔርን እንድትወድና ምንጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ እምትጠብቅ ከሆነ፥ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። ጌታ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስና በሚፈሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ። “ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፥ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፥ ቢገድለውና፥ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፥ የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት። አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ። “አምላክህ ጌታ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ለአንተ በሚተላለፍልህ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልጀራህን የድንበር ምልክት አታንሣ። “በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፥ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ጉዳዩ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት መረጋገጥ አለበት። ተንኰለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ቢከስ፥ ሁለቱም ወገኖች በጌታ ፊት፥ በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ። ፈራጆችም ጉዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክሩ በወንድሙ ላይ የሐሰት ክስ አቅርቦ ከተገኘ፥ በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በእርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከልህ ከቶ አይደገምም። ዓይንህም አትራራለት፥ ሕይወት በሕይወት፥ ዐይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥ ይመለስ።” “ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ጌታ ከአንተ ጋር ነውና፥ ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፥ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሠራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው። ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፥ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሕዝቡ ይናገር፤ እንዲህም ይበል፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤ ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ አብሮአችሁ የሚወጣው ጌታ እግዚአብሔር ነውና።’ “አለቆቹም ለሠራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ ‘አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል። ወይን ተክሎ ገና ያልበላለት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ወይኑን ሌላ ሰው ይበላዋል። ሚስት አጭቶ ያላገባት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ ያለበለዚያ በጦርነቱ ይሞትና ሌላ ሰው ያገባታል።’ “ከዚያም አለቆቹ፥ ‘የሚፈራ ወይም ልቡ የሚባባ ሰው አለን? የወንድሞቹም ልብ እንዳይባባ ወደ ቤቱ ይመለስ’ በማለት ጨምረው ይናገሩ። አለቆቹ ለሠራዊቱ ተናግረው ሲያበቁ፥ አዛዦችን በሠራዊቱ ላይ ይሹሙ። “አንድን ከተማ ለመውጋት በምትዘምትበት ጊዜ፥ አስቀድመህ ለሕዝቧ የሰላም ጥሪ አስተላልፍ፤ ከተቀበሉህና ደጃቸውን ከከፈቱልህ በከተማዋ ውስጥ ሕዝብ ሁሉ ገባርህ ይሁን፤ ያገልግልህም። ዕርቀ ሰላምን ባለ መቀበል ውጊያን ከመረጡ፤ ከተማዪቱን ክበባት። አምላክህ ጌታ አሳልፎ በእጅህ በሰጠህ ጊዜ፥ በውስጧ ያሉትን ወንዶች በሙሉ በሰይፍ ግደላቸው። ነገር ግን ሴቶቹን ሕፃናትን፥ እንስሳቱንና በከተማዪቱ ውስጥ የሚገኘውን ማናቸውንም ነገር በምርኮ ለራስህ አድርግ አምላክህ ጌታ ከጠላቶችህ የሚሰጥህን ምርኮ ልትጠቀምበት ትችላለህ። እንግዲህ የአካባቢህ አሕዛብ ከተሞች ባልሆኑትና ከአንተ እጅግ ርቀው በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ላይ የምታደርገው ይኸው ነው። “አምላክህ ጌታ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በአሕዛብ ከተሞች ውስጥ፥ እስትንፋስ ያለውን ነገር አታስተርፍ፤ ኬጠያዊውን፥ አሞራዊውን፥ ከነዓናዊውን፥ ፌርዛዊውን፥ ኤዊያዊውን፥ ኢያቡሳዊውን አምላክህ ጌታ ባዘዘህ መሠረት ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ አለበለዚያ አማልክታቸውን በሚያመልኩበት ጊዜ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሁሉ ታደርግ ዘንድ ያስተምሩሃል፤ በጌታ በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ትሠራለህ። “አንድን ከተማ ተዋግተህ ለመያዝ የረጅም ጊዜ ከበባ ካደረግህ፥ ዛፎቹን በመጥረቢያ ጨፍጭፈህ አታጥፋ፤ የእነርሱን ፍሬ መብላት ትችላለህና አትቁረጣቸው፤ ከበህ የምታጠፋቸው የሜዳ ዛፎች ሰዎች ናቸውን? ለመብል የማይሆኑትን የምታውቃቸውን ዛፎች ታጠፋቸዋለህ፥ ትቆርጣቸዋለህ፥ እስክታሸንፋትም ድረስ በምትዋጋህ ከተማ ላይ ምሽግ ትመሽጋለህ።” “አምላክህ ጌታ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር አንድ ሰው ተገድሎ ሜዳ ላይ ቢገኝና ገዳዩም ማን እንደሆነ ባይታወቅ፥ ሽማግሌዎችህና ዳኞችህ ወጥተው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት አንሥቶ በአቅራቢያው እስከሚገኙት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ። ከዚያም ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ በጣም ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችና ቀንበር ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፥ ከዚያ በፊት ታርሶ ወይም ተዘርቶበት ወደ የማይታወቅ ወራጅ ውሃ ወዳለበት ሸለቆ ያምጡት። በዚያ ሸለቆም የጊደሪቱን አንገት ይስበሩት፤ እንዲያገለግሉና በጌታ ስም እንዲባርኩ፥ በማንኛውም የክርክርና የጥቃት ጉዳዮች ሁሉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ፥ አምላክህ ጌታ መርጦአቸዋልና የሌዊ ልጆች ካህናቱ ወደ ፊት ይቅረቡ። ከዚያም ሬሳው በተገኘበት አቅራቢያ ባለችው ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሁሉ፥ በሸለቆው ውስጥ፥ አንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ። እንዲህም ብለው ይናገሩ፦ ‘እጆቻችን ደም አላፈሰሱም፤ ድርጊቱ ሲፈጸምም ዐይኖቻችን አላዩም። ጌታ ሆይ፤ ስለ ተቤዥኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፤ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ።’ ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል። አንተም በጌታ ፊት ቀና የሆነውን ስታደርግ፥ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከልህ ታስወግዳለህ። “ከጠላቶችህ ጋር ጦርነት ልትገጥም ወጥተህ አምላክህም ጌታ እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶህ በማረክህ ጊዜ፥ ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፥ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ። ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጉሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቆረጥ። ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፥ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፥ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች። በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፥ ወደምትፈልገው እንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና አትሽጣት ወይም እንደ ባርያ አትቁጠራት። “አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፤ አንደኛዋን የሚወዳት፥ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፥ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኩር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥ ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፥ የብኩርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኩር ልጅ ገፎ፥ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ፥ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤ ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኩርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኃይል መጀመሪያ ነውና፤ የብኩርና መብት የእርሱ ነው። “አንድ ሰው፥ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፥ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤ ‘ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው’ ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው። ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ ክፉውንም ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል። “አንደ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና በድኑ በዕንጨት ላይ ቢሰቀል፤ በድኑን በዕንጨት ላይ እንደ ተሰቀለ አታሳድረው፤ ምክንያቱም በዕንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና፤ አምላክህ ጌታ ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ በዚያኑ ዕለት ቅበረው።” “የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፥ ወደ ወንድምህ መልሰው። ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘህ ወደ ቤትህ ትገባለህ፥ ወንድምህ እስኪፈልገው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣል፥ ለእርሱም ትመልሰዋለህ። እንደዚሁም ሁሉ በአህያው ወይም በልብሱ ታደርጋለህ፥ ወንድምህ በጠፋው ማንኛውም ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፥ ቸል ልትለውም አይገባህም። የወንድምህ አህያ ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ከእርሱ ጋር ሆነህ በማንሣት እርዳው እንጂ ቸል አትበለው። “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፥ ይህን የሚያደርግ በጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው። “በመንገድ ስትሄድ አንዲት ወፍ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ጫጩቶችዋንም ሆነ እንቁላሎችዋን ዐቅፋ የተቀመጠችበትን ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ወፍ ከነጫጩቶችዋ አትውሰድ። ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም እንዲረዝም፥ ጫጩቶቹን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ግን ልቀቃት። “አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፥ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፥ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት። “የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ። “በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ። “ሱፍና በፍታ ተቀላቅሎ አብሮ የተሠራ ልብስ አትልበስ። “በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ። “ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ ከደረሰባትም በኋላ ቢጠላት፥ የነውር ነገር አውርቶ፦ ‘እኔ ይህችን ሴት ሚስት አድርጌ አገባኋት፥ በደርስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም’ ብሎ በክፉ ስም ቢያሳጣት፥ የብላቴናይቱ አባትና እናት የድንግልናዋን ምልክት ወስደው በበሩ በአደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፥ የብላቴናይቱም አባት ሽምግሌዎቹን፦ ‘እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት እርሱም ጠላት፥’ እነሆም፦ ‘በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም’ ብሎ የነውር ነገር አወራባት፥ የልጄም ምልክት ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ። የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ያንን ሰው ወስደው ይግረፉት፥ በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል በማስከፈል ለብላቴናይቱም አባት ይስጡት፥ እርሷም ሚስቱ ሆና ትኑር፥ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም።” “ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ በብላቴናይቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥ ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፥ ይህን በማድረግም ክፉውን ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ። “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለቱም ይገደሉ። በዚህም ዓይነት ይህን ክፉ ነገር ከእስራኤል አስወግዱ። “ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፥ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፥ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዬውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፥ በዚህም ዓይነት ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ። “ነገር ግን አንድ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ አግኝቶ በማስገደድ ቢደፍራት፥ ይህን ድርጊት የፈጸመው ሰው ብቻውን ይገደል። እርሷ ለሞት የሚያበቃ በደል ስላልፈጸመች በልጃገረዲቱ ላይ ምንም ነገር አይድረስባት፤ ይህ ዓይነቱ ጉዳይ አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ከሚገድል ሰው አድራጎት ጋር የሚመሳሰል ነው። በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ብትጮህም የሚደርስላት አልነበረም። “ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ ወስዶም ቢደርስባት፥ ቢያገኙትም፥ ያ የደረሰባት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፥ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይችልም። “ማንም ሰው የአባቱ ሚስት ከሆነችው ከማንኛይቱም ሴት ጋር ግንኙነት በማድረግ አባቱን አያሳፍር።” “የተኰላሸ ወይም ብልቱም የተሰለበ ሰው ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። “ከጋብቻ ውጪ የተወለደ ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ፤ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። “አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማናቸውም የእርሱ ዘር፥ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳን ቢሆን ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። ምክንያቱም ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በጉዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ይኖር የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምም አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዝተውት ነበር። ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር በለዓምን መስማት አልፈለገም፥ ጌታ እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ። በዘመንህ ሁሉ ለዘለዓለም ሰላምና ልማት ለእነርሱ አትሻ። “ኤዶማዊ ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፥ ግብፃዊውንም በአገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ ጌታ ጉባኤ ይግቡ።” “ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። ከእናንተ መካከል ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፥ እዚያው ይቆይ። በመሸም ጊዜ በውኃ ይታጠብ፥ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ። “ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። ከመሣሪያህም ጋር መቆፈሪያ ያዝ፥ በሜዳም በተቀመጥህ ጊዜ ትምስበታለህ፥ ዞረህም ከአንተ የወጣውን በአፈር ትከድነዋለህ። ጌታ እግዚአብሔር ሊያድንህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥ በሰፈርህ መካከል ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ፥ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሰፈርህ የተቀደስ ይሁን።” “ከጌታው ኮብልሎ ወደ አንተ የመጣውን ባርያ ለጌታው አሳልፈህ አትስጥ። ከደጆችህ በሚመርጣት በአንዲቱ በሚወድዳት ስፍራ ከአንተ ጋር በመካከልህ ይቀመጥ፥ አንተም አታስጨንቀው። “ከእስራኤል ወንድ ወይም ሴት የቤተጣዖት አመንዝራ አይሁን። ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የአመንዝራይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ቤት አታቅርብ፥ ሁለቱም በጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና። “ለወንድምህ በወለድ አታበድር፥ የብር ወይም የእህል ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ። ለእንግዳው በወለድ አበድረው፥ ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ እንዲባርክህ ለወንድምህ በወለድ አታበድር። ለእግዚአብሔር ለጌታ ስእለት በተሳልህ ጊዜ እግዚአብሔር ጌታ ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆንብሃልና ከመክፈል አታዘገይ። ባትሳል ግን ኃጢአት የለብህም። በአፍህ የተናገርኸውን ለእግዚአብሔር ለጌታ በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። “ወደ ባልንጀራህ ወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ፥ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አትውሰድ። ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ፥ ወደ አልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታስገባ።” “አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባት በኋላ፥ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፥ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፥ ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍቺ ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰዳት ወይም ቢሞት፥ ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፥ የረከሰች በመሆኗ እንደገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በጌታ ፊት አስጸያፊ ነው። ጌታ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኃጢአት አታምጣ። “አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፥ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቆይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት። “ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም ቢሆን፥ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና። “አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባርያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ፈንጋዩ ይሙት። በዚህ ዓይነት ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። “የለምጽ ደዌን በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል። ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ ጌታ እግዚአብሔር በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ። “ማናቸውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ። አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ። ሰውየው ድኻ ከሆነ፥ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት። መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በጌታ በእግዚአብሔር ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቆጠርልሃል። “ድኻና ችግረኛ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፥ ከከተሞችህ በአንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤ የሠራበትን ሒሣብ በዕለቱ፥ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጉጉት ይጠባበቀዋል። ያለበለዚያ ወደ ጌታ ይጮኽና ኃጢአት ይሆንብሃል። “አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፥ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል። “ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ። አንተም በግብጽ ባርያ እንደ ነበርህና ጌታ እግዚአብሔር ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። “የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፥ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፥ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። ጌታ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። የወይራ ዛፍህን ፍሬ በምታራግፍበት ጊዜ በየቅርንጫፉላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰህ አትሂድ፤ ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። የወይን ተክልህን ፍሬ ስትሰበስብ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለስበት፤ የቀረውን ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። በግብጽ ባርያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።” “በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፥ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፥ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ። በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ። ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፥ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር። “ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ የሟቹ ሚስት ከቤተሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ። ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፥ ሴትዮዋ በከተማዋ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፥ ‘የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈጸመልኝም’ ትበላቸው። ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፥ ‘እርሷን ላገባት አልፈልግም’ ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፥ የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፥ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና ‘የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል’ ትበል። የዚያም ሰው የዘር ሐረግ በእስራኤል ዘንድ፥ ‘ጫማው የወለቀበት ቤት’ ተብሎ ይታወቃል። “ሁለት ሰዎች ቢደባደቡ፥ የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል መጥታ፥ እጅዋን ዘርግታ ብልቱን ብትይዘው፥ እጅዋን ቁረጠው፤ አትራራላት። “በከረጢትህ ውስጥ ከባድና ቀላል የሆኑ ሁለት የተለያዩ ሚዛኖች አይኑሩህ። በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መስፈሪያዎች አይኑሩህ። ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፥ ትክክለኛና የታመነ ሚዛንና መስፈሪያ ይኑርህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽመውንና የሚያምታታውን ሁሉ ይጸየፈዋልና። “ከግብጽ በወጣህ ጊዜ፥ አማሌቅ በመንገድ በአንተ ላይ ያደረገብህን አስታውስ፤ ደክመህና ዝለህ በነበርህበት ጊዜ፥ በጉዞ ላይ አግኝተውህ፥ ከኋላ ያዘግሙ የነበሩትን ሁሉ ገደሉ፤ እግዚአብሔርንም አልፈሩም። ጌታ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ዙሪያ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ ባሳረፈህ ጊዜ፥ ከሰማይ በታች ያለውን የአማሌቅን መታሰቢያ መደምሰስን፥ ይህንን አትርሳ።” “ጌታ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፥ ስትወርሳትና ስትኖርባት፥ ጌታ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ሰብል በኲራቱን ሁሉ ውሰድ፤ በቅርጫትም ውስጥ አድርገው፤ ከዚያም ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ጌታ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። በዚያም ወቅት ለሚያገለግለው ካህን፥ ‘ጌታ ለእኛ ሊሰጠን ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደገባሁ ዛሬ በጌታ እግዚአብሔር ፊት እናገራለሁ’ በለው። “ካህኑም ቅርጫቱን ከእጅህ ተቀብሎ በጌታ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ለፊት ያስቀምጠዋል። አንተም በጌታ እግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፥ ‘አባቴ ከቦታ ወደ ቦታ በመዞር የሚኖር ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋር ወደ ግብጽ ወርዶ እዚያ ተቀመጠ። ከዚያም ታላቅ፥ ኀያልና ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ። ግብፃውያን ግን አንገላቱን፤ አሠቃዩንም፤ በባርነት የጭካኔ ቀንበር ጫኑብን። ከዚያ በኋላ የአባቶቻችን አምላክ ወደ ሆነው ወደ ጌታ ጮኽን፤ ጌታም ጩኸታችንን ሰማ። ጉስቁልናችንን፥ ድካማችንንና መጨቆናችንን ተመለከተ። ከዚያም በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በታላቅ ድንጋጤ፥ በተአምራትና በድንቅም ጌታ ከግብጽ አወጣን። ወደዚህም ስፍራም አስገብቶን ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን። እነሆም፥ ጌታ ሆይ፥ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን ፍሬ በኵራት አቅርቤአለሁ።’ አንተም በአምላክህ በጌታ ፊት አኑረው፥ በአምላክህም በጌታ ፊት ስገድ። አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ ጌታ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ። “አሥራት በምታወጣት በሦስተኛው ዓመት ከምርትህ አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፥ ለሌዋዊው፥ ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፥ ከዚያ በኋላ ለጌታህ እግዚአብሔር እንዲህ በል፦ ‘ከቤቴ የተቀደሰውን ድርሻ ወስጄ በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት ለሌዋዊው፥ ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም። በኀዘኔም ጊዜ ከተቀደሰው ክፍል ላይ ምንም አልበላሁም፤ ወይም ንጹህ ባልነበርኩ ጊዜ ያነሣሁትም ሆነ ለሙታን ያቀረብሁት መባ የለም፤ ለአምላኬ ጌታ ድምጽ ታዝዣለሁ፤ ያዘዝኸኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ። ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለእኛ የሰጠኸንን ይህችን ማርና ወተት የምታፈሰውን ምድር ለአባቶቻችን በቃልህ እንደገባኸው መሓላ መሠረት ባርክ።’ “አምላክህ ጌታ ይህን ሥርዓትና ሕግ እንድትጠብቅ ዛሬ ያዝሃል፤ ስለዚህ አንተም በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ ለመፈጸም ተጠንቀቅ። ጌታ አምላክህ እንደሆነ በመንገዱም እንደምትሄድ፥ ሥርዓቱን፥ ትእዛዙንና ሕጉን እንደ ምትጠብቅና እንደምትታዘዝለት ተናግረሃል። ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ ዛሬ ተናግሮአል፤ ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋናና በስም፥ በክብር ከፍ እንደሚያደርግህና እርሱም እንደ ተናገረ ለጌታ እግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ አደረገህ።” ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሕዝቡን እንዲህ ብለው አዘዙ፦ “ዛሬ የማዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ ጌታ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራም ምረጋቸው። የአባቶችህ አምላክ ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ጌታ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገር፥ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው። ዮርዳኖስን እንደ ተሻገርህም፥ ዛሬ ባዘዝሁህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ ላይ ትከላቸው፤ በኖራም ምረጋቸው። እዚያም ለጌታ ለእግዚአብሔር የድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ በድንጋዮቹም ላይ ማናቸውንም የብረት መሣሪያ አታሳርፍባቸው። ካልተጠረበም ድንጋይ የጌታን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፥ ለጌታ እግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት። የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዋበት፥ በዚያም ብላ፤ በጌታም እግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ግልጽ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ።” ሙሴና ሌዋውያን ካህናትም ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ አሉ፦ “እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብለህ አድምጥ! አንተ ዛሬ የጌታ እግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል። ጌታ እግዚአብሔርን ታዘዝ፤ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ጠብቅ።” ሙሴም በዚያኑ ዕለት ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ “ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ። ለእርግማንም በዔባል ተራራ ላይ መቆም የሚገባቸው ሮቤል፥ ጋድ፥ አሴር፥ ዛብሎን፥ ዳንና ንፍታሌምም ናቸው። ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦ “‘በጌታ ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘የባልንጀራውን የድንበር ምልክት ከቦታው የሚያንቀሳቅስ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘ዐይነ ስውሩን በተሳሳተ መንገድ የሚመራ፥ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘በመጻተኛው፥ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ሚስት ገልቧልና የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘ከማናቸውም እንስሳ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው እኅቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘ከዐማቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘በድብቅ ባልንጀራውን የሚገድል የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘ንጹሕን ሰው ለመግደል ጉቦ የሚቀበል የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል። “‘የዚህን ሕግ ቃሎች በመፈጸም የማይጸና የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ፥ ‘አሜን!’ ይበል።” “ለጌታ እግዚአብሔር ፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፥ ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ብትታዘዝ፥ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይደርሱሃል፤ አይለዩህምም። “በከተማ ትባረካለህ፥ በዕርሻህም ትባረካለህ። “የማሕፀንህ ፍሬ፥ የምድርህ አዝመራ፥ የእንስሳትህ ግልገሎች፥ የከብትህ ጥጃ፥ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ። “እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካል። “ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ። “ጌታ በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ። “ጌታ በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ ላይ በረከቱን ይልካል። ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል። “የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፥ እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። የምድር አሕዛብም ሁሉ በጌታ ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። ጌታ ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ ብልጽግና ይሰጥሃል። ጌታ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ይሰጣል፤ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርካል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም። ጌታም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትታዘዝ በጥንቃቄም ብትጠብቅ ሁልጊዜም በላይ እንጂ እታች አትሆንም። ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል። “ነገር ግን ለጌታ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፥ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦ “በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ። “እንቅብህና ቡሓቃህ የተረገሙ ይሆናሉ። “የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህ መንጋ፥ የበግና የፍየል መንጋ ይረገማሉ። “ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ። “እርሱን በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፥ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ ጌታ ርግማንን፥ ሁከትንና መደናገርን ይልክብሃል። ጌታ ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪያጠፋህ ድረስም ቀሣፊ በሽታ ይልክብሃል። ጌታ እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ በሽታ ንዳድና ዕባጭ፥ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፥ ዋግና አረማሞ ይመታሃል። ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ፥ ናስ፥ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም፥ ብረት ይሆናል። ጌታ የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ እስክትጠፋም ድረስ ይህ ከሰማይ ይወርድብሃል። “ጌታ በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ በሚደርስብህም ነገር ለምድር መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ። ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት መብል ይሆናል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም። በማትድንበት በግብጽ ብጉንጅ፥ በእባጭ፥ በሚመግል ቁስልና በዕከክ ጌታ ያሠቃይሃል። ጌታ በእብደት፥ በዕውርነትና ግራ በማጋባት ይመታሃል። በእኩለ ቀን ዕውር በዳበሳ እንደሚሄደው ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። ዘወትር ትጨቆናለህ፤ ያለማቋረጥም ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም። “ሚስት ለማግባት ታጫለህ፤ ሌላም ሰው ከእርሷ ጋር ይተኛል። ቤት ትሠራለህ፥ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም። በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ አንዳች ግን አትቀምሰውም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ ለአንተም አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚረዳህ ማንም አይኖርም። ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ምንም ለማድረግ አትችልም፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በማለትም ዐይኖችህ ሁልጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ። የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል። ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በማያቋርጥ ጭቆና ትኖራለህ። ዐይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። ጌታ ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጉር በሚዛመት፥ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቁስል ጉልበትህንና እግርህን ይመታሃል። “ጌታ አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል። በዚያም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። ጌታ እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ ድንጋጤ፥ መቀለጃና መዘባበቻ ትሆናለህ። “በእርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል። ወይን ተክለህ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ትል ስለሚበላው ዘለላውን አትሰበስብም ወይም ከወይኑ አትጠጣም። የወይራ ዛፍ በምድርህ ሁሉ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን ዘይቱን አትቀባም። ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ ያንተ አሆኑም። ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ ኩብኩባ ይወረዋል። “በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። እርሱ ያበድርሃል፤ አንተም ትበደረዋለህ። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ። “ጌታ እግዚአብሔርን ስላልታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዓት ስላልጠበቅህ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፥ እስክትጠፋ ድረስ ያሳድዱህማል፥ ይወርሱሃል። በአንተና በዘርህ ለዘለዓለም ለምልክትና ለግርምት ይኖራሉ። ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ ጌታ እግዚአብሔርን በልቡና ደስታና ሐሤት አላገለገልኸውምና፥ ጌታ የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ በራብና በጥማት፥ በእርዛትና በማጣት እስኪያጠፉህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭኑብሃል። ጌታ እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋው የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፥ ከምድርም ዳርቻ ያስነሣብሃል፤ እርሱም ሽማግሌ የማያከብርና ለብላቴና የማይራራ፥ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው። እስክትጠፋም ድረስ የከብትህን ፍሬና የምድርህን ፍሬ ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ የእህል፥ የወይን ወይም የዘይት፥ የከብትህን ጥጃ ወይም የበግና ፍየል መንጋህን አይተውልህም። የምትተማመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪማረኩ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከባል፤ ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወራቸዋል። “ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፥ ከሥቃይ የተነሣ፥ ጌታ እግዚአብሔር የሰጠህን፥ የሆድህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ፥ አቅፋውም ለምትተኛ ለሚስቱ፥ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይሳሳም። ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ምክንያቱም ከተሞችህ ሁሉ ጠላቶችህ ከበው ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ከዚህ በቀር የተረፈው የለም። በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ እግሮችዋ ዐፈር ነክቶት የማያውቁ ሴት ዐቅፋው ለምትተኛው ባሏና በገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆችዋ ላይ ትከፋለች። ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጅንና የምትወልዳቸውን ልጆች ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ እነርሱን ተደብቃ ለመብላት ስትል ነው። “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የጌታ እግዚአብሔርን ስም ባታከብር፥ ጌታ አስፈሪ መቅሠፍት፥ አስጨንቆህ የሚቆይ መዓት መቅሠፍት፥ አሠቃቂና ጽኑ በሽታ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል። ደግሞም የምትፈራውን የግብጽ በሽታ ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ። በተጨማሪም ጌታ በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም በሽታና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል። ለጌታ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዛችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ። ጌታ እናንተን በማበልጸግና ቁጥራችሁን በማብዛት ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ጌታ እናንተን ሲያጠፋችሁና ሲያፈራርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ እንድትወርሱአት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ። “ከዚያም ጌታ ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። በዚያም ጌታ የሚርድ ልብ፥ ፈዛዛ ዐይኖች፥ ደካማም ነፍስ ይሰጥሃል። ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፥ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፥ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ። ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፥ ሲነጋ፥ ‘ይመሽ ይሆን?’ ሲመሽ ደግሞ፥ ‘ይነጋ ይሆን?’ ትላለህ። ከእንግዲህ ወዲያ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም ጌታ በመርከብ ወደ ግብጽ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፥ የሚገዛችሁ ግን አይገኝም።” ጌታ በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች የሚከተሉት ናቸው፦ ሙሴም እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ በዐይኖቻችሁ ፊት በግብጽ ምድር፥ በፈርዖን፥ በአገልጋዮቹ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን አይታችኋል። ዐይኖቻችሁ ከባድ ፈተናዎችን፥ ታምራዊ ምልክቶችንና ታላላቅ ድንቆች አይተዋል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ጌታ የሚያስተውል ልቡና ወይም የሚያዩ ዐይኖች ወይም የሚሰሙም ጆሮች አልሰጣችሁም። አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ስመራችሁ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም። ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው። ወደዚህም ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፥ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ነገር ግን ድል አደረግናቸው። ምድራቸውንም ወርሰን ለሮቤላውያን፥ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን። ስለዚህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወንላችሁ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ። “እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፥ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ፥ በሰፈራችሁም ያለ እንጨትህን የሚቆርጥ ውኃህንም የሚቀዳ መጻተኛ አብረውህ ቆመዋል። እዚህ የቆምኸው ጌታ ዛሬ ከአንተ ጋር ወደሚያደርገውና በመሓላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከጌታህ ከእግዚአብሔር ጋር ትገባ ዘንድ፥ ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ ይሆን ዘንድ፥ አንተም ሕዝቡ መሆንህን፥ በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው። “እኔም ይህን የመሓላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በጌታ ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር እንዲሁም ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው። “በግብጽ ምድር እንዴት እንደ ኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፥ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል። የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከጌታ ከእግዚአብሔር የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ቤተሰብም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መርዘኛና መራራ የሆነ ፍሬ የሚያበቅል አይገኝባችሁ። እንደዚህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፥ በልቡ ራሱን በመባረክ፥ ‘ምንም እንኳ እንደ ልቤ ደንዳናነት ብሄድ ሰላም አለኝ’ ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል። ጌታ በእርሱ ላይ ቁጣውና ቅናቱ ይነድበታል እንጂ ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግም። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ ጌታ ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት ጌታ እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል። “የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና ጌታ ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ። ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው፥ ዐመድም እንደ ሆነች፥ እንዳይዘራባት፥ እንዳይበቅልባትም፥ ማናቸውም ሣር እንዳይወጣባት፥ ጌታ በታላቅ ቁጣና መዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፥ እንደ አዳማና ጺባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥ አሕዛብም ሁሉ፥ ‘ጌታ በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪ ቁጣስ ንዴት ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ ‘የአባቶቻቸው አምላክ ጌታ ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የገባውን ኪዳን ትተዉ፥ ወጥተውም የማያውቋቸውን፥ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም። ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣ ድረስ የጌታ ቁጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ። በቁጣና በመቅሠፍት፥ በታላቅም መዓት ጌታ ከምድራቸው ነቀላቸው፤ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው። ዛሬም በዚያው ይገኛሉ።’ “ምስጢሩ ለአምላካችን ለጌታ ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ እንድንከተል ለዘለዓለም ለእኛና ለልጆቻችን ነው።” “እንዲህም ይሆናል፥ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ በወረደብህ ጊዜ አምላክህ ጌታ በትኖህ በምትኖርበት አሕዛብ መካከል ሆነህ በልብህ አስታውሰህ፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ ጌታ ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥ ጌታ አምላክህ ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከል ጌታ እግዚአብሔር እንደገና ይሰበስብሃል። የፈለስክበት ስፍራ ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ቢሆን እንኳ፥ ጌታ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም መልሶ ያመጣሃል። የአባቶችህ ወደ ሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። ጌታ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወደው፥ በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህ ጌታ የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። ጌታ አምላክህም ይህን ርግማን ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያደርገዋል። አንተም ተመልሰህ ለጌታ ቃል ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝህንም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጋለህ። ጌታ በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደገና በአንተ ደስ ይለዋልና፥ ጌታ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ፥ በሆድህም ፍሬ፥ እንዲሁም በከብትህም ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ያበለጽግሃል። የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ከሰማህ፥ በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ለመጠበቅ፥ በፍጹምም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ ጌታ ወደ አምላክህ ተመለስ። “ዛሬ የምሰጥህ ትእዛዝ እጅግ አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም። ‘ሰምተን እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ ማን ወደ ሰማይ ይወጣልናል?’ እንዳትል፥ በላይ በሰማይ አይደለችም። ደግሞም፥ ‘ሰምተን እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፥ ማን ባሕሩን ይሻገርልናል?’ እንዳትልም፥ ከባሕር ማዶ አይደለችም። ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው። “እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ። ጌታ አምላክህን በመውደድ፥ በመንገዱም በመሄድና ትእዛዙን፥ ሥርዓቱንና ሕጉን በመጠበቅ ያዘዝሁን ካደርግክ፤ በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ ጌታ አምላክም ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል። ልብህ ግን ርቆ አንተም ባትሰማ፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድላቸውና ብታመልካቸው ግን፥ ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ እንድትወርሳትም በምትገባባት ምድር ረጅም ዘመን አትኖርም። ሕይወትንና ሞትን፥ በረከትንና መርገምን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ። ጌታ አምላክህን ውደደው፤ ለቃሉም ታዘዝ፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ። ጌታ ለአባቶችህም ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር የዕድሜህም ዘመን ሕይወትም ማለት ነው።” ሙሴም ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤ “እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ ጌታም ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤ ጌታ አምላክህም ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ ጌታ እንደ ተናገረው ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል። ጌታ የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው እነዚህንም ያጠፋቸዋል። ጌታ እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኳችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ። ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። ጌታ አምላክህም ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።” ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “ጌታም ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፥ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን። ጌታ ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቁረጥ።” ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፥ የጌታን የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፥ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ። ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፥ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፥ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፥ እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በጌታህ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ። ይሰሙና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ። ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።” ጌታ ሙሴን፥ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቧል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ። ጌታም በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ። በዚያች ቀን እቀጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፥ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፥ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ። “እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ። ወተትና ማር ወደምታፈሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፥ ከበለጸጉም በኋላ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል። በዘራቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደ ማልሁላቸው ምድር ሳላስገ ባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳን አስቀድሜ ዐውቃለሁ።” ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው። ጌታም ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፥ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገ ባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው። ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፥ የጌታን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በጌታ በእግዚአብሔር የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤ እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፥ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በጌታ ላይ ዐምፃችኋል፥ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፥ እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፥ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ስለምታስቆጡት በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።” ሙሴም የዚህን መዝሙር ቃል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ፥ ለተሰበሰበው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በጆሮአቸው እንዲህ ሲል አሰማ፦ “ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ። ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይዝነብ፤ ንግግሬ እንደ ጠል ይንጠባጠብ፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ፥ በቡቃያም ላይ እንደሚወርድ ዝናብ፥ የጌታን ስም አውጃለሁ፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ!” “እርሱ ዐለት፥ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፥ የታመነ አምላክ፥ ተንኮል የሌለበት፥ እርሱ ቀጥተኛና ጻድቅ ነው። በእርሱ ፊት ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው። አንተ የማታስተውልና ኀሊና ቢስ ሕዝብ፥ ለጌታ ምላሽህ እንዲህ ነው? እርሱ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና የሠራህ ያጸናህም እርሱ አይደለምን?” “የቀድሞውን ዘመን አስታውስ፤ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፥ አባትህን ጠይቅ፥ እርሱም ያስታውቅሃል፥ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ እነርሱም ይነግሩሃል። ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የሰውን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ። ሕዝቡ የጌታ ድርሻ ነው፥ ያዕቆብም የተለየ ርስቱ ነው።” “በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት በምድረ በዳ አገኘው፥ መከታ ሆነለት፥ ተጠነቀቀለትም፥ እንደ ዐይን ብሌኑም ጠበቀው። ንስር ጎጆዋን ቆስቁሳ፥ በጫጩቶቿም ላይ እንደምትሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ይወስደዋል፥ በክንፎቹም ያዝለዋል። ጌታ ብቻውን መራው፥ ከእርሱም ጋር ባዕድ አምላክ አልነበረም።” “በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፥ የምድሩንም ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ ማር፥ ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው። የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውንም ወተት፥ ከሰቡት በጎችና ፍየሎች ጋር፥ የባሳንንም አውራ በጎች፥ ፍየሎችም፥ ከምርጥ ስንዴ ጋር በላህ፥ ከወይኑም ዘለላ የወይን ጠጅ ጠጣህ።” “ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፥ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፥ የፈጠረውንም አምላክ ተወ፥ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ። በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፥ በርኩሰታቸውም አስቆጡት። አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ። የወለደህን አምላክ ተውህ፥ የፈጠረህን እግዚአብሔር ረሳህ።” “ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቆጡት ጌታ አይቶ ጣላቸው። እርሱም እንዲህ አለ፦ ‘ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸውና፥ ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፥ ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ አያለሁ። አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ በምናምንቴዎቻቸውም አስቆጡኝ፥ እኔም በተናቀ ሕዝብ አስቀናቸዋለሁ፥ በማያስተውል ሕዝብ አስቆጣቸዋለሁ። እሳት ከቁጣዬ ትነድዳለች፤ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፤ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፤ የተራሮችን መሠረትም ታነድዳለች።’” “‘በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ፤ ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ። በሚያቃጥል ንዳድና በራብ ያልቃሉ፤ በወረርሽኝ መቅሠፍት ይጠፋሉ፤ ተናካሽ አውሬዎችን፥ ከሚሳቡ መርዘኛ እባቦችን ጋር እሰድባቸዋለሁ። ወጣት ወንዶችና ሴቶች፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በየመንገዱ ላይ በጦርነት፥ በቤትም ውስጥ በድንጋጤ ያጠፋቸዋል። ፈጽሜ እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ፤’ አልኩ። ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፦ ‘እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ ጌታ ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፥ ስለ ጠላት ትንኮሳ አሰብኩ ።” “ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው። አስተዋዮች ቢሆኑ፥ ይህንን በተገነዘቡ፥ ፍጻሜያቸውንም ባሰቡ ነበር! እርሱ አንባቸው ካልሸጣቸው፥ ጌታም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ እንዴት አንዱ ሺህን ያሳድዳል? ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺህ ያባርራሉ? ጠላቶቻችን እንኳ እንደሚስማሙበት፥ ዓለታቸው እንደ እኛ ዓለት አይደለም። ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ይመጣል፤ ፍሬያቸው በመርዝ የተሞላ፥ ዘለላቸውም መራራ ነው። ወይናቸው የእባብ መርዝ፥ የጨካኝ እፉኝት መርዝ ነው።” “ይህስ በእኔ ዘንድ የተጠበቀ፥ በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን? በቀልና ብድራት መመለስ የእኔ ነው፤ እግራቸው የሚሰናከልበት ጊዜው፥ የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧልና፥ የሚመጣባቸው ፍርድ ይፈጥናል። ጌታ ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ለአገልጋዮቹም ያዝናል። ኃይላቸውም እንደደከመ፥ የታሰረም ሆነ የተለቀቀ እንደሌለ ሲያዩ፥ እርሱም ሕዝቡን እንዲህ ይላል፦ ‘ይታመኑባቸው የነበሩት አምባዎች፥ አማልክቶቻቸው የት ናቸው? እነዚያ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ መለማመኛቸውንም ወይን የጠጡ? እስቲ እነርሱ ይነሡና ይርዱአችሁ! እስቲ መጠጊያም ይሁኑላችሁ!’” “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ እገድላለሁ፤ በሕይወትም አኖራለሁ፤ እኔ አቆስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም። እጄን ወደ ሰማይ ዘርግቼ፥ ለዘለዓለም እኔ ሕያው እንደሆንኩ፥ እምላለሁ። የሚያንጸባርቅ ሰይፌን ከሳልኩ፥ እጄም ለፍርድ ካነሳችው፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እመልሳለሁ። ከተገደሉት ደም፥ ከተማረኩትም ደም፥ ከጠላት አለቆችም ራስ፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፥ ሰይፌም ሥጋ ይቆራርጣል።” “የአገልጋዮቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና፥ እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።” ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ። ሙሴ እነዚህን ቃላት ሁሉ ለመላው እስራኤል አሰምቶ ከጨረሰ በኋላ፥ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህን ሕግ ቃላት በጥንቃቄ መጠበቅ ይችሉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዙ፥ እኔ ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን የምሰጣችሁን ቃላት ሁሉ በልባችሁ አኑሩት። ይህ ነገር ለእናንተ ሕይወታችሁ ነው እንጂ ከንቱ ነገር አይደለም። በዚህም ነገር ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ለመውረስ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።” በዚያም ቀን ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፥ ከዓባሪም ተራራዎች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ነቦ ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት። ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፥ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ። ምክንያቱም ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፥ በቃዴስ በመሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው። ከሩቅ ሆነህ ምድሪቱን ባሻገር ታያለህ፤ ነገር ግን እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደማወርሳት ወደዚያች ምድር አትገባም።” የጌታ ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ሕዝብ የባረከበት ቃለ ቡራኬ ይህ ነው። እንዲህም አለ፦ “ጌታ ከሲና ተራራ መጣ፥ በሴይርም እንደ ንጋት ተገለጠ፥ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ በስተቀኙም ከእሳት ነበልባል ጋር፥ ከአእላፋት ቅዱሳኑም ጋር መጣ። በእርግጥ ሕዝቡን ይወዳል፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጁ ናቸው፤ እነርሱም በእግሮችህ ሥር ይሰግዳሉ፤ መመሪያህንም ከአንተ ይቀበላሉ። ይህ ሙሴ የሰጠን ሕግ፥ የያዕቆብ ጉባኤ ርስት ነው። የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ጋር ሆነው፥ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ፥ እርሱ በይሹሩን ላይ ንጉሥ ነበር።” “ሮቤል በሕይወት ይኑር፥ አይሙት፥ ሰዎቹም በቍጥር አይነሱ።” ስለ ይሁዳም እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አምጣው። እጆቹንም አጠንክርለት፤ ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋም ረዳት ሁነው።” ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦ “ማሳህ በተባለው ቦታ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፥ ቱሚምህን ለሌዊ ስጠው፥ ኡሪምህም ለዚህ ቅዱስ ሰው ነው፤ ለአንት ሲል እናቱንና አባቱን፥ ‘አላየሁም’ ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፥ ቃልህን ላከበረ፥ ቃል ኪዳንህንም ለጠበቀ። ሥርዓትህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፥ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባሉ። ጌታ ሆይ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የጠላቱን አከርካሪ ስበር፤ የሚጠሉትም ዳግመኛ አይነሡ።” ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦ “በጌታ የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጠብቀዋል፤ በትከሻዎቹም መካከል ያርፋል።” ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ “ምድሩ ከጌታ ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ ከሰማያት በሚዘንበው የላቀ ስጦታ፥ ከታችም ከጥልቀት ከሚገኘው ውሃ፥ ከፀሐዩ ሙቀት ከሚገኘው ምርጥ ፍሬ፥ ከወራት መፈራረቅ ከሚገኘው ምርት፥ ከቀደሙትም ከጥንት ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘለዓለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥ በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቁጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ። ለላሞች በኩር ግርማ ይሆናል፥ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፥ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፥ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።” ስለ ዛብሎን ስለ ይሳኮር ነገዶችም እንዲህ አለ፦ “ዛብሎን በመርከብ ስትጓዝ ደስ ይበልህ፤ ይሳኮርም በቤትህ ሆነህ ደስ ይበልህ። የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፥ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።” ስለ ጋድም እንዲህ አለ፥ “ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፥ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፥ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል። በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፥ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፥ የጌታንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።” ስለ ዳንም እንዲህ አለ፥ “ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፥ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።” ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦ “ንፍታሌም በሞገስ ጠግቧል፥ የጌታንም በረከት ተሞልቶአል፥ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።” ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦ “አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፥ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፥ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ። ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፥ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል። “ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ ጌታ ያለ ማንም የለም። መኖሪያህ የዘለዓለም አምላክ ነው፥ የዘለዓለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፥ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፥ ሰማያትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፥ በጌታ የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፥ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።” ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፒስጋ ራስ ወጣ፥ ጌታም እስከ ዳን ድረስ ያለውን የገለዓድን ምድር፥ የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴንም ምድር፥ እስከ ምዕራብም ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፥ ደቡቡንም፥ እስከ ጾዓር ድረስ ያለውንም የዘንባባ ዛፎች ያሉባትን ከተማ የኢያሪኮን ሸለቆ ሜዳ አሳየው። ጌታም፦ “ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፥ በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም” አለው። የጌታ ባርያም ሙሴ እንደ ጌታ ቃል በሞዓብ ምድር ሞተ። በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም። ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ፥ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጉልበቱም አልደነገዘም። የእስራኤልም ሕዝብ የሐዘኑ ጊዜ እስከሚያበቃ ድረስ ለሙሴ በማዘንሠላሳ ቀን በሞዓብ ሜዳ አለቀሱለት። ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፤ ሙሴንም ጌታ እንዳዘዘው አደረጉ። ጌታን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም። በግብጽ ምድር በፈርዖንና በባርያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን እንዲያደርግ ጌታ የላከው፥ እንደ ሙሴ በእስራኤል ሁሉ ፊት ያሳየውን የጸና ክንድ ያሳየ ወይም ያደረገውን አስፈሪ ነገር የፈጸመ ማንም የለም። እንዲህም ሆነ፤ የጌታ ባርያ ሙሴ ከሞተ በኋላ ጌታ የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ባርያዬ ሙሴ ሞቷል፤ እንግዲህ አሁን አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ፥ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ግዛታችሁ ይሆናል። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህምም። ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግም በርታ፤ ባርያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ከእርሱ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአንደበትህ አይለይ፥ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ እንድትጠብቅና እንድታደርገው በቀንም በሌሊትም አሰላስለው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቃናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ ጌታ አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?” ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ “በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም እንዲህ ብላችሁ እዘዙ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር በሦስት ቀን ውስጥ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ።’ ” ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ ጌታ እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ ጌታ አምላካችሁ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የጌታ ባርያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱዋታላችሁም።” እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ ሁሉ እንሄዳለን። በሁሉም ነገር ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ ጌታ አምላክህ ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። በትእዛዝህ የሚያምፅ ሁሉ የምታዝዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰማ፥ እርሱ ይገደል፤ ብቻ ጽና፥ አይዞህ።” የነዌም ልጅ ኢያሱ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ሄዱ፥ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ።” ሄዱም፤ ረዓብም ወደሚሉአት አመንዝራ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። ለኢያሪኮም ንጉሥ እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ።” የኢያሪኮም ንጉሥ እንዲህ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ፦ “አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ።” ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርሷም እንዲህ አለች፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩ በሚዘጋበት ጊዜ ሲመሻሽ ሰዎቹ ወጥተው ሄደዋል፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ትደርሱባቸዋላችሁ።” እርሷ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ እስከሚወስደው መንገድ ድረስ አሳደዱአቸው፤ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተዘጋ። እነርሱም ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ “ጌታ ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ ከእናንተም የተነሣ በፍርሃት መዋጣችንን፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ በፍርሃት እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ጌታ የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ ጌታ አምላካችሁም በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእግዲህ ወዲያ ሰው ሁሉ ሐሞተ ቢስ ሆኖአል። አሁንም፥ እባካችሁ፥ በጌታ ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት ሥሩ፥ አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፥ ነፍሳችንንም ከሞት ታደጉ።” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፦ “ይህን ነገራችንን ለማንም ባትናገሩ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፤ ጌታም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ለአንቺ ቸርነትንና ታማኝነትን እናደርጋለን።” ቤትዋም የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ነበረና፥ እርሷም በቅጥሩ ውስጥ ተቀምጣ ነበር፤ እነርሱንም በመስኮቱ በኩል በገመድ አወረደቻቸው። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ ከዚያም በኋላ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፦ “እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን ማንም ሰው እጁን ቢጭንበት ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። ይህንን ነገራችንን ግን ብትናገሪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።” እርሷም እንዲህ አለች፦ “እንደ ቃላችሁ ይሁን፤” ከዚያም በኋላ በደኅና አሰናበተቻቸው እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “በእውነት ጌታ አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ ከእኛም የተነሣ በአገሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፍርሃት ቀልጠዋል። ” በማግስቱም ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ። ሕዝቡንም እንዲህ ብለው አዘዙ፦ “የአምላካችሁን የጌታን ቃል ኪዳን ታቦቱንና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ እርሱን በመከተል፥ በዚህ መንገድ በፊት አላለፋችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ ታውቃላችሁ። በእናንተና በታቦቱ መካከል ግን ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።” ኢያሱም ሕዝቡን፦ “ነገ ጌታ በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ” አለ። ኢያሱም ካህናቱን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ፤” እነርሱም የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን እንዲያውቁ በዚህ ቀን አንተን በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ከፍ ከፍ ማድረግ እጀምራለሁ። አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት እንዲህ ብለህ እዘዝ፦ ‘በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ።’ ” ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፦ “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የጌታን ቃላት ስሙ” አለ። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደሆነ፥ እርሱም ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ከፊታችሁ ፈፅሞ እንደሚያሳድድ በዚህ ታውቃላችሁ። እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል። እንግዲህ አሁን ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ምረጡ። እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የጌታን ታቦት የተሸከሙ ካህናት የእግሮቻቸው ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።” እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት በሚሻገሩ ጊዜ የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳንስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር። እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሕዝቡ ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ምረጥ፤ እንዲህም ብለህ እዘዛቸው፦ ‘በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው።’” ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች የሾማቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ። ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “በአምላካችሁ በጌታ ታቦት ፊት በዮርዳኖስ መካከል እለፉ፤ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በትከሻው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም። ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፤ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ ‘ለእናንተ እነዚህ ድንጋዮች የሚሰጡት ትርጒም ምንድነው?’ ብለው ሲጠይቁአችሁ፥ እናንተ እንዲህ ትሉአቸዋላችሁ፦ በጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ የሆኑ ናቸው።” የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፤ ጌታም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርዳኖስ መካከል ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው። ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አኖረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። ሙሴም ኢያሱን እንዳዘዘው ሁሉ፥ ጌታ ኢያሱን ለሕዝቡ እንዲነግር ያዘዘው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ነበርና፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ። ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ እያዩ የጌታ ታቦትና ካህናቱ ተሻገሩ። ሙሴም እንዳዘዛቸው የሮቤል ልጆች፥ የጋድም ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእስራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ። አርባ ሺህ ያህል ሰዎች መሣርያ ታጥቀው ለጦርነት በጌታ ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ። በዚያም ቀን ጌታ ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ አደረገው፤ ሙሴንም ይፈሩት እንደ ነበር እንዲሁ ኢያሱን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ፈሩት። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “የምስክሩን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዝ።” ኢያሱም ካህናቱን፦ “ከዮርዳኖስ ውጡ” ብሎ አዘዛቸው። የጌታንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ከዮርዳኖስ መካከል በወጡ ጊዜ፥ የካህናቱም እግር ጫማ ደረቅ መሬት መርገጥ በጀመረ ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ውኃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፥ ቀድሞም እንደ ነበረ ከአፉ እስከ ደፉ ሞልቶ በዳርቻው ሁሉ ፈሰሰ። ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ከዮርዳኖስ ወጡ፥ በኢያሪኮም ዳርቻ በምሥራቅ በኩል በጌልገላ ሰፈሩ። ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አኖራቸው። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን፦ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ሲጠይቁ፥ ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ፦ ‘እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ምድር ላይ ተሻገረ፤’ እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ ጌታ የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። ይኸውም የጌታ እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ፥ አምላካችሁንም ጌታን ለዘለዓለሙ እንድትፈሩ ነው።” እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የከነዓናውያን ነግሥታት ሁሉ፥ ጌታ ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩት ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ከዚያ ወዲያ ሐሞተ ቢስ ሆኑ። በዚያን ጊዜም ጌታ ኢያሱን፦ “የባልጩት መቁረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው” አለው። ኢያሱም የባልጩት መቁረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ። ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነበር፤ ከግብጽ ከወጣው ሕዝብ መካከል ወንዶች ተዋጊዎች ሁሉ ከግብጽ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞተው ስለ ነበረ ነው። የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ነገር ግን ከግብጽ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በመንገድ እየተጓዙ ሳሉ የተወለዱት ልጆች ሁሉ አልተገረዙም ነበር። ጌታም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ እንዲሰጠን ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ የጌታንም ቃል ያልሰሙ፥ ሕዝብ ሁሉ፥ ከግብጽ የወጡ ተዋጊዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር። ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፥ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፤ በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና። ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተገረዙ ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ በየስፍራቸው ተቀመጡ። ጌታም ኢያሱን፦ “ዛሬ የግብጽን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” አለው፤ ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ። የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ። ከፋሲካውም በኋላ በማግስቱ የምድሪቱን ፍሬ እርሾ ያልገባበትን የቂጣ እንጎቻና ቆሎ በዚያው ቀን በሉ። በማግስቱም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ። እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፦ “አንተ ከእኛ ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን?” አለው። እርሱም፦ “አይደለሁም፤ እኔ የጌታ ሠራዊት አዣዥ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ” አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ “ጌታዬ ለባርያው የሚነግረው ምንድነው?” አለው። የጌታም ሠራዊት አዣዥ ኢያሱን፦ “አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ። ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርሷ የሚገባ ከእርሷም የሚወጣ ማንም አልነበረም። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። እናንተም ከተማይቱን ትዞሩአታላችሁ፥ ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ ከተማይቱን በቀን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።” የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በጌታ ታቦት ፊት ይሸከሙ።” ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ተዋጊዎቹም በጌታ ታቦት ፊት ይሂዱ።” ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።” እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ። ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አመንዝራይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ።” ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማይቱንም በእርሷም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ ብቻ በጌታ ግምጃ ቤት አኖሩት። ኢያሪኮንም ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርሷም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች። በዚያን ጊዜም ኢያሱ እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በጌታ ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ።” ጌታም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ተሰማ። የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ፤” ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው እንዲህ አሉት፦ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም።” ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም ላይ ሳሉ መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በጌታ ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ልትሰጠን ልታጠፋንም ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስራኤል ከጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድነው?” ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ለምን በግምባርህ ተደፍተኽ ትሰግዳለህ? ቁም፤ እስራኤል ኃጢአት ሠርቶአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስከ ነገ ተቀደሱ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፦ “እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም።” ነገ ጧት በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ ጌታም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ቤተሰብ በየሰዉ ይቀርባል። እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የጌታን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል ፈጽሟልና እርሱና የእርሱ የሆነው ነገር ሁሉ በእሳት ይቃጠል።’ ” ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፤ የይሁዳም ነገድ ተለየ፤ የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፤ የዛራንም ወገን ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ዘንበሪም ተለየ፤ የቤቱንም ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የዛራ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የከርሚ ልጅ አካን ተለየ። ኢያሱም አካንን እንዲህ አለው፦ “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ።” አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእውነት በእስራኤል አምላክ በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ፤ በምርኮ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም ኀምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው።” ኢያሱም መልክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በጌታም ፊት አኖሩት። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። ኢያሱም፦ “ለምን መከራን አመጣህብን? ጌታ ዛሬ መከራን ያመጣብሃል” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ ጌታም ከጽኑ ቁጣው ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፥ አትደንግጥ፤ ተዋጊዎቹን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ።” ኢያሱም ተዋጊዎቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፤ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ነቅታችሁ ጠብቁ፤ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ እነርሱም፦ ‘እንደ ቀድሞው ከእኛ ዘንድ እየሸሹ ናቸው’ ይላሉና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ ጌታም አምላካችሁ እርሷን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ ጌታ ቃል አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።” ኢያሱም ሰደዳቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። ኢያሱም ማልዶ በጠዋት ተነሣ፥ ሕዝቡንም ሰበሰበ፤ እርሱም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ ወጥተው በመጓዝ ወደ ከተማይቱ ቀረቡ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው። በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የኋላ ደጀን የሆነውን ሕዝብ አኖሩ፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት በሸለቆው ውስጥ አደረ። የጋይም ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ቸኩለው በማለዳ ተነሡ፤ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በጦርነት ለመግጠም ወጡ፤ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ። በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እነርሱን እዲያሳድዱአቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት። ጌታ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በእርሷ ላይ ዘርጋ፤” ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ። የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት። የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሸው ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ስለ ተመለሱ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ ወደ ላይ እንደ ጤሰ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ። ሌሎቹም በእነርሱ ላይ ከከተማይቱ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፤ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው። የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። እንዲህም ሆነ፤ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከፈጁአቸው በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት። በዚያም ቀን የሞቱት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ነበሩ። ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስከሚያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋበትን እጁን አላጠፈም። ነገር ግን ጌታ ኢያሱን ባዘዘው ቃል መሠረት የዚያችን ከተማ ከብትና ምርኮ ብቻ እስራኤል ለራሳቸው ዘረፉ። ኢያሱም ጋይን አቃጠላት፥ እስከ ዛሬም ድረስ የፍርስራሽ ክምር ለዘለዓለም አደረጋት። የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ሬሳውንም ከዛፍ አወረዱት፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ጣሉት፥ በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት። ከዚህም በኋላ ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ መሠዊያን ሠራ። የጌታ ባርያ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዘ፥ በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደተጻፈው፥ “መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ”፤ በእርሱም ላይ ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ የአንድነትንም መሥዋዕት ሠዉ። የእስራኤልም ልጆች እያዩ በዚያ ስፍራ በድንጋዮቹ ላይ የሙሴን ሕግ ጻፈባቸው። የእስራኤልንም ሕዝብ አስቀድሞ እንዲባረኩ የጌታ ባርያ ሙሴ እንዳዘዘ፥ እስራኤል ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ፈራጆቻቸውም፥ የአገሩ ተወላጆችም፥ መጻተኞችም፥ እኩሌቶቹ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት እኩሌቶቹም በጌባል ተራራ ፊት ለፊት ሆነው፥ የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፥ በታቦቱም ፊት በወዲህና በወዲያ ቆመው ነበር። ከዚህም በኋላ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፥ የሕጉን ቃላት ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ። ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል እንኳ ሳያስቀር ሁሉን አነበበ። እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላማውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠገነም የወይን ጠጅ አቁማዳ ጫኑ። ያረጀና የተጠጋገነ ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ አሉ፦ “ከሩቅ አገር መጥተናል፤ እንግዲህ አሁን ከእኛ ጋር የቃል ኪዳን አድርጉ።” የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያን እንዲህ አሉአቸው፦ “ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን?” ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ነን።” ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “ከአምላክህ ከጌታ ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባርያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብጽም ያደረገውን ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ እንዲህ አሉን፦ ‘ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ እንዲህም በሉአቸው፦ “እኛ ባርያዎቻችሁ ነን፤ እንግዲህ አሁን ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ።” ’ ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፤ አሁን ግን እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም፤ እነዚህም የወይን ጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል።” የእስራኤልም አለቆች ከስንቃቸው ወሰዱ፥ የጌታንም ምሪት አልጠየቁም። ኢያሱም ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት አደረገ፥ በሕይወት እንዲኖሩም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው። ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ በመካከላቸውም እንደሚኖሩ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች ተጉዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው መጡ፤ ከተሞቻቸው ገባዖን፥ ከፊራ፥ ብኤሮት፥ ቂርያት-ይዓሪም ነበሩ። የሕዝቡም አለቆች በእስራኤል አምላክ በጌታ ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በአለቆቹ ላይ አጉረመረሙ። አለቆቹም ሁሉ ለማኅበሩ ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፦ “በእስራኤል አምላክ በጌታ ምለንላቸዋል፤ ስለዚህም እንነካቸው ዘንድ አይገባንም። ስለ ማልንላቸው መሓላ ቁጣ እንዳይወርድብን ይህን እናድርግባቸው፥ በሕይወትም እንዲኖሩ እንተዋቸው።” አለቆቹም፦ “በሕይወት ይኑሩ” አሉአቸው፤ አለቆቹም እንደ ተናገሩአቸው ለማኅበሩ ሁሉ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች ሆኑ። ኢያሱም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ በመካከላችን ስትኖሩ፦ ‘ከእናንተ እጅግ የራቅን ነን’ ብላችሁ ለምን አታለላችሁን? እንግዲህ አሁን የተረገማችሁ ናችሁ፤ እናንተም ለአምላኬ ቤት እንጨት ቈራጭ ውኃም ቀጂ ባርያዎች ለዘለዓለም ትሆናላችሁ።” መልሰውም ኢያሱን እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ምድሪቱን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ በእርሷም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ እንዲያጠፋ ጌታ አምላክህ ባርያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፥ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ስለ ፈራን ይህን ነገር አድርገናል። እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ በእጅህ ውስጥ ነን፤ ለዓይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን።” እንዲሁም አደረገባቸው፥ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፥ አልገደሉአቸውምም። በዚያም ቀን ኢያሱ በመረጠው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ለማኅበሩና ለጌታ መሠዊያ እንጨት ቈራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው። እንዲህም ሆነ፤ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ኢያሱ ጋይን እንደ ያዘ ፈጽሞም እንዳጠፋት፥ በኢያሪኮና በንጉሥዋም ያደረገውን እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ እንዳደረገ፥ የገባዖንም ሰዎች ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው በመካከላቸውም እንደ ሆኑ በሰማ ጊዜ፥ ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለ ነበረች፥ ከጋይም ስለ ምትበልጥ፥ ሰዎችዋም ሁሉ ኃያላን ስለ ነበሩ፥ እጅግ ፈራ። ስለዚህም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ሆሃም፥ ወደ የርሙት ንጉሥም ወደ ጲርአም፥ ወደ ለኪሶ ንጉሥም ወደ ያፊዓ፥ ወደ ዔግሎም ንጉሥም ወደ ዳቤር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ወደ እኔ ውጡ፥ ከኢያሱና ከእስራኤልም ልጆች ጋር የሰላም ስምምነት አድርገዋልና ገባዖንን ለመምታት አግዙኝ።” አምስቱም የአሞራውያን ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ የዔግሎም ንጉሥ፥ እነርሱና ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር ተሰብስበው ወጡ፥ በገባዖንም ዙርያ ሰፈሩ በእርሷም ላይ ጦርነት አደረጉ። የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው እንዲህ አሉት፦ “ባርያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ አድነንም እርዳንም።” ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድም ሰው የሚቋቋምህ የለም።” ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። ጌታም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም በጽኑ ውግያ ድል አደረጓቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በሆነው መንገድ ላይ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ የቤትሖሮንን ቁልቁለት በመውረድ ላይ ሳሉ፥ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ ጌታ ከሰማይ ታላላቅ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። ጌታም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ ለጌታ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ የእስራኤልም ልጆች እያዩ እንዲህ አለ፦ “በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤” ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመች፥ ጨረቃም ዘገየች። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ጸንታ ቆመች፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለችም። ጌታ ለእስራኤል ይዋጋ ነበረና ጌታ የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም። ኢያሱም ከእርሱ ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈራቸው ወደ ጌልገላ ተመለሱ። እነዚህም አምስት ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተሸሸጉ። ለኢያሱም፦ “አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ተሸሽገው ተገኝተዋል” ብለው ነገሩት። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወደ ዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ፥ እንዲጠብቋቸው ሰዎችን በዚያ አኑሩ፤ እናንተ ግን አትዘግዩ፥ ጠላቶቻችሁንም አሳድዷቸው፥ ከኋላ በኩል እየተከተላችሁም ምቱአቸው፤ አምላካችሁም ጌታ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሉአቸው።” እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በጽኑ ውግያ ድል ማድረጋቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥ ሕዝብ ሁሉ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ በደኅና ተመለሱ፤ በእስራኤል ልጆች ላይ ደፍሮ ቃል የሚነናገር ማንም ሰው አልነበረም። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “የዋሻውን አፍ ክፈቱ፥ እነዚያንም አምስት ነገሥታት ከዋሻው ወደ እኔ አውጡአቸው።” እንዲህም አደረጉ፤ አምስቱንም ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ የኬብሮንንም ንጉሥ የየርሙትንም ንጉሥ የለኪሶንም ንጉሥ የዔግሎምንም ንጉሥ፥ ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡአቸው። እነዚያንም ነገሥታት ወደ ኢያሱ ባወጡአቸው ጊዜ ኢያሱ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፥ ከእርሱም ጋር የሄዱትን የተዋጊዎቹን የጦር አዛዦች እንዲህ አላቸው፦ “ቅረቡ፥ በእነዚህም ነገሥታት አንገት ላይ እግራችሁን አኑሩ።” ቀረቡም በአንገታቸውም ላይ እግራቸውን አኖሩ። ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጋልና አትፍሩ፥ አትደንግጡ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ።” ከዚህም በኋላ ኢያሱ መትቶ ገደላቸው፥ በአምስትም ዛፎች ላይ ሰቀላቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፎቹ ተሰቅለው ቈዩ። ፀሐይም ልትገባ በቀረበች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ከዛፎችም አወረዱአቸው፥ ተሸሽገውም በነበሩበት ዋሻ ጣሉአቸው፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ ተደርጎአል። በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዛት፥ እርሷንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ከእነርሱም አንድም እንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ ላይ እንዳደረገው እንዲሁ በመቄዳ ንጉሥ ላይ አደረገ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፥ ልብናንም ወጉ። ጌታም እርሷንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ እርሷንም በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፥ በእርሷም አንድም እንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ ላይ እንዳደረገው እንዲሁ በልብና ንጉሥ ላይ አደረገ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ለኪሶ አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም። ጌታም ለኪሶን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፥ በሁለተኛውም ቀን ያዙአት፤ በልብናም እንዳደረጉት ሁሉ፥ እርሷን በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱአቸው። በዚያን ጊዜም የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ኢያሱም አንድም እንኳ ሳይቀር እርሱንና ሕዝቡን መታ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከለኪሶ ወደ ዔግሎም አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም፤ በዚያም ቀን ያዙአት፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፤ በለኪሶም እንዳደረገው ሁሉ፥ በእርሷ ያሉትን ሰዎች ሁሉ በዚያ ቀን ፈጽሞ አጠፋ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከዔግሎም ወደ ኬብሮን ወጡ፥ ወጉአትም፥ ያዙአትም፤ እርሷንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ሁሉ በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ በዔግሎም እንዳደረገው ሁሉ ማንንም አላስቀረም፤ እርሷንም በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ዳቤር ተመለሱ፥ እርሷንም ወጉአት፥ እርሷንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ሁሉ ያዙ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ በእነርሱም ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፈጽመው አጠፉ፤ ማንንም አላስቀረም፤ በኬብሮን፥ ደግሞ በልብናና በንጉሥዋ እንዳደረገው እንዲሁ በዳቤርና በንጉሥዋ አደረገ። እንዲሁም ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ተራራማውን አገር ደቡቡንም ቈላውንም የተዳፋቱንም ስፍራ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ መታ፤ ማንንም አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዳዘዘውም እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ ድረስ የጎሶምንም ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታ። የእስራኤልም አምላክ ጌታ ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ። ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈሩ ወደ ጌልገላ ተመለሱ። እንዲህም ሆነ፤ የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አክሻፍም ንጉሥ፥ በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ፥ በቍጥር ም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ከሚሆን ብዙ ሕዝብ፥ እጅግም ከሚበዙ ፈረሶችና ሰረገሎች ጋር በመሆን ወጡ። እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ኃይላቸውን አስተባብረው እስራኤልን ለመውጋት መጡ፤ በማሮንም ውኃ አጠገብ በአንድ ላይ ሰፈሩ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ጊዜ እኔ ሁሉንም እንደሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ።” ኢያሱም ከተዋጊዎቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ በእነርሱም ላይ ጥቃት ፈጸመ። ጌታም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ አንድም ሳያስቀሩ መቱአቸው። ኢያሱም ጌታ እንዳዘዘው በእነሱ ላይ አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሦርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሦርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፤ አሦርንም በእሳት አቃጠላት። የጌታም ባርያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። ዳሩ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአሦር ብቻ በቀር እስራኤል በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም። የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። ጌታም ባርያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ ቈላውም እስከ ሴይር ከሚያወጣው ከሐላቅ ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በአልጋድ ድረስ ነበር፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፤ ሁሉንም በጦርነት ድል አድርገው ያዙ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ፥ እንዲያጠፉአቸው ምሕረትንም ሳያደርጉ ፈጽመው እንዲፈጅዋቸው፥ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከጌታ ዘንድ ሆነ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። ጌታም ለሙሴ እንደ ተናገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደየነገዳቸው ድርሻ ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከጦርነት ዐረፈች። የእስራኤልም ልጆች ያሸነፉአቸው፥ ከአርኖንም ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በምሥራቅ ያለውን ዓረባ ሁሉ በዮርዳኖስም ማዶ በፀሐይ መውጫ ያለውን አገራቸውን የወረሱአቸው ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ በሐሴቦን የተቀመጠው የአሞራውያን ንጉሥ ሴዎን፥ ይገዛ የነበረው በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር፥ ከሸለቆውም መካከል ጀምሮ የገለዓድን እኩሌታ እስከ ያቦቅ ወንዝ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ ሲሆን፥ በምሥራቅም በኩል ያለውን ዓረባ እስከ ኪኔሬት ባሕር ድረስ፥ በቤትየሺሞት መንገድ አጠገብ እስካለው እስከ ዓረባ ባሕር እስከ ጨው ባሕር ድረስ፥ በደቡብም በኩል ከፈስጋ ተራራ አፋፍ በታች ያለውን ምድር ነበር፤ ከራፋይምም ወገን የቀረ፥ በአስታሮትና በኤድራይ የተቀመጠው የባሳን ንጉሥ ዐግ፥ ይገዛ የነበረው የአርሞንዔምን ተራራ፥ ሰልካን፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ፥ የገለዓድንም እኩሌታ እስከ ሐሴቦን ንጉሥ እስከ ሴዎን ዳርቻ ድረስ ነበር። የጌታ ባርያ ሙሴና የእስራኤል ልጆች አሸነፉአቸው፤ የጌታም ባርያ ሙሴ ርስት አድርጎ ለሮቤል ልጆች ለጋድም ልጆች ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ምድሪቱን ሰጣቸው። ኢያሱና የእስራኤል ልጆች ያሸነፉአቸው የምድሪቱ ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም የነበሩት በዮርዳኖስም ማዶ በምዕራብ በኩል በሊባኖስ ሸለቆ ካለችው ከበኣልጋድ ወደ ሴይር ተራራ እስከሚያወጣው እስከ ሐላቅ ተራራ ድረስ ኢያሱ በየድርሻቸው ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገድ በሰጣት ምድር፥ በተራራማው አገር፥ በቈላውም፥ በዓረባም፥ በቁልቁለቱም፥ በምድረ በዳውም፥ በደቡቡም ያሉ ኬጢያውያን አሞራውያንም ከነዓናውያንም ፌርዛውያንም ኤዊያውያንም ኢያቡሳውያንም ዘንድ ነበር። የኢያሪኮ ንጉሥ፥ በቤቴል አጠገብ ያለችው የጋይ ንጉሥ፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ የዔግሎም ንጉሥ፥ የጌዝር ንጉሥ፥ የዳቤር ንጉሥ፥ የጌድር ንጉሥ፥ የሔርማ ንጉሥ፥ የዓድራ ንጉሥ፥ የልብና ንጉሥ፥ የዓዶላም ንጉሥ፥ የመቄዳ ንጉሥ፥ የቤቴል ንጉሥ፥ የታጱዋ ንጉሥ፥ የኦፌር ንጉሥ፥ የአፌቅ ንጉሥ፥ የለሸሮን ንጉሥ፥ የማዶን ንጉሥ፥ የአሦር ንጉሥ፥ የሺምሮን ሚሮን ንጉሥ፥ የአክሻፍ ንጉሥ፥ የታዕናክ ንጉሥ፥ የመጊዶ ንጉሥ፥ የቃዴስ ንጉሥ፥ በቀርሜሎስ የነበረ የዮቅንዓም ንጉሥ፥ በዶር ኮረብታ የነበረ የዶር ንጉሥ፥ በጌልገላ የነበረ የጎይም ንጉሥ፥ የቲርሳ ንጉሥ፥ ነገሥታቱ ሁሉ ሠላሳ አንድ ናቸው። ኢያሱም ሸመገለ ዕድሜውም ስለ ገፋ አረጀ፤ ጌታም እንዲህ አለው፦ “አንተ ሸምግለሃል፥ ዕድሜህም ስለ ገፋ አርጅተሃል፤ ያልተወረሰ እጅግ ብዙ ምድር ገና ይቀራል፤ ሳይያዝ የቀረውም ምድር ይህ ነው፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ በግብጽ ፊት ለፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ናቸው፥ የኤዋውያን የሆኑትም እንዲሁ፥ በደቡብም በኩል የነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ የጌባላውያንም ምድር፥ በፀሐይም መውጫ በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፥ እኔ ራሴ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ብቻ ርስት አድርገህ አካፍላቸው። እንግዲህ አሁን ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።” የጌታ ባርያ ሙሴ እንደሰጣቸው ከሌሎቹ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ብቻ ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አድርጎ አስወጣቸው። የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላስወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ እርሱ እንደ ተናገራቸው እንዲሁ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ርስታቸው ነው። ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥ ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥ ቤትባኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥ ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥ ቤተ ፌጎር፥ የፈስጋ ተዳፋት መሬት፥ ቤትየሺሞት፥ የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም ሴዎንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን ድል ነሣቸው። ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት። የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። ግዛታቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት ለፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የተቀረውም የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር። የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፤ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ድርሻቸው ይህ ነበረ። ግዛታቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ድርሻቸው ሆነ። ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ ያከፋፈለው ርስት ይህ ነው። ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንደ ነገራቸው እንዲሁ ርስታቸው እርሱ ነው። የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር የወረሱት፥ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ የእስራኤልም ልጆች ነገድ የአባቶቻቸው አለቆች ያከፋፈሉአቸው ርስት ይህ ነው፤ ጌታ በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው በየርስታቸው በዕጣ አከፋፈሉአቸው። ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ ርስት ሰጥቶ ነበረ፤ ነገር ግን በመካከላቸው ለሌዋውያን ርስት አልሰጣቸውም። የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም ከሚቀመጡባቸው ከተሞች ለእንሰሶቻቸውና ለከብቶቻቸውም ከሚሆን ማሰማርያ በቀር በምድሩ ውስጥ ድርሻ አልሰጡአቸውም። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፥ ምድሪቱንም ተካፈሉ። የይሁዳም ልጆች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ቄኔዛዊውም የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፦ “ለእግዚአብሔር ሰው ለሙሴ ስለ እኔና ስለ አንተ ጌታ በቃዴስ በርኔ የተናገረውን ነገር ታውቃለህ። የጌታ ባርያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ጎልማሳ ነበርሁ እኔም ተመልሼ በልቤ የነበረውን ቃል ተናገርሁ። ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ በፍርሃት አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን ጌታን ፈጽሜ ተከተልሁ። ሙሴም በዚያ ቀን እንዲህ ብሎ ማለ፦ ‘አምላኬን ጌታን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘለዓለም በእርግጥ ርስት ይሆናል።’ እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ ጌታ ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረው ጌታ እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ እኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ እንዲሁ ዛሬም ብርቱ ነኝ፤ ጉልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው። አሁን እንግዲህ በዚያን ቀን ጌታ የተናገረውን ይህን ተራራማ አገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ ምናልባት ጌታ ከእኔ ጋር ይሆናል፥ ጌታም እንደ ተናገረኝ አሳድዳቸዋለሁ።” ኢያሱም ባረከው፤ ለዮፎኒም ልጅ ለካሌብ ኬብሮንን ርስት አድርጎ ሰጠው። ስለዚህም የእስራኤል አምላክ ጌታን ፈጽሞ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ ዛሬ ለቄኔዛዊው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነች። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያት-አርባቅ ትባል ነበር፤ ይህም አርባቅ በዔናቅ ሰዎች መካከል ታላቅ ሰው ነበረ። ምድሪቱም ከውጊያ ዐረፈች። የይሁዳም ልጆች ነገድ ዕጣ በየወገናቸው እስከ ጺን ምድረ በዳ እስከ ደቡብ መጨረሻ እስከ ኤዶምያስ ዳርቻ ድረስ ይደርሳል። በደቡብም በኩል ያለው ድንበራቸው እስከ ጨው ባሕር መጨረሻ ወደ ደቡብ ትይዮ እስከ ባሕሩ ልሳን ድረስ ነበረ። ከዚያም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ወጣ፥ ወደ ጺንም አለፈ፥ በቃዴስ በርኔ ወደ ደቡብ በኩል ወጣ፥ በሐጽሮንም በኩል አለፈ፥ ወደ አዳርም ወጣ፥ ወደ ቀርቃ ዞረ፥ ወደ ዓጽሞንም አለፈ፥ በግብጽም ወንዝ በኩል ወጣ፥ የድንበሩም መጨረሻ በባሕሩ አጠገብ ነበረ፤ በደቡብ በኩል ያለው ድንበራቸው ይህ ነው። በምሥራቅም በኩል ያለው ድንበር እስከ ጨው ባሕር እስከ ዮርዳኖስም መጨረሻ ነበረ። በሰሜንም በኩል ያለው ድንበር በዮርዳኖስ መጨረሻ እስካለው እስከ ባሕሩ ልሳን ድረስ ነበረ፤ ከዚያም ድንበሩ ወደ ቤትሖግላ ወጣ፥ በቤትዓረባ በሰሜን በኩል አለፈ፥ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወጣ፤ ድንበሩም ከአኮር ሸለቆ ወደ ዳቤር ወጣ፥ በሰሜን በኩል በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት፥ በሸለቆው በደቡብ በኩል ወዳለችው ወደ ጌልገላ ታጠፈ፤ ድንበሩም ወደ ቤት ሳሚስ ውኃ አለፈ፥ ማብቂውም በዓይንሮጌል አጠገብ ነበረ፤ ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ አጠገብ ኢየሩሳሌም ወደምትባለው ወደ ኢያቡሳዊው ወደ ደቡብ ወገን ወጣ፤ ድንበሩም በራፋይም ሸለቆ ዳር በሰሜን በኩል ባለው በሄኖም ሸለቆ ፊት ለፊት በምዕራብ ወገን ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ወጣ፤ ድንበሩም ከተራራው ራስ ወደ ኔፍቶ ውኃ ምንጭ ደረሰ፥ ከዚያም ተነስቶ ወደ ዔፍሮን ተራራ ከተሞች ወጣ፤ ቂርያት-ይዓሪም ወደምትባል ወደ በኣላ ታጠፈ፤ ድንበሩም ከበኣላ በምዕራብ በኩል ወደ ሴይር ተራራ ዞረ፤ ክሳሎን ወደምትባል ወደ ይዓርም ተራራ ወገን በሰሜን በኩል አለፈ፤ ወደ ቤት ሳሚስ ወረደ፥ በተምና በኩልም አለፈ። ድንበሩም ወደ አቃሮን ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፤ ወደ ሽክሮን ታጠፈ፤ ወደ በኣላ ተራራ አለፈ፥ በየብኒኤልም በኩል ወጣ፤ የድንበሩም መጨረሻ በባሕሩ አጠገብ ነበረ። በምዕራብም በኩል ያለው ድንበር እስከ ታላቁ ባሕርና እስከ ዳርቻው ድረስ ነበረ። ለይሁዳ ልጆች በየወገናቸው በዙሪያው ያለ ድንበራቸው ይህ ነው። ጌታም ኢያሱን እንዳዘዘው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ቂርያት-አርባቅ የምትባለውን ከተማ ድርሻ አድርጎ ሰጠው፤ እርሷም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ከዚያ ስፍራ አሳደደ። እነዚህም የዓናቅ ትውልድ ነበሩ። ከዚያም በዳቤር ሰዎች ላይ ወጣ፤ የዳቤርም ስም አስቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበረ። ካሌብም፦ “ቂርያትሤፍርን ለሚመታ ለሚይዛትም ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ” አለ። የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ስለዚህ ካሌብ ልጁን ዓክሳንን አጋባው። እርሷም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው፤ እርሷም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም፦ “ምን ፈለግሽ?” አላት። እርሷም እንዲህ አለችው፦ “በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብም በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ።” እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት። በየወገኖቻቸውም የይሁዳ ልጆች ነገድ ርስት ይህ ነው። በደቡብም በኩል በምድራቸው ዳርቻ አጠገብ እስከ ኤዶምያስ ድንበር ያሉት የይሁዳ ልጆች ነገድ ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ ቀብሴኤል፥ ዔደር፥ ያጉር፥ ቂና፥ ዲሞና፥ ዓድዓዳ፥ ቃዴስ፥ ሐጾር፥ ዪትናን፥ ዚፍ፥ ጤሌም፥ በዓሎት፥ ሐጾርሐዳታ፥ ሐጾር የምትባለውም ቂርያትሐጾር፥ አማም፥ ሽማዕ፥ ሞላዳ፥ ሓጸርጋዳ፥ ሐሽሞን፥ ቤትጳሌጥ፥ ሐጸርሹዓል፥ ቤርሳቤህ፥ ቢዝዮትያ፥ በኣላ፥ ዒዪም፥ ዓጼም፥ ኤልቶላድ፥ ኪሲል፥ ሔርማ፥ ጺቅላግ፥ ማድማና፥ ሳንሳና፥ ልባዎት፥ ሺልሂም፥ ዐይን፥ ሪሞን፤ ሀያ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። በቈላው ኤሽታኦል፥ ጾርዓ፥ አሽና፥ ዛኖዋ፥ ዓይንገኒም፥ ታጱዋ፥ ዓይናም፥ የርሙት፥ ዓዶላም፥ ሰኰት፥ ዓዜቃ፥ ሽዓራይም፥ ዓዲታይም፥ ግዴራ፥ ግዴሮታይም፤ ዐሥራ አራት ከተሞችና መንደሮቻቸው። ጽናን፥ ሐዳሻ፥ ሚግዳልጋድ፥ ዲልዓን፥ ምጽጳ፥ ዮቅትኤል፥ ለኪሶ፥ ቦጽቃት፥ ዔግሎም፥ ከቦን፥ ለሕማስ፥ ኪትሊሽ፥ ግዴሮት፥ ቤትዳጎን፥ ናዕማ፥ መቄዳ፤ ዐሥራ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። ልብና፥ ዔቴር፥ ዓሻን፥ ይፍታሕ፥ አሽና፥ ንጺብ፥ ቅዒላ፥ አክዚብ፥ መሪሳ፤ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። አቃሮን ከተመሸጉና ካልተመሸጉ መንደሮችዋ ጋር፤ ከአቃሮንም ጀምሮ እስከ ባሕሩ ድረስ በአዛጦን አጠገብ ያሉት ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር። አዛጦንና የተመሸጉና ያልተመሸጉ መንደሮችዋም፥ ጋዛና የተመሸጉ ያልተመሸጉም መንደሮችዋ፥ እስከ ግብጽ ወንዝና እስከ ታላቁ ባሕር ዳርቻ ድረስ። በተራራማው አገር ሳምር፥ የቲር፥ ሶኮ፥ ደና፥ ዳቤር የምትባለው ቂርያትሰና፥ ዓናብ፥ ኤሽትሞዓ፥ ዓኒም፥ ጎሶም፥ ሖሎን፥ ጊሎ፤ ዐሥራ አንድ ከተሞችና መንደሮቻቸው። አራብ፥ ዱማ፥ ኤሽዓን፥ ያኒም፥ ቤትታጱዋ፥ አፌቃ፥ ሑምጣ፥ ኬብሮን የምትባል ቂርያት-አርባቅ፥ ጺዖር፤ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። ማዖን፥ ቀርሜሎስ፥ ዚፍ፥ ዩጣ፥ ኢይዝራኤል፥ ዮቅድዓም፥ ዛኖዋሕ፥ ቃይን፥ ጊብዓ፥ ተምና፤ ዐሥር ከተሞችና መንደሮቻቸው። ሐልሑል፥ ቤትጹር፥ ጌዶር፥ ማዕራት፥ ቤትዓኖት፥ ኤልትቆን፤ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። ቂርያት-ይዓሪም የምትባለው ቂርያትበኣል፥ ረባት፤ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። በምድረ በዳ ቤትዓረባ፥ ሚዲን፥ ስካካ፥ ኒብሻን፥ የጨው ከተማ፥ ዓይንጋዲ፤ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። በኢየሩሳሌም የተቀመጡትን ኢያቡሳውያንን ግን የይሁዳ ልጆች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ኢያቡሳውያንም እስከ ዛሬ በይሁዳ ልጆች መካከል በኢየሩሳሌም ውስጥ ተቀምጠዋል። የዮሴፍም ልጆች ዕጣ በኢያሪኮ ወንዝ አጠገብ በምሥራቁ በኩል ካለው ከዮርዳኖስ አንሥቶ በምድረ በዳው አድርጎ ከኢያሪኮ በተራራማው አገር በኩል ወደ ቤቴል ወጣ፤ ከቤቴል ወደ ሎዛ ወጣ፥ በአርካውያንም ግዛት በኩል ወደ ዓጣሮት አለፈ፥ ወደ ምዕራብም እስከ የፍሌጣውያን ድንበር እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ድንበር እስከ ጌዝር ድረስ ወረደ፥ መጨረሻውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የዮሴፍም ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ወረሱ። የኤፍሬምም ልጆች ድንበር በየወገኖቻቸው እንደዚህ ነበረ፤ በምሥራቅ በኩል የርስታቸው ድንበር አጣሮትአዳር እስከ ላይኛው ቤትሖሮን ድረስ ነበረ፤ ከዚያም ተነሥቶ ድንበሩ ወደ ባሕሩ በኩል ወጣ፤ በሰሜን በኩል ሚክምታት ይገኝ ነበር፤ ድንበሩም ወደ ምሥራቅ ወደ ተአናትሴሎ ዞረ፥ ወደ ኢያኖክ በምሥራቅ በኩል አለፈ፥ ከኢያኖክም ወደ አጣሮትና ወደ ነዓራት ወረደ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሰ፥ መጨረሻውም ዮርዳኖስ ነበር። ድንበሩም ከታጱዋ ወደ ምዕራብ እስከ ቃና ወንዝ ድረስ አለፈ፥ መጨረሻውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የኤፍሬም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ይኸውም በምናሴ ልጆች ርስት መካከል ለኤፍሬም ልጆች ከተለዩ ከተሞች ጋር፥ እነዚህም ከተሞች ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር ርስታቸው ነበሩ። በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላሳደዱአቸውም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ከነዓናውያን በኤፍሬም መካከል ተቀምጠዋል፤ እነርሱም የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ባሮች ሆነዋል። ለምናሴ ነገድ ዕጣው ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኩር እርሱ ነውና። የምናሴም በኩር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ተዋጊ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ። ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለአቢዔዝር ልጆች፥ ለኬሌግ ልጆች፥ ለዐሥርኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች፥ ለሸሚዳ ልጆች ሆነ፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ወንዶች ልጆች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው። ለምናሴ ልጅ፥ ለማኪር ልጅ፥ ለገለዓድ ልጅ፥ ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “ጌታ በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዘዘ፤” ጌታም እንዳዘዘ በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው። በዮርዳኖስ ማዶ ካለው ከገለዓድና ከባሳን አገር ሌላ ለምናሴ ዐሥር ዕጣ ደረሰው፤ የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆች መካከል ርስት ስለወረሱ፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ስለሆነ ነው። የምናሴም ግዛት ከአሴር ጀምሮ በሴኬም ፊት ለፊት እስካለው እስከ ሚክምታት ድረስ ነበረ፤ ድንበሩም በቀኝ በኩል ወደ ዓይንታጱዋ ሰዎች አለፈ። የታጱዋ ምድር ለምናሴ ነበረ፤ በምናሴ ዳርቻ ያለው ታጱዋ ግን ለኤፍሬም ልጆች ሆነ። ድንበሩም ወደ ቃና ወንዝ ወረደ፤ በምናሴም ከተሞች መካከል ከወንዙ በደቡብ በኩል የሚገኙት እነዚህ ከተሞች ለኤፍሬም ሆኑ፤ የምናሴም ድንበር በወንዙ በኩል በሰሜን ወገን ነበረ፥ መጨረሻውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፥ በሰሜንም በኩል ያለው ለምናሴ ነበረ፥ ድንበሩም የባሕሩ ዳርቻ ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ደረሰ። በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ ዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ዓይነዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ታዕናክና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ መጊዶና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ሦስቱ ኮረብቶች ለምናሴ ነበሩ። የምናሴ ልጆች ግን የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። የእስራኤልም ልጆች በጸኑ ጊዜ ከነዓናውያንን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አደረጉአቸው፥ ፈጽመውም አላሳደዱአቸውም። የዮሴፍ ልጆች ነገድ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “እኔ ብዙ ሕዝብ ስለ ሆንኩ እስከ አሁንም ጌታ ስለ ባረከኝ ለምን አንድ ድርሻ አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸኝ?” ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “ብዙ ሕዝብስ ከሆንህ ተራራማውም የኤፍሬም አገር ጠብቦህ እንደሆነ ወደ ዱር ወጥተህ በፌርዛውያንና በራፋይም ምድር ለአንተ ስፍራ መንጥር።” የዮሴፍም ልጆች እንዲህ አሉት፦ “ተራራማው አገር አይበቃንም፤ በሸለቆውም ውስጥ የሚኖሩት፥ በቤትሳና በመንደሮችዋ በኢይዝራኤልም ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን የብረት ሰረገሎች አላቸው።” ኢያሱም የዮሴፍ ወገን ለሚሆኑ ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፦ “አንተ ብዙ ሕዝብ ነህ፥ ጽኑም ኃይል አለህ፤ አንድ ዕጣ ብቻ አይወጣልህም። ነገር ግን ተራራማው አገር ለአንተ ይሆናል፥ ዱር እንኳን ቢሆንም ትመነጥረዋለህ፥ ለአንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የብረት ሰረገሎች ቢኖሩአቸው የበረቱም ቢሆኑ ታሳድዳቸዋለህ።” የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፤ እነርሱም የምድሪቱ ገዢዎች ሆኑ። ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ የሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ እስከ መቼ ቸል ትላላችሁ? ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፤ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይመዘግቡታል፤ ከዚያም በኋላ ወደ እኔ ይመለሳሉ። በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል ባለው ግዛት ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል ባለው ግዛት ውስጥ ይቀመጣሉ። እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወደዚህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በጌታ ፊት በዚህ ዕጣ እጥልላችኋለሁ። ነገር ግን የጌታ ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ ድርሻ የላቸውም፤ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የጌታ ባርያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።” ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ተመልክተው ሊጽፉ የሄዱትን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ እዩና ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በጌታ ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ።” ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ በከተሞቹም ልክ በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ። ኢያሱም በጌታ ፊት በሴሎ ዕጣ ጣለላቸው፤ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደየድርሻቸው ምድሩን ከፈለ። የብንያምም ልጆች ነገድ ዕጣ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ የዕጣቸውም ግዛት በይሁዳ ልጆችና በዮሴፍ ልጆች መካከል ወጣ። በሰሜን በኩል ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ጀመረ፤ ድንበሩም ወደ ኢያሪኮ ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፥ ከዚያም በተራራማው አገር በኩል ወደ ምዕራብ ወጣ፥ መጨረሻውም በቤትአዌን ምድረ በዳ ነበረ። ድንበሩም ከዚያ በደቡብ በኩል በሎዛ አቅጣጫ ቤቴል ወደምትባል ወደ ሎዛ ወገን አለፈ፤ ድንበሩም በታችኛው ቤትሖሮን በደቡብ በኩል ባለው ተራራ ወደ አጣሮትአዳር ወረደ። ድንበሩም ወደ ምዕራብ ሄደ፥ በቤትሖሮንም ፊት ለፊት ካለው ተራራ ወደ ደቡብ ዞረ፤ መጨረሻውም ቂርያት-ይዓሪም በምትባል በቂርያትበኣል በይሁዳ ልጆች ከተማ ነበረ፤ ይህ የምዕራቡ ዳርቻ ነበረ። የደቡብም ዳርቻ የሚጀምረው ከቂርያት-ይዓሪም ዳርቻ አጠገብ ነበረ፤ ድንበሩም በምዕራቡ በኩል ወደ ነፍቶ ውኃ ምንጭ ወጣ። ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ፊት ለፊት ወዳለው ተራራ መጨረሻ ወረደ፥ እርሱም በራፋይም ሸለቆ በሰሜን በኩል ነው፤ ወደ ሄኖም ሸለቆ ወደ ኢያቡስ ወገን በደቡብ በኩል ወረደ፥ ወደ ዓይንሮጌልም ወረደ። ወደ ሰሜንም ታጥፎ በቤትሳሚስ ምንጭ ላይ ወጣ፥ በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ጌሊሎት ደረሰ፤ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወረደ፤ በሰሜንም ወገን ወደ ዓረባ አጠገብ አለፈ፥ ወደ ዓረባም ወረደ፤ ድንበሩም ወደ ቤትሖግላ ወደ ሰሜን ወገን አለፈ፤ የድንበሩም መጨረሻ በዮርዳኖስ መጨረሻ በደቡብ በኩል ባለው በጨው ባሕር ልሳን አጠገብ ነበረ፤ ይህ የደቡቡ ዳርቻ ነበረ። በምሥራቅም በኩል ድንበሩ ዮርዳኖስ ነበረ። ይህ በዙርያቸው ያለው ዳርቻ በየወገኖቻቸው የብንያም ልጆች ርስት ነበረ። የብንያምም ልጆች ነገድ ከተሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ኢያሪኮ፥ ቤትሖግላ፥ ዓመቀጺጽ፥ ቤትዓረባ፥ ዘማራይም፥ ቤቴል፥ ዓዊም፥ ፋራ፥ ዖፍራ፥ ክፊርዓሞናይ፥ ዖፍኒ፥ ጋባ፤ ዐሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። ገባዖን፥ ራማ፥ ብኤሮት፥ ምጽጳ፥ ከፊራ፥ ሞጻ፥ ሬቄም፥ ይርጵኤል፥ ተርአላ፥ ጼላ፥ ኤሌፍ፥ ኢየሩሳሌም የምትባል ኢያቡስ፥ ጊብዓና ቂርያትይዓሪም፤ ዐሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የብንያም ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሁለተኛውም ዕጣ ለስምዖን ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ ርስታቸውም በይሁዳ ልጆች ርስት መከከል ነበረ። እነዚህም ርስታቸው ሆኑላቸው፤ ቤርሳቤህ፥ ሤባ፥ ሞላዳ፥ ሐጸርሹዓል፥ ባላ፥ ዔጼም፥ ኤልቶላድ፥ በቱል፥ ሔርማ፥ ጺቅላግ፥ ቤትማርካቦት፥ ሐጸርሱሳ፥ ቤተ-ለባኦት፥ ሻሩሔን፤ ዐሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው፤ ዐይን፥ ሪሞን፥ ዔቴር፥ ዓሻን፤ አራት ከተሞችና መንደሮቻቸው፤ እስከ ባዕላት-ብኤርና እስከ ደቡቡ ራማት ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ያሉ መንደሮች ሁሉ። የስምዖን ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። የይሁዳ ልጆች ግዛት በሆነው ክፍል ውስጥ የስምዖን ልጆች ርስት ሆነ፥ የይሁዳም ልጆች ድርሻ ስለ በዛባቸው የስምዖን ልጆች በርስታቸው መካከል ወረሱ። ሦስተኛውም ዕጣ ለዛብሎን ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ፤ የርስታቸውም ድንበር እስከ ሣሪድ ደረስ ይደርስ ነበር፤ ድንበራቸውም በምዕራብ በኩል ወደ መርዓላ ወጣ፥ እስከ ደባሼትም ደረሰ፤ በዮቅንዓም ፊት ለፊት ወዳለው ወንዝ ደረሰ፤ ከሣሪድም ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ ወደ ኪስሎትታቦር ዳርቻ ዞረ፤ ወደ ዳብራትም ወጣ፥ ወደ ያፊዓም ደረሰ፤ ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ጋት-ሔፍርና ወደ ዒታ-ቃጺን አለፈ፤ ወደ ሪምን በመውጣት ወደ ኒዓ ታጠፈ፤ ድንበሩም በሰሜን በኩል ወደ ሐናቶን ዞረ፥ መጨረሻውም በይፍታሕ-ኤል ሸለቆ ነበረ። ቀጣት፥ ነህላል፥ ሺምሮን፥ ይዳላ፥ ቤተልሔም፤ ዐሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የዛብሎን ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። አራተኛውም ዕጣ ለይሳኮር ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ። ድንበራቸውም የሚያጠቃልለው ኢይዝራኤልን፥ ከስሎትን፥ ሱነምን፥ ሐፍራይምን፥ ሺኦንን፥ አናሐራትን፥ ረቢትን፥ ቂሶንን፥ አቤጽን፥ ሬሜትን፥ ዐይን-ጋኒምን፥ ዐይን-ሐዳን፥ ቤት-ጳጼጽን ነበረ፤ ድንበሩም ወደ ታቦርና ወደ ሻሕጹማ፥ ወደ ቤት-ሳሚስ ደረሰ፥ የድንበራቸውም መጨረሻ ዮርዳኖስ ነበረ፤ ዐሥራ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የይሳኮር ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። አምስተኛውም ዕጣ ለአሴር ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ። ድንበራቸውም ሔልቃት፥ ሐሊ፥ ቤጤን፥ አክሻፍ፥ አላሜሌክ፥ ዓምዓድ፥ ሚሽአል ነበረ፤ በምዕራብ በኩል ወደ ቀርሜሎስና ወደ ሺሖር-ሊብናት ደረሰ፤ ወደ ፀሐይም መውጫ ወደ ቤትዳጎን ዞረ፥ ወደ ዛብሎንም ወደ ይፍታሕኤል ሸለቆ፥ በሰሜን በኩል ወደ ቤት-ዔሜቅና ወደ ንዒኤልም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ሰሜን ወደ ካቡል ወጣ፤ ከዚያም ወደ ዔብሮን፥ ወደ ረዓብ፥ ወደ ሐሞን፥ ወደ ቃና እስከ ታላቁ ሲዶናም ደረሰ። ድንበሩም ወደ ራማ፥ ወደ ተመሸገውም ከተማ ወደ ጢሮስ ዞረ፤ ድንበሩም ወደ ሖሳ ዞረ፤ መጨረሻውም በአክዚብ በኩል ወደ ባሕሩ ነበረ፤ ዑማ፥ አፌቅ፥ ረዓብ ደግሞ ነበሩ፤ ሀያ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የአሴር ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። ስድስተኛውም ዕጣ ለንፍታሌም ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ። ድንበራቸውም ከሔሌፍ፥ በጸዕነኒም ካለው ከባሉጥ ዛፍ፥ ከአዳሚ-ኔቄብ፥ ከየብኒኤል እስከ ለቁም ድረስ ነበረ፤ መጨረሻውም በዮርዳኖስ ነበረ። ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ አዝኖት-ታቦር ዞረ፥ ከዚያም ወደ ሑቆቅ ወጣ፤ ከዚያም በደቡብ በኩል ወደ ዛብሎን፥ በምዕራብ በኩል ወደ አሴር፥ በዮርዳኖስም በፀሐይ መውጫ ወደ ይሁዳ ደረሰ። የተመሸጉትም ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ ጺዲም፥ ጼር፥ ሐማት፥ ረቃት፥ ኬኔሬት፥ አዳማ፥ ራማ፥ አሦር፥ ቃዴስ፥ ኤድራይ፥ ዐይን-ሐጾር፥ ይርኦን፥ ሚግዳል-ኤል፥ ሖሬም፥ ቤት-ዓናት፥ ቤት-ሳሚስ፤ ዐሥራ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። የንፍታሌም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። ሰባተኛውም ዕጣ ለዳን ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ። የርስታቸውም ግዛት የሚያጠቃልለው፤ ጾርዓን፥ ኤሽታኦልን፥ ዒር-ሼሜሽን፥ ሸዕለቢንን፥ ኤሎንን፥ ይትላን፥ ኤሎንን፥ ትምናን፥ አቃሮንን፥ ኢልተቄን፥ ገባቶንን፥ ባዕላትን፥ ይሁድን፥ ብኔ-ብረቅን፥ ጋት-ሪሞንን፥ ሜያ-ርቆንን፥ በኢዮጴ ፊት ለፊት ካለው ዳርቻ ጋር ራቆንን ነበር። የዳንም ልጆች ግዛታቸውን መቆጣጠር ባለልቻሉ ጊዜ ከሌሼም ጋር ሊዋጉ ወጡ፥ ያዙአትም፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፥ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም፤ ሌሼም የነበረውን ስምዋንም በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት። የዳን ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። ምድሩንም ሁሉ በየግዛቱ ርስት እንዲሆን አከፋፍለው ከጨረሱ በኋላ፥ የእስራኤል ልጆች ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በመካከላቸው ርስት ሰጡት። በኤፍሬም ተራራማ አገር ያለችውን እንዲሰጡት የጠየቃቸውን ተምናሴራ የምትባለውን ከተማ እንደ ጌታ ትእዛዝ ሰጡት፤ ከተማም ሠርቶ ተቀመጠባት። ካህኑ አልዓዛር፥ የነዌም ልጅ ኢያሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ነገዶች የአባቶች አለቆች በጌታ ፊት በሴሎ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በዕጣ ያከፋፈሉት ርስት ይህ ነው። ምድሪቱንም አከፋፍለው ጨረሱ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘በሙሴ አማካይነት የነገርኋችሁን መማፀኛ ከተሞችን ለዩ፤ እነዚህም ከተሞች በስሕተት ሳያውቅም ሰውን የገደለ ገዳይ እንዲሸሽባቸው ከደም ተበቃዩ መማፀኛ ይሆኑላችኋል። ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ይሸሻል፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሞ በከተማይቱ ሽማግሌዎች ጆሮ ነገሩን ይናገራል፤ እነርሱም ወደ ከተማይቱ ይቀበሉታል፥ የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል ከእነርሱም ጋር ይቀመጣል። ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን ሳያውቅ ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፤ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፥ ወደ ከተማውም ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣበትም ከተማ ይገባል።’ ” በንፍታሌም ባለው በተራራማው አገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው አገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው አገር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያት-አርባቅን ለዩ። በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ራሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። በማኅበሩ ፊት እስኪቆም ድረስ በደም ተበቃዩ እጅ እንዳይሞት ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመካከላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተለዩ ከተሞች እነዚህ ናቸው። የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፤ በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ “ጌታ በሙሴ አማካይነት የምንቀመጥባቸውን ከተሞችና ለከብቶቻችን መሰማሪያቸውን እንዲሰጠን አዝዞአል።” የእስራኤልም ልጆች እንደ ጌታ ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ። ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ዐሥር ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ ዐሥራ ሁለት ከተሞች ወሰዱ። ጌታም በሙሴ አማካይነት እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ። የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያት-አርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰማሪያ ሰጡአቸው፤ እርሷም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንና መሰማሪያዋን፥ ልብናንና መሰማሪያዋን፥ የቲርንና መሰማሪያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰማሪያዋን፥ ሖሎንንና መሰማሪያዋን፥ ዳቤርንና መሰማሪያዋን፥ ዓይንንና መሰማሪያዋን፥ ዮጣንና መሰማሪያዋን፥ ቤት-ሳሜስንና መሰማሪያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰማሪያዋን፥ ናሲብንና መሰማሪያዋን፥ አናቶትንና መሰማሪያዋን፥ አልሞንና መሰማሪያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ። የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ሁሉ ከመሰማሪያቸው ጋር ዐሥራ ሦስት ከተሞች ናቸው። ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች የሌዋውያን ለሆኑ የቀዓት ወገኖች የዕጣቸው ከተሞች ከኤፍሬም ነገድ ደረሱአቸው። እነዚህንም ከተሞች ሰጡአቸው፤ በኤፍሬም ተራራማ አገር ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ሴኬምንና መሰማሪያዋን፥ ጌዝርንና መሰማሪያዋን፥ ቂብጻይምንና መሰማሪያዋን፥ ቤት-ሖሮንንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። ከዳንም ነገድ ኤልተቄንና መሰማሪያዋን፥ ገባቶንንና መሰማሪያዋን፥ ኤሎንንና መሰማሪያዋን፥ ጋትሪሞንንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ታዕናክንና መሰማሪያዋን፥ ጋት-ሪሞንንና መሰማሪያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። የቀሩት የቀዓት ልጆች ወገኖች ከተሞች ሁሉ ከመሰማሪያቸው ጋር ዐሥር ናቸው። ለሌዋውያንም ወገኖች ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ በባሳን ውስጥ የሆነቸውን ጎላንንና መሰማሪያዋን፥ በኤሽትራንና መሰማሪያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። ከይሳኮርም ነገድ ቂሶንንና መሰማሪያዋን፥ ዳብራትንና መሰማሪያዋን፥ የርሙትንና መሰማሪያዋን፥ ዐይን-ጋኒምንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። ከአሴርም ነገድ ሚሽአልንና መሰማሪያዋን፥ ዓብዶንንና መሰማሪያዋን፥ ሔልቃትንና መሰማሪያዋን፥ ረዓብንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። ከንፍታሌምም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገሊላ ውስጥ ቃዴስንና መሰማሪያዋን፥ ሐሞት-ዶንና መሰማሪያዋን፥ ቀርታንንና መሰማሪያዋን፤ ሦስቱን ከተሞች ሰጡአቸው። የጌድሶን ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው ዐሥራ ሦስት ከተሞች ከመሰማሪያቸው ጋር ነበሩ። ከሌዋውያንም ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ወገን ከዛብሎን ነገድ ዮቅንዓምንና መሰማሪያዋን፥ ቀርታንና መሰማሪያዋን፥ ዲሞናንና መሰማሪያዋን፥ ነህላልንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። ከሮቤልም ነገድ ቦሶርንና መሰማሪያዋን፥ ያሀጽንና መሰማሪያዋን፥ ቅዴሞትንና መሰማሪያዋን፥ ሜፍዓትንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። ከጋድም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገለዓድ ውስጥ ራሞትንና መሰማሪያዋን፥ መሃናይምንና መሰማሪያዋን፥ ሐሴቦንንና መሰማሪያዋን፥ ኢያዜርንና መሰማሪያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። ከሌዋውያን ወገኖች የቀሩት የሜራሪ ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ዕጣቸውም ዐሥራ ሁለት ከተማ ነበረ። በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰማሪያቸው ነበሩ። እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው መሰማሪያዎች ነበራቸው፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። ጌታም ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። ጌታም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ማንም ሰው ሊቋቋማቸው አልቻለም፤ ጌታም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ጌታ ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም። በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች፥ የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤ ይህንንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የጌታን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። እንግዲህ አሁን አምላካችሁ ጌታ እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ ስለዚህ አሁን ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የጌታ ባርያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የጌታ ባርያ ሙሴ አምላካችሁን ጌታን እንድትወድዱ፥ መንገዱንም ሁሉ እንድትሄዱ፥ ትእዛዙንም እንድትጠብቁ፥ እርሱንም በጽኑ እንድትይዙት፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን በጥንቃቄ አድርጉ።” ኢያሱም ባረካቸው፥ እንዲሄዱም አሰናበታቸው፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው ባሰናበታቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “በብዙ ሀብት እጅግም ብዙ በሆነ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ እጅግም ብዙ በሆነ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በሙሴ አማካይነት በተሰጠ በጌታ ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ለመግባት በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተለይተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ የሚል ወሬ ሰሙ፦ “እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል።” የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። ከእርሱም ጋር ዐሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፤እንያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቆች ነበሩ። በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው፦ “የጌታ ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው፦ ‘ዛሬ ጌታን ከመከተል በመመለሳችሁ፥ መሠዊያም ሠርታችሁ ዛሬ በጌታ ላይ በማመፃችሁ ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት አለመታመን ምንድነው? በጌታ ማኅበር ላይ መቅሰፍት ያወረደውና እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? እናንተ ዛሬ ጌታን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በጌታ ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል። ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የጌታ ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ ጌታ ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፤ ከአምላካችንም ከጌታ መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በጌታና በእኛ ላይ አታምፁ። የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ስላልታመነ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቁጣ አልወረደምን? እርሱም በበደሉ ብቻውን አልሞተም።’ ” የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ነገድ አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው፦ “የአማልክት አምላክ ጌታ! የአማልክት አምላክ ጌታ! እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ራሱ ይወቀው፤ በጌታ ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደሆነ ዛሬ አታድነን፤ ጌታን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቁርባን እንድናሳርግበት፥ የአንድነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደሆነ ጌታ እርሱ ራሱ ይበቀለን፤ ይልቁንም ይህን ያደረግነው ከልባችን ፍርሃት የተነሣ ሲሆን እንዲህም አልን፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ ‘ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ጋር ምን ነገር አላችሁ? እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ ጌታ በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በጌታ ዘንድ ድርሻ የላችሁም ይሉአቸዋል።’ በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን ጌታን እንዳይፈሩ ያደርጓቸዋል። ስለዚህም፦ ‘ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ያልሆነን መሠዊያ እንስራ አልን፤ ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቁርባን በአንድነትም መሥዋዕታችን ጌታን እንድናገለግል፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻንን፦ “በጌታ ዘንድ ድርሻ የላችሁም” እንዳይሉ ምስክር ይሆናል።’ ስለዚህም እንዲህ አልን፦ በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ እኛ እንዲህ እንላለን፦ ‘እነሆ፥ አባቶቻችን የሠሩትን የጌታን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፤ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለማቅረብ አይደለም።’ በማደሪያው ፊት ለፊት ካለው ከአምላካችን ከጌታ መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቁርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በጌታ ላይ በማመፅ ጌታንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ።” ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ነገድ አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃላት በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “ይህን መተላለፍ በጌታ ላይ አላደረጋችሁምና ጌታ በመካከላችን እንዳለ ዛሬ አውቀናል፤ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከጌታ እጅ አድናችኋል።” የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም ይዘውላቸው መጡ። ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፤ የእስራኤልም ልጆች ጌታን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ለማጥፋት ወጥተን እንወጋታለን ብለው አልተናገሩም። የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም፦ “ጌታ አምላክ እንደሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው” ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት። እንዲህም ሆነ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ፥ ጌታም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ባሳረፋቸው ጊዜ፥ ኢያሱም በሸመገለ ዕድሜውም በገፋ ጊዜ፥ ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ ሽማግሌዎቻቸውንም አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምንቶቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ሸምግያለሁ፥ ዕድሜዬም ገፍቷል፤ እናንተም ጌታ አምላካችሁ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ ጌታ አምላካችሁ ነው። እነሆ፥ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታልቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ሰጠኋችሁ። ጌታ አምላካቸሁም እርሱ ከፊታችሁ በብርቱ ገፍቶ ያስወጣቸዋል፥ ከፊታችሁም ያሳድዳቸዋል፤ ጌታ አምላካችሁ እንደ ተናገራችሁም ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ከእነዚህ አሕዛብ ጋር አትቀላቀሉ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ግን ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ተጠጉ። ጌታ ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አሳድዶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። ጌታ አምላካችሁ እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። ጌታን አምላካችሁንም የምትወድዱ መሆናችሁን እጅግ በጥንቃቄ አስተውሉ። እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ከእነርሱ እነርሱም ከእናንተ ጋር በጋብቻ ቢተሳሰሩ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድና አሽክላ፥ ለጎናችሁም መቅሠፍት፥ ለዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ ጌታ አምላካችሁ ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንደማያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ። “እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም ጌታ ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉም ነገር ተከነናውኖላችኋል፤ ከእርሱም አንድም የቀረ ነገር የለም። ጌታ አምላካችሁ የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ተከናወነላችሁ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ ጌታ እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። ጌታ አምላካችሁ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የጌታ ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።” ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምንቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በጌታ ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብጽ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብጽን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን አወጣሁ። አባቶቻችሁንም ከግብጽ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ ጌታም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብጽ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልፈለግሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን በፊታችሁም ተርብ ሰድጄ ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ጌታን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማገልገል ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ ጌታ አምላካችን ነውና። ጌታ አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና ጌታን እናገለግላለን።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና ጌታን ማገልገል አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። ጌታን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን እናገለግላለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እንድታገለግሉት እናንተ ጌታን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ፤” እነርሱም፦ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ አዘንብሉ።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “ጌታ አምላካችንን እናገለግላለን፥ ድምፁንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም እነዚህን ቃላት በጌታ ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በጌታ መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የተናገረንን የጌታን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል።” ኢያሱም እያንዳንዱን ሰው ሕዝቡን ወደ ርስቱ እዲሄድ አደረገ። እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የጌታ ባርያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ግዛት በተምና-ሴራ ቀበሩት። ኢያሱ በኖረበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የጌታን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል ጌታን አገለገሉ። የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ ብር በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፤ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት። ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በቅድሚያ ይወጣልናል?” ብለው ጌታን ጠየቁ። ጌታም፥ “ይሁዳ በቅድሚያ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ” አለ። ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን፦ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻዬ ወደ ሆነው ምድር አብረን እንውጣ፤ እኔም እንደዚሁ ድርሻህ ወደ ሆነው ምድር አብሬህ እወጣለሁ” አለው። ስለዚህም ከእርሱ ጋር ሄደ። ከዚያ በኋላ ይሁዳ ሕዝብ ዘመተ፤ ጌታም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በቤዜቅም ዐሥር ሺህውን ድል ነሡ። አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ። አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ። አዶኒቤዜቅም፥ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ። የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መተው፥ በእሳት አቃጠሏት። ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፥ በኔጌብና በቈላማው አገር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤ የይሁዳ ሰዎች በኬብሮን በሚኖሩ ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ኬብሮን ቀደም ሲል ቂርያት-አርባዕ ተብላ ትጠራ ነበር፤ እነርሱም ሼሻይን፥ አሒማንንና ታልማይኖችን ድል አደረጉ። ከዚያም ተነሥተው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ፤ የዳቤር የቀድሞ ስም ቂርያት ሴፌር ነበር። ካሌብም፥ “ቂርያት ሴፌርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ። የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ያዛት፥ ልጁንም ዓክሳን ዳረለት። እርሷም ወደ ዖትኒኤል በመጣች ጊዜ፥ ከአባቷ የእርሻ መሬት እንዲጠይቅ መከረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት። እርሷም “የሰጠኸኝ የኔጌብ መሬት በመሆኑ፥ የውሃ ምንጮችን እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት። የቄናዊው የሙሴ አማት ዘሮች ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከዘንባባዋ ከተማ ተነሥተው፥ ዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋር አብረው ሄዱ፥ እዚያም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ። የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋር ሆነው በጽፋት ከተማ በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማይቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት፤ ስለዚህ ከተማይቱ ሖርማ ተብላ ተጠራች። ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛን ከነግዛቶቿ፥ አስቀሎን ከነግዛቶቿ፥ አቃሮን ከነግዛቶቿ ያዙ። ጌታ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳማው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም። ሙሴም እንደ ተናገረው ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዐናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ። ነገር ግን የብንያም ሰዎች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ አላስወጧቸውም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያን ጋር በዚያ አብረው ይኖራሉ። የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ሊወጉ ወጡ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ነበር። እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፥ ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማይቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት። እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተሰቡ በስተቀር የከተማይቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ። ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው። የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፥ በታዕናክ፥ በዶር፥ በይብለዓም፥ በመጊዶንና በየአካባቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፥ ከነዓናውያን ኑሮአቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ። እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም። እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ። ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከለቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው። አሴርም በዓኮ፥ በሲዶን፥ በአሕላብ፥ በአክዚብ፥ በሒልባ፥ በኣፌቅና በረአብ የሚኖሩትን ሕዝብ በምድሪቱ ካሉት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ። በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ። ንፍታሌምም በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጉልበት ሥራ ተገደው ይሠሩ ነበር። የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም። አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፥ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም። የአሞራውያን ድንበር አቅራቢያም መተላለፊያ እስከ ሴላዕና ከዚያም የሚያልፍ ነበር። የጌታ መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድነው? ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” የጌታም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። ያንን ስፍራ ቦኪምሠ ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለጌታ መሥዋዕት አቀረቡ። ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደ የርስቱ ሄደ። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ ጌታ ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ ጌታን አመለኩ። የጌታ አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በቲምናሔሬስ ቀበሩት። ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ ጌታንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። ከዚያም እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ተው፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኩአቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም፤ ጌታንም አስቈጡት፤ ጌታን ትተው በዓልንና አስታሮትን አመለኩ፤ ስለዚህ ጌታ በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደተናገረውና እንደማለው እንዲሸነፉ የጌታ እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ። ጌታም ከእነዚህ ወራሪዎች እጅ የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሣላቸው። እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው ጌታን በመታዘዘ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፥ አባቶቻቸው የጌታን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። ጌታ መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ ከመስፍኑ ጋር ስለሚሆን፥ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ጌታ ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ ጌታ ይራራላቸው ነበር። መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፥ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር። ስለዚህ ጌታ በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለተላለፈ፥ እኔንም ስላልሰማ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። ይህን የሚያደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፥ እስራኤላውያን የጌታን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” ስለዚህ ጌታ እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳዶ አላስወጣቸውም። በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፥ ጌታ ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው። እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማትስ መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነርሱም ጌታ በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከአሞራውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ አምላካቸውን ጌታንም ረሱ፤ በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። ጌታ በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኩሽን-ሪሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ለኩሽን-ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ ጌታ በጮኹ ጊዜ ግን፥ ጌታ የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የጌታም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ ጌታ የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሽን ሪሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሽን-ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች። እስራኤላውያን እንደገና በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ይህን ክፋት በጌታ ፊት በማድረጋቸው፥ ጌታ የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎን በእስራኤል ላይ እንዲበረታባቸው አደረገ። እርሱም አሞናውያንንና አማሌቃውያንን ካስተባበረ በኋላ እስራኤልን ወግቶ የዘንባባ ዛፎችበ ከተማ የሆነችውን ኢያሪኮን ያዙ። እስራኤላውያንም ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን ዐሥራ ስምንት ዓመት ተገዘሉት። እስራኤላውያን እንደገና ወደ ጌታ ጮኹ፤ ጌታም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ፥ ግራኙን፥ ኤሁድን ነጻ እንዲያወጣቸው አስነሣው። እስራኤላውያን ኤሁድን ግብር አስይዘው ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት። እርሱም በሁለት በኩል ስለታም የሆነና አንድ ክንድ ተኩል ርዝመትተ ያለው ሰይፍ አዘጋጅቶ በልብሱ ውስጥ በቀኝ ጭኑ ላይ አሰረው። ግብሩንም ወፍራም ለነበረው ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን አቀረበ። ኤሁድ ግብሩን ካቀረበ በኋላ፥ ግብር ተሸክመው የመጡትን ሰዎች ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ። እርሱ ራሱ ግን ጌልጌላ አጠገብ ድንጋዮች ተጠርበው ከሚወጡበት አካባቢ ሲደርስ ወደ ኋላ በመመለስ ወደ ንጉሡ ሄዶ፥ “ንጉሥ ሆይ፤ በምስጢር የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። ንጉሡም፥ “ጸጥታ” ሲል፤ አጠገቡ የነበሩትአገልጋዮች በሙሉ ትተውት ወጡ። ንጉሡ ሰገነት ላይ ባለው ነፋሻ ዕልፍኝ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ሳለ ኤሁድ ቀረብ ብሎ፥ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ያመጣሁት መልእክት አለኝ” አለው፤ ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሣ። ኤሁድ ግራ እጁን ሰደድ በማድረግ ሰይፉን ከደበቀበት ከቀኝ ጭኑ መዝዞ በንጉሡ ሆድ ሻጠው። እጀታው ሳይቀር ሰይፉ እንዳለ ሆዱ ውስጥ ገባ፤ ሞራውም ስለቱን ሸፈነው፤ ስለቱም በጀርባው ወጣ፤ ኤሁድ ሰይፉን ስላልነቀለው አንጀቱ ተዘረገፈ። ከዚያም በኋላ ኤሁድ በዕልፍኙ መግቢያ ወጣ፤ የዕልፍኙንም በር በንጉሡ ላይ ዘግቶ ቈለፈው። ኤሁድ ከሄደ በኋላ፥ የንጉሡ አገልጋዮች ሲመጡ፥ የዕልፍኙ በር ተቈልፎ አገኙት፤ እነርሱም፥ “በውስጠኛው ክፍል እየተጸዳዳ ይሆናል” አሉ፤ እስኪደክማቸውም ድረስ ጠበቁ፤ ነገር ግን ንጉሡ የእልፍኙን በሮች ባለመክፈቱ ቊልፍ ወስደው ከፈቱ፤ በዚያም ጌታቸው ሞቶ፥ በወለሉም ላይ ተዘርግቶ አገኙት። የንጉሡ አገልጋዮች በዕልፍኙ በር ላይ ቆመው ሲጠባበቁ ኤሁድ ርቆ ሄደ፤ ድንጋዮች ተጠርበው በሚወጡበት በኩል ወደ ሴርታ ይም አመለጠ። እዚያም እንደ ደረሰ፥ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ እስራኤላውያንም በእርሱ መሪነት ከኰረብታው ላይ አብረውት ወረዱ። እርሱም “ጠላታችሁን ሞዓብን ጌታ በእጃችሁ አሳልፎ ስለሰጣችሁ ተከተሉኝ” በማለት አዘዛቸው፤ እነርሱም ተከትለውት ወረዱ፤ ከዚያም ከዮርዳኖስ ወደ ሞዓብ የሚያሻግሩትን ስፍራዎች በመያዝ አንድም ሰው እንዳያልፍ ከለከሉ። በዚያን ጊዜ ብርቱና ይለኛ የሆኑ ዐሥር ሺህ ሞዓባውያንን ገደሉ፤ አንድም ሰውአላመለጠም። በዚያን ቀን ሞዓብ በእስራኤል ድል ሆነች፤ ምድሪቱም ለሰማንያ ዓመት ሰላም አገኘች። ከኤሁድ በኋላ ስድስት መቶ ፍልስጥኤማውያንን በበሬ መንጃ የገደለው የዓናት ልጅ ሻምጋር ተነሣ፤ እርሱም እንደዚሁ ደግሞ እስራኤልን አዳነ። ኤሁድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደገና በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ። ስለዚህም ጌታ በሐጾር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነዓን ንጉሥ ለያቢን አሳልፎ ሰጣቸው። የያቢን ሠራዊት አዛዥ፥ በሐሮሼትሐጎይም የሚኖረው ሲሣራ ነበረ። እርሱም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩት እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት እጅግ አስጨነቃቸው፤ እነርሱም ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጌታ ጮኹ። በዚያን ጊዜ የለፊዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበረች። እርሷም በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፥ በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እርሷ ይመጡ ነበር። ዲቦራ በንፍታሌም ውስጥ ቃዴስ በተባለች ከተማ ይኖር የነበረውን የአቢኒኤምን ልጅ ባራቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ሲል ያዝሃል፤ ‘ተነሣ፤ ከንፍታሌምና ከዛብሎን ዐሥር ሺህ ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፤ እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አዛዥ ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ጋር ቂሶን ወንዝ እንዲመጣ አነሣሣዋለሁ፤ በእጅህም አሳልፌ እሰጥሃለሁ።’” ባራቅም፥ “አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት። ዲቦራ መልሳ፥ “ይሁን እሺ፤ መሄዱን አብሬህ እሄዳለሁ፤ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ግን ክብሩ ለአንተ አይሆንም፤ ጌታ ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና” አለችው። ስለዚህ ዲቦራ ከባራቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች፤ ባራቅ ለዛብሎንና ለንፍታሌም ሰዎች ጥሪ አስተላለፈ፤ ዐሥር ሺህ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም አብራው ሄደች። በዚያን ጊዜ ቄናዊው ሔቤር፥ ዐማች የአባብ ልጆች ከሆኑት ከሌሎቹ ቄናውያን ተለይቶ በቃዴስ አጠገብ ጻዕናይም ከተባለ ቦታ ከሚገኘው ባሉጥ ዛፍ አጠገብ ድንኳኑን ተክሎ ነበር። የአቢኒዔም ልጅ ባራቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱን ሲሣራ በሰማ ጊዜ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከሐሮሼት ሐጎይም እስከ ቂሶን ወንዝ ያለውን ሠራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ። በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባራቅን፥ “ተነሣ! ጌታ ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሰጠባት ቀን ይህች ናት፤ እነሆ ጌታ በፊትህ ቀድሞ ወጥቶአል” አለችው። ስለዚህ ባራቅ ዐሥር ሺህ ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ። ጌታም ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባራቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። ባራቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሠራዊቱን እስከ ሐሮሼት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሠራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። በሐጾር ንጉሥ በየቡስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደ ሆነችው ወደ ያዔል ድንኳን ሮጠ። ያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበ ለችውና፥ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው። ሲሣራም፥ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ጮጮውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደገናም ሸፈነችው። እርሱም፥ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፥ ‘እዚህ ሰው አለ?’ ቢልሽ፥ ‘የለም በይ’” አላት። የሔቤር ሚስት ያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፥ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፥ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋር ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ። ባራቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፥ ያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከእርሷ ጋር ወደ ድንኳንዋ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ። በዚያች ዕለት እግዚአብሐር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው። ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ። በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባራቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ፦ በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ ጌታን አመስግኑ። ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፥ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ እዘምራለሁ። አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፥ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ። ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ፊት፥ በሲናው ጌታ ፊት ተራሮች ቀለጡ። በዓናት ልጅ በሻምጋር ዘመን፥ በያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፥ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር። አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም። አዲሶች አማልክትን መረጡ፥ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፥ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም። ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፥ ጌታን አመስግኑ። በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ። በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የጌታን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፥ ከዚያም በኋላ የጌታ ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ። ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፥ ባራቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ። በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፥ ጌታም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ። በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፥ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ። የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፥ ይሳኮርም እንደ ባራቅ ነበረ፥ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፥ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ። መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ። ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፥ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ። ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው። ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። የጌታ መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ ጌታን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ ጌታን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥ በተከበረ ጽዋ እርጎ አቀረበችለት። እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦ “ስለምን ለመምጣት ሠረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሠረገላው መንኰራኵር ቈየ?” ብላ ጮኸች። ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥ እርሷ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ “ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጉርጉር ልብስ።” አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች። እንደገና እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ጌታም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ገዟቸው። እስራኤላውያን የምድያማውያን ኃይል ስለበረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፥ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ። እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፥ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር። እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህልዘር አያስተርፉም፥ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር። ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቁጠር አዳጋች ሲሆን፥ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር። ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለጣሏቸው፥ ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጌታ ጮኹ። ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ ጌታ ጮኹ። ጌታ አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ።” እናንተንም፥ “‘እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።” የጌታ መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፥ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፥ ምድያማውያን እንዳያዩት ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” ጌታም፥ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፥ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። የጌታ መልአክ፥ “ሥጋውን እርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፥ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የጌታ መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የጌታን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። ጌታም፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ጌታ ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። በዚህ ፍርስራሽ ጉብታ ላይ ለአምላክህ ለጌታ የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር። ሌሊቱ ነግቶ የከተማው ሕዝብ ከመኝታው ሲነሣ፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ በአጠገቡ የቆመው የአሼራ ምስል ተሰባብሮ፥ አዲስ በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ወይፈን ተሠውቶ ነበር። እነርሱም፥ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ነገሩን በጥብቅ ሲከታተሉም፥ “የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት።” የከተማይቱም ሰዎች ኢዮአስን፥ “የበኣልን መሠዊያ ያፈረሰና በአጠገቡ የቆመውን የአሼራን ምስል ዐምድ የሰበረው ልጅህ በመሆኑ መሞት ስላለበት አውጣልን አሉት።” በዚህ ጊዜ ኢዮአስ በቊጣ ለገነፈለውና በዙሪያው ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ለበኣል ትሟገቱለታላችሁን? ልታድኑትስ ትሞክራላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ቢኖር እስከ ጠዋት ይሙት! እንግዲህ በኣል በእርግጥ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ሊከላከል ይችላል።” ስለዚህም፥ “መሠዊያውን አፍርሶበታልና ራሱ በኣል ይሟገተው” ሲሉ በዚያ ዕለት ጌዴዎንን፥ “ይሩበኣል” ብለው ጠሩት። በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፥ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ያላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ። ከዚያም የጌታ መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ እርሱም መለከት ነፋ፤ አቢዔዝራውያን እንዲከተሉት ጠራቸው። እንዲሁም በመላው የምናሴ ምድር መልእክተኞቹን ልኮ እንዲከተሉት ጥሪ አደረገ፤ ደግሞም የአሴር፥ የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች ወጥተው እንዲገጥሟቸው መልእክተኛ ላከባቸው። ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “በተናገርኸው መሠረት እስራኤላውያንን በእጄ የምታድናቸው ከሆነ፥ እነሆ፤ የበግ ጠጉር ባዘቶ በአውድማው ላይ አኖራለሁ። ምድሩ በሙሉ ደረቅ ሆኖ ባዝቶው ላይ ብቻ ጤዛ ቢኖር፥ እንዳልከው እስራኤላውያንን በእኔ እጅ እንደምታድናቸው አውቃለሁ።” እንደዚሁም ሆነ፤ ጌዴዎን በማግስቱ ጠዋት ማልዶ ተነሣ፤ ባዘቶውንም ሲጨምቅ የወጣው ውሃ አንድ ቆሬ ሞላ። ከዚያም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ አንዲት ጥያቄ እንደገና ልጠይቅ። በጠጉሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፤ በዚህ ጊዜ ምድሩ ሁሉ በጤዛ ተሸፍኖ ባዘቶው ደረቅ ይሁን።” በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር እንደጠየቀው አደረገ፤ ባዘቶው ብቻ ደረቅ ሲሆን፥ ምድሩ በሙሉ በጤዛ ተሸፍኖ ነበር። ይሩበኣል የተባለው ጌዴዎን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጠዋት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተ ሰሜን በኩል፥ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ። ጌታም ጌዴዎንን፦ ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፥ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም። አሁንም እንግዲህ፦ የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ ዐሥርም ሺህ ቀሩ። ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እጸልይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ’ የምለው፥ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን፥ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ’ የምለው፥ ከአንተ ጋር አይሄድም።” ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዞአቸው ወረደ፤ እዚያም ጌታ፥ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፥ በምላሳቸው የሚጠጡትን፥ በጉልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው። ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጉልበታቸው ተንበረከኩ። ጌታም ጌዴዎንን፥ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችሃለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው። ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ። በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆአማው ውስጥ ነበር። በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና። አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፥ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ። ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፥ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም። አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፥ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፥ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታተም ኀይለኛነት የተነሣድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር። ጓደኛውም መልሶ፥ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው። ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለጌታ ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፥ “ጌታ የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ!” አላቸው። ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፥ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ። ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ “እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ። እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻቸሁን እየነፋችሁ፥ ‘ለጌታና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።” ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፥ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ። በሦስት ቡድን የተከፈሉት ሰዎች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ማሰሮቻቸውንም ሰበሩ፤ ችቦዎቻቸውን በግራ እጆቻቸው፥ ቀንደ መለከቶቻቸውንም በቀኝ እጆቻቸው ይዘው፥ “የጌታና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ። እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ የተመደበበትን ቦታ እንደያዘም ምድያማውያኑ እየጮሁ ሸሹ። የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደተሰማም ጌታ በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሠራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ እስከ ቤትሺጣ፥ ከዚያም አልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልመሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ። በንፍታሌም፥ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ። ጌዴዎንም በኤፍሬም ኰረብታማ አገር ለሚኖሩት ሁሉ፥ “በምድያማውያን ላይ ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስ ወንዝ ቀድማችሁ ያዙ” አላቸው። ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጡ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስን ወንዝ ያዙ። እንዲሁም ሔሬብና ዜብ የተባሉትን ሁለቱን የምድያም መሪዎች ያዙ። ሔሬብን በሔሬብ ዐለት አጠገብ፥ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሏቸው፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብን ራስ ቈርጠው ጌዴዎን ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ይዘው መጡ። በዚያን ጊዜ የኤፍሬም ሰዎች፥ “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ ለምን አልጠራኸንም? ለምንስ እንዲህ ያለ ነገር አደረግህ?” በማለት ጌዴዎንን እጅግ ነቀፉት። ጌዴዎን ግን፥ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር የእኔ ከምን ይቈጠራል? የኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ተጠቃሎ ከገባው ከአቢዔዝር የወይን መከር አይበልጥምን? እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቊጣቸው በረደ። ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር። የሱኮትንም ሰዎች፥ “የምድያምን ነገሥታት ዜባሕንና ጻልሙናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንኩ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙ ብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው። የሱኮት ሹማምንት ግን፥ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት። ጌዴዎንም መልሶ፥ “እንግዲህ ደህና፤ ጌታ ዜባሕንና ጻልሙናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እገርፋለሁ” አላቸው። ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር ተመሳሳይ ነበር። እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፥ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ዜባሕና ጻልሙና ዐሥራ አምስት ሺህ ከሆነ ሠራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺህ ሰይፍ ታጣቂ ሠራዊት የተረፈው ነበር። ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሠራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ። ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ጻልሙና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳዶ ያዛቸው፤ መላ ሠራዊታቸውንም እጅግ በታተነው። ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ ዳገት በኩል ከጦርነቱ ተመለሰ፤ እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምንትና የከተማይቱንም አለቆች ስም ጻፈለት። ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዜባሕና ጻልሙና እነዚሁላችሁ።” ጌዴዎን የከተማይቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው። እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማይቱንም ሰዎች ገደለ። ዜባሕና ጻልሙናንም፥ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሁሉም እንዲህ እንዳንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት። ጌዴዎንም፥ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው ጌታ ስም አረጋግጥላችሁ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። ከዚያም የበኲር ልጁ ወደ ሆነው ዮቴር ዘወር ብሎ፥ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። ዜባሕና ጻልሙናም፥ “የሰው ጉልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና፥ አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤” ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ። እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፥ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፥ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት። ጌዴዎን ግን መልሶ፥ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ ጌታ ነው” አላቸው። እርሱም “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጉትቻችሁን እንድትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጉትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና። እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጉትቻ ጣል ጣል አደረጉለት። ሌሎቹን ጌጣ ጌጦች ይኸውም የአንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፥ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው አንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጉትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል ያህል መዘነ። ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፥ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ። ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች። የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፥ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን ጌታ አምላካቸውን አላሰቡትም። እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም። የይሩባኣል ልጅ አቤሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቁራጭ፥ ያጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።” የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል” ብለዋልና፥ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ወደሱ አዘነበለ። እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት። ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ። የሴኬምና የቤትሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ። ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፥ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምጽን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፥ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤ ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፥ “አንተ ንጉሣችን ሁን” አሉት። የወይራ ዛፍም፥ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፥ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?” አለ። ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፥ “መጥተህ ንጉሣችን ሁን” አሉት። በለስ ግን፥ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፥ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?” አለ። ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፥ “መጥተህ ንጉሣችን ሁን” አሉት። የወይን ተክሉም፥ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፥ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን?” አለ። በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቊጥቋጦን፥ “መጥተህ ንጉሣችን ሁን” አሉት። የእሾኽ ቊጥቋጦውም ዛፎቹን፥ “በእርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾ ቊጥቋጦው ይነሣ፤ የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ” አላቸው። “እንግዲህ አቤሜሌክን ስታነግሡት በቅንነትና በእውነት አድርጋችሁት ከሆነ፥ ይሩበኣልንና ቤተሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፥ አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፥ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን አሰባችሁ ማለት ነው። ነገር ግን እናንተ ዛሬ በአባቴ ቤተሰብ ላይ ዐመፃችሁ፤ ሰባ ልጆቹን በአንዲት ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ዘመዳችሁ ስለ ሆነም አባቴ ከባርያው የወለደውን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ነዋሪዎች ላይ አነገሣችሁት። እንግዲህ ዛሬ በይሩበኣልና በቤተሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና በቅንነት ከሆነ እናንተ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቤሜሌክ ትውጣና እናንተን፥ የሴኬምንና የቤትሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፥ ከሴኬምና ከቤትሚሎን ነዋሪዎች ትውጣና አቤሜሌክን ትብላ።” ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር። አቤሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፥ እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ነዋሪዎች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቤሜሌክን ከዱት። እግዚአብሔር ይህን ያደረገውም፥ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፥ ወንድማቸውን አቤሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ሰዎች ለመበቀል ነው። የሴኬም ነዋሪዎችም አቤሜሌክን ሸምቀው የሚጠባበቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቤሜሌክ ደረሰው። በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች ተማመኑበት። ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቤሜሌክን ሰደቡ። የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቤሜሌክ እንገዛለን? ምነው ይህን ሕዝብ የማዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ፥ አቤሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሠራዊትህን አብዝተህ እስቲ ውጣ! እለው ነበር።’” የከተማይቱ ገዥ ዜቡል፥ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ወደ አቤሜልክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማይቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል። ስለዚህ በሌሊት ሰዎችህን ይዘህ ወጥተህ ሜዳው ላይ ማድፈጥ አለብህ፤ ጠዋት ፀሓይ ስትወጣም ወደ ከተማይቱ ገሥግሥ፤ ገዓልና ሰዎቹ ሊገጥሙህ በሚወጡበት ጊዜ እጅህ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርግ።” ስለዚህ አቤሜሌክና ሰዎቹ በሙሉ በሌሊት ወጡ፤ በአራት ምድብ ሆነውም በሴኬም አጠገብ አደፈጡ። የአቤድ ልጅ ገዓል ከከተማይቱ ወጥቶ በመግቢያው በር ላይ ሲቆም፥ አቤሜሌክና ሰዎቹ ካደፈጡበት ወጡ። ገዓል ባያቸው ጊዜ ዜቡልን፥ “ተመልከት፤ ከተራራው ጫፍ ሕዝብ እየወረደ ነው” አለው። ዜቡልም መልሶ፥ “የተራሮች ጥላ ሰዎች መስሎ ተሳስተህ ነው” አለው። ገዓልም፥ “ተመልከት እንጂ ሕዝብ እኮ ከተራራው ወገብ ላይ እየደረሰ ነው፤ አንዱ ክፍልም በአስማተኞች የባሉጥ ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” ብሎ እንደገና ተናገረ። ከዚያም ዜቡል፥ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜልክ ማን ነው? ብለህ የደነፋኸው አሁን የት አለ? ያቃለልካቸውስ ሰዎች እነዚህ አይደሉምን? በል ውጣና ግጠማቸው” አለው። ገዓል የሴኬምን ሰዎች መርቶ በመውጣት አቤሜሌክን ተዋጋው፤ ሆኖም አቤሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ። አቤሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው። በማግስቱ የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቤሜሌክ ተነገረው፤ እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቤሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማይቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ። ከዚያም አቤሜሌክና አብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማይቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፥ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው። በዚያን ዕለት አቤሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማይቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማይቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት። በሴኬም ግምብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ። አቤሜሌክም በዚያ መመሸጋቸውን ሲሰማ፥ እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውምላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፥ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው። ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቤሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ምሽግ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ። ከዚያም አቤሜሌክ ወደ ቴመስ በመሄድ ከተማይቱን ከቦ ያዛት። ሆኖም በከተማይቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፥ የከተማይቱ ሕዝብ በሙሉ ወንድ ሴት ሳይባል ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣሪያ ወጡ። አቤሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኮስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፥ አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በራሱ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው። ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፥ “‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ። እስራኤላውያንም አቤሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ወደየቤታቸው ተመለሱ። አቤሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ ስላደረሰው በደል እግዚአብሔር የእጁን ከፈለው። በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰው፤ የይሩበኣል ልጅ የኢዮአታም ርግማን ደረሰባቸው። ከአቤሜሌክ በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ፥ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ሳምር በምትባል መንደር ይኖር ነበር። ቶላ በእስራኤል ላይ ሃያ ሦስት ዓመት በፈራጅነት ከተቀመጠ በኋላ ሞተ፤ በሳምርም ተቀበረ። ከቶላ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ያኢር ተነሣ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ ሃያ ሁለት ዓመት በፈራጅነት ተቀመጠ። ያኢር በሠላሳ አህዮች የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ልጆቹም እስከ ዛሬ ድረስ የያኢር መንደሮች ተብለው የሚጠሩ ሠላሳ ከተሞች በገለዓድ ምድር ነበሯቸው። ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ። እስራኤላውያን እንደገና በጌታ ላይ ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ በኣልንና አስታሮትን እንዲሁም የሶሪያን፥ የሲዶናን፥ የሞዓብን፥ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፤ እስራኤላውያን ጌታን ስለተዉና ስላላገለገሉት፥ የጌታ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በፍልስጤማውያንና በአሞናውያን እጅም አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፥ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ዐሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው። የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፥ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ። “ከዚያም እስራኤላውያን አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደ ጌታ ጮኹ። ጌታም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብፃውያን፥ አሞራውያን፥ አሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያን፥ ሲዶናውያን፥ አማሌቃውያንና ማዖናውያን አሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን? እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤ ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስቲ ያድኗችሁ” እስራኤላውያንም ጌታን፥ “ኃጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤ ጌታንም አመለኩ፤ እርሱም የእስራኤልን መከራ ሊታገሠው የማይቻለው ሆነ። አሞናውያን ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በገለዓድ በሰፈሩ ጊዜ፥ እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ። የገለዓድ ሕዝብ አለቆችም እርስ በእርሳቸው፥ “በአሞናውያን ላይ ጦርነቱን የሚጀምር ሰው በገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል” ተባባሉ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ኃያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች። የገለዓድ ሚስትም ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፥ “ከሌላ ሴት ስለተወለድህ ከቤተሰባችን ምንም ዓይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት። ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፥ የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ። እነርሱም፥ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት። ዮፍታሔም፥ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው። የገለዓድ አለቆችም፥ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት። ዮፍታሔም፥ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና ጌታ በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው። የገለዓድ አለቆችም፥ “ጌታ ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት። ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በጌታ ፊት ደገመው። ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፥ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ። የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፥ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው። ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ። እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፥ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ። “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፥ በምድረ በዳው ተጉዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም። “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፥ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው። ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሠራዊቱንም ሰብስቦ በያሃጽ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። “ከዚያም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤” አሸነፏቸውም፤ እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤ ከአርኖን እስከ ያቦቅ፥ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ። “እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ጌታ አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳዶ ካስወጣቸው፥ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ? አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ አይደለምን? እኛስ እንደዚሁ አምላካችን ጌታ የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን ልንወርስ አይገባንምን? አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቶአልን? ወይስ ተዋግቶአልን? እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለምን አልወሰዳችኋቸውም? እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጅ የሆነው ጌታ በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።” የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም። ከዚያም የጌታ መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ፤ ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው። ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለጌታ ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለጌታ ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ጌታ እነርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ። ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፥ “ወይኔ ልጄ ጉድ አደረግሽኝ ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለጌታ ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ። እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለጌታ ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን ጌታ ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ። ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።” እርሱም፥ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ። ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፥ የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ኀዘን ያደርጉላታል። የኤፍሬም ሰዎች ኃይላቸውን አሰባስበው ወደ ጻፎን በመሻገር ዮፍታሔን፥ “አሞናውያንን ለመውጋት ስትወጣ አብረንህ እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምንድን ነው? ቤትህን በላይህ ላይ እናቃጥለዋለን አሉት።” ዮፍታሔም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔና ሕዝቤ ከአሞናውያን ጋር ከፍተኛ ትግል ገጥመን በነበረበት ጊዜ ጠርቼያችሁ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም፤ እኔም እንደማትረዱኝ በተረዳሁ ጊዜ በሕይወቴ ቈርጬ አሞናውያንን ለመውጋት ተሻገርሁ፤ ጌታም ድሉን ሰጠኝ፤ ታዲያ ዛሬ እኔን ለመውጋት የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ከዚያም ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋር ተዋጋ። ኤፍሬማውያን ገለዓዳውያንን፥ “እናንተ ገለዓዳውያን ከኤፍሬምና ከምናሴ የከዳችሁ ናችሁ” ይሏቸው ስለ ነበር በብርቱ መቷቸው። ገለዓዳውያን ወደ ኤፍሬም የሚያሻግሩትን የዮርዳኖስን መሻገሪያዎች ያዙ፤ ታድያ አምልጦ የሚሸሽ አንድ ኤፍሬማዊ ለመሻገር በሚጠይቃቸው ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ ያም ሰው፥ “አይደለሁም” ብሎ ከመለሰላቸው፥ እስቲ “ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ ታዲያ ቃሉን በትክክል ማለት ሳይችል ቀርቶ “ሲቦሊት” ካለ ይዘው እዚያው መሻገርያው ላይ ይገድሉታል፤ በዚያ ጊዜም አርባ ሁለት ሺህ ኤፍሬማውያን ተገደሉ። ዮፍታሔ በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ። ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። እርሱም ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ሴቶች ልጆቹንም ከጐሣው ውጭ ለሆኑ ሰዎች ዳራቸው፤ ጐሣው ውጭ የሆኑ ሠላሳ ልጃገረዶች አምጥቶ ከወንዶች ልጆቹ ጋር አጋባቸው። ኢብጻን በእስራኤል ላይ ሰባት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ኢብጻን ሞተ፤ በቤተልሔምም ተቀበረ። ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ዐሥር ዓመት ፈራጅ ሆነ። ከዚያም ኤሎም ሞተ፤ በዛብሎን ምድር በኢያሎን ተቀበረ። ከኤሎም ቀጥሎ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ፈራጅ ሆነ። እርሱም በሰባ አህዮች ላይ የሚቀመጡ አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ወንዶች የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ከዚያም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፤ ኰረብታማ በሆነው በአማሌቃውያን አገር በኤፍሬም ምድር በጲርዓቶን ተቀበረ። እስራኤላውያን እንደገና በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ስለዚህም ጌታ በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው። ማኑሄ የተባለ ከዳን ወገን የተወለደ አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስተ መካን ስለ ነበረች ልጅ አልወለደችም። የጌታም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኩስ ነገርም አትብይ፤ ምክንያቱም ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል።” ከዚያም ሴቲቱ ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ የሚመስልና እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር። ከየት እንደመጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤ ነገር ግን፥ ‘ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኩስ ነገር አትብይ፤ ልጁም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና’ ብሎኛል።” ከዚያም ማኑሄ፥ “ጌታ ሆይ፥ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ አንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደኛ የላከው የእግዚአብሔር ሰው እንደገና እንዲመጣ እለምንሃለሁ” ብሎ ወደ ጌታ ጸለየ። እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም። እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፥ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው። ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደደረሰም፥ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው። ማኑሄም፥ “ያልከው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው። የጌታም መልአክ እንዲህ አለው፤ “ሚስትህ የነገርኋትን ሁሉ ታድርግ። ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኩስ ነገር አትብላ፤ እኔ ያዘዝኳትን ሁሉ ታድርግ።” ከዚያም ማኑሄ የጌታን መልአክ “የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይ” አለው። የጌታም መልአክ፥ “የግድ ብታቈየኝ እንኳ የምታቀርበውን ማንኛውንም ምግብ አልበላም፤ ነገር ግን የሚቃጠል መሥዋዕት የምታዘጋጅ ከሆነ እርሱን ለጌታ አቅርበው” አለው። የሚያነጋግረው የጌታ መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። ማኑሄ የጌታን መልአክ፥ “የተናገርከው ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” በማለት ጠየቀው። የጌታም መልአክ፥ “ስሜ ድንቅ ስለ ሆነ፥ ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው። ማኑሄም የፍየሉን ጠቦት ከእህል ቁርባኑ ጋር ወስዶ በዐለት ላይ ለጌታ ሠዋው። ማኑሄና ሚስቱ እያዩ ጌታ አስደናቂ ነገር አደረገ፤ የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ፥ የጌታ መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ዐረገ። ማኑሄና ሚስቱ ይህን ሲመለከቱ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። የጌታም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ ባለመገለጡ፥ ቀደም ሲል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ መሆኑን ማኑሄ ዐወቀ። ሚስቱንም፥ “እግዚአብሔርን ስላየን ያለ ጥርጥር እንሞታለን” አላት። ሚስቱ ግን መልሳ እንዲህ አለችው፥ “ጌታ ሊገድለን ቢፈልግ ኖሮ፥ የሚቃጠለውን መሥዋትና የእህል ቁርባኑን ከእጃችን ባልተቀበለን፤ ደግሞም ይህን ነገር ሁሉ ባላሳየንና እንዲህ ያለውንም ነገር በዚህ ጊዜ ባልነገረን ነበር።” ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁ አደገ፤ ጌታም ባረከው፤ የጌታም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ሳለ ያነቃቃው ጀመር። ሶምሶን ወደ ቲምና ወረደ፤ እዚያም አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አየ። እንደተመለሰም አባቱንና እናቱን፥ “በቲምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው። አባቱና እናቱም፥ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት አሕዛብ ዘንድ ሚስት ፍለጋ የሄድከው?” አሉት። ሳምሶንም አባቱን፥ “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን አጋባኝ” አለው። በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ገዦቹ ፍልስጥኤማውያን ስለ ነበሩ፥ ከፍልስጥአማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር ጌታ ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሆኑን አባቱና እናቱ አላወቁም ነበር። ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናንቱ ጋር ወደ ቲምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፥ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። በዚህ ጊዜ የጌታ መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደርገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር። ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት። ከጥቂት ቀን በኋላም ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት፤ በእጁ ወስዶም መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ከወላጆቹም ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ። ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን መሆኑን አልነገራቸውም ነበር። የሳምሶን አባት ልጅቱን ሊያይ ወረደ፤ ሳምሶንም በወጣቶች የተለመደ በነበረው መሠረት በዚያ ግብዣ አደረገ። እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፥ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት። ሳምሶን እንዲህ አላቸው፤ “እንድ እንቈቅልሽ እነግራችኋለሁ፤ ታዲያ ፍቺውን በሰርጉ በዓል ሰባት ቀኖች ውስጥ ከሰጣችሁኝ፥ ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጣችኋለሁ። እንቈቅልሹን ካልፈታችሁልኝ ግን ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳውን የክት ልብስ እናንተ ትሰጡኛላችሁ።” እነርሱም፥ “በል እንቈቅልሽህን ንገረንና እንስማው” አሉት። ሳምሶንም፥ “ከበላተኛው መብል፥ ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው። እነርሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቈቅልሹን መፍታት አልቻሉም ነበር። በአራተኛው ቀን የሳምሶንን ሚስት፥ “የእንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን፤ ጠርታችሁ የጋበዛችሁን ልትዘርፉን ነው እንዴ?” አሏት። ከዚያ የሳምሶን ሚስት ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ከፊቱ በመቅረብ፥ “ለካስ ትጠላኛለህ በእርግጥ አትወደኝም” አለችው። እርሱም፥ “ይህን ለአባቴም ሆነ ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት። ሚስቱም በሰርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ እያለቀሰች ጨቀጨቀችው፤ አጥብቃ ስለ ነዘነዘችውም በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርሷም በበኩሏ የእንቈቅልሹን ፍች ለሕዝቧ ነገረች። በሰባተኛው ቀን ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት የከተማው ሰዎች፥ “ከማር የጣፈጠ ምን ተገኝቶ? ከአንበሳስ ወዲያ ብርቱ ከየት መጥቶ” አሉት። ሳምሶንም መልሶ፥ “በጊደሬ ባላረሳችሁ፥ እንቈቅልሼንም ባልፈታችሁ” አላቸው። ከዚያም የጌታ መንፈስ በሳምሶን ላይ በኃይል ወረደበት፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል ሠላሳውን ገደለ፤ ያላቸውንም ከገፈፈ በኋላ ልብሶቻቸውን አምጥቶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው። በቁጣ እንደነደደም ተነሥቶ ወደ አባቱ ቤት ወጣ። የሳምሶንም ሚስት ለሚዜው ተዳረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፥ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጉላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም። አባትየውም፥ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከእርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው። ሳምሶንም መልሶ፥ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው። ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋር አሰረው። ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ። ፍልስጥኤማውያን፥ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፥ “ሚስተ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የቲምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ። ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው። ሳምሶንም፥ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ። ክፉኛ መታቸው፤ ከነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኢታም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ። ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ። የይሁዳም ሰዎች፥ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልና ስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው። ከዚያም ሦስት ሺህ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤታም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፥ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። ሳምሶንም፥ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረ ጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው። እነርሱም፥ “አስረን ለፍልስጥአማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት። ሳምሶንም፥ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው። እነርሱም፥ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት። ሳምሶን ሌሒ እንደደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የጌታ መንፈስ በሳምሶን ላይ በኃይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ። ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። ሳምሶንም፥ “በአንድ የአህያ መንጋጋ፥ ሺህ ሰው ዘራሪ፤ በአንድ የአህያ መንጋጋ፥ ሺህ ሬሳ አነባባሪ!” ብሎ ፎከረ። ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒሰ ተብሎ ተጠራ። እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” በማለት ወደ ጌታ ጮኸ። እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውኃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬሸ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል። ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅቀ ሆነ። አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ እዚያም አንዲት ዝሙት አዳሪ አየ፤ አብሮአት ለማደርም ገባ። የጋዛ ሰዎች፥ “ሳምሶን እዚህ ነው!” የሚል ወሬ ደረሳቸው፤ ስለዚህም ሰዎቹ ቦታውን ከበው፤ ሌሊቱን በሙሉ በከተማይቱ ቅጥር በር ላይ አድፍጠው ጠበቊት፤ “በማለዳ እንገድለዋለን” በማለትም ሌሊቱን በሙሉ እንዳደፈጡ አደሩ። ነገር ግን ሳምሶን እዚያ የተኛው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ተነሥቶም የከተማይቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቸ ጋር መወርወሪያውንና ማያያዣውን ጭምር በሙሉ ነቅሎ በትከሻው ላይ ካደረገ በኋላ፥ በኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኰረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞት ወጣ። ከጊዜ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፥ “እርሱን አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብይው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት። ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፥ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቊጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሳምሶንም፥ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው። ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፥ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደሆነ ሊታወቅ አልቻለም። ደሊላም ሳምሶንን፥ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው። እርሱም፥ “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፥ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው። ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፥ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም መልሶ፥ “የራስ ጠጉሬን ሰባት ቈንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጉነሽ በችካል ብትቸክይው፥ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ቈንዳላዎቹን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤ ከችካልም ጋር ቸከለችው። እንደገናም፥ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፥ ከነቈንዳላው ነቀለው። ከዚያም፥ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኃይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው። በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው። ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንኩ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጉር ቢላጭ ግን ኃይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላ ሁሉንም ነገር እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ፥ ለፍልስጥኤማውያን ገዦች “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና ተመልሳችሁ ኑ” ብላ ላከችባቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም ብሩን ይዘው ተመልሰው መጡ። ደሊላ፥ ሳምሶንን በጭኗ ላይ አስተኝታ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገች በኋላ አንድ ሰው ጠርታ ሰባቱን የጠጉር ቈንዳላዎቹን አስላጨቻቸው፤ እርሷም ታስጨንቀው ጀመር፤ ኃይሉም ተለየው። እርሷም፥ “ሳምሶን፤ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቅቶ፥ “እንደ ወትሮው አደርጋለሁ” አለ፤ ነገር ግን ጌታ እንደ ተወው አላወቀም ነበር። ከዚያም ፍልስጥኤማውያን ያዙት፤ ዐይኖቹን አውጥተው ወደ ጋዛ ይዘውት ወረዱ፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም እስር ቤት ውስጥ እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤ ነገር ግን ከተላጨ በኋላ ጠጉሩ እንደገና ማደግ ጀመረ። በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፥ “አምላካችን ዳጎን፥ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ፥ አምላካቸውን ዳጎንን በማመስገን፥ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ብዙ ሰው የገደለብንን፥ ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ። እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፥ “እንዲያዝናናን ሳምሶንን አምጡት” አሉ፤ ስለዚህ ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠርተው አስመጡት፤ በፊታቸውም ተጫወተ። በምሶሶዎቹ መካከል ባቆሙት ጊዜ፥ ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፥ “ቤተ ጣዖቱ ደግፈው ወደ ያዙት ምሰሶዎች አስጠጋኝና ልደገፋቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ቤተ ጣዖቱን ሞልተውት ነበር፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም በሙሉ በዚያ ነበሩ፤ ሳምሶን ሲጫወት ለማየት ሦስት ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ። ሳምሶንም ወደ ጌታ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።” ከዚያም ቤተ ጣዖቱን መካከል ላይ ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አንዱን በቀኙ፥ አንዱን በግራ እጁ አቅፎ በመያዝ፥ “ከፍልስጥኤማውያን ጋር አብሬ ልሙት” በማለት ባለ ኃይሉ ሲገፋው፥ ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው፤ ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤተሰብ ሬሳውን ለማምጣት ወደዚያ ወረዱ፤ አምጥተውም የአባቱ የማኑሄ መቃብር ባለበት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ቀበሩት። ሳምሶን እስራኤልን ለሃያ ዓመት መሪ ሆኖ ነበር። ሚካ የተባለ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር ሰው ነበር። እናቱን፥ “አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ብር ተሰርቆብሽ፥ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት። ከዚያም እናቱ፥ “ልጄ፤ ጌታ ይባርክህ” አለችው። አንድ ሺህ አንድ መቶውን ሰቅል ብር በመለሰላት ጊዜ፥ እናቱ “ብሬን የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት ለማበጀት ስለ ልጄን ለጌታ እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተው መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው። ስለዚህ ብሩን ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱም ከላዩ ሁለት መቶ ጥሬ ብር ወስዳ ለብር አንጥረኛ ሰጠች፤ አንጥረኛውም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት አደረገው፤ ምስሎቹም በሚካ ቤት ተቀመጡ። ሚካ የተባለው ይህ ሰው የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ አንድ ኤፉድና ተራፊም ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው አደረገ። በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። በይሁዳ ምድር፥ በይሁዳ ነገድ መካከል በቤተልሔም የሚኖር አንድ ሌዋዊ ወጣት ነበር። ይህም ሰው ሌላ መኖሪያ ስፍራ ለመፈለግ ከተማይቱን ለቆ ሄደ። በሚጓዘበትም ጊዜ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ወዳለው ወደ ሚካ ቤት መጣ። ሚካም፥ “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “እኔ በይሁዳ ምድር ከምትገኝ ከቤተልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ መኖሪያ ስፍራ እፈልጋለሁ” አለው። ሚካም፥ “እንግዲያውስ አብረኸኝ ተቀመጥ፤ አባትም ካህንም ሁነኝ፤ እኔም በዓመት ዐሥር ሰቅል ብር እንዲሁም ልብስና ምግብ እሰጥሃለሁ” አለው። ስለዚህ ሌዋዊው አብሮት ለመኖር ተስማማ፤ ወጣቱም ለሚካ ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። ሚካም ሌዋዊውን ካህን አድርጎ አስቀመጠው፤ ወጣቱም ካህኑ ሆነ፤ በቤቱም ኖረ። ሚካም፤ “አሁን ሌዋዊ ካህን ስላገኘሁ፥ ጌታ በጎ ነገር እንደሚያደርግልኝ አሁን ተረዳሁ” አለ። በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ የዳን ነገድም በእስራኤል ነገዶች መካከል የርስት ድርሻውን ገና ስላልወሰደ፥ የሚሰፍርበትን የራሱን ርስት ይፈልግ ነበር። ስለዚህ ዳናውያን ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ አምስት ኃያላን ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ወደዚያ ላኩ፤ እነዚህም ነገዶቻቸውን ሁሉ የሚወክሉ ነበሩ። የላኳቸውም ሰዎች፥ “ሂዱ፤ ምድሪቱን ሰልሉ” አሏቸው። መልእክተኞቹም ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ገቡ፤ ወደሚያድሩበትም ወደ ሚካ ቤት መጡ። በሚካ ቤት አጠገብ እንደ ደረሱም የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ ዐወቁ፤ ስለዚህ ወደዚያ ጐራ ብለው፥ “ወደዚህ ያመጣህ ማን ነው? እዚህ ምን ትሠራለህ? የመጣኸውስ ለምንድን ነው?”። ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፥ “ሚካ ይህን ይህን አደረገልኝ፥ ቀጠረኝ፤ ካህኑም ሆንሁ” አላቸው። እነርሱም፥ “መንገዳችን መቃናት አለመቃናቱን እንድናውቅ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት። ካህኑም፥ “የምትሄዱበት መንገድ በጌታ ፊት ነውና በሰላም ሂዱ” ብሎ መለሰላቸው። ስለዚህ አምስቱ ሰዎች ከዚያ ተነሥተው ወደ ላይሽ መጡ፤ ሲዶናውያን ያለ ስጋት በጸጥታ እንደሚኖሩ ሁሉ፥ በዚያም የሚኖረው ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር አዩ። ምድሪቱ አንዳች የሚጐድላት ነገር ባለ መኖሩ ሕዝቡ ባለጸጋ ነበር። እንዲሁም ከሲዶናውያን ርቆ የሚኖር ሲሆን፥ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ግንኙነት አልነበረውም። ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል እንደተመለሱ ወገኖቻቸው፥ “የሄዳችሁበት ጉዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው። መልእክተኞቹም እንዲህ አሏቸው፤ “ምድሪቱ እጅግ መልካም መሆኗን አይተናል፤ እንግዲህ ተነሡ ሄደን እንዋጋቸው፤ ተነሡ እንጂ ዝም ትላላችሁን? ወደዚያው ሄዳችሁ ምድሪቱን ለመያዝ አታመንቱ! እዚያ ስትደርሱም ያለ ሥጋት የሚኖር ሕዝብ፥ እግዚአብሔር በእጃችሁ የሚሰጣችሁን አንዳች ነገር ያልጐደላትን ሰፊ ምድር ታገኛላችሁ።” ከዚያ በኋላም ከዳን ወገን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ። ወጥተውም በይሁዳ ምድር ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ እንግዲህ ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ያለው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር መባሉ ከዚህ የተነሣ ነው። ከዚያም ተጉዘው ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር በመሄድ ወደ ሚካ ቤት መጡ። የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፥ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፥ ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው። ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት። ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር። ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፥ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፥ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ። እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፥ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፥ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው። እነርሱም፥ “ዝም በል አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋር ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት። ይህም ካህኑን ደስ አሰኘው፤ እርሱም ኤፉዱን፥ ተራፊሙንና የተቀረጸውን ምስል ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ። እነርሱም ሕፃናታቸውን፥ የከብቶቻቸውን መንጋና ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ፊት በማስቀደም ተመልሰው ሄዱ። ከሚካ ቤት ጥቂት ራቅ እንዳሉም፥ የሚካ ጎረቤቶች ለርዳታ ተጠርተው ተሰበሰቡ፤ የዳን ሰዎችንም ተከታትለው ደረሱባቸው። ከበሰተኋላቸው ሆነው ሲጮሁባቸውም፥ የዳን ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው ሚካን፥ “ሰዎችህን ለውጊያ አሰባስበህ መምጣትህ ምን ሆነህ ነው?” አሉት። እርሱም፥ “እንዴት፥ ‘ምን ሆንክ’ ብላችሁ ትጠይቁኛላችሁ? የሠራኋቸውን አማልክቴንና ካህኔን ወስዳችሁ ሄዳችኋል፤ ምን የቀረኝ ነገር አለ?” አላቸው። የዳን ሰዎች፥ “አትሟገተን፤ ያለዚያ የተቈጡ ሰዎች ጉዳት ላይ ይጥሉሃል፤ አንተም ቤተሰብህም ሕይወታችሁን ታጣላችሁ” አሉት። የዳን ሰዎች ይህን ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም የማይችላቸው መሆኑን በማየት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚያም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወስደው ወደ ላይሽ በመሄድ፥ በሰላምና ያለ ስጋት ይኖር የነበረውን ሕዝብ በሰይፍ መቱት፤ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሏት። የሚኖሩት ከሲዶና በጣም ርቀው ስለ ነበርና ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸው የሚታደጋቸው አንድም አልነበረም፤ ከተማይቱም የምትገኘው በቤትሮዓብ አጠገብ ነበረ። የዳንም ሰዎች ከተማይቱን እንደገና ሠርተው መኖሪያቸው አደረጓት። ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሯት፤ ቀድሞ ግን ስሟ ላይሽ ይባል ነበር። እዚያም የዳን ሰዎች ለራሳቸው ጣዖታት አቆሙ፤ የሙሴ ልጅ፥ የጌርሳም ልጅ ዮናታንና የእርሱም ልጆች ምድሪቱ እስከ ተማረከችበት ጊዜ ድረስ ለዳን ነገድ ካህናት ሆኗቸው፤ ስለዚህም ሚካ የሠራቸውን ጣዖታት፥ የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ አቆሙ። በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ በዚሁ ጊዜም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር አንድ ሌዋዊ ከይሁዳ ምድር ከቤተልሔም አንዲቱን ሴት ቁባት አድርጎ ወሰዳት። ሴቲቱ ግን በታማኝነት አልጸናችም፤ ትታውም በይሁዳ ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ወደ ቤተልሔም ሄደች፤ እዚያም አራት ወር ከቈየች በኋላ፥ ባሏ ታርቆ ሊመልሳት ወደ እርሷ ሄደ፤ ሲሄድም አሽከሩንና ሁለት አህዮችን ይዞ ነበር፤ ሴቲቱም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው፤ አባቷም ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው። የልጂቱ አባትም እዚያው እንዲቈይ አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ እየበላ እየጠጣ ሦስት ቀን አብሮት ተቀመጠ። በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፤ እንግዳውም ለመሄድ ተዘጋጀ፤ የልጂቱ አባት ግን፥ “እንድትበረታ እህል ቅመስ፤ ከዚያም መሄድ ትችላለህ” አለው። ስለዚህ ሁለቱ ለመብላትና ለመጠጣት አብረው ተቀመጡ። የልጂቷም አባት፥ “እባክህ ዛሬም እዚሁ አድረህ ተደሰት” አለው። ሰውየው ለመሄድ ሲነሣም ዐማቱ እንዲያድር ለመነውና እዚያው አደረ። በአምስተኛውም ቀን ጠዋት ሌዋዊው ለመሄድ ሲነሣ፥ የልጂቱ አባት “ሰውነትህን አበርታ፤ ጥላው እስኪበርድም ድረስ በዚሁ ቈይ” አለው፤ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ። ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ፥ የልጅቱ አባት ዐማቱ “እነሆ ጊዜው እየመሸ ነው፤ እዚሁ እደሩ፤ ቀኑ እየተገባደደ ነው፤ እዚሁ አድራችሁ ተደሰቱ፤ ነገ ጠዋት ማልዳችሁ በመነሣት መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለው። ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ የቡስ ሄደ። ወደ የቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፥ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ የቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው። ጌታውም፥ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው። ቀጥሎም፥ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው። ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደ ሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች። ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማይቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር። በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ። ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማይቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፥ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ ጌታ ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም። ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፥ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።” ሽማግሌውም፥ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በዐደ ባባይ ግን አትደሩ” አለው። ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም። በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፥ ጥቂት የከተማይቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፥ “ዝሙት እንድንፈጽም በት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት። የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ። እነሆ ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቊባት አሉ፤ እነርሱን አሁኑኑ ላውጣላችሁና አስነውሯቸው፤ ያሻችሁንም አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙበት።” ሆኖም ሰዎቹ ሊሰሙት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ሌዋዊው ቁባቱን ወደ ውጭ አወጣላቸው፤ ሰዎቹም አመነዘሩባት፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲፈራረቁባት አድረው ጐሕ ሲቀድ ለቀቋት። በነጋም ጊዜ ሴቲቱ ጌታዋ ወዳለበት ቤት ተመልሳ ሄደች። ደጃፉ ላይ ወድቃ ፀሓይ እስክትወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች። ጌታዋ በጠዋት ተነሥቶ በሩን በመክፈት መንገዱን ለመቀጠል ሲወጣ፥ ቁባተ እጅዋን ከደጃፉ መድረክ ላይ እንደ ዘረጋች ከቤቱ በራፍ ላይ ተዘርራ ወድቃ አገኛት። ሌዋዊውም፥ “በይ ተነሺና እንሂድ” አላት፤ ነገር ግን መልስ አልነበረም። ከዚያም በአህያው ላይ ከጫናት በኋላ ወደ ቤቱ ጉዞውን ቀጠለ። ቤቱ እንደደረሰም ቢላዋ አንሥቶ ቁባቱን ዐሥራ ሁለት ቦታ በመቈራረጥ ወደ እስራኤል ምድር ሁሉ ሰደደ። ያየም ሁሉ፥ “እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልታየም፤ አልተደረገም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም በነገሩ አስቡበት፤ ተመካከሩ በት” ተባባሉ። ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም በጌታ ፊት ተሰበሰቡ። የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ሁሉ ቁጥራቸው አራት መቶ ሺህ በሚሆን፥ ሰይፍ በሚመዙ እግረኞች ወታደሮች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ መካከል ተገኙ። በዚህ ጊዜ ብንያማውያን፥ እስራኤላውያን ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ፤ ከዚያም እስራኤላውያን፥ “ይህ ክፉ ድርጊት እንዴት እንደ ተፈጸመ እስቲ ንገሩን” ተባባሉ። ስለዚህ የተገደለችው ሴት ባል ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና አባቴ በዚያ ለማደር በብንያም ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ መጣን። የጊብዓም ሰዎች በሌሊት ሊገድሉኝ ያደርኩበትን ቤት ከበቡት፤ ከዚያም በቁባቴ ላይ ስለ አመነዘሩባት ሞተች። የቁባቴንም ሬሳ ከቈራረጥሁ በኋላ እያንዳንዱን ቁራጭ፥ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ወዳለበት አገር ሰደድሁ፤ ይህን ያደረግሁትም ሰዎቹ በእስራኤል ዘንድ አሠቃቂና አስነዋሪ ድርጊት ስለፈጸሙ ነው። አሁንም እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት፤ ፍርዳችሁንም ስጡ።” ከዚያም ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመነሣት እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፤ ማንኛችንም ወደ ቤታችን አንመለስም። ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን። ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሠራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፥ ከመቶው ዐሥር፥ ከሺው አንድ መቶ፥ ከዐሥር ሺው ደግሞ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሠራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጊብዓ በሚደርስበት ጊዜ፥ ነዋሪዎችዋ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።” ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማይቱ ላይ ዘመቱባት። የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፥ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድነው? አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፥ እነዚያን የጊብዓን ነውረኞች አሳልፋችሁ ስጡን።” ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤ ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ። ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፥ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺህ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ። በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጉር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ። እስራኤላውያን፥ ብንያማውያንን ሳይጨምር፥ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺህ ተዋጊዎች አሰባሰቡ። እስራኤላውያን ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። ጌታም፥ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ። በማግሥቱ ጧት እስራኤላዋያን ነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤ የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ። እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በጌታ ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንውጣን?” ብለው ጌታን ጠየቁ። ጌታም፥ “አዎን፤ ውጡና ውጉቸው” ብሎ መለሰላቸው። በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ። በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፥ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ። የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በጌታ ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ። እስራኤላውያንም የጌታን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤ የአሮን ልጅ፤ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፥ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ። ጌታም፥ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ። በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ብንያማውያንም ሊገጥሟቸው ወጡ፤ ከከተማይቱም ርቀው እንዲሄዱ ተደረጉ፤ እንደ በፊቱም እስራኤላውያንን ይገድሉ ጀመር። ከዚህ የተነሣም በሜዳው እንዲሁም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስደው መንገዶች ላይ ሠላሳ ያህል ሰዎች ወድቀው ነበር። ብንያማውያኑ፥ “እንደ በፊቱ ይሄው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፥ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፥ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማይቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር። የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ። ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፥ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር። ጌታም ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ። ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ። ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላይቱን ከተማ በሰይፍ መቱ። የእስራኤል ሰዎች የሸመቀው ጦር በከተማይቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳዩ ተስማሙ፤ እስራኤላውያንም ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ነበር። ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፥ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፥ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ። ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማይቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፥ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላይቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ። ከዚያም እስራኤላውያን ዞረው አጠቋቸው፤ በዚህ ጊዜ ብንያማውያን ጥፋት እንደ ደረሰባቸው ስላወቁ እጅግ ደነገጡ። ስለዚህም ጀርባቸውን አዙረው ከእስራኤላውያን ፊት ወደ ምድረ በዳው ሸሹ፤ ሆኖም ከጦርነት ማምለጥ አልቻሉም፤ ከየከተሞቹ የወጡ እስራኤላውያንም በዚያው ገደሏቸው። ብንያማውያንንም ከበቧቸው፤ አሳደዷቸው፤ ከጊብዓ በስተ ምሥራቅ ትይዩ ባለውም ስፍራ አሳደው አሸነፏቸው፤ በጦርነቱም ላይ ዐሥራ ስምንት ሺህ ብንያማውያን ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። ብንያማውያን ወደ ሁላ ዙረው በምድረ በዳው በኩል ወደ ሬሞን ዐለት በሚሸሹበት ጊዜ፥ እስራኤላውያን በመንገድ ላይ አምስት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ እስከ ጊድኦምም ድረስ ተከታትለው ሁለት ሺህ ሰዎች በተጨማሪ ገደሉ። በዚያች ዕለት ሰይፍ የታጠቊ ሃያ አምስት ሺህ ብንያማውያን በጦር ሜዳ ወደቊ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። ነገር ግን ስድስት መቶ ሰዎች ወደ ሁላ ዙረው በምድረ በዳው ውስጥ ወዳለው ወደ ሬሞን ዐለት ሸሹ፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጡ። ከዚያም እስራኤላውያን ወደ ብንያም ምድር ተመልሰው ከተሞቻቸውን በሙሉ እንዲሁም እንስሳቱንና በዚያ ያገኙትን ሁሉ በሰይፍ መቱ፤ በመንገዳቸው ያገኙትን ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። እስራኤላውያን በምጽጳ፥ “ከእኛ አንድም ሰው ሴት ልጁን በጋብቻ ለብንያማውያን መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር። ሕዝቡ ወደ ቤቴል ሄደው በዚያም እስከ ማታ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ አምርረው አለቀሱ፤ እንዲህም አሉ፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፤ ይህ ለምን በእስራኤል ላይ ሆነ? ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዴት ይታጣ?” በማግሥቱ ጠዋት ሕዝቡ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ። በምጽጳ፥ በጌታ ጉባኤ ፊት ያልተገኘ ማንኛውም ሰው መገደል አለበት ብለው እስራኤላውያን ተማምለው ስለ ነበር፥ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በጌታ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን አለ?” ሲሉ ጠየቁ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤ ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በጌታ ስለማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?” ከዚያም፥ “ከእስራኤል ነገዶች ምጽጳ ላይ በጌታ ጉባኤ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን ነው” ሲሉ ጠየቁ፤ ታዲያ ከያቤሽ ገለዓድ አንድም ሰው ለጉባኤው ወደ ሰፈሩ አለመምጣቱን ተረዱ፤ ሕዝቡን ሲቈጥሩም ከያቤሽ ገለዓድ ሰዎች አንድም ሰው አልነበረምና። ስለዚህ ዐሥራ ሁለት ሺህ ተዋጊዎች ወደ ያቤሽ ገለዓድ ሄደው በእዚያ የሚኖሩትን በሙሉ ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጭምር በሰይፍ እንዲፈጇቸው ጉባኤው መመሪያ ሰጥቶ ላካቸው። እነርሱም፥ “እንግዲህ የምታደርጉት ይህ ነው፤ ወንዱን በሙሉ እንዲሁም ድንግል ያልሆኑትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ” አሏቸው። በያቤሽ ገለዓድ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ወንድ ያልደረሰባቸው አራት መቶ ደናግል አገኙ፤ በከነዓን ምድር በሴሎ ወደሚገኘውም ሰፈር አመጧቸው። ከዚያም ጉባኤው በሙሉ በሬሞን ዐለት ወዳሉት ብንያማውያን የሰላም ጥሪ አስተላለፈ። ስለዚህ በዚህን ጊዜ ብንያማውያን ተመለሱ፤ ከመገደል የተረፉትንም የኢያቢስ ገለዓድ ሴቶች ሰጧቸው፤ ይሁን እንጂ የሴቶቹ ቊጥር ለሁሉም የሚበቃ አልነበረም። ጌታ በእስራኤል ነገዶች መካከል አስደንጋጭ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ለብንያማውያን አዘነ። የጉባኤውም መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ የብንያም ሴቶች አልቀዋል፤ ታዲያ ለቀሩት ወንዶች ሚስት የምናገኝላቸው እንዴት ነው? ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው እንዳይጠፋ አሁን በሕይወት ያሉት ብንያማውያን ወራሽ የሚሆን ዘር ሊኖራቸው ይገባል። ‘ልጁን ለብንያማዊ የሚድር ርጉም ይሁን’ ብለን እኛ እስራኤላውያን ስለ ተማማልን እንግዲህ ልጆቻችንን ልንድርላቸው አንችልም፤ ይሁን እንጂ ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ ባለችው በሴሎ የጌታ በዓል በየዓመቱ ይከበራል።” ስለዚህም ለብንያማውያን እንዲህ ሲሉ መመሪያ ሰጧቸው፤ “ሄዳችሁ በወይኑ የአትክልት ስፍራ ተደበቁ፤ አድፍጣችሁ ተጠባበቁ። የሴሎ ልጃገረዶች ለጭፈራ ወደዚያ በሚወጡበት ጊዜ፥ ከወይኑ አትክልት ቦታ ወጥታችሁ ከልጃገረዶቹ ለየራሳችሁ ሚስት ጥለፉ፤ ወደ ብንያምም ምድር ሂዱ። አባቶቻቸውም ሆኑ ወንድሞቻቸው ቢቃወሙ፥ ‘በጦርነት ጊዜ ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶች ስላላገኘን ነውና እነርሱን በመርዳት ምሕረት አድርጉልን፤ እናንተም ደግሞ ልጆቻችሁን ፈቅዳችሁ ያልዳራችሁ በመሆናችሁ በደለኞች አትሆኑም’ እንላቸዋለን።” ብንያማውያን እንደ ተባሉት አደረጉ፤ ልጃገረዶቹ በሚጨፍሩበትም ጊዜ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እየጠለፈ ሚስት እንድትሆነው ይዞ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ርስታቸው ተመለሱ፤ ከተሞቻቸውንም አድሰው በዚያ ኖሩ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ያን ቦታ ትተው ወደየቤታቸው፥ ወደየርስታቸው፥ ወደየጐሣቸውና ወደየነገዳቸው ሄዱ። በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። መሳፍንት ይፈርዱ በነበረበት ዘመን በአገሩ ላይ ረሀብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ለመቀመጥ ከቤተልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ። የሰውዬው ስም ኤሊሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ናዖሚ፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፥ እነርሱም የቤተልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ፥ በዚያም ተቀመጡ። የናዖሚም ባል ኤሊሜሌክ ሞተ፥ እርሷም ከሁለቱ ልጆችዋ ጋር ቀረች። እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፥ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ። መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፥ ሴቲቱም ሁለቱን ልጆችዋንና ባልዋን አጥታ ብቻዋን ቀረች። እርሷም በሞዓብ ምድር ሳለች ጌታም ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እህልም እንደሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች። እርሷም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፥ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ መንገድ ጀመሩ። ናዖሚም ምራቶችዋን፦ “ሂዱ፥ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፥ ለእኔና ለሞቱት እንዳደረጋችሁት፥ ጌታም ቸርነት ያድርግላችሁ። ጌታም በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” አለቻቸው። ሳመቻቸውም፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ። እነርሱም፦ “ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን” አሉአት። ናዖሚም አለች፦ “ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች በማህፀኔ ይዣለሁን? ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፥ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በእነርሱስ ምክንያት ባል ሳታገቡ ትቆያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሆንም፥ እኔን ጌታ ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ።” ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደገና አለቀሱ፥ ዖርፋም አማቷን ሳመች፥ ሩት ግን አማቷ ጋር ተጣበቀች። እሷም፦ “እነሆ ዋርሳሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፥ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለች፦ “እንድተውሽ ተለይቼሽም እንድመለስ አታስገድጅኝ፤ በምትሄጅበት እሄዳለሁ፥ በምታድሪበትም አድራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር ጌታ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ከእርሷ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ ናዖሚ ከመናገር ዝም አለች። ስለዚህ ሁለቱም እስከ ቤተልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተልሔምም በደረሱ ጊዜ፥ ያገሩ ሰዎች ሁሉ ታወኩ ስለ እነርሱ፥ ሴቶቹም፦ “ይህች ናዖሚን ናትን?” አሉ። እሷም፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ‘ማራ’ በሉኝ እንጂ ‘ናዖሚ’ አትበሉኝ። በሙላት ወጣሁ፥ ጌታም ባዶዬን መለሰኝ፤ ጌታ በእኔ ላይ ሰቆቃን ሲያደርስ፥ ሁሉን የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና፥ ናዖሚ ብላችሁ ለምን ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው። ስለዚህ ናዖሚ፥ ከሞአባዊት ምራትዋ ከሩት ጋር፥ ከሞዓብ አገር ተመለሰች። የገብስም መከር መሰብሰቢያ ጅማሬ ላይ ቤተልሔም መጡ። ለናዖሚም በባልዋ የሚዛመዳት ሰው ከኤሊሜሌክ ወገን የሆነ ስሙ ቦዔዝ የተባለ ኃያል ሰው ነበረ። ሞአባዊቱም ሩት ናዖሚንን፦ “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው ተከትዬ እህል ለመቃረም ወደ እርሻ ልሂድ” አለቻት። እርሷም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሂጂ” አለቻት። ስለዚህም ሄደች፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፥ እንደ አጋጣሚም የኤሊሜሌክ ወገን ወደነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። ከጥቂት ጊዜ በኋላም፥ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ ይባርክህ” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን አገልጋዩን፦ “ይህች ብላቴና የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ፦ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከናዖሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ብላቴና ናት፥” ብሎ መለሰ። “እርሷም፦ ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ’ ብላ፥ መጣች፤ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም” አለው። ቦዔዝም ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን አገልጋዮቼን ተከትለሽ ቃርሚ። ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፥ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፥ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ” አላት። በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት፦ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለሁ፥ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ፥ እንዴት በፊትህ ሞገስ አገኘሁ?” አለችው። ቦዔዝም፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። ለሠራሽው ሥራ ጌታ ይክፈልሽ፥ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በጌታ ዘንድ ዋጋሽ ፍጹም ይሁን” አላት። እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባርያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ” አለችው። በምሳ ሰዓትም ቦዔዝ፦ “ወደዚህ ቅረቢ፥ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሺ አላት። ” በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ ተረፋትም። ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ብላቴኖቹን፦ “በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አትከልክሏት፥ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፥ እርሷም ትቃርም፤ አትከልክሉአትም” ብሎ አዘዛቸው። በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፥ የቃረመችውንም ወቃችው፥ ዐሥር ኪሎ ያህልም ገብስ ሆነ። ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፥ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። አማትዋም፦ “ዛሬ ከየት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን” አለቻት። እርሷም፦ “ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል” ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማቷ ነገረቻት። ናዖሚም ምራትዋን፦ “በሕያዋን እና በሙታን ላይ ቸርነቱ የማያልቅበት ጌታ የተባረከ ይሁን” አለቻት። ናዖሚም ደግሞ፦ “ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው” አለቻት። ሞዓባዊቱ ሩትም፦ “ደግሞ፥ መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ፥ አለኝ” አለቻት። ናዖሚም ምራትዋን ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ከሴት አገልጋዮቹ ጋር ብትወጪ ይሻላል፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው” አለቻት። ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝ ሠራተኞች አጠገብ እየቃረመች ቈየች፥ ከአማቷም ሳትለይ አብራ ተቀመጠች። አማቷም ናዖሚ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። አሁንም ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። እንግዲህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፥ የክት ልብስሽንም ልበሺ፥ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። በሚተኛም ጊዜ፥ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም፦ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ወደ አውድማው ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፥ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፥ እነሆም፥ አንዲት ሴት በግርጌው ተኝታ ነበር። እርሱም፦ “ማን ነሽ?” አለ። እርሷም፦ “እኔ ባርያህ ሩት ነኝ፥ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባርያህ ላይ ጣል አለችው። ” ቦዔዝም አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በጌታ የተባረክሽ ሁኚ፥ ባለ ጠጋ ይሁን ወይም ድሀ፥ ወጣቶችን መርጠሽ መሄድ አልፈለግሽምና ከፊተኛው ይልቅ አሁን ባደረግሽው ታማኝነትን አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ። የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፥ ነገር ግን ከእኔ ይልቅ ቅርብ የሆነ ሌላ ዘመድ አለ፤ ዛሬ ሌሊት እደሪ፥ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፥ ዋርሳ ሊሆን ባይወድ ግን፥ ሕያው ጌታን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፥ እስኪ ነጋ ድረስ ተኚ።” እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፥ ቦዔዝም፦ “ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ” ብሎ ነበርና ማንም ሊያያት በማይችልበት ሰዓት በማለዳ ከመኝታዋ ተነሣች። እርሱም፦ “የለበስሽውን ልብስ አምጥተሽ ያዥው” አላት፤ በያዘችም ጊዜ ወደ ኻያ ኪሎ የሚጠጋ ገብስ ሰፍሮላት አሸከማት። እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም በመጣች ጊዜ አማቷ፦ “ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ?” አለቻት፥ እርሷም ሰውየው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት። “ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ፥ ብሎ ይህን ኻያ ኪሎ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት። እርሷም፦ “ልጄ ሆይ! ሰውዬው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና፥ ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ጠብቂ” አለቻት። ቦዔዝም ወደ ከተማይቱ በር አደባባይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። እነሆም፥ ከዚህ በፊት ቦዔዝ ስለ እርሱ የተናገረው የእርሱ የቅርብ ዘመድ ወደዚያው ቦታ መጣ፤ ቦዔዝም ጠርቶ፦ “ወዳጄ ሆይ! ቀረብ በልና አጠገቤ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ቀረብ ብሎ ተቀመጠ። ቦዔዝም ከከተማይቱ ሽማግሌዎች ዐሥር ሰዎች ጠርቶ፦ “በዚህ ተቀመጡ” አላቸው። እነርሱም ተቀመጡ። ቦዔዝም የቅርብ ዘመዱን፦ “ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ናዖሚ የወንድማችንን ኤሊሜሌክን መሬት መሸጥ ትፈልጋልች። አንተም ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የሚገባህ ይመስለኛል፤ እንግዲህ መሬቱን ከፈለግኸው እዚህ በተቀመጡትና በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት ለራስህ ልታስቀረው ትችላለህ፤ የማትፈልገው ከሆነ ግን ቁርጡን ንገረኝ፤ መሬቱን የማስቀረት ቅድሚያ ያለህ አንተ ነህ፤ ከአንተም ቀጥሎ እኔ ነኝ።” ሰውየውም “እኔም እቤዥዋለሁ” አለ። ቦዔዝም “መሬቱን ከናዖሚ የምትገዛ ከሆነ በውርሱ የሟቹን ስም ታስጠራ ዘንድ ባልዋ የሞተባትን ሞአባዊትዋን ሩትንም አብረህ ትወስዳለህ” አለው። የቅርብ ዘመዱም፦ “የራሴን ርስት እንዳላበላሽ መውሰድ አልችልም፥ እኔ የራሴ ላደርገው አልችልምና አንተ እንድትወስደው ፈቅጄልሃለሁ” አለው። በጥንት ጊዜም፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ። ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ውል ለመፈጸሙ ማረጋገጫ ነበር። የቅርብ ዘመዱም ቦዔዝን፦ “አንተ ግዛው” አለው፤ ጫማውንም አወለቀ። ቦዔዝም ሽማግሌዎችንና ሕዝቡን ሁሉ፦ “ለኤሊሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከናዖሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ። ደግሞም የምዋቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል ከአገሩም ደጅ እንዳይጠፋ፥ የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፥ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው። በከተማይቱ በር አደባባይም የነበሩ ሽማግሌዎችና ሌሎችም ሰዎች ሁሉ፦ “እኛ ምስክሮች ነን፥ ጌታ ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ፥ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፥ አንተም በኤፍራታ ባለ ጠጋ ሁን፥ ስምህም በቤተልሔም ይጠራ። ቤትህም ጌታ ከዚህች ቈንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደች እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን” አሉት። ቦዔዝም ሩትን ወሰደ፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደ እርሷም ገባ፤ እግዚአብሔርም ፅንስ ሰጣት፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ሴቶችም ናዖሚንን፦ “ዛሬ ዋርሳ ያላሳጣሽ ጌታ ይባረክ፥ ስሙም በእስራኤል ይጠራ። ምራትሽ በጣም ትወድሻለች፤ ሰባት ልጆች ከሚያደርጉልሽ የበለጠ አድርጋልሻለች፤ አሁን ደግሞ ሕይወትሽን የሚያድስልሽና በእርጅናሽ ወራት የሚጦርሽን ወንድ ልጅ ወልዳልሻለች።” ናዖሚም ሕፃኑን ወሰደች አቀፈችውም፥ ሞግዚትም ሆነችው። የጐረቤት ሴቶች ልጁን “ኢዮቤድ” ብለው ስም አወጡለት፤ “ለናዖሚ ወንድ ልጅ ተወለደላት!” እያሉም ለሰው ሁሉ አወሩ። የንጉሥ ዳዊት አባት የሆነውን እሴይን የወለደ ይኸው ኢዮቤድ ነው። የዳዊት የዘር ሐረግ የፋሬስም ትውልድ ይህ ነው፥ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፥ ኤስሮምም አራምን ወለደ፥ አራምም አሚናዳብን ወለደ፥ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፥ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፥ ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፥ ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፥ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የይሮሐም ልጅ፥ የኤሊዩ ልጅ፥ የቶሑ ልጅ፥ የናሲብ ልጅ ሲሆን ከኤፍሬም ነገድ ነበረ። እርሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ስማቸውም አንዲቱ ሐና፥ ሁለተኛዪቱም ጵኒና ነበር። ጵኒና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም። ያም ሰው በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ የጌታ ካህናት ነበሩ። ሕልቃና መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፥ ለሚስቱ ለጵኒና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። ሐናንም ይወዳት ስለ ነበር ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ ጌታ ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። ጌታ ማሕፀኗን ስለዘጋም ጣውንቷ ሆን ብላ ታስቆጣት፥ ታበሳጫትም ነበር። ወደ ጌታ ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ ይህ በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ታበሳጫት ነበር። ባሏ ሕልቃናም እርሷን፥ “ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በጌታ ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሷም ከልቧ ኀዘን የተነሣ ምርር ብላ እያለቀሰች ወደ ጌታ ጸለየች። እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሠራዊት ጌታ ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ ለአገልጋይህም ወንድ ልጅ ብትሰጣት፥ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለጌታ እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አያርፍም።” ጸሎትዋንም ባለማቋረጥ ወደ ጌታ ባቀረበች ጊዜ፥ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። ሐናም በልቧ ትጸልይ የነበረ በመሆኑ፥ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምጿ አይሰማም ነበር፤ ስለዚህ ዔሊ እንደ ሰከረች አድርጎ ቆጠራት “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” ሲልም ዔሊ ተናገራት። ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፥ “ጌታዬ ሆይ፤ አይደለም፤ እኔስ ልቧ ክፉኛ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ የልቤን ኀዘን በጌታ ፊት አፈሰስሁ እንጂ፥ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም። ይህን ያህል ጊዜ የጸለይኩት ከባድ ከሆነው ጭንቀቴና መከራዬ የተነሣ ስለሆነ፥ አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አትቁጠረኝ።” ከዚያም ዔሊ፥ “በሰላም ሂጂ! የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ይስጥሽ!” አላት። እርሷም፥ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም ተነሥታ መንገዷን ቀጠለች፤ ምግብም በላች፤ በፊቷም ገጽ ኀዘን መታየቱ ቆመ። በማግስቱ ጠዋት ተነሥተው በጌታ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ ጌታም አሰባት፤ ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ “ከጌታ ለምኜዋለሁ” ስትል ስሙን “ሳሙኤል” ብላ ጠራችው። ሰውዬውም ሕልቃና ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ለጌታ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት፥ ስእለቱንም ለማድረስ ወደ ሴሎ ወጣ። ሐና ግን አልሄደችም፤ ምክንያቱም ለባሏ፥ “ሕፃኑ ጡት እንደተወ፥ በጌታ ፊት ቀርቦ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ እንዲኖር፥ አመጣዋለሁ” ብላው ነበርና ነው። ባሏ ሕልቃናም፥ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥይው ድረስ እዚሁ ቆይ፤ ብቻ ጌታ ቃሉን ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሴቲቱ ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች። ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፥ በሴሎ ወዳለው ወደ ጌታ ቤት አመጣችው፤ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ። ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት። እርሷም እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! እዚህ ቦታ ላይ በፊትህ ቆማ ወደ ጌታ ስትጸልይ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። ስለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ ጌታም የለመንሁትን ሰጠኝ። ስለዚህ እኔም ለጌታ እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለጌታ የተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያ ለጌታ ሰገደ። ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፦ “ልቤ በጌታ ደስ ይለዋል፥ ቀንዴም በጌታ ከፍ ከፍ ብሏል፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛልና፥ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ። እንደ ጌታ ያለ ቅዱስ የለም፥ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችንን የሚመስልም ዓለት የለም። እጅግ በመኩራራት አትናገሩ፥ የእብሪትም ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፥ ጌታ አምላክ አዋቂ ነውና፥ በእርሱም ሥራዎች ይመዘናሉ። የኀያላን ቀስቶች ተሰበሩ፤ ደካሞች ግን በብርታት ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ አጥተው ለእንጀራ ተገዙ፤ ተርበው የነበሩ ግን ከራብ ዐርፈዋል። መካኒቱ ሰባት ወለደች፥ ብዙ የወለደችው ግን ብቻዋን ቀረች። ጌታ ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ከሲኦልም ያወጣል። ጌታ ድሀ ያደርጋል፤ ሀብታምም ያደርጋል፤ ያዋርዳል ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። ወደ ልዑላንም ደረጃ ከፍ ሊያደርጋቸው፥ የክብርንም ዙፋን ሊያወርሳቸው፥ እርሱ ድኾችን ከትቢያ፥ ምስኪኖችንም ከዐመድ ላይ ያነሣል፤ የምድር መሠረቶች የጌታ ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አኖረ። እርሱ የታማኞቹን እግር ይጠብቃል ሰው በኃይሉ አይበረታምና፥ ኃጥአን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይጣላሉ። ጌታ! እርሱን የሚቃወሙ ይደቅቃሉ፥ ከሰማይም ያንጐደጉድባቸዋል፥ ጌታ እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፥ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፥ የመሢሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።” ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ ራማ ሄደ፤ ብላቴናውም በካህኑ በዔሊ ፊት ጌታን ያገለግል ነበር። የዔሊም ልጆች ለጌታ ክብር የማይሰጡ ስድ አደጎች ነበሩ። የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ አገልጋይ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ይህንንም ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ ያደርጉ ነበር። ከዚህም ሌላ፥ ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ አገልጋይ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ “ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም፦ “አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት፥ ከዚያም በኋላ ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ያህል ትወስዳለህ” ቢለው፥ እርሱ፦ “አይሆንም፥ አሁን ልትሰጠኝ ይገባል፤ ካልሆነ ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዓይነት የጌታን መሥዋዕት ስላቃለሉ፥ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በጌታ ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በጌታ ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም በየዓመቱ ከባሏ ጋር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ “ለጌታ ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት ጌታ ዘር ይስጥህ” ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። ጌታም ሐናን አሰበ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በጌታ ፊት አደገ። ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና፥ ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ፥ የጌታን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም። ሰውስ በሰው ቢበድል እግዚአብሔር ይታደገዋል፤ ሰው ግን ጌታን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው?” እነርሱ ግን ጌታ ሊገድላቸው ወድዷልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። ብላቴናው ሳሙኤልም እያደገና፥ በጌታም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ። አንድ እግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘በግብጽ በፈርዖን ቤት ባርያ ሳሉ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤ ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፋድንም በፊቴ እንዲለብስ ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የሚያቀርቡትን የሚቃጠል መሥዋዕት ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። በማደሪያዬ እንዲያቀርቡት ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቁርባኔን ስለምን ረገጣችሁ? ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቁርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር፥ ከእኔ ይልቅ ለልጆችህ ስለምን ክብር ሰጠህ?’ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነት ቤትህ፥ የአባትህም ቤት ለዘለዓለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤’ አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ ከእኔ ይራቅ። እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ የአንተንም ክንድ፥ የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል። እነሆ በእስራኤል በረከት ሁሉ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ፤ በቤትህም ለዘለዓለም ሽማግሌ አይገኝም። በመሠዊያዬ ከምታገለግሉት ከእናንተ መካከል ሳላጠፋ የማስቀረው አንድ ሰው ዐይንህን በእንባ የሚያጠፋና ልብህን የሚያሳዝን ይሆናል፤ የቤተሰብህ አባሎች ሁሉ ግን በሰዎች ሰይፍ ያልቃሉ። ይህ በሁለቱ ልጆችህ በሖፍኒና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ። የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፤ እንደ ልቤና እንደ ሐሳቤም የሚያደርግ ይሆናል፤ እኔም የጸና ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑንም ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፤ በፊቱም ሰግዶ፦ ቁራሽ እንጀራ እንድበላ ከካህናት ስፍራ ወደ አንዲቱ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ የዕለት ምግብ ብቻ ለማግኘት ይለምናል።’” ብላቴናው ሳሙኤል ከዔሊ በታች ሆኖ ጌታን ያገለግል ነበር። በዚያም ዘመን የጌታ ቃል ዘወትር የሚሰማ አልነበረም፤ ራእይም አይታይም ነበር። በዚያን ጊዜ ዐይኖቹ ከመድከማቸው የተነሣ ማየት የተሳነው ዔሊ አንድ ሌሊት በስፍራው ተኝቶ ነበር። የእግዚአብሔር መብራትም ገና አልጠፋም ነበር፤ ሳሙኤል ደግሞ የጌታ ታቦት ባለበት፥ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ተኝቶ ነበር። ጌታም ሳሙኤልን ጠራው፤ ሳሙኤልም፥ “እነሆኝ” አለ፤ ወደ ዔሊም ሮጦ በመሄድ፥ “ስለ ጠራኸኝ እነሆ! መጥቻለሁ” አለው። ዔሊ ግን፥ “እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው፤ እርሱም ሄዶ ተኛ። ደግሞም እግዚአብሔር፥ “ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሣና ወደ ዔሊ ሄዶ፥ “ስለ ጠራኸኝ እነሆ! መጥቻለሁ” አለው። ዔሊም ግን፥ “ልጄ ሆይ፤ እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው። በዚያም ጊዜ ሳሙኤል ጌታን ገና አላወቀም ነበር፤ የጌታም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር። ጌታም ሳሙኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው፤ አሁንም ሳሙኤል ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ፥ “ስለ ጠራኸኝ እነሆ! መጥቻለሁ” አለው። ዔሊም በዚህ ጊዜ ሳሙኤልን ይጠራ የነበረው ጌታ መሆኑን ተረዳ። ስለዚህም ዔሊ ሳሙኤልን፥ “ሂድና ተኛ፤ ከእንግዲህ ቢጠራህ ግን፥ ‘ጌታ ሆይ፤ አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር’ በል” አለው። ሳሙኤልም ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ። ጌታም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፥ “አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” አለ። ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ጆሮ ሁሉ ዝግንን የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ። በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ። ልጆቹ አስጸያፊ ነገር ሲያደርጉ እርሱ ባለመከልከሉ፥ ዔሊ በሚያውቀው ኃጢአት ምክንያት በቤተሰቡ ላይ ለዘለዓለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር። ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቁርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።” ሳሙኤል እስኪ ነጋ ድረስ ተኛ፤ ከዚያም ተነሥቶ የጌታን ቤት በሮች ከፈተ፤ ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ፤ ዔሊ ግን ሳሙኤልን፥ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም፥ “እነሆኝ” ሲል መለሰ። ዔሊም፥ “እርሱ የነገረህ ነገር ምንድነው? አትደብቀኝ፤ ከነገረህ ውስጥ አንዲቱን እንኳ ብትደብቀኝ እግዚአብሔር እንደዚያው ያድርግብህ፤ ከዚያ የከፋም ያምጣብህ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ምንም ነገር ሳይደብቅ ሁሉንም ነገረው። ዔሊም፥ “እርሱ ጌታ ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ። ሳሙኤል አደገ፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነበረና፥ ከሚናገረው ቃል አንዳች በምድር አይወድቅም ነበር። ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል የታመነ የጌታ ነቢይ መሆኑን ዐወቁ። ጌታም በሴሎ ይገለጥ ነበር፤ በዚያም ጌታ በቃሉ አማካይነት ራሱን ለሳሙኤል ገለጠ። የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እነርሱ በአቤንኤዘር ሲሰፍሩ፥ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሠራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፥ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ። ሠራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፥ “ዛሬ ጌታ በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የጌታን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፥ በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሠራዊት ጌታን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የጌታ የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፥ ምድር እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የሆታ ድምፅ አሰሙ። ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ የሆታ ድምፅ ሲሰሙ፥ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ የሆታ ድምፅ ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ። የጌታም ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቷል፤ ወዮልን! ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞን አያውቅም። ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ! ወንድነታችሁም ይታይ፤ ያለዚያ ባርያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፥ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባርያ ያደርጓችኋል። ስለዚህ በወንድነት ጠንክራችሁ ተዋጉ!” ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ እልቂትም ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኛ ወታድሮች ወደቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ ተገደሉ። አንድ የብንያም ወገን የሆነ ሰው ልብሱን ቀዶ፥ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ፥ ከጦሩ ሜዳ እየበረረ ወደ ሴሎ መጣ። እዚያ እንደደረሰም፥ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ስለ ተጨነቀ፥ በመንገድ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወደ ከተማው ገብቶ የሆነውን ሁሉ ባወራ ጊዜ፥ ከተማው ሁሉ በጩኸት ተናወጠ። ዔሊም ጩኸቱን በሰማ ጊዜ፥ “የምን ጩኸት ነው?” ሲል ጠየቀ። ሰውየውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው፤ ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ስለ ነበር ዐይኖቹ ደክመው ማየት ተስኗቸው ነበር። ሰውየውም ዔሊን፥ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው። ዔሊም፥ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ። ወሬውን ያመጣውም ሰው፥ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሠራዊቱም ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ ሖፍኒና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኳል” ብሎ መለሰለት። ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፥ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፥ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱ ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበር። በዚያን ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት፥ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፥ የእግዚአብሔርን ታቦት መማረክ፥ የዐማቷንና የባሏንም መሞት በሰማች ጊዜ ምጡ ስለ ጠናባት ተንበርክካ ወለደች። ለመሞትም በምታጣጥርበት ጊዜ፥ በአጠገቧ የነበሩት ሴቶች፥ “አይዞሽ፤ ወንድ ልጅ ወልደሻልና በርቺ” አሏት። እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላዳመጠችም። የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከ፥ ዐማቷና ባሏም ስለ ሞቱ፥ “ክብር ከእስራኤል ተለይቷአል” ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ አለችው። ከዚያም፥ “የእግዚአብሔር ታቦት ተማርኳልና ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” አለች። ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ፥ ከአቤንኤዘር ወደ አሽዶድ ወሰዱት። ከዚያም ወደ ዳጎን ቤተ ጣዖት አግብተው፥ በዳጎን አጠገብ አኖሩት። የአሽዶድም ሰዎች በማግስቱ ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ እነሆ፥ ዳጎን በጌታ ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። ከዚያም አንሥተው ዳጎንን ወደ ቦታው መለሱት። ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነሥተው ሲመለከቱ፥ ዳጎን በጌታ ታቦት ፊት፥ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ነበር፤ ራሱና እጆቹ ተሰባብረው በደጃፉ ላይ የወደቁ ሲሆኑ፥ የቀረው ሌላው አካሉ ብቻ ነበር። የዳጎን ካህናትም ሆኑ ሌሎች በአሽዶድ ወዳለው የዳጎን ቤት የሚገቡ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸው ደጃፉን እንዳይረግጥ ተራምደው የሚያልፉት በዚሁ ምክንያት ነው። የጌታ እጅ በአሸዶድ ሕዝብና በአካባቢዋ ላይ ጠነከረ፤ እርሱም ጥፋት አመጣባቸው፤ በዕባጭም መቅሠፍት መታቸው። የአሽዶድ ሰዎች ይህን ባዩ ጊዜ፥ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክሯልና የእስራኤል አምላክ ታቦት በእኛ ዘንድ መቆየት የለበትም” አሉ። ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያንን ገዢዎች በሙሉ ጠርተው፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን እናድርገው?” ሲሉ ጠየቁ። እነርሱም፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደ ጋት ውሰዱት” አሏቸው። ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወሰዱት። ነገር ግን ታቦቱን ወደዚያ ከወሰዱትም በኋላ የጌታ እጅ በከተማዪቱ ላይ ሆነ፤ ታላቅ መሸበርም አመጣባቸው፤ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል ሕዝቡን በእባጭ መቅሠፍት መታ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ዔቅሮን ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ዔቅሮን በገባ ጊዜም፥ የዔቅሮን ሕዝብ፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ያመጡብን እኛንና ሕዝባችንን ለማስፈጀት ነው” በማለት ጮኹ። የእግዚአብሔር እጅ በርትቶባቸው ስለ ነበር፥ ሞት ከተማዪቱን እጅግ አስደንግጧት ነበርና ሕዝቡ የፍልስጥኤማውያንን ገዢዎች በሙሉ ጠርተው፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ ወደ ገዛ ስፍራው ይመለስ፤ ያለበለዚያ እኛንም ሕዝባችንንም ይፈጃል” አሉ። ያልሞቱትን ደግሞ ዕባጩ ያሠቃያቸው ስለ ነበር፥ የከተማዪቱ ጩኸት እስከ ሰማይ ወጣ። የጌታም ታቦት በፍልስጥኤማውያን ሀገር ሰባት ወር ተቀመጠ። ፍልስጥኤማውያን ካህናትንና ጠንቋዮችን ጠርተው፥ “የጌታን ታቦት ምን እናድርገው? ወደ ስፍራው እንዴት መመለስ እንደሚገባን ንገሩን” አሏቸው። እነርሱም፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋር ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያን ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው። እነርሱም፥ “የምንልከው የበደል መሥዋዕት ምን መሆን አለበት?” ሲሉ ጠየቁ። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተንም ሆነ አለቆቻችሁን የመታው መቅሠፍት አንድ ዓይነት በመሆኑ፥ በፍልስጥኤማውያን ገዥዎች ቍጥር አምስት የወርቅ ዕባጮችና አምስት የወርቅ ዐይጦች ላኩ። አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዓይነት ምስሎችን ሠርታችሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፥ ከአማልክቶቻችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል። ግብፃውያንና ፈርዖን እንዳደረጉት ልባችሁን የምታደነድኑት ለምንድን ነው? እነርሱ እስራኤላውያንን የለቀቋቸው እርሱ በጽኑ ከቀጣቸው በኋላ አይደለምን? ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞች አዘጋጁ። ላሞቹን በሠረገላው ጥመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ወደ ቤት መልሷቸው። የጌታን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን ልዩ ልዩ የወርቅ ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፤ መንገዱንም እንዲሄድ ልቀቁት። ከዚያም ወዴት እንደሚሄድ ተመልከቱ፤ ወደ ገዛ አገሩ ወደ ቤትሼሜሽ አቅጣጫ የሚሄድ ከሆነ፥ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እርሱ ነው። ወደዚያ ካልሄደ ግን፥ መከራው በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የእርሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን።” እነርሱም እንደዚሁ አደረጉ። ሁለቱን ላሞች ወስደው በሠረገላው ጠመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውንም በቤት ውስጥ ዘጉባቸው። የጌታን ታቦት በአይጦችና በእባጮች ምስል ከተሠራ ወርቅ ከተሞላበት ሣጥን ጋር በሠረገላው ላይ አስቀመጡ፤ ከዚያም ላሞቹ መንገዳቸውን በመያዝ፥ እምቧ እያሉ፥ ቀጥ ብለው ወደ ቤትሼሜሽ አመሩ። የፍልስጥኤም ገዢዎችም እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ተከተሏቸው። በዚህ ጊዜ የቤትሼሜሽ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴአቸውን ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው ሲመለከቱም ታቦቱን በማየታቸው በጣም ደስ አላቸው። ሠረገላውም ወደ ቤትሼሜሽ ወደ ኢያሱ እርሻ መጥቶ ቆመ። በዚያ ስፍራ አንድ ትልቅ ቋጥኝ ነበር። ሕዝቡም የሠረገላውን ዕንጨት ፈለጡት፤ ላሞቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለጌታ አቀረቡ። ሌዋውያኑም የጌታን ታቦትና የወርቅ ዕቃዎቹን የያዘውን ሣጥን አውርደው በትልቁ ቋጥኝ ላይ አኖሩ። በዚያችም ዕለት የቤትሼሜሽ ሕዝብ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ። አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎችም ይህን ተመልክተው፥ በዚያው ዕለት ወደ ዔቅሮን ተመለሱ። ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለጌታ የላኳቸው የወርቅ ዕባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዱ ስለ አሽዶድ፥ አንዱ ስለ ጋዛ፥ አንዱ ስለ አስቀሎና፥ አንዱ ስለ ጌት፥ አንዱ ስለ ዔቅሮን የቀረቡ ነበሩ። የወርቅ ዐይጦቹም ቍጥር፥ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎች በሚያስተዳድሯቸው የተመሸጉ ከተሞችና ከእነዚህ ውጭ ባሉት መንደሮቻቸው ቍጥር ልክ ነው። በቤትሼሜሻዊው በኢያሱ እርሻ ውስጥ የጌታን ታቦት ያስቀመጡበት ያ ትልቅ ቋጥኝ እስከ ዛሬ ምስክር ነው። ጌታም ከቤትሼሜሽ ሰዎች ጥቂቱን መታ፤ ምክንያቱም ወደ ጌታ ታቦት ውስጥ በመመልከታቸው ነበር። ከመካከላቸው ሰባ ሰዎችን ገደለ፤ ጌታ እጅግ ስለ መታቸውም ሕዝቡ አለቀሱ። የቤትሼሜሽም ሰዎች፥ “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ በጌታ ፊት ማን መቆም ይችላል? ታቦቱስ ከዚህ ወጥቶ ወደ ማን ይሂድ?” አሉ። ከዚያም ወደ ቂርያትይዓሪም ሰዎች መልእክተኞች ልከው፥ “ፍልስጥኤማውያን የጌታን ታቦት መልሰውልናል፤ መጥታችሁ ወደ እናንተ ውሰዱት” አሏቸው። የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የጌታን ታቦት ይዘው ወጡ፤ ከዚያም በኮረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት ወሰዱት። የጌታን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ረዥም ጊዜ ሆነው፤ ሃያ ዓመትም ያህል ኖረ። በዚያን ጊዜ የእስራኤል ቤት ሁሉ አዝኖ ጌታን ፈለገ። ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ “በፍጹም ልባችሁ ወደ ጌታ የምትመለሱ ከሆነ፥ ባዕዳን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለጌታ አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው። ስለዚህ እስራኤላውያን የበዓልንና የዐስታሮትን አማልክት አስወግደው፥ ጌታን ብቻ አመለኩ። ከዚያ በኋላ ሳሙኤል፥ “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ጌታ እጸልያለሁ” አለ። እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ውሃ ቀድተው በጌታ ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለትም ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” አሉ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር። ፍልስጥኤማውያንም እስራኤል በምጽጳ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ፥ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ሊወጓቸው ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ። ሳሙኤልንም፥ “አምላካችን ጌታ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ወደ እርሱ መጸለይህን አታቋርጥ” አሉት። ስለዚህ ሳሙኤል አንድ የሚጠባ የበግ ግልገል ወስዶ ሙሉ ለሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለጌታ አቀረበው፤ ስለ እስራኤልም ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም መለሰለት። ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያሳርግበት ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት ቀረቡ። ጌታ ግን በዚያ ዕለት በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ አንጐዳጐደባቸው፤ እነርሱም እጅግ ተሸበሩ፤ በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመተውም ሸሹ። እስራኤላውያንም ከምጽጳ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን እስከ ቤትካር በታች እያሳደዱ በየመንገዱ ገደሉአቸው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አቆመው፤ “ጌታ እስከ አሁን ድረስ ረድቶናል” ሲል ስሙን “አቤንኤዘር” ብሎ ጠራው። በዚህ ሁኔታ ፍልስጥኤማውያን ድል ስለተመቱ የእስራኤልን ምድር ዳግመኛ አልወረሩም። ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ የጌታ እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል የወሰዷቸው ከዔቅሮን እስከ ጌት የነበሩ ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱላት፤ ግዛታቸውም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ነፃ ወጣች፤ በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ሰላም ወርዶ ነበር። ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ እስራኤልን ይዳኝ ነበር። በየዓመቱ በቤቴል፥ በጌልጌላና በምጽጳ እየተዘዋወረ፥ በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። ከዚያም በራማም ወዳለው ቤት ይመለስ ነበር፤ በዚያም ደግሞ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። በዚያም ለጌታ መሠዊያ ሠራ። ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን ፈራጆች አድርጎ በእስራኤል ላይ ሾማቸው። የበኩር ልጁ ስም ኢዩኤል ሲሆን፥ የሁለተኛው ልጁ ስም አቢያ ነበረ፤ እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር። ልጆቹ ግን የአባታቸውን ፈለግ አልተከተሉም፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከመንገዱ ወጡ፤ ጉቦ ተቀበሉ፤ ፍርድም አጣመሙ። ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ሳሙኤል ወዳለበት ወደ ራማ መጡ። እነርሱም፥ “አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ ስለዚህ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት። ነገር ግን፥ “የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም፤ ስለዚህ ወደ ጌታ ጸለየ። ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ። ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አሁንም የሚሉህን ስማ፤ ግን በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በብርቱም አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም የጌታን ቃል ሁሉ፥ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ። እንዲም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ። አንዳንዶቹን ሻለቆችና አምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፥ ሌሎቹን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቶ ቀማሚ፥ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል። ከእርሻችሁ፥ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ወስዶ ያሠራቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተም ባርያዎቹ ትሆናላችሁ። ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ጌታ አይመልስላችሁም።” ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እምቢ በማለት፥ እንዲህ አሉ፦ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን። እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፥ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።” ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ ለጌታ ተናገረ። ጌታም፥ “አድምጣቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፥ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው። ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጸሮር ልጅ፥ የበኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፊሐ ልጅ ነበር። ቂስም ከእስራኤል ልጆች መካከል በመልከ ቀናነት ተወዳዳሪ የማይገኝለት፥ ቁመቱም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ፥ ሳኦል የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው። በዚያም ጊዜ የሳኦል አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን፥ “ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልግ” አለው። ስለዚህ በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኘም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። ከዚያም በብንያም ምድር በኩል አለፉ፤ ሆኖም አላገኟቸውም። ወደ ጹፍ ምድር በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፥ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፥ ና እንመለስ” አለው። አገልጋዩ ግን፥ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ሊነግረን ይችል ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት። ሳኦልም አገልጋዩን፥ “ብንሄድስ ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቋአል፤ ለዚያ የእግዚአብሔር ሰው የምንሰጠው ስጦታ የለንም፤ ምን አለን?” አለው። አገልጋዩ፦ “እነሆ፥ እኔ የአንድ ጥሬ ብር አንድ አራተኛው እጅ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ ለሳኦል መለሰለት። ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፥ “ኑ፥ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና። ሳኦልም፥ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፥ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፥ “ባለ ራእዩ እዚህ አለን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፥ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤ ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፥ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት ሕዝቡ እርሱ ከመምጣቱ በፊት አይበላም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።” እነርሱም ወደ ከተማይቱ ወጡ፤ ወደ ከተማይቱም በመግባት ላይ ሳሉ፥ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ጌታ ለሳሙኤል እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤ “ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቀባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ የስቃይ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሷልና።” ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ ጌታ፥ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ! እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው። ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፥ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው። ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ፤ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጠዋት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ። ተገኝተዋልና፥ ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ ማን ነው? ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተሰብ ሁሉ አይደለምን?” ሳኦልም፥ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው። ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፥ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው። ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፥ “ይህ፥ እንግዶችን ጋብዣለሁ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ፥ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ። ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ። በነጋም ጊዜ በማለዳ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፥ “ላሰናብትህ ስለሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፥ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ። ወደ ከተማዪቱ ዳርቻ እየወረዱ ሳለ፥ ሳሙኤል ሳኦልን፥ “አገልጋይህ ወደ ፊት ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው፤ አገልጋይህም እንዳለፈ፥ አንተ ግን ከጌታ የተላከ መልእክት እንድነግርህ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ቆይ” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፥ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ ሳመው፥ እንዲህም አለው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ ጌታ ቀብቶህ የለምን? ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፥ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፥ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፥ ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ እያለ በመጨነቅ ላይ ነው” ይሉሃል። “አንተም ጉዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው ባሉጥ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፥ ሌላው ሦስት ዳቦ፥ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል። እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ከእጃቸው ትቀበላለህ። ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስክም የነቢያት ጉባኤ በበገና፥ በከበሮ፥ በዋሽንትና በመሰንቆ ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። የጌታም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነትት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ግን ሰባት ቀን መቆየት አለብህ።” ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ። ጊብዓ በደረሱ ጊዜ፥ እነሆ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ። ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፥ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ። በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፥ “አባታቸውስ ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፥ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፥ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እርሱም፥ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። የሳኦል አጎትም፥ “እባክህ፥ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው። ሳኦልም መልሶ፥ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጦ ነገረን” አለው። ነገር ግን ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም። ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ምጽጳ ወደ ጌታ ፊት ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።’ ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ሆናችሁ በጌታ ፊት ቅረቡ።” ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፥ የብንያም ነገድ ተመረጠ። ከዚያም የብንያምን ነገድ በየወገኑ ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ቤተሰብም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም። ሰዎቹም፥ “ሰውየው መጥቷልን?” ሲሉ ጌታን ጠየቁ። ጌታም፥ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጓል” አለ። እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር። ሳሙኤልም መላውን ሕዝብ፥ “ጌታ የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” አለ። ከዚያም ሕዝቡ፥ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ ይሁን!” ብሎ ጮኸ። ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ተግባርና ሥርዓት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በጌታ ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ። ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ። አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች ግን፥ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ። አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ያቢሽ ገለዓድን ከበባት፤ የያቢሽም ሰዎች ሁሉ ናዖስን፥ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። አሞናዊው ናዖስ ግን፥ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። የያቢሽም ሽማግሌዎች፥ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ ለአንተ እንገዛለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከእርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፥ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የያቢሽ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ቁጣውም እጅግ ነደደ። ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቆራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፥ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቆራረጣል!” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከጌታ ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሠራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቁጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺህ፥ ከይሁዳም ሠላሳ ሺህ ነበር። ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፥ “ለያቢሽ ገለዓድ ሰዎች፥ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለያቢሽ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ተደሰቱ። የያቢሽም ሰዎች፥ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው። በማግስቱ ሳኦል ሠራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳን ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። ሕዝቡ ሳሙኤልን፥ “ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል! ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት። ሳኦል ግን፥ “ይህ ዕለት ጌታ እስራኤልን የታደገበት ቀን ሰለሆነ፥ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፥ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውንም እናጽና” አለ። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በጌታ ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት በጌታ ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ በታላቅ ደስታ አከበሩት። ሳሙኤል ለመላው እስራኤል እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ያላችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ። ንጉሥ ሆኖ የሚመራችሁንም ሰው እነሆ፤ አግኝታችኋል። እኔም ዕድሜዬ ገፍቷል፤ ጠጉሬም ሸብቷል፤ ልጆቼም አብረዋችሁ አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቆይቻለሁ። እነሆ፤ ከፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንን አህያ ወሰድሁ? ማንን አታለልሁ? በማንስ ላይ ግፍ ሠራሁ? አይቶ እንዳላየ ለመሆንስ ከማን እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።” እነርሱም፥ “አላታለልኸንም ወይም ግፍ አልሠራህብንም፤ ከማንም እጅ አንዳች ነገር አልተቀበልህም” ብለው መለሱለት። ሳሙኤልም፥ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ ጌታና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው” አላቸው። እነርሱም፥ “እርሱ ምስክር ነው” አሉ። ከዚያም ሳሙኤል ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ሙሴንና አሮንን የመረጠ፥ የቀድሞ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ያወጣ ጌታ ነው። አሁንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ጌታ ስላደረገው የጽድቅ ሥራ ሁሉ በጌታ ፊት ስለምሟገታችሁ በዚህ ቁሙ። ያዕቆብ ወደ ግብጽ ከገባ በኋላ፥ አባቶቻችሁ ጌታ እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ጮኹ፤ ጌታም የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር አውጥተው በዚህ ስፍራ እንዲኖሩ ያደረጉትን ሙሴንና አሮንን ላከላቸው። እነርሱ ግን አምላካቸውን ጌታን ረሱት፤ ስለዚህ ለሓጾር የጦር አዛዥ ለሲሣራ፥ ለፍልስጥኤማውያንና ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ሰጣቸው። እነርሱም፥ ‘ጌታን ትተን በዓልንና አስታሮትን በማምለካችን፥ ኃጢአት ሠርተናል። አሁን ግን ከጠላቶቻችን እጅ ታደገን፤ እኛም አንተን እናመልካለን’ ሲሉ ወደ ጌታ ጮኹ። ከዚያም ጌታ ይሩበኣልን፥ ባርቅን፥ ዮፍታሔንና ሳሙኤልን ልኮ በሰላም ትኖሩ ዘንድ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ እጅ ታደጋችሁ። የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ እንደመጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ ግን፥ አምላካችሁ ጌታ ንጉሣችሁ ቢሆንም እንኳን፥ ‘አይሆንም፤ የሚገዛን ንጉሥ እንፈልጋለን’ አላችሁ። አሁንም የጠየቃችሁትና የመረጣችሁት ንጉሥ ይኸው፤ እነሆ፥ ጌታ በላያችሁ አነገሠላችሁ። የምትፈሩና የምታመልኩ፥ የምትታዘዙትና በትእዛዛቱ ላይ የማታምጹ ከሆነ፥ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን ጌታን ከተከተላችሁ፥ መልካም ይሆንላችኋል። ጌታን የማትሰሙና የማትታዘዙ፥ በትእዛዛቱም ላይ የምታምጹ ከሆነ ግን፥ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ጌታ በዐይናችሁ ፊት የሚያደርገውንም ይህን ታላቅ ነገር ተመልከቱ! አሁን የስንዴ መከር ጊዜ አይደለምን? እኔ ነጐድጓድና ዝናብ እንዲልክ ወደ ጌታ እጮኻለሁ፤ እናንተም ንጉሥ እንዲነግሥላችሁ በመጠየቃችሁ በጌታ ፊት የቱን ያህል የከፋ ድርጊት እንደፈጸማችሁ ያንጊዜ ታውቃላችሁ።” ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ወደ ጌታ ጮኸ፤ በዚያኑ ዕለት ጌታ ነጐድጓድና ዝናብ ላከ። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ ጌታንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ። ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን፥ “ሌላው በደላችን ሳያንስ፥ ንጉሥ እንዲነግሥልን በመጠየቃችን ተጨማሪ ክፋት ስላደረግን እንዳንሞት፥ ለአገልጋዮችህ ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ጸልይልን” አሉት። ሳሙኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል፤ ሆኖም ጌታን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ ጌታን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። ሊጠቅሟችሁ ወይም ሊያድኗችሁ የማይችሉ ከንቱ ነገሮችን አትከተሉ፤ ምክንያቱም ከንቱ ናቸው። ጌታ የራሱ ሕዝብ ሊያደርጋችሁ ስለ ወደደ፥ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ጌታ ሕዝቡን አይተውም። ከዚህም በላይ እኔ ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት ጌታን እንዳልበድል ይህ ከእኔ ይራቅ፤ እኔ መልካምና ቅን የሆነውን መንገድ አስተምራችኋለሁ። ብቻ ጌታን ፍሩ፤ በፍጹም ልባችሁ በታማኝነት አምልኩት፤ ያደረገላችሁንም ታላላቅ ነገሮች አስቡ። በክፉ ሥራችሁ ብትጸኑ ግን፥ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።” ሳኦል በእስራኤልም ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ እንዲህ ሆነ፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱ ሺህ በማክማስና በተራራማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፥ አንዱ ሺህ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ ድንኳኖቻቸው እንዲሄዱ አሰናበተ። ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፥ “ዕብራውያን ይስሙት!” በማለት በሀገሩ ሁሉ መለከት አስነፋ። እስራኤላውያን ሁሉ፥ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ የተጠሉ ሆኑ” የሚለውን ወሬ ሰሙ። ሕዝቡም ከሳኦል ጋር ለመሰለፍ ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያን ሠላሳ ሺህ ሠረገሎች፥ ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ቁጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሠራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን ያሉበት ሁኔታ እጅግ አስጊ መሆኑንና ሠራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፥ በየዋሻውና በየቁጥቋጦው፥ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጉድጓዱ ሁሉ ተሸሸጉ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበር፤ አብሮት የተሰለፈው ሠራዊት ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰዎች መበታተን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፥ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ፥ ወዲያውኑ ሳሙኤል ደረሰ፤ እርሱም ሊቀበለው ወጣ። ሳሙኤል ግን “ያደረግኸው ነገር ምንድነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ሠራዊቱ መበታተኑን፥ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፥ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የጌታን ርዳታ አልለመንሁም፥ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ። ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ ጌታ የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ ጌታ እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የጌታን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፥ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።” ከዚያ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ሄደ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፤ ስድስት መቶ ያህል ነበሩ። ሳኦል፥ ልጁ ዮናታንና ሠራዊታቸው በብንያም ግዛት ውስጥ ጌባዕ ተብላ በምትጠራው ስፍራ ነበሩ፤ የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች ግን በሚክማስ ሰፍረው ነበር፤ በሦስት ምድብ የተከፈሉ ወራሪዎች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጡ፤ አንዱ ምድብ በሹዓል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቅጣጫ አመራ፤ ሌላው ምድብ ወደ ቤትሖሮን፥ ሌላው ምድብ ደግሞ ከጸቦዒም ሸለቆና ከምድረ በዳው ፊት ለፊት ወደሚገኘው ድንበር አለፈ። በመላው የእስራኤል ምድር ብረት አቅልጦ ሠሪ አይገኝም ነበር፤ ምክንያቱም ፍልስጥኤማውያን፥ “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር ለራሳቸው አይሥሩ” ብለው ስለ ነበር ነው። ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ማረሻቸውንና ዶማቸውን ለማሾል፥ መጥረቢያቸውንና ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርዱ ነበር። ማረሻና ዶማ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ ሁለት ሦስተኛ ሰቅል ሲሆን፥ መጥረቢያ ለማሳል፥ መውጊያ ለማበጀት ደግሞ ዋጋው አንድ ሦስተኛ ሰቅል ነበር። ስለዚህ ጦርነቱ በተደረገበት ዕለት ከሳኦልና ከልጁ ከዮናታን በስተቀር፥ አብረዋቸው ከነበሩት ወታደሮች መካከል ሰይፍ ወይም ጦር የያዘ አንድም ሰው አልነበረም። በዚያን ጊዜ አንድ የፍልስጥኤማውያን የጦር ምድብ የሚክማስን መተላለፊያ ለመቆጣጠር ወጣ። አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን ፥ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የጌታ ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ሕዝቡም ዮናታን አለመኖሩን አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ ሁለት ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱ ስም ቦጼጽ ሲሆን፥ ሌላው ሴኔ ተብሎ ይጠራል። ከድንጋዮቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ ወደነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም ጌታ ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን ጌታን የሚያግደው የለምና” አለው። ወጣቱ ጋሻ ጃግሬም፥ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፥ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው። እነርሱም፥ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፥ ስፍራችንን ይዘን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፥ ‘ወደ እኛ ኑ’ ካሉን፥ ጌታ እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለሆነ፥ ወደ እነርሱ እንወጣለን።” ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ሠራዊት በታዩ ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን፥ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ። የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፥ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ የምናሳያችሁ ነገር ይኖራል” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው። ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ ጌታ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው። ዮናታን በእጁና በእግሩ ወደ አፋፉ፥ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። በዮናታንም እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተኋላው እየተከተለ ገደላቸው። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳያቸው በአንድ ጥማድ የእርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ። በሰፈር በእርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር። በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ጠባቂዎች፥ የፍልስጥኤም ሠራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፥ “ሠራዊቱን ቁጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ ለዩ” አላቸው። በቆጠሩም ጊዜ፥ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። ሳኦልም አኪያን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር። ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው። ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት በታላቅ ትርምስ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደነበሩት እስራኤላውያን ገቡ። በተራራማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱም አጥብቀው በመከታተል ሊወጉአቸው አሳደዷቸው። በዚያ ቀን ጌታ እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤትአዌን ዘልቆ ሄደ። ሳኦል፥ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት፥ እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አስምሎ ስለ ነበር፥ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፥ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር። ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፥ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ ወደ ምድር መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሓላውን ፈርቶ ስለ ነበር፥ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም። ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ። ከሕዝቡም አንድ ሰው፥ “አባትህ ሕዝቡን፥ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት በጽኑ መሓላ አስጠንቅቆናል” አለው። ሰው ሁሉ ተዳክሞ ነበር። ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ! ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቍጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።” በዚያች ዕለት ፍልስጥኤማውያንን ከሚክማስ እስከ አያሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ ሕዝቡ እጅግ ዝለው ነበር። በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፥ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት። ከዚያም ለሳኦል፥ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት ጌታን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው። ሳኦልም፥ “ይህ የክሕደት ተግባር ነው! አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ ወደዚህ አምጡልኝ” አለ። ሳኦልም፥ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፥ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት ጌታን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ። ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ አረደው። ሳኦልም ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ለጌታ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። ከዚያም በኋላ ሳኦልም፥ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪ ነጋ ድረስ እንዝረፋቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስቀርላቸው” አለ። እነርሱም “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት። ካህኑ ግን፥ “ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ” አለ። ሳኦልም፥ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እርሱ ግን በዚያች ቀን አልመለሰለትም። ሳኦል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፥ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም። እስራኤልን የታደገ ሕያው ጌታን! አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም። ለእስራኤላውያን ሁሉ፥ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው። ሰዎቹም፥ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” አሉት። ሳኦል፥ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ” ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ። ሳኦልም፥ “በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ። ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፥ “ያደረግኸውን ነገር ንገረኝ” አለው። ዮናታንም፥ “በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆኝ፥ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው። ሳኦልም፥ “ዮናታን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ፤ እንዲህም ይጨምርብኝ፤ ዛሬ ፈጽመህ ትሞታለህ” አለ። ሕዝቡ ግን ሳኦልን፥ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? ይህ አይሆንም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለ ሆነ፥ ሕያው ጌታን! ከራስ ጠጉሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ። ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ተመለሱ። ሳኦል በእስራኤል ላይ ከነገሠ በኋላ፥ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ሞዓብን፥ አሞናውያንን፥ ኤዶምን፥ የጾባን ነገሥታትና ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በተዋጋበት ስፍራ ሁሉ ድል አድራጊ ነበር። በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው። የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ ይሽዊና ማልኪሹዓ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፥ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር። የሳኦል ሚስት አሒኖዓም የምትባል የአሒማዓጽ ልጅ ነበረች፤ የሠራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የሳኦል አጎት የኔር ልጅ ነበረ። የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር የአቢኤል ልጆች ነበሩ። በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ሳኦልም ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቍጥር ወደ ራሱ ይሰበስብ ነበር። ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እንድቀባህ ጌታ ላከኝ፤ አሁንም የጌታን ቃል ስማ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ ስለ ተቃወሙት እቀጣቸዋለሁ። አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንም ሴቱንም፥ ልጁንም ሕፃኑንም፥ የቀንድ ከብቱንም በጉንም፥ ግመሉንም አህያውንም ግደል።’ ” ስለዚህ ሳኦል ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ ጤሌም በሚባል ስፍራ ቆጠራቸው፤ የእግረኛ ወታደሮቹ ብዛት ሁለት መቶ ሺህና ከይሁዳ ዐሥር ሺህ ሰዎች ሆነው ተገኙ። ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ሄዶ በሸለቆ ውስጥ አደፈጠ። እርሱም ቄናውያንን፥ “ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከአማሌቃውያን ራቁ፤ ተለዩአቸውም፤ ምክንያቱም እናንተ እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ቸርነት አድርጋችሁላቸዋልና” አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለዩ። ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ በምሥራቅ ግብጽ እስካለው እስከ ሱር ድረስ ወጋቸው። የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው። ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ አጋግን፥ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፥ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፥ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ። የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፤ “እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና፥ ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ።” ሳሙኤልም እጅግ ተቆጥቶ፥ ሌሊቱን ሁሉ ወደ ጌታ ጮኸ። ሳሙኤልም ጠዋት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፥ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዷል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዷል” ተብሎ ተነገረው። ሳሙኤልም ባገኘው ጊዜ ሳኦል፥ “ጌታ ይባርክህ! የጌታን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው። ሳሙኤል ግን፥ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድነው?” ሲል ጠየቀ። ሳኦልም፥ “ሠራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለጌታ ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “ስማ! ትናንት ማታ ጌታ የነገረኝን ልንገርህ?” አለው። ሳኦልም፥ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “ስለ ራስህ የነበረህ ግምት ታናሽ የነበር ቢሆንም፥ የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? ጌታም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። ጌታም፥ ‘ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። ታዲያ የጌታን ቃል ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?” ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የጌታን ቃል ታዝዣለሁ፤ ጌታ በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። ሕዝቡ ግን በጌልገላ ለአምላክህ ለጌታ ለመሠዋት ከምርኮው ከተለዩት መካከል፥ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ ወስደዋል።” ሳሙኤልም፦ “ጌታ ለቃሉ በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፥ ጌታ፥ በሚቃጠል ቁርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ሟርተኛነት ያለ ኃጢአት፥ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው፤ አንተ የጌታን ቃል ንቀሃልና እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የጌታን ትእዛዝና የአንተን ቃል አልጠበቅሁም፤ ሕዝቡን በመፍራት የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ አሁንም፥ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።” ሳሙኤል ግን ሳኦልን፥ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የጌታን ቃል ንቀሃል፤ ጌታም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው። ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፥ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፤ ልብሱም ተቀደደ። ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “ጌታ የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል። የእስራኤል ክብር የሆነው እርሱ አይዋሽም፤ አይጸጸትምም፤ እርሱ ይጸጸት ዘንድ ሰው አይደለም።” ሳኦልም መልሶ፥ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ነገር ግን በሕዝቤ አለቆች ፊትና በእስራኤል ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለጌታ እሰግድ ዘንድ እባክህ አብረኸኝ ተመለስ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል አብሮት ተመለሰ፤ ሳኦልም ለጌታ ሰገደ። ከዚያም ሳሙኤል፥ “የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ። አጋግም፥ “በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን?” በማለት እየተንቀጠቀጠ መጣ። ሳሙኤልም፥ “ሰይፍህ ሴቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፥ እናትህም በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች” ሲል አጋግን ጌልገላ ላይ በጌታ ፊት ቆራረጠው። ከዚያም ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ። ሳኦል ግን ወደ ቤቱ ወደ ሳኦል-ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤል ለሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳ እስከሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፤ ጌታም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጸተ። ጌታ ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፥ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው። ሳሙኤል ግን፥ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ‘ለጌታ ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል። እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።” ሳሙኤል ጌታ ያለውን ነገር አደረገ። ቤተልሔም እንደደረሰም፥ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፥ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት። ሳሙኤልም፥ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለጌታ መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው። እዚያ በደረሱ ጊዜም፥ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፥ “በእርግጥ ጌታ የቀባው ሰው እነሆ፤ በጌታ ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ። ጌታ ግን ሳሙኤልን፥ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። ጌታ የሚያየው፥ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ ጌታ ግን ልብን ያያል” አለው። ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፥ “ጌታ ይህንንም አልመረጠውም” አለው። እሴይም ሻማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፥ “እርሱንም ጌታ አልመረጠውም” አለ። እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፥ “ጌታ እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው። ቀጥሎም እሴይን፥ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም፥ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም እሴይን፥ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥም” አለው። ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፥ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። ጌታም፥ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቀባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የጌታ መንፈስ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ ራማ ተመለሰ። የጌታ መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከጌታ ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር። የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፥ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።” ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሳኦል፥ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ፥ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፥ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። ከዚያም ሳኦል፥ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ። ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ተልኮ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፥ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር። ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፥ በይሁዳ ምድር በሰኮ ላይ አከማቹ፤ በሰኮና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌስደሚምም ሰፈሩ። ሳኦልና እስራኤላውያን ደግሞ ተሰብስበው በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ተሰለፉ። በመካከላቸው ሸለቆ ሆኖ፥ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ተራራ እስራኤላውያን ደግሞ ሌላውን ተራራ ያዙ። ከጋት ከተማ የመጣ፥ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የነበር ጎልያድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግዙፍ ዋነኛ ጀግና ሰው፥ ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። እርሱም ከናስ የተሠራ የናስ ቁር ደፍቶ፥ ክብደቱ አምስት ሺህ ሰቅል የሆነ የናሐስ ጥሩርም ለብሶ ነበር። በእግሮቹም ላይ የሐናስ ገምባሌ አድርጎ፥ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናሐስ ጭሬ ይዞ ነበር። የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፥ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሠራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፥ እኛ ባርያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባርያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፥ “ዛሬ የእስራኤልን ሠራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊት፥ በይሁዳ ስምንት ወንዶች ልጆች የነበሩት፥ የቤተልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይም በሳኦል ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤሊአብ፥ ሁለተኛው አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሻማ ይባላሉ፤ ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ እየመጣ በመቆም ይታያቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለሻለቃው የጦር አዛዥ አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፥ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።” ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፥ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጉዞ ጀመረ። ልክ ሠራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፥ እነሆ፥ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሃት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፥ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፥ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፥ “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፥ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤሊአብ፥ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውካቸው? ዕብሪትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልምን?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፥ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፥ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ እኔ አገልጋይህ ሄጄ እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና ልጅ ነህ፥ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፥ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፥ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፥ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባርያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ ጌታ አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሲል ዳዊት ተናገረ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ከናሐስ የተሠራ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበሰው። ዳዊትም ይህን ዓይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፥ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ እርሱም ሳኦልን፥ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ያንን አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፥ ወንጭፉን በእጁ ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ። ጌታ ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቆርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ጌታ ያለ ሰይፍ ወይም ያለ ጦር እንደሚያድን ያውቃሉ፤ ሰልፉ የጌታ ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፥ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ በግምባሩም ምድር ላይ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጋት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓራይም አንሥቶ እስከ ጋትና ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወደቀ። እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን አሳደው ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ። ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የጦር መሣሪያዎቹን ግን በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም ሲሄድ ሳኦል ተመልክቶ የሠራዊቱን አዛዥ አበኔርን፥ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው። አበኔርም፥ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፥ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፥ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦልም “አንተ ወጣት የማን ልጅ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። ዳዊትም “የቤተልሔም ነዋሪ የሆነው የአገልጋይህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰለት። ዳዊት ከሳኦል ጋር የሚያደርገውን ንግግር እንዳበቃ፤ የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቆራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን አብሮት እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም። ዮናታን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ኪዳን አደረገ፤ ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከነጦር ልብሱ፥ በተጨማሪም ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ሰጠው። ሳኦል በሚልከው በማናቸውም ስፍራ፥ ዳዊት ተልእኮውን በሚገባ ይፈጽም ስለ ነበር፥ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ ይህም ሕዝቡን በሙሉ፥ የሳኦልንም የጦር ሹማምንት ደስ አሰኘ። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ከገደለ በኋላ፥ ሰዎቹ ወደየቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ፥ ሴቶች ከበሮና መሰንቆ ይዘው እየዘፈኑ፥ እየጨፈሩና እልል እያሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። ሴቶችም “ሳኦል ሺ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺ ገዳይ!” እያሉ በቅብብል ይዘፍኑ ነበር። ሳኦል እጅግ ተቆጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፥ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው!” አለ። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር። በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቆራኘው፥ ሳኦል በቤቱ ሆኖ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት በየእለቱ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር። እርሱም፥ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። ጌታ ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለሆነ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺህ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር። ጌታም ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም፥ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈራው፤ መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና ዳዊትን ወደዱት። ሳኦል ዳዊትን፥ “ታላቋ ልጄ ሜራብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የጌታንም ጦርነቶች ተዋጋልኝ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፥ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበር። ዳዊት ግን ሳኦልን፥ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤም ሆነ የአባቴ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድነው?” አለው። ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤድሪኤል ተዳረች። በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው። ሳኦልም በልቡ፥ “ወጥመድ እንድትሆነው፥ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን፥ “እነሆ፤ ዛሬ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው። ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፥ “ለዳዊት፥ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ ዐማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቆጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እውቅና የሌለኝ መሆኔን አጣችሁትን?” አላቸው። የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን ነገሩት። ሳኦልም፥ “ዳዊትን፥ ‘ንጉሡም ለልጅቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር። ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፥ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፥ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቁጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። ሳኦል፥ ጌታ ከዳዊት ጋር እንደ ሆነና ልጁ ሜልኮልም እንደወደደችው በተረዳ ጊዜ፥ ሳኦል ከቀድሞው ይልቅ ዳዊትን ፈራው፤ እስከ ዕድሜ ልኩም ጠላቱ ሆነ። የፍልስጥኤማውያን ጦር አዛዦች እንደ ወትሮው ሁሉ ለጦርነት ይወጡ ነበር፤ ዳዊትም ከቀሩት የሳኦል መኳንንት የበለጠ ድል አገኘ፤ ስሙም እጅግ የታወቀ ሆነ። ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፥ ከጌታ ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ያንጊዜ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር እግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፥ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፥ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፥ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፥ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፥ “እገድለው ዘንድ ከነአልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ፥ እነሆ፥ የጣዖት ምስሉ በአልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጉር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፥ “እንዲህ አድርገሽ ለምን አታለልሽኝ? ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፥ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ ያለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት። ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፥ ወደ ራማ ወደ ሳሙኤል ሄደ፥ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ናዮት ሄደው በዚያ ተቀመጡ። ለሳኦልም፥ “እነሆ፤ ዳዊት ራማ በምትገኘው በናዮት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ እነርሱም የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። በመጨረሻም፥ እርሱ ራሱ ወደ ራማ ሄደ፤ ከዚያም በሴኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንደ ደረሰ፥ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። አንድ ሰውም “በራማ በምትገኘው የራማዋ ናዮት ናቸው” ብሎ ነገረው። ስለዚህ ሳኦል በራማ ወደምትገኘው ወደ የራማዋ ናዮት ሄደ፤ ሲሄድ ሳለም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ናዮት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። እርሱም ልብሱን አውልቆ፥ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቁቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፥ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቆጠረ?” ካለው የተነሣ ነው። ከዚህ በኋላ ዳዊት በራማ ካለችው የራማዋ ከናዮት ሸሽቶ ወደ ዮናታን በመሄድ፥ “ምን አድርጌአለሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? አባትህ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገውስ በፊቱ ምን ተገኝቶብኝ ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮናታንም፥ “ይህስ ካንተ ይራቅ! አትሞትም! እነሆ፤ አባቴ ትልቅም ይሁን ትንሽ ማናቸውንም ነገር አስቀድሞ ሳይነግረኝ አያደርገውም። ታዲያ አባቴ ይህንንስ ለምን ይደብቀኛል? እንዲህስ አይሆንም!” ብሎ መለሰለት። ዳዊት ግን፥ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሏል፤ ነገር ግን ሕያው ጌታን! በነፍስህ እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቷል” ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን፥ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው። ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለሆነ፥ ከንጉሡ ጋር ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤ አባትህ ከፈለገኝ፥ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለሆነ፥ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው። እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፥ አገልጋይህን የሚያሰጋው የለም፤ ከተቆጣ ግን፥ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግጣለህ። አንተ ግን ከአገልጋይህ ጋር በጌታ ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ። እኔ በደለኛ ከሆንኩ፥ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!” ዮናታንም፥ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው። ዳዊትም፥ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው። ዮናታን፥ “ና! ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ። ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ምስክር ይሁን! ነገ በዚህ ሰዓት ወይም በሦስተኛው ቀን፥ ስለ አንተ መልካም አስተሳሰብ ያለው መሆኑን አባቴን ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ፥ ስለዚሁ ጉዳይ የሚገልጥልህ መልእክተኛ እልክብሃለሁ፤ ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፥ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፥ ጌታ ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። ጌታ ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን። እኔም እንዳልሞት፥ በሕይወት እስካለሁ የጌታን ታማኝ ፍቅር አሳየኝ፤ ጌታ የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከምድረ ገጽ በሚደመስስበት ጊዜ እንኳ፥ ታማኝነትህ ከቤተሰቤ በፍጹም አይቋረጥ።” ስለዚህ ዮናታን፥ “የዳዊትን ጠላቶች ጌታ ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታን ከፍቅሩ የተነሣ ዳዊትን የሚወደውም እንደ ራሱ አድርጎ ነበርና ዳዊት እንደገና እንዲምልለት አደረገ። ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፥ አለመኖርህ ይታወቃል። ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤጼል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቆይ። እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤ ከዚያም፥ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፥ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፥ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደሆነ፥ በሕያው ጌታ ስም! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ ውጣና ና፤ አደጋ እንደማይኖርም እምልልሃለሁ። ነገር ግን ልጁን፥ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት ከአንተ ወዲያ ዐልፎ ነው’ ያልሁት እንደሆነ ጌታ እንድትሄድ ፈቅዷልና ሂድ። አንተና እኔ ስለ ተነጋገርነው ነገር እነሆ፤ ጌታ በመካከላችን ለዘለዓለም ምስክር ነው።” ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደበቀ፤ የወር መባቻ በዓል በተከበረበት ጊዜ፥ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ፤ ንጉሡ እንደ ወትሮው በግድግዳው አጠገብ ተቀመጠ፤ ዮናታን ከፊት ለፊቱ፥ አበኔር ደግሞ ከአጠገቡ ተቀመጡ፤ የዳዊት መቀመጫ ግን ባዶ ነበር። ሳኦልም፥ “ዳዊት በሥርዓቱ መሠረት እንዳይነጻ የሚያደርገው አንድ ነገር ገጥሞታል፤ በእርግጥም አልነጻም” ብሎ ስላሰበ፥ በዚያ ቀን ምንም አልተናገረም። በማግስቱም፥ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፥ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፥ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ። እርሱም ‘ቤተሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።” ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቆጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፥ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋር መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ? የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንህ መንግሥትህ አትጸኑም። መሞት ስለሚገባው፥ ሰው ላክና አስመጣልኝ!” ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል “ስለምን ይሞታል? ምንስ አደረገ?” ሲል መለሰ። ሳኦልም ዮናታንን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ ዮናታን፥ አባቱ ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ መነሣቱን ዐወቀ። ዮናታንም በታላቅ ቁጣ ከግብሩ ላይ ተነሣ፤ አባቱም ዳዊትን ስላዋረደው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ምግብ አልበላም። በማግስቱ ጠዋት ዮናታን አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ፥ ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ሄደ፤ ልጁንም፥ “ሩጥ! የምሰዳቸውን ፍላጻዎች ፈልጋቸው” አለው፤ ልጁም በሮጠ ጊዜ፥ ከእርሱ አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ። ልጁም የዮናታን ፍላጻ ባረፈበት ስፍራ እንደ ደረሰ፤ ዮናታን ጠራውና፥ “ፍላጻው ካንተ ወዲያ ዐልፎ የለምን?” አለው። እርሱም “ቶሎ በል! ፍጠን! አትቁም!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው ተመለሰ። ከዮናታንና ከዳዊት በስተቀር ልጁ ስለዚህ ነገር የሚያውቀው አንዳች አልነበረም። ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያውን ለልጁ ሰጥቶ፥ “ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው። ልጁ ከሄደ በኋላ፥ ዳዊት ከድንጋዩ በስተ ደቡብ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ በዮናታን ፊት ሦስት ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደለት፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱም፤ በይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር። ዮናታንም ዳዊትን፤ “ ‘በአንተና በእኔ፥ በዘሮችህና በዘሮቼ መካከል ጌታ ለዘለዓለም ምስክር ነው’ ተባብለን ወዳጅነታችን እንዲጸና በጌታ ስም ስለ ተማማልን እንግዲህ በሰላም ሂድ” አለው። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ። ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፥ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን አብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው። ዳዊት፥ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፥ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ። ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።” ካህኑም፥ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፥ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው። ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ በተራ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?” ሲል መለሰ። ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከጌታ ፊት ተነሥቶ በትኩስ እንጀራ ከተተካው ከኅብስት በስተቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና። በዚያችም ዕለት ከሳኦል አገልጋዮች አንዱና የእረኞቹ አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያው በጌታ ፊት እንዲቆይ ተገዶ ነበር። ዳዊት አቢሜሌክን፥ “የንጉሡ ጉዳይ ስላስቸኮለኝ፥ ሰይፌንም ሆነ ሌላ የጦር መሣሪያ አላመጣሁም፤ እዚህ ካንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አይገኝምን?” ሲል ጠየቀው። ካህኑም፥ “በኤላ ሸለቆ አንተ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ እዚህ አለ፤ ከኤፉዱ በስተ ኋላ በጨርቅ ተጠቅልሏል፥ እነሆ፥ ከፈለግህ ውሰደው፤ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ሰይፍ እዚህ የለም” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም “እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱኑ ስጠኝ” አለው። በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጋት ንጉሥ ወደ አኪሽ ሄደ። የአኪሽ አገልጋዮችም፥ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ዐሥር ሺህ ገደለ’ ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት። ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጋትን ንጉሥ አኪሽንም እጅግ ፈራው። ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፥ ለሐጩንም በጢሙ ላይ እያዝረከረከ እንደ እብድ ሆነ። አኪሽም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስቲ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ አጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?” ዳዊት ከጋት ተነስቶ ወደ ዓዶላም ዋሻ ሸሸ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተሰቦች ይህን በሰሙ ጊዜ፥ እርሱ ወዳለበት ወደዚያው ወረዱ። የተጨነቁ፥ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፤ እርሱም መሪያቸውም ሆነ። እነርሱም አራት መቶ ያህል ሰዎች ነበሩ። ዳዊት ከዚያ ተነሥቶ፥ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ለሞዓብ ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ፥ አባቴና እናቴ መጥተው ካንተ ዘንድ እንዲቀመጡ ፈቃድህ ነውን?” አለው። እርሱም በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ አስቀመጣቸው፤ ዳዊት በዐምባ ውስጥ እስከቆየበትም ጊዜ ድረስ ከንጉሡ ዘንድ ተቀመጡ። ይሁን እንጂ ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፥ “በዐምባው ውስጥ አትቆይ፤ ሂድና ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ። ሳኦልም፥ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በሰማ ጊዜ፥ በጊብዓ ኰረብታ ላይ ታማሪስክ ተብሎ የሚጠራ ዛፍ ሥር፥ ጦሩን በእጁ ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ አገልጋዮቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር። ሳኦልም እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የብንያም ሰዎች ስሙ! በውኑ የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን? በእኔ ላይ የዶለታችሁት ለዚህ ነውን? ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ማንም አልነገረኝም፤ ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፥ ልጄ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሣሣቱን ከእናንተ ስለ እኔ ተቆርቆሮ የነገረኝ ማንም የለም።” ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የሳኦል አገልጋዮች ጋር ቆሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ እንዲህ አለ፥ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወዳለው ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ። ዳዊትም ምን ማድረግ እንደሚገባው አቢሜሌክ ጌታን ጠይቆለታል፤ ለዳዊትም ጥቂት ምግብና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጥቶታል” ሲል ተናገረ። ከዚያም ንጉሡ፥ የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን፥ በኖብ ካህናት የነበሩትን የአባቱን ቤተሰብ በሙሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ። ሳኦልም፤ “የአኪጦብ ልጅ ሆይ፤ እንግዲህ ስማ” አለው። አቢሜሌክም፥ “እሺ ጌታዬ” ብሎ መለሰ። ሳኦልም፤ “ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፥ በእኔ ላይ እንዲያምፅብኝና እንዲያደባብኝ፥ እንጀራና ሰይፍ በመስጠት፥ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ በመጠየቅ ከእሴይ ልጅ ጋር ለምን ዶለታችሁብኝ?” አለው። አቢሜሌክም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ዐማች፥ የክብር ዘቦችህ አዛዥና በቤተሰብህ ዘንድ እጅግ የተከበረው ዳዊትን የመሰለ ታማኝ ከአገልጋዮችህ ሁሉ ማን አለ? ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ስጠይቅስ ያ ቀን የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተ አገልጋይህ የሚያውቀው ምንም ነገር ስለ ሌለ ንጉሥ እኔን አገልጋዩን ወይም ከአባቴ ቤተሰብ ማንንም ጥፋተኛ አያድርግ።” ንጉሡ ግን፥ “አቢሜሌክ ሆይ፤ አንተም የአባትህም ቤተሰብ በሙሉ በእርግጥ ትሞታላችሁ” አለው። ከዚያም ንጉሡ በአጠገቡ የቆሙትን ዘቦች፥ “እነዚህም የጌታ ካህናት ከዳዊት ጋር ስላበሩ፥ ዳዊት መኰብለሉንም እያወቁ ስላልነገሩኝ ዞራችሁ ግደሏቸው” ሲል አዘዛቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን እጃቸውን አንሥተው የጌታን ካህናት ለመምታት ፈቃደኞች አልሆኑም። ንጉሡም ኤዶማዊውን ዶይቅን፥ “እንግዲያውስ አንተው ዞረህ ካህናቱን ግደላቸው” ብሎ አዘዘው። ኤዶማዊው ዶይቅም ዞረና ገደላቸው። በዚያች ዕለት ሰማንያ አምስት የበፍታ ኤፉድ የለበሱ ካህናትን ገደለ። የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ መታት፥ በዚያ የሚኖሩትንም ወንዶችንና ሴቶችን፥ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን፥ እንዲሁም በሬዎችንና አህያዎችን፥ በጎችንም ሁሉ በሰይፍ ስለት አስገደለ። የአኪጦብ ልጅ፥ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ግን አምልጦ ዳዊት ወዳለበት ሸሸ። እርሱም ሳኦል የጌታን ካህናት እንደ ገደላቸው ለዳዊት ነገረው። ዳዊትም አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ያን ዕለት ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለ ነበር፥ ነገሩን በትክክል ለሳኦል እንደሚናገር አውቄአለሁ፤ ለመላው የአባትህ ቤተሰብ ዕልቂት ተጠያቂው እኔ ነኝ። አሁንም ከእኔ ጋር ቆይ፤ አትፍራ፤ የአንተን ሕይወት የሚፈልግ የእኔን ሕይወት ይፈልጋል። አብረኸኝ በሰላም ትኖራለህ።” ከዚህ በኋላ “እነሆ፤ ፍልስጥኤማውያን በቅዒላ ላይ ጦርነት ከፍተው፥ ዐውድማውን እየዘረፉት ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። እርሱም፥ “እነዚህን ፍልስኤማውያን ሄጄ ልምታን?” ሲል ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “ሂድ፤ ፍልስጥኤማውያንን ምታ፤ ቅዒላንም አድናት” ብሎ መለሰለት። የዳዊት ሰዎች ግን፥ “እዚሁ በይሁዳ ምድር እያለን እየፈራን ነው፤ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመውጋት ወደ ቅዒላ የምንሄድ ከሆነማ ምን ያህል የሚያስፈራ ነው?” አሉት። ዳዊት እንደገና ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥ፥ ወደ ቅዒላ ውረድ” አለው። ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ቅዒላ ሄደው፥ ፍልስጥኤማውያንን ወጉ፤ እንስሶቻቸውን ማርከው ወሰዱ፤ በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ ጉዳት አደረሱ፤ ዳዊትም የቅዒላን ሕዝብ ታደገ። የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ቅዒላ ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ፥ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር። ሳኦል የዳዊትን ወደ ቅዒላ መሄድ በሰማ ጊዜ፥ “ዳዊት መዝጊያና የብረት መወርወሪያ ወዳላት ከተማ መግባቱ፥ ራሱን በራሱ እንደ ማሰር ስለ ሆነ፥ ይህን ሰው እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጠኝ ነው” አለ። ይህን ብሎም ሳኦል ወደ ቅዒላ ወርደው ዳዊትንና ሰዎቹን እንዲከቡ ሠራዊቱን በሙሉ ለጦርነት ጠራ። ዳዊትም ሳኦል ክፉ እንዳሰበበት ባወቀ ጊዜ፥ ካህኑን አብያታርን፥ “ኤፉዱን አምጣ” አለው። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፤ ሳኦል ወደ ቅዒላ መጥቶ፥ በእኔ ምክንያት ከተማዪቱን ለማጥፋት ማሰቡን ባርያህ በትክክል ሰምቷል። የቅዒላ ሰዎች አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? ባርያህ እንደሰማውም ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፤ ለአገልጋይህ እንድትነግረው እለምንሃለሁ።” ጌታም፥ “አዎን ይወርዳል” አለው። ዳዊትም፥ “የቅዒላ ነዋሪዎች እኔንና ሰዎቼን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡናል?” ሲል ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን አሳልፈው ይሰጧችኋል” አለው። ስለዚህ ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎቹ ከቅዒላ ተነሥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ፤ ዳዊት ከቅዒላ መሸሹን በሰማ ጊዜ፥ ሳኦል ወደዚያ መሄዱን ተወ። ዳዊት በምድረ በዳ ባሉ ምሽጎችና በዚፍ ምድረ በዳ ኰረብታዎች ተቀመጠ፤ ሳኦልም በየዕለቱ ይከታተለው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዳዊትን አሳልፎ አልሰጠውም። ዳዊት በዚፍ ምድረ በዳ ሖሬሽ በተባለ ቦታ ሳለ፥ ሳኦል ሊገድለው መምጣቱን አየ። የሳኦል ልጅ ዮናታንም ዳዊት ወዳለበት ወደ ሖሬሽ ሄዶ፥ በእግዚአብሔር ስም አበረታታው፤ እርሱም፥ “አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል እጁን በአንተ ላይ አያሳርፍም፤ በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ ይህንም አባቴ ሳኦል እንኳ ያውቀዋል” አለው። ሁለቱም በጌታ ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ከዚያም ዮናታን ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊት ግን እዚያው ሖሬሽ ተቀመጠ። የዚፍ ሰዎች ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል ወጥተው፦ “እነሆ፤ ዳዊት ከየሴሞን በስተ ደቡብ በሐኪላ ኰረብታ ላይ በሖሬሽ ምሽጎች ውስጥ በመካከላችን ተደብቆ ይገኛል። አሁንም ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ደስ ባለህ ጊዜ ናና፥ እርሱን ለንጉሡ አሳልፎ መስጠት የእኛ ድርሻ ነው” አሉት። ሳኦል እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለእኔ ስለ ተቆረቆራችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ አሁንም ሂዱና አጣሩ ዘወትር የት እንደ ሆነና በዚያ ያየውን ሰው ለይታችሁ ዕወቁ፤ እጅግ ተንኰለኛ መሆኑን ሰምቻለሁ። ስለዚህ የሚደበቅባቸውን ቦታዎች ሁሉ ካያችሁ በኋላ ግልጽ መረጃ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አብሬችሁ እሄዳለሁ፤ ብቻ በዚያ አገር ይገኝ እንጂ በይሁዳ ነገዶች ሁሉ መካከል ከገባበት ጉድጓድ ገብቼ አወጣዋለሁ።” ሰዎቹም ሳኦል ከመሄዱ በፊት ወደ ዚፍ ተመለሱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሴሞን በስተ ደቡብ በዓረባ ውስጥ ባለው በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ። ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትን ሊፈልጉት ሄዱ፤ እርሱም ይህን በሰማ ጊዜ፥ ወደ ዐለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦልም ይህን እንደሰማ፥ ዳዊትን በማሳደድ ወደ ማዖን ምድረ በዳ ዘልቆ ገባ። ሳኦል በተራራው በአንዱ በኩል ሆኖ ሲያሳድድ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ በተራራው በሌላ በኩል ከሳኦል ለማምለጥ ይጣደፉ ነበር። ሳኦልና ወታደሮቹ ዳዊትንና ሰዎቹን ከበው ለመያዝ ተቃርበው ሳሉ፥ አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ፥ “ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወረውታልና ቶሎ ድረስ!” አለው። ከዚያም ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ፥ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ሄደ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “የመለያያ ዓለት” ብለው ጠሩት። ዳዊትም ከዚያ ወደ ላይ ወጥቶ በዔንገዲ ምሽጎች ተቀመጠ። ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፥ “እነሆ፥ ዳዊት በዔንገዲ ምድረ በዳ አለ” ብለው ነገሩት። ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ “የሜዳ ፍየሎች ዓለት” ወደ ተባለው ቦታ አቅራቢያ ሄደ። ሳኦልም በመንገድ ዳር ወዳለው ወደ አንድ የበጎች ማደሪያ በደረሰ ጊዜ፥ ዋሻ አግኝቶ ወገቡን ሊሞክር ወደዚያ ገባ። ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። የዳዊት ሰዎችም ዳዊትን፥ “ጌታ፥ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” አሉት። ዳዊትም በልቡ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ማንም ሳያውቅ ቆርጦ ወሰደ። ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቁረጡ ልቡ በኀዘን ተመታ። ለሰዎቹም፥ “ጌታ በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና ጌታ የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት ጌታ ይጠብቀኝ” አላቸው። ዳዊት ሰዎቹን በዚህ ቃል ከለከላቸው፤ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ከዋሻው ወጥቶ ሄደ። ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፥ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤ ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፥ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ? በዛሬው ዕለት በዋሻው ውስጥ ጌታ አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ላይ እንደጣለህ እነሆ በገዛ ዓይንህ አይተሃል፤ አንዳንዶች እንድገድልህ ገፋፍተውኝ ነበር፤ እኔ ግን፥ ‘ጌታ በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ በማለት ራራሁልህ። አባቴ ሆይ፤ የልብስህ ቁራጭ ይኸው በእጄ ላይ ተመልከተው! የልብስህን ጫፍ ቆረጥሁ እንጂ አንተን አልገደልኩህም። አሁንም ክፋት ወይም ዐመፅ አለመፈጸሜን ዕወቅልኝ፤ ተረዳልኝም፤ እኔ ክፉ አልሠራሁብህም፤ አንተ ግን ሕይወቴን ለማጥፋት እያሳደድኸኝ ነው። ጌታ በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ ጌታ ይበቀልህ እንጂ እጄንስ በአንተ ላይ አላነሳም፤ ጥንት፥ ‘ክፋት ክፋትን ይወልዳል’ እንደተባለ፤ አሁንም እጄ በአንተ ላይ አትሆንም። የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? አንተስ የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተ ውሻን? ወይስ ቁንጫ? አሁንም ጌታ ዳኛ ሆኖ በመካከላችን ይፍረድ፤ ጉዳዬን ተመልክቶ እርሱው ይሟገትልኝ፤ እኔንም ከእጅህ ነጻ ያውጣኝ።” ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲያበቃ ሳኦል፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ የአንተ ድምፅ ነውን?” ሲል ጠየቀው፤ ሳኦል ጮኾም አለቀሰ። እንዲህም አለ፤ “ክፉ ሳደርግብህ፥ በጎ መልሰህልኛልና፥ አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። ያደረግህልኝን በጎ ነገር ይኸው ነግረኸኛል፤ ጌታ እኔን በእጅህ ቢጥልልህም አንተ ግን አልገደልኸኝም። ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጉዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ማን ነው? ዛሬ ስላደረግህልኝ ቸርነት ጌታ ይመልስልህ። እነሆ፤ አንተ በእርግጥ እንደምትነግሥና የእስራኤል መንግሥት በእጅህ እንደምትጸና ዐውቃለሁ። ዘሮቼን እንዳታጠፋ ስሜንም ከአባቴ ቤት እንዳትደመስስ አሁን በጌታ ማልልኝ።” ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ተመለሰ። ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ አምባው ወጡ። ሳሙኤልም ሞተ፤ መላው እስራኤል ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፤ ራማ ባለው ቤቱም ቀበሩት። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ። በማዖን ምድር በቀርሜሎስ ንብረት ያለው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ፤ እርሱም አንድ ሺህ ፍየሎችና በቀርሜሎስ የሚሸልታቸው ሦስት ሺህ በጎች ነበሩት። የሰውየው ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢጌል ነበረ። እርሷም አስተዋይና ውብ ነበረች፤ ባሏ ግን ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከካሌብ ወገን ነበር። ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። እንዲህም በሉት፤ ‘ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን። በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ፥ ያደረስንባቸው ጉዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። አመጣጣችን በግብዣ ቀን በመሆኑ እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ” የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፥ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር። ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደመጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?” የዳዊት ሰዎችም ወደመጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፥ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጌል እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረበዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው። እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጉዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር አብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፥ ምንም ነገር አልጠፋብንም። በጎቻችንን እየጠበቅን አብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፥ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን አጥር ሆነውን ነበር። አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለሆነ፥ ምን እንደምታደርጊ አስቢበት፤ እርሱ እንደሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለሆነ፥ ማንም ደፍሮ የሚነግረው የለም።” አቢጌልም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስት የተሰናዱ በጎች፥ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፥ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፥ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚያም አገልጋዮቹን፥ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም። እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። ነገ ጠዋት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፥ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!” አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፥ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁምነገር አይቁጠረው፤ ስሙ ራሱ ሞኝ ማለት ስለሆነ፥ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ሞኝነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጐልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ በሕያው ጌታ፥ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ ጌታ ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጐልማሶች ይሰጥ። ጌታዬ የጌታን ጦርነት ስለሚዋጋ ጌታም ለጌታዬ የታመነ ቤት በእርግጥ ለዘለዓለም የሚያጸናለት በመሆኑ፥ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፥ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በጌታ ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፥ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። ጌታም በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርብህም፤ ምክንያቱም በከንቱ ያፈሰስከው ደም ወይም በገዛ እጅህ የወሰድከው በቀል የለምና። ስለዚህ ጌታ ለጌታዬ በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜም፥ እኔንም አገልጋይህን አስበኝ።” ዳዊትም አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ የተመሰገነ ይሁን! ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጉዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው ጌታን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፥ እስኪ ነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፥ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት። አቢጌልም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፥ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪ ነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም። ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፥ ጌታ ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ። ዳዊትም ናባል መሞቱን በሰማ ጊዜ፥ “የናባልን ስድብ የተበቀለልኝና እኔን አገልጋዩን ክፉ ከማድረግ የጠበቀኝ ጌታ ይመስገን፤ ናባል የሠራውንም ክፉ ነገር በራሱ ላይ መለሰበት” አለ። ዳዊትም አቢጌል ሚስት ትሆነው ዘንድ በመጠየቅ መልእክት ላከባት። አገልጋዮቹም ወደ ቀርሜሎስ ሄደው አቢጌልን፥ “ሚስት ትሆኚው ዘንድ እንድንወስድሽ ዳዊት ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት። እርሷም ተነሥታ በግምባሯ በመደፋት እጅ ከነሣች በኋላ፥ “እነሆ፤ እኔ አገልጋይህ አንተን ለማገልገል፥ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች። አቢግያም ወዲያውኑ በአህያ ላይ ተቀምጣ አምስት አገልጋዮቿን በማስከተል፥ ከዳዊት መልእክተኞች ጋር ሄደች፤ ለዳዊትም ሚስት ሆነችው። እንዲሁም ዳዊት ኢይዝራኤላዊቷን አሒኖዓምን አግብቶ ነበር፥ ሁለቱም ሚስቶቹ ሆኑ። ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን፥ ለጋሊም ተወላጅ ለሌሳ ልጅ ለፓልጢ ሰጥቶ ነበር። የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው፦ “እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በሐኪላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጓል” አሉት። ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፤ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ወረደ። ሳኦልም በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በሐኪላ ኰረብታ ላይ በመንገድ ዳር ሰፈረ፤ ዳዊት ግን በምድረ በዳ ነበር። ዳዊትም ሳኦል እዚያ ድረስ እንደ ተከተለው ባወቀ ጊዜ፥ ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ። ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ፥ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሠራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ፥ ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ነበር። ዳዊትም ሒታዊውን አቢሜሌክንና የጸሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፥ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው። አቢሳም፥ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ። ስለዚህም በዚያው ምሽት ዳዊትና አቢሳን ወደ ሳኦል ሰፈር ገቡ፤ ሳኦልንም በሰፈሩ መካከል ተኝቶ አገኙት፤ ጦሩም በራስጌው በኩል መሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተዋል፤፥ አቢሳም ዳዊትን፥ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው። ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! ጌታ በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው? ሕያው ጌታ አለ፥ ጌታ ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም የመሞቻው ቀን ይመጣል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል፤ ይጠፋልም። ጌታ በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት ጌታ ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።” ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለ ወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና። ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር። ዳዊት ሠራዊቱንና የኔርን ልጅ አቤኔርን፥ “አቤኔር ሆይ፥ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ። አቤኔርም፥ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው አይደለህምን? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለ ምንድነው? ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፥ አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ ጌታ የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁም። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?” ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ በእርግጥ የአንተ ድምፅ ነውን?” አለው። ዳዊትም፥ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤ በመቀጠልም፥ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለ ምንድነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባርያውን ቃል ያድምጥ፤ ጌታ በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፥ መሥዋዕት ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፥ በጌታ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፥ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በጌታ ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና። አሁንስ ከጌታ ርቄ በባዕድ አገር እንድገደል አታድርግ፤ አሁንም በተራራው ላይ ቆቅን እንደሚሻ ሰው ይህን ያህል የእስራኤል ንጉሥ እኔን ስለምን ያሳድዳል?” ሳኦልም፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ! በእርግጥ ተሳስቻለሁ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለከበረች ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ ይሄው፥ የሞኝ ሥራ ሠራሁ፤ አብዝቼም ተሳሳትኩ” አለ። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ! እነሆ ጦርህ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት። ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬ አንተን ጌታ በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ ጌታ በቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም። እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፥ የእኔም ሕይወት በጌታ ዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።” ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ብዙ ነገር ታደርጋለህ፤ በእርግጥም ይከናወንልሃል” አለው። ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ። ዳዊት በልቡ፦ “ከእነዚህ ቀናት በአንዱ በሳኦል እጅ መገደሌ ስለማይቀር፥ የሚበጀኝ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር መሸሽ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላም ሳኦል በእስራኤል ሁሉ እኔን ማሳደዱን ይተዋል፤ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ” ብሎ አሰበ። ስለዚህ ዳዊትና አብረውት ያሉት ስድስት መቶ ሰዎች ተነሥተው የጋት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ማዖክ ልጅ ወደ አኪሽ ሄዱ። ዳዊትና ሰዎቹ በጋት በአኪሽ ዘንድ ተቀመጡ፤ እያንዳንዱ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ነበረ፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር፥ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአሒኖዓም እና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ አቢጌል ጋር ነበር። ሳኦልም፥ ዳዊት ወደ ጋት እንደ ሸሸ በሰማ ጊዜ፥ እርሱን ማሳደዱን ተወ። ከዚያም ዳዊት አኪሽን፥ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ እኖር ዘንድ ስፍራ ይሰጠኝ፤ ስለምን አገልጋይህ ካንተ ጋር በንጉሥ ከተማ ይቀመጣል?” አለው። ስለዚህ በዚያ ዕለት አኪሽ ጺቅላግን ከተማ ሰጠው፤ ጺቅላግም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ ሆነች። ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ምድር አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ። በዚያ ጊዜም ዳዊትና ሰዎቹ ወጥተው ጌሪሹራውያንን፥ ጌዛውያንንና አማሌቃውያንን ወረሩ። እነዚህ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ፥ እስከ ሱርና እስከ ግብጽ ባለው ምድር ላይ ይኖሩ ነበር። ዳዊትም ምድሪቱን በመታበት ጊዜ፥ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አላስቀረም፤ በጎችንና ላሞችን፥ አህዮችንና ግመሎችን እንዲሁም ልብሶችን ወሰደ፤ ወደ አኪሽም ይዞ ተመለሰ። አኪሽም፥ “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ሲል በጠየቀው ጊዜ ዳዊት፥ “የዘመትነው በይሁዳ፥ ወይም በይራሕመኤላውያን፥ ወይም በቄናውያን ላይ ነው” እያለ ይመልስለት ነበር። ዳዊት “ ‘እርሱ እንዲህ አድርጓል’ ብለው ይነግሩብናል” ብሎ ስላሰበ፥ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስቀርቶ ወደ ጋት አላመጣም። በፍልስጥኤም ግዛት በኖረበት ዘመን ሁሉ እንዲህ ማድረጉ የተለመደ ነበር። አኪሽም በልቡ፥ “እርሱ ራሱ የገዛ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እጅግ እንዲጠሉት ስላደረገ፥ ለዘለዓለም አገልጋዬ ይሆናል” ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው። በዚያን ዘመን ፍልስጥኤማውያን፥ እስራኤልን ለመውጋት ሠራዊታቸውን ሰበሰቡ። አኪሽም ዳዊትን፥ “አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ለጦርነት መውጣት እንዳለባችሁ ትረዳኛለህ” አለው። ዳዊትም፥ “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ ያንጊዜ አንተው ራስህ ታያለህ” አለው። አኪሽም፥ “መልካም፤ በዘመኔ ሁሉ የራሴ የክብር ዘብ አደርግሃለሁ” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ በገዛ ከተማው በራማ አልቅሰው ቀበሩት። ሳኦልም ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ አባሯቸው ነበር። ፍልስጥኤማውያን ተሰብስበው በመምጣት በሹኔም ሲሰፍሩ፥ ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሰፈረ። ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ። እርሱም ጌታን ጠየቀ፤ ጌታ ግን በሕልምም ሆነ በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። ሳኦልም አገልጋዮቹን፥ “እስቲ ሙታን ጠሪ ሴት ፈልጉልኝና ሄጄ ልጠይቃት” አላቸው። እነርሱም፥ “እነሆ፤ ሙታን የምትጠራ ሴት በዔንዶር አለች” አሉት። ስለዚህ ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ መልኩን ለውጦ ከሁለት ሰዎች ጋር በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄደ። እርሱም፥ “እባክሽ፥ መናፍስትን ጠይቂልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት። ሴትዮዋ ግን፥ “እነሆ፤ ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ እንዴት እንዳጠፋና ያደረገባቸውን ታውቃለህ፤ ታዲያ፥ ታስገድለኝ ዘንድ በሕይወቴ ላይ ወጥመድ የዘረጋኸው ለምንድን ነው?” አለችው። ከዚያም ሳኦል “በዚህ ነገር ምንም ዓይነት ቅጣት እንደማይደርስብሽ በሕያው ጌታ ስም ምዬ ቃል እገባልሻለሁ” ሲል በጌታ ስም ማለላት። ሴትዮዋም፥ “ማንን ላስነሣልህ?” ብላ ጠየቀችው። እርሱም፥ “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት። ሴትዮዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታልቅ ድምፅ ጮኽች፤ ሳኦልንም፥ “አንተ ሳኦል ሆነህ ሳለ፥ ለምን አታለልኸኝ?” አለችው። ንጉሡም፥ “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት። ሴትዮዋም፥ “አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ” አለችው። እርሱም፥ “መልኩ ምን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት። እርሷም፥ “ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየወጣ ነው” አለችው። ሳኦልም ሴትዮዋ ያየችው ሳሙኤል መሆኑን ዐወቀ፤ በመሬትም ላይ ተደፍቶ እጅ ነሣ። ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድነው?” አለው፤ ሳኦልም፥ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው። ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ታዲያ ጌታ ከራቀህ፥ ጠላትም ከሆነህ ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ጌታ በእኔ የተናገረውን አድርጓል፤ ጌታ መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። ምክንያቱም አንተ ለጌታ ቃል ታዛዥ ሆነህ አልተገኘህም፤ዐማሌቃውያንና የእነርሱ የሆነውንም ሁሉ አልደመሰስክም፤ ስለዚህ ጌታ አሁን ይህን ሁሉ አደረገብህ። ገና ጌታ አንተንና እስራኤልን ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል፤ አንተና ልጆችህም ነገ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።” ሳሙኤል ከተናገረው ቃል የተነሣ፥ ሳኦል በፍርሀት ተውጦ ወዲያውኑ በቁመቱ ሙሉ መሬት ላይ ወደቀ፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ እህል ስላልቀመሰ ጉልበቱ ዝሎ ነበር። ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጥታ ሲንቀጠቀጥ ስላየችው እንዲህ አለችው፦ “እኔ አገልጋይህ የአንተን ቃል ሰምቼ ሕይወቴን እስከ ማሳለፍ ደርሼ አለሁ፤ ያልከኝንም ነገር አዳመጥኩ፤ አሁንም እባክህ አገልጋይህ የምትልህን ስማ፤ ብርታት አግኝተህ መሄድ እንድትችል፥ ጥቂት ምግብ ላቅርብልህና ብላ።” እርሱም፥ “አልበላም” በማለት እምቢ አለ። ነገር ግን የራሱ ሰዎች ከሴትዮዋ ጋር ሆነው አጥበቀው ስለ ለመኑት ቃላቸውን ሰማ። ከመሬትም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ። ሴትዮዋም በቤቷ የሠባ ጥጃ ስለነበራት፥ ፈጥና ዐረደችው፤ ዱቄት ወስዳ ለወሰች፥ እርሾ የሌለው እንጀራም ጋገረች። ከዚያም ለሳኦልና ለሰዎቹ አቀረበችላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ በዚያም ሌሊት ተነሥተው ሄዱ። ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ሁሉ በአፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ሸለቆ ባለው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች በመቶና በሺህ ሆነው ሲዘምቱ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ከአኪሽ ጋር ደጀን ሆነው ይከተሉ ነበር። የፍልስጥኤም ጦር አዛዦችም እነርሱን ባዩ ጊዜ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ይሠራሉ?” ሲሉ ጠየቁ፤ አኪሽም፥ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የነበረው ዳዊት አይደለምን? ከእኔ ጋር መኖር ከጀመረ እነሆ ዓመት አለፈው፤ እኔን ከተጠጋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አላቸው። የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን በአኪሽ ላይ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህን ሰው እንዲመለስ አድርግ፤ ወደ ሰጠኸው ቦታ ይመለስ ዘንድ ስደደው፤ በውጊያው ላይ ተመልሶ ጠላት እንዳይሆን ከእኛ ጋር አይወርድም። እዚህ ያሉትን የእኛን ሰዎች ራስ ቆርጦ ካልወሰደ በስተቀር፥ ከጌታው ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል? በዘፈን እየተቀባበሉ፥ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ’ ብለው የዘመሩለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?” ስለዚህም አኪሽ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “አንተ ለእኔ ታማኝ ስለ መሆንህ በሕያው ጌታ እምላለሁ፤ ወደዚህም ጦርነት ዘምተህ ብትዋጋ ደስ ባለኝ ነበር፤ ወደ እኔ ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ እኔን ማሳዘን የሚችል በደል ሠርተህ አላገኘሁህም፤ ግን ሌሎቹ ገዢዎች የአንተን አብሮ መዝመት አልፈቀዱም። እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዢዎች ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ” ዳዊትም ለአኪሽ፥ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፥ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፥ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ስለ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። አኪሽም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፥ ‘አብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል። አሁንም አብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማለዳ ተነሡ፤ በጥዋት ፀሐይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው። ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ለመመለስ በማለዳ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ። በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ጺቅላግ ደረሱ፤ በዚህ ጊዜ አማሌቃውያን ደቡቡን አገርና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ ጺቅላግንም ወግተው አቃጥለው ነበር። ሴቶቹን፥ በዚያ የነበሩትን ወጣቶችና ሽማግሌዎቹን ሁሉ ማርከው ወሰዱ፤ የማረኩትንም ይዘው ከመሄድ በስተቀር አንዱንም አልገደሉም ነበር። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ እንደ ደረሱም፥ እነሆ፤ ከተማዪቱ በእሳት ጋይታ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው አገኙ። በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ማልቀስ እስከሚያቅታቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ተማርከው ነበር። ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተማርራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በጌታ በረታ። ከዚያም ዳዊት የአቤሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፥ “ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው፤ አብያታርም አመጣለት፤ ዳዊትም፥ “ይህን ወራሪ ሠራዊት ልከተለውን? እደርስባቸዋለሁን?” ሲል ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “በእርግጥ ትደርስባቸዋለህ፤ ምርኮውንም ትመልሳለህ፤ ተከተላቸው!” ሲል መለሰለት። ስለዚህ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ብሦር ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ ሲደርሱ፤ ጥቂቶቹ በብሦር ወንዝ ቆዩ። ሁለት መቶዎቹ እጅግ ዝለው ስለ ነበር ወንዙን መሻገር አልቻሉም። ነገር ግን ዳዊትና አራት መቶ ሰዎች መከታተላቸውን ቀጠሉ። እነርሱም በምድረ በዳ አንድ ግብፃዊ አገኙ፤ ወደ ዳዊትም አመጡት። የሚጠጣውን ውሃና የሚበላውን ምግብ ሰጡት። እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቁራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፥ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች። ዳዊትም፥ “አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔ ግብፃዊ ስሆን፥ የአንድ አማሌቃዊ አገልጋይ ነኝ፤ ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ በነበረበት ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። የከሪታውያንን ደቡብ፥ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።” ዳዊትም፥ “ታዲያ ወራሪው ሠራዊት ወዳለበት መርተህ ትወስደኛለህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው። ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፥ እነሆ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፥ ይጠጡና ይዘፍኑ፥ ይጨፍሩም ነበር። ዳዊት፥ ከዚያች እለት ምሽት ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፥ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም። ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ። ትንሽም ሆነ ትልቅ፥ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፥ ምርኮም ሆነ ሌላ፥ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም። ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ። እንዲሁም ዳዊት የበጉን፥ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር። ከዚያም ዳዊት እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በብሦር ወንዝ ቀርተው ወደነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው። ከዳዊት ተከታዮች ክፉዎቹና ምግባረ ቢሶቹ ግን፥ “አብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውም፤ እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ብቻ ይዞ መሄድ ይችላል” አሉ። ዳዊትም እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼ ሆይ፤ የጠበቀን፥ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን ጌታ ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር አስተውሉ፤ ይህን ማድረግ አይገባችሁም። የምትሉትን ማን ይቀበላችኋል? ከጓዝ ጋር የቀረው ሰው ድርሻ ለጦርነት ከወጣው ሰው ድርሻ ጋር አይበላለጥም፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉ።” ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል እንደ ሕግና ሥርዓት አደረገው። ዳዊት ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ፥ ወዳጆቹ ለሆኑት ለይሁዳ ሽማግሌዎች፥ “ከጌታ ጠላቶች የተማረከ ስጦታ እነሆ ይሄው፤” በማለት ከምርኮው ላይ ከፍሎ ላከላቸው። ይህንም፥ በቤትኤል፥ በደቡብ ራሞትና በያቲር ለነበሩ ላከላቸው። በአሮዔር፥ በሲፍሞት፥ በኤሽተሞዓና፥ በራካል ለሚገኙ፥ እንዲሁም ለይራሕመኤል ከተሞች፥ ለቄናውያን ከተሞችም፥ በሖርማ፥ በቦርዓሻን፥ በዐታክና፥ በኬብሮን ለነበሩ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሁሉ ላከላቸው። በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት፥ በጊልቦዓ ተራራ ላይ የወደቁትን ጥለው ሸሹ። ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው ተከታተሉ፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፥ አቢናዳብንና ማልኪሹዓን ገደሉ። ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም አገኙት፥ በቀስታቸውም ወግተው ክፉኛ አቆሰሉት። ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፥ “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝ፥ እንዳያዋርዱኝም፥ አንተው ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፥ እምቢ አለው። ስለዚህ ሳኦል የራሱን ሰይፍ ወስዶ በላዩ ላይ ወደቀበት። ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ባየ ጊዜ፥ እርሱም እንደዚሁ በሰይፉ ላይ ወድቆ አብሮት ሞተ። ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ፥ አብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በዚያኑ ቀን ነበር። በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን የእስራኤል ሠራዊት መሸሹን፥ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ሰዎች ለመግፈፍ ሲመጡ፥ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገቿቸው። ከዚያም የሳኦልን ራስ ቆርጠው፥ የጦር መሣሪያውንም ገፈው፥ የምሥራቹን በየቤተ ጣዖቶቻቸውና በሕዝባቸው መካከል እንዲናገሩ ወደ ፍልስጥኤም ምድር ሁሉ መልክተኞች ላኩ። የጦር መሣሪያውን በአስታሮት ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውን ደግሞ በቤት ሻን ግንብ ላይ አንጠለጠሉት። በገለዓድ የሚኖሩ የያቤሽ ሰዎችም ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉበትን ነገር በሰሙ ጊዜ፥ ጀግኖቻቸው ሁሉ በሌሊት ወደ ቤትሻን ሄዱ። የሳኦልንና የልጆቹንም ሬሳ ከግንቡ ላይ አውርደው ወደ ያቤሽ አምጥተው አቃጠሉ። ከዚያም ዐጥንቶቻቸውን ወስደው በኢያቢስ ባለው ታማሪስክ ተብሎ የሚጠራ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ። ሳኦል ከሞተ በኋላ፥ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ ሲመለስ፥ ሁለት ቀን በጺቅላግ ቆየ። በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ የተቀደደ ልብስ የለበሰ፥ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት መጥቶም በግምባሩ በመደፋት እጅ ነሣ። ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ መጣሁ” በማለት መለሰለት። ዳዊትም፥ “እስቲ ምን ነገር እንደተፈጠረ ንገረኝ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋልም፤ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ። ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው። ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ሳለ፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከትለው ደረሱበት፤ ወደ ኋላውም ዞር ሲል አየኝና ጠራኝ፤ እኔም፥ ‘እነሆ አለሁ!’ አልኩት። እርሱም፥ ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስኩለት። ከዚያም፥ ‘እኔ የሞት ጣር ይዞኛል፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ። እኔም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፥ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና በክንዱ ላይ የነበረውን አንባር ወስጄ፥ እነሆ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።” ከዚያም ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ። የወደቁት በሰይፍ ነበርና፥ ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለጌታ ሠራዊትና ለእስራኤል ቤትም አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፥ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ። ዳዊትም፥ “ታዲያ ጌታ የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው። ከዚህ በኋላ ዳዊት ከጉልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፥ “በል ቅረብና ግደለው!” አለው። እርሱም መታው፤ ገደለውም። ዳዊትም፥ “ ‘ጌታ የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፥ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው። ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ የይሁዳንም ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ እነሆ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል! ኀያላኑ እንዴት ወደቁ! የፍልስጥኤም ቆነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፤ ያልተገረዙት ሴት ልጆች እልል እንዳይሉ፤ ይህን በጌት አትናገሩ፤ በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁ፤ እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤ በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፤ የሳኦል ጋሻ በዘይት መወልወሉ ቀርቶአልና፤ ጠልም ሆነ ዝናብ አይውረድባችሁ፤ የቁርባን እህል የሚያበቅሉም እርሻዎች አይኑራችሁ። ከሞቱት ሰዎች ደም፥ ከኀያላኑም ሥብ፥ የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም። ሳኦልና ዮናታን፥ የተዋደዱና የተስማሙ፤ በሕይወትም ሆነ በሞት ያልተለያዩ፤ ከንስርም ይልቅ የፈጠኑ፥ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። እናንት የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ! ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፥ ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፥ ለሳኦል አልቅሱ። ኀያላን እንዴት በጦርነት ወደቁ! ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤ ከሴት ፍቅርም ይልቅ የበረታ ነበር። ኀያላን እንዴት ወደቁ! የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ጠፉ!” ከዚህ በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ወጣ፤ ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ከእርሱ ጋር ነበሩ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፥ እርሱም ወደ ያቤሽ ገለዓድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት በማሳየታችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ አሁንም ጌታ ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ! እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፥ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።” በዚህ ጊዜ የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፥ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ ማሕናይም አሻገረው፤ እርሱንም በገለዓድ ላይ፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። ዳዊት በኬብሮን ነግሶ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔር፥ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኲሬ አጠገብ ተገናቿቸው፤ አንዱ ወገን በኲሬው ወዲህ ማዶ፥ ሌላው ወገን ደግሞ በኲሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። ከዚያም አበኔር፥ ኢዮአብን፥ “ጉልማሶች ይነሡና በፊታችን ትግል ይግጠሙ” አለው። ኢዮአብም፥ “ይሁን እሺ ይግጠሙ” ብሎ መለሰ። ስለዚህም ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፥ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት አገልጋዮቹ ተነሥተው ተቆጠሩ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በጐኑ ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የስለታም ሰይፍ ምድር” ተባለ። የዚያን ዕለት ፍልሚያ እጅግ መራር ነበር፤ በዳዊትም አገልጋዮች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብ፥ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ አቤኔርን ለመያዝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል ተከተለው። አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፥ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል፥ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም አበኔር፥ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ ምርኮውን ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ። እንደገናም አበኔር፥ “እኔን ማሳደድህን ተው! እኔስ ስለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። አሣሄል ግን ማሳደዱን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በጀርባው በኩል ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወድቆም በነበረበት ስፍራ ሞተ። እያንዳንዱም ሰው አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ ፀሐይ ስትጠልቅ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጊያሕ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደርሱ። ከዚያም የብንያም ሰዎች ተሰብስበው ከአበኔር ጀርባ በመሆን ግንባር ፈጠሩ፤ በኰረብታውም ጫፍ ላይ ተሰለፉ። አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፥ “ሰይፍ በውኑ እስከ ዘለዓለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደሆነ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ነው?” አለው። ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፥ ሰዎቹ እስኪ ነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተዉ ውጊያውንም አቆሙ። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓራባን አልፈው ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ ማሕናይም መጡ። ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፥ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፥ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። የዳዊት አገልጋዮች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያን ገደሉ። አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተልሔም በሚገኘው በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው፥ ኬብሮን ንጋት ሆነ። በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቆየ፤ ሆኖም ዳዊት እያየለ ሲሄድ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ ነበር። ዳዊት በኬብሮን እያለ፥ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ የበኲር ልጁ፥ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥ ሁለተኛው፥ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው፥ ተልማይ ከተባለው ከገሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፥ አራተኛው፥ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፥ ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥ ስድስተኛው፥ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረዓም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን እያለ የተወለዱለት ናቸው። የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፥ አበኔር በሳኦል ቤት ሆኖ ኀይሉን ያጠናክር ነበር። ሳኦልም ሪጽፋን የምትባለውን የአያን ልጅ በዕቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፥ “ለምንድን ነው ከአባቴ ዕቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው። ይህ የአበኔር ንግግር እጅግ ያስቆጣው ኢያቡስቴ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፥ ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ፥ ታማኝነቴን ሳላጎድል ይሄው አለሁ፤ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፥ ዛሬ ግን አንተ በዚህች ሴት ትከሰኛለህን? በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝ? ጌታ ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ ከፍጻሜ ሳላደርስ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ይፍረድ፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ ተስፋ ተሰጥቶታልና።” ኢያቡስቴም አበኔርን ስለ ፈራ ሌላ ቃል ሊመልስለት አልደፈረም። ከዚያም አበኔር ለዳዊት እንዲህ ሲሉ ለዳዊት እንዲነግሩት መልክተኞች ላከ፥ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ።” ዳዊትም፥ “ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፥ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም” አለ። ከዚያም ዳዊት፥ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት። ኢያቡስቴም መልክተኛ ልኮ፥ ሜልኮልን ከባሏ ከላይሽ ልጅ ከፓልጢኤል ወሰዳት። ባሏም እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፥ “ሂድ፥ ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ። አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ተመካከረ፥ “ቀደም ሲል ዳዊት ንጉሣችሁ እንዲሆን ፈልጋችሁ ነበር፤ ስለዚህ ጌታ ለዳዊት፥ ‘በአገልጋዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፥ ይህን አሁን አድርጉ።” እንዲሁም አበኔር ሄዶ ይህንኑ ለብንያማውያን ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ፤ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። ከዚያም አበኔር ዳዊትን፥ “ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ልሂድ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ። በዚያን ጊዜም የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮአብ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለ ሄደ፥ በኬብሮን አልነበረም። ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፥ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጣ፥ አሰናበተውም እርሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮአብ ነገሩት። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምንድነው ያደረግከው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ፥ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትኸው ለምንድነው? የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፥ መውጫና መግቢያህን ሊያውቅብህና፥ የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልልህ ነው።” ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ፊት እንደ ወጣ፤ ወደ አበኔር መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሲራ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር። አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፥ ኢዮአብ ለብቻው የሚያነጋግረው በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው። ዳዊት ይህን ነገር ቆይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በጌታ ፊት ለዘለዓለም ንጹሕ ነን፤ ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ከኢዮአብ ቤት ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት፥ በምርኲዝ የሚሄድ አንካሳ፥ ወይም በሰይፍ ተመቶ የሚሞት ወይም የሚበላው ያጣ ራብተኛ አይታጣ።” አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፥ እነርሱም አበኔርን ገደሉት። ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፥ “ልብሳችሁን ቀዳችሁና ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ጮኾ በአበኔር መቃብር ላይ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ “አበኔር እንደ ተራ ሰው ይሙት? እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅ አንተም እንደዚሁ ወደቅህ።” ሕዝቡም ሁሉ እንደገና አለቀሱለት። ከዚያም ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፥ “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ያድርግብኝ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ። ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው። በዚያን ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልነበረበት ዐወቁ። ከዚያም ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፥ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። ጌታ ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።” የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ አበኔር በኬብሮን መሞቱን በሰማ ጊዜ ወኔ ከዳው፤ መላው እስራኤልም ተሸበረ። በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ የወራሪ ጭፍራ ቡድን መሪዎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ አንዱ በዓና ሌላው ደግሞ ሬካብ ይባሉ ነበር። እነርሱም የበኤሮት ተወላጅ የሆነው የሬሞን ልጆች የነበሩ ሲሆን፥ በኤሮትም ከብንያም ክፍል እንደ አንዱ ተቆጥራ ነበር። የበኤሮት ሕዝብ ወደ ጊታይም በመሸሽ እስከ ዛሬም በመጻተኝነት እዚያው ይኖራሉ። የሳኦል ልጅ ዮናታን ሁለት እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው። እርሱም የሳኦልና የዮናታን አሟሟት ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ። ሽባ የሆነውንም በዚህ ጊዜ ሞግዚቱ አንሥታው በጥድፊያ ስትሸሽ በመውደቁ ነው። ስሙም መፊቦሼት ይባል ነበር። በዚህ ጊዜ የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ሬካብና በዓና ወደ ኢያቡስቴ ቤት ለመሄድ ተነሡ፤ እርሱም የቀትር ጊዜ ዕረፍት ለማድረግ አልጋው ላይ ተኝቶ እያለ፥ እኩለ ቀን ላይ ደረሱ፤ እነሆም ስንዴ እንደሚፈልግም ሰው ሆነው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ሆዱ ላይ ወጉት። ከዚያም ሬካብና ወንድሙ በዓና አመለጡ። ወደ ቤቱ ውስጥ የገቡት ኢያቡስቴ በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ነበር፤ ወግተው ከገደሉትም በኋላ ራሱን ቆርጠው በመውሰድ፥ ሌሊቱን ሁሉ በዓራባ መንገድ ተጓዙ። የኢያቡስቴንም ራስ ወደ ኬብሮን ዳዊት ዘንድ አምጥተው ንጉሡን፥ “አንተን ሊገድል ይፈልግ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ፤ እነሆ ጌታ በዛሬው ቀን ስለ ጌታዬ ስለ ንጉሡ ሳኦልንና ዘሩን ተበቅሎአል” አሉት። ዳዊትም ለበኤሮታዊው ለሬሞን ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ከመከራ ሁሉ ባዳነኝ በጌታ ስም እምላለሁ፥ የምሥራች ያመጣልኝ መስሎት፥ ‘ሳኦል ሞተ’ ብሎ የነገረኝን ሰው ይዤ ጺቅላግ ላይ ገደልሁት፤ ለዚያ ሰው ስላመጣው ምሥራች የሸለምሁት ይህን ነበር። ታዲያ በገዛ ቤቱ፥ በገዛ አልጋው ላይ ዐርፎ የተኛውን ንጹሕ ሰው የገደሉትን ክፉ ሰዎች እንዴት የባሰ ቅጣት አይገባቸውም? ደሙን ከእጃችሁ መፈለግ፥ እናንተን ከምድሪቱ ማጥፋት የለብኝምን?” ስለዚህም ዳዊት የራሱን ሰዎች አዘዘ፤ እነርሱንም ገደሏቸው፤ እጅና እግራቸውንም ቆርጠው በኬብሮን ካለው ኲሬ አጠገብ ሰቀሏቸው። ነገር ግን የኢያቡስቴን ራስ ወስደው ኬብሮን በሚገኘው በአበኔር መቃብር አጠገብ ቀበሩት። የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፥ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤ እንደ ትላንትና እንዳለፉት ሦስት ቀናት ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረ ጊዜ፥ እስራኤልን በጦርነት የምትመራቸው አንተ ነበርህ፤ ጌታም፥ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይ በጌታ ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም በእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን ቀቡት። ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ። በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፥ በኢየሩሳሌም፥ በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ዘመቱ። እነርሱም፥ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፥ “ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ስለሚከላከሉህ ወደዚህች አትገባም” አሉት። ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ጠንካራ ምሽግ ያዘ፤ እርሷም አሁን የዳዊት ከተማ ናት። በዚያም ዕለት ዳዊት፥ “ኢያቡሳውያንን መግደል የሚፈልግ፥ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፥ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ይውጣ” አለ። ለዚህም ነበር፥ “አንካሶችና ዕውሮች ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” የተባለው። ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በምሽጉ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራው። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባው። የሠራዊት አምላክ፥ ጌታ፥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፥ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልዕክተኞችን፥ የዝግባ ዕንጨት፥ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችንም ላከ፥ ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። ጌታ በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፥ ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ። ዳዊት ከኬብሮን ከመጣ በኋላ፥ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ዕቁባቶችን አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሻሙዓ፥ ሾባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ይብሐር፥ ኤሊሹዓ፥ ኔፌግ፥ ያፊዓ፥ ኤሊሻማዕ፥ ኤልያዳዕና ኤሊፌሌጥ ነበሩ። ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፥ ፍልስጤማውያን ሁሉ ዳዊትን ለመፈለግ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ። ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት ጌታን፥ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸው? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?” ሲል ጠየቀ። ጌታም፥ “ሂድ፤ በእርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ስለዚህም ዳዊት ወደ ባዓል ፈራጺም ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፥ ጌታም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። በዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም ባዓል ፈራጺም ተባለ። ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሹ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው። ፍልስጥኤማውያን እንደገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም እንዲህ አለው፤ “በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤ በሾላው ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማም፥ ጌታ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቶአል ማለት ነውና በዚያን ጊዜ ፍጠን።” ስለዚህም ዳዊት ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖን እስከ ጌዜር ድረስ መታቸው። ዳዊት እንደገና ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው በዓል ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፥ በኰረብታ ላይ ካሚገኘው ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአቢናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፥ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፥ በበገና፥ በመሰንቆ፥ በከበሮ፥ በጽናጽልና በቃጭል ድምፅ በጌታ ፊት ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ናኮን አውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለተደናቀፉ፥ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፥ የጌታ ቁጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ። የጌታ ቁጣ ዖዛን ስለሰበረው ዳዊት አዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፌሬጽ ዑዛ ተብሎ ይጠራል። ዳዊት በዚያን ቀን ጌታን ስለ ፈራ “የጌታ ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ። ስለዚህ ዳዊት የጌታን ታቦት አብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ ዖቤድ ኤዶም ቤት ወሰደው። የጌታም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በዖቤድ ኤዶም ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ጌታም ዖቤድ ኤዶምና ቤተሰቡን ሁሉ ባረከ። በዚህ ጊዜ፥ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የዖቤድ ኤዶም ቤተሰቡና ያለውን ሁሉ ጌታ ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፥ የእግዚአብሔርን ታቦት ከዖቤድኤዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው። እነዚያ የጌታን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት ርምጃ በሄዱ ቍጥር፥ በሬና የሰባ ፍሪዳ ይሠዋ ነበር። ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኀይሉ በጌታ ፊት ይጨፍር ነበር። እንዲህ ባለ ሁኔታም ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት እየጨፈሩና ቀንደ መለከቱን እየነፉ የጌታን ታቦት አመጡ። የጌታ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ፥ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት በጌታ ፊት ሲዘልና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው። ከዚያም የጌታን ታቦት አምጥተው፥ ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ በተዘጋጀለት ስፍራ አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠል መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት በጌታ ፊት አቀረበ። ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ ስም ባረከ። የእስራኤል ወገን ለሆነው ለሕዝቡ ሁሉ፥ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድ ቁራጭ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተሰቡን ለመመረቅ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ግን ልትቀበለው ወጣችና፥ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቁቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” አለችው። ዳዊትም ሜልኮልን እንዲህ አላት፤ “አዎን ያሸበሸብኩት በጌታ ፊት ነው፤ በአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ አስበልጦ በጌታ ሕዝብ በእስራኤል ላይ ገዥ አድርጎ በመረጠኝ በጌታ ፊት አሁንም እጨፍራለሁ። እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፤ ከዚህም የባሰ በፊትሽ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ።” የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እሰከሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር። ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ከተቀመጠና ጌታም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፥ ነቢዩን ናታንን፥ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። ናታንም፥ “ጌታ ካንተ ጋር ስለሆነ፥ በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያች ሌሊት ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤ “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን፥ ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን?’ እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም ከእስራኤላውያን ሕዝብ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፥ ‘ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?’ ያልሁት አለን? አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አስወገድሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁነውም፤ ከዚህ በፊት እንደ ሆነው፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። ከዚህም በላይ ጌታ ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤ ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ፥ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ። አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል በሚፈጽምበትም ጊዜ ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ። ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል ምሕረቴን እንዳራቅሁ ከእርሱ ግን አላርቅም። ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘለዓለም የጸና ይሆናል።’ ” ናታንም ይህንን ቃል በሙሉ፥ ይህንንም ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በጌታ ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድንነው? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የአገልጋይህ ቤት ተናገርህ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው? ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አገልጋይህን አንተ ታውቀዋለህና! ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ አገልጋይህንም እንዲያውቀው አደረግህ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ታላቅ ነህ! የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደሰማነው ሁሉ፥ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፥ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፥ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክቶቻቸውን ከፊቱ አሳዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብጽም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? ሕዝብህን እስራኤልን ለዘለዓለም ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ ጌታ ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል። አሁንም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአገልጋይህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘለዓለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ ስለዚህ ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሆናል፤ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይባላል። የአገልጋይህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለአገልጋይህ ገልጸህለታል። ስለዚህ አገልጋይህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት አግኝቶአል። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንንም መልካም የተስፋ ቃል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል። በፊትህ ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር፥ አሁንም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የአገልጋይህ ቤት ለዘለዓለም ይባረክ።” ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው፤ በቁጥጥሩም ሥር አደረጋቸው፥ ሜተግ አማ የተባለችውንም ከተማ ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ። እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፥ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር። ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት ተገዢዎች ሆኑ፤ ገበሩለትም። ዳዊት በተጨማሪ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ፥ የጾባን ንጉሥ የረሖብን ልጅ ሀዳድዔዜርን ወጋው። ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገሎች፥ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ሃያ ሺህ እግረኞች ማረከበት። ቁጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቆረጠ። የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የጾባን ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለባቸው። ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው የሶርያውያን ግዛት የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። ሶርያውያን ተገዙለት፤ ገበሩለትም። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው። ዳዊት የሀዳድዔዜር ሹማምንት ያነገቧቸውን የወርቅ ጋሻዎች ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው። ንጉሡ ዳዊት ቤጣህና ቤሮታይ ከተባሉ ከሀዳድዔዜር ከተሞችም እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ። የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት መላውን የሀዳድዔዜርን ሠራዊት ማሸነፉን በሰማ ጊዜ፥ ቶዒ ከሀዳድዔዜር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ስለ ነበር፥ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ለሰላምታና በሀዳድዔዜር ላይ ሰለተቀዳጀውም ድል ደስታውን እንዲያቀርብለት ላከው፤ ልጁም የብር፥ የወርቅና የናስ ዕቃ ይዞ መጣ። ንጉሥ ዳዊትም ቀድሞ ካስገበራቸው መንግሥታት ሁሉ በገባለት ብርና ወርቅ እንዳደረገው እነዚህንም ለጌታ ቀደሳቸው። የገበሩትም መንግሥታት ኤዶምና ሞዓብ፥ አሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያንና አማሌቃውያን ነበሩ። እንዲሁም ከጾባ ንጉሥ ከረሖብ ልጅ ከሀዳድዔዜር የወሰደውን ምርኮ ለጌታ ቀደሰ። ዳዊት የጨው ሸለቆ በተባለው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ። በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያን ሁሉ ለዳዊት ተገዙ፤ ጌታም ዳዊት በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው። ስለዚህ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ትክክለኛ ፍርድ አሰፈነላቸው። የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሠራዊቱ አለቃ ሲሆን፥ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥም ታሪክ ጸሓፊ ነበረ። እንዲሁም የአሒጦብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አሂሜሌክ ካህናት ሲሆኑ፥ ሠራያ ጸሓፊ ነበረ፤ የዮዳሔ ልጅ በናያ የከሪታውያንና የፈሊታውያን አለቃ ሲሆን፥ የዳዊት ወንዶች ልጆች ደግሞ አማካሪዎች ነበሩ። ዳዊትም፥ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ። በዚያን ጊዜ ከሳኦል ቤት ጺባ የሚባል አንድ አገልጋይ ስለ ነበር ወደ ዳዊት ጠሩት። ንጉሡም፥ “ጺባ የምትባለው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “አዎን እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ። ንጉሡም፥ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው። ጺባም ለንጉሡ፥ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፥ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ። ጺባም፥ “ሎደባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፥ መፊቦሼትን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው። የሳኦል ልጅ፥ የዮናታን ልጅ መፊቦሼት ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ። ዳዊትም፥ “መፊቦሼት!” ብሎ ጠራው። እርሱም፥ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ። ዳዊትም፥ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግልሃለሁ። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው። መፊቦሼት ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፥ “እንደ ሞተ ውሻ ለምቆጠር ለእኔ ይህን ያህል የምታደርግልኝ አገልጋይህ ኧረ ማን ነኝ?” አለ። ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ጺባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቸዋለሁ። አንተ፥ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን እረሱለት፥ ምርቱንም አግቡለት። የጌታህ የልጅ ልጅ መፊቦሼት ግን ምንጊዜም ከማእዴ ይበላል።” በዚያን ጊዜ ጺባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት። ከዚያም ጺባ ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ፥ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፥ አገልጋይህ ይፈጽመዋል” አለው። ስለዚህም መፊቦሼት እንደ አንዱ ሆኖ ከዳዊት ማእድ ይበላ ነበር። መፊቦሼት ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የጺባ ቤተሰቦች በሙሉ መፊቦሼትን ያገለግሉት ነበር። መፊቦሼትም ሁልጊዜ ከንጉሥ ማእድ ስለሚበላ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ። ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሐኑንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። ዳዊትም፥ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ፥ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኑን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ስለዚህ ስለ አባቱ ሞት የተሰማውን ኀዘን እንዲገልጹለት ዳዊት መልክተኞችን ላከ። የዳዊት ሰዎች ወደ አሞናውያን ምድር በደረሱ ጊዜ፥ የአሞናውያን መኳንንት፥ ጌታቸው ሐኑንን፥ “ዳዊት የተሰማውን ኀዘን ለመግለጽ ሰዎች መላኩ አባትህን ለማክበር አስቦ ይመስልሃል? የላካቸው ሰዎች ከተማዪቱን እንዲመረምሩ፥ እንዲሰልሉና እንዲያጠፏት አይደለምን?” አሉት። ስለዚህ ሐኑን የዳዊትን አገልጋዮች ይዞ፥ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፥ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ሰደዳቸው። ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፥ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፥ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪ፥ ቆዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው። አሞናውያን፥ ዳዊት እንደጠላቸው ባወቁ ጊዜ፥ ከቤትረሖብና ከጾባ ሃያ ሺህ ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን እንዲሁም ንጉሥ መዓካን ከአንድ ሺህ ሰዎቹ ጋር ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ። ዳዊት ይህን ሲሰማ፥ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሠራዊት ጋር ላከው። አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ተሰለፉ፤ የጾባና የረሖብ ሶርያውያን እንዲሁም የጦብና የመዓካ ሰዎች ለብቻ ሜዳው ላይ ተሰለፉ። ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፥ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው። የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ግንባር አሰለፋቸው። ኢዮአብም እንዲህ አለ “ሶርያውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ ደግሞ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ። እንግዲህ በርታ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ ጌታም በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ።” ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ። ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፥ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፥ እንደገና ተሰባሰቡ። ሀዳድዔዜር መልክተኞችን ሰዶ ከወንዙ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጣ፤ እነርሱም በሀዳድዔዜር ሠራዊት አዛዥ በሾባክ መሪነት ወደ ሔላም ሄዱ። ለዳዊት ይህ በተነገረው ጊዜ፥ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ። ሶርያውያንም ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን በግንባር ገጠሙት፤ ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ ፈረሰኞችን ገደለባቸው። እንዲሁም የሠራዊታቸውን አዛዥ ሾባክን አቁስሎት ስለ ነበር እዚያው ሞተ። በሀዳድዔዜር ሥር የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ፤ ተገዙላቸውም። ከዚያም በኋላ ሶርያውያን ዳግመኛ ዐሞናውያንን ለመርዳት ፈሩ። ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት በጸደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን ከአገልጋዮቹና ከመላው እስራኤል ጋር አዘመተው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ራባ የተባለችውንም ከተማ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። አንድ ቀን ማታ፥ ዳዊት ከአልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፥ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ ውብ ነበረች። ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ። እርሱም፥ “ይህች የኤሊዓም ልጅ፥ የሒታዊው የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ። ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች። ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፥ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት። ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፥ “ሒታዊውን ኦርዮንን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ኦርዮንን ወደ ዳዊት ላከው። ኦርዮን በመጣ ጊዜም፥ ዳዊት የኢዮአብንና የሠራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። ከዚያም ዳዊት ኦርዮንን፥ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም የምግብ ስጦታ ላከለት። ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር። ዳዊት፥ “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮንን፥ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኦርዮም ዳዊትን፥ “ታቦቱ፥ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፥ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፥ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም” አለው። ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፥ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮ በዚያ ዕለትና በማግስቱ በኢየሩሳሌም ቆየ። በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮ በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አገልጋዮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት፤ በደብዳቤውም ላይ፥ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ። ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፥ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮንን መደበው። የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሠራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ሒታዊው ኦርዮንም ሞተ። ከዚያም ኢዮአብ በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፥ ንጉሡ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዲህ ይልህ ይሆናል፥ ‘ለመውጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለ ምንድነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል? የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤጽ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ አንተም መልሰህ፥ ‘አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞቷል’ ብለህ ንገረው።” ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደደረሰም ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው። ከዚያም ባለፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፥ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞተ።” ዳዊትም፥ መልእክተኛውን፥ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፥ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን’ ” አለው። የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ ኀዘን ተቀመጠች። የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፥ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ ጌታን አላስደሰተውም ነበር። ጌታ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ሀብታም ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ሀብታሙ እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። እየተንከባከበ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ሀብታሙም ቤት እንግዳ መጣ፤ ሀብታሙ ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ የድኻውን ግልገል ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ጌታ ምስክሬ ነው! ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ ግልገሊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፥ ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በእቅፍህ አኖርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤትም ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፥ የጌታን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ሒታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የሒታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና፥ ሰይፍ ለዘለዓለም ከቤትህ አይርቅም።’ ” ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።” ከዚያም ዳዊት ለናታን፥ “ጌታን በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፥ “ጌታ ኃጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፥ የጌታ ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፥ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፥ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን ጌታ ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያሰነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ምግብ አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፥ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፥ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፥ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፥ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ጌታ ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፥ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፥ ‘ጌታ ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፥ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፥ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ። ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። ጌታም ወደደው፤ ጌታ ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ። በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ራባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ራባን ወግቼ የውሃውንም ከተማ ይዤአለሁ፤ እንግዲህ የቀረውን ሠራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ ያለበለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።” ስለዚህ ዳዊት መላውን ሠራዊት አሰባስቦ ወደ ራባ በመሄድ ወግቶ ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት የሚመዝነው አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን፥ በከበረ ዕንቁም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፥ የብረት መቆፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ትዕማር የምትባል ቆንጆ እኅት ነበረችው፤ የዳዊት ልጅ አምኖንም ወደዳት። እኅቱን ትዕማርን ያፈቀረው አምኖን እስኪታመም ድረስ እጅግ ተሰቃየ፤ ድንግል ነበረችና አንዳች ነገር እንዳያደርግባት የማይታሰብ ሆኖበት አስጨነቀው። ነገር ግን አምኖን በጣም ዘዴኛ የሆነ፥ ዮናዳብ ተብሎ የሚጠራ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ነበር፤ እርሱም አምኖንን፥ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳው ለምንድነው? ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው። አምኖንም፥ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው። ዮናዳብም፥ “እንግዲያው የታመምህ መስለህ አልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፥ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ትስጠኝ፤ እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ምግብ አዘጋጅታ እርሷ ራስዋ እንድታጐርሰኝ እፈልጋለሁ’ በለው” አለው። ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፥ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፥ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው። ከዚያም ዳዊት፥ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” የሚል ትእዛዝ ለትዕማር ላከ። ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ ጋገረችው፤ ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም። አምኖንም፥ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ሰውም ሁሉ ትቶት ወጣ። ከዚያም አምኖን ትዕማርን፥ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች። ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፥ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት። እርሷም እንዲህ አለችው፤ “አይሆንም፥ ወንድሜ፥ ተው አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አስነዋሪ ድርጊት አትፈጽም። እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ ትቆጠራለህ፤ እባክህ ለንጉሡ ጠይቀው፤ እኔንም አይከለክልህም።” እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፥ በግድ አስገድዶ ደፈራት። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፥ አስቀድሞም ሲወዳት ከነበረው ፍቅሩ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥላቻ አየለ። አምኖንም፥ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት። እርሷም፥ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፥ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን ሊሰማት አልፈቀደም፤ ወጣት አገልጋዩንም ጠርቶ፥ “ይህቺን ሴት ከፊቴ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ በዚያን ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን እጅጌ ረዥም የነበረ መጐናጸፊያ ለብሳ ነበር። ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነስንሳ፤ ለብሳው የነበረውን መጐናጸፊያ ቀዳደደች፤ እጇንም በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች። ወንድሟ አቤሴሎምም፥ “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፥ በይ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለሆነ፥ ነገሩን በልብሽ አትያዠው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች። ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፤ አቤሴሎም ግን አምኖን እኅቱን ትዕማርን ስለደፈራት፥ ከጥላቻው የተነሣ አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አንዳች ቃል አልተናገረውም። ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በበዓለ ሐጾር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ከዚያም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት አቤሴሎም ጋበዛቸው። ወደ ንጉሡም ሄዶ፥ “እነሆ፤ አገልጋይህ በጎቹን ይሸልታል፤ ንጉሡና ሹማምንቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው። ንጉሡም አቤሴሎምን፥ “ልጄ ሆይ፥ ሸክም ስለምናበዛብህ ሁላችንም መሄድ የለብንም” ሲል መለሰለት። አቤሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ መሄድ አልፈለገም፤ ነገር ግን መርቆ አሰናበተው። ከዚያም አቤሴሎም፥ “እምቢ ካልህ እሽ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው። ንጉሡም፥ “አብሮህ የሚሄደው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፥ አምኖንና የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ አደረገ። ከዚያም አቤሴሎም አገልጋዮቹን፥ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ እኔ ‘አምኖንን፥ ምቱት’ በምላችሁ ጊዜ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔው ስለሆንኩ አትፍሩ፤ ብርቱዎች ሁኑ፥ ጨከን በሉም” ብሎ አዘዛቸው። የአቤሴሎምም አገልጋዮች በአምኖን ላይ አቤሴሎም ያዘዛቸውን ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ። እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፥ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። የዳዊት ወንድም የሻምዓ ልጅ ዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የተገደሉት የንጉሡ ልጆች በሙሉ እንደ ሆኑ አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ የሞተው አምኖን ብቻ ነው። አምኖን እኅቱን ትዕማርን በግድ ከደፈራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ይህን ጉዳይ ቆርጦ የተነሣበት ነበር። አሁንም የሞተው አምኖን ብቻ ስለሆነ፥ የንጉሡ ልጆች በሙሉ እንደተገደሉ አድርጎ ንጉሥ ጌታዬ በልቡ ማሰብ የለበትም።” አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ተመለከተ፤ እነሆም፥ በኋላው ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ሲመጡ አየ። ዮናዳብም ለንጉሡ፥ “እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኖአል” አለው። እርሱም ተናግሮ እንዳበቃ፥ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ አምርረው አለቀሱ። አቤሴሎም ግን ኰብልሎ የገሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ፤ ዳዊትም ዘወትር ስለ ልጁ ያለቅስ ነበር። አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ገሹር ከሄደ በኋላ፥ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። ንጉሥ ዳዊትም በልጁ ሞት ከደረሰበት ኀዘን ተጽናና፤ ከዚያም መንፈሱ ወደ አቤሴሎም ለመሄድ ናፈቀ። የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ተቆዓ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ኀዘንተኛ በመምሰል የኀዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት ትሆኛለሽ፤ ከዚያም ወደ ንጉሡ ሂጂ፤ እንዲህም በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ መናገር ያለባትን ነገር ነገራት። የተቆዓዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፥ በንጉሡ ፊት በግምባሯ በምድር ላይ ተደፍታ እጅ በመንሣት፥ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች። ንጉሡም፥ “ችግርሽ ምንድነው?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤ እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፥ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆ ዘመዶቼ ሁሉ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው፥ ‘ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፥ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለን’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን በማጥፋት፥ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።” ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። ነገር ግን የተቆዓዪቱም ሴት፥ “ንጉሥ ጌታዬ፥ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች። ንጉሡም፥ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አይነካሽም” ሲል መለሰላት። እርሷም፥ “ደም ተበቃዮቹ ተጨማሪ ደም እንዳያፈሱ ልጄም እንዳይገደል፥ ንጉሡ ጌታ አምላኩን ያስብ” አለች። ንጉሡም፥ “ሕያው በሆነው ጌታ እምላለሁ! ከልጅሽ አንድ ጠጉር በምድር ላይ አይወድቅም” አላት። ከዚያም ሴቲቱ፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። ሴቲቱም እንዲህ አለችው፥ “አንተስ እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ከአገር የተሰደደውን ልጁን ንጉሡ ባለመመለሱ፥ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን? እኛ ሁላችን መሞታችን አይቀሬ ነው፤ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር የተሰደደ ሰው በስደት በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤’ ብዬ አሰብሁ፤ ‘እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊያጠፋን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’ አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆነ፥ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ከአንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።” ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፥ “የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂኝ መልሽልኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ንጉሥ ሆይ! ጠይቀኝ” አለችው። ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት። ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። ይህን እንድናገር ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አፍ ያደረገው አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም የነገሩን መልክ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ ያለው ጥበብ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ ስለሚመስል፥ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።” ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው። ኢዮአብም መሬት ላይ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባርኮ፥ ኢዮአብ፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ልመና ስለተቀበልከኝ፥ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን ዛሬ ለማወቅ ችያለሁ” አለ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ገሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። ንጉሡ ግን፥ “እዚያው ቤቱ ይሂድ፤ ፊቴን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም። የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በመላው እስራኤል ከቶ አልነበረም፤ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ የራስ ጠጉሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቆርጠው ነበር፤ የተቆረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥት ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር። አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች። አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ አልመጣም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ። ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ፥ የኢዮአብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይ የገብስ ሰብል አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው እርሻውን በእሳት አቃጠሉት። ከዚያም ኢዮአብ ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ቤት መጣና፦ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው እርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው። አቤሴሎምም፥ ኢዮአብን፥ “‘ከገሹር ለምን መጣሁ? ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሏል፥’ ብለህ እንድትነግርልኝ ወደ ንጉሡ ልልክህ ወደ እኔ ና ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ እፈልጋለሁ፤ ምንም ዓይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው። ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ። አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ከሊታውያን፥ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያን ሁሉን ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። ንጉሡም የጌታዊውን ሰው ኢታይን እንዲህ አለው፤ “አንተም ከእኛ ጋር አብረህ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሥ አቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ እኮ ከስፍራህ በግዞት የመጣህ መጻተኛ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? ተነሥ ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ ታማኝነትና እውነተኛነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። ኢታይ ግን፥ “በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው እሆናለሁ” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም ኢታይን፥ “እንግዲያውስ ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይ ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተሰቦቹን ይዞ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው አመሩ። ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቆ እስኪ ወጣ ድረስ፥ አብያታር አጠገብ አስቀመጡ። ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፤ በጌታ ፊት ሞገስ ያገኝሁ እንደሆነ፥ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤ ነገር ግን እርሱ፥ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፥ እነሆኝ፥ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ።” እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? ይሄውልህ አንተም ልጅህን አሒማአስን፥ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ” ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊት ግን እያለቀሰ፥ ራሱን ተከናንቦ፥ ባዶ እግሩን የደብረ ዘይትን ተራራ ወጣ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ተራራውን ይወጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፥ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ “ጌታ ሆይ! እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ሲል ጸለየ። ዳዊት ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ በደረሰ ጊዜ፥ አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊያገኘው መጣ። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፥ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር በዚያ ከአንተው ጋር አይደሉምን? ስለዚህ ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አሒማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው አብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት ወደ ከተማዋ ደረሰ። ዳዊት ከተራራው ጫፍ ባሻገር ጥቂት እልፍ ብሎ እንደ ሄደ፥ ጺባ የተባለው የመፊቦሼት አገልጋይ፥ ሁለት መቶ ሙልሙል ዳቦ፥ አንድ መቶ ጥፍጥፍ ዘቢብ፥ አንድ መቶ እስር ፍራፍሬና አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ሊያገኘው መጣ። ንጉሡም ጺባን፥ “ይህን ያመጣኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ጺባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተሰቦች እንዲቀመጡባቸው፥ ዳቦውንና ፍራፍሬውን ወጣቶቹ እንዲበሉት፥ የወይን ጠጁን ደግሞ በምድረ በዳ የደከሙት እንዲጠጡት ነው” አለው። ከዚያም ንጉሡ፥ “የጌታህ ልጅ የት ነው?” ሲል ጠየቀው። ጺባም፥ “ ‘የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል’ ብሎ ስለሚያስብ፥ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል” አለው። ከዚያም ንጉሡ ጺባን፥ “የመፊቦሼት የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው። ጺባም፥ “እጅ እነሣለሁ፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው። ንጉሥ ዳዊት ወደ ባሑሪም ሲደርስ፥ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ወጣ፤ ስሙ ሺምዒ ሲሆን የጌራ ልጅ ነው፤ እየተራገመም ወደ እርሱ ይመጣ ነበር። በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኀያላኑ ሁሉ ቢኖሩም እንኳ፥ ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሥ ዳዊት አገልጋዮችም ድንጋይ ይወረውር ነበር፤ ሺምዒ እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ምናምንቴ፤ መንግሥቱን የወሰድክበትን የሳኦልን ቤተሰቡ ደም ሁሉ ጌታ ወደ አንተው እየመለሰው ነው። ጌታ መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለሆንህ እነሆ፥ መጥፊያህ ደርሶአል።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፤ “ይህ የሞተ ውሻ፥ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሂድና ራሱን ልቁረጠው” አለ። ንጉሡ ግን፥ “እናንት የጽሩያ ልጆች እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ጌታ፥ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፥ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው። ከዚያም ዳዊት አቢሳንና አገልጋዮቹን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣ ልጅ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፥ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ ጌታ በል ብሎት ነውና ይራገም፤ ጌታ ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል” አላቸው። ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሺምዒ በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም ድንጋይም ይወረውር፥ ዐፈርም ይበትን ነበር። ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጣም ደክሞአቸው ስለ ነበር በዚያ ዐረፉ። በዚህን ጊዜ አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አኪጦፌልም አብሮት ነበር። የዳዊት ወዳጅ አርካዊው ሑሻይም ወደ አቤሴሎም መጥቶ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘለዓለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ ለዘለዓለም ንገሥ” አለው። አቤሴሎምም፥ ሑሻይን፥ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት እስከዚህ ድረስ ነው? ለምን ከወዳጅህ ጋር አልሄድህም?” ሲል ጠየቀው። ሑሻይም፥ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “እንዲህስ አይሆንም! እኔ በጌታ፥ በዚህ ሕዝብና በእስራኤል ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ፤ አብሬውም እኖራለሁ፤ እንግዲህ ልጁን ካላገለገልሁ ማንን ላገለግል ነው? አባትህን እንዳገለገልሁ ሁሉ፤ አንተንም አገለግላለሁ።” አቤሴሎምም አኪጦፌልን፤ “እስቲ ምክር አምጣ፤ ምን እናድርግ?” አለው። አኪጦፌልም መልሶ፥ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ዕቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፤ ከዚያም አንተ፥ አባትህን እጅግ የጠላህ መሆንህን መላው እስራኤል ይሰማና አብሮህ ያለው ሁሉ ክንዱ ይበረታል” አለው። ስለዚህ ለአቤሴሎም በሰገነቱ ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ እዚያም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ዕቁባቶች ጋር ተኛ። በዚያም ጊዜ አኪጦፌል የሚሰጠው ምክር ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ይቆጠር ነበር፤ በዳዊትም ሆነ በአቤሴሎም የአኪጦፌል ምክር ይከበር ነበር። አኪጦፌልም፥ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰው ልምረጥና፥ ዛሬ ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን አሳድደዋለሁ፤ በደከመውና በዛለ ጊዜም ሽብር እለቅበታለሁ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ ትቶት ይሸሻል፤ ንጉሡን ብቻውን እመታዋለሁ፥ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፤ አንተ የምትፈልገው የአንድ ሰው መሞት ብቻ ነውና፥ ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይኖራል።” ምክሩም አቤሴሎምንና አብረውት የነበሩትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ። ከዚያም አቤሴሎም፥ “እስቲ ደግሞ አርካዊውን ሑሻይን ጥሩትና የሚለውን እንስማ” አለ። ሑሻይም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፥ “አኪጦፌል ይህን ምክር አቅርቧል፤ ታዲያ የእርሱን ምክር እንከተል? ካልሆነ እስቲ አንተ ተናገር” አለው። ሑሻይም አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “አኪጦፌል የሰጠው ምክር በዚህ ጊዜ መልካም አይደለም፤” ሑሻይም በተጨማሪ እንዲህ አለው፥ “አባትህና ሰዎቹ ብርቱ ጦረኞችና ግልገሎችዋም እንደተነጠቁባት የዱር ድብ አምርረው የሚነሡ መሆኑን ታውቃለህ፤ በተጨማሪም አባትህ በጦር ሜዳ ልምድ ያለው ነው፤ ሌሊቱን ከሠራዊቱ ጋር አያድርም፤ እነሆ፥ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል። ጥቂት ሰዎች በመጀመሪያ በሚጥልባቸው ጥቃት ቢሞቱ ይህን የሰማ ሁሉ፥ ‘አቤሴሎምን የተከተለው ሠራዊት ተፈጀ’ ብሎ ያወራል። አባትህ ታላቅ ጦረኛ፥ አብረውት ያሉትም ጀግኖች መሆናቸውን እስራኤል ሁሉ ስለሚያውቅ፥ ልቡ እንደ አንበሳ ልብ የሚደፍረው እንኳ በፍርሀት ይርዳል። እኔ የምመክርህ፥ ቁጥሩ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛው፥ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው እስራኤል ሁሉ ወዳንተ ይሰብሰብና አንተው ራስህ ወደ ጦርነቱ ምራው፤ ከዚያም እርሱ ይገኝበታል የተባለው ቦታ ገብተን እናገኝዋለን፥ ጠል መሬት ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ሰዎቹ አንድ እንኳ አይተርፉም፤ ከአንዲቱ ከተማ ቢገባ፥ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይቀር ድረስ፥ ከተማዪቱን ወደ ሸለቆ ስበን እንከታታለን።” አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉም “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የሑሻይ ምክር ይሻላል” አሉ፤ ጌታ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት፥ ጌታ መልካም የነበረው የአኪጦፌል ምክር ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎአል። ሑሻይ ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲህ አላቸው፥ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች እንዲህ እንዲህ አድርጉ ሲል መክሮአቸው ነበር፤ እኔ ግን እንዲህ እንዲህ አድርጉ ብዬ መክሬአቸዋለሁ። አሁንም በፍጥነት ላኩና፥ ‘ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ እንዳትዋጡ፥ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ መሻገሪያ እንዳታድር ሳትዘገይ ተሻገር፤’ ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፤ አላቸው።” በዚህ ጊዜ ዮናታንና አሒማዓጽ ወደ ከተማዪቱ ከገቡ ስለሚታዩ በዔንሮጌል ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይ ወደዚያ እየሄደች በምትነግራቸው ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ይህንኑ ወስደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር። ሆኖም አንድ ወጣት አይቷቸው ለአቤሴሎም ነገረው፤ ሁለቱም በፍጥነት ተነሥተው በባሑሪም በግቢው ውስጥ ጉድጓድ ወደሚገኝ ወደ አንድ ሰው ቤት ሄዱ፤ ወደዚያም ውስጥ ወረዱ። ሚስቱም በጉድጓዱ አፍ ላይ የስጥ ማስጫ ዘርግታ እህል አሰጣች፤ ማንም ይህን አላወቀም ነበር። የአቤሴሎም ሰዎች እዚያ ቤት ወደ ሴቲቱ ዘንድ መጥተው፥ “አሒማዓጽና ዮናታን የት አሉ?” ብለው ጠየቋት። ሴቲቱም፥ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” ብላ መለሰችላቸው፤ እነርሱም ፈልገው ስላጧቸው፥ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ሰዎቹ ከሄዱ በኋላ ሁለቱም ከጉድጓዱ ወጥተው ሄዱ፤ ለንጉሥ ዳዊትም፥ “አኪጦፌል በአንተ ላይ እንዲህ እንዲህ ብሎ ስለመከረብህ ተነሥተህ በፍጥነት ወንዙን ተሻገር” አሉት። ስለዚህ ዳዊትና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ተነሥቶ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም። አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉት ባየ ጊዜ፥ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወደሚገኝበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም አስተካክሎ በገዛ እጁ ታነቀ፤ ከሞተ በኋላ በአባቱም መቃብር ተቀበረ። አቤሴሎም ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ሲሻገር፥ ዳዊት ግን ማሕናይም ደርሶ ነበር። አቤሴሎምም በኢዮአብ ምትክ አማሳይን በሠራዊቱ ላይ ሾመ፤ አማሳይ የእስማኤላዊው የዮቴር ልጅ ነበረ፤ ዮቴርም የኢዮአብን እናት፥ የጽሩያን እኅት፥ የናዖስን ልጅ አቢግያንሰ አግብቶ ነበር። እስራኤላውያንና አቤሴሎም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ። ዳዊት ማሕናይም ሲደርስ፥ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፥ የናዖስ ልጅ ሾቢ፥ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ መተኛ ምንጣፎች፥ ወጭቶችና የሸክላ ዕቃዎች ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ስንዴና ገብስ፥ ዱቄትና የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላና ምስር፥ ማር፥ እርጎ፥ በጎችና የላም አይብ እንዲበሉ ለዳዊትና ለሕዝቡ አመጡላቸው፤ ይህን ያደረጉትም፥ “ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፤ ደክሞአል፤ ተጠምቶአል” ብለው ነው። ዳዊት አብሮት የነበረውን ሕዝብ ቆጠረ፤ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው። ሠራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፥ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩያ ልጅ በአቢሳይ፥ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው። ንጉሡም ለሠራዊቱ፥ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ እወጣለሁ” አላቸው። ሰዎቹ ግን፥ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፥ ስለኛ ምንም አይገዳቸውም፤ ግማሾቻችን እንኳ ብንሞት፥ ስለኛ ምንም አይገዳቸውም፤ አንተ ግን ብቻህን ከእኛ ከዐሥሩ ሺህ ትበልጣለህ! ስለዚህ በከተማ ሆነህ ብትረዳን ይሻላል” አሉት። ንጉሡም፥ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ፥ ንጉሡ በቅጥሩ በር ቆሞ ነበር። ንጉሡም ኢዮአብን፥ አቢሳንና ኢታይን፥ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በኤቤሴሎም ላይ ጉዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለአዛዥዎቹ ትእዛዝ ሲሰጥ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ። ሠራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ። እዚያም የእስራኤል ሠራዊት በዳዊት አገልጋዮች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺህም ሰዎችም ሞቱ። ውጊያው በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ፤ በዚያን ቀን ሰይፍ ከጨረሰው ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረው ሰው በለጠ። በዚህ ጊዜ አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ጋር ድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ይሄድ ስለ ነበር፥ በቅሎዋ ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው ትልቅ ባሉጥ ሥር በምታልፍበት ጊዜ፥ የአቤሴሎም ራስ በባሉጡ ቅርንጫፍ ተያዘ፤ የተቀመጠበትም በቅሎ በሥሩ ስታልፍ፥ እርሱ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠልጥሎ ቀረ። አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፥ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው። ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፥ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መተህ ምድር ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፥ ዐሥር ብርና ዝናር እሸልምህ ነበር” አለው። ሰውየው ግን ለኢዮአብ እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፥ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጉዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’ ተብሎ አንተን፥ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለሆነ፥ አንድ ሺህ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፥ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም። በሌላ በኩል ደግሞ በነፍሴ ቆርጬ ሕይወቱን ባጠፋው ኖሮ፥ ከንጉሡ ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለ ሌለ፥ አንተም ራስህ በተነሣህብኝ ነበር” ብሎ መለሰለት። ኢዮአብም፥ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እባሉጥ ዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው። እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት። ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ ሠራዊቱ እስራኤልን እንዳያሳድዱም ስለከለከለ ከማሳደድ ተመለሰ። አቤሴሎምን ጫካ ወስደው በትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በላዩም ትልልቅ ድንጋይ ከመሩበት። እስራኤልም ሁሉ ወደየቤታቸው ሸሹ። አቤሴሎም፥ “ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም” በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ ለራሱ ሐውልት አቁሞ ስለ ነበር፥ እስከ ዛሬ ድረስ የአቤሴሎም ሐውልት ተብሎ ይጠራል። ከዚህ በኋላ የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ፥ “ጌታ ጠላቶቹን የተበቀለለት መሆኑን ሮጬ ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው” አለ። ኢዮአብም፥ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፥ ዛሬ ሳይሆን የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው። ከዚያም ኢዮአብ ለኢትዮጵያዊው፥ “ሂድና ያየኸውን ለንጉሡ ንገር” አለው። ኢትዮጵያዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ። የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽም እንደገና ኢዮአብን፥ “የመጣው ይምጣ፤ እባክህ ኢትዮጵያዊውን ተከትየው ልሩጥ” አለው። ኢዮአብ ግን፥ “ልጄ ሆይ፥ የምሥራቹ ሽልማት እንደማያሰጥህ እያየህ መሄድ ለምን አስፈለገህ?” ብሎ መለሰለት። አሒማዓጽም፥ “የመጣው ይምጣ፤ መሄድ እፈልጋለሁ” አለ። ስለዚህም ኢዮአብ፥ “ሩጥ!” አለው። ከዚያም አሒማዓጽ በሜዳው መንገድ ሮጦ ኢትዮጵያዊውን ቀድሞት ሄደ። ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ጠባቂውም ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጣ፤ ቀና ብሎም ሲመለከት አንድ ሰው ብቻውን እየሮጠ ሲመጣ አየ፤ ጠባቂው ተጣራና ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ ንጉሡም፥ “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ ይሆናል” አለ። ሰውየውም እየቀረበ መጣ። ከዚያም ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውን ተጣራና፥ “ተመልከት! ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለው። ንጉሡም፥ “ይኸኛውም መልካም ወሬ ይዞ የመጣ ይሆናል” አለ። ጠባቂውም፥ “የመጀመሪያው ሰው ሩጫ የሳዶቅን ልጅ የአሒማዓጽን ሩጫ ይመስለኛል” አለ። ንጉሡም፥ “እርሱ ጥሩ ሰው ነው፤ ቢመጣም የምሥራች ይዞ ነው” አለ። አሒማዓጽም ጮኾ ንጉሡን፥ “ሁሉም ደህና ሆኖአል” አለ፤ ከዚያም ወደ መሬት ለጥ ብሎ በንጉሡ ፊት እጅ ነሣና፥ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ ጌታ አምላክህ የተመሰገነ ይሁን!” አለ። ንጉሡም፥ “ወጣቱ አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀ። አሒማዓጽም፥ “ኢዮአብ የንጉሡን አገልጋይና እኔንም አገልጋይህን ሊልክ ሲል፥ ትልቅ ሁካታ አይቻለሁ፤ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም” ብሎ መለሰ። ንጉሡም፥ “እልፍ በልና ቁም” አለው፤ ስለዚህ እልፍ ብሎ ቆመ። ከዚያም ኢትዮጵያዊው ደርሶ፥ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ የምሥራች! ዛሬ ጌታ ከተነሡብህ ጠላቶችህ ሁሉ ታድጎሃል” አለው። ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን፥ “ወጣቱ አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊውም፥ “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶችና ሊጐዱህ የሚነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ” ሲል መለሰ። ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም፥ ልጄን፥ ወየው ልጄን!” ይል ነበር። ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፥ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሠራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፥ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሠራዊት ዘንድ ወደ ኀዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ድምፅ ሳያሰማ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥ ልጄን! ልጄን!” እያለ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፥ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የዕቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳልሆኑ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በጌታ ስም እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያሰከትልብሃል።” ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፥ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር። በመላው የእስራኤል ነገዶችም፥ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዶአል፤ በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ስለ ንጉሡ የመመለስ ጉዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?” ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለሆነ፥ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ አማሳይንም፥ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፥ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፥ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።” እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳም ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። የባሑሪም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ሄደ። ከእርሱም ጋር አንድ ሺህ ብንያማውያን፥ እንዲሁም የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ ጺባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ፈጥነው ተሻገሩ። የንጉሡን ቤተሰብ ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፥ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አትቁጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ አገልጋይህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ በልብህም አታኑርብኝ። እኔ አገልጋይህ ኃጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ እነሆ፥ ዛሬ ግን ጌታዬ ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ መጥቻለሁ።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፥ “ሺምዒ በጌታ የተቀባውን የረገመ ስለሆነ፥ መሞት አይገባውምን?” አለ። ዳዊትም፥ “እናንት የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬ ማንስ ቢሆን በእስራኤል ዘንድ መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ንጉሡ ሺምዒን፥ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት። የሳኦል ልጅ መፊቦሼትም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ መጫሚያ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር። እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “መፊቦሼት፥ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፥ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ አታለለኝ። በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የአገልጋይህን ስም አጥፍቶአል፤ ንጉሥ ጌታዬ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆንህ ደስ ያሰኘህን አድርግ። የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን አገልጋይህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?” ንጉሡም፥ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ጺባ እርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው። መፊቦሼትም ንጉሡን፥ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፥ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው። እንዲሁም ገለዓዳዊው ባርዚላይ ከሮገሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ። ባርዚላይ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በማሕናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር። ንጉሡም ባርዚላይ፥ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ የሚያስፈልግህን እኔ አደርግልሃለሁ” አለው። ባርዚላይ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው? እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ የሚያስደስቱና የማያስደስቱ ነገሮችን መለየት እችላለሁን? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንስ መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል? አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው? በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እንድቀበር፥ እባክህ፥ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ኪምሃም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።” ንጉሡም፥ “ኪምሃም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው። ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ንጉሡም ተሻገረ። ንጉሡ ባርዚላይን ስሞ መረቀው፤ ባርዚላይም ወደ ቤቱ ተመለሰ። ንጉሡ ወደ ጌልገላ ሲሄድ፥ ኪምሃም አብሮት ሄደ። የይሁዳ ሠራዊት በሙሉ እንዲሁም ግማሹ የእስራኤል ሠራዊት ንጉሡን አጅበው አሻገሩት። ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው፥ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን በሹልክታ ለብቻቸው ይዘው እርሱንና ቤተሰቡን ከተከታዮቹ ጋር ዮርዳኖስን ለምን አሻገሩ?” አሉት። የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ ለእስራኤል ሰዎች፥ “ይህን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለሆነ ነው፤ ታዲያ ይህ እናንተን የሚያስቆጣ ነገር ነው? እኛ ከንጉሡ ተቀብለን አንዳች በልተናልን? ለራሳችንስ ምን የወሰድነው ነገር አለ?” አሉአቸው። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፥ “እኛ እኮ ከንጉሡ ዐሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ከዚህም በተጨማሪ በዳዊት ዘንድ ከእናንተ ይልቅ እኛ የበለጠ መብት አለን፤ ታዲያ እኛን የናቃችሁን ስለ ምንድነው? ንጉሣችን እንዲመለስ በመጀመሪያ የጠየቅነው እኛ አይደለምን?” አሉ። ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር። በዚህ ጊዜ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሼባዕ የተባለ አንድ ከንቱ ብንያማዊ በዚያ ነበረ፤ እርሱም መለከት ነፍቶ እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እኛ ከዳዊት ድርሻ የለንም፤ ከእሴይም ልጅ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፤ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ!” ስለዚህ የእስራኤል ሰው ሁሉ ዳዊትን ከድቶ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ተከተለ። የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንሥቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው ሳይለዩ አብረውት ሄዱ። ዳዊት ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በተመለሰ ጊዜ፤ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ትቶአቸው የሄደውን ዐሥሩን ዕቁባቶቹን ወሰደ፤ በአንድ ቤትም ውስጥ እንዲጠበቁ አደረገ። ቀለብ ሰጣቸው፤ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ አልገባም ነበር፤ እነርሱም እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ መበለት ሆነው፥ ለብቻቸው ተገልለው ተቀመጡ። ከዚያም ንጉሡ አማሳይን፥ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ፥ ወደ እኔ እንዲመጡ ጥራልኝ፤ አንተ ራስህም እንድትገኝ” አለው። አማሳይ ይሁዳን ለመጥራት ሄደ፤ ነገር ግን ንጉሡ ከወሰነው ጊዜ በላይ ቆየ። ዳዊትም አቢሳን፥ “ከአቤሴሎም ይልቅ አሁን የቢክሪ ልጅ ሼባዕ የበለጠ ጉዳት ሊያደርስብን ስለሆነ የጌታህን አገልጋዮች ይዘህ አሳደው፤ ያለዚያ የተመሸገ ከተማ አግኝቶ ያመልጠናል” አለው። አቢሳንም ተከትለው የኢዮአብ ሰዎች ከሊታውያን፥ ፈሊታውያን፥ እንዲሁም ሌሎች ኀያላን ጦረኞች በሙሉ ወጡ፤ የቢክሪ ልጅ ሼባዕን ለማሳደድ ከኢየሩሳሌም ወጡ። በገባዖን ከታላቁ ቋጥኝ አጠገብ እንደ ደረሱ፥ አማሳይ ሊገናኛቸው መጣ፤ ኢዮአብ የጦር ሜዳ ልብሱን ለብሶ ሰይፉን ከሰገባው በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ ወደ ፊት ራመድ እንዳለም ሰይፉ ከሰገባው ወጥቶ ወደቀ። ኢዮአብም አማሳይን፥ “ወንድሜ ሆይ፤ እንደ ምንድንነህ?” አለው፤ ከዚያም አማሳይን የሚስም መስሎ በቀኝ እጁ ጢሙን ያዘው። አማሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ሰይፍ መኖሩን ልብ ስላላለ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ስለዚህ ኢዮአብ ሰይፉን ሆዱ ላይ ሻጠበት፤ አንጀቱም መሬት ላይ ተዘረገፈ፤ መድገምም አላስፈለገውም፥ አማሳይ በዚያው ሞተ። ከዚህ በኋላ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ፥ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ማሳደድ ጀመሩ። በአማሳይ ሬሳ አጠገብ ከቆሙት ከኢዮአብ ሰዎች አንዱ፤ “ኢዮአብን የሚወድ፥ የዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል!” አለ። በዚህን ጊዜ የአማሳይ ሬሳ በደም ተጨማልቆ በመንገዱ መካከል ወድቆ ነበር፤ በዚያ የሚያልፈው ሠራዊት ሁሉ መቆሙን ያ ሰው አየ፤ ወደ ሬሳው የደረሰው ሠራዊት ሁሉ መቆሙን በተረዳ ጊዜም፥ የአማሳይን ሬሳ ከመንገድ ወደ እርሻ ፈቀቅ አድርጎ በልብስ ሸፈነው። የአማሳይ ሬሳ ከመንገድ ላይ ከተነሣ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ኢዮአብን ተከትሎ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ሊያሳድድ ሄደ። ሼባዕም በእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ዐልፎ ወደ አቤል ቤት ማዓካ ወደ መላው የቢክሪያውያን ግዛት መጣ፤ የቢክሪ ሰዎችም ተሰብስበው ተከተሉት። ከኢዮአብ ጋር ያለውም ሠራዊት መጥቶ ሼባዕን በአቤል ቤት መዓካ በኩል ከበበው፤ በስተ ውጭም እስከ ከተማዪቱ ግንብ ጫፍ ድረስ ዙሪያውን የዐፈር ድልድል ሠሩ፤ ግንቡን ለመናድ በኃይል ይደበድቡት ነበር፤ ከዚያ አንዲት ብልኅ ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፥ “ስሙ! ስሙ! ኢዮአብን ላነጋግርህ እንድችል ወደዚህ ና በሉት” አለቻቸው። ኢዮአብ ወደ እርሷ ቀረበ፤ እርሷም፥ “ኢዮአብ አንተ ነህ?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም፥ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰላት። እርሷም፥ “እንግዲህ አገልጋይህ የምትለውን አድምጥ” አለችው። እርሱም፥ “እያዳመጥኩ ነው” አላት። ከዚያ በመቀጠልም እንዲህ አለች፤ “በቀድሞው ጊዜ ሰዎች፥ ‘ምክርን ከአቤል ጠይቁ’ ይሉ ነበር፤ ነገሩም እንዳሉት ይፈጸም ነበር፤ በእስራኤል ሰላማዊና ታማኝ ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዷ እኔ ነኝ፤ አንተ በእስራኤል እናት የሆነችውን ከተማ ለማጥፋት ትሻለህ፤ የጌታን ርስት ለመዋጥ የፈለግኸው ለምንድን ነው?” ኢዮአብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይህስ ከእኔ ይራቅ! መዋጡና ማጥፋቱ አሁንም ከእኔ ይራቅ! ነገሩስ እንዲህ አይደለም፤ የኰረብታማው የኤፍሬሙ አገር ሰው፥ የቢክሪ ልጅ ሼባዕ እጁን በንጉሡ በዳዊት ላይ አንሥቶአል፤ እናንተ ይህን ሰው ብቻ ስጡኝ እንጂ እኔ ከተማዪቱን ትቼ እሄዳለሁ” አላት። ሴቲቱም ኢዮአብን፥ “የሰውየው ራስ ተቆርጦ በግንቡ ላይ ይወረወርልሃል” አለችው። ከዚህም በኋላ ሴቲቱ ብልኅ ምክሯን ይዛ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሼባዕን ራስ ቆርጠው ለኢዮአብ ወረወሩለት፤ ስለዚህ ኢዮአብ መለከቱን ነፋ፤ ሰዎቹም ከከተማዪቱ ርቀው በየአቅጣጫው ተበታተኑ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው ሄዱ፤ ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ኢዮአብ በእስራኤል ሠራዊት ሁሉ ላይ አዛዥ ሆነ፤ የዮዳሄ ልጅ በናያ ደግሞ በከሊታውያንና በፈሊያታውያን ላይ አዛዥ ሆነ። አዶራም በግዳጅ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ሰዎች አለቃ ሲሆን፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ ታሪክ ጸሓፊ ነበር፤ ሱሳ ጸሓፊ፥ ሳዶቅና አብያታር ካህናት ነበሩ፤ እንዲሁም የያኢር ሰው ዒራ የዳዊት ካህን ነበር። በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፥ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። ንጉሡም ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፥ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊትም ገባዖናውያንን፥ “ምን ላድርግላችሁ? የጌታን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተሰረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው። ገባዖናውያንም፥ “በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ጉዳይ አይደለም፥ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፥ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው ከእርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከጌታ በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በጌታ ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፥ “እሺ! እሰጣችኋለሁ” አለ። ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በጌታ ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፥ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን ከሞት አተረፈ። ነገር ግን ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን፤ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለመሖላታዊው ለባርዚላይ ልጅ ለአድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ ከዚያም ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በጌታ ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ የተገደሉትም እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ነበር። የአያ ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፥ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ የሳኦል ዕቁባት የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፥ ዳዊት ሄዶ፥ ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤት ሻን አደባባይ ከሰረቁት ከያቤሽ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አምጥቶ፥ የእነዚያን የተሰቀሉትን ሰዎች ዐፅምም ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ። እንደገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ ዳዊትም ደከመው። ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢበኖብ የተባለ ዳዊትን ለመግደል አሰበ። የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ። የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፥ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት። ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያን ጊዜም የሑሻው ተወላጅ ሲበካይ፥ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን ሳፍን ገደለው። ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ሌላ ጦርነትም፥ የቤተልሔሙ የያዒር ዓርጊምን ልጅ ኤልሐናን፥ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለው። እንደገና ጌት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ። ይህም ሰው እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፥ የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናታን ገደለው። እነዚህ አራቱ በጌት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ። ጌታ ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦልም እጅ በታደገው ጊዜ፥ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃል ለጌታ ዘመረ፤ እንዲህም አለ፤ ጌታ ዐለቴ ዐምባዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምደገፍበት፥ ዐለቴ፥ ጋሻዬና የመዳኔ ቀንድ ነው። እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፥ መጠጊያና አዳኜ ነው፤ አንተ ከጨካኞች ታድነኛለህ። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ሞገድ ከበበኝ፤ የጥፋትም ጐርፍ አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞትም ወጥመድ ተጋረጠብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፤ ወደ አምላኬም ጮኽሁ። እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ። ምድርም ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ የሰማያትም መሠረቶች ተናጉ፤ እርሱ ተቆጥቶአልና ራዱ። ከአፍንጫው የቁጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ ከእርሱ የሚንበለበል ፍም ወጣ። ሰማያትን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሲከንፍ ታየ። ሁለንተናውን በጨለማ ሰወረ፥ በውሃ በተሞላ ጥቅጥቅ ደመና፥ ራሱን ከበበ። በፊቱ ካለው ብርሃን የእሳት ፍም ነደደ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፤ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ። ፍላጻውን ሰደደ፤ በተናቸውም፤ በመብረቁም ብልጭታ አወካቸው። ከጌታ ተግሣጽ፥ ከአፍንጫው ከሚወጣው፥ ከእስትንፋሱ ቁጣ የተነሣ፥ የባሕር መተላለፊያዎች ታዩ፤ የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ። በርትተውብኝ ነበርና፥ ከብርቱ ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም ታደገኝ። በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ ጌታ ግን ደገፈኝ። ሰፊ ወደ ሆነ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ፤ የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ ከአምላኬ ክፋት በማድረግ አልተለየሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁም። በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤ ራሴንም ከኃጢአት ጠብቄአለሁ። ጌታም እንደጽድቄ፥ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ። “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ለቅን ሰው አንተም ቅን ሆነህ ትታያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ ሆነህ ትታያለህ፥ ለጠማማ ሰው ግን ጠማማ ሆነህ ትታያለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፥ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። ጌታ ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ ጌታም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ርዳታ ሠራዊት አልፌ ወደ ፊት እሮጣለሁ፤ በአምላኬም ኃይል ቅጥሩን እዘላለሁ። የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የጌታም ቃል የጠራ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው፤ ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቀና እግዚአብሔር ነው። እግሮቼን እንደ ብሆር እግር ያበረታል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። ክንዶቼም የናስ ቀስት መሳብ እንዲችሉ፥ እጆቼን ለጦርነት ያሰለጥናል። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ምላሽህም ታላቅ አድርጎኛል። እርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም። ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤ ሳላጠፋቸው ወደ ኋላ አልተመለስሁም። ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ አስጨነቅኻቸው ተመልሰውም እንዳይቆሙ፥ ከእግሬም ሥር ወድቀዋል። ለጦርነት ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛለህ። የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። ለርዳታ ጮኹ፤ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ ጌታ ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አደቀቅዃቸው፤ በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም። ከሕዝቤ ጥቃት አዳንከኝ፤ የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ፤ የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤ ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤ እንደ ሰሙኝም በፍጥነት ይታዘዙኛል። ባዕዳን ፈሩ፤ ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ። ጌታ ሕያው ነው! ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤ የመዳኔ ዓለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል። የሚበቀልልኝ አምላክ፥ ሕዝቦችን ከሥሬ የሚያስገዛልኝ፤ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ የሚያወጣኝ እርሱ ነው። በጠላቶቼ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ። ስለዚህ ጌታ ሆይ፥ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ። ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤ ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፥ የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳያል፥ ይህንንም ለዘለዓለም ያደርጋል።” የዳዊት የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፥ የእስራኤል ተወዳጁ ዘማሪ የሆነው፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት የትንቢት ቃል ይህ ነው፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ነው። የእስራኤል አምላክ ተናገረ፤ የእስራኤልም ዓለት እንዲህ አለኝ፦ ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት የሚያስተዳድር፥ እርሱ፥ እንደ ንጋት ብርሃን እንደ ማለዳ ፀሐይ አወጣጥ፥ ደመና በሌለበት ማለዳ እንደምታበራ የብርሃን ጸዳል፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል። ሁሉንም ነገር አዘጋጅቶና ጠብቆ፥ ከእኔ ጋር ዘላለማዊ ኪዳን ያደረገ፥ መዳኔን ከፍጻሜ የሚያደርሰው፥ መሻቴን ሁሉ የሚሰጠኝ እርሱ አይደለምን? በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ አይደለምን? ነገር ግን ክፉ ሰዎች ሁሉ፥ በእጅ እንደማይሰበሰብ እንደ እሾኽ ይጣላሉ። እሾኽ የሚነካ ሁሉ፥ የብረት መሣሪያ ወይም የጦር ዘንግ ይይዛል፤ እነሱም ባሉበት ስፍራ ፈጽመው በእሳት ይቃጠላሉ።” የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሼብ ባሼቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፥ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው በአንዴ የገደለ ነው። ከእርሱ ቀጥሎ የአሆህዊው የዶዶ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፥ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች አፈገፈጉ። እርሱ ግን ተነስቶ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ። ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። ከእርሱም ቀጥሎ የሃራርታዊው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት ሌሒ በተባለ ስፍራ አንድ እርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ነበር። ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሻማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዱላም ዋሻ መጡ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በቤተልሔም ነበረ፤ ዳዊትም በናፍቆት፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። ሦስቱም ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፥ በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በጌታ ፊት አፈሰሰው፤ “እርሱም፥ ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቆርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ብሎ፥ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱ ኀያላን ሰዎች የፈጸሙአቸው ተግባሮች እነዚህ ነበሩ። የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና ስሙም ከሦስቱ ኀያላን ጋር የሚጠራ ነበረ። እርሱ ከሠላሳው ይልቅ እጅግ ዝነኛ ስለ ነበር፤ አለቃቸው ሆኖ ነበር፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም። የቃብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያም ታላቅ ተግባር የፈፀመ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ ሁለቱን በጣም የታወቁ የሞዓብን ሰዎችን ገድሎአል፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፤ አንድ ማራኪ ግብፃዊንም ገድሎአል፤ ግብፃዊው በእጁ ጦር ይዞ፥ በናያ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ነበር ወደ እርሱ የሄደው፤ ከግብፃዊውም እጅ የገዛ ጦሩን በመንጠቅ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ በናያ ያደረገው ይህ ነው፥ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። ከሠላሳዎቹ ይልቅ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው። ከሠላሳዎቹ መካከል፦ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፥ ሐሮዳዊው ሻማ፥ ሐሮዳዊው ኤሊቃ፥ ፈሌጣዊው ሴሌስ፥ የቴቆአዊው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፤ ሑሻዊው መቡናይ፥ አሆሃዊው ጻልሞን፥ ነጦፋዊው ማህራይ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ተወላጅ የሆነው የጊብዓ ሰው የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያ፥ የገዓሽ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ ባርሑማዊው ዓዝማዌት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የያሼን ልጆች፤ ዮናታን፥ የሐራራዊው የሻማ ልጅ፥ የሐራራዊው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፥ የጊሎናዊው የአሒጦፌል ልጅ ኤሊአም፥ ቀርሜሎሳዊው ሔጽሮ፤ አርባዊው ፈዓራይ፥ የጾባዊው የናታን ልጅ ይግዓል፥ አሞናዊው ጸሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረው በኤሮታዊው ናሕራይ፥ ያቲራዊው ዒራ፥ ያቲራዊው ጋሬብ፥ ሒታዊው ኦርዮ፤ በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ። እንደገናም የጌታ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ዳዊትንም፥ “ሂድ እስራኤልንና ይሁዳን ቁጠር” በማለት በእነርሱ ላይ አነሣሣው። ስለዚህም ንጉሡ ኢዮአብንና አብረውት የነበሩትን የጦር አዛዦች፥ “ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወዳሉት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ሂዱ፤ ምን ያኽል ሕዝብ እንዳለ ማወቅ ስለምፈልግ ሕዝቡን ቁጠሩ።” አላቸው። ኢዮአብ ግን ንጉሡን፥ “ጌታ አምላክህ ሕዝቡን መቶ ዕጥፍ ያድርገው፤ የጌታዬ የንጉሡ ዐይን ይህን ለማየት ያብቃው፤ ንጉሡ ጌታዬ ግን ይህን ለማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” ሲል መለሰለት። ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮአብንና የሠራዊቱን አዛዦች አሸነፋቸው፤ ስለዚህ የእስራኤልን ሕዝብ ለመቁጠር ከፊቱ ወጥተው ሄዱ። ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ፥ በሸለቆው ውስጥ ካለችው ከተማ በስተ ደቡብ በምትገኘው በአሮዔር አጠገብ ሰፈሩ፤ ከዚያም በጋድ በኩል አድርገው ወደ ያእዜር ሄዱ፤ እንዲሁም ወደ ገለዓድና በሒታውያን ግዛት ወዳለው ወደ ቃዴስ ዘለቁ፤ ከዚያም ወደ ዳን፥ ከዳንም ወደ ሲዶና ዞሩ፤ ከዚያ ወደ ጢሮስ ምሽግ፥ ወደ ሒዋውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች፥ በይሁዳ ደቡብ ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ። ምድሪቱን ሁሉ ሲዞሩ ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ነበር። ኢዮአብም የሕዝቡን ጠቅላላ ቍጥር ለንጉሡ አሳወቀ፤ በእስራኤል ስምንት መቶ ሺህ፥ በይሁዳ አምስት መቶ ሺህ ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ዳዊት ሕዝቡን ከቆጠረ በኋላ ኅሊናው ወቀሰው፤ ዳዊትም ጌታን፥ “ባደረግሁት ነገር የፈጸምኩት ታላቅ ኃጢአት ነው፤ አሁን ግን፥ ጌታ ሆይ፤ የአገልጋይህን በደል ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ የፈጸምኩት ታላቅ የሞኝነት ሥራ ነውና” አለ። በማግስቱ ጠዋት ዳዊት ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ የጌታ ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደ ሆነው ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ መጣ፤ “ሂድና ዳዊትን፥ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፤ ሦስት ነገሮችን አቅርቤልሃለሁ፤ በአንተ ላይ እንዳደርግብህ አንዱን ምረጥ’ በለው” አለው። ስለዚህም ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ፥ “በምድርህ ሦስት ዓመት ራብ ከሚሆን፥ ለሦስት ወር ጠላቶችህ ከሚያሳድዱህና በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን የቸነፈር መቅሠፍት ከሚሆን የትኛውን ትመርጣለህ? እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስበህበት ወስን” አለው። ዳዊትም ጋድን፥ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በጌታ እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው። ስለዚህም ጌታ ከዚያች ዕለት ጥዋት አንሥቶ እስከ ተወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤ በዚህም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺህ ሰው አለቀ። የጌታ መልአክ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ጌታ ስለ ክፉው ነገር አዘነ፤ ሕዝቡን የሚቀሥፈውንም መልአክ “ይበቃል! እጅህን መልስ” አለው። በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። ዳዊት ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ ባየ ጊዜ ጌታን፥ “እነሆ፥ ኃጢአት የሠራሁት እኔ ነኝ! የተሳሳትሁም እኔ ነኝ! እነዚህ በጎች ግን ምን አጠፉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ” አለ። በዚያን ቀን ጋድ ወደ ዳዊት መጥቶ፥ “ውጣና በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለጌታ መሠዊያ ሥራ” አለው። ስለዚህ ዳዊት፥ ጌታ ያዘዘውን ለማድረግ የጋድን ቃል ሰምቶ ወጣ። ኦርናም ቁልቁል ሲመለከት፥ ንጉሡና አገልጋዮቹ ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ ኦርናም ወጥቶ በንጉሡ ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፋ። ኦርናም፥ “ንጉሥ ጌታዬ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለ። ዳዊትም፥ “መቅሠፍቱ ከሕዝቡ እንዲከለከል ለጌታ መሠዊያ እንድሠራ ዐውድማህን ልገዛ ነው” ሲል መለሰለት። ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ጌታዬ ደስ ያለውን ወስዶ መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች፥ ለሚነደውም ዕንጨት፥ የመውቂያው ዕቃና የበሬ ቀንበር አለ። ንጉሥ ሆይ፥ ይህን ሁሉ ኦርና ለንጉሡ ይሰጣል።” እንዲሁም ኦርና፥ “ጌታ አምላክህ ይቀበልህ” አለው። ንጉሡ ግን ኦርናን፥ “መክፈል ያለብኝን ዋጋ ላንተ ከፍዬ እንጂ እንዲሁማ አይሆንም፤ ለጌታም ለአምላኬ የሚቃጠል መሥዋዕት ያለ ዋጋ አላቀርብም” አለው። ስለዚህም ዳዊት ዐውድማውንና በሬዎቹን በአምሳ ሰቅል ብር ገዛ፤ በዚያም ዳዊት ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት አቀረበ። ከዚያም ጌታ ለምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት ሰማ፤ በእስራኤል ላይ የመጣውም መቅሰፍት ቆመ። ንጉሡ ዳዊትም ዕድሜው ገፍቶ ስለ ሸመገለ፥ ልብስ ደራርበው ቢያለብሱትም ሙቀት ሊሰጠው አልቻለም ነበር። ባርያዎቹም፦ “ንጉስ ሆይ! ከአንተ ጋር ሆና የምትንከባከብህ ወጣት ልጃገረድ ፈልገን እናምጣ፤ በጌታችንም በንጉሡ እቅፍ ተኝታ ታሞቅሃለች” አሉት። በሁሉም የእስራኤል ግዛት የተዋበች ቆንጆ ፈለጉ፤ አቢሻግንም ሹኔም ከምትባል ስፍራ አገኙ፤ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ። ልጃገረዲቱም እጅግ ውብ ነበረች። ለንጉሡም ረዳትና አገልጋይ ሆነች፤ ንጉሡ ግን ከእርሷ ጋር ግንኙነት ፈጽሞ አያውቅም ነበር። ያንጊዜ የሐጊት ልጅ አዶንያስ፦ “ንጉሥ እሆናለሁ” ብሎ ተነሣሣ፤ ለራሱም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን፥ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎችን አዘጋጀ። አባቱም በሕይወቱ ሳለ፦ “እንዲህ ለምን ታደርጋለህ?” ብሎ ከቶ ተቆጥቶት አያውቅም ነበር። ደግሞም መልከ መልካም ነበር፤ የተወለደውም ከአቤሴሎም በኋላ ነበር። ስለዚህ ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር አሴረ፤ እነርሱም አዶንያስን ደገፉት። ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያ፥ ነቢዩም ናታን፥ ሺምዒና ሬዒ፥ የዳዊትም ተዋጊዎች ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም። አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዔንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይጋ ሠዋ፥ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባርያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም። ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት፦ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የሐጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን? አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ። ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባርያህ፦ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው። እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።” ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ እልፍኝ ገባች፥ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሹኔማይቱም አቢሻግ ታገለግለው ነበር። ቤርሳቤህም አጎንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፥ ንጉሡም፦ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አለ። እርሷም አለችው፦ “ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባርያህ፦ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ በጌታ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፥ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፥ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፥ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፥ ባርያህን ስሎሞንን ግን አልጠራውም። አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዐይን ይመለከትሃል። ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቆጠራለን።” እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ። ለንጉሡም፦ “እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቷል” ብለው ነገሩት፥ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ። ናታንም አለ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ፦ ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን? እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን። ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፥ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ፦ ‘አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ’ ይላሉ። ነገር ግን እኔን ባርያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባርያህንም ሰሎሞንን አልጠራም። በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባርያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?” ንጉሡም ዳዊት፦ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች። ንጉሡም፦ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ባዳነኝ በሕያው ጌታ ቃል እገባለሁ! በእውነት ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በጌታ እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ” ብሎ ማለ። ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና፦ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘለዓለም በሕይወት ይኑር!” አለች። ንጉሡም ዳዊት፦ “ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ። ንጉሡም አላቸው፦ “የጌታችሁን ባርያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፥ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቀቡት፥ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ፥ ‘ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ’ በሉ። በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፥ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፥ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።” የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፦ “ያበጅ ያድርግ፥ የጌታዬም የንጉሥ ጌታ ይህን ይናገር። ንጉሥ ሆይ! ጌታ ከአንተ ጋር እንደሆነ ሁሉ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ መንግሥቱንም በዘመንህ ከነበረው የበለጠ ታላቅ ያድርገው!” አለው። ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት። ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅባቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፥ ቀንደ መለከትም ነፉ፥ ሕዝቡም ሁሉ፦ “ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ!” አሉ። ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፥ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች። አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፥ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ፦ “ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድነው?” አለ። እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፥ አዶንያስም፦ “አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ” አለ። ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው። ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ላከ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት። ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፥ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፥ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው። ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል። የንጉሡም ባርያዎች ገብተው፦ ‘እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ!’ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፥ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ። ንጉሡም ደግሞ፦ ‘ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይመስገን!’ አለ።” አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ። አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ። ለሰሎሞንም፦ “እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ፦ ‘ንጉሡ ሰሎሞን ባርያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ’ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል” አሉት። ሰሎሞንም፦ “እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጉር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፥ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደሆነ ይሞታል” አለ። ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፥ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም፦ “ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ዳዊት የሚሞትበት ወቅት በተቃረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ይህን የመጨረሻ ትእዛዝ ሰጠው፤ “እነሆ እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞት የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እንግዲህ በርታ! ቆራጥ ሰው ሁን፤ አምላክህ ጌታ እንድታደርግ የሚያዝህን ሁሉ አድርግ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ የምታደርገው ማንኛውም ነገር እንዲከናወንልህ በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፈቃድ ሁሉ ጠብቅ፤ በዚህ ሁሉ ነገር ታዛዥ ብትሆንለት፥ ‘ዘሮችህ በጥንቃቄ ተጠብቀው ቢኖሩ፥ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በፊቴ በቅንነት ቢመላለሱ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ነግሦ የሚገዛ ዘር አላሳጣህም’ ብሎ ጌታ የነገረኝን የተስፋ ቃል ይፈጽማል። “የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የእስራኤል ሕዝብ የጦር መሪዎች ከነበሩት በኔር ልጅ አበኔርና በይቴር ልጅ ዐማሣ ላይ ያደረገውን ታስታውሳለህ፤ ሁለት በጦርነት ጊዜ ላፈሰሱት ደም በቀል በሰላም ጊዜ እነርሱን ገድሎ የወገቡን መታጠቂያ የእግሩን ጫማ በደም በክሎ በእኔ ላይ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ። እንግዲህ ባለህ ጥበብ፥ ሊፈጸም የሚገባውን ነገር አድርግ፤ ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንዲሞት አትፍቀድለት። “ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ የቸርነት ሥራ ስላደረጉልኝ ለገለዓዳዊው ለባርዚላይ ልጆች ግን መልካም ነገር በማድረግ ተንከባከባቸው፤ በማዕድህም ከሚመገቡት መካከል ይሁኑ። “ከዚህም ጋር መረሳት የሌለበት የብንያም ክፍል በሆነችው በባሑሪም ከተማ ውስጥ የሚኖረው የጌራ ልጅ ሺምዒ አለ፤ እርሱ ወደ ማሕናይም በሄድኩበት ቀን በእኔ ላይ የስድብ ውርጅብኝ አውርዶብኛል፤ ይሁን እንጂ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባገኘኝ ጊዜ እንደማላስገድለው በጌታ ስም ቃል ገብቼለት ነበር፤ አንተ ግን እርሱንም ከቅጣት ነጻ አታድርገው፤ ባለህ ጥበብ ምን መደረግ እንዳለበት አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ በሞት የሚቀጣ መሆኑንም አትዘንጋ።” ዳዊት ሞተ፤ የእርሱ ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ተቀበረ። ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት በድምሩ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ። ሰሎሞንም በአባቱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የመንግሥቱም ሥልጣን እጅግ የጸና ሆነ። የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እርሷም “ጉዳይህ ምንድነው?” አለችው። አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከጌታ ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።” ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድነው?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት። እርሷም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ እርሷም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድነው” አላት። እርሷም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው። ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በጌታ ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው። ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም” አለው። ስለዚህ ሰሎሞን አብያታርን የጌታ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዓይነት ጌታ በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ። በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ጌታ ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ። ኢዮአብ ወደ ጌታ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። እርሱም ወደ ጌታ ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ። በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው። ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፤ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም ጌታ ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የጌታ ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።” ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።” ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባርያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በጌታ ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። “ታዲያ፥ በጌታ ስም ከማልክ በኋላ ለምን መሐላውን አልጠበቅህም? ያዘዝኩህን ትእዛዝስ ለምን አላከበርክም? በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር ጌታ ራሱ ይቀጣሃል፤ እኔን ንጉሥ ሰለሞንን ግን ጌታ ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ። ሰሎሞን የግብጽን ንጉሥ ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፤ እርሷንም አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፥ የጌታን ቤትና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጽር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት። በዚያን ጊዜ በጌታ ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ሰሎሞን ጌታን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብ፥ ዕጣንም ያጥን ነበር። ታላቁ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕትን ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። በዚያች ሌሊት ጌታ በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው። ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት ደግ፥ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን ስታሳየው ኖረሃል፤ ዛሬም በእርሱ እግር ተተክቶ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል። አቤቱ፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ እኔ በዕድሜ አነስተኛ ነኝ፤ የአመራር ልምድም የለኝም፤ አንተ ግን በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል። እነሆ እኔ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል እገኛለሁ። ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በትክክለኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?” ሰሎሞን ይህን በመጠየቁ ጌታን ደስ አሰኘው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ስለ ጠየቅህ፥ እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደፊትም ሊያገኘው ከሚችለው የበለጠ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ። ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማንኛውም ሌላ ንጉሥ ያላገኘውን ብልጽግናና ክብር አበዛልሃለሁ። አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድና ለእኔም ብትታዘዝ፥ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።” ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለባለሟሎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ። አንድ ቀን ሁለት ጋለሞታዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ። ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ሆይ! ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር በዚያው በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ። እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች፤ በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም። ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጇ ሞተ። እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርሷ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጇን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጐኔ አስተኛችው። በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ የሞተ ሆኖ አገኘሁት፤ ትኲር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።” ሁለተኛይቱ ሴት ግን፥ “አይደለም! በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!” አለች። የመጀመሪያይቱ ሴት “አይደለም! የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው!” አለች። በዚህም ዓይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን “አንደኛዋ ‘በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!’ ትላለች፤ ሌላይቱ ደግሞ ‘አይደለም! የአንቺ ልጅ ሞቷል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው!’ ትላታለች አለ።” ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት። “በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቁረጡና ለእያንዳንዷ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ” ሲል አዘዘ። እውነተኛይቱ እናት ግን ለልጇ በመራራት አዝና፥ “ንጉሥ ሆይ! እባክህ ልጁን አትግደለው! ለእርሷ ይሰጣት!” አለች። ሌላይቱ ሴት ግን “ለእኔም ለእርሷም አይሁን! ለሁለት ይቆረጥ!” አለች። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን “ሕፃኑን አትግደሉት! እውነተኛይቱ እናት እርሷ ስለ ሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት!” ሲል አዘዘ። እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት። ንጉሡ ሰሎሞን በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ። የሾማቸው ባለ ሥልጣኖች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፤ እነርሱም፦ ዓዛርያስ የተባለው የሳዶቅ ልጅ፦ ካህን፤ ኤሊሖሬፍና አኪያ የተባሉት የሺሻ ልጆች፥ የቤተ መንግሥት ጸሐፊዎች፤ ኢዮሣፍጥ የተባለው የአሒሉድ ልጅ፥ ታሪክ ጸሐፊና የመዛግብት ኀላፊ። በናያ የተባለው የዮዳሄ ልጅ፦ የጦር ሠራዊት አዛዥ፤ ሳዶቅና አብያታር፦ ካህናት። ዓዛርያስ የተባለው የናታን ልጅ፦ የክፍላተ ሀገር ገዢዎች የበላይ ኀላፊ፤ የናታን ልጅ ካህኑ ዛቡድ፦ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ። አሒሻር የተባለው፦ የቤተ መንግሥት አገልጋዮች ኀላፊ፤ አዶኒራም የተባለው የዓብዳ ልጅ፦ የግዳጅ ሥራ ተቆጣጣሪ ነበሩ። ሰሎሞን በመላው እስራኤል ዐሥራ ሁለት የክፍላተ ሀገር ገዢዎችን ሾመ፤ የእነርሱም ተግባር ከየግዛታቸው ለንጉሡና ለንጉሡ ቤተሰብ ቀለብ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ማቅረብ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በዓመት ውስጥ ለአንድ ወር ቀለብ የማቅረብ ግዴታ ነበረባቸው። የእነዚህም ዐሥራ ሁለት የክፍላተ ሀገር ገዢዎችና የሚያስተዳድሩአቸውም ግዛቶች ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው፥ ቤንሑር፦ ኰረብታማ የሆነችው የኤፍሬም አገር ገዢ፤ ቤንዴቀር፦ የማቃጽ፥ የሻዓልቢም፥ የቤትሼሜሽ፥ የኤሎንና የቤት ሐናን ከተሞች ገዥ። ቤንሔሴድ፦ የአሩቦትና የሶኮ ከተሞች፥ እንዲሁም የመላው የሔፌር ግዛት አስተዳዳሪ። ጣፋት የተባለችውን የሰሎሞንን ሴት ልጅ አግብቶ የነበረው ቤን አሚናዳብ የመላው የዶር ግዛት አስተዳዳሪ። በዓና የተባለው የአሒሉድ ልጅ፦ የታዕናክና የመጊዶ ከተሞች፥ እንዲሁም በቤት ሻን አጠገብ ያለው ግዛት በሙሉ፥ በጻርታን ከተማ አጠገብ ያለው ግዛትና በኢይዝራኤል ከተማ በስተ ደቡብ ያለው ግዛት፥ እንዲሁም አቤልመሖላና ዮቅመዓም ተብለው እስከሚጠሩት ከተሞች ድረስ ያለው ግዛት ሁሉ አስተዳዳሪ። በገለዓድ ራሞት ቤን ጌቤር ተብላ የምትጠራው ከተማ፥ በገለዓድ የምናሴ ዘር የሆነው የያኢር ጐሣ ይዞታዎች የሆኑት መንደሮች፥ በባሳን አርጎብ ተብላ የምትጠራው ግዛት፥ እንዲሁም በሮቻቸው የነሐስ መወርወሪያ ባሉአቸው የቅጽር ግንቦች የተመሸጉ በድምሩ የስድሳ ታላላቅ መንደሮች አስተዳዳሪ። አሒናዳብ የተባለው የዒዶ ልጅ፦ የማሕናይም ክፍለ ሀገር ገዢ። ከሰሎሞን ሴቶች ልጆች መካከል ባስማት ተብላ የምትጠራውን አግብቶ የነበረ አሒመዓጽ፦ የንፍታሌም ግዛት አስተዳዳሪ። በዓና የተባለው የሑሻይ ልጅ፦ የአሴር ግዛትና የበዓሎት ከተማ ገዢ። ኢዮሣፍጥ የተባለው የፋሩሕ ልጅ፦ የይሳኮር ግዛት አስተዳዳሪ። ሳሚ የተባለው የኤላ ልጅ፦ የብንያም ግዛት አስተዳዳሪ። ጌቤር የተባለው የኡሪ ልጅ፦ በአሞራውያን ንጉሥ ሲሖንና በባሳን ንጉሥ ዖግ ትገዛ የነበረችው የገለዓድ ግዛት አስተዳዳሪ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን አስተዳዳሪዎች የሚቆጣጠር በመላ አገሪቱ ሌላ አንድ የበላይ ኀላፊ ነበር። የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ብዛት እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ነበር፤ እነዚህ ሁሉ እየበሉና እየጠጡ ዘወትር ደስ ይሰኙ ነበር። የሰሎሞንም ግዛት ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ግዛት፥ ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ወሰን ያለውን አገር ሁሉ ያጠቃልል ነበር፤ የእነዚህም አገሮች ሕዝቦች በጠቅላላ ሰሎሞን በነበረበት ዘመን ሁሉ ለእርሱ ተገዢዎች ሆነው ይገብሩለት ነበር። ሰሎሞንም በየቀኑ ለቀለብ የሚሆን አምስት ሺህ ኪሎ ያኽል ምርጥ ዱቄት፥ ዐሥር ሺህ ኪሎ ያኽል መናኛ ዱቄት። በበረት ውስጥ እየተመገቡ የደለቡ ዐሥር ሰንጋዎችና በግጦሽ መስክ ተሰማርተው የተመገቡ ኻያ ፍሪዳዎችና አንድ መቶ በጎች፥ ከዚህም ሌላ አጋዘኖች፥ የሜዳ ፍየሎች፥ ሚዳቋዎችና ምርጥ ወፎች ያስፈልጉት ነበር። ሰሎሞን ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ ያለውን ምድር ሁሉ ከቲፍሳሕ ከተማ ጀምሮ እስከ ጋዛ ከተማ ድረስ ይገዛ ነበር፤ ይህም ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኙትን ነገሥታትን ሁሉ ያጠቃልላል፤ ጐረቤቱ ከሆኑት አገሮችም ሁሉ ጋር በሰላም ይኖር ነበር። በኖረበትም ዘመን ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ መላው የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ያለ ስጋት በሰላም ይኖር ነበር፤ እያንዳንዱም ቤተሰብ የራሱ የሆነ የወይን ተክልና የበለስ ዛፍ ስለ ነበረው በእነዚህ ተክሎች ጥላ ሥር ያርፍ ነበር። ሰሎሞን ሠረገላ የሚስቡ አርባ ሺህ ቅልብ ፈረሶችና ለጦርነት የሚያገለግሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት። ለሰሎሞንና በቤተ መንግሥቱ ለሚቀለቡት ሁሉ የሚያስፈልገውን ምግብ የሚያቀርቡት ዐሥራ ሁለቱ የክፍላተ ሀገር ገዢዎች እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው ወር ምንም ነገር ሳያጓድሉ በወቅቱ ያመጡ ነበር። ከዚህም በቀር እያንዳንዱ ገዢ እንደ አስፈላጊነቱ የሚደርስበትን ሠረገላ ለሚስቡ ፈረሶችና ሌላም አገልግሎት ለሚያበረክቱ የጋማ ከብቶች ገብስና ገፈራ ያቀርብ ነበር። እግዚአብሔር ለሰሎሞን እጅግ አስደናቂ የሆነ ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሁም ወሰን የማይገኝለትን ዕውቀት ሰጠው። ሰሎሞን ከምሥራቅ አገርና ከግብጽም ጥበበኞች እጅግ የላቀ ጥበብ ነበረው። እርሱ ከሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ጥበበኛ ነበረ። ከኤዝራሐዊው ኤታን፥ የማሖል ልጆች ከሆኑት ከሄማን፥ ከካልኮልና ከዳርዓዕ የሚበልጥ ጥበበኛ ነበረ፤ ዝናውም ከፍ ብሎ በጐረቤት ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ አስተጋባ። ሦስት ሺህ ምሳሌዎችንና አንድ ሺህ አምስት የመዝሙር ድርሰቶችን ደረሰ፤ ሰሎሞን ከሊባኖስ ዛፍ ጀምሮ በቤት ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ድረስ ስለ ዛፎችና ስለ ተክሎች በምሳሌ እየመሰለ ተናግሮአል፤ እንዲሁም ስለ ልዩ ልዩ እንስሶች፥ ስለ ወፎች በሆዳቸው እየተሳቡ ስለሚሄዱ ፍጥረቶችና ስለ ዓሣዎችም አስተምሮአል። በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሥታት ስለ ሰሎሞን ጥበብ ሰምተው የእርሱን ጥበብ ያዳምጡ ዘንድ መልእክተኞቻቸውን ይልኩ ነበር። የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ከዳዊት ጋር ወዳጅነቱን አጽንቶ ቆይቶ ነበር፤ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት እግር መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መልእክተኞቹን ላከ። ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ላከ። “አባቴ ዳዊት በዙሪያው ከነበሩት የጠላት አገሮች ሠራዊት ጋር ሲዋጋ መኖሩን አንተ ራስህ ታውቀዋለህ፤ በጠላቶቹ ላይ ጌታ ድልን እስኪያጐናጽፈው ድረስ ለእግዚአብሔር ለጌታው ቤተ መቅደስ ለመሥራት አለመቻሉንም ታስታውሳለህ። አሁን ግን ጌታ እግዚአብሔር በሀገሬ ድንበር ዙሪያ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ምንም ዓይነት አደጋ የሚጥል ጠላት የለብኝም። ጌታ ለአባቴ ለዳዊት ‘ከአንተ በኋላ የማነግሠው ልጅህ ለእኔ ቤተ መቅደስ ይሠራልኛል’ ሲል ተስፋ ሰጥቶት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ለጌታ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት እነሆ፥ አሁን ወስኛለሁ። ስለዚህ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የሚቆርጡ ሰዎችን ወደ ሊባኖስ ላክልኝ፤ የእኔም ሰዎች ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ አደርጋለሁ፤ ለሰዎችህም አንተ የምትወስነውን ደመወዝ እከፍላለሁ፤ አንተ እንደምታውቀው የእኔ ሰዎች ስለ ዛፍ አቆራረጥ የአንተን ሰዎች ያኽል ዕውቀት የላቸውም።” ኪራምም የሰሎሞን መልእክት ሲደርሰው እጅግ ስለ ተደሰተ፥ “በእርሱ እግር ተተክቶ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ ይህን የመሰለ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ ጌታ ይመስገን!” አለ። ከዚህ በኋላ ኪራም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለሰሎሞን ላከ፦ “ያስተላለፍከው መልእክት ደርሶኛል፤ አንተ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባውን ግንድ አዘጋጅቼ አቀርብልሃለሁ። የእኔ ሰዎችም ግንዶቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ አንድነት ጠፍረው አስረውም አንተ ወደምትመርጠው ጠረፍ ተንሳፍፈው እንዲደርሱ ያደርጋሉ፤ በዚያም የእኔ ሰዎች ማሰሪያውን ፈተው ለአንተ ሰዎች ያስረክቡአቸዋል፤ አንተም በበኩልህ በቤተ መንግሥቴ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምግብ በመላክ ፍላጎቴን ታረካለህ።” በዚህ ዓይነት ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖስን ዛፍና የዝግባ ግንድ ሁሉ አቀረበለት። ሰሎሞንም በበኩሉ በኪራም ቤተ መንግሥት ውስጥ ላሉት ሰዎች ቀለብ የሚሆን ሁለት ሺህ ቶን ስንዴና አራት መቶ ሺህ ሊትር ንጹሕ የወይራ ዘይት በየዓመቱ ይሰጥ ነበር። ጌታ አስቀድሞ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከል ሰላም ስለ ነበረ ሁለቱም የጋራ ስምምነት ውል አደረጉ። ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል ሠላሳ ሺህ የግዳጅ ሠራተኞችን መለመለ። በእነርሱ ላይ አዶኒራም የተባለውን ሰው ኀላፊ አድርጎ ሾመ፤ ሠራተኞቹንም ዐሥር ዐሥር ሺህ አድርጎ በሦስት ቡድን በመክፈል እያንዳንዱ ቡድን ተራ ገብቶ አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠራ፥ ሁለት ወር ደግሞ በቤቱ እንዲያርፍ ወሰነ። ንጉሥ ሰሎሞን በኮረብታማው አገር ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ፥ የተፈለጠውን ድንጋይ ተሸክመው የሚያመጡ ሰባ ሺህ ሰዎችን መደበ። የእነዚህ ሠራተኞች የበላይ ሆነው ሥራውን የሚቆጣጠሩ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ሰዎችን አዘጋጀ። በዚህ ዓይነት ሠራተኞቹ በንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆኑ ታላላቅ ድንጋዮችን ፈለጡ። የሰሎሞንና የኪራም ጥበበኞች ሠራተኞችና እንዲሁም የቢብሎስ ሰዎች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ አዘጋጁ። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር የጌታን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። ለጌታ የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር። በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር። ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ከውስጥ ሰፋ፥ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት። የቤተ መቅደሱን ሕንጻ አስጠግቶ በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ። የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የሁለተኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከሰባ ሳንቲ ሜትር፥ የመጨረሻው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሦስት ሜትር ከዐሥር ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የእያንዳንዱም ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ። ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት፤ በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፥ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር። ተጨማሪ ሆኖ የተሠራው ሕንጻ የታችኛው ፎቅ መግቢያ በር የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል ነበር፤ እርሱም ከሁለተኛውና ከሦስተኛው ፎቅ ጋር የሚያገናኙት ደረጃዎች ነበሩት። በዚህ አኳኋን ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ለበደው። የእያንዳንዱ ፎቅ ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንጻ ከዋናው ሕንጻዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ሠረገሎች የተያያዘ ነበር። የጌታ ቃል ወደ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል መጣ፦ “ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት ሕጎቼን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቴን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል ለአንተ አጸናለሁ። በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም ከቶ አልለያቸውም።” በዚህ ዓይነት ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ። የቤተ መቅደሱ ግንብ ከውስጥ በኩል ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ተለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር። ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፤ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመቱ ዐሥራ ስምንት ሜትር ነበር። የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበደ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር። ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተ ኋላ በኩል የጌታ የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል ተሠራ። ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ሲሆን በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም በወርቅ በተለበጠው ውስጠኛ ክፍል መግቢያ በር ክፈፉንም በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የሚገኘውን መሠዊያ ጭምር መላውን ቤተ መቅደስ ከውስጥ በኩል በወርቅ ለበጠው። የእያንዳንዳቸው ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ፥ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ። የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፥ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው። የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፥ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዓይነት ነበሩና። የየአንዳንዱ ኪሩብ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር። ኪሩቤልንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር። ሁለቱንም ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው። የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል እንኳ በወርቅ ለበጣቸው። ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተከፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር። ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፥ ኪሩቤልን፥ የዘንባባ ዛፎቹን፥ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። እንዲሁም ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት። ሁለቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። እነርሱንም ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ። የጌታ ቤት መሠረት የተጣለው በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው ወር ነበር። ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ፥ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሥራ ልክ በታቀደው መሠረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሰባት ዓመት ነበር። ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፥ ወርዱ አምሳ ክንድ፥ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፥ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰ ሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፥ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፥ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ። “ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው። ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት። እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የጌታ ቤት ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ። ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ። ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ። ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጉልላቶችን ሠራ። በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ። በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጉልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር። እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጉልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ። ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዓይነት ተፈጸመ። ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር። ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጉንጉን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። እንግዲህ ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዓይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ። ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎችን ሠራ፤ እያንዳንዱም ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር። ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው። ሑራም ድስቶችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ፤ በዚህ ዓይነትም ለንጉሥ ሰሎሞን ሊሠራለት የጀመረውን የጌታን ቤት ሥራ ፈጸመ፤ ከሠራቸውም ነገሮች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ሁለቱ ምሰሶዎች፥ በምሰሶዎቹም ላይ የነበሩትን ማቶቶች የሚመስሉ ጉልላቶች፥ በምሰሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑት ሁለቱ መረቦች። በእያንዳንዱ ጉልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፥ በእያንዳንዱ ጉልላት ቅርጽ ላይ በሁለት ረድፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ፥ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርጾች። ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥ ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች። ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥ ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች። ድስቶቹ፥ መጫሪያዎቹና ጐድጓዳ ሳሕኖቹ፤ ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሑራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለ ንጹሕ ነሐስ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በብረት ማቅለጫ ስፍራ ነበር። ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፥ ሰሎሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፤ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያኽል እንደሆነ ተወስኖ አልታወቀም። ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰሎሞን የሚከተሉትን ዕቃዎች አሠራ፤ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ። በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተ ደቡብ፥ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፥ አበባዎች፥ የመብራት ቀንዲሎች፥ የእሳት መቆስቆሻዎች፥ ጽዋዎች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያዎች፥ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎች፥ ማንደጃዎች፥ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችና ለቤተ መቅደሱ ውጫዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የጌታ ቤት ሁሉንም ሥራ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለጌታ ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፥ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በጌታ ቤት ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት ለማምጣት፥ ወደ ቤተ መቅደሱም ለማስገባት፥ የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ። የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። የጌታን ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ እንዲሁም በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ፥ ሌዋውያንና ካህናት አመጡ። ንጉሥ ሰሎሞንና በፊቱ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ሕዝብ፥ ከእርሱ ጋር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ሆነው፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይቆጠር ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። ካህናቱም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት፥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ስለ ነበር ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን በኪሩቤል ተሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ይታይ ነበር፤ በውጭ በኩል ግን አይታዩም፤ እስከ ዛሬ ድረስም በዚያው ይገኛሉ። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ፥ ጌታ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ደመና የጌታን ቤት ሞላው። በደመናውም ውስጥ የነበረው የጌታ ክብር የጌታን ቤት ስለ ሞላው ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ አለ፥ “ጌታ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ አለ። እኔም አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ማደሪያ ቤት ሠርቼልሀለሁ፤ ለዘለዓለም ማደሪያህ ቦታም ይሆናል።” ንጉሥ ሰሎሞንም የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ወደ እነርሱ ፊቱን ዞር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ ባረከ። እንዲህም አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን በአፉ እንደ ተናገረ፥ በእጁም ፈጽሙአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ፥ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዓይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ።’ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር። ጌታም አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ለመስራት በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። ነገር ግን ለስሜ ቤት የሚሠራው ከአንተ የሚወለደው ልጅ እንጂ አንተ አይደለህም’። “እነሆ ጌታ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ ቦታ ተተክቼ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀመጥኩ፤ ጌታም ቃል እንደገባው፥ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ለስሙ ቤት ሠራሁ። ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ጌታ ያደረገው ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ማኖሪያ አዘጋጅቼአለሁ።” ከዚያም ሰሎሞን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉም በተገኙበት ተነሥቶ በጌታ መሠዊያ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ። እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፥ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ አገልጋዮችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፤ ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል የጠበቅህ፥ በአፍህ እንደተናገርከው ሁሉ እነሆ ዛሬ በእጅህ ፈጸምከው። አሁንም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ በፊቴ ትሄድ እንደነበረው ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ መቼም አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም! አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ። “በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! አቤቱ ጌታ፥ አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። ‘ስሜ ይጠራበታል’ ወዳልከው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ፤ አገልጋይህም በዚህ ስፍራ የምጸልየውን ጸሎት ስማ። አገልጋይህና ሕዝብህ እስራኤል በዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማን፤ ሰምተህም ይቅር በለን። “አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ አለመበደሉን በመሐላ እንዲያረጋግጥ ሲጠየቅ፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በሚገኘው መሠዊያ ፊት መሐላ ቢያደርግ፥ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ አድርግም፥ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ ስለአካሄዱም ቅጣው፤ ንጹሑንም ነጻ አውጣው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢመቱ፥ ነገር ግን ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሳቸው። “አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ። “በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር ቢመጣ፥ በውርጭ፥ በዋግና በአንበጣ ወይም በኩብኩባ መንጋ ቢትወረር፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ ልብን የሚያሸብር መራር ኀዘን ደርሶባቸው፥ ከማንም ሰው ወይም ከሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ቤተ መቅደስ እጃቸውን በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በደላቸውን ይቅር በል፤ እርዳቸው፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው። በዚህም ዓይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ። “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፥ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፥ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፥ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፥ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፥ አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ። “ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ። “መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቆጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥ ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥ ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው። ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤ እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው። “በጠሩህም ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።” ሰሎሞን ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላ እጆቹን እንደ ዘረጋ ተንበርክኮ ከነበረበት መሠዊያ ፊት ተነሥቶ ቆመ። ድምፁንም ከፍ በማድረግ በዚያ ተሰብስቦ በነበረው ሕዝብ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር በረከት እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ለሕዝቡ ሰላምን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ከሰጠውም መልካም ተስፋ ምንም የቀረ የለም። አምላካችን እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛ ጋርም ይኑር፤ ምንጊዜም፤ አይተወንም፤ አይጥለንም፤ ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን ትእዛዞች፥ ደንቦችና ሥርዓቶችን በመጠበቅ እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር እንድንችል ለእርሱ ታዛዦች እንድንሆን ያድርገን። የእኔ ያገልጋዩና የሕዝቡ የእስራኤል የየዕለት ፍላጎት ይሟላ ዘንድ እነዚህ ለእግዚአብሔር ያቀረብኳቸው ልመናዎች ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር አምላክ ይቅረቡ። በዚህ ዓይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱም ሌላ አምላክ አለመኖሩን ያውቃሉ፤ በዛሬው ቀን እንዳደረጋችሁት በድንጋጌው ትኖሩና ትእዛዞቹንም ታከብሩ ዘንድ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ።” ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና ከእርሱ ጋር እስራኤላውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችንና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዓይነት ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ። እንዲሁም በዚያኑ ቀን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል ቁርባንና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው። በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር። በሚቀጥለውም ቀን ሰሎሞን ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ ሁሉም ሰሎሞንን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስለ አደረገው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ብሎአቸው ወደየቤታቸው ሄዱ። ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱንና ሊሠራው የፈለገውን ሌላውንም ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፥ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት በገባዖን እንደ ተገለጠለት አሁንም እንደገና ተገለጠለት። “በፊቴ ያቀረብከውን ጸሎትና ልመና ሰምቼአለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን የሠራኸውን ቤተ መቅደስ ቀድሼዋለሁ፤ ዘወትርም እጠብቀዋለሁ። አንተ ግን አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በቅንነትና በታማኝነት እኔን ብታገለግል፥ የእኔን ሕግና ሥርዓት ብትጠብቅ፥ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብትፈጽም፥ ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘሮችህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም’ በማለት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል በመጠበቅ፥ ዙፋንህ በእስራኤል ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር አደርጋለሁ። ነገር ግን አንተ ወይም ዘሮችህ እኔን መከተል ትታችሁ የሰጠኋችሁን ሕጎችና ትእዛዞች ባትፈጽሙና ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ተነቃቅለው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ስሜ እንዲጠራበት የቀደስኩትንም ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በየአገሩ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እስራኤልን መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጓታል። ይህ ከፍ ከፍ ብሎ የሚታየው ቤተ መቅደስ ፈርሶ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ በዚያ በኩል የሚያልፉ ሰዎች ይህን አይተው በመደንገጥ ‘እግዚአብሔር ይህን አገርና ይህን ቤተ መቅደስ ለምን እንዲህ አደረገ?’ በማለት ይሳለቁበታል። ራሳቸው የሚሰጡትም መልስ ‘የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ምድር ያወጣ ጌታ አምላካቸውን በመተዋቸው ምክንያት ነው፤ ከዚህም በቀር ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት ትተው ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ የጥፋት መቅሠፍት ያመጣባቸውም ስለዚህ ነው’ የሚል ነው።” ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ኻያ ዓመት ነበር። የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዚህ ሁሉ ሥራ ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖስ ዛፍና ዝግባ ከብዙ ወርቅ ጋር ሰጥቶት ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ሰሎሞን በገሊላ ምድር የሚገኙትን ኻያ ታናናሽ ከተሞችን ለኪራም ሰጠው። ኪራምም ሄዶ ከተሞቹን አየ፤ ነገር ግን ደስ አላሰኙትም። ሰሎሞንን “ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ ከተሞች ለካ እነዚህ ናቸውን?” አለው፤ በዚህ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ ያ አካባቢ በሙሉ ካቡል እየተባለ ይጠራል። ኪራም ለሰሎሞን የላከለት ወርቅ አራት ሺህ ኪሎ ግራም ያኽል የሚመዝን ነበር። ለሰሎሞን ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱን፥ የኢየሩሳሌምን ቅጽር የሠሩለትና ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ያለውን ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ ሞልተው ያስተካከሉለት የጉልበት ሥራ ለመሥራት የሚገደዱ ሠራተኞች ነበሩ፤ እንዲሁም ሐጾር፥ መጊዶና ጌዜር ተብለው የሚጠሩ ከተሞችንም እንዲሠሩለት አደረገ። ቀደም ሲል የግብጽ ንጉሥ በጌዜር ላይ አደጋ ጥሎ፥ ነዋሪዎችዋን ከነዓናውያንን ገድሎ ከተማይቱንም አቃጥሎ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ሴት ልጁን ለሰሎሞን በዳረለት ጊዜ የጌዜርን ከተማ ማጫ አድርጎ ሰጣት። ሰሎሞንም ጌዜርንና የታችኛውን ቤትሖሮን እንደገና አሠራ። ባዕላት፥ በይሁዳ በረሓማ አገር የምትገኝ ታማር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች እንደገና ሠራ። እነዚህም የስንቅ ማከማቻዎች፥ ፈረሶችና ሠረገሎች የሚጠበቁባቸው፥ ከተሞችን ከተመ፤ ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም፥ በሊባኖስና በግዛቱ ሁሉ የሚፈልገውን ገነባ። ከእስራኤል ሕዝብ ያልሆኑትን ከአሞራውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤው ያውንና ከኢያቡሳውያን ሕዝቦች ሁሉ የተረፉትን፥ እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ለማጥፋት ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን እነዚህን እስከ ዛሬ እንደሚደረገው ሁሉ፥ ሰሎሞን ለግዳጅ ሥራ መለመላቸው። ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ወገን ማንንም ባርያ አድርጎ አላሠራም፤ እነርሱ ባለ ሥልጣኖች፥ ወታደሮች፥ የጦር መኰንኖች፥ የጦር አዛዦች፥ ሠረገላ ለሚነዱ ሁሉ ኀላፊዎችና ፈረሰኞች ሆነው ያገለግሉ ነበር። ሰሎሞን ለሚያከናውነው የሕንጻ ሥራ የጉልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለተመደቡት ሰዎች አምስት መቶ ኀምሳ ኀላፊዎች ነበሩአቸው። የግብጽ ንጉሥ ልጅ የነበረችው ሚስቱ ከዳዊት ከተማ ራሱ ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከተዘዋወረች በኋላ ሰሎሞን ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን ጐድጓዳ ስፍራ ተሞልቶ በመስተካከል እንዲሠራ አደረገ። ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በዓመት ሦስት ጊዜ ያቀርብ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ለእግዚአብሔር ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህም ዓይነት የቤተ መቅደሱ ሥራ ተፈጸመ። እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን በኤዶም ምድር በቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው በኤላት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። ንጉሥ ኪራምም ከሰሎሞን ሰዎች ጋር የሚያገለግሉ የሠለጠኑ መርከበኞችን ላከለት። እነርሱም በመርከብ ተጉዘው ወደ ኦፊር ምድር ከሄዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ሲመለሱ ከዐሥራ አራት ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ይዘውለት መጡ። ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫኑ ሽቶ፥ የከበረ ዕንቁና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በሐሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጉምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዓይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች። በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዓይነት፥ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የደንብ ልብሳቸውንም ዓይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞንንም እንዲህ አለችው፦ “ስለ ሥራህ ውጤትና ስለ ጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው! ነገር ግን እዚህ ድረስ መጥቼ በዐይኔ እስካየው ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አይሆንም፤ በእርግጥም ጥበብህና ሀብትህ በአገሬ ሳለሁ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል። በፊትህ ሁልጊዜ በመገኘት ጥበብ የሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ሰዎችህና ባለሟሎችህ እንዴት የታደሉ ናቸው! ጌታ አምላክህ ይመስገን! እርሱ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ በማድረግ በአንተ መደሰቱን ገልጦልሃል፤ ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ዘላለማዊ ስለ ሆነ ጽድቅና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎሃል።” ንግሥተ ሳባ ያመጣችለትን ስጦታ ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን አበረከተችለት፤ ይኸውም ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ዕንቁ ነበር፤ እርሷ ለሰሎሞን ያበረከተችው የሽቶ ብዛት ከዚያ በኋላ ከቀረበለት የሽቶ ገጸ በረከት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ነበር። ከኦፊር ወርቅ ያመጡለት የኪራም መርከቦች ከዚያው ከኦፊር ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቁ አምጥተውለት ነበር። ሰሎሞን ከዚሁ ሰንደል እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን መከታዎች፥ መዘምራን የሚያገለግሉባቸውን በገናዎችና መሰንቆዎች አሠራ፤ ይህም የሰንደል እንጨት ወደ እስራኤል አገር ከመጣው የሰንደል እንጨት ሁሉ የሚበልጥ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ይህን የመሰለ የሰንደል እንጨት ከቶ ታይቶ አያውቅም። ንጉሥ ሰሎሞን ከተለመደው የልግስና ስጦታው ጋር የሳባ ንግሥት የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚህ በኋላ ንግሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች። ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር። ይህም ሁሉ ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ ከንግድ ከሚገኘው ትርፍ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ጋር ተጨማሪ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን ጋሻ በሰባት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው። እንዲሁም ሦስት መቶ ታናናሽ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን በሁለት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው፤ እነዚህንም ሁሉ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው። እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው። ወደ ዙፋኑ መወጣጫ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ የዙፋኑ ጀርባ ራስጌው ክብ ነበር፤ በዙፋኑ ግራና ቀኝ የክንድ ማሳረፊያዎች ነበሩ፤ በክንድ ማሳረፊያዎቹ ጐን አንዳንድ የአንበሳ ምስሎች ቆመው ነበር። በየአንዳንዱ ደረጃ በሁለት በኩል አንዳንድ የአንበሳ ምስል በድምሩ ዐሥራ ሁለት የአንበሳ ምስሎች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በሌላ በየትኛውም አገር ተሠርቶ አይታወቅም። በሰሎሞን ዘመን ብር ምንም ዋጋ ስላልነበረው ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎች ሁሉና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ እንጂ ከብር አልተሠሩም፤ ሰሎሞን ከኪራም መርከቦች ጋር በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ ሌሎች የተርሴስ መርከቦችም ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመት ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር። በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ወደ እርሱ መምጣት ይፈልጉ ነበር። ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር። ሰሎሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉ ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም፥ ሌሎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ። በግዛቱም ዘመን ሁሉ በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅለው ሾላ ይቆጠር ነበር። ሰሎሞን ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ ያስመጣ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ፈረሶችን በገንዘብ ገዝተው ከቀዌ ያመጡለት ነበር። ሠረገሎችን ከግብጽ አገር በማስመጣት፥ ለእያንዳንዱ ሠረገላ ስድስት መቶ ጥሬ ብር፥ ለእያንዳንዱም ፈረስ አንድ መቶ ኀምሳ ጥሬ ብር ይከፍሉ ነበር፤ ከዚያም እነርሱ ለሒታውያንና ለሶርያ ነገሥታት ይሸጡላቸው ነበር። ሰሎሞን ብዙ የባዕዳን አገሮችን ሴቶች አፈቀረ፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ንጉሥ ልጅ ሌላ የሒታውያን፥ የሞዓባውያን፥ የዐሞናውያን፥ የኤዶማውያንና የሲዶናውያን ሴቶች ልጆችን አፈቀረ። ጌታ ለእስራኤላውያን፥ “አሕዛብ ሴቶችን ያገባችሁ እንደሆነ በእርግጥ ወደ አማልእክታቸው ስለሚስቡአችሁ እነርሱን አታግቡ” ብሎ አስጠንቅቆአቸው ነበር፤ እነዚህን ሰሎሞን የወደዳቸው ሴቶች ጌታ እንዳይጋቡ ከከለከላቸው ሕዝቦች መካከል ናቸው፤ ሰሎሞን ግን ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተሰባበረ። ሰሎሞን የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ እነርሱም ሰሎሞንን ከጌታ እንዲርቅ አደረጉት። በተለይም በዕድሜ እየሸመገለ በሄደ መጠን ለባዕዳን አማልክት እንዲሰግድ አደረጉት፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። የሲዶናውያን ሴት አምላክ ለነበረችው ለዐስታሮትና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለአጸያፊው ለዐሞናውያን አምላክ ሰገደ። በደል በመሥራትም ጌታን አሳዘነ፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በቅንነት በመከተል ረገድ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ተራራ ላይ አጸያፊዎች ለሆኑት ኬሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአባውያን አምላክና ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞናውያን አምላክ የመስገጃ ስፍራዎችን አዘጋጀላቸው። እንዲሁም የባዕዳን አገሮች ሚስቶቹ ለየአማልክታቸው ዕጣን የሚያጥኑባቸውንና መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸውን ስፍራዎች ሠራ። ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ጌታ ልቡ ስለሸፈተ፥ እግዚአብሔር ተቈጣው። ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፥ ሰሎሞን የጌታን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ እንዲህም አለው፤ “ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ሆን ብለህ ስላፈረስክና ሕጌንም ስላልፈጸምክ፥ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ ልሰጠው ወስኛለሁ። ይሁን እንጂ ለአባትህ ለዳዊት ስል ይህን የማደርገው አንተ ባለህበት ዘመን ሳይሆን በልጅህ መንግሥት ጊዜ ይሆናል። ከልጅህም ቢሆን መንግሥቱን በሙሉ አልወስድበትም፤ ለአገልጋዬ ለዳዊትና ለራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል አንድ ነገድ እተውለታለሁ።” ስለዚህም ጌታ የኤዶም ንጉሣዊ ቤተሰብ ወገን የሆነውን ሀዳድን በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣበት። ዳዊት ከኤዶማውያን ጋር ይዋጋ በነበረ ጊዜ የጦር አዛዡ ኢዮአብ የሞቱትን ለመቅበር ወጥቶ የኤዶማውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ ፈጅቶ ነበር። ኢዮአብና የእስራኤል ሠራዊት የኤዶምን ወንዶች ልጆች ገድለው እስኪጨርሱ ድረስ ስድስት ወራት በዚያ ቆይተዋል። ከሞት የተረፉት ሀዳድና ወደ ግብጽ ሸሽተው የሄዱ ጥቂቶች ኤዶማውያን የአባቱ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜ ሀዳድ ገና ሕፃን ነበር። እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ በዚያም ጥቂቶች ሰዎች ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ግብጽ ተጉዘው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም ለሀዳድ መሬትና አንድ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ ምግብ ፈቀደለት። ሀዳድም የንጉሡ ወዳጅ ሆነ፤ ንጉሡም የሚስቱን የጣፍኔስን እኅት ለሀዳድ ዳረለት። እርሷም ገኑባት ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርሱንም ንግሥቲቱ ወስዳ በቤተ መንግሥት አሳደገችው፤ ከንጉሡም ወንዶች ልጆች ጋር አብሮ ኖረ። ሀዳድ በግብጽ ሳለ የንጉሥ ዳዊትንና የሠራዊቱን አዛዥ የኢዮአብን መሞት በሰማ ጊዜ “ወደ አገሬ ተመልሼ እንድሄድ አሰናብተኝ” ሲል ንጉሡን ጠየቀ። ንጉሡም “ስለምን ትሄዳለህ? ወደ አገርህ ለመሄድ ያሰብከው ከቶ ምን ጎድሎብህ ነው?” አለው። ሀዳድም “ምንም የተጓደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ ወደ ትውልድ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ” ሲል ለንጉሡ መለሰ፤ እንደገናም ጌታ ረዞን ተብሎ የሚጠራውን የኤሊዓዳን ልጅ በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣ፤ ረዞን የጾባ ንጉሥ ከነበረው ከጌታው ከሀዳድዔዜር ኮብልሎ፥ የሽፍቶች አለቃ ሆኖ ነበር፤ ይህም የሆነው ዳዊት ሀዳድዔዜርን ድል ነሥቶ የእርሱ ጦር ተባባሪዎች የሆኑትን ሶርያውያንን ከፈጀ በኋላ ነበር፤ ረዞንና ተከታዮቹም ወደ ደማስቆ ሄዱ፤ በዚያም ሲኖሩ እርሱን የሶርያ ንጉሥ እንዲሆን አደረጉት። ሰሎሞን በኖረበት ዘመን ሁሉ ሃዳድ ካደረሰበት ችግር በተጨማሪ ረዞን የእስራኤል ጠላት ሆነ። ስለዚህ ረዞን በሶርያ ላይ ገዢ ሆኖ በእስራኤል ላይ ጠላትነቱን ቀጠለ። በሰሎሞን ላይ ያመፀው ሌላው ሰው በኤፍሬም ጸሬዳ ተብላ የምትጠራው ክፍለ ሀገር ተወላጅ የሆነ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነው፤ እርሱም ከሰሎሞን አገልጋዮች አንዱ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ ተብላ የምትጠራ ባሏ የሞተባት ሴት ነበረች። ኢዮርብዓም ለዐመፅ የተነሣሣበትም ታሪክ እንደሚከተለው ነው፥ በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ በመሙላት እየደለደለና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጽሮች እየጠገነ በማደስ ላይ ነበር። ኢዮርብዓም ከፍ ያለ የሥራ ችሎታ ያለው ወጣት ነበር፤ ሰሎሞንም ይህ ወጣት ትጉህና ብርቱ ሠራተኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ በምናሴና በኤፍሬም ነገዶች ግዛት ውስጥ ባሉት ገባሮች ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው። አንድ ቀን ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በጉዞ ላይ ሳለ አዲስ መጐናጸፊያ የለበሰ፥ ከሴሎ የመጣው ነቢዩ አኪያ ከከተማ ውጪ መንገድ ላይ ብቻውን አገኘው። አኪያም የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ አውልቆ ከዐሥራ ሁለት ቆራረጠው። ኢዮርብዓምንም እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቁራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ‘መንግሥትን ከሰሎሞን ወስጄ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ለአገልጋዬ ለዳዊትና ከሌላው የእስራኤል ምድር የራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል ለሰሎሞን አንድ ነገድ አስቀርቼለታለሁ። ይህንንም የማደርገው ሰሎሞን እኔን ትቶ ባዕዳን የሆኑትን ዐስታሮት ተብላ የምትጠራውን የሲዶና አምላክ፥ ኬሞሽ ተብሎ የሚጠራውን የሞዓብ አምላክና ሚልኮም ተብሎ የሚጠራውን የዐሞን አምላክ ስላመለከ ነው፤ ሰሎሞን ለእኔ ታዛዥ አልሆነም፤ እርሱ አባቱ ዳዊት ለእኔ ይታዘዝ እንደ ነበር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ባለመጠበቁ በድሎአል። ይሁን እንጂ ከሰሎሞን መንግሥትን በሙሉ አልወስድበትም፤ በሕይወት እስካለም ድረስ በሥልጣን እንዲቆይ አደርገዋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ለመረጥኩትና ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ለፈጸመው ለአገልጋዬ ለዳዊት ስል ነው። ስለዚህ መንግሥትን ከሰሎሞን ልጅ ወስጄ ለአንተ ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። ይሁን እንጂ ስሜ እንዲጠራባት በመረጥኳት በኢየሩሳሌም አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ አንድ ዘር ይኖረው ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። ኢዮርብዓም ሆይ! እኔ አንተን የእስራኤል ንጉሥ አደርግሃለሁ፤ አንተ በወደድከው ግዛት ሁሉ ላይ መሪ ትሆናለህ። አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው በፍጹም ልብህ ብትታዘዘኝ፥ በሕጎቼና በትእዛዞቼ ጸንተህ ብትኖር፥ በእኔ ፊት ሞገስ ብታገኝ፥ እኔ ዘወትር ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥም አደርግሃለሁ፤ ለዳዊት ባደረግሁት ዓይነት ዘሮችህ ከአንተ በኋላ እንደሚነግሡ አረጋግጥልሃለሁ። በሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት የዳዊትን ትውልዶች እቀጣለሁ፤ ይሁን እንጂ የምቀጣቸው ለዘለዓለም አይደለም።’” ከዚህም የተነሣ ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ሞከረ፤ ነገር ግን ኢዮርብዓም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በመኰብለል አመለጠ፤ ሰሎሞንም እስከሞተበት ጊዜ ድረስ እዚያው ቆየ። ሰሎሞን ያደረገው ሌላው ነገር፥ ያከናወነው ተግባርና ጥበቡ ሁሉ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቧል። ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነው። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሞተ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓምም በአባቱ በሰሎሞን እግር ተተክቶ ነገሠ። ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፤ በዚያም እርሱን ለማንገሥ የፈለጉ በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ እስራኤላውያን ተሰብስበው ይጠብቁት ነበር። ከንጉሥ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ በዚያው በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ መጣ። እርሱንም በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ ነገዶች መልእክት ልከው አስጠሩት፤ ከእርሱም ጋር አብረው ወደ ሮብዓም በመቅረብ፥ “አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖ አስጨንቆን ነበር፤ አሁን ይህን ከባድ ሸክም ብታቃልልልንና ኑሮአችንን ብታሻሽልልን እኛ ለአንተ እንገዛልሃለን” አሉት። ሮብዓምም “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱ የሰሎሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ “እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሽማግሌዎቹም “ዛሬ ለእነዚህ ሰዎች ታዛዥ ሆነህ ብታገለግላቸውና ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ ብትሰጣቸው፥ እነርሱም ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ሮብዓም ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት አብሮ ዐደጎቹ ወደነበሩት፥ አሁን ደግሞ አማካሪዎቹ ወደ ሆኑት ወጣቶች ዘንድ ሄዶ፤ “ላደርገው ስለሚገባኝ ነገር ምን ትመክሩኛላችሁ? የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝስ ሰዎች ምን መልስ ልስጣቸው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንተ የምትሰጣቸው መልስ ይህ ነው፤ ‘የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች! አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ ይኸውም አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!’” ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ሮብዓም በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ እርሱ መጡ። ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ውድቅ አድርጎ ሕዝቡን በማመናጨቅ መናገር ጀመረ። ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!” ሲል መለሰላቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ጌታ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ንጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን ሐሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት ጌታ ይህን ለውጥ ለማድረግ ስለ ወሰነ ነው። ሕዝቡ፥ ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄውን እንዳልተቀበለው በተገነዘበ ጊዜ “ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ከዳዊት ጋር ምን ርስት አለን፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደየድኳንኖችህ ሂድ! ዳዊት ሆይ የራስህን ቤት ጠብቅ!” ብለው መለሱለት። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደየቤቱ ሄደ። ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖሩት ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ ኀላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህን ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊ ክፍል እስራኤል በሚል ስም በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ። እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመልሶ መምጣቱን በመገንዘብ ወደ ጉባኤአቸው ጠርተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፤ ለዳዊት ትውልዶች ታማኝ ሆኖ የቀረም የይሁዳ ነገድ ብቻ ነበር። ሮብዓም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች ተውጣጥተው የተመለሱ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ምርጥ ወታደሮች ጠርቶ በአንድነት ሰበሰበ፤ ይህንንም ያደረገው የእስራኤልን ነገዶች ወግቶ ግዛቱን እንደገና በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዐቅዶ ስለ ነበር ነው። ነገር ግን የጌታ ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማዕያ መጣ፥ ለሮብዓም እንዲሁም ለመላው የይሁዳና የብንያም ነገዶች፥ ለቀሩትም ሰዎች ሁሉ “ወንድሞቻችሁ በሆኑት በእስራኤላውያን ላይ አደጋ አትጣሉ፤ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ፤ ይህ የሆነውም በእኔ ፈቃድ ነው” ብሎ እንዲነግር አዘዘው። እነርሱም ሁሉ ለጌታ ቃል ታዛዦች በመሆን ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ። የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኘውን የሴኬምን ከተማ ምሽግ አድርጎ በዚያ ለጥቂት ጊዜ ቆየ፤ ከዚያም በመነሣት የፐኑኤልን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ “መንግሥቱ ለዳዊት ቤት የሚመለስ ይመስላል፤ ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፥ እንደገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።” በዚህም ጉዳይ ከመከረበት በኋላ የሁለት ጥጆችን ምስል ከወርቅ አሠርቶ ለሕዝቡ “ከዚህ በፊት ታደርጉት በነበረው ዓይነት ለመስገድ እስከ ኢየሩሳሌም መሄድ ይበቃችኋል፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነሆ እነዚህ ናቸው!” አለ። ከዚህም በኋላ ከወርቅ የተሠሩት ሁለት የኰርማ ምስሎች አንዱን በቤትኤል፥ ሁለተኛውንም በዳን አቆመ። ሰዎቹም እስከ ዳን ድረስ በጣዖቱ ፊት ተሰልፈው ሄዱ፤ በዚህም ሁኔታ ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ሠሩ። እንዲሁም ኢዮርብዓም በኮረብታዎች ላይ የማምለኪያ ስፍራዎችን አዘጋጅቶ የሌዊ ነገድ ካልሆኑ ቤተሰቦች መካከል ማንኛውንም ሰው ካህን አድርጎ ሾመ። ኢዮርብዓም በይሁዳ በሚደረገው በዓል ዓይነት ስምንተኛው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የባዕድ አምልኮ በዓል እንዲደረግ ወሰነ፤ ከወርቅ ላሠራቸውም ምስሎች በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይ ለጥጃው ምስል መሥዋዕት አቀረበ፤ በዚያም በቤትኤል ለማምለኪያ ባሠራቸው ስፍራዎች የሚያገለግሉ ካህናትን መደበ። በዓል እንዲሆን እርሱ ራሱ በወሰነው ስምንተኛው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን ወደ ቤትኤል ሄደ፤ በዚያም ለእስራኤል በወሰነላቸው መሠረት በዓል ለማክበር በመሠዊያው ላይ መሥዋዕትን አቀረበ። ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በጌታ ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ ነቢዩም ጌታ ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! ጌታ ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። ጌታ ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’” አለ። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። የእግዚአብሔርም ነቢይ በጌታ ስም እንደ ተናገረው መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ ጌታ ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል” ሲል መለሰለት። ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ። በዚያን ጊዜ በቤትኤል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ወንዶች ልጆቹ ወደ እርሱ ቀርበው፥ ከይሁዳ የመጣው ነቢይ በቤትኤል ስላደረገውና በንጉሥ ኢዮርብዓምም ላይ ስለ ተናገረው ቃል ሁሉ አወሩለት። አባታቸውም “ታዲያ ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ከዚያ ተነሥቶ በየትኛው መንገድ ሄደ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም የሄደበትን መንገድ በማመልከት አሳዩት። ከዚህም በኋላ እርሱ “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ ልጆቹም አህያውን ጭነውለት ሽማግሌው ነቢይ በአህያው ላይ ተቀምጦ፥ ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አቅጣጫ ይዞ ተከተለው፤ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው። ሽማግሌውም “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት። ሽማግሌውም “ወደ ቤቴ መጥተህ ከእኔ ጋር እህል ብላ” አለው። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከአንተ ጋር አብሬ መመለስ አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት እህልም ውሃም አልቀምስም። በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል።” ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከጌታ የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ነገር ግን ዋሽቶ ነበር። ስለዚህ እርሱም ከእርሱ ጋር አብሮት ወደ ቤቱ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ዳቦ በላ፥ ውሀም ጠጣ። በገበታም ቀርበው ሳሉ የጌታ ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤ ከይሁዳ ለመጣው ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ አለው፤ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ጌታ አምላክህ ያዘዘህን ትእዛዝ ባለመታዘዝ የጌታን ቃል አላከበርክም። ይህን በማድረግ ፈንታ እኔ በዚያ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳትቀምስ ወዳዘዝኩህ ቦታ ተመልሰህ በላህ፤ ይህንንም በማድረግህ ምክንያት ትገደላለህ፤ ሬሳህም በቤተሰብህ መቃብር አይቀበርም።’” የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፥ ያ መልሶ ያመጣዉ ነቢይ አህያውን ጫነለት። እርሱም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በመንገድም አንበሳ አገኘውና ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆመው ነበር። አንዳንድ ሰዎች በዚያ በኩል ሲያልፉ አጠገቡ ከቆመው አንበሳ ጋር ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ አዩ፤ ሽማግሌው ነቢይ ወደሚኖርበት ወደ ቤቴል ከተማ መጥተው አወሩ። ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን በሰማ ጊዜ “ይህ የጌታን ቃል ያቀለለው ያ ጌታ ሰው ነው፤ ጌታ ባስጠነቀቀው መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ። ከዚህም በኋላ ልጆቹን “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት፤ በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ የነቢዩንም ሬሳ አህያውና አንበሳው እስከ አሁን በአጠገቡ እንደ ቆሙ በመንገድ ላይ ተጋድሞ አገኘው። አንበሳውም የነቢዩን ሬሳ አልበላም፤ በአህያውም ላይ አደጋ አልጣለበትም ነበር። ነቢዩም ሬሳውን አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነው፤ እንዲለቀስለትና እንዲቀበር ወደ ቤትኤል መልሶ ወሰደው፤ በገዛ ራሱም ቤተሰብ መቃብር ቀበረው፤ እነርሱም “ወንድሜ ሆይ! ወንድሜ ሆይ!” እያሉ አለቀሱለት። ከቀብሩም ሥነ ሥርዓት በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ስሞት በዚሁ መቃብር ቅበሩኝ፤ ሬሳዬንም ከእርሱ ሬሳ አጠገብ አጋድሙት፤ በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይና በሰማርያ ታናናሽ ከተሞች በየኮረብታው ባሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ከጌታ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት የተናገረው የትንቢት ቃል በእርግጥ ይፈጸማልና።” ይህም ሁሉ ሆኖ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሚያደርገው ክፉ ነገር ሁሉ አልተመለሰም፤ ይልቁንም እርሱ በሠራቸው መሠዊያዎች የሚያገለግሉ ከሌዊ ዘር ውጪ ከሆኑ ቤተሰቦች መምረጡን ቀጥሎ ካህን ለመሆን ከፈለገ ማንኛውንም ሰው ይሾመው ነበር፤ ይህም ኃጢአቱ ለሥረወ መንግሥቱ መጥፋትና በሙሉ ለመደምሰሱ ምክንያት ሆነ። በዚያን ጊዜ የንጉሥ ኢዮርብዓም ወንድ ልጅ አቢያ ታሞ ነበር። ስለዚህ ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፦ “የእኔ ሚስት መሆንሽን ማንም እንዳያውቅ ልብስሽን ለውጠሽ ሌላ ሴት በመምሰል እኔ የእስራኤል ንጉሥ እንደምሆን የትንቢት ቃል የተናገረው ነቢዩ አኪያ ወደሚኖርባት ወደ ሴሎ ሂጂ።፤ ዐሥር እንጀራ፥ ጥቂት ሙልሙል ዳቦና አንድ ገንቦ ማር ውሰጂለት፤ ስለ ልጁ ሁኔታ እርሱ ይነግርሻል።” ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ይህን ሁሉ አዘጋጅታ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች፤ ነቢዩ አኪያም በዕድሜው ከመሸምገሉ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዘው ነበር። ይሁን እንጂ የኢዮርብዓም ሚስት ስለታመመው ልጇ ልትጠይቀው እንደምትመጣና ምን ሊነግራት እንደሚገባውም ጌታ አስቀድሞ ለነቢዩ አኪያ ገልጦለት ነበር። የኢዮርብዓም ሚስት እዚያ በደረሰች ጊዜ ሌላ ሴት ለመምሰል ሞከረች። ነገር ግን ነቢዩ አኪያ ወደ በሩ ስትቀርብ የኮቴዋን ድምፅ ሰምቶ እንዲህ አላት፥ “ግቢ! የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ ሌላ ሴት ለመምሰል ስለምን ሞከርሽ? ለአንቺ እነግርሽ ዘንድ የታዘዝኩት አሳዛኝ ዜና አለ። ወደ ኢዮርብዓም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለውን ንገሪው፤ ቃሉም ይህ ነው፤ ‘ከሕዝብ መካከል መርጬ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ። መንግሥትንም ከዳዊት ትውልድ ወስጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ ይሁን እንጂ አንተ ለእኔ ፍጹም ታማኝ ሆኖ ትእዛዞቼን እንደ ጠበቀውና እኔ ደስ የምሰኝበትን ነገር ሁሉ ያደርግ እንደነበረው እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ሆነህ አልተገኘህም። ይልቁንም ከአንተ በፊት መሪዎች ከነበሩ ሰዎች የከፋ ኃጢአት ሠራህ፤ እኔንም ትተህ ጣዖቶችና ከብረት የተቀረጹ ምስሎችን ለማምለክ በመሥራትህ ቁጣዬን አነሣሥተሃል፤ በዚህ ምክንያት እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ ከቤቱም ነጻም ሆነ ባርያ፥ ወንድ ልጅንም ሁሉ ከእስራኤል አጠፋለሁ፤ ፋንድያን አቃጥለው እንደሚጨርሱት የኢዮርብዓምን ቤት አወድማለሁ። በከተማይቱ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ ገላጣ በሆነው ገጠር የሚሞቱትንም አሞራ ይበላቸዋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ ነኝ።’” አኪያም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል ለኢዮርብዓም ሚስት እንዲህ አላት፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ ወደ ከተማም እንደ ገባሽ ወዲያውኑ ልጁ ይሞታል። እስራኤላውያንም ሁሉ በማዘን አልቅሰው ይቀብሩታል፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የተደሰተበት ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ከኢዮርብዓምም ቤተሰብ መካከል ሥርዓተ ቀብር በሚገባ የሚፈጸምለት እርሱ ብቻ ይሆናል። ጌታ ለራሱ የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ ዛሬ ያስነሣል፤ ይኸውም አሁን ነው። ጌታ እስራኤልን ይቀጣል፤ እርሷም በውሃ ምንጭ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸምበቆ ትንቀጠቀጣለች፤ አሽሪም ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ጣዖት በመሥራት ስላስቆጡት፤ የእስራኤልንም ሕዝብ ከዚህች ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ለም ምድር ነቃቅሎ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲበታተኑ ያደርጋል። ኢዮርብዓም ኃጢአት ስለሠራና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ስለ መራ፥ ጌታ እስራኤልን ይተዋል።” የኢዮርብዓም ሚስት ወደ ቲርጻ ተመልሳ ወደ ቤትዋ ደጃፍ እንደ ደረሰች ወዲያውኑ ልጁ ሞተ። ጌታ ለአገልጋዩ ለነቢዩ አኪያ በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በኀዘን አልቅሰው ቀበሩት። ንጉሥ ኢዮርብዓም ያደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ፥ የተዋጋቸው ጦርነቶችና አገዛዙም እንዴት እንደ ነበር ሁሉም ነገር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢዮርብዓም ንጉሥ ሆኖ ኻያ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ሞቶ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ ናዳብ ተተክቶ ነገሠ። የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመቱ ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን ጌታ ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች። የይሁዳ ሕዝብ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ የቀድሞ አባቶቹ ሲያደርጉት ከነበረው ይበልጥ በክፉ ሁኔታ በራሱ ላይ የጌታ ቁጣ አነሣሣ። ለባዕዳን አማልክትም የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ በኮረብታዎች ላይና በዛፎች ጥላ ሥር የሚያመልኩአቸውን የድንጋይ ቅርጾችንና የአሼራን ምስሎች አቆሙ፤ ከዚህም ሁሉ የከፋ በእነዚያ ሕዝቦች የማምለኪያ ስፍራዎች የቤተጣዖት አመንዝራዎች ነበሩ፤ እስራኤላውያን ወደ አገሪቱ ለመግባት እየገፉ በሄዱ መጠን ጌታ ከፊታቸው ነቃቅሎ ያባረራቸው አሕዛብ ይፈጽሙት የነበረውን አሳፋሪ ነገር ሁሉ የይሁዳም ሕዝብ ይፈጽመው ነበር። ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ። በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ተከማችቶ የነበረውንም ሀብት ሁሉ፥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ። እነርሱንም ለመተካት ንጉሥ ሮብዓም ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በር የመጠበቅ ኀላፊነት ባላቸው የዘብ አለቆች እንዲጠበቁ አደረገ። ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣ ቍጥር፥ የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ጋሻዎችን አንግበው ይቀበሉታል፤ ከሄደም በኋላ ጋሻዎቹን መልሰው በዘበኞች በሚጠበቁበት ክፍል ያኖሩአቸው ነበር። ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚህም ዘመን ሁሉ ሮብዓምና ኢዮርብዓም እርስ በርሳቸው በማያቋርጥ ጦርነት ላይ ነበሩ፤ ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታቱ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አቢያ ተተክቶ ነገሠ። የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች። ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አቢያም፥ እንደ ታላቁ አያቱ እንደ ዳዊት በጌታ ዘንድ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በመገኘት ፈንታ፥ አባቱ ሮብዓም ይፈጽመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራቱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም በሰላም እንዲጠብቅ ጌታ አምላኩ ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው። ጌታ ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሒታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር ጌታን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረጉና ትእዛዙንም በብርቱ ጥንቃቄ በመጠበቁ ነው። በአቢያ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፥ በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦርነት ሳያቋርጥ ቀጠለ። አቢያ ያደረገውም ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ። ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፤ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ፥ የቀድሞ አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ ጌታን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ንጉሥ አሳ በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የቤተ ጣዖትን አመንዝራዎችን ሁሉ ከሀገሪቱ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖቶችንም ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ። አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው። አሳ በኰረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ ባያስወግድም እንኳ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ለጌታ ታማኝ ሆኖ ኖረ። አባቱ ለጌታ የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ ከወርቅና ከብር አሠርቶ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ያደረጋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ። የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ በማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። ባዕሻ ይሁዳን በመውረር ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፤ ይህንንም ያደረገው ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባና ከዚያም ማንም እንዳይወጣ ለመከልከል ነው። በዚህም ምክንያት ንጉሥ አሳ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ በማውጣት በባለሟሎቹ እጅ፥ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የጣብሪሞን ልጅ፥ የሔዝዮን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዓይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላክኹልህ ገጸ በረከት ነው፤ እንግዲህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላክ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ እነርሱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘውን አገርና የንፍታሌምን ግዛት ሁሉ ያዙ። ንጉሥ ባዕሻ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ራማን የመመሸጉ ሥራ እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ፥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ ምጽጳንና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት። ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ የጀግንነት ሥራውና የመሸጋቸውም ከተሞች ጭምር በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ግን ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር። እርሱም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሁለት ዓመት ገዛ። ከእርሱም በፊት እንደነበረው እንደ አባቱ ኃጢአት በመሥራት የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ። የይሳኮር ነገድ የሆነው የአኪያ ልጅ ባዕሻ በናዳብ ላይ ዐምፆ ገደለው፤ በዚያም ጊዜ ናዳብና ሠራዊቱ በፍልስጥኤም ግዛት የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ በመክበብ ላይ ነበሩ። ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው፤ በዚህ ዓይነት ባዕሻ በናዳብ እግር ተተክቶ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። ወዲያውኑም የኢዮርብዓምን ቤተሰብ አባላት ሁሉ መፍጀት ጀመረ፤ ጌታ የሴሎ ተወላጅ በሆነው በአገልጋዩ በነቢዩ አኪያ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት የኢዮርብዓም ቤተሰብ በሙሉ ተገደሉ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም አልነበረም። ይህም የሆነበት ምክንያት ኢዮርብዓም ራሱ በሠራው ኃጢአትና የእስራኤልም ሕዝብ ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ ስላነሣሣ ነው። ናዳብ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። የይሁዳ ንጉሥ አሳ እና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ የማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባዕሻ በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ በማድረግ ኻያ አራት ዓመት ገዛ። ከእርሱም በፊት እንደነበረው እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ባዕሻ ራሱ ኃጢአት በመሥራትና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራት ጌታን አሳዘነ። የሐናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካይነት ጌታ ስለ ባዕሻ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ “እኔ ግን ከትቢያ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ ታዲያ አንተ እንደ ኢዮርብዓም ኃጢአት ሠራህ፤ ሕዝቤንም ወደ ኃጢአት መራህ፤ የኃጢአታቸውም ብዛት የእኔን ቁጣ አነሣሥቶአል። ስለዚህም ኢዮርብዓምን እንዳስወገድኩ አንተንና ቤተሰብህንም አስወግዳለሁ። በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ በየገጠሩም ሜዳ ላይ የሚሞተውን አሞራዎች ይበሉታል።” ባዕሻ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራዎቹም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ባዕሻ ሞተ፤ በቲርጻም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኤላ ነገሠ። ጌታ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻና በቤተሰቡ ላይ ያን የትንቢት ቃል የተናገረበት ምክንያት፥ ባዕሻ በፈጸመው ኃጢአት ጌታን ስላሳዘነ ነበር፤ ባዕሻ ጌታን ያስቆጣውም ከእርሱ ፊት የነበረው ንጉሥ ባደረገው ዓይነት ስለ ሠራው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን የኢዮርብዓምንም ቤተሰብ ሁሉ በመግደሉ ጭምር ነው። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባዕሻ ልጅ ኤላ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። የሠረገላዎቹ እኩሌታ ኀላፊ የሆነ ዚምሪ ተብሎ የሚጠራ ከጦር መኰንኖቹ አንዱ በንጉሡ ላይ ዐደመ፤ አንድ ቀን ኤላ በቲርጻ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው አርጻ ተብሎ በሚጠራው ባለሟሉ ቤት ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ዚምሪ ወደዚያ ቤት ሰተት ብሎ ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነበር። ዚምሪ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የባዕሻ ቤተሰብ አባላት የሆኑትን በሙሉ ገደለ፤ የባዕሻ ዘመድና ወዳጅ የሆነውን ወንድ ሁሉ በሞት ቀጣ። በዚህም ዓይነት ጌታ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባዕሻ ላይ ባናገረው ትንቢት መሠረት ዚምሪ የባዕሻን ቤተሰብ በሙሉ ፈጀ። ይህም የሆነበት ምክንያት ባዕሻና ልጁ ኤላ ጣዖት በማምለካቸውና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራታቸው የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ በማነሣሣታቸው ነው። ኤላ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዚምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በቲርጻ አድርጎ በእስራኤል ላይ ሰባት ቀን ብቻ ነገሠ፤ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጥኤም የምትገኘውን የጊበቶንን ከተማ ከበው ነበር። ዚምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን በሰሙ ጊዜ በዚያው እንዳሉ ወዲያውኑ የጦር አዛዣቸው የነበረውን ዖምሪን አነገሡ። ዖምሪና ወታደሮቹ የጊበቶንን ከበባ አቆሙ፤ ከዚያም ገሥግሠው ሄደው ቲርጻን ከበቡ። ዚምሪ ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ ክፍል ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበት፤ እርሱም በእሳት ነበልባል ተቃጥሎ ሞተ። ይህ የሆነበት ምክንያት በሠራው ኃጢአት ጌታን በማሳዘኑ ነው፤ እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና እስራኤልንም ወደ ኃጢአት በመምራቱ ምክንያት ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢዮርብዓም ጌታን አስቆጥቶአል። ዚምሪ የሠራው ሌላው ነገር ሁሉና ያደረገውም ሤራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ወገን በመለየት ከሁለት ተከፍለው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አንደኛው ክፍል ቲብኒ ተብሎ የሚጠራውን የጊናትን ልጅ ለማንገሥ ሲፈልግ፥ ሌላው ክፍል ደግሞ ዖምሪን ለመደገፍ ይሻ ነበር። በመጨረሻም የዖምሪ ደጋፊዎች አሸነፉ፤ ስለዚህም ቲብኒ ተገደለ፤ ዖምሪም ንጉሥ ሆነ። በዚህ ዓይነት አሳ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነግሦ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ዓመቶች የገዛውም መኖሪያውን በቲርጻ አድርጎ ነበር። ከዚያም በኋላ ሼሜር ተብሎ ከሚጠራው ሰው የሰማርያን ኰረብታ በስድስት ሺህ ጥሬ ብር ገዛ፤ ዖምሪ ኰረብታውን ከመሸገ በኋላ ከተማ ቆረቆረ፤ ከተማይቱንም ቀድሞ የኮረብታው ባለንብረት በሆነው በሼሜር ስም “ሰማርያ” ብሎ ሰየማት። ዖምሪ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ይበልጥ የከፋ ኃጢአት በመሥራቱ ጌታን አሳዘነ። እርሱ ራሱ በሠራው ኃጢአትና፥ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአትና ወደ ዋጋ ቢስ ጣዖት አምልኮ በመምራቱ ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢዮርብዓም የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ አነሣሣ። ዖምሪ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉና ያከናወነውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ዖምሪ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አክዓብ ነገሠ። አሳ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዖምሪ ልጅ አክዓብ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ እርሱም መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ኻያ ሁለት ዓመት ገዛ። አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የከፋ ኃጢአት በመሥራቱ ጌታን አሳዘነ፤ አክዓብ፥ ንጉሥ ኢዮርብዓም የሠራውን ኃጢአት እንደ ቀላል ነገር አድርጎ በመቁጠር እርሱም ራሱ ያንኑ ኃጢአት ሠራ፤ ከዚህም ሁሉ አልፎ የሲዶና ንጉሥ የኤትበዓል ልጅ የሆነችውን አረማዊቷን ኤልዛቤልን አገባ፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውንም ጣዖት አመለከ፤ ሰገደለትም። በሰማርያም ለባዓል ቤተ መቅደስ አሳንጾ መሠዊያ ሠራለት። አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስል አቆመ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩትም የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ የሚያነሣሣ ኃጢአት ሠራ። በአክዓብ ዘመነ መንግሥት ሒኤል ተብሎ የሚጠራ የቤትኤል ተወላጅ ኢያሪኮን መልሶ ሠራ፤ ጌታ በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው ቃል መሠረት ሒኤል የኢያሪኮን የመሠረት ድንጋይ በሚያኖርበት ጊዜ የበኩር ልጁ አቢራም ሞተበት፤ የቅጽርዋንም በሮች በሚሠራበት ጊዜ ታናሹ ልጁ ሠጉብ ሞተ። በገለዓድ የምትገኘው የቱቢ ተወላጅ የሆነውና ኤልያስ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ፤ ንጉሥ አክዓብን “በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር በሚቀጥሉት ዓመቶች በምድር ላይ ጠል ወይም ዝናብ እንደማይኖር እኔ በማገለግለው በእስራኤል አምላክ፥ በሕያው ጌታ ስም እነግርሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤልያስ መጣ። “ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ እዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ከሪት ተብሎ በሚጠራው ሸለቆ ተሸሸግ። የምትጠጣውንም ውሃ ከዚያው ወንዝ ታገኛለህ፤ ቁራዎችም ምግብ እንዲያመጡልህ አዝዣለሁ።” ኤልያስም ጌታ ባዘዘው መሠረት ሄዶ በከሪት ሸለቆ ተቀመጠ። ከወንዙም ውሃ ጠጣ፤ ቁራዎችም ዘወትር ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር። ዝናብ ጠፍቶ ድርቅ ከመሆኑ የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ። ከዚህ በኋላ ጌታ ኤልያስን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ከዚህ ተነሥተህ ሂድና በሲዶና በምትገኘው በስራጵታ ከተማ ተቀመጥ፤ እነሆ በዚያ የምትኖር አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ወደ ሰራጵታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም ቅጽር በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባሏ የሞተባት ሴት እንጨት ስትለቅም አይቶ “እባክሽ የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ” አላት። ውሃም ልታመጣለት በመሄድ ላይ ሳለች ወዲያውኑ ጠርቶ “እባክሽ በተጨማሪ ትንሽ እንጀራ አምጪልኝ” አላት። እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ምንም እንጀራ እንደሌለኝ በአምላክህ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፤ በዱቄት ዕቃዬ ውስጥ ካለችው ከአንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮዬ ውስጥ ካለችው ከጥቂት የወይራ ዘይት በቀር ምንም የለኝም፤ ወደዚህ የመጣሁት ትንሽ እንጨት ለቃቅሜ ወደ ቤቴ በመመለስ ይህችኑ ያለችኝን ትንሽ ዱቄት ለልጄና ለእኔ ለመጋገር ነው፤ ይህችም የመጨረሻ ምግባችን ናት፤ ከዚያም በኋላ በራብ ከመሞት አንተርፍም።” ኤልያስም እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትጨነቂ! ሄደሽ ምግብሽን አዘጋጂ፤ አስቀድመሽ ግን ከዚያችው ካለችሽ ዱቄት ለእኔ ትንሽ እንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ የቀረውንም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪው፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ‘ጌታ ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮው ዘይት አያልቅም።’” እርሷም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህም ዓይነት እርሷ፥ ቤተሰብዋና ኤልያስም ለብዙ ቀን የሚሆን በቂ ምግብ አገኙ። ጌታ በኤልያስ አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው አላለቀም። ከጥቂት ጊዜም በኋላ የዚያች ባሏ የሞተባት ሴት ልጅ ታመመ፤ ሕመሙም እየባሰበት ስለ ሄደ በመጨረሻ ሞተ። እርሷም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን?” ስትል ጠየቀችው። ኤልያስም “ልጅሽን ወደ እኔ አምጪው” አላት። ልጁንም ከዕቅፍዋ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አጋደመው። ከዚህ በኋላ ኤልያስ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታ አምላኬ ሆይ! ስለምን በዚህች ባሏ በሞተባት ሴት ላይ ይህን የመሰለ አሠቃቂ ነገር አደረግህ? እርሷ እኔን በማስተናገድ ታላቅ ቸርነት አድርጋልኛለች፤ ታዲያ አንተ ስለምን ልጇ እንዲሞት አደረግህ?” ሲል ጸለየ። ከዚህ በኋላ ኤልያስ በልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርሮ “ጌታ አምላኬ ሆይ! እባክህ ይህን ልጅ ከሞት አስነሣው!” ሲል ጸለየ። ጌታም የኤልያስን ጸሎት ሰማ፤ የልጁም እስትንፋስ እንደገና ተመልሶለት ዳነ። ኤልያስ ልጁን ከሰገነት ወደ ምድር ቤት አውርዶ ለእናቱ በመስጠት “ተመልከቺ፤ እነሆ ልጅሽ ከሞት ወደ ሕይወት ተመልሶአል!” አላት። ሴትዮዋም “እነሆ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህንና በአፍህ ያለው የጌታ ቃል እውነት እንደሆነ አሁን አወቅሁ!” ስትል መለሰችለት። ከብዙ ጊዜ በኋላ በሦስተኛው ዓመት ጌታ ኤልያስን “ሄደህ ራስህን ለንጉሥ አክዓብ ግለጥለት፤ እኔም በምድር ላይ ዝናብን አዘንባለሁ” አለው። ኤልያስም በታዘዘው መሠረት ወደ አክዓብ ሄደ፤ በዚህ ጊዜ በሰማርያ ረሀብ እጅግ ጸንቶ ነበር። ስለዚህም ንጉሥ አክዓብ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ ጌታን የሚፈራ መንፈሳዊ ሰው ነው። ኤልዛቤል የጌታን ነቢያት ታስገድል በነበረችበትም ጊዜ አብድዩ አንድ መቶ የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን ነቢያት ከሁለት ከፍሎ ኀምሳ፥ ኀምሳውን በዋሻዎች ከሸሸጋቸው በኋላ እህልና ውሃ በማቅረብ ይመግባቸው ነበር። አክዓብ አብድዩን “ፈረሶችንና በቅሎዎችን ከሞት የምናድንበት በቂ ሣር እናገኝ እንደሆን በምድሪቱ ወደሚገኘው ምንጭና ወንዝ እስቲ ሂድና እይ፤ ምናልባት እንስሶቻችንን ከሞት ማዳን እንችል ይሆናል” አለው። እያንዳንዳቸው በአገሪቱ ወደየትኛው ክፍል ሄደው መፈለግ እንዳለባቸው ከተስማሙ በኋላ አክዓብና አብድዩ ለየብቻቸው በሁለት አቅጣጫ ተሰማሩ። አብድዩ በሚሄድበት መንገድ ላይ ሳለ በድንገት ኤልያስን አገኘው፤ ኤልያስ መሆኑንም ስላወቀ በግንባሩ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ከነሣው በኋላ “ጌታዬ ኤልያስ! በእውነት አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “አዎ! እኔ ነኝ፤ እዚህ መሆኔን ሄደህ ለጌታህ ንገረው” ሲል መለሰለት። አብድዩም እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ አክዓብ እኔን ባርያህን ይገድለኝ ዘንድ በእጁ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን በደል ሠርቼ ነው? ንጉሡ አንተን ለማግኘት ፈልጎ በዓለም ላይ መልእክተኛ ያልላከበት አገር እንደሌለ በአምላክህ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፤ የአንድ አገር መሪ አንተ በአገሩ ውስጥ አለመኖርክን ባስታወቀው ቍጥር ንጉሥ አክዓብ የአንተን አለመኖር በመሐላ እንዲያረጋግጥለት ጠይቆአል። አሁን አንተ ግን ኤልያስ ተገኝቶአል ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ። እኔ ከዚህ እንደ ሄድኩ ወዲያውኑ የጌታ መንፈስ አንተን ወዳልታወቀ ቦታ ቢወስድህ እኔ ምን ይበጀኛል? አንተ በዚህ ቦታ መኖርኽን ለአክዓብ ነግሬው ሳያገኝህ ቢቀር እርሱ እኔን በሞት ይቀጣኛል፤ ከልጅነቴ ጀምሬ ጌታን የምፈራ ሰው መሆኔን አስታውስ። ደግሞስ ኤልዛቤል የጌታን ነቢያት ስታስገድል በነበረችበት ጊዜ አንድ መቶ የሚሆኑትን ነቢያት ከሁለት በመክፈል ኀምሳ ኀምሳውን በዋሻዎች ውስጥ ሸሽጌ እህልና ውሃ በማቅረብ ስመግባቸው መኖሬን አልሰማህምን? ታዲያ፥ አሁን አንተ እዚህ መሆንህን ሄደህ ለንጉሥ አክዓብ ንገር ትለኛለህን? ይህን ባደርግ ንጉሡ ይገድለኛል!” ኤልያስም “ዛሬ እኔ ለንጉሡ ራሴን እንደምገልጥለት በማገለግለውና ሁሉን ቻይ በሆነው በጌታ ስም ቃል እገባልሃለሁ!” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ አብድዩ ሄዶ ለንጉሥ አክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ተነሥቶ ኤልያስን ለመገናኘት ሄደ። አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜም “በእስራኤል ላይ ይህን ከባድ ችግር ያመጣህ አንተ ለካ እዚህ ነህን?” አለው። ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በመጣስ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው የባዕድ አምላክ ምስሎች በመስገድ ችግር የምታመጡ አንተና የአባትህ ቤተሰብ ናችሁ እንጂ እኔ በእስራኤል ላይ ችግር የማመጣ አይደለሁም! ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን ሁሉ እንዳገኛቸው በቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብልኝ፤ በንግሥት ኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያትንና አራት መቶ የአሼራ ነቢያትን ጭምር ይዘህ ና።” ስለዚህም አክዓብ ለእስራኤላውያን ሁሉና ለነቢያት በሙሉ ጥሪ አድርጎ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበሰቡ አስደረገ። ኤልያስም ወጥቶ ለሰዎቹ፦ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት ልብ ስታወላውሉ ትኖራላችሁ? እንግዲህ ጌታ እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱን አምልኩ! ወይም ባዓል እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱኑ አምልኩ!” አላቸው፤ ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱም። ከዚህ በኋላ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ “ከጌታ ነቢያት የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያት ግን እነሆ በዚህ አሉ፤ እንግዲህ ሁለት ኰርማዎችን አምጡና የባዓል ነቢያት አንዱን ወስደው ይረዱት፤ ሥጋውንም ቆራርጠው እንጨት በመረብረብ በዚያ ላይ ያኑሩት፤ ነገር ግን በእሳት አያቀጣጥሉት፤ እኔም ሁለተኛውን ኰርማ ወስጄ እንደዚሁ አደርጋለሁ። ከዚህ በኋላ የባዓል ነቢያት ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም ወደ ጌታ እጸልያለሁ፤ እሳትን ወደ መሥዋዕቱ በመላክ መልስ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።” ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በዚህ ሐሳብ መስማማቱን ገለጠ። ከዚህ በኋላ ኤልያስ የበዓልን ነቢያት “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ኰርማ መርጣችሁ በማረድ ወደ አምላካችሁ ጸልዩ፤ ነገር ግን እንጨቱን በእሳት አታቀጣጥሉ” አላቸው። እነርሱም የመጣላቸውን ኰርማ ወስደው ለመሥዋዕት አዘጋጅተው እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወደ ባዓል ጸለዩ። “ባዓል ሆይ! እባክህ ስማን!” እያሉም ጮኹ። በሠሩትም መሠዊያ እየዘለሉ ዞሩ፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኙም። እኩለ ቀን ሲሆን ኤልያስ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጸልዩ! እርሱ አምላክ አይደለም እንዴ እርሱ በሐሳብ ተውጦ ይሆናል! ወይም ራሱን ያዝናና ይሆናል! ወይም ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ይሆናል! ወይም ተኝቶ ያንቀላፋ ይሆናልና እንዲነቃ ቀስቅሱት!” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር። ስለዚህም የሐሰት ነቢያቱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጸለዩ በሥርዓታቸው መሠረት ደማቸው እስኪፈስ ድረስ በቢላዋና በጩቤ ሰውነታቸውን ያቆስሉ ነበር። እኩለ ቀን ካለፈም በኋላ የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ እየተራወጡ ይቀባጥሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምንም መልስ አላገኙም፤ ድምፅም አልተሰማም። ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የጌታ መሠዊያ በማደስ ሠራው። ጌታ ከዚያ በፊት “እስራኤል” ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ በተወለዱት በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ወሰደ። እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በጌታ ስም መሠዊያ ሠራ፤ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጉድጓድ ማሰ። እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኰርማውን በብልት በብልቱ ቆራርጦ በእንጨቱ ላይ ካኖረ በኋላ፥ “በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ “አሁንም ጨምሩበት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ እርሱም “አሁንም እንደገና አንድ ጊዜ ጨምሩ!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጉድጓዱንም ሞላው። ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንክን፥ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን፥ እኔም ይህን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፤ አምላኬ ሆይ! ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ስማኝ!” ከዚህ በኋላ ጌታ እሳትን ላከ፤ ያም እሳት መሥዋዕቱን፥ እንጨቱንና ድንጋዩን አቃጠለ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጉድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፤ ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ “ጌታ አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው!” አሉ። ኤልያስም “የባዓልን ነቢያት ያዙ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዘ፤ሕዝቡም በሙሉ ያዛቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ወንዝ እየመራ ወስዶ በዚያ ሁሉንም ገደላቸው። ከዚህ በኋላ ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን “እንግዲህ ሄደህ እህልና ውሃ ቅመስ፤ እኔ አሁን የከባድ ዝናም ነጐድጓድ ድምፅ መቃረቡን እየሰማሁ ነው” አለው። አክዓብ እህልና ውሃ ለመቅመስ ሲሄድ፥ ኤልያስ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ እዚያም በሁለቱ ጉልበቶቹ መካከል ራሱን ወደ መሬት ደፋ። አገልጋዩን፥ “ሂድና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት!” አለው። አገልጋዩም ሄዶ ሲመለስ “ምንም ነገር አይታየኝም” አለው፤ አገልጋዩ እየተመላለሰ ያይ ዘንድ ኤልያስ ሰባት ጊዜ አዘዘው። በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ ተመልሶ “ከአንድ ሰው መዳፍ የማትበልጥ ትንሽ ደመና ከባሕር ስትወጣ አየሁ” አለው። ኤልያስም “ወደ ንጉሥ አክዓብ ሂድና ‘ዝናቡ ሳያቋርጥህ በፍጥነት ወደ ሠረገላህ ገብተህ ወደ ቤትህ ተመልሰህ ሂድ’ ብለህ ንገረው” ሲል አዘዘው። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሰማዩ በጥቁር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱም ይነፍስ፥ ብርቱ ዝናብም ይዘንብ ጀመረ፤ ንጉሥ አክዓብም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ የጌታም ኃይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን በወገቡ ዙሪያ ጠበቅ አድርጎ በመታጠቅ እስከ ኢይዝራኤል መግቢያ በር ድረስ በአክዓብ ፊት ቀድሞ ይሮጥ ነበር። ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና የበዓልንም ነቢያት በሙሉ በሞት እንዴት እንደ ቀጣ ንጉሥ አክዓብ ለሚስቱ ለኤልዛቤል ነገራት። ስለዚህ እርሷ “በእነዚያ ነቢያት ላይ ያደረግኸውን እኔም ነገ ልክ በአሁኑ ሰዓት በአንተ ላይ ሳላደርግብህ ብቀር አማልክት በሞት ይቅሠፉኝ!” ስትል ወደ ኤልያስ የዛቻ መልእክት ላከች። ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ። አገልጋዩንም በዚያ ተወው። ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጉዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “ጌታ ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ። ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ። የጌታም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው። ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኃይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ። እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም ጌታ “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። ጌታም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ጌታ በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረብቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ ጌታ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ ጌታ ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ ጌታ ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ። ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔን እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ሲል መለሰ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “በደማስቆ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓ ተመልሰህ ሂድ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ አዛሄልን ቀብተህ በሶርያ ላይ አንግሠው። የኒምሺን ልጅ ኢዩንም ቀብተህ በእስራኤል ላይ አንግሠው፤ የአቤል መሖላ ተወላጅ የሆነውን የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕንም ቀብተህ በአንተ እግር ነቢይ እንዲሆን አድርገው። ከአዛሄል እጅ ከመገደል ተርፎ የሚያመልጠውን ማንኛውንም ሰው ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ እጅ የሚያመልጠውንም ኤልሳዕ ይገድለዋል። ይሁን እንጂ ለእኔ ታማኞች የሆኑ፥ ለባዓል ያልሰገዱና ምስሉንም ያልተሳለሙ ሰባት ሺህ ሰዎችን በእስራኤል ምድር በሕይወት እንዲተርፉ አደርጋለሁ።” ኤልያስ ከዚያ ከሄደ በኋላ የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ሁለት በሬዎች ጠምዶ ሲያርስ አገኘው፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ በዐሥራ አንድ ጥማድ በሬዎች የሚያርሱ ደቦኞች ነበሩ፤ ኤልሳዕም በመጨረሻው ዐሥራ ሁለተኛ ጥማድ ያርስ ነበር፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን አውልቆ በኤልሳዕ ላይ ደረበለት። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ወደ ኤልያስ በመሮጥ “አባትና እናቴን ስሜ እንድሰናበት ፍቀድልኝ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። ኤልያስም “እሺ፥ ተመልሰህ ሂድ፤ እኔ አልከለክልህም!” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ወደ ጥማድ በሬዎቹ ተመልሶ ዐረዳቸው፤ የተጠመዱበትንም ቀንበር በማንደድ ሥጋቸውን ቀቅሎ ለሰዎቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስን ተከትሎ በመሄድ ረዳቱ ሆነ። የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በአንድነት ሰበሰበ፤ ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ባሉአቸው ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ተደግፎ በመዝመት የእስራኤል ዋና ከተማ የሆነችውን ሰማርያን ከቦ አደጋ ጣለባት። ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቤንሀዳድ በከተማይቱ ወደሚገኘው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ፥ “ቤንሀዳድ እንዲህ ይላል ብሎ መልእክተኞችን ላከ፦ ብርህና ወርቅህ፥ ውብ የሆኑት ሚስቶችህና ጠንካሮች የሆኑ ልጆችህ የእኔ ናቸው።” አክዓብም “ለጌታዬ ለንጉሥ ቤንሀዳድ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ እኔና የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው።” አለ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ እነዚያው መልእክተኞች ከንጉሥ ቤንሀዳድ ሌላ ትእዛዝ ይዘው እንደገና ወደ አክዓብ መጡ፤ ትእዛዙም እንዲህ የሚል ነበር፤ “ብርህንና ወርቅህን፥ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድታስረክበኝ መልእክት ልኬብህ እንደ ነበር ይታወሳል። አሁን ደግሞ ቤተ መንግሥትህንና የባለሥልጣኖችህን ቤት ሁሉ በርብረው ዋጋ ያለውን ንብረት ሁሉ ይዘው እንዲመጡ የጦር መኰንኖቼን እልካለሁ፤ እነርሱም ነገ ጧት በዚሁ ሰዓት እዚያ ይደርሳሉ።” ንጉሥ አክዓብም የሀገሪቱን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ “ይህ ሰው ምን ዓይነት ጠብ እንደሚፈልግ ተመልከቱ። ከዚህ በፊት ሚስቶቼንና ልጆቼን፥ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው ጠይቆኝ ተስማምቼ ነበር” አላቸው። ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም “እርሱ ለሚልህ ነገር ሁሉ ግምት አትስጠው፤ እሺም አትበለው” አሉት። ስለዚህም አክዓብ ለቤንሀዳድ መልእክተኞች “ለጌታዬ ለንጉሡ፥ ከዚህ በፊት ባቀረብክልኝ ጥያቄ ተስማምቼ ነበር፤ አሁን ባቀረብክልኝ በሁለተኛው ጥያቄ ግን ልስማማበት አልችልም ብሏል ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ተመልሰው በመሄድ መልሱን ነገሩት፤ ቤንሀዳድም “በሰማርያ ለያንዳንዱ ወታደር አንዳንድ ጭብጥ ዐፈር ሊዳረስ እስከማይችል ድረስ ብዙ ወታደሮችን ባላሰልፍ አማልክት ይቅሠፉኝ!” ብሎ የዛቻ መልእክቱን መልሶ ላከበት። ንጉሥ አክዓብ መልእክተኞቹን “እውነተኛ ወታደር መደንፋት የሚገባው ከጦርነት ድል በኋላ እንጂ ከጦርነት በፊት አይደለም ብላችሁ ለንጉሥ ቤንሀዳድ ንገሩት” ሲል መለሰላቸው። ቤንሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቹ የሆኑ ሌሎችም ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው ሲጠጡ ሳሉ የአክዓብ መልእክት ደረሰ፤ በዚህን ጊዜ ቤንሀዳድ በከተማይቱ ላይ አደጋ ለመጣል እንዲዘጋጁ ትእዛዝ ሰጠ፤ ስለዚህም እነርሱ ፈጥነው በመንቀሳቀስ ቦታ ቦታቸውን ያዙ። በዚህን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ “ጌታ ‘ከቤንሀዳድ ሠራዊት ብዛት የተነሣ አትፍራ! እኔ ዛሬ በዚህ ሠራዊት ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርጋለሁ፤ አንተም ደግሞ እኔ ጌታ መሆኔን ታውቃለህ’ ይልሃል” አለው። አክዓብም “ግንባር ቀደም ሆኖ የሚዘምተው ማን ይሁን?” ሲል ጠየቀ። ነቢዩም “ጌታ ‘በአውራጃ አስተዳዳሪዎች የሚታዘዙ ወጣትነት ያላቸው ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ይዝመቱ’ ይላል” አለው፤ ንጉሡም “ጦርነቱን ማን ይጀምር” ሲል ጠየቀ፤ ነቢዩም “አንተ ራስህ ጀምር” አለው። ስለዚህ ንጉሡ ብዛታቸው ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ብቻ የሆነ በአውራጃ አስተዳዳሪዎች ትእዛዝ ሥር የሆኑትን ወጣትነት ያላቸውን ወታደሮች ጠራ፤ ቀጥሎም ጠቅላላ ብዛቱ ሰባት ሺህ የሆነ የእስራኤልን ሠራዊት ጠራ። ቤንሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች የሆኑ ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ በመጠጥ ሰክረው በነበሩበት ጊዜ እኩለ ቀን ላይ የእስራኤል ሠራዊት ወጣ። ወጣቶቹም ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወደ ፊት አመሩ፤ ቤንሀዳድ ልኮአቸው የነበሩትም ቃፊሮች “አንድ የወታደሮች ቡድን ከሰማርያ ወጥቶ ወደዚህ እየመጣ ነው” ብለው ነገሩት። ቤንሀዳድም “ቃፊሮቹ አመጣጣቸው ለጦርነትም ይሁን ለሰላም፥ ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጡልኝ” ሲል አዘዘ። በእስራኤል ሠራዊት ደጀንነት ወጣቶቹ ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወጡ። እያንዳንዱም ውጊያ የገጠመውን ጠላቱን ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዱአቸው ጀመር፤ ቤንሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ በመቀመጥ ከጥቂት ፈረሰኞች ጋር ሸሽቶ አመለጠ። ንጉሥ አክዓብም ወደ ጦሩ ሜዳ ገብቶ የጠላትን ፈረሶችና ሠረገሎች ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ታላቅ ጥፋት በማድረስ ድል አደረጋቸው። ከዚህ በኋላ ነቢዩ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው የጸደይ ወራት እንደገና አደጋ ስለሚጥልብህ “ተመልሰህ ሂድና ሠራዊትህን በማጠናከር አደራጅ፤ ጥንቃቄ የሞላበትንም የጦርነት ስልት አዘጋጅ” አለው። ባለሟሎቹ የሆኑ ባለ ሥልጣኖች ንጉሥ ቤንሀዳድን እንዲህ አሉት፤ “የእስራኤል አማልክት የተራራ አማልክት ናቸው፤ እስራኤላውያን እኛን ማሸነፍ የቻሉት ስለዚህ ነው፤ በሜዳማ ስፍራዎች ጦርነት ብንገጥማቸው ግን እናሸንፋለን። ስለዚህ አሁን ሠላሳ ሁለቱን ነገሥታት ከጦር አዛዥነታቸው ሽረህ፥ በእነርሱ ቦታ ሌሎችን የጦር አዛዦች ሹም። ከዚህ በፊት የተደመሰሰውን የሚያኽል ብዙ ሠራዊትና እንዲሁም በቀድሞዎቹ ልክ ፈረሶችንና ሠረገሎችን አደራጅ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤላውያንን በሜዳ ተዋግተን ድል እንነሣቸዋለን።” ንጉሥ ቤንሀዳድም በእነርሱ ምክር ተስማምቶ ለመፈጸም ወሰነ። ስለዚህም በተከታዩ የጸደይ ወቅት ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ በእስራኤል ላይ አደጋ ለመጣል ወደ አፌቅ ከተማ ገሠገሠ። እስራኤላውያንም ተጠርተው ከሚያስፈልጋቸው ስንቅና ትጥቅ ጋር ለጦርነት ተዘጋጁ፤ እነርሱም ወደ ጦርነቱ በመዝመት በሁለት ቡድን ተከፍለው ከሶርያውያን ፊት ለፊት ባለው ቦታ ሰፈሩ፤ የእስራኤል ወታደሮች ቍጥር አገሩን ካጥለቀለቀው ከሶርያውያን ሠራዊት ብዛት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት የተከፈሉ የጥቂት ፍየሎች መንጋዎች ይመስሉ ነበር። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ “ጌታ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘ሶርያውያን ጌታ የኮረብቶች አምላክ እንጂ የሜዳዎች አምላክ አይደለም’ ብለዋል፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እጅግ ብዙ በሆነው ሠራዊታቸው ላይ ድልን አቀዳጅሃለሁ፤ አንተና ሕዝብህም እኔ ጌታ መሆኔን ታውቃላችሁ” አለው። ሶርያውያንና እስራኤላውያን ፊት ለፊት ተፋጠው በየጦር ሰፈራቸው እስከ ሰባት ቀን ቆዩ፤ በሰባተኛውም ቀን ጦርነት ጀምረው በዚያኑ ቀን እስራኤላውያን አንድ መቶ ሺህ የሶርያውያንን እግረኛ ጦር ወታደሮችን ገደሉ። ከሞት የተረፉትም ሶርያውያን ሸሽተው ወደ አፌቅ ከተማ ገቡ፤ በዚያም ቁጥራቸው ኻያ ሰባት ሺህ በሚሆኑት ወታደሮች ላይ የከተማው ቅጽር ተንዶባቸው አለቁ። ቤንሀዳድም አምልጦ ወደ ከተማይቱ በመግባት ከአንድ ቤት በስተ ኋላ በኩል ባለው ክፍል ውስጥ ተደበቀ። ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖችም ወደ እርሱ ቀርበው “የእስራኤል ነገሥታት ምሕረት አድራጊዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ ስለዚህ በወገባችን ማቅ ታጥቀን፥ በራሳችንም ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ ዘንድ ሄደን ምሕረት እንድንጠይቀው ፍቀድልን፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፍ ይሆናል” አሉት። ከዚህም በኋላ እነርሱ በወገባቸው ማቅ ታጥቀው፥ በራሳቸውም ገመድ ጠምጥመው ወደ ንጉሥ አክዓብ በመሄድ “አገልጋይህ ቤንሀዳድ ምሕረት አድርገህ ሕይወቱን እንድታተርፍለት ይማጠንሃል” አሉት። አክዓብም “እርሱ እስከ አሁን በሕይወት አለ ማለት ነውን? ከሆነስ መልካም ነው፤ እንግዲህ እርሱ ለእኔ እንደ ወንድም ነው!” ሲል መለሰላቸው። የንጉሥ ቤንሀዳድ ባለሟሎች የምሕረት መልእክት ይጠባበቁ ስለ ነበር፥ አክዓብ “ወንድሜ” ሲል በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ቀበል አድርገው “አንተ እንዳልከው ቤንሀዳድ በእርግጥ ወንድምህ ነው!” አሉት። አክዓብም “ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። ቤንሀዳድም በመጣ ጊዜ፥ አክዓብ ወደ ሠረገላው ገብቶ እንዲቀመጥ ቤንሀዳድን ጋበዘው። ቤንሀዳድም አክዓብን “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ የንግድ ማእከል ልታቋቁም ትችላለህ” አለው። አክዓብም “እንግዲያውስ በዚህ ስምምነት መሠረት እኔም በነጻ እለቅሃለሁ” ሲል መለሰለት። አክዓብም በዚህ ዓይነት ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ በነጻ እንዲሄድ ፈቀደለት። የነቢያት ወገን የሆነ አንድ ነቢይ በጌታ ታዞ የእርሱ ጓደኛ የሆነውን ሌላ ነቢይ “ምታኝ!” አለው። ነቢዩ ግን እርሱን ለመምታት አልፈቀደም። ስለዚህም ያ ነቢይ “የጌታን ትእዛዝ መፈጸም እምቢ ስላልክ፥ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድክ ወዲያውኑ አንድ አንበሳ ይገድልሃል” አለው፤ በእርግጥም ከእርሱ ተለይቶ እንደ ሄደ አንበሳ በድንገት ወደ እርሱ መጥቶ ገደለው። ከዚህም በኋላ ነቢዩ ወደ ሌላ ሰው ሄዶ “ምታኝ!” አለው፤ ያም ሰው “እሺ” በማለት በኃይል ደብድቦ አቆሰለው። ነቢዩ ማንነቱ እንዳይታወቅ ፊቱን በጨርቅ ሸፈነ፤ ሄዶም በዚያ በኩል የሚያልፈውን የእስራኤልን ንጉሥ ለመጠበቅ በመንገድ ዳር ቆመ። ንጉሡም በአጠገቡ ሲያልፍ፥ ነቢዩ ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ በጦርነት ውስጥ በውጊያ ላይ ነበርኩ፤ በዚያን ጊዜም ከወታደሮቹ አንዱ ከጠላት ወገን አንድን ሰው ማርኮ በማምጣት ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ ግን በእርሱ ፈንታ አንተ ትገደላለህ ወይም ሠላሳ አራት ኪሎ የሚመዝን ጥሬ ብር መቀጫ ትከፍላለህ’ አለኝ። ነገር ግን እኔ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያና ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።” ንጉሡም “በራስህ ላይ ስለ ፈረድህ መቀጣት ይገባሃል” አለው። ነቢዩ ፊቱ የተሸፈነበትን ጨርቅ ፈጥኖ አወለቀ፤ ንጉሡም ይህ ሰው ከነቢያት ወገን አንዱ መሆኑን ወዲያውኑ ዐወቀ። ከዚህ በኋላ ያ ነቢይ ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ጌታ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ ‘እኔ ይገደል’ ብዬ የፈረድኩበትን ሰው እንዲያመልጥ ስለ ፈቀድህ በእርሱ ፈንታ አንተ በሞት ትቀጣለህ፤ የዚያ ሰው ሠራዊት አምልጦ እንዲሄድ ስላደረገ ሠራዊትህም ይደመሰሳል።” ንጉሡም በማዘንና በመበሳጨት በሰማርያ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ሄደ። የሶርያም ንጉሥ የአዴር ልጅ ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፥ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ንጉሦች ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፥ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም። ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ፦ የአዴር ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፥ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው” ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ። የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፥ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለ። ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው፦ የአዴር ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር። ነገም በዚህ ጊዜ ባርያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባርያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፦ “ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንደሚሻ እዩ፥ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም” አለ። ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ፦ “አትስማው፥ እሺም አትበለው” አሉት። ለአዴርም ልጅ መልአክተኞች፦ “ለጌታዬ ለንጉሥ፥ ለእኔ ለባርያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፥ ይህ ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት” አላቸው፤ መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት። የአዴርም ልጅ፦ “ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ” ብሎ ላከበት። የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፦ “በቃ፥ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ” አለው። የአዴርም ልጅ ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባርያዎቹንም፦ “ተሰለፉ” አላቸው፥ እነርሱም በከተማይቱ ትይዩ ተሰለፉ። እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃለህ’ አለ።” አክዓብም፦ “በማን?” አለ፥ እርሱም፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በአውራጆቹ አለቆች ጉልማሶች’” አሉ፤ እርሱም፦ “ሰልፉን ማን ይጀምራል?” አለ፤ እርሱም፦ “አንተ” አለው። የአውራጆቹንም አለቆች ጉልማሶች ቆጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፥ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ቆጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ። ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፥ የአዴር ልጅ ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር። የአውራጆቹም አለቆች ጉልማሶች አስቀድመው ወጡ፥ የአዴርም ልጅ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም፦ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል” ብለው ነገሩት። እርሱም፦ “ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው” አለ። እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጉልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፤ ሠራዊትም ተከተላቸው። ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፤ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ የአዴር ልጅ በፈረሱ አመለጠ። የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፤ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊያ ገደላቸው። ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ፦ “የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ” አለው። የሶርያም ንጉሥ ባርያዎች እንዲህ አሉት፦ “አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፥ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፥ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን። ይህንም አድርግ፥ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። አንተም ቀድሞ እንደጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሠረገላውንም በሠረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቁጠር፥ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን።” ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። በሚመጣውም ዓመት የአዴር ልጅ ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፥ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፥ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር። የጌታም ሰው ቀርቦ “የእስራኤልን ንጉሥ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሶርያውያን ጌታ የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” አለው። እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፤ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ። ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ጦርነት ተወግዶ ሰላም ሰፍኖ ነበር። ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጐብኘት ወረደ። አክዓብ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለ ሥልጣኖች “በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትን ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዓይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት!” አላቸው። ኢዮሣፍጥንም “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ለመዝመት ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢዮሣፍጥም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው” አለው። “ነገር ግን መጀመሪያ የጌታን ፈቃድ ጠይቅ” ሲል መለሰለት። ስለዚህ አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ አደጋ ልጣልባት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት። ኢዮሣፍጥ ግን “የጌታን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላስ ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይም አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም!” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “ይህን ማለት አይገባህም!” አለው። ከዚህ በኋላ አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው። በዚህም ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር። ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚጠራው የከናዕና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶችን ይዞ አክዓብን “ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’” አለው። ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ይሰጥሃል” አሉት። ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “ጌታ የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በጌታ ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ ጌታም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሏል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ጌታ የሚለውን ስማ! ጌታ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ ጌታም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር። በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ። ጌታም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው ጌታ ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ ጌታ ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የጌታ መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቆይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ። ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ። ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቆስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቁስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ። ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዓይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ ጌታም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሠራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። እርሱም በሠላሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ነግሦ ኻያ አምስት ዓመት በኢየሩሳሌም ገዛ፤ እናቱም ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች። ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ አሳ በጌታ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ሠራ፤ ይሁን እንጂ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን አልደመሰሰም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በእነዚያ ቦታዎች መሥዋዕት ማቅረብና ዕጣን የማጠን ተግባሩን አልተወም ነበር፤ ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ነበር። ኢዮሣፍጥ ያደረጋቸው ነገሮችና፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነትም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ከአባቱ ከአሳ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተረፉትንና በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶችና ሴቶች አመንዝራዎችን ሁሉ አስወገደ። በዚያን ዘመን የኤዶም ምድር የራስዋ ንጉሥ አልነበራትም፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ንጉሥ በሚሾመው እንደ ራሴ ትገዛ ነበር። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ውቅያኖስን አቋርጠው ከኦፊር ወርቅ የሚያመጡለትን የተርሴስን ዓይነት መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ነገር ግን መርከቦቹ በኤጽዮንጋብር ወደብ ላይ ስለ ተሰበሩ መጓዝ አልቻሉም። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ መርከበኞቹ ከኢዮሣፍጥ መርከበኞች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ የውል ድርድር አቅርቦ ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ሐሳቡን አልተቀበለም። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። እርሱም የአባቱን የአክዓብን፥ የእናቱን የኤልዛቤልንና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል በጌታ ፊት በደል ሠራ። ከእርሱም በፊት እንደነበረው እንደ አባቱ በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ በመስገድና በማገልገል የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ አነሣሣ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ በብርቱ ስለ ቆሰለ ታሞ ነበር፤ እርሱም “እኔ ከዚህ ሕመም እድን ወይም አልድን እንደሆነ በፍልስጥኤም የዔክሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡልን ጠይቃችሁልኝ ኑ” ብሎ መልእክተኞቹን ላከ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት፥ በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ በማሰብ ነውን?’ ስለዚህም እግዚአብሔር፥ ‘እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም! ከተኛህበት አልጋም አትነሣም! ብሎሃል’ በሉት።” ስለዚህ ኤልያስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ መልእክተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም “ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድነው? በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብለህ በማሰብህ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም! ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!’” ንጉሡም “በመንገድ ያገኛችሁትና ይህን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ጠጉራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡም “እርሱማ ኤልያስ ነው!” አለ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፤ መኰንኑም ኤልያስን በአንድ ኰረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ በዚያም ጊዜ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ። ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል!” አለው። ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ። ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኰንን ላከ፤ ይህኛው መኰንን ግን ወደ ኰረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን! ሕይወታችንንም ከሞት አድን! ሌሎቹን ሁለት መኰንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ!” በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ኤልያስን “ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ” አለው። ስለዚህም ኤልያስ ከመኰንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቁጠር፥ የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁልህ መልእክተኞች በመላክህ ምክንያት ትሞታለህ እንጂ አትድንም!’” አለው። እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረውም ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፤ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ እግር ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ፤ ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር። ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጉዞ ጀመሩ፤ በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን “እነሆ፥ አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ቤትኤል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ከቶ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤትኤል ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ!” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃውም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ በዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም “የአንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችል መንፈስ በእጥፍ ስጠኝ” ሲል መለሰለት። ኤልያስም “ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየቅኸውን ስጦታ መቀበል ትችላለህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም” ሲል መለሰለት። እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ የእሳት ፈረሶች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ኤልሳዕም ይህን ሁሉ እያየ “የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች የሆንክ አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!” እያለ ወደ ኤልያስ ጮኸ፤ ከዚያም በኋላ ኤልያስን ዳግመኛ አላየውም። ኤልሳዕም ከኀዘን ብዛት የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደ፤ ከኤልያስም የወደቀውን ካባ ከመሬት አነሣ፤ ከዚያም ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ቆመ። ውሃውንም በኤልያስ ካባ መትቶ፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ፤ ከዚያም በኋላ እንደገና በመታው ጊዜ ውሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎለት ወደ ማዶ ተሻገረ፤ ከኢያሪኮ የመጡት ነቢያት እርሱን ባዩት ጊዜ “በኤልያስ ላይ ዐድሮ የነበረው የመንፈስ ኃይል በኤልሳዕ ላይ አርፏል!” አሉ፤ ወደ እርሱም በመቅረብ ጐንበስ ብለው እጅ ነሡት “እነሆ! በዚህ ጠንካሮች የሆንን ኀምሳ ሰዎች አለን፤ እንሂድና ጌታህን እንፈልገው፤ ምናልባት የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወስዶ በአንድ ተራራ ላይ ወይም ሸለቆ ውስጥ አሳርፎት ይሆናል።” ኤልሳዕም “አትላኩአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱ ግን እምቢ ለማለት እስኪያሳፍረው ድረስ አጥብቀው ስለ ለመኑት በጉዳዩ ተስማማና ኀምሳ ሰዎች ሄደው ሦስት ቀን ሙሉ ኤልያስን ፈለጉት፤ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፤ ከዚያም በኋላ በኢያሪኮ ሆኖ ወደሚጠብቃቸው ወደ ኤልሳዕ ተመለሱ፤ ኤልሳዕም “እኔ ቀድሞውንስ አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው። ጥቂት ሰዎች ከኢያሪኮ ወደ ኤልሳዕ መጥተው “ጌታችን አንተ እንደምታውቀው ይህች ምድር መልካም ናት፤ ውሃው ግን መጥፎ በመሆኑ ምድሪቱ ምርት አትሰጥም” አሉት። ኤልሳዕም “በአዲስ አፍላል ማሰሮ ውስጥ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” ብሎ አዘዘ። እነርሱም እንዳዘዛቸው አድርገው አመጡለት። እርሱም ወደ ምንጩ ሄዶ ጨውን በውሃው ውስጥ በመጨመር፥ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ‘እኔ ይህን ውሃ በመፈወስ ንጹሕ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የሞትና የምርት አልባነት ምክንያት አይሆንም’” ሲል ተናገረ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤልሳዕ በተናገረው መሠረት ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሕ ነው። ኤልሳዕም ወደ ቤትኤል ለመሄድ ከኢያሪኮ ተነሣ፤ በመንገድ ሳለ ከከተማይቱ በርከት ያሉ ልጆች ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “አንተ ራሰ መላጣ ከዚህ ውጣ!” እያሉ ጮኹበት። ኤልሳዕም መለስ ብሎ ዙሪያውን በመቃኘት፥ አተኲሮ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ በዚህም ጊዜ ሁለት እንስት ድቦች ከጫካ ወጥተው ከእነዚያ ልጆች መካከል አርባ ሁለቱን ሰባብረው ጣሉአቸው። ኤልሳዕም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ ዘግየት ብሎ ግን ወደ ሰማርያ ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ እርሱ የአባቱንና የእናቱን የኤልዛቤልን ያኽል መጥፎ ሰው አልነበረም፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ባዕድ አምላክ ለማምለክ አባቱ አሠርቶት የነበረውን ምስል አስወገደ፤ ይህም ሆኖ ከእርሱ በፊት እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራው የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን አምልኮ ተከተለ እንጂ አላስወገደውም። የሞዓብ ንጉሥ ሜሻዕ በግ አርቢ ነበር፤ በየዓመቱም አንድ መቶ ሺህ ጠቦትና የአንድ መቶ ሺህ በጎች ጠጉር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር፤ ነገር ግን የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሞተ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሜሻዕ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። በዚያን ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ወዲያውኑ ከሰማርያ ወጥቶ ወታደሮቹን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥም “የሞዓብ ንጉሥ በእኔ ላይ አምፆብኛል፤ በእርሱ ላይ በማደርገው ጦርነት ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” የሚል መልእክት ላከ። ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “አዎ እተባበርሃለሁ፤ እኔን እንደ አንተ፥ ሠራዊቴን እንደ ሠራዊትህ፥ ፈረሶቼን እንደ ፈረሶችህ መቁጠር ትችላለህ” ሲል ከመለሰ በኋላ፥ ዳሩ ግን “አደጋ ለመጣል የምንጓዘው በየትኛው መንገድ ነው?” ሲል ጠየቀው። ንጉሥ ኢዮራምም “በኤዶም በረሓ የሚገኘውን ዙሪያ መንገድ ይዘን እንጓዛለን” ሲል መለሰለት። ስለዚህም ንጉሥ ኢዮራምና እንዲሁም የይሁዳና የኤዶም ነገሥታት ለዘመቻ ወጡ፤ ከሰባት ቀን ጉዞም በኋላ ውሃ አለቀባቸው፤ ለሠራዊቱም ሆነ ለጭነት እንስሶች ምንም ውሃ አልነበረም። ንጉሥ ኢዮራምም “እግዚአብሔር ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ሊሰጠን ነውና ወዮልን!” ሲል ጮኸ። ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንድንችል በዚህ አንድም ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። ከንጉሥ ኢዮራም ሠራዊት አዛዦች አንዱ፥ “ቀድሞ የኤልያስ ረዳት የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ” ሲል መልስ ሰጠ። ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ከዚያም በኋላ ሦስቱም ነገሥታት ወደ ኤልሳዕ ሄዱ። ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ ኢዮራምን፥ “እኔ አንተን የምረዳህ ስለምንድን ነው? ሄደህ አባትህና እናትህ ይጠይቁአቸው የነበሩትን እነዚያን ነቢያት ጠይቅ!” አለው። ንጉሥ ኢዮራምም መልሶ፥ “አይደለም እኮ! ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ለመስጠት የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ። ኤልሳዕም “እኔ በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! አንተን ለመርዳት ለመጣው ለይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ስል ነው እንጂ፥ ለአንተስ ምንም ነገር ላደርግልህ ባልተገባ ነበር፤ አሁንም በገና የሚደረድር ሰው አምጡልኝ” አለ። ባለ በገናውም በሚደረድርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በኤልሳዕ ላይ ወርዶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በዚህ የደረቀ ሸለቆ ሁሉ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሩ፤ ምንም ዝናብና ነፋስ ባታዩም፥ ይህ ሸለቆ በውሃ የተሞላ ይሆናል፤ እናንተ፥ የቀንድ ከብቶቻችሁና የጭነት እንስሶቻችሁ ሁሉ የምትጠጡት በቂ ውሃ ታገኛላችሁ።’ ነገር ግን ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀላል ነገር ነው፤ ከዚህም በላይ እርሱ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል። የተመሸጉና ምርጥ የሆኑ ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል አድርጋችሁ ትይዛላችሁ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን ትደፍናላችሁ፤ ለም የሆኑ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በማበላሸት ድንጋይ ትከምሩባቸዋላችሁ።” በማግስቱም ጠዋት መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ከኤዶም በኩል የውሃ ምንጭ ፈልቆ ምድሩን ሸፈነው። ሞዓባውያንም ሦስቱ ነገሥታት አደጋ ሊጥሉባቸው መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ፥ ከሽማግሌ እስከ ወጣት መሣሪያ መያዝ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው በመውጣት በጠረፉ ላይ ተጠባበቁ። በማግስቱም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ፥ በውሃው ላይ የሚያበራው የፀሐይ ነጸብራቅ እንደ ደም መስሎ ታያቸው፤ ስለዚህም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ “ይህ ነገር ደም ነው! የሦስቱ ጠላቶቻችን ሠራዊቶች እርስ በርሳቸው በመተራረድ ተላልቀዋል! እንግዲህ ሄደን ሰፈራቸውን እንዝረፍ!” ተባባሉ። ነገር ግን እነርሱ ወደ ሰፈር በደረሱ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው አደጋ በመጣል ወደ ኋላ መለሱአቸው፤ እስራኤላውያን አገሪቱን ወረው ሞዓባውያንን ጨፈጨፉአቸው። ከተሞቻቸውን ደመሰሱ፤ ለም በሆነው እርሻ ውስጥ በሚያልፉበትም ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውርበት ስለ ነበር በመጨረሻ እርሻዎቹ ሁሉ በድንጋይ ተሸፈኑ፤ ምንጮቻቸውን ደፈኑ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውንም ሁሉ ቆረጡ፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረችው ቂርሔሬስ ብቻ ቀረች፤ እርሷንም ድንጋይ የሚያወነጭፉ ጦረኞች ከበው አደጋ ጣሉባት። የሞዓብ ንጉሥ ድል እንደ ተመታ ባረጋገጠ ጊዜ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎችን አስከትሎ የጠላት ጦር የተሰለፈበትን መስመር ጥሶ ለማምለጥና ወደ ሶርያ ንጉሥ ለመሄድ ቢሞክርም ከቶ አልተሳካለትም። ስለዚህም በእርሱ ምትክ መንገሥ የሚገባውን የመጀመሪያ ልጁን በከተማይቱ ግንብ ላይ ለሞዓብ አምላክ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እስራኤላውያንም በነገሩ ስለ ተሠቀቁ ከተማይቱን ለቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ። የነቢያት ጉባኤ አባል የነበረ ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት ወደ ኤልሳዕ መጥታ “ጌታዬ ሆይ! ባሌ ሞቶብኛል! እርሱም አንተ እንደምታውቀው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ለባሌ ገንዘብ አበድሮት የነበረ አንድ ሰው በባሌ ዕዳ ፈንታ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ወስዶ ባርያ አድርጎ ሊገዛቸው ፈልጎአል” አለችው። ኤልሳዕም “ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽም ምን እንዳለሽ ንገሪኝ” ሲል ጠየቃት። እርሷም “በትንሽ ማሰሮ ከሚገኝ የወይራ ዘይት በቀር ሌላ ምንም የለኝም” ስትል መለሰች። ኤልሳዕም እንዲህ አላት፦ “ወደ ጐረቤቶችሽ ሄደሽ ማግኘት የምትችዪውን ያኽል ባዶ ማድጋ ለምኚ፤ ከዚህም በኋላ አንቺና ልጆችሽ ወደ ቤት ገብታችሁ መዝጊያውን ዝጉ፤ የማሰሮውንም ዘይት ወደ ማድጋዎቹ ማንቆርቆር ጀምሩ፤ እያንዳንዱ ማድጋ በሚሞላበት ጊዜ ለብቻው በማግለል አኑሩት።” ስለዚህም ሴትዮዋ ወደ ቤትዋ ሄዳ ከልጆችዋ ጋር በሩን ዘጋች፤ ዘይት የነበረበትን ትንሽ ማሰሮ አንሥታ ልጆችዋ እያቀረቡላት በማንቆርቆር በየማድጋዎቹ ሞላች። ማድጋዎቹንም ሁሉ ከሞሉ በኋላ “ሌላ ትርፍ የለም ወይ?” ስትል ጠየቀች፤ ከልጆችዋም አንዱ “ሌላ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም በኋላ ዘይቱ መውረዱን አቆመ፤ እርሷም ተመልሳ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ሄደች፤ እርሱም “እንግዲህ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን በሙሉ ክፈይ፤ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ የሚሆንም ብዙ ገንዘብ ይተርፍሻል” አላት። አንድ ቀን ኤልሳዕ አንዲት ሀብታም ሴት ወደምትኖርበት ወደ ሱነም ሄደ፤ እርሷም ምግብ እንዲበላ ጋበዘችው፤ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ወደ ሱነም በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ በቤትዋ ይመገብ ነበር፤ እርሷም ባሏን እንዲህ አለችው፤ “ብዙ ጊዜ ወደ ቤታችን የሚመጣው ይህ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሰው ስለ መሆኑ እርግጠኛ ነኝ፤ ስለዚህም በሰገነቱ ላይ አንድ ትንሽ ክፍል ሠርተን በዚያች ውስጥ አንድ አልጋ፥ አንድ ጠረጴዛ፥ አንድ ወንበርና አንድ የፋኖስ መብራት እናኑርለት፤ እርሱም እኛን ለመጐብኘት በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።” አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ተመልሶ ሄደ፤ ዕረፍት ለማድረግም ወደ ተሠራለት ክፍል ገብቶ ዐረፈ፤ ግያዝ ተብሎ የሚጠራውንም አገልጋዩን፥ “ሄደህ ሱነማዊትን ጥራ” አለው፤ እርሷም መጥታ በፊቱ ቆመች። ግያዝ “ለእኛ ስላደረገችው መልካም ነገር ሁሉ ምን አደርግላት ዘንድ እንደምትፈልግ ጠይቃት፤ ምናልባት ወደ ንጉሡ ወይም ወደ ጦር አዛዡ ዘንድ ሄጄ የምነግርላት ጉዳይ ሊኖር ይችላል” አለው። እርሷም “በዘመዶች መካከል በምኖርበት በዚህ ስፍራ ምንም የሚቸግረኝ ነገር የለም” ስትል መለሰችለት። ኤልሳዕም ግያዝም “ታዲያ ምን ላደርግላት እችላለሁ?” ሲል ጠየቀው። ግያዝም “እነሆ፥ ልጅ የላትም፤ ባሏም ሽማግሌ ነው” ሲል መለሰ። ኤልሳዕም “እንድትመጣ ንገራት” ብሎ አዘዘው። እርሷም መጥታ በበሩ አጠገብ ቆመች፤ ኤልሳዕም “በመጪው ዓመት ልክ ይህን ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት። እርሷም፦ “አይደለም! ጌታዬ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እባክህ የማይፈጸም የተስፋ ቃል አትንገረኝ!” አለችው። ነገር ግን ሴቲቱ ፀነሰች፤ ልክ ኤልሳዕ የተናገረው ጊዜ ሲደርስ በተከታዩ ዓመት ወንድ ልጅ ወለደች። ሕፃኑም አደገ፤ በመከር ወራት አንድ ቀን ጧት ያ ልጅ ከአጫጆች ጋር በእርሻ ውስጥ ወደነበረው ወደ አባቱ ሄደ፤ በድንገትም “ራሴን! ራሴን!” ብሎ ወደ አባቱ ጮኸ። አባትየውም አንዱን አገልጋይ ጠርቶ፥ “ልጁን ወደ እናቱ ውሰድ” ሲል አዘዘው። አገልጋዩም ያን ልጅ ተሸክሞ በመውሰድ ለእናቱ ሰጣት፤ እርሷም እንደ ታቀፈችው ቆይቶ እኩለ ቀን ላይ ሞተ፤ እርሱንም አውጥታ ለኤልሳዕ በተሠራው ክፍል በማስገባት በአልጋው ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ተመልሳ ሄደች። ባሏንም ጠርታ “አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ሰው ዘንድ መሄድ ይገባኛል፤ በተቻለም መጠን ፈጥኜ እመለሳለሁ” አለችው። ባሏ ግን “ዛሬ ስለምን ትሄጂአለሽ? ሰንበት ወይም የጨረቃ በዓል የሚከበርበት ጊዜ አይደለም” አላት። እርሷም “ግድ የለም፤ እንዳልኩህ አድርግ” አለችው፤ እርሷም አህያው እንዲጫንላት ካደረገች በኋላ አገልጋዩን “በሚቻል መጠን አህያው እንዲፈጥን አድርግ፤ እኔም ካልነገርኩህ በቀር ቀስ ብሎ እንዲሄድ ፋታ አትስጠው” ስትል አዘዘችው። እርሷም ከዚያ ተነሥታ ኤልሳዕ ወደ ነበረበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣች። ኤልሳዕም ገና በሩቅ ሳለች ወደ እርሱ ስትመጣ አይቶ አገልጋዩን ግያዝን “ተመልከት! ያቺ ሴት ከሱነም ወደዚህ በመምጣት ላይ ናት! ፈጠን ብለህ ሂድና የእርሷን፥ የባሏንና የልጇን ደኅንነት ጠይቃት” አለው። እርሷም ግያዝን “ሁላችንም ደኅና ነን” ስትል ነገረችው። ወደ ኤልሳዕ በቀረበች ጊዜ ግን ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት እግሮቹን ያዘች፤ በዚህ ጊዜ ግያዝ ገፍቶ ሊያስወግዳት ቃጣ፤ ኤልሳዕ ግን “ተዋት፤ ምን ያኽል ጭንቀት እንዳለባት አታይምን? እግዚአብሔርም ስለ እርሷ ችግር የገለጠልኝ ነገር የለም” አለው። ሴቲቱም “ጌታዬ፥ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‘የማይፈጸምስ የተስፋ ቃል አትስጠኝ’ ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?” አለችው። ኤልሳዕም ወደ ግያዝ መለስ ብሎ “በፍጥነት ተነሥና የእኔን ምርኲዝ ይዘህ ሂድ! ለአንድም ሰው ሰላምታ ለመስጠት እንኳ በመንገድ አትቁም፤ ማንም ሰው ሰላምታ ቢሰጥህ አጸፋውን ለመመለስ ጊዜ አታጥፋ፤ በቀጥታ ወደ ቤት ሄደህ የእኔን ምርኲዝ በልጁ ፊት ላይ አኑር!” አለው። የልጁ እናት ግን ኤልሳዕን “በምተማመንበት በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከቶ አንተን ትቼ አልሄድም!” አለችው፤ ስለዚህ እርሷን ተከትሎ ለመሄድ ተነሣ፤ ግያዝም ወደ ፊት ቀድሞአቸው ሄደና የኤልሳዕን ምርኲዝ በልጁ ፊት ላይ አኖረ፤ ነገር ግን ድምፅም ሆነ ሌላ የሕይወት ምልክት አልነበረም፤ ስለዚህም ተመልሶ ሄዶ ኤልሳዕን “ልጁ አልተነሣም” አለው። ኤልሳዕም በደረሰ ጊዜ ብቻውን ወደ ክፍሉ ገብቶ፥ ልጁ ሞቶ በአልጋው ላይ መጋደሙን አየ፤ ከልጁ ጋር ብቻውን ሆኖ፥ ክፍሉንም ዘግቶ፥ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ከዚህም በኋላ አፉን ከአፉ፥ ዐይኖቹን ከዐይኖቹ፥ እጆቹን ከእጆቹ ጋር ገጥሞ በልጁ ሬሳ ላይ ተጋደመ፤ ኤልሳዕም ተዘርግቶ እንደ ተጋደመበት የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ። ኤልሳዕም ተነሥቶ በክፍሉ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ጀመር፤ እንደገናም ተመለሰና በመዘርጋት በልጁ ላይ ተጋደመ፤ ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዐይኖቹን ከፈተ። ኤልሳዕም ግያዝን “ሱነማይቱን ጥራ” አለው፤ እርሷም በመጣች ጊዜ ኤልሳዕ “ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። እርሷም ወደ መሬት ለጥ ብላ በኤልሳዕ ጫማ ላይ በመውደቅ እጅ ነሣች፤ ከዚያም በኋላ ልጇን ይዛ ሄደች። በመላ አገሪቱ ራብ በነበረበት በአንድ ወቅት ኤልሳዕ ወደ ጌልጌላ ተመልሶ መጣ፤ በዚያም የነቢያትን ጉባኤ በማስተማር ላይ ሳለ አገልጋዩን “ትልቅ ድስት ጥደህ ወጥ ሥራላቸው” አለው። ከነቢያቱም አንዱ ጎመን የሚመስል ቅጠላ ቅጠል ለመልቀም ወደ ሜዳ ሔደ፤ እርሱም በዱር ውስጥ የበቀለ የቅል ሐረግ አገኘ፤ መሸከም የሚችለውን ያኽል በርከት ያለ ቅል ቆርጦ አመጣ፤ የዚያንም ምንነት ሳያውቅ ከትፎ ወጡ ውስጥ ጨመረው፤ ነቢያትም እንዲመገቡት የወጣላቸውን ወጥ ቀምሰው “በዚህ ወጥ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!” ብለው ወደ ኤልሳዕ ጮኹ፤ ሊመገቡትም አልቻሉም፤ ኤልሳዕም ዱቄት እንዲሰጡት ጠይቆ በድስቱ ውስጥ ጨመረውና “ወጡን እያወጣህ ጨምርላቸው” ሲል አዘዘ፤ በዚህም ጊዜ በወጡ ውስጥ ምንም ዓይነት መራራነት አልነበረም። ሌላም ጊዜ በዓልሻሊሻ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ አንድ ሰው በመከር ጊዜ በመጀመሪያ ከተወቃው ገብስ የተጋገሩ ኻያ የዳቦ ሙልሙሎችና አዲስ የተቆረጠ እሸት ለኤልሳዕ ይዞለት መጣ፤ ኤልሳዕም “ለነቢያት ጉባኤ አቅርብላቸውና ይብሉ” ብሎ አገልጋዩን አዘዘው፤ አገልጋዩ ግን “ይህ ለመቶ ሰው የሚበቃ ይመስልሃልን?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም “እንዲበሉ አቅርብላቸው፤ በልተው መጥገብ ብቻ ሳይሆን እንደሚተርፋቸውም እግዚአብሔር ተናግሮአል” አለው። ስለዚህም አገልጋዩ ምግቡን አቀረበላቸው፤ እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላም የተረፈ ምግብ ነበር። እግዚአብሔር በንዕማን አማካይነት ለሶርያ ሠራዊት ድልን ስለ አጐናጸፈ፥ የሶርያ ጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን በሶርያ ንጉሥ ዘንድ እጅግ የተከበረና የተወደደ ባለሟል ነበር፤ ታዲያ ንዕማን ጀግና ወታደር ሆኖ ሳለ፥ በቆዳ በሽታ ይሠቃይ ነበር። ሶርያውያን በእስራኤላውያን ላይ ወረራ በፈጸሙበት በአንድ ወቅት፥ አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ ማርከው ወስደው ነበር፤ እርሷም ለንዕማን ሚስት፥ ገረድ ሆና ትኖር ነበር። አንድ ቀን እመቤትዋን፥ “ጌታዬ ንዕማን በሰማርያ ወደሚገኘው ነቢይ ቢሄድ መልካም ይመስለኛል! ነቢዩ ከዚህ የቆዳ በሽታው ሊያነጻው ይችላል!” አለቻት። ንዕማንም ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ልጃገረዲቱ ያለችውን ሁሉ ነገረው፤ ንጉሡም “ይህን ደብዳቤ ይዘህ ወደ እስራኤል ንጉሥ ሂድ” ብሎ ፈቀደለት። ስለዚህም ንዕማን ሠላሳ ሺህ ጥሬ ብር፥ ስድስት ሺህ መሐለቅ ወርቅና ምርጥ የሆነ ዐሥር መለወጫ ልብስ አስጭኖ፥ ጉዞውን ቀጠለ፤ ይዞት የሄደውም መልእክት “ይህ ደብዳቤ የእኔ ሠራዊት አዛዥ ስለ ሆነው ስለ ንዕማን ጉዳይ የሚገልጥ ነው፤ ከቆዳ በሽታ በማንጻት እንድትፈውሰው እፈልጋለሁ” የሚል ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ በቁጣ ልብሱን ቀደደ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ “የሶርያ ንጉሥ ይህን ሰው እንደምፈውስለት አድርጎ እንዴት ይገምታል? እኔ ሰውን ከቆዳ በሽታ እፈውስ ዘንድ የማዳንና የመግደል ሥልጣን ያለኝ እግዚአብሔር መሰልኩትን? በእርግጥ ይህ አባባል ከእኔ ጋር ጠብ መፈለጉን በግልጥ ያሳያል!” አለ። ነቢዩ ኤልሳዕም የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ መልእክት ልኮ “ስለምን ልብስህን ቀደድክ? ሰውየውን ወደ እኔ ላከው፤ እኔም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን አሳየዋለሁ!” አለው። ስለዚህም ንዕማን ፈረሶች በሚስቡት ሠረገላ ተቀምጦ በመሄድ ወደ ኤልሳዕ ቤት በሚያስገባው በር ላይ ሲደርስ ቆመ። ኤልሳዕም አንዱን አገልጋይ “‘ሄደህ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠብ፤ ከበሽታህም ፈጽሞ ትነጻለህ’ ብለህ ለዚህ ሰው ንገረው” ሲል አዘዘው፤ ንዕማን ግን ተቆጥቶ ወደ አገሩ ለመመለስ ተነሣ፤ እንዲህም እያለ ያጉረመርም ነበር፤ “እኔ እኮ ነቢዩ መጥቶ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የቆዳው በሽታ ባረፈበት ገላዬ ላይ እጆቹን በመወዝወዝ ይፈውሰኛል ብዬ አስቤ ነበር! የውሃ የውሃማ በእስራኤል ከሚገኙት ወንዞች ይልቅ በአገሬ በደማስቆ የሚገኙት አባናና ፋርፋር አይሻሉምን? እንዲህ ከሆነማ በእነርሱ ታጥቤ በነጻሑ ነበር!” የንዕማንም አሽከሮች ወደ እርሱ ቀረብ ብለው፥ “ጌታችን ሆይ፥ ነቢዩ ሌላ ከባድ ነገር እንድታደርግ ቢያዝህ ኖሮ ትፈጽመው ነበር፤ ታዲያ ነቢዩ ባዘዘህ መሠረት ታጥበህ ከበሽታህ መንጻት ምን ይከብድሃል?” አሉት። ስለዚህም ንዕማን የእግዚአብሔር ሰው ባዘዘው መሠረት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠበ፤ ከበሽታውም ፈጽሞ ነጻ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ገላ በመታደስ ፍጹም ጤናማ ሆነ፤ ከዚህም በኋላ ከተከታዮቹ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሶ መጥቶ፦ “ከእስራኤል አምላክ በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እነሆ፥ አሁን ተረዳሁ፤ ስለዚህም ጌታዬ ሆይ፥ እባክህ ይህን ስጦታ ተቀበለኝ” አለው። ኤልሳዕም “በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ምንም ነገር አልቀበልም” ሲል መለሰለት። ንዕማንም ስጦታውን እንዲቀበልለት አጥብቆ ቢለምነውም ኤልሳዕ ሊቀበለው አልፈቀደም፤ ስለዚህም ንዕማን እንዲህ አለ፦ “ስጦታዬን የማትቀበለኝ ከሆነ ከአሁን ጀምሮ ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ለሌሎች ባዕዳን አማልክት የሚቃጠልም ሆነ ወይም ሌላ ዓይነት መሥዋዕት ስለማላቀርብ የሁለት በቅሎ ጭነት ዐፈር ይዤ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ ስለዚህም የሀገሬን ንጉሥ በማጀብ ሪሞን የተባለ የሶርያ አምላክ ወደሚመለክበት መቅደስ ብገባና ብሰግድም እንኳ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በእርግጥም ይቅር ይለኛል።” ኤልሳዕም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ንዕማንም ተሰናብቶ ሄደ። እርሱም ጥቂት ራቅ ብሎ እንደ ሄደ፥ የኤልሳዕ አገልጋይ የሆነው ግያዝ፥ “ጌታዬ ንዕማንን ምንም ነገር ሳያስከፍል አሰናብቶታል፤ ያ ሶርያዊ ሰው ያቀረበለትን ስጦታ መቀበል ይገባው ነበር፤ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፥ በፍጥነት በመሮጥ ተከትየው ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ሲል በልቡ አሰበ። ስለዚህም ግያዝ ንዕማንን ከኋላው ተከተለው፤ ንዕማንም መለስ ብሎ አንድ ሰው እየሮጠ ሲከተለው ባየ ጊዜ፥ ከሠረገላው ወርዶ “ምነው፥ በደኅና መጣህን?” ሲል ጠየቀው። ግያዝም “መምጣትስ በደኅና ነው የመጣሁት፤ ነገር ግን ጌታዬ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖሩ ሁለት የነቢያት ጉባኤ አባላት ድንገት በእንግድነት ስለ መጡበት፥ ሦስት ሺህ ብርና ሁለት መቀየሪያ ልብስ እንድትሰጣቸው እነግርህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” ሲል መለሰለት። ንዕማንም “እንግዲያውስ እባክህ ስድስት ሺህ ብር ልስጥ” ሲል መለሰለት፤ በዚህም አሳቡ በመጽናት ብሩን በሁለት ከረጢት ሞልቶ ከሁለት መለወጫ ልብሶች ጋር በሁለት አገልጋዮች አስይዞ ከግያዝ ቀድመው በፊት በፊቱ እንዲሄዱ አደረገ። ኤልሳዕ ወደሚኖርባትም ኰረብታ በደረሱ ጊዜ፥ ግያዝ ሁለቱን ከረጢት ተቀብሎ ወደ ቤት አስገባ፤ ከዚያም በኋላ የንዕማንን አገልጋዮች አሰናብቶአቸው ሄዱ። ወደ ቤት ተመልሶ ገባ፤ ኤልሳዕም “እስከ አሁን የት ነበርክ?” ሲል ጠየቀው። ግያዝም “ጌታዬ፥ ኧረ እኔ የትም አልሄድኩም” ሲል መለሰ። ኤልሳዕም “ሰውየው ሊያነጋግርህ ከሠረገላው ላይ ሲወርድ እኔ በመንፈስ ከአንተ ጋር አልነበርኩምን? እነሆ አሁን ገንዘብና ልብስ፥ የወይራና የወይን ተክል ቦታ፥ በግና የቀንድ ከብት ወይም አገልጋዮችን ለመቀበል ጊዜው አይደለም! ከዚህም የተነሣ እነሆ፥ የንዕማን የቆዳ በሽታ ወደ አንተ ይተላለፋል፤ አንተና ዘሮችህ ለዘለዓለም ከዚያ በሽታ አትነጹም!” አለው። ግያዝም ወጥቶ ሲሄድ፥ ያ የቆዳ በሽታ ስለ ተጋባበት ገላው እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። በኤልሳዕ ኀላፊነት ሥር የነበሩት የነቢያት ጉባኤ አባላት፥ “የምንኖርበት ስፍራ ጠባብ ነው፤ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደን ዛፍ በመቁረጥ የምንኖርበት ቤት በዚያ እንድንሠራ ፍቀድልን!” አሉት። ኤልሳዕም “እሺ መልካም ነው!” አላቸው። ከነቢያቱም አንዱ ኤልሳዕን አብሮአቸው እንዲሄድ ጠየቀው፤ ኤልሳዕም በጥያቄው ተስማማ፤ አብረውም ሄዱ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ ዛፍ የመቁረጥ ተግባራቸውን ጀመሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ዛፍ በመቁረጥ ላይ ሳለ በድንገት መጥረቢያው ከዛቢያው ላይ ወድቆ ውሃ ውስጥ ገባ፤ እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጮኽ “ጌታዬ ሆይ! እንግዲህ ምን አደርጋለሁ? መጥረቢያው የተውሶ ነው!” ሲል ለኤልሳዕ ነገረው። ኤልሳዕም “በየት በኩል ነው የወደቀው?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም መጥረቢያው የወደቀበትን ስፍራ ባሳየው ጊዜ እርሱ አንድ እንጨት ቆርጦ ወደ ውሃው ውስጥ በመጣል መጥረቢያው እንዲንሳፈፍ አደረገው፤ ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “አውጥተህ ውሰድ” አለው፤ ሰውየውም ጐንበስ ብሎ አነሣው። እነሆ፥ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር በጦርነት ላይ ነበር፤ እርሱም ከጦር አዛዥውቹ ጋር ተማክሮ የሚሰፍሩበትን ቦታ መረጠ፤ ኤልሳዕ ግን “ሶርያውያን ደፈጣ አድርገው ስለሚጠብቁህ ወደዚያ ስፍራ አትቅረብ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ በዚያ የሚኖሩትን ወታደሮቹን ስላስጠነቀቃቸው ነቅተው ይጠባበቁ ነበር፤ ይህም ድርጊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ተፈጸመ። “ከእኛ መካከል ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ግኑኝነት ያለው ማን እንደሆነ አትነግሩኝምን?” ሲል ጠየቃቸው። ከእነርሱም አንዱ “ንጉሥ ሆይ፥ ከእኛ መካከል ይህን የሚያደርግ ማንም የለም፤ በመኝታ ክፍልህ እንኳ ሆነህ የምትናገረውን ሁሉ ሳይቀር ለእስራኤል ንጉሥ ምሥጢሩን የሚገልጥለት ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ ነው” ሲል መለሰለት። የሶርያም ንጉሥ “እርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ፈልጉ፤ እኔም ልኬ እማርከዋለሁ” አላቸው። በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ በዶታን የሚኖር መሆኑ ተነገረው፤ ንጉሡ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሠራዊት ወደዚያ ላከ፤ እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማይቱን ከበቡ። በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ፥ ከቤት ሲወጣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማይቱን መክበባቸውን አየ፤ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም “አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል” አለው። ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕ አገልጋይ ዐይኖቹ እንዲከፈቱለት ስላደረገ፥ በኰረብታው ጐን ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተሰልፈው የሚጠብቁት መሆናቸውን ተመለከተ። ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን ጸሎት በመስማት፥ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ። ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ወደ እነርሱ ቀረብ ብሎ “መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልመራችሁ ስለምችል ተከተሉኝ” ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው። ወደ ከተማይቱም እንደ ገቡ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ግለጥላቸው!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን ተረዱ። የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ “ጌታዬ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው። ኤልሳዕም “አይሆንም! እንኳን እነዚህን፥ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኻቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ” አለው። ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በእስራኤል ላይ በማዝመት፥ የሰማርያን ከተማ ከበበ፤ ከበባውም የምግብን እጥረትና ብርቱ ራብ ከማስከተሉ የተነሣ፥ የአንድ አህያ ራስ ዋጋ እስከ ሰማኒያ ጥሬ ብር፥ ሁለት መቶ ግራም የሚያኽል የርግብ ኩስ ዋጋ ደግሞ አምስት ጥሬ ብር ማውጣት ጀመረ። አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከተማይቱ የቅጽር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ንጉሥ ሆይ፥ እባክህ እርዳኝ!” ስትል ጮኸች። ንጉሡም “እግዚአብሔር ሊረዳሽ ካልፈቀደ እኔ ምን ዓይነት እርዳታ ልሰጥሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይስ ከወይን መጭመቂያው? ምን ያለኝ ይመስልሻል? ለመሆኑ ችግርሽ ምንድነው?” ሲል ጠየቃት። እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ ስትል ሐሳብ አቀረበች። ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‘ልጅሽን አምጪና እንብላ’ ብዬ ጠየቅኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።” ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ ከልብሱ በውስጥ በኩል ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ። ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ “የዛሬይቱ ጀንበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቆረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!” ሲል ተናገረ። ወዲያውኑም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ። በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ ሊጐበኙት ከመጡ ጥቂት ሽማግሌዎች ጋር በቤት ውስጥ ነበር፤ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን “ያ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ፥ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል” አላቸው። ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ “ይህን መከራ በእኛ ላይ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እርሱ አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ከዚህ በላይ ምን ልጠብቅ?” አለ። ኤልሳዕም “እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! ነገ ይህን ጊዜ በሰማርያ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ የንጉሡ የቅርብ ባለሟል የሆነ አገልጋዩ ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” ሲል በመጠራጠር ተናገረ። ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም!” አለው። ሰውነታቸው የቆዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች ከሰማርያ ቅጽር በር ውጪ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ ስለምን በዚህ እንቆያለን? ወደ ከተማይቱ መግባት ምንም ጥቅም የለውም፤ እዚያ ከገባን በራብ እንሞታለን፤ እዚህም ብንቀር ከመሞት አንድንም፤ ስለዚህ ተነሥተን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ እነርሱም ቢሆኑ ከመግደል የከፋ ሌላ ምንም ነገር ሊያደርጉብን አይችሉም፤ ምናልባትም ሕይወታችንን ያተርፉ ይሆናል።” ከዚህም በኋላ ቀኑ ሊመሽ ሲል ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ነገር ግን እዚያ ሲደርሱ ማንም ሰው አልነበረም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ሶርያውያንን በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀበ የብዙ ሠራዊት ግሥጋሤ የሚመስል ድምፅ አሰምቶአቸው ስለ ነበር ነው፤ ይኸውም ሶርያውያን እንዳሰቡት የእስራኤል ንጉሥ የሒታውያንና የግብጽ ነገሥታትን ከነሠራዊቶቻቸው ቀጥሮ አደጋ ሊጥልባቸው የመጣ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህም በዚያን ቀን ምሽት ሶርያውያን ድንኳኖቻቸውን፥ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን በጠቅላላም ሰፈራቸውን ሁሉ እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽተው ሄደዋል። አራቱ ሰዎች ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ውስጥ ገቡ፤ በዚያም ያገኙትን ነገር ሁሉ በልተውና ጠጥተው ያገኙትን ብር፥ ወርቅና ልብስ ይዘው ሄደው ደበቁ፤ እንደገናም ተመልሰው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት እንደዚያው አደረጉ፤ ከዚህም በኋላ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፥ “መልካም አላደረግንም! እነሆ፥ ዛሬ ታላቅ የምሥራች አግኝተናል፤ ይህንንም መልካም ዜና ደብቀን ልናስቀር አይገባንም! ይህን የምሥራች ሳንነግር እስኪ ነጋ ብንቆይ በእርግጥ ቅጣት ይደርስብናል፤ ስለዚህም አሁኑኑ ሄደን ለንጉሡ የጦር መኰንኖች እንንገር!” ከዚያም በኋላ ከሶርያውያን ሰፈር በመነሣት ወደ ሰማርያ ተመልሰው ሄዱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የከተማይቱን ቅጽር በር ዘበኞች ጠርተው “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ምንም ያየነው ሰው ወይም የሰማነው ድምፅ እንኳ የለም፤ ፈረሶችና አህዮች እንደ ታሰሩ ናቸው፤ ድንኳኖቹም ሶርያውያን ትተዋቸው ስለ ሄዱ ባዶአቸውን ናቸው” ሲሉ ነገሩአቸው። ዘብ ጠባቂዎቹም ወሬውን ስለ ነዙት እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ተሰማ። ጊዜውም ገና ሌሊት ነበር፤ ንጉሡ ግን ከመኝታው ተነሥቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለ ሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፤ “የሶርያውያንን ዕቅድ ልንገራችሁ! እነርሱ በዚህ ስላለው ራብ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ሰፈራቸውን ለቀው በገጠር ለመሸሸግ ሄደዋል፤ እኛም ምግብ ፍለጋ ብንወጣ ከነሕይወታችን ማርከው ከተማችንን ይወስዳሉ።” ከባለሟሎቹም አንዱ “በዚህች ከተማ ውስጥ የተረፈው ሕዝብ ከዚህ በፊት እንደ ሞቱት ሰዎች ሁሉ ከሞት የሚያመልጥ አይደለም፤ ስለዚህ የሆነውን ነገር ማወቅ እንድንችል ጥቂት ሰዎችን መርጠን ከሞት ከተረፉት አምስት ፈረሶች ጋር እንላክ” ሲል ሐሳብ አቀረበ። እነርሱም ጥቂት ሰዎችን መረጡ፤ ንጉሡም እነዚያን ሰዎች በሁለት ሠረገሎች እንዲቀመጡ አድርጎ በሶርያውያን ሠራዊት ላይ የደረሰውን ሁኔታ መርምረው እንዲመለሱ መመሪያ በመስጠት ላካቸው። ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ዘልቀው ሄዱ፤ በየመንገዱም ሶርያውያን ሲሸሹ ጥለውት የሄዱትን ልብስና መሣሪያ ሁሉ አዩ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰው መጥተው ይህን ሁሉ ለንጉሡ ነገሩ። ሕዝቡም በፍጥነት እየተራወጠ ወጥቶ የሶርያን ሰፈር ዘረፈ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ በተናገረውም መሠረት ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ተሸመተ። በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ የከተማይቱ ቅጽር በር የቅርብ ባለሟሉ በሆነው አገልጋዩ ኀላፊነት ሥር እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ያንን አገልጋይ ሕዝቡ ስለ ረጋገጠው በዚያ ሞተ፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ኤልሳዕን ለማነጋገር በሄደ ጊዜ ኤልሳዕ በዚያ አገልጋይ ላይ የተናገረበት የትንቢት ቃል ስለ ተፈጸመ ነው። በዚያን ጊዜ ኤልሳዕ ለንጉሡ “በነገው ዕለት በሰማርያ ከተማ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ብሎ ነግሮት ነበር፤ ለዚህም ቃል ያ አገልጋዩ የሰጠው መልስ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” የሚል ነበር። ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም” ብሎት ነበር። እንግዲህ ያ አገልጋይ በሰማርያ ከተማ ቅጽር በር ላይ ሕዝብ ረጋግጦት ለመሞት የበቃው ይህ ትንቢት ስለ ተፈጸመበት ነበር። ልጇን ከሞት ያስነሣላትን፥ በሱነም ትኖር የነበረችውን ሴት እነሆ፥ ኤልሳዕ አስቀድሞ እንዲህ ሲል ነግሮአት ነበር፥ “እግዚአብሔር እስከ ሰባት ዓመት የሚቆይ ራብ በዚህች ምድር ላይ ልኮአል፤ ከቤተሰብሽ ጋር በሕይወት ለመትረፍ ከዚህ ተነሥተሽ ወደ ሌላ ስፍራ ሂጂ።” ስለዚህም የኤልሳዕን ምክር ሰምታ ከነቤተሰብዋ ወደ ፍልስጥኤም አገር በመሰደድ እስከ ሰባት ዓመት ቆየች። ከሰባቱም የራብ ዓመቶች ፍጻሜ በኋላ ወደ እስራኤል ተመለሰች፤ መኖሪያ ቤትዋና የእርሻ መሬትዋ እንዲመለስላት ለመጠየቅ ወደ ንጉሡ ቀረበች። ንጉሡንም የኤልሳዕ አገልጋይ ከሆነው ከግያዝ ጋር ሲነጋገር አገኘችው፤ ንጉሡ ከግያዝ ጋር የሚነጋገረውም ኤልሳዕ ስላደረጋቸው ተአምራት ለማወቅ ፈልጎ ነበር፤ ኤልሳዕ የሞተ ሰው ማስነሣቱን ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ጊዜ ሴቲቱ መጥታ አቤቱታዋን ለንጉሡ አቀረበች፤ ግያዝ “ንጉሥ ሆይ! ሴትዮዋ እነሆ፥ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣውም ልጇ ይሄ ነው!” በማለት ለንጉሡ አስረዳ። ግያዝ ለንጉሡ የሰጠውን መልስ ሴትዮዋ ለንጉሡ እውነት መሆኑን አረጋገጠችለት፤ ስለዚህም ንጉሡ አንድ ባለ ሥልጣን ጠርቶ፥ የእርሷ የሆነው ማናቸውም ነገርና እንዲሁም የእርሻ መሬትዋ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያስገኘው የእህል ሰብል ጭምር እንዲመለስላት ትእዛዝ ሰጠላት። የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ በታመመ ጊዜ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ ንጉሡም የኤልሳዕን መምጣት ሰማ፤ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለ ሥልጣኖች አንዱ የሆነውን አዛሄልን ጠርቶ፥ “ለነቢዩ ስጦታ ይዘህ ሂድና እኔ ከዚህ በሽታ እድን ወይም አልድን እንደሆነ እግዚአብሔርን እንዲጠይቅልኝ ለምነው” አለው። ስለዚህም አዛሄል በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ የምድር በረከት ሁሉ በአርባ ግመሎች ጭኖ ወደ ኤልሳዕ ሄደ፤ አዛሄልም ኤልሳዕን ባገኘው ጊዜ “ልጅህ ንጉሥ ቤንሀዳድ ከሕመሙ ይድን ወይም አይድን እንደሆነ እንድትነግረው እጠይቅህ ዘንድ ልኮኛል” አለው። ኤልሳዕም “ቤንሀዳድ እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል፤ አንተ ግን ትድናለህ ብለህ ንገረው” አለው፤ ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ፊቱን በማጥቆር በሚያስፈራ ሁኔታ አዛሄልን ተመለከተው፤ ከዚህም የተነሣ አዛሄል ተጨነቀ፤ ወዲያውም ኤልሳዕ እንባውን ማፍሰስ ጀመረ፤ አዛሄልም “ጌታዬ ስለምን ታለቅሳለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም “በእስራኤል ሕዝብ ላይ የምትፈጽመውን አሠቃቂ ነገር ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ወጣቶቻቸውን ታርዳለህ፤ ሕፃናታቸውን በድንጋይ ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ እርጉዞች የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትሰነጥቃለህ” ሲል መለሰለት። አዛሄልም “እኔ ለምንም የማልጠቅም ኢምንት ነኝ! ታዲያ ይህን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችለውን ኃይል ከቶ ከየት አገኛለሁ?” ሲል ጠየቀ። ኤልሳዕም “አንተ የሶርያ ንጉሥ እንደምትሆን እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት። ከዚህም በኋላ አዛሄል ተመልሶ ሲመጣ “ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ቤንሀዳድ ጠየቀው። አዛሄልም “አንተ በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት። ነገር ግን በማግስቱ አዛሄል ብርድልብስ ወስዶ ውሃ ውስጥ ነከረ፤ በዚያም ንጉሡን አፍኖ ገደለው። አዛሄልም በቤንሀዳድ እግር ተተክቶ የሶርያ ንጉሥ ሆነ። የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ። ሚስቱም የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች እንደ አክዓብ ቤተሰብ የእስራኤል ነገሥታት ይፈጽሙት የነበረውን የክፋት መንገድ ተከተለ፤ በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እግዚአብሔር ግን ከዘሩ መንግሥትን እንደማያጠፋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ተስፋ ሰጥቶት ስለ ነበር ይሁዳን መደምሰስ አልፈለገም። በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐመፀ፤ የራሱንም ነጻ መንግሥት ዐወጀ፤ ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን በመላ አሰልፎ ወደ ጻዒር ዘመተ፤ የኤዶም ሠራዊትም ከበባቸው፤ በሌሊትም እርሱና የሠረገላዎቹ አዛዦች ከበባውን ጥሰው ሲያመልጡ፥ ወታደሮቹ ወደየቤታቸው ተበታተኑ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤዶም ከይሁዳ ተገዢነት ነጻ ወጣች፤ በዚያኑ ጊዜም የልብና ከተማ ዐመፀች። ኢዮራም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ኢዮራም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ ውስጥ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አንድ ዓመት ብቻ ገዛ፤ እናቱ ዐታልያ ተብላ የምትጠራው የአክዓብ ልጅ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች። አካዝያስ የንጉሥ አክዓብ ዐማች ከመሆኑ የተነሣ ልክ እንደ አክዓብ ቤተሰብ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ። በሶርያው ንጉሥ አዛሄል ላይ በታወጀው ጦርነት፥ ንጉሥ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ተባባሪ በመሆን ዘመተ፤ የሁለቱም ነገሥታት ሠራዊት ከሶርያውያን ሠራዊት ጋር በገለዓድ በምትገኘው በራሞት ጦርነት በገጠመ ጊዜ ኢዮራም በውጊያው ላይ ቆሰለ፤ ኢዮራምም ከንጉሥ አዛሄል ጋር ሆኖ በሬማት በተደረገው ጦርነት የደረሰበትን ቁስል ለመፈወስ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ተመለሰ። የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በደረሰበት ጉዳት እርሱን ለመጠየቅ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ። በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ደቀመዛሙርቱ ከሆኑት ነቢያት አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ራሞት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሣፍጥ ልጅ፥ የኒምሺ የልጅ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በማስገለል ወደ ጓዳ አስገባው፤ ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበት፤ ‘አንተ ተቀብተህ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ ብለህም ንገረው፤ ከዚህም በኋላ በሩን በመክፈት በተቻለ ፍጥነት ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ።” ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ራሞት ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ የጦር መኰንኖች ተቀምጠው ሲወያዩ አግኝቶ “ጌታዬ ለአንተ የምሰጥህ መልእክት አለኝ” አለው። ኢዩም “ከእኛ መካከል ለማንኛችን ነው የምትናገረው?” ሲል ጠየቀው። ነቢዩም “የምናገረው ለአንተው ነው” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ ሁለቱ ወደ ቤት ውስጥ ገብተው ወጣቱ ነቢይ የወይራውን ዘይት በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ አድርጌሃለሁ፤ አንተም የአክዓብ ልጅ የሆነውን ጌታህን ንጉሡን መግደል አለብህ፤ በዚህም ዓይነት የእኔን ነቢያትና ሌሎችንም አገልጋዮቼን የገደለችውን ኤልዛቤልን እበቀላታለሁ፤ መላው የአክዓብ ቤተሰብና ትውልዱ ሁሉ መሞት አለባቸው፤ እኔ ከእርሱ ቤተሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባርያም ሆነ ነጻ ሰው አስወግዳለሁ። የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምና በአኪያል ልጅ በበዕሻ ቤተሰቦች ላይ ያደረግኹትን፥ ሁሉ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ እፈጽማለሁ። ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የእርሷም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤’” ይህን ሁሉ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወጣቱ ነቢይ በሩን በመክፈት ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ። ኢዩም፦ ጓደኞቹ ወደ ሆኑት ወደ ጦር መኰንኖቹ በመጣ ጊዜ “ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ከአንተ ምን ይፈልጋል?” ሲሉ ጠየቁት። ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ” አላቸው። እነርሱም “ኧረ እኛ አናውቅም፤ ምን እንደ ተናገረ አስረዳን!” ሲሉ መለሱለት። ኢዩም፦ “‘በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ አለኝ” ሲል አስረዳቸው። ወዲያውኑ የኢዩ ጓደኞች የነበሩት የጦር መኰንኖች ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢዩ ነግሦአል!” ሲሉ ጮኹ። ስለዚህ የናሜሲ የልጅ ልጅ፥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ አሤረ። በዚህ ጊዜ ኢዮራምና እስራኤል ሁሉ በሬማት የምትገኘውን ገለዓድን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጥቃት ለማዳን ይጠብቁ ነበር። ንጉሥ ኢዮራም ግን የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ጦርነት በገጠመው ጊዜ፥ ሶርያውያን ካደረሱበት ቊስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም፥ “እንግዲህ ሐሳባችሁ እንዲህ ከሆነ፥ ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፥ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ። ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቁስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ይገኝ ነበር። በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ቃፊር ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ መቃረባቸውን አይቶ፥ “ሰዎች እየጋለቡ ሲመጡ አያለሁ!” ሲል የጥሪ ድምፅ አሰማ። ኢዮራምም “አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ” አለው። መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን “ንጉሡ አመጣጥህ በወዳጅነት እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል” ሲል ጠየቀው። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት። በከተማይቱም መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ዘብ “መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ሲል አስረዳ፤ ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፤ ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት። “ዘበኛውም እንደገና መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ካለ በኋላ “የጭፍራው መሪ ሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው ነው! እንዲያውም ልክ ኢዩን ይመስላል!” ሲል ተናገረ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮራም “ሠረገላዬን አዘጋጅልኝ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት እርሱና ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላቸው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፤ እነርሱም ኢዩን ቀድሞ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት። ኢዮራምም “ኢዩ ሆይ፥ አመጣጥህ በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀ። ኢዩም፦ “እናትህ ኤልዛቤል ባመጣችው አስማትና የጣዖት አምልኮ ውስጥ ተነክረን እስካለን ድረስ ምን ሰላም አለ?” ሲል መለሰለት። ኢዮራምም ድምፁን ከፍ በማድረግ “አካዝያስ ሆይ! ይህ እኮ ክሕደት ነው!” እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ። ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኃይል በመጠቀም ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል እስከ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ። ኢዩ ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የቅርብ ረዳቱን “ሬሳውን አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው፤ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተ ኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፤ ‘ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ’ የሚል ነበር።” ስለዚህ ኢዩ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው” ሲል የቅርብ ረዳቱን አዘዘ። ንጉሥ አካዝያስ የሆነውን ነገር ሁሉ በተመለከተ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤትሀጋን ከተማ ሸሽቶ ሄደ፤ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው “እርሱንም ግደሉት!” ሲል ለወታደሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አካዝያስን ተከታትለው በዪብለዓም ከተማ አጠገብ በምትገኘው በጉር የአቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ሲበር መትተው አቆሰሉት፤ እርሱ ግን እንደ ምንም ጨክኖ መጊዶ ከተማ እስኪደርስ ተጓዘ፤ በዚያም ሞተ፤ ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት። አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር። በዚህም ጊዜ ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ደረሰ፤ ኤልዛቤልም ይህን የሆነውን ነገር ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጉርዋንም ተሠርታ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ በመስኮት አዘንብላ ቁልቁል መንገዱን ትመለከት ነበር። ኢዩ የቅጽሩን በር አልፎ ሲገባ “አንተ ዚምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ ደግሞ እዚህ ምን አመጣህ?” ስትል ጮኸችበት። ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?” ሲል ጮኸ፤ ቁጥራቸው ከሁለት እስከ ሦስት የሆነ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ብቅ ብለው ወደ እርሱ ተመለከቱ፤ ኢዩም “ኤልዛቤልን ወደ ታች ወርውሩአት!” አላቸው፤ እነርሱም አንሥተው በወረወሩአት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ፤ ኢዩም በሬሳዋ ላይ ፈረሶቹንና ሠረገላውን ነዳበት፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም ገብቶ ተመገበ፤ ከዚህም በኋላ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ነችና፥ ያችን የተረገመች ሴት ወስዳችሁ ቅበሩ” አለ። ሊቀብሩአት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፥ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ አጥንት በቀር ምንም አላገኙም፤ ይህንንም ሁሉ ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “ይህ ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ ቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‘የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤ ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርሷነትዋን ለይቶ በማወቅ፦ ይህች ኤልዛቤል ናት፥ ሊል አይችልም’ ያለው ነው።” ብዛታቸው ሰባ የሚሆን የአክዓብ ልጆች በሰማርያ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ የደብዳቤውን አንዳንድ ቅጂ ለከተማይቱ ገዢዎች፥ ለታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና የአክዓብን ተወላጆች ለሚያሳድጉ ሞግዚቶች ሁሉ ላከ፤ የደብዳቤውም ቃል፥ “እናንተ ለንጉሡ ተወላጆች ኃላፊዎች ናችሁ፤ ፈረሶችና ሠረገሎች የጦር መሣሪያዎችና የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ በእናንተ እጅ ይገኛሉ፤ እንግዲህ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ፥ ከንጉሡ ተወላጆች የተሻለውን አንዱን መርጣችሁ አንግሡት፤ ለእርሱም በመከላከል ተዋጉለት!” የሚል ነበር። ከዚህም የተነሣ የሰማርያ ገዢዎች በፍርሃት ተሸብረው፥ “ንጉሥ ኢዮራምና ንጉሥ አካዝያስ ሊቋቋሙ ያልቻሉትን እኛ እንዴት ኢዩን ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ። ስለዚህም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊና የከተማይቱ ገዢ ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና ከአሳዳጊ ሞግዚቶች ጋር በመተባበር ለኢዩ “እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ አንተ የምታዘንን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ አንተ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ሲሉ መልእክት ላኩ። ኢዩም “እናንተ ከእኔ ጋር ከተባበራችሁና ትእዛዜንም ለመፈጸም ዝግጁዎች ከሆናችሁ፥ ነገ በዚህ ጊዜ የንጉሥ አክዓብን ዘሮች ሁሉ ራሶቻቸውን ቆርጣችሁ ይዛችሁልኝ ኑ” ሲል ሌላ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ሰባው የንጉሥ አክዓብ ተወላጆች በሰማርያ አሳዳጊዎቻቸው በሆኑ በታወቁ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ ሥር ነበሩ፤ የኢዩ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው የሰማርያ መሪዎች ሰባውንም የአክዓብ ተወላጆች በሙሉ ገደሉ፤ ራሶቻቸውንም በመቁረጥ በቅርጫት ሞልተው በኢይዝራኤል ወደነበረው ወደ ኢዩ ላኩለት። ኢዩ የአክዓብ ትውልድ ራሶች ተቆርጠው መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በከተማይቱ ቅጽር በር በሁለት ረድፍ ተከምረው እስከ ተከታዩ ቀን ጧት ድረስ እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጠ፤ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር ሄዶ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “በንጉሥ ኢዮራም ላይ በማሤር የገደልኩት እኔ ነበርኩ፤ ስለዚህም እናንተ በዚያ ጉዳይ አትጠየቁበትም፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የገደለ ማን ነው? ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈጽሞታል።” ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶች፥ ባለሟሎቹ የነበሩትን ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ። ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም “የእረኞች ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፥ ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢዩም “እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!” ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸውና ኢዩ በዚያው በውሃ ጉድጓድ አጠገብ ገደላቸው። ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም። ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጉዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “እኔና አንተ በሐሳብ አንድ ነን፤ ታዲያ ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም “አዎ እተባበርሃለሁ” ሲል መለሰ። ኢዩም “እንግዲያውስ ጨብጠኝ” ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠውና፥ “ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያኽል ታማኝ እንደሆንኩ ራስህ ተመልከት” አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር። ኢዩ የሰማርያን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ንጉሥ አክዓብ በዓልን ያገለገለው በመጠኑ ነበር፤ እኔ ግን ከእርሱ ይበልጥ ላገለግለው እፈልጋለሁ፤ ስለዚህም የበዓልን ነቢያት በሙሉ፥ በዓልን የሚያመልኩትንና ካህናቱን ጭምር በአንድነት ጠርታችሁ ሰብስቡልኝ፤ በምንም ምክንያት የሚቀር አይኑር፤ እኔ ለበዓል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ በዚያ የማይገኝ ማንም ሰው ቢኖር በሞት ይቀጣል።” ይህም ሁሉ በዓልን የሚያመልኩትን ሁሉ ለመግደል ኢዩ ያቀደው የተንኰል ዘዴ ነበር። ከዚህም በኋላ ኢዩ “በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት ክብረ በዓል ይደረግ!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህም በዐዋጅ ተነገረ። ኢዩም በእስራኤል ምድር ሁሉ መልእክት አስተላለፈ፤ በዓልን የሚያመልኩ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ አንድም እንኳ የቀረ ሰው አልነበረም፤ ሁሉም ወደ በዓል ቤተ መቅደስ ገብተው ዳር እስከ ዳር ሞሉት፤ ከዚህም በኋላ ኢዩ የተቀደሱ አባላት ኃላፊ የሆነውን ካህን አልባሳቱን ሁሉ አውጥቶ ለበዓል አምላኪዎች ያጐናጽፋቸው ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ኢዩ ራሱ የሬካብ ልጅ ከሆነው ከኢዮናዳብ ጋር አብሮ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ፤ በዚያም ለሕዝቡ “እንግዲህ በዚህ የሚገኙት የበዓል አምላኪዎች ብቻ መሆናቸውንና እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንድም አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ” ሲል ተናገረ፤ ወዲያውም እርሱና ኢዮናዳብ ለበዓል የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ፤ ከዚህም ቀደም ብሎ ኢዩ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰማኒያ ወታደሮች በማሰለፍ “እነዚህን ሁሉ ሰዎች እንድትገድሉ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ እንዲያመልጥ የሚያደርግ ማንም ሰው ቢኖር በዚያ ሰው ምትክ እርሱ ራሱ ይገደላል!” ሲል መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር። ኢዩ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ወዲያውኑ ለዘብ ጠባቂዎችና ለጦር መኰንኖች “ገብታችሁ እነዚህን ሁሉ ግደሉ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሰይፍ ሰይፋቸውን በመምዘዝ ገብተው ሁሉንም ገደሉ፤ ሬሳቸውንም ሁሉ እየጐተቱ ወደ ውጪ አወጡት፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ገብተው፥ በዚያ ያመልኩት የነበረውን የድንጋይ ዐምድ ወደ ውጪ አውጥተው በእሳት አቃጠሉት፤ በዚህም ዓይነት ጣዖት አምላኪዎቹ የተቀደሰ ነው ብለው የሚያምኑበትን የድንጋይ ዐምድና ቤተ መቅደሱን አፈራረሱ፤ ቤተ መቅደሱንም መጸዳጃ አደረጉት፤ ዛሬም በዚሁ ዓይነት ይገኛል። ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የበዓልን ጣዖታዊ አምልኮ ያስወገደው በዚህ ዓይነት ዘዴ ነበር፤ ነገር ግን ኢዩ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን የኃጢአት መንገድ ከመከተል አልተገታም፤ ኢዩ ራሱ ቀደም ሲል የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤልና በዳን ላቆማቸው የወርቅ ጥጃ ምስሎች መስገዱ አልቀረም። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ኢዩን “በአክዓብ ተወላጆች ሁሉ ላይ ልታደርግ የሚገባህን ባዘዝኩህ መሠረት ፈጽመሃል፤ ከዚህም የተነሣ የአንተ ትውልድ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ላይ እንደሚነግሡ የተስፋ ቃል እሰጥሃለሁ” አለው። ኢዩ ግን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራቸውን የኢዮርብዓምን ክፉ አርአያነት ተከተለ። በዚያም ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤል ግዛት ስፋቱ እንዲቀነስ ማድረግ ጀመረ፤ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤልን ድል ነሥቶ የእስራኤልን ግዛት ሁሉ ያዘ። እርሱም የያዘው ግዛት፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፥ በስተ ደቡብ በኩል ከአርኖን ወንዝ በላይ እስከምትገኘው እስከ አሮዔር ከተማ የሚደርስ ሲሆን ይህም የጋድ፥ የሮቤልና በምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩባቸው የነበሩትን የገለዓድንና የባሳንን ግዛቶች ያጠቃልላል። ኢዩ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ከዚህም በኋላ ኢዩ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ፤ ኢዩ መኖሪያውን በሰማርያ በማድረግ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበር። የንጉሥ አካዝያስ እናት ዐታልያ የልጇን መገደል እንደ ሰማች ወዲያውኑ የይሁዳ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጠች። ከእርሷም እጅ ማምለጥ የቻለ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ እርሱም እንኳ ከሌሎቹ ጋር እንዲገደል ተመክሮበት ነበር፤ ነገር ግን አክስቱ የነበረችው በአባትዋ በኩል የንጉሥ አካዝያስ እኅት የሆነችው፥ የንጉሥ ኢዮራም ልጅ ይሆሼባዕ በመደበቅ ከሞት አዳነችው፤ እርሷም እርሱንና ሞግዚቱን ወስዳ በቤተ መቅደሱ ግቢ በሚገኘው ማረፊያ ክፍል ውስጥ ስለ ደበቀችው በዐታልያ እጅ ሳይገደል ቀረ። ዐታልያ በነገሠችበትም ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ፥ ይሆሼባዕ ሕፃኑን ኢዮአስን በቤተ መቅደስ በመንከባከብ አሳደገችው። ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ለንጉሡ ክብር ዘቦችና ለቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ሁሉ ኃላፊዎች ወደ ሆኑት የጦር መኰንኖች ሁሉ ልኮ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አስጠራቸው፤ በዚያም ሊያደርገው ያቀደውን ይስማሙበት ዘንድ በመሐላ እንዲያረጋግጡለት አደረገ፤ ከዚያም በኋላ የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን አሳያቸውና፥ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ በምትሰማሩበት ጊዜ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ የሱርን የቅጽር በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሦስተኛ እጅ ደግሞ ከሌሎቹ ዘቦች በስተ ኋላ ያለውን ቅጽር በር ይጠብቅ። በሰንበት ቀን ከዘብ ጥበቃ ነጻ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ግን በንጉሡ ላይ አደጋ እንዳይደርስበት ለመከላከል ቤተ መቅደሱን ይጠብቁ፤ ንጉሥ ኢዮአስን በዙሪያው በምትጠብቁበትም ጊዜ ሰይፋችሁን መዛችሁ ወደሚሄድበት ስፍራ ሁሉ አብራችሁ ሂዱ፤ ወደ እናንተ ለመቅረብ የሚደፍር ማንም ቢኖር ይገደል።” የጦር መኰንኖቹም ዮዳሄ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ የሚሰማሩትንና ከዘብ ጥበቃም የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ጭምር አሰልፈው ወደ እርሱ አመጡ። ዮዳሄም በቤተ መቅደስ ተቀምጠው ይጠበቁ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች አውጥቶ ለጦር አለቆቹ ሰጣቸው፤ ጭፍሮቹም ሰይፋቸውን እንደ መዘዙ ንጉሡን ከአደጋ ለመከላከል በመሠዊያው በኩል በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ዙሪያውን እንዲሰለፉ አደረጋቸው። ከዚያም በኋላ ዮዳሄ ኢዮአስን አውጥቶ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነበት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጂ አስረከበው፤ በዚህ ዓይነት ኢዮአስ ተቀብቶ ነገሠ፤ ሕዝቡም እያጨበጨበ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ!” አለ። ንግሥት ዐታልያም የክብር ዘቦቹንና የሕዝቡን ጩኸት ድምፅ በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት ቤተ መቅደስ ፈጥና ሄደች። እዚያም እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባህል መሠረት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ ቆሞ አየችው፤ እርሱም በጦር አዛዦችና በእምቢልታ ነፊዎች ታጅቦ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል እያሉ እምቢልታ ይነፉ ነበር፤ ዐታልያም በድንጋጤ ልብስዋን ቀዳ “ይህ በክሕደት የተፈጸመ ሤራ ነው! ሤራ ነው!” ስትል ጮኸች። ዮዳሄ በበኩሉ ዐታልያ በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ እንድትገደል አልፈለገም፤ ስለዚህም የጦር አለቆቹን “ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርሷን ለመከተል የሚሞክር ቢኖር ይገደል” ሲል አዘዛቸው። እነርሱም እርሷን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያም የፈረስ መግቢያ ቅጽር በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት። ዮዳሄ፥ ንጉሡና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፤ እንዲሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ። ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ወደ በዓል ቤተ መቅደስ ሄዶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበረ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የበዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደለው። ዮዳሄ ቤተ መቅደሱን በየተራ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ፤ ከዚህም በኋላ እርሱ፥ የጦር አለቆች፥ የንጉሡ ክብር ዘብና የቤተ መንግሥቱ ዘብ ጠባቂዎች ንጉሡን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት አጅበው እንዲሄዱና ሕዝቡም ሁሉ ከኋላ እንዲከተል አደረገ፤ ኢዮአስም በዘብ ጠባቂዎች ቅጽር በር በኩል ገብቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። ዐታልያ ስለ ተገደለች ሰው ሁሉ ተደሰተ፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ኢዮአስም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር። ኢዩ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ ዓመት ገዛ፤ የእርሱ እናት ጺቢያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች። ካህኑ ዮዳሄ ይመክረውና ያስተምረው ስለ ነበር፥ ኢዮአስ በዕድሜው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታዎች ላይ የሚገኙት የአሕዛብ ማምለኪያዎች ስላልተደመሰሱ፥ ሕዝቡ በዚያ ዕጣን እያጠኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር። ኢዮአስም ካህናቱን ጠርቶ በቤተ መቅደስ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ መባ ሆኖ የሚገባውን ገንዘብ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አዘዘ፤ ይኸውም ቋሚ ከሆነው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር መባ ሆኖ የሚቀርበውንና በበጎ ፈቃድ ሕዝቡ የሚያመጣውን ስጦታ ሁሉ የሚያጠቃልል ነበር። እያንዳንዱ ካህን ከሚያገለግላቸው ሰዎች የሚገኘውን የገንዘብ መባ ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጠው፤ ገንዘቡንም እንዳስፈላጊነቱ ለቤተ መቅደሱ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሉት ነገራቸው። ነገር ግን ኢዮአስ እስከ ነገሠበት እስከ ሀያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ላይ ምንም ዓይነት እድሳት አላደረጉም፤ ስለዚህም ኢዮአስ ዮዳሄንና ሌሎቹንም ካህናት ወደ እርሱ ጠርቶ “ቤተ መቅደሱን ያላደሳችሁበት ምክንያት ምንድነው? ከዛሬ ጀምሮ የምትቀበሉትን ገንዘብ መያዝ የለባችሁም፤ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ይውል ዘንድ ገንዘቡን አስረክቡ” አላቸው። ካህናቱም በዚህ ተስማምተው ቤተ መቅደሱን ለማደስ የነበራቸውን ተግባር አቆሙ። ከዚህ በኋላ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም ወስዶ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ በስተ ቀኝ በሚገኘው መሠዊያ አጠገብ አኖረው፤ የየዕለቱ ተረኞች የነበሩትም ካህናት ለስግደት የሚመጡት ሰዎች የሚሰጡትን የገንዘብ መባ እየተቀበሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡት ነበር፤ ሣጥኑም በሚሞላበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ እየመጡ ብሩን በመቁጠር በከረጢት እያሰሩ ያኖሩት ነበር። ትክክለኛውንም ሒሳብ አጣርተው ከመዘገቡ በኋላ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ ኃላፊዎች ያስረክቡ ነበር፤ እነርሱም ገንዘቡን ተረክበው ለአናጢዎችና፥ ለግንበኞች ይሰጡ ነበር፥ ለድንጋይ ጠራቢዎች፥ ለማደሻ አገልግሎት የሚውል እንጨትና ድንጋይ ለሚገዙና እንዲሁም ለልዩ ልዩ አስፈላጊ ነገሮች ለሚውል ተግባር ሁሉ ይከፍሉ ነበር። ሆኖም ከብር ለሚሠሩ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያ፥ ጐድጓዳ ወጭት፥ እምቢልታ ወይም ደግሞ ከብርም ሆነ ከወርቅ ለሚሠሩ ንዋያተ ቅድሳት ከዚያ ገንዘብ ላይ ተነሥቶ የሚከፈል ሒሳብ አልነበረም። ያ ገንዘብ በሙሉ በቤተ መቅደሱ እድሳት ተግባር ላይ ለተሰማሩት ሠራተኞች ብቻ የሚውል ነበር። ለሥራው ኃላፊነት የተመረጡትም ሰዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ነበሩ ገንዘቡን የሰጡአቸውን ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር። ስለ በደልና ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚከፈለው ገንዘብ ግን ለካህናቱ ጥቅም የሚውል እንጂ ወደ ቤተ መቅደሱ ሣጥን ውስጥ አይገባም ነበር። በዚያን ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በጋት ከተማ ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ቀጥሎም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ወሰነ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስም ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነገሥታት፥ ማለትም ኢዮሣፍጥ፥ ኢዮራምና አካዝያስ ለእግዚአብሔር ለይተው ያኖሩትን መባና የራሱን መባ ጨምሮ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች የነበረውን ወርቅ ሁሉ በመሰብሰብ ገጸ በረከት አድርጎ ለንጉሥ አዛሄል ላከለት፤ አዛኤልም ይህን ተቀብሎ ሠራዊቱን ከኢየሩሳሌም መለሰ። ንጉሥ ኢዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። የቀረውም የኢዮአስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ባርያዎቹም ተነሥተው ዐመፁበት፥ ወደ ሲላ በሚወርደውም መንገድ በሚሎ ቤት ገደሉት። ባርያዎቹም የሰምዓት ልጅ ዮዘካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት መቱት፥ ሞተም፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፥ ልጁም አሜስያስ በፋንታው ነገሠ። የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በይሁዳ በነገሠ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እርሱም ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እስራኤልንም ወደ ኃጢአት መራ፤ ከክፉ ሥራውም ከቶ አልተገታም። ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ለሶርያ ንጉሥ አዛሄል፥ እንዲሁም ለልጁ ለቤንሀዳድ በተደጋጋሚ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል። ከዚህ በኋላ ኢዮአካዝ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ የፈጸመባቸው ግፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ተመልክቶ የኢዮአካዝን ጸሎት ሰማ። ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤልን ከሶርያውያን እጅ ነጻ የሚያወጣቸው መሪ ላከላቸው፤ እነርሱም ከዚያ በፊት በነበረው ዓይነት በሰላም ኖሩ። ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ኢዮርብዓም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከበደል ሥራቸው አልተመለሱም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በኃጢአታቸው ጸንተው አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል በሰማርያ ማምለክ ቀጠሉ። ንጉሥ ኢዮአካዝ ከኀምሳ ፈረሰኞች፥ ከዐሥር ሠረገሎችና ከዐሥር ሺህ ወታደሮች በቀር ሌላ የተደራጀ የጦር ኃይል አልነበረውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሌላውን ሠራዊቱን የሶርያ ንጉሥ በአውድማ እንዳለ እብቅ ስለ ደመሰሰበት ነው። ንጉሥ ኢዮአካዝ የፈጸመው ሌላው ተግባርና የጀግንነት ሥራው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢዮአካዝ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ዮአስ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ። ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፥ ድምፁን ከፍ በማድረግ “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!” እያለ አለቀሰለት። ኤልሳዕም ንጉሡን “አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ” ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደ ታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም “ፍላጻዎቹን ለማስፈንጠር ተዘጋጅ” አለው፤ ንጉሡም እንደ ታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ። ኤልሳዕ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም “ፍላጻውን አስፈንጥር!” አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፥ “ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ።” ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን “ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!” አለው። ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፤ ይህም ኤልሳዕን አስቆጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ” አለው። ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም። ከሞዓብ የሚመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወሩ ነበር። አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጽምበት ሰዓት ከእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለ ታየ፥ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኰላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስከሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ። ኢዮአካዝ በነገሠበት ዘመን ሁሉ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤላውያንን በመጨቆን ያስጨንቃቸው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ ምሕረትን በማድረግ ረዳቸው እንጂ እንዲደመሰሱ አልፈቀደም፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን ቃል ኪዳን በማሰብ ሕዝቡን ስላልረሳው ነው። የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በሞተ ጊዜ፥ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ ቤንሀዳድ ነገሠ። ከዚህም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ቤንሀዳድን ሦስት ጊዜ ድል ነሥቶ በአባቱ በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ቤንሀዳድ ይዞአቸው የነበሩትን ከተሞች አስመለሰ። የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሀያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ከኢየሩሳሌም ይሆዓዲን ተብላ የምትጠራ ነበረች። አሜስያስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቶአል፤ ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞ አያቱ እንደ ንጉሥ ዳዊት አልነበረም፤ እንደ ዳዊት በመሆን ፈንታ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ። ይኸውም በየኰረብታዎች ላይ የተሠሩትን የአሕዛብ ማምለኪያዎችን አላፈረሰም፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ በየኮረብታዎቹ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጠኑን እንደ ቀጠለ ነበር። አሜስያስ መንግሥቱን አደላድሎ እንደ ያዘ ወዲያውኑ፥ ቀደም ሲል ነግሦ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባለ ሥልጣኖች በሞት ቀጣ፤ ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ይልቁንም በኦሪት ሕግ እግዚአብሔር “ልጆቻቸው በፈጸሙት ኃጢአት ወላጆች በሞት አይቀጡበትም፤ ወላጆችም በፈጸሙት ኃጢአት ልጆች በሞት አይቀጡበትም፤ እያንዳንዱ ሰው ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ በሞት ይቀጣ” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሞአል። አሜስያስ “የጨው ሸለቆ” እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ዐሥር ሺህ የሚሆኑ የኤዶም ወታደሮችን ፈጀ፤ ሴላዕ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ይዞ “ዮቅትኤል” ብሎ ጠራት፤ እስከ አሁንም በዚሁ ስም ትጠራለች። ከዚህ በኋላ አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞች በመላክ “እንግዲህ ና ይዋጣልን!” ሲል ለጦርነት አነሣሣው፤ ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት “አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኲርንችት የሊባኖስ ዛፍ ‘ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ’ ስትል መልእክት ላከችበት፤ ነገር ግን አንድ የሊባኖስ አውሬ እግረ መንገዱን በዚያ ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኲርንችት ሞተች፤ አሜስያስ ሆይ! እነሆ፥ አንተም ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ በአገኘኸውም ድል በመደሰት ዐርፈህ በቤትህ ብትቀመጥ ይሻልሃል፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መቅሠፍትን የሚያስከትል ነገር ለመቆስቆስ ስለምን ትፈልጋለህ?” አሜስያስ ግን የዮአስን መልስ ከምንም አልቆጠረውም፤ ስለዚህም ንጉሥ ዮአስ ሠራዊቱን አስከትሎ በአሜስያስ ላይ በመዝመት በይሁዳ ምድር በምትገኘው በቤትሼሜሽ ጦርነት ገጠመው፤ ይሁዳም ድል ተመታ፤ ወታደሮቹም ሁሉ ተበታትነው ወደየቤታቸው ተመለሱ። ዮአስም የአካዝያስን ልጅ፥ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመድረስ ገሠገሠ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ከኤፍሬም ቅጽር በር “የማእዘን ቅጽር በር” ተብሎ እስከሚጠራው በር ድረስ ጠቅላላ ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር የሆነውን የቅጽር ግንብ አፈረሰ። በዚያም ያገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳትና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ሁሉ ጭኖ ወደ ሰማርያ ተመለሰ፤ በመያዣ ስም የተማረኩ ሰዎችንም ይዞ ሄደ። ንጉሥ ዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው የጀግንነት ሥራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ፥ የይሁዳ ንጉሥ የዮአስ ልጅ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ቆየ፤ አሜስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሜስያስን ለመግደል በኢየሩሳሌም ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ ስለዚህ አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ከተማ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶች ወደ ላኪሽ ሰዎችን ልከው እዚያ አስገደሉት። ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ። የይሁዳም ሕዝብ ዐሥራ ስድስት ዓመት ዕድሜ የነበረውን ልጁን ዖዝያን አነገሡ፤ ዖዝያም ቀድሞ ተይዛ የነበረችውን ኤላትን ከአባቱ ሞት በኋላ በጦር ኃይል ድል ነሥቶ በማስመለስ እንደገና ሠራት። የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ እርሱም መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ። ዳግማዊ ኢዮርብዓምም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ ከእርሱ በፊት የነበረውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ቀድሞ የእስራኤል ይዞታ የነበረውን በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ ጀምሮ በስተ ደቡብ እስከ ሙት ባሕር የሚገኘውን ግዛት ሁሉ ድል ነሥቶ እንደገና አስመለሰ፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በጋትሔፌር ተወላጅ አገልጋይ በሆነው በአሚታይ ልጅ በነቢዩ ዮናስ አማካይነት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ነው። እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን አሠቃቂ መከራ ተመለከተ፤ በእስራኤል ውስጥ ባርያዎችም ሆኑ ነጻ ሰዎች፥ ረዳት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ እነርሱ ለዘለዓለም ፈጽሞ እንዲደመሰሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፤ ስለዚህም በዳግማዊ ኢዮርብዓም አማካይነት አዳናቸው። ዳግማዊ ኢዮርብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነት፥ እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩት ደማስቆና ሐማት ለእስራኤል እንዲመለሱ ያደረገበት ታሪካዊ ዝክረ ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ሞተ፤ በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ዘካርያስ ነገሠ። ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሀያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዖዝያ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኃምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አልደመሰሰም፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ በኋላም እግዚአብሔር በዖዝያ ላይ የቆዳ በሽታ አሳደረበት፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቆየው ልጁ ኢዮአታም ነበር። ንጉሥ ዖዝያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ዖዝያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ስድስት ወር ገዛ፤ እርሱም ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ ሻሉም ተብሎ የሚጠራው የያቤሽ ልጅ ሤራ በማድረግ ዪብለዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ” ሲል የተናገረው የተስፋ ቃል ተፈጸመ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የያቤሽ ልጅ ሻሉም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ አንድ ወር ብቻ ገዛ። ምናሔም ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ሻሉምንም ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። ሻሉም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ እግረ መንገዱን የቲፍሳሕን ከተማ፥ ነዋሪዎችዋንና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ዐሥር ዓመት ገዛ። እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለቲግላት ፐሌሴር ሰጠው። ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እያንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር። በዚህም ዓይነት ቲግላት ፐሌሴር በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ። ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ምናሔም ሞተ፤ ተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ፈቃሕያ ነገሠ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፈቃሕያ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ከፈቃሕያ ሠራዊት መካከል ፈቁሔ ተብሎ የሚጠራ የረማልያ ልጅ የሆነ አንድ የጦር መኰንን ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፈቃሕያን ከአርጎብና ከሃርዬ ጋር ገድሎ በፈቃሕያ እግር ተተክቶ ነገሠ። ፈቃሕያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኃምሳ ሁለተኛው ዓመት የረማልያ ልጅ ፈቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሀያ ዓመት ገዛ። እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነትን በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ዒዮን፥ አቤልቤትማዕካ፥ ያኖሐ፥ ቄዴሽና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች፥ እንዲሁም የገለዓድን፥ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደውም ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር። የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ፈቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሩሻ ተብላ የምትጠራ የጻዶቅ ልጅ ነበረች። የአባቱንም የዖዝያን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ መሠዊያዎችን አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጽር በር ያሠራ ይኸው ኢዮአታም ነበር። ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና፥ የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፤ ኢዮአታም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ። የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ ዓመት ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እርሱም የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት አልተከተለም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ አምላኩን እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ሥራ ሠራ፤ የእስራኤልንም ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ የገዛ ልጁን እንኳ ሳይቀር ለጣዖቶች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ይህንንም የፈጸመው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ አገር ለመግባት ወደ ፊት እየገፉ በመጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያች ምድር ነቃቅሎ ያስወገዳቸው አሕዛብ ይሠሩት የነበረውን አጸያፊ ድርጊት በመከተል ነው። አካዝ በየኰረብቶች ላይ በተሠሩት የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና በእያንዳንዱም ዛፍ ሥር መሥዋዕት በማቅረብ ዕጣን አጠነ። የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል ከበቡአት፤ ነገር ግን አካዝን ድል ሊያደርጉት አልቻሉም። በዚያኑ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረጺን የኤላትን ከተማ አስመልሶ በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ በዚያ የነበሩትን አይሁድ አስወጣ፤ ያንጊዜ በኤላት የሰፈሩት ኤዶማውያን እስከ አሁን በዚያ ይገኛሉ። ከዚህም የተነሣ ንጉሥ አካዝ ወደ አሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ቲግላት ፐሌሴር “እኔ ለአንተ ታማኝ አገልጋይህ ነኝ፤ ስለዚህም ወደ እኔ መጥተህ አደጋ ከጣሉብኝ ከሶርያና ከእስራኤል ነገሥታት እጅ አድነኝ” የሚል ጥያቄ የያዙ መልእክተኞች ላከ። ከዚህም በቀር አካዝ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ሰብስቦ ለዚሁ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት በማድረግ ላከለት። የአካዝን ጥያቄ በመቀበል ቲግላት ፐሌሴር ዘምቶ ደማስቆን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፤ ንጉሥ ረጺንንም ገደለ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ቂር ተብላ ወደምትጠራው ስፍራ ወሰደው። ንጉሥ አካዝ ወደ ደማስቆ ሄዶ ከንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ጋር በተገናኘ ጊዜ በዚያ አንድ መሠዊያ አየ፤ ያንን መሠዊያ በተመሳሳይ ሁኔታ መሥራት የሚያስችለውን ቅርጽ አዘጋጅቶ ለካህኑ ለኡሪያ ላከለት፤ ስለዚህም ኡሪያ ንጉሥ አካዝ ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ልክ ያንኑ የሚመስል መሠዊያ ሠራ፤ አካዝም ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ ያ መሠዊያ በትክክል መሠራቱን ለማየትና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ፤ እንዲሁም በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል የእንስሶች መሥዋዕትና የእህል መባ አቀረበ፤ የመባውን ወይን ጠጅና የኅብረት መሥዋዕት ደም አፈሰሰበት። ከነሐስ ተሠርቶ ለእግዚአብሔር የተለየውም መሠዊያ በዚያ አዲስ መሠዊያና በቤተ መቅደሱ መካከል ነበር፤ አካዝም ያንን መሠዊያ አስነሥቶ እርሱ ባሠራው በአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው፤ ከዚህ በኋላ ኡሪያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ይህን የእኔን ታላቅ መሠዊያ ማለዳ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ በምሽት ለሚቀርበውም የእህል መባ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡ የሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ የሚቀርብበትና የሕዝቡ የወይን ጠጅ መባ የሚፈስበት እንዲሆን አድርግ፤ የሚሠውትንም የእንስሶች ደም ሁሉ በእርሱ ላይ አፍስስ፤ ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ግን እኔ ራሴ የምፈልገውን ነገር የምጠይቅበት እንዲሆን አድርግ።” ኡሪያም ንጉሡ እንዳዘዘው አደረገ። ንጉሥ አካዝ በቤተ መቅደስ ውስጥ መገልገያ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ መንኰራኲሮች ቆርጦ ልሙጥ የሆነውን ነገር ከጐናቸው ወሰደ። በእነርሱ ላይ የነበሩትንም የመታጠቢያ ሳሕኖች ወሰደ፤ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ከታች በኩል ተሸክመውት ከነበሩት ከነሐስ ከተሠሩት ከዐሥራ ሁለት የበሬ ቅርጾች ጀርባ ላይ አንሥቶ፥ ከድንጋይ በተሠራ መሠረት ላይ አኖረው። አካዝ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለማስደሰት ሲል ንጉሣዊ ዙፋን የሚዘረጋበትን ሉዓላዊ ስፍራ አስወገደ፤ ከዚያ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ወደ ቤተ መቅደስ ይገባበት የነበረውንም ልዩ በር ዘጋ። ንጉሥ አካዝ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ አካዝ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ። አካዝ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ የእርሱ በደል ከእርሱ በፊት የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያኽል አልነበረም፤ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር ጦርነት በገጠመው ጊዜ ተሸንፎ እጁን በመስጠት በየዓመቱ ይገብርለት ጀመረ። ነገር ግን ከጥቂት ዓመቶች በኋላ ንጉሥ ሆሴዕ፥ ሶእ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ግብጽ ንጉሥ መልእክተኞች በመላክ ይረዳው ዘንድ ጠየቀ፤ በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ይሰጠው የነበረውንም ግብር አቆመ፤ ሰልምናሶር ይህን በሰማ ጊዜ ሆሴዕን አስይዞ ወህኒ ቤት አስገባው። ከዚህ በኋላ ሰልምናሶር አገሪቱን ወረረና ሰማርያን ለሦስት ዓመት ከበባት፤ ይኸውም ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰልምናሶር ድል አድርጎ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም ማርኮ በእስረኛነት ወደ አሦር ወሰዳቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ፥ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ እንዲሁም ሌሎቹ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ከግብጽ ንጉሥ እጅ በመታደግ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው ነበር፤ ይኸውም ለባዕዳን አማልክት ሰገዱ፤ ሕዝቡ ወደ ፊት እየገፋ በመጣ ጊዜ ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸውን የአሕዛብን መጥፎ ልማድ ተከተሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ያሠራጩትን መጥፎ ልማድ ተቀባዮች ሆኑ። እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር የሚጠላውን ነገር ሁሉ አደረጉ፤ ከዘብ ጠባቂዎች ማማ አንሥቶ እስከ ትልቅ ከተማ ድረስ በገጠር ከተሞቻቸው ሁሉ በየኰረብታዎቹ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ በኰረብቶች ሁሉ ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር የድንጋይ ዐምዶችንና አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎች አቆሙ፤ እግዚአብሔር ከምድሪቱ ነቃቅሎ ያስወጣቸውን የአረማውያንን ሕዝብ ልማድ በመከተል በአሕዛብ መሠዊያዎች ሁሉ ላይ ዕጣን አጠኑ፤ በዚህም ክፉ ሥራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፤ እግዚአብሔር ለጣዖት እንዳይሰግዱ ያዘዛቸውንም ሕግ ሁሉ አፈረሱ። እግዚአብሔርም እስራኤልንና ይሁዳን የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችንና ነቢያትን በመላክ “ከክፉ መንገዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፤ አገልጋዮቼ በሆኑት ነቢያትና ባለ ራእዮች አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተም በሰጠሁት ሕጎችና ትእዛዞች የተጻፈውን ሥርዓቴን ጠብቁ” ብሎ ነግሮአቸው ነበር። እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልኸኞች ሆኑ፤ የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሳሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ በመሻር በዙሪያቸው የሚኖሩ የአሕዛብን ልማድ ሁሉ ተከተሉ። የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ በመጣስ የሚሰግዱላቸውን ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፤ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፤ ለከዋክብት ሰገዱ፤ በዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ። ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ። እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ተቆጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በመተው እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ። ነገር ግን የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ፥ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፤ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ በዝባዦች ለሆኑት ጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተው በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፤ እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም። ጌታ በባርያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፥ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል። የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው። በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ በዚህም ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር። ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ። እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው። የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሀያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። የአሕዛብን የማምለኪያ ስፍራዎችን ደመሰሰ፤ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አንኮታክቶ ጣለ፤ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ግን እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር። ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፤ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእርሱ መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆኖ ስለሚረዳው የሚሠራው ሁሉ በተቃና ሁኔታ ይከናወንለት ነበር፤ ሕዝቅያስ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ። ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ መንደር እስከ ታላቅ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት ጭምር እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ ወረረ። ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይህም ማለት ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፤ በተከበበችበትም በሦስተኛው ዓመት ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፥ ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ ሌሎቹ ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። ሰማርያ የወደቀችበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ በሆነው በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ቃሉን ማዳመጥም ሆነ ሕጉን መጠበቅ አልፈለጉም። ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ያዘ፤ ሕዝቅያስም በላኪሽ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም “እኔ በድያለሁ፤ እባክህን አቁም፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ” ሲል መልእክት ላከ፤ ንጉሠ ነገሥቱም “እኔ የምፈልገው ዐሥር ሺህ ኪሎ ብርና አንድ ሺህ ኪሎ ወርቅ እንድትልክልኝ ነው” ሲል መለሰለት። ሕዝቅያስም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ። ይህ በዚህ እንዳለ የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከላኪሽ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ያም ሠራዊት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኲሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም ባለሟሎቹ የሆኑ ሦስት ባለ ሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፤ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነ የሒልቂያ ልጅ ኤልያቄም፥ እንዲሁም የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሼብናና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአሕ ነበሩ፤ ከአሦር የጦር አዛዦች አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ለመሆኑ እንደዚህ አድርገህ የተማመንክበት ነገር ምንድነው? የቃላት ጋጋታ የጦርነትን ስልትና ኃይል የሚተካ ይመስልሃልን? ማን ይረዳኛል ብለህ ነው በአሦር ላይ ለማመፅ ያሰብከው? የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኰዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው’ ሲል የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይጠይቅሃል።” የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ አድርገህ ታስባለህን? ይህማ እንዳይሆን፥ አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ ‘የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው’ ብለህ ወስነሃል። አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ እንደሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ! አንተ እኮ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኰንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው። እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል።” ከዚህም በኋላ ኤልያቄምና፥ ሼብና እንዲሁም ዮአሕ ይህን የጦር አዛዥ “ፍቹን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት። እርሱም “የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት የሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆኑ፥ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት ነው” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ያ የአሦር ባለ ሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፤ “የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ! በሕዝቅያስ አትታለሉ! እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም! ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙ፤ ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት፤ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ይታደጋችኋል’ እያለ በመስበክ አያሞኛችሁ፤ ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን? ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን? የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከንጉሠ ነገሥታቶቻችን እጅ አገሮቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?” ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያቄምና ሼብና እንዲሁም ዮአሕ በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን ባለ ሥልጣን የተናገረውን አስረዱት። ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ወዲያውም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ጸሐፊ ሼብናንና ሽማግሌዎች ካህናትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ራሳቸው ማቅ ለብሰው ነበር፤ ለኢሳይያስም እንዲነግሩት የላከው መልእክት ከዚህ የሚከተለው ነው፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ለተረፉት ሰዎች እባክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።” የንጉሥ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፥ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብላችሁ ለጌታችሁ ንገሩት አላቸው፤ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ሲሰድቡኝ ስለ ሰማችሁት ቃል አትፍሩአቸው። እነሆ፥ እኔ የሽብር ወሬ የሚያሰማ መንፈስ እልክበታለሁ፤ ስለዚህም ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሄድና እዚያም በገዛ ምድሩ በሰይፍ ተመትቶ እንዲሞት አደርጋለሁ።’” የአሦር የጦር አዛዥ፥ የአሦር ንጉሥ ከሰፈሩ ከላኪሽ ተነሥቶ ሊብናን ሊያጠቃ እንደ ሄደ በመስማቱ እርሱም ወደዚያው ሄደ። በኢትዮጵያ ንጉሥ በቲርሃቃ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን አሦራውያን ሰሙ፤ ወዲያውኑ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኞች እጅ ላከ፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ፥ የምትታመንበት አምላክ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አትወድቅም’ ብሎ አያታልህ፤ የአሦር ነገሥታት አገሮችን ሁሉ እንዴት ፈጽመው እንደ ደመሰሱ ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፥ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር የሚኖሩትን የዔዳንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ከአማልክታቸው አንድ እንኳ ሊያድናቸው ችሎአልን? ለመሆኑ የሐማት፥ የአርፋድ፥ የሰፋርዋይም፥ የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት የት አሉ?” ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልክተኞች ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው፤ እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ኪሩቤል ተብለው በሚጠሩ መላእክት ላይ የተቀመጥህ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ የዓለምንም መንግሥታት የምትመራ አንተ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፤ አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ተመልከት፥ ሕያው አምላክን አንተን በመስደብ ሰናክሬም የተናገረውን የዛቻ ቃል ሁሉ አድምጥ፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ የአሦር ነገሥታት ብዙ ሕዝቦችና ምድራቸውን መደምሰሳቸው እርግጥ ነው። ከእንጨትና ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት ስላልነበሩ በእሳት ላይ ጥለው አጠፉአቸው። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦር ንጉሥ በመታደግ አድነን።” ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሠ ነገሥት ስለ ሰናክሬም ዛቻ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቻለሁ፤ ስለ እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ የጽዮን ድንግል ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ አንተ እየሸሸህ ሳለህ፥ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች ከኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል። የሰደብከውና የተዳፈርከው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው በማን ላይ ነው? በትዕቢትስ ዐይንህን ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ነው። በመልክተኞችህ አማካይነት፥ በእግዚአብሔር ላይ ስድብህን ከምረሃል፤’ ‘በሠረገሎቼ ከፍተኛ ወደ ሆኑት ተራራዎች፤ ወደ ሊባኖስ ጫፍ ወጥቼአለሁ፤ ረጃጅሞቹን የሊባኖስ ዛፎችዋንና ምርጦች ዝግባ ቆርጬአለሁ፤ ወደ ዳርቻዋና ውብ ወደ ሆነው ጫካዋ ደርሼአለሁ፤’ ብለሃል። ‘በባዕድ አገር ጉድጓድ ቆፍሬ፥ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ኮቴዎች የግብጽን ወንዞች አድርቄአለሁ’ ብለህ ታብየሃል። ሰናክሬም ሆይ! አስተውል፤ ጥንቱኑ እኔ እንደ ወሰንኩት፥ በቀድሞ ዘመን እንደ ዐቀድኩትና አሁን በሥራ ላይ ባዋልኩት መሠረት የተጠናከሩ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንድትለውጥ ያደረግኹህ እኔ መሆኔን አልሰማህምን? የእነዚያ አገር ነዋሪዎች ኃይላቸው ተዳክሞ፥ ተስፋ በመቁረጥ እንዳያፍሩ ተደርገው በምሥራቅ ነፋስ እንደ ተመቱ፥ የመስክ አትክልቶች፥ እንደ ቀጨጩ አረንጓዴ ቡቃያዎች፥ በጣራ ላይ እንደ በቀለ ሣር ናቸው። እኔ ግን መነሣትህንና መቀመጥህን፥ መውጣትህንና መግባትህን፥ እንዲሁም እኔን መቃወምህን ዐውቃለሁ። በእኔ ላይ ያለው ተቃውሞህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ በአፍንጫህ ስናጋ፥ በአፍህ ልጓም አድርጌ፥ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፥ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የሚበቅለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰድዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ፤ ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ተራራ የተረፉት ወገኖች ይወጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ከመፈጸም አይመለስም።” እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሠ ነገሥት የተናገረውም ቃል ይህ ነው፦ “ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርሷ አይቀርብም፤ በዐፈር ቁልልም አትከበብም። እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለ ራሴ ክብር እንዲሁም ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ ተከላክዬ አድናታለሁ።” በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ። ከዚህ በኋላ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ወደ ኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመለሰ። ከዕለታት በአንዱ ቀን ኒስሮክ በሚል ስም በሚጠራው ባዕድ አምላኩ ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ፥ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አድራሜሌክና ሣሬጼር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶ የተባለው ነገሠ። በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጐበኘው ሄዶ “እግዚአብሔር ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ሁሉን ነገር አስተካክል’ ብሎሃል” ሲል ነገረው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ፥ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደ ነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!” እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢሳይያስ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ የቤተ መንግሥቱን መካከለኛ አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፦ “ሕዝቤን ወደሚመራው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ተመልሰህ በመግባት እንዲህ በለው፦ ‘እኔ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም ተመልክቻለሁ፤ እኔ እፈውስሃለሁ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤ በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ በመታደግ አድናለሁ፤ ስለ ክብሬና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ከተማይቱን በመከላከል እጠብቃታለሁ።’” ከዚህም በኋላ ኢሳይያስ የንጉሡን አገልጋዮች፥ “የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ አምጡልኝ” ብሎ አመጡለት፤ በቁስሉ ላይ ባደረጉለት ጊዜ የሕዝቅያስ ቁስል ተፈወሰ። ንጉሥ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን “እግዚአብሔር እንደሚፈውሰኝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ እንደምችል በምን ምልክት ዐውቃለሁ?” ሲል ጠየቀው። ኢሳይያስም “እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ ራሱ ምልክት ይሰጥሃል፤ እንግዲህ አሁን የምትመርጠው ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ነው? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ ይቀላል፤ ስለዚህ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርግልኝ” አለው። ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ንጉሥ አካዝ ባሠራው ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ። በዚያኑ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን፥ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ የነበረ መሆኑን ሰማ፤ ስለዚህም ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት፤ ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ፥ ብሩንና ወርቁን፥ ቅመማ ቅመሙንና ሽቶውን፥ የጦር መሣሪያውንም ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው አንድም አልነበረም። በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ፥ “እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?” ብሎ ጠየቀው። ሕዝቅያስም “እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው” ሲል መለሰለት። ኢሳይያስም “በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤቱ ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው አንድም ነገር የለም” አለ። ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የቀድሞ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ያከማቹት በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርም፤ ከዘሮችህም አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።’” ንጉሥ ሕዝቅያስም በተለይ በእርሱ ዘመን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለ ስለ ተረዳ “ከእግዚአብሔር ተልከህ የተናገርከኝ ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ። ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራው ጭምር፥ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ግድብ እንዴት እንደ ሠራና ወደ ከተማይቱ ውሃ ለማምጣት ያስቆፈረው የመሬት ውስጥ ቦይ አሠራር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ሕዝቅያስም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ። ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሔፍጺባ ተብላ የምትጠራ ነበረች፤ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ ደምስሶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች እንደገና እንዲሠሩ አደረገ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ባደረገውም ዓይነት በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፥ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስልን ሠራ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ። እግዚአብሔር እንዲመለክበት ባዘዘው ስፍራ ማለትም በቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን አቆመ። በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፤ የገዛ ልጁንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት በመሥራቱ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሣ። በቤተ መቅደሱም ውስጥ የአሼራን ምስል አኖረ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን “ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እኔ ለዘለዓለም እመለክበት ዘንድ ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት ስፍራ ነው፤ የእስራኤል ሕዝብ ትእዛዞቼን ቢጠብቁና ለአገልጋዬ ለሙሴ የሰጠሁትንም ሕግ ቢፈጽሙ፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ከዚህች ምድር ተነቃቅለው እንዲጠፉ አላደርግም” ሲል ነግሮአቸው የነበረው ነው፤ የይሁዳ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ይልቁንም ምናሴ እስራኤላውያን ወደ ፊት እየገፉ ሲመጡ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸው ሕዝቦች ይፈጽሙት ከነበረው ይበልጥ ወደ ከፋ ኃጢአት መራቸው። እግዚአብሔርም በአገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ቀድሞ ከነዓናውያን ይፈጽሙት ከነበረው ሁሉ የከፋ ነው፤ በሠራቸውም ጣዖቶች የይሁዳን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፤ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እኔ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የማመጣው በጣም ከባድ መቅሠፍት ይህ ነው፤ ስለ እርሱም የሚሰማ ሰው ሁሉ በድንጋጤ ጭው ይላል፤ ሰማርያንና የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ከነዘሮቹ እንደ ቀጣሁ ሁሉ ኢየሩሳሌምንም እቀጣለሁ፤ ሳሕን ከተወለወለ በኋላ ተደፍቶ እንደሚቀመጥ፥ እኔም ኢየሩሳሌምን ከኃጢአት አጸዳታለሁ። ከጥፋት የተረፈውን ሕዝቤን ለጠላቶቹ ተላልፎ እንዲሰጥ እተወዋለሁ፤ እርሱም ይማረካል፤ ንብረቱም ይዘረፋል። በእነርሱም ላይ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ኃጢአት ሠርተው እኔን በማሳዘናቸውና ቁጣዬን በማነሣሣታቸው ነው።” ምናሴ የይሁዳን ሕዝብ ወደ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔርን ወደሚያሳዝን ኃጢአት ከመምራት አልፎ፥ ንጹሓን የሆኑትን ብዙ ሰዎችን በመፍጀት የኢየሩሳሌምን መንገዶች በደም እንዲጥለቀለቁ አድርጎአል። ምናሴ ያደረገው ሌላው ነገርና የፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ምናሴ ሞተ፤ በቤተ መንግሥቱ ግቢ “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ። አሞን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው ሀያ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም መሹሌሜት ተብላ የምትጠራ የያጥባ ከተማ ተወላጅ የሐሩጽ ልጅ ነበረች፤ አሞን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። የአባቱንም መጥፎ አርአያነት ሁሉ ተከተለ፤ አባቱ ይሰግድላቸው የነበሩትንም ጣዖቶች አመለከ፤ የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርንም ተወ፤ ለእግዚአብሔርም ቃል ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልሆነም። ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም በአሞን ላይ አድመው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት፤ የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ደምስሰው ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ። አሞን ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። አሞን “የዑዛ የአትክልት ስፍራ” ተብሎ በሚጠራው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ። ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የቦጽቃት ከተማ ተወላጅ የሆነው የዐዳያ ልጅ ነበረች፤ ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተልና ለእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ታዛዥ በመሆን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የመሹላም የልጅ ልጅ፥ የአጻልያ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ሳፋንን ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፤ “ሒልቂያ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሂድ፤ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያኽል ገንዘብ እንደ ሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ ና፤ ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የጌታን ቤተ መቅደስ ለሚያ ድሱት ይክፈሏቸው፤ የሚከፍሉትም ለአና ጺዎች፥ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት። የሥራው ኃላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቆጣጠር አያስፈልግም።” ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለሒልቂያ ሰጠ፤ ሒልቂያም “የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ” ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደና “አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኃላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል” ሲል አስረዳ፤ ከዚያም ቀጠል በማድረግ፥ “ካህኑ ሒልቂያ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ ይኸው” ብሎ ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወዲያውኑ ለካህኑ ለሒልቂያ፥ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአሒቃም፥ የሚካያ ልጅ ለሆነው ለዐክቦር፥ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፤ “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቆጥቶአል።” ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባሏ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኃላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ። እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖቶች ሁሉ እኔን አስቆጥተውኛል፤ ቁጣዬም አይበርድም፤ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፥ ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድ፥ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣው ቅጣት አንተ በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ። ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ፤ እነርሱም ካህናት፥ ነቢያት፥ ሌሎችም ሰዎች ከታናሾች ጀምሮ እስከ ታላቆች ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፤ ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና ሐሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፥ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳኑን አደሰ፤ ስለዚህም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ፤ ሕዝቡም በቃል ኪዳኑ ተባበረ። ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ሒልቅያን፥ ረዳቶቹ የሆኑትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን መግቢያ በር ዘብ የሚጠብቁ ተረኞችን ጠርቶ ለበዓልና አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ፥ እንዲሁም ለከዋክብት ማምለኪያ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ንጉሡም እነዚያን ዕቃዎች ሁሉ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባለው በቄድሮን ሸለቆ በእሳት አቃጥሎ ዐመዱን ወደ ቤትኤል ወሰደው፤ በይሁዳ ከተማዎችና በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉት ስፍራዎች ሁሉ በየኰረብታው ላይ በነበሩት መሠዊያዎች መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ የይሁዳ ነገሥታት ሾመዋቸው የነበሩትን ካህናት ሁሉ ከሥራ አሰናበተ፤ በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ፥ ለፀሐይ፥ ለጨረቃ፥ ፀሐይን ለሚዞሩ ዓለማትና ለከዋክብት መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉ ካህናትን ሁሉ ሻረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ከቤተ መቅደስ ነቅሎ ከከተማይቱ በማውጣት ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ትቢያ እስኪሆንም አድቅቆ፥ በሕዝብ መቃብር ላይ በተነው። ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉበትንና ሴቶችም አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ መጋረጃ የሚፈትሉበትን ክፍል ሁሉ ደመሰሰ። በይሁዳ ከተሞችና በመላ ሀገሪቱ ከገባዕ እስከ ቤርሳቤህ የነበሩትን ካህናት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፤ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ርኩስ መሆናቸውን ዐወጀ፤ እንዲሁም የከተማይቱ ገዢ ኢያሱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ከዋናው ቅጽር በር በስተ ግራ በኩል ባሠራው ቅጽር በር አጠገብ የሚገኙትን መስገጃዎች አፈራረሰ። እነዚያም ካህናት በቤተ መቅደስ ከማገልገል ታገዱ፤ ይሁን እንጂ ለጓደኞቻቸው ካህናት ይሰጥ የነበረውን እርሾ ያልነካው ኅብስት እንዲመገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር። ንጉሥ ኢዮስያስ በሒኖም ሸለቆ የነበረው “ቶፌት” ተብሎ የሚጠራው የአሕዛብ ማምለኪያ ቦታ የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ከዚህም የተነሣ “ሞሌክ” ተብሎ ለሚጠራው አምላክ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንም እንዳይኖር ተከለከለ፤ የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ አምልኮ መድበዋቸው የነበሩትን ፈረሶች ሁሉ አስወገደ፤ ለዚሁ አምልኮ የሚያገለግሉ የነበሩትን ሠረገሎች አቃጠለ፤ እነዚህ ሁሉ ቀደም ሲል ታላቁ ባለ ሥልጣን ናታን ሜሌክ በሚኖርባቸው ክፍሎች አጠገብና በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቅጽር በር አጠገብ ይገኙ ነበር፤ ንጉሥ አካዝ ባሠራቸው መኖሪያ ክፍሎች ጣራ ላይ በሚገኘው ቤተ መንግሥት የይሁዳ ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን መሠዊያዎችና በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ንጉሥ ምናሴ አሠርቶአቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ኢዮስያስ ደመሰሳቸው፤ መሠዊያዎቹንም አንኮታክቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ ጣላቸው። እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኲሰት ተራራ በስተ ደቡብ ዐስታሮት ተብላ ለምትጠራው ለሲዶና አምላክ፥ ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞዓብ አምላክና ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞን አምላክ ንጉሥ ሰሎሞን አሠርቶአቸው የነበሩት አጸያፊዎች ምስሎች ሁሉ የረከሱ መሆናቸውን አስገነዘበ። ንጉሥ ኢዮስያስ የድንጋይ ዐምዶችን ሁሉ ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስሎች አንኮታክቶ ጣለ፤ እነርሱ ቆመውበት የነበረውንም ስፍራ የሙታን አጥንት ሞላበት። እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤል አሠርቶት የነበረውን የማምለኪያ ቦታ ኢዮስያስ አፈራርሶ ጣለ፤ መሠዊያውን ነቅሎ፥ የተሠራበትን ድንጋይ ሁሉ ሰባብሮ በማድቀቅ እንደ ትቢያ አደረገው፤ የአሼራንም ምስል በእሳት አቃጠለ፤ ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት፥ በኰረብቶች ላይ የተሠሩ መቃብሮችን አየ፤ በእነዚያም መቃብሮች ውስጥ የነበረውን ዐፅም ሁሉ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በእሳት አቃጠለው፤ በዚህም ዓይነት መሠዊያው የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ኢዮስያስ ይህንን ሁሉ በማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት በተደረገ የአምልኮ በዓል ላይ ንጉሥ ኢዮርብዓም በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ ነቢዩ የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ፤ ንጉሥ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት ይህን ትንቢት ተናግሮ የነበረው ነቢይ የተቀበረበትን መካነ መቃብር አይቶ፥ “ያ መቃብር የማን ነው?” ሲል ጠየቀ። የቤትኤልም ሕዝብ “ከይሁዳ መጥቶ በዚህ መሠዊያ ላይ ይህን አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምበት ተናግሮ የነበረው የነቢዩ መቃብር ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢዮስያስም “እንዳለ ይኑር፤ ተውት፤ የእርሱ ዐፅም ከዚህ መንቀሳቀስ የለበትም!” ሲል መለሰ። ስለዚህም የእርሱም ሆነ የሰማርያው ነቢይ ዐፅሞች ከዚያ እንዲነሡ አልተደረገም። ንጉሥ ኢዮስያስ በማንኛይቱም የእስራኤል ከተማ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማነሣሣት ምክንያት የሆኑትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሁሉ አፈራረሰ፤ በቤትኤል ያደረገውን ሁሉ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ፈጸመ፤ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ያገለግሉ የነበሩትንም አሕዛብ ካህናትን ገደለ፤ በመሠዊያዎቹም ላይ አጥንት አቃጠለባቸው። ይህን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ንጉሥ ኢዮስያስ በቃል ኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ያከብሩ ዘንድ ሕዝቡን አዘዘ። መሳፍንት የሕዝቡ ገዢዎች ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን በማንኛዎቹም የእስራኤል ወይም የይሁዳ ነገሥታት አማካይነት ይህን የመሰለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም። ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ተከበረ። ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ በቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው ሕግ ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማሰብ፥ ንጉሥ ኢዮስያስ ከኢየሩሳሌምና ከሌላውም የይሁዳ ከተማ ሁሉ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሁሉ የቤተሰብ አማልክትን፥ ጣዖቶችንና ሌሎችንም አረማዊ የአምልኮ መፈጸሚያ ዕቃዎችን ሁሉ አስወገደ። ለኦሪት ሕግ በመታዘዝ በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ ከእርሱም በፊት ሆነ ከእርሱ ወዲህ ከቶ አልነበረም። ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ምናሴ ባደረገው ክፉ ነገር ምክንያት በይሁዳ ላይ የነደደው አስፈሪ የእግዚአብሔር ቁጣ እስከ አሁን ድረስ ገና አልበረደም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በእስራኤል ላይ ያደረግኹትን ነገር ሁሉ በይሁዳም ላይ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ሕዝብ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራል ብዬ የነበረውንም ቤተ መቅደስ እተዋለሁ።” ንጉሥ ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ነኮ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፤ ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እዚያ በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ። የይሁዳም ሰዎችም የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን መረጡ፤ ቀብተውም አነገሡት። ኢዮአካዝ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ ሦስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤ ኢዮአካዝም የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። እርሱንም ኒካዑ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ኢዮአካዝ በኢየሩሳሌም እንዳይነግሥ በሐማት ምድር በምትገኘው በሪብላ እስረኛ በማድረግ፥ ይሁዳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ብር፥ ሠላሳ አራት ኪሎ ወርቅ ግብር እንዲከፍል ባደረገው ጊዜ የኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ። ንጉሥ ኒካዑ የኢዮስያስ ልጅ ኤልያቄም በአባቱ በኢዮስያስ እግር ተተክቶ በይሁዳ እንዲነግሥ አደረገ፤ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፤ ኢዮአሐዝም በንጉሥ ነኮ ተማርኮ ወደ ግብጽ ተወሰደ፤ በዚያም ሞተ። ኢዮአቄም ንጉሥ ነኮ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህንንም ለማድረግ እንደየችሎታው በሕዝቡ ላይ ግብር ጣለ። ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ዘቢዳ ተብላ የምትጠራ የሩማ ከተማ ተወላጅ የሆነው የፐዳያ ልጅ ነበረች። ኢዮአቄም የቀድሞ አባቶቹ እንደ አደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ከገበረለት በኋላ እንደገና ዐመፀ፤ እግዚአብሔር ባገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፥ ሶርያውያንን፥ ሞአባውያንንና ዐሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት። ይህም ሁሉ የሆነው ንጉሥ ምናሴ ስለ ፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ከፊቱ ለማስወገድ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፤ በተለይም ምናሴ የንጹሓን ሰዎችን ደም በማፍሰሱና ኢየሩሳሌምንም በንጹሓን ደም በመሙላቱ ምክንያት ይህ ሁሉ ሊፈጸም ችሎአል፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለምናሴ ምሕረት ሊያደርግለት አልፈቀደም። ኢዮአቄም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ኢዮአቄም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢኮንያን ነገሠ። የባቢሎን ንጉሥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ግብጽ ሰሜናዊ ጠረፍ ድረስ የግብጽ ይዞታ የነበረውን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ስለ ነበረ የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ ከዚያን በኋላ ከግብጽ ውጪ ዘመቻ አላደረጉም፤ ኢኮንያን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ነሑሽታ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች። አባቱ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። በናቡከደነፆር የጦር አዛዦች የሚመራው የባቢሎን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘምቶ የከበባትም በዚሁ በዮአኪን ዘመነ መንግሥት ነበር። በከበባውም ጊዜ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ ንጉሥ ኢኮንያን ከእናቱ፥ ከልዑላን መሳፍንቱ፥ ከጦር አዛዦቹና ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለ ሥልጣኖች ጋር ቀርቦ ለባቢሎናውያን እጁን ሰጠ፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ያዘው፤ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ቀደም ሲል እግዚአብሔር በተናገረውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረው። ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ፥ ልዑላን መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎችን ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤ ከእነርሱም ጋር የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎችን ድኾች ብቻ ነበር። ናቡከደነፆር ኢኮንያንን አስሮ ከነእናቱ ከሚስቶቹ፥ ባለሟሎቹ ከሆኑ ባለሥልጣኖችና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን፥ እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና እደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ። ናቡከደነፆር በኢኮንያን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጐት በይሁዳ አነገሠ፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው። ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ አንድ ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የነበረው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤ ኢዮአቄም ባደረገው ዓይነት ሴዴቅያስ ክፉ አደረገ። እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ከፊቱ አስወገዳቸው፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ። ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር መላው ሠራዊቱን አስከትቶ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፥ ዐሥረኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ወታደሮቹ ከከተማይቱ ውጪ ሰፍረው ዙሪያውን የሚከብብ የዐፈር ቁልል ሠሩ፤ ከበባውም እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆየ፤ በዚያው ዓመት አራተኛው ወር በገባ በዘጠነኛው ቀን ራቡ በጣም ስለ ጸና ሕዝቡ የሚመገበው አንዳችም ምግብ አልነበረም። የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ፤ የባቢሎን ወታደሮች ከተማይቱን ዙሪያውን ከበው በመያዝ ቢጠብቁም እንኳ የይሁዳ ንጉሥ ወታደሮች በሌሊት አምልጠው ወጡ፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ ከሚያስገባው መንገድ ተነሥተው ሁለቱን ቅጽሮች በሚያያይዘው የቅጽር በር በኩል በማለፍ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ። የባቢሎን ሠራዊት ግን ንጉሥ ሴዴቅያስን እያሳደደ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ማረከው፤ ወታደሮቹም ጥለውት ሸሹ፤ ሴዴቅያስም ተይዞ በሪብላ ከተማ ወደሚገኘው ወደ ናቡከደነፆር ተወሰደ፤ በዚያም ናቡከደነፆር ፍርድ አስተላለፈበት፤ ይኸውም ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ልጆቹ በፊቱ ታረዱ፤ ከዚህም በኋላ ናቡከደነፆር የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ አሳወረው፤ እጆቹንም በሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው። ናቡከደነፆር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፥ አምስተኛው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ናቡዛርዳን ተብሎ የሚጠራው የናቡከደነፆር የክብሩ ዘበኞቹ አዛዥ ኢየሩሳሌም ገባ። እርሱም ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱን፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የታላላቅ ሰዎችን ቤቶችና በከተማው ውስጥ የሚገኙትንም ሌሎች ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ በክብር ዘቡ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ወታደሮች የኢየሩሳሌም ዙሪያ አጥር ከዚህም በኋላ ናቡዛርዳን በከተማይቱ ቀርተው የነበሩትንና ሌሎችን ሰዎች፥ እንዲሁም ከድተው ወደ ባቢሎናውያን የተጠጉትን ሁሉ ይዞ ወደ ባቢሎን አጋዛቸው፤ ነገር ግን ምንም ሀብት የሌላቸውን የመጨረሻ ድኾች፥ አትክልት ኰትኳቾችና መሬት አራሾች ይሆኑ ዘንድ በይሁዳ ምድር ትቶአቸው ሄደ። ባቢሎናውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን የነሐስ ዐምዶች፥ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችና ከነሐስ የተሠራውን ታላቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት። እነርሱም ምንቸቶችን፥ መጫሪያዎችን፥ መኰስተሪያዎችን፥ የዕጣን ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠሩ የቤተ መቅደሱ መገልገያ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰዱ። ጽናዎችንና ዱካዎችን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ በመሆናቸው ወሰዱአቸው። ንጉሥ ሰሎሞን ለቤተ መቅደስ ያሠራቸውን ሁለቱን ዐምዶች፥ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችና ታላቁን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥ በክብደታቸው ምክንያት ሊመዝኑአቸው አልቻሉም። አንዱ ዐምድ ስምንት ሜትር ነበረው፤ ጉልላቱ ከነሐስ የተሠራ ነበር፤ የጉልላቱም ቁመት አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በዙሪያውም ከነሐስ በተሠራ መረብ ላይ የሮማን ፍሬ ቅርጽ የመሰለ ፈርጠኛ ጌጥ ተሠርቶበት ነበር። የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዛርዳን ሊቀ ካህናቱን ሤራያን በማዕረግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስና ሦስቱን የቤተ መቅደስ ዘበኞች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው፤ ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነው አንድ ባለ ሥልጣን፥ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ የነበሩትን አምስቱን የንጉሥ አማካሪዎች፥ የአገሩን ሕዝብ ለወታደርነት ይመለምል የነበረውን መኰንንና ሌሎችንም ሥልሳ ሰዎችን ወሰደ፤ ናቡዛርዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ በሐማት ግዛት በምትገኘው በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፤ ንጉሡም በዚያ እነርሱን አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው። በዚህም ዓይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የሳፋን የልጅ ልጅ የአሒቃም ልጅ ገዳልያን ወደ ባቢሎን ተማርከው ሳይወሰዱ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ ኃላፊ ይሆን ዘንድ የይሁዳ ገዢ አድርጎ ሾመው። እጃቸውን ያልሰጡ የይሁዳ የጦር መኰንኖችና ወታደሮች የባቢሎን ንጉሥ ገዳልያን ገዢ አድርጎ እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ ወደ ምጽጳ መጥተው ከእርሱ ጋር ተገናኙ፤ እነዚህም የጦር መኰንኖች የነታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋ ከተማ ተወላጅ የሆነው የታንሑሜት ልጅ ሠራያና የማዕካ ተወላጅ የሆነው የዛንያ ነበሩ፤ ገዳልያም እነርሱንና ወታደሮቻቸውን እንዲህ አላቸው፤ “ከባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች የተነሣ ምንም ዓይነት ፍርሀት ሊያድርባችሁ እንደማይገባ ቃል እገባላችኋለሁ፤ በዚህች ምድር ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁሉ ነገር ይቃናላችኋል።” ነገር ግን በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዘር የነበረውና የኤሊሻማዕ የልጅ ልጅ የሆነው የነታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ምጽጳ ሄደ፤ በዚያም አደጋ ጥሎ ገዳልያን ገደለው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተገኙትን እስራኤላውያንንና ባቢሎናውያንን ሁሉ ገደለ፤ ከዚህም የተነሣ ባቢሎናውያንን ስለ ፈሩ እስራኤላውያን ሀብታሞችም ድኾችም ከጦር ሠራዊት መኰንኖች ጋር በአንድነት ተነሥተው ወደ ግብጽ ሸሹ። ዮርማሮዴቅ ኤዊልመሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከእስራት በመፍታት ምሕረት አደረገለት፤ ይህም የሆነው ኢኮንያን በእስረኛነት ተማርኮ በሄደ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ በዐሥራ ሁለተኛው ወር በሃያ ሰባተኛው ቀን ነው። ኤዊልመሮዳክ ለዮአኪን መልካም ነገር አደረገለት፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩ ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ማዕርግ ሰጠው፤ ስለዚህም ኢኮንያን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ እንዲመገብ ተፈቀደለት፤ በኖረበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር። አዳም፥ ሴት፥ ሄኖስ፥ ቃይናን፥ መላልኤል፥ ያሬድ፥ ሄኖክ፥ ማቱሳላ፥ ላሜሕ፥ ኖኅ፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት። የያፌት ልጆች፤ ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ ያዋን፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ ናቸው። የጋሜርም ልጆች፤ አስከናዝ፥ ሪፋት፥ ቴርጋማ ናቸው። የያዋንም ልጆች፤ ኤሊሳ፥ ተርሴስ፥ ኪቲም፥ ሮድኢ ናቸው። የካምም ልጆች፤ ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው። የኩሽም ልጆች፤ ሴባ፥ ሐዊላ፥ ሰብታ፥ ራዕማ፥ ሰብቃታ ናቸው። የራዕማም ልጆች፤ ሳባ፥ ድዳን ናቸው። ኩሽም ናምሩድን ወለደ፤ እርሱም በምድር ኃያል መሆንን ጀመረ። ምጽራይምም የወለደው ሉዲምን፥ ዐናሚምን፥ ላህቢምን፥ ነፍተሂምን፥ ፈትሩሲምን፥ ፍልስጥኤማውያን አባት ከስሉሂምን፥ ከፍቶሪምን ነበር። ከነዓንም የወለደው የበኩር ልጁን ሲዶንን፥ ሔትን፥ ኢያቡሳዊውን፥ አሞራዊውን፥ ጌርጌሳዊውን፥ ኤዊያዊውን፥ ዐርካዊውን፥ ሲኒያዊውን፥ አራዴዎንን፥ ሰማሪዎንን፥ አማቲንን ነበር። የሴምም ልጆች፤ ኤላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ፥ አራም፥ ዑፅ፥ ሑል፥ ጌቴር፥ ሞሳሕ ናቸው። አርፋክስድም ሼላሕን ወለደ፤ ሼላሕም ዔቦርን ወለደ። ለዔቦርም ሁለት ልጆች ተወለዱለት፤ በዘመኑ ምድር ተከፍላለችና የአንደኛው ስም ፋሌቅ ተባለ፤ የወንድሙም ስም ዮቅጣን ይባል ነበር። ዮቅጣንም የወለደው አልሞዳድን፥ ሼሌፍን፥ ሐጻርማዌትን፥ ያራሕን፥ ሀዶራምን፥ ኡዛልን፥ ዲቅላን፥ ዖባልን፥ አቢማኤልን፥ ሳባን፥ ኦፊርን፥ ሐዊላን፥ ዮባብን ነበር፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ነበሩ። ሴም፥ አርፋክስድ፥ ሼላሕ፥ ዔቦር፥ ፋሌቅ፥ ራግው፥ ሴሮሕ፥ ናኮር፥ ታራ፥ አብርሃም የተባለ አብራም። የአብርሃምም ልጆች፤ ይስሐቅና እስማኤል ናቸው። ትውልዳቸውም እንደዚህ ነው። የእስማኤል በኩር ልጅ ነባዮት፤ ከዚህ በኋላ ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ይጡር፥ ናፊሽ፥ ቄድማ ነበሩ፤ እነዚህ የእስማኤል ልጆች ናቸው። የአብርሃምም ቊባት የኬጡራ ልጆች፤ ዚምራን፥ ዮቅሻን፥ ሜዳን፥ ምድያም፥ የሽቦቅ፥ ሹሐን ናቸው። የዮቅሻንም ልጆች፤ ሳባና ድዳን ናቸው። የምድያምም ልጆች፤ ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ነበሩ። አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ። የይስሐቅም ልጆች ዔሳውና እስራኤል ነበሩ። የዔሳው ልጆች፤ ኤልፋዝ፥ ራጉኤል፥ የዑስ፥ የዕላም፥ ቆሬ ናቸው። የኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጎቶም፥ ቄኔዝ፥ ቲምናዕ፥ አማሌቅ ናቸው። የራጉኤል ልጆች፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሣማ፥ ሚዛህ ናቸው። የሴይርም ልጆች፤ ሎጣን፥ ሦባል፥ ጽብዖን፥ ዓና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን ናቸው። የሎጣንም ልጆች፤ ሖሪ፥ ሔማም ናቸው፤ ቲሞናዕ የሎጣን እኅት ነበረች። የሦባል ልጆች፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ አውናም ናቸው። የጽብዖንም ልጆች፤ አያነና ዓና ናቸው። የዓና ልጅ፤ ዲሶን። የዲሶንም ልጆች፤ ሔምዳን፥ ኤስባን፥ ይትራን፥ ክራን ናቸው። የኤጽር ልጆች፤ ቢልሐን፥ ዛዕዋን፥ ዓቃን ናቸው። የዲሳን ልጆች፤ ዑፅና አራን ናቸው። በእስራኤልም ልጆች ላይ ገና ንጉሥ ሳይነግሥ በኤዶምያስ ምድር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። የቢዖር ልጅ ባላቅ፤ የከተማይቱም ስም ዲንሃባ ነበረ። ባላቅም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የባሶራ ሰው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ። ኢዮባብም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የቴማን አገር ሰው ሑሳም ነገሠ። ሑሳምም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ በሞዓብ ሜዳ ምድያምን የመታው የባዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማይቱም ስም ዓዊት ነበረ። ሃዳድም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የመሥሬቃ ሰው ሠምላ ነገሠ። ሠምላም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ በወንዙ አጠገብ ያለችው የረሆቦት ሰው ሳኡል ነገሠ። ሳኡልም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ነገሠ። በኣልሐናንም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማይቱም ስም ፋዑ ነበረ፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ የመጥሬድ ልጅ መሄጣብኤል ነበረች፤ ሃዳድም ሞተ። የኤዶምያስም አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥ አህሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥ ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብሳር አለቃ፥ መግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፤ እነዚህ የኤዶምያስ አለቆች ነበሩ። የእስራኤልም ልጆች፤ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ ዳን፥ ዮሴፍ፥ ብንያም፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር ናቸው። የይሁዳ ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም ናቸው፤ እነዚህ ሦስቱ ከከነዓናዊቱ ሴዋ የተወለዱለት ልጆች ናቸው። የይሁዳም የበኩር ልጅ ዔር በጌታ ፊት ክፉ ነበረ፤ እርሱም ገደለው። ምራቱም ትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደችለት፤ የይሁዳም ልጆች ሁሉ አምስት ነበሩ። የፋሬስ ልጆች፤ ኤስሮምና ሐሙል ናቸው። የዛራም ልጆች፤ ዘምሪ፥ ኤታን፥ ሄማን፥ ከልኮል፥ ዳራ ናቸው፤ አምስት ነበሩ። የከርሚም ልጅ እስራኤልን ያስጨነቀ፥ እርሙንም ሰርቆ የበደለ አካን ነበረ። የኤታንም ልጅ አዛርያ ነበረ። ለኤስሮም የተወለዱለት ልጆች፤ ይረሕምኤል፥ አራም፥ ካልብ ነበሩ። አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም የይሁዳን ልጆች አለቃ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፥ ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፥ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤ እሴይም የወለደው የበኩር ልጁን ኤልያብን፥ ሁለተኛውንም አሚናዳብን፥ ሦስተኛውንም ሳምዓ፥ አራተኛውንም ናትናኤልን፥ አምስተኛውንም ራዳይን፥ ስድስተኛውንም አሳምን፥ ሰባተኛውንም ዳዊትን ነበረ፤ እኅቶቻቸውም ጽሩያና አቢግያ ነበሩ። የጽሩያም ልጆች፤ አቢሳ፥ ኢዮአብ፥ አሣሄል ናቸው፤ ሦስቱ ነበሩ። አቢግያም አሜሳይን ወለደች፤ የአሜሳይም አባት እስማኤላዊው ዬቴር ነበር። የኤስሮምም ልጅ ካሌብ ከሚስቱ ከዓዙባ ከይሪዖትም ልጆች ወለደ፤ ልጆቹዋም ያሳር፥ ሶባብ፥ አርዶን ነበሩ። ዓዙባም ሞተች፥ ካሌብም ኤፍራታን አገባ፤ እርሷም ሆርን ወለደችለት። ሆርም ኡሪን ወለደ፥ ኡሪም ባስልኤልን ወለደ። ከዚያም በኋላ ኤስሮም ስልሳ ዓመት በሆነው ጊዜ ወዳገባት ወደ ገለዓድ አባት ወደ ማኪር ልጅ ገባ፤ ሠጉብንም ወለደችለት። ሠጉብም ኢያዕርን ወለደ፤ ሠጉብም በገለዓድ ምድር ሀያ ሦስት ከተሞች ነበሩትን ጌሹርን ወለደ። ጌሹርና አራምም የኢያዕርን ከተሞች ከቄናትና ከመንደሮችዋ ጋር ስልሳውን ከተሞች ወሰዱባቸው። እነዚህ ሁሉ የገለዓድ አባት የማኪር ልጆች ነበሩ። ኤስሮምም በካሌብ ኤፍራታ ከሞተ በኋላ የኤስሮም ሚስት አቢያ የቴቁሔን አባት አሽሑርን ወለደችለት። የኤስሮምም የበኩር ልጁ የይረሕምኤል ልጆች በኩሩ ራም፥ ቡናህ፥ ኦሬን፥ ኦጼም፥ አኪያ ነበሩ። ለይረሕምኤል ዓጣራ የተባለች ሌላ ሚስት ነበረችው፤ እርሷም የኦናም እናት ነበረች። የይረሕምኤል የበኩሩ የራም ልጆች መዓስ፥ ያሚን፥ ዔቄር ነበሩ። የኦናምም ልጆች ሸማይና ያዳ ነበሩ። የሸማይ ልጆች ናዳብና አቢሱር ነበሩ። የአቢሱርም ሚስት አቢካኢል ትባል ነበር፤ አሕባንንና ሞሊድን ወለደችለት። የናዳብም ልጆች ሴሊድና አፋይም ነበሩ፤ ሴሌድም ያለ ልጆች ሞተ። የአፋይምም ልጅ ይሽዒ፥ የይሽዒም ልጅ ሶሳን፥ የሶሳንም ልጅ አሕላይ ነበረ። የሸማይም ወንድም የያዳ ልጆች ዬቴርና ዮናታን ነበሩ፤ ዬቴርም ያለ ልጆች ሞተ። የዮናታንም ልጆች ፌሌትና ዛዛ ነበሩ፤ እነዚህ የይረሕምኤል ልጆች ነበሩ። ለሶሳንም ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ ለሶሳንም ኢዮሄል የተባለ ግብጻዊ አገልጋይ ነበረው። ሶሳንም ለአገልጋዩ ለኢዮሄል ልጁን አጋባት፥ እርሷም ዓታይን ወለደችለት። አታይም ናታንን ወለደ፤ ናታንም ዛባድን ወለደ፤ ዛባድም ኤፍላልን ወለደ፤ ኤፍላልም ዖቤድን ወለደ፤ ዖቤድም ኢዩን ወለደ፤ ኢዩም ዓዛርያስን ወለደ፤ ዓዛርያስም ኬሌስን ወለደ፤ ኬሌስም ኤል-ዓሣን ወለደ፤ ኤል-ዓሣም ሲስማይን ወለደ፤ ሲስማይም ሰሎምን ወለደ፤ ሰሎምም የቃምያን ወለደ፤ የቃምያም ኤሊሳማን ወለደ። የይረሕምኤልም ወንድም የካሌብ ልጆች በኩሩ የዚፍ አባት ሞሳ፥ የኬብሮንም አባት የመሪሳ ልጆች ነበሩ። የኬብሮንም ልጆች ቆሬ፥ ተፉዋ፥ ሬቄም፥ ሽማዕ ነበሩ። ሽማዕም የዮርቅዓምን አባት ረሐምን ወለደ፤ ሬቄምም ሸማይን ወለደ። የሸማይም ልጅ ማዖን ነበረ፤ ማዖንም የቤት-ጹር አባት ነበረ። የካሌብም ቁባት ዔፋ ሐራንን፥ ሞዳን፥ ጋዜዝን ወለደች፤ ሐራንም ጋዜዝን ወለደ። የያህዳይም ልጆች ሬጌም፥ ኢዮታም፥ ጌሻን፥ ፋሌጥ፥ ሔፋ፥ ሸዓፍ ነበሩ። የካሌብም ቁባት ማዕካ ሼቤርንና ቲርሐናን ወለደች። ደግሞም የመድማናን አባት ሸዓፍንና የመክቢናንና የጊብዓን አባት ሱሳን ወለደች፤ የካሌብም ሴት ልጅ ዓክሳ ነበረች። የካሌብ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የኤፍራታ የበኩሩ የሆር ልጅ የቂርያት-ይዓሪም አባት ሦባል፥ የቤተልሔም አባት ሰልሞን፥ የቤት-ጋዴር አባት ሐሬፍ። ለቂርያት-ይዓሪምም አባት ለሦባል ልጆች ነበሩት፤ ሀሮኤ የመናሕታውያን እኩሌታ። የቂርያት-ይዓሪምም ወገኖች፤ ይትራውያን፥ ፉታውያን፥ ሹማታውያን፥ ሚሽራውያን ነበሩ፤ ከእነዚህም ጾርዓውያንና ኤሽታኦላውያን ወጡ። የሰልሞንም ልጆች ቤተልሔም፥ ነጦፋውያን፥ ዓጣሮት-ቤት-ዮአብ፥ የመናሕታውያን እኩሌታ፥ ጾርዓውያን ነበሩ። በያቤጽም የተቀመጡ የጸሐፊዎች ወገኖች፤ ቲርዓውያን፥ ሺምዓታውያን፥ ሡካታውያን ነበሩ፤ እነዚህ ከሬካብ ቤት አባት ከሐማት የወጡ ቄናውያን ናቸው። በኬብሮንም ለዳዊት የተለወዱለት ልጆች እነዚህ ናቸው። በኩሩ አምኖን ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም፥ ሁለተኛውም ዳንኤል ከቀርሜሎሳዊቱ ከአቢግያ፤ ሦስተኛው አቤሴሎም የመዓካ ልጅ እርሷም የጌሹር ንጉሥ የተልማይ ልጅ ነበረች፥ አራተኛው አዶንያስ የአጊት ልጅ፤ አምስተኛው ሰፋጥያስ ከአቢጣል፥ ስድስተኛው ይትረኃም ከሚስቱ ከዔግላ፤ ስድስቱ በኬብሮን ተወለዱለት፤ በዚያም ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። እነዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም ተወለዱለት፤ ከዓሚኤል ልጅ ከቤርሳቤህ አራት ልጆች እነርሱም ሳምዓ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፤ ከዚያም በኋላ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት ዘጠኝ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ከቁባቶች ልጆች በቀር የዳዊት ልጆች ነበሩ፤ ትዕማርም እኅታቸው ነበረች። የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም ነበረ፤ ልጁ አቢያ፥ ልጁ አሳ፥ ልጁ ኢዮሣፍጥ፥ ልጁ ኢዮራም፥ ልጁ አካዝያስ፥ ልጁ ኢዮአስ፥ ልጁ አሜስያስ፥ ልጁ ዓዛርያስ፥ ልጁ ኢዮአታም፥ ልጁ አካዝ፥ ልጁ ሕዝቅያስ፥ ልጁ ምናሴ፥ ልጁ አሞጽ፥ ልጁ ኢዮስያስ ነበሩ። የኢዮስያስም ልጆች፤ በኩሩ ዮሐናን፥ ሁለተኛውም ኢዮአቄም፥ ሦስተኛውም ሴዴቅያስ፥ አራተኛውም ሰሎም ነበሩ። የኢዮአቄምም ልጆች፤ ልጁ ኢኮንያንና ልጁ ሴዴቅያስ ነበሩ። የምርኮኛውም የኢኮንያን ልጆች፤ ልጁ ሰላትያል፥ መልኪራም፥ ፈዳያ፥ ሼናጻር፥ ይቃምያ፥ ሆሻማ፥ ነዳብያ ነበሩ። የፈዳያ ልጆች ዘሩባቤልና ሰሜኢ ነበሩ፤ የዘሩባቤልም ልጆች፤ ሜሱላም፥ ሐናንያ፥ እኅታቸውም ሰሎሚት ነበረች። ሐሹባ፥ ኦሄል፥ በራክያ፥ ሐሳድያ፥ ዮሻብ-ሒሴድ አምስት ናቸው። የሐናንያም ልጆች ፈላጥያና የሻያ ነበሩ። የረፋያ ልጆች፥ የአርናን ልጆች፥ የአብድዩ ልጆች፥ የሴኬንያ ልጆች። የሴኬንያም ልጅ ሸማያ ነበረ። የሸማያም ልጆች ሐጡስ፥ ይግዓል፥ ባርያሕ፥ ነዓርያ፥ ሻፋጥ ስድስት ነበሩ። የነዓርያም ልጆች ኤልዮዔናይ፥ ሕዝቅያስ፥ ዓዝርቃም ሦስት ነበሩ። የኤልዮናይም ልጆች ሆዳይዋ፥ ኤልያሴብ፥ ፌልያ፥ ዓቁብ፥ ዮሐናን፥ ደላያ፥ ዓናኒ ሰባት ነበሩ። የይሁዳ ልጆች ፋሬስ፥ ኤስሮም፥ ከርሚሆር፥ ሦባል ናቸው። የሦባልም ልጅ ራያ ኢኤትን ወለደ፤ ኢኤትም አሑማይንና ላሃድን ወለደ። እነዚህ የጾርዓውያን ወገኖች ናቸው። እነዚህም የኤጣም አባት ልጆች ናቸው፤ ኢይዝራኤል፥ ይሽማ፥ ይድባሽ፥ እኅታቸውም ሃጽሌልፎኒ ትበባል ነበር። የጌዶርም አባት ፋኑኤል፥ የሑሻም አባት ኤጽር ነበር፤ እነዚህ የቤተልሔም አባት የኤፍራታ የበኩሩ የሆር ልጆች ናቸው። ለቴቁሔም አባት ለአሽሑር ሔላና ነዕራ የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። ነዕራም አሑዛምን፥ ኦፌርን፥ ቴምኒን፥ አሐሽታሪን ወለደችለት። እነዚህ የነዕራ ልጆች ናቸው። የሔላም ልጆች ዴሬት፥ ይጽሐር፥ ኤትናን ናቸው። ቆጽ ዓኑብን፥ ጾቤባን፥ የሃሩምንም ልጅ የአሐርሔልን ወገኖች ወለደ። ያቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ፤ እናቱም፦ “በጣር ወልጄዋለሁና” ብላ ስሙን፦ ያቤጽ ብላ ጠራችው። ያቤጽም፦ “እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ይሁን፤ እንዳይጎዳኝም ከክፋት ጠብቀኝ” ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው። የሹሐም ወንድም ክሉብ የኤሽቶንን አባት ምሒርን ወለደ። ኤሽቶንም ቤትራ-ፋንና ፋሴሐን የዒርናሐሽንም አባት ተሒናን ወለደ፤ እነዚህ የሬካ ሰዎች ናቸው። የቄኔዝም ልጆች ጎቶንያልና ሠራያ ነበሩ። የጎቶንያልም ልጅ ሐታት ነበረ። መዖኖታይ ዖፍራን ወለደ። ሠራያም የጌ-ሃራሽምን አባት ኢዮአብን ወለደ፤ እነርሱም ጠራቢዎች ነበሩ። የዮፎኒም ልጅ ካሌብ ልጆች ዒሩ፥ ኤላ፥ ነዓም ነበሩ፤ የኤላም ልጅ ቄኔዝ ነበረ። የይሃሌልኤል ልጆች ዚፍ፥ ዚፋ፥ ቲርያ፥ አሣርኤል ነበሩ። የዕዝራም ልጆች ዬቴር፥ ሜሬድ፥ ዔፌር፥ ያሎን ነበሩ፤ የሜሬድም ሚስት ማርያምን፥ ሸማይን፥ የኤሽትምዓን አባት ይሽባን ወለደች። አይሁዳዊቱም ሚስቱ የጌዶርን አባት ዬሬድን፥ የሦኮንም አባት ሔቤርን፥ የዛኖዋንም አባት ይቁቲኤልን ወለደች። እነዚህም ሜሬድ ያገባት የፈርዖን ልጅ የቢትያ ልጆች ናቸው። የሆዲያ ሚስት የነሐም እኅት ልጆች የገርሚው የቅዒላ አባትና ማዕካታዊው ኤሽትሞዓ ነበሩ። የሺሞንም ልጆች አምኖን፥ ሪና፥ ቤን-ሐናን፥ ቲሎን ነበሩ። የይሽዒም ልጆች ዞሔትና ቢን-ዞሔት ነበሩ። የይሁዳም ልጅ የሴሎም ልጆች የሌካ አባት ዔር፥ የመሪሳ አባት ለዓዳ፥ ከአሽቤዓ-ቤት የሚሆኑ ጥሩ በፍታ የሚሠሩ ወገኖች፥ ዮቂም፥ የኮዜባ ሰዎች፥ ኢዮአስ፥ ሞዓብን የገዛ ሣራፍ፥ ያሹቢሌሔም ነበሩ። ይህ መዝገብ ጥንታዊ ነው። እነዚህ በነጣዒምና በጋዴራ የሚቀመጡ ሸክላ ሠራተኞች ነበሩ። በዚያ የንጉሡን ሥራ ለመሥራት በእርሱ ዘንድ ይቀመጡ ነበር። የስምዖንም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ያሚን፥ ያሪን፥ ዛራ፥ ሳኡል ነበሩ፤ እንዲሁም ልጁ ሰሎም፥ ልጁ ሚብሣም፥ ልጁ ሚሽማዕ ነበሩ። የሚሽማዕም ልጆች፤ ልጁ ሃሙኤል፥ ልጁ ዘኩር፥ ልጁ ሰሜኢ ነበሩ። ለሰሜኢም ዐሥራ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ለወንድሞቹ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፥ ወገናቸውም ሁሉ እንደ ይሁዳ ልጆች አልተባዙም። እነርሱ የሰፈሩት በቤር-ሳቤህ፥ በሞላዳ፥ በሐጸርሹዓል፥ በቢልሃ፥ በዔጼም፥ በቶላድ፥ በቤቱኤል፥ በሔርማ፥ በጺቅላግ፥ በቤት-ማርካቦት፥ በሐጸር-ሱሲም፥ በቤት-ቢሪ፥ በሸዓራይም ነበር። እስከ ዳዊትም መንግሥት ድረስ ከተሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። መንደሮቻቸው ኤጣም፥ ዐይን፥ ሬሞን፥ ቶኬን፥ ዓሻን፥ አምስቱ ከተሞች ነበሩ፤ እስከ በኣልም ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበሩ መንደሮቻቸው ሁሉ ነበሩ። መቀመጫቸውና የትውልዳቸው መዝገቦች እነዚህ ናቸው። ምሾባብ፥ የምሌክ፥ የአሜስያስ ልጅ ኢዮስያ፥ ኢዮኤል፥ የዮሺብያ ልጅ፥ የሠራያ ልጅ የዓሢኤል ልጅ ኢዩ፥ ኤልዮዔናይ፥ ያዕቆባ፥ የሾሐያ፥ ዓሣያ፥ ዓዲዔል፥ ዩሲምኤል፥ በናያስ፥ የሺፊ ልጅ ዚዛ፥ የአሎን ልጅ የይዳያ ልጅ የሺምሪ ልጅ የሸማያ ልጅ፤ እነዚህ በስማቸው የተጠሩ በወገኖቻቸው ላይ አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች እጅግ በዝተው ነበር። ለመንጎቻቸው መሰማሪያ ለመፈለግ ወደ ጌዶር መግቢያ እስከ ሸለቆው ምሥራቅ ድረስ ሄዱ። የለመለመም እጅግም ያማረ መሰማሪያ አገኙ፥ ምድሪቱም ሰፊ ጸጥታም ያለላትና ሰላም የሰፈነባት ነበረች፤ በቀድሞም ጊዜ በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ከካም ወገን ነበሩ። እነዚህም በስማቸው የተጻፉ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን መጥተው ድንኳኖቻቸውንና በዚያ የተገኙትን ምዑናውያንን መቱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ፈጽመው አጠፉአቸው፤ በዚያም ለመንጎቻቸው መሰማሪያ ነበረና በስፍራቸው ተቀመጡ። የስምዖንም ልጆች አምስት መቶ ሰዎች ወደ ሴይር ተራራ ሄዱ፤ አለቆቻቸውም የይሽዒ ልጆች፥ ፈላጥያ፥ ነዓርያ፥ ረፋያ፥ ዑዝኤል ነበሩ። ያመለጡትንም የአማሌቃውያንን ትሩፋን መቱ፥ በዚያም እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጠዋል። የእስራኤልም በኩር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኩር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኩርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኩርናው ጋር አልተቈጠረም። ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኩርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ። የእስራኤል በኩር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ። የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥ ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ ልጁ ሚካ፥ ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ የአሦር ንጉሥ ቴልጌል-ቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱም የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ። ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥ ዘካርያስ፥ እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ ነበር፤ በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ። በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ። የጋድም ልጆች ከሮቤል ነገድ አጠገብ ባለው በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ ተቀመጡ። አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በባሳን ተቀመጡ። የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ እነርሱም ሰባት ነበሩ። እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ። የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ አኪ ነበረ። በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰማሪያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር። እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ። የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ የውግያ ስልት የሚያውቁ ተዋጊዎችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ። ከአጋራውያንና ከይጡር ከናፊሽና ከናዳብ ጋር ተዋጉ። በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ እነርሱንም ረዳቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተላልፈው ተሰጡ። ከእንስሶቻቸውም ኀምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ። ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ። የምናሴ የነገድ እኩሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣል-አርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ። የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ። የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ። የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌል-ቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ አቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው። የሌዊ ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ነበሩ። የቀዓትም ልጆች፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ነበሩ። የእንበረምም ልጆች፤ አሮን፥ ሙሴ፥ ማርያም ነበሩ። የአሮን ልጆች፤ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ነበሩ። አልዓዛር ፊንሐስን ወለደ፤ ፊንሐስ አቢሱን ወለደ፤ አቢሱም ቡቂን ወለደ፤ ቡቂም ኦዚን ወለደ፤ ኦዚም ዘራእያን ወለደ፤ ዘራእያም መራዮትን ወለደ፤ መራዮት አማርያን ወለደ፤ አማርያም አኪጦብን ወለደ፤ አኪጦብም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪማአስን ወለደ፤ አኪማአስም ዓዛርያስን ወለደ፤ ዓዛርያስም ዮሐናንን ወለደ፤ ዮሐናንም ዓዛርያስን ወለደ፤ እርሱም ሰሎሞን በኢየሩሳሌም በሠራው ቤት በክህነት ያገለግል ነበረ፤ ዓዛርያስም አማርያን ወለደ፤ አማርያም አኪጦብን ወለደ፤ አኪጦብም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም ሰሎምን ወለደ፤ ሰሎምም ኬልቅያስን ወለደ፤ ኬልቅያስም ዓዛርያስን ወለደ፤ ዓዛርያስም ሠራያን ወለደ፤ ሠራያም ኢዮሴዴቅን ወለደ፤ ጌታም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን በናቡከደነፆር እጅ ባስማረከ ጊዜ ኢዮሴዴቅ ተማርኮ ሄደ። የሌዊ ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ነበሩ። እነዚህም የጌድሶን ልጆች ስሞች ናቸው፤ ሎቤኒ እና ሰሜኢ። የቀዓትም ልጆች፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ነበሩ። የሜራሪ ልጆች፤ ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው። ከጌድሶን፤ ልጁ ሎቤኒ፥ ልጁ ኢኤት፥ ልጁ ዛማት፥ ልጁ ዮአክ፥ ልጁ አዶ፥ ልጁ ዛራ፥ ልጁ ያትራይ ነበሩ። የቀዓት ልጆች፤ ልጁ አሚናዳብ፥ ልጁ ቆሬ፥ ልጁ አሴር፥ ልጁ ሕልቃና፥ ልጁ አቢሳፍ፥ ልጁ አሴር፥ ልጁ ኢኢት፥ ልጁ ኡርኤል፥ ልጁ ዖዝያ፥ ልጁ ሳውል ነበሩ። የሕልቃናም ልጆች፥ አማሢ፥ አኪሞት። የሕልቃናም ልጆች፤ ልጁ ሱፊ፥ ልጁ ናሐት፥ ልጁ ኤልያብ፥ ልጁ ይሮሐም፥ ልጁ ሕልቃና ነበሩ። የሳሙኤልም ልጆች፤ በኩሩ ኢዮኤል፥ ሁለተኛውም አብያ ነበሩ። የሜራሪ ልጆች፤ ሞሖሊ፥ ልጁ ሎቤኒ፥ ልጁ ሰሚኢ፥ ልጁ ዖዛ፥ ልጁ ሳምዓ፥ ልጁ ሐግያ፥ ልጁ ዓሣያ ነበሩ። ዳዊትም ታቦቱ ዐርፎ ከተቀመጠ በኋላ በጌታ ቤት ያቆማቸው የመዘምራን አለቆች እነዚህ ናቸው። እነርሱም ሰሎሞን የጌታን ቤት በኢየሩሳሌም እስኪሠራ ድረስ በመገናኛ ድንኳን ማደሪያ ፊት እያዜሙ ያገለግሉ ነበር፤ በየተራቸውም ያገለግሉ ነበር። አገልጋዮቹና ልጆቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከቀዓት ልጆች ዘማሪው ኤማን ነበረ፤ እርሱም የኢዮኤል ልጅ፥ የሳሙኤል ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የይሮሐም ልጅ፥ የኤሊኤል ልጅ፥ የቶዋ ልጅ፥ የሱፍ ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የመሐት ልጅ፥ የአማሢ ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የኢዮኤል ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የሶፎንያስ ልጅ፥ የታሐት ልጅ፥ የአሴር ልጅ፥ የአብያሳፍ ልጅ፥ የቆሬ ልጅ፥ የይስዓር ልጅ፥ የቀዓት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የእስራኤል ልጅ ነበር። በቀኙም የቆመ ወንድሙ አሳፍ ነበረ፤ አሳፍም የበራክያ ልጅ፥ የሳምዓ ልጅ፥ የሚካኤል ልጅ፥ የበዓሤያ ልጅ፥ የመልክያ ልጅ፥ የኤትኒ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ የዓዳያ ልጅ፥ የኤታን ልጅ፥ የዛማት ልጅ፥ የሰሜኢ ልጅ፥ የኢኤት ልጅ፥ የጌድሶን ልጅ፥ የሌዊ ልጅ ነበር። በግራቸውም በኩል ወንድሞቻቸው የሜራሪ ልጆች ነበሩ፤ ኤታን የቂሳ ልጅ፥ የአብዲ ልጅ፥ የማሎክ ልጅ፥ የሐሸብያ ልጅ፥ የአሜስያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ የአማሲ ልጅ፥ የባኒ ልጅ፥ የሴሜር ልጅ፥ የሞሖሊ ልጅ፥ የሙሲ ልጅ፥ የሜራሪ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ ነበር። ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ቤት ማደሪያ አገልግሎት ሁሉ ተሰጡ። አሮንና ልጆቹ ግን የእግዚአሔር ባርያ ሙሴ እንዳዘዘው ሁሉ ለቅድስተ ቅዱሳን ሥራ ሁሉ ስለ እስራኤልም ለማስተስረይ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ይሠዉ ነበር፥ በዕጣኑም መሠዊያ ላይ ያጥኑ ነበር። የአሮንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ልጁ አልዓዛር፥ ልጁ ፊንሐስ፥ ልጁ አቢሱ፥ ልጁ ቡቂ፥ ልጁ ኦዚ፥ ልጁ ዘራእያ፥ ልጁ መራዮት፥ ልጁ አማርያ፥ ልጁ አኪጦብ፥ ልጁ ሳዶቅ፥ ልጁ አኪማአስ። ማደሪያዎቻቸውም በየሰፈራቸው በየዳርቻቸው እነዚህ ናቸው፤ አንደኛው ዕጣ የወጣው ለአሮን ልጆች ለቀዓት ወገኖች ነበረ። ለእነርሱ በይሁዳ አገር ያለችውን ኬብሮንን፥ በእርሷ ዙሪያ የነበረውን መሰማሪያ ሰጡ፤ የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጡ። ለአሮንም ልጆች እነዚህን የመማፀኛ ከተሞች ሰጡ፤ እርሱም፦ ኬብሮን፥ ልብናና መሰማሪያዋ፥ ደግሞ የቲር፥ ኤሽትሞዓና መሰማሪያዋ፥ ሖሎንና መሰማሪያዋ፥ ዳቤርና መሰማሪያዋ፥ ዓሳንና መሰማሪያዋ፥ ቤት-ሳሚስና መሰማሪያዋ ናቸው፤ እንዲሁም ከብንያምም ነገድ ጌባንና መሰማሪያዋን፥ ጋሌማትንና መሰማሪያዋን፥ ዓኖቶትንና መሰማሪያዋን ሰጡ። ከተሞቻቸው ሁሉ በየወገናቸው ዐሥራ ሦስት ነበሩ። ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከነገዱ ወገን ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተሰጡ። ለጌድሶንም ልጆች በየወገናቸው ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ፥ ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተሰጡ። ለሜራሪ ልጆች በየወገናቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ፥ ዐሥራ ሁለት ከተሞች በዕጣ ተሰጡ። የእስራኤልም ልጆች ለሌዋውያን ከተሞችን ከመሰማሪያዎቻቸው ጋር ሰጡ። ከይሁዳም ልጆች ነገድ፥ ከስምዖንም ልጆች ነገድ፥ ከብንያምም ልጆች ነገድ፥ እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ከተሞች በዕጣ ሰጡ። ከቀዓትም ልጆች ወገኖች ለአንዳንዶቹ ከኤፍሬም ነገድ ከተሞች ድርሻ ነበራቸው። እነዚህም የመማፀኛ ከተሞች ለእነርሱ ተሰጣቸው፤ እነርሱም፦ በተራራማው በኤፍሬም አገር ያለችውን ሴኬምና መሰማሪያዋ፥ ደግሞም ጌዝርና መሰማሪያዋ፥ ዮቅምዓምና መሰማሪያዋ፥ ቤት-ሖሮንና መሰማሪያዋ፥ ኤሎንና መሰማሪያዋ፥ ጋት-ሪሞንና መሰማሪያዋ ናቸው። እንዲሁም ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ዓኔርንና መሰማሪያዋን፥ ቢልዓምንና መሰማሪያዋን፥ ከቀዓት ልጆች ወገን ለቀሩት ተሰጣቸው። ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ወገን በባሳን ያለችው ጎላንና መሰማሪያዋ፥ አስታሮትና መሰማሪያዋ ተሰጣቸው፤ ከይሳኮርም ነገድ ቃዴስና መሰማሪያዋ፥ ዳብራትና መሰማሪያዋ፥ ራሞትና መሰማሪያዋ፥ ዓኔምና መሰማሪያዋ፤ ከአሴርም ነገድ መዓሳልና መሰማሪያዋ፥ ዓብዶንና መሰማሪያዋ፥ ሑቆቅና መሰማሪያዋ፥ ረአብና መሰማሪያዋ፤ ከንፍታሌምም ነገድ በገሊላ ያለችው ቃዴስና መሰማሪያዋ፥ ሐሞንና መሰማሪያዋ፥ ቂርያታይምና መሰምርያዋ ተሰጣቸው። ከሌዋውያን ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ከዛብሎን ነገድ ሬሞንና መሰማሪያዋ፥ ታቦርና መሰማሪያዋ ተሰጣቸው፤ እንዲሁም ከሮቤልም ነገድ በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል በምድረ በዳ ያለችው ቦሶርና መሰማሪያዋ፥ ያሳና መሰማሪያዋ፥ ቅዴሞትና መሰማሪያዋ፥ ሜፍዓትና መሰማሪያዋ፤ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ያለችው ሬማትና መሰማሪያዋ፥ መሃናይምና መሰማሪያዋ፥ ሐሴቦንና መሰማሪያዋ፥ ኢያዜርና መሰማሪያዋ ተሰጣቸው። የይሳኮርም ልጆች፥ ቶላ፥ ፉዋ፥ ያሱብ ሺምሮን፥ አራት ናቸው። የቶላም ልጆች፥ ኦዚ፥ ራፋያ፥ ይሪኤል፥ የሕማይ፥ ይብሣም፥ ሽሙኤል፥ የአባታቸውም የቶላ ቤት አለቆች፥ በትውልዳቸው ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በዳዊት ዘመን ቁጥራቸው ሀያ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ። የኦዚም ልጆች ይዝረሕያ፤ የይዝረሕያም ልጆች ሚካኤል፥ አብድዩ፥ ኢዮኤል፥ ይሺያ አምስት ናቸው፤ ሁሉም አለቆች ነበሩ። ከእነርሱም ጋር በየትውልዳቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ለውግያ የተዘጋጁ የሠራዊት ጭፍሮች ነበሩ፤ ብዙም ሴቶችና ልጆች ነበሩአቸውና ሠላሳ ስድስት ሺህ ነበሩ። የይሳኮር ወገኖች የሆኑ ወንድሞቻቸው ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች በትውልዳቸው ሁሉ የተቈጠሩት ሰማኒያ ሰባት ሺህ ነበሩ። የብንያም ልጆች ቤላ፥ ቤኬር፥ ይዲኤል ሦስት ነበሩ። የቤላም ልጆች፥ ኤሴቦን፥ ኦዚ፥ ዑዝኤል፥ ኢያሪሙት፥ ዒሪ፥ አምስት ነበሩ፤ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በትውልድ የተቈጠሩ ሀያ ሁለት ሺህ ሠላሳ አራት ነበሩ። የቤኬርም ልጆች፤ ዝሚራ፥ ኢዮአስ፥ አልዓዛር፥ ኤልዮዔናይ፥ ዖምሪ፥ ኢያሪሙት፥ አብያ፥ ዓናቶት፥ ዓሌሜት፤ እነዚህ ሁሉ የቤኬር ልጆች ነበሩ። በየትውልዳቸው መዝገብ የተቈጠሩ፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ሀያ ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። የይዲኤልም ልጅ ቢልሐን ነበረ፤ የቢልሐንም ልጆች፤ የዑስ፥ ብንያም፥ ኤሁድ፥ ክንዓና፥ ዜታን፥ ተርሴስ፥ አኪሳአር ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የይዲኤል ልጆች ነበሩ፤ በየአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጭፍራ እየሆኑ ወደ ውግያ የሚወጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ዐሥራ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። ደግሞም ሳፊን፥ ሑፊም የዒር ልጆች፥ ሑሺም የአሔር ልጆችም ነበሩ። የንፍታሌም ልጆች፥ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም ነበሩ፤ እነርሱም ከባላ የዘር ሐጋቸው ይመዘዛል። የምናሴ ልጆች ሶርያይቱ ቁባቱ የወለደችለት እስርኤልና የገለዓድ አባት ማኪር ናቸው። ማኪርም ከሑፊምና ከሳፊን ወገን ሚስት አገባ፤ የእኅትዋም ስም መዓካ ነበረ፤ የሁለተኛውም ስም ሰለጰአድ ነበረ፤ ለሰለጰዓድም ሴቶች ልጆች ነበሩት። የማኪርም ሚስት መዓካ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው፤ የወንድሙም ስም ሱሮስ ነበረ፤ ልጆቹም ኡላም፥ ራቄም ነበሩ። የኡላምም ልጅ ባዳን ነበረ፤ እነዚህ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ነበሩ። እኅቱ መለኬት ኢሱድን፥ አቢዔዝርን፥ መሕላን ወለደች። የሸሚዳም ልጆች አሒያን፥ ሴኬም፥ ሊቅሒ፥ አኒዓም ነበሩ። የኤፍሬም ልጆች፤ ሹቱላ፥ ልጁ ባሬድ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ኤልዓዳ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ዛባድ፥ ልጁ ሹቱላ፥ የአገሩም ተወላጆች የጌት ሰዎች ከብቶቻቸውን ሊወስዱ ወርደው ነበርና የገደሉአቸው ልጆቹ ኤድርና ኤልዓድ ነበሩ። አባታቸውም ኤፍሬም ብዙ ቀን አለቀሰ፥ ወንድሞቹም ሊያጽናኑት መጡ። ኤፍሬምም ወደ ሚስቱ ገባ፥ አረገዘችም፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ በቤቱም መከራ ሆኖአልና ስሙ በሪዓ ብሎ ጠራው። ሴት ልጁም ታችኛውንና ላይኛውን ቤት-ሖሮንንና ኡዜን-ሼራን የሠራች ሲኦራ ነበረች። ወንዶች ልጆቹም ፋፌ፥ ሬሴፍ፥ ልጁ ቴላ፥ ልጁ ታሐን፥ ልጁ ለአዳን፥ ልጁ ዓሚሁድ፥ ልጁ ኤሊሳማ፥ ልጁ ነዌ፥ ልጁ ኢያሱ ነበሩ። ግዛታቸውና ማደሪያቸው ቤቴልና መንደሮችዋ፥ በምሥራቅም በኩል ነዓራን፥ በምዕራብም በኩል ጌዝርና መንደሮችዋ፥ ሴኬምና መንደሮችዋ ጋዛና መንደሮችዋ ነበሩ፤ እንዲሁም በምናሴም ልጆች ዳርቻ ቤት-ሳንና መንደሮችዋ፥ ታዕናክና መንደሮችዋ፥ መጊዶና መንደሮችዋ፥ ዶርና መንደሮችዋ ነበሩ፤ በእነዚህ የእስራኤል ልጅ የዮሴፍ ልጆች ተቀመጡ። የአሴር ልጆች ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸውም ሤራሕ። የበሪዓም ልጆች፤ ሔቤር፥ የቢርዛዊት አባት የነበረው መልኪኤል ነበሩ። ሔቤርም ያፍሌጥን፥ ሳሜርን፥ ኮታምን፥ እኅታቸውንም ሶላን ወለደ። የያፍሌጥም ልጆች ፋሴክ፥ ቢምሃል፥ ዓሲት ነበሩ፤ እነዚህ የያፍሌጥ ልጆች ነበሩ። የሳሜርም ልጆች አኪ፥ ሮኦጋ፥ ይሑባ፥ አራም ነበሩ። የወንድሙም የኤላም ልጆች ጾፋ፥ ይምና፥ ሰሌስ፥ ዓማል ነበሩ። የጾፋም ልጆች ሱዋ፥ ሐርኔፍር፥ ሦጋል፥ ቤሪ፥ ይምራ፥ ቤጼር፥ ሆድ፥ ሳማ፥ ሰሊሳ፥ ይትራን፥ ብኤራ ነበሩ። የዬቴር ልጆች ዮሮኒ፥ ፊስጳ፥ አራ ነበሩ። የዑላ ልጆች ኤራ፥ ሐኒኤል፥ ሪጽያ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የአሴር ልጆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ የተመረጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች፥ የመኳንንቱ አለቆች ነበሩ። በትውልዳቸውም በጦርነት ላይ ለመዋጋት የተቈጠሩ ሀያ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ። ብንያምም በኩሩን ቤላን፥ ሁለተኛውንም አስቤልን፥ ሦስተኛውንም አሐራን፥ አራተኛውንም ኖሐን፥ አምስተኛውንም ራፋን ወለደ። ለቤላም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም አዳር፥ ጌራ፥ አቢሁድ፥ አቢሱ፥ ናዕማን፥ ኦሖዋ፥ ጌራ፥ ሰፉፋም፥ ሑራም ናቸው። እነዚህ የኤሁድ ልጆች ናቸው፤ እነዚህ በጌባ የሚቀመጡ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ናቸው፤ እነርሱም ወደ መናሐትም ተማረኩ፤ ናዕማን፥ አኪያ፥ ሔግላ የተባለው ጌራ ዖዛንና አሒሑድን ወለደ። ሸሐራይምም ሚስቶቹን ሑሺምንና በዕራን እንዲሄዱ ካሰናበተ በኋላ በሞዓብ ሜዳ ልጆች ወለደ። ከሚስቱ ከሖዴሽ ዮባብን፥ ዲብያን፥ ማሴን፥ ማልካምን፥ ይዑጽን፥ ሻክያን፥ ሚርማን ወለደ። እነዚህም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። ከሑሺምም አቢጡብንና ኤልፍዓልን ወለደ። የኤልፍዓልም ልጆች፤ ዔቤር፥ ሚሻም አኖንና ሎድን መንደሮቻቸውንም የሠራ ሻሚድ ነበሩ፤ በሪዓና ሽማዕ የጌትን ሰዎች ያሳደዱ የኤሎን ሰዎች የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ፤ አሒዮ፥ ሻሻቅ፥ ይሬምት፥ ዝባድያ፥ ዓራድ፥ ዔድር፥ ሚካኤል፥ ይሽጳ፥ ዮሐ የበሪዓ ልጆች ነበሩ። ዝባድያ፥ ሜሱላም፥ ሕዝቂ፥ ሔቤር፥ ይሽምራይ፥ ይዝሊያ፥ ዮባብ የኤልፍዓል ልጆች ነበሩ። ያቂም ዝክሪ፥ ዘብዲ፥ ኤሊዔናይ፥ ጺልታይ፥ ኤሊኤል፥ ዓዳያ፥ ብራያ፥ ሺምራት፥ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ፤ ይሽጳን፥ ዔቤር፥ ኤሊኤል፥ ዓብዶን፥ ዝክሪ፥ ሐናን፥ ሐናንያ፥ ኤላም፥ ዓንቶትያ፥ ዩፍደያና ፋኑኤል ተብለው የሚጠሩ ናቸው። ሸምሽራይ፥ ሸሃሪያ፥ ጎቶልያ፥ ያሬሽያ፥ ኤልያስ፥ ዝክሪ፥ የይሮሐም ልጆች ነበሩ። እነዚህ በትውልዶቻቸው አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ፤ እነዚህ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው በገባዖን የተቀመጠው የገባዖን አባት ይዒኤል፥ የበኩር ልጁ ዓብዶን፥ ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ናዳብ፥ ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር፥ ሳምአን የወለደው ሚቅሎት ነበሩ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ተቀመጡ። ኔር ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሜልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስባኣልን ወለደ። የዮናታንም ልጅ መሪ-በኣል ነበረ፤ መሪ-በኣልም ሚካን ወለደ። የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሬዓ፥ አካዝ ነበሩ። አካዝም ይሆዓዳን ወለደ፤ ይሆዓዳም ዓሌሜትን፥ ዓዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ። ሞጻም ቢንዓን ወለደ፤ ልጁም ረፋያ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል ነበሩ፤ ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ ስማቸውም ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሽዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን ይባሉ ነበር፤ እነዚህ ሁሉ የኤሴል ልጆች ነበሩ። የወንድሙም የአሴል ልጆች፤ በኩሩ ኡላም፥ ሁለተኛውም ኢያስ፥ ሦስተኛውም ኤሊፋላት ነበሩ። የኡላም ልጆች ጽኑዓን ኃያላንና ቀስተኞች ነበሩ፤ ለእነርሱም መቶ ኀምሳ የሚያህሉ ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆች ነበሩአቸው፤ እነዚህ ሁሉ የብንያም ልጆች ነበሩ። እስራኤልም ሁሉ በየትውልዳቸው ተቈጠሩ፤ እነሆም፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጻፉ። ይሁዳም ስለ ኃጢአታቸው ወደ ባቢሎን ተማረኩ። በአውራጃዎቻቸውና በከተሞቻቸው መጀመሪያ የተቀመጡ እስራኤልና ካህናት ሌዋውያንም የቤተ መቅደሱም አገልጋዮች ነበሩ። ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች ከኤፍሬምና ከምናሴ ልጆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። ከይሁዳ ልጅ ከፋሬስ ልጆች የባኒ ልጅ የአምሪ ልጅ የዖምሪ ልጅ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ ደግሞ በዚያ ተቀመጠ። ከሴሎናውያንም በኩሩ ዓሣያና ልጆቹ በዚያ ተቀመጡ። ከዛራም ልጆች ይዑኤልና ወንድሞቻቸው፥ ስድስት መቶ ዘጠና ነበሩ። ከብንያምም ልጆች የሐስኑአ ልጅ የሆዳይዋ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሉ ነበር፤ የይሮሐም ልጅ ብኔያ፤ የሚክሪ ልጅ የኦዚ ልጅ ኤላ ነበር፤ የይብንያ ልጅ የራጉኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ ሜሱላም ነበር፤ በየትውልዳቸውም ወንድሞቻቸው ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ። ከካህናቱም ዮዳኤ፥ ዮአሪብ፥ ያኪን ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ የመራዮት ልጅ የሳዶቅ ልጅ የሜሱላም ልጅ የኬልቅያስ ልጅ ዓዛርያስ ነበር፤ የመልክያ ልጅ የጳስኮር ልጅ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ ነበር፤ የኢሜር ልጅ የምሺላሚት ልጅ የሜሱላም ልጅ የየሕዜራ ልጅ የዓዲኤል ልጅ መዕሣይ ነበር፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ወንድሞቻቸው ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ፤ ለእግዚአብሔር ቤት ለሚከናወነው የአገልግሎት ሥራ እጅግ ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ከሌዋውያንም የሜራሪ ልጆች የአሳብያ ልጅ የዓዝሪቃም ልጅ የአሱብ ልጅ ሸማያ ነበር፤ በቅበቃር፥ ኤሬስ፥ ጋላል፥ የአሳፍ ልጅ የዝክሪ ልጅ የሚካ ልጅ መታንያ ነበር፤ የኤዶታም ልጅ የጋላል ልጅ የሰሙስ ልጅ አብድያ ነበር፤ በነጦፋውያንም መንደሮች የተቀመጠው የሕልቃና ልጅ የአሳ ልጅ በራክያ ነበር። በርም ጠባቂዎች ሰሎም፥ ዓቁብ፥ ጤልሞን፥ አሒማን፥ ወንድሞቻቸውም ነበሩ፤ ሰሎምም አለቃ ነበረ። እስከ ዛሬም ድረስ በንጉሥ በር በምሥራቅ በኩል ሰፍረዋል፤ ለሌዊ ልጆች ሰፈር በርም ጠባቂዎች ነበሩ። የቆሬም ልጅ የአብያሳፍ ልጅ የቆሬ ልጅ ሰሎም ከአባቱም ቤት የነበሩ ወንድሞቹ ቆሬያውያን በማገልገል ሥራ ላይ ነበሩ፥ አባቶቻቸውም የጌታን ሰፈር መግቢያ ይጠብቁ እንደ ነበር እንዲሁ የድንኳኑን የመግቢያ ደጅ ይጠብቁ ነበር።። አስቀድሞም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ አለቃቸው ነበረ፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነበረ። የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ የመገናኛው ድንኳን ደጅ ጠባቂ ነበረ። የመግቢያው ደጅ ጠባቂዎች እንዲሆኑ የተመረጡ እነዚህ ሁሉ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል በሥራቸው ያቆሙአቸው እነዚህ በመንደሮቻቸው በየትውልዳቸው ተቈጠሩ። እነርሱና ልጆቻቸውም በጌታ ቤት በድንኳኑ ደጆች ላይ ዘበኞች ነበሩ። በአራቱ ማዕዘኖች፥ በምሥራቅ፥ በምዕራብ፥ በሰሜን፥ በደቡብ፥ ጠባቂዎች ነበሩ። በመንደሮቸቻቸውም የነበሩ ወንድሞቻቸው በየሰባትም ቀን ከእነርሱ ጋር አብረው ለመሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይመጡ ነበር። ከሌዋውያንም የነበሩ አራቱ የጠባቂዎች አለቆች በሥራቸው ታማኞች ነበሩ፤ በጌታም ቤት ባሉ ጓዳዎችና ቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው ነበር። የእግዚአብሔርንም ቤት የሚጠብቁ፥ ጥዋት ጥዋትም ደጆቹን የሚከፍቱ እነርሱ ነበሩና በዚያ ያድሩ ነበር። ዕቃውም በቍጥር፥ ይገባና ይወጣ ነበርና ከእነዚህ እያንዳንዱ በመገልገያው ዕቃ ላይ ሹሞች ነበሩ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ በመቅደሱ ዕቃ ሁሉ በመልካሙም ዱቄት፥ በወይን ጠጁም፥ በዘይቱም፥ በዕጣኑም፥ በሽቶውም ላይ ሹሞች ነበሩ። ከካህናቱም ልጆች አንዳንዶቹ የሽቶውን ቅባት ይቀምሙ ነበር። የቆሬያዊውም የሰሎም በኩር ሌዋዊው ማቲትያ በምጣድ በሚጋገረው ኅብስት ላይ ሹም ነበረ። ከወንድሞቻቸውም ከቀዓታውያን አንዳንዶቹን በየሰንበቱ የተቀደሰውን ኅብስት እንዲያዘጋጁ ሹሞች ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች የነበሩ መዘምራን እነዚህ ናቸው፤ ሥራቸውም ሌሊትና ቀን ነበረና ያለ ሌላ ሥራ በየእልፍኛቸው ይቀመጡ ነበር። እነዚህ ከሌዋውያን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች በየትውልዳቸውም አለቆች ነበሩ። እነዚህም በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ነበር። የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው በገባዖን የተቀመጠው የገባዖን አባት ይዒኤል፥ የበኩር ልጁም ዓብዶን፥ ከዚያም በኋላ ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ኔር፥ ናዳብ፥ ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር፥ ሚቅሎት ነበሩ። ሚቅሎትም ሳምአን ወለደ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ይቀመጡ ነበር። ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሜልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስባኣልን ወለደ። የዮናታንም ልጅ መሪበ-ኣል ነበረ፤ መሪበ-ኣልም ሚካን ወለደ። የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሪዓ፥ አካዝ ነበሩ። አካዝም የዕራን ወለደ፤ የዕራም ዓሌሜትን፥ ዕዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ። ሞጻም ቢንዓን ወለደ፥ ልጁም ረፋያ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል ነበሩ፤ ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ የኤሴል ልጆች ነበሩ። ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን ተከታትለው አባረሩአቸው፤ የፍስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። ውጊያውም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እነርሱም አቈሰሉት። ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፦ “እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። ሳኦልና ሦስቱም ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ሠራዊቱ እንደ ሸሸ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። በማግስቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች እንዲናገሩ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ መልእክተኞችን ላኩ። መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት። የኢያቢስ-ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ ጽኑዓን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከባሉጥ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ። እንዲሁ ሳኦል በጌታ ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የጌታንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ፥ ጌታንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አስተላለፈ። እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤ አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ ጌታ አምላክህም፦ ‘ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በጌታ ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም አንደበት እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን ቀቡት። ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን፦ “ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት። ዳዊትም፦ “ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ አለቃም ሆነ። ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት። ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አደሰ። ዳዊትም የሠራዊት ጌታ ከእርሱ ጋር ነበረና እየበረታ ሄደ። ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል ሊያነግሡት ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት። የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሦስቱ ኃያላን አለቃ የሐክሞናዊው ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበረ። እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለውጊያ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። እርሱና ዳዊት በእርሻውም መካከል ጸንተው ቆሙ፤ ስፍራውንም አላስደፈሩም፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ ጌታም በታላቅ ድል አድራጊነት አዳናቸው። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተልሔም ነበረ። ዳዊትም፦ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” ብሎ ተመኘ። እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት በመካከላቸው ጥሰው አለፉ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልፈለገም፥ ነገር ግን ለጌታ እንደ መባ አፈሰሰው፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ “ይህን እንዳደርግ አምላኬ አይፈቅድልኝም፤ በነፍሳቸው የደፈሩትን የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣለሁን? ነፍሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው አምጥተውታል።” ስለዚህም ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም ነበር። በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤልን ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጉድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብፃዊው እጅ ጦሩን ነጠቀው፥ በገዛ ጦሩም ገደለው። የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበረ። እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው። ደግሞም በሠራዊቱ ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥ የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ሴቤካይ፥ አሆሃዊው ዔላይ፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥ ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ ዓረባዊው አቢኤል፥ ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ ምኬራታዊው ኦፌር፥ ፍሎናዊው አኪያ፥ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥ የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥ አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥ አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥ የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥ መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻውያ፥ የኤልነዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥ ኤሊኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል ነበሩ። በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በጦርነትም ካገዙት ኃያላን መካከል ነበሩ። ቀስተኞችም ነበሩ፥ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ። አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፥ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ ሁለቱም የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ነበሩ፤ እንዲሁም ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች ነበሩ፤ በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥ ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኃያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥ ገድሮታዊው ዮዛባት፥ ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፥ ቆሬያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ ዓዘርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾብዓም ነበሩ፤ የጌዶር ሰው የይሮሐም ልጆች ዮዔላ፥ ዝባድያ ነበሩ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአምባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ በጋሻና በጦር ስልታቸው የተካኑ፥ ጽኑዓን ኃያላን፥ ተዋጊዎች፥ ወደ እርሱ መጡ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፥ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥ ሦስተኛው ኤልያብ፥ አራተኛው መስመና፥ አምስተኛው ኤርምያስ፥ ስድስተኛው ዓታይ፥ ሰባተኛው ኤሊኤል፥ ስምንተኛው ዮሐናን፥ ዘጠኝኛው ኤልዛባድ፥ አሥረኛው ኤርምያስ፥ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ ነበሩ። እነዚህ የጋድ ልጆች የሠራዊቱ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ የመቶ አለቃ፥ ታላቁ የሺህ ማዕርግ ያላቸው ነበሩ። በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ። ዳዊትም ወደ ነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ። ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጣ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን ለመርዳት በሰላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደሆነ ልቤ ከእንናተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደሆነ ግን፥ በእጄ ዓመጽ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከት፤ ፍርድም ይስጥ።” መንፈስም በሠላሳው አለቃ በዓማሣይ ላይ ወረደ፥ እርሱም እንዲህ አለ፦ “ዳዊት ሆይ! እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ! እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፥ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን።” ዳዊትም ተቀበላቸው፥ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው። ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን፦ “በራሳችን ላይ ጉዳት አምጥቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ሲሉ ተማክረው እንዲመለስ አድርገውታልና እርሱ አልረዱአቸውም። ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ። ሁሉም ጽኑዓን ኃያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ጭፍሮች ላይ ዳዊትን አገዙት። እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር። እንደ ጌታም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ለመመለስ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው። ጋሻና ጦር ተሸክመው ለውግያ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። ለውግያ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤ ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኃያል ጎልማሳ ሳዶቅ ነበረ፥ ከአባቱም ቤት ሀያ ሁለት የጦር አዛዦች ነበሩ። የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ልጆች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ። ጽኑዓን ኃያልን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሀያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ለማንገሥ የመጡ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ። እስራኤልም የሚገባውን እንዲፈጽም የዘመኑን ሁኔታ የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር። በጽኑ የሠለጠኑ ተዋጊዎች ለውግያም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ የታጠቁ የዛብሎን ሰዎች ኀምሳ ሺህ ነበሩ። የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የታጠቁ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ። ለውጊያም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሀያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። በጽኑ የሠለጠኑ ተዋጊዎች፥ ለውጊያም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ። በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ታጥቀው የመጡ መቶ ሀያ ሺህ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ተዋጊዎች በሰልፍ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ለማንገሥ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ለማንገሥ በአንድ ልብ ነበሩ። ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ። ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና ከይሳኮርና ከዛብሎን ከንፍታሌምም ድረስ በእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራ ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢብ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዛት ያመጡ ነበር። ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከሹማምንቱም ሁሉ ጋር ተማከረ። ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “መልካም መስሎ ቢታያችሁ፥ የጌታም የአምላካችን ፈቃድ ቢሆን፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማሪያዎቻቸውም ለተቀመጡት ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ እንዲሰበሰቡ እንላክባቸው፤ በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ።” ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ፦ “እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያት-ይዓሪም ለማምጣት ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሆር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የጌታን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያት-ይዓሪም ወደተባለች ወደ በኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር። ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በዝማሬና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጸልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። የጌታም ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። ጌታም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ-ስብራት ብሎ ጠራው። በዚያም ቀን ዳዊት፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ። ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢ-ዳራ ቤት ወሰደው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም። የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢ-ዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ጌታም የአቢ-ዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤት እንዲሠሩለት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ። ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ እጅግ ከፍ ብሏልና ጌታ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ አገባ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶችን ልጆች ወለደ። በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም፤ ሳሙስ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት ተብለው ይጠሩ ነበር። ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እነርሱን ሊወጋቸው ወጣ። ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ። ዳዊትም፦ “ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። ጌታም፦ “በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ” አለው። ወደ በኣል-ፐራሲምም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት ድል ነሣቸው። ዳዊትም፦ “ግድቡን አፍርሶ እንደሚወጣ ጎርፍ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው” አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣል-ፐራሲም ብለው ጠሩት። አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሉአቸው። ዳግመኛም ፍልስጥኤማውያን በሸለቆው አደጋ ጣሉ። ዳዊትም እንደገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ። በሾላውም ዛፍ አናት የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ውግያ ውጣ።” ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት። የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ መፈራቱንም ጌታ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው። ዳዊትም በራሱ ከተማ ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት። በዚያን ጊዜም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲሸከሙ፥ ለዘለዓለሙም እንዲያገለግሉት ጌታ ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የጌታን ታቦት ሊሸከም አይገባውም።” ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የጌታን ታቦት ለማምጣት እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያን ሰበሰበ። ከቀዓት ልጆች፤ ከመቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኡርኤል ነበር፤ ከሜራሪ ልጆች፤ ከሁለት መቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ዓሣያ ነበር፤ ከጌድሶን ልጆች፤ ከመቶ ሠላሳ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኢዮኤል ነበር፤ ከኤሊጻፋን ልጆች፤ ከሁለት መቶ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ሸማያ ነበር፤ ከኬብሮን ልጆች፤ ከሰማንያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኤሊኤል ነበር፤ ከዑዝኤል ልጆች፤ ከመቶ ዐሥራ ሁለት ወንድሞቹ ጋር አለቃው አሚናዳብ ነበር። ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠራቸው፤ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የጌታን ታቦት እንድታመጡ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። ቀድሞም አልተሸከማችሁትምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና ጌታ አምላካችን በመካከላችን ቊጣውን አወረደ።” የእስራኤልንም አምላክ የጌታን ታቦት ለማምጣት ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ። ሙሴም እንዳዘዘው እንደ ጌታ ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ። ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን እንዲሾሙ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን ሾሙ፤ ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ደረጃ ያሉትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅኔያን፥ ደጁንም የሚጠብቁትን ዖቤድ-ኤዶምንና ይዒኤልን ሾሙ። መዘምራንም የነበሩት ኤማንና አሳፍ ኤታምንም የናሱን ጸናጽል ድምፅ ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር። መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኔያ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ ዜማን አዋቂ ስለ ነበር ዜማውን እንዲመራ ተሾሞ ነበር። በራክያና ሕልቃናም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ። ካህናቱም ሰበኒያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድ-ኤዶምና ይሒያም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ። ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዖቤድ-ኤዶም ቤት በደስታ ለማምጣት ሄዱ። የጌታንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ። ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም ኤፉድ ያለበት በፍታ ለብሶ ነበር። እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ። የጌታም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲያሸበሽብና ሲዘል አይታ በልብዋ ናቀችው። የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕትም በጌታ ፊት አቀረቡ። ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቅርቦ በፈጸመ ጊዜ በጌታ ስም ሕዝቡን ባረከ። ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቁራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። በጌታም ታቦት ፊት እንዲያገለግሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ጌታን እንዲወድሱት፥ እንዲያመሰግኑትና እንዲያከብሩትም ከሌዋውያን ወገን ሾመ። አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ መሰንቆና በገና ይጫወቱ የነበሩት ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል ነበሩ፤ አሳፍም የጸናጽልን ድምፅ ያሰማ ነበረ። ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ አንደበት ጌታን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ። ጌታን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ክብር ይሁን፤ ጌታን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። ጌታን ፈልጉት፥ ብርታቱን እሹ፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። ተአምራቱንም የተናገረውንም ፍርድ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፤ እናንተ ባርያዎቹ የሆናችሁ የእስራኤል ዘር ሆይ! ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ! እርሱ ጌታ አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፤ እንዲህም አለ፦ “ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ድርሻ እሰጣለሁ፤” ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች በነበሩ ጊዜ ነው። ከአንድ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ፥ ከአንድም መንግሥት ወደ ሌላ ሕዝብ ተንከራተቱ። ማንም ሰው ግፍ እንዲያደርግባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። እንዲህም አለ፦ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴ ክፉ አታድርጉ።” ምድር ሁሉ ጌታን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለሰዎች ሁሉ ንገሩ። ጌታ ታላቅ፥ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋልና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ ጌታ ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው። የአሕዛብ ወገኖች ለጌታ የሚገባውን ስጡ፥ ለጌታ ተገቢውን ክብርና ኃይል ስጡ። ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ቁርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ፤ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። ምድር ሁሉ በፊቱ ትናወጥ፤ ዓለሙም ፍጹም እንዳይናወጥ በጽኑ ይታነጻል። ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤ በአሕዛብም መካከል፦ “ጌታ ነግሷል” ይበሉ። ባሕርና ሞላዋ በጩኽት ያስገምግሙ፤ በረሀ በእርሷም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ። በምድር ሊፈርድ ይመጣልና፥ የዱር ዛፎች በዚያን ጊዜ በጌታ ፊት ደስ ይላቸዋል። መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ። እንዲህም በሉ፦ “የመዳናችን አምላክ ሆይ! አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እንድናመሰግን፥ በምስጋናህም እንድንከብር፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበኸን ታደገን። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ።” ሕዝቡም ሁሉ “አሜን” አሉ፤ ጌታንም አመሰገኑ። እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት በየቀኑ እንደሚገባቸው በታቦቱ ፊት ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና ወንድሞቹን፥ ዖቤድ-ኤዶምንም፥ ስልሳ ስምንቱንም ወንድሞቻቸውን በዚያ በጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው። የኤዶታምም ልጅ ዖቤድ-ኤዶምና ሖሳ የደጁ ጠባቂዎች እንዲሆኑ አድርጎ ከስልሳ ስምንት ወድሞቹ ጋር ዖቤድ-ኤዶምን በዚያ ተወው። ካህኑን ሳዶቅንና ካህናቱን ወንድሞቹን በገባዖን በኮረብታው መስገጃ ባለው በጌታ ማደሪያ ፊት እንዲያገለግሉ በዚያ ተዋቸው፤ በዚያም ለእስራኤልም ባዘዘው በጌታ ሕግ እንደ ተጻፈ ሁሉ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁልጊዜ ጥዋትና ማታ ለጌታ ያቀርባሉ። ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን እንዲያመሰግኑ ኤማንንና ኤዶታምን፥ በስማቸውም የተጻፉትን ተመርጠው የቀሩትን ከእነርሱ ጋር በዚያ ተዋቸው። ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ከፍ አድርገው ለማሰማት መለከትና ጸናጽል ለእግዚአብሔርም መዝሙራት የዜማ ዕቃ ይዘው ነበር፤ የኤዶታምም ልጆች ጠባቂዎች ነበሩ። ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊትም ቤተሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ። እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ ዳዊት ነቢዩን ናታንን፦ “እነሆ፥ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የጌታም ቃል ኪዳን ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦአል” አለው። ናታንም ዳዊትን፦ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያም ሌሊት የጌታ ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦ “ሂድ፥ ለባርያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከድንኳን ወደ ድንኳን፥ ከማደሪያም ወደ ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርሁምና። ከእስራኤል ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ “ቤትን ከዝግባ እንጨት ለምን አልሠራችሁልኝም?” ብዬ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኳቸው ለማናቸውም ለእስራኤል ፈራጆች በውኑ ተናግሬአለሁን?’ አሁንም ባርያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ እንድትሆን አንተን ከማሰማርያው፥ ከበግ እረኝነት ወሰድሁህ። በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆች ስም የአንተን ስም ታላቅ አደርጋለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራን እሰጠዋለሁ፥ በዚያም እተክለዋለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ ከእንግዲህም ወዲያ እንደ ቀድሞው ዘመን ዓመፀኞች አያስጨንቁትም፤ ይህም የሆነው በእስራኤል ላይ ፈራጆች ባሥነሣሁ ጊዜ ነበር፤ ጠላቶችህንም ሁሉ በሥርህ እንዲገዙ አደርለሁ። ጌታ ደግሞ ቤት እንደሚሠራልህ እነግርሃለሁ። ወደ አባቶችህም ለመሄድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከልጆችህ የሚሆነውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። እርሱ ቤት ይሠራልኛል፤ ዙፋኑንም ለዘለዓለም አጸናለሁ። እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድሁ ከእርሱ ላይ ከቶውንም አልወስድም። በቤቴና በመንግሥቴም ለዘለዓለም አቆመዋለሁ፥ ዙፋኑም ለዘለዓለም ይጸናል።’ ” ይህንን ቃል ሁሉ ይህንንም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው። ንጉሡም ዳዊት ገባ፥ በጌታም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ “አቤቱ አምላክ ሆይ! እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው? አምላክ ሆይ! ይህ በፊትህ ጥቂት የሆነ ነገር ነበረ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ! ስለ ባርያህ ቤት ደግሞ ስለ ወደ ፊቱ ሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕረግ ሰው ተመለከትኸኝ። አንተ ባርያህን ታውቀዋለህና ለባርያህ ስለተደረገው ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምን ነገር አለው? አቤቱ፥ ስለ ባርያህ ስትል እንደ ልብህ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ በማስታወቅ ይህን ተአምራት ሁሉ አድርገሃል። አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። አንተ እግዚአብሔር ከግብጽ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ በታላቅና በሚያስፈራ ነገር ስምህን እንዳስጠራህ፥ ለአንተም ሕዝብ እንዲሆን ለመቤዠት እንደ ሄድህለት እንደ አንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን? ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነኸዋል። አሁንም፥ አቤቱ፥ ስለ ባርያህና ስለ ቤቱ የተናገርኸው ቃል ለዘለዓለም የጸና ይሁን፤ እንደ ተናገርህም አድርግ። ስምህ፦ ‘የሠራዊት ጌታ እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፥ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው’ በሚለው ውስጥ ለዘለዓለም ጽኑና ታላቅ ይሆናል፤ የባርያህም የዳዊት ቤት በፊትህ ጸንቶአል። አምላኬ ሆይ! ቤት እንደምትሠራለት ለባርያህ ገልጠህለታልና ስለዚህ ባርያህ ወደ አንተ ለመጸለይ በልቡ ደፈረ። አሁንም፥ አቤቱ፥ አንተ አምላክ ነህ፥ ይህንም መልካም ነገር ለባርያህ ተናግረሃል። ስለዚህ አሁን በፊትህ ለዘለዓለም እንዲኖር የባርያህን ቤት ለመባረክ ፈቅደሃል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አንተ የባረከው ለዘለዓለም ይባረካል።” ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አስገበራቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ መታ። ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊትም ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቆረጠ። ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ የጦር ሠራዊት አሰፈረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል አድራጊ አደረገው። ዳዊትም የአድርአዛር ባርያዎች ይሸከሟቸው የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኩሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ። የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሠራዊት ሁሉ ድል እንዳደረገ ሰማ። ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ድል ስለ አደረገው ደኅንነቱን እንዲጠይቀውና እንዲመርቀው ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለጌታ ቀደሰ። ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ ዐሥራ ስምንት ሽህ ሰዎች ገደለ። በኤዶምያስም የጦር ሠራዊት አሰፈረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል አድራጊ አደረገው። ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊቱ አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ። የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሊክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ። የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ። ከዚህም በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ዳዊትም፦ “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባርያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። የአሞን ልጆች ሹማምንት ግን ሐኖንን እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባርያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?” ሐኖንም የዳዊትን ባርያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው፤ እነርሱም ወደመጡበት ተመለሱ። ዳዊትም በሰዎቹ ላይ የተደረገውን በነገረሩት ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ስላፈሩ እንዲቀበሏቸው መልእክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፦ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አለ። የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራም-መዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመቅጠር አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ። ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሠራዊት ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ውግያ መጡ። ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ለውግያ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ነበሩ። ኢዮአብም ውግያው በፊትና በኋላ እንደሚደረግ ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው። የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ እነርሱም በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ ጌታም ደስ ያሰኘውን ያድርግ።” ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለውግያ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ። ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ ለውግያ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ። ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። የአድርአዛርም ባርያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ለመርዳት እንቢ አሉ። እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ጦርነት በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፥ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር። ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፥ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቁ ነበረበት፥ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ተደረገ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ። ፍልስጥኤማውያንም ተሸነፉ። ዳግመኛም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ተደርጎ ነበር፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ እጀታ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ። ደግሞ በጌት ላይ ጦርነት ተደርጎ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ባጠቃላይ ሀያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባርያዎቹም እጅ ወደቁ። ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም እንዲቈጥር ዳዊትን አነሣሣው። ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች፦ “ሂዱ፥ ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቁጠሩ፥ ድምራቸውንም እንዳውቅ ተመልሳችሁ አስታውቁኝ” አላቸው። ኢዮአብም አለ፦ “ጌታ ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሁሉ የጌታዬ ባርያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለምን ያመጣል?” ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ። የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፥ እስራኤልንም ቀሠፈ። ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ይህን ባለማወቅ አድርጌአለሁና የባርያህን ኃጢአት እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለው። ጌታም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ፦ “ሂድ፥ ለዳዊት፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ በአንተ ላይ እንዳደርግብህ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ’ ብለህ ንገረው” ብሎ ተናገረው። ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የምትወድደውን ምረጥ፤ የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህም ፊት እንድትሰደድ፥ ወይም ሦስት ቀን የጌታ ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ እንዲሆን፥ የጌታም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ጥፋትን እንዲያመጣ ምረጥ፤’ ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አሁን ወስን።” ዳዊትም ጋድን፦ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በጌታ እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው። ጌታም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች አለቁ። እግዚአብሔርም ለማጥፋት ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ላከ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ ጌታ አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተፀፀተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ፦ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የጌታም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የጌታ መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። ዳዊትም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እንዲቈጠር ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ! እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፥ ነገር ግን መቅሰፍት በሕዝብህ ላይ አይሁን።” የጌታም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለጌታ መሠዊያ እንዲሠራ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። ዳዊትም በጌታ ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ቃል ወጣ። ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆች ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ቀና ብሎ ተመለከተ ዳዊትንም አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ። ዳዊትም ኦርናን፦ “በላዩ ለጌታ መሠዊያ እንድሠራ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ ሙሉ ዋጋ ልክፈልና ስጠኝ፤ መቅሰፍቱም ከሕዝቡ ይከለከላል” አለው። ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ለአንተ ውሰደው፥ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለማገዶም የአውድማውን መውቅያ፥ ለእህልም ቁርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ።” ንጉሡም ዳዊት ኦርናን፦ “አይደለም፥ ነገር ግን የአንተ የሆነውን ለጌታ አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ” አለው። ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። ዳዊትም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቀረበ፥ ጌታንም ጠራ፤ ጌታም ከሰማይ የሚቃጠለው መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት። ጌታም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው። በዚያን ጊዜ ጌታ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ። ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የጌታ ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። ዳዊት ግን የጌታን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ መሄድ አልቻለም። ዳዊትም፦ “ይህ የጌታ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል የሚቃጠለው መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ ነው” አለ። ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች እንዲሰበስቡ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች እንዲወቅሩ ጠራቢዎችን አኖረ። ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር የሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለጌታም የሚሠራው ቤት በአገሩ ሁሉ በስሙና በክብሩ እጅግ ታላቅና ዝነኛ ሊሆን ይገባል፤ እኔም ስለዚህ ዝግጅትን አደርጋለሁ።” ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ የግንባታ ቁሳቁስ አዘጋጀ። ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ስም ቤት እንዲሠራ አዘዘው። ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ሆይ! እኔ ለአምላኬ ለጌታ ቤት እንድሠራ በልቤ አስቤ ነበር። ነገር ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ ‘እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ውግያ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። እነሆ፥ ልጅ ይወለድልሃል፤ እርሱም ሰላም ያለው ሰው ይሆናል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ።’ አሁንም፥ ልጄ ሆይ! ጌታ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የጌታን ቤት ሥራ። ብቻ የአምላክህን የጌታን ሕግ እንድትጠብቅ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሰልጥንህ። ጌታ ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ለመፈጸም ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ። አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለጌታ ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ በሚዛንም የማይመዘን ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም በዚያ ላይ ጨምርበት። በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይ ወቃሪዎችና እንጨት ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉህ። የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ ጌታም ከአንተ ጋር ይሁን።” ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን እንዲያግዙት የእስራኤልን ሹማምንት ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “አምላካችሁ ጌታ ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በጌታና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። አሁንም አምላካችሁን ጌታን ለመሻት ልባችሁንና ነፍሳችሁን ለእርሱ አሳልፋችሁ ስጡ፤ ለጌታም ስም ወደሚሠራው ቤት የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ለማምጣት ተነሥታችሁ የጌታን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።” ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። የእስራኤልንም ሹማምንት ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። ሌዋውያንም ዕድሜአቸው ሠላሳ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ተቈጠሩ፤ በእያንዳንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ተቈጠሩ፤ ድምራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ የጌታን ቤት ሥራ የሚሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ። ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ። አራቱ ሺህም የደጁ ጠባቂዎች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሰሩት በዜማ ዕቃዎች ጌታን ያመሰግኑ ነበር። ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው። ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ። የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ። የቀነዓት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ እንዲሆን ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘለዓለም በጌታ ፊት እንዲያጥኑና እንዲያገለግሉ፥ በስሙም ለዘለዓለም እንዲባርኩ ተለይተው ነበር። የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማሪያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ። የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ። የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ። የጌታን ቤት አገልግሎት በሠሩ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘለዓለም ይቀመጣል። ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም።” በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። “ሥራቸውም የጌታን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ በሚሰጡተት አገልግሎት አሮንን ልጆች መርዳት፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት መሥራት ነበረ። ደግሞም የተቀደሰ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቁርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በመለክያ ሁሉ ያገልግሉ ነበር። እንዲሁም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው ጌታን በማመስገንና በማክበር፥ በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በጌታ ፊት ዘወትር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ፥ ለጌታም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት በመጠበቅ ያገለግሉ ነበረ።” የአሮንም ልጆች አመዳደብ ይህ ነው። የአሮን ልጆች ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ነበሩ። ናዳብና አብዩድ ግን ልጆች ሳይወልዱ ከአባታቸው በፊት ሞቱ፤ አልዓዛርና ኢታምርም ካህናት ሆኑ። ዳዊትም ከአልዓዛር ልጆች ከሳዶቅ ጋር፥ ከኢታምርም ልጆች ከአቢሜሌክ ጋር ሆኖ እንደ አገልግሎታቸው ሥርዓርት ከፍሎ መደባቸው። የአልዓዛርም ልጆች አለቆች ከኢታምር ልጆች አለቆች በልጠው ተገኙ፤ እንዲህም ተመደቡ፤ ከአልዓዛር ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች ዐሥራ ስድስት፥ ከኢታምርም ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች ስምንት አለቆች ነበሩ። ከአልዓዛርና ከኢታምርም ልጆች መካከል የመቅደሱና በእግዚአብሔር የተሾሙ አለቆች ነበሩና እነዚህና እነዚያ እንዲህ በዕጣ ተመደቡ። ከሌዊያውያንም ወገን የነበረው የናትናኤል ልጅ ጸሐፊው ሸማያ በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት፥ በካህኑ በሳዶቅና በአብያታርም ልጅ በአቤሜሌክ ፊት፥ በካህናቱና በሌዋውያኑ አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት ጻፋቸው፤ አንዱንም የአባት ቤት ለአልዓዛር፥ አንዱንም ለኢታምር ተመረጠ። መጀመሪያውም ዕጣ ለዮአሪብ ወጣ፥ ሁለተኛው ለዮዳኤ፥ ሦስተኛው ለካሪም፥ አራተኛው ለሥዖሪም፥ አምስተኛው ለመልክያ፥ ስድስተኛው ለሚያሚን፥ ሰባተኛው ለአቆስ፥ ስምንተኛው ለአብያ፥ ዘጠኝኛው ለኢያሱ፥ አሥረኛው ለሴኬንያ፥ ዐሥራ አንደኛው ለኤልያሴብ፥ ዐሥራ ሁለተኛው ለያቂን፥ ዐሥራ ሦስተኛው ለኦፓ፥ ዐሥራ አራተኛው ለየሼብአብ፥ ዐሥራ አምስተኛው ለቢልጋ፥ ዐሥራ ስድስተኛው ለኢሜር፥ ዐሥራ ሰባተኛው ለኤዚር፥ ዐሥራ ስምንተኛው ለሃፊጼጽ፥ ዐሥራ ዘጠኝኛው ለፈታያ፥ ሀያኛው ለኤዜቄል፥ ሀያ አንደኛው ለያኪን፥ ሀያ ሁለተኛው ለጋሙል፥ ሀያ ሦስተኛው ለድላያ፥ ሀያ አራተኛው ለመዓዝያ ዕጣ ወጣ። የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዳዘዘ፥ አባታቸው አሮን እንደሰጣቸው ሥርዓት ወደ ጌታ ቤት የሚገቡበት የአገልግሎታቸው ሥርዓት ይህ ነበረ። ከቀሩትም የሌዊ ልጆች፤ ከእንበረም ልጆች ሱባኤል፤ ከሱባኤል ልጆች ዬሕድያ፤ ከዓረብያ፤ የዓረብያ ልጆች አለቃው ይሺያ፤ ከይስዓራውያን ሰሎሚት፤ ከሰሎሚት ልጆች ያሐት ነበረ፤ ከኬብሮንም ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛ ይቀምዓም ነበሩ፤ የዑዝኤል ልጅ ሚካ፤ ከሚካ ልጆች ሻሚር ነበረ፤ የሚካ ወንድም ይሺያ፤ ከይሺያ ልጆች ዘካሪያስ ነበረ፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ፤ ከያዝያ ልጆች በኖ ነበረ፤ የሜራሪ ልጆች፤ ከያዝያ በኖ፥ ሾሃም፥ ዘኩር፥ ዔብሪ ነበሩ፤ ከሞሖሊ አልዓዛር፥ እርሱም ልጆች አልነበሩትም፤ ከቂስ፤ የቂስ ልጅ ይረሕምኤል ነበረ፤ የሙሲም ልጆች፤ ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ነበሩ። እነዚህም እንደ አባቶቻቸው ቤቶች የሌዋውያን ልጆች ነበሩ። እነዚህም ደግሞ በንጉሡ በዳዊትና በሳዶቅ በአቤሜሌክም በሌዋውያንና በካህናት አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት፥ ታላቁም እንደ ታናሹ፥ እንደ ወንድሞቻቸው እንደ አሮን ልጆች ዕጣ ተጣጣሉ። ዳዊትና የሠራዊቱ አለቆችም ከአሳፍና ከኤማን ከኤዶታም ልጆች በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም ትንቢት የሚናገሩትን ሰዎች ለማገልገል ለዩ፤ በአገልግሎታቸውም ሥራ ይሠሩ የነበሩት ሰዎች ቍጥር ይህ ነበረ። ከአሳፍ ልጆች፤ ዘኩር፥ ዮሴፍ፥ ነታንያ፥ አሸርኤላ ነበሩ፤ እነዚህ የአሳፍ ልጆች በንጉሡ ትእዛዝ ትንቢት ከተናገረው ከአሳፍ ትእዛዝ በታች ነበሩ። ከኤዶታም የኤዶታም ልጆች፤ ጎዶልያስ፥ ጽሪ፥ የሻያ፥ ሰሜኢ፥ ሐሸብያ፥ መቲትያ፥ እነዚህ ስድስቱ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር በመሰንቆ ትንቢት ከተናገረው ከአባታቸው ከኤዶታም ትእዛዝ በታች ነበሩ። ከኤማን የኤማን ልጆች፤ ቡቅያ፥ መታንያ፥ ዑዝኤል፥ ሱባኤል፥ ኢያሪሙት፥ ሐናንያ፥ ሐናኒ፥ ኤልያታ፥ ጊዶልቲ፥ ሮማንቲ-ዔዘር፥ ዩሽብቃሻ፥ መሎቲ፥ ሆቲር፥ መሐዝዮት ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ቀንደ መለከቱን ከፍ እንዲያደርጉ በእግዚአብሔር ቃል የንጉሡ ባለ ራእይ የሆነው የኤማን ልጆች ነበሩ። እግዚአብሔርም ለኤማን ዐሥራ አራት ወንዶች ልጆችንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ሰጠው። እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት በጸናጽልና በበገና በመሰንቆም እንዲዘምሩ፥ በእግዚአብሔርም ቤት እንዲያገለግሉ ከአባታቸው ትእዛዝ በታች ነበሩ፤ አሳፍም ኤዶታምም ኤማንም ከንጉሡ ትእዛዝ በታች ነበሩ። ጌታን ለማወደስ ዜማ የተማሩት ከወንድሞቻቸው ጋር በቊጥር ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ነበሩ። ሁሉም ብልሃተኞች ነበሩ። ታናሹ እንደ ታላቁ፥ አስተማሪው እንደ ተማሪው፥ ሁሉም በተመሳሳይ መልኩ፥ ለሰሞናቸው ዕጣ ተጣጣሉ። የፊተኛው ዕጣ ከአሳፍ ወገን ለነበረው ለዮሴፍ ወጣ፤ ሁለተኛው ለጎልዶያስ ወጣ፤ እርሱ ወንድሞቹም ልጆቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሦስተኛው ለዘኩር ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ አራተኛው ለይጽሪ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ አምስተኛው ለነታኒያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ስድስተኛው ለቡቅያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሰባተኛው ለይሽርኤል ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ስምንተኛው ለየሻያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዘጠኝኛው ለመታንያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለቱ ነበሩ፤ አሥረኛው ለሰሜኢ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ አንደኛው ለዓዛርኤል ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ሁለተኛው ለሐሽብያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ሦስተኛው ለሱባኤል ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ አራተኛው ለመቲትያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ አምስተኛው ለኢያሪሙት ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ስድስተኛው ለሐናንያ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ሰባተኛው ለዮሽብቃሻ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ስምንተኛው ለሐናኒ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ዐሥራ ዘጠኝኛው ለመሎቲ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሀያኛው ለኤልያታ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሀያ አንደኛው ለሆቲር ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሀያ ሁለተኛው ለጊዶልቲ ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሀያ ሦስተኛው ለመሐዝዮት ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ሀያ አራተኛው ለሮማንቲዔዘር ወጣ፤ ልጆቹም ወንድሞቹም ዐሥራ ሁለት ነበሩ። የደጁም ጠባቂዎች ምድባቸው እንደዚህ ነበር፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም። ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥ አራተኛው የትኒኤል፥ አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ ነበሩ። ዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥ ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ ነበሩ፤ እንዲህም የሆነለት እግዚአብሔር ስለ ባረከው ነበር። ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ። የሸማያ ልጆች፤ ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ኤልዛባድ ነበሩ፤ ኤልዛባድም ኃያላን ወንድሞች የነበሩት እነርሱም ኤሊሁና ሰማክያ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ስልሳ ሁለት ነበሩ። ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ ዐሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት። ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኩር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤ ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበሩ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ ዐሥራ ሦስት ነበሩ። እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በጌታ ቤት እንዲያገለግሉ በየአለቆቻቸው የደጁ ጠባቂዎች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ። በበሩም ሁሉ ለማገልገል በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ በተመሳሳይ መልኩ ይዕጣ ተጣጣሉ። ለሰሌምያም በምሥራቅም በኩል ዕጣ ወጣለት። ለልጁም ብልህ አማካሪ ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ የእርሱም ዕጣ በሰሜን በኩል ወጣ። ለዖቤድ-ኤዶም ዕጣው በደቡብ በኩል ወጣ፥ ለልጆቹም የዕቃ ግምጃ ቤቱን እንዲጠብቁ ዕጣ ወጣላቸው። ለሰፊንና ለሖሳ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በምዕራብ በኩል ዕጣ ወጣላቸው፤ ይህም ጥበቃ ከጥበቃ ትይዩ ነበር። በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ። በምዕራብ በኩል በምሶሶው አጠገብ ባለው መንገድ አራት፥ በምሶሶም አጠገብ ሁለት ነበሩ። ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የደጁ ጠባቂዎች ሰሞን ይህ ነበረ። ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅዱሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። የለአዳን ልጆች፤ የለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊው ከለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ ነበር፤ የይሒኤሊ ልጆች፤ በጌታ ቤት በቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው የነበሩት ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዮኤል ነበሩ። ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤ የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሹሞ ነበር። ወንድሞቹም፤ ለአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት ነበሩ። ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አዛዦች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር። በጦርነትም ከተገኘው ምርኮ የጌታን ቤት ለመሥራት ስጦታ ቀድሰው ሰጡ። ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ ሥልጣን በታች ነበረ። ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች እንዲሆኑ በውጭው በሚከናወነው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለጌታ ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይሪያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤ ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኩሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው። የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ምደባ ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉት ሹማምንት እንደ ቁጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሀያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ውስጥ ባሉት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። ለመጀመሪያው ወር የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም በአንደኛው ክፍል ላይ ተሹሞ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያ ወር በሠራዊቱ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር። በሁለተኛውም ወር ባለው ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የሠራዊቱ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእነርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኃያል ሆኖ ሠላሳውን ያዝ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ተሹሞ ነበር። ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባለላት ነበሩ። ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለዘጠነኛው ወር የዘጠነኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶናዊው አቢዔዘር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለአሥረኛው ወር አሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለዐሥራ አንደኛው ወር ዐሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። ለዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስማዖናውያን ላይ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ አለቃ ነበረ፤ በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸብያ አለቃ ነበረ፤ በአሮን ላይ ሳዶቅ አለቃ ነበረ፤ በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኢሊሁ አለቃ ነበር፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ አለቃ ነበረ፤ በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ አለቃ ነበረ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት አለቃ ነበረ፤ በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ አለቃ ነበረ፤ በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል አለቃ ነበረ፤ በገለዓድ ባለው በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ አለቃ ነበረ፤ በብንያም ላይ የአብኔር ልጅ የዕሢኤል አለቃ ነበረ፤ በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል አለቃ ነበረ፤ እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። ጌታ ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ለማብዛት ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሀያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቁጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቁጣ ወረደ፥ ቁጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም። በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዛሞት ሹም ነበረ፤ በአገሩም በከተሞቹም በመንደሮቹም በግንቦቹም ባሉ ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ መሬቱን በሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚቀርበው በወይኑ ምርት ላይ ሸፋማዊው ዘቢድ ሹም ነበረ። በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ ሹም ነበረ፤ በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ዬሕድያ ሹም ነበረ፤ በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ። አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል የንጉሡን ልጆች ያገለግል ነበረ፤ አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤ ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ። ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉ፥ የነገዶቹንም አለቆች፥ ንጉሡንም በክፍል የሚያገለግሉትን የሠራዊቱ አለቆች፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆቹንም፥ በንጉሥና በልጆቹ ሀብትና ግዛት ላይ የተሾሙትን፥ ጃንደረቦችንም፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። ንጉሡም ዳዊት ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ! ስሙኝ፤ ለጌታ ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን የማረፍያ ቤት ለመሥራት እኔ በልቤ አስቤያለሁ፤ ለግንባታም የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤ እግዚአብሔር ግን፦ ‘የጦር አርበኛ ነህና፥ ደምም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም’ ብሎኛል። ነገር ግን የእስራኤል አምላክ ጌታ በእስራኤል ላይ የዘለዓለም ንጉሥ እንድሆን ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳንም አለቃ እንዲሆን መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ሊያነግሠኝና ሊመርጠኝ ወደደ። ጌታም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በጌታ መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ልጅ እንዲሆንልኝ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል። ትእዛዜንና ፍርዴንም በማድረግ እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘለዓለም አጸናዋለሁ።’ አሁንም የጌታ ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱ፥ ለልጆቻችሁም ለዘለዓለም እንድታወርስዋት የአምላካችሁን የጌታን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፥ ፈልጉም። “አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ! እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘለዓለም ይጥልሃል። አሁንም፥ እነሆ፥ ጌታ ለመቅደስ የሚሆን ቤትን እንድትሠራ መርጦሃልና በርትተህ በቈራጥነት ፈጽመው።” ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ንድፈ ሐሳቡን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። ደግሞም ለጌታ ቤት አደባባዮችና በዙሪያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት በመንፈሱ ያሰበውን ንድፈ ሐሳብ ሁሉ ሰጠው። የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን በጌታም ቤት ለሚያገልግሉበት ሥራ ሁሉ አስታወቀው። በጌታም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤ ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎቹም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩም መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለተቀደሰው ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች ሰጠው፤ ለሜንጦቹና ለድስቶቹ ለመቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን፥ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለዕጣኑም መሠዊያ ንጹሑን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሠረገላ ንድፈ ሐሳብ ሰጠው። ዳዊትም፦ “የሥራውን ሁሉ ንድፈ ሐሳብ እንዳውቅ ይህ ሁሉ በጌታ እጅ ተጽፎ መጣልኝ” አለ። ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ “ጠንክር፥ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፥ አትደንግጥም፥ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፥ አይጥልህምም። እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥራ በብልሃትና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል።” ንጉሡም ዳዊት ለጉባኤው ሁሉ እንዲህ አለ፦ “በብቸኛነት እግዚአብሔር የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ብላቴና ለጋ ነው፤ ሕንጻው ግን ለጌታ ለአምላክ ነው እንጂ ለሰው አይደለምና ሥራው ታላቅ ነው። እኔም እንደ ጉልበቴ ሁሉ ለአምላኬ ቤት ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን፥ ለናሱም ዕቃ ናሱን፥ ለብረቱም ዕቃ ብረቱን፥ ለእንጨቱም ዕቃ እንጨቱን፥ ደግሞ መረግድንና በፈርጥ የሚገባ ድንጋይን፥ የሚለጠፍ ድንጋይን፥ ልዩ ልዩ መልክ ያለውንም ድንጋይ፥ የከበረውንም ድንጋይ ከየዓይነቱ፥ ብዙም እብነ በረድ አዘጋጅቻለሁ። ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። የቤቶቹ ግንብ እንዲለብጡበት ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥ በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለጌታ የሚቀድስ ማን ነው?” የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ። ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና ዐሥር ሺህ ዳሪክ፥ ዐሥር ሺህም መክሊት ብር፥ ዐሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። ዕንቁም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ። ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለጌታ በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ፍጹም ደስ ተሰኘ። ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት ጌታን ባረከ፤ ዳዊትም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ! ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ተባረክ። አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን መስጠት በእጅህ ነው። አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ! እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል በፈቃደኝነት ልናቀርብልህ የምንችል እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? አባቶቻችንም ሁሉ እንደ ነበሩ እኛ በፊትህ እንግዶችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፥ አይጸናም። አቤቱ አምላካችን ሆይ! ለቅዱስ ስምህ ቤት እንድንሠራ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፥ ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ! ልብን እንደምትመረምር፥ ቅንነትንም እንደምትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱና ደስ ተሰኝቶ እንዳቀረበልህ አይቻለሁ። አቤቱ፥ የአባቶቻችን የአብርሃም፥ የይሰሐቅና የእስራኤል አምላክ ሆይ! ይህን አሳብ በሕዝብህ ልብ ለዘለዓለም ጠብቅ፥ ልባቸውንም ወደ አንተ አቅና። ትእዛዝህንም ምስክርህንም ሥርዓትህንም እንዲጠብቅ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ እንዲያደርግ ያዘጋጀሁለትንም ቤት እንዲሠራ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው።” ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ፦ “አምላካችሁን ጌታን ባርኩ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ባረኩ፥ ራሳቸውንም አዘንብለው ለጌታና ለንጉሡ ሰገዱ። በማግስቱም ለጌታ መሥዋዕት ሰዉ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ለጌታ አቀረቡ፤ አንድ ሺህ ወይፈን፥ አንድ ሺህም አውራ በጎች፥ አንድ ሺህም የበግ ጠቦቶች፥ የመጠጥ ቁርባናቸውንም፥ ስለ እስራኤልም ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ። በዚያም ቀን በታላቅ ደስታ በጌታ ፊት በሉ ጠጡም። የዳዊትንም ልጅ ሰሎሞንን ሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ እርሱንም ልዑል እንዲሆን ለጌታ ቀቡት፥ ሳዶቅንም ካህን እንዲሆን ቀቡት። ሰሎሞንም ለጌታ በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፥ ተከናወነለትም፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት። ሹማምንቶቹም ሁሉ፥ ኃያላኑም፥ ደግሞም የንጉሡ የዳዊት ልጆች ሁሉ ለንጉሡ ለሰሎሞን ታማኞች እንደ ሆኑ ቃል ገቡለት። ጌታም ሰሎሞንን በእስራኤል ሁሉ ፊት እጅግ አገነነው፤ ከእርሱ በፊትም ለነበሩት ለእስራኤል ነገሥታት ያልሆነውን የመንግሥት ክብር ሰጠው። የእሴይም ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ። በእስራኤልም ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ፤ ሰባት ዓመት በኬብሮን ነገሠ፥ ሠላሳ ሦስትም ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ። ዕድሜም፥ ባለጠግነትም፥ ክብርም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ልጁም ሰሎሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል። እንደዚሁም የመንግሥቱ ነገርና ኃይሉ ሁሉ በእርሱም በእስራኤልም በአገሮችም መንግሥታት ሁሉ ላይ ያለፉት የታሪክ ክሰስተቶች ተጽፈዋል። የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በመንግሥቱ ላይ ራሱን አጸና፤ ጌታ አምላኩም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው። ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ። ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የጌታ ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው ወደ ኮረብታማው ስፍራ ሄዱ። ለጌታ ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያት-ይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ ታቦቱን አምጥቶት ነበር። የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በጌታ ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። ሰሎሞንም በጌታ ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። በዚያም ሌሊት ጌታ፦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ነገር ጠይቀኝ” ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ። ሰሎሞንም ጌታን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅና ጽኑ ፍቅር አሳይተኸዋል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ቁጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃልህ ይጽና። አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት ለመውጣትና ለመግባት እንድችል ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ሊፈርድ የሚችል ማን ነው?” ጌታም መልሶ ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ “ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጸግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልጠየቅህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ እንድትችል ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ጠይቀሃልና፥ ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድም እንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር አድርጌ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ።” ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው ስፍራ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። አንዱም ሠረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ ኀምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ያስመጡ ነበር፤ እነርሱም መልሰው ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ ይልኩ ነበር። ሰሎሞንም ለጌታ ስም ቤተ መቅደስ፥ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥትን ለመሥራት አሰበ። ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፦ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ለመሥራት የዝግባ እንጨት እንደ ላክኽለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በጌታ ፊት መዓዛው ያማረውን ሽቶ ዕጣን ለማጠን፥ የተቀደሰውንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በጌታ በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለጌታ ስም ቤት ልሠራለትና ልቀድስለት አሰብሁ። አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ የሆነ ነው። ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ እርሱን ለመያዝ አይችልምና ለእርሱ ቤት መሥራት ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት ልሠራለት የምችል እኔ ማን ነኝ? አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር አብሮ የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። ደግሞም ባርያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቁረጥ እንደሚያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ላክልኝ፤ እነሆ፥ ባርያዎቼ ከባርያዎችህ ጋር በመሆን ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኛል፥ ስለ ሆነም የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናል። እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባርያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።” የጢሮስ ንጉሥም ኪራም ለሰሎሞን በላከው ደብዳቤ እንዲህ ብሎ መለስ ሰጠ፦ “ጌታ ሕዝቡን ወድዶአልና በእነርሱ ላይ አነገሠህ።” እንዲሁም ኪራም እንዲህ አለ፦ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለጌታም ቤተ መቅደስ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥት እንዲሠራ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ ጌታ ቡሩክ ይሁን። “አሁንም ኪራም-አቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ልኬልሃለሁ። እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ለመሥራት፥ ቅርጽም ለመሥራት ንድፍም ለመንደፍ ሌላም ነገር ሁሉ ለማድረግ እውቀት አለው፥ እርሱም ከብልሃተኛዎችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር አብሮ ይሁን። አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባርያዎቹ ይላክ፤ እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እናመጣለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።” ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ የሕዝቡንም ሥራ ለሚቆጣጠር የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን ሾመ። ሰሎሞንም ጌታ ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የጌታን ቤት መሥራት ጀመረ። በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር በሁለተኛውም ቀን መሥራት ጀመረ። ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው መለክያ መሠረት ስልሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ። በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት። ቤቱንም በዕንቁ አስጌጠው፤ ወርቁም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ። ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ። ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው። የምስማሮቹም ሚዛን ኀምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ። በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱን ኪሩቤል ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበረ። የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር። ሰሎሞንም ከሰማያዊው ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት። በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጉልላት አምስት ክንድ ነበረ። እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በዓምዶቹ ራስ ላይ አኖራቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው። ዓምዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፥ በቀኝም የነበረውን ስም ያኪን በግራም የነበረውን ስም ቦዔዝ ብሎ ጠራቸው። ንጉሥ ሰሎሞንም ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ዐሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። ከቀለጠም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ ዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኩሬ ሠራ። በበታቹም ለአንድ ክንድ ዐሥር፥ ለአንድም ክንድ ዐሥር፥ እንደ በሬዎች ያሉ ቅርጾች በኩረው ላይ አዞረበት፤ ኩሬውንም በቀለጠ ጊዜ የበሬዎቹም ቅርጾች በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። በዓሥራ ሁለትም በሬዎችም ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን ሦስቱም ወደ ምዕራብ ሦስቱም ወደ ደቡብ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኩሬውም በእነርሱ ላይ ተቀምጦ ነበረ፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር። እንዲሁም ንጉሡ ዐሥር የመታጠቢያ ሳሕኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበውን ነገር ሁሉ እንዲያጥቡበት አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኩሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር። አሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ አምስቱን በግራ በመቅደስ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ። እንዲሁም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፥ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። ኩሬውንም በቤቱ ቀኝ በደቡብ ምሥራቅ በኩል አኖረው። ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በጌታ ቤት የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። ሁለቱን ዓምዶች፥ ጽዋዎቹንም፥ በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን ሁለት ጉልላቶች፥ በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን የጉልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ። በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች እንዲሸፍኑ፥ ለእያንዳንዱ መረበብ በሁለት በሁለት ረድፍ ያሉ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሳሕኖች ሠራ፤ እንዲሁም አንዱንም ኩሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን ዐሥራ ሁለት በሬዎች አበጀ። ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም-አቢ ለንጉሡ ለሰሎሞን ለጌታ ቤት ከተሰነገለ ናስ ሠራ። ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በሸክላው መሬት ላይ አስፈሰሰው። ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም መጠን በቍጥር አይታወቅም ነበር። ሰሎሞንም በጌታ ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ፥ የወርቁንም መሠዊያ፥ የተቀደሰውንም ኅብስት የሚቀመጥባቸውን ገበታዎች ሠራ፤ እንዲሁም በቅድስተ ቅዱሳንም ፊት እንደ ሥርዓታቸው እንዲያበሩ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከንጹሕ ወርቅ አበጀ። አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። ጉጠቶቹንም ድስቶቹንም ሙዳዮቹንም ጀሞዎቹንም ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ። እንዲሁም ሰሎሞን ለጌታ ቤት የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን የብርና የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰሎሞን አምጥቶ በጌታ ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አኖረው። በዚያን ጊዜም ሰሎሞን የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በዓሉን በሚያከብሩ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፥ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሡ። ታቦቱንም የመገናኛውንም ድንኳን በድኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በታቦቱ ፊት ሆነው ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና በቍጥር የማይለኩትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። ካህናቱም የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በመቅደሱ በውስጠኛው ክፍል በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፥ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ከውስጠኛው ክፍል ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ ሁሉም ተቀድሰው ነበር፥ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር፤ መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጽናጽልና በገና መሰንቆም ይዘው በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ መለከት የሚነፉ ካህናት ነበሩ፤ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው በአንድ ድምፅ ጌታን እያመሰገኑና እያከበሩ፦ “ጌታ መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና” ጌታን አመስግኑ እያሉ ድምጻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ ጌታን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው ቤቱን፥ የጌታን ቤት ሞላው። የጌታም ክብር የጌታን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልቻሉም። ሰሎሞንም እንዲህ አለ፦ “ጌታ፦ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሏል፤ እኔ ግን ለዘለዓለም እንድትኖርበት ታላቅ የሆነ ማደሪያ ቤትን ሠራሁልህ።” ንጉሡም ፊቱን ወደ ጉባኤ ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ ብሎ በአፉ የተናገረው በእጁም የፈፀመው የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ፤ እርሱም እንዲህ አለው፦ ‘ህዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤት በዚያ እንዲሠራልኝ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥሁም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ እንዲሆን ማንንም አልመረጥሁም፤ ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ።’ አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ቤት ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር። ጌታም አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። ነገር ግን ከአብራክህ የተገኘው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።’ ጌታም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ ጌታም ተስፋ እንደሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለጌታ ስም ቤት ሠራሁ። ከእስራኤልም ልጆች ጋር ያደረገው የጌታ ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ።” ሰሎሞንም የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ እያዩት በጌታ መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ዘረጋ፤ ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፥ በእርሱም ላይ ቆመ፥ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘርግቶ፥ እርሱ እንዲህ አለ፦ “አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባርያዎችህ ቃል ኪዳንንና ጽኑ ፍቅርን የምትጠብቅ፥ ለባርያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። እንግዲህ አሁን፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ‘አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ እንዲሄዱ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም’ ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለባርያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። ስለዚህ፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባርያህ ለዳዊት የተናገረኸው ቃል ይጽና። “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ አንተን መያዝ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን? ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባርያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ባርያህም በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። ባርያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት እንድትሰማ በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ። ባርያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። “ሰው በባልንጀራው ላይ ኃጢአት ቢሠራ፥ እርሱም መሐላ እንዲምል ቢደረግ፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ አድርግም፥ በባርያዎችህንም ፍረድ፥ በደለኛውንም እንደ በደሉ ክፈለው፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። “ሕዝብህም እስራኤል በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢጠሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። “በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢጠሩ፥ ባሠቃየሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ የባርያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ። “በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥ ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ እያንዳንዱም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው። ስለዚህ ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፍሩህ በመንገዶችህም ይሂዱ። “ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ ስለ ብርቱውም እጅህ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን እንዲያውቁ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል እንዲፈሩህ፥ ይህም የሠራሁት ቤት በስምህ እንደ ተጠራ እንዲያውቁ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። “ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው። “ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለምና በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ፥ ተቈጥተህም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር ቢማርኩአቸው፥ በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም አገር ሳሉ ተመልሰው፦ ‘ኃጢአት ሠርተናል፥ ስሕተት ፈጽመናል፥ ክፉም አድርገናል’ ብለው ቢለምኑህ፥ በተማረኩበትም በምርኮአቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው፤ በአንተም ላይ ኃጢአት የሠሩብህን ሕዝብህን ይቅር በል። “አሁንም፥ አምላኬ ሆይ! በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮችህም የሚያደምጡ እንዲሆኑ እባክህ እለምንሃለሁ። አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ተነሥተህ አንተና የኃይልህ ታቦት ወደ ማረፍያ ስፍራህ ሂዱ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ! ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው። አቤቱ አምላክ ሆይ! የቀባኸውን ሰው አታሳፍረው ለባርያም ለዳዊት ያደረግህለትን ጽኑ ፍቅር አስብ።” ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውን መሥዋዕት በላ፤ የጌታም ክብር ቤቱን ሞላ። የጌታም ክብር የጌታን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ ጌታ ቤት መግባት አልቻሉም። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የጌታም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ እንዲህም ብለው ጌታን አመሰገኑ፦ “እርሱ መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና።” ንጉሡም ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ፊት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የጌታን ቤት ቀደሱ። ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ፦ ጽኑ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት ጌታን ለማመስገን የሠራውን የጌታን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር። ሰሎሞንም በጌታ ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩን ውስጥ ቀደሰ፤ ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን ስቡንም መያዝ አልቻለምና የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት ስብ በዚያ አቀረበ። ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆኑ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያሉ እስራኤል ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። ሰባት ቀንም መሠዊያውን ቀድሰው፥ ሰባት ቀንም በዓል አድርገው ነበርና በስምንተኛው ቀን የተቀደሰውን ጉባኤ አደረጉ። በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛውም ቀን ሕዝቡን ወደ ድንኳናቸው አሰናበተ፤ ጌታ ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ደስ ብሎአቸው ሐሴትን እያደረጉ ሄዱ። ሰሎሞንም የጌታን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በጌታ ቤትና በራሱ ቤት ለመሥራት በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ። ጌታም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ራሳቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ እንዲኖር ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንደ ሄደው በፊቴ ብትሄድ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ ከአባትህ ከዳዊት ጋር፦ ‘በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ከዘርህ አይታጣም’ ብዬ ቃል ኪዳን እንዳደረግሁ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ። “እናንተ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትተዉ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላችኋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ አርቄ እጥለዋለሁ፥ በአሕዛብም ሁሉ መካከል ምሳሌና መሳለቂያ አደርገዋለሁ። ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውንም ይህን ቤት እያዩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ፦ ‘ጌታ በዚህ አገርና በዚህ ቤት ለምን እንዲህ አደረገ?’ ብለው ይደነቃሉ። መልሰውም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው።’ ” እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የጌታን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ዳግመኛ ሠራቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አሰፈረባቸው። ሰሎሞንም ወደ ሐማት-ሱባ ሄደ አሸነፋትም። በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ሠራ። ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መቀርቀሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤት-ሖሮን ታችኛውንም ቤት-ሖሮን ሠራ። ባዓላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉ ከተሞች ሁሉ፥ የሠረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ለመሥራት የፈለገውን ሁሉ ሠራ። ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከኤዊያውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባርያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ወታደሮች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ። እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሥልጣን የነበራቸው የንጉሥ ሰሎሞን ከፍተኛ ሹማምት ሁለት መቶ ኀምሳ ነበሩ። ሰሎሞንም፦ “የጌታ ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም” ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ ወደ ሠራላት ቤት አመጣት። በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በጌታ መሠዊያ ላይ ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው ዘወትር በየቀኑ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቁርባን ያቀርቡ ነበር። የጌታም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው እንዲያመሰግኑ፥ በካህናቱም ፊት እንዲያገለግሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ ጠባቂዎችንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። የጌታም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰበት ጊዜ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተሳካ ነበረ። የጌታም ቤት ተፈጸመ። ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮን-ጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ። ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባርያዎቹ እጅ ላከለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባርያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ኀምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቶና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ልትፈትነው መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ስውር ነገር አልነበረም። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት በተመለከተች ጊዜ፥ የማዕዱንም መብል፥ የሹማምንቱንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም አለባበሳቸውንም፥ በጌታም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች። ንጉሡንም እንዲህ አለችው፦ “ስለ ስኬትህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔ ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኩሌታ አልነገሩኝም፤ ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ። በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባርያዎችህ ብፁዓን ናቸው። በአምላክህ በጌታ ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ሊያስቀምጥህ የወደደህ አምላክህ ጌታ ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘለዓለም ሊያጸናቸው ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድና ጽድቅ እንድታደርግ በእነርሱ ላይ አነገሠህ።” ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቶ የከበረም ዕንቁ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቶ ከቶ አልነበረም። ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም ባርያዎችና የሰሎሞን ባርያዎች የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቁ ደግሞ አመጡ። ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለጌታ ቤትና ለንጉሡ ቤት እርከኖችን፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና ሠራ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የፈለገችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርሷም ተመልሳ ከባርያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች። በየዓመቱ ወደ ሰሎሞን የሚመጣው ወርቅ በሚዛን ሲለካ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ሲሆን፥ ነጋድራሶችና ነጋዴዎች የሚያመጡትን ወርቅ የሚጨምር አልነበረም፤ የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድሩም ሹማምንት ወርቅና ብር ወደ ሰሎሞን ያመጡ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። ከጥፍጥም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አስቀመጣቸው። ንጉሡም ደግሞ ከዘሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በንጹሕ ወርቅም አስለበጠው። ከዙፋኑም ጋር ተጋጥመው ወደ ዙፋኑም የሚያስኬዱ ስድስት እርከኖችና የወርቅ ብርኩማ ዙፋኑ ነበረው፤ በዚህና በዚያም በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎችም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በማናቸውም መንግሥታት እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የነበረው ዕቃ ሁሉ ንጹሕ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር እንደ ምንም አይቈጠርም ነበር። ለንጉሡም ከኪራም ባርያዎች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር የዝሆንም ጥርስ ዝንጀሮና ዝጉርጉር ወፍም ይዘው ይመጡ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በሀብትና በጥበብ በለጠ። የምድርም ነገሥታት ሁሉ ጌታ በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። እያንዳንዱም ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቶውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። ሰሎሞንም ለፈረሶችና ለሰረገሎች አራት ሺህ ጋጥ፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። ከኤፍራጥስም ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባውንም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። ለሰሎሞንም ፈረሶች ከግብጽና ከየአገሩ ሁሉ ያመጡለት ነበር። የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ተግባራት በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ በቃላት የተጻፈ አይደለምን? ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። እስራኤልም ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ። ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦ “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ ስለዚህ አሁን አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እናገለግልሃለን።” እርሱም፦ “ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። ንጉሡም ሮብዓም፦ “ለዚህ ሕዝብ እንድመልስለት የምትመክሩኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። እነርሱም እንዲህ ብለው ተናገሩት፦ “ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘለዓለም ባርያዎች ይሆኑልሃል።” እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልን’ ለሚሉኝ ሕዝብ እንድመልስላቸው የምትመክሩኝ ምንድነው?” ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች እንዲህ በላቸው ብለው ተናገሩት፦ “ ‘አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን’ ለሚሉህ ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ‘ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ” ንጉሡም፦ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓብ መጡ። ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ፦ “አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። ጌታም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከጌታ ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “በዳዊት ዘንድ ምን ድርሻ አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ! ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ! አሁን ቤትህን ተመልከት።” እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ላከ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ላይ ዓመፀ። ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ለመመለስ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ወታደሮች ሰበሰበ። የጌታም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” የጌታንም ቃላት ሰሙ፥ ኢዮርብዓምንም ሄደው ከመውጋት ተመለሱ። ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። እርሱም ቤተ ልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን ቆረቆረ፤ እንዲሁም ቤት-ጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥ ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥ አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥ ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ፤ እነዚህም የተመሸጉ ከተሞች በይሁዳና በብንያም የሚገኙ ነበሩ። ምሽጎቹንም አጠነከረ፥ አዛዦችንም አኖረባቸው፥ ምግቡንም ዘይቱንም የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ። ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ። በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። የጌታም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰማሪያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች ለአጋንንቱም ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን ሾመ። ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለጌታ ለመሠዋት ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፥ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ። ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች። እርሷም የዑስ፥ ሰማራያ፥ ዘሃም የሚባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ከእርሷም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት። ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስልሳ ቁባቶች ነበሩት፥ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስልሳ ሴቶች ልጆች ወለደ። ሮብዓምም ንጉሥ ሊያደርገው አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። ተጠበበም፥ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በተመሸጉትም ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ስንቅ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው። እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የጌታን ሕግ ተዉ። በጌታ ላይ አልታመኑምና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊወጋት ወጣ፥ እርሱም ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስልሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ነበር። ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። የይሁዳም የነበሩትን የተመሸጉ ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’ ” የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ፦ “ጌታ ጻድቅ ነው” ብለው ራሳቸውን አዋረዱ። ጌታም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፦ “ራሳቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቁጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይወርድም፤ ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለሌሎች ለምድሪቱ ነገሥታት መገዛትን እንዲያውቁ ለእርሱ ይገዙለታል።” የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የጌታንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ነገር ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። ንጉሡም ወደ ጌታ ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር። ራሱንም ባዋረደ ጊዜ የጌታ ቁጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ሁኔታ ተፈጠረ። ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ ጌታም ስሙን እንዲያኖርባት ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። ጌታንም ለመሻት ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ። የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ተዋጊዎች ይዞ ወደ ጦርነት ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ የጨው ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደሰጠ በውኑ አታውቁምን? የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባርያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዓመፀ። ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት። “እንግዲህ አሁን እናንተ እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁና፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸውና በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የጌታን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። የአሮንን ልጆች የጌታን ካህናትና ሌዋውያንን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ለራሳችሁ ካህናትን አልሾማችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ለመቀደስ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። ለእኛ ግን አምላካችን ጌታ ነው፥ አልተውነውም፤ የጌታም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው። በየጥዋቱና በየማታውም ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መዓዛው ያማረ ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የተቀደሰውንም ኅብስት በንጹሕ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የጌታን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል። እነሆም፥ ጌታ በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ የጦርነት ማስጠንቀቅያ ድምፅ ያሰማሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ! አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከጌታ ጋር አትዋጉ።” ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ለፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ ግን በስተ ኋላቸው ነበረ። ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጦርነቱ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ ጌታም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ ጌታ ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው። የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ ጌታም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። አብያና ሕዝቡ በታላቅ ውግያ ድል አደረጓቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በጌታ ታምነው ነበርና አሸነፉ። አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ ጌታም ቀሰፈው፥ ሞተም። አብያም ጸና፥ ዐሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ወለደ። የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል። አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። አሳም በአምላኩ በጌታ ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰባበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን እንዲሹ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲያደርጉ ይሁዳን አዘዘ። ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የዕጣን መሠዊያዎቹን አስወገደ፤ መንግሥቲቱም በእርሱ ሥር ሰላም የሰፈነባት ሆነች። ምድሪቱ ሰላም ሰፍኖባት ስለ ነበር በይሁዳ የተመሸጉትን ከተሞችን ሠራ፤ እንዲሁም ጌታ ዕረፍትን ሰጠጥቶት ስለ ነበር በዚያም ዘመን ጦርነት አልነበረበትም። ይሁዳንም እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርና ግንብ፥ መዝጊያና መቀርቀሪያ እናድርግባቸው፤ አምላካችንን ጌታን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም ድረስ የኛው ነች፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል።” እነርሱም ሠሩ ተከናወነላቸውም። ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። አሳም እንዲህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ ጌታ ጮኸ፦ “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህምና፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ።” ጌታም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን ድል ነሣ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በጌታና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። ከጌታም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ያዛቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ድል በማድረግ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ። የጌታም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ መጣ፤ አሳንም ሊያገኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤ እናንተ ከጌታ ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉትም ታገኙታላችሁ፤ ብትተውት ግን ይተዋችኋል። እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ሁከት ስለ ነበር በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረውም። ጌታ በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር። እናንተ ግን ለሥራችሁ ሽልማት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።” አሳም እነዚህን ቃላትና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በጌታም ቤት ፊት የነበረውን የጌታን መሠዊያ አደሰ። ጌታ አምላኩም ከእርሱ ጋር እንደሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። አሳም በነገሠ ዐሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለጌታ ሠዉ። በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ለመሻት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ የእስራኤልንም አምላክ ጌታን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ እንዲገደል ማሉ። ለጌታም በታላቅ ድምፅና በዕልልታ፥ እምቢልታንና ቀንደ መለከትንም እየነፉ ማሉ። በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥ በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ ጌታም በዙሪያቸው እረፍት ሰጣቸው። ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስላደረገች ከእቴጌነትዋ ሻራት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም ራሱ የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ ጌታ ቤት አገባ። አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ጦርነት አልነበረም። አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። አሳም ከጌታ ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ወደ ተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “በአባቴና በአባትህ መካከል እንደነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሁን፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ።” ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱንም የጦር አዛዦች በእስራኤል ከተሞች ላይ ላከ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና ለንፍታሌም እንደ ግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ያዙ። ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ። ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ ዓናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በጌታ አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል። ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ሠራዊት አልነበሩምን? በጌታ ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጌታ ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ለማጽናት ዐይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። እንግዲህ አሁን የሞኞችን ተግባር ፈጽመሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ጦርነት ይደረግብሃል።” አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በቊራኛ አስሮ በወህኒ ቤት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ፥ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አሠቃየ። የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ ጌታን አልፈለገም። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቶ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት። በእርሱ ፋንታ ልጁ ኢዮሣፍጥ በየይሁዳ ላይ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ኃይሉን አጠናከረ። በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ። በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና ጌታም ከኢዮሣፍጥ ጋር ነበረ፤ በኣሊምንም አልፈለገም፥ ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ እንደ እስራኤልም ያለ ሥራ አልሠራም። ስለዚህም ጌታ መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሣፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ሀብትና ክብር ሆነለት። ልቡም በጌታ መንገድ ላይ ለመመላለስ ድፍረት ነበረው፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ። በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ላከ። ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ላከ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን አብሮ ላከ። እነርሱም የጌታን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር። በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ጌታ ፍርሃት አሳረባቸው፥ ከኢዮሣፍጥም ጋር አልተዋጉም። ከፍልስጥኤማውያንም ለኢዮሣፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበሩ፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር። ኢዮሣፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሠራ። በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩት። ቁጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለጌታ የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ ከእርሱም በኋላ ዩዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለጦርነት የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር። ለኢዮሣፍጥም ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ እርሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ትስስርን አደረገ። ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ እንዲሄድ አባበለው። የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፦ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በጦርነቱም ላይ ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፦ “የጌታን ቃል አስቀድመህ እንድትጠይቅ እለምንሃለሁ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን ሰብስቦ፦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን፦ “እንድንጠይቀው የጌታ ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ጌታን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ስለ እኔ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው።” ኢዮሣፍጥም፦ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፦ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር። የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ። ነቢያትም ሁሉ፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድ፥ ለአንተም ይከናወንልሃል” እያሉ ተመሳሳይ የሆነን ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ ሚክያስን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ ድምፅ ሆነው ለንጉሡ መልካም ነገር ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ።” ሚክያስም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። እርሱም መለልሶ እንዲህ አለው፦ “ውጣ፥ ይከናወንልህ፤ በእጅህም ተላልፈው ይሰጣሉ።” ንጉሡም፦ “በጌታ ስም ከእውነት በቀር ምንም ዓይነት ነገር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ እንዲወድቅ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ያታለለው ማን ነው?’ አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም መጣ፥ በጌታም ፊት ቆሞ፦ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። ጌታም፦ ‘በምን ዓይነት መንገድ?’ አለው። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ።’ ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘ታታልለዋለህ፤ ይከናወንልሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ። እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ ጌታ በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አኑሮአል፤ ጌታም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።’” የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና እንዲህ አለ፦ “የጌታ መንፈስ ከአንተ ጋር ለመነጋገር በምን ዓይነት መንገድ ከእኔ አለፈ?” ሚክያስም፦ “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ይታይሃል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ እናንተም እንዲህ በሉ፦ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በወህኒ ቤት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት።’ ” ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “በደህና የተመለስህ እንደሆነ ጌታ በእኔ አልተናረም።” ዳግመኛም እርሱ፦ “እናንተ ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙኝ!” አለ። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፦ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ጦርነቱም ገቡ። የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበር፦ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ።” የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፦ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፥ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ ጌታም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም፦ “ተወግቻለሁና ሠረገላውን አዙር ከጦርነቱም ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ጦርነቱ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሠረገላው ላይ ራሱን አስደግፎ ተንጋለለ፤ ፀሐይም በጠለቀች ጊዜ ሞተ። የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ ጌታን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከጌታ ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል። ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድሪቱ አስወግደሃልና፥ ጌታን ለመፈለግ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል።” ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ዳግመኛም ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ ጌታ መለሳቸው። በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። ፈራጆቹንም እንዲህ አላቸው፦ “ለጌታ እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ልብ ብላችሁ ተገንዘቡ። እንግዲህ አሁን ጌታን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በጌታ ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉንም ነገር ተጠንቅቃችሁ አድርጉ።” ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በጌታ ስም ፍርድን እንዲፈርዱ በሙግትም ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እንዲህ ስታደርጉ ጌታን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻቸሁ ዘንድ ስለ ደም መፋሰስ ስለ ሕግና ስለ ትእዛዝ ስለ ሥርዓትና ስለ ፍርድም ማናቸውም ጉዳይ ወደ እናንተ ቢመጣ ጌታን እንዳይበድሉ፥ ቁጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። እነሆም፥ ለጌታ በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሹመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ ጌታም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።” እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ። ሰዎችም መጥተው እንዲህ በማለት ለኢዮሣፍጥ አወሩለት፦ “ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዐይን-ጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ይገኛሉ።” ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ ጌታንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ። ይሁዳም ጌታን ይፈልግ ዘንድ ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ጌታን ለመሻት መጡ። ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በጌታ ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ! በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም። አምላካችን ሆይ! በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘለዓለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን? እነርሱም ተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት እንዲህ አሉ፦ ‘ክፉ ነገር፥ ሰይፍ ወይም ፍርድ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮሃለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ።’ እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ እንዳይወርሯቸው ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ትተዋቸው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥ እነሆ፥ ለበጎነታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ሊያወጡን መጥተዋል። አምላካችን ሆይ! አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን ልንቋቋመው አንችልም፤ ዐይኖቻችን ወደ አንተ ከማንሣት በቀር የምናደርገውን ነገር አናውቅም።” የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በጌታ ፊት ቆመው ነበር። የጌታም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካርያስ ልጅ በየሕዝኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤ እንዲህም አለ፦ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ ጌታ እንዲህ ይላችኋል፦ ‘ውግያው የጌታ ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ አቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። እናንተ በዚህ ውግያ ላይ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ! ተሰለፉ፥ ጸንታችሁም ቁሙ፥ የሚሆነውንም የጌታን ድል አድራጊነት እዩ፤’ ጌታም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም በእነርሱ ላይ ውጡ።” ኢዮሣፍጥም በግንባሩ ወደ ምድር ሰገደ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በጌታ ፊት በምድር በግንባራቸው ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን እጅግ ታላቅ በሆነ ድምፅ ሊያመሰግኑት ቆሙ። ማልደውም በመነሣት ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በጌታ እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሳካላችኋል።” ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፦ “ጽኑ ፍቅሩ ለዘዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ” የሚሉትንም ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለጌታም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሙዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ ጌታ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተሸነፉ። የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ሊገድሉአቸውና ሊያጠፉአቸውም ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ አንዱ ሌላውን በማገዝ እርስ በርስ ተጠፋፉ። የይሁዳም ሰዎች በምድረ በዳ ወዳለው የመጠበቅያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም። ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ለመውሰድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ለመሸከም አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም ጌታን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ ጌታ በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። በበገናና በመሰንቆ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ጌታ ቤት ገቡ። ጌታ የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የጌታር ፍርሃት አደረባቸው። የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጠጥታ ሰፈነበት፥ አምላኩም በዙርያው ካሉ አሳረፈው። ኢዮሣፍጥም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላደረጉም ነበር። የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል። ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ። ኢዮሣፍጥም ወደ ተርሴስ የሚሄዱትን መርከቦች ለመሥራት ከእርሱ ጋር ተባበረ፤ መርከቦቹንም በዔጽዩን-ጋብር አሠሩ። የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር፦ “ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና ጌታ ሥራህን አፍርሶታል” ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ለመሄድ አልቻሉም። ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን የበኩር ልጁ ስለ ሆነ ለኢዮራም ሰጠ። ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ሥልጣን ይዞ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። የአክአብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገው እንዲሁ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በጌታም ዘንድ ክፉ የሆነውን ነገር አደረገ። ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራት ለመስጠት ስላደረገው ተስፋ፥ ጌታ የዳዊትን ቤት ለማጥፋት አልፈለገም። በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዓመፀ፥ ለራሱም ንጉሥ አነገሠ። ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ። ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዓመፀ፥ በዚያንም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዓመፀ፥ የአባቶቹን አምላክ ጌታን ትቶ ነበርና። ዳግምም በይሁዳ ተራሮች ላይ በከፍታ ላይ የሚገኙ የማምለኪያ ሥፍራዎችን ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፥ ይሁዳንም አሳተው። ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ መጣለት፦ “የአባትህ የዳዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ እነሆ፥ ጌታ ሕዝብህንና ልጆችህን ሚስቶችህንም ያለህንም ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይቀስፋል። አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪ ወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትያዛለህ።’ ” ጌታም የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን የቊጣ መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ። ወደ ይሁዳም ወጡ፥ ወረርዋትም፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም ሴቶች ልጆቹንም ማረኩ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አላስቀሩለትም። ከዚህም ሁሉ በኋላ ጌታ በማይፈወስ ደዌ አንጀቱን ቀሰፈው። ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፥ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበረ ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። መንገሥም በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናበተ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልቀበሩትም። በኢየሩሳሌም የነበሩትም ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ገድለዋቸው ነበርና። የይሁዳም ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች። እናቱም ክፉ እንዲያደርግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ አባቱም ከሞተ በኋላ የአባቱ አመካሪዎች መጥፊያው እስኪሆኑ ድረስ አማከካሪዎቹ ነበሩና። በምክራቸውም ሄደ፥ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት። ከሶርያም ንጉሥ ከአዛኤል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቁስል ለመታከም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ። አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ እዲጠፋ የጌታ ፈቃድ ነበረ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር ጌታ የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ ወደ ቀባው ወደ ናሜሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ። ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድን ሲፈጽም የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው። አካዝያስንም ፈልገው፥ በሰማርያም ተሸሽጎ ሳለ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉት እንዲህም ብለው ቀበሩት፦ “በፍጹም ልብ ጌታን የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው።” ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥቱን ለመግዛት የሚችል አልነበረም። የአካዝያስም እናት ጎቶሊያ ልጇ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን የነገሥታት ዘር ሁሉ አጠፋች። የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ ጎቶሊያ እንዳታስገድለው የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት እንዲሁ ሸሸገችው። በእነርሱም ዘንድ ተሸሽጎ በጌታ ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድሪቱ ላይ ነገሠች። በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፥ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛሪያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ይሁዳንም ዞሩ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ጉባኤውም ሁሉ በጌታ ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ጌታ ስለ ዳዊት ልጆች እንደ ተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስቱ አንዱ በመግቢያ በሮች ላይ ጠባቂዎች ሁኑ፤ ከሦስቱም አንዱ በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ እንዲሁም ከሦስቱ አንዱ በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ቤት አደባባይ ይሁኑ። ወደ ጌታ ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ግን የጌታን ሕግ ይጠብቅ። ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።” ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ። ካህኑም ዮዳሄ በጌታ ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፥ ምስክሩንም ሰጡት፥ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም፦ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ ቀቡት። ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ ጌታ ቤት መጣች። እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ፦ “ዓመጽ ነው፥ ዓመጽ ነው” ብላ ጮኸች። ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች፦ “ከሰልፉ መካከል አውጡአት የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል” ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም፦ “በጌታ ቤት ውስጥ አትግደሉአት” አለ። እጃቸውን በእስዋ ላይ ጭነው ያዝዋት፤ እርሷም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፥ በዚያም ገደሉአት። ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የጌታ ሕዝብ እንዲሆኑ ቃል ኪዳን አደረገ። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ባዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የባዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በጌታ ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በጌታ ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በጌታ ቤት በር በጠባቂዎችን አኖረ። የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከጌታ ቤት ወስደው በላይኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት። ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆች ወለደ። ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የጌታን ቤት ለማደስ አሰበ። ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፥ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ።” ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ላይ ሌዋውያን እንዲሰበስቡ ለምን አላተጋሃቸውም?” ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የጌታን ቤት አፍርሰዋልና፤ በጌታም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለባዓል ተጠቅመውበታልና። ንጉሡም አዘዘ፥ ሣጥንም ሠርተው በጌታ ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። የጌታም ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለጌታ እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው ግብሩን አመጡ፥ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምንት በመጣ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የታላቁ ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥኑ ውስጥ ያወጡ ነበር፥ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲህም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፥ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። ንጉሡና ዮዳሄም በጌታ ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የጌታን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የጌታንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። ሠራተኞችም ሠሩ፥ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የጌታንም ቤት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መለሱት፥ አጽንተውም አቆሙት። በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ በእርሱም ለጌታ የቤት ዕቃ፥ የአገልግሎትና የቁርባን ዕቃ፥ ሙዳዮቹም፥ የወርቅና የብርም ዕቃ ተሠራበት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። ዮዳሄም ሸመገለ፥ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። በእስራኤልም፥ ለጌታና ለቤቱም ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሰማቸው። የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ ወረደ። ወደ ጌታም እንዲመልሱአቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፥ እነርሱ ግን አላደመጡም። የጌታም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የጌታን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ለእናተም አሳካላችሁም፤ ጌታን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል።’ ” ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በጌታ ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፦ “ጌታ ይየው፥ ይበቀለውም” አለ። በዓመቱ መጨረሻ በኢዮአስ ላይ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፥ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ ጌታ ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት። እርሱንም ትተውት በሄዱ ጊዜ በጽኑ አቊስለውት ነበር፤ የገዛ ባርያዎቹም የካህኑ የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል ሲሉ አሴሩበት፥ በአልጋውም ላይ ገደሉት፥ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። ያሴሩበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የጌታንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። ፍጹምም ልብ ሳይኖረው አሜስያስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። መንግሥትም በጸናለት ጊዜ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባርያዎች ገደለ። አሜስያስ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም ነበር ምክንያቱም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፥ ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበርና፦ “ሰው ሁሉ በገዛ ኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች ፋንታ አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች ፋንታ አይሙቱ።” አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ሥር እንዲሆኑ አደረገ፤ ዕድሜአቸው ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቈጠረ፥ ለጦርነትም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎችን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ! ጌታ ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ጋር አይደለምና የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር አይውጣ። ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የመርዳትና የመጣል ኃይል ከጌታ ዘንድ ነውና ጌታ በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።” አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሠራዊት የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሆን?” የጌታም ሰው እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “ጌታ ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል።” አሜስያስም ከኤፍሬም የመጡትን ሠራዊት ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቁጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፥ ወደ አገራቸውም በጽኑ ቁጣ ተመለሱ። አሜስያስም በረታ፥ ሕዝቡንም አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፥ ከሴይርም ልጆች ዐሥር ሺህ ገደለ። የይሁዳም ልጆች ደግሞ ዐሥር ሺህ ሰዎችን በሕይወታቸው ማረኩ፥ ወደ ዓለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ እነርሱንም ከዓለቱ ራስ ላይ ጣሉአቸው፥ ሁሉም ተፈጠፈጡ። አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮች ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሖሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ሰዎች ገደሉ፥ ብዙ ምርኮም ማረኩ። አሜስያስም የኤዶማውያንን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፥ የእርሱም አማልክት እንዲሆኑ አቆማቸው፥ ይሰግድላቸውም ያጥንላቸውም ነበር። ስለዚህም የጌታ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ እንዲህ ብሎ የሚናገረውን ነቢይም ላከበት፦ “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ለምን ፈለግሃቸው?” እርሱም እየተናረ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሾመነሃልን? ተው፤ እንዲገድሉህ ለምን ትሻለህ?” ነቢዩም፦ “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና ጌታ ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ተወ። የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ተማክሮ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ።” የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮስያስ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “የሊባኖስ ኩርንችት፦ ‘ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው’ ብሎ ወድ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኩርንችቱን ረገጠ። አንተም፦ ‘እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ’ ብለህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር አብረህ ለመውደቅ ለምን መከራ ትሻላህ?” የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው የጌታ ፈቃድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት-ሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፥ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤት-ሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በጌታም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ የንጉሡም ቤት መዛግብት፥ በመያዣ የተያዙትንም ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። የቀረውም የፊተኛውና የኋላኛው የአሜስያስ ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? አሜስያስም ጌታን ከመከተል ከራቀ በኋላ በኢየሩሳሌም ሤራን አሤሩበት፥ ወደ ለኪሶም ኰበለለ፤ ከኋላውም የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩበት፥ በዚያም ገደሉት። በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ዕድሜ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት። ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። ጌታንም መፍራት ባስተማረው ዘካርያስ በእርሱም ዘመን ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቀና፤ ጌታንም በፈለገ ጊዜ ጌታ ነገሩን አከናወነለት። ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው። አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ። ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው። ብዙም እንስሶች ነበሩትና በምድረ በዳውና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጉድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት። ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊቱ ውስጥ ለውግያ ብቁ የሆኑ ወታደሮች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቁጥራቸው ይወጡ ነበር። የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። ንጉሡንም በጠላቱ ላይ እንዲያግዝ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ጦርነት የሚወጣ፥ በትእዛዛቸው ሥር የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። ዖዝያንም ለሠራዊቱ ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቁርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚቀመጡትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች ሠራ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ አገር ድረስ ተሰማ። ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም ጌታን በደለ፤ ወደ ጌታ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ። ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማኒያ የጌታ ካህናት ተከትለውት ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ እንዲህ አሉት፦ “ዖዝያን ሆይ! ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለጌታ እንድታጥን ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከጌታ ዘንድ ክብር አያስገኝልህም።” ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በጌታ ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም እንዲወጣ አስገደዱት፥ እርሱም ደግሞ ጌታ ቀሥፎት ነበርና ለመውጣት ቸኮለ። ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከጌታ ቤት ተነጥሎአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል። ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ እነርሱም፦ “ለምጻም ነው” ብለው ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ኢዮአታምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ትባል ነበር። አባቱም ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ወደ ጌታ መቅደስ አልገባም፤ ሕዝቡም ገና ይበድል ነበር። የጌታን ቤት የላይኛውን በር ሠራ፥ በዖፌልም ቅጥር ላይ መጠነ ሰፊ ግንብ ገነባ። በተራራማውም በይሁዳ አገር ላይ ከተሞችን ሠራ፥ በዱር ስፍራዎችም አምባዎችንና ግንቦችን ሠራ፥ ከአሞንም ልጆች ንጉሥ ጋር ተዋጋ አሸነፋአቸውም። በዚያም ዓመት የአሞን ልጆች መቶ መክሊት ብር፥ ዐሥር ሺህም የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ ዐሥር ሺህም የቆሬስ መስፈሪያ ገብስ ሰጡት። እንዲሁም ደግሞ የአሞን ልጆች በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ተመሳሳ መጠን ያለውን ግብር ገበሩለት። ኢዮአታምም በአምላኩ በጌታ ፊት መንገዱን አቅንቶአልና በረታ። የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ ያደረገውም ጦርነት ሁሉ፥ ሥራውም፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በጌታ ፊት ቅን ነገር አላደረገም። ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፥ ደግሞም ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችን ሠራ። ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዐጠነ፤ ጌታ ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር። ስለዚህ ጌታ አምላኩ በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶሪያውያንም ድል አደረጉት፥ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞች ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡ። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ ውግያ ድል አደረገው። የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው ነበርና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ገደለ፤ ሁሉም ጽኑዓን ነበሩ። ከኤፍሬም ወገን የነበረው ኃያል ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕረግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፥ ብዙም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ። በዚያም ዖዴድ የተባለ የጌታ ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አላቸው፦ “እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቁጣ ገደላችኋቸው። አሁንም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ልጆች ባርያዎች ሆነው እንዲገዙላችሁ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን አምላካችሁን ጌታን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን? አሁንም ስሙኝ፤ የጌታ ቁጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።” ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የሰሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነት በተመለሱት ላይ ተቃወሙአቸው። እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፦ “በጌታ ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኃጢአታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የመቅሰፍቱም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነውና።” ተዋጊዎቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤው ሁሉ ፊት ተው። በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፥ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፥ አጎናጸፉአቸውም፥ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፥ መገቡአቸውም፥ አጠጡአቸውም፥ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፥ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማሪያም ተመለሱ። በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። ደግሞም ፍልስጤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። የይሁዳም ንጉሥ አካዝ ጌታን ክዷልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቋልና ጌታ ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው። የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። አካዝም ከጌታ ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኩሌታውን ገፈፈ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረጉ አንዳች አልጠቀመውም። ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ ጌታን መበደል አበዛ። ድል ለነሡትም ለደማስቆ አማልክት፦ “የሶሪያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን እንዲረዱኝ እሠዋላቸዋለሁ” ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ። አካዝም የጌታን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፥ የጌታንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ። በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ለማጠን የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ የአባቶቹንም አምላክ ጌታን አስቈጣ። የቀረውም ነገርና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኛውና የኋለኛው፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በከተማይቱም በኢየሩሳሌም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጎልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር። አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያውም ወር የጌታን ቤት ደጆች ከፈተ፥ አደሳቸውም። ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፥ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “ሌዋውያን ሆይ! ስሙኝ፤ ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የጌታን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በጌታ ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከጌታ መኖሪያ መልሰዋል፥ ወደ እርሷም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም ዋና የመግቢያ ደጆችን ዘጉ፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። ስለዚህም የጌታ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ። አሁንም የቁጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ በልቤ አስቤአለሁ። ልጆቼ ሆይ! በፊቱ ቆማችሁ እንድታገለግሉት፥ አገልጋዮቹም እንድትሆኑ፥ እንድታጥኑለትም ጌታ መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።” ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፥ ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ። ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ የጌታንም ቃላት መሠረት አድርጎ ንጉሡ እንዳዘዘው የጌታን ቤት ለማንጻት ገቡ። ካህናቱም መቅደሱን ለማንጻት ወደ ጌታ ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፥ በጌታም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ ጌታ ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀድሱ ጀመር፥ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ ጌታ ቤት ዋና የመግቢያ ደጅ ደረሱ የጌታንም ቤት በስምንት ቀን ውስጥ ቀደሱት፥ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የጌታን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የተቀደሰውም ሕብስት የሚቀመጥበትን ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በጌታ መሠዊያ ፊት ተቀምጠዋል።” ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፥ ወደ ጌታም ቤት ወጣ። ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢአት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን፦ “በጌታ መሠዊያ ላይ አሳርጉአቸው” አላቸው። ወይፈኖቹንም አረዱ፥ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፥ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። የኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፥ እጃቸውንም ጫኑባቸው፥ ካህናቱም አረዱአቸው፤ ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢአት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተሰረያ እንዲያደርጉ የኃጢአቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ። ይህንም ትእዛዝ ጌታ በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በጌታ ቤት አቆመ። ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያ ላይ እንዲያሳርጉ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማሳረግ በተጀመረ ጊዜ የጌታ መዝሙር ደግሞ ይዘመር ጀመር፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ መዝሙሩን ያጅብ ነበር። ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ያለማቋረጥ ተከነናወነ። ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም። ንጉሡም ሕዝቅያስና ሹማምንቱ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል ጌታን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። በደስታም እያመሰገኑ፥ አጐነበሱም ሰገዱም። ሕዝቅያስም፦ “አሁን ለጌታ ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፥ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ ጌታ ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ በሬዎች፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። የተቀደሱትም ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበሩ። ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። እጅግ ብዙ ከነበረው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የአንድነቱ መሥዋዕት ስብ ነበረ፤ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው የመጠጥ ቁርባን በዚያ ነበረ። እንዲህ ባለ መንገድ የጌታ ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ ጌታ ለሕዝቡ ስላዘጋጀላቸው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ። ለእስራኤልም አምላክ ለጌታ ፋሲካን ለማክበር ወደ ጌታ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፥ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤ ጻፈ። ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ለማክበር ተመካክረው ነበር። ዳሩ ግን በጊዜው ለማክበር አልቻሉም ነበር ምክንያቱም በቊጥር በቂ የሆኑ ካህናት ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰባሰቡ ነበር። ነገሩም በንጉሡና በጉባኤው ሁሉ ዘንድ መልካም ነበረ። እንደ ተጻፉትም ያህል በብዙ ቍጥር ፋሲካን አላከበሩም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የጌታን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለማክበር እንዲመጡ ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የሹማምንቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ እንዲህም አሉ፦ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታ ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠ የእናንተ ወደ ሆኑት ትሩፋን እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ እስራኤልም አምላክ ተመለሱ። እናንተም እንደምታዩት መሣቀቅያ እስኪያደርጋቸው ድረስ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለጌታ ስጡ፥ ለዘለዓለም ወደተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቁጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን ጌታን አገልግሉ። አምላካችሁ ጌታ ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ ጌታ ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።” መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ በእዚያ ያሉ ሰዎች ግን በንቀት ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም። ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም ጥቂት ሰዎች ብቻ ራሳቸውን አዋረዱ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ደግሞም አንድ ልብ እንዲሰጣቸው፥ በጌታም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የሹማምንቱን ትእዛዝ እንዲያደርጉ የጌታ እጅ በይሁዳ ላይ ነበረ። በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ሊያከብር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ። ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፥ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። በሁለተኛውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን ጠቦት አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አዋረዱ፥ ተቀደሱም፥ ወደ ጌታም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በሥርዓታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። በጉባኤውም ያልተቀደሱ እጅግ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለጌታ የተቀደሱ ለማድረግ ንጹሐን ላልሆኑት ሁሉ የፋሲካውን ጠቦት ያርዱላቸው ነበር። እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ብዙ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “ቸሩ ጌታ ሆይ! ሁሉንም ሰው ይቅር በል፤ እንደ መቅደሱ የማንጻት ሥርዓት ሳይሆን የአባቶቹን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቅንቶአልና።” ጌታም ሕዝቅያስን ሰማው፥ ሕዝቡንም ፈወሰ። በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አከበሩ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለጌታ እየዘመሩ ዕለት ዕለት ጌታን ያመሰግኑ ነበር። ሕዝቅያስም በጌታ አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ ያበረታታ ነበር። የአንድነትንም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ለሰባት ቀን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ማዕድ በሉ። ከካህናቱም እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና ጉባኤው ሁሉ እንደገና ሰባት ቀን በዓሉን ለማክበር ተማከሩ፤ በደስታም እንደገና ሰባት ቀን በዓሉን አከበሩ፤ እንዲህም ያከበሩት የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንደ ቁርባን ስለሚቀርበው መሥዋዕት አንድ ሺህ ወይፈኖችና ሰባት ሺህ በጎች እንዲሁም ሹማምንቱ አንድ ሺህ ወይፈኖችና ዐሥር ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥተው ስለ ነበረ ነው። የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም አገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተከበረም ነበር። ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምጻቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ መኖሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ። ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉንም ፈጽመው እስከሚያጠፏቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ። ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በጌታ ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ እንዲያገለግሉ፥ እንዲያመሰግኑም ክብርም እንዲሰጡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ። በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፈለውን ወሰነ። የጌታንም ሕግ በጽኑ እንዲያገለግሉ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሚገባቸውን ድርሻ እንዲሰጡአቸው በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በብዛት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት በብዛት አቀረቡ። በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳም ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለጌታ የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አስቀመጡት። በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። ሕዝቅያስና ሹማምንቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ። ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። ከሳዶቅም ወገን የሆነ ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፦ “ሕዝቡ ቁርባኑን ወደ ጌታ ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ ጌታ ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው” ብሎ ተናገረ። ሕዝቅያስም በጌታ ቤት ውስጥ ግምጃ ቤት እንዲያዘጋጁ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። ቁርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም ነገሮች በታማኝነት ወደዚያ አስገቡ። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕረግ ሁለተኛ ነበረ፤ በንጉሡም በሕዝቅያስና በጌታ ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ ጠባቂ ቆሬ የጌታን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያከፋፍል ሕዝቡ ለጌታ በፈቃድ ባቀረቡት መባ ላይ ተሾመ። በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ድርሻቸውን በታማኝነት እንዲሰጡ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ የቆሬ ረዳቶች ነበሩ። በትውልዳቸው ከተቈጠሩት በቀር ዕድሜያቸው ሦስት ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ በየሰሞናቸውም ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ ጌታ ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤ በየአባቶቻቸውም ቤት ካህናቱ ተቈጠሩ፤ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ዕድሜያቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ ሌዋውያኑ ተቈጠሩ። በታማኝነትም ቅድስናቸውን ጠብቀዋልና ካህነናቱ በየትውልዳቸው ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻቸው እንዲሁም ከማኅበሩ ሁሉ ጋር ተቈጠሩ። በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰማሪያዎች ውስጥ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ድርሻቸውን እንዲሰጡአቸው በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ። ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በጌታ ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ። ስለ ጌታም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም። ከዚህም ነገርና በታማኝነት ከተደረገው ነገር በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፥ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፥ የራሱም ሊያደርጋቸው አሰበ። ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደመጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ለመድፈን ከሹማምንቱና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት። እጅግም ሰዎች ተሰብስበው፦ “የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ለምን ያገኛሉ?” ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ዥረት ደፈኑ። ንጉሥ ሕዝቅያስም ራሱን ለሥራ ጽኑ አደረገ፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም የጦር መሣሪያና ጋሻ ሠራ። የጦር አዛዦቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፥ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰበሰበ፥ እንዲህም ብሎ አበረታታቸው፦ “ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና የአሦርን ንጉሥና ከእርሱ ጋር ያለውን ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ከእርሱ ጋር ያለው ሥጋዊው ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን ጌታ አምላካችን ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃላት ተበረታታ። ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ሳለ ባርያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦ “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? “ጌታ አምላካችን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል” እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ለመስጠት የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? “በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፥ በእርሱም ላይ ዕጠኑ” እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ለማዳን በውኑ ችለዋልን? አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ለማዳን የቻለ ማንስ ነበር፤ እናንተንስ አምላካችሁ ከእጄ ለማዳን የሚችል ይመስላችኋልን? አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፥ እንዲህም አያባብላችሁ፥ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ለማዳን ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ሊያድናቸሁ እንዴት ይችላል?’ ” ባርያዎቹም ደግሞ አምላክ በሆነው በጌታና በባርያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። ደግሞም የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር፦ “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ለማዳን እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። ከተማይቱንም ወርሮ ለመውሰድ፥ በቅጥርም ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለማስፈራራትና ለማስደንገጥ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር። በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ። ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ነገር ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ። ጌታም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን የጦር አዛዦቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ላከ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከአብራኩ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። እንዲሁም ጌታ ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። ብዙዎቹም ለጌታ መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፥ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ። በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ ጌታም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው። ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቁጣ ሆነ። ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኩራት ራሱን አዋረደ፥ የጌታም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም። ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀበትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቁና ለሽቶው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ። ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንሰሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። ጌታም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ። ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለተደረገው ተአምራት ለመጠየቅ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ ጌታ እርሱን ለመፈተንና በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ ሲል ተወው። የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥርዓት አደረጉለት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። ጌታም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኩሰት በጌታ ፊት ክፉ ነገር አደረገ። አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊምም መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፥ አገለገላቸውም። ጌታም፦ “ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል” ባለው በጌታ ቤት መሠዊያዎችን ሠራ። በጌታም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት በማቃጠል እንደ መሥዋዕት አቀረበ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መተተኛም ነበረ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ጌታንም ለማስቈጣት በጌታ ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። ጌታ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን፦ “በዚህ ቤት ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤” ባለበት በጌታ ቤት የሠራውን ጣዖት የቀረጸውን ምስል አቆመ። እንዲሁም ጌታ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን፦ “እኔ ያዘዝኋቸውን ሁሉ፥ በሙሴም በኩል የተሰጠውን ሕግና ሥርዓት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር እስራኤል እንደገና እንዲሰደዱ አላደርግም” ብሎ ነበር። ምናሴም ጌታ ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ እንዲሠሩ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ። ጌታም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። ስለዚህም ጌታ የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፥ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን ጌታን ፈለገ፥ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ፥ ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፥ ጸሎቱንም ሰማው፥ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እርሱ ጌታ አምላክ እንደሆነ አወቀ። ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፥ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከጌታ ቤት አራቀ፥ የጌታም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። የጌታንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፥ የአንድነትንና የምስጋናንም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ ጌታን እንዲያገለግሉ አዘዘ። ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ግን እንዲህ የሚያደርገው ለአምላኩ ለጌታ ብቻ ነበረ። የምናሴም የቀረው ነገር፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በጌታ ስም የነገሩት የነቢያት ቃላት፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። ደግሞም ጸሎቱ፥ ጌታም እንደ ተለመነው፥ ኃጢአቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ራሱንም ሳያዋርድ የኮረብታው መስገጃዎችን የሠራበት የማምለኪያ ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዮቹ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፥ አገለገላቸውም። አባቱም ምናሴ በጌታ ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንዲሁ እርሱ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ። ባርያዎቹም አሤሩበት፥ በቤቱም ውስጥ ሳለ ገደሉት። የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሤሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ። ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። በጌታም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም። በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በዓሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረፁትና ቀልጠው ከተሰሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። የበኣሊምንም መሠዊያዎች በእርሱ ፊት አፈረሱ፤ በእነርሱም ላይ የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎቹን የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረፁትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። የምናሴንና የኤፍሬምንም የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረፁትን ምስሎች አደቀቀ፥ በእስራኤልም አገር ሁሉ የዕጣን መሠዊያዎቹን ሁሉ ቈራረጠ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። በነገሠም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የጌታን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የጌታን የአምላኩን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው። ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም የደጆቹም ጠባቂዎች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ ጌታ ቤት ያመጡትን ገንዘብ ሰጡት። የጌታንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ በጌታም ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ቤቱን ለሚጠግኑና ለሚያድሱ ሠራተኞች ሰጡ። እነርሱም የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች እንዲሠሩ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ እንዲገዙ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም የደጁም ጠባቂዎች ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ወደ ጌታም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የጌታን የሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን፦ “የሕጉን መጽሐፍ በጌታ ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም እንዲህ ብሎ አወራለት፦ “ባርያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ እያደረጉ ነው፤ በጌታም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ።” ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ፦ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን ቃላት በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለማድረግ አባቶቻችን የጌታን ቃል ስላልጠበቁ፥ በእኛ ላይ የነደደው የጌታ ቁጣ እጅግ ታላቅ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት ጌታን ጠይቁ።” ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርሷም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ አመጣለሁ። በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቁጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። ጌታን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃላት፥ ልብህ ተጸጽቶአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ የተናገርሁትን ቃላቴን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩባትም ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት። ንጉሡም ላከ፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀመሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ ጌታ ቤት ወጡ፤ በጌታም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ እየሰሙት አነበበ። ንጉሡም በስፍራው ቆሞ ጌታን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዛቱንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በጌታ ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንደሚያዝዘው አደረጉ። ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩስ የሆነውን ነገር ሁሉ አስወገደ፥ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን ጌታን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ከመከተል አልራቁም። ኢዮስያስም ለጌታ በኢየሩሳሌም ፋሲካን አከበረ፤ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን መሥዋዕት አረዱ። ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፥ በጌታም ቤት እንዲያገለግሉ አጸናቸው። እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለጌታም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ራሳችሁን አዘጋጁ፤ እንደ ሕዝቡም እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱ ለተከፋፈሉትም ለአባቶች ቤቶች ሌዋውያን ይኑሯቸው፤ ፋሲካውንም እረዱ፥ እናንተም ተቀደሱ፥ ጌታም በሙሴ አንደበት የተናገረውን ቃል እንዲያደርጉ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም በሬዎች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የጌታም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ። አገልግሎቱም በተዘጋጀ ጊዜ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለጌታ እንዲያቀርቡ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። የፋሲካውንም መሥዋዕት እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቁርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ የደጁም ጠባቂዎች በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው እንዲርቁ አያስፈልጋቸውም ነበር። እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በጌታ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ፋሲካውንም እንዲያከብሩ የጌታ አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አከበሩ። ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳከበሩት ያለ ፋሲካ ያከበረ የለም። ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ተከበረ። ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ባሰናዳ ጊዜ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ሄደ። ኒካዑም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ውግያ የማደርገው በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ ጌታም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው ጌታ እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ።” ኢዮስያስ ግን ማንነቱን ሸሽጎ ለመዋጋት ወጣ እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በጌታም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ለመዋጋት መጣ። ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ “ክፉኛ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። አገልጋዮቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት። ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። የግብጽም ንጉሥ ከኢየሩሳሌም ከመንግሥቱ አወረደው፥ በምድሪቱም በሚኖሩት ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለባቸው። የግብጽም ንጉሥ ወንድሙን ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው፤ ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብጽ ወሰደው። ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ በአምላኩም በጌታ ፊት ክፉ አደረገ። የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደናፆር በኢዮአቄም ላይ መጣበት፤ እርሱንም ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በሰንሰለት አሰረው። ናቡከደናፆርም ከጌታ ቤት ዕቃ አያሌውን ወደ ባቢሎን አጋዘ፥ በባቢሎንም በመቅደሱ ውስጥ አኖረው። የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ ያደረገውም ርኩሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ ልጁም ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ዮአኪንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወርና ዐሥር ቀን ነገሠ፤ በጌታም ፊት ክፉ አደረገ። ዓመቱ ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደናፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፥ የከበረውንም የጌታን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ ወንድሙንም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ። ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። በአምላኩም በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ ከጌታም አንደበት የመጣውን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊት ራሱን አላወረደም። ደግሞም በጌታ አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደናፆር ላይ ዓመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ ጌታ እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ ልቡንም አጠነከረ። ደግሞም የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝቡም እንደ አሕዛብ ያለ ርኩሰት ሁሉ በመከተል መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም ጌታ ራሱ የቀደሰውን የጌታን ቤት አረከሱ። የአባቶቻቸውም አምላክ ጌታ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ መልክተኞቹን ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወርድባቸው ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በጌታ መልክተኞች ይሳለቁ፥ ቃላቱንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጉልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጎልማሳውንና ድንግሊቱን ሽማግሌውንና አዛውንቱን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ታላቁንና ታናሹን፥ የጌታንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የሹማምንቱን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፥ የንጉሥ ቅጥሮችዋንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፥ ዕንቊውንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ። ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባርያዎች ሆኑ፤ በኤርምያስ አንደበት የተናገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አደረገች። በኤርምያስም አንደበት የተነገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ጌታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ ነገረ፥ ደግሞም በጽሑፍ እንዲህ ብሎ አወጀ፦ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ጌታ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ጌታ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም ይውጣ።’ ” በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ በኤርምያስ አፍ የተናገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም፥ ጌታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፥ ይህም በመንግሥቱ ሁሉ በአዋጅና በጽሑፍ እንዲያስነግር ነው፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማያት አምላክ ጌታ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፥ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ ማንም በእናንተ ውስጥ የሚኖር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ የጌታ የእስራኤል አምላክን ቤት ይሥራ፥ እርሱም በኢየሩሳሌም ያለ አምላክ ነው፤ ከሁሉም ስፍራዎች የተረፈው ሁሉ መፃተኛ ሆኖ በሚኖርበት የሰፈሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፥ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት መባ ጋር ይሁን።” እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም የአባቶች አለቆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት ለመሥራት ተዘጋጁ። በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት መባ ሁሉ በተጨማሪ በእጃቸው፥ በብር ዕቃና በወርቅ፥ በዕቃዎችና በእንስሶችና በውድ ነገሮች አበረታቱአቸው። ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የጌታን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገብ ቤቱ በሚትረዳት እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሼሽባጻር ቆጠራቸው። ቁጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ ሰሐኖች፥ አንድ ሺህ የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝ ቢላዋዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ ዐሥር ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ። የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሼሽባጻር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ። የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው። ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከሠራያ፥ ከረዔላያ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከቢልሻን፥ ከሚስፋር፥ ከቢግዋይ፥ ከሬሁምና፥ ከባዓና ጋር መጡ። የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው። የፓርዖሽ ልጆች፥ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሁለት። የሸፋጥያ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት። የአራሕ ልጆች፥ ሰባት መቶ ሰባ አምስት። የፓሐት ሞዓብ ልጆች የኢያሱ ዮአብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ዐሥራ ሁለት። የዔላም ልጆች፥ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። የዛቱ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ አርባ አምስት። የዘካይ ልጆች ሰባት መቶ ስድሳ። የባኒ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት። የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ሦስት። የዓዝጋድ ልጆች፥ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሀያ ሁለት። የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት። የቢግዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ አምሳ ስድስት። የዓዲን ልጆች፥ አራት መቶ አምሳ አራት። ከሕዝቅያ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት። የቤፃይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሃያ ሦስት። የዮራ ልጆች፥ መቶ ዐሥራ ሁለት። የሐሹም ልጆች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት። የጊባር ልጆች፥ ዘጠና አምስት። የቤተልሔም ልጆች፥ መቶ ሀያ ሦስት። የኔፆፋ ሰዎች፥ አምሳ ስድስት። የዓናቶት ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት። የዓዝማቬት ልጆች፥ አርባ ሁለት። የቂርያትዓሪም፥ ከፊራና ብኤሮት ልጆች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት። የራማና የጋባዕ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ። የሚክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት። የቤት-ኤልና የዐይ ሰዎች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት። የንቦ ልጆች፥ አምሳ ሁለት። የማግቢሽ ልጆች፥ አንድ መቶ አምሳ ስድስት። የሌላኛው ዔላም ልጆች፥ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። የሐሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ። የሎድ የሐዲድና የኦኖ ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አምስት። የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት። የስናአ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ። ካህናቱ ከኢያሱ ቤት የሆነው ይዳዕያ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት። የኢሜር ልጆች፥ አንድ ሺህ አምሳ ሁለት። የፓሽሑር ልጆች፥ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት። የሐሪም ልጆች፥ አንድ ሺህ ዐሥራ ሰባት። ሌዋውያኑ፥ ከሆዳቭያ ወገን የኢያሱና የቃድምኤል ልጆች፥ ሰባ አራት። መዘምራኑ፦ የአሳፍ ልጆች፥ አንድ መቶ ሀያ ስምንት። የበር ጠባቂዎች ልጆች፦ የሻሉም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጣልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሾባይ ልጆች፥ ሁሉ አንድ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ። የቤተ መቅደስ አገልጋዮች፥ የፂሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥ የጣባዖት ልጆች የቄሮስ ልጆች፥ የሲዓሃ ልጆች፥ የፓዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥ የሐጋባ ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጋብ ልጆች፥ የሻምላይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥ የጊድል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥ የርአያ ልጆች፥ የረፂን ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ የጋዛም ልጆች፥ የዑዛ ልጆች፥ የፓሴሐ ልጆች፥ የቤሳይ ልጆች፥ የአስና ልጆች፥ የምዒኒም ልጆች፥ የንፊሲም ልጆች፥ የባቅቡቅ ልጆች፥ የሐቁፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥ የባፅሉት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥ የሐርሻ ልጆች፥ የባርቆስ ልጆች፥ የሲሥራ ልጆች፥ የታማሕ ልጆች፥ የንፂሐ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች። የሰሎሞንም አገልጋዮች ልጆች፦ የሶጣይ ልጆች፥ የሃሶፌሬት ልጆች፥ የፕሩዳ ልጆች፥ የያዕላ ልጆች፥ የዳርቆን ልጆች፥ የጊዴል ልጆች፥ የሽፋጥያ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፎኬሬት ሃፂባይም ልጆች፥ የአሚ ልጆች። እነዚህ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ሁሉና የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ። ከቴልሜላሕ፥ ቴልሐርሻ፥ ክሩብ፥ ዓዳን፥ ኢሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ማስታወቅ አልቻሉም፤ የድላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የንቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ። ከካህናቱም ልጆች፦ የሖባያ ልጆች፥ የሃቆፅ ልጆች፥ የባርዚላይ ልጆች ከገለዓዳዊው ባርዚላይ ሚስት ያገባ፥ በስማቸውም የተጠራ ነው። እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፥ ነገር ግን አልተገኙም፤ እንደ ርኩሳን ከክህነት ተከለከሉ። አስተዳዳሪውም፦ በኡሪምና በቱሚም የሚጠይቅ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳን አትበሉም አላቸው። ከምርኮ የተመለሱ ሰዎች አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ። በተጨማሪም ወንዶች አገልጋይዮቻቸውና ሴቶች አገልጋዮቻቸው እነዚህ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ነበሩ ሌላ ሁለት መቶ ወንዶች መዘምራንና ሴቶች መዘምራን ነበሩአቸው። ፈረሶቻቸው ሰባት መቶ ሠላሳ ስድስት፥ በቅሎዎቻቸው ሁለት መቶ አርባ አምስት፥ ግመሎቻቸው አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸውም ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ። ከአባቶች ቤቶች አለቆች አንዳንዶች፥ በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ጌታ ቤት በመጡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ቤት በስፍራው እንዲሠራ በፈቃዳቸው መባ ሰጡ። ስድሳ አንድ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ አምስት ሺህ ምናን ብር፥ አንድ መቶ የካህናት ልብስ እንደየአቅማቸው ወደ ሥራው ቤተ መዛግብት አቀረቡ። ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ ከሕዝቡም አንዳንዶች፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹና፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ፥ በከተሞቻቸው፥ እስራኤልም ሁሉ በከተሞቻቸው ተቀመጡ። ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞች ነበሩ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ ተነሣ፥ ወንድሞቹ ካህናትና፥ የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሊያቀርቡበት የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። በምድሩ ካሉት ሕዝቦች የተነሣ ፈርተው ነበርና፥ መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት በጠዋትና በማታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለጌታ አቀረቡ። እንደተጻፈውም የዳስ በዓል አከበሩ፤ እንደ ሥርዓቱም የዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በዕለቱ በቍጥር አቀረቡ፤ የዕለቱን ነገር በዕለቱ። ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የወር መባቻና፥ የተመረጡና የተቀደሱ የጌታ በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለጌታ በፈቃድ የሰጠውን ቁርባን አቀረቡ። ከሰባተኛው ወር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ ነገር ግን የጌታ መቅደስ አልተመሠረተም ነበር። ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ወደ ያፎ ባሕር እንዲያመጡ ለሲዶናውያንና ለጢሮሳውያን መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ። በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤል፥ የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ፥ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የጌታን ቤት ሥራ እንዲቆጣጠሩ መረጧቸው። ኢያሱ፥ ልጆቹ፥ ወንድሞቹ፥ የይሁዳም ልጆች ቃድሚኤልና ልጆቹ፥ የሔናዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን እንዲቆጣጠሩ እንደ አንድ ቆሙ። ግንበኞቹም የጌታን መቅደስ መሠረቱ፤ ካህናቱ ሙሉ ልብስ ለብሰው፥ መለከት ይዘው፥ የአሳፍ ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት ጌታን እንዲያመሰግኑ መረጧቸው። ደግሞም ጌታን እያከበሩና እያመሰገኑ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ ዘመሩ። ሕዝቡ ሁሉ ጌታን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ፥ ይህም የጌታ ቤት ስለ ተመሠረተ ነው። የመጀመሪያውን ቤት ያዩ ብዙ ካህናት፥ ሌዋውያን፥ የአባቶች አለቆችና ሽማግሌዎች ግን ይህ ቤት በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፥ ብዙ ሰዎችም በደስታ እልል ይሉ ነበር፤ ሕዝቡ ግን ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት አልቻለም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ እልል ይሉ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር። የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ መቅደስ እየገነቡ እንደሆነ ሰሙ። ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች አለቆች ቀርበው፦ “እንደ እናንተ አምላካችሁን እንፈልገዋለን፥ የአሦር ንጉሥ ኤሳርሐዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለእርሱ እንሠዋ ነበርና፥ ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሉአቸው። ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የቀሩትም የእስራኤል አባቶች አለቆች፦ “የአምላካችንን ቤት ማነፅ ለእኛና ለእናንተ አይደለም፥ እኛ ለብቻችን ሆነን ንጉሥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ እንዳዘዘን ለጌታ ለእስራኤል አምላክ ቤት እንገነባለን” አሉአቸው። የምድሪቱም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይገነቡም ያስፈራሯቸው ነበር፤ ከቂሮስ የፋርሱ ንጉሥ ዘመን ሁሉ ጀምሮ እስከ ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ መንግሥት ድረስ ሥራቸውን እንዲያፈርሱ ባለሥልጣኖችን ቀጠሩባቸው። በአሐሽኤሩስ መንግሥት፥ በመንግሥቱም መጀመሪያ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ ክስ ጻፉ። በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትረዳት፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ አርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ ኢየሩሳሌምን የሚመለከት አንድ ደብዳቤ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ ብለው ጻፉ፤ አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዳኞቹ፥ ባለሥልጣኖቹ፥ አስተዳዳሪዎቹ፥ ጸሐፍያን፥ የኤርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱሳንካውያን፥ ዴሐውያን፥ ዔላማውያን፥ ታላቁና የተከበረው አስናፋር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ። አሁንም የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው፦ “ለንጉሡ ለአርጤክስስ፥ አገልጋዮችህ በወንዙ ማዶ ያለ አገር የሚኖሩ ሰዎች፤ አሁንም ከአንተ ዘንድ የመጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደመጡ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ዓመፀኛይቱንና ክፉይቱን ከተማ በመስራት፥ ቅጥሮቿንም በማደስ፥ መሠረትዋንም በመጠገን ላይ ናቸው። አሁንም ይህች ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ ንጉሡንም እንደሚጎዳ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ስለዚህ አሁን ሁላችን የቤተ መንግሥቱን ጨው እንበላለንና፥ የንጉሡ አለመከበር ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታወቅን፤ በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርሷ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። ይህችም ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ በወንዝ ማዶ ባለ አገር ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።” ንጉሡ እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፦ “ለአዛዡ ለሬሑምና ለጸሐፊውም ለሺምሻይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ባለ አገር ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው ሰላም! አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ በግልፅ ተነበበ። እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፥ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርሷም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለምን ይሄዳል?” የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሑምና በጸሐፊው በሺምሻይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ። ነቢያቱ ሐጌና የዒዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእነርሱ ላይ በነበረው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። በዚያን ጊዜ የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤል የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸው የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ። በዚያው ዘመን በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ወደ እነርሱ መጥተው እንዲህ አሏቸው፦ “ይህን ቤት ለመሥራት፥ ቅጥሩንም ለማደስ ማን አዘዛችሁ?” ደግሞም፦ “ይህንስ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ስም ማን ነው?” ብለው ጠየቁአቸው። የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፥ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አላስቆሙአቸውም። የደብዳቤውንም ግልባጭ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው በወንዙ ማዶ የነበሩ ባለ ሥልጣናት ወደ ንጉሡ ዳርዮስ ላኩለት፤ እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት፦ “ለንጉሡ ዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤ ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁ አምላክ ቤትም እንደ ሄድን በንጉሡ ዘንድ ይታወቅ፥ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፥ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፥ ያም ሥራ በጥንቃቄ ይሠራል፥ በእጃቸውም ይከናወናል። እኛም ሽማግሌዎቹን፦ ‘ይህን ቤት እንድትሠሩ፥ ይህንንም ቅጥር እንድታድሱ ማን አዘዛችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው። ደግሞም እንድታውቅ፥ በእነርሱ ላይ ያሉትን መሪዎች ስም እንድንጽፍልህ ስማቸውን ጠየቅን። የመለሱልን መልስ ይህ ነው፦ ‘እኛ የሰማያትና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፥ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረ፥ ታላቅ የእሥራኤል ንጉሥ ሠርቶ የፈጸመውን ቤት እንሠራለን። ነገር ግን አባቶቻችን የሰማያትን አምላክ ስላስቆጡት በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፥ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት እንዲሠሩ አዘዘ። ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያመጣውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅንና የብርን ዕቃዎች ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ሼሽባጻር ለተባለው፥ ገዢ ላደረገው ሰጠው፤ እነዚህን ዕቃዎች ውሰድ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ አስቀምጠው የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ’” አለው። በዚያን ጊዜ ይህ ሼሽባጻር መጣ፥ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ ነው አላለቀምም። “አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዐይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም እንዲሠራ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፥ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።” በዚን ጊዜ ንጉሡ ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ። በባቢሎን መዛግብት ባሉበት ቤተ መጻሕፍት ምርመራ ተደረገ። በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በቤተ መንግሥት ውስጥ አንድ ጥቅል ተገኘ፥ በውስጡም እንዲህ የሚል ተጽፎ ነበር፤ “ማስታወሻ በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ስላለው ስለ እግዚአብሔር ቤት እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ መሥዋዕት የሚሠዋበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ ስፋቱም ስድሳ ክንድ ይሁን። በሦስት መደዳ ታላላቅ ድንጋይ፥ አንድ መደዳ እንጨት ይደረግ፤ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ይመለስ፥ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።” “አሁንም በወንዝ ማዶ ያለውን አካባቢ ገዢ የሆንህ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻቸው ባለ ሥልጣናት ከዚያ ራቁ፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ ተዉ፥ የአይሁድ አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው እንዲሠሩ ተዉአቸው። ይህን የእግዚአብሔርን ቤት እንዲሠሩ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን አዝዣለሁ፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት ይሰጣቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው። ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። ይህም ለሰማያት አምላክ መልካም መዓዛ እንዲያቀርቡ፥ ለንጉሥና ለልጆቹ ሕይወትም እንዲጸልዩ ነው። ይህንም ትእዛዝ የሚያደናቅፍ ሁሉ፥ ምሰሶ ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰካበት፥ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይሁን ብዬ አዝዣለሁ። ይህን ሊለውጡ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ሊያፈርሱ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙን በዚያ ያኖረው አምላክ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፥ በትጋት ይፈጸም።” ከዚያ በኋላ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ ሐጌና በዒዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተበረታቱ ሠሩ ተከናወነላቸውም። በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ቂሮስ ትእዛዝ እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሥ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤል ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በደስታ አከበሩ። ለዚህ የእግዚአብሔር ቤት ምረቃ አንድ መቶ ወይፈኖች፥ ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶ የበግ ጠቦቶችን፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕረጋቸው ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቡአቸው። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ አንድ ሰው ሆነው እራሳቸውን አነጹ፥ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፥ ከምርኮ ለተመለሱ ሕዝቦች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱና ለራሳቸው ፋሲካውን አረዱ። ከምርኮ የተመለሱት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉት። ጌታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤትም ለመሥራት እጃቸውን እንዲያጸኑ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ። ከነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የሒልቂያ ልጅ፥ የሻሉም ልጅ፥ የጻዶቅ ልጅ፥ የአሒጡብ ልጅ፥ የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ የዘራሕያ ልጅ፥ የዑዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ የአቢሹዓ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የኤልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩ የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ፥ ከካህናቱም አንዳንዶቹ፥ ሌዋውያኑ፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹና፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። በንጉሡ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛውም ወር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። በመጀመሪያው ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን መውጣት ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ዕዝራም የጌታን ሕግ ሊፈልግና ሊያደርግው፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ሊያስተምር ልቡን አዘጋጅቶ ነበር። የጌታን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው፦ “ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ ለሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ዕዝራ፤ አሁንም በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ፥ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ የሚፈልግ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ። በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል፤ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚሰጡትን ይዘህ ሂድ። ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወይፈኖችን፥ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን ከእህል ቁርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቁርባኖቻቸው ጋር ተግተህ ግዛ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። የሚቀረውን ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ለማድረግ ደስ የሚላችሁን ነገር አድርጉ። ለአምላክህ ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃዎች በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ። ከዚህ በላይ ለአምላክህ ቤት የሚያስፈልግህን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ቤተ መዛግብት ውሰድ። እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ለምትገኙ ገንዘብ ያዦች ሁሉ፦ የሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ እስከ መቶ መክሊት ብር፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶ የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት፥ ጨውም የሚፈልገውን ያህል ሳትጽፉ ስጡት። በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቁጣ እንዳይሆን፥ የሰማያት አምላክ የሚያዘው ሁሉ ልክ እንዳዘዘው ለሰማያት አምላክ ቤት ይደረግ። ደግሞም በካህናቱ፥ በሌዋውያኑ፥ በመዘምራኑ፥ በበር ጠባቂዎቹና፥ በቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም ለመጣል ሥልጣን እንደሌላችሁ እወቁ። አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ እንዲፈርዱ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፥ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው። የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ትእዛዝ በማያደርግ በማንም ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ንብረት መወረስ ወይም ግዞት በፅኑ ይፈረድበት።” በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት እንዲያሳምር እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ የአባቶቻችን አምላክ ጌታ ይባረክ። በንጉሡ፥ በአማካሪዎቹና በኃያላን ባለሥልጣኖቹም ሁሉ ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኔ ላይ ዘረጋ፤ እኔም በላዬ ባለችው በእግዚአብሔር እጅ ራሴን አበረታሁ፥ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል አለቆችን ሰበሰብሁ። በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች አለቆች እነዚህ ናቸው ትውልዳቸውም ይህ ነው፤ ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶን፥ ከኢታማር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡሽ፥ ከሽካንያ ልጆች፥ ከፓርዖሽ ልጆች ዘካርያስና፥ ከእርሱም ጋር መቶ ሃምሳ ወንዶች ተመዝግበው ነበር። ከፓሐት ሞዓብ ልጆች የዝራሕያ ልጅ ኤልይሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች፤ ከሽካንያ ልጆች የያሐዚኤል ልጅ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች፤ ከዓዲን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋር ሃምሳ ወንዶች። ከዔላም ልጆች የዓታልያ ልጅ ይሻዕያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች፤ ከሽፋጥያ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች። ከዮአብ ልጆች የይሒኤል ልጅ ዖባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች፤ ከሽሎሚት ልጆች የዮሲፍያ ልጅ፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ስድሳ ወንዶች። ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሀያ ስምንት ወንዶች፤ ከዓዝጋድ ልጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ዐሥር ወንዶች። ከአዶኒቃም ልጆች የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፌሌጥ፥ ይዒኤልና ሽማዕያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች፤ ከቢጉቫይ ልጆች ዑታይና ዛቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም። ወደ አለቆቹም ወደ ኤሊዔዘር፥ አሪኤል፥ ሽማዕያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስ፥ ሜሹላምና እንዲሁም ወደ መምህራኑ ወደ ዮያሪብና ኤልናታን ላክሁ። በካሲፍያ ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ኢዶ ላክኋቸው፥ ለአምላካችን ቤት አገልጋዮችን እንዲያመጡልን በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለኢዶና ለወንድሞቹ ለቤተ መቅደስ አገልጋዮች ምን የሚነግሩአቸውን አስታወቅኳቸው። የአምላካችን መልካም እጅ በላያችን ላይ ስለ ነበረች፥ የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ ከሆነው ከማሕሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሼሬብያን፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን። እንዲሁም ሐሻብያ ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን ይሻዕያና ወንድሞቹንና ልጆቻቸው ሀያ ወንዶች። ዳዊትና ባለሥልጣኖቹ ሌዋውያንን እንዲያገለግሉ ከመረጧቸው የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችን አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየሥማቸው ተጠቅሰዋል። በአምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንድንለምን በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። ንጉሡንም፦ “የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፥ ኃይሉና ቁጣውም እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው” ብለን ተናግረን ነበርና በመንገድ ካለው ጠላት እንዲያድኑን ወታደሮችና ፈረሰኞች ከንጉሡ ለመጠየቅ አፍሬ ነበር። ጾምን፥ አምላካችንን ስለዚህ ነገር ለመንን፤ እርሱም ልመናችንን ሰማ። ከካህናቱ መሪዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሼሬብያን፥ ሐሻብያንና ከእነርሱም ጋር ዐሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤ ንጉሡ፥ አማካሪዎቹ፥ ባለሥልጣናቱ በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ፤ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን የብሩንና፥ የወርቁን፥ የዕቃውንም ስጦታ መዝኜ ሰጠኋቸው። ስድስት መቶ ሃምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፥ አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሀያ የወርቅ ሳሕኖች፥ ሁለት እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩ ከሚያንጸበርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠኋቸው። እኔም አልኋቸው፦ “እናንተ ለጌታ ተቀድሳችኋል፥ ዕቃዎቹም ቅዱስ ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለጌታ በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው፤ በካህናት አለቆች፥ በሌዋውያን በእስራኤል አባቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በጌታ ቤት ክፍሎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።” ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ለመውሰድ ብሩንና ወርቁን ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ። በመጀመሪያው ወር በዓሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ እርሱም ከጠላት እጅና በመንገድ ላይም ከሚሸምቅ አዳነን። ወደ ኢየሩሳሌም ደረስን፥ በዚያም ሦስት ቀን ቆየን። በአራተኛውም ቀን ብሩ፥ ወርቁና ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኡሪያ ልጅ በምሬሞት እጅ ተመዘነ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ። ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባድና የቢኑይ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። በዚያን ሰዓት ሁሉም ነገር ተመዘነ፤ በሚዛንና በቍጥር ም ተመዘገበ። ከእስር የመጡት ከምርኮ የተመለሱት ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ እስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስት አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባት ጠቦቶች፥ ለኃጢአት መሥዋዕት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዝ ማዶ ላሉት ለንጉሡ እንደራሴዎችና ገዢዎች ሰጡ፥ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ። እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው፦ “የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም እንደ ከነዓናውያን፥ ሒቲያውያን፥ ፌርዛውያን፥ ኢያቡሳውያን፥ አሞናውያን፥ ሞዓባውያን፥ ግብጻውያንና አሞራውያን ርኩሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር ሕዝቦች እራሳቸውን አልለዩም፤ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻቸውን ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፥ ቅዱሱንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ አለመታመን የአለቆቹና የባለሥልጣኖቹ እጅ ቀዳሚ ነበር።” ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና ካባዬን ቀደድሁ፥ የራሴን ጠጉርና ጢሜንም ነጨሁ፥ ደንግጬም ተቀመጥሁ። በእስራኤል አምላክ ቃል የሚንቀጠቀጡ ሁሉ ስለ ምርኮኞቹ አለመታመን ወደ እኔ ተሰበሰቡ፥ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ። በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና ካባዬ እንደተቀደደ ከተዋረድኩበት ተነሣሁ፥ በጉልበቴም ተንበርክኬ ወደ ጌታ አምላኬ እጄን ዘረጋሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ “አምላኬ ሆይ፥ አፍሬአለሁ፤ አምላኬ ሆይ፥ ፊቴንም ወደ አንተ ለማንሣት እፈራለሁ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ከፍ ብሏልና፥ በደላችንም ወደ ሰማያት ወጥቷልና። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ በደል ነበርን፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናቶቻችን ለሰይፍ፥ ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተሰጠን። አሁንም ትሩፋን እንዲያስቀርልን፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን እንዲሰጠን፥ አምላካችንም ዓይናችንን እንዲያበራ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን እንዲሰጠን ለጥቂት ጊዜ ከጌታ ከአምላካችን ሞገስ ተሰጥቶናል። ባርያዎች ነን፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፥ የአምላካችንን ቤት እንድንሠራና ፍርስራሾቹን እንድንጠግን መታደስን ሊሰጠን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ግንብ ሊሰጠን በፋርስ ነገሥታት ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኛ ላይ ዘረጋ። ስለዚህ አምላካችን ሆይ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዛትህን ትተናልና፤ በአገልጋዮችህ በነቢያት እንዲህ ስትል ያዘዝኸውን ‘ልትወርሱአት የምትገቡባት ምድር፥ በምድሩ ሕዝቦች ርኩሰት የረከሰች ምድር ናት፤ ከዳር እስከ ዳርም በርኩሰታቸውና በአጸያፊ ተግባራቸው ተሞልታለች። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፥ ሰላማቸውንና ደኅነንታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። ይህም እንድትበረቱ፥ የምድሩንም መልካም ነገር እንድትበሉ፥ ለልጆቻችሁ ለዘለዓለምም ውርስ እንድታወርሱ ነው።’” በክፉ ሥራችንና በታላቁ በደላችን ከደረሰብን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ትሩፋንን ሰጠኸን። ትእዛዝህን ለማፍረስ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም ሕዝቦች ጋር ለመጋባት እንመለሳለንን? አንተስ ትሩፋን የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቆጣምን? የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ እንደ ዛሬው እኛ አምልጠን ቀርተናል፥ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፥ በዚህ ምክንያት በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም። ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት በግንባሩ ወድቆ እያለቀሰ በሚጸልይበትና በሚናዘዝበት ጊዜ፤ ወንዶች፥ ሴቶችና ሕፃናት የሚገኙበት እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፥ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። ከዔላም ልጆች ወገን የነበረ፥ የይሒኤል ልጅ ሽካንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአምላካችን ታማኞች አልሆንም፥ የምድሪቱን ሕዝቦች እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፥ አሁንም ግን በዚህ ነገር ለእስራኤል ተስፋ አለ። ስለዚህ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፥ ሚስቶችን ሁሉ ከእነርሱ የተወለዱትንም እንላካቸው፤ እንደ ጌታዬና በአምላካችን ትእዛዝ እንደሚንቀጠቀጡ ሕዝቦች ምክር፥ እንደ ሕጉም ይደረግ። ተነሥ ይህም ነገር የአንተ ሥራ ነውና፥ እኛም ከአንተ ጋር እንሆናለን፤ በርታ፥ አድርገውም።” ዕዝራም ተነሣ፤ አለቆቹን፥ ካህናቱን፥ ሌዋውያኑንና እስራኤልንም ሁሉ እንደዚህ ቃል እንዲያደርጉ አስማላቸው፥ እነርሱም ማሉ። ዕዝራም ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሣ፥ ወደ ኤልያሺብ ልጅ ወደ ይሆሐናን ክፍል ገባ፤ ስለ ምርኮኞቹ አለመታመን አዝኖ ነበርና በዚያ ገብቶ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ምርኮኞቹ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አዋጅ ነገሩ። በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ሁሉ እንደ አለቆቹና እንደ ሽማግሌዎቹ ምክር ንብረቱ ሁሉ ይወረስ፥ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ ይለይ፤ በሦስት ቀን ውስጥ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። ካህኑ ዕዝራም ተነሣ እንዲህም አላቸው፦ “አልታመናችሁም፥ የእስራኤልን በደል ልታበዙ እንግዶች ሴቶችን አግብታችኋል። ስለዚህ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለጌታ ተናዘዙ፥ ፈቃዱንም አድርጉ፤ እራሳችሁንም ከምድሪቱ ሕዝቦችና ከእንግዶች ሴቶች ለዩ።” ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብለው መለሱ፦ “እንደ ተናገርኸን ማድረግ ይገባናል። ነገር ግን ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ጊዜውም የዝናብ ጊዜ ነው፥ በውጭ ልንቆም አንችልም፥ በዚህ ነገር እጅግ ተላልፈናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። አለቆቻችንም ለጉባኤው ሁሉ ይቁሙ፥ ስለዚህም ነገር የአምላካችን የነደደው ቁጣ ከእኛ እንዲመለስ፥ እያንዳንዳቸው በከተሞቻችን ያሉ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፥ ከእነርሱም ጋር የከተማ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” የዐሣሄል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ያሕዝያ ብቻ ይህን ነገር ተቃወሙ፤ ምሹላምና ሌዋዊውም ሻብታይ ደገፏቸው። ምርኮኞቹም እንዲህ አደረጉ፥ ካህኑ ዕዝራ፥ የአባቶችን መሪዎች መረጠ፤ በየአባቶቻቸው ቤቶች ተለዩ፥ ሁሉም በየስማቸው ተጻፉ፥ በአሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ሊመረምሩ ተቀመጡ። እስከ መጀመሪያው ወር፥ መጀመሪያው ቀን ድረስ እንግዶች ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ። ከካህናቱ ልጆች እንግዶቹን ሴቶች ያገቡ ሰዎች ተገኙ፥ ከዮፃዳቅ ልጅ ከኢያሱ ልጆችና ከወንድሞቹ፥ ማዕሤያ፥ ኤሊዔዜር፥ ያሪብና ግዳልያ፤ ሚስቶቻቸውን ለማሰናበት እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም ከመንጋው አንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ። ከኢሜርም ልጆች፥ ሐናኒና ዝባድያ፤ ከሐሪም ልጆችም፦ ማዕሤያ፥ ኤልያ፥ ሽማዕያ፥ ይሒኤል፥ ዑዚያ፤ ከፓሽሑር ልጆችም፦ ኤልዮዔናይ፥ ማዕሤያ፥ ዪሽማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባድ፥ ኤልዓሣ። ከሌዋውያንም፦ ዮዛባድ፥ ሺምዒ፥ ቅሊጣ የሚባል ቄላያ፥ ፕታሕያ፥ ይሁዳ፥ ኤሊዔዜር። ከመዘምራንም፦ ኤልያሺብ፥ ከበረኞችም፥ ሻሉም፥ ጤሌምና ኡሪ። ከእስራኤልም ከፓርዖሽ ልጆች፦ ራምያ፥ ዪዚያ፥ ማልኪያ፥ ሚያሚን፥ ኤልዓዛር፥ ማልኪያና ብናያስ። ከዔላም ልጆችም፦ ማታንያ፥ ዘካርያ፥ ይሒኤል፥ ዓብዲ፥ የሬሞትና ኤሊያ። ከዛቱ ልጆችም፦ ዔልዮዔያይ፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ ይሬሞት፥ ዛባድ፥ ዓዚዛ። ከቤባይ ልጆችም፦ ይሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዘባይ፥ ዓትላይ። ከባኒ ልጆችም፦ ምሹላም፥ ማሉክ፥ ዓዳያ፥ ያሹብ፥ ሽአል፥ ራሞት። ከፓሐት ሞዓብ ልጆች፦ ዓድና፥ ክላል፥ ብናያስ፥ ማዕሤያ፥ ማታንያ፥ ብጻልኤል፥ ቢኑይና ምናሴ። ከሓሪም ልጆችም፦ ኤሊዔዜር፥ ዪሺያ፥ ማልኪያ፥ ሽማዕያ፥ ስምዖን፥ ብንያም፥ ማሉክና ሽማርያ። ከሐሹም ልጆች፦ ማትናይ፥ ማታታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፌሌጥ፥ ይሬማይ፥ ምናሴ፥ ሺምዒ። ከባኒ ልጆችም፦ ማዕዳይ፥ ዓምራምና ኡኤል፥ ብናያ፥ ቤድያ፥ ክሉሂ ዋንያ፥ ምሬሞት፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ ማትናይና ያዐሦ፥ ባኒ፥ ቢኑይ፥ ሺምዒ፥ ሼሌምያ፥ ናታንና ዓዳያ ማክናድባይ፥ ሻሻይ፥ ሻራይ፥ ዓዛርኤል፥ ሼሌምያሁ፥ ሽማርያ፥ ሻሉም፥ አማርያና ዮሴፍ። ከንቦ ልጆችም፦ ይዒኤል፥ ማቲትያ፥ ዛባድ፥ ዝቢና፥ ያዳይ፥ ዮኤል፥ ብናያ። እነዚህ ሁሉ እንግዶች ሚስቶችን አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ሚስቶች ልጆችን ወልደው ነበር። የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል። በሃያኛው ዓመት በኪስሌው ወር በሱሳ ግንብ ሳለሁ፥ እንዲህ ሆነ፤ ከወንድሞቼ አንዱ ሐናኒ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከይሁዳ መጡ፥ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት የአይሁድ ትሩፋንና ሰለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው። እነርሱም፦ “በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ትሩፋን በታላቅ መከራና በመሰደብ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ። እነዚህን ቃላት በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ። ለብዙ ቀኖች አዘንሁ፤ በሰማይ አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥ እንዲህም አልሁ፦ ታላቅና የተፈራ አምላክ፥ ለሚወድዱትና ትእዛዙን ለሚጠብቁ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የሚጠብቅ፥ የሰማይ አምላክ ጌታ ሆይ፥ እኔ አገልጋይህ ዛሬ በፊትህ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ያድምጥ፥ ዐይኖችህም ይከፈቱ፥ በአንተ ላይ ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዛለሁ፤ እኔና የአባቴ ቤት ኃጢአት አድርገናል። በአንተ ላይ ታላቅ ክፋት ሠርተናል፤ ለአገልጋይህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ሕጎች፥ ትእዛዛትና ፍርድ አልጠበቅንም። ለአገልጋይህ ለሙሴ እንዲህ ብለህ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። “ታማኞች ካልሆናችሁ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ ብትመለሱ ትእዛዛቴን ብትጠብቁ ብትፈጽሟቸውም፥ ከእናንተ ውስጥ የሆኑ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ እንኳ ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜ እንዲኖርበት ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።” እነዚህም በታላቁ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባርያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባርያህን ጸሎት፥ ስምህን በመፍራት የሚደሰቱትን የባርያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬ ለባርያህ እባክህን አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ሞገስን ስጠው። እኔም የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበርኩ። እንዲህም ሆነ በንጉሡ አርታሕሻስት በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር፥ የወይን ጠጅ በፊቱ ነበረ፥ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ከዚህ ቀደም በፊቱ አዝኜ አላውቅም። ንጉሡም፦ “አልታመምክም ታዲያ ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኃዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለኝ። እኔም እጅግ በጣም ፈራሁ። ንጉሡንም እንዲህ አልሁት፦ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ስትፈርስ፥ በሮችዋም በእሳት ሲቃጠሉ ፊቴ ለምን አያዝን?” ንጉሡም፦ “ምን ትፈልጋልህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። ንጉሡንም፦ “ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ አገልጋይህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ መልሼ እንድሠራው የአባቶቼ መቃብር ወዳለበት ከተማ ወደ ይሁዳ እንድትልከኝ ነው” አልሁት። ንግሥቲቱ በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ፦ “መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ሊልከኝ ወደደ፤ እኔም ጊዜውን ወሰኜ ነገርኩት። ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡ መልካም ፈቃዱ ቢሆን፥ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ እንዲያሳልፉኝ ከወንዙ ማዶ ላሉት ገዢዎች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ በቤቱ አጠገብ ላለው ምሽግ በሮች፥ ለከተማው ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይሰጠኝ” አልኩት። ንጉሡም በእኔ ላይ እንዳለችው እንደ አምላኬ መልካም እጅ ሰጠኝ። በወንዙ ማዶ ወዳሉት ገዢዎች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። ንጉሡ ከእኔ ጋር የጦር አለቆችና ፈረሰኞች ልኮ ነበር። ሖሮናዊው ሳንባላጥና አገልጋይ የሆነው አሞናዊው ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደመጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ። ኢየሩሳሌም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ። በሌሊት ተነሣሁ፥ እኔና ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን አምላኬ ለኢየሩሳሌም እንዳደርገው በልቤ ያስቀመጠውን ነገር ለማንም አልተናገርኩም። ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። በሌሊትም በሸለቆው በር ወጣሁ፥ ወደ “የዘንዶ ምንጭ” እና ወደ “የፍግ በር” ሄድኩ፤ የፈረሰውን የኢየሩሳሌምን ቅጥርና በእሳት የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትኩ። ወደ “የምንጭ በር” እና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍኩ፤ ሆኖም ተቀምጬበት የነበረውን እንስሳ አያሳልፈውም ነበር። በሌሊት በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትኩ፤ ተመልሼም በሸለቆው በር ገባሁ፥ ከዚያም ተመለስኩ። ለአይሁድ ወይም ለካህናቱ ወይም ለታላላቆች ወይም ለሹማምቱ ወይም ሥራ ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ስላልተናገርኩ፥ ሹማምንቱ ወዴት እንደ ሄድኩ ወይም ምን እንዳደረግሁ አላወቁም። እኔም፦ “ያለንበትን ችግር፥ ኢያሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” አልኋቸው። መልካም የሆነችው የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ እንደሆነችና ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም፦ “እንነሣና እንሥራ” አሉ። ለመልካም ሥራ እጃቸውን አበረቱ። ሖሮናዊው ሳንባላጥ፥ አገልጋይ የሆነው አሞናዊው ጦብያና ዓረባዊው ጌሻም ይህንን ሰሙ፤ አፌዙብን፤ አንቋሸሹንም፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድነው? በንጉሡ ላይ እያመፃችሁ ነውን?” አሉ። እኔም፦ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም አገልጋዮቹ እንነሳለን፥ እንሠራለንም፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ድርሻ ወይም መብት ወይም መታሰቢያ የላችሁም” ብዬ መለስኩላቸው። ሊቀ ካህኑ ኤልያሺብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው “የበግ በር” ሠሩ፤ ቀደሱት፥ በሩንም አቆሙ፤ እስከ “ሜአ ግንብ” እና እስከ “አሐናንኤል ግንብ” ድረስ ቀደሱት። በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገቡም የኢምሪ ልጅ ዛኩር ሠራ። የስናአ ልጆች “የዓሣ በር” ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ በሮቹን አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም ሠሩ። በአጠገባቸውም የቆጽ ልጅ የኡሪያ ልጅ ሜሬሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የመሼዛቤል ልጅ የቤሬክያ ልጅ ሜሹላም አደሰ። በአጠገባቸውም የባዓና ልጅ ጻዶቅ አደሰ። በአጠገባቸውም ቴቁአውያን አደሱ፤ መኳንንቶቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አልሰጡም ። የፋሴሐ ልጅ ዮያዳ የቤሶዴያ ልጅ ሜሹላም “አሮጌ በር” አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ በሮቹንም አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። በአጠገባቸውም ጊብዖናዊው ሜላጥያ፥ ሜሮኖታዊው ያዶንና ከወንዙ ማዶ ያለው ገዢ ሥር የሆኑት የጊብዖንና የሚጽጳ ሰዎች አደሱ። በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዚኤል አደሰ። በአጠገቡም የሽቶ ቀማሚዎች ልጅ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን አደሱ። በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የሁር ልጅ ሬፋያ አደሰ። በአጠገባቸውም የሐሩማፍ ልጅ ዬዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የሐሻቤኔያ ልጅ ሐጡሽ አደሰ። የሐሪም ልጅ ማልኪያና የፓሐት ሞዓብ ልጅ ሐሹብ ሌላውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” አደሱ። በአጠገባቸውም እሱና ሴት ልጆቹ የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የሆነው የሃሎሔሽ ልጅ ሻሉም አደሰ። ሐኑንና የዛኖሐ ሰዎችም “የሸለቆ በር” አደሱ፤ መልሰው ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጁ፤ ደግሞም እስከ “የፍግ በር” ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ። የቤትሐካሪም አውራጃ ገዢ የሬካብ ልጅ ማልኪያ “የፍግ በር” አደሰ፤ መልሶ ሠራው፥ በሮቹን አቆመ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጀ። የሚጽጳም አውራጃ ገዢ የኮልሖዜ ልጅ ሻሉን “የምንጭ በር” አደሰ፤ መልሶ ሠራው፥ ከደነውም፥ በሮቹን አቆመ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጀ፤ በንጉሡ አትክልት ቦታ አጠገብ ያለውን የሼላሕን መዋኛ ቅጥር ከዳዊት ከተማ ወደ ታች እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር ፊት ለፊት እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራው መዋኛ ስፍራና እስከ ኃያላኑ ቤት ድረስ አደሰ። ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሑም አደሱ። በአጠገቡ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዢ ሐሻብያ ስለ አውራጃው ብሎ አደሰ። ከእርሱም በኋላ ወንድሞቻቸው፥ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዚ የሆነው የሔናዳድ ልጅ ባዋይ አደሱ። በአጠገቡ የሚጽጳ ገዢ የኢያሱ ልጅ ዔዜር በግንቡ መደገፊያ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት መወጣጫ ፊት ለፊት ያለውን ሁለተኛውን ክፍል አደሰ። ከእርሱም በኋላ የዛባይ ልጅ ባሮክ ሌላኛውን ክፍል ከግንቡ መደገፊያ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሺብ ቤት መግቢያ ድረስ በቀናኢነት አደሰ። ከእርሱም በኋላ የቆጽ ልጅ የኡሪያ ልጅ ሜሬሞት ከኤልያሺብ ቤት በር ጀምሮ እስከ ኤልያሺብ ቤት መጨረሻ ድረስ ያለውን ክፍል አደሰ። ከእርሱ በኋላ የአካባቢው ሰዎች ካህናቱ አደሱ። ከእነርሱም በኋላ ብንያምና ሐሹብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የአናንያ ልጅ የማዓሤያ ልጅ አዛርያ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ። ከእርሱም በኋላ የሔናዳድ ልጅ ቢኑይ ከዓዛርያ ቤት ጀምሮ እስከ የግንቡ መደገፊያ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ። የኡዛይ ልጅ ፓላል በግንቡ መደገፊያ ፊት ለፊት ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ፥ ከእርሱም በኋላ የፋኖስ ልጅ ፈዳያ ሠራ። በዖፌል የተቀመጡ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በምሥራቅ በኩል ካለው ከ “የውኃ በር” ፊት ለፊት ጀምሮ እስከ “የወጣው ግንብ” ድረስ አደሱ። ከእርሱም በኋላ ቴቁአውያን ታላቁ “የወጣው ግንብ” ፊት ለፊት ጀምሮ እስከ “ዖፌል ቅጥር” ድረስ ያለውን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከ “የፈረሶች በር” በላይ ጀምሮ በየቤታቸው ትይዩ ያለውን ካህናቱ እያንዳንዳቸው አደሱ። ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ጻዶቅ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ። ከእርሱም በኋላ “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሼካኔያ ልጅ ሼማዔያ አደሰ። ከእርሱ በኋላ የሼሌምያ ልጅ ሐናንያና የጻላፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኑን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከእርሱ በኋላ የቤሬክያ ልጅ ሜሹላም ከክፍሉ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ። ከእርሱም በኋላ የወርቅ አንጥረኛው ልጅ ማልኪያ ከ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ቤት፥ የነጋዴዎቹ ቤት ጀምሮ እስከ “የመሰብሰቢያ በር” ፊት ለፊት ያለውንና እስከ ማዕዘኑ ላይኛው ክፍል ድረስ አደሰ። ከማዕዘኑ ላይኛው ክፍል ጀምረው እስከ “የበግ በር” ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ። ሳንባላጥ ቅጥሩን እየሠራን እንደሆነ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድ ላይም አፌዘ። በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊት ፊት፦ “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን እየሠሩ ነው? ለራሳቸው መልሰው እየገነቡ ነው? መሥዋዕትን ሊያቀርቡ ነው? በአንድ ቀንስ ይጨርሱታል? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ሊያድኑት ነው?” አለ። አሞናዊው ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ ነበር፥ እንዲህም አለ፦ “የሚገነቡት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢወጣበት የድንጋይ ግንባቸውን ያፈርሰዋል፤” አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው። በደላቸውን አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ ሠራተኞችን በፊታቸው አስቆጥተዋቸዋልና። ቅጥሩን ሠራን፤ የሕዝቡ ልብ ለሥራ ስለተነሣሣ ቅጥሩ ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ። ሳንበላጥ፥ ጦብያ፥ ዓረባውያን፥ አሞናውያንና አሽዶዳውያን የሚታደሰው የኢየሩሳሌም ቅጥር ከፍ እያለ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም እየተጠገነ እንደሆነ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ። መጥተው ኢየሩሳሌምን ሊወጉና ሊሸብሩ ሁሉም በአንድነት አሴሩ። ወደ አምላካችን ጸለይን፥ በእነርሱም ምክንያት በሌሊትና በቀን በእነሱ ላይ ጠባቂ አቆምን። ይሁዳም፦ “የተሸካሚዎች ኃይል ደክሟል፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩን መሥራት አንችልም” አለ። ጠላቶቻችንም፦ “በመካከላቸው እስክንገባና እስክንገድላቸው ድረስ፥ ሥራቸውንም እስክናስተጓጉል ድረስ አያውቁም፥ አያዩምም” አሉ። በአጠገባቸው የተቀመጡ አይሁድ መጥተው፦ “ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል” ብለው ዐሥር ጊዜ ነገሩን። እኔም ከቅጥሩ በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ ጦራቸውንና ቀስታቸውን አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኳቸው። አየሁና ተነሣሁ፥ መኳንንቶቹን፥ ሹማምቱንና የተቀረው ሕዝብ፦ “አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስታውሱ፥ ስለ ወንድሞቻችሁ፥ ስለ ወንዶች ልጆቻች፥ ስለ ሴቶች ልጆቻችሁ፥ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤቶቻችሁ ተዋጉ።” አልኳቸው። እንዲህም ሆነ፥ ጠላቶቻችን በእኛ ዘንድ እንደታወቀ፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው በሰሙ ጊዜ፥ እኛ ሁላችንም ወደ ቅጥሩ፥ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። ከዚያን ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ጎልማሶች ሥራ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጋሻ፥ ጦር፥ ቀስትና ጥሩር ይይዙ ነበር፤ ሹማምቱም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። ቅጥሩን የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ፥ በአንድ እጃቸው ደግሞ የጦር መሣሪያ ይይዙ ነበር። እያንዳንዱ ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋውም በአጠገቤ ነበረ። መኳንንቱን፥ ሹማምቱንና የቀሩትን ሕዝብ እንዲህ አልኋቸው፦ “ሥራው ብዙና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ አንዱ ከሌላው ርቆ ተለያይተናል፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ በምትሰሙበት ስፍራ በዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።” እኛ ሥራውን ሠራን፤ እኩሌቶቹ ደግሞ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ ጦር ይይዙ ነበር። እንዲሁም ደግሞ በዚያ ጊዜ ሕዝቡን፦ “በሌሊት ጠባቂዎች፥ በቀንም ሥራ እንዲሰሩልን እያንዳንዱ ከአገልጋዩ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ ይደር፤” አልኋቸው። እኔ፥ ወንድሞቼ፥ ጎበዛዝቶቼና ከኋላዬ የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር። ወደ ውኃም ስንሄድ እያንዳንዱ መሣሪያውን ይዞ ይሄድ ነበር። የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት በወንድሞቻቸው በአይሁድ ላይ ትልቅ ሆነ። እንዲህ የሚሉ ነበሩ፦ “እኛ፥ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ብዙ ነን፤ እንድንበላና በሕይወት እንድንኖር እህልን እንውሰድ” እንዲህ የሚሉም ነበሩ፦ “በራቡ ጊዜ እህል እንድንወስድ እርሻችን፥ የወይን ቦታችንንና ቤታችንን አስይዘናል” እንዲህ የሚሉ ደግሞ ነበሩ፦ “ለንጉሡ ግብር ለመክፈል እርሻችንንና የወይን ቦታችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ባርያዎች እንዲሆኑ ለማምጣት ተገደናል፥ አንደንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም ለባርነት ተወስደዋል፤ እርሻችንና የወይን ቦታችን ለሌሎች ስለሆነ ኃይል በእጃችን የለም ።” እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን ቃላት በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቆጣሁ። በልቤም አሰብሁና መኳንንቶቹንና ሹማምቱን ተከራከርኋቸው፥ እንዲህም አልኋቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ለወንድማችሁ በአራጣ ታበድራላችሁ”፤ ትልቅ ጉባኤም ሰበሰብሁባቸው። እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “ለአሕዛብ የተሸጡትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን ተቤዠን፥ እናንተ ደግሞ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ? እነርሱስ ለእኛ ይሸጣሉን? እነርሱም ዝም አሉ፥ የሚመልሱትንም ቃል አጡ። እንዲህም አልኳቸው፦ የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት መሄድ አይገባችሁምን? እኔ፥ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ ገንዘብና እህል አበድረናቸዋል፤ ይህን አራጣ ግን እባካችሁ እንተወው። በብድር የያዛችሁትን እርሻቸውን፥ የወይን ቦታቸውን፥ ወይራቸውን፥ ቤታቸውን፥ ከመቶ አንድ የወሰዳችሁትን ብር፥ እህሉን፥ አዲሱን ወይን ጠጅና ዘይት እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።” እነርሱም፦ “እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንፈልግም፤ አንተ እንዳልኸው እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ ቃል እንደገቡት እንዲያደርጉ አስማልኳቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፦ “ይህን ቃል የማይፈጽመውን ሰው እግዚአብሔር ከቤቱና ከንብረቱ እንደዚሁ ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፦ “አሜን” አሉና ጌታን አመሰገኑ፤ ሕዝቡ ቃል ኪዳኑ አደረጉ። በይሁዳ ምድር ላይ ገዢ እንድሆን ከተሾምሁበት፥ ከንጉሡ አርታሕሻስት ከሀያኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ የንጉሡን ምግብ አልበላንም። ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞ ገዢዎች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደውባቸው ነበር፥ ምግብ፥ ወይና አርባ ሰቅል ብር ከእነሱ ይወስዱ ነበር፤ አገልጋዮቻቸው ደግሞ ሕዝቡን ይጨቁኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። በተጨማሪም ለዚህ የቅጥር ሥራ እራሴን ሰጠሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ። በዙሪያችን ካሉት፥ ወደ እኛ ከመጡት አሕዛብ ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ። ለአንድ ቀን ይሠራ የነበረው አንድ በሬ፥ ስድስት የተመረጡ በጎች ነበር፤ ዶሮዎችም ይዘጋጁልኝ ነበር፥ በየዐሥር ቀኑም ብዛት ያለው ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ይህም ሆኖ ግን የንጉሡን ምግብ አልሻም ነበር በዚህ ሕዝብ ላይ ሥራው ከብዶ ነበርና። አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያድረግሁትን ሁሉ ለመልካምነት አስብልኝ። እንዲህም ሆነ ምንም እንኳ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን ባልገጥምም ቅጥሩን እንደሠራሁ፥ አንድም የፈረሰ እንዳልቀረ ሰንባላጥ፥ ጦቢያና ዓረባዊው ጌሼም የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፥ ሰንባላጥና ጌሼም እንዲህ ብለው ላኩብኝ፦ “ናና በኦኖ ሜዳ ባሉት መንደሮች እንገናኝ፤” ነገር ግን ክፉ ሊያደርሱብኝ አቅደው ነበር። እኔም እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው፦ “ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ መውረድም አልችልም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ሥራው ለምን ይቆማል?” ይህንኑ ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም ይህንኑ ቃል መለስኩላቸው። ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ የተከፈተ ደብዳቤ በእጁ አስይዞ ይህንኑ ቃል በአገልጋዩ ለአምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤ በውስጡ የተጻፈውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተና አይሁድ ልታምጹ እንዳቀዳችሁ፥ ለዚህም ቅጥሩን እንደሠራህ፥ ንጉሣቸውም ልትሆን እንደምትፈልግ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል ጌሼምም ብሎታል። ‘ንጉሥ በይሁዳ አለ’ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም እንዲናገሩ ነቢያትን ሾመሃል፤ አሁንም ይህን ነገር በንጉሡ ዘንድ ይሰማል፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።” እኔም እንዲህ ብዬ ላክሁበት፦ “አንተ ከምትለው ነገር አንድም አልተደረገም፥ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋልና” ሁሉም እንዲህ እያሉ አስፈራሩን፦ “ከሥራው እጃቸውን ያላላሉ፥ አይሠራምም” አሁንም እጄን አበርታ ። እኔም ወደ ሜሔጣብኤል ልጅ፥ ወደ ዴላያ ልጅ፥ ወደ ሼማዕያ ቤት ሄድሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና፦ “በእግዚአብሔር ቤት፥ በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፥ የመቅደሱንም በሮች እንዝጋ፤ ሊገድሉህ ይመጣሉና፥ በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉና” አለ። እኔም፦ “እንደ እኔ ያለ ሰው ይሸሻልን? እንደ እኔ ያለ ነፍሱን ሊያድን ወደ መቅደስ የገባ ማን አለ? አልገባም” አልሁ። እነሆ እግዚአብሔር እንዳልላከው አወቅሁ፥ በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦቢያና ሰንባላጥ ገዝተውት ስለ ነበረ ነው። ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ። አምላኬ ሆይ፥ ጦቢያን፥ ሰንባላጥን ስለዚህ ሥራቸው ደግሞም ሊያስፈራሩኝ ነቢያቱን ኖዓድያና የተቀሩት ነቢያትን አስብ። ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ። እንዲህም ሆነ፦ ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ ዓይናቸውም እያየ ብዙ ውድቀት ሆነ፥ ይህ ሥራ በአምላካችን እንደ ተከናወነ አወቁ። ደግሞም በእነዚያ ቀኖች የይሁዳ መኳንንቶች ብዙ ደብዳቤዎቻቸውን ወደ ጦቢያ ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር። በይሁዳ ለእርሱ የማሉለት ብዙ ሰዎች ነበሩና፤ የአራሕ ልጅ የሼካንያ አማች ነበረና፥ ልጁ ይሆሐናንም የቤራክያን ልጅ የሜሹላምን ሴት ልጅ አግብቷልና። በተጨማሪም መልካም ሥራውን በፊቴ ይናገሩ ነበር፥ እኔ ያልሁትንም ለእርሱ ይነግሩት ነበር፤ ጦቢያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር። እንዲህም ሆነ ቅጥሩ ከተሠራ በኋላ፥ በሮቹን ካቆምሁ በኋላ፥ በር ጠባቂዎች፥ መዘምራንና ሌዋውያን ተሾሙ፤ ወንድሜን ሐናኒንና የምሽጉ አዛዥ ሐናንያን በኢየሩሳሌም ላይ ኀላፊነት ሰጠኋቸው፤ እርሱም እውነተኛና ከሌሎች ይልቅ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበረ። እኔም እንዲህ አልኋቸው፦ የኢየሩሳሌም በሮች ፀሐይ ሞቅ እስኪል ድረስ አይከፈቱ፥ በሚቆሙበት ጊዜ በሮቹን ይዝጉ፥ ይቆልፉትም፤ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አንዳንዱን በተራው አንዳንዱን ደግሞ በየቤቱ አጠገብ ጠባቂዎች ይሾሙ። ከተማይቱ ሰፊና ታላቅ ነበረች፤ በውስጧ የነበሩ ሕዝብ ግን ጥቂቶች ነበሩ፤ ቤቶችም አልተሠሩም ነበር። አምላኬም መኳንንቱን፥ ሹማምቱንና ሕዝቡን ሰብስቤ እንድቆጥራቸው በልቤ አስቀመጠ፤ አስቀድመው የመጡትን ሰዎች የትውልድ መጽሐፋቸውን አገኘሁ፥ በእርሱም እንደዚህ ተጽፎ አገኘሁ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ ገዛ ከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው። ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከዓዛርያ፥ ከራዓምያ፥ ከናሐማኒ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከቢልሻን፥ ከሚስፌሬት፥ ከቢግዋይ፥ ከኔሑም፥ ከባዓና ጋር የመጡ የእስራኤል ሕዝብ የሰዎች ቍጥር ይህ ነው። የፓርዖሽ ልጆች፥ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሁለት። የሽፋጥያ ልጆች ሦስት መቶ ሰባ ሁለት። የአራሕ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት። ከኢያሱና ከዮአብ ልጆች የሆኑ የፓሐት ሞዓብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ዐሥራ ስምንት። የዔላም ልጆች፥ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። የዛቱ ልጆች፥ ስምንት መቶ አርባ አምስት። የዛካይ ልጆች፥ ሰባት መቶ ስድሳ። የቢኑይ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ስምንት። የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ስምንት። የዓዝጋድ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሀያ ሁለት። የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት። የቢግዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስድሳ ሰባት። የዓዲን ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ አምስት። የሕዝቅያስ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት። የሐሹም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ ስምንት። የቤጻይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ አራት። የሐሪፍ ልጆች፥ መቶ ዐሥራ ሁለት። የገባዖን ልጆች፥ ዘጠና አምስት። የቤተ ልሔምና የነጦፋ ሰዎች፥ መቶ ሰማንያ ስምንት። የዓናቶች ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት። የቤትዓዝማዌት ሰዎች፥ አርባ ሁለት። የቂርያትይዓሪም፥ የከፊራና የብኤሮት ሰዎች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት። የራማና የጌባዕ ሰዎች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ። የሚክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት። የቤቴኤልና የዓይ ሰዎች፥ መቶ ሃያ ሦስት። የሌላኛው ነቦ ሰዎች፥ አምሳ ሁለት። የሌላኛው ዔላም ልጆች ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። የሐሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ። የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት። የሎድ፥ የሐዲድና የኦኖ ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አንድ። የሰናአ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ። ካህናቱ፥ የኢያሱ ቤት የይዳዕያ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት። የኢሜር ልጆች፥ አንድ ሺህ አምሳ ሁለት። የፓሽሑር ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት። የሐሪም ልጆች፥ ሺህ ዐሥራ ሰባት። ሌዋውያኑ፥ የሆድዋ ወገን የኢያሱና የቃድሚኤል ልጆች፥ ሰባ አራት። መዘምራኑ፥ የአሳፍ ልጆች፥ አንድ መቶ አርባ ስምንት። በር ጠባቂዎች፥ የሻሉም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጣልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሾባይ ልጆች፥ አንድ መቶ ሠላሳ ስምንት። የቤተ መቅደስ አገልጋዮች የጺሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥ የጣባዖት ልጆች፥ የቄሮስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፥ የፓዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥ የሐጋባ ልጆች፥ የሻልማይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥ የጊዴል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥ የረአያ ልጆች፥ የረጺን ልጆች፥ የነቆዳ ልጆች፥ የጋዛም ልጆች፥ የዑዛ ልጆች፥ የፓሴሐ ልጆች፥ የቤሳይ ልጆች፥ የምዑኒም ልጆች፥ የነፉሽሲም ልጆች፥ የባቅቡቅ ልጆች፥ የሐቁፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥ የባጽሊት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥ የሐርሻ ልጆች፥ የባርቆስ ልጆች፥ የሲስራ ልጆች፥ የታማሕ ልጆች፥ የንጺሐ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች። የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች፤ የሶጣይ ልጆች፥ የሶፌሬት ልጆች፥ የፕሪዳ ልጆች፥ የያዕላ ልጆች፥ የዳርቆን ልጆች፥ የጊዴል ልጆች፥ የሽፋጥያ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፖኬሬት ሃፅባይም ልጆች፥ የአሞን ልጆች። የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ሁሉና የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ። ከቴልሜላሕ፥ ከቴል ሀርሻ፥ ከክሩብ፥ ከአዶንና ከኢሜር የወጡ እነዚህ ናቸው፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤትና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ማስረዳት አልቻሉም፤ የድላያ ልጆች፥ የጦቢያ ልጆች፥ የንቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት። ከካህናቱም የሐባያ ልጆች፥ የሃቆጽ ልጆች፥ የባርዚላይ ልጆች እሱም ከገለዓዳዊው የባርዚላይ ሴቶች ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስማቸውም የተጠራ ነው። እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፥ ነገር ግን አልተገኘም፤ ከክህነትም ተከለከሉ። ገዢውም ፦ በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ደረስ ከተቀደሰው ነገር እንዳይበሉ ነገራቸው። ጉባኤው ሁሉ አንድ ላይ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበር፥ ከወንድ አገልጋዮቻቸውና ከሴት አገልጋዮቻቸው ሌላ፥ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ነበሩ፥ ሁለት መቶ አርባ አምስት ወንዶችና ሴቶች መዘምራንም ነበሩአቸው። ግመሎቻቸው አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸው ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ። ከአባቶች አለቆች ለሥራው ስጦታ ሰጡ። አገረ ገዢውም አንድ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ አምሳ ድስቶች፥ አምስት መቶ ሠላሳ የካህናት ልብስ ለግምጃ ቤት ሰጠ። የአባቶች አለቆች ለሥራው ለግምጃ ቤት ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ምናን ብር ሰጡ። የቀሩት ሕዝብ የሰጡት ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክና ሁለት ሺህ ምናን ብርና ስድሳ ሰባት የካህናት ልብስ ነበረ። ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ በር ጠባቂዎቹ፥ መዘምራኑ፥ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና እስራኤልም ሁሉ በገዛ ከተሞቻቸው ተቀመጡ፥ ሰባተኛውም ወር መጣ የእስራኤል ልጆችም በገዛ ከተሞቻቸው ተቀምጠው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፤ ጌታ ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ እንዲያመጣ ለጸሐፊው ለዕዝራ ነገሩት። ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን ወንዶች፥ ሴቶችና አስተውለው መስማት የሚችሉ ባሉበት በጉባኤው ሁሉ ፊት አመጣው። በውኃው በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ ወንዶች፥ ሴቶች፥ የሚያስተውሉም ባሉበት፥ ከማለዳ ጀመሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው፤ የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ በጽሞና ያደምጥ ነበር። ጸሐፊውም ዕዝራ ለዚህ ተብሎ በተሠራ የእንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡ ማቲትያ፥ ሼማዕ፥ ዓናያ፥ ኡሪያ፥ ሒልቅያና ማዓሴያ በቀኙ በኩል፤ ፐዳያ፥ ሚሻኤል፥ ማልኪያ፥ ሐሹም፥ ሐሽባዳና፥ ዘካርያስ፥ ሜሹላም በግራው በኩል ቆመው ነበር። ዕዝራም ከሕዝቡ ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ነበርና በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ፊት መጽሐፉን ከፈተ፤ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። ዕዝራም ታላቁን አምላክ ጌታን ባረከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በመዘርጋት፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውን አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። ደግሞ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ሼሬብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሻብታይ፥ ሆዲያ፥ ማዓሤያ፥ ቅሊጣ፥ አዛርያ፥ ዮዛባድ፥ ሐናን፥ ፐላያና ሌዋውያኑ ሕጉን ለሕዝቡ ያስረዱ ነበር፤ ሕዝቡም በቆሙበት ነበሩ። በመጽሐፉ ያለውን የእግዚአብሔርን ሕግ በግልጽ አነበቡ፥ የተነበበው እንዲገባቸውም ያስረዷቸው ነበር። ገዢው ነህምያ፥ ጸሐፊው ካህኑ ዕዝራ፥ ሕዝቡን የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ “ይህ ቀን ለጌታ አምላካችሁ ቅዱስ ነው፤ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ” አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። እርሱም፦ “ሂዱ፥ የሰባውን ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያ ምንም ላልተዘጋጀላቸው ድርሻቸውን ላኩ፤ ይህ ቀን ለጌታችን ቅዱስ ነውና፤ አትዘኑ የጌታ ደስታ ኃይላችሁ ነውና” አላቸው። ሌዋውያንም፦ “ቀኑ ቅዱስ ነውና ዝም በሉ፥ አትዘኑም” እያሉ ሕዝቡን ሁሉ ዝም አሰኙት። ሕዝቡም ሁሉ ሊበሉ፥ ሊጠጡ፥ ለሌላቸው ድርሻቸውን ሊልኩና ታላቅ ደስታ ሊያደርጉ ሄዱ፤ የተነገራቸውን ቃል ማስተዋል ችለው ነበርና። በሁለተኛው ቀን ከሕዝቡ ሁሉ አለቆች የሆኑ አባቶች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል እንዲተረጉምላቸው ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። በሰባተኛው ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ እንዲቀመጡ ጌታ በሙሴ በኩል ያዘዘውን በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ በከተሞቻቸው ሁሉና በኢየሩሳሌምም፦ “እንደተጻፈው ዳሶችን ለመስራት ወደ ተራራ ውጡ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ፥ የባርሰነት፥ የዘንባባና የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ” ብለው ይናገሩና ያውጁ። ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱ በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በየግቢያቸው፥ በእግዚአብሔር ቤት ግቢ፥ በ “ውኃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳሶችን ሠሩ። ከምርኮ የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳሶችን ሠሩ፥ በዳሶቹም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ ነገር አድርገው አያውቁም ነበርና። እጅግ ታላቅ ደስታም ሆነ። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕዝራ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛው ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ። በዚሁ ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰውና በላያቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ተሰበሰቡ። የእስራኤል ዘር ከባዕድ ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ። በየስፍራቸውም ቆመው የጌታ አምላካቸውን የሕግ መጽሐፍ የቀኑ ሩብ ያህል አነበቡ፥ የቀኑ ሩብ ደግሞ እየተናዘዙና፥ ለጌታ አምላካቸው እየሰገዱ አሳለፉ። በሌዋውያኑ መድረክ ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድምኤል፥ ሽባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ ቆመው ወደ ጌታ አምላካቸው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፥ ቃድምኤል፥ ባኒ፥ ሐሻብንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሽባንያ፥ ፕታሕያ እንዲህ አሉ፦ “ቁሙ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጌታ አምላካችሁን ባርኩ። ከበረከትና ከምስጋና ሁሉ በላይ ከፍ ያለው የክብርህን ስም ይባርኩ። አንተ ብቻህን ጌታ ነህ፥ ሰማይንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርሷ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጠርህ፥ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አብራምን የመረጥህ፥ ከከለዳውያን ኡር የአወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም ያልኸው፥ አንተ ጌታ አምላክ ነህ። ልቡም በፊትህ ታማኝ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውን፥ የኬጢያዊው፥ የአሞራዊውን፥ የፌርዛዊውን፥ የኢያቡሳዊውንና የጌርጌሳዊውን ምድር ለዘሩ ልትሰጥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።” “በግብጽ የአባቶቻችንን መከራ አየህ፥ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ፤ በፈርዖን፥ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፤ በእነርሱ ላይ መታበያቸውን አውቀህ ነበርና፥ እስከ ዛሬም እንዳለው ለራስህ ስምን ሠራህ። በፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ አሳዳጆቻቸውን ግን በኃይለኛ ውኃ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። በሚሄዱበትን መንገድ ልታበራላቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ መራሃቸው። በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅን ፍርዶችን፥ ታማኝ ሕጎችን፥ መልካም ሥርዓቶችና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። ቅዱስ ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዞችን፥ ሥርዓቶችንና ሕግን በባርያህ በሙሴ በኩል አዘዝሃቸው። ለረኃባቸው ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው ወደ ማልክላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ነገርካቸው።” “እነርሱና አባቶቻችን ግን ታበዩ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ ትእዛዞችህንም አልሰሙም፤ ለመስማትም እንቢ አሉ፥ በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት አላስታወሱም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፥ ቸር፥ ርኅሩኅ፥ ለቁጣ የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ፥ አልተውካቸውምም።” ከቀለጠ ብረት የተቀረጸ ጥጃ ሠርተው “ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” አሉ፥ ብዙ ተሳደቡ፥ አንተ ግን ከርኅራኄህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውካቸውም፤ በመንገድ እንዲመራቸው የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ እንዲያበራላቸው የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልተለየም። እንዲያስተምራቸው መልካሟን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህን ከአፋቸው አልከለከልክም፥ ለጥማታቸውም ውኃን ሰጠሃቸው። አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብካቸው፤ ምንም አላጡም፤ ልብሳቸው አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም። “መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ እንዲገቡና እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ወደ ነገርሃቸው ምድር አገባሃቸው። ልጆቹም ገብተው ምድሪቷን ወረሱ፤ የምድሪቱን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው ደመሰስካቸው፥ የወደዱትን ነገር እንዲያደረጉባቸው ከነገሥታቶቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጉድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።” “ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቆጡህ። ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውካቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥ ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፥ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፥ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርክባቸው፥ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውካቸውምም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነብዮቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባርያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርሷ ባርያዎች ነን፥ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።” በዚህም ሁሉ የታመነውን ቃል ኪዳን አድርገን እንጽፋለን፤ መሪዎቻችን፥ ሌዋውያኖቻችንና ካህናቶቻችን ያትሙበታል። ያተሙትም እነዚህ ናቸው፤ የሐካልያ ልጅ ገዢው ነህምያ፥ ጺድቂያ፥ ሠራያ፥ አዛርያ፥ ኤርምያስ፥ ፓሽሑር፥ አማርያ፥ ማልኪያ፥ ሐጡሽ፥ ሽባንያ፥ ማሉክ፥ ሐሪም፥ ምሬሞት፥ አብድዩ፥ ዳንኤል፥ ጊንቶን፥ ባሩክ ሜሹላም፥ አቢያ፥ ሚያሚን፥ ማዓዝያ፥ ቢልጋይ፥ ሽማዕያ፤ እነዚህ ካህናት ነበሩ። ሌዋውያኑ ደግሞ፦ የአዛንያ ልጅ ኢያሱ፥ ከሔናዳድ ልጆች ቢኑይ፥ ቃድሜል፥ ወንድሞቻቸው ሽባንያ፥ ሆዲያ፥ ቅሊጣ፥ ፕላያ፥ ሐናን፥ ሚካ፥ ርሖብ፥ ሐሻብያ፥ ዛኩር፥ ሼሬብያ፥ ሽባንያ፥ ሆዲያ፥ ባኒ፥ ብኒኑ። የሕዝቡ መሪዎች፦ ፓርዖሽ፥ ፓሓት ሞዓብ፥ ዔላም፥ ዛቱ፥ ባኒ፥ ቡኒ፥ ዓዝጋድ፥ ቤባይ፥ አዶኒያ፥ ቢግዋይ፥ ዓዲን፥ አጤር፥ ሕዝቅያስ፥ ዓዙር፥ ሆዲያ፥ ሐሹም፥ ቤጻይ፥ ሐሪፍ፥ ዓናቶት፥ ኖባይ፥ ማግፒዓሽ፥ ምሹላም ሔዚር፥ ምሼዛብኤል፥ ጻዶቅ፥ ያዱዓ፥ ፕላጥያ፥ ሐናን፥ ዓናያ፥ ሆሴዕ፥ ሐናንያ፥ ሓሹብ፥ ሃሎሔሽ፥ ፒልሐ፥ ሾቤቅ፥ ርሁም፥ ሐሻብና፥ ማዓስያ አሒያ፥ ሐናን፥ ዓናን፥ ማሉክ፥ ሐሪም፥ ባዓና። የቀሩት ሕዝብ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ በር ጠባቂዎቹ፥ መዘምራን፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች፥ ከምድር ሕዝቦች ወደ እግዚአብሔር ሕግ ራሳቸውን የለዩ ሁሉ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው፥ የሚያውቁትና የሚያስተውሉት ሁሉ፥ ከወንድሞቻቸውና ከመኳንንቶቻቸው ጋር በመሆን በእግዚአብሔር ባርያ በሙሴ እጅ በተሰጠው በእግዚአብሔር ሕግ ለመሄድ፥ የጌታ አምላካችንን ትእዛዞቹን ሁሉ፥ ፍርዶቹንና ሥርዓቶቹን ለመጠበቅና ለማድረግ ወደ እርግማንና መሐላ ገቡ ። ሴቶች ልጆቻችንን ለምድሪቱ ሕዝቦች አንሰጥም፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችን አንወስድም፤ የምድሪቱ ሕዝቦች ሸቀጥ ወይም ልዩ ልዩ እህል ለመሸጥ በሰንበት ቀን ቢያመጡ፥ በሰንበት ወይም በተቀደሰ ቀን ከእነርሱ አንገዛም፤ በሰባተኛው ዓመትም ምድሪቱን እናሳርፋታለን፥ ዕዳንም ሁሉ እንሰርዛለን። ለአምላካችን ቤት አገልግሎት የሚውል አንድ ሦስተኛ ሰቅል በየዓመቱ ለመስጠት በራሳችን ላይ ትእዛዝ እናስቀምጣለን። ስለ ገጸ ኅብስትም፥ ዘወትርም በሰንበትና በመባቻ ስለ ማቅረብ ስለ እህሉ ቁርባንና ስለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ በዓላትም፥ ስለ ተቀደሱትም ነገሮች፥ ለእስራኤልም ስለሚያስተሰርየው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት፥ ስለ አምላካችንም ቤት ሥራ ሁሉ በየዓመቱ የሰቅል ሢሶ እናመጣ ዘንድ ትእዛዝ በራሳችን ላይ አደረግን። እኛም፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ ሕዝቡም፥ እንደ አባቶቻችን ቤቶች በተወሰነ ጊዜ በየዓመቱ ወደ አምላካችን ቤት አምጥተን በሕጉ እንደ ተጻፈ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይቃጠል ዘንድ ስለ እንጨት ቁርባን ዕጣ ተጣጣልን፥ በየዓመቱም የመሬታችንን በኵራት የሁሉ ዓይነት ዛፍ የፍሬ ሁሉ በኵራት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት እናመጣ ዘንድ፥ በሕጉም እንደ ተጻፈ የልጆቻችንና የእንስሶቻችንን በኵራት፥ የበሬዎቻችንንና የበጎቻችንን በኵራት፥ በአምላካችን ቤት ወደ ሚያገለግሉት ካህናት ወደ አምላካችን ቤት እናመጣ ዘንድ፥ የእህላችንንም በኵራት፥ የእጅ ማንሣታችንን ቁርባን፥ የዛፍ ሁሉ ፍሬ፥ ወይኑንና ዘይቱንም ወደ ካህናቱ ወደ አምላካችን ቤት ጓዳዎች እናመጣ ዘንድ፥ ሌዋውያኑም ከከተሞቻችን እርሻ ሁሉ አሥራት ይቀበላሉና የመሬታችንን አሥራት ወደ ሌዋውያን እናመጣ ዘንድ ማልን። ሌዋውያኑም አሥራቱን በተቀበሉ ጊዜ የአሮን ልጅ ካህኑ ከሌዋውያን ጋር ይሁን፥ ሌዋውያኑም የአሥራቱን አሥራት ወደ አምላካችን ቤት ወደ ጓዳዎች ወደ ዕቃ ቤት ያምጡት። የእስራኤል ልጆችና የሌዊ ልጆችም የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም የማንሣት ቁርባንን የመቅደሱ ዕቃዎችና የሚያገለግሉት ካህናት በረኞቹና መዘምራኑ ወዳሉባቸው ጓዳዎች ያግቡት፥ እንዲሁም የአምላካችንን ቤት ከቶ አንተውም። የሕዝቡ መሪዎች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፤ ከቀረው ሕዝብ ከአሥሩ አንዱ እጅ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፥ የቀሩት ዘጠኙ ደግሞ በሌሎች ከተሞች እንዲቀመጡ ዕጣ ተጣጣሉ። ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ለመኖር በፈቃደኝነት ራሳቸውን የሰጡትን ሰዎች ሁሉ ባረኩ። በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የአውራጃው መሪዎች እነዚህ ናቸው፤ እስራኤል፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች እያንዳንዱ በየርስቱና በየከተማቸው በይሁዳ ከተሞች ኖሩ። ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች የተወሰኑት በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። ከይሁዳ ልጆች፦ ከፋሬስ ልጆች የማሃላልኤል ልጅ፥ የሽፋጥያ ልጅ፥ የአማርያ ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የዑዚያ ልጅ ዓታያ፤ የሺሎናዊው ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ የዮያሪብ ልጅ፥ የዓዳያ ልጅ፥ የሐዛያ ልጅ፥ የኮልሖዜ ልጅ፥ የባሩክ ልጅ ማዓሤያ። በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የፋሬስ ልጆች ሁሉ አራት መቶ ስድሳ ስምንት ኃያላን ነበሩ። የብንያምም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የይሻዕያ ልጅ፥ የኢቲኤል ልጅ፥ የማዓሤያ ልጅ፥ የቆላያ ልጅ፥ የፕዳያ ልጅ፥ የዮዔድ ልጅ የምሹላም ልጅ ሳሉ። ከእርሱም በኋላ ጋባይ፥ ሳላይ፥ ዘጠኝ መቶም ሀያ ስምንት። አለቃቸውም የዚክሪ ልጅ ኢዮኤል ነበር፤ የሃስኑአ ልጅ ይሁዳ ደግሞ በከተማው ላይ ሁለተኛ የተሾመ ነበረ። ከካህናቱ፦ የዮያሪብ ልጅ ይዳዕያ፥ ያኪን፥ የእግዚአብሔር ቤት አለቃ የአሒጡብ ልጅ የምራዮት ልጅ፥ የጻዶቅ ልጅ የምሹላም ልጅ፥ የሒልቂያ ልጅ ሥራያ፥ የቤቱን ሥራ የሠሩ ወንድሞቻቸው ስምንት መቶ ሀያ ሁለት፤ የማልኪያ ልጅ፥ የፓሽሑር ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የአምጺ ልጅ፥ የፍላልያ ልጅ፥ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፥ ወንድሞቹ የአባቶች መሪዎች ሁለት መቶ አርባ ሁለት፤ የኢሜር ልጅ፥ የምሺሌሞት ልጅ፥ የአሕዛይ ልጅ፥ የዓዛርኤል ልጅ ዓማሽሳይ፥ ወንድሞቻቸው መቶ ሀያ ስምንት ጽኑዓን ኃያላን፤ አለቃቸውም የሃግዶሊም ልጅ ዛብዲኤል ነበረ። ከሌዋውያንም የቡኒ ልጅ፥ የሐሻብያ ልጅ፥ የዓዝሪቃም ልጅ፥ የሐሹብ ልጅ ሽማዕያ፤ ከእግዚአብሔር ቤት በውጭ በነበረው ሥራ ላይ የነበሩ የሌዋውያን አለቆች ሻብታይና ዮዛባድ፤ ምስጋናውን በጸሎት ለመጀመር መሪ የነበረው የአሳፍ ልጅ፥ የዛብዲ ልጅ፥ የሚካ ልጅ ማታንያ፤ ከወንድሞቹ ሁለተኛ የነበረው ባቅቡቅያ፤ የይዱቱን ልጅ፥ የጋላል ልጅ፥ የሻሙዓ ልጅ ዓብዳ። በቅድስቲቱ ከተማ የነበሩ ሌዋውያን ሁሉ ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ነበሩ። በር ጠባቂዎቹ፥ ዓቁብ፥ ጣልሞንና በሮቹን የሚጠብቁ ወንድሞቻቸው፥ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ነበሩ። ከእስራኤል የቀሩት ካህናቱና ሌዋውያኑ እያንዳንዱ በየርስቱ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ነበሩ። የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹም በዖፌል ተቀመጡ፤ ጺሓና ጊሽፓ በቤተ መቅደስ አገልጋዮች ላይ አለቆች ነበሩ። በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ከነበሩ መዘምራን ከአሳፍ ልጆች ወገን የሚካ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሓሻብያ ልጅ፥ የባኒ ልጅ ዑዚ በኢየሩሳሌም የሌዋውያን አለቃ ነበረ። ስለ እነርሱ የንጉሥ ትእዛዝ ነበረ የመዘምራኑም ሥርዓት ለየዕለቱ የተሠራ ነበረ። ከይሁዳ ልጅ ከዜራሕ ወገኖች የምሼዛቤል ልጅ፥ ፕታሕያ ሕዝቡን በሚመለከት ጉዳይ ሁሉ በንጉሡ አጠገብ ነበረ። በሜዳዎቻቸው ስለ ነበሩ ስለ መንደሮቻቸው፦ ከይሁዳ ልጆች አንዳንዶቹ በእነዚህ ቦታዎች ተቀመጡ፦ በቂርያት አርባዕና በመንደሮችዋ፥ በዲቦንና በመንደሮችዋ፥ በይቃብጽኤልና በመንደሮችዋ፥ በኢያሱ፥ በሞላዳ፥ በቤት ጳሌጥ፥ በሓጻር ሹዓል፥ በቤርሳቤህና በመንደሮችዋ በጺቅላግ፥ በምኮናና በመንደሮችዋ፥ በዔን ሪሞን፥ በጻርዓና ያርሙት፥ ዛኖሓ፥ ዓዱላምና በመንደሮቻቸው፥ ላኪሽና ሜዳዎችዋ፥ ዓዚቃና በመንደሮችዋ፤ እንዲሁ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ድረስ ሰፈሩ። የብንያምም ልጆች ከጋባዕ ጀምሮ በሚክማስ፥ ዓያ፥ ቤትኤልና በመንደሮችዋ፥ ዓናቶት፥ ኖብ፥ አናንያ፥ ሐጾር፥ ራማ፥ ጊታይም፥ ሐዲድ፥ ጽቦዒይም፥ ንባልጥ፥ ሎድና በእጀ ጠቢባን ሸለቆ በኦኖ ተቀመጡ። በይሁዳ ከነበሩ ከሌዋውያን አንዳንድ ክፍሎች ወደ ብንያም ሆኑ። ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር የወጡት ካህናትና ሌዋውያን እነዚህ ናቸው፤ ሥራያ፥ ኤርምያስ፥ ዕዝራ፥ አማርያ፥ ማሉክ፥ ሐጡሽ፥ ሽካንያ፥ ርሁም፥ ምሬሞት፥ ዒዶ፥ ጊንቶይ፥ አቢያ፥ ሚያሚን፥ ማዓድያ፥ ቢልጋ፥ ሽማዕያ፥ ዮያሪብ፥ ይዳዕያ፥ ሳሉ፥ ዓሞቅ፥ ሒልቂያ፥ ይዳዕያ፤ እነዚህ በኢያሱ ዘመን የካህናቱና የወንድሞቻቸው መሪዎች ነበሩ። ሌዋውያኑም፦ ኢያሱ፥ ቢኒዊ፥ ቃድሚኤል፥ ሼሬብያ፥ ይሁዳና ከወንድሞቹ ጋር በመሆን የምስጋና መዝሙር ኃላፊ የነበረው ማታንያ። ወንድሞቻቸው ባቅቡቅያና ዑኖ በአገልግሎቱ ጊዜ በፊት ለፊታቸው ይቆሙ ነበር። ኢያሱም ዮያቂምን ወለደ፥ ዮያቂም ኤልያሺብን ወለደ፥ ኤልያሺብ ዮያዳዕን ወለደ፥ ዮያዳዕ ዮናታንን ወለደ፥ ዮናታን ያዱዓን ወለደ። በዮያቂም ዘመን የአባቶች መሪዎች ካህናቱ እነዚህ ነበሩ፦ ከሥራያ ቤተሰብ ምራያ፥ ከኤርምያስ ሐናንያ፥ ከዕዝራ ምሹላም፥ ከአማርያ ይሆሐናን፥ ከምሉኪ ዮናታን፥ ከሽባንያ ዮሴፍ፥ ከሐሪም ዓድና፥ ከምራዮት ሔልቃይ፥ ከዒዶ ዘካርያስ፥ ከጊንቶን ምሹላም፥ ከአቢያ ዚክሪ፥ ከሚንያሚን፥ ከሞዓድያ፥ ፒልጣይ፥ ከቢልጋ ሻሙዓ፥ ከሽማዕያ ይሆናታን፥ ከዮያሪብ ማትናይ፥ ከይዳዕያ ዑዚ፥ ከሳላይ ቃላይ፥ ከዓሞቅ ዔቤር፥ ከሒልቂያ ሐሻብያ፥ ከይዳዕያ ናትናኤል። ከሌዋውያኑም በኤልያሺብ፥ ዮያዳዕ፥ ዮሐናን፥ ያዱዓ ዘመን የአባቶች መሪዎችና ካህናቱ በፋርሳዊው በዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ተመዝግበው ነበር። የሌዊ ልጆች የአባቶች መሪዎች እስከ ኤልያሺብ ልጅ እስከ ዮሐናን ዘመን ድረስ በታሪክ መጽሐፍ ተመዝግበው ነበር። የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሻብያ፥ ሼሬብያ፥ የቃድሚኤል ልጅ ኢያሱና ወንድሞቻቸው ደግሞ ከፊት ለፊታቸው ሆነው የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ክፍል በክፍል ትይዩ ሆነው ያወድሱና ያመሰግኑ ነበር። ማታንያ፥ ባቅቡቅያ፥ አብድዩ ፥ ምሹላም፥ ጣልሞን፥ ዓቁብ በበሮቹ አጠገብ የሚገኙትን ዕቃ ቤቶች የሚጠብቁ በር ጠባቂዎች ነበሩ። እነዚህ በዮፃዳቅ ልጅ በኢያሱ ልጅ በዮያቂም ዘመንና በገዢው በነህምያና በጸሐፊው በካህኑ በዕዝራ ዘመን ነበሩ። የኢየሩሳሌም ቅጥር ሲመረቅ ምረቃውን በደስታ፥ በምስጋና፥ በመዝሙር፥ በጸናጽል፥ በበገናና በክራር ለማክበር ሌዋውያኑን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በየሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ፈለጉ። የመዘምራኑ ልጆች ከኢየሩሳሌም ዙሪያና ከነጦፋውያን መንደሮች፥ ተሰበሰቡ፤ መዘምራኑም በኢየሩሳሌም ዙሪያ መንደሮች ሠርተው ነበርና ከቤትጌልገላም፥ ከጌባና ከዓዝሞት እርሻዎች ተሰበሰቡ። ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አነጹ፤ ሕዝቡን፥ በሮቹንና ቅጥሩንም አነጹ። የይሁዳንም አለቆች ወደ ቅጥሩ ላይ አወጣኋቸው፥ አመስጋኞቹንም በሁለት ታላላቅ ተርታ አቆምኋቸው፥ አንዱም ወደ ቀኝ በቅጥሩ ላይ ወደ ጉድፍ መጣያው በር ሄደ። ከእነርሱም በኋላ ሆሻዕያና የይሁዳ መሪዎች እኩሌታ ሄዱ፥ አዛርያ፥ ዕዝራ፥ ምሹላም፥ ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሸማዕያና ኤርምያስ፥ መለከት የያዙ ጥቂት የካህናቱ ልጆች፥ የአሳፍ ልጅ፥ የዛኩር ልጅ፥ የሚካያ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሸማዕያ ልጅ፥ የዮናታን ልጅ ዘካርያስ፥ ወንድሞቹም ሸማዕያ፥ ዓዛርኤል፥ ሚላላይ፥ ጊላላይ፥ መዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳና ሐናኒ የእግዚአብሔር ሰው የዳዊትን የዜማ መሣሪያ ይዘው ሄዱ፤ ጸሐፊው ዕዝራም በፊታቸው ነበረ። “በምንጭ በር” አቅንተው ሄዱ፤ በዳዊትም ከተማ ደረጃ፥ በቅጥሩም መውጫ፥ ከዳዊትም ቤት በላይ እስከ ውኃው በር ድረስ በምሥራቅ በኩል ሄዱ። ከፊት ይሄድ የነበረው ሁለተኛው የምስጋና መዘምራን ክፍል ነበር፤ እኔና የሕዝቡ እኩሌታ በስተ ኋላቸው ነበርን፤ በቅጥሩም ላይ፥ ከ “የእቶኑ ግንብ” በላይ እስከ “ሰፊው ቅጥር” ድረስ፥ ከ “ኤፍሬም በር” በላይ፥ ከ “አሮጌው በር” በላይ፥ በ “ዓሣ በር” በ “ሐናንኤል ግንብ”፥ በሃሜአ ግንብ እስከ በጎች በር ድረስ ሄዱ፥ በዘበኞችም በር አጠገብ ቆሙ። ሁለቱ የምስጋና መዘምራን ክፍሎች በእግዚአብሔር ቤት ቆሙ፥ እኔና ከመሪዎቹ እኩሌታ በተጨማሪ፥ ካህናቱ ኤልያቂም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ሚካያ፥ ኤልዮዕናዪ፥ ዘካርያስ፥ ሐናንያ መለከት ይዘው፥ መዕሤያ፥ ሽማዕያ፥ አልዓዛር፥ ኡዚ፥ ይሆሐናን፥ ማልኪያ፥ ዔላም፥ ዓዜር ቆምን። መዘምራኑም በዪዝራሕያ መሪነት በታላቅ ድምፅ ዘመሩ። እግዚአብሔር በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፥ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ የኢየሩሳሌምም ደስታ ከሩቅ ተሰማ። በዚያን ቀን በይሁዳም በአገልጋዮቹ ካህናትና ሌዋውያን ደስ ስላላቸው፥ የካህናቱንና የሌዋውያኑን እድል ፈንታ እንደ ሕጉ ከከተሞች እርሻዎች ያከማቹ ዘንድ ለእጅ ማንሣት ቁርባንና ለበኵራት ለአሥራትም በየዕቃ ቤቶቹ ላይ በዚያ ቀን ሰዎች ተሾሙ። እነርሱም መዘምራኑና በረኞቹም የአምላካቸውን ሥርዓት የመንጻታቸውንም ሥርዓት እንደ ዳዊትና እንደ ልጁ እንደ ሰሎሞን ትእዛዝ ጠበቁ። አስቀድሞም በዳዊትና በአሳፍ ዘመን እግዚአብሔርን በዜማ ለማመስገንና ለማክበር የመዘምራን አለቆች ነበሩ። እስራኤልም ሁሉ በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን ለመዘምራኑና ለበረኞቹ እድል ፈንታቸውን በየዕለቱ ይሰጡ ነበር፥ የተቀደሰውንም ነገር ለሌዋውያን ሰጡ፥ ሌዋውያኑም ከተቀደሰው ነገር ለአሮን ልጆች ሰጡ። በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ ከፍ ባለ ድምፅ አነበቡ፤ አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘለዓለም እንዳይገባ የሚል በዚያ ተጽፎ ተገኘ። ይህም ደግሞ የእስራኤልን ልጆች በምግብና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና እንዲረግማቸውም በለዓምን ስለ ገዙት ነው፤ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው። እንዲህም ሆነ ሕጉን በሰሙ ጊዜ የተደባለቀውን ዘር ሁሉ ከእስራኤል ለዩ። ከዚህ ቀደም በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሺብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥ ትልቅ ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቁርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር። በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ በባቢሎን ንጉሥ በአርታሕሻስት በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከንጉሡ ፈቃድ ጠየቅሁ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፥ ኤልያሺብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። እጅግም አስከፋኝ፥ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ። ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ። ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ። እኔም፦ የእግዚአብሔር ቤት ስለምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፥ ከእነርሱም ጋር የማታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፥ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፥ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ። በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጥመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከመሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ በለሱንም ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፥ ገበያ ባደረጉበትም ቀን አስመሰከርሁባቸው። ደግሞም በእርሷ የተቀመጡ የጢሮስ ሰዎች ነበሩ፥ እነርሱም ዓሣዎችን ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር። ከይሁዳም ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና፦ ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን? አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ አልኋቸው። ከዚህ በኋላ ከሰንበት በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖቼ በአያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ። ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር። እኔም አስመሰከርሁባቸውና፦ በቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደገና ብታደርጉት እጆቼን አነሣባችኋለሁ አልኋቸው። ከዚያም ወዲያ በሰንበት ቀን እንደገና አልመጡም። ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ። ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ። ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፥ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር። ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፥ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፦ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ። የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፥ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፥ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት። በውኑ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት እንሠራ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችንን እንበድል ዘንድ እናንተን እንስማ? ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ ለሖሮናዊው ለሰንበላጥ አማች ነበረ፥ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት። አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው። ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥ በየጊዜውም ለእንጨት ቁርባን ለበኩራቱም ሥርዓት አደረግሁ። አምላኬ ሆይ፥ በመልካም አስበኝ። ... ... ... ... ... ... ... ... ... ... ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችም ነበሩት። ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎች፥ አምስት መቶ እንስት አህዮችና እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት። ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያሰናዱ ነበር፥ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ፦ “ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል” ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፥ ኢዮብም ማልዶ ይነሣና እንደ ቁጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ኢዮብም ሁልጊዜ እንዲህ ያደርግ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በጌታ ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። ጌታም ሰይጣንን፦ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፦ “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርሷም ተመላለስሁ” ብሎ ለጌታ መለሰ። ጌታም ሰይጣንን፦ “በውኑ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” አለው። ሰይጣንም ለጌታ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ንብረቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” ጌታም ሰይጣንን፦ “እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” አለው። ሰይጣንም ከጌታ ፊት ወጣ። አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። መልክተኛም ወደ ኢዮብ መጣ፤ እንዲህም ኣለው፦ “በሬዎች እያረሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ተሰማርተው ሳሉ፥ የሳባ ሰዎች አደጋ ጣሉና ወሰዱአቸው፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ” አለው። እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ፦ “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎቹንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችንም በላች፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ” አለው። እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ፦ “ከለዳውያን በሦስት ረድፍ ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ” አለው። እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፥ እነሆም፥ ብርቱ ነፋስ ከምድረበዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፥ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፥ ሞቱም፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ።” ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፥ እንዲህም አለ፦ “ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፥ ጌታ ሰጠ፥ ጌታ ወሰደ፥ የጌታ ስም የተባረከ ይሁን።” በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፥ እግዚአብሔርንም አላማረረም። ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ልጆች በጌታ ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በጌታ ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ። ጌታም ሰይጣንን፦ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፦ “በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርሷም ተመላለስሁ” ብሎ ለጌታ መለሰ። ጌታም ሰይጣንን፦ “በውኑ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፥ ያለ ምክንያት ይጠፋ ዘንድ በእርሱ ላይ ብትገፋፋኝም እንኳን፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ጠብቋል።” ሰይጣንም መልሶ ጌታን እንዲህ አለው፦ “በቆዳ ላይ ቆዳ ፥ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” ጌታም ሰይጣንን፦ “ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው” አለው። ሰይጣንም ከጌታ ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ መርገጫ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው። ኢዮብም ሥጋውን ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። ሚስቱም፦ “እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። እርሱ ግን፦ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም። ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፥ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው ቢልዳድ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ። ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፥ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፥ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተው ነበርና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም። ከዚያም በኋላ ኢዮብ መናገር ጀመረ፤ የተወለደበትንም ቀን ረገመ። ኢዮብም እንዲል ሲል ተናገረ፦ “ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥ እንዲሁም፦ ‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ’ የተባለበት ሌሊት። ያ ቀን ጨለማ ይሁን፥ እግዚአብሔር ከላይ አይፈልገው፥ ብርሃንም አይብራበት። ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፥ ዳመናም ይረፍበት፥ የቀን ጨለማ ያሸብረው። ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፥ በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤ በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር። እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፥ እልልታ አይግባበት። ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት። የንጋቱ ኮከቦች ይጨልሙ፤ ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥ የንጋትንም ቅንድብ አይይ፥ የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥ መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና። በማኅፀን ሳለሁ ስለምን አልሞትሁም? ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ስለምን ፈጥኜ አልጠፋሁም? ጉልበቶች ስለምን ተቀበሉኝ? ጡትስ ስለምን ጠባሁ? አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፥ አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤ የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት ከምድር ነገሥታትና አማካሪዎች ጋር፥ ወይም ወርቅ ከነበራቸው ገዢዎች፥ ቤታቸውንም በብር ከሞሉ ጋር፥ ወይም እንደ ተደበቀበ ጭንጋፍ፥ ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር። ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፥ በዚያም ደካሞች ያርፋሉ። በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፥ የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም። ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፥ አገልጋይም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል። በመከራ ላሉት ብርሃን፥ ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥ የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥ መቃብርን ባገኙ ጊዜ በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ ሕይወት ስለምን ተሰጠ? መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥ እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው ብርሃን ስለምን ተሰጠ? ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥ ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል። የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል። ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፥ ነገር ግን መከራ መጣብኝ።” ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “አንድ ሰው ከአንተ ጋር ለመናገር ቢሞክር ትቀየማለህን? ቃልንስ ከመናገር ማን ሊቀር ይችላል? እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥ ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥ አንተም የሚብረከረከውን ጉልበት ታጸና ነበር። አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቷል፥ አንተም ደከምህ፥ ደርሶብሃል፥ አንተም ተረበሽህ። አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥ የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን? እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው? እኔ እንዳየሁት፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ። በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥ በቁጣውም መንፈስ ያልቃሉ። የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥ የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ። አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥ የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ። ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች። በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥ የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥ ድንጋጤ ወደቀብኝ፥ እንዲሁም መንቀጥቀጥ አጥንቶቼን ሁሉ ተነዋወጡ። መንፈስም በፊቴ አለፈ፥ የሥጋዬ ጠጉር ቆመ። እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፥ ዝምታም ነበር፥ ድምፅም ሰማሁ፦ ‘በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን? እነሆ፥ በአገልጋዮቹ እንኳን አይተማመንም፥ በመላእክቱንም ላይ ስሕተት ያገኛል፥ ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥ መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥ ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ? በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፥ ማንም ሳያስብ ለዘለዓለም ይጠፋሉ። ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን? አለጥበብም ይሞታሉ።’” “አሁንም ተጣራ፥ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ? አላዋቂውን ሰው ቁጣ ይገድለዋል፥ ሞኙንም ቅንዓት ያጠፋዋል። አላዋቂውን ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ። ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚደርስላቸውም የለም። የሰበሰበውንም የተራበ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፥ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ። ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፥ ሰው ለመከራ ተወልዶአል የአሞራ ግልገሎች ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንደሚሉ። እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር። የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል። የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ያዘኑትን ለደኅንነት ከፍ ያደርጋቸዋል። የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል፥ እጃቸውም ደባቸውን ከግብ እንዳያደርስ። ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፥ የጠማሞችንም ምክር ያጠፋል። በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። ድሀውን ከአፋቸው ሰይፍ አንዲሁም ከኃያላን እጅ ያድነዋል። ለምስኪኑም ተስፋ አለው፥ ግፍ ግን አፍዋን ትዘጋለች። እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፥ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ቢያቈስልም ይጠግናልና፥ ቢሰብርም፥ እጆቹ ይፈውሳሉና። ከስድስት ችግሮች ያድንሃል፥ በሰባተኛውም ውስጥ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ጊዜ ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፥ የጥፋት አደጋ ሲመጣም አትፈራም። በጥፋት አደጋና በራብ ላይ ትስቃለህ፥ የምድረ በዳ አራዊትንም አትፈራም፥ ቃል ኪዳንህ ከምድረበዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና ፥ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ድንኳንህ ሰላምን እንደሚያገኝም ታውቃለህ፥ በረትህን ትጐበኛለህ፥ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘርህም እንደሚበዛ፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር ብዙ እንደሚሆን ታውቃለህ። የእህሉ ነዶ ወራቱ ሲደርስ ወደ አውድማ እንደሚገባ፥ ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፥ አንተም ለራስህ እወቀው።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ! መከራዬም በሚዛን ላይ ምነው በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ ነበርና፥ ለዚህም ነው ቃሌ ደፋር የሆነው። ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥ የእግዚአብሔር ሽብሮች በኔ ላይ ተሰልፈዋል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ እያለው ይጮኻልን? የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን? ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ፥ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። እጠብቅ ዘንድ ጉልበቴ ምንድነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድነው? ጉልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? ሥጋዬስ ነሐስ ነውን? በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?” “ቸርነትን ለወዳጁ የሚነፍግ፥ ሁሉን ቻይ አምላክን መፍራት የተወ ነው። ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ። ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፥ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፥ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ። በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፥ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ። የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው። ተስፋ አድርገውባቸው ነበርና አፈሩ፥ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው። አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፥ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። በውኑ፦ አንዳች ነገር አምጡልኝ፥ ወይስ፦ ከብልጽግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፥ ወይስ፦ ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፥ ወይስ፦ ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን? አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፥ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ። የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል? ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን? በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፥ ለወዳጆቻችሁም ጉድጓድ ትቈፍራላችሁ። አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም። እባካችሁ፥ ተመለሱ፥ በደል አይሁን፥ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ። በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? ምላሴ የተንኰልን ቃና መለየት አይችልምን?” “የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ቀኖቹ እንደ ምንደኛ ቀኖች አይደሉምን? አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪ ነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥ ቆዳዬ ያፈከፍካል እንደገናም ይመግላል። ቀኖቼ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኩላሉ፥ ያለ ተስፋም ያልቃሉ።” “ሕይወቴ እስትንፋስ እንደሆነ አስታውስ፥ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።” “ስለዚህም ከመናገር አፌን አልከለክልም፥ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጉራለሁ። እኔ ባሕር ነኝ ወይስ ዓሣ አንበሪ? ባላዬ ጠባቂ የምታኖርብኝ? እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጉርጉሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥ ከዚህ ሥጋ ይልቅ ነፍሴ መታነቅንና ሞትን መረጠች። ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘለዓለም ልኖር አልወድድም፥ ቀኖቼ እስትንፋስ ናቸውና ተወኝ። ሰው ምንድነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደሆነ ምን ላድርግልህ? ስለምን እኔን ዒላማ አደረግኸኝ? ስለምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? ስለምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥ ትፈልገኛለህ፥ እኔ ግን የለሁም።” ሹሐዊውም ቢልዳድ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል? በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በድለውት እንደሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። እግዚአብሔርን ብትሻ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትማጸን፥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት እርሱ አንተን ነቅቶ ይጠብቅሃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያረጋግጥልሃል። ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።” “እንግዲህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትኩረት ስጥ፥ እኛ የትናንት ብቻ ነን፥ ምንም አናውቅም፤ ቀኖቻችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ናቸውና። እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን?” “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? ገና ሲለመልም ሳይቀጠፍም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፥ የአምላክ አልባ ሰውም ተስፋ ይጠፋል። ተስፋው ይቈረጣል፥ መተማመኛው እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል። ቤቱን ይደገፈዋል፥ ነገር ግን አይቆምለትም፥ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም። ከፀሐይም ትኩሳት በፊት እርጥብ ነው፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል። በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፥ የድንጋዩቹን ቦታ ይመለከታል ። ከቦታው ቢጠፋ፦ አላየሁህም ብሎ ይክደዋል። እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፥ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ።” “እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የክፉዎችን እጅ አያበረታም። አፍህን እንደገና በሳቅ፥ ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላዋል። የሚጠሉህ ኃፍረት ይከናነባሉ፥ የክፉዎችም ድንኳን አይገኝም።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በእውነት እንዲህ እንደሆነ አወቅሁ፥ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል? ከእርሱ ጋር መከራከር ቢፈልግ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም። ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ እርሱንስ ተዳፍሮ በደኅና የቆየ ማን ነው? ተራሮችን ይነቅላል፥ ነገር ግን አያውቁትም፥ በቁጣውም ይገለብጣቸዋል። ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ። ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፥ ከዋክብትንም ያትማል። ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል። ድብ የሚባለውን እና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥ በደቡብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ሠርቶአል። የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል። እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፥ ቢያልፍብኝም አላውቀውም። እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?” “እግዚአብሔር ቁጣውን አይመልስም፥ ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ። ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥ ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ጻድቅ ብሆንም እንኳን ልመልስለት አልችልም፥ ፈራጄን እማጸናለሁ እንጂ። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን ሰማ ብዬ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቁስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ከሆነ፥ ኃያሉ እርሱ እነሆ፥ የፍርድ ነገር ከሆነም፥ የችሎቱን ጊዜ ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን እንኳን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦ ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ። መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል። ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥ ይህንን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ሌላ ማን ነው?” “ቀኖቼ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናሉ፥ ይሸሻሉ፥ መልካምንም አያዩም። የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋሉ። እኔ፦ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እረሳለሁ፥ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥ ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ የተነሣ እፈራለሁ። በደለኛ እሆናለሁ፥ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ? በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል። እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፥ እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።” “ሕይወቴ ሰለቸኝ፥ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እለቅቀዋለሁ፥ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ። እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦ አትፍረድብኝ፥ የምትከራከረኝ ለምን እንደሆነ ንገረኝ። ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅ የክፉዎችንስ ምክር ልታበራ በአንተ ዘንድ መልካም ነውን? በውኑ የሥጋ ዐይን አለህን? ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን? ቀኖችህ እንደ ሰው ቀኖች ናቸውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ቀናት ናቸውን? ታዲያ ክፋቴን የምትከታተለው፥ ኃጢአቴንም የምትመረምረው ለምንድን ነው? ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ። እጆችህ ቀረጹኝ ሠሩኝም፥ ከዚያም ተመልሰህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ። ከጭቃ እንደሠራኸኝ አስታውስ፥ ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን? በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን? ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥ በአጥንትና በጅማትም አጠንከርኸኝ። ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፥ መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች። እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ፥ ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ። ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፥ ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም። በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፥ ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፥ ጉስቁልናን ተሞልቻለሁና፥ መከራዬንም ተመልክቻለሁና። ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፥ ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ። ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፥ ቁጣህንም ታበዛብኛለህ፥ ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ።” “ስለምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዐይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ። እንዳልነበረ በሆንሁ፥ ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ። የሕይወቴ ቀኖች ጥቂት አይደሉምን? ወደማልመለስበት ስፍራ ሳልሄድ፥ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥ እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።” ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በውኑ ነገር ለሚያበዛ መልስ መስጠት አይገባምን? ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን? ከንቱ ልፍለፋህ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን? ብትሳለቅስ የሚያሳፍርህ የለምን? አንተ፦ ትምህርቴ የተጣራ ነው፥ በዓይንህም ፊት ንጹሕ ነኝ ትላለህ። ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት! የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ማስተዋሉ እጥፍ ነውና። እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ።” “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ሁሉን የሚችል አምላክን ፍጻሜ ልትመረምር ትችላለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፥ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፥ ምን ልታውቅ ትችላለህ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል። እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥ የሚከለክለው ማን ነው? የማይረቡ ሰዎችን ያውቃልና፥ በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም። የሜዳ አህያ ሰው ሆኖ ሲወለድ፥ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል።” “አንተ ልብህን ቅን ብታደርግ፥ እጆችህን ወደ እርሱ ትዘረጋለህ፥ በእጅህ በደል ቢኖር አርቀው፥ በድንኳንህም ኃጢአት አይኑር፥ በዚያን ጊዜ በእውነት ፊትህን ያለ ነውር ታነሣለህ፥ ትበረታለህ፥ አትፈራምም። መከራህንም ትረሳለህ፥ እንዳለፈ ውኃ ታስበዋለህ። ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ያበራል፥ ጨለማም ቢሆን እንደ ጥዋት ይሆናል። ተስፋም ስላለህ ተማምነህ ትቀመጣለህ፥ በዙሪያህ ትመለከታለህ ፥ በደኅንነትም ታርፋለህ። ትተኛለህ፥ የሚያስፈራህም የለም፥ ብዙ ሰዎችም ልመና ያቀርቡልሃል። የክፉዎች ዐይን ግን ትጨልማለች፥ የሚሸሹበትንም ያጣሉ፥ ተስፋቸውም ነፍስን አሳልፎ መስጠት ነው።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በእርግጥም እናንተ የሕዝብ ድምፅ ናችኋ! ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ! ነገር ግን እኔም እንደ እናንተ ማስተዋል እችላለሁ፥ ከእናንተም አላንስም፥ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው? ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፥ እግዚአብሔርን የጠራሁ እኔ፥ እርሱም የመለሰልኝ፥ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል። ተደላድሎ የተቀመጠ ሰው መከራን ይንቃል፥ እግሩን ያዳለጠውንም ለመገፍተር ተዘጋጅቶአል። የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዝናንተው ተቀምጠዋል፥ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።” “አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፥ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። ወይም ለምድር ተናገር፥ እርሷም ታስተምርሃለች፥ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል። የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው? የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ እስትንፋስ በእጁ ናት። ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፥ ጆሮም የቃላትን እውነት ይለይ የለምን? ጥበብ በሽምግልና፥ ማስተዋል በረጅም ዕድሜ ይገኛሉ።” “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፥ በእርሱ ዘንድ ምክርና ማስተዋል አለ። እነሆ፥ ካፈረሰ፥ የፈረሰው ተመልሶ አይሠራም፥ በሰውም ላይ ከዘጋ፥ ሊከፈት አይችልም። እነሆ፥ ውኆቹን ቢከለክል፥ እነርሱ ይደርቃሉ። እንደገና ቢለቃቸው፥ ምድሪቱን ያጥለቀልቃሉ። ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፥ የሚስተውና የሚያስተው የእርሱ ናቸው። አማካሪዎችንም እራቁታቸውን ይሰዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ሞኝ ያደርጋል። የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል። ካህናትን እንደ ምርኮኛ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል። ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል። በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል። ከጨለማ ውስጥ ጥልቅን ነገር ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ይለውጣል።” አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፥ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል። ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ያስወግዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል። ብርሃንም በሌለበት ጨለማ ይርመሰመሳሉ፥ እንደ ሰካራም ያቅበዘብዛቸዋል። “እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፥ ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው። እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፥ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም። ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ። እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፥ ሁላችሁም የማትጠቅሙ ሐኪሞች ናችሁ። ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ! ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር። አሁንም ክርክሬን ስሙ፥ የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ። በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን? ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን? ለእርሱ እያዳላችሁ ነውን? ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን? ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን? ወይስ በሰውን እንደምታታልሉ ልታታልሉት ትፈልጋላችሁን? በስውር ብታዳሉ በጥብቅ ይገሥጻችኋል። ክብሩስ አያስፈራችሁምን? ግርማውስ አይወድቅባችሁምን? ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፥ ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው።” “ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፥ የፈለገ ነገር ይምጣብኝ። ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ። እነሆ፥ ሊገድለኝ ይችላል፥ ተስፋም ባይኖረኝ፥ ነገር ግን ስለ መንገዴ በፊቱ እሟገታለሁ። ክፉ ሰው በፊቱ አይቀርብምና፥ እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል። ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥ ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ። እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ። ጽድቄም እንደሚገለጽ አውቃለሁ። ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው? አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ። ነገር ግን ሁለት ነገሮችን አድርግልኝና፥ የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፥ እጅህን ከእኔ አርቅ፥ ግርማህም አታስደንግጠኝ። ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ። ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ። ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው? መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ። ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ለምንድነው? የረገፈውን ቅጠል ታስደነግጣለህን? ወይስ የደረቀውን ገለባ ታሳድዳለህን? የመረረ ነገር ጽፈሕብኛልና፥ የልጅነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ። እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥ መንገዴንም ሁሉ ተቆጣጥረሃል፥ የእግሬንም ዱካ ወስነሃል። እኔ እንደሚበሰብስ የተበላሸ ነገር፥ ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።” “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ በመከራም የተሞላ ነው። እንደ አበባ ይፈካል፥ ይረግፋልም፥ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም። እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዐይኖችህን ትተክላለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን? ከርኩስ ነገር ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል? አንድ እንኳን የሚችል የለም። የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት። እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል።” “ዛፍ እንኳን ተሰፋ አለው፥ ቢቈረጥ የማቈጠቁጥ፥ ቅርንጫፉም የማደግ እድል አለው። ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥ በውኃ ሽታ ያቈጠቁጣል፥ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል። ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፥ ሰውም ነፍሱ ትወጣለች፥ እርሱስ ወዴት አለ? ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፥ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል። ሰውም እንዲሁ ተኝቶ አይነሣም፥ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? ዕረፍቴ እስኪመጣ ድረስ፥ የአገልግሎቴን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፥ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር። አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፥ ይልቁንም ኃጢአቴን ባልተጠባበቅህ። መተላላፌን በከረጢት ውስጥ ታትሞ፥ ኃጢአቴንም በለበጥህበት ነበር።” “ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፥ ውኆች ድንጋዮቹን ይፍቃሉ፥ ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፥ እንዲሁም የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ። ለዘለዓለም ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፥ ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ። ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፥ ቢዋረዱም አያይም። ነገር ግን የገዛ ሥጋው ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል።” ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ነፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን? ሆዱንስ በምሥራቅ ነፋስ ይሞላልን? ከማይረባ ነገር፥ ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን? አንተም ፈሪሃ እግዚአብሔርን እስከ መተው ደርሰሃል፥ በእግዚአብሔርም ፊት አምልኮን ታስቀራለህ። በደልህ ንግግርህን ይመራዋል፥ የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ። የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፥ ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።” “በውኑ መጀመሪያ የተወለደው የሰው ልጅ አንተ ነህን? ከተራሮች በፊትስ ተፀንሰሀልን? የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን? ጥበብን የግልህ ለማድረግ ትመኛለህን? እኛ ሳናውቀው አንተ የምታወቀው ምንድነው? ከእኛ ዘንድስ ሳይኖር የምታስተውለው ምንድነው? በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ። በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥ በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን? ልብህስ ለምን ወደ ሌላ ይወስድሃል? ዐይኖችህስ ለምን ይገላምጣሉ? ቁጣህን በእግዚአብሔር ላይ እስከ ማንሣት ደርሰህ፥ እነኚህንም ቃላት ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ። ከንጹሕ ለመመደብ የሰው ልጅ ምንድነው? ጻድቅስ ለመባል ከሴት የተወለደ ምንድነው? እነሆ፥ ቅዱሳኑን እንኳን አያምናቸውም፥ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። ታዲያ አስጸያፊና የረከሰ፥ በደልን እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?!” “ስማኝ ልንገርህ፥ እነሆም ያየሁትን ልተርክልህ፤ ጠቢባን የተናገሩትን፥ አባቶቻቸውም ያልሰወሩትን፤ ምድሪቱ ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታለችና፥ በመካከላቸውም እንግዳ አልገባባቸውም። ክፉ ሰው ዕድሜ ልኩን ሲሠቃይ ይኖራል፥ እንዲሁም ግፈኛ በተመደቡለት ዓመታት በሙሉ። የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፥ በሰላምም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል። ከጨለማ ተመልሼ እወጣለሁ ብሎ አያምንም፥ ሰይፍም ይሸመቅበታል። ተቅበዝብዞም፦ ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፥ የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል። መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፥ ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል። እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥ ሁሉን የሚችል አምላክን ደፍሮአልና፥ በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ ጋሻው እየገሠገሠ ወደ እርሱ ይመጣበታልና፥ በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥ በውፍረትም ወገቡ ተሸፍኗልና፥ በተደመሰሱም ከተሞች ውስጥ፥ ሰውም በሌለባቸው፥ ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና ባለ ጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፥ ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፥ ከጨለማ አይወጣም፥ ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥ አበባዎቹም ይረግፋሉ። ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና። ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥ ቅርንጫፉም አይለመልምም። እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፥ እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል። የአምላክ አልባ ሰው ጉባኤ ፍሬ የለውም፥ የጉቦ ድንኳኖችንም እሳት ትበላለች። ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥ ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እንደዚህ ያለ ነገር አብዝቼ ሰማሁ፥ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ። በውኑ ከንቱ ቃል መጨረሻ የለውምን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድነው? እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፥ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር። በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፥ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።” “እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፥ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም። አሁን ግን አድክሞኛል፥ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል። መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፥ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፥ በፊቴም ይመሰክርብኛል። በቁጣው ቆራረጠኝ፥ እርሱም ጠላኝ፥ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፥ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፥ እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፥ እያላገጡ ጉንጬን ጠፈጠፉኝ፥ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ። እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፋዎችም እጅ ጣለኝ። በርጋታ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፥ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፥ እንደ ዒላማ አድርጎ አቆመኝ። ቀስተኞቹ ከበቡኝ፥ ኩላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፥ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ። በቁስል ላይ ቁስል ጨመረብኝ፥ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል። በቆዳዬ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ። ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፥ የሞት ጥላ በዐይኖቼ ቆብ ላይ አለ፥ ነገር ግን በእጄ ዓመጽ የለም፥ ጸሎቴም ንጹሕ ነው።” “ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይኑር። አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው። ወዳጆቼ ናቁኝ፥ ዓይኔም በእግዚአብሔር ፊት እንባ ታፈሳለች። የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ! ጥቂት ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።” መንፈሴ ደከመ፥ ቀኖቼ አለቁ፥ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል። አላጋጮች በእኔ ዘንድ አሉ፥ ዓይኔም ማስቈጣታቸውን ትመለከታለች። “እባክህን፥ አንተ ዋስ ሁነኝ፥ ለእኔ ተያዥ የሚሆነኝ ማን ነው? ልባቸውም እንዳያስተውል ከልክለኸዋል፥ ስለዚህ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም። ለብዝበዛ ባልንጀሮቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዐይን ይጨልማል።” “ለሕዝብም ምሳሌ አደረገኝ፥ በፊቱ ላይ እንደሚተፉበት ሰው ሆንሁ። ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ፈዘዘች፥ መላ ሰውነቴ እንደ ጥላ ሆነ። ቅኖች ሰዎች በዚህ ነገር ይረበሻሉ፥ ንጹሕም አምላኩን በሚክድ ላይ ይበሳጫል። ጻድቅ ግን መንገዱን ያጠነክራል፥ እጁም ንጹሕ የሆነ ሰው ኃይልን እየጨመረ ይሄዳል። ነገር ግን እናንተ ሁሉ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፥ በእናንተም ዘንድ ጠቢብ አላገኝም። ቀኖቼ አለፉ፥ ዕቅዴና የልቤ ምኞት ቀለጠ። ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፥ ብርሃኑም ወደ ጨለማ የቀረበ ይመስላቸዋል። ተስፋ ባደርግ ሲኦል ቤቴ ናት፥ ምንጣፌንም በጨለማ ዘርግቻለሁ። መበስበስን፦ አንተ አባቴ ነህ፥ ትልንም፦ አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ። እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው? ወደ ሲኦል ይወርዳልን? አብረን ወደ አፍር ውስጥ እንገባ የለምን?” ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “እስከ መቼ ቃላትን ታበዛለህ? አስተውል፥ ከዚያም እኛ እንናገራለን። ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን? ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ቀለልን? ቁጣ ወርሶሃል፥ ስለ አንተ ሲባል፥ ምድር ባድማ ትሆናለችን? ወይስ ዓለት ከስፋራው ይነቀላልን?” “የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም። ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱም በላዩ ይጠፋል። የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች። እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብም ላይ ይሄዳል። አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ ወጥመድም ይበረታበታል። በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች። ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥ በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች። ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል። የሰውነቱ ክፍሎች ይጠፋሉ፥ የሞትም የበኩር ልጅ ሰውነቱን ይበላል። ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፥ ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኩሉታል። በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፥ በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል። ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ ጫፉም ከበላይ ይረግፋል። መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥ በሜዳም ስም አይቀርለትም። ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ ከዓለምም ያሳድዱታል። ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፥ በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም። የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥ እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ። በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ነፍሴን የምትነዘንዙት፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው? ይኸው ስትሰድቡኝ ዐሥር ጊዜ ነው፥ ስታሰቃዩኝም አላፈራችሁም። በእውነትም የሳትሁ እንደሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች። በእውነትም ብትኩራሩብኝ፥ በመዋረዴም ብታሳብቡ፥ እንግዲህ እግዚአብሔር ጥፋተኛ እንዳደረገኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ። እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፥ ድረሱልኝ ብዬ ብጣራ ፍርድ የለኝም። እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል። ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ። በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፥ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፥ ቁጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ። ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።” “ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ። ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ። እንግዶቼ በቤቴ፥ ሴቶች አገልጋዮቼም እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፥ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ። አገልጋዬን ብጠራ አይመልስልኝም፥ በአፌም መለማመጥ አለብኝ። ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ተጸየፉኝ። ሕፃናት እንኳ አጠቁኝ፥ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ። አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፥ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ። አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፥ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ። እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ራሩልኝ፥ ራሩልኝ፥ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና። ስለምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለምን አትጠግቡም?” “ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘለዓለም ቢቀረጽ! እኔን ግን የሚቤዥኝ ሕያው እንደሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንደሚቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዐይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። በእውነት፦ እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቁጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።” ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “እንድመልስ ሐሳቤ ይገፋፋኝል፥ ስለዚህም ውስጤ መታገሥ አቅቶታል። የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥ የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል። ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥ የክፉ ሰዎች ፉከራ አጭር መሆኑን አምላክን የሚክዱ ደስታቸው ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን? ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥ ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥ እንደ ፋንድያ ለዘለዓለም ይጠፋል፥ ያዩትም፦ ወዴት ነው ያለው? ይላሉ። እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፥ እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል። ያየችውም ዐይን ዳግመኛ አታየውም፥ ለስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ ይሰወራል። ልጆቹ ድሆቹን ይክሳሉ፥ በገዛ እጆቹ ሀብቱን ይመልሳል። አጥንቶቹ በወጣት ኃይል ተሞልተው ነበር፥ ነገር ግን አሁን ያ የወጣትነት ኃይሉ ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።” “ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥ ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥ ቢጠብቀውም ባይተወውም፥ በጉሮሮውም ቢይዘው፥ መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፥ እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል። የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፥ እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል። የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፥ የእባብም ምላስ ይገድለዋል። ወንዞቹን አይመለከትም፥ የማሩንና የቅቤውን ጅረት አያይም። የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፥ እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም። ድሀውን ረግጦአል፥ ትቶታልም፥ ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል።” “ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና የወደደው ነገር አላዳነውም። እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፥ ስለዚህ በረከቱም አይጸናም። በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፥ የጉስቁልናም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች። ሆዱን ሳያጠግብ እግዚአብሔር የቁጣውን ትኩሳት ይሰድድበታል፥ በምግብ መልክም ያዘንብበታል። ከብረት መሣሪያም ቢሸሽ፥ የናስ ቀስት ይወጋዋል። እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፥ ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፥ ፍርሃትም ይወድቅበታል። ለከበሩ ዕቃዎቹ ጨለማ ተዘጋጅቶአል፥ በሰው እፍ ያልተባለች እሳት ትበላዋለች፥ በድንኳኑ ውስጥ የቀረውም ይጋያል። ሰማይ በደሉን ይገልጥበታል፥ ምድርም ትነሣበታለች። የቤቱም ንብረት ይሰናበታል፥ በቁጣው ቀን በጐርፍ ተጠራርጎ ይወሰዳል። ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥ ከአምላክ የተመደበለት ርስቱ ይህ ነው።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፥ ይህም እንደ ማጽናናት ይቆጠርላችሁ። እናገር ዘንድ ተውኝ፥ ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ። በውኑ የኀዘን እንጉርጉሮዬን ለሰው እናገራለሁን? አለመታገሤ ተገቢ አይደለምን? ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፥ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ። እኔ ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፥ ሰውነቴንም መንቀጥቀጥ ይይዘዋል። ስለምን ክፉዎች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? ኃይላቸውንስ ስለምን ያጠነክራሉ? ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው። ቤታቸው በሰላም ከፍርሃት ነጻ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም። ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፥ ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም። ሕፃኖቻቸውን እንደ መንጋ ይለቃሉ፥ ልጆቻቸውም ይቧርቃሉ። ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል። ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፥ በሰላምም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።” እግዚአብሔርንም፦ “ከእኛ ዘንድ ራቅ፥ መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም። እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው? ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል?” ይላሉ። “እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን? የክፉዎች ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።” “የክፉዎች መብራት የጠፋው፥ መቅሠፍትም የመጣባቸው፥ እግዚአብሔርም በቁጣው መከራ የከፈላቸው፥ በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?” እናንተ፦ “እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል” ብላችኋል። ይልቁንም እራሳቸው ይረዱት ዘንድ ፍዳን ይክፈላቸው። ዐይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ቁጣ ይጠጡ። የወራታቸውስ ቍጥር ከተቈረጠ፥ ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል? ከፍ ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርደው እግዚአብሔር ሰው እውቀትን ሊያስተም ይችላልን? አንድ ሰው በሰላም ተረጋግቶ ሲቀመጥ ከነሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል። በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥ የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል። ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ በተመረረች ነፍስ ይሞታል። በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ ትልም ይከድናቸዋል። “እነሆ፥ ሐሳባችሁን፥ የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ። እናንተ፦ የከበርቴው ቤት የት ነው? ክፉዎች ያደሩበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል። መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን? ምስክርነታቸውንስ አትረዱምን? ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚተርፍ፥ በቁጣው ቀን እንደሚድን። ስለ መንገዱ ፊቱ ለፊት የሚወቅሰው ማን ነው? ስለ ሠራውስ የሚቀጣው ማን ነው? እርሱን ግን ለቀብር ይሸከሙታል፥ መቃብሩም ይጠበቃል። የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፥ በኋላውም ሰው ሁሉ ይከተለዋል፥ በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ። የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?” ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን? ይልቁንም ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል። ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን? መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን? እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን? ክፋትህስ ብዙ አይደለምን? ለዐመፅህም ወሰን የለውም። ከወንድሞችህ አላግባብ መያዣ ወስደሃል፥ የታረዙትንም ልብስ ዘርፈሃል። በጥም የደከመውን ውኃ አላጠጣህም፥ የተራበውንም እንጀራ ከልክለሃል። ኃይለኛ ሰው መሬት ገዛ፥ የተከበረ ሰው ተቀመጠባት። መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰድደሃቸዋል፥ የወላጅ አልቦችም ክንዶች ተሰብረዋል። ስለዚህ ወጥመዶች ከብበውሃል፥ ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል። እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥ የውኆችም ሙላት አሰጠመህ።” “እግዚአብሔር በላይ በሰማያት አይደለምን? ከዋክብትም እንዴት ከፍ ባለ ስፍራ ላይ እንዳሉ ተመልከት።” አንተም፦ “እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን? እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፥ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል” ብለሃል። “በውኑ ክፉ ሰዎች የሄዱበትን የዱሮውን መንገድ ትከተላለህን? ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፥ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።” እነርሱም እግዚአብሔርን፦ “ከእኛ ዘንድ ራቅ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል?” አሉት። “ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞልቶት ነበር፥ የክፉ ሰው ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት። ይህንን አይተው ጻድቃን ደስ ይላቸዋል፥ ንጹሑም ሰው ይስቅባቸዋል። በእውነት ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፥ ከንብረታቸው የተረፈውንም እሳት በላች።” “እንግዲህ አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፥ በዚያም መልካምን ታገኛለህ። ከአፉም ትምህርቱን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፥ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ትደረጃለህ ፥ ክፋትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ ወርቅን በአፈር ውስጥ ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፥ ስእለትህንም ትሰጣለህ። በጉዳዮችም ላይ ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፥ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል። ቢያዋርዱ፥ አንተ ‘መነሣት አለ’ ትላለህ፥ ትሑቱንም ሰው ያድነዋል። ንጹሑን ሰው ያድነዋል፥ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ዛሬም ደግሞ የኀዘን እንጉርጉሮዬ ገና መራራ ነው፥ በመቃተት ብጮኽም እጁ በእኔ ላይ እንደ ከበደች ናት። እርሱን እንዴት እንደማገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ! በፊቱ አቤቱታዬን አቀርብ ነበር፥ አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር። የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደሆነ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር። በታላቅ ኃይሉ ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? ይልቁንም! ማዳመጥ ይበቃው ነበር። የሚከራከረው ቅን ሰው መሆኑን ይመሰክር ነበር፥ እኔም በፈራጅ ፊት ለዘለዓለም ነፃ እወጣ ነበር።” “እነሆ፥ ወደፊትም ብሄድ፥ እርሱ የለም፥ ወደ ኋላም ብሄድ፥ አላየውም፥ ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አይታየኝም፥ በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፥ የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፥ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ። እግሬ ዱካውን ተከትሎአል፥ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ከመስመር አልወጣሁም። ከተናገራቸው ትእዛዛት አልኮበለልኩም፥ የአፉን ቃል በልቤ ደብቄአለሁ። እርሱ ግን የሚተካከለው የለውም፥ ማንስ ውሳኔውን ያስቀይረዋል? የወደደውንም ያደርጋል። በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፥ እንደዚህ ያሉ ብዙ ብያኔዎች እንዳሉት። ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፥ ባሰብሁም መጠን ፈራሁት። እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል። በጨለማው አልተደመሰስኩም፥ ነገር ግን ድቅድቁ ጨለማ ፊቴን ሸፈነ።” “ሁሉን የሚችል አምላክ የወሰናቸውን ጊዜያት ለምን አያሳውቅም? የሚያውቁትስ ቀኖቹን ለምን አያዩም? የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥ መንጋዎቹን ቀምተው ያሰማራሉ። የወላጅ አልባውን አህያ ይነዳሉ፥ የመበለቲቱን በሬ ለመያዣነት ይወስዳሉ። ድሆቹን ከመንገድ ያስወጣሉ፥ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ። እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል። እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ። ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ የሚደረብ የላቸውም። ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ። አባቱ የሞተበትን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ። ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥ ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ ፥ በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያወጣሉ፥ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ። በከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ያቃስታሉ፥ ቁስለኞችም ለእርዳታ ይጮኻሉ፥ እግዚአብሔር ግን ልመናቸውን አይመለከትም።” “እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም። ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው። የአመንዝራ ሰው ዐይን ጨለማን ይጠብቃል፦ የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። ቤቶቹን በጨለማ ይሰረስራሉ፥ በቀን ይሸሸጋሉ፥ ብርሃንም አያውቁም። የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥ የሞትን ጥላ አስደንጋጭነት ያውቃሉና።” “እነርሱ በውኃ ላይ ተንሳፈው ያልፋሉ፥ ድርሻቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይመለሱም። ድርቅና ሙቀት የበረዶውን ውኃ ያጠፋሉ፥ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች። ማኅፀን ትረሳዋለች፥ ትልም በደስታ ይጠባዋል፥ ዳግመኛም የሚያስታውሰው የለም፥ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።” “የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥ ለመበለቲቱም መልካም አያደርግም። ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ያስቀጥላል፥ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፥ ዐይኖቹ ግን መንገዳቸውን ይመለከታሉ። ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ። እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ከንቱ የሚያደርገው ማን ነው?” ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ገዢነትና መፈራት በእርሱ ዘንድ ናቸው፥ በከፍታውም ሰላምን የሚያሰፍን ነው። በውኑ ለሠራዊቱ ቍጥር ስፍር አለውን? ብርሃኑስ የማይወጣው በማን ላይ ነው? ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል? እነሆ፥ ጨረቃ እንኳ ብሩህ ካልሆነች፥ ከዋክብትም በፊቱ ንጹሐን ካልሆኑ። ይልቁንስ ፈራሽ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ!” ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው! ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት! ይህንንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? ያነሣሣህስ የማን መንፈስ ነው? ሙታን ከውኆች በታች፥ በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ በታች ይንቀጠቀጣሉ። ሲኦል በፊቱ ራቁትዋን ናት፥ ለጥፋትም መጋረጃ የለውም። ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም ያለአንዳች ድጋፍ ያንጠለጥላል። ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፥ ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም። የዙፋኑን ፊት ይሸፍናል፥ ደመናውንም ይዘረጋበታል። ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥ በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አሰመረ። የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ። በኃይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥ በማስተዋሉም ረዓብን ይመታል። በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም የሚሸሸውን እባብ ወጋች። እነሆ፥ እነኚህ የሥራዎቹ ጫፎች ብቻ ነው፥ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ማን ማስተዋል ይችላል?” ኢዮብም ምሳሌውን ቀጠለ፥ እንዲህም አለ፦ “ፍርዴን ያስቀረ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም ያስመረራት ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን! እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥ ከንፈሬ ኃጢአትን አይናገርም፥ አንደበቴም ሽንገላን አያወጣም። እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፥ እስክሞት ድረስ ንጹሕነቴን ከእኔ አላርቅም። በጽድቄ እጸናለሁ እርሱንም አልተውም፥ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱም እንኳን ኅሊናዬ አይወቅሰኝም።” “ጠላቴ እንደ በደለኛ፥ በእኔ ላይም የሚነሣ እንደ ኃጢአተኛ ይሁን። እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በወሰደ ጊዜ፥ አምላክን የካደ ሰው ተስፋው ምንድነው? በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን? ሁሉንስ በሚችል አምላክ ደስ ይለዋልን? እግዚአብሔርንስ ሁልጊዜ ይጠራልን? እኔ ስለ እግዚአብሔር ሥራዎች አስተምራችኋለሁ፥ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውን አልሸሽግም። እነሆ፥ ሁላችሁም አይታችኋል፥ ታዲያ ለምን በከንቱ ትባክናላችሁ?” “እነሆ የበደለኛ እድል ፈንታ ከእግዚአብሔር ዘንድ፥ ግፈኛም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበላት ርስት ይህችው፥ ልጆቹ ቢበዙ በሰይፍ ይሞታሉ፥ ዘሩም በቂ እንጀራ ከቶ አያገኝም። ለእርሱ የተረፉትም በቸነፈር ይቀበራሉ፥ መበለቶቻቸውም አያለቅሱላቸውም። እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢከምር፥ ልብስንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥ እርሱ ያዘጋጀው ይሆናል፥ ነገር ግን ጻድቅ ይለብሰዋል፥ ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል። የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር፥ ጠባቂም እንደሚሠራው ጎጆ ነው። ባለ ጠጋ ሆኖ ይተኛል፥ ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ ነው፥ ዓይኑን ሲከፍት፥ እርሱም የለም ። ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ታገኘዋለች፥ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች። የምሥራቅ ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ይሄዳል፥ ከቦታውም ይጠርገዋል። ነፋሱ ይጥልበታል፥ አይራራለትም፥ እርሱ ግን ከእጁ ፈጥኖ ለመሸሽ ይታገላል። ነፋሱ ያጨበጭብበታል፥ ከስፍራውም በፉጨት ያስወጣዋል።” “በእውነቱ ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ። ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፥ ከቀለጠ ድንጋይም መዳብ ይወጣል። ለጨለማ ወሰን ይደረጋል፥ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ጫፍ ድረስ ይፈላልጋል። ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ በመንገድኞችም ተረስተዋል፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ። ምድር እንጀራን ታበቅላለች፥ ከበታቿ ያለው ግን እንደ እሳት ይገለባበጣል። እዚያ ድንጋዮችዋ የሰንፔር መከማቻ ናቸው፥ የወርቅም ድቃቂ ይገኛል።” “መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዐይን አላየውም። ኩሩ አውሬዎች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።” “ሰው ወደ ጠንካራ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል። ከድንጋይ ውስጥ መተላለፍያ ይሠራል፥ ዓይኑም ዕንቁን ሁሉ ታያለች። የወንዞችን መነሻዎች ይፈልጋል ፥ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።” “ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? ሰው መንገድዋን አያውቅም፥ በሕያዋን አገር አትገኝም። ቀላይ፦ በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፥ ባሕርም፦ በእኔ ዘንድ የለችም ይላል። በንጹሕ ወርቅ አትገኝም፥ ዋጋዋም በብር አይተመንም። በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም። ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ ከጥሩ ወርቅ በተሠራ ዕቃም አትለወጥም። ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ይበልጣል። የኢትዮጵያ ቶጳዝዩን አይተካከላትም፥ በንጹሕ ወርቅም አትገመትም።” “እንግዲያውስ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? ከሕያዋን ሁሉ ዐይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎችም ተሸሽጋለች። ጥፋትና ሞት፦ ስለ እርሷ በወሬ ሰማን ብለዋል።” “እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል። እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል። ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥ ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፥ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት። ሰውንም፦ ‘እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፥ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።” ኢዮብም ንግግሩን ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ! በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥ ብርቱ እንደ ነበርኩበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን ይጠብቅ በነበረበት ጊዜ፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥ መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ዓለቱ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ። ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥ ወጣቶች እኔን አይተው ይሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ይቆሙ ነበር። መኮንኖች ከመናገር ዝም ይሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር። የታላላቅ ሰዎች ድምፅ ይደበቅ፥ ምላሳቸውም ከትናጋቸው ጋር ይጣጋ ነበር። የሰማችኝ ጆሮ ታሞግሰኝ፥ ያየችኝም ዐይን ትመሰክርልኝ ነበር፥ የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ወላጅ አልባውንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና። ለሞት የቀረበው ሰው በረከት በላዬ ይደርስ ነበር፥ የመበለቲቱንም ልብ እልል አሰኝ ነበር። ጽድቅን ለበስሁ እርሷም ለበሰችኝ፥ ፍርዴም እንደ ካባና እንደ ቆብ ነበረ። ለዐይነ ስውር ዐይን፥ መሄድ ለተሳነው እግር ነበርሁ። ለድሀው አባት ነበርሁ፥ ለማላውቀውም ሰው ጠበቃ ነበርሁ። የግፈኛውን መንጋጋ እሰብር፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጥል ነበር። እኔም፦ ‘በልጆቼ መካከል በክብር እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፥’ እል ነበር፤ ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግተው፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድር ነበር፤ ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶ፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞ ነበር። ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ። ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፥ ንግግሬም በእነርሱ ላይ ተንጠባጠበ። ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፥ የበልግን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ። እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፥ የፊቴም ብርሃን አበረታታቸው። መንገዳቸውን መረጥሁ፥ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፥ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኀዘንተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።” “አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ። የቀድሞ ጥንካሬአቸው ጠፍቶ ነበርና የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል? በችግርና በራብ መንምነው፥ በፈረሰውንና በተተወው የጨለመ ምድረ በዳን ሥራ ሥሮችን ያኝካሉ። በቁጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን ቅጠላ ቅጠል ይቀጥፋሉ፥ እንዲሞቃቸውም የክትክታ ሥር ይበላሉ። ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፥ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል። በሸለቆ ጉድጓድ፥ በምድርና በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ። በጫካ ውስጥ ይጮኻሉ፥ ከቁጥቋጦ በታች ተሰብስበዋል። የአላዋቂና የነውረኞች ልጆች ናቸው፥ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።” “አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው። ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፥ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም። የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፥ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል ። በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ያሰናክላሉ፥ የጥፋታቸውን መንገዶች በእኔ ላይ ይቀይሳሉ። ጐዳናዬን ያበላሻሉ፥ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ። በሰፊው መከላከያን ጥሰው እንደሚመጡ ይመጡብኛል፥ በፍርስራሽ ውስጥ ይንከባለላሉ። ድንጋጤ በላዬ ተመለሰብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱታል፥ ብልጽግናዬም እንደ ደመና አልፋለች።” “እነሆ ሕይወቴ እያለቀች ነው፥ የመከራም ዘመን ያዘኝ። የሌሊቱ ስቃይ እስከ አጥንቶቼ ድረስ ይዘልቃል፥ ሁለመናዬንም ስለሚበላኝ ጅማቶቼ አያርፉም። ከሕመሜ ብርታት የተነሣ ልብሴ ተበላሸ፥ እንደ ቀሚስ ክሳድ ያንቀኛል። በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ። ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፥ ተነሣሁ፥ ነገር ግን ዝም ብለህ ተመለከትኸኝ። ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፥ በጠንካራ እጅህም አሰቃየኸኝ። በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስጋለብከኝ፥ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ። ለሞት፥ ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።” “ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጅ አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን? ለተጨነቁት አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን? ነገር ግን በጎነትን ስጠባበቅ ክፉ ነገር መጣብኝ፥ ብርሃንን ተስፋ ሳደርግ ጨለማ መጣ። አንጀቴ ተናወጠ፥ አላረፈምም፥ የመከራም ዘመን መጣብኝ። በፀሐይ ሳይሆን በትካዜ ጠቁሬ ሄድሁ፥ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ። ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ። ቆዳዬ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፥ አጥንቴም ከትኩሳት የተነሣ ተቃጠለ። ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ መሳርያ ሆነ።” “ከዐይኖቼ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ፥ እንግዲህ ቈንጆይቱን እንዴት በፍትወት እመለከታለሁ? የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስትስ ከአርያም ምንድነው? መዓትስ ለኃጢአተኛ፥ መገለልስ ለሚበድሉ ሰዎች አይደለችምን? መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?” “በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ። በሐሰት ሄጄ እንደሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኩላ እንደሆነ፥ እርምጃዬ ከመንገድ ወጥቶ፥ ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ ነውርም ነገር ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደሆነ፥ እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፥ የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።” “ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደሆነ፥ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርሷ ላይ ይጐንበሱ። ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፥ ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚያቃጥል ነውና።” “ወንዶችና ሴቶት አገልጋዮቼ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን ንቄ እንደሆነ፥ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታልሁ? እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?” “ድሀውን ከሚያስፈልገው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዐይን አጨልሜ እንደሆነ፥ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደሆነ፥ ወላጅ አልባውም ሳይደርሰው ቀርቶ እንደሆነ፥ ለነገሩማ ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባት ሆኜ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ መበለቲቱንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፥ ከልብስ እጦት የተነሣ አንድ ሰው ሲጠፋ አይቼ፥ ወይም ድሀ የሚሸፈንበት ሲያጣ ተመልክቼ፥ ማን ነው ከአንጀቱ ያልባረከኝ፥ በበጎቼም ጠጉር ያልሞቀ? በይፋ ድጋፍ አለኝ ብዬ፥ በወላጅ አልባ ላይ እጄን አንሥቼ የቃታሁ እንደሆነ፥ ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር። የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፥ በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።” “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ ንጹሑንም ወርቅም መተማመኛዬ ብዬ ጠርቼው እንደሆነ፥ ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደሆነ፥ ፀሐይ ስታበራ ጨረቃም በክብር ስትሄድ አይቼ፥ ልቤ በስውር ተታልሎ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደሆነ፥ ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና፥ ይህ ደግሞ በፈራጆች የሚያስቀጣ በደል በሆነ ነበር።” “በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደሆነ፥ ነገር ግን ነፍሱ እንዲጠፋ በመራገም አንደበቴ ኃጢአት እንዲሠራ አልፈቀድሁም፥ በድንኳኔ ሥር የሚኖሩ ሰዎች፦ ‘በሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል?’ ይሉ የለምን? እንግዳው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፥ በደሌንም በውስጤ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደሆነ፥ ከሕዝብ ብዛት የተነሣ ፈርቼ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደሆነ፥ የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ! እነሆ የእጄ ምልክት፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፥ ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ! በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ ላይ አስረው ነበር፥ የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥ እንደ መስፍንም ሆኜ እቀርብለት ነበር።” “እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኾ እንደሆነ፥ ትልሞቹም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደሆነ፥ ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥ የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደሆነ፥ በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥ በገብስም ፋንታ ኩርንችት ይውጣብኝ።” የኢዮብ ቃል ተፈጸመ። ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቁጣ ነደደ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። እንዲሁም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ኤሊሁ ከኢዮብ ጋር የሚናገርበትን ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አንደበት መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቁጣው ነደደ። የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ “እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፥ ስለዚህም ሰጋሁ፥ የማውቀውን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። እንደዚህም አልሁ፦ ‘ዕድሜ ይናገር፥ ረጅም ዕድሜም ጥበብን ያስታውቅ።’ ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። በዕድሜ ያረጁ የግድ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም የግድ ፍርድን አያስተውሉም። ስለዚህም፦ ‘ስሙኝ፥ እኔ ደግሞ እውቀቴን ልግለጥላችሁ’ አልሁ።” “እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ ሙግታችሁን አዳመጥሁ። እንዲሁም ልብ በማድረግ ሰማኋችሁ፥ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም። እናንተም፦ ጥበብን አግኝተናል፥ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ። እርሱ እኔን አይደለም የተናገረው፥ እኔም በእናንተ አነጋገር ዓይነት አልመልስለትም። እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፥ የሚናገሩትንም አጡ። እነርሱ አልተናገሩምና፥ ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን? እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥ እውቀቴንም እገልጣለሁ፥ እኔ በቃላት ተሞልቻለሁና፥ በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና። እነሆ፥ አንጀቴ በአዲስ ወይን ጠጅ ተሞልቶ ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥ መውጫም እንደሚፈልግ ወይን ጠጅ ሆነ። ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፥ ከንፈሮቼን ከፍቼ እመልሳለሁ። በማንም ሰው ፊት ግን አላደላም፥ ማንንም አላቈላምጥም። በማቈላመጥ መናገር አላውቅምና፥ ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ባጠፋኝ ነበር።” “እንግዲህ፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ። እነሆ፥ ለመናገር ተዘጋጅቻለሁ፥ አንደበቴም ቃላትን አሰናድቷል። ቃሎቼ የልቤን ቅንነት ያሳያሉ፥ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ። የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ። ይቻልህ እንደሆነ መልስልኝ፥ የምትለውን አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም። እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ እኔም እንዳንተ ከጭቃ የተቀረጽሁ ነኝ። እነሆ፥ ግርማዬ አያስፈራህም፥ እኔም አልጫንህም።” “በጆሮዬ ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፤ እንዲህም ብለሃል፦ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፥ በደል የለብኝም፤ ያለ እንከን ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፥ እነሆ፥ ሊወቅሰኝ ምክንያት ይፈጥራል፥ እንደ ጠላቱም ይቈጥረኛል፥ እግሬን በግንዶች መካከል ያጣብቃል፥ መንገዶቼን ሁሉ ይቆጣጠራል።’ እነሆ፥ አንተ በዚህ አቋምህ ትክክል አይደለህም፥ ‘እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል’ ብዬ እመልስልሃለሁ። አንተ፦ ‘በፍጹም ለቃሌ መልስ አይሰጥም’ ብለህ፥ ስለምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ? እግዚአብሔር በአንድም በሁለትም መንገድ ይናገራል፥ ሰው ግን አያስተውለውም። በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ፥ ሰውንም ከትዕቢት ይቆጥበው ዘንድ፥ ነፍሱን ከጉድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።” “ደግሞ በአልጋ ላይ በስቃይ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱም ሁሉ ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣል። ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች። ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፥ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል። ነፍሱ ወደ ጉድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች። የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጉም መልአክ ቢገኝለት፥ እየራራለት፦ እሱን መታደጊያ ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ መቃብር እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥ ሥጋው እንደ ልጅ ሥጋ ይለመልማል፥ ወደ ወጣትነቱም ጊዜ ይመለሳል። ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ይሰማዋል፥ ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፥ ለሰውም የጽድቁን ዋጋ ይመልስለታል። እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ፦ እኔ በድያለሁ፥ ቀናውንም አጣምሜአለሁ፥ የሚገባኝንም ቅጣት አልተቀበልሁም፥ ነፍሴ ወደ መቃብር እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል።” “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፥ ይህም ነፍሱን ከመቃብር ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው። ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፥ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ። የምትናገረው ቢኖርህ መልስልኝ፥ ትክክል መሆንህን እወድዳለሁና ተናገር። አለበለዚያም እኔን ስማ፥ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።” ኤሊሁም ደግሞ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፥ እናንተም አዋቂዎች፥ ወደ እኔ አድምጡ። ምላስ መብልን እንደሚያጣጥም፥ ጆሮም ቃላትን ይለያልና። ፍትሕን እንምረጥ፥ መልካሙንም ነገር በመካከላችን እንወቅ። ኢዮብ፦ እኔ ንጹሕ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን ፍርድ ከለከለኝ፥ ምንም እውነተኛ ብሆን እንደ ውሸተኛ ተቈጠርሁ፥ ምንም ባልበድል ቁስሌ የማይፈወስ ነው ብሏል። ኢዮብም፦ በእግዚአብሔር መደሰት ለሰው ምንም አይጠቅምም ብሏልና፥ ከበደለኞች ጋር የሚተባበር፥ ክፉ ከሚያደርጉስ ጋር የሚሄድ፥ ሹፈትን እንደ ውኃ የሚጠጣት እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?” “ስለዚህ የምታስተውሉ ሰዎች፥ ስሙኝ፥ ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር፥ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ። ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፥ ሰውም እንደ መንገዱ ያገኝ ዘንድ ያደርጋል። በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም። ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው? ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው? እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥ መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል።” “አስተዋይ ከሆንክ ይህን ስማ፥ ንግግሬንም አድምጥ። በውኑ ጽድቅን የሚጠላ ሊገዛ ይገባዋልን? ጻድቅና ኃያል የሆነውንስ በደለኛ ታደርገዋለህን? ማንም ሰው ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ፥ መኰንኖቹን፦ ክፉዎች ናችሁ ይላልን? እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና ለአለቆች አያደላም፥ ሀብታሙንም ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም። እነርሱ በእኩለ ሌሊት በድንገት ይሞታሉ፥ ሕዝቡ ተንቀጥቅጦ ያልፋል፥ ኃያላንም ያለ ምንም ድካም ይወገዳሉ። ዐይኖቹ የሰውን መንገድ ይመለከታሉ፥ የሰውን እርምጃ በሙሉ ያያል። ክፋትን የሚሠሩ የሚደበቁበት ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም። ሰው ወደ እግዚአብሔር ለፍርድ ለመቅረብ ቀጠሮ አይሰጠውም። ኃያላንን ያለ ምርመራ ይሰባብራል፥ በእነርሱም ፋንታ ሌሎችን ያቆማል። ሥራቸውን ያውቃል፥ በሌሊት ይገለባብጣቸዋል፤ እነርሱም ይደቃሉ። ሰዎች እያዩ እንደ ክፉዎች ይመታቸዋል፥ የድሀውን ልቅሶ እስኪሰማ ድረስ፥ የችግረኛውን ድምፅ እስኪሰማ ድረስ፥ እርሱን ከመከተል ርቀዋልና፥ ከመንገዱም አንዱንም አልተመለከቱምና። ሕዝብንም ሆነ ሰውን በተመለከተ፥ ዝም ቢል የሚፈርድ ማን ነው? ፊቱንስ ቢሰውር የሚያየው ማን ነው? ይህም እግዚአብሔርን የሚክድ እንዳይነግሥ፥ በሕዝቡም ላይ ወጥመድ የሚዘረጋ እንዳይኖር ነው። እግዚአብሔርን፦ እኔ ሳልበድል ቅጣት ተቀበልሁ፥ የማላየውን ነገር አንተ አስተምረኝ፥ ኃጢአትንም ሠርቼ እንደሆነ፥ ደግሜ አልሠራም የሚለው ማን ነው? በውኑ አንተ ተቃውመኸዋልና ሽልማቱ አንተ እንደምትወድደው ይሆናልን? እኔ ሳልሆን አንተ ነህ የምትመርጠው፥ ስለዚህ የምታውቀውን ተናገር። የሚሰሙኝ ጥበበኞች ሁሉ፥ አስተዋዮችም እንዲህ ይሉኛል፦ ኢዮብ ያለ እውቀት ተናግሮአል፥ ንግግሩም ማስተዋል ይጎድለዋል። ኢዮብ እስከ መጨረሻ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ! እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና፥ በኃጢአቱም ላይ ዓመፅን ጨምሮአልና፥ በእኛም መካከል በፌዝ ያጨበጭባልና፥ እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ቃላትን ያበዛልና።” ኤሊሁም ደግሞ ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ትክክል ነው ብለህ ታስባለህን? ወይስ፦ በእግዚአብሔር ፊት እኔ ጻድቅ ነኝ ትላለህን? አንተ፦ ምን ትጠቀማለህ? ኃጢአት ባልሠራስ ምን እጠቀማለሁ? ብለህ ጠይቀሃልና። እኔ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉትም ባልንጀሮችህ እመልሳለሁ። ዐይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ እይ፥ ከአንተም በላይ ከፍ ያሉትን ደመናት ተመልከት። ኃጢአት ብትሠራ ምን ትጐዳዋለህ? መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ? ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል? ክፋትህ እንደ አንተ ያለውን ሰው ይጐዳዋል፥ ለሰውም ልጅ ጽድቅህ ይጠቅመዋል። ከግፍ ብዛት የተነሣ ሰዎች ይጮኻሉ፥ ከኃያላንም ክንድ የተነሣ ለእርዳታ ይጣራሉ። ነገር ግን፦ በሌሊት የደስታ መዝሙሮችን የሚለግስ፥ ከምድርም እንስሶች ይልቅ የሚያስተምረን ከሰማይም ወፎች ይልቅ ጥበበኞች የሚያደርገን ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም። በዚያ ስለ ክፉ ሰዎች ትዕቢት ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይመልስላቸውም። በእውነት እግዚአብሔር ከንቱ ነገርን አይሰማም፥ ሁሉን የሚችል አምላክም አይመለከተውም፥ እንዲያውም፦ ‘አላየውም፥ ጉዳዩ በእርሱ ፊት ነው፥ እኔም አጠብቀዋለሁ’ ስትልማ የባሰ ነው። አሁን ግን በቁጣው ስላልቀጣ፦ ትዕቢት ምን እንደሆነ የማያውቅ መሰለህ? ስለዚህ ኢዮብ ከንቱ ንግግርን ከአፉ ያወጣል፥ ያለ እውቀትም ቃሉን ያበዛል።” ኤሊሁም ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦ “ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ። እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ፈጣሪዬም ጻድቅ መሆኑን አሳይሃለሁ። ቃሌ በእውነት ሐሰት የለበትም፥ በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ። እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፥ እርሱም በጥበባዊ ኃይሉም ጽኑ ነው። እርሱ በደለኛን በሕይወት አይጠብቅም፥ ለችግረኞች ግን ይፈርዳል። ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፥ ለዘለዓለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ። በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥ ተግባራቸውንና መተላለፋቸውን በትዕቢትም እንደሚሠሩም ይናገራቸዋል። ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥ ከክፋትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል። ከሰሙትና ካገለገሉት፥ ዕድሜአቸውን በብልጽግና፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ። ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥ ያለ እውቀትም ይሞታሉ። ልበ ደንዳኖች ግን ቁጣን ይወዳሉ፥ እርሱም ባሠራቸው ጊዜ አይጮኹም። በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥ ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል። የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፥ በመከራም እንዲሱሙ ያደርጋቸዋል ። እንዲሁም አንተን ከመከራ ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥ በማዕድህም ላይ ቅባት የሞላበት ምግብ በተዘጋጀ ነበር። አንተ ግን የበደለኞች ፍርድ ደረሰብህ፥ ፍርድና ብይን እንደሚይዛቸው። ሀብት ወደ ስድብ አስቶ እንዳይወስድህ፥ ትልቅ ጉቦም ከመስመር እንዳያስወጣህ። ብልጽግናህና ኃይልህ በሙሉ ከችግር የሚጠብቅህ ይመስልሃልን? ሰዎች ድንገት የሚሞቱበትን ሌሊትን አትመኛት። አሁን ከመከራ የምትፈተነው ለዚሁ ነውና፥ ወደ በደል እንዳትመለስ ተጠንቀቅ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ልዑል ነው፥ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው? ማነው መንገዱን የሚያሳየው? ወይስ፦ ‘ተሳስተሃል’ የሚለው ማን ነው? ይልቁንም ሰዎች የዘመሩለትን ሥራውን ማክበርን አስታውስ። ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፥ ሰውም ከሩቅ ያየዋል። እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፥ ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በገፍ ያፈሳሉ። የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው? እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፥ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል። በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፥ ብዙም ምግብ ይሰጣል። መብረቅን በእጆቹ ይይዛል፥ ያዘዘውንም እንዲመታ ያደርገዋል፥ የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፥ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።” “ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥ ከስፍራውም ውጭ ዘለለ። የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጉርምርምታ አድምጡ። መብረቁንም ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ወደ ምድርም ዳርቻ ይሰድዳል። ከበስተኋላው ድምፅ ያገሣል፥ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጉዳል፥ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም። እግዚአብሔር በአስደናቂ ሁኔታ በድምፁ ያንጐደጉዳል፥ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ፦ በምድር ላይ ውደቁ ይላል። ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ። ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥ ከሰሜንም ብርድ ይወጣል። ከእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ተሰጥቶአል፥ የውኆችም ስፋት ይጠጥራል። የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፥ የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፥ ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረትም ቢሆን፥ ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ፈቃዱ ወደ መራቸው ይዞራሉ። ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፥ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ። በውኑ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያዝዛቸው፥ የደመናውንም ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን? ወይስ የደመናውን መንሳፈፍ፥ ወይስ በእውቀት ፍጹም የሆነውን ተአምራት አውቀሃልን? በደቡብ ነፋስ ምድር ጸጥ ባለች ጊዜ፥ ልብስህ የሞቀች አንተ ሆይ፥ እንደ ቀለጠ መስተዋት ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን? እኛ ከጨለማ የተነሣ በሥርዓት መናገር አንችልምና ለርሱ የምንለውን አስታውቀን። ማንም በእርሱ ላይ ቢናገር ፈጽሞ ይዋጣልና እኔ መናገር እንደምፈልግ መንገር ድፍረት አይሆንምን? አሁንም ነፋስ አልፎ ካጠራቸው በኋላ፥ ሰው በሰማያት የሚበራውን ብርሃን ሊመለከት አይችልም። ከሰሜን ወርቅ የሚመስል ጌጠኛ ብርሃን ይወጣል፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈራ ግርማ አለ። ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፥ በኃይል ታላቅ ነው፥ በፍርድና በጽድቅም ሃብታም ነው፤ አይጨቁንምም። ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፥ በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም።” እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እውቀት በጎደለው ንግግር ምክርን የሚያጨልመው ማነው? እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ታሳውቀኛለህ። ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? ታስተውል እንደሆንህ ተናገር። የምታውቅ እንደሆነ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋም የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥ ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦ እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ። በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘህ ታውቃለህን? ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን? የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርሷም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁም እርሱ ይለወጣል፥ ፍጥረትም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል። ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል። ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገበተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን? የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን? ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደሆነ ተናገር። ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ? በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለውጊያና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው። ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፋፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል? ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ ... ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብ እንዲዘንብ፥ ለፈሳሹ ውኃ መተላለፊያውን፥ ወይም ለሚያንጐደጉድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይም የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል። በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲፈጸም ማድረግ ትችላለህን? የውኆች ሙላት ይሸፍንህ ዘንድ። ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? መብረቆች ሄደው፦ ‘እነሆ፥ እዚህ አለን’ ይሉህ ዘንድ፥ ልትልካቸው ትችላለህን? በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ደመና ለዝናብ ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው? በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን? ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?” “የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን? ከእርሷ የሚወስዱባትንስ ወራት መቁጠር ትችላለህን? የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን? ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥ ከምጣቸውም ያርፋሉ። ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥ በሜዳም ያድጋሉ፥ ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም። የሜዳውንስ አህያ ማን ነፃ ለቀቀው? የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው? በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፥ መኖሪያውም በጨው ምድር ነው። በከተማ ውካታ ይስቃል፥ የነጂውን ጩኸት አይሰማም። ተራራውን እንደ መሰማርያው ይቃኘዋል፥ ለምለሙንም ሣር በሙሉ ይፈልጋል። ጐሽ ሊያገለግልህ ፈቃደኛ ነውን? ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን? ጐሽ እንዲተልምልህ ልታጠምደው ትችላለህን? ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጉላልን? ጉልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ በእርሱ ትታመናለህን? አድካሚ ሥራህን ለእርሱ ትተዋለህን? ወደ አንተ እንደሚመለስና፥ ሰብልህንስ በአውድማህስ እንደሚያከማችልህ ትተማመናለህን? ምንም እንኳን እንደ ሸመላ ባትበርም፥ የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤ እንቁላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፥ እግር ሊሰብረው እንደሚችል፥ የምድረ በዳም አውሬ ሊረግጠው እንደሚችል ትረሳለች። የእርሷ ያልሆኑ ይመስል በልጆችዋ ትጨክናለች፥ ድካምዋ ከንቱም ሊሆን ቢችልም አትፈራም፥ እግዚአብሔር ጥበብን ነሥቷታልና፥ ማስተዋልንም አላደላትምና። ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች። ለፈረስ ጉልበቱን ትሰጠዋለህን? አንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን? እንደ አንበጣስ ታፈናጥረዋለህን? ግርማዊ ማንኰራፋቱ እጅግ ያስፈራል። በሸለቆው ውስጥ በኮቴው ይጐደፍራል፥ በጉልበቱም ደስ ይለዋል፥ ሰይፍ የታጠቁትንም ለመጋፈጥ ይወጣል። በፍርሃት ላይ ይስቃል፥ በጭራሽ አይደነግጥም፥ ሰይፍም አያሸሸውም። በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆ፥ የሚብለጨልጭ ጦርና ሰላጢን ያንኳኳሉ። በነውጥና በቁጣ መሬትን ይውጣል፥ የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም። የመለከትም ድምፅ ሲሰማ፦ እሰይ! ይላል፥ ከሩቅ ሆኖ የሠራዊቱን ውካታ፥ ፍልምያውንና የአለቆቹን ጩኸት፥ ያሸታል። በውኑ ጭልፊት የሚያንዣብበው፥ ክንፎቹንስ ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ጥበብ ነውን? ንስር ከፍ ከፍ የሚለው፥ ቤቱንም በከፍታ ላይ የሚያደርገው በአንተ ተእዛዝ ነውን? የሌሊት መኖርያው ዓለት ነው፥ የዓለት ጫፍም መከላከያ ይሆነዋል። በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፥ ዐይኖቹም ከሩቅ ይመለከታሉ። ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፥ በድን ባለበትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።” እግዚአብሔርም ቀጠለ፤ ኢዮብንም እንዲህ አለው፦ “በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን የሚችል አምላክን መተቸት ይችላልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።” ኢዮብም መለሰ፤ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፥ የምመልስልህ ምንድነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ። አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፥ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።” ጌታም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ላይ ትፈርዳለህን? እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጉዳለህን? ግርማንና ልዕልናን ተላበስ እንጂ፥ ሞገስንና ክብርን ተጐናጸፍ። የቁጣህን ሙላት አፍስስ፥ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው። ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፥ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው። በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፥ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን። በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ልታድንህ እንደምትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ። አንተን እንደሠራሁ የሠራሁትን ጉማሬ ፥ እስኪ፥ ተመልከት፥ እንደ በሬ ሣር ይበላል። እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፥ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው። ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፥ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው። አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፥ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው። እርሱ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ አውራ ነው፥ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው። የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል። ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል። ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፥ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል። እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፥ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል። ዐይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን? በውኑ አዞውን በመንጠቆ ታወጣለህን? ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን? ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር መንጋጋውን ትበሳለህን? በውኑ ወደ አንተ በእጅግ ይማጸናልን? በለሰለሰ ቃል ይናገርሃልን? በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘለዓለም ባርያ ታደርገዋለህን? ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ ለሴት ልጆችህ መዝናኛ እንዲሆን ታስረዋለህን? አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን? ወይስ ነጋዴዎች ያካፋፍሉታልን? በውኑ ቆዳውን በጦር፥ ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን? እስቲ እጅህን በላዩ ጫን፥ ፍልሚያውን በሚገባ ታስታውሳለህ፥ ሁለተኛም አይለምድህም።” “እነሆ፥ ተስፋ ማድረግ ከንቱ ነው፥ እርሱን ማየቱ ብቻ ያብረከርካል። ማንም ሊቀሰቅሰው የሚደፍር የለም፥ እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው? እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው? ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው። ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥ ስለ መልካም ሰውነቱም ዝም አልልም። የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል? በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል? የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ። የጀርባው ቆዳዎች ጠንካራ ናቸው፤ አቤት ኩራት! በጥብቅ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው። እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም። እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፥ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል። ሲያስነጥስ ብልጭታ ያወጣል፥ ዐይኖቹም እንደ ንጋት ወገግታ ናቸው። ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥ የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል። እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል። እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥ ነበልባልም ከአፉ ይወጣል። አንገቱ በጣም ጠንካራ ነው፥ ግርማ በፊቱ ይዘፍናል። ሥጋውም እርስ በርስ የተጣበቀ ነው፥ ምንም ላያንቀሳቅሳቸው በእርሱ ላይ ጸንተዋል። ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፥ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው። በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፥ ከድንጋጤም የተነሣ ይናወጣሉ። ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም። ብረትን እንደ ገለባ፥ ናስንም እንደ ነቀዝ እንጨት ይቆጥራል። ቀስት ሊያባርረው አይችልም፥ የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል። ዱላን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፥ ሰይፎች ሲንቀጠቀጡ ይስቃል። የአካሉ ታችኛው ክፍል እንደ ስለታም ገል ነው፥ እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል። ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፥ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል። በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፥ ቀላዩም ሽበት ይመስላል። ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም። ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፥ በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።” ኢዮብም መለሰ፤ ጌታንም እንዲህ አለው፦ “ሁሉንም ማድረግ እንድምትችል፥ ሐሳብህም ሊከለከል ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፥ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አሳውቀኝ። መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፥ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፥ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፥ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።” ጌታም ይህንን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፥ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፦ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ አገልጋዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ጥፋታችሁ እንዳላደርግባችሁ ጸሎቱን እሰማለሁ፥ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።” ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ጌታም የኢዮብን ጸሎት ሰማ። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ሲጸልይ ጌታ ምርኮውን መለሰለት፥ ጌታ ቀድሞ በነበረው ፋንታ በሁለት እጥፍ አሳድጎ ለኢዮብ ሰጠው። ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፥ ስለ እርሱም አዘኑለት፥ ጌታም ካመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አጽናኑት፥ እያንዳንዳቸውም ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት። ጌታም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፥ ዐሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት። ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት። የመጀመሪያይቱንም ይሚማ፥ ሁለተኛይቱንም ቃስያ፥ ሦስተኛይቱንም ቄሬንህፉክ ብሎ ሰየማቸው። እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆችም ያሉ የተዋቡ ሴቶች በአገሩ ሁሉ አልተገኙም፥ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ። ብፁዕ ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በፌዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በጌታ ሕግ ደስ የሚለው፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለ፥ ፍሬውን በየጊዜው እንደሚሰጥ፥ ቅጠሉም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፥ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም። ጌታ የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች። አሕዛብ ለምን ያጉረመርማሉ? ለምንስ ከንቱዉን ያሰላስላሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በጌታና በመሢሑ ላይ ተማከሩ፦ ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል ። በሰማያት የሚቀመጠውም እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቁጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል። እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። ትእዛዙን እናገራለሁ፥ ጌታ አለኝ፦ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።” ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ታደቃቸዋለህ። አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፥ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። ለጌታ በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቁጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው። ከልጁ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸ ጊዜ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው። ብዙ ሰዎች ነፍሴን፦ አምላክሽ አያድንሽም አልዋት። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ጋሻዬ ነህ፥ ክብሬና ራሴንም ቀና የምታደርገው አንተ ነህ። በሙሉ ድምጽ ወደ ጌታ እጮሃለሁ፥ ከተቀደሰ ተራራውም ይሰማኛል። እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፥ ጌታም ደግፎኛልና ነቃሁ። የሚከቡኝን አእላፍ ሕዝብ አልፈራም። ተነሥ፥ አቤቱ፥ አምላኬ ሆይ፥ አድነኝ፥ አንተ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና፥ የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና። ማዳን የጌታ ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው። ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች፥ የዳዊት መዝሙር። የጽድቄ አምላክ ሆይ በጠራሁህ ጊዜ መልስልኝ፥ በጭንቀቴም አሰፋህልኝ፥ ማረኝ፥ ጸሎቴንም ስማ። እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ክብሬን ታዋርዳላችሁ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወድዳላችሁ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ? በጻድቁ እንደ ተገለጠ እወቁ፥ ጌታ ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል። ፍሩ ፥ ኃጢአትንም አትሥሩ፥ በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፥ ዝምም በሉ። የጽድቅን መሥዋዕት ሠዉ፥ በጌታም ታመኑ። በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህን ብርሃን በላያችን አንሣ። በልቤ ደስታን ጨመርህ፥ ከስንዴ ፍሬያቸውና ከወይናቸው ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፥ አቤቱ፥ አንተ ብቻ በደኅንነት ታሳድረኛለህና። ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ቃሌን አድምጥ፥ መቃተቴንም አስተውል፥ የጩኸቴን ድምፅ አድምጥ፥ ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁና። በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም። አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፥ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም። በከንቱ የሚመኩ በዐይኖችህ ፊት አይኖሩም፥ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ። ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፥ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው ጌታ ይጸየፋል። እኔ ግን በቸርነትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፥ አንተን በመፍራት ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ። አቤቱ፥ በጠላቶቼ ምክንያት በጽድቅህ ምራኝ፥ መንገዴን በፊትህ አቅና። በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፥ ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ይሸነግላሉ። አቤቱ፥ ፍረድባቸው፥ በምክራቸውም ይውደቁ፥ ስለ ክፋታቸውም ብዛት አስወግዳቸው፥ እነርሱ ዐምፀውብሃልና። በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ሐሴትን ያድርጉ፥ ለዘለዓለሙ በደስታ ይዘምሩ፥ እነርሱንም ትጠብቃቸዋለህ፥ ስምህንም የሚወድዱ ሁሉ በአንተ ይደሰቱ። አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፥ አቤቱ፥ እንደ ጋሻ በሞገስ ከለልኸን። ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ ስምንተኛ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በቁጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። ዝያለሁና አቤቱ፥ ማረኝ፥ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ። ነፍሴም እጅግ ታወከች፥ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ። በሞት የሚያስታውስህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው? በመቃተቴ ደክሜአለሁ፥ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን በእንባ አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። ዓይኔ ከኀዘን ዕንባ የተነሣ ታወከች፥ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ ደከመች። ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ ጌታ የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና። ጌታ ልመናዬን ሰማኝ፥ ጌታ ጸሎቴን ተቀበለ። ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቁሉ፥ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ። ስለ ብንያማዊ ሰው ስለ ኩዝ ቃል ለጌታ የዘመረው የዳዊት መዝሙር። አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥ ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር። አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህ አድርጌ ከሆነ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥ መልካም ላደረጉልኝም ክፉን መልሼላቸው ከሆነ፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ከሆነ፥ ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት። አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቁጣ ተነሣባቸው፥ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ። የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ። ጌታ በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል፥ አቤቱ፥ እንደጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ። የክፉዎች በደል ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፥ እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል። ጋሻዬ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው። እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፥ ሁልጊዜ ትክክለኛ ፈራጅ ነው፥ ለማይመለስ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ወጥሮአል አዘጋጅቷልም፥ የሞት መሣርያንም አሰናድቷል፥ ፍላጻዎቹንም የሚንበለበሉ አደረገ። እነሆ፥ ክፋትን ያማጠ ተንኮልን ፀነሰ፥ ውሸትንም ወለደ። ጉድጓድን ማሰ ቈፈረም። በሠራውም ጉድጓድ ይወድቃል። ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች። ጌታን ስለ ጽድቁ አመሰግነዋለሁ፥ ለልዑል ጌታም ስም እዘምራለሁ። ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ ምን ያህል ገናና ነው፥ ክብርህን በሰማዮች ላይ የምታኖር። በጠላቶችህ ምክንያት ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት። የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችህን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፥ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፥ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ። ለመዘምራን አለቃ፥ በሙትላቤን፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ። እደሰታለሁ፥ በአንተም ሐሤትን አደርጋለሁ፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ። ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ። ትክክለኛ ፍርድና ዳኝነት አድርገህልኛልና፥ በጽድቅ እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ። አሕዛብን ገሠጽህ፥ ክፉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። ጠላቶች በጦር ለዘለዓለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም ጠፋ። ጌታ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፥ እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል። ጌታ ለተጨቆኑ መጠጊያ ይሁናቸው፥ በመከራም ጊዜ መሸሸጊያ ይሁንላቸው። ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና። በጽዮን ለሚኖር ለጌታ ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል ድንቅ ሥራውን ንገሩ፥ ደምን የሚበቀል እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና። አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፥ ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፥ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል። አሕዛብ በሠሩት ጉድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች። ጌታ ተገለጠ፥ ፍርድንም አከናወነ፥ ክፉ በገዛ እጆቹ ሥራ ተጠመደ። ክፉዎች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም በሙሉ። ድሀ ለዘለዓለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘለዓለም አይጠፋም። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው። አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው አኑር፥ አሕዛብም ደካማ ሰዎች መሆናቸውን ይወቁ። አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ? በክፉዎች ትዕቢት ምስኪኖች ይሰደዳሉ፥ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ። ክፉ በነፍሱ ፈቃድ ይኮራልና፥ ስግብግብም ይረግማል፥ ጌታንም ይንቃል። ክፉ በትዕቢቱ ጌታን አይፈልገውም፥ በሐሳቡ በሙሉ እግዚአብሔር የለም። መንገዱ ሁልጊዜ የጸና ነው፥ ፍርድህ ከእርሱ በላይ እጅግ ከፍ ያለ ነው፥ በጠላቶቹ ላይ ግን ይቀልዳል። በልቡ፦ “ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም” ይላል። አፉ በመርገም፥ በሽንገላና በዐመፃ የተመላ ነው፥ ከምላሱ በታች ተንኰልና ክፋት አሉ። በመንደሮች ሸምቆ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፥ ዐይኖቹም ወደ ምስኪኑ ይመለከታሉ። እንደ አንበሳ በዱር በስውር ይሸምቃል፥ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፥ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል። ምስኪኑ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፥ በኃያላኑም እጅ ይወድቃል። በልቡም እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ረስቶኛል፥ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ”። አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህንም ከፍ ከፍ አድርግ፥ ድሆችን አትርሳ። ክፉ ስለምን እግዚአብሔርን ናቀ? በልቡም፦ “ፈልጎ አያገኘኝም” ይላልና። አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቁጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፥ ምስኪን እራሱን ለአንተ አሳልፎ ይሰጣል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ። የክፉዉንና የግፈኛውን ክንድ ሰባብር፥ ምንም እስከማይገኝ ድረስ ክፋቱን ፈልገህ አግኝ። ጌታ ለዘለዓለም ንጉሥ ነው፥ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ። ጌታ ሆይ የምስኪኖችን ምኞት ሰማህ፥ ልባቸውንም ታጸናለህ፥ ጆሮህንም ታዘነብላለህ፤ ፍርዱ ለወላጅ አልባና ለተጨቆነ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ ማሸበራቸውን እንዳይቀጥሉ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። በጌታ ታመንሁ፥ ነፍሴን፦ እንዴት እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ሽሺ ትሉአታላችሁ? እነሆ ክፉዎች ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ። መሠረቶቹ ከፈረሱ፥ ጻድቅ ምን ማድረግ ይችላል? ጌታ በተቀደሰው መቅደሱ ነው፥ ጌታ፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፥ ዐይኖቹ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። ጌታ ጻድቅንና ክፉን ይመረምራል፥ ዓመፃ የሚወደውን ግን ነፍሱ ትጠላለች። በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምንና ዲንን ያዘንባል የሚያቃጥል ነፋስም የጽዋቸው እድል ፈንታ ነው። ጌታ ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፥ ቅን ሰው ፊቱን ያየዋል። ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ስምንተኛው፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ አድነኝ፥ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና። እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፥ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ። የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ ጌታ ያጠፋቸዋል፥ የትዕቢት ነገርን የምትናገረውን ምላስ ምላሳችንን እናበረታለን፥ ከንፈራችን የእኛ ነው፥ ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን። ስለ ምስኪኖች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት ጌታ፦ አሁን እነሣለሁ ይላል፥ የተጠሙትንም ደኅንነት አመጣላቸዋለሁ። በምድር ምድጃ ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የጌታ ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው። አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘለዓለም ታደገን። በሰው ልጆች ዘንድ ከንቱነት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ሁሉ ይመላለሳሉ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ? እስከ መቼ በነፍሴ እጨነቃለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ዕለቱን በሙሉ በልቤ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይሸልላል? አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዐይኖቼን አብራ ጠላቴ፦ “አሸነፍሁት እንዳይል”፥ የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው። እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል። ለረዳኝን ጌታ እዘምራለሁ፥ መልካምን አድርጎልኛልና። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አላዋቂ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐሰቈሉ፥ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም። የሚያስተውል እግዚአብሔርንም? የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ ጌታ ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉም ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፥ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፥ አንድም እንኳ የለም። ክፉ አድራጊዎች አያስተውሉምን? እንጀራን እንደሚበሉ ሕዝቤን የሚያኝኩ፥ ጌታን አይጠሩምን፥ እዚያም ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋል፥ አግዚአብሔር በጻድቃን ዘንድ ነውና፥ የምስኪኖችን ዕቅድ ታዛባላችሁ፥ ጌታ ግን መጠለያቸው ነው፥ ከጽዮን መድኃኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? ጌታ የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር። በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ የሚቀርቡትን የማይሰድብ። ኃጢአተኛ ሰው በፊቱ የተናቀ፥ ጌታን የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ቢጎዳም የማለውን የማይከዳ። ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘለዓለም አይታወክም። የዳዊት ቅኔ። አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። ጌታን፦ “አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ”፥ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። ደስታዬ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳንና ክቡራን ላይ ነው። ወደ ሌላ አምላክ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፥ የቁርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም። ጌታ የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣ ፈንታዬንም የምታጸና አንተ ነህ። ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ። የመከረኝን አምላክ እባርካለሁ፥ ደግሞም በሌሊት ኩላሊቶቼ ይገሥጹኛል። ሁልጊዜ ጌታን በፊቴ አየዋለሁ፥ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ነፍሴም ሐሴት አደረገች፥ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፥ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፥ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘለዓለም ፍሥሐ አለ። የዳዊት ጸሎት። አቤቱ፥ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ተንኰል ከሌለበት ከንፈር የሚወጣውንም ጸሎቴን አድምጥ። ፍርዴ ከፊትህ ይውጣ፥ ዐይኖችህም በቅንነት ይዩ። ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፥ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም። የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፥ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ። እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ። የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው። እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ። አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ። አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፥ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ። እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጉጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው። አቤቱ፥ ተነሥ፥ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፥ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት። አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፥ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፥ ልጆቻቸው ተትረፍርፎላቸዋል የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ። እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፥ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ። ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ ጌታ ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለጌታ የተናገረው የጌታ ባርያ የዳዊት መዝሙር። እንዲህም አለ፦ አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመዶች ጠፍረው ያዙኝ፥ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፥ የሲኦል ገመዶች ተበተቡኝ፥ የሞት ወጥመዶችም ደረሱብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፥ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ ተናጉም እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፥ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ሠረገላ ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ አንዣበበ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፥ በዙሪያውም ድንኳኑ፥ በውሃ የተሞሉ ጥቁር ደመናዎች ሸፍነውታል። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። በረዶና የእሳት ፍምም፤ ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፥ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከአፍንጫህ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፥ ጌታ ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፥ ወድዶኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። ጌታም እንደጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ብልህ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። አንተ መብራቴን ታበራለህና፥ ጊታ አምላኬ ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ግብረ ኃይል አጠቃለሁ፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ። የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የጌታም ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያበረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ። ለደኅንነቴም ጋሻን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም አሳደገችኝ፥ አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። አስጨንቃቸዋለሁ፥ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። ለጦርነት ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋቸዋለሁ። ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፥ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ነገር ግን አልመለሰላችውም። እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ። ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፥ የባዕድ ልጆች ያጐነብሱልኛል። የባዕድ ልጆች ጠወለጉ፥ በመንቀጥቀጥም ከምሽጋቸው ወጥተው ወደ እኔ መጡ። ጌታ ሕያው ነው፥ አምላኬም መጠጊያዬ ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል። በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል። ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፥ በእኔም ላይ ከቆሙት በላይ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘለዓለም ይሰጣል። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ ጠፈርም የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ንግግርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ንግግር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፥ እንደ አርበኛ በመንገዱ መሮጥ ደስ ይለዋል። አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙሪቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፥ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም። የጌታ ሕግ ፍጹም ነው፥ ነፍስን ይመልሳል፥ የጌታ ምስክር የታመነ ነው፥ የዋሆችን ጠቢባን ያደርጋል። የጌታ ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፥ የጌታ ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል። ጌታን መፍራት ንጹሕ ነው፥ ለዘለዓለም ይኖራል፥ የጌታ ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ናቸው። ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፥ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። አገልጋይህ ደግሞ ይጠብቀዋል፥ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል። ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ አገልጋይህን ጠብቅ፥ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ዓለቴና ቤዛዬ፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። በመከራ ቀን ጌታ ይስማህ፥ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ። ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ይደግፍህ። መባዎችህን ሁሉ ያስብልህ፥ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ። እንደ ልብህ ምኞት ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ። በማዳንህ ደስ ይለናል፥ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፥ ልመናህን ሁሉ ጌታ ይፈጽምልህ። ጌታ የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፥ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፥ በቀኙ ብርታት ማዳን አለና። እነኚህ በሠረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፥ እኛ ግን በአምላካችን በጌታ ስም ከፍ ከፍ እንላለን። እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፥ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን። አቤቱ፥ ንጉሥን አድነው፥ በጠራንህም ቀን ስማን። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፥ በማዳንህም እንዴት አብዝቶ ሐሤትን ያደርጋል! የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም። በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፥ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ። ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም፥ ለረጅም ዘመን ለዘለዓለም ዓለም። በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፥ ሞገስንና ግርማን በላዩ አኖርህ። የዘለዓለም በረከትን ሰጥተኸዋልና፥ በፊትህም ደስ ታሰኘዋለህ። ንጉሥ በጌታ ተማምኖአልና፥ በልዑልም ጽኑ ፍቅር አይናወጥም። እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታገኛቸዋለች፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታገኛቸዋለች። በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን ታደርጋቸዋለህ፥ ጌታ በቁጣው ይውጣቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች። ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ። ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ። ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፥ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ። አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፥ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን። ለመዘምራን አለቃ ስለ ንጋት ኃይል፥ የዳዊት መዝሙር። አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ለምን ራቅህ? አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፥ በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም። በእስራኤል ውዳሴዎች የምትኖር አንተ ግን ቅዱስ ነህ። አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው። ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ በአንተንም ተማመኑ አላፈሩም። እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፥ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ። የሚያዩኝ ሁሉ ያፌዙበኛል፥ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይሳለቃሉ፦ በጌታ ተማመነ፥ እርሱም ያድነው፥ ቢወድደውስ ያድነው። አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ። ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፥ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ። ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ። ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም የባሳን ፍሪዳዎች አገቱኝ፥ እንደ ነጣቂና እንደሚያገሣ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ። እንደ ውኃ ፈሰስሁ፥ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፥ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ። ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጉሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አፈር አወረድኸኝ። ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፥ የክፋተኞች ጉባኤም አገተኝ፥ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፥ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፥ አንተ ጉልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥ ሕይወቴንም ከውሾች እጅ። ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ከጐሽ ቀንድም ጠብቀኝ፥ መለስክልኝ! ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ። ጌታን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፥ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት። የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፥ ፊቱንም አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኸ ጊዜ ሰማው። በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው። እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ። ችግረኞች ይበላሉ፥ ይጠግቡማል፥ ጌታንም የሚሹት ያመሰግኑታል፥ ልባቸውም ለዘለዓለም ሕያው ይሁን። የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ ጌታም ይመለሱ፥ የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ። መንግሥት ለጌታ ነውና፥ እርሱም አሕዛብን ይገዛል። የምድር ደንዳኖች ሁሉ ይበላሉ ይሰግዳሉም፥ ወደ መሬት የሚወርዱት ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፥ ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች። ትውልድ ይገዛለታል፥ የሚመጣው ትውልድ ስለ ጌታ ይነገረዋል፥ ጽድቁንም ለሚወለደው ሕዝብ፥ ጌታ ያደረገውን ይነግራሉ። የዳዊት መዝሙር። ጌታ እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፥ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬንም እስከ አፉ ሞላህ። ቸርነትና ምሕረት በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘለዓለም እኖራለሁ። የዳዊት መዝሙር ። ምድርና ሞላዋ የጌታ ናቸው፥ ዓለምና በእርሷም የሚኖሩ ሁሉ። እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቶአታልና፥ በፈሳሾችም ላይ አጽንቶአታልና። ወደ ጌታ ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ በሽንገላ ያልማለ። እርሱ ከጌታ ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ጽድቅን ይቀበላል። ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ። እናንት በሮች ራሳችሁን ከፍ አድርጉ፥ የዘለዓለም ደጆችም ተከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? ጌታ ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ ጌታ ነው፥ በሰልፍ ኃያል። እናንተ በሮች ራሳችሁን ከፍ አድርጉ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የሠራዊት ጌታ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ። አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ። አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፥ በከንቱ የሚከዱ ያፍራሉ። አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፈለግህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፥ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፥ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። ጌታ ቸርና ቅን ነው፥ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። ትሑታንን በፍርድ ይመራል፥ ለትሑታን መንገድን ያስተምራቸዋል። የጌታ መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። አቤቱ፥ በደሌ ብዙ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ። ጌታን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ እርሱን ያስተምረዋል። ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል። ጌታ ለሚፈሩት ወዳጃቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል። እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዐይኖቼ ሁልጊዜ ወደ ጌታ ናቸው። እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ መልስ ማረኝም። የልቤ ችግር ብዙ ነው፥ ከጭንቀቴ አውጣኝ። ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። ጠላቶቼ እንደበዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፥ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና ፍጽምናና ቅንነት ይጠብቁኝ። አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ እኔ በቅንነት ሄጃለሁና ፍረድልኝ፥ በጌታም አምኛለሁና አልናወጥም። አቤቱ፥ ፈትነኝ መርምረኝም፥ ኩላሊቴንና ልቤን መርምር። ቸርነትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ። ከአታላዮች ጋር አልተቀመጥሁም፥ ከአስመሳዮችም ጋር አልገባሁም። የክፉ አድራጊዎቸን ማኅበር ጠላሁ፥ ከክፉዎችም ጋር አልቀመጥም። እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፥ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ። በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም በጉቦ ተሞልታለች። እኔ ግን በቅንነት ሄጃለሁ፥ አድነኝ ማረኝም። እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፥ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ። ሳይቀባ፥ የዳዊት መዝሙር። ጌታ ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፥ የሚያስፈራኝ ማን ነው? ጌታ የሕይወቴ ከለላዋ ነው፥ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ለመብላት በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ። ሠራዊትም ቢከብበኝ ልቤ አይፈራም፥ ጦርነትም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ። ጌታን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት እኖር ዘንድ፥ ጌታን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ። በመከራ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፥ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለጌታ እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ፥ ማረኝና አድምጠኝ። “ፊቴን እሹት” የሚለውን ቃልህን በልቤ አሰብኩኝ፦ አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባርያህ ፈቀቅ አትበል፥ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተወኝ። አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ ጌታ ግን ተቀበለኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ በጠላቶቼም ምክንያት በቀና መንገድ ምራኝ። የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ። የጌታን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ አምናለሁ። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ በርታ፥ ልብህም ይጽና፥ በጌታ ተስፋ አድርግ። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፥ ዝም ብትለኝ ወደ ጉድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ ዓለቴ ሆይ፥ ዝም አትበለኝ። ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ። ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፥ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ። እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፋት ስጣቸው፥ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፥ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ። ወደ ጌታ ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም። የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና ጌታ ይመስገን። ጌታ ኃይሌና ጋሻዬ ነው፥ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፥ ልቤም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ። ጌታ ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው። ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፥ ጠብቃቸው፥ ለዘለዓለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው። ከድንኳን በሚወጣበት ጊዜ፥ የዳዊት መዝሙር። የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለጌታ አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለጌታ አምጡ። የስሙን ክብር ለጌታ አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለጌታ ስገዱ። የጌታ ድምፅ በውኆች ላይ፥ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ አምላክ በብዙ ውኆች ላይ። የጌታ ድምፅ በኃይል ነው፥ የጌታ ድምፅ በታላቅ ክብር የተሞላ ነው። የጌታ ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፥ ጌታ የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል። እንደ ጥጃ ሊባኖስን ፥ እንደ ጎሽ ጥጃ ስርዮንን ያዘልላቸዋል። የጌታ ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል። የጌታ ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ ጌታ የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል። የጌታ ድምፅ ዋላዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ጫካዎቹንም ይገልጣል፥ ሁሉም በመቅደሱ፦ ምስጋና ይላል። ጌታ የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፥ ጌታ ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል። ጌታ ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፥ ጌታ ሕዝቡን በሰላም ይባርካል። ለቤቱ መመረቅ ምስጋና፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ አንተም ፈወስከኝ። አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጉድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ። ቅዱሳን ሆይ፥ ለጌታ ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ። ቁጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፥ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል። እኔም በደስታዬ፦ ለዘለዓለም አልታወክም አልሁ። አቤቱ፥ በፈቃድህ እንደ ጽኑ ተራራ አጠነከርከኝ፥ ፊትህን ስትሰውር፥ እኔም ደነገጥሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ። ወደ ጉድጓድ ብወርድ ከደሜ ምን ጥቅም ይገኛል? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን? ጌታ ሰማ ማረኝም፥ ጌታ ረዳቴ ሆነኝ። ልቅሶዬን ወደ እልልታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ። ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል፥ አቤቱ አምላኬ፥ ለዘለዓለም አመሰግንሃለሁ። ለመዘምራን አለቃ፥ በማድነቅ ጊዜ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ በአንተ ታመንሁ፥ ለዘለዓለም አልፈር፥ በጽድቅህም አድነኝ። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፥ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ። አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም። አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ። በእጅህ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ፥ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል። ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላህ፥ እኔ ግን በጌታ ታመንሁ። መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ። በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ። ተቸግሬአለሁና አቤቱ ምራኝ፥ ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ደከመ፥ ነፍሴም ሆዴም። ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፥ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ። በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፥ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ። እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ። የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፥ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፥ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ። አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፥ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ። ርስቴ በእጅህ ነው፥ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። ፊትህን በባርያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ። አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፥ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ። በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደምን በዛች! በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ። በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ ጌታ ይመስገን። እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፥ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ። ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ ጌታን ውደዱት፥ ጌታ እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። በጌታ የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና። የዳዊት ትምህርት። መተላለፉ ይቅር የተባለችለት፥ ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። ጌታ በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ብፁዕ ነው። ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፥ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ ጉልበቴ በበጋ ትኩሳት ዛለ። ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፥ መተላለፌን ለጌታ እነግራለሁ አልሁ፥ አንተም የኃጢአቴን ሸክም ተውህልኝ። ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፥ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም። አንተ ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከጭንቅ ትጠብቀኛለህ፥ ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ። አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፥ ዐይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ። ወደ አንተ እንዳይቀርቡ በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጉሙአቸው፥ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ። በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፥ በጌታ የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል። ጻድቃን ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ፥ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፥ እልል በሉ። የዳዊት መዝሙር። ጻድቃን ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ፥ ለቅኖች ምስጋና ይገባል። ጌታን በመሰንቆ አመስግኑት፥ ዐሥር አውታርም ባለው በገና ዘምሩለት። አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፥ የጌታ ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ የታመነ ነውና። ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፥ የጌታ ቸርነት ምድርን ሞላች። በጌታ ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ በአፉም እስትንፋስ ሠራዊታቸው ተፈጠረ፥ የባሕርን ውኃ በኰዳ የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው። ምድር ሁሉ ጌታን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉ ይደንግጡ። እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፥ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም። ጌታ የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል። የጌታ ምክር ግን ለዘለዓለም ይኖራል፥ የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው። ጌታ አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። ጌታ ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥ እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፥ ኃያልም በጉልበቱ አያመልጥም። ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፥ በኃይሉም ብዛት አያስመልጥም። እነሆ፥ የጌታ ዐይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በቸርነቱም ወደሚታመኑ፥ ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ በሕይወት ይጠብቃቸው ዘንድ። ነፍሳችን ጌታን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና ጋሻችን እርሱ ነውና። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። አቤቱ፥ ቸርነትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን። ባሳደደው በአቤሜሌክ ፊት መልኩን በለወጠ ጊዜ በሄደም ጊዜ፥ የዳዊት መዝሙር። ጌታን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር ከአፌ አይለይም። ነፍሴ በጌታ ትከብራለች፥ ገሮችም ሰምተው ደስ ይላቸዋል። ጌታን ከእኔ ጋር አክብሩት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። ጌታን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከምፈራውም ሁሉ አዳነኝ። ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም በፍጹም አያፍርም። ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ ጌታም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው። የጌታ መልአክ ጌታን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። ጌታ ቸር እንደሆነ ቅመሱ፥ እዩም፥ በእርሱ የሚታመን ሰው ብፁዕ ነው። የሚፈሩት ምንም አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ ጌታን ፍሩት። የአንበሳ ደቦሎች ተቸገሩ፥ ተራቡም፥ ጌታን የሚፈልጉት ግን መልካሙን ሁሉ አያጡም። ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፥ ጌታን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ሕይወትን የሚመኝ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? አንደበትህን ከክፉ ነገር፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን ከመናገር ከልክል። ከክፉ ነገር ሽሽ መልካምንም አድርግ፥ ሰላምን እሻ ተከተላትም። የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የጌታ ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ተነሥቶአል። ጻድቃን ጮኹ፥ ጌታም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። ጌታ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ ጌታ ግን ከሁሉ ያድናቸዋል። አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። ክፉዎቹን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል። የባርያዎቹን ነፍስ ጌታ ይቤዣል፥ ወደ እርሱ የሚጠጉ ሁሉ አይፈረድባቸውም። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ የሚከሱኝን ክሰሳቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። ሰይፍንና ጦርን ምዘዝ፥ የሚያሳድዱኝን ለመቃወም፥ ነፍሴን፦ መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት። ነፍሴን ሊያጠፉ የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቁሉም፥ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይዋረዱ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የጌታም መልአክ ያስጨንቃቸው። መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የጌታም መልአክ ያሳድዳቸው። በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና። ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፥ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። ነፍሴ ግን በጌታ ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ። የሐሰት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። በበጎ ፈንታ ክፋትን መለሱልኝ፥ ለብቻዬም ቀረሁ። እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፥ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፥ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፥ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላወቅሁም፥ መቦጫጨቃቸውን አላቆሙም። ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብቸኛዪቱንም ከአንበሶች አድናት። አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። ከሐዲ ጠላቶቼ በእኔ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጠቃቀሱብኝ። በእርጋታ በምድሪቱ ለተቀመጡት ሰላምን አይናገሩምና፥ በቁጣም ሽንገላን ይመክራሉ። አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፥ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ። አቤቱ፥ አንተ አየኸው፥ ዝም አትበል፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ። አምላኬ ጌታዬም፥ ትፈርድልኝ ዘንድ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ። አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በእኔም ምክንያት ደስ አይበላቸው። በልባቸው፦ እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፥ ደግሞም፦ ዋጥነው አይበሉ። በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቁሉ፥ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጉስቁልናን ይልበሱ። ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፥ የባርያውን ሰላም የሚወድድ ጌታ ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ። ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል። ለመዘምራን አለቃ፥ የጌታ ባርያ የዳዊት መዝሙር። ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዐይኖቹ ፊት የለም። እራሱን ሸንግሎአልና፥ ኃጢአቱን መቀበልና መጥላት ይሳነዋል። የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው፥ ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ። በመኝታው ጠማማነትን አሰበ፥ መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፥ ክፋትን አይቃወማትም። አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህ በሰማይ ነው፥ ታማኝነትህም ወደ ደመናት ትደርሳለች። ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች፥ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት፥ አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ። አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህን እንዴት አበዛህ! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ። ከቤትህ ሙላት ይጠግባሉ፥ ከተድላህም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ። የሕይወት ምንጭ በአንተ ዘንድ ነውና፥ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን። ጽኑ ፍቅርህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ። የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የዐመጸኞችም እጅ አያስተኝ። ዓመፃን የሚያደርጉ ሁሉ ከዚያ ወደቁ፥ ወድቀዋል፥ መቆምም አይችሉም። የዳዊት መዝሙር። በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፥ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። በጌታ ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። በጌታ ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለጌታ አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣዋል። በጌታ ጽና በተዕግሥትም ጠብቀው። መንገዱም በቀናችለትና በሚያደባ ሰው አትቅና። ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፥ እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፥ በጌታ ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ጥቂት ጊዜ ቆይቶ፥ ክፉ አድራጊ አይኖርም፥ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ክፉ በጻድቁ ላይ ያደባል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል። ጌታ ግን ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና። ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ፥ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፥ ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። በጻድቅ ዘንድ ያለው ጥቂት ነገር ከብዙ ክፉዎች ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ንድ ትሰበራለችና፥ ጌታ ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። የንጹሓንን ቀኖች ጌታ ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘለዓለም ትሆናለች፥ በክፉ ዘመንም አያፍሩም፥ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎቸ ግን ይጠፋሉ፥ የጌታ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት፥ እንደ ጢስም ተንነው ይጠፋሉ። ክፉ ይበደራል አይከፍልምም፥ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም። እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፥ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ። መንገዱን በወደደ ጊዜ፥ የሰው አካሄድ በጌታ ይጸናል። ቢወድቅም አይጣልም፥ ጌታ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። ጐለመስሁ አረጀሁም፥ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፥ ለዘለዓለምም ትኖራለህ። ጌታ ፍርድን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፥ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፥ የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘለዓለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ያናገራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም። ክፉ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል። ጌታ ግን በእጁ አይተወውም፥ በፍርድም እንዲሸነፍ አይፈቅድም። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፥ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ። ክፉን በጭቆና ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት፥ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፥ ለሰላም ሰው ተተኪ ይወጣለታልና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፥ የክፉዎቸ ዘር ይጠፋል። የጻድቃን መድኃኒታቸው በጌታ ዘንድ ነው፥ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። ጌታ ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከከፉዎችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ በእርሱ ታምነዋልና። ለሰንበት መታሰቢያ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በቁጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም በላዬ ላይ አክብደህብኛልና። ከቁጣህ የተነሣ ሥጋዬ ጤና የለውም፥ ከኃጢአቴም የተነሣ አጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። ዐመፃዎቼ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብለዋልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብደዋልና። ከአላዋቂነቴ የተነሣ ቁስሌ ሸተተ በሰበሰም፥ እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ። ወገቤ በትኩሳት ተሞልቷልና፥ ሥጋዬም ጤና የለውምና። ዛልኩኝ እጅግም ደቀቅሁ፥ ከልቤ መጠበብ የተነሣ ጮኽሁ። አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም። ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዐይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ። ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቁስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ። ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ። እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ። እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፥ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ። ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። እኔስ ለመውደቅ ተቃርቤአለሁና፥ ቁስሌም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ። ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ። ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል። አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፥ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ። አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ለመዘምራን አለቃ፥ ለኤዶታም፥ የዳዊት መዝሙር። በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፥ ክፉ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ ሁሉ በአፌ ላይ ልጓም አኖራለሁ አልሁ። ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ሥቃዬም ተቀሰቀሰብኝ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፥ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ፦ አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቁጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ረጋፊ እንደሆንኩ አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን ከእጅ መዳፍ አሳጠርካቸው፥ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ነው። በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፥ በእውነት በከንቱ ይታወካል። ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። አቤቱ አሁንስ ማንን እጠብቃለሁ? ተስፋዬ በአንተ ነው።። ከመተላለፌ ሁሉ አድነኝ፥ የሞኞች መሳለቂያ አታድርገኝ። አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም። መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና። በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ የሚመኘውንም እንደ ብል ታጠፋበታለህ፥ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው። አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፥ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝና። ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። በትዕግሥት ጌታን ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኸቴንም ሰማኝ። ከጥፋት ጉድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፥ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፥ አረማመዴንም አጸና። አዲስ ዝማሬን ለአምላካችን ምስጋና በአፌ ጨመረ፥ ብዙዎች ያያሉ ይፈሩማል፥ በጌታም ይታመናሉ። ጌታን የታመነ ወደ ትዕቢተኛና ወደ ሐሰተኛ ያልተመለከተ ሰው ብፁዕ ነው። አቤቱ አምላኬ፥ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፥ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ። መሥዋዕትንና ቁርባንን አልወደድህም፥ የሚሰማ ጆሮ ሰጠኸኝ፥ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፦ “እነሆ፥ መጣሁ፥ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።” በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አበሠርሁ፥ እነሆ፥ ከንፈሮቼን አላግድም፥ አቤቱ፥ አንተ ታውቃለህ። አዳኝ ጽድቅህን በልቤ ውስጥ አልሰወርኩም፥ ታማኝነትህንና ማዳንህንም ተናገርሁ፥ ጽኑ ፍቅርህንና እውነትህን ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም። አቤቱ፥ አንተ ርኅራኄህን ከእኔ አታርቅ፥ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ። ቍጥር የሌለው ክፋት ከቦኛልና፥ ኃጢአቶቼ ያዙኝ፥ ማየትም ተስኖኛል ከራሴ ጠጉር ይልቅ በዙ፥ ልቤም ተወኝ። አቤቱ፥ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፥ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ለማጥፋት የሚወድዱ ይፈሩ፥ በአንድነትም ይዋረዱ፥ በእኔ ላይ ክፋትን ሊያደርጉ የሚወድዱ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይጐስቁሉም። እሰይ እሰይ የሚሉኝ እፍረታቸውን ወዲያው ይከፈሉ። አቤቱ፥ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ፥ ሁልጊዜ ማዳንህን የሚወድዱ ዘወትር፦ ጌታ ታላቅ ይሁን ይበሉ። እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ ጌታ ግን ያስብልኛል፥ አንተ ረዳቴና አዳኜ ነህ፥ አምላኬ ሆይ፥ አትዘግይ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፥ ጌታ በክፉ ቀን ያድነዋል። ጌታ ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ብፁዕ ያደርጋቸዋል፥ ለጠላቶቹም አሳልፈህ አትሰጠውም። ጌታ በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፥ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል። እኔስ፦ “አቤቱ፥ ማረኝ፥ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት” አልሁ። ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ፦ መቼ ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ። እኔን ለመጠየቅ የሚገባ ከንቱን ይናገራል፥ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፥ ወደ ውጭ ይወጣል ይናገራልም። በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ያንሾካሽካሉ፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ። ክፉ ነገር መጣበት፥ ከተኛበት ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ። ደግሞ የሰላሜ ሰው፥ የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ። አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ፥ እመልስላቸውም ዘንድ አቁመኝ። ጠላቴ እልል አይልብኝምና በዚህም በእኔ እንደ ተደሰትክ አወቅሁ። እኔንም ስለ ቅንነቴ ደገፍከኝ፥ በፊትህም ለዘለዓለም አጸናኸኝ። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ። አሜን አሜን። ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች ትምህርት። ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ አንተን ትናፍቃለች። ነፍሴ እግዚአብሔርን፥ ሕያው አምላክን ተጠማች፥ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ዘወትር፦ አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ። ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፥ በዓል የሚያከብሩ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፥ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስታውስሃለሁ። በፏፏቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፥ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ። ጌታ በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፥ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። እግዚአብሔርን፦ አንተ መጠጊያዬ ነህ፥ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ፦ አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። አቤቱ፥ ፍረድልኝ፥ ከጽድቅ በራቁም ሕዝብ ዘንድ ተሟገትልኝ፥ ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ። አንተ አምላኬ ኃይሌም፥ ለምን ትተወኛለህ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፥ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ። ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጉልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፥ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች ትምህርት። አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን። እጅህ አሕዛብን አባረረች፥ እነርሱንም ተከልህ፥ አሕዛብን አስጨንቀህ እነሱን አለመለምክ። በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፥ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ፥ ወድደሃቸዋልና። አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፥ ለያዕቆብ መድኃኒትን እዘዝ። በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም የሚነሡብንን እንረግጣለን። በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፥ አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው። ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን። አሁን ግን ጣልከን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም። ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን። እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን። ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም። ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን። በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ መናቂያ አደረግኸን። ጉስቁልናዬ ሁልጊዜ በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ። ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው። ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም። ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፥ በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና። የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና። ስለ አንተ ሁልጊዜ ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል። አቤቱ፥ ንቃ፥ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን። ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ጭንቃችንን ለምን ትረሳለህ? ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቁላለችና፥ ሆዳችንም ከምድር ጋር ተጣብቃለችና። አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ጽኑ ፍቅርህም ተቤዠን። ለመዘምራን አለቃ፥ በመለከቶች፥ የቆሬ ልጆች ትምህርት፥ የፍቅር መዝሙር። ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፥ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው። ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፥ ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባረከህ። ኃያል ሆይ፥ በግርማህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፥ ቀኝህም በክብር ይመራሃል። ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፥ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፥ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ። በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፥ በዝሆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶች ይልቅ የበገናና የመሰንቆ ድምጽ ደስ ያሰኙሃል። የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፥ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፥ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፥ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና እጅ ንሺው። የጢሮስ ሴት ልጅ፥ የምድር ባለ ጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ደጅ ይጠናሉ። ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፥ ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው። በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፥ በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥ ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል። በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ። ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፥ ስለዚህ ለዓለምና ለዘለዓለም አሕዛብ ይገዙልሃል። ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ምሥጢር፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትለዋወጥ፥ ተራሮችም በባሕር ልብ ውስጥ ቢናወጡ አንፈራም። ውኆቻቸው እየገነፈሉ ጮኹ፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተንቀጠቀጡ። የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፥ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ። እግዚአሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል። አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተረበሹ፥ እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች። የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፥ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። የጌታን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ያስቆማል፥ ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቆራርጣል፥ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል። ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደሆንሁ እወቁ፥ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፥ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ። ጌታ ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና። አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። ለሚወደው ለያዕቆብ ኩራት የሆነችውን ርስታችንን እርሱ ይመርጥልናል። አምላክ በእልልታ፥ ጌታ በመለከት ድምፅ ዐረገ። ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፥ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፥ በጥበብ ዘምሩ። እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፥ እግዚአብሔር በተቀደሰው ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። የአሕዛብ አለቆች፥ እንደ አብርሃም አምላክ ሕዝብ ተሰበሰቡ፥ የምድር ጋሻዎች የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱም እጅጉን ከፍ ብሏል። በሁለተኛ ሰንበት የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ጌታ ትልቅ ነው፥ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰው ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው። በሰሜን በኩል በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው፥ እርሷም የትልቁ ንጉሥ ከተማ ነች። እግዚአብሔር በአዳራሾችዋ መጠጊያ ሆኖ ይታወቃል። እነሆ፥ ነገሥታት ተከማችተው በአንድነት መጥተዋል። እነርሱስ አይተው ተደነቁ፥ ደነገጡ፥ ሸሹም። በዚያ እንደ ወላድ ምጥ መንቀጥቀጥ ያዛቸው። በኃይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትሰብራለህ። እንደ ሰማን እንዲሁ አየን በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፥ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ያጸናታል። አምላክ ሆይ፥ በመቅደስህ ውሰጥ ርኅራኄህን አሰላሰልን። አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ ምስጋናህም እንዲሁ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው፥ ቀኝህ ጽድቅን የተሞላች ናት። አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራራ ደስ ይበለው፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ሐሤት ያድርጉ። ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቁጠሩ፥ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፥ ቅጥሮችዋን መርምሩ፥ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ። ለዓለምና ለዘለዓለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘለዓለም ይመራናል። ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። አሕዛብ ሁላችሁ፥ ይህን ስሙ፥ በዓለም የምትኖሩትም ሁላችሁ፥ አድምጡ፥ ዝቅተኞችና ከፍተኞች፥ ሀብታሞችና ድሆች በአንድነት። አፌ ጥበብን ይናገራል፥ የልቤም አስተንትኖ ማስተዋልን። ጆሮዬን ወደ ምሳሌዎች አዘነብላለሁ፥ በበገናም ምሥጢሬን እገልጣለሁ። በደል ተረከዜን በከበበኝ ጊዜ በክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ? በኃይላቸው የሚታመኑ፥ በሀብታቸውም ብዛት የሚመኩ፥ በእውነት ማንም እራሱን አያድንም፥ ማንም ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥ የነፍሳቸው ዋጋ ክቡር ነው፥ መቼውንም በቂ አይሆንም፥ ሰው ገና እንዲኖርና አዘቅቱንም እንዳያይ ጠቢባን እንደሚሞቱ፥ ሰነፎችና ደንቆሮች በአንድነት እንደሚጠፉ፥ ገንዘባቸውንም ለሌሎች እንደሚተዉ አይቶአል። ብዙ መሬት በስማችው ቢያስጠሩም እንኳን፥ መቃብራቸው የዘለዓለም ቤታቸው፥ ለልጅ ልጅ የሚሆን ማደሪያቸውም ነው። ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፥ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። ይህች መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥ ከእነርሱም በኋላ የሚመጡ በንግግራቸው ይደሰታሉ። እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው፥ እረኛቸውም ሞት ነው፥ ቅኖችም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥ ውበታቸውም ከመኖሪያቸው ተለይታ በሲኦል ታረጃለች። ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል። የሰው ሀብት የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ አትፍራ፥ በሞተ ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና። በሕይወቱ ሳለ ነፍሱን ባርኮአልና ለሰውነቱ መልካም በማድረጉ ይወደሳልና። ሆኖም ወደ አባቶቹ ትውልድ ይወርዳል፥ ለዘለዓለም ብርሃንን ወደ ማያዩበት። አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። የአሳፍ መዝሙር። የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት። ከጽዮን፥ ከውበት ሙላቱ እግዚአብሔር ያበራል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፥ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ ነፋስ አለ። በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም እንዲሁ በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል፥ “ከእኔ ጋር በመሥዋዕት ኪዳን ያቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡልኝ” ይላል። ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና። ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፥ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፥ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ። ስለ ቁርባንህ አልወቅስህም፥ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፥ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፥ በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ። ክፉውን ግን እግዚአብሔር አለው፦ ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ? ኪዳኔንም በአፍህ ለምን ትይዛለህ? አንተስ ተግሣጼን ጠላህ፥ ቃሎቼንም ወደ ኋላህ ጣልህ። ሌባውን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ትሮጥ ነበር እድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ። አፍህ ክፋትን አበዛ፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ። ተቀምጠህ በወንድምህን ላይ ክፉን ተናገርህ፥ የእናትህንም ልጅ አማህ። ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ፥ እኔ እንደ አንተ የምሆን መሰለህ፥ እዘልፍሃለሁ በፊትህም እቆማለሁ። እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ፥ አለዚያ ግን ስበታትናችሁ የሚያድንም የለም። ምስጋናን የሚሠዋ ያከብረኛል፥ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፥ አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፥ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። እነሆ፥ በዓመፃ ተወለድሁ፥ እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ። እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፥ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፥ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ። ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች። አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ይናገራል። መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፥ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም። አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ። የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያንጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ። ለመዘምራን አለቃ የዳዊት ትምህርት። ኤዶማዊው ዶይቅ መጥቶ ለሳኦል፦ ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቷል ብሎ በነገረው ጊዜ፥ ኃያል ሆይ፥ በክፋት ለምን ትኩራራለህ? ሁልጊዜስ በመተላለፍ? አንደበትህ ጥፋትን ያስባል፥ እንደ ተሳለ ምላጭ ሽንገላን አደረግህ። ከመልካም ይልቅ ክፋትን፥ ጽድቅንም ከመናገር ይልቅ ዓመፃን ወደድህ። የሚያጠፋ ቃልን ሁሉ፥ የሽንገላ ምላስን ወደድህ። ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ያፈርስሃል፥ ከድንኳንም ይነቅልሃል ያፈልስሃልም፥ ሥርህንም ከሕያዋን ምድር። ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፥ በእርሱም ይሥቃሉ እንዲህም ይላሉ፦ እግዚአብሔርን ረዳቱ ያላደረገ፥ በሀብቱም ብዛት የታመነ፥ በከንቱ ነገርም የበረታ ያ ሰው እነሆ። እኔስ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ ነኝ፥ ለዓለምና ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ርኅራኄ ታመንሁ። አድርገህልኛልና ለዘለዓለም አመሰግንሃለሁ፥ በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ። ለመዘምራን አለቃ፥ በማኽላት፥ የዳዊት ትምህርት። ኣላዋቂ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል። ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ፥ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም። የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉም በደሉ፥ አብረውም ረከሱ፥ አንድ እንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም። እንጀራ እንደሚበላ ሕዝቤን የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም። በዚያ የሚያስፈራ ሳይኖር እጅጉን ፈሩ፥ እግዚአብሔር የከበቡህን አጥንቶች በትኖአልና፥ እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና አሳፈርሃቸው። መድኃኒትን ከጽዮን ለእስራኤል ማን በሰጠ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል። ለመዘምራን አለቃ፥ በበገናዎች፥ የዳዊት ትምህርት። ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል፦ እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፥ አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ። አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፥ እንግዶች ተነሥተውብኛልና፥ ጨካኞችም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም። እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታም ለሕይወቴ ደጋፊ ነው። ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፥ በእውነትህም አጥፋቸው። በፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፥ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፥ ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም የጠላቶቼን ውድቀት አይታለችና። ለመዘምራን አለቃ፥ በበገናዎች፥ የዳዊት ትምህርት። አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል። ተመልከተኝ መልስም ስጠኝ፥ በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፥ ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፥ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና። ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ። ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ መዘግነን ሸፈነኝ። በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ! እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፥ ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ። አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው አንደበታቸውንም ቁረጥ። በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፥ በደልና ሁከት በመካከልዋ ነው፥ በውስጧ ጥፋት አለ፤ ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም። ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፥ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር። አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፥ መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፥ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን። ሞት ይምጣባቸው፥ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፥ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና። እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ጌታም ያድነኛል። በማታና በጥዋት በቀትርም አቤቱታ አቀርባለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል። በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከተቃጣብኝ ጦርነት ነፍሴን በሰላም ያድናታል። አይለወጡምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቁላቸዋል። ወዳጄ ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፥ ኪዳኑንም አፈረሰ። አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ውስጥ ግን ጦርነት ነበረ፥ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ ነገር ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው። ሸክምህን በጌታ ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፥ ለጻድቁም ለዘለዓለም ሁከትን አይሰጠውም። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ታወርዳቸዋለህ፥ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፥ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ በአንተ እታመናለሁ። ለመዘምራን አለቃ፥ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ፥ ፍልስጥኤማውያን በጋት በያዙት ጊዜ፥ የዳዊት ቅኔ። አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፥ ሁልጊዜም ተዋጊ አስጨንቆኛል። የሚዋጉኝ በዝተዋልና ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ። እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ። በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሥጋ ምን ያደርገኛል? ሁልጊዜ ቃሎቼን ይጠመዝዙብኛል፥ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው። ይሸምቁብኛል ይሸሸጋሉ፥ ተረከዜን ይከታተላሉ፥ ነፍሴንም ለማጥፋት ይጠብቃሉ። መቼም አታድናቸውም! አቤቱ አሕዛብን በቁጣ ጣላቸው። አምላክ ሆይ፥ መዋተቴን ነገርሁህ፥ እንባዬን በአቁማዳ ውስጥ አኑር። በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፥ አንተ አምላኬ ከእኔ ጋር እንደሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ። በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በጌታ ቃሉን እወድሳለሁ። በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል? አቤቱ፥ በአንተ ዘንድ ሰእለት አለብኝ፥ የምስጋና መሥዋዕት አቀርብልሀለሁ፥ ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን በእግዚአብሔር ዘንድ እመላለስ ዘንድ። ለመዘምራን አለቃ፥ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፥ የዳዊት ቅኔ። ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፥ ጉዳት እስኪያልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ። እቅዱን በእኔ ላይ ወደሚፈጽመው አምላክ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ። ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፥ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ። ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፥ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው። አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን። ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፥ ጉድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ። ልቤ ጽኑ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑ ነው፥ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ። ክብሬ ይነሣ ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፥ እኔም ማልጄ እነሣለሁ። አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፥ ርኅራኄህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ። አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን። ለመዘምራን አለቃ፥ አታጥፋ። የዳዊት ቅኔ። በእውነት ጽድቅን ትናገራላችሁን፥ ገዢዎች ሆይ፥ በቅን ትፈርዳላችሁን? በልባችሁ በምድር ላይ ግፍን ትሠራላችሁና፥ እጆቻችሁም ዐመጽን ይፈጽማሉና። ክፉዎች ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፥ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፥ ሐሰትንም ተናገሩ። የእባብ መርዝ ዓይነት መርዝ አላቸው፥ ጆሮውን እንደደፈነ እባብ ናቸው፥ አስማተኛ ሲደግምባት የአስማተኛውን ቃል እንደማትሰማ። አምላክ ሆይ ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ስበር፥ የአንበሶቹን መንጋጋቸውን አድቅቅ። እንደሚፈስስ ውኃ ይጥፉ፥ ቀስትን ሲገትሩ ፍላጻው ይጣመም። እንደሚሟሟ ቀንድ አውጣ፥ ፀሐይን እንዳላየ ጭንጋፍ ይሁኑ። ድስታችሁ የእሾኽን መቀጣጠል ከመስማቱ በፊት፥ ሕያዋን ሳላችሁ በመዓቱ ጠራርጎ ያጠፋል። ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል፥ በክፉዉም ደም እግሮቹን ይታጠባል። ሰውም፦ “በእውነት ለጻድቅ ፍሬ አለው፥ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ” ይላል። ለመዘምራን አለቃ፥ አታጥፋ። ሳኦል ይገድሉት ዘንድ ቤቱን እንዲጠብቁ በላከ ጊዜ፥ የዳዊት ቅኔ። አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፥ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ። ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ። እነሆ፥ በነፍሴ ላይ አድብተዋልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ፥ አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም። ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፥ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም። አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፥ ክፉ ከዳተኞችን ሁሉ አትማራቸው። ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ያላዝኑ፥ በከተማም ይዙሩ። እነሆ፥ በአፋቸው ግሳት ይናገራሉ፥ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፥ ማን ይሰማል? ይላሉ። አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ማላገጫ ታደርጋቸዋለህ። እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ። የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል። ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፥ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም። ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ። በቁጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፥ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንደሚገዛ ይወቁ። ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፥ ያልጠገቡ እንደሆነም ያላዝኑ። እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፥ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፥ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና። ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፥ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ የቸርነትም አምላኬ ነህና። ለመዘምራን አለቃ፥ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ። የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ ዐሥራ ሁለት ሺህ በገደለ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፥ ተቈጣኸን ጠግነን። ምድርን አናወጥሃት አወክሃትም፥ ተናውጣለችና ቁስልዋን ፈውስ። ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን። ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም። እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፥ “በድል መንፈስ፥ ሴኬምንም እከፋፍላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እለካለሁ። ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፥ ኤፍሬም የራሴ ቁር ነው። ይሁዳ ንጉሤ በትሬ ነው፥ ሞዓብ መታጠቢያ ሳህኔ ነው፥ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፥ በፍልስጥኤም ላይ በድል እጮኻለሁ። ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?” አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም። በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፥ እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና። ለመዘምራን አለቃ፥ በበገናዎች፥ የዳዊት መዝሙር። አምላክ ሆይ፥ ጩኸቴን ስማ፥ ጸሎቴንም አድምጥ። ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ ከፍ ባለ ዓለት ላይ ትመራኛለህ። በጠላት ፊት ጽኑ ግንብ፥ መጠጊያዬም ሆነኸኛልና። በድንኳንህ ለዘለዓለም እኖራለሁ፥ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ፥ አቤቱ፥ አንተ ስእለቴን ሰምተሃልና፥ ስምህንም ለሚፈሩ ርስትን ሰጠሃቸው። ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀን ትጨምራለህ፥ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናሉ። በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም ይኖራል፥ ይጠብቁት ዘንድ ቸርነትንና እውነትን አዘጋጅለት። እንዲሁ ለስምህ ለዘለዓለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ። ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ኤዶታም፥ የዳዊት መዝሙር ነፍሴ በጸጥታ እግዚአብሔርን ትጠብቅ የለምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና። እርሱ ብቻ ዓለቴና መድኃኒቴም ነው፥ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ በፍጹም አልታወክም። እስከ መቼ በሰው ላይ ትነሣላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድላላችሁ። ከከፍታ ያናውጡት ዘንድ መከሩ፥ ሐሰትንም ይወድዳሉ፥ በአፋቸው ይባርካሉ፥ በልባቸውም ይረግማሉ። ነገር ግን፥ ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን በጸጥታ ጠብቂ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና። እርሱ ዓለቴም መድኃኒቴም ነውና፥ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ አልታወክም። መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፥ ጠንካራ ዓለቴና መጠለያዬ እግዚአብሔር ነው። ሕዝቦች ሆይ፥ ሁልጊዜ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፥ እግዚአብሔር መጠጊያችን ነው። ነገር ግን የሰው ልጆች ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፥ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው። ዓመፃን ተስፋ አታድርጉ፥ ቅሚያንም አትተማመኑት፥ ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኩራ። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፥ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥ አቤቱ፥ ቸርነትም ያንተ ነው፥ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍላለህና። በኤዶምያስ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፥ የዳዊት መዝሙር። አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፥ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች በደረቅ መሬት፥ ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ። ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ። ቸርነትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ። ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ። በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም ስለ አንተ አሰላስላለሁ፥ ረዳቴ ሆነኸኛልና፥ በክንፎችህም ጥላ በደስታ እዘምራለሁ። ነፍሴ ከኋላህ ተቆራኘች፥ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ። እነርሱ ግን ነፍሴን ለከንቱ ፈለጓት፥ ወደ ምድር ጥልቅ ይገባሉ። ለሰይፍ እጅ አልፈው ይሰጣሉ፥ የቀበሮም እድል ፈንታ ይሆናሉ። ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱ የሚምል ሁሉ ይከብራል፥ ሐሰትን የሚናገር አፍ ይዘጋልና። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በሮሮዬ ድምፄን ስማ፥ ከጠላትም ፍርሃት ነፍሴን አድን። ከክፉዎች ደባ፥ ከዓመፀኞችም ብዛት ሰውረኝ። እንደ ሰይፍ ምላሳቸውን አሰሉ፥ እንደ ፍላጻ መራራ ነገርን ለመወርወር፥ ንጹሕንም በስውር ለመንደፍ ቀስትን ገተሩ፥ ድንገት ይነድፉታል አይፈሩምም። ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፥ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፥ ማንስ ያየናል? ይላሉ። ዓመፃን ፈለጓት፥ ሲፈትኑም አለቁ፥ የሰው የውስጥ አሳቡና ልቡ የጠለቀ ነው፥ እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። ድንገተኛ ፍላጻም ያቈስላቸዋል፥ አንደበታቸው ያሰናክላቸዋል፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ይደነግጣሉ። ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ። ጻድቅ በጌታ ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፥ ልባቸውም ቅን የሆነ ሁሉ እልል ይላሉ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ስእለት ይቀርባል። ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ሥጋ ሁሉ ይመጣል። የዓመፃ ነገር በረታብን፥ መተላለፋችንንስ አንተ ይቅር ትላለህ። አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው ምስጉን ነው፥ ከቤትህ፥ ከቅዱስ መቅደስህ፥ በረከት እንጠግባለን። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ በጽድቅ፥ በድንቅ ነገሮች መለስክልን። በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል። የባሕሩን ማጓራት፥ የሞገድንም ጩኸት፥ የአሕዛብንም ማጉረምረም ዝም ታሰኛለህ። ከተኣምራትህ የተነሣ በምድር ዳርቻ የሚኖሩ ይፈራሉ፥ የጥዋትንና የማታን መውጫዎች ደስ ታሰኛቸዋለህ። ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፥ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፥ ምግባቸውን አዘጋጀህ፥ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፥ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ፈለጎችህ ስብን ይጠግባሉ። የምድረ በዳ መስኮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፥ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም። ለመዘምራን አለቃ፥ የመነሣት የምስጋና መዝሙር። በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ። እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፦ “ሥራህ እንዴት ግሩም ነው፥ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ።” ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፥ ከሰው ልጆች ይልቅ በግብሩ ግሩም ነው። ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፥ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል። በኃይሉ ለዘለዓለም ይገዛል፥ ዐይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፥ ዓመፀኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድርጉ። አሕዛብ ሆይ፥ አምላካችንን ባርኩ፥ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ። ነፍሴን በሕይወት ያኖራታል፥ እግሮቼንም ለመናወጥ አልሰጠም። አቤቱ፥ ፈትነኸናልና፥ ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና። ወደ ወጥመድ አገባኸን፥ በጀርባችንም መከራን አኖርህ። ሰው በራሳችን ላይ እንዲረማመድ አደረግህ፥ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ በረከትም አወጣኸን። ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፥ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን በከንፈሮቼም ቃል የገባሁልህንስእለቴን እፈጽማለሁ። ከወጠጤዎች መዓዛ ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለሁ፥ ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልሃለሁ። እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሁሉ፥ ኑ፥ ስሙኝ፥ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ። በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፥ በአንደበቴም አመሰገንሁት። በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ፥ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ። ጸሎቴን ያልከለከለኝ ቸርነቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን። ለመዘምራን አለቃ፥ በበገናዎች፥ የዳዊት መዝሙር። እግዚአብሔር ይማረን ይባርከንም፥ ፊቱንም በላያችን ያብራ፥ መንገድህንም በምድር፥ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ማዳንህን እናውቅ ዘንድ። አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ። ለአሕዛብ በቅን ትፈርድላቸዋለህና፥ አሕዛብንም በምድር ላይ ትመራለህና አሕዛብ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ። አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ። ምድር ፍሬዋን ሰጠች፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል። እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ። ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፥ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ክፉዎች ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ። ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም እልል ይበሉ። ለእግዚአብሔር ተቀኙ ለስሙም ዘምሩ፥ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፥ ስሙ ጌታ ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ። እግዚአብሔር በቅዱስ መኖሪያው ወላጅ ለሞቱባቸው አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፥ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ። አቤቱ፥ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥ ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠባጠቡ። አቤቱ፥ የተትረፈረፈ ዝናብ ለርስትህ አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው። እንስሶችህ በውስጡ አደሩ፥ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ። ጌታ ትእዛዙን ሰጠ፥ የሚያበሥሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው። የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፥ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች። በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ። ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ። መለኮታዊ ተራራ፥ የባሳን ተራራ ፥ የጸና ተራራና የባሳን ተራራ። ጽኑ ተራራዎች ሆይ ለምን በቅናት ታያላችሁ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው፥ በእውነት ጌታ ለዘለዓለም ያድርበታል። የእግዚአብሔር ሠረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፥ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው። ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ከሰዎች ወሰድህ፥ ከዓመፀኞችም ጭምር፥ በዚያም ጌታ ያድር ዘንድ። በየዕለቱ የሚንከባከበን ጌታ የተመሰገነ ይሁን፥ እግዚአብሔር ያድነናል። አምላካችንስ የሚያድን አምላክ ነው፥ ከሞት ማምለጫውም ከጌታ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፥ በበደል የሚሄድንም የጠጉሩን አናት ይቀጠቅጣል። ጌታ እንዲህ አለ፦ ከባሳን አመጣቸዋለሁ፥ ከባሕርም ጥልቅ እመልሳቸዋለሁ፥ እግሮችህ በደም ይረገጡ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶች ላይ ይሆን ዘንድ። አምላክ ሆይ ጉዞህን አዩት፥ የአምላኬና የንጉሤ ንግደት ወደ ቤተ መቅደስ። አለቆች ቀደሙ፥ መዘምራንም ተከተሉ፥ ከበሮን በሚመቱ በቈነጃጅት መካከል። እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ የእስራኤል ምንጭ ጌታችንንም አመስግኑት። ወጣቱ ብንያም በጉልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች፥ የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች። አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፥ አቤቱ፥ ለእኛ የሠራኸውን አጽናው። በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ። በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን መንጋ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፥ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው። መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፥ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ። በምሥራቅ በኩል በሰማየ ሰማያት ላይ ተቀምጦ ለሚጓዘው የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል። ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፥ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው። እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፥ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፥ እግዚአብሔር ይመስገን። ለመዘምራን አለቃ፥ በመለከቶች፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ። በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቆሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ። በጩኸት ደከምሁ ጉሮሮዬም ሰለለ፥ አምላኬን ስጠብቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ። በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጉር በዙ፥ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፥ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ። አቤቱ፥ አንተ ቅብጠቴን ታውቃለህ፥ ጥፋቴም ከአንተ አልተሰወረም። አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ። ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና። ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው። የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና። ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው። በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፥ ሰካራሞች በእኔ ላይ ይዘፍናሉ። አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፥ አቤቱ፥ በቸርነትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ። እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፥ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ። የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጉድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ። አቤቱ፥ ቸርነትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፥ ከባርያህም ፊትህን አትሰውር፥ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ መልስልኝ። ወደ ነፍሴ ቀርበህ ተቤዣት፥ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ። አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፥ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው። ስድብ እስክታመም ድረስ ልቤን ሰበረው፥ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም፥ የሚያጽናናኝም አጣሁ። ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ። ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፥ ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ወገባቸውም ዘወትር ይንቀጥቀጥ። መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቁጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው። ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፥ አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ ባቈሰልከውም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩ። በበደል ላይ በደልን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ። ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ። እኔ ችግረኛና ቁስለኛ ነኝ፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህ ያቁመኝ። የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ቀንድና ሰኰና ካበቀለ ኰርማ ወይም ወይፈን ይልቅ ጌታን ደስ ያሰኘዋል። ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ። ጌታ ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና። ሰማይና ምድር ባሕርም በእርሷም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል። እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፥ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል። የአገልጋዮቹ ልጆች ይኖሩባታል፥ ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ። ለመዘምራን አለቃ፥ ለመታሰቢያ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ አድነኝ፥ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቁሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም። እሰይ እሰይ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ። የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስ ይበላቸው፥ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ፦ እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ። እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ አቤቱ፥ እርዳኝ፥ ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፥ አቤቱ፥ አትዘግይ። አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፥ ለዘለዓለም አልፈር። በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም። ሁልጊዜ የምጠጋበት ዓለት ሁነኝ፥ ጠንካራ መሸሸጊያ፥ ዓለቴና መጠጊያዬ አንተ ነህና። አምላኬ፥ ከክፉ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ። አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ አቤቱ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና። ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው። ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፥ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ። አፌን ምስጋና ሞላ ሁልጊዜ ክብርህንና እዘምር ዘንድ። በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ። ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፥ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ፦ “እግዚአብሔር ትቶታል፥ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።” አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፥ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጉዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ። እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ። መዘርዘር ከምችለው በላይ ቢሆንም፥ አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል። በጌታ ኃይል እገባለሁ፥ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ። አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፥ እስከ ዛሬም ተኣምራትህን እነግራለሁ። እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ። አቤቱ፥ ጽድቅህ እስከ አርያም ይደርሳል፥ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፥ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፥ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኸኝ። ክብሬን ታበዛለህ፥ ተመልሰህም ደስ ታሰኘኛለህ፥ እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፥ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ እንዲሁ። ጉዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል። ስለ ሰሎሞን። አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥ ሕዝብህን በጽድቅ፥ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ። በጽድቅ፥ ተራሮችና ኰረብቶች ለሕዝብህ ሰላምን ይቀበሉ። ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ይፍረድ፥ የድሆችንም ልጆች ያድን፥ ጨቋኙንም ይጨፍልቅ። ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለፊት ለልጅ ልጅ ይኑር። እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይውረድ። በዘመኑም ጽድቅ ያብብ፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ይብዛ። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይግዛ። በፊቱም የኢትዮጵያ ሰዎች ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፥ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ። ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል። ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፥ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፥ ደማቸው በፊቱ ክቡር ነው። በሐወት ይኑር፥ ከዓረብም ወርቅ ይሰጠው፥ ሁልጊዜም ስለ እርሱ ይጸልይ፥ ዘወትርም ይባረክ። በምድር ላይ እህሉ ይትረፍረፍ፥ በተራሮችም ላይ ሰብል ይወዛወዝ፥ ፍሬውም እንደ ሊባኖስ ከፍ ከፍ ይበል፥ ሰዎችም በከተማ እንደ ምድር ሣር ይለምልሙ። ስሙ ለዘለዓለም ይታወስ፥ እንደ ፀሐይ ዕድሜ ስሙ ጸንቶ ይኑር፥ የምድር አሕዛብ ሁሉ በርሱ ይባረኩ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመሰግኑት፥ ብቻውን ተኣምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ። የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘለዓለም ይባረክ፥ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። አሜን፥ አሜን። የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎቶች ተፈጸሙ። የአሳፍ መዝሙር። እግዚአብሔር ለእስራኤል እንዴት ቸር ነው፥ ልባቸው ንጹሕ ለሆነ። እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ በአረማመዴም ልወድቅ ትንሽ ቀረኝ። የክፉዎችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። ለሞታቸው ስቃይ የለውምና፥ ሰውነታቸውም ጤናማ ነው። እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም። ስለዚህ ትዕቢት የአንገት ሐብላቸው፥ ዓመጽ መጐናጸፊያቸው ሆነ። ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፥ ልባቸውም በቅዥት ተሞላ። በሹፈት ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ። በሰማይ ላይ በድፍረት ተናገሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ። ስለዚህ ሕዝቤም ወደ እነርሱ ይመለሳሉ፥ ከሞላ ውሃቸውም ይጋታሉ ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለን? ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ክፉዎቸ ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ሀብታቸውን ያበዛሉ። እንዲህም አልሁ፦ በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። “እንደዚህ እናገራለሁ” ብል ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ። ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ። በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ፥ በድንጋጤ ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ መልካቸውን ትንቃለህ። ልቤ ነድዶአልና፥ ኩላሊቴም ቀልጦአልና፥ እኔ የተናቅሁ ነኝ አላወቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ። እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በአንተ ምክር መራኸኝ፥ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ። በሰማይ ከአንተ ሌላ ማን አለኝ? በምድርስ ከአንተ ጋር ሆኜ ሌላ ምን እሻለሁ? ልቤና ሥጋዬ አለቀ፥ እግዚአብሔር ግን ዘለዓለም የልቤ ኃይልና እድል ፈንታዬ ነው። እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፥ በማመንዘር ከአንተ የሚርቁትን ሁሉ አጠፋኻቸው። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፥ መጠለያዬም ጌታ ነው ሥራህን ሁሉ እናገር ዘንድ። የአሳፍ ትምህርት። አቤቱ፥ ስለምን ለሁልጊዜ ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቁጣህ ስለምን ጨሰ? አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዠሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርሷ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ። መጠን ወደሌላቸው ፍርስራሶች እርምጃህን አቅና፥ ጠላት በመቅደስ ያለውን ሁሉ አጥፍቶአል። ጠላቶችህ በአደባባይህ ላይ አገሡ፥ ለድል ምልክት ዐላማቸውን አኖሩ። በላይኛው መግቢያ ውስጥ፥ በዱር፥ በመጥረቢያ እንጨቶችን የሚቆርጡ ሰዎችን ይመስላሉ። እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት። መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፥ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ። አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው፦ ኑ፥ የእግዚአብሔርን የተቀድሱ ቦታዎችን አቃጠሉ። ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ አይኖርም፥ ይህም እስከ መቼ እንደሚቆይ የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም። አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ለሁልጊዜ ያቃልላልን? እጅህንም ለምን ትመልሳለህ? ቀኝ እጅህንም ለምን በብብትህ መካከል ታቆያለህ? እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። አንተ ባሕርን በኃይልህ ከፈልካት፥ የአውሬዎችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። አንተ የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፥ ለኢትዮጵያ ሰዎችም እንደ ምግብ ሰጠሃቸው። አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፥ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ። ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፥ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ። አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ አረጋገጥህ፥ በጋንም ክረምትንም አንተ ሠራህ። ይህንንም አስታውስ፥ ጠላት በጌታ ተሳለቀ፥ አላዋቂ ሕዝብም በስምህ ቀለደ። የምትገዛልህን እርግብ ለአራዊት አትስጣት፥ የችግረኞችህን ነፍስ መቼውንም አትርሳ። ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በዓመፅ ቤቶች ተሞልተዋልና። ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፥ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ። አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፥ አላዋቂዎች ዘወትር የተሳለቁብህን አስብ። የጠላቶችህን ቃል አትርሳ፥ የተቃዋሚዎችህ ድንፋታ ሳያቋርጥ ወደ አንተ ይወጣል። ለመዘምራን አለቃ፥ አታጥፋ። የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። አቤቱ፥ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን፥ ስምህም ቅርብ ነው፥ ተኣምራትህን ሁሉ እንናገራለን። “በወሰንኩት ጊዜ እኔ በቅን እፈርዳለሁ።” ምድርና በእርሷ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ይናወጣሉ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ። ትምክህተኞችን፦ “አትኩሩ፥ ክፉዎችንም፦ ቀንዳችሁን አታንሡ ፥” አልኋቸው ቀንዳችሁን እስከ ላይ አታንሡ፥ በእብሪተኛ አንገት አትናገሩ። ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረበዳ የለምና፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህንን ያዋርዳል ያንንም ያከብራል። ጽዋ በጌታ እጅ ነውና፥ ኃይለኛ የወይን ጠጅ ሞላበት፥ ከዚህ ወደዚያ አገላበጠው፥ ነገር ግን አተላው አልፈሰሰም፥ የምድር ክፉዎች ሁሉ ይጠጡታል። እኔ ግን ለዘለዓለም ደስ ይለኛል፥ ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬን አቀርባለሁ። “የክፉዎችን ቀንዶች ሁሉ እሰብራለሁ፥ የጻድቃን ቀንዶች ግን ከፍ ከፍ ይላሉ።” ለመዘምራን አለቃ፥ በበገናዎች፥ ስለ አሦራውያን፥ የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው። ድንኳኑ በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው። በዚያም የሚያንጸባርቁ ፍላጻዎችን፥ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ፥ አንተ በዘለዓለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ። ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ እንቅልፋቸውንም አንቀላፉ፥ የጦር ሰዎች በሙሉ በእጃቸው ምንም ማድረግ አልቻሉም። የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ፈረሶች አንቀላፉ። አንተ ግን፥ አንተ ግሩም ነህ፥ ቁጣህን ማን ይቃወማል? ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፥ ምድር ፈራች ዝምም አለች፥ የምድር ትሑታንን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ። የሰውም ቁጣ ሳይቀር ክብርህን ይገልጣል፥ ከዚህ የሚተርፈውንም ትታጠቀዋለህ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ስእለትን ክፈሉ፥ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ለሚያስፈራው እጅ መንሻን ያስገቡ። የመኳንንትን ነፍስ ያወጣል፥ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል። ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ኤዶታም፥ የአሳፍ መዝሙር። በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ። በመከራዬ ቀን ጌታን ፈለግሁት፥ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም። እግዚአብሔርን ሳስታውስ እተክዛለሁ ፥ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች። ዐይኖቼ እንዲተጉ ያዝሃቸው፥ ስለተረበሽኩ አልተናገርሁም። የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፥ የጥንቱን ዓመታት አሰብሁ፥ በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት። ጌታ ለዘለዓለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን? ለዘለዓለምስ ርኅራኄው ተቈረጠችን? የሰጠውስ ቃል ኪዳን ለዘመናት አልቆአልን? እግዚአብሔርስ ማዘኑን ረሳን? በቁጣውስ ርኅራኄውን ዘጋውን? ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ መለወጡ። የጌታን ሥራ አስታወስሁ፥ የቀደመውን ተኣምራትህን አስታወሳለሁና፥ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ ሥራህንም አሰላስላለሁ። አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልህን አስታወቅሃቸው። የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው። አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፥ ጥልቆችም ተነዋወጡ። ደመኖች ውሃን አዘነቡ፥ ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም በየአቅጣጫው ወጡ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነበረ፥ መብረቆች ለዓለም አበሩ፥ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም። መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፥ ያለፍከውም ኃይለኛ ውኆች በኩል ነው፤ ዱካህ ግን አልታወቀም። በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው። የአሳፍ ትምህርት። ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፥ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ። አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፥ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም እንቆቅልሽ እናገራለሁ። የሰማነውንና ያወቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ከልጆቻቸው አንሰውረውም፥ ለሚመጣውም ትውልድ የጌታን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት እንናገራለን። ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፥ የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው እንዲናገሩ ነው፥ ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፥ እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ዐመፀኛና የሚያስመርር ትውልድ፥ ልቡን ያላቀና ትውልድ፥ መንፈሱም በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነ። የኤፍሬም ልጆች ለውጊያ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በጦርነት ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ። የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፥ መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥ በግብጽ አገርና በጾዓን አገር በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት። ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፥ ውኆችን እንደ ግንብ አቆመ። ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን። ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፥ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው። ውኃን ከዓለት አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ። ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት። የተመኙትን መብል እየጠየቁ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት። እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት፦ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን? ዓለቱን መታ፥ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፥ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?” ጌታም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፥ በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በማዳኑም አልተማመኑምና። ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፥ ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እህል ሰጣቸው። የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው። ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፥ ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፥ በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ። በሉ እጅግም ጠገቡ፥ የተመኙትንም ሰጣቸው። ከወደዱትም አላሳጣቸውም፥ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ጠንካሮችን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች መታ። ከዚህም ሁሉ ጋር እንደገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፥ ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በሽብር። በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፥ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፥ ዓለታቸው እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደሆነ አስታወሱ። በአፋቸው ሸነገሉት፥ በአንደበታቸውም ዋሹት፥ ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ ለቃል ኪዳኑም አልታመኑም። እርሱ ግን ርኅሩኅ ነው፥ በደላቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፥ ከቁጣውም መመለስን አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም። ወጥቶ የማይመለስ ነፋስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ። በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት። መላልሰው፥ እግዚአብሔርንም ተፈታተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥ በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጾዓን አገር ያደረገውን ድንቁን። ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን እንዳይጠጡ። ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፥ በጓጉንቸርም አጠፋቸው። ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ። እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለመብረቅ ሰጠ። የቁጣውን ንዳድ በላያቸው ሰደደ፥ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ። ለቁጣው መንገድን ጠረገ፥ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ ሕይወታቸውንም ለመቅሰፍት አሳልፎ ሰጠ። በኩሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች መታ። ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው። በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው። ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ገዛችው ወደዚህች ተራራ፥ ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በድንኳናቸው አኖረ። ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት፥ ዐመፁበትም፥ ትእዛዙንም አልጠበቁም፥ ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፥ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፥ በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት። እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ፥ የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረባትን ድንኳኑን፥ ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ። ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ በርስቱም ላይ ንዴቱን ገለጠ። ጉልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ልጃገረዶቻቸውም የሰርግ ዘፈን አላዩም። ካህኖቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ መበለቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም። ጌታ ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ በወይን ኃይል እንደተበረታታ ጀግና፥ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፥ የዘለዓለምን ውርደት አከናነባቸው። የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፥ የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ። መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት። ዳዊትንም ባርያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፥ ከሚያጠቡ በጎችም በኋላ፥ ባርያውን ያዕቆብን ርስቱንም እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው። በልቡ ቅንነት ጠበቃቸው፥ በእጁም ብልሃት መራቸው። የአሳፍ መዝሙር። አቤቱ፥ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፥ ቅዱሱን መቅደስህንም አረከሱ፥ ኢየሩሳሌምንም አፈራረሱአት። የባርያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፥ ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፥ የሚቀብራቸውም አጡ። ለጎረቤቶቻችንም ስድብ ሆንን፥ በዙሪያችንም ላሉ መሳቂያና መሳለቂያ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘለዓለም ትቈጣለህ? ቅንዓትህም እንደ እሳት ይነድዳል? በማያውቁህ አሕዛብ ላይ፥ ስምህንም በማይጠሩ መንግሥታት ላይ መዓትህን አፍስስ፥ ያዕቆብን በልተውታልና፥ መኖርያውንም ባድማ አድርገዋልና። የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተዋርደናልና። አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ እርዳን፥ ስለ ስምህ ክብር፥ አቤቱ፥ ታደገን፥ ስለ ስምህም ኃጢአታችንን አስተሰርይልን። አሕዛብ፦ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ለምን ይበሉ፥ የፈሰሰውን የባርያዎችህን ደም በቀል በዐይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ። የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፥ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን። አቤቱ፥ የተዘባበቱብህን መዘባበታቸውን ለጎረቤቶቻችን ሰባት እጥፍ በብብታቸው ክፈላቸው። እኛ ሕዝብህ ግን፥ የማሰማርያህም በጎች፥ ለዘለዓለም እናመሰግንሃለን፥ ለልጅ ልጅም ምስጋናህን እንናገራለን። ለመዘምራን አለቃ፥ በመለከቶች፥ ስለ አሦራውያን፥ የአሳፍ የምስክር መዝሙር። ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ብርሃንህን አብራ። በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና። አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን። የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ በሕዝብህ ጸሎት ላይ እስከ መቼ ትቈጣለህ? የእንባ እንጀራን መገብካቸው፥ እንባም በስፍር አጠጣሃቸው። ለጎረቤቶቻችን መከራከርያ አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም ይሣለቁብናል። የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን። ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፥ አሕዛብን አባረርህ እርሷንም ተከልህ። በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች። ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ። ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች። አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል። የዱር እርያ አረከሳት፥ የአገር አውሬም ተሰማራባት። የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፥ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ። ቀኝህ እጅህ የተከለውን፥ ለራስህ ያጸናኸውን ልጅ ጠብቅ። በእሳት ተቃጥላለች ተነቅላማለች ከፊትህ ተግሣጽም የተነሣ ይጠፋሉ። እጅህ በቀኝህ ሰው ላይ፥ ለአንተ ባጸናኸው በሰው ልጅ ላይ ትሁን። ከአንተም አንራቅ፥ አድነን ስምህንም እንጠራለን። የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን። ለመዘምራን አለቃ፥ በዋሽንት፥ የአሳፍ መዝሙር። ለኃይላችን ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ። ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፥ በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፥ ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ። ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አድርጎ አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ። ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ። በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ ከተሰወረ የሞገድ ስፍራ መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ። ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ እነግርሃለሁም፥ እስራኤል ሆይ፥ ምነው በሰማኸኝ! አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም። ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ ጌታ አምላክህ ነኝና፥ አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም። ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም። እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ። ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፥ የጌታ ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘለዓለም በሆነ ነበር፥ ከስንዴም ስብ ባበላኋቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገብኋቸው ነበር። የአሳፍ መዝሙር። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ጉባኤ ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል። እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼስ ለክፉዎች ታደላላችሁ? ለድሆችና ወላጅ ለሞተባቸው ፍረዱ፥ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ፍትሕን አድርጉ፥ ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፥ ከክፉዎችም እጅ አስጥሉአቸው። አያውቁም፥ አያስተውሉም፥ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ፥ የምድር መሠረቶች ሁሉ ተናወጡ። እኔ ግን፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ አልሁ፥ ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ። አቤቱ፥ ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍረድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና። የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። አቤቱ፥ በጸጥታ አትቆይ፥ አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል። እነሆ፥ ጠላቶችህ ጮኽዋልና፥ የሚጠሉህም ራሳቸውን አንሥተዋልና። ሕዝብህን በምክር ሸነገሉአቸው፥ በቅዱሳንህም ላይ ተማከሩ። ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፥ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ። በአንድ ልብ በአንተ ላይ ተማከሩ፥ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፥ የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም፥ ሞዓብም አጋራውያንም፥ ጌባል አሞንም አማሌቅም፥ ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋር፥ አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ፥ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ሆኗቸው። እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፥ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው። በዓይንዶር ጠፉ፥ እንደ ምድርም ጉድፍ ሆኑ። አለቆቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ፥ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸው፦ የእግዚአብሔርን መስክ እንወርሳለን የሚሉትን። አምላኬ ሆይ፥ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው። እሳት ደንን እንደሚያቃጥል፥ ነበልባልም ተራሮችን እንደሚያነድድ፥ እንዲሁ በቁጣህ አሳድዳቸው፥ በመቅሠፍትህም አስደንግጣቸው። ፊታቸውን እፍረት ሙላው፥ አቤቱ፥ ስምህንም ይፈልጋሉ። ይፈሩ ለዘለዓለሙም ይታወኩ፥ ይጐስቁሉ ይጥፉም። ስምህም “ጌታ” እንደሆነ፥ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንህ ይወቁ። ለመዘምራን አለቃ፥ በዋሽንት፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው! ነፍሴ የጌታን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፥ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ። ወፍ ለእርሷ ቤትን አገኘች፥ ዋኖስም ጫጩቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች፥ በመሠውያህ አጠገብ፥ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፥ በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፥ ለዓለምና ለዘለዓለምም ያመሰግኑሃል። አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው። በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ ሲያልፉ የምንጭ ቦታ ያደርጉታል፥ የበልግም ዝናብ በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፥ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል። የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ አድምጥ። አቤቱ፥ መታመናችንን እይልን፥ ወደ ቀባኸውም ፊት ተመልከት። ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፥ በክፉዎች ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት ደጃፍ ላይ መቅረትን መረጥሁ። ጌታ አምላክ ፀሐይና ጋሻ ነው፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፥ ጌታ በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያስቀራቸውም። የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው። ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። አቤቱ፥ ምድርህን በመልካም ጎበኘህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ። የሕዝብህን በደል አስቀረህ፥ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይቅር አልክ። መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፥ ከቁጣህ መቅሠፍት ተመለስህ። የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቁጣህንም ከእኛ መልስ። በውኑ ለዘለዓለም ትቈጣናለህን? ቁጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን? አቤቱ፥ ሕይወትን ልትሰጠን አትመለስምን? ሕዝብም በአንተ ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህን አሳየን፥ አቤቱ፥ ማዳንህንም አሳየን። እግዚአብሔር የሚናገረውን እሰማለሁ፥ ወደ እብደታቸው ካልተመለሱ በቀር ጌታ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ይናገራልና። ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው። ጽኑ ፍቅርና እውነት ተገናኙ፥ ጽድቅና ሰላም ተቃቀፉ። እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። ጌታም በጎ ነገርን ይሰጣል፥ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፥ የእርምጃውንም ዱካ በመንገድ ውስጥ ያኖራል። የዳዊት ጸሎት አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ደሃና ችግረኛ ነኝና። ታማኝ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፥ አምላኬ ሆይ፥ በአንተ የታመነውን አገልጋይህን አድነው። አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ። የአገልጋይህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና። አቤቱ፥ አንተ መልካምና ይቅር ባይ ነህና፥ ጽኑ ፍቅርህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና። አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ። ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ። አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ ሥራህንም የሚመስል የለም። ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፥ አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና። አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፥ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘለዓለምም ስምህን አከብራለሁ፥ ጽኑ ፍቅርህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና። አቤቱ፥ ትዕቢተኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፥ ላንተም ምንም ቦታ የላቸውም። አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፥ ለቁጣ የዘገየህ፥ ጽኑ ፍቅርህና እውነትህ የበዛ፥ ወደ እኔ ተመልከት፥ ራራልኝ፥ ኃይልህን ለአገልጋይህ፥ ማዳንህንም ለአግልጋይቱ ልጅ ለእኔ ስጥ። ለመልካም የሚሆን ምልክትን ከእኔ ጋር አድርግ፥ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽናንተኸኛልምና። የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፥ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ ጌታ የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ ስለ አንቺ የተከበረ ነገር ይባላል። ከሚያውቁኝ መሃል ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፥ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን፥ ጢሮስና የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ። ስለ ጽዮን ሰው እንዲህ ይላል፥ “ሰው ሁሉ በውስጥዋ ተወለደ ”፥ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። ጌታ እያለ ሕዝቦችን ይመዘግባል። “እገሌ በውስጥዋ ተወለደ” እያለ፥ በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል። የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ለመዘምራን አለቃ በማኸላት ለመዘመር፥ የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት። አቤቱ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ በቀንና በሌሊት በፊትህ ጮኽሁ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፥ ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና። ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ለዘለዓለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፥ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ። በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጉድጓድ አስቀመጥኸኝ። በእኔ ላይ ቁጣህ ጸና፥ ማዕበልህንም ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ። የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅህ፥ በእነርሱ ዘንድ አጸያፊ አደረግኸኝ፥ ተዘግቶብኛል፥ መውጫም የለኝም። ዐይኖቼም በመከራ ፈዘዙ፥ አቤቱ፥ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ። በውኑ ለሙታን ድንቅ ነገሮችን ታደርጋለህን? ጥላዎችስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? በመቃብርስ ውስጥ ጽኑ ፍቅርህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይነገራሉን? ድንቅ ሥራህ በጨለማ፥ ጽድቅህም በሚረሳበት ምድር ትታወቃለችን? አቤቱ፥ እኔ ግን ወደ አንተ ጮኽሁ፥ በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች። አቤቱ፥ ነፍሴን ለምን ትጥላለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ? እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብሁ ነኝ፥ በአስደንጋጭ ነገሮችህ ተሰቃየሁ፤ ምንም አቅም የለኝም። ቁጣህ በላዬ አለፈ፥ አስፈሪ ድርጊቶችህ አደቀቁኝ። ሁልጊዜ እንደ ውኃ ከበቡኝ፥ በአንድ ላይም አጥለቀለቁኝ። ወዳጄንና ባልንጀራዬን ከእኔ አራቅህ፤ ጨለማም ዘመዴ ሆነ። የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት። አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህን ለዘለዓለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ። እንዲህ ብለሃልና፦ ጽኑ ፍቅርህ ለዘለዓለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል። ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለአገልጋዬም ለዳዊት ማልሁ፦ ዘርህን ለዘለዓለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ። አቤቱ፥ ሰማያት ድንቅ ሥራህን ታማኝነትህንም፥ በቅዱሳን ማኅበር፥ ያመሰግናሉ። ጌታን በደመናት የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች ጌታን ማን ይመስለዋል? በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፥ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው። አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል። የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ። አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃያሉ ክንድህ ጠላቶችህን በተንሃቸው። ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፥ ዓለምንና ሞላውንም አንተ መሠረትህ። ሰሜንንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፥ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል። ኃያል ክንድ አለህ፥ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች። የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ፥ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ። እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ብፁዕ ነው፥ አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ። በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፥ የኃይላቸው ክብር አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና። ጋሻችን ከጌታ ነው፥ ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና። በዚያ ጊዜ ለታማኞችህ በራእይ ተናገርህ፥ እንዲህም አልህ፦ ረድኤቴን በኃያል ላይ አኖርሁ፥ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ። አገልጋዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ በቅዱስ ዘይቴም ቀባሁት። እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች። ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም። ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ። እውነቴና ጽኑ ፍቅሬም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ። እርሱ፦ አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል። እኔም ደግሞ በኩሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል። ለዘለዓለምም ጽኑ ፍቅሬን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው። ዘሩንም ለዓለምና ለዘለዓለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ። ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፥ ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፥ ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ። ጽኑ ፍቅሩን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፥ ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም። ዳዊትን በፍጹም እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ። ዘሩ ለዘለዓለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል። ለዘለዓለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፥ ምስክርነቱ በደመና የታመነ ነው። አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ በቀባኸውም ላይ በቁጣ ተነሣህ። የአገልጋይህን ኪዳን አፈረስህ፥ ዘውዱንም በምድር አረከስህ። ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ። መንገድ አላፊም ሁሉ ዘረፈው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ። የተቃዋሚዎቹን ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ። የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በጦርነትም ውስጥ አልደገፍኸውም። በትረ መንግሥትን ሻርህ፥ ዙፋኑንም በምድር ላይ ጣልህ። ዕድሜውንም አሳጠርህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው። አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘለዓለም ፊትህን ትሰውራለህ? እስከ መቼስ ቁጣህ እንደ እሳት ይነድዳል? ጊዜዬ ምን ያህል ውስን መሆኑን አስታውስ፥ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን? ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው? ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ጽኑ ፍቅርህ ወዴት ነው? አቤቱ፥ የአገልጋዮችህን ስድብ፥ በእቅፌ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥ አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን አንተ የቀባኸውን የሰደቡትን አስታውስ። ጌታ ለዘለዓለም ይባረክ። አሜን፤ አሜን። የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት። አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ። ሰውን ወደ አፈር ትመልሳለህ፥ “የሰው ልጆች ሆይ”፥ ተመለሱ ትላለህ፥ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ጥቂት ሰዓት ነውና። ታጥለቀልቃቸዋለህ፥ እንደ ሕልም ናቸው፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ሣር። ማልዶ ያብባል፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቁጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። የተሰወረውን መተላለፋችንን በፊትህ ብርሃን፥ ምሥጢራችንን በፊትህ አስቀመጥህ። ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፥ ዘመኖቻችንንም እንደ ትንፋሽ ይሆናሉ። የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፥ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፥ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንጠፋለንና። የቁጣህን ጽናት ማን ያውቃል? የቁጣህንስ ግርማ ማን ያውቃል? በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኖቻችንን እንዴት እንደምንቆጥር እንዲህ አስታውቀን። አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ለአገልጋዮችህ ራራ። በማለዳ ጽኑ ፍቅርህን እንጠግባለን፥ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን። መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ አሰኘን። ሥራህ ለአገልጋዮችህ ይታይ፥ ግርማህም ለልጆቻቸው ይሁን። የጌታ አምላካችን ቸርነት በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና። በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። ጌታን፦ “አንተ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ ነህ እለዋለሁ”፥ የምታመንበት አምላኬ ነውና። እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ ከክንፎቹም በታች ትጠለላለህ፥ ታማኝነቱ እንደ ጋሻና እንደ ቅጥር ይከብብሃል። ከሌሊት ሽብር፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚጓዝ መቅሰፍት፥ በቀትር ከሚደመስስ አደጋ አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም ዐሥር ሺህ ይወድቃሉ፥ ወደ አንተ የሚጠጋ የለም። በዐይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ቅጣት ታያለህ። ጌታን፥ “አንተ ተስፋዬ ነህ” ብለህ፥ ልዑልን መጠጊያህ አድርገሃልና። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኩላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፥ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፥ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ ። ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፥ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር። ጌታን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፥ በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት ዐሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፥ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና። አቤቱ፥ ሥራህ እንዴት ትልቅ ነው! ሐሳብህም እንዴት ጥልቅ ነው! የማያስተውል ሰው አያውቅም። አላዋቂ አይረዳውም። ኃጢአተኞች እንደ ሣር ቢበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ቢለመልሙ፥ ለዘለዓለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው። አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘለዓለም ልዑል ነህ፥ አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና። እንደ ጐሽ አጠነከርከኝ ፥ በአዲስ ዘይትም ቀባኸኝ። ዓይኔም ጠላቶቼን ቃኘች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ የተነሡትን ክፉዎች ሰማች። ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በጌታ ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ። ያንጊዜ ገና በሽምግልናም ያፈራሉ ገና ወተታማና አርንጓዴ ሆነው ይኖራሉ። ጌታ ትክክለኛ እንደሆነ ይነግራሉ፥ ዓለቴ ነው፤ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም። ጌታ ነገሠ፥ ግርማን ተጐናጸፈ፥ ጌታ ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፥ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የጸና ነው፥ አንተም ከዘለዓለም ጅምሮ አለህ። አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ድምፃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ ጌታ በከፍታው ድንቅ ነው። ምስክርነትህ እጅግ የታመነ ነው፥ አቤቱ፥ ለረጅም ዘመን፥ ለቤትህ ቅድስና ይገባል። እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ። የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ተነሥ፥ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው። አቤቱ፥ ክፉዎች እስከ መቼ? ክፉዎች እስከ መቼ ይኮራሉ? ይደነፋሉ፥፥ ክፉ አድራጊዎች ይታበያሉ። አቤቱ፥ ሕዝብህን ረገጡ፥ ርስትህንም ጨቆኑ። መበለቲቱንና ስደተኛውን አረዱ፥ ወላጅ አልባውንም ገደሉ። ጌታ አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ። የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፥ ሞኞችስ መቼ ጠቢብ ትሆናላችሁ? ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን? አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይቀጣምን? የሰዎች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ጌታ ያውቃል። ለክፉ ሰው ጉድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከአስከፊ ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ብፁዕ ነው። ጌታ ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና ፍርድ ወደ ጽድቅ እስክትመለስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል። በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚነሣ ማን ነው? ዓመፅንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው? ጌታ ባይረዳኝ ኖሮ ነፍሴ ወዲያው ሲኦል በወረደች ነበር። እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህ ረዳኝ። አቤቱ፥ የልቤ መረበሽ በበዛ መጠን፥ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት። በሕግ ስም ዓመፅን የሚሠራ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን? የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደም ላይም ይፈርዳሉ። ጌታ መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የመጠለያዬ ዓለት ነው። እንደ በደላቸውም፥ እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ ጌታ አምላካችን ያጠፋቸዋል። ኑ፥ በጌታ ደስ ይበለን፥ ለመዳናችን ዓለት እልል እንበል። በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፥ ጌታ ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና። የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው። ባሕር የእርሱ ናት እርሱም ፈጠራት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት። ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፥ በፈጠረን በእርሱ በጌታ ፊት እንበርከክ፥ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። በምድረ በዳ፥ በመሪባና በማሳ እንዳደረጋችሁት፥ ልባችሁን አታጽኑ። የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ምንም እንኳን ሥራዬን ቢያዩም ፈተኑኝ። ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተጸየፍኳት፦ ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ “እነርሱም መንገዴን አላወቁም” አልሁ። “ወደ ዕረፍቴም ጨርሶ አትገቡም” ስል በቁጣዬ ማልሁ። ለጌታ አዲስ መዝሙር ዘምሩ፥ ምድር ሁሉ፥ ለጌታ ዘምሩ። ለጌታ ዘምሩ ስሙንም ባርኩ፥ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ፥ ጌታ ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ ከአማልክትም ሁሉ በላይ የተፈራ ነውና። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖቶች ናቸውና፥ ጌታ ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ውበት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። የአሕዛብ ወገኖች፥ ለጌታ አቅርቡ፥ ክብርና ኃይልን ለጌታ አቅርቡ፥ ለስሙ የሚገባ ክብርን ለጌታ ስጡ፥ ቁርባን ያዙ፥ ወደ አደባባዮችም ግቡ። በቅድስናው ስፍራ ለጌታ ስገዱ፥ ምድር ሁሉ በፊቱ ትናወጥ። በአሕዛብ መካከል፦ “ጌታ ነገሠ” በሉ። እንዳይናወጥም ዓለሙን እርሱ አጸናው፥ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል። ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፥ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ፥ መስክና በእርሷም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ፥ የዱር ዛፎችም ሁሉ በጌታ ፊት ደስ ይበላቸው፥ ይመጣልና፥ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፥ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል። ጌታ ነገሠ፥ ምድር ሐሤትን ታድርግ፥ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው። ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፥ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው። እሳት በፊቱ ይሄዳል፥ ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል። መብረቆቹ ለዓለም አበሩ፥ ምድር አየችና ተናወጠች። ተራሮችም በጌታ ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ። ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ። ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፥ አማልክት በሙሉ፥ ስገዱለት። አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው፥ አቤቱ አንተ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ነህና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃልና። ጌታን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፥ እርሱ የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከክፉዎችም እጅ ያድናቸዋል። ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ። ጻድቃን፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ፥ የማይረሳውን ቅድስናም አወድሱ። የዳዊት መዝሙር። ለጌታ አዲስ መዝሙር ዘምሩ፥ ድንቅ ነገሮችን አድርጎአልና፥ ቀኙ፥ የተቀደሰ ክንዱም ለእርሱ ማዳን አደረገ። ጌታ ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ። ለእስራኤል ቤት ያለውን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት አስታወሰ፥ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ። ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለጌታ እልል በሉ፥ በደስታ ፈንድቁ፥ ዘምሩም። ለጌታ በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ። በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሡ በጌታ ፊት እልል በሉ። ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርሷም የሚኖሩ ይናወጡ። ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፥ ተራሮችም በደስታ ይዘምሩ፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና። ዓለምንም በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል። ጌታ ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፥ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ። ጌታ በጽዮን ታላቅ ነው፥ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ። ቅዱስ ነውና ሁሉም ታላቅና ግሩም ስምህን ያመስግኑ። ፍርድን የምትወድ ኃያል ንጉሥ፥ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ በያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ ፈጽምህ። ጌታ አምላካችንን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መርገጫ ስገዱ። ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው፥ ጌታን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው። በደመና ዓምድም ተናገራቸው፥ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ። አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፥ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ጥፋታቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው። ጌታ አምላካችንን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፥ ጌታ እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና። የምስጋና መዝሙር። ምድር ሁሉ፥ ለጌታ እልል በሉ፥ በደስታም ለጌታ ተገዙ፥ በእልልታም ወደ ፊቱ ግቡ። ጌታ እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ፥ እርሱ ሠራን፥ እኛም የእርሱ ነን፥ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን። ወደ ደጆቹ በውዳሴ፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፥ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፥ ጌታ ቸር፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም፥ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ። ነቀፋ በሌለበት መንገድን እጓዛለሁ፥ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ። በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፥ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ። ጠማማ ልብም ከእኔ ይርቃል፥ ክፉን አላውቀውም። ባልንጀራውን በቀስታ የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፥ በዓይኑ ትዕቢተኛ፥ በልቡ ኩራተኛ የሆነውን አልታገሥም። ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ ዐይኖቼ በምድር ምእመናን ላይ ናቸው፥ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል። አታላይ በቤቴ መካከል አይኖርም፥ ሐሰትን የሚናገር በዓይኔ ፊት አይቆምም። ዓመፃ የሚያደርጉትን ሁሉ ከጌታ ከተማ አጠፋቸው ዘንድ፥ የምድርን ክፉዎች ሁሉ በማለዳ አጠፋቸዋለሁ። ባዘነና ልመናውን በጌታ ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የችግረኛ ጸሎት። አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ። በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ። ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና፥ አጥንቶቼም እንደ ማንደጃ ተቃጥለዋልና። ልቤም እንደ ተመታ ሣር ደረቀ፤ እህል መብላትም ተረሳኝ። ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ። እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፥ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጉጉት ሆንሁ። ነቅቼ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥ የሚያሳድዱኝም በእኔ ስም ይራገማሉ። አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና፥ ከቁጣህና ከመዓትህም የተነሣ፥ አንሥተኸኛልና፥ ጥለኸኝማልና። ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፥ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘለዓለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው። አንተ ተነሥ ለጽዮንም ራራ፥ የጸጋዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፥ አገልጋዮችህ ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና። አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፥ ጌታ ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና። ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥ ልመናቸውንም አልናቀም። ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለጌታ እልል ይላል፥ ጌታ ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፥ የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ይፈታ ዘንድ፥ የጌታን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፥ አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለጌታ ይገዙ ዘንድ። በመንገዴ ጉልበቴ ዛለ፦ ዘመኔም አጠረ። ለእኔም ንገረኝ፥ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ፥ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፥ ሁላቸውም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጣሉም፥ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። የአገልጋዮችህ ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም በፊትህ ትጸናለች። የዳዊት መዝሙር። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ ውለታውንም ከቶ አትርሺ፥ ጥፋትሽንም ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በፍቅርና በርኅራኄ የሚከልልሽ፥ ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጎልማሳነትሽን እንደ ንስር ያድሳል። ጌታ ጽድቅን ይፈጽማል፥ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል። ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም ድንቅ ሥራዎቹን። ጌታ ርኅሩኅና ቸር ነው፥ ከቁጣ የራቀ ፍቅሩም የበዛ። ሁልጊዜም አይከስም፥ ለዘለዓለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ ጌታም ለሚፈሩት ይራራል፥ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን ያስታውሳል። ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፥ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፥ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና። የጌታ ጽኑ ፍቅር ግን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚፈሩት ላይ፥ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፥ ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፥ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው። ጌታ ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፥ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። ቃሉን የምትፈጽሙ መላእክቱ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ ጌታን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፥ ክብርንና ግርማን ለበስህ። ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፥ ሰማይንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፥ እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥ ነፋሳትን መልእክተኞቹ የሚያደርግ፥ የእሳት ነበልባልም አገልጋዮቹ። ለዘለዓለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት። በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። ከቁጣህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነብራሉ፥ ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፥ እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ተመልሰው ምድርን እንዳይከድኑ። ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች ይልካል፥ በተራሮችም መካከል ያልፋሉ፥ የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማቸውን ያረካሉ። የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በቅጠሎች መካከል ያዜማሉ ይጮኻሉ። ተራሮችን ከላይ የምታጠጣቸው፥ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ሣርን ለእንስሳ፥ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል። የጌታ ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። በዚያም ወፎች ጎጆአቸውን ይሠራሉ፥ ሽመላዎችም ከበላያቸው ቤታቸውን ያበጃሉ። ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው። ወቅቶችን ለማመልከት ጨረቃን አደረግህ፥ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። ጨለማን ታስቀምጣለህ፥ ሌሊትም ይሆናል፥ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ፥ በየዋሻቸውም ይተኛሉ። ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥ በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል ። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ። የጌታ ክብር ለዘለዓለም ይሁን፥ ጌታ በሥራው ደስ ይለዋል። ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፥ ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም። በሕይወቴ ሳለሁ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በጌታ ደስ ይለኛል። ኀጥኣን ከምድር ይጥፉ፥ ዓመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ድንቅ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ክበሩ፥ ጌታን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። ጌታንና ኃይሉን ፈልጉ፥ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። አገልጋዮቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራውን ድንቅ ሥር አስቡ፥ ተአምራቱን የተናገረውንም ፍርድ። እርሱ ጌታ አምላካችን ነው፥ ፍርዱ በምድር ሁሉ ላይ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፥ ለይስሐቅም የማለውን፥ ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን፥ ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፥ እንዲህም አለ፦ ለአንተ የከነዓንን ምድር የተመደበላችሁን ርስታችሁን እሰጣለሁ፥ ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር አነስተኛና፥ ለሀገሩም እንግዶች በነበሩበት ጊዜ ነው። ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። የቀባኋቸውን አትንኩ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ። በፊታቸው ሰውን ላከ፥ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ። እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የጌታ ቃል ፈተነው። ንጉሥ ላከና ፈታው፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው። የቤቱ ጌታ፥ የንብረቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥ መኰንኖቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ። ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በአገልጋዮቹም ላይ ተንኰል ይፈጽሙ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። አገልጋዩን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ። ተኣምራቱን በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረጉ። ጨለማን ላከ፥ ጨለመባቸውም፥ በቃሉም ዐመፁ ። ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። ምድራቸውና የንጉሦቻቸው ቤቶች በእንቁራሪት ተሞሉ። ተናገረ፥ የዝንብ መንጋና ተናካሽ ትንኞች በዳርቻቸው መጡ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ በምድራቸውም የእሳት ነበልባል ወረደ ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥ የአገራቸውንም ተክሎች ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ። የአገራቸውንም በኩር ሁሉ፥ የጉልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ። ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ የተደናቀፈ አልነበረም። ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት። ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት እንዲያበራላቸው። ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈለቀ፥ ወንዞች በበረሃ ፈሰሱ፥ ለአገልጋዩ ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስታውሶአልና። ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ። የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ ከሕዝቦችም ድካም ወረሱ፥ ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ። የጌታን ታላላቅ ሥራዎች ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል? ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው። አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበኝ፥ በመድኃኒትህም ጐብኘኝ፥ የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እኮራ ዘንድ። ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአት ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም። አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የፍቅርህንም ብዛት አላሰቡም፥ በቀይ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ። ስለ ስሙ፥ ኃይሉንም ለማስታወቅ አዳናቸው። ቀይ ባሕርን ገሠጸው፥ እርሱም ደረቀ፥ እንደ ምድረ በዳ በጥልቁ መራቸው። ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው። ያሳደዱአቸውንም ውኃ ዋጣቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም። በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ። ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ ምክሩን እንኳን አልጠበቁም። በምድረ በዳም በምኞትን ተቃጠሉ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። የለመኑትንም ሰጣቸው፥ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ። ሙሴንም፥ ጌታ የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው። ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፥ በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባም ክፉዎችን አቃጠላቸው። በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ። ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካም ምድር፥ ግሩም ነገርንም በቀይ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ። እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው እንደ ነበረ ተናገረ። የምትወደደውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥ በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፥ የጌታን ቃል አልሰሙም። በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው። ከባዓል ፔዖርም ጋር ተጣበቁ ፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ፥ በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ። ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፥ ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፥ በእነርሱም የተነሣ ሙሴ ተበሳጨ፥ በከንፈሮቹም ያለማስተዋል ተናገረ። ጌታ እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፥ ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው። ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠዉአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች። በሥራቸው ረከሱ፥ በድርጊታቸውም አመነዘሩ። የጌታም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ። በአሕዛብም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው። ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ። ብዙ ጊዜ አዳናቸው፥ እነርሱ ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በስሕተታቸውም ተዋረዱ። እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፥ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ጽኑ ፍቅሩም ብዛት ተጸጸተ። በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው። ጌታ አምላካችን ሆይ፥ አድነን፥ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ፥ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ፥ ጌታ የታደጋቸው፥ ከጠላትም እጅ ያዳናቸው ይናገሩ። ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው። በበረሃ፥ በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፥ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። ተራቡ፥ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፥ ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ በቀና መንገድን መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የተጠማችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራበችን ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና። በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ ልባቸው በድካም ተዋረደ፥ ተሰናከሉ የሚረዳቸውም አጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ ሰንሰለታቸውንም በጣጠሰ። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የናሱን ደጆች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈራርጦአልና። በዓመፅ መንገዳቸው አላዋቂ ሆኑ፥ በጥፋታቸው ተጎሳቆሉ። ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜም ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከአዘቅትም አዳናቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ። በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላላቅ ውኆች ሥራቸውን የሚሠሩ፥ እነርሱ የጌታን ሥራ፥ በታላቅ አዘቅትም ያሉትን ድንቅ ሥራዎች አዩ። ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገዶችንም አስነሣ። ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፥ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች። ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱን አስቆመ፥ ሞገዱም ጸጥ አለ። ዝም ብለዋልና ደስ አላቸው፥ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው። ስለ ጽኑ ፍቅሩ፥ ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ጌታን ያመስግኑ። በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት። ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ መሬት አደረገው፥ ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት። ምድረ በዳን ወደ ውኃ ማጠራቀምያ፥ ደረቁንም ምድር ወደ ውኃ ምንጭነት ቀየረ። በዚያም ረሀብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። እርሻዎችንም ዘሩ፥ ወይኖችንም ተከሉ፥ ፍሬንም ሰበሰቡ። ባረካቸውም እጅግም በዙ፥ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም። እነርሱ በጭቈና፥ በስቃይና በኃዘን ተዋርደው እያነሱ ሄዱ፥ በመኰንኖችም ላይ ውርደትን ዘረገፈ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አንከራተታቸው። ችግረኛንም ከመከራው አወጣው፥ ቤተሰቦችን እንደ በጎች መንጋ አበዛ። ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፥ ክፋት በሙሉ አፉን ይዘጋል። ጠቢብ ማነው? ይህንን ይፈጽም፥ እርሱ የጌታንም ጽኑ ፍቅር ይገነዘባል። የዳዊት የምስጋና መዝሙር። አምላኬ ሆይ ልቤ ጽኑ ነው፥ እቀኛለሁ፥ በክብሬም እዘምራለሁ። በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም እንዲሁ፥ እኔም ማለዳን ልቀስቅሰው። አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፥ በሕዝቦችም መካከል እዘምርልሃለሁ፥ ጽኑ ፍቅርህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና። አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን። ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፥ በቀኝህ አድን አድምጠኝም። እግዚአብሔር በመቅደሱ ተናገረ፦ “ደስ እያለኝ ሴኬምንም እከፋፍላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ። ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው፥ ኤፍሬም የራሴ መከላከያ ቁር ነው። ይሁዳ በትረ መንግሥቴ፥ ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፥ በፍልስጥኤም ላይ ድሌን ዐውጃለሁ። ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? እስከ ኤዶምያስ ድረስስ ማን ይመራኛል? አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር መውጣት አቆምህ። በጥቃታችን ድረስልን፥ የሰውም ማዳን ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፥ እርሱም የሚያስጨንቁንን ይረጋግጣቸዋል።” ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አምላክ ሆይ፥ ምስጋናዬን ዝም አትበል፥ የክፉና የተንኰለኛ አፎች በላዬ ተላቅቀውብኛልና፥ በሐሰት አንደበትም በላዬ ተናገሩ፥ በጥላቻ ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም አጠቁኝ። በፍቅሬ ፋንታ ከሰሱኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ። በመልካም ፋንታ ክፉን፥ በፍቅር ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ። በላዩ ክፉ ሰውን ሹም፥ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም። በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፥ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት። ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፥ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ። ልጆቹም ያለ አባት ይቅሩ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን። ልጆቹም እጅጉን ይቅበዝበዙ፥ ይለምኑም፥ ከፈራረሱ ቤቶቻቸውም ሳይቀር ይባረሩ። ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት። በቸርነት የሚያግዘውንም አያግኝ፥ ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር። ተተኪ አይኑረው፥ በቀጣይ ትውልድ ስማቸው ይደምሰስ። የአባቶቹ ጥፋት በጌታ ፊት ትታወስ፥ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ። በጌታ ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፥ መታሰቢያቸውም ከምድረ ገጽ ይጥፋ። በቸርነት ለመመላለስ አላሰበምና፥ ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ለመግደል ያሳድድ ነበር። መራገምን ወደደ፥ ወደ እርሱም መጣች፥ በረከትንም አልመረጠም፥ ከእርሱም ራቀች። መራገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች። እንደሚለብሰው ልብስ፥ ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ትሁነው። ይህ ቅጣት በሚከሱኝና በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ላይ ከጌታ ዘንድ ይሁን። አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ስትል ታደገኝ፥ ጽኑ ፍቅርህ መልካም ናትና አድነኝ። እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ በውስጤም ልቤ ቆስሎአል። እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ። ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፥ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ። እኔም በእነርሱ ዘንድ መሳለቂያ ሆንሁ፥ ሲያዩኝ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ጽኑ ፍቅርህም አድነኝ። አቤቱ፥ እጅህ ይህች መሆኗን፥ አንተም ይህንን እንዳደረግህ ይወቁ። እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ትባርካለህ፥ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ አገልጋይህ ግን ደስ ይበለው። የሚከሱኝ እፍረትን ይልበሱ፥ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት። ጌታን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፥ ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ ከድሀ በኩል ቆሞአልና። የዳዊት መዝሙር። ጌታ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” ጌታ የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፥ በጠላቶችህም መካከል ግዛ። ግርማዊ ክብር ከልደትህ ጊዜ አንሥቶ፥ የተቀደሰ ሞገስም ከማኅጸን፥ የወጣትነትም ጠል የአንተ ነው። “እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ ብሎ”፥ ጌታ ማለ፥ አይጸጸትምም። ጌታ በቀኝህ፥ ነገሥታትን በቁጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ይከምራል፥ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል። በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፥ ከዚህም የተነሣ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ! በቅኖች ሸንጎ በጉባኤም ጌታን በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ። የጌታ ሥራዎች ታላላቅ ናቸው፥ ደስ በሚሰኙባቸው ሁሉ ይፈለጋሉ። ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፥ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል። ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፥ ጌታ መሓሪና ርኅሩኅ ነው። ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፥ ኪዳኑንም ለዘለዓለም ያስባል። የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ። የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ናቸው፥ ትእዛዛቱም በሙሉ የታመኑ ናቸው፥ ለሁልጊዜና ዘለዓለምም የጸኑ ናቸው፥ በእውነትና በጽድቅም የተሠሩ ናቸው። ለሕዝቡ መዳንን ላከ፥ ኪዳኑንም ለዘለዓለም ደነገገ፥ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው። የጥበብ መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ የሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋልን ያገኛሉ፥ ውዳሴውም ለዘለዓለም ይኖራል። ሃሌ ሉያ። ጌታን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ብፁዕ ነው። ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፥ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች። ክብርና ሀብት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል። ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፥ መሓሪ፥ ርኅሩኅና ጻድቅ ነው። ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ ነገሩንም በቀና መንገድ ይፈጽማል። ለዘለዓለም አይናወጥም፥ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል። ክፉ ዜናን አይፈራም፥ ልቡ የጸና፥ በጌታም የታመነ ነው። በጠላቶቹ ላይ እስኪኮራ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፥ አይፈራምም። በተነ፥ ለችግረኞችም ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘለዓለም ዓለም ይኖራል፥ ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል። ክፉ ሰውም አይቶት ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፥ የክፉዎች ምኞት ትጠፋለች። ሃሌ ሉያ። የጌታ አገልጋዮች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የጌታንም ስም አመስግኑ። ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ የጌታ ስም ቡሩክ ይሁን። ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የጌታ ስም ይመስገን። ጌታ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ልዑል ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው። እንደ ጌታ እንደ እግዚአብሔር የሚሆን ማን ነው? በላይ የሚኖር፥ በሰማይና በምድር ያሉትን ለማየት ዝቅ የሚል፥ ከመኰንኖች ጋር ከሕዝቡም መኰንኖች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፥ መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! እስራኤል ከግብጽ፥ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ ሕዝብ በወጣ ጊዜ፥ ይሁዳ መቅደሱ፥ እስራኤልም ግዛቱ ሆነ። ባሕር አየች፥ ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ። ተራሮች እንደ አውራ በጎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ። አንቺ ባሕር የሸሸሽው፥ አንቺስ ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽው፥ ምን ሆናችሁ ነው? እናንተም ተራሮች፥ እንደ አውራ በጎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? በያዕቆብ አምላክ ፊት፥ በጌታ ፊት ምድር ተናወጠች፥ ዐለቱን ወደ ውኃ መቆሚያ፥ ድንጋዩንም ወደ ውኃ ምንጭ ይለውጣል። ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥ ነገር ግን ለስምህ ስለ ጽኑ ፍቅርህና ስለ እውነትህም ክብርን ስጥ። አሕዛብ፦ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ለምን ይበሉ? አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፥ የፈቀደውን ሁሉ አደረገ። የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው አይናገሩምም፥ ዐይን አላቸው አያዩምም፥ ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፥ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፥ እጅ አላቸው አይዳስሱምም፥ እግር አላቸው አይሄዱምም፥ በጉሮሮአቸውም ድምፅ አያሰሙም። የሚሠሩአቸው፥ የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በጌታ ታመኑ፥ ረድኤታቸውና መከታቸው እርሱ ነው። የአሮን ቤት ሆይ፥ በጌታ ታመኑ፥ ረድኤታቸውና መከታቸው እርሱ ነው። ጌታን የምትፈሩ፥ በጌታ ታመኑ፥ ረድኤታቸውና መከታቸው እርሱ ነው። ጌታ አሰበን፥ ይባርከንማል፥ የእስራኤልን ቤት ይባርካል፥ የአሮንንም ቤት ይባርካል። ጌታን የሚፈሩትን፥ ትንንሾችንና ትልልቆችን ይባርካል። ጌታ በላያችሁ፥ በላያችሁና በልጆቻችሁ ላይ ይጨምር። እናንተ ሰማይንና ምድርን በሠራ ጌታ የተባረካችሁ ሁኑ። ሰማያት የጌታ ሰማያት ናቸው፥ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት። አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም፥ ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፥ እኛ ሕያዋን ግን ከአሁን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ጌታን እንባርካለን። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! ጌታ የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሏልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። የሞት ገመዶች ወጠሩኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፥ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ። የጌታን ስም ጠራሁ፦ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። ጌታ መሓሪና ጻድቅ ነው፥ አምላካችንም ርኅሩኅ ነው። ጌታ የዋሆችን ይጠብቃል፥ ተዋረድሁ፥ እርሱም አዳነኝ። ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ ጌታ መልካም አድርጎልሻልና፥ በእርግጥም ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድነሃል። በሕያዋን አገር በጌታ ፊት እሄዳለሁ። አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ፥ እኔም እጅግ ተቸገርሁ። እኔም ከድንጋጤዬ የተነሣ፦ “ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው አልሁ”። ስላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለጌታ ምንን እመልሳለሁ? የመድኃኒትን ጽዋ ከፍ አደርጋለሁ ፥ የጌታንም ስም እጠራለሁ። በሕዝቡ ሁሉ ፊት፥ እነሆ ስእለቴን ለጌታ እፈጽማለሁ። የቅዱሳኑ ሞት በጌታ ፊት የከበረ ነው። አቤቱ፥ እኔ አገልጋይህ ነኝ፥ አገልጋይህ፥ የሴት አገልጋይህም ልጅ ነኝ፤ ሰንሰለቴን ሰበርህ። ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የጌታንም ስም እጠራለሁ። በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለጌታ እፈጽማለሁ፥ በጌታ ቤት አደባባይ፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በመካከልሽም እንዲሁ። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! አሕዛብ ሁላችሁ፥ ጌታን አመስግኑት፥ ሕዝቦችም በሙሉ አመስግኑት፥ ፍቅሩ በእኛ ላይ ጸንቶአልና፥ የጌታም እውነት ለዘለዓለም ትኖራለች። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ ጌታን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ። በተጨነቅሁ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ መለሰልኝ፥ አሰፋልኝም። ጌታ ከጎኔ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? ጌታ ሊረዳኝ ከጎኔ ነው፥ እኔም ጠላቶቼን በኩራት አያለሁ። በሰው ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል። በኃያላን ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል። አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው፥ መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው። ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንደሚነድድ ነደዱ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው። ገፈተሩኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፥ ጌታ ግን አገዘኝ። ኃይሌም ዝማሬዬም ጌታ ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ። የእልልታና የመዳን ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፥ የጌታ ቀኝ እጅ ኃይሉን አከናወነ። የጌታ ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፥ የጌታ ቀኝ እጅ ኃይሉን አከናወነ። አልሞትም፥ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የጌታንም ሥራ እናገራለሁ። መገሠጽስ ጌታ ገሠጸኝ፥ ለሞት ግን አልሰጠኝም። የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፥ ወደ እነርሱ ገብቼ ጌታን አመሰግናለሁ። ይህች የጌታ ደጅ ናት፥ ወደ እርሷ ጻድቃን ይገባሉ። ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥ ይህች ከጌታ ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት። ጌታ የሠራት ቀን ይህች ናት፥ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርሷም ደስ ይበለን። አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፥ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና። በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፥ ከጌታ ቤት መረቅናችሁ። ጌታ አምላክ ነው፥ ለእኛም አበራልን፥ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ፥ ቅርንጫፎች ይዘን፥ ለበዓሉ ዑደት እናድርግ አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንሃለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ። ጌታን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ። ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች። ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ። ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው። ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ። ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ። የሐሰትን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ የሕግህንም ጸጋ ስጠኝ፥ የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም። አቤቱ፥ ሕግህን ተጠጋሁ፥ አታሳፍረኝ። ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዞችህ መንገድ ሮጥሁ። አቤቱ፥ የደንቦችህን መንገድ አስተምረኝ፥ ለትሩፋትም እጠብቀዋለሁ። እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እንድጠብቅ፥ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ። እርሷን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ። ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን። ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፥ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ። እንዲፈራህ ባርያህን በቃልህ አጽና። ፍርድህ መልካም ናትና የምፈራውን ስድብ ከእኔ አርቅ። እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ። በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ለዘለዓለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ። በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፥ እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፥ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ። ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ። በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ። እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች። ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ። ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ። የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው። የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም። እጅግ ተቸገርሁ፥ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፥ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም። የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘለዓለም ወረስሁ። ለዘለዓለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ። ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ። አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር። እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ። ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፥ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ባርያህን በመልካም ጠብቀው፥ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ። ዐይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ። ለባርያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። እኔ ባርያህ ነኝ፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ። ለጌታ የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት። ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፥ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው። የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፥ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና። ስምህን ለሚወድዱ እንደምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም። አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፥ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ። ከሰው ግፍ አድነኝ፥ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ። በባርያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዐይኖቼ ፈሰሰ። አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው። ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባርያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም። ጽድቅህ የዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው። መከራና ችግር አገኙኝ፥ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው። ምስክርህ ለዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ። በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፥ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ። ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ። ማለዳ ጮኽሁ፥ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ። ቃልህን አስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ። አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ። አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው። ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ። ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም። ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፥ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መድኃኒት ከኀጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፥ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ። ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፥ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህም ፍርድ ሁሉ ለዘለዓለም ነው። ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፥ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ። ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፥ ሕግህን ግን ወደድሁ። ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም። አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ። ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው። መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፥ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፥ እንደ ቃልህ አድነኝ። ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ። ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን። አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፥ ሕግህም ተድላዬ ነው። ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፥ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው። የዕርገት መዝሙር። በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኽሁ፥ ሰማኝም። ከዓመፀኛ ከንፈር ከሸንጋይም አንደበት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። ስለ ሽንገላ አንደበት ምንን ይሰጡሃል? ምንስ ይጨምሩልሃል? እንደ በረሃ እንጨት ፍም የኃያላን ፍላጾች የተሳሉ ናቸው። መኖሪያዬ የራቀ እኔ ወዮልኝ፥ በቄዳር ድንኳኖች አደርሁ። ሰላምን ከሚጠሉ ጋር ነፍሴ ብዙ ጊዜ ኖረች። እኔ ስለ ሰላም ስናገር፥ እነሱ ግን ስለ ጦርነት ያወራሉ። የዕርገት መዝሙር። ዐይኖቼን ወደ ተራሮቹ አነሣሁ፥ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከጌታ ዘንድ ነው። እግርህ እንዲናወጥ አይፈቅድም፥ የሚጠብቅህም አይተኛም። እነሆ፥ የእስራኤል ጠባቂ አይተኛም አያንቀላፋምም። ጌታ ጠባቂህ ነው፥ ጌታ በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። ፀሐይ በቀን አይመታህም፥ ጨረቃም በሌሊት እንዲሁ። ጌታ ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ጌታ መውጣትህንና መግባትህን ይጠብቃል። የዳዊት የዕርገት መዝሙር። ወደ ጌታ ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ። ኢየሩሳሌምስ እርስ በርስዋ እንደ ተገጠገጠች ከተማ ተሠርታለች። የጌታን ስም ያመሰግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የጌታ ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ። ዙፋኖች በዚያ ለፍርድ ተቀምጠዋልና፥ የዳዊት ቤት ዙፋኖች። ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ፥ አንተንም ለሚወድዱ መረጋጋት ይሁን። በቅጥሮችሽ ውስጥ ሰላም፥ በግምቦችሽም ውስጥ መረጋጋት ይሁን። ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም፦ “በውስጥሽ ሰላም ይሁን” ልበል። ስለ ጌታ አምላካችን ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ። የዕርገት መዝሙር። በሰማይ የምትኖር ሆይ፥ ዐይኖቼን ወደ አንተ አነሣሁ። እነሆ፥ የአገልጋዮች ዐይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደ ሆኑ፥ የአገልጋዪቱም ዐይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደሆነ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ ጌታ አምላካችን ነው። ማረን፥ አቤቱ፥ ማረን፥ ብዙ ንቀት አጠግቦናልና፥ የትምክሕተኞችን ሹፈትና የትዕቢተኞችን ንቀት ነፍሳችን እጅግ ጠገበች። የዳዊት የዕርገት መዝሙር። ጌታ ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል፦ ጌታ ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥ ቁጣቸው በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፥ በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ወራጅ ውኃ ባለፈ ነበር፥ በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር። ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን ጌታ ይመስገን። ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች፥ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን። ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በጌታ ስም ነው። የዕርገት መዝሙር። በጌታ የታመኑ እንደማይታወክ ለዘለዓለም እንደሚኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው። ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ሆኑ፥ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም ጌታ በሕዝቡ ዙሪያ ነው። ጻድቃን እጃቸውን ወደ ክፋት እንዳይዘረጉ የክፉዎች በትር በጻድቃን ዕጣ ላይ አይኖርም። አቤቱ፥ ለመልካሞች፥ ልባቸውም ለቀና መልካምን አድርግ። ወደ ጠማማነት የሚመለሱትን ግን ዓመፅን ከሚሠሩት ጋር ጌታ ይወስዳቸዋል። ሰላም በእስራኤል ላይ ይሁን። የዕርገት መዝሙር። ጌታ የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ሕልም የምናይ መስሎን ነበር። በዚያን ጊዜ አፋችን በሳቅ፥ አንደበታችንም በእልልታ ተሞላ፥ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ፦ ታላቅ ነገርን አደረገላቸው ተባለ። ጌታ ለኛ ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን። አቤቱ፥ በደቡብ እንዳሉ ፈሳሾች ምርኮአችንን መልስ። በዕንባ የሚዘሩ በእልልታ ይለቅማሉ። መሄድስ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፥ መመለስስ፥ ነዶአቸውን ተሸክመው በእልልታ ይመጣሉ። የዕርገት መዝሙር። ጌታ ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፥ ጌታ ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ማለዳ መነሣታችሁ፥ አምሽታችሁም መተኛታችሁ ከንቱ ነው። እርሱ ለሚወዱት እንቅልፍን ይሰጣልና። እነሆ፥ ልጆች የጌታ ስጦታ ናቸው፥ የማሕጸንም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው። ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ሰው የታደለ ነው፥ ጠላቶቻቸውን በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ እርሱ አያፍርም። የመዓርግ መዝሙር። ጌታን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፥ ምስጉን ነህ፤ መልካምም ይሆንልሃል። ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፥ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው። እነሆ፥ ጌታን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል። ጌታ ከጽዮን ይባርክህ፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ የኢየሩሳሌምን መልካምነትዋን ታያለህ። የልጆችህንም ልጆች ታያለህ። በእስራኤል ላይ ሰላም ይሁን። የዕርገት መዝሙር። እስራኤል፦ “ከትንሽነቴ ጀምሮ አብዝተው አጠቁኝ” ይበል፥ ከትንሽነቴ ጀምሮ አብዝተው አጠቁኝ፥ ነገር ግን አላሸነፉኝም። አራሾች በጀርባዬ ላይ አረሱ፥ ትልማቸውን አስረዘሙ። ጌታ ጻድቅ ነው፥ የክፉዎችን ገመድ ቈረጠ። ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፥ ሳይነቀል እንደሚደርቅ፥ ለሚያጭደው እጁን፥ ነዶዎቹን ለሚሰበስብ እቅፉን እንደማይሞላ ይሁኑ። በመንገድም የሚያልፉ፦ የጌታ በረከት በእናንተ ላይ ይሁን፥ በጌታ ስም እንመርቃችኋለን አይሉም። የዕርገት መዝሙር። አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ። አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፥ ጆሮህ የልመናዬን ቃል ያድምጥ። አቤቱ፥ ኃጢአትን ብትይዝ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? ይቅርታ በአንተ ዘንድ ነውና። አቤቱ ተስፋ አደረግሁ፥ ነፍሴ ጠበቀች፥ በቃሉ ታመንኩ። ማለዳን ከሚጠብቁ የሌሊት ጠባቂዎች ይልቅ፥ ነፍሴ ጌታን ትጠብቃለች፥ ማለዳን ከሚጠብቁ ጠባቂዎች ይልቅ። ከጌታ ጋር ጽኑ ፍቅር፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን አለና እስራኤል በጌታ ይታመን። እርሱም እስራኤልን ከበደሉ ሁሉ ያድነዋል። የዳዊት የዕርገት መዝሙር። አቤቱ፥ ልቤ አይታበይም፥ ዐይኖቼም ከፍ ከፍ አይሉም፥ ለትልልቅ ነገሮች፥ ከዐቅሜም በላይ ለሆኑት አልጨነቅም። ነፍሴን አሳረፍኋት፥ የእናቱንም ጡት እንዳስተዉት ሕጻን ዝም አሰኘኋት፥ ነፍሴ የእናቱን ጡት እንዳስተዉት በእኔ ውስጥ ናት። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እስራኤል በጌታ ይታመን። የዕርገት መዝሙር። አቤቱ፥ ዳዊትን፥ መከራውንም ሁሉ አስታውስ፥ ለጌታ እንደማለ፥ ለያዕቆብም ኀያል እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዐይኖቼም መኝታ፥ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ አልሰጥም፥ ለጌታ ስፍራ፥ ለያዕቆብ ኀያል ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በጁኦሪም ምድር አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንግባ፥ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንስገድ። አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት። ካህናትህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ጻድቃንህም ደስ ይበላቸው። ስለ ዳዊት ስለ ባርያህ ብለኽ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ። ጌታ ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ፦ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ። ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተማራቸውን ኪዳኔን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ። ጌታ ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ “ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፥ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። ስንቆቿን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ። ካህናትዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ጻድቃኗም እጅግ ደስ ይላቸዋል። በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ ፥ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ። ጠላቶቹንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፥ በእርሱ ግን ዘውዱ ያንጸባርቃል።” የዳዊት የዕርገት መዝሙር። ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ እንዴት መልካም፥ እንዴት ውብ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም እንደሚፈስስ፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፥ በዚያ ጌታ በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘለዓለም አዝዞአልና። የዕርገት መዝሙር። እነሆ፥ ጌታን ባርኩ፥ በአምላካችን ቤት አደባባዮች የምትቆሙ እናንተ የጌታ ባርያዎች ሁላችሁ። በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ ጌታንም ባርኩ። ሰማይንና ምድርን የሠራ ጌታ ከጽዮን ይባርክህ። ሃሌ ሉያ! የጌታን ስም አመስግኑ፥ እናንተ የጌታ ባርያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ በጌታ ቤት ውስጥ፥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ። ጌታ ቸር ነውና ጌታን አመስግኑ፥ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፥ ጌታ ያዕቆብን ለራሱ፥ እስራኤልንም ግዛቱ አድርጎ መርጦታልና፥ ጌታ ታላቅ እንደሆነ፥ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ አውቄአለሁና። በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ ጌታ የወደደውን ሁሉ አደረገ። ከምድር ዳርቻ ደመናትን ያወጣል፥ በዝናብ ጊዜ መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል። የግብጽን በኩር ልጆች ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ። ግብጽ ሆይ፥ በመካከልሽ በፈርዖንና በባርያዎቹ ሁሉ ላይ ተኣምራትንና ድንቅን ሰደደ። ብዙ አሕዛብን መታ፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ። የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥ የከነዓንን መንግሥታት ሁሉ ገደለ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ። አቤቱ፥ ስምህ ለዘለዓለም ነው፥ ዝክርህም ለልጅ ልጅ ነው፥ ጌታ ለሕዝቡ ይፈርዳልና፥ ባርያዎቹንም ይረዳልና። የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው፥ አይናገሩምም፥ ዐይን አላቸው፥ አያዩምም፥ ጆሮ አላቸው፥ አይሰሙምም፥ እስትንፋስም በአፋቸው የለም። የሚሠሩአቸው ሁሉ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ጌታን ባርኩት፥ የአሮን ቤት ሆይ፥ ጌታን ባርኩት፥ የሌዊ ቤት ሆይ፥ ጌታን ባርኩት፥ ጌታን የምትፈሩት ሆይ፥ ጌታን ባርኩት። በኢየሩሳሌም የሚያድር ጌታ ከጽዮን ይባረክ፥ ሃሌ ሉያ። ጌታን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። የአማልክትን አምላክ አመስግኑ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። የጌቶችን ጌታ አመስግኑ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ሰማያትን በጥበቡ የሠራውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ምድርን በውኃ ላይ ያጸናውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን የሠራውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ፀሐይን በቀን ላይ እንድትሠለጥን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ጨረቃንና ከዋክብትን በሌሊት እንዲሠለጥኑ ያደረገ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ከበኩራቸው ጋር ግብጽን የመታውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ እስራኤልንም ከመካከላቸው ያወጣውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ የኤርትራን ባሕር በየክፍሉ የከፈለውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ታላላቅ ነገሥታትን የመታውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት የገደለውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ የባሳንን ንጉሥ ዐግን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠውን፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ለባርያው ለእስራኤል ርስት፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። እኛን በመዋረዳችን አስቦናልና፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ከጠላቶቻችንም እጅ አድኖናልና፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና፥ ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። የሰማይን አምላክ አመስግኑ፥ ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና። በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፥ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። በአኻያ ዛፎች ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የጌታን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን? ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ ። ባላስታውስሽ፥ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፥ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ። አቤቱ፥ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ፦ እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን። አንቺ ፈራሽ የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው። ሕፃኖችሽን ይዞ በዓለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ። ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፥ ስለ ጽኑ ፍቅርሀና ስለ ታማኝነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህንና ቃልህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና። በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፥ ነፍሴን በኃይልህ አጸናሃት። አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና። በጌታም መንገድ ይዘምራሉ፥ የጌታ ክብር ታላቅ ነውና። ጌታ ከፍ ያለ ነውና፥ ዝቅተኞችን ይመለከታልና፥ ትዕቢተኞችን ግን ከሩቅ ያውቃል። በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፥ በጠላቶቼ ቁጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች። ጌታ ብድራትን ይመልስልኛል፥ አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህ ለዘለዓለም ነው፥ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፥ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ጉዞዬንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። ከኋላና ከፊት ጠበቅኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ እጅጉን ያስደንቃል፥ ከከፍታውም ብዛት ልደርስበት አልችልም። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ ሐሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፥ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። አቤቱ፥ አንተ ክፉዉን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ “ከእኔ ፈቀቅ በሉ”። በክፋት ይናገሩብሃልና፥ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል። አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? በአንተ ላይ የሚነሡትንም አልናቅሁምን? ጨርሶ ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ። አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፥ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፥ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፥ የዘለዓለምንም መንገድ ምራኝ። ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ፥ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ከሚከማቹ። ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፥ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ አለ። አቤቱ፥ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ። ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፥ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ። ጌታንም፦ አንተ አምላኬ ነህ፥ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት። አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጉልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ። አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለክፉዎች አትስጠኝ፥ ተንኮላቸው እንዲሳካ አትፍቀድ። የሚከብቡኝ ራሳቸውን አነሡ ፥ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው። የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፥ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ አዘቅት ይጣሉ። ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፥ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል። ጌታ ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንደሚያደርግ አወቅሁ። ጻድቃንም በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፥ ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ። የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ በፍጥነት ድረስልኝ፥ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ድምፅ ስማ። ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን፥ እጆቼን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ይሁን። አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ። ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፅን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለክፋት ምክንያት እንዳልሰጥ፥ ከድግሳቸውም አልቅመስ። ጻድቅ በጽኑ ፍቅር ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የክፉ ሰው ዘይት ግን ራሴን አይቀባ፥ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና። አለቆቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፥ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ። በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ። አቤቱ ጌታ፥ ዐይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፥ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አትተዋት። ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ። እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ክፉዎች በወጥመዳቸው ይውደቁ። ጸሎት፥ በዋሻ በነበረ ጊዜ፥ የዳዊት ትምህርት። በሙሉ ድምጼ ወደ ጌታ ጮኽሁ፥ በሙሉ ድምጼ ወደ ጌታ ለመንሁ። ሮሮዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፥ መከራዬንም በፊቱ እናገራለሁ። መንፈሴ በዛለ ጊዜ መንገዴን አወቅሁ፥ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ። ወደ ቀኝ ተመለከትሁ አየሁም፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፥ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ነፍሴም የሚያስብ የለም። አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፦ አንተ መጠጊያዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ አልሁ። እጅግ ተቸግሬአለሁና ጩኸቴን አድምጥ፥ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፥ ስለ ምታጠግበኝ ጻድቃን እኔን ይከባሉ። ልጁ ባሳደደው ጊዜ፥ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ልመናዬን አድምጥ፥ በታማኝነትህ፥ በጽድቅህም መልስልኝ። ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባርያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ። ጠላት ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ አጐስቁሎአታል፥ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል። ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ። የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፥ የእጅህንም ሥራ አስተዋልሁ። እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፥ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፥ መንፈሴ ዛለ፥ ፊትህን ከኔ አትሰውር፥ ወደ ጉድጓድም እንደሚወርዱ እንዳልሆን። አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ጽኑ ፍቅርህን አሰማኝ፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አሳውቀኝ። አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ። አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፥ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ። አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፥ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት። በጽኑ ፍቅርህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባርያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው። ስለ ጎልያድ፥ የዳዊት መዝሙር። ጌታዬ ዐለቴ፥ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን፥ ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር፥ መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፥ ረዳቴና መታመኛዬም፥ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ። አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፥ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፥ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም። መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፥ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም። እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ፥ ዐሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ። ለነገሥታት መድኃኒትን የሚሰጥ፥ ባርያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው። አድነኝ፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። ልጆቻቸን በጉልማስነታቸው እንደ አዲስ አትክልት ይሁኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸንም እንደ እልፍኝ ይመሩና ያጊጡ፥ ዕቃ ቤቶቻቸንም ይሞሉ፥ በየዓይነቱም ዕቃ ይኑራቸው፥ በጎቻቸንም ብዙ ይውለዱ፥ በማሰማርያችንም ይብዙ፥ ላሞቻቸንም የሰቡ ይሁኑ፥ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ አይኑረው፥ በአደባባዮቻችንም ዋይታ አይኑር፥ እንደዚህ የሚሆንለት ሕዝብ የተመሰገነ ነው፥ ጌታ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ምስጉን ነው። የዳዊት የምስጋና መዝሙር። አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘለዓለም ዓለምም እባርካለሁ። በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘለዓለም ዓለምም አመሰግናለሁ። ጌታ ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፥ ታላቅነቱም የማይመረመር ነው። ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ። የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ። የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ። የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ። ጌታ ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቁጣ የራቀ፥ ጽኑ ፍቅሩም ብዙ ነው፥ ጌታ ለሁሉም ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው። አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥ ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ መንግሥትህ የዘለዓለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። ጌታ በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፥ ጌታ የሚወድቁትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ ያጎነበሱትንም ያነሣቸዋል። የሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፥ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ። ጌታ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። ጌታ ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያሳካል፥ ጩኸታቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። ጌታ የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፥ ክፉዎችንም ሁሉ ያጠፋል። አፌ የጌታን ምስጋና ይናገራል፥ ሥጋም ሁሉ ለዘለዓለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ። ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን አመስግኚ። በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ጌታን አመሰግናለሁ፥ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ። ማዳን በማይችሉ በአለቆች፥ በሰው ልጅ፥ አትታመኑ። ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፥ ያንጊዜ እቅዶቹ በሙሉ ይጠፋሉ። የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በጌታ በአምላኩ የሆነ ሰው ምስጉን ነው፥ እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፥ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፥ እውነትን ለዘለዓለም የሚጠብቅ፥ ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። ጌታ የታሰሩትን ይፈታል፥ ጌታ የዕውሮችን ዐይን ያበራል፥ ጌታ የወደቁትን ያነሣል፥ ጌታ ጻድቃንን ይወድዳል፥ ጌታ ስደተኞችን ይጠብቃል፥ ወላጆች የሞቱባቸውንና ባልቴቶችን ይቀበላል፥ የክፉዎችንም መንገድ ያጠፋል። ጌታ ለዘለዓለም ይነግሣል፥ ጽዮን ሆይ፥ አምላክሽ ለልጅ ልጅ ነው። ሃሌ ሉያ። ጌታን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው። ጌታ ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል። ልባቸው የተሰበረባቸውን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል። የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር ስፍር የለውም። ጌታ የተዋረዱትን ያነሣል፥ ክፉዎችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል። ለጌታ በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፥ ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፥ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል። ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል ለሚጠሩት ለቁራዎች ጫጩቶችም እንዲሁ። በፈረስ ኃይል አይደሰትም፥ በሰውም ጡንቻ ሐሴት አያደርግም። ጌታ በሚፈሩት፥ በጽኑ ፍቅሩ በሚታመኑት ይደሰታል። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጌታን አመስግኚ፥ ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና። በወሰንሽም ሰላምን አደረገ፥ የስንዴንም ስብ አጠገበሽ። መልእክቱን ወደ ምድር ይልካል፥ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል። አመዳዩን እንደ ባዘቶ ይሰጣል፥ ጉሙን እንደ አመድ ይበትነዋል፥ በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፥ በቁሩ ፊት ማን ይቆማል? ቃሉን ልኮ ያቀልጠዋል፥ ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችንም ያፈስሳል። ቃሉን ለያዕቆብ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል። ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፥ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ። ጌታን ከሰማያት አመስግኑት፥ በአርያም አመስግኑት። መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፥ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት። ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፥ የምታበሩ ከዋክብት ሁሉ፥ አመስግኑት። ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፥ ከሰማያት በላይ ያላችሁም ውኃዎችም እንዲሁ። የጌታን ስም ያመስግኑት፥ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩ። ለዘለዓለም ዓለም አቆማቸው፥ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉትምም። የባሕር አራዊትና ጥልቆችም ሁሉ፥ ጌታን ከምድር አመስግኑት፥ እሳትና በረዶ አመዳይና ጉም፥ ቃሉን የሚፈጽም ዐውሎ ነፋስም፥ ተራሮችና ኰረብቶች ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍና ዝግባ ሁሉ፥ አራዊትና እንስሳት ሁሉ፥ የሚሳቡና የሚበርሩ ወፎችም፥ የምድር ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ፥ አለቆችና የምድር ፈራጆች ሁሉ፥ ጉልማሶችና ልጃገረዶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፥ የጌታን ስም ያመስግኑ፥ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሏልና፥ ክብሩም በሰማይና በምድር ላይ ነው። የሕዝቡንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ የቅዱሳኑንም ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ። ለጌታ አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፥ ውዳሴው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው። እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፥ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያድርጉ። ስሙን በሽብሸባ ያወድሱ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት። ጌታ በሕዝቡ ተደስቶአልና፥ የዋሃንንም በማዳኑ ያስጌጣቸዋል። ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፥ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ። የእግዚአብሔር ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው፥ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው፥ በአሕዛብ ላይ በቀልን፥ በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፥ ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት፥ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ፥ የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ። ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት። ሃሌ ሉያ። ሃሌ ሉያ። ጌታን በመቅደሱ አወድሱት፥ በኃይሉ ጠፈር አወድሱት። ስለ ታላላቅ ሥራዎቹ አወድሱት፥ እንደ ታላቅነቱ ብዛት አወድሱት። በመለከት ድምፅ አወድሱት፥ በበገናና በመሰንቆ አወድሱት። በከበሮና በሽብሸባ አወድሱት፥ በባለ አውታር መሣሪያና በእምቢልታ አወድሱት። ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አወድሱት፥ ድምፁ በሚሰማ ጸናጽል አወድሱት። እስትንፋስ ያለው ሁሉ ጌታን ያወድስ። ሃሌ ሉያ። የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፥ ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥ የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥ ብልሃትን ለአላዋቂዎች ለመስጠት ለወጣቶችም እውቀትንና ጥንቃቄን፥ ጠቢብ እነዚህን በመስማት ዐዋቂነትን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። ምሳሌንና ምሥጢርን የጠቢባንን ቃልና ዕንቆቅልሸ ለማስተዋል። የዕውቀት መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ሞኞች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው፥ ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ሐብል ይሆንልሃልና። ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል። ደምን ለማፍሰስ “ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት” ቢሉ፥ “በሙሉ ሕይወት እያሉ፥ ከነነፍሳቸው፥ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ ወደ ጉድጓድ እንደሚወድቁም ይሁኑ፥ መልካምና ውድ ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፥ ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፥ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ”፥ ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን አርቅ፥ እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። ወጥመድ በወፎች ዐይን ፊት በከንቱ ይተከላልና። እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፥ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ። በግፍ ማትረፍ የሚፈልግ ሁሉ መንገዱ እንዲሁ ነው። የግፉ ባለቤትም ነፍስ ይነጠቃል። ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፥ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፥ ግርግር ባለበት አደባባይ ትጣራለች፥ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች፦ “እናንት አላዋቂዎች፥ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? ሞኞችም እውቀትን ይጠላሉ? ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፥ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ ፥ ቃሌን አስተምራችኋለሁ። በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥ ምክሬን ሁሉ ግን ችላ ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፥ እኔም በእናንተ መጥፋት እስቃለሁ፥ ሽብር በመጣባችሁ ጊዜ አላግጥባችኋለሁ ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ። የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፥ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም። እውቀትን ጠልተዋልና፥ ጌታንም መፍራት አልመረጡምና፥ ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ተግሣጼንም ሁሉ ንቀዋልና፥ ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ የገዛ ራሳቸውን ምክር ይጠግባሉ። አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሞኞችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና። የሚሰማኝ ግን ተረጋግቶ ይቀመጣል፥ ከክፉም ሥጋት ያርፋል።” ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ማመዛዘንን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እንደ ተደበቀ ዕንቁም ብትሻት፥ የዚያን ጊዜ ጌታን መፍራትን ትገነዘባለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። ጌታ ጥበብን ይሰጣልና፥ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፥ እርሱ ለቅኖች ስምረትን ያከማቻል፥ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፥ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፥ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ። ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፥ ማመዛዘን ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይከላከልልሃል፥ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፥ እነርሱም በጨለማ መንገድ ለመሄድ የቀናውን ጎዳና የሚተዉ፥ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ሐሤትን የሚያደርጉ፥ መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፥ ከእንግዳይቱ ሴት አንተን ለመታደግ፥ ቃሏን ከምታለዝብ ከማትታወቀው ሴት፥ የወጣትነት ወዳጅዋን የምትተወው ሴት የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳዋ፥ ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፥ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ። ወደ እርሷ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ ወደ ሕይወት ጎዳናም አይደርሱም፥ አንተም በመልካም ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ። ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፥ ፍጹማንም በእርሷ ይኖራሉና፥ ክፉዎች ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርሷ ይነጠቃሉ። ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ቀኖች፥ የሕይወት ዓመታትና ሰላምም ይጨምሩልሃልና። ደግነትና እውነት አይተዉህ፥ በአንገትህ ላይ እሰራቸው፥ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። በፍጹም ልብህ በጌታ ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፥ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፥ ጌታን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፥ ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም መታደስ። ከሀብትህ አስበልጠህ ጌታን አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት ይልቅ፥ ጐተራህም እህልን ይሞላል፥ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። ጌታ የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ። ጥበብን የሚያገኝ ሰው ብጹዕ ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው፥ በእርሷ የሚገኘው ትርፍ ከብር ከሚገኘው፥ ገቢዋም ከወርቅ ይሻላልና። ከውድ ዕንቁም ትከብራለች፥ ከምትመኘው ነገር አንዳችም አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር ። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርሷ ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው። ጌታ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥ ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥ ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና። ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን፥ ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ከማድረግ አትቆጠብ። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፥ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ። እርሱ ክፉ ካልሠራብህ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በጌታ ፊት ርኩስ ነውና፥ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የጌታ መርገም በክፉ ሰዎች ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፥ ሞኞች ግን መዋረድን ይቀበላሉ። ልጆች ሆይ፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፥ መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፥ ሕጌን አትተዉ። እኔም አባቴን የምሰማ ትንሽ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር። ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር፦ “ልብህ ቃሌን በጥብቅ ይያዘው፥ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ። ጥበብን አግኝ፥ ማስተዋልን አግኝ፥ አትርሳም፥ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል። አትተዋት፥ ትጠብቅሃለች፥ ውደዳት፥ ትንከባከብህማለች። የጥበብ መጀመሪያ እነሆ፥ ጥበብን አግኝ፥ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ከፍ ከፍ አድርጋት፥ እርሷም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፥ ብታቅፋትም ታከብርሃለች። በራስህ የጸጋ አክሊልን ታኖራለች፥ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትልሃለች።” ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ንግግሬንም ተቀበል፥ የሕይወትህም ዓመታት ይበዙልሃል። የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፥ በቀናች ጎዳና መራሁህ። በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይታገድም፥ ብትሮጥም አትሰናከልም። ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፥ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና። በክፉዎች መንገድ አትግባ፥ በመጥፎ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። ከእርሷ ራቅ፥ አትሂድባትም፥ ራቅ በል ተዋትም። ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፥ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና። የክፋትን እንጀራ ይበላሉና፥ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና። የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። የክፋት መንገድ እንደ ጨለማ ነው፥ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም። ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሎቼም ጆሮህን አዘንብል። ከዓይንህ አታርቃቸው፥ በልብህም ውስጥ ጠብቃቸው። ለሚያገኙአቸው ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና። ከሁሉ አስበልጠህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት ምንጭ እርሱ ነውና። ጠማማ ንግግርን ከአንተ አስወግድ፥ አሳሳች ቃሎችን ከአንተ አርቅ። ዐይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ አተኩረው ፊት ለፊት ይመልከቱ። የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፥ እግርህንም ከክፉ መልስ። ልጄ ሆይ፥ ጥበቤን አድምጥ፥ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ አዘንብል፥ ጥንቃቄን ትጠብቅ ዘንድ ከንፈሮችህም እውቀትን እንዲጠብቁ። ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከዘይት የለዘበ ነውና፥ ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም፥ የተሳለ ነው። እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፥ የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፥ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፥ የሚታወቅም አይደለም። አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ ከአፌም ቃል አትራቁ። መንገድህን ከእርሷ አርቅ፥ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ፥ ክብርህን ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ዕድሜህንም ለጨካኝ፥ ሌሎች ከኃይልህ እንዳይጠግቡ፥ ድካምህም ወደ ባዕድ ሰው ቤት እንዳይሄድ። በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥ ትላለህም፦ “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ! የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። በማኅበርና በጉባኤ መካከል ለክፉ ሁሉ ለመዳረግ ጥቂት ቀረኝ።” ከጉድጓድህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ። ምንጮችህ ወደ ሜዳ፥ ወንዞችህ ወደ አደባባይ ይፈስሳሉን? ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ። ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፥ ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ። ልጄ ሆይ፥ ስለምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ? የሌላይቱንስ ብብት ለምን ታቅፋለህ? የሰው መንገድ በጌታ ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና። ክፉ በክፋቱ ይጠመዳል፥ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። አልተቀጣምና እርሱ ይሞታል፥ በአላዊቅነትም ብዛት ይስታል። ልጄ ሆይ፥ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፥ ለእንግዳ ሰው ቃል ብትገባ፥ በአፍህ ቃል ከተጠመድህ፥ በአፍህ ቃል ከተያዝህ። ልጄ ሆይ፥ ይህን አድርግ ራስህንም አድን፥ በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፥ ፈጥነህ ሂድ፥ ጎረቤትህንም ነዝንዘው። ለዓይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጉልቻን አትስጥ፥ እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ። አንተ ሰነፍ፥ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብሏን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች። አንተ ሰነፍ፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት መተኛት፥ ጥቂት ማንቀላፋት፥ ለመተኛት ጥቂት እጅን ማጣጠፍ፥ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። ከንቱና ክፉ ሰው ጠማማ ንግግር ይዞ ይዞራል፥ በዓይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ያስተምራል፥ ጠማማነት በልቡ አለ፥ ሁልጊዜም ክፋትን ያቅዳል፥ ጠብንም ይዘራል። ስለዚህ ጥፋት ድንገት ይደርስበታል፥ ድንገት ይደቅቃል፥ ፈውስም ከቶ የለውም። ጌታ የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፋቸዋለች፥ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያቅድ ልብ፥ ወደ ክፉ የሚሮጡ እግሮች፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ትምህርት አትተው፥ ሁልጊዜም በልብህ አኑራቸው፥ በአንገትህም እሰራቸው። ስትሄድም ይመሩሃል፥ ስትተኛ ይጠብቁሃል፥ ስትነሣ ያነጋግሩሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ትምህርትም ብርሃን ነውና፥ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ከሌላይቱም ሴት አታላይ ምላስ። ውበትዋን በልብህ አትመኘው፥ በዐይኖችዋም አትማረክ። የሴተኛ ዐዳሪዋ ዋጋ እስከ አንዲት እንጀራ ነው፥ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች። በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፥ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፥ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል። ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጐደለው ነው፥ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል። ቁስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም። ቅንዓት ለሰው የቁጣ ትኩሳት ነውና፥ በበቀልም ቀን አይራራለትምና። እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፥ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም። ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ። ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፥ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፥ በጣቶችህ እሰራቸው፥ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። ጥበብን፦ “አንቺ እኅቴ ነሽ” በላት፥ ማስተማውልንም፦ “ዘመዴ” ብለህ ጥራት፥ ከአምንዝራ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ፥ ቃሏን ካለዘበች ከሌላይቱ ሴት። በቤቴ መስኮት ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፥ ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፥ ከወጣቶችም መካከል አንዱ አእምሮ ጐድሎት አየሁ፥ በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፥ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርሷ አቀና፥ ማታ ሲመሽ፥ ጀምበር ስትጠልቅ፥ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ። እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የአምንዝራ ሴት ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች። ሁከተኛና እንቢተኛ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፥ አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች። ያዘችውም ሳመችውም፥ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው፦ “መሥዋዕትንና የደኅንነት ቁርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፥ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ። ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም። በአልጋዬ ላይ ማለፊያ የአልጋ ልብስ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ያማሩ አልባሳት አንጥፌበታለሁ። በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ። ና፥ እስኪ ነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን። ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፥ በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፥ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል።” በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፥ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች። እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንደሚነዳ፥ አጋዘን ቸኩሎ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ፥ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚጣደፍ፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ። ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ የአፌንም ቃል አድምጡ። ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል በጎዳናዋ አትሳት። ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፥ እርሷም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው። ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፥ ወደ ሞት ማደርያዎች የሚወርድ ነው። በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አታሰማምን? በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች። በበሮች አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፥ በደጆች መግቢያ ትጮኻለች፦ “እናንተ ሰዎች፥ እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው። እናንተ አላዋቂዎች፥ ማመዛዘንን ተረዱ፥ እናንተም ሞኞች አስተውሉ። ክቡር ነገርን እናገራለሁና ስሙ፥ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ። አፌ እውነትን ይናገራልና፥ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ። የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፥ በውስጣቸውም ምንም ጠማማና ጠመዝማዛ ነገር የለም። እነርሱ ለሚያስተውል የቀኑ ናቸው፥ እውቀትንም ላገኟት ትክክል ናቸው። ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከተመረጠ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ። ጥበብ ከዕንቁ ትበልጣለችና የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም። እኔ ጥበብ፥ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ። ጌታን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፥ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም ንግግር እጠላለሁ። ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፥ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ። ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምንትም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ። ባለ ሥልጣኖች በእኔ ይመራሉ፥ ክቡራን ምድርን ያስተዳድራሉ። እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል። ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥ ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ። ጌታ የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘለዓለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፥ የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፥ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ። አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከጌታም ሞገስን ያገኛልና። እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፥ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።” ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን አዘጋጀች ፥ ማዕድዋን አሰናዳች። ሴቶች አገልጋዮችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች፦ “አላዋቂ የሆነ በዚህ በኩል ይለፍ፥” አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች፦ “ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ ያጣፈጥኩትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ክፉንም የሚዘልፍ ኃፍረት ይገጥመዋል። ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፥ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ይበልጡን ጠቢብ ይሆናል፥ ጻድቅንም አስተምረው፥ ይበልጡን አዋቂ ይሆናል። የጥበብ መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና። ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፥ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትን ለብቻህ ትሸከማለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚገዛ ነው፥ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ረስቷልና፥ የሚሠማራባትን መንገድ እንዲስት አድርጓልና፥ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፥ ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፥ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል። አላዋቂ ሴት ሁከተኛ ናት፥ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም። በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥ በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት፦ “አላዋቂ የሆነ በዚያ ይለፍ፥” አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች፦ “የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል።” ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ ተጋብዦችዋም በሲኦል ጥልቀት ውስጥ እንዳሉ አያውቅም። የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥ አላዋቂ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው። በክፋት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል። ጌታ የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፥ የክፉዎችን ምኞት ግን ይገለብጣል። የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፥ የትጉ እጅ ግን ሀብታም ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፥ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፥ የክፉዎች አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፥ የክፉ ስም ግን ይጠፋል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፥ በከንፈሩ ሞኝ የሆነ ግን ይወድቃል። ያለ ነውር የሚመላለስ ተማምኖ ይሄዳል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፥ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል ። የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ማፍለቂያ ናት፥ የክፉዎች አፍ ግን ዐመፅን ይሸፍናል። ጥላቻ ክርክርን ታስነሣለች፥ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ትከድናለች። በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፥ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን እውቀትን ያከማቻሉ፥ የአላዋቂ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። የሀብታም መዝገቡ የጸናች ከተማ ናት፥ የድሆች ውድቀት ድህነታቸው ነው። የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፥ የክፉ ገቢው ግን ለኃጢአት ነው። ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፥ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል። ጥላቻን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፥ ሐሜትንም የሚገልጥ አላዋቂ ነው። በቃል ብዛት ውስጥ መተላለፍ ሳይኖር አይቀርም፥ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፥ የክፉ ልብ ግን ዋጋ ቢስ ነው። የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፥ አላዋቂዎች ግን ከማስተዋል ጉድለት የተነሣ ይሞታሉ። የጌታ በረከት ሀብታም ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም። ክፉ ነገር ማድረግ ለአላዋቂ ጨዋታ ነው፥ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው። የክፉ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች። ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ክፉ ሰው አይገኝም፥ ጻድቅ ግን የዘለዓለም መሠረት ነው። ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥ ሰነፍም ለላኩት እንዲሁ ነው። ጌታን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፥ የከፉዎች ዕድሜ ግን ታጥራለች። የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፥ የክፉዎች ተስፋ ግን ይጠፋል። የጌታ መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ክፋትን ለሚያደርጉ ግን ጥፋት ነው። ጻድቅ ለዘለዓለም አይናወጥም፥ ክፉዎች ግን በምድር ላይ አይቀመጡም። የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፥ የመጥመም ምላስ ግን ትቈረጣለች። የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፥ የክፉዎች አፍ ግን ጠማማ ነገር ይናገራል። የሐሰት ሚዛን በጌታ ፊት አስጸያፊ ነው፥ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፥ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፥ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች። በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፥ ክፉ ግን በክፋቱ ይወድቃል። ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፥ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ክፉ ግን የእርሱን ቦታ ይወስዳል። እኩይ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፥ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ። በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በክፉዎችም ጥፋት እልል ትላለች። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፥ በክፉዎች አፍ ግን ትገለበጣለች። ወዳጁን የሚንቅ ልበ ጐደሎ ነው፥ አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል። ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፥ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል። መልካም ምክር በሌለበት ሕዝብ ይወድቃል፥ በአማካሪዎች ብዛት ግን ዋስትና ይገኛል። ለእንግዳ ሰው የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፥ ዋስ መሆንን የሚጠላ ግን ይድናል። ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ኃያላንም ሀብትን ያገኛሉ።። ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፥ ጨካኝ ግን ራሱን ይጐዳል። ክፉ ሰው የሐሰት ደመወዝ ያገኛል፥ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው። በጽድቅ የሚጸና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ ክፋትን የሚከተል ግን ወደ ሞት ይሄዳል። ልበ ጠማሞች በጌታ ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፥ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው። ክፉ ሰው በእርግጠኛነት ሳይቀጣ አይቀርም፥ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል። በዐሣማ አፍንጫ ላይ የወርቅ ቀለበት፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴት። የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፥ የክፉዎች ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው። በልግስና የሚሰጥ ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፥ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም። በረከትን የምታካፍል ነፍስ ትጠግባለች፥ ውሃን የሚያጠጣ እርሱ ደግሞ ይረካል። እህልን የሚደብቅ ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፥ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው። መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፥ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል። በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል፥ ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ። ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፥ አላዋቂም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል። የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚማርክ እርሱ ጠቢብ ነው ። እነሆ፥ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፥ ይልቁንስ ክፉዎችና ዓመፀኞችስ እንዴት ይሆኑ! ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፥ እርማትን የሚጠላ ግን ሞኝ ነው። መልካም ሰው ከጌታ ዘንድ ሞገስን ያገኛል፥ ተንኰለኛውን ሰው ግን ጌታ ይፈርድበታል። ክፋት ለሰው ዋስትና አያስገኝም፥ የጻድቃንን ሥር ግን ምንም አያንቀሳቅሰውም። ጐበዝ ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፥ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት። የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፥ የክፉዎች ምክር ግን ሽንገላ ነው። የክፉ ሰዎች ቃላት ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ የቅኖች አፍ ግን ያድናቸዋል። ክፉ ሰዎች ይወድቃሉ፥ ፈጽሞም አይገኙም፥ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፥ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። ምግብ ሳይኖረው ከሚኮራ ሰው አገልጋይ ኖሮት የተዋረደ ሰው ይሻላል። ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፥ የክፉ ሰው ርኅራኄ ግን ጭካኔ ነው። መሬቱን የሚቆፍር ሰው እንጀራ ይጠግባል፥ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን ማስተዋል የተሣነው ነው። ክፉ ሰዎች በክፉዎች ወጥመድ ይደሰታሉ፥ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል። ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል። የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፥ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፥ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፥ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል። የትጉ እጅ ትገዛለች፥ የታካች እጅ ግን ትገብራለች። ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፥ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፥ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፥ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው። በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም። ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል፥ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም። ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፥ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች። አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፥ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋት ያገኘዋል። የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፥ አንዳችም አታገኝም፥ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች። ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፥ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም። በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፥ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል። ራሱን ሀብታም የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፥ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፥ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም። ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፥ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል። በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፥ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት። በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፥ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፥ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት። ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፥ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል። ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው። መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፥ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት። ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፥ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል። መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፥ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው። ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፥ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል። የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፥ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ። ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፥ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፥ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ። ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፥ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች። በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፥ ከፍርድ መጉደል የተነሣ ግን ይጠፋል። በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፥ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጸዋል። ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፥ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል። ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፥ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች። በቅን የሚሄድ ሰው ጌታን ይፈራል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል። በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፥ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፥ ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው። የታመነ ምስክር አይዋሽም፥ የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፥ ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም። ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥ በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና። የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፥ የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው። ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፥ በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች። የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፥ ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም። የኀጥኣን ቤት ይፈርሳል፥ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው። ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥ ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ። የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፥ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል። ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፥ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። ቁጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፥ አስተዋይ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፥ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ። ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥ ኀጥኣንም በጻድቃን በር። ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው፥ የሀብታም ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው። ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል፥ ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው። ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፥ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው። በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፥ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ። የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፥ የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው። እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል፥ በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው። ጌታን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል። ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ ጌታን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው። የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፥ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፥ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል። ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፥ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል። ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፥ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል። ኀጥእ በክፋቱ ይደፋል፥ ጻድቅ ግን በእውነቱ ይታመናል። በአዋቂ ልብ ጥበብ ትቀመጣለች፥ በሰነፎች ውስጥ ግን አትታወቅም። ጽድቅ፥ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፥ ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች። አስተዋይ አገልጋይ በንጉሥ ዘንድ ይወደዳል፥ በሚያሳፍር ላይ ግን ቁጣው ይሆናል። የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፥ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች። የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፥ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል። የጌታ ዐይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፥ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ። ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፥ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል። ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፥ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው። በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፥ የኀጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው። የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፥ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። የኀጥኣን መሥዋዕት በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። የኀጥኣን መንገድ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል። ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥ ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል። ሲኦልና ጥፋት በጌታ ፊት የታወቁ ናቸው፥ ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው። ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥ ወደ ጠቢባንም አይሄድም። ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፥ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች። የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፥ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል። ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፥ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው። ጌታን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። ቁጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፥ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል። የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፥ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፥ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል። ምክር ከሌለች የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፥ መካሮች በበዙበት ግን ይጸናል። ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፥ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው! በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል። ጌታ የትዕቢተኞችን ቤት ይነቅላል፥ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል። የበደለኛ አሳብ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ናት፥ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው። ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፥ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል። የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል፥ የኀጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል። ጌታ ከኀጥኣን ይርቃል፥ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል። የዐይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል። የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል። ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፥ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል። ጌታን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች። የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፥ የምላስ መልስ ግን ከጌታ ዘንድ ነው። የሰው መንገድ ሁሉ በዐይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፥ ጌታ ግን መንፈስን ይመዝናል። ሥራህን ለጌታ አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች። ጌታ ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን። በልቡ የታበየ ሁሉ በጌታ ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም። በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥ ጌታንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል። የሰው አካሄድ ጌታን ደስ ያሰኘው እንደሆነ፥ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል። በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል። የሰው ልብ መንገዱን ያዘጋጃል፥ ጌታ ግን አካሄዱን ያቀናለታል። የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥ አፉም በፍርድ አይስትም። እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የጌታ ናቸው፥ የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው። ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና። የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥ በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል። የንጉሥ ቁጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፥ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል። የንጉሥ ፊት ሲፈካ ብርሃን አለ፥ መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው። ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው። የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፥ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል። ትዕቢት ጥፋትን፥ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል። ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፥ በጌታ የታመነ ምስጉን ነው። ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥ በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል። ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፥ ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው። የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥ ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል። ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፥ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። ሠራተኛን የዕለት ጉርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፥ ረሀቡ ይጐተጉተዋልና። ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ። ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፥ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል። ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል። ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፥ ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል። የሸበተ ጠጉር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል። ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ ስሜቱን የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል። ዕጣ በጉያ ይጣላል፥ መደብዋ ሁሉ ግን ከጌታ ዘንድ ነው። ጥል ባለበት ዘንድ ግብዣ ከሞላበት ቤት ይልቅ በጸጥታ ደረቅ ቁራሽ ይሻላል። አስተዋይ ባርያ ነውረኛውን ልጅ ይገዛል፥ በወንድማማች መካከልም ርስትን ይካፈላል። ማቅለጫ ለብር፥ ከውር ለወርቅ ነው፥ ጌታ ግን ልብን ይፈትናል። ክፉ ሰው የበደለኛን ከንፈር ይሰማል፥ ሐሰተኛም ወደ ተንኰለኛ ምላስ ያደምጣል። በድሀ የሚያላግጥ ፈጣሪውን ይሰድባል፥ በጥፋትም ደስ የሚለው ሳይቀጣ አይቀርም። የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፥ የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው። ለሰነፍ የኩራት አነጋገር አይገባውም፥ ይልቁንም ሐሰተኛ ከንፈር ለመኰንን አይገባውም። ገንዘብ ባደረገው ፊት መማለጃ እንደ ተዋበ ዕንቁ ነው፥ ወደ ዞረበትም ስፍራ ሁሉ ሥራውን ያቀናል። ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፥ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል። መቶ ግርፋት በሰነፍ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሣጽ በአስተዋይ ሰው ጠልቆ ወደ ልቡ ይገባል። ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል፥ ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል። ሰነፍን በስንፍናው ከመገናኘት ልጆችዋ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል። በመልካም ፋንታ ክፉን የሚመልስ፥ ክፉ ነገር ከቤቱ አትርቅም። የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው፥ ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው። ኀጥኡን የሚያጸድቅና በጻድቁ ላይ የሚፈርድ፥ ሁለቱ በጌታ ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው። በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፥ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። አእምሮ የጐደለው ሰው አጋና ይመታል፥ በባልንጀራውም ፊት ይዋሳል። ዓመፃን የሚወድድ ክርክርን ይወድዳል፥ ደጁንም ዘለግ የሚያደርግ ውድቀትን ይሻል። ጠማማ ልብ ያለው መልካምን አያገኝም፥ ምላሱንም የሚገለብጥ በክፉ ላይ ይወድቃል። ሰነፍን የሚወልድ ኀዘን ይሆንበታል፥ የደንቆሮ ልጅም አባት ደስ አይለውም። ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፥ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ኀጥእ የፍርድን መንገድ ለማጥመም ከብብት መማለጃን ይወስዳል። በአስተዋይ ፊት ጥበብ ትኖራለች፥ የሰነፍ ዐይን ግን በምድር ዳርቻ ነው። ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ምሬት ነው። ጻድቅን መቅጣት፥ ጨዋ ሰውንም በጻድቅነቱ መምታት መልካም አይደለም። ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፥ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው። ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ፦ ባለ አእምሮ ነው ይባላል። መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፥ በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ። ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር። የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፥ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው። የጻድቅ ፍርድ ይጠምም ዘንድ፥ ለኀጥእም ማድላት መልካም አይደለም። የሰነፍ ከንፈር በጥል ውስጥ ትገባለች፥ አፉም በትርን ትጠራለች። የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው። የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጉርጆች ድረስ ይወርዳል። በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው። የጌታ ስም የጸና ግምብ ነው፥ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል። ለሀብታም ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፥ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር። ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች። ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል። የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፥ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል? የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች። የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች። ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፥ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል። ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥ በኃያላንም መካከል ትበይናለች። የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፥ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው። የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል፥ ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል። ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፥ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ። ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከጌታም ሞገስን ይቀበላል። ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፥ ሀብታም ግን በድፍረት ይመልሳል። ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፥ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ። በከንፈሩ ከሚወሳልት ሰነፍ ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል። ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፥ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል። የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፥ ልቡም በጌታ ላይ ይቈጣል። ባለጠግነት ብዙ ወዳጆች ይጨምራል፥ የድሀ ወዳጅ ግን ከእርሱ ይርቃል። ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በሐሰትም የሚናገር አያመልጥም። ብዙ ሰዎች ለጋሱን ያቈላምጣሉ፥ ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ ነው። ድሀን ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፥ ይልቁንም ወዳጆቹ ከእርሱ ይርቃሉ። እነርሱንም በቃል ቢከተላቸው አንዳች አይረቡትም። ጥበብን የሚያገኝ ነፍሱን ይወድዳል፥ ማስተዋልንም የሚጠብቅ መልካም ነገርን ያገኛል። ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በሐሰትም የሚናገር ይጠፋል። ለሰነፍ ቅምጥልነት አይገባውም፥ ይልቁንም ባርያ በአለቆች ላይ ይገዛ ዘንድ። ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፥ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል። እንደ አንበሳ ግሣት የንጉሥ ቁጣ ነው፥ ሞገሱም በመስክ ላይ እንዳለ ጠል ነው። ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ኀዘን ነው፥ ጠበኛም ሚስት ሳያቋርጥ እንደሚያንጠባጥብ ውሃ ናት። ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፥ አስተዋይ ሚስት ግን ከጌታ ዘንድ ናት። ሥራ መፍታት እንቅልፍን ታመጣለች፥ የታካችም ነፍስ ትራባለች። ትእዛዝን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፥ መንገዱን ቸል የሚል ግን ይጠፋል። ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለጌታ ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል። ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ። ንዴተኛ ሰው መቀጮ ይከፍላል፥ ብታድነውም ደግሞ ትጨምራለህ። ምክርን ስማ፥ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ። በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፥ የጌታ ምክር ግን እርሱ ይጸናል። የሰው ቸርነት የእርሱ ፍሬ ነው፥ ከሐሰተኛ ሀብታምም እውነተኛ ድሀ ይሻላል። ጌታን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፥ የሚፈራውም ጠግቦ ይኖራል፥ ክፉ ነገርም አያገኘውም። ታካች ሰው እጁን በወጭቱ ያጠልቃታል፥ ወደ አፉ ስንኳ አይመልሳትም። ፌዘኛ ብትገርፈው አላዋቂ ብልሃተኛ ይሆናል፥ አስተዋይን ሰው ብትገሥጸው እውቀትን ያገኛል። አባቱን የሚያስከፋ እናቱንም የሚያሳድድ የሚያሳፍርና ጐስቋላ ልጅ ነው። ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ከሰማህ በኋላ ከእውቀት ቃል መሳሳትን ተው። ወስላታ ምስክር በፍርድ ያፌዛል፥ የኀጥኣንም አፍ ክፋትን ይውጣል። ለሚያፌዙ ሰዎች ፍርድ ተዘጋጅታለች፥ ለሰነፎችም ጀርባ በትር። የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፥ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም። የንጉሥ ቁጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፥ የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል። ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው፥ ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል። ታካች ሰው በብርድ ምክንያት አያርስም፥ ስለዚህ በመከር ይለምናል፥ ምንም አያገኝም። ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፥ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል። ብዙ ሰዎች ቸርነታቸውን ያወራሉ፥ የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል? ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳል፥ ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው። በፍርድ ወንበር የተቀመጠ ንጉሥ ክፉውን ሁሉ በዐይኖቹ ይበትናል። ልቤን አነጻሁ፥ ከኃጢአትም ጠራሁ የሚል ማን ነው? ሁለት ዓይነት ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ፥ ሁለቱ በጌታ ፊት ርኩሳን ናቸው። ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል። የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥ ሁለቱን ጌታ ፈጠራቸው። ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ፥ ዓይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ። ዕቃ የሚገዛ “አይረባም አይረባም” ብሎ ያራክሳል፥ ገዝቶ ሲመለስ ግን በገዛው ዕቃ ይኩራራል። ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቁ ይገኛል፥ የእውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት። ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው። የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፥ ከዚያ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል። አሳብ በምክር ትጸናለች፥ በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ። ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፥ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው። አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፥ በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል። በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም። ክፉ እመልሳለሁ አትበል፥ ጌታን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል። ሁለት ዓይነት ሚዛን በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም። የሰው አካሄዱ ከጌታ ዘንድ ነው፥ እንግዲስ ሰው መንገዱን እንዴት ያስተውላል? ሰው በችኰላ፦ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ነው። ጠቢብ ንጉሥ ኀጥኣንን በመንሽ ይበትናቸዋል፥ መንኰራኵሩንም በእነርሱ ላይ ያንኰራኩርባቸዋል። የሰው መንፈስ የጌታ መብራት ነው የሆዱን ጉርጆች ሁሉ የሚመረምር። ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፥ ዙፋኑም በቸርነት ይበረታል። የጎበዛዝት ክብር ጉልበታቸው ናት፥ የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው። የሰንበር ቁስል ክፉዎችን ያነጻል፥ ግርፋትም ወደ ሆድ ጉርጆች ይገባል። የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በጌታ እጅ ነው፥ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፥ ጌታ ግን ልብን ይመዝናል። ጌታ ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ይወድዳል። ትዕቢተኛ ዓይንና ደፋር ልብ የኀጥኣንም እርሻ ኃጢአት ነው። የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፥ ችኩል ሰው ግን ለመጉደል ይቸኩላል። በሐሰተኛ ምላስ መዝገብ ማከማቸት የሚበንን ጉም ነው፥ ይህን የሚፈልጉ ሞትን ይፈልጋሉ። ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አይወድዱምና የኀጥኣን ንጥቂያ ራሳቸውን ያጠፋቸዋል። የበደለኛ መንገድ የጠመመች ናት፥ የንጹሕ ሥራ ግን የቀና ነው። ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጪ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። የኀጥእ ነፍስ ክፉን ትመኛለች፥ በፊቱም ባልንጀራው ሞገስን አያገኝም። ፌዘኛ ቅጣትን በተቀበለ ጊዜ አላዋቂ ሰው ጥበብን ያገኛል፥ ጠቢብም ቢማር እውቀትን ይቀበላል። ጻድቅ ስለ ኀጥእ ቤት ያስባል፥ ኀጥኣንም ለጥፋት እንደ ተገለበጡ። የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም። ስጦታ በስውር ቁጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ ጽኑ ቁጣን ታበርዳለች። ፍርድን ማድረግ ለጻድቅ ደስታ ነው፥ ኃጢአትን ለሚያደርጉ ግን ጥፋት ነው። ከማስተዋል መንገድ የሚሳሳት ሰው በሙታን ጉባኤ ያርፋል። ተድላ የሚወድድ ድሀ ይሆናል፥ የወይን ጠጅንና ዘይትንም የሚወድድ ሀብታም አይሆንም። ኀጥእ የጻድቅ ቤዛ ነው፥ በደለኛም የቅን ሰው ቤዛ ነው። ከጠበኛና ከቁጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል። የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፥ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ያሟጥጠዋል። ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል። ጠቢብ የኃያላንን ከተማ ይገባባታል፥ የሚታመኑበትንም ኃይል ያፈርሳል። አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ ነፍሱን ከመከራ ይጠብቃል። ኩሩና ተጓዳጅ ሰው ፌዘኛ ይባላል፥ እርሱም በትዕቢት ቁጣ ያደርጋል። ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና። ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፥ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። የክፉዎች መሥዋዕት አስጸያፊ ነው፥ ይልቁንም በክፉ አሳብ ሲያቀርቡት አስጸያፊ ነው። ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፥ የሚሰማ ሰው ግን ተጠንቅቆ ይናገራል። ኀጥእ ፊቱን ያጠነክራል፥ ቅን ሰው ግን መንገዱን ያጸናል። ያለ ጌታ የሚሠምር፥ ጥበብም የለም፥ ማስተዋልም የለም፥ ምክርም የለም። ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፥ ድል ግን ከጌታ ዘንድ ነው። መልካም ስም ከብዙ ሃብት ይሻላል፥ መልካም ሞገስም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል። ሀብታምና ድሀ ይገናኛሉ፥ ሁለቱንም የፈጠራቸው ጌታ ነው። ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፥ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይሄዱና ይጐዳሉ። የትሕትናና ጌታን የመፍራት ውጤት ሀብት፥ ክብርና ሕይወት ናቸው። እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ላይ ይገኛሉ፥ ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል። ልጅን ሊሄድ በሚገባው መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም። ሀብታም ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ጥገኛ ነው። ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥ የቁጣውም በትር ይጠፋል። ርኅሩህ የተባረከ ይሆናል፥ ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቶአልና። ፌዘኛን ብታስወጣ ክርክር ይቆማል፥ ጠብና ስድብም ያልቃል። የልብን ንጽሕናን የሚወድና ንግግሩ ለዛ ያለው ሰው፥ ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል። የጌታ ዐይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፥ የአታላዩን ቃላት ግን ይገለብጣል። ሰነፍ ሰው፦ “ውጪ አንበሳ አለ፤ ብወጣ፥ በመንገዱ ላይ እሞታለሁ” ይላል። የአመንዝራ ሴት አፍ የጠለቀ ጉድጓድ ነው፥ ጌታ የተቈጣው በውስጡ ይወድቃል። ቂልነት በልጅ ልብ ውስጥ ተተብትቧል፥ የተግሣጽ በትር ግን ነፃ ያደርገዋል። ለራሱ ጥቅም ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለሀብታም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፥ እነርሱን በውስጥህ ብትጠብቅ፥ በከንፈሮችህም ላይ የተዘጋጁ ቢሆኑ፥ አስደሳች ነገር ይሆንልሃልና። እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ እነሆ እነርሱን ዛሬ አስታወቅሁህ። የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፥ ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፥ በምክርና በእውቀት ሠላሳ ምሳሌዎችን አልጻፍሁልህምን? ድሀን አትግፈፈው ድሀ ነውና፥ ችግረኛውንም በበር አትጨቁነው፥ ምክንያቱም ጌታ ለእነርሱ ይሟገታልና፥ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና። ከቁጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከንዴተኛም ጋር አትሂድ፥ መንገዱን ተምረህ፥ ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። የምር ቃል እንደሚገቡ፥ ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን፥ መክፈል ባትችል፥ ለምን የምትተኛበት አልጋ ይወሰድብሃል? አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፋልስ። በሥራው ብልህ ሰው ትመለከታለህን? በነገሥታት ፊት ያገለግላል፥ በተራ ሰዎችም ፊት ሊያገለግል አይቆምም። ከባለ ሥልጣን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፥ ሰውነትህም ቢጎመጅ፥ በጉሮሮህ ላይ ካራ አድርግ። ጣፋጩ መብል አይመርህ የሐሰት እንጀራ ነውና። ሀብታም ለመሆን አትድከም፥ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። ቀና ብለህ እያየኸው ይጠፋል፥ ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና። የንፉግን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፥ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፥ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ። በሞኝ ጆሮ ምንም አትናገር፥ በቃልህ ጥበብ ያፌዛልና። የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፥ ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፥ ታዳጊአቸው ኃያል ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና። ልብህን ለምክር ስጥ፥ ጆሮህንም እንዲሁ ለእውቀት ቃላት። ልጅን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና። በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ታድናለህ። ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን የእኔም ልብ ደስ ይለዋል፥ ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ ኩላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል። ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፥ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ ጌታን በመፍራት ኑር፥ በእውነት መጨረሻህ ያምራልና፥ ተስፋህም አይጠፋምና። ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ጠቢብም ሁን፥ ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ። ከወይን ጠጅ ጠጪዎች ጋር አትቀመጥ እንዲሁም ሥጋ ከማይጠግቡ ጋር፥ ሰካራሞችና ሆዳሞች ይደኸያሉና፥ የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና። የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት። እውነትን ገንዘብህ አድርግ፥ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም ግዛ። የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት። ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዐይኖችህም መንገዴን ይውደዱ። ሴተኛ አዳሪ የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥ ዘማዊትም ሴት የጠበበች ጉድጓድ ናትና። እንደ ሌባ ታደባለች የእምነተቢሶችንም ቍጥር ታበዛለች። ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቁሰል ለማን ነው? የዐይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ሳይታክቱ ለሚሞክሩ አይደለምን? ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት ሲቀላ፥ መልኩም በብርጭቆ ሲያንጸባርቅ፥ እየጣፈጠም ሲገባ። በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያሰራጫል። ዐይኖችህ ልዩ ነገሮችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በመርከብም ምሶሶ ላይ እንደ ተኛ። መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፥ ደበደቡኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እፈልጋለሁ ትላለህ። በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትመኝ፥ ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ተንኮልን ትናገራለችና። ቤት በጥበብ ይሠራል፥ በማስተዋልም ይጸናል፥ በእውቀት የቤት ክፍሎች በከበረውና ባማረው ሀብት ሁሉ ይሞላሉ። ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥ አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል። በመልካም አመራር ጦርነትን ትመራለህ፥ ብዙ ምክር ባለበትም ድል ይገኛል። ጥበብ ለሞኝ ሰው ከፍ ብላ የራቀች ናት፥ በከተማውም በር ላይ መናገር አይችልም። ክፉ ለማድረግ የሚያውጠነጥን፥ ተንኰለኛ ይባላል። የሞኝ እቅድ ኃጢአት መሥራት ነው። ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል። በመከራ ቀን ብትዝል፥ በእርግጥም ጉልበትህ ትንሽ ነው ማለት ነው። ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፥ ለመታረድ የተወሰነባቸውን አድን። እነሆ፥ ይህን አላውቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን? ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፥ ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው። ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፥ ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም። እንደ ክፉ ሰው በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፥ ማደሪያውንም አታውክ። ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፤ ደግሞም ይነሣል፥ ክፉዎችን ግን መጥፎ ነገር ሲገጥማቸው ይወድቃሉ። ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥ ጌታ ይህንን አይቶ እንዳያዝንብህ፥ ቁጣውንም ከእርሱ ላይ እንዳያነሣ። በክፉ አድራጊዎች የተነሣ አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና። ለክፉ ሰው የወደፊት ተስፋ የለውምና፥ የክፉዎች መብራት ይጠፋልና። ልጄ ሆይ፥ ጌታንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ። መከራቸው ድንገት ይነሣልና፥ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፥ የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፥ ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም። የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፥ ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም። ሰይፈ መዓቱ ብትሳል ግን ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፥ ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች። እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው። በፍርድ ላይ ማዳለት መልካም አይደለም። ክፉዉን፦ “ጻድቅ ነህ” የሚለውን ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፥ የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥ በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች። በቀና ነገር የሚመልስ በፍቅር ይሰማል። ሥራህን በውጭ አሰናዳ፥ ለራስህ በእርሻ ውስጥ አዘጋጀው፥ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ። በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥ በከንፈርህም አታባብለው። እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥ እንደ ሥራውም እበቀለዋለሁ አትበል። በሰነፍ ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ። እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል። ተመለከትሁና አሰብሁ፥ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ። ትንሽ መተኛት፥ ትንሽ ማንቀላፋት፥ ለማረፍ እጅህን ታጥፋለህ፥ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። (በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል)። እነኚህም የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የገለበጧቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው። የእግዚአብሔር ክብር በምሥጥራዊ መንገድ ነገርን ማከናወን ነው፥ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው። እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም። ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል። ከንጉሥ ፊት ክፉ ሰዎችን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች። በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላላቆችም ስፍራ አትቁም፥ ዐይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ፦ “ወደዚህ ከፍ በል” ብትባል ይሻልሃልና። ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለሙግት ወደ ሽንጎ ፈጥነህ አትውጣ፥ ሙግትህን ከባልንጀራህ ጋር በቀጥታ ፈጽም፥ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥ የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ ስምህንም ለሁልጊዜ እንዳያጠፋው፤ በአግባብ የተነገረ ቃል፥ በብር ፃሕል ላይ እንደተቀመጠ ወርቅ ነው። የሚሰማን ጆሮ የሚገሥጽ ጠቢባዊ ምክር፥ እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቁ ነው። ለላኩት የታመነ መልእክተኛ፥ በመከር ወራት ደስ እንዲሚያሰኝ የውርጭ ጠል ነው፥ የጌታውን ነፍስ ያሳርፋልና። ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው። በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ ገር ምላስ አጥንትን ይሰብራል። በጣም እንዳትጠግብና እንዳትተፋው፥ ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ። እንዳይሰለቸውና እንዳይጠላህ፥ አዘውትረህ ወደ ባልንጀራህ ቤት አትሂድ። በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ቀስት ነው። ከሃዲን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው። ባዘነ ሰው ላይ የሚዘምር፥ በብርድ ቀን ልብስን እንደሚገፍና በቁስልም ላይ ሆምጣጤ እንደሚጨምር ሰው ነው። ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፥ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና፥ ጌታም ይሸልምሃልና። የሰሜን ነፋስ ዝናብ ያመጣል፥ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል። ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። የቀዘቀዘ ውኃ ለደረቀ ጉሮሮ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምሥራች እንዲሁ ነው። በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ምንጭና እንደ ተበከለ ኩሬ ነው። ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፥ ክቡር ነገሮችን መፈለግ ግን የሚያስከብር ነው። ራሱን መቆጣጠር የማይችል ሰው፥ ቅጥር እንደሌለው እንደ ፈረሰ ከተማ ነው። በረዶ በበጋ ዝናብም በመከር እንደማይፈልግ ሁሉ፥ እንዲሁም ለሞኝ ክብር አይገባውም። ወዲያና ወዲህ እንደሚበርር ድንቢጥ ወይም ጨረባ፥ እንዲሁም ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም። አለንጋ ለፈረስ፥ ልጓም ለአህያ፥ በትርም ለሞኝ ጀርባ ነው። አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሞኝ እንደ ሞኝነቱ አትመልስለት። ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሞኝ እንደ ሞኝነቱ መልስለት። በሞኝ አማካኝነት መልእክት የሚልክ፥ እግሮቹን ይቈርጣል፥ ግፍንም ይጠጣል። በምሳሌ የሚናገር ሞኝ፥ እንደተንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች ነው። ለሞኝ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው። በሞኝ የሚነገር ምሳሌ፥ በሰካራም እጅ እንዳለ እሾኽ ነው። ሞኝን ወይንም አላፊ አግዳሚውን የሚቀጥር ሰው ነው፥ ሁሉን እንደሚያቆስል አዳኝ ነው። ወደ ሞኝነቱ የሚመለስ ሰው፥ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ነው። ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኽውን? ከእርሱ ይልቅ ሞኝ ተስፋ አለው። ሰነፍ ሰው፦ “አንበሳ በመንገድ ላይ አለ፥ አንበሳ በጎዳናዎች ላይ አለ” ይላል። መዝጊያ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ሰነፍ ሰው በአልጋው ላይ ይገላበጣል። ሰነፍ ሰው እጁን ወደ ሳህን ያጠልቃል፥ ወደ አፉም መመለስ ለእርሱ ድካም ነው። ሰነፍ ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል። በማይመለከተው ገብቶ የሚሟገት፥ ውሻን በጆሮው እንደሚይዝ ነው። ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥ ባልንጀራውን የሚያታልል፦ “ስቀልድ ነው” የሚል ሰውም እንዲሁ ነው። እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፥ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል። ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቁጡ ሰው ጠብን ያበዛል። የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጉርጆች ድረስ ይወርዳል። ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው። ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል። በልቡ ሰባት ርኩሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው። ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል። ጉድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል። ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፥ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል። ቀኑ ምን እንደሚያመጣ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። ሌላ ያመስግንህ እንጂ ከአንተ አፍ አይውጣ፥ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይሁን። ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም እንዲሁ፥ ከሁለቱ ግን የሞኝ ቁጣ ይከብዳል። ቁጣ ጭካኔን ያስከትላል፥ ንዴትም እንደ ጎርፍ ነው፥ በቅንዓት ፊት ግን ማን መቆም ይችላል? ግልጽ ተግሣጽ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። የወዳጅ ማቁሰል ለክፉ አይሰጥም፥ የጠላት መሳም ግን የውሸት ነው። የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፥ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር እንኳ ጣፋጭ ነው። ከቦታው ርቆ የሚሄድ ሰው ከጎጆዋ ርቃ እንደምትበርር ወፍ ነው። ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፥ ነፍስም በወዳጅ ምክር ደስ ይላታል። ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፥ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፥ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ። ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፥ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይሄዱና ይጐዳሉ። ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ ሰው የተዋሰውንም ለመያዣነት አስቀረው። በማለዳ ባልንጀራውን በታላቅ ድምጽ የሚባርክ ሰው እንደሚራገም ያህል ነው። በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፥ እርሷንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው። ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን እንዲሁ። በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል። ውኃ ፊትን እንደሚያሳይ፥ እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል። ሲኦልና ጥፋት እንደማይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዐይን አይጠግብም። ብር በእሳት ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፥ ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል። ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ሞኝነቱ ከእርሱ አይርቅም። የበጎችህን ሁኔታ አስተውለህ እወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፥ ሃብት ለዘለዓለም አይኖርምና፥ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና። ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥ ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ በጎች ለልብስህ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ። ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ ለሴት አገልጋዮችህ ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል። ክፉ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፥ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል። አገሪቱ ዓመፀኛ ስትሆን መሪዎችዋ ብዙ ሆኑ፥ በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል። ድሆችን የሚያስጨንቅ ድሃ ሰው እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው። ሕግን የሚተዉ ሰዎች ክፉዎችን ያመሰግናሉ፥ ሕግ ጠባቂዎች ግን ይቃወሟቸዋል። ክፉዎች ሰዎች ፍትሕን አያስተውሉም፥ ጌታን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ። በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ሀብታም ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል። ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፥ ራሳቸውን የማይቆጣጠሩትን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል። ሀብቱን በአራጣ ብዛትና በቅሚያ የሚያበዛ ለድሀ ለሚራራ ያከማችለታል። ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ እንኳን ሳይቀር አስጸያፊ ናት። ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥ እርሱ ወደ ጉድጓዱ ይወድቃል፥ ፍጹማን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ። ሀብታም ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፥ አስተዋይ ድሀ ግን ይመረምረዋል። ጻድቃን ድል ባደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ፥ ክፉዎች ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ ግን ሰው ይሸሸጋል። ጥፋቱን የሚሰውር አይለማም፥ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። ሁልጊዜ የሚጠነቀቅ ሰው ብፁዕ ነው፥ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል። በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መሪ እንደሚያገሣ አንበሳና እንደ ተራበ ድብ ነው። አእምሮ የጐደለው መኰንን ትልቅ ግፈኛ ነው፥ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል። የሰው ደም ያለበት ሰው እስከጉድጓድ ይሸሻል፥ ማንም አያስጠጋውም። በቅንነት የሚሄድ ይድናል፥ በጠማምነት የሚሄድ ግን ወዲያው ይወድቃል። ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፥ የማይረቡ ሰዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል። የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፥ ሀብታም ለመሆን የሚቸኩል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ማዳላት መልካም አይደለም፥ አንዳንድ ሰው ግን ለቁራሽ ሲል ጥፋት ይፈጽማል። ምቀኛ ሰው ሀብታም ለመሆን ይጣደፋል ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም። በምላሱ ከሚሸነግል ይልቅ ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል። ከአባቱና ከእናቱ እየሰረቀ፦ “አላጠፋሁም” የሚል የአጥፊ ሰው ባልንጀራ ነው። ስግብግብ ሰው ክርክርን ያነሣሣል፥ በጌታ የሚታመን ግን ይጠግባል። በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሞኝ ነው፥ በጥበብ የሚመላለስ ግን ይድናል። ለድሀ የሚሰጥ አያጣም፥ በድሆች ላይ ዐይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል። ክፉዎች በተነሡ ጊዜ ሰዎች ይሸሸጋሉ፥ እነርሱ በጠፉ ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ። ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም። ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል፥ ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ግን ሕዝብ ያለቅሳል። ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፥ አመንዝሮችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያጠፋል። ንጉሥ በፍትሕ አገሩን ያጸናል፥ ጥቅም የሚወድድ ግን ያፈርሰዋል። ወዳጁን በሽንገላ የሚናገር ሰው ለእግሩ ወጥመድን ይዘረጋል። ክፉ ሰው በጥፋቱ ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ደስ ይለዋል፥ እልልም ይላል። ጻድቅ የድሆችን መብት ይመለከታል፥ ክፉ ሰው ግን ይህንን አያስተውልም። ፌዘኞች ከተማቸውን ያቃጥላሉ፥ ጠቢባን ግን ቁጣን ያስቀራሉ። ጠቢብ ከሞኝ ጋር ቢጣላ፥ ሞኙ ወይም ይቈጣል ወይም ይስቃል፥ ዕረፍትም አይኖርም። ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ንጹሑን ሰው ይጠላሉ፥ እንዲሁም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ። ሞኝ ሰው ቁጣውን ሁሉያለችግር ያወጣል፥ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል። አስተዳዳሪ ለሐሰተኛ ነገር ትኩረት ቢሰጥ፥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፀኞች ይሆናሉ። ድኀና ግፈኛ ተገናኙ፥ ጌታ የሁለቱንም ዐይን ያበራል። ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥ ዙፋኑ ለዘለዓለም ይጸናል። በትርና ተግሣጽ ጥበብን ይሰጣሉ፥ ያልተቀጣ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል። ክፉ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙ ሕግ መጣስ ይበዛል፥ ጻድቃን ግን ውደቀታቸውን ያያሉ። ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፥ ለነፍስህም ደስታን ይሰጣታል። ራእይ ከሌለ ሕዝብ ከመስመር ይወጣል፥ ሕግን የሚጠብቅ ግን ብፁዕ ነው። አገልጋይ በቃል ብቻ አይገሠጽም፥ ቢያስተውል እንኳ አይመልስምና። በችኮላ የሚናገረውን ሰው አየኸውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። ባርያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል። ቁጡ ሰው ክርክርን ያነሣሣል። ወፈፍተኛ ሰውም ኃጢአትን ያበዛል። ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፥ መንፈሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል። ከሌባ ጋር የሚካፈል ነፍሱን ይጠላል፥ መርገምን ይሰማል፥ ነገር ግን ምንም አይገልጥም። ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፥ በጌታ የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። ብዙ ሰዎች የሹምን ፊት ይሻሉ፥ የሰው ፍርድ ግን ከጌታ ዘንድ ነው። ኃጢአተኛ በጻድቃን ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ በቀና መንገድ የሚሄደውም በኀጥኣን ዘንድ አስጸያፊ ነው። የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል። ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል፦ እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኝም። ጥበብንም አልተማርሁም፥ ቅዱሱንም አላወቅሁትም። ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው? የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ የጠራ ነው፥ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው። እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር። ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፥ ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፥ ድህነትንና ሀብታምነትን አትስጠኝ፥ የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦ “ጌታስ ማን ነው?” እንዳልል፥ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ የአምላኬንም ስም እንዳላረክስ። እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን ባርያን በጌታው ፊት በሐሰት አትተች። አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማያመሰግን ትውልድ አለ። ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ግን ያልጠራ ትውልድ አለ። በትዕቢት ከፍ ከፍ ያሉ ዐይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ። ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ለማጥፋትና ለመጨረስ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ። አልቅት “ስጠን ስጠን” የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት። ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም፦ “በቃን” የማይሉ ናቸው፥ እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን፥ ውኃ የማትጠግብ ምድርና፦ “በቃኝ” የማትል እሳት ናቸው። በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዐይን የሸለቆ ቁራዎች ይጐጠጉጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል። ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም። እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው። የአመንዝራ ሴት መንገድም እንዲሁ ነው። በልታ አፍዋን የምታብስ፦ “አንዳች ክፉ ነገርም አላደረግሁም” የምትል። በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም። አገልጋይ በነገሠ ጊዜ፥ ሞኝ እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥ የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት አገልጋይም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ። በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፥ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፥ ገብረ ጉንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ። ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ። አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸውም ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ። እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል። መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፥ የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ ማንንም ፈርቶ የማይመለስ፥ በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፥ መንጋን የሚመራ አውራ ፍየል፥ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ። ከፍ ከፍ በማለት የተሞኝህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን። ወተት መናጥ ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣል፥ እንዲሁም ቁጣን መጐተት ጠብን ያመጣል። እናቱ ያስተማረችው የማሣ ንጉሥ፥ የልሙኤል ቃል። ልጄ ሆይ፥ ምንድነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው? ጉልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥ መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ። ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ሊጠጡ፥ መሳፍንትም፦ ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ሊሉ አይገባም፥ ጠጥተው ሕግን እንዳይረሱ፥ የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ። ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፥ ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጉስቁልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ። ስለ ዲዳው ተናገር፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ። ተናገር፥ በእውነትም ፍረድ፥ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ። ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል። የባሏ ልብ ይታመንባታል። መልካም ነገር አይጐድልበትም። ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። የበግ ጠጉርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። እርሷ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፥ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። ገና ሳይነጋ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለአገልጋዮችዋም ሥራ ትሰጣለች። እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፥ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች። ማትረፍዋን ታስተውላለች፥ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። ለቤትዋ ሰዎች ብርድን አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና። ለራስዋም የአልጋ ልብስ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች። ባሏ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። የበፍታ ልብስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፥ በሚመጣውም ዘመን ላይ ትስቃለች። በጥበብ ትናገራለች፥ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጉን ነሽ ይሏታል፥ ባሏ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል፦ “መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።” ደም ግባት ሐሰት ነው፥ ውበትም ከንቱ ነው፥ ጌታን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች። ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት። በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድነው? ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘለዓለም ናት። ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኩላለች። ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፥ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል። ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፥ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ። ነገር ሁሉ ያደክማል፥ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፥ ዐይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። የሆነው ነገር ወደፊትም የሚሆነው ነው፥ የተደረገውም ነገር ወደ ፊት የሚደረገው ነው፥ ከፀሐይም በታች ምንም አዲስ ነገር የለም። ማንም፦ እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ማለት ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል። ለፊተኞቹም ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፥ ለኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ። ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ ይደክሙባት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጣት ከባድ ጥረት ናት። ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም መከተል ነው። ጠማማ ሊቀና አይችልም፥ የጐደለም ሊቈጠር ዘንድ አይችልም። እኔ በልቤ፦ እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፥ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ። ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ ይህም ደግሞ ነፋስን መከተል እንደሆነ አስተዋልሁ። በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፥ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና። እኔ በልቤ እራሴን እንዲህ አልኩት፦ “ና ደስታን በማቅመስ ልፈትንህ፥ መልካምንም ቅመስ፤” ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። “ሳቅን፦ ዕብደት፥ ደስታንም፦ ዋጋ ቢስ” አልሁት። ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት አላዋቂነትንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ፤ ይህም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት የሚገባ መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስካይ ድረስ ነው። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ገነባሁ፥ ወይንንም ተከልሁ፥ የአትክልት ሥፍራዎችንና ገነትን አሰናዳሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ሠራሁ። ወንዶችንና ሴቶችን ባርያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባርያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችን፥ ለሰዎች ልጆች ተድላ የሚሰጡ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸናች። ዐይኖቼ የፈለጉትን እንዳያዩ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና አለማወቅን ለመመርመር ወሰንኩ፥ በፊት የተደረገውን መድገም ካልሆነ በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከአለማወቅ እንደሚበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ሆኖም የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፦ በአላዋቂ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘለዓለም የሚሆን የጠቢብና የአላዋቂ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል! ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ይሠለጥንበታል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እኔም ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተመልሼ ልቤን ተስፋ አስቈረጥሁት። ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም ጉዳት ነው። ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ መጨነቅ የሰው ልጅ ምን ጥቅም ያገኛል? ዘመኑ ሁሉ ስቃይ፥ ጥረትም ትካዜ ነው፥ ልቡም በሌሊት አያርፍም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው በመብላትና በመጠጣት፥ እንዲሁም በመጣር ከሚያገኘው ደስታ የሚሻለው ነገር የለም፥ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደተሰጠ አየሁ። ያለ እርሱ ፈቃድ ማን ይበላል፥ ማንስ ተድላን ይቀምሳል? እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፥ ለኃጢአተኛው ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ሥራን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለልደት ጊዜ አለው፥ ለሞትም ጊዜ አለው፥ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፥ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፥ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመገንባትም ጊዜ አለው፥ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፥ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፥ ድንጋይን ለመበተን ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፥ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፥ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፥ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፥ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፥ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፥ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፥ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድነው? እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለማዊነትን በልቡ ሰጠው። ሰው ደስ ከሚሰኝበትና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚፈጽምበት በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው። እግዚአብሔር የሚያደርገው ሁሉ ለዘለዓለም እንደሚኖር አወቅሁ፥ ምንም የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስለት የለም፥ እግዚአብሔርም ሰዎች ይፈሩ ዘንድ አደረገ። አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፥ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል። ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ክፋት፥ በጽድቅም ስፍራ ክፋት እንዳለ አየሁ። እኔም በልቤ፦ ለማንኛውም ነገርና ለማንኛውም ሥራ ጊዜ አለውና በጻድቅና በክፉ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ። እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች፦ እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ። የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፥ አንድ ዓይነት መጨረሻ ይገጥማቸዋል፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፥ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፥ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፥ ሁሉም ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። የሰው ልጆች መንፈስ ወደ ላይ እንደሚወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚሰኝበት ነገር በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፥ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውንስ ወስዶ ማን ያሳየዋል? እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ፥ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፥ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፥ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል። ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራም ዘንድ ቅንዓት እንደሚያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። አላዋቂ እጆቹን አጥፎ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ፥ በእርጋታ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል። እንደገና፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። አንድ ሰው ብቻውን ይኖራል፥ ማንም አብሮት የለም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙም መጨረሻ የለውም፥ ዐይኖቹም ሳይቀሩ ሀብትን አይጠግቡም። እንግዲህ ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው። ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፥ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፥ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? አንዱም አንድን ሰው ቢያሸንፍ፥ ሁለቱ ግን ይቋቋሙታል፥ በሦስትም የተገመደ ገመድ በፍጥነት አይበጠስም። ድኀና ጠቢብ ወጣት ተግሣጽን መቀበል ካቃተው አላዋቂ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። ምንም እንኳን ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከእስር ቤት ለመንገሥ ወጥቶአልና። ከፀሐይ በታች የሚሄዱት ሕያዋን በሙሉ እርሱን የተካውን ወጣት ሲከተሉ አየሁ። ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ ስፍር ቍጥር አልነበራቸውም፥ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፥ ለመስማት መቅረብ ከአላዋቂዎች መሥዋዕት ይበልጣልና፥ እነርሱም ክፉ እንደሚያደርጉ አያውቁምና። እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትቸኩል፥ ልብህም በእግዚአብሔር ፊት ቃልን ለመናገር አይቸኩል፥ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፥ እንዲሁም የአላዋቂም ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። አላዋቂዎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፥ የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ ካለመፈጸም ባትሳል ይሻላል። አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲወስድህ አትፍቀድለት፥ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል፥ እግዚአብሔር በቃልህ ለምን ይቈጣ? ለምንስ የእጅህንም ሥራ ያጥፋ? ብዙ ሕልም ባለበት፥ እንዲሁም ብዙ ቃል ባለበት፥ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፥ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ። ከፍ ካለው ባለ ሥልጣን በላይ ሌላ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አትደነቅ። በጠቅላላው ይህ ለአገሩ ይጠቅማል፤ ንጉሥም ከእርሻ ይጠቀማል። ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፥ ሀብትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፥ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? ጥቂትም በላ ብዙ፥ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል። ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፥ ራስን ለመጉዳት በባለቤቱ ዘንድ የተቀመጠ ሀብት። ያችም ሀብት በክፉ ነገር ትጠፋለች፥ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፥ ከጥረቱም በእጁ ሊወስደው የሚችለው ምንም ነገር የለም። ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፥ እንደመጣ እንዲሁ ይሄዳል፥ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድነው? ዘመኑን በሙሉ በጨለማ፥ በከባድ ብስጭት፥ በደዌና በቁጣ ይጨርሳል። እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ቢኖር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሲበላና ሲጠጣ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ሲለው ነው፥ ይህ እድል ፈንታው ነውና። እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ሀብትና ንብረት መስጠቱ፥ ከእርሷም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ሥልጣን መስጠቱ ነው፥ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር በልቡ ደስታን እስካኖረ ድረስ፥ እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግም አያስብም ። ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ሀብትን፥ ንብረትንና ክብርን ሰጠው፥ ከወደደውም ነገር ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር ሥልጣን አልሰጠውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር፥ ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነገር ግን ነፍሱ መልካምን ነገር ባትጠግብ፥ መቃብርንም ባያገኝ፥ ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። በከንቱ መጥቷል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፥ ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፥ ቢሆንም እርሱ ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። ለሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር፥ ነገር ግን መልካምን ባያይ፥ ሁሉም ወደ አንድ ስፍራ ይሄድ የለምን? የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። ጥበበኛ ከአላዋቂ ምን የተሻለ ጥቅም ያገኛል? ሕይወትን መምራት የሚያውቅ ድሀስ ምን ይጠቀማል? በዐይን ማየት በምኞት ከመቅበዝበዝ ይሻላል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የሆነው ነገር በሙሉ ስሙ አስቀድሞ ተጠርቷል፥ ሰውም ማን እንደሆነ ታወቀ፥ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር መፋረድ አይችልም። ንግግር በበዛ መጠን፥ ከንቱነትም ይበዛል፤ ለሰውስ ምን ይጠቅመዋል? ሰው በከንቱ የሕይወቱ ቀናት ቍጥር ና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ለሰው ማን ይነግረዋል? ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፥ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፥ የአላዋቂዎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። ሰው የአላዋቂዎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ከድስት በታች እንደሚቀጣጠል እሾህ ድምፅ የአላዋቂ ሳቅ እንዲሁ ነው፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፥ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፥ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፥ ቁጣ በአላዋቂ ብብት ያርፋልና። ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፥ ይህንን ነገር የመትጠይቀው ክጥበብ ተነሥተህ አይደለምና። ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፥ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፥ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን መስጠትዋ ነው። የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንንም ያንንም እንዲሁ ሠርቶአል። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ክፉም በክፋቱ ረጅም ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ ለምን ራስህን ታጠፋለህ? እጅግ ክፉ አትሁን፥ አላዋቂም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ ለምን ትሞታለህ? እግዚአብሔርን የሚፈራ በሁሉም ይዋጣለታልና ይህን ብትይዝ፥ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው። በከተማ ከሚኖሩ ከዐሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ፥ ምንም ኃጢአት የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። አገልጋይህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፥ አንተ ደግሞ ሌሎችን የረገምክበትን ጊዜ ልብህ ያውቃልና። ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርሷ ግን ከእኔ ራቀች። የሆነው ነገር ራቀ፥ እጅግም ጠለቀ፥ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ ትርጒም እፈልግ ዘንድ፥ ክፋትም አላዋቂነት፥ አላዋቂነትም እብደት እንደሆነ አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርሷም ልብዋ ወጥመድና መረብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፥ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርሷ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ ትርጒም እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፥ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ። ጠቢብን የሚመስለው? የነገሮችንስ ትርጒም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድንዳኔ ትለውጣለች። እኔ፦ በመለኮታዊ መሐላ መሠረት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ለመራቅ አትቸኩል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፥ “ይህንስ ለምን ታደርጋለህ?” ማን ይለዋል? ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉ ነገር አይገጥመውም፥ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። የሚሆነውንም አያውቅም፥ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? መንፈስን ለማገድ በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፥ በሞቱም ቀን ላይ ሥልጣን የለውም፥ በጦርነትም ውስጥ መሰናበቻ የለም፥ ክፋትም ሠሪውን አያድነውም። ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ለተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፥ ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፥ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይበየንምና በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ክፉን መሥራት ጠነከረ። ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት መልካም እንደሚሆን አውቃለሁ፥ ለክፉ መልካም አይሆንም፤ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም። በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በክፉዎች ላይ የሚደረገው የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው የሚደርስላቸው ክፉዎችም አሉ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። ከመብላትና ከመጠጣት፥ ደስም ከመሰኘት በቀር ለሰው ልጅ ከፀሐይ በታች ሌላ ምንም መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፥ ይህም እግዚአብሔር ከፀሐይም በታች በሰጠው በሕይወቱ ዘመን በድካሙ ከእርሱ ጋር ይኖራል። ጥበብን አውቅ ዘንድ፥ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን በሰጠሁ ጊዜ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እርሱም ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ሰው ማግኘት አለመቻሉን፥ ሰውም በመፈለግ እጅግ ቢደክምም መርምሮ አለማግኘቱን ነው፥ ደግሞም ጠቢብ ሰው አውቀዋለሁ ቢልም እንኳን ይህንን ለማግኘት አይችልም። ጻድቃንና ጠቢባን፥ ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅርም ሆነ ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፤ ሁሉም በፊታቸው ነው። የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ መልካሙ ሰው እንደ ኃጢአተኛው፥ የሚምለው ሰው መሐላን እንደሚፈራው ነው። ለሁሉም አንድ ዓይነት ዕጣ ክፍል መኖሩ ከፀሐይ በታች በሚደረገው ነገር በሙሉ ይህ ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ በክፋት ተሞልታለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ውስጥ ይኖራል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳችም ነገር አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ከወዲሁ ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘለዓለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ፍልምያ ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ሀብትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ። ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርሷም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፥ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፥ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። እኔም፦ ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፥ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ። በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፥ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል። የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፥ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል። የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው። ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው። ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቁጣ የተነሣብህ እንደሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ፥ ባለ ጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። ባርያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባርያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ። ጉድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል። ብረት ቢደነዝዝ ሰውም ባይስለው ኃይልን ሊያበዛ ይገባዋል፥ ጥበብ ግን ሥራውን ለማከናወን ትጠቅመዋለች። ደጋሚ ሳይደግምባት እባብ ብትነድፍ ለደጋሚው ትርፍ የለውም። የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፥ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል። የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩ ፍጻሜም ክፉ እብደት ነው። ሰነፍ ቃሉን ያበዛል፥ ሰው ግን የሚሆነውን አያውቅም፥ ከእርሱስ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል? የሰነፍ ሥራ ያደክመዋል ወደ ከተማ መሄድ አያውቅምና። ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ! ንጉሥሽ የከበረ ልጅ የሆነ፥ ለብርታት እንጂ ለስካር ያይደለ በጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። ተግባር በመፍታት ጣራው ይዘብጣል፥ በእጅም መታከት ቤት ያፈስሳል። እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል። የሰማይ ወፍ ቃሉን ይወስደዋልና፥ ባለ ክንፎችም ነገሩን ይናገራሉና በልብህ አሳብ እንኳ ቢሆን ንጉሥን አትስደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትስደብ። እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው፥ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኛዋለህና። ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታን ክፈል፥ በምድር ላይ የሚሆነውን ክፉ ነገር ምን እንደሆነ አታውቅምና። ደመናት ዝናብ በሞሉ ጊዜ በምድር ላይ ያፈስሱታል፥ ዛፍም ወደ ደቡብ ወይም ወደ ሰሜን ቢወድቅ፥ ዛፉ በወደቀበት ስፍራ በዚያ ይኖራል። ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም። የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፥ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም። ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፥ በማታም እጅህን አትተው። ብርሃን ጣፋጭ ነው ፀሐይንም ማየት ለዐይን መልካም ነው። ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ይበለው፥ ሆኖም የጨለማውን ዘመን ያስብ፥ ብዙ ቀን ይሆናልና። የሚመጣው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው። አንተ ጐበዝ፥ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ ዐይኖችህም በሚያዩት ሂድ፥ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ። ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ጭንቀትን አርቅ፥ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ። የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፥ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፥ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፥ ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፥ የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፥ ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፥ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ፥ ሰው ወደ ዘለዓለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፥ የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኩስኩስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጉድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፥ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ። የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፥ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። ከዚህም ሁሉ በላይ፥ ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ስማ፥ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፥ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል። የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፥ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፥ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና። ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና። ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፥ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፥ ንጉሥ ወደ ቤቱ አገባኝ፥ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፥ በቅንነት ይወድዱሃል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ውብም ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንኩ አትዩኝ፥ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፥ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም። ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ? አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ። የጉንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቁ ድሪ ያማረ ነው። ባለ ብር ጉብጉብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን። ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው። ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፥ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፥ ዐይኖችሽም እርግቦች ናቸው። ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፥ አልጋችንም ለምለም ነው። የቤታችን ሠረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው። እኔ የሳሮን ጽጌረዳ የቈላም አበባ ነኝ። በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በልጃገረዶች መካከል ናት። በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በጐልማሶች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው። ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና። ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አስምላችኋለሁ። እነሆ፥ የውዴ ድምፅ! በተራሮች ላይ ሲዘልል በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፥ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የዋኔዋም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፥ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ። በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥ ድምፅሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥ ድምፅሽንም አሰሚኝ። ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ትናንሾችን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን። ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፥ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል። ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፥ በወጣ ገባ ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል። ሌሊት በመኝታዬ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፥ ፈለግሁት አላገኘሁትም። እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፥ ፈለግሁት አላገኘሁትም። ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፥ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም። ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም ወደ እናቴም ቤት ወደ ወለደችኝም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈንጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሡትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አስምላችኋለሁ። መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረበዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት? እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፥ ከእስራኤል ኃያላን መካከል ስድሳ ኃያላን በዙሪያው ናቸው። ሁሉም ሰይፍ የያዙና ጦርነት የለመዱ ናቸው፥ በሌሊት ከሚከሰት አደጋ የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ። ንጉሡ ሰሎሞን መቀመጫ ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ። ምሰሶቹን የብር፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፥ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው። እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት፥ ውጡ፥ እናቱ በሰርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ። ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፥ እነሆ፥ አንቺ ወብ ነሽ፥ ዐይኖችሽ በመሸፈኛሽ ውስጥ ርግቦች ናቸው ፥ ጠጉርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው። ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው ። ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ አፍሽም ያማረ ነው፥ በመሸፈኛሽ ውስጥ ጉንጭና ጉንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። አንገትሽ ለጦር ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፥ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል። ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው። ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ። ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም። ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፥ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች። እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ልቤን በደስታ አሳበድሽው፥ አንድ ጊዜ በዐይኖችሽ፥ ከአንገትሽስ ድሪ በአንዱ ልቤን በደስታ አሳበድሽው። እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ! ሙሽራዬ ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠበጠባል፥ ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ መዓዛ ነው። እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተቈለፈ ገነት፥ የታተመም ምንጭ ናት። ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ዕፀ ሕና ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥ ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋ፥ ከልዩ ልዩ የዕጣን ዕፀዋት ጋር፥ ከርቤና እሬት ከምርጥ ቅመሞች ሁሉ ጋር። የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጉድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስሱ ወንዞች። የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፥ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱውም ይፍሰስ፥ ውዴ ወደ ገነቱ ይግባ ምርጡንም ፍሬ ይብላ። እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥ ከርቤዬን ከቅመሜ ጋር ለቀምሁ፥ እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥ የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ። ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፥ ጠጡ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ እስክትረኩ ድረስ ጠጡ ። እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፥ የውዴ ድምፅ ነው፥ እርሱም ያንኳኳል፥ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ የእኔ እንከን የለሽ፥ ራሴ በጠል፥ ጸጉሬም በሌሊት ነጠብጣብ ርሶአል። ቀሚሴን አወለቅሁ፥ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፥ እንዴት አሳድፈዋለሁ? ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ። ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፥ እጆቼ በደጁ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠባጠቡ። ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከመራቁ የተነሣ ደነገጠች፥ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፥ ጠራሁት፥ ነገር ግን አልመለሰልኝም። ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፥ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፥ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አስምላችኋለሁ፥ ውዴን ያገኛችሁት እንደሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት። አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ፍቅረኛሽ ምን አለው? ይህን የሚያህል የምታስምይን? ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ፍቅረኛሽ ምን አለው? ውዴ ብሩህና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው። ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፥ ጸጉሩ የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራም ጥቁር ነው። ዐይኖቹ በውሃ ምንጮች አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው። ጉንጩና ጉንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፥ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ። እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ ያለበት የወርቅ ቀለበት ናቸው፥ አካሉ በሰንፔር ያጌጠ የዝሆን ጥርስ ነው። እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ ላይ የተመሠረቱ የዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፥ መልኩ እንደ ሊባኖስ፥ እንደ ዝግባ ዛፍ ምርጥ ነው ። አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፥ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው። ውድሽ ወዴት ሄደ? አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ፥ ከአንቺ ጋር እንፈልገው ውድሽ ወዴት ፈቀቅ አለ? ውዴ በገነቱ መንጋውን ያሰማራ ዘንድ አበባውንም ይሰበስብ ዘንድ ወደ ሽቱ መደብ ወደ ገነቱ ወረደ። እኔ የውዴ ውዴም የእኔ ነው፥ በሱፉ አበባ መካከል መንጋውን ያሰማራል። ወዳጄ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ውብ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌምም ያማርሽ ነሽ፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ። አውከውኛልና ዐይኖችሽን ከፊቴ መልሺ፥ ጠጉርሽ ከገለዓድ እንደ ወረደ እንደ ፍየል መንጋ ነው። ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ወጡ ሁሉ መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው። በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጉንጭና ጉንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። ስልሳ ንግሥቶች ሰማንያም ቁባቶች ቍጥር የሌላቸውም ቈነጃጅት አሉ። ርግቤ፥ የእኔ እንከን የለሽ አንዲት ናት፥ ለእናትዋ አንዲት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው ብፅዕት አሉአት፥ ንግሥቶችና ቁባቶችም አመሰገኑአት። ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት? የወንዙን ዳር ልምላሜ አይ ዘንድ፥ ወይኑ አብቦ ሮማኑም አፍርቶ እንደሆነ እመለከት ዘንድ ወደ ለውዝ ገነት ወረድሁ። ሳላውቅ ነፍሴ በከበረው ሠረገላ ላይ አስቀመጠችኝ። አንቺ ሱላማጢስ ሆይ። ተመለሽ፥ ተመለሽ፥ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርሷ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት። አንቺ ልዕልት ሆይ፥ እግሮችሽ በነጠላ ጫማ ውስጥ እንዴት ውብ ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቁዎች ይመስላሉ። እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፥ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው። አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፥ ዐይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ የሚግኙ ኩሬዎች ናቸው፥ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው ። ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፥ የራስሽም ጠጉር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል። ፍቅር ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! በተድላ ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም አስካሉን ይመስላሉ። ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፥ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። አፍሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፥ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደሆነ እንይ፥ በዚያ ፍቅሬን እሰጥሃለሁ። ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፥ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፥ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ። አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ! በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር። መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥ በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፥ እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር። ግራው ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም ባቀፈችኝ ነበር። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አስምላችኋለሁ። በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረበዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፥ በዚያ እናትህ ወለደችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ። እንደ ማኅተም በልብህ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፥ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው። ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፥ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል። እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እኅት አለችን፥ ስለ እርሷ በሚናገሩበት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት? እርሷ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፥ ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን። እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፥ በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ። ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፥ የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፥ ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር። ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፥ ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥ ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል። በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ድምፅ ይሰማሉ፥ ድምፅሽን አሰሚኝ። ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፥ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል። በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፤ በኢዮአታም፤ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ። ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፤ “ልጆች ወለድሁ፤ አሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመጹብኝ። በሬ ጌታውን፤ አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤ እስራኤል ግን አላወቀም፤ ሕዝቤም አላስተዋለም።” እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፤ በደል የሞላበት ወገን፤ የክፉ አድራጊ ዘር፤ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! ጌታን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤ ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል። ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታሞአል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኮአል። ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጉራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቁስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም። አገራችሁ ባድማ፤ ከተሞቻችሁ በእሳት የተቃጠሉ ይሆናሉ፤ ዐይናችሁ እያየ መሬታችሁ በባዕድ ይነጠቃል፤ ጠፍም ይሆናል። የጽዮን ሴት ልጅ በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ፤ በዱባ ተክል ወስጥ እንደሚገኝ ጐጆ፤ እንደ ተከበበም ከተማ ተተወች። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፤ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር። እናንተ የሰዶም ገዦች፤ የጌታን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሰዎች፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ። “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?” ይላል ጌታ። የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሰቡ እንስሳትን ስብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም። በፊቴ ለመቅረብ ስትመጡ፤ ይህን ሁሉ እንድታመጡ፤ የመቅደሴን ደጅ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤ የወር መባቻ በዓላችሁን፤ ሰንበቶቻችሁን፤ ጉባኤያችሁንና በክፋት የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ አልቻልሁም። የወር መባቻችሁንና የተደነገጉ በዓሎቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ መታገሥም አልቻልሁም። እጆቻቸሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፤ ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤ ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤ መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፤ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። “ኑና፤ እንዋቀስ” ይላል ጌታ፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል። እሺ ብትሉ፤ ብትታዘዙም የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብላችሁ ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል።” የጌታ አፍ ይህን ተናግሮአልና። ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ! ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፤ ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤ አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች! ብርሽ ዝጎአል፤ ምርጥ የወይን ጠጅሽ ውሃ ገባው፤ ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጉቦን ይወዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም። ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ “በባላንጣዎቼ ላይ ቁጣዬን እገልጣለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ። እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ ዝገትሽን ፈጽሜ አጠራለሁ፤ ጉድፍሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ። ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፤ አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤ ከዚያም የጽድቅ መዲና፤ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። ጽዮን በፍትሕ፤ በንስሓ የሚመለሱ ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይዋጃሉ። ዐመፀኞችና ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይደቅቃሉ፤ ጌታንም የሚተዉ ይጠፋሉ። ደስ በተሰኛችሁባቸው የባሉጥ ዛፎች ታፍራላችሁ፤ በመረጣችኋቸውም የአትክልት ቦታዎች ትዋረዳላችሁ። ቅጠሉ እንደ ጠወለገ ወርካ፤ ውሃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ። ብርቱ ሰው እንደ ገለባ፤ ሥራውም እንደ ብልጭታ ይሆናል፤ ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤ እሳቱንም የሚያጠፋው የለም።” የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፤ በዘመኑም ፍጻሜ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ። ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ ጌታ ተራራ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን።” ሕግ ከጽዮን፤ የእግዚአብሔር ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና። እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል። እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም። እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ ኑ፤ በጌታ ብርሃን እንመላለስ። የያዕቆብ ቤት የሆነውን፤ ሕዝብህን ትተሃል፤ እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤ እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤ ከባዕዳን ጋር ተባብረዋል። ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤ ሀብታቸውም ልክ የለውም። ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤ የሠረገሎቻቸውም ብዛት ልክ የለውም። ምድራቸው በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸው ላበጇቸው፤ ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ። ሰው ዝቅ ብሏል፤ የሰው ልጅም ተዋርዶአል፤ ስለዚህ በደላቸውን ይቅር አትበል። ከጌታ አስፈሪነት ከግርማው ሽሽ፤ ወደ ዐለቶች ሂድ፤ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ። የእብሪተኛ ሰው ዐይን ይሰበራል፤ የሰዎችም ትዕቢት ይዋረዳል፤ በዚያን ቀን ጌታ ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፤ የተኩራራውን በሙሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው። ረዥምና ከፍ ከፍ ያሉትን የሊባኖስ ዝግባዎች ሁሉ፤ የባሳንን የወርካ ዛፎች ሁሉ፤ ታላላቁን ተራራ ሁሉ፤ ከፍ ያለው ኮረብታ ሁሉ፤ ረጃጅሙን ግንብ ሁሉ፤ የተመሸገውን ቅጥር ሁሉ፤ የተርሴስን መርከቦች ሁሉ፤ የክብር ጀልባዎችን ሁሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው። የሰው እብሪት ይዋረዳል፤ የሰውም ኩራት ይወድቃል፤ በዚያን ቀን ጌታ ብቻ ከፍ ከፍ ይላል፤ ጣዖቶች ሁሉ ፈጽሞ ይወድማሉ። ጌታ ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፤ ሰዎች ከአስፈሪነቱ ከግርማውም የተነሣ፤ ወደ ዐለት ዋሻ ወደ መሬትም ጉድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ። በዚያን ቀን ሰዎች ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፤ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ። ጌታ ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፤ ሰዎች ከአስፈሪነቱ እንዲሁም ከግርማው የተነሣ፤ ወደ ድንጋይ ዋሻ፤ ወደ ዐለት ስንጣቂ ሮጠው ይገባሉ። እስትንፋስ አፍንጫው ላይ ባለች በሰው አትታመኑ፤ ከቶ ምን የሚበጅ ነገር አለው! እነሆ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፉንና ርዳታውን፤ የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤ ጀግናውንና ተዋጊውን፤ ፈራጁንና ነቢዩን፤ አስማተኛውንና ሽማግሌውን፤ የአምሳ አለቃውንና ባለ ማዕረጉን፤ አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፤ ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል። ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤ ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል። ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤ ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፤ ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፤ ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል። ሰውም በአባቱ ቤት ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፤ “አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤ ይህንንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል። እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምጽን ከፍ አድርጎ፤ “እኔ መፍትሔ አልሆንም፤ በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤ የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል። ኢየሩሳሌም ተንገዳገዳለች፤ ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው ጌታን የሚቃወም፤ የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና። የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ ወዮላቸው! ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና። የእጃቸውን ያገኛሉና። በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት ይመጣባቸዋል፤ ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ ከመንገድህም መልሰውሃል። ጌታ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦአል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቶአል። ጌታ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤ ሕዝቤን በችግር ስታደቁት፤ የድኾችንም ፊት በኀዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እንዲህ ይላል፤ የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤ ዐንገታቸውን እያሰገጉ፤ በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤ እየተቈነኑ በመራመድ፤ የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ። ስለዚህ፤ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ ቆረቆር ያመጣል፤ ጌታም ራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል። በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፤ የጠጉር ጌጡን፤ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፤ የጆሮ ጉትቻውን፤ የእጅ አንባሩን፤ የፊት መሸፈኛውን፤ የራስ መሸፈኛውን፤ ዐልቦውን፤ ሻሹን፤ የሽቶ ብልቃጡን፤ አሸን ክታቡን፤ የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፤ ያማረውን ቀሚስ፤ የውስጥ ልብሱን፤ ካባውን፤ የእጅ ቦርሳውን፤ መስታወቱን፤ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፤ የራስ ጌጡን፤ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል። በሽቶ ፈንታ ግማት፤ በሻሽ ፈንታ ገመድ፤ አምሮ በተሠራ ጠጉር ፈንታ ቡሀነት፤ ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፤ በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል። ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፤ ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ። የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች። በዚያን ቀን ሰባት ሴቶች አንዱን ወንድ ይዘው፤ “የራሳችንን ምግብ እንበላለን፤ የራሳችንንም ልብስ እንለብሳለን፤ በአንተ ስም ብቻ እንጠራና፤ ውርደታችንን አስቀርልን” ይሉታል። በዚያን ቀን የጌታ ዛፍ ቅርንጫፍ ውብና የከበረ ይሆናል፤ የምድሪቱም ፍሬ ከጥፋት ለተረፈው የእስራኤል ወገን በጽዮን የቀሩት፤ በኢየሩሳሌምም የተረፉት፤ በኢየሩሳሌም በሕይወት ከተመዘገቡት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ፤ ኩራትና ክብርም ይሆናል። ጌታ የጽዮንን ሴቶች እድፍ ያጥባል፤ ኢየሩሳሌምንም ከተነከረችበት ደም በፍርድና በሚያቃጥል መንፈስ ያነጻታል። ከዚያም ጌታ በጽዮን ተራራ ላይና በዚያ በሚሰበሰቡትም ሁሉ ላይ በቀን ደመናንና ጢስን፤ በሌሊትም የሚንበለበለውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በክብሩ ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል፤ ከቀኑ ሙቀት ጥላና መከለያ፤ ከውሽንፍርና ከዝናብም መጠጊያና መሸሸጊያ ስፍራ ይሆናል። ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤ ስለ ወዳጄ፤ ወዳጄ በለምለም ኮረብታ ላይ መሬቱን ቈፈረ፤ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤ የወይን መጭመቂያ ጉድጓድም አበጀ፤ ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ አሰበ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። “እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ። ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፤ መረጋገጫም ይሆናል። የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኩርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የወይን ቦታ የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ። ምንም ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ ድረስ፤ ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፤ መሬትን ከመሬት ጋር በማያያዝ፤ ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ! የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፤ የሚያማምሩም ቤቶች ነዋሪ ያጣሉ። ከሩብ ጋሻ የወይን ቦታ አንድ የባዶስ መስፈሪያ ያህል የወይን ጭማቂ ብቻ ይገኛል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር ተዘርቶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ብቻ ይሰጣል። የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፤ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው! በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፤ ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤ ነገር ግን ለጌታ ሥራ ቦታ አልሰጡም፤ ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም። ስለዚህ ሕዝቤ ዕውቀት በማጣቱ ይማረካል፤ መኳንንቱም በራብ ይሞታሉ፤ ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል። ስለዚህ ሲኦል ሆዷን አሰፋች፤ አፏንም ያለ ልክ ከፈተች፤ መኳንንቱና ሕዝቡ ከረብሸኞቻቸውና ከጨፋሪዎቻቸው ጋር ወደዚያ ይወርዳሉ። ሰውም ዝቅ ዝቅ ይላል፤ ሰው ይዋረዳል፤ የእብሪተኛውም ዐይን ይሰበራል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል። በጎችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደሚሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤ የበግ ጠቦቶችም በባለጠጎች ፍርስራሽ ላይ ሣር ይበላሉ። ኃጢአትን በማታለል ገመድ ለሚስቡ፤ በደልንም በሠረገላ ማሰሪያ ለሚጐትቱ ወዮላቸው! በዐይናችን እንድናይ እግዚአብሔር ይቸኩል፤ ሥራውንም ያፋጥን፤ የእስራኤልን ቅዱስ፤ የእርሱን ዕቅድ እንድናውቃት ትቅረብ፤ ትምጣም ለሚሉ ወዮላቸው!” ክፉውን መልካም፤ መልካሙን ክፉ ለሚሉ ብርሃኑን ጨለማ፤ ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፤ ጣፋጩን መራራ፤ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፤ በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው! የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፤ የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው! ጉቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፤ ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው! ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፤ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፤ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃለዋል። የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነዶአል፤ እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤ ተራሮች ራዱ፤ ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደ ተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቁጣው ገና አልተመለሰም፤ እጁም እንደ ተነሣ ነው። ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ። በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤ የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤ የወገባቸው መቀነት አይላላም፤ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም። ፍላጻቸው የተሳለ፤ ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤ የሠረገሎቻቸውም መንኮራኩሮች እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው። ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤ ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም። በዚያን ቀን እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤ ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፥ ጨለማንና መከራን ያያል፤ ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል። ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፍ ነበራቸው። በሁለት ክንፍ ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግራቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበሩ ነበር፤ እርስ በርሳቸው በመቀባበልም “ቅዱስ፤ ቅዱስ፤ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለች” ይሉ ነበር። ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ። እኔም፤ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይቷልና ጠፍቻለሁ፤ ወዮልኝ!” አልሁ። ከዚያም ከሱራፌል አንዱ፤ ከመሠዊያው ላይ የእሳት ፍም በጉጠት ወስዶ፤ ወደ እኔ እየበረረ መጣ። አፌንም በእሳቱ ነክቶ፤ “እነሆ፤ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ተሰርዮልሃል” አለኝ። ከዚያም የጌታ ድምፅ፤ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁት። እኔም፤ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ ‘መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም’ ብለህ ንገራቸው። የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሮአቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፤ በዐይናቸው አይተው፤ በጆሮአቸው ሰምተው፤ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።” እኔም፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” አልሁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፤ “ከተሞች እስኪፈራርሱና፤ የሚኖሩባቸው እስኪያጡ፤ ቤቶችም ወና እስኪሆኑና፤ ምድርም ፈጽሞ ባድማ እስክትሆን ድረስ፤ ጌታም ሰዎችን እስከሚያርቅ፤ ምድሪቱም ጨርሶ ባዶ እስክትሆን፤ ከዐሥር አንድ ሰው እንኳን በምድሪቱ ቢቀር፤ እርሱም ደግሞ ይጠፋል፤ ነገር ግን የኮምበልና የባሉጥ ዛፍ በተቈረጠ ጊዜ ጉቶ እንደሚቀር፤ ቅዱሱም ዘር እንዲሁ በምድሪቱ ጉቶ ሆኖ ይቀራል።” የዖዝያን የልጅ ልጅ፤ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። ለዳዊት ቤት፤ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፤ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። ጌታም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “‘አንተና ልጅህ ሸአር-ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤’” እንዲህም በለው፤ “‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጉማጆች፤ በሶርያና በንጉሷ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቁጣ አትሸበር።’ ሶርያ ኤፍሬምና፤ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ ‘ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።’ ልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ የሶርያ ራስ ደማስቆ፤ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በሥልሳ አምስት ዓመት ውስጥ፤ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፤ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፤ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ እንደገናም ጌታ አካዝን እንዲህ አለው፤ ‘ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከጌታ ከአምላክህ ለምን።’ አካዝ ግን፤ አልለምንም፤ ጌታንም አልፈታተንም” አለ። ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፤ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው። በዚያን ቀን ጌታ ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፤ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። እነርሱም በሙሉ መጥተው፤ በየበረሓው ሸለቆ፤ በየዐለቱ ንቃቃት፤ በየእሾኩ ቁጥቋጦና በየውሃው ጉድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። በዚያን ቀን፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፤ ማለትም በአሦር ንጉሥ፤ የራስና የእግር ጠጉራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። በዚያን ቀን፤ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። በዚያን ቀን ሺህ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺህ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፤ ኩርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። ምድሪቱ በኩርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፤ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ ኩርርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።” ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ፤ ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’ ብለህ በተለመደው በሰው ፊደል ጻፍበት። እኔም፤ ካህኑን ኡሪያንንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ታማኝ ምስክሮቼ እንዲሆኑ እጠራቸዋለሁ።” እኔም ወደ ነቢዪቱ ሄድሁ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጌታም፤ እንዲህ አለኝ፦ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽባዝ ብለህ ጥራው። ሕፃኑም፤ ‘አባባ’ ወይም ‘እማማ’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት፤ የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳል።” ጌታም እንደገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ “ይህ ሕዝብ በጸጥታ የሚፈሰውን የሰሊሆምን ውሆች ትቶ፤ በረአሶንና በሮሜልዩ ልጅ ተደስቶአልና። ስለዚህ ጌታ ታላቁንና ብርቱውን የጐርፍ ውሃ፤ የአሦርን ንጉሥ ከነግርማ ሞገሱ ሁሉ ያመጣባቸዋል። ውሃውም ከቦዩ ዐልፎ ተርፎ በወንዙ ዳር ያለውን ምድር ሁሉ ያጥለቀልቃል፤ እየጠራረገ ወደ ይሁዳ ይወርዳል፤ እያጥለቀለቀ ያልፋል፤ እስከ ዐንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፤ የተዘረጉ ክንፎቹ ምድርህን ከዳር እስከ ዳር ይሸፍናሉ።” እናንተ አሕዛብ፤ ፎክሩ፤ ግን ደንግጡ። በሩቅ አገር ያላችሁ አድምጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤ ተመካከሩ፤ ግን አይሳካም፤ ዕቅድ አውጡ፤ ሆኖም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። ጌታ ብርቱ እጁን በላዬ አድርጎ የእነዚህን ሰዎች መንገድ እንዳልከተል አስጠነቀቀኝ፤ እንዲህም አለኝ፤ “እነዚህ ሰዎች፤ ‘አድማ’ ብለው የሚጠሩትን፤ ማንኛውንም ነገር፤ ‘አድማ’ አትበሉ፤ እነርሱ የሚፈሩትን አትፍሩ፤ አትሸበሩለትም። ልትቀድሱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ ልትፈሩት የሚገባው እርሱን ነው፤ ልትንቀጠቀጡለት የሚገባውም እርሱ ነው። እርሱም መቅደስ ይሆናል፤ ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግን የሚያደናቅፍ ድንጋይ የሚያሰናክልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ወጥመድና አሽክላ ይሆናል። ከእነርሱ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ ይወድቃሉ፤ ይሰበራሉ፤ ወጥመድ ይገባሉ፤ ይያዛሉም።” ምስክርነቱን አሽገው፤ ሕጉንም በደቀ መዛሙርቴ መካከል አትመው። ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሸሸገውን ጌታን እጠብቃለሁ፤ እርሱንም ተስፋ አደርጋለሁ። እነሆ፤ እኔና ጌታ የሰጠኝ ልጆች በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ለእስራኤል ምልክትና ድንቅ ነን። ሰዎች፤ የሚያነበንቡትንና የሚያንሾካሹኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፤ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም። ተጨንቀውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ክፉኛ ሲራቡም ይቈጣሉ፤ ወደ ላይ እየተመለከቱ ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይራገማሉ። ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታሉ፤ የሚያዩትም ጭንቀት፤ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ። ነገር ግን ተጨንቀው የነበሩ ከእንግዲህ ተስፋ ቢስ አይሆኑም። በቀደመው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አዋረደ፤ በሚመጣው ዘመን ግን ከዮርዳኖስ ማዶ፤ በባሕር መንገድ አጠገብ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ለኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው። ሕዝብን አበዛህ፤ ደስታቸውንም ጨመርህ፤ ሰዎች ምርትን ሲሰበስቡ፤ ምርኮንም ሲከፋፈሉ ደስ እንደሚላቸው ሁሉ፤ እነርሱም በፊትህ ደስ ይላቸዋል። ምድያም ድል በተመታ ጊዜ እንደ ሆነው፤ የከበዳቸውን ቀንበር፤ በትከሻቸው ላይ የነበረውን በትር፤ የተጨቈኑበትንም ዘንግ ሰብረህላቸዋል። የጦረኞች ጫማ ሁሉ፤ በደም የተለወሰ ልብስም ሁሉ፤ ለእሳት ይዳረጋል፤ ይማገዳልም። ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፤ ድንቅ መካር፤ ኀያል አምላክ፤ የዘለዓለም አባት፤ የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፤ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም፤ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የዘለዓለም አባት ቅናት ይህን ያደርጋል። ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃል ላከ፤ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። ሕዝቡ በሙሉ፤ ኤፍሬምና የሰማርያ ነዋሪዎች ይህን ያውቃሉ፤ በትዕቢትና በልብ እብሪትም እንዲህ ይላሉ፤ ጡቦቹ ወድቀዋል፤ እኛ ግን በጥርብ ድንጋይ መልሰን እንገነባለን፤ የሾላ ዛፎቹ ተቈርጠዋል፤ እኛ ግን በዝግባ እንተካለን። ነገር ግን ጌታ የረአሶንን ጠላቶች ያጠናክራል፤ በእነርሱም ላይ ያመጣባቸዋል፤ ባለጋራዎቻቸውንም ያነሣሣባቸዋል። ሶርያውያን ከምሥራቅ፤ ፍልስጥኤማውያን ከምዕራብ፤ አፋቸውን ከፍተው እስራኤልን ይቦጫጭቋታል። ይህም ሁሉ ሆኖ፤ ቁጣው ገና አልበረደም፤ እጁ እንደ ተዘረጋ ነው። ሕዝቡ ግን ወደ ቀጣቸው ፊታቸውን አልመለሱም፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርንም አልፈለጉም። ስለዚህ ጌታ ራስንና ጅራትን፤ የዘንባባውን ቅርንጫፍና ሸምበቆውን ከእስራኤል በአንድ ቀን ይቈርጣል። ሽማግሌዎችና የተከበሩ ሰዎች ራስ፤ ሐሰትን የሚያስተምሩ ነቢያት ደግሞ ጅራት ናቸው። ይህን ሕዝብ የሚመሩት ያስቱታል፤ የሚመራውም ሕዝብ ከመንገድ ወጥቶ ይባዝናል። ስለዚህ ጌታ በጎበዛዝት ደስ አይሰኝም፤ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች አይራራም፤ ሁሉም ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላደረበትና ክፉ አድራጊ ነው፤ የሁሉ አፍ አስጸያፊ ቃል ይናገራልና። ይህም ሁሉ ሆኖ፤ ቁጣው ገና አልበረደም፤ እጁም እንደ ተዘረጋ ነው። እንግዲህ ርኩሰት እንደ እሳት ይቀጣጠላል፤ እሾህንና ኩርንችትን ይበላል፤ ጥቅጥቅ ያለውን ደን ያነዳል፤ ጢሱም ተትጐልጉሎ እንደ ዐምድ ይቆማል። በሠራዊት ጌታ ቁጣ ምድር ትጋያለች፤ ሕዝቡም እሳት ውስጥ እንደሚጨመር ማገዶ ይሆናል፤ ወንድሙንም ማዳን የሚችል ማንም የለም። በቀኝ በኩል ይጐርሳሉ፤ ነገር ግን ራባቸው አይታገሥም፤ በግራም በኩል ይበላሉ፤ ነገር ግን አይጠግቡም፤ እያንዳንዱም የገዛ ወገኑን ሥጋ ይበላል። ምናሴ ኤፍሬምን፤ ኤፍሬም ምናሴን ይበላል፤ በይሁዳም ላይ በአንድነት ይነሣሉ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ፤ ቁጣው ገና አልበረደም፤ እጁም እንደ ተዘረጋ ነው። ፍትሕ የጐደለውን ሕግ ለሚያወጡ፤ ጭቈና የሞላበትን ሥርዓት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የድኾችን መብት ለሚገፉ፤ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፤ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፤ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው! በምትጎበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል? ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ? ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ? ከእስረኞች ጋር ከመርበትበት፤ ከታረዱትም ጋር ከመጣል በቀር ምንም አይተርፋችሁም። ይህም ሁሉ ሆኖ፤ ቁጣው ገና አልበረደም። እጁም እንደ ተዘረጋ ነው። የቁጣዬ በትር ለሆነ፤ የመቅሠፍቴም ዱላ በእጁ ላለው ለአሦራዊው ወዮለት! ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፤ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፤ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፤ አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፤ በሚያስቆጣኝም ሕዝብ ላይ እሰደዋለሁ። እርሱ ግን እንዲህ አላሰበም፤ በልቡም ይህ አልነበረም፤ ነገር ግን ዕቅዱ ለማጥፋት፤ ብዙ ሕዝቦችንም ለመደምሰስ ነበር። እንዲህም ይል ነበር፤ “የጦር አዛዦቹ በሙሉ ነገሥታት አይደሉምን? ካልኖ እንደ ከርከሚሽ፤ ሐማት እንደ አርፋድ፤ ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደሉምን? የጣዖታትን መንግሥታት፤ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ መንግሥታት የሚበልጡትን እጄ እንደ ያዘች ሁሉ፤ በሰማርያና በጣዖቶቿ ያደረግሁትን፤ በኢየሩሳሌምና በተቀረጹ ምስሎቿስ እንዲሁ አላደርግምን?” ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፤ እንዲህ ይላል የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤ “‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤ ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና። የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤ ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤ ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ። ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፤ እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤ ሰዎች የተተወ ዕንቁላል እንደሚሰበስቡ፤ እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን ያራገበ የለም፤ አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’” መጥረቢያ በሚቆርጥበት ሰው ላይ ይኩራራልን? መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን? በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፤ ዘንግም ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኩራራ ነው። ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ይለኰሳል። የእስራኤል ብርሃን እሳት፤ ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤ በአንድ ቀንም እሾኹንና ኩርንችቱን እሳት ይበላዋል፤ ሕመምተኛ እየመነመነ እንደሚሞት፤ የደኑን ክብርና የለማውን ዕርሻ፤ ነፍስና ሥጋንም ፈጽሞ ያጠፋል። በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ሕፃን ልጅ እንኳ ቆጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል። በዚያን ቀን ከእስራኤል ዘር የተረፉት፤ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመታቸው ላይ አይታመኑም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በጌታ ላይ፤ በእውነት ይታመናሉ። የተረፉት ይመለሳሉ፤ ከያዕቆብ ቤት የተረፉት እንኳን ሳይቀሩ ወደ ኀያሉ አምላክ ይመለሳሉ። እስራኤል ሆይ፤ ሕዝብህ እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም፤ የተረፉት ብቻ ይመለሳሉ። ታላቅና ጻድቅ የሆነ ጥፋት ታውጆአል። ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ የወሰነውን ጥፋት በምድር ሁሉ ላይ ያመጣል። ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በጽዮን የምትኖሩ ሕዝቤ ሆይ፤ ግብጽ እንዳደረገብህ ሁሉ በትር ያነሡብህን፤ በሽመል የደበደቡህን አሦራውያንን አትፍራቸው። በአንተ ላይ ያመጣሁትን ቅጣት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቆማለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን አመጣለሁ።” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድያምን በሔሬብ ዐለት አካባቢ እንደ መታ፤ በጅራፍ ይገርፋቸዋል፤ በግብጽ እንዳደረገውም ሁሉ፤ በትሩን በውሆች ላይ ያነሣል። በዚያን ቀን ሸክማቸው ከትከሻህ፤ ቀንበራቸውም ከዐንገትህ ላይ ይነሣል፤ ከውፍረትህም የተነሣ ቀንበሩ ይሰበራል። ወደ ዐያት ይገባሉ፤ በሚግሮን ያልፋሉ፤ ጓዛቸውንም በማክማስ ያከማቻሉ። መተላለፊያውን ዐልፈው እንዲህ ይላሉ፤ “በጌባዕ ሰፍረን እናድራለን።” ራማ ደነገጠች፤ የሳኦል ከተማ ጊብዓ ሸሸች። የጋሊም ሴት ልጅ ሆይ፤ ጩኺ! ላይሻ ሆይ፤ አድምጪ! ምስኪን ዓናቶት ሆይ፤ መልሺላት! ማድሜናህ በሽሽት ላይ ነች፤ የጌቢም ሕዝብ ሊደበቅ ይሮጣል። በዚህ ቀን ኖብ ይደርሳሉ፤ እጃቸውን በኢየሩሳሌም ኰረብታ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ላይ በዛቻ ነቀነቁ። እነሆ፥ ልዑል እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ፤ በታላቅ ኃይል ቅርንጫፎችን ይቈራርጣል፤ ረጃጅም ዛፎች ይገነደሳሉ፤ ከፍ ከፍ ያሉትም ይወድቃሉ። ጥቅጥቅ ያለውን ደን በመጥረቢያ ይቈራርጣል፤ ሊባኖስም በኀያሉ ፊት ይወድቃል። ከእሴይ ግንድ ቁጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል። የጌታ መንፈስ፤ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፤ የምክርና የኃይል መንፈስ፤ የዕውቀትና ጌታን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። ጌታን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል፤ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፤ ታማኝነትም የጐኑ መቀነት ይሆናል። ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፤ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጉድጓድ ይከትታል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፤ ምድር ሁሉ ጌታን በማወቅ ትሞላለችና። በዚያን ቀን፤ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ መንግሥታት ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል። በዚያን ቀን፤ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደገና የተረፈውን የሕዝቡን ትሩፍ ከአሦር፤ ከታችኛው ግብጽ፤ ከላይኛው ግብጽ፤ ከኢትዮጵያ፤ ከኤላም፤ ከባቢሎን፤ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል። ለመንግሥታት ምልክትን ያቆማል፤ ከእስራኤልም የተሰደዱትን መልሶ ያመጣቸዋል፤ የተበተኑትን የይሁዳ ሕዝብ፤ ከአራቱ የምድር ማእዘን ይሰበስባል። የኤፍሬም ምቀኝነት ያከትማል፤ የይሁዳ ጠላቶችም ይቈረጣሉ፤ ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናም፤ ይሁዳም ኤፍሬምን አይጠላም። በምዕራብ በኩል በፍልስጥኤም ተረተር ላይ ይወርዳሉ፤ ሁለቱም ተባብረው በምሥራቅ ያለውን ሕዝብ ይዘርፋሉ፤ በኤዶምና በሞዓብ ላይ እጃቸውን ያነሣሉ፤ አሞናውያንም ይገዙላቸዋል። ጌታ በሚጋረፍም ነፋስ የግብጽን ባሕረ ሰላጤ ያደርቃል፤ እጁን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ይዘረጋል፤ ሰባት ታናናሽ ጅረትም አድርጎ ይለያየዋል፤ ስለዚህ ሰዎች ከነጫማቸው መሻገር ይችላሉ። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ እንደ ሆነው ሁሉ፤ ከአሦር ለተረፈው ቅሬታ ሕዝብ፤ እንዲሁ ጐዳና ይዘጋጅለታል። በዚያን ቀን እንዲህ ትላለህ፤ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ ተቈጥተኸኝ ነበር፤ አሁን ግን ከቁጣህ ተመለስህ፤ ደግሞም አጽናንተኸኛልና እወድስሃለሁ። እነሆ፤ ጌታ መዳኛዬ ነው፤ እታመናለሁ፤ ደግሞም አልፈራም፤ ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ የመዳኔ ምክንያትም ሆኖአል።” ከመድኀኒቴ ምንጮች ውሃ በደስታ ትቀዳላችሁ። በዚያን ቀን እንዲህ ትላላችሁ፤ “ጌታን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ። ለጌታ ዘምሩ፤ ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና፤ ይህም ለዓለም ሁሉ ይታወቅ። የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ እልል በሉ፤ በደስታም ዘምሩ፤ በመካከላችሁ ያለው የእስራኤል ቅዱስ ታላቅ ነውና።” የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ያየው ትንቢት፤ በተራቈተ ኰረብታ ዐናት ላይ ምልክት ስቀሉ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ፤ በመሳፍንቱም በር እንዲገቡ፤ በእጅ ምልክት ስጡ። በድል አድራጊነቴ ደስ የሚላቸውን ቅዱሳኔን አዛለሁ፤ ቁጣዬንም እንዲፈጽሙ፤ ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ። በተራሮች ላይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፤ የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ! በመንግሥታትም መካከል፤ እንደ ተጨናነቀ ሕዝብ ድምፅ የሆነውን ውካታ ስሙ! የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሠራዊቱን ለጦርነት አሰልፎአል። ጌታና የቁጣው ጦር መሣሪያ፤ ምድሪቱን በሙሉ ለማጥፋት፤ ከሩቅ አገር፤ ከሰማያትም ዳርቻ መጥተዋል። የጌታ ቀን ቀርቦአልና አልቅሱ፤ ሁሉን ቻይ ከሆነ አምላክ ቀኑ እንደ ጥፋት ይመጣል። ስለዚህ እጆች ሁሉ ሽባ ይሆናሉ፤ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል። ሽብር ይይዛቸዋል፤ ሥቃይና ጭንቀት ይደርስባቸዋል፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ያምጣሉ፤ እርስ በርሳቸው በድንጋጤ ይተያያሉ፤ ፊታቸውም በፍርሀት ቀይ ይሆናል። እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤ ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፤ በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፤ ከመዓትና ከብርቱ ቁጣ ጋር ይመጣል። የሰማይ ከዋክብትና ሠራዊታቸው፤ ብርሃን አይሰጡም፤ ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም። ዓለምን ስለ ክፋቷ፤ ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤ የጨካኞችንም ጉራ አዋርዳለሁ። ሰውን ከነጠረ ወርቅ ይልቅ ውድ፤ ከኦፊርም ወርቅ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ። ስለዚህ በሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መዓት፤ ቁጣው በሚነድበት ቀን፤ ሰማያትን እነቀንቃለሁ፤ ምድርንም ከስፍራዋ አናውጣለሁ። እንደሚታደን ሚዳቋ፤ እረኛም እንደሌለው የበግ መንጋ፤ እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፤ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል። የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል። ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤ ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ። እነሆ፤ ለብር ደንታ የሌላቸውን፤ በወርቅም ደስ የማይሰኙትን፤ ሜዶናውያንን አስነሣባቸዋለሁ። ቀስታቸው ጐበዞችን ይፈጃል፤ ሕፃናትን አይምሩም፤ ዐይናቸውም ለልጆች አይራራም። የመንግሥታት ዕንቁ፤ የከለዳውያን ትምክሕት፤ የሆነችውን ባቢሎንን፤ እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል። በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤ የሚቀመጥባትም የለም ዐረብ በዚያ ድንኳኑን አይተክልም፤ እረኛም መንጋውን በዚያ አያሳርፍም። ነገር ግን የምድረ በዳ አራዊት በዚያ ይተኛሉ፤ ቀበሮዎች ቤቶቿን ይሞላሉ፤ ጉጉቶቿ በዚያ ይኖራሉ፤ በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም ይዛለሉበታል። ተኩላዎችም በግንቦቻቸው፥ ቀበሮዎችም በተዋቡ ቤተ መንግሥቶቿ ይጮኻሉ፤ ጊዜዋ ቀርቦአል፤ ቀኗም አይራዘምም። ጌታ ግን ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተሳሰራል። አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ፦ አስጨናቂ እንዴት አበቃለት! አስገባሪነቱስ እንዴት አከተመ! ጌታ የክፉዎችን ዘንግ፥ የገዢዎችንም በትረ መንግሥት ሰብሯል። ሕዝቦችንም በማያቋርጥ ቁጣ የመታውን፥ ያለ ርኅራኄ ያለማቋረጥ ቀጥቅጦ አሕዛብን በማይበርድ ቁጣው የገዛውን ሰብሮአል። ምድርም ሁሉ አርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። ጥድና የሊባኖስ ዝግባ፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፥ የምድርንም ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴትስ ወደ ምድር ተጣልክ! አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። የሚያዩህ ይመለከቱሃልና፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ ዓለሙን ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልላከ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጉድጓዱ ድንጋዮች የወረዱ ከድነውሃል፤ እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘለዓለም የተጠራ አይሆንም። እንዳይነሱም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል ጌታ። የጃርት መኖርያ የውሃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ምሏል፦ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንዳሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። አሦርን በምድሬ ላይ እሰብራለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሳል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት።” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው? ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዘመን ይህ ሸክም ሆነ። ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። የድሆችም የበኩር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል፥ አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መልስ ይሰጣል? “ጌታ ጽዮንን መሥርቷል፥ ከሕዝቡም ችግረኞች በእርሷ ውስጥ መጠጊያን ያገኛሉ።” የሞዓብ ኤር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ። ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባውና በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቷል። በየመንገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል። ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮሁ፥ ድምፃቸው እስከ ያሀፅ ድረስ ተሰማ፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍሱም ራደች። ልቤ ስለ ሞዓብ አለቀሰ፤ ከእርሷ የሚሸሹ ወደ ዞዐር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኮበለሉ፤ በሉሒት አቀበት ላይ እያለቀሱ ወጡ፤ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኽት አሰሙ። የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፤ ለጋውም ጠውልጓል፤ ልምላሜውም ሁሉ የለም። ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል። ጩኸት በሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ያስተጋባል፤ ዋይታም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ። የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ ገና በዲሞን ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን እሰዳለሁ። በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ በምድር ላይ ገዢ ለሆነው ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦቶችን ስደዱ። ከጎጆቸው ተበትነው እንደሚበሩ ወፎች፥ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን መሻገሪያዎች እንዲሁ ይሆናሉ። ምክርን ለግሺ፥ ፍትህን አስፍኚ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አጢይ፤ ስደተኞችን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አሳልፈሽ አትስጪ። ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ዘንድ ይኑሩ፤ ስደተኞቹን ከሚሳድዷቸው መሸሸጊ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቷል፤ ጨቋኞች የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። ዙፋኑም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም በዳዊት ድንኳን ፍትህን የሚሻ ትክክል የሆነውን ለመፈጸም የሚፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል። የሞዓብን ኩራት፥ እጅግ መታበዩን! ስለ እብሪቱና ስለ ኩራቱ፥ ስለ ስድነቱም ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ከንቱ ነው። ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማ፤ ሁሉም ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች ኢያዜርን አልፈው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቁጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ግንድ ከኢያዜር ልቅሶ ጋር አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አርስሻለሁ። ደስታና ሐሴትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፤ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ በገና የኀዘን እንጉርጉሮ ታሰማለች። ሞዓም ወደ ኮረብታ ወጥቶ ራሱን ቢያደክም፥ ለጸሎት ወደ መቅደሱ ቢገባም በከንቱ ይደክማል እንጂ አያሸንፍም። ጌታ በሞዓብ ላይ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሞዓብ ክብር፥ ምንም ያህል ሕዝቡ ቢበዛ፥ በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፈውም ሕዝብ እጅግ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።” ስለ ደማስቆ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማነቷ ይቀራል፤ የፍርስራሽም ክምር ትሆናለች። ከተሞችዋ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማርያ ይሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም። ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ይወገዳል፤ የሶርያም ትሩፍ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል፤ ይላል የሠራዊት ጌታ። በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይደበዝዛል፥ የሰውነቱም ውፍረት ይመነምናል። አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ፥ በራፋይም ሸለቆ እንደሚለቀም ቃርሚያ ይሆናል። የወይራ ዛፍ ሲያራግፉት በቅርንጫፉ ራስ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት ፍሬ ችፍግ ባለው ቅርንጫፍ ላይ እንደሚገኝ፥ እንዲሁ ጥቂት ቃርሚያ ይቀራል፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ። በዚያ ቀን ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤ ዐይኖቻቸውም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ወዳበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች ወይም ወደ ማምለኪያ ዐምዶች አይመለከቱም። በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የአሞራውያንና የኤዊያውያን ከተሞች ምድረ በዳ እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ጠንካራ ከተሞችህ ባድማም ይሆናሉ። አዳኝ አምላክህን ረስተሃል፤ መሸሸጊያ ዐለትህንም አላሰብክም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ብትተክልም እንግዳንም ዘር ብትዘራ፥ በተከልክበት ቀን እንዲበቅል፥ በዘራህበት ማግስት እንዲያብብ ብታደርግ እንኳን፥ ነገር ግን በኀዘንና በብርቱ ደዌ ቀን መከሩ እንዳልነበር ይሆናል። እንደ ባሕር ሞገድ ለሚተም የብዙ ሕዝቦች ጩኸት፥ እንደ ኃያል የውኃ ሞገድ የሚያስገመግም ድምጽ ለሚያሰሙ ሕዝቦች ወዮላቸው! ሕዝቦች እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፤ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፤ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረውም ትቢያ ይበተናሉ። በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሽብር አለ! ከመንጋቱም በፊት አንዳቸውም አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙንም ዕጣ ይህ ነው። በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥ መልእክተኞችን በባሕር ላይ፥ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣን መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከቅርብም ከሩቅም አስፈሪ ወደ ሆነ ሕዝብ፥ ኀያል ወደሆነና ወደሚገዛ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ። እናንት በዓለም ውስጥ ያላችሁና በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በሚወጣ ጊዜ ተመልከቱ! መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ! ጌታ፥ “በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ” ብሎኛል። እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ፥ አበባው ያበበ የወይንም ፍሬ ሲይዝ፥ የወይኑን ዘንግ በመግረዣ ይገርዘዋል፤ ጫፎቹንም መልምሎ ያስወግዳል። በተራራ ላይ ላሉ ነጣቂ ወፎች፥ ለምድርም አውሬዎች ይተዋሉ። ነጣቂ ወፎችም በጋውን ሁሉ ይበጁባቸዋል፤ የምድርም አውሬዎች ክረምቱን ሁሉ ሲበሉት ይከርማሉ። በዚያን ጊዜ ለሠራዊት ጌታ፥ ከረጅምና ከለስላሳ ሕዝብ፥ ከቅርብም ከሩቅም አስፈሪ ከሆነ ሕዝብ፥ ኀያል ከሆነና ከሚገዛ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ከሚከፍሉት ሕዝብ ዘንድ ስጦታ ይመጣለታል፤ ስጦታውም የሠራዊት ጌታ ስም ወደሚገኝበት ወደ ጽዮን ተራራ ይቀርባል። ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ጌታ በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል። ግብፃውያንን በግብፃውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድም ወንድሙን፥ ባልንጀራም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል። የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን፥ የሙታን መናፍስትን፥ መናፍስት ጠሪዎቻቸውንና የጠንቋዮቻቸውን ምክር ይጠይቃሉ። ግብጻውያንንም ለጨካኝ ገዢዎች አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል፥ ይላል ልዑል የሠራዊት ጌታ። የዐባይ ወንዝ ይጎድላል፤ ወንዙም እያነሰም ይሄዳል ደረቅም ይሆናል። መስኖዎቹም ይከረፋሉ፥ የግብጽም ጅረቶች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል። በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ፥ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፤ ይበተናል፤ ምንም አይቀርም። ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፤ በዐባይ ወንዝ ላይ መንጠቆአቸውን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት በድካም ይዝላሉ። የተነደፈ የተልባ እግር ለሚፈትሉ፥ የተባዘተ ጥጥ የሚሰሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቆርጣሉ። ሸማኔዎችዋም ሁሉ ቅስማቸው ይሰበራል፥ የደመወዘኞችም ልብ ይሰበራል። የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሞኞች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው እርባና ቢስ ይሆናል። ፈርዖንን “እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን” እንዴት ትሉታላችሁ? አሁንስ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ። የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤ የሜምፎስም አለቆች ተታለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑት ግብጽን አስተዋታል። ጌታ ግራ የመጋባት መንፈስ በውስጥዋ አፍሶባታል፤ ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ እንድትንገዳገድ አደረጓት። ራስ ይሁን ጅራት፥ የዘንባባ ዝንጣፊ ይሁን ደንገል፥ ለግብጽ አንዳች ነገር ሊያደርጉላት አይችሉም። በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ የተነሣ ይርዳሉ ይፈራሉም። የይሁዳም ምድር ለግብጽ ሽብር ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል። በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከንዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዷ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች። በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለጌታ መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ለጌታ ዓምድ ይቆማል። ይህም ለሠራዊት ጌታ በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው ምክንያት ወደ ጌታ በመጮኻቸው፥ እርሱ መድኃኒትንና ኃያልን ሰዶ ያድናቸዋል። በዚያም ቀን ጌታ ለግብጻዊያን ራሱን ይገልጣል፤ ግብጻውያንም ጌታን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በእህል ቁርባንም ያመልኩታል፤ ለጌታም ስእለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽማሉ። ጌታም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ ጌታም ይመለሳሉ፥ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል። በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራዊያንም ወደ ግብጽ፥ ግብፃዊውም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብፃውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ። በዚያ ቀን እስራኤል፤ ከግብጽና ከአሦር ጋር የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች። የሠራዊት ጌታ፥ “ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል። የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥ በዚያ ጊዜ ጌታ የዓሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፥ “ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውርድ፤ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ” ብሎ ተናገረው። እንደተባለውም አደረገ፤ ራቁቱን ሆኖ በባዶ እግሩም ሄደ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “አገልጋዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት እንዲሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥ እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጉስቁልና ይነዳቸዋል። እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ፤ ያፍራሉም። በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ፥ ‘እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን?’ ይላሉ።” በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ትንቢት። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረበዳ ይወጣል። አስጨናቂ ራእይ ተነገረኝ፤ ከሓዲ አሳልፎ ይሰጣል፤ አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ! ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፤ ጭንቀቷን ሁሉ አጠፋለሁ። ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት አስጨነቀኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። ልቤ ራደ፥ ድንጋጤ አስደመመኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ ፍርሃት አሳደረብኝ። ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበላሉም፥ ይጠጣሉም፤ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ። ጌታ እንዲህ ብሎኛልና፦ ሂድ ጉበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር። በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ። ያየውም፦ ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፤ እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ፦ ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ። እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኳችሁ። ስለ ኤዶሚያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር፦ “ጉበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጉበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው?” ብሎ ጠራኝ። ጉበኛውም፦ “ይነጋል ደግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ” አለ። ስለ አረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ወስጥ ታድራላችሁ። በቴማም የሚትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ፤ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና። ጌታ እንዲህ ብሎኛልና፦ እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ ተናግሮአል። ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ራእይ። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታችሁ ምን ማለት ነው? አንቺ ጩኸትና ፍጅት የሞላብሽ ከተማ፥ የፈንጠዚያ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉምን፥ በሰልፍስ የሞቱ አይደሉም? አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ እርቀው ቢሸሹም አንቺ ጋር የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ። ስለዚህ፦ “ከእኔ እራቁ፤ መራራ ልቅሶ ላልቅስበት፤ ስለ ሕዝቤ ጥፋት ልታጽናኑኝ አትድከሙ” አልኩ። ከሠራዊት ከጌታ በራእይ ሸለቆ ውስጥ የድንጋጤና የመረገጥ፥ ግራ የመጋባት፥ የቅጥር መፍረስና ወደ ተራራ ለእርዳታ የሚጮኽበት ቀን ሆኖአል። ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን አነገበ። ምርጦቹም ሸለቆችሽ ሠረገሎች ሞሉባቸው፤ ፈረሰኞችም በሮች ላይ ቆመዋል። የይሁዳንም መጋረጃ ገልጧል። በዚያም ቀን በዱር ግምጃ ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፤ የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደበዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኩሬ ውኃ አጠራቅማችኋል። የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ፥ ቅጥሩንም ለመጠገን ቤቶችን አፈረሳችሁ። በአሮጌው ኩሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ አቅዶ የሠራውንም አላስታወሳችሁም። በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ፥ ጠጉራችሁን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራችሁ። ነገር ግን እናንተ፦ “ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣም” በማለት እነሆም፥ በሐሤትና በደስታ በሬንና በጉንም ስታርዱ፥ ሥጋንም ስትበሉ፥ የወይን ጠጅንም ስትጠጡ ነበር። ይህም ነገር የሠራዊት ጌታ ይህንን በጆሮዬ ነገረኝ፤ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ መጋቢ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፦ መቃብር በዚህ ያስወቀርህ፥ ከፍ ባለው ሥፍራ መቃብር ያሠራህ፥ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖሪያ ያሳነጽክ በዚህ ስፍራ ምን መብት አለህ? በዚህስ ለአንተ ወገን የሆነ ማን አለ? እነሆ ወዳጄ፥ ጌታ በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጥብቆም ሊጨብጥህ ነው፤ ጠቅልሎም ያንከባልልሃል፥ ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይወረውርሃል፤ አቤት፥ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያም ትሞታለህ፥ በዚያም የክብርህ ሠረገላዎች ይቀራሉ። ከማዕረግህ አወርድሃለሁ፤ ከሹመትህም ትሻራለህ። በዚያም ቀን አገልጋዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥ መጎናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፥ በመታጠቅያህም አስታጥቀዋለሁ፥ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል። የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋም፤ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍትም። በአስተማማኝ ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፥ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል። የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፥ እያንዳንዷን ትንንሽ ዕቃ፥ ከሲኒ ጀምሮ እስከ ጋን ድረስ ያለ የቤት ዕቃ ሁሉ በርሱ ላይ ይንጠለጠላል። በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ በአስተማማኝ ስፍራ የተተከለው ችንካር ይወልቃል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፤ በእርሱም ላይ የተንጠለጠለው ሸክም ይጠፋል፤ ይህን ጌታ ተናግሮአል። ስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት። እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ወደባቹህ ፈርሷልና አልቅሱ፤ ዜናው ከኪትም ምድር ደርሷችኋል። እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፥ በባሕርም የሚሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች የሞሉባችሁ፥ ጸጥ በሉ። በጥልቅ ውኆቿ ላይ የሺሖር እህልና የዓባይ ወንዝ መከር ገቢዋ ነበር፤ እርሷም የአሕዛብ የንግድ መናኸሪያ ነበረች። ባሕሩ “አላማጥሁም፤ አልወለድሁም፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አላሳደግሁም” ብሏልና፥ አንቺ ሲዶና ሆይ፥ አንቺ የባሕር ምሽግ ሆይ፥ እፈሪ። ከጢሮስ የሚመጣው ዜና፤ በግብጽ በሚሰማበት ጊዜ ጭንቅ ይይዛቸዋል። ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ። በጥንት ዘመን ተቆርቁራ የነበረችው፥ እሩቅ ምድር ድረስ እድትሰፍር እግሮችዋ ያጓጓዟት፥ የደስታችሁ ከተማ ይህች ናት? አክሊል በተቀዳጀች፥ ነጋዴዎችዋ መሳፍንት በሆኑ፥ በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፥ በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር? የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊሽር፥ የምድርንም ክብር ሁሉ ሊያስንቅ የሠራዊት ጌታ ይህን ወስኗል። የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በምድርሽ ላይ ፍሰሺ። እጁን በባሕር ላይ ዘረግቶ መንግሥታትንም አናውጧል፤ የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ ጌታ አዟል። አንቺ የተሰባበርሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ። እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት። እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። ከሰባ ዓመትም በኋላ ጌታ ጢሮስን ይጎበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትመለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች። ንግድዋና ዋጋው ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋንም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በጌታ ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም። እነሆ፥ ጌታ ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ ነዋሪዎቿንም ይበትናል። በሕዝቡ ላይ የሚሆነው እንዲሁ ካህኑ ላይ ይሆናል፤ በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በአስተዳዳሪው፥ በአገልጋይቱም የሚሆነው እንዲሁ በእመቤትዋ፥ በሸማቹ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በሻጩ፥ በአበዳሪው የሚሆነው እንዲሁ በተበዳሪው፥ በዕዳ አስከፋዩም የሚሆነው እንዲሁ በዕዳ ከፋዩ ይሆናል። ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ ፈጽማም ትበላሻለች፤ ጌታ ይህን ቃል ተናግሮአል። ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ታላላቅ ሕዝቦች ዛሉ። ምድርም በነዋሪዎቿ ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘለዓለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል። ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች፥ ነዋሪዎቿም ስለ ጥፋታቸው ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ግንድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክር መጠጥ የሚጠጡት መራራ ይሆንባቸዋል። ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ማንም እንዳይገባበት የሁሉም ቤት ተዘጋ። ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በፍርስራሽ ተለውጧል። የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድርና በአሕዛብም መካከል ይሆናል። እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ ጌታ ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። ስለዚህ ጌታን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የጌታንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን፦ ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ከሀዲዎች ክህደትን ፈጽመዋል፤ ከሀዲዎች አስከፊ ክህደት ፈጽመዋል አልሁ። በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና፥ ከሽብር ድምጽ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። ምድር እንደ ሰካራም ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ከብዷታል፥ ትወድቃለች፥ ደግማም አትነሣም። በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ ጌታ በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። በጉድጓድ እንደሚከማቹ እስረኞች በአንድነት ይከማቻሉ፤ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይቀጣሉ። የሠራዊት ጌታም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚነግሥ በሽማግሌዎቹ ፊት ክብር ይሆናል፤ ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል። አቤቱ ጌታ፥ አንተ አምላኬ ነህ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፤ ድንቅ ነገር በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናሁ። ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ደግማም አትገነባም። ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች። የጨካኞችም ቁጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መሸሸጊያ፥ ከውሽንፍር መጠለያ፥ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል። የሠራዊት ጌታም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ መልካምና የበሰለ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘለዓለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ ይህን ጌታ ተናግሮአል። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ ጌታ ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ይባላል። የጌታም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፤ ጭድም በጭቃ ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በሥፍራው ይረገጣል። ዋናተኛም ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፥ እንዲሁ በመካከሉ እጁን ይዘረጋል፤ ነገር ግን ትዕቢቱን ከእጁ ተንኮል ጋር ያዋርዳል። የተመሸገውንም ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፥ ያዋርደማል፤ ትብያ አፈር እስኪሆን ድረስ ይጥለዋል። በዚያም ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፦ የጸናች ከተማ አለችን፤ ቅጥሯንና ምሽጓን ለደኅንነታችን አኑሮታል። በእምነቱ የጸና ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ። በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ በአንተ ላይ ታምናለችና በሰላም ትጠብቃታለህ። ጌታ እግዚአብሔር የዘለዓለም ዐለት ነውና ለዘለዓለም በጌታ ታመኑ። በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፥ እስከ ትቢያም ድረስ ይጥላታል። እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም ኮቴ፥ ትረግጣታለች። የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንክ የጻድቃንን መንገድ ታቀናለህ። አቤቱ ጌታ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው። ፍርድህን በምድር ላይ በፈረድክ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች። ክፉዎች እድል ቢሰጣቸው እንኳን ጽድቅን አይማሩም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋሉ፥ የጌታንም ግርማ አያዩም። አቤቱ ጌታ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች። አቤቱ ጌታ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ። አቤቱ አምላካችን ጌታ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን የአንተን ስም ብቻ እናስባለን። እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጎብኝተሃቸዋል፤ አጥፍተሃቸውማል፤ መታሰቢያቸውንም ሁሉ እንዳልነበር አድርገሃል። ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ ጌታ፥ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። አቤቱ ጌታ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሠጽሐቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ። የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ አንደምትጮኽ፥ አቤቱ ጌታ፥ በፊትህ እንዲሁ ሆነናል። እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላመጣንም፤ በዓለም እንዲኖሩም ሕዝብ አልወለድንም። ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም። ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን ከጀርባህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ሊያመጣባቸው፥ እነሆ፥ ጌታ ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ያፈሰሰችውን ደም ትገልጣለች፥ የተገደሉትንም ከእንግዲህ ወዲህ አትሸሽግም። በዚያም ቀን ጌታ ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን፥ የሚጠቀለለውንም እባብ ሌዋታንን፥ በጠንካራ በታላቅ፥ በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፤ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል። በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። እኔ ጌታ ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ ውሃ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጎዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ። እሾህና ኩርንችት ቢያበቅልብኝ፥ እኔ አልቈጣም፥ በእነርሱ ላይ ተራምጄ አቃጥላቸዋለሁ። ይህ ካልሆነ ግን ጉልበቴን ለእርዳታ ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያቈጠቁጣል፥ ያብባልም፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ በተገደሉበት አገዳደል እርሱ ተገድሏል? የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው፤ በጦርነት ሰደዳቸው፥ ቀሰፋቸውም። ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኃጢአትን የማስወገድ ፍሬ ነው። የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፤ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተተወች መኖሪያ ሆናለች፤ በዚያም ጥጃ ይሰማራል፥ በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል። ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ፈጣሪው አይራራለትም፤ ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። በዚያ ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝ ጌታ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለጌታ ይሰግዳሉ። ለኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል ለሆነች፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ፥ በለምለሙ ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮላት! እነሆ፥ በጌታ ዘንድ ኃያልና ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም ጎርፍ፥ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላታል። የኤፍሬም ሰካራሞች የትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤ በለምለሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ያያት ሁሉ እጁን ሰዶ ይበላታል። በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤ በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ጦርንም ከከተማይቱ በር ላይ ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል። እነዚህ ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይንገዳገዳሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይቀባዥራሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይንገዳገዳሉ፤ ራእይ ሲያዩ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ። ማዕዱ ሁሉ በትፋት ተሞልቶአል፤ ምንም ንጹሕ ስፍራ የለም። “እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን?” በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም፦ “ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ በወጥመድም እንዲያዙ፥ የጌታ ቃል በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል። ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ። እናንተም፦ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ስላላችሁ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ “የሚያምን አያፍርም።” ለገመድ ፍትህን፥ ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ እለት ከእለት፥ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ ወሬውንም መስማት ፍርሃት ያሳድራል። ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጎናጸፊያ ጠባብ ነው። ጌታም፥ በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው፥ በገባዖንም ሸለቆ እንዳደረገው፥ ሥራውን ለመሥራት፥ አስደናቂ ሥራውን! ተግባሩን ለመፈጸም፥ አስገራሚ ተግባሩን! ይነሣል፤ ይነሣሣልም። አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ። አድምጡ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ መሬቱን ሲገለብጥ፥ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማል? እርሻውን አስተካክሎ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃውንም በደረጃው አይዘራምን? ይህንም ብልሃት አምላኩ ያሳውቀዋል ያስተምረውማል። ጥቁሩ አዝሙድ በመውቂያ አይወቃም፥ ከሙንም የሠረገላ መንኰራኵር አይዞርበትም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ ነገር ግን ለዘለዓለም አይፈጨውም፤ የሠረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቀውም። ይህም ደግሞ በምክሩ ድንቅ በጥበቡ የላቀ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ወጥቶአል። ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ አርኤል፥ አንቺ አርኤል ወዮልሽ! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመላለሱ። ግን አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እሷም እንደ አርኤል ትሆንልኛለች። በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ የጥበቃ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። ትዋረጃለሽ፥ መሬት ላይ ተደፍተሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም በዝግታ ከአፈር ይወጣል፤ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ድምፅ ይሆናል፥ ንግግርሽም ከአፈር በሹክሹክታ ይወጣል። ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርሷንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና፥ እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም እንደተጠማ አለ፤ የጽዮንን ተራራም የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደዚሁ ይሆናል። ተደነቁ ደንግጡም፤ ጨፍኑ ታወሩም! ስክሩም፥ በወይን ጠጅ አይደለም፤ ተንገዳገዱ፥ በመጠጥ አይደለም። ጌታ የሚደብት የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል፤ ዐይኖቻችሁን፥ ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል፤ ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል። ይህ ሁሉ ራእይ እንደ ታተመ የመጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው ባዘዙት ጊዜ እርሱ፦ “ታሽጓልና አልችልም” ይላቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል። ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛል። ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ አስደማሚ ነገርን ተአምራትንም እንደገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከጌታ ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው! ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ “አታስተውልም” ይለዋልን? ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን ቀርቶት የለምን? በዚያም ቀን ደንቆሮዎች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዐይኖች ጭጋግና ጨለማው ተገፎላቸው ያያሉ። የዋሃን ደስታቸውን በጌታ ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም ያደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉ፤ እነርሱም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ ጌታ ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። በመንፈስም የሳቱ ወደ ማስተዋል ይደርሳሉ፤ የሚያጉረመርሙም ምክርን ይቀበላሉ። ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው! ይላል ጌታ፤ ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ምክር ይመክራሉ፥ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ለመጨመር ከመንፈሴ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ። ከአፌ ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ለመጽናት በግብጽም ጥላ ለመታመን ወደ ግብጽ ይወርዳሉ። ስለዚህ የፈርዖን ኃይል እፍረት፥ በግብጽም ጥላ መታመን ስድብ ይሆንባቸዋል። አለቆች ምንም በጣኔዎስ ቢሆኑ፥ መልእክተኞችም ምንም ወደ ሐኔስ ቢደርሱ፥ ሁሉም ስለማይጠቅሟቸው፥ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኗቸው ሕዝቡ ያፍራሉ። በደቡብ ስላሉ እንስሶች የተነገረ ራእይ። ተባትና እንስት፥ አንበሳ እፉኝትም፥ ተወርዋሪ እባብም በሚወጡባት፥ በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል፥ ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ፥ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሟቸው ሕዝብ ይሄዳሉ። የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምንም ነው፤ ስለዚህ ስሙን፦ “በቤት የሚቀመጥ ረዓብ” ብዬ ጠርቼዋለሁ። አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘለዓለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው። ዓመጸኛ ወገንና የጌታን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤ ባለ ራእዮችን፦ “አትመልከቱ” ይላሉ፥ ነቢያትንም፦ “ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን፤ ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥ ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ” ይሏቸዋል። ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና፥ ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል። የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት፥ ወይም ውኃ ከጉድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ ኃይላችሁ በጸጥታና በመታመን ይሆናል፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ፥ ነገር ግን፦ “በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም” አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፦ “በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን” አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዷችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። ጌታም የፍርድ አምላክ ነው፤ ስለ ሆነም ጌታ ይራራላችኋልና ይታገሣል፤ ሊምራችሁም ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖር ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዐይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ “መንገዷ ይህች ናት በእርሷም ሂድ” የሚለውን ቃል ይሰማሉ። በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን፥ በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ “ከእኔ ራቁ!” ትላቸዋለህ። በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፤ መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ። በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ በረጅሙ ተራራ ሁሉ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ፥ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይወርዳሉ። ጌታም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ መቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል። እነሆ፥ የጌታ ስም ከሚነድ ቁጣ፥ ከሚንቦለቦልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም በቁጣ የተሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፤ እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፤ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል። በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩ እንደምትዘምሩ ዝማሬ፥ ወደ ጌታም ተራራ ወደ እስራኤል ዐለት እንቢልታ ይዞ በእልልታ እንደሚወጣ ሰው የልብ ሐሴትን ያደርጋል። ጌታም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድ ቁጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በበረዶ፥ ጠጠርም ይገልጣል። አሦርም በበትር ከመታው ከጌታ ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል። ጌታ በላዩ የሚወርድበት የታዘዘበት የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ የታጀበ ይሆናል፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል። ከቀድሞም ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች፤ ለንጉሥም ተበጅታለች፤ ጥልቅና ሰፊም አድርጎአታል፤ እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፤ የጌታም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል። ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ ጌታንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ ጌታ እጁን በሚዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። ጌታም እንዲህ ይለኛልና፦ አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሣ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንደዚሁም የሠራዊት ጌታ በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ለመዋጋት ይወርዳል። እንደሚበር ወፍ እንደዚሁ የሠራዊት ጌታ ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤ እንዲሁም ያድናታል። እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ። በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻል ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ። አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ ጌታ። እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍትህ ያስተዳድራሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል። የሚያዩትም ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ የሚሰሙትም ጆሮዎች ያደምጣሉ። ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፤ የተብታቦችም ምላስ ተፍታታና ደኅና አድርጋ ትናገራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ጨዋ ተብሎ አይጠራም፤ ሸንጋይ ሰው የተከበረ አይባልም። ሰነፍ ግን የስንፍናን ነገር ይናገራል፤ ልቡም በጌታም ላይ ስህተትን ለመናገር፥ የተራበችውንም ሰውነት ረሃቡን እንዳያስታግስ፥ የተጠማም ሰው ጥሙን እንዳይቆርጥ በደልን ለመሥራት ክፋትን ያቅዳል። የሸንጋይ ሽንገላ ክፉ ናት፤ የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆንም እንኳን በሐሰት ቃል ድሀውን ለማጥፋት ክፉን አሳብ ያስባል። ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፤ ለመከበርም ጸንቶ ይኖራል። እናንተ ዓለመኛ ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴት ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቁረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ። እናንተ ዓለመኛ ሴቶች ሆይ፥ በፍርሃት ራዱ፤ ተማምናችሁ የምትቀመጡ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለ ለሙ እርሻ፥ ስለፍሬያማውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኩርንችት ይበቅልባቸዋል። አዳራሹ ወና ይሆናል፥ በሰው የተጨናነቀውም ከተማ ወና ይሆናል፤ ምሽጉና ግንቡም ለዘለዓለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናል። መንፈስ ከላይ እስኪፈስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይህ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፍትህ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘለዓለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ፥ በታመነ ቤት፥ በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል። ደኑ ፈጽሞ ይጠፋል፤ ከተማም እንዳልነበረ ትፈራርሳለች። እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውሃ ዳርቻ የምትዘዋወሩ ምን ያህል ትደሰቱ! አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፥ አንተም ሳትካድ ክህደትን የምትፈጽም ወዮልህ! ማጥፋትን በተውክ ጊዜ ትጠፋለህ፤ መካድን በተውክ ጊዜ ትካዳለህ። አቤቱ ጌታ ሆይ፥ ማረን፤ አንተን እንጠባበቃለን፤ በየእለቱ ክንዳችን፥ በመከራም ጊዜ መድኅኒት ሁነን። ከፍጅት ድምፅ ሕዝቦች ሸሹ፤ በመነሣትህም መንግሥታት ተበተኑ። አንበጣ እንደሚሰበሰብ ምርኮአችሁ ትሰብስባለች፤ ኩብኩባም እንደሚዘል ሰዎች ይዘልሉበታል። ጌታም በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ ከፍ አለ፤ ጽዮንን በፍትህና በጽድቅ ሞላት። የዘመንህም ጸጥታ የመድኃኒት፥ የጥበብና የእውቀት ብዛት ይሆናል፤ ጌታን መፍራት ሀብቱ ነው። እነሆ፥ ኃይለኞቻቸው በሜዳ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። አውራ ጎዳናዎች ባድማ ሆኑ፥ መንገዶችም የሚያልፍባቸው ጠፋ፤ እርሱም ቃል ኪዳንን አፈረሰ ከተሞችንም ናቀ፥ ሰውንም አልተመለከተም። ምድሪቱ አለቀሰች ከሳችም፤ ሊባኖስ አፈረ ጠወለገም፤ ሳሮን እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ። “አሁን እነሣለሁ” ይላል ጌታ፥ “አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ። ገለባን ትጸንሳላችሁ፥ ዕብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት። አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፥ ተቆርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ።” እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፤ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እውቁ። በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፤ አምላክ የሌላቸው በፍርሃት ራዱ፤ “ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ መሀል ማን አለ? ለዘለዓለምም ከምትነድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ መሀል ማን አለ?” በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በጭቆና የሚገኝ ትርፍን የሚጸየፍ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚሰበስብ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚከልል፥ ክፋትንም ከማየት ዐይኖቹን የሚጨፍን ነው። እርሱ ከፍ ባለ ሥፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የማታቋርጥ ትሆናለች። ዐይኖችህ ንጉሡን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ይመለከታሉ። ልብህም፦ “ጸሐፊ ወዴት አለ? መዛኝስ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ?” ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል። ከእንግዲህ ወዲህ ጨካኝን ሕዝብ፥ ቋንቋው ለማስተዋል የማይገባ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ አታይም። የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዐይኖችህ የሰላም ማደሪያ፥ የማይወገድ ድንኳን፥ ካስማውም ለዘለዓለም የማይነቀል፥ አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ። ጌታ ግን በእነዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ በግርማ ከእኛ ጋር ይሆናል፤ የሚቀዘፉ መርከቦች አይገቡባትም፤ ታላላቅ መርከቦች አያልፉባትም። ጌታ ፈራጃችን ነው፥ ጌታ ሕግን ሰጪያችን ነው፥ ጌታ ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል። ገመዶችህ ላልተዋል፥ ችካላቸውንም አልጸናም፥ ሸራውንም መወጠር አልቻሉም። በዚያን ጊዜ የብዙ ምርኮ ሀብት ይከፋፈላል፤ አንካሶች እንኳ ከክፍፍሉ ይደርሳቸዋል። በዚያም የሚኖር ማንም፦ “ታምሜአለሁ” አይልም፤ በእርሷም ለሚኖሩ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል። እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሞላዋ፥ ዓለምና ከእርሷ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ። የጌታ ቁጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ። ሬሳቸውም ይከረፋል፤ ተራሮችም በደማቸው ይርሳሉ። የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፤ ሠራዊታቸው ሁሉ ከወይንና ከበለስ ላይ እንደሚረግፍ ቅጠል ይረግፋል። ሰይፌ በሰማይ ሆና ጠጥታ በምትረካበት ጊዜ፥ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። ጌታ መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና፥ የጌታ ሰይፍ በደም ትርሳለች፤ ስብ ትጠግባለች፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኩላሊት ስብ ትወፍራለች። ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትርሳለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች። ጌታ የበቀል ቀን፥ ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለው። የኤዶሚያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች። በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፤ ጢስዋም ለዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘለዓለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጉጉትና ቁራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የመጥፋት ቱንቢ ይዘረጋባታል። መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምቴዎች ይሆናሉ። በአዳራሾችዋም እሾህ፥ በቅጥሮችዋም ሳማና አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጎን ሥፍራ ትሆናለች። የምድረ በዳም አራዊት ከጅቦች ጋር ይገናኛሉ፤ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያም ትኖራለች፤ ለእርሷም ማረፊያ ታገኛለች። በዚያም ጉጉት ጎጆ ሠርታ እንቁላልን ትጥላለች፥ ትቀፈቅፋለችም፤ ጫጩቶቿንም በክንፏ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች ጥንድ ጥንድ ሆነው ይሰበሰባሉ። በጌታ መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ የጌታ አፍ አዝዞአልና፥ መንፈሱ ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ጥንዱን የሚያጣ የለም። እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም ለክታ ከፈለችላቸው፤ ለዘለዓለም የእነርሱ ትሆናለች፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይኖሩባታል። ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሃውም ሐሤት ያደርጋል፥ እንደ ጽጌረዳም ይፈካል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የጌታንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ። የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው፦ “እነሆ፥ አምላካችሁ ለበቀል፥ ብድራት ለመመለስ ይመጣል፤ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ!” በሉአቸው። በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዐይን ይበራል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ምንጭ ይፈልቃልና አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳም ምላስ ይዘምራል። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፥ የተጠማች መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ለምለም፥ ሸምበቆው ደንገል ይበቅልበታል። በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፥ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐን ያልሆኑ አያልፉበትም፥ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ግን ያልፉበታል፤ ተጓዦች ሆኑ፥ ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ እነዚህ ከዚያ አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤ ጌታም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፥ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላላም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ። በንጉሡ በሕዝቅያስ በዓሥራ አራተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ተመሸጉት ወደ ይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወረራ በመፈጸም ያዛቸው። ከዚያ የአሦር ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። እርሱም በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ላይ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ በቆመ ጊዜ፥ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኤልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሐፊውም ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ፥ ወደ እርሱ መጡ። ራፋስቂስም እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የምትተማመንበት መተማመኛ ምንድነው? ባዶ ቃል የጦር ስልትና ኃይል የሚሆንህ ይመስልህል? አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ የሸንበቆ በትር በግብጽ ተማምነሀል፤ ሰው ተማምኖ ቢመረኰዘው እጁን ወግቶ ያቈስለዋል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ ‘በአምላካችን በጌታ እንታመናለን’ ብትለኝ፥ ‘በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ’ ብሎ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ ያስፈረሰው እርሱ አይደለምን? እንግዲህ አሁን ናና፥ ከአለቃዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተደራደርና፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ካገኘህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከአለቃዬ ባርያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ለመቃወም እንዴት ይቻልሃል? አሁንም ቢሆን፥ ጌታ፦ ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ እንጂ፥ በውኑ ያለ ጌታ ይህን አገር ለማጥፋት የዘመትኩ ይመስልሃል?” ከዚያም ኤልያቄም፥ ሳምናስና ዮአስ ራፋስቂስን፦ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሚገባን በሶርያ ቋንቋ ለአገልጋዮችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ መግባቢያ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን” አሉት። ራፋስቂስ ግን፦ “አለቃዬ ይህን ቃል እንድናገር ወደ እናንተና ወደ አለቃችሁ ብቻ ልኮኛልን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኩስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ “የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ ሊያድናችሁ አይችልምና አያታላችሁ፤ ሕዝቅያስ፥ ጌታ በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም፥ ብሎ በጌታ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስን አትስሙ፤’ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ‘ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ኑ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጉድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስ፥ ጌታ ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋል? የሐማትና የአልፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታል? ጌታ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ፥ ከእነዚህ አገሮች ሁሉ አማልክት አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?’” እነርሱ ግን ዝም አሉ፥ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና “አንዳችም አልመለሱለትም”። የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሐፊውም ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ፥ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት። ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ ጌታም ቤት ገባ። የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። እነርሱም፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ብርታቱ የለም። ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ አለቃው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ ጌታ ሰምቶ እንደሆነ፥ አምላክህ ጌታም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደሆን፥ ስለዚህ አንተም በሕይወት ስለተረፉት ቅሬታ ጸልይ አሉት።” ከዚያም የንጉሡ የሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ መጡ። ኢሳይያስም፥ “ለአለቃችሁ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም ላይ በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት’ ” አላቸው። ራፋስቂስም ተመለሰ፤ የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ስለ ነበር በልብና ከተማ ሲዋጋ አገኘው። የአሦርም ንጉሥ፦ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቷል” የሚል ወሬ ሰማ። ይህን በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህም አለው፦ “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክ አያታልህ። እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፍስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸው? የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?” ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ጌታ ቤት ሕዝቅያስም ወጥቶ በጌታ ፊት ዘረጋው። ወደ ጌታ እንዲህ በማለት ሕዝቅያስ ጸለየ፦ “አቤቱ የሠራዊት ጌታ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ለመገዳደር የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። ጌታ ሆይ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፤ አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ፥ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። እንግዲህም አምላካችን ጌታ ሆይ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ ጌታ እንደሆንህ እንዲያውቁ ከእጁ አድነን።” የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሀልና ጌታ ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ስትሸሽ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደርግህበት፥ ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ አይደለምን!’ አንተም እንዲህ አለክ፦ በሠረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሲባኖስ ጥግ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን ዝግባዎች፥ የተመረጡትን ጥንዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ፤ ቈፈርኩ ውኃም ጠጣሁ፥ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደረቅኩ።” ይህን እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? እሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግኩ። ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሏል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቁጣ አውቄአለሁ። ቁጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። ይህ ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዳላችሁ፤ ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። የተረፈው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። ከኢየሩሳሌም ቅሬታ፥ ከጽዮን ተራራ ያመለጡት ይመጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ ቅንዓት ይህን ያደርጋል። “ስለዚህም ጌታ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም አይደለድልባትም። በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፤ ወደዚችም ከተማ አይመጣም፥ ይላል ጌታ። ስለ እኔም ስለ አገልጋዬም ዳዊት ይህችን ከተማ አድናታለሁ፥ እጋርዳታለሁም።” የጌታም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፈንታ ነገሠ። በዚያም ጊዜ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያደርስ ህመም ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ ጌታ ጸለየ፦ “ጌታ ሆይ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። ከዚያም የጌታም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ። አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ። “ጌታም የተናገረውን ነገር እንደሚፈጽመው ከጌታ ይህ ምልክት ይሆንልሃል። እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት መቁጠሪያ ላይ በደረጃዎች ያለውን ከፀሐይ ጋር የወረደውን ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላው የሰዓት ስፍራ ላይ በወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ከበሽታው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሑፍ ይህ ነው፦ እኔ፦ በሕይወት ዘመኔ እኩሌታ ከሕይወት ልለይ ይገባልን? በቀረው ዘመኔስ ወደ ሲኦል በሮች መግባት አለብኝን? አልኩ። ደግሞም፦ በሕያዋን ምድር ጌታን አላይም፤ በዓለምም የሚኖሩትን ሰዎች ከእንግዲህ አልመለከትም አልኩ። ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልኩት፤ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው። እስኪ ነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው። እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጉረመረምሁ፤ ዐይኖቼ ወደ ላይ በማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። ግን ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስከኝ ወደ ሕይወትም መለስከኝ። እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ምክንያት ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጉድጓድ አዳንካት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ። ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጉድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። እኔ ዛሬ እንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆቹ እውነትህን ያስታውቃል። ጌታ ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።” ኢሳይያስም፦ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር። ሕዝቅያስም፦ “ወደ ጌታ ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድነው?” ብሎ ነበር። በዚያም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ ታምሞ እንደ ተፈወሰ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ላከለት። ሕዝቅያስም ደስ አለው፤ ግምጃ ቤቱንም፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣርያም ያለበትን ቤት ሁሉ፥ በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ፦ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ?” አለው። ሕዝቅያስም፦ “ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡልኝ” አለው። እርሱም፦ “በቤትህ ያዩት ምንድነው?” አለው፤ ሕዝቅያስም፦ “በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም” አለው። ኢሳይያስም ሕዝቅያስን፦ “የሠራዊትን ጌታ ቃል ስማ። እነሆ፥ በቤትህ ያለውን ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል ጌታ። ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ” አለው። ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፦ “የተናገርኸው የጌታ ቃል መልካም ነው” አለው። ደግሞም፦ “በዘመኔ ሰላምና እውነት ይሁን” አለ። አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፤ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከጌታም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርሷ ጩኹ። የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ “የጌታን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሀ አስተካክሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጉጡም ሜዳ ይሆናል፤ ከዚያም የጌታ ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የጌታ አፍ ይህን ተናግሮአል።” አንድ ድምጽ “ጩኽ!” አለኝ፤ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልኩ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የጌታ እስትንፋስ ይነፍስበታል፤ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች። የምሥራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወደለው ተራራ ውጪ፤ የምሥራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? የጌታን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍትህንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው? እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል። ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምንም እንደሚያንሱ፥ እንደ ባዶ ነገር ይቈጠራሉ። እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት ቅርጽ እንዲሰጥ አፍስሶለታል። ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። አላወቃችሁም? ወይስ አልሰማችሁ ይሆን? ከጥንትስ አልተወራላችሁም? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁም? እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርሷም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ መስፍኖችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። እንግዲህ የሚስተካከለኝ ማን አለ? ከማንስ ጋር አመሳሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በክህሎቱ ብርታት አንድ እንኳ አይጎለውም። ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤል ሆይ፦ “መንገዴ ከጌታ ተሰውራለች፥ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህም? አልሰማህም? ጌታ የዘለዓለም አምላክ ነው፤ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ፥ ይታክታሉም፤ ጐበዛትም ፈጽሞ ይወድቃሉ። ጌታን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም። ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ። ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ፥ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት ሰላማዊ መንገድ አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራው ማን ነው? እኔ ጌታ፥ መጀመሪያም እስከ መጨረሻውም የምኖር፥ እኔ ነኝ። ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም፦ “አይዞህ” ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያጽናናዋል፥ ስለ ብየዳ ሥራውም፦ “መልካም ነው” ይለዋል፤ እንዳይላቀቅም በችንካር ያጋጥመዋል። አገልጋዬ እስራኤል፥ የመረጥኩህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና፦ “አንተ አገልጋዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ፥ አልጥልህም!” ያልሁህ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሀለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዳሉም፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፋሉም። የሚጣሉህንም ትፈልጋቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ ጌታ ነኝ፦ “አትፍራ፥ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝህን የያዝኩ። አንተ ትል ያዕቆብ፥ ታናሽ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በጌታ ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ ማከማቻ ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፤ ዝግባን፤ ግራርን፤ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሃ፤ ጥድን፤ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ የጌታ እጅ ይህን እንዳደረገ፥ የእስራኤል ቅዱስ እንደፈጠረው፥ ሰዎች እንዲያዩና እንዲያውቁ፥ በአንድነት እንዲገነዘቡ፤ እንዲያስተውሉም። ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ፥ ይላል ጌታ፤ ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እድናደርግ፥ ፍጻሜአቸውንም እድናውቅ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን። አማልክትም መሆናችሁን እድናውቅ፥ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንድንደነግጥም፥ በአንድነትም እንድናይ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ። እነሆ፥ እንዳልነበረ ናችሁ፥ ሥራችሁም ከንቱ ነው፤ የሚመርጣችሁም አስጸያፊ ነው። አንዱን ከሰሜን አነሣሁ መጥቶአልም፤ አንዱም ከፀሐይ መውጫ ስሜን የሚጠራ ይመጣል፤ በጭቃ ላይ እንደሚመጣ ሰው አፈርም እንደሚረግጥ ሸክለኛ በአለቆች ላይ ይመጣል። እድናውቀው ከጥንት የተናገረው፦ እውነት ነው፥ እንድንልም ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፥ የሚገልጥም የለም፥ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም። በመጀመሪያ ለጽዮን፦ እነሆ ተመልከች፥ እላለሁ፤ ለእየሩሳሌምም የምሥራች ነጋሪን እሰጣለሁ። ብመለከት ማንም አልነበረም፤ ብጠይቃቸውም የሚመልስልኝ አማካሪ በመካከላቸው የለም። እነሆ፥ እነርሱ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፤ ሥራቸውም ምንም ናት፤ ቀልጠው የተሠሩት ምስሎቻቸውም ባዶ ነፋስ ናቸው። እነሆ ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፤ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፤ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ። እኔ ጌታ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርሷም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ፥ ለጌታ አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለጌታ ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። ጌታ እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያውቁት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ በማያውቁትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውም። በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፦ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ። እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ። ከአገልጋዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹም ተገዢዬ ወይም እንደ ጌታ አገልጋይ ዕውር የሆነ ማን ነው? ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፥ ነገር ግን አትሰሙም። ጌታ ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ። ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁሉም በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል፤ በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ተበዝብዘዋል የሚያድንም የለም፥ ተማርከዋል፤ “መልሷቸው” የሚል ማንም የለም። ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው? ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፥ እነርሱም በመንገዱ ለመሄድ ያልወደዱት፥ ለሕጉም ያልታዘዙለት ጌታ እርሱ አይደለምን? ስለዚህ የቁጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰባቸው፤ በዙሪያቸውም አነደደው፤ እነርሱ ግን አላወቁም፥ አቃጠላቸውም እነርሱ ግን ልብ አላሉም። አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰምጡህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ ጌታ መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ እሰጣለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ፥ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ “መልሰህ አምጣ፥” ደቡብንም፦ “ልቀቅ፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ አምጣ እለዋለሁ፤ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ።” ዐይኖች ያሏቸውን ዕውር ሕዝቦችን፥ ጆሮዎችም ያሏቸውን ደንቆሮቹን አውጣ! አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፥ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? እንዲጸድቁ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ “እውነት ነው” ይበሉ። ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም አገልጋዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል ጌታ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፥ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ፥ አድኛለሁ፥ አሳይቻለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል ጌታ። እኔም አምላክ ነኝ፥ ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ ጌታ እኔ ነኝ። ጌታ እንዲህ ይላል፥ በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤ ሠረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል። የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ ይህን እናንተም አታውቁም? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን እዘረጋለሁ። የምድረ በዳ አራዊት፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖች ያከብሩኛል፤ ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ ላጠጣ፥ በምድረ በዳ ውሃ፤ በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁ። ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን እንዲያውጅ ይህን አደርጋለሁ። ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል። ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም፤ በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቁርባን አላስቸገርሁህም፤ በዕጣንም አላደከምሁህም። ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም፤ በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርከኝ፥ በበደልህም አደከምከኝ። መተላለፍህን፦ ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም። አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር። ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል። ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስኩ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ። አሁንም አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም ጌታ እንዲህ ያልል፦ አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ። በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፥ በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ። ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል፤ በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል። የእስራኤል ንጉሥ ጌታ፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ፥ እኔ ፍጻሜም ነኝ፤ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገረኝ። አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱም ጀምሬ አልነገርኋችሁም? ወይስ አላሳየኋችሁም? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? ሌላ ዐለት የለም፤ አንድም አላውቅም። የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፤ የወደዱትም ነገር አይጠቅማቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያስተውሉም ደግሞ አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። ጣዖትን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባን ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ባለሙያዎቹም ከሰው ወገን ናቸው፤ ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፤ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይርበዋል ይደክማልም፤ ውኃም ለመጠጣት ይታክታል። ጠራቢው ገመድ ይዘረጋል፥ በጠመኔም ምልክት ያኖራል፥ በመሮም ይቀርጸዋል፥ በመለኪያም ይለከዋል፤ በቤትም ውስጥ እንዲቀመጥ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ይቀርጸዋል። የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል እንዲጠነክር ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል፥ ዝናብም ያበቅለዋል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፤ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፤ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፦ “እሰይ ሞቅሁ፥ ሙቀት ተሰማኝ” ይላል። የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። በልቡም ማንም አያስብም፦ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን?” ለማለት እንኳን እውቀትና ማስተዋል የለውም። አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ “በቀኝ እጄ ሐሰት አለ?” ብሎም አይጠይቅም። ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም አገልጋዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳህ ትሆናለህ። መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። ሰማያት ሆይ፥ ጌታ አድርጎታልና ዘምሩ፤ ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ። ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ፥ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤ የባርያዬን ቃል አጸናለሁ፤ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች፦ ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ። ቀላዩም፦ “ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ” እላለሁ፤ ቂሮስንም፦ “እርሱ እረኛዬ ነው”፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ “ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል” ይላል፤ እኔም “ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” እላለሁ። ጌታ ለቀባው፥ አሕዛብንም በፊቱ እንዲገዙለት፥ የነገሥታትንም ወገብ እዲፈታ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹ በፊቱ እንዲከፈቱለት፥ ቀኝ እጁን ለያዘው ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም እደለድላለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ ጌታ እኔ እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ። ስለ አገልጋዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቁልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም። እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ አንተ ባታውቀኝም እኔ አስታጠኩህ፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ፥ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ይወቁ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤ ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ ጌታ ነኝ። እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፥ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ ጌታ ፈጥሬዋለሁ። ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ እጅ የለውም ይላልን? አባትን፦ ምን ወልደሃል? ወይም ሴትን፦ ምን አማጥሽ? ለሚል ወዮ! የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፥ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ። እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርሷ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቻለሁ፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፥ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፥ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ። ጌታ ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፥ እናንተም ለዘለዓለም አታፍሩምና አትዋረዱም። ሰማያትን የፈጠረ ጌታ፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። በስውር ወይም በጨለማ ምድር አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ ጌታ እውነትን እናገራለሁ ትክክለኛውንም አወራለሁ። እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም። ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ ጌታ አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፦ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። ስለ እኔም፦ በጌታ ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፥ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፥ በእርሱም ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ። የእስራኤልም ዘር ሁሉ በጌታ ይጸድቃሉ፥ ይመካሉም ይከብራሉም። ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል። ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ፤ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፥ ራሳቸው ግን ተማረኩ። እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁን፥ ስሙኝ። እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻችኋለሁ እኔም አነሣችኋለሁ፤ እኔ እሸከማችኋለሁ እኔም አድናችኋለሁ። በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? ወርቁን ከኮሮጆ የሚያፈስሱ፥ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል። በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል፤ በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፤ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ “ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ” እላለሁ። ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራለሁ። ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ። እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፤ ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቼአለሁ። አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ ከዚህ በኋላ ቅንጡና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ። ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፤ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣይው፤ ባትሽን ግለጪ፥ ወንዙን ተሻገሪ። ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፤ እኔ እበቀላለሁ፥ ለማንም አልራራም። ታዳጊያችን፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ ነው፥ እርሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው። የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ፦ የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ። በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ ርስቴንም አረከስሁ፤ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፤ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል። አንቺም፦ “እኔ ለዘለዓለም እመቤት እሆናለሁ” ብለሻል፤ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም። አሁንም አንቺ ተድላን የምትወጅ፥ በምቾትም የምትቀመጪ፥ በልብሽም፦ “እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ መበለትም ሆኜ አልኖርም፥ የወላድ መካንነትንም አላውቅም” የምትዪ ይህን ስሚ፤ አሁን ግን እነዚህ ሁለት ነገሮች፥ የወላድ መካንነትና መበለትነት፥ በአንድ ቀን በድንገት ይመጡብሻል፤ ምንም መተት ብታበዥና ምንም ዓይነት አስማት ቢኖርሽም ፈጽሞ አይቀሩልሽም። በክፋትሽ ታምነሻል፤ “የሚያየኝ የለም” ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም፦ “እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ብለሻል። በዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፥ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤ ጉዳት ይወድቅብሻል ልታስወግጂውም አትችይም፤ የማታውቂያትም ጉስቁልና ድንገት ትመጣብሻለች። ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደሆነ፥ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ። በምክርሽ ብዛት ደክመሻል፤ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፥ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፥ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ። እነሆ፥ እንደ እብቅ ይሆናሉ፥ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፤ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፍም፥ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ዓይነት አይደለም። የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፥ የሚያድንሽ አይገኝም። እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በጌታ ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ። የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል፥ አሳይቼውማለሁ፤ ድንገት አድርጌው ተፈጽሞዋል። አንተ እልከኛ፥ አንገትህን የብረት ጅማት፥ ግንባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፤ ስለዚህ፥ አንተ፦ “ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ” እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር፥ ከመሆኑም በፊት አሳይቼህ ነበር። ሰምተሃል፤ አሁን ይህን ሁሉ ተመልከት፤ ይሄን ራስህ አትመሰክርም? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲስ ነገሮችን ከአሁን ጀምሬ አሳይችኋለሁ። እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም፦ “እነሆ፥ አስቀድሜ አውቄአቸዋለሁ” እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደ ተጠራህ አውቄአለሁና። ስለ ስሜ ቁጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳለጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ። እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ፤ ስለምን ስሜ ይነቀፋል? ክብሬን ለሌላ አልሰጥም። ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? ጌታ የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። እኔ እራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርኩም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርኩ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ ጌታ ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፥ ይህንንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩ፦ “ጌታ ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል!” በሉ። በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል ጌታ። ደሴቶች ሆይ፥ ስሙኝ፥ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፥ አድምጡ፤ ጌታ ከማኅፀን ጠርቶኛል፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንስቶአል፤ አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፥ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፤ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፥ በሰገባውም ውስጥ ሸሽጎኛል። እርሱም፦ “እስራኤል ሆይ፥ አንተ አገልጋዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ” አለኝ። እኔ ግን፦ “በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጉልበቴን ፈጀሁ፤ ፍርዴ ግን በጌታ ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው” አልኩ። አሁንም ከማኅፀን ጀምሮ በሠራኝ በጌታ ዐይን ከብሬአለሁና፥ አምላኬም ጉልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ አገልጋዩ አድርጎኝ ጌታ እንዲህ ይላል። እርሱም፦ “የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የተረፉትን እንድትመልስ አገልጋዬ እንድትሆን እጅግ ቀላል ነገር ነውና ማዳኔ እስከ ምድር ዳር እንዲደርስ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል። የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ ጌታ፥ ሰዎች በሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው፥ ለገዢዎች አገልጋይ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ታማኙ ስለ ጌታ ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ።’ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፥ ምድርንም እንድታቀና፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች እንድታወርስ፥ የተሰሩትንም፦ ‘ውጡ’ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ‘ተገለጡ’ እንድትል ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በገላጣ ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል። የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ የበረኅ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም። ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ።” ጌታ ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ። ጽዮን ግን፦ “ጌታ ትቶኛል፥ እርሱ ረስቶኛል” አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ የተወለደው ሕጻን ልጇን ትረሳለች? ርህራሄ አልባስ እስክመሆን ትደርሳለች? አዎን፥ እርሷ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ። ልጆችሽ ይፈጥናሉ፥ ሊያፈረሱሽና ሊያወደሙሽ ከአንቺ ይወጣሉ። ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል ጌታ። ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተነሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉ። የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ፦ “ስፍራ ጠብቦኛልና እድንቀመጥ ቦታ አስፊልን” ይላሉ። አንቺም በልብሽ፦ “የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁ፥ ተቅበዝብዤአለሁ፥ እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ?” ትያለሽ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በዕቅፋቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዝቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ፤ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይነጠቃል? ወይስ ከጨካኙ ምርኮኞችን ማስመለጥ ይቻላል? ጌታ ግን እንዲህ ይላል፦ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁና፥ በኃያላን የተማረኩ እንኳን ይወሰዳሉ፥ የጨካኞች ብዝበዛም ቢሆን ያመልጣል። አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሠክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ ጌታ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደሆንሁ ያውቃል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናታችሁን የፈታሁበት የፍቺዋ ጽሕፈት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥሁ ከአበዳሪዎች ለየትኛው ነው? እነሆ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ተሸጣችኋል፥ ስለ በደላችሁም እናታችሁ ተፈታለች። በመጣሁስ ጊዜ ሰው ስለምን አልነበረም? በጠራሁስ ጊዜ የሚመልስ ስለምን አልነበረም? መታደግ እንዳትችል እጄ አጭር ሆናለችን? ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝም? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ውኃም አጥተው ዓሦቻቸው ይገማሉ፥ በጥማትም ይሞታሉ። ሰማያትን ጥቁረት አለብሳቸዋለሁ፥ መጋረጃቸውንም ማቅ አደርጋለሁ። የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ እንዳውቅ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም እንድትሰማ ጆሮዬን ያነቃቃል። ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም። ጀርባዬን ለገራፊዎች፥ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ፤ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና አልታወክሁም፤ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፥ ኀፍረት ላይ እንደማልወድቅም አውቃለሁ። የሚያጸድቀኝ ቅርብ ነው፤ ከእኔስ ጋር የሚከራከር ማን ነው? በአንድነት እንቁም፤ የሚከራከረኝ ማን ነው? ወደ እኔ ይቅረብ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ ማን ይፈርድብኛል? እነሆ፥ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ ብልም ይበላቸዋል። ከእናንተ ጌታን የሚፈራ፥ የአገልጋዩንም ቃል የሚሰማ፥ በጨለማም የሚሄድ፥ ብርሃንም የሌለው፥ ነገር ግን በጌታ ስም የሚታመን፥ በአምላኩም የሚደገፍ ማን ነው? እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ፥ የእሳትንም ወላፈን የምትታጠቁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ነበልባል ባነደዳችሁትም ወላፈን ሂዱ! ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል፤ በኅዘን ትተኛላችሁ። እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ ጌታንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ዐለት ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ። ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም። ጌታም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርሷም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፤ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔድን በረሀዋንም እንደ ጌታ ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል። ወገኔ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፥ ማዳኔም ወጥቶአል፥ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፥ በክንዴም ይታመናሉ። ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያትን እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘለዓለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም። ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ። እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፥ እንደ በግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘለዓለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል። የጌታ ክንድ ሆይ! ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን? ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅከው፥ የዳኑትም እንዲሻገሩ ጥልቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን? ጌታ የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ስለምን ትፈራለህ? ሰማያትን የዘረጋውን ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን ጌታን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቁጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቁጣ የት አለ? ምርኮኛው ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጉድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም። ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ ጌታ እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ ነው። ሰማያትን እንድዘረጋ ምድርንም እንድመሠርት፥ ጽዮንንም፦ “አንቺ ሕዝቤ ነሽ” እንድል ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ። ከጌታ እጅ የቁጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ! ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል። ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት፥ ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ በየአደባባዩ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በጌታ ቁጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል። ስለዚህ ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቁጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። ነፍስሽንም፦ “በአንቺ ላይ እንድንረማመድ ዝቅ በዪ” በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው። ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፥ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፥ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፥ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው። ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል ጌታ፤ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፥ ይላል ጌታ፥ ስሜም ያለማቋረጥ በየእለቱ ቀኑን ሙሉ ይሰደባል። ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፥ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፤ እነሆ፥ እኔ ነኝ። የምሥራች የሚናገር፥ ሰላምንም የሚያወራ፥ የመልካምንም ወሬ የምሥራች የሚናገር፥ መድኃኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም፦ አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ውብ ነው። እነሆ፥ ጉበኞችሽ ጮኸዋል፤ ጌታ ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዐይን በዐይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፥ ጌታ ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፥ በአንድነትም ዘምሩ። ጌታ የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ። እናንተ የጌታን ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንጹሐን ሁኑ። ጌታ ቀድሟችሁ ያልፋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኮላ አትወጡም፤ በመኮብለልም አትሄዱም። እነሆ፥ አገልጋዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል። ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቁሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤ ያልተነገረላቸውን ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ። የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የጌታስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እድንወደው ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው፥ ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚያዞርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን እንደ ተመታ፥ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ፥ እንደ ስቃይተኛም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ ጌታም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ፥ ተሰቀየም፥ አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? አሟሟቱን ከክፉዎችም ጋር፥ መቃብሩን ከባለጠጎችም ጋር አደረጉ፤ ግፍ ግን አላደረገም ነበር፤ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። ጌታም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የጌታም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ አገልጋዬ በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፤ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአል፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ። አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል ጌታ። የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትስፋፊያለሽ፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳሉ፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋሉ። አታፍሪምና አትፍሪ፤ አትዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም። ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዳጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል። ጌታ እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ። ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ። በጥቂት ቁጣ ለቅጽበተ ዐይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፥ በዘለዓለምም ቸርነት እምርሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ ጌታ። ይህ ለኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፥ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ። ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል የሚራራልሽ ጌታ። አንቺ የተሸገርሽ በአውሎ ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። የግንብሽንም ጉልላት በቀይ ዕንቁ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቁ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። ልጆችሽም ሁሉ ከጌታ የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አይቀርብም። እነሆ፥ ጥቃት ቢደርስብሽ፥ ከእኔ ዘንድ ግን አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚነሡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ። እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ አንጥረኛን የፈጠርኩ እኔ ነኝ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ። በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም የሚነሣብሽን ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የጌታ አገልጋዮች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል ጌታ። እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። እንጀራ ላልሆነ ነገር ገንዘብን ለምን ታባክናላችሁ፥ የድካማችሁንም ዋጋ በማያጠግብ ነገር ለምን ትለውጣላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ሰውነታችሁ በሕይወት እንድትኖር ስሙኝ፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ ጌታ የማያውቅህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣል። ጌታ በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ ጌታም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፤ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል ጌታ። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ እንድታበቅልና እንድታፈራም እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ፥ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፤ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል ይላሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፈንታ ጥድ፥ በኩርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለጌታም መታሰቢያና ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ፤ ጽድቅንም አድረጉ። ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ፥ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። ወደ ጌታም የተጠጋ መጻተኛ፦ “በእውነት ጌታ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ ጃንደረባም፦ “እነሆ፥ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰንበቴን ለሚጠብቁ፥ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ለሚመርጡ፥ ቃል ኪዳኔንም ለሚይዙ ጃንደረቦች፥ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ሁሉ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ። ያገለግሉት ዘንድ የጌታንም ስም ለመውደድ አገልጋዮቹም ለመሆን ወደ ጌታ የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን፥ በቃል ኪዳኔኔም የሚጸኑትን ሁሉ፥ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ። ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስብለታለሁ ይላል። እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ፥ እናንተም የዱር አራዊት ሁሉ፥ ትበሉ ዘንድ ቅረቡ። ጉበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉም እውቀት የላቸውም፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው፤ መጮኽ አይችሉም፤ ሕልምን ያልማሉ፤ ይተኛሉ፤ እንቅልፍ ይወድዳሉ። መብል የሚወዱ ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፤ እረኞቹም ማስተዋል የማይችሉ ናቸው፤ ሁሉም ወደ መንገዳቸው ዞሩ፥ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ፥ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል። “ኑ የወይን ጠጅ እንውሰድ፥ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፤ ዛሬም እንደሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፥ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል” ይላሉ። ጻድቅ ይሞታል፥ ማንም ልብ አይለውም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጻድቃን ከክፉ እንዲድኑ መወሰዳቸውን ማንም አያስተውልም። ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአምንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? እናንተ በባሉጥ ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣዎችሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቁርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቁርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣም? ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን፦ ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጉልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው፥ ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረዳሽም። ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። እርሱም፦ “ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል። ለዘለዓለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘለዓለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። ኃጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቁጣ ከእርሱ ሰወርኩ፤ እርሱ ግን በመንገዱ ገፋበት። መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እሰጣለሁ። የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል ጌታ። ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ሊል አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጉድፍ ያወጣሉ። ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ። በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ለማወቅ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝቦች እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወዳሉ። “ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ለማሰማት ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነው? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ እንዲያደርግ፥ ማቅንና አመድንም በበታቹ እንዲያነጥፍ ነው? በውኑ ይህን ጾም፥ በጌታ ዘንድ የተወደደ ቀን ብለህ ትጠራዋለህ? እኔስ የመረጥሁት ጾም፥ የበደልን እስራት እንድትፈቱ፥ የቀንበርንስ ጠፍር እንድትለቁ፥ የተገፉትን አርነት እንድታወጡ፥ ቀንበሩን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ እንድትቈርስ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ እንድታስገባ፥ የተራቈተውን ብታይ እንድታለብሰው፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የጌታም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ ጌታም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ በጣትህም መጠቆም ብትተው፥ ባታንጐራጉርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። ጌታም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የአውራ መንገድ አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ፥ እግርህን ወደ ሰንበት፥ ሰንበትንም ደስታ፥ ጌታንም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ በራስህ መንገድህን ከመጓዝ፥ ፈቅድህንም ከመፈጸም፥ ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ በዚያን ጊዜ በጌታ ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ ይህን የጌታ አፍ ተናግሮአልና። እነሆ፥ የጌታ እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም መስማት አልተሳናትም፤ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል የመለያያ አጥር ሆናለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፤ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በእርባና ቢስ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጉዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል። የእባብን እንቁላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ ራሳቸውንም በሠሩት መሸፈን አይችሉም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጉስቁልናና ውድመት በሚሄዱበት አለ። የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በአካሄዳቸውም ፍትህ የለም፤ መንገዳቸውን አጣመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም። ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፤ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፤ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን። እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዐይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን። ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፤ እንደ ርግብ በመቃተት እንጮኻለን፤ ፍትህን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱ ግን የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል። ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ ጌታን ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። ፍትህም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለም። እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ተበዝባዥ ሆኗል። ጌታም አየ፥ ፍትህም ስለ ሌለ ተከፋ። ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ የራሱም ጽድቅ ደገፈው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቁጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል። እርሱ የጌታ ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የጌታን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል ጌታ። ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይለይም፥ ይላል ጌታ። ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የጌታም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ ጌታ ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፥ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሟቸዋል። በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጽግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ከከሳባ የሆኑት ሁሉ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፥ የጌታን ምስጋና ያወራሉ። የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። ርግቦች ወደ ጎጇቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለጌታ ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ፥ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ለማምጣት፥ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል። በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና ባዕዳን ቅጥርሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል። በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጽግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ለማምጣት ሌሊትና ቀን አይዘጉም። ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ። የመቅደሴንም ስፍራ ለማስጌጥ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው፥ ባርሰነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ። የአስጨናቂዎችሽ ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የጌታም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል። ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘለዓለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ። የአሕዛብንም ወተት ትጠጫልሽ፥ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም ጌታ፥ የያዕቆብ ኃያል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደሆንሁ ታውቂያለሽ። በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤ ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ። ከዚያ በኋላ ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽም ይሆናልና በቀን ብርሃንሽ ፀሐይ መሆኑ ይቀራል፤ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያስፈልግሽም። ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም፥ ጨረቃሽም አትገባም። ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እንድከብር የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘለዓለም ይወርሳሉ። ታናሹ ለሺህ፥ የሁሉም ታናሹ ኃያል መንግሥት ይሆናል፤ እኔ ጌታ በዘመኑ ይህን በፍጥነት አደርገዋለሁ። የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ ጌታ ቀብቶኛልና፥ ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፥ ለተማረኩትም ነጻነትን፥ ለታሰሩትም መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት፥ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እንዳውጅ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ እንዳጽናና፥ ጌታ ለክብሩ የተከላቸው ጽድቃዊ የባሉጥ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች በአመድ ፋንታ አክሊልን እንዳደርግላቸው፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እንድሰጣቸው ልኮኛል። ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ፥ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ይሠራሉ። መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ባዕዳንም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የጌታ ካህናት ትባላላችሁ፤ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በሀብታቸውም ትከብራላችሁ። በኀፍረታችሁ ፈንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፤ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፋንታችሁ ደስ ይለዋል፤ ስለዚህ የምድራቸውን ሁለት እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘለዓለምም ደስታ ይሆንላቸዋል። እኔ ጌታ ፍትህን የምወድ፥ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ፤ ፍዳቸውንም በእውነት እሰጣቸዋለሁ፥ ከእነርሱም ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ። ዘራቸውም በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ ጌታ የባረከው ዘር እንደ ሆኑ ይገነዘባል። አክሊልን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማትዋም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች። ምድርም ቡቃያዋን እንደምታወጣ፥ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፥ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል። ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪ ወጣ ድረስ፥ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም አላርፍም። አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የጌታም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። በጌታ እጅ የውበት አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን ጌታ ደስታዬ ባንቺ ነው ብሏታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች። ጎልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም። እናንት ወደ ጌታ አቤት፤ አቤት የምትሉ፤ ፈጽሞ አትረፉ፤ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ለእርሱም ዕረፍት አትስጡት። ጌታ፦ ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤ ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል ጌታንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሏል። እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጎዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓርማ አሳዩ። እነሆ፥ ጌታ ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፦ ለጽዮን ልጅ፦ “እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር፥ ሥራውም በፊቱ አለ” በሏት። “ጌታ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተፈለገች፥ ያልተተወችም ከተማ” ትባያለሽ። ይህ ከኤዶምያስ፥ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፥ አለባበሱ ያማረ፥ በጉልበቱ ጽናት የሚራመድ ማን ነው? “በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ።” “ቀሚስህ ስለምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለምን መሰለ?” “መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቁጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፥ ልብሴንም ሁሉ አሳድፌአለሁ። የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና። ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቁጣዬም አጸናኝ። በቁጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸውንም ምድር ላይ አፈሰስኩት።” ጌታ ስላደረገልን ሁሉ፥ የጌታን ቸርነትና የጌታን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን የተትረፈረፈ ጽኑ ፍቅር እናገራለሁ። እርሱም፦ “በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው” አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ጠላታቸው ሆነ፤ እርሱ ራሱ ተዋጋቸው። እርሱም የቀደመውን ዘመን እንዲህ ብሎ አሰበ፦ የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለው? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለው? የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘለዓለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ እንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የጌታ መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ለእኔ ተከለከለ? አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ ጌታ አንተ አባታችን ነህ፤ ስምህም ከዘለዓለም ታዳጊያችን ነው። አቤቱ ጌታ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ አገልጋዮችህ ስትል ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ። የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም መቅደስን ረግጠውታል። ከዘለዓለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል። ምነው ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ! ምነው ተራሮችም ቢናወጡ! እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ እንዲገለጥ፥ አሕዛብም በፊትህ እንዲንቀጠቀጡ፤ ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ አንተ ወረድህ፥ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ማንም አልሰሙም፥ የትኛውም ጆሮ አልተቀበለውም፥ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላችው ከአንተ አምላካችን በቀር ሌላ ማንም አላየውም። ጽድቅን የሚያደርገውን፥ በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ። እኛ ኃጢአት ሠራን፤ እነሆ፥ አንተ ተቈጥተህ ነበር፤ ፊትህን ስለሰወርክብን እኛ ተሳሳትን። ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል። አሁን ግን፥ አቤቱ ጌታ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። አቤቱ ጌታ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘለዓለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፥ እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ፥ ኢየሩሳሌምም የተተወች ሆናለች። አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፤ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈራርሷል። አቤቱ ጌታ፥ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን? ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ፦ “አለሁኝ፥ አለሁኝ” አልኩት። መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። ይህ ሕዝብ ዘወትር በፊቴ ቁጣን ይቀሰቅሳሉ፥ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ፥ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥ በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ ምሽቱንም በስውርም ስፍራ የሚያሳልፉ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። ማሰሮዎቻቸው በረከሰ ነገር የተሞሉ ናቸው። እነርሱም፦ “ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ” ይላሉ፤ እነዚህ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት፥ በአፍንጫዬ ስር የምታልፍ ጢስ ናቸው። እነሆ፥ በፊቴ እንዲህ ተጽፎአል፦ “ዝም አልልም፤ ነገር ግን እንደ ሥራው እሰጠዋለሁ፤ የእጃቸውንም እከፍላቸዋለሁ። በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው ለሠሩት ሥራቸውን የእጃቸውን እሰጣቸዋለሁ።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ፥ “በረከት በእርሷ ላይ አለና አታጥፉት” እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ አገልጋዮቼ እንዲሁ አደርጋለሁ። ከያዕቆብም ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኳቸው ይወርሷታል፥ አገልጋዬቼም በዚያ ይኖራሉ። ለፈለገኝ ሕዝቤ ሳሮን የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮር ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ይሆናል። እናንተን ጌታን የተዋችሁትን ግን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ዕጣ ፋንታ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን የቀዳችሁትን፥ እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝም፤ በተናገርኩም ጊዜ አልሰማችሁኝም። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ። ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ አገልጋዮቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ ምክንያቱም የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአል፥ ከዓይኔም ተሰውሮአል። እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁ፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ትውስታቸውም አይኖርም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ የመቶ ዓመት ሳይሆነው የሚሞት እንደተረገመ ኃጢአተኛ ይታያል። ቤትም ይሠራሉ ይኖሩበታል፤ ወይንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል። እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም። እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ። ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሠማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ጉዳት አያደርሱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለች፤ እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል ጌታ። ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቁርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው። እጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል፤ እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ። ምክንያቱም በፊቴ ክፉ ነገርን አድርገዋል፥ ያልወደድሁትንም መርጠው በጠራኋቸው ጊዜ አልመለሱልኝም፤ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝም። እናንት በቃሉ ፊት የምትርዱ፥ የጌታን ቃል ስሙ፦ የጠሉአችሁ የናንተው ሕዝብ፥ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ፦ “ደስታችሁን እንድናይ ጌታ ይክበር” ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ። የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የጌታ ድምፅ ተሰምቶአል። ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያስጭንቃት ወንድ ልጅን ወለደች። ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳል? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ እንዳይወለድ አደርጋለሁን? ይላል ጌታ፤ ሊወልድ የተቃረበውን ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ። እናንተ የምትወዷት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፤ ስለ እርሷም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርሷ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፤ እንድትጠቡ ከማጽናናትዋም ጡት እንድትጠግቡ፥ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ እንዲላችሁ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆም፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጉልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏችኋል። እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የጌታም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል። እነሆ፥ ጌታ መዓቱን በቁጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። ጌታም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በጌታም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ። በመሀከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ መናፈሻ ስፍራው ለመግባት ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ፥ አስጸያፊ ነገርንም፥ አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ። ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቃለሁ፤ አሕዛብንና ልሣናትን ሁሉ የምትሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፤ እነርሱም ይመጣሉ፥ ክብሬንም ያያሉ። በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ያዋን፥ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ ጌታ ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለጌታ ቁርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል ጌታ። ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል ጌታ። እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል ጌታ። እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ለመስገድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል ጌታ። ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ። በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃላት። በይሁዳ ንጉሥ በአሞን ልጅ በኢዮስያስ ዘመን፥ በመንግሥቱ በዓሥራ ሦስተኛው ዓመት የጌታ ቃል ወደ እርሱ መጣ። በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “በማሕፀን ውስጥ ሳልሠራህ በፊት አውቄሃለሁ፥ ከማሕፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።” እኔም፦ “ወዮ! ጌታ አምላኬ፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እንዴት እንደምናገር አላውቅም” አልሁ። ጌታ ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ብላቴና ነኝ’ አትበል፤ ወደ ምልክህ ሁሉ ትሄዳለህ፥ የማዝህንም ሁሉ ትናገራለህ። እኔ ላድንህ ከአንተ ጋር ነኝና በእነርሱ ምክንያት አትፍራ፥ ይላል ጌታ።” ጌታም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ፥ ቃሎቼን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ እነሆ፥ ዛሬ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፥ እንድታጠፋና እንድትገለባብጥ፥ እንድታንጽና እንድትተክል ሾሜሃለሁ።” ደግሞ የጌታ ቃል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም “የለውዝ በትር አያለሁ” አልኩት። ጌታም “ቃሌን ልፈጽመው ነቅቼ እየጠበቅሁ ነኝና መልካም አይተሃል” አለኝ። ሁለተኛም ጊዜ የጌታ ቃል “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም “የሚፈላ የሸክላ ድስት ከሰሜን ፊቱን አዘንብሎ አያለሁ” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለኝ “ከሰሜን በኩል የሚነሣ ጥፋት በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ በድንገት ይመጣባቸዋል። እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋም ባለ ቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ፥ እኔን ትተውኛል፤ ለሌሎችም አማልክት ዕጣንን አጥነዋል፤ ለእጃቸውም ሥራዎች ሰግደዋልና። አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ በእነርሱ ፊት እንዳላስፈራህ አትፍራቸው። እነሆ እኔም፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ የተመሸገ ከተማ፥ የብረትም ዓምድ፥ የናስም ቅጥሮች ዛሬ አድርጌሃለሁ። ከአንተም ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አንተን ላድንህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል ጌታ።” የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮዎች ላይ አውጅ፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ጽኑ ፍቅር የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስታውሼዋለሁ። እስራኤል ለጌታ ቅዱስ ነበረ፥ የአዝመራውም በኵራት ነበረ፤ የበሉት ሁሉ እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፥ ክፉም ነገር ይመጣባቸዋል፥ ይላል ጌታ።” የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “አባቶቻችሁ ከእኔ የራቁት፥ ከንቱነትንም የተከተሉት፥ ከንቱም የሆኑት ምን ስሕተት አግኝተውብኝ ነው? እነርሱም፦ ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ ጉድጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን ጌታ ወዴት አለ?’ አላሉም። ፍሬዋንና በረከትዋንም እንድትበሉ ወደ ፍሬያማ ምድር አስገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፥ ርስቴንም የተጠላች አደረጋችሁ። ካህናቱም፦ ‘ጌታ ወዴት አለ?’ አላሉም፥ የሕግ አዋቂዎች አላወቁኝም፤ ገዢዎችም ዐመፁብኝ፥ ነቢያትም በበዓል ትንቢት ተናገሩ፥ የማይረባውንም ነገር ተከተሉ። “ስለዚህ ከእናንተ ጋር ገና እከራከራለሁ፥ ይላል ጌታ፥ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ። ወደ ኪቲም ደሴቶች ተሻገሩና ተመልከቱ፥ ወደ ቄዳርም ላኩና በጣም በጥንቃቄ መርምሩ፥ እነሆ እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ እንደሆነ እዩ። በውኑ አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ክብሩን በማይረባ ነገር ለወጠ። ሰማያት ሆይ! በዚህ ተሣቀቁ፥ እጅግም ደንግጡና ተንቀጥቀጡ ይላል ጌታ። ሕዝቤ ሁለት ክፉ ነገሮችን ሠርቷል፤ እኔን የሕይወት ውኃ ምንጭን ትተውኛል፥ ውኃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጉድጓዶች ለራሳቸው ቆፍረዋል። “በውኑ እስራኤል ባርያ ነውን? ወይስ በቤት የተወለደ አገልጋይ ነውን? ስለምን ለብዝበዛ ሆነ? የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፥ ድምፃቸውንም አሰሙ፤ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፥ ከተሞቹም ፈርሰዋል የሚቀመጥባቸውም የለም። ደግሞም የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች የእራስሽን ዘውድ የሆነውን ፀጉርሽን ይላጩሻል። በመንገድ በመራሽ ጊዜ ጌታ አምላክሽን በመተው በራስሽ ላይ ይህን አላመጣሽምን? አሁንስ የሺሖርን ውኃ ለመጠጣት ወደ ግብጽ በመሄድሽ የምታገኚው ምን ነገር አለ? የኤፍራጥስንም ውኃ ለመጠጣት ወደ አሦር በመሄድሽ የምታገኚው ምን ነገር አለ? ክፋትሽ ይቀጣሻል ክህደትሽ ይገሥጽሻል፤ ጌታን አምላክሽን መተውሽ ምን ያኽል ክፉና መራራ ነገር እንደሆነ እወቂም፥ ተመልከቺም፤ እኔን መፍራት በአንቺ ውስጥ የለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብረሻል እስራትሽንም በጥሰሻል፤ አንቺም፦ ‘አላገለግልም’ አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ። እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን የተበላሸ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ? በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙናን አብዝተሽ ብትጠቀሚ እንኳ፥ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። አንቺስ፦ ‘ራሴን አላረከስኩም በዓሊምንም አልተከተልኩም’ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፥ ምን እንዳደረግሽም እወቂ፤ በመንገዶችዋ ላይ ወድያና ወዲህ የምትቅበዘበዥ ወጣት ግመል ሆነሻል፤ በምኞትዋ ነፋስን እንደምታሸትት፥ በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ፤ ከጋለው ምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚሹአት ሁሉ አይደክሙም፥ በወራትዋ ያገኙአታል። በባዶ እግርሽ ከመሄድ፥ ጉሮሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፤ አንቺ ግን፦ ‘ተስፋ የለኝም፥ አይሆንም! እንግዶችን ወድጄአለሁና፥ እከተላቸዋለሁም’ አልሽ። “ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር እንዲሁ የእስራኤል ቤት፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነብዮቻቸውም ያፍራሉ። ግንዱን፦ ‘አንተ አባቴ ነህ፤’ ድንጋዩንም፦ ‘አንቺ ወለድሺኝ’ ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፥ በመከራቸው ጊዜ ግን፦ ‘ተነሥተህ አድነን’ ይላሉ። ለራስህ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር ብዛት እንዲሁ ናቸውና እስቲ ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ። “ከእኔ ጋር የምትከራከሩት ለምንድን ነው? ሁላችሁ ዐምፃችሁብኛል ይላል ጌታ። ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፤ ተግሣጽን አልተቀበሉም፤ ሰይፋችሁ እንደሚሰባብር አንበሳ ነብዮቻችሁን በልቶአል። ትውልድ ሆይ! የጌታን ቃል ተመልከቱ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንኩባትን? ሕዝቤስ ስለምን፦ ‘እኛ ፈርጥጠናል፤ ዳግመኛ ወደ አንተ አንመጣም’ ይላሉ? በውኑ ኰረዳ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጣጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን በቍጥር ለማይቆጠሩ ቀናቶች ረስተውኛል። ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት በጥንቃቄ ታስተካክያለሽ! ስለዚህም ለክፉዎች ሴቶች እንኳ መንገድሽን አስተምረሻል። እንዲሁም ሲምሱ አልያዝሻቸውም ነገር ግን በልብሶችሽ ላይ የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብትፈጽሚም እንኳ አንቺ ግን፦ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ በእውነት ቁጣው ከእኔ ተመልሶአል’ አልሽ። እነሆ፦ ‘ኃጢአት አልሠራሁም’ ብለሻልና በፍርድ እከስሻለሁ። መንገድሽን ለመለወጥ ለምን በጣም ትሮጫለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ እንዲሁ ያሳፍርሻል። ከዚያ ደግሞ እጆችሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ትወጫለሽ፥ ምክንያቱም ጌታ የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽም።” እነሆ፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ብትሄድ ሌላም ወንድ ብታገባ፥ በውኑ በድጋሚ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ያች ምድር እጅግ የረከሰች አትሆንምን? አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል ጌታ። ወደ ተራቈቱ ኮረብቶች አይኖችሽን አንሺ፥ ተመልከቺም፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ልክ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አረባዊ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸዋለሽ፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የበልጉም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ቢኖርሺም እንኳ ለማፈር ግን እንቢ አልሽ። አሁን፦ ‘አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? ‘ለዘለዓለምስ ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን?’ እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገሮች አደረግሽ።” ጌታም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም አመነዘረች። ‘ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች’ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ፤ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርሷም ደግሞ ሄዳ እንደ አመነዘረች አየሁ። አመንዝራነትዋንም እንደ ቀላል በመቁጠሩዋ ምድሪቱን አረከሰች፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ ግን አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም፥ ይላል ጌታ። “ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። ሂድና ይህን ቃላት ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ! ተመለሽ፥ ይላል ጌታ፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣም፥ በአንቺ ላይ ፊቴን አላጠቁርም፥ ይላል ጌታ። በአምላክሽ በጌታ ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ድምፄንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል ጌታ። ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ ጌታችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል ጌታ፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤” እንደ ልቤም የሆኑ እረኞችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ያሰማርዋችኋል። በምድርም ላይ በበዛችሁና በበረከታችሁ ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያ ዘመን፦ “የጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት” ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስታውሱትም፥ አይሹትምም፤ በድጋሚም አይሠራም። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የጌታ ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ በጌታ ስም አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልኸኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳሉ፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ። እኔ ግን፦ “‘ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አስቀምጥሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር እጅግ የከበረችውን የአሕዛብን ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ፦ አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ፤ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር። የእስራኤል ቤት ሆይ! በእውነት ሚስት ባልዋን እንደምታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ ይላል ጌታ።’” የእስራኤል ልጆች መንገዳቸውን አጣምመዋልና፥ አምላካቸውንም ጌታን ረስተዋልና በተራቈቱ ኮረብቶች ላይ የልመናቸው የለቅሶ ድምፅ ተሰማ። “ከዳተኞች ልጆች ሆይ! ተመለሱ፥ ከዳተኛነታችሁንም እፈውሳለሁ።” “እነሆ፥ አንተ አምላካችን ጌታ ነህና ወደ አንተ መጥተናል። በእውነት ኮረብቶች ሐሰት ናቸው፥ በተራሮችም ላይ ሁከት ነው፤ በእውነት የእስራኤል መዳን በአምላካችን በጌታ ነው።” “ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችን ድካም፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ አሳፋሪ ነገር በልቶባቸዋል። ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የጌታን ድምፅ አልሰማንምና፥ በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይሸፍነን።” “እስራኤል ሆይ! ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል ጌታ፤ ርኩሰትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥ ‘በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ እራሳቸውን በእርሱ ይባርካሉ በእርሱም ይመካሉ።” ጌታ ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና፦ “ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ! ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለጌታ እራሳችሁን ግረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።” በይሁዳ ላይ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውጁ፦ “በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም፦ ‘ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ’ በሉ። ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፤ ሽሹ፥ አትዘግዩ። አንበሳ ከችፍግ ዱሩ ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚያጠፋ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ለማድረግ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ። የጌታ ጽኑ ቁጣ ከእኛ ላይ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ።” “በዚያም ቀን፥ ይላል ጌታ፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይሣቀቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ።” እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ፥ አንተ በእውነት ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ፦ ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ” አልሁ። በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም፦ “ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከተራቈቱ ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፤ ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።” እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን! ኢየሩሳሌም ሆይ! እንድትድኚ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያውጃል። ለአሕዛብ አሳውቁ፦ “እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ። በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል ጌታ። መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል።” አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ! የመለከትን ድምፅና የጦርነትን ሁካታ ሰምተሻልና ዝም ማለት አልችልም። መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል፤ ምድሪቱም ሁሉ ጠፍታለችና፤ በድንገትም ድንኳኔ በዐይን ቅጽበትም መጋረጃዎቼ ጠፉ። ዓላማውን የምመለከት፥ የመለከቱንስ ድምፅ የምሰማ እስከ መቼ ነው? “ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም፤ ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም።” ምድሪቱን አየሁ፥ እነሆም፥ ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም፤ ሰማያትንም አየሁ፥ ብርሃንም አልነበረባቸውም። ተራሮችን አየሁ፥ እነሆም፥ ተንቀጠቀጡ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ተናወጡ። አየሁ፥ እነሆም፥ ሰው አልነበረም፥ የሰማይም ወፎች ሁሉ ሸሽተው ነበር። አየሁ፥ እነሆም፥ ፍሬያማው እርሻ ምድረ በዳ ሆኖ፥ ከተሞችም ሁሉ ከጌታ ፊት ከጽኑ ቁጣው የተነሣ ፈርሰው ነበር። ጌታም እንዲህ ይላል፦ “ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፥ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም። ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፥ በላይም ሰማይ ይጠቁራል፤ ተናግሬአለሁና፥ አስቤአለሁም፤ አልጸጸትም ከእርሱም አልመለስም።” ከፈረሰኛና ከቀስተኛ ድምፅ የተነሣ ከተማ ሁሉ ትሸሻለች፤ ጥቅጥቅ ወዳለ ዱርም ይገባሉ በቋጥኝ ላይም ይወጣሉ፤ ከተማ ሁሉ ተለቅቃለች የሚቀመጥባትም ሰው የለም። አንቺም የተደመሰስሽ ሆይ! ምን ታደርጊአለሽ? ቀይ በለበስሽ ጊዜ፥ በወርቅ አንባርም ባጌጥሽ ጊዜ፥ ዓይንሽንም በኩል ተኩለሽ በተቆነጀሽ ጊዜ፥ በከንቱ እራስሽን ታጌጫለሽ፤ ውሽሞችሽ አቃለሉሽ፥ ነፍስሽን ይሹአታል። እንደታመመች የበኩርዋንም እንደምትወልድ ሴት የጭንቀት ድምፅ ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ታቃስታለች፥ እጆችዋንም በመዘርጋት፦ “በነፍሰ ገዳዮች ፊት ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ!” አለች። በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ። እነርሱም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ቢሉም እንኳ የሚምሉት በሐሰት ነው። አቤቱ! ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸዋልም ነገር ግን ተግሣጽን ለመቀበል እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ለመመለስ እንቢ አሉ። እኔም፦ “የጌታን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ ተሞኝተው ይህን አድርገዋል በእውነት ድሆች ናቸው፤ ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እነርሱንም አናግራቸዋለሁ፤ የጌታን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና” አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል። ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የከዳተኝነታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተኩላ ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ነቅቶ ይጠብቃል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል። “በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል፥ አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ። እንደ ተቀለቡ ምኞትም እንዳላቸው ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ። በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? “በወይኗ ትልሞች በመካከል ሂዱና አበላሹ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ የጌታ አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ። የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ አታለዋል ይላል ጌታ። “እነርሱም፦ ‘ምንም አያደርግም፤ ክፉ ነገርም አይመጣብንም፥ ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥ ቃሉም በእነርሱ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል’ ብለው ጌታን ክደዋል።” ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህን ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት፥ ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸዋለችም። የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ጽኑ ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው። የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ ሁሉም ኃያላን ናቸው። መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፤ የምትተማመንባቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደመስሳሉ። ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።” እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ፦ “አምላካችን ጌታ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለምን አደረገብን?” ቢሉ፥ አንተ፦ “እንደ ተዋችሁኝ፥ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳገለገላችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ታገለግላላችሁ” ትላቸዋለህ። ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ፦ እናንተ ሰነፎችና ልበ ቢሶች፥ ዐይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ! ይህን ስሙ። በውኑ እኔን አትፈሩምን? ይላል ጌታ፤ ከፊቴስ አትደነግጡምን? አልፎት እንዳይሻገር አሸዋን በዘለዓለም ትእዛዝ ለባሕር ድንበር አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፈውም። ይህ ሕዝብ ግን እልኸኛና ዐመፀኛ ልብ አለው፤ ዐምፀዋል ሄደዋልም። በልባቸውም፦ “የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን ጌታን እንፍራ” አላሉም። በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ። በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ ወፍ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ። ወፍ እንደሞላበት የወፍ ቀፎ፥ እንዲሁ ቤቶቻቸው በሽንገላ ተሞልቶአል፤ ስለዚህም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል። ወፍረዋል ሰብተዋልም፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆንላቸው አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግርተኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም። በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? አሠቃቂና አስደንጋጭ ነገር በምድሪቱ ላይ ሆኖአል፤ ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ወድደዋል፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ? እናንተ የብንያም ልጆች ሆይ! ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ለደህንነታችሁ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ። የተዋበችውንና የተቀማጠለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሳቁላለሁ። እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርሷ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል። “በእርሷ ላይ ጦርነት አዘጋጁ፤ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ።” “ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን!” “ተነሡ፥ በሌሊትም እንውጣ፥ የንጉሥ ቅጥሮቿንም እናፍርስ።” የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “ዛፎችዋን ቁረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ በመካከልዋ ያለው ነገር ሁሉ ግፍ ብቻ ነው። በጉድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርሷ ውስጥ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርሷ መካከል ይሰማል፥ ደዌና ቁስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ። ኢየሩሳሌም ሆይ! ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ማንም የማይኖርባት ምድር እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።” የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ወይኑን እንደሚለቅም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የተረፉትን ፈጽሞ ይለቅሙአችኋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ በቅርንጫፎቹ ላይ ዳግመኛ ዘርጋ።” እንዲሰሙኝስ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘ ነው፥ መስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የጌታ ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም። ስለዚህ በጌታ ቁጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ “በጎዳና ባሉ ሕፃናት ላይ በጉልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ደግሞም ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም በእድሜአቸው ከገፉት ጋር ይያዛሉና። እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና፤ ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥” ይላል ጌታ። “ከታናናሾቻቸው ጀምሮ እስከ ታላላቆቻቸ ድረስ ሁሉም በግፍ ለሚገኝ ጥቅም ስስታም ናቸውና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም ተንኰልን ይፈጽማሉ። የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ‘ሰላም ሰላም’ ይላሉ። ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርሷም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ ‘አንሄድባትም’ አሉ። እኔም፦ ‘የመለከቱን ድምፅ አድምጡ’ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን፦ ‘አናደምጥም’ አሉ። አሕዛብ ሆይ! ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ! በእነርሱ ምን እንደሚደርስባቸው እወቁ። ምድር ሆይ! ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሎቼን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉት፥ በዚህ ሕዝብ ላይ የሐሳባቸውን ፍሬ፥ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ። ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር የከበረውንም ዘይት ታመጡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም፥ ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራውም ይጠፋሉ።’ ” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻዎች ይነሣል። ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኻል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ! ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።” ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል። የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በመንገድም ላይ አትሂዱ። የሕዝቤ ሴት ልጅ ሆይ! ማቅ ልበሺ፥ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ። “መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል አቅላጭና ፈታኝ አድርጌሃለሁ። እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኩሰትን ያደርጋሉ። ወናፉ በኃይል አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል ነገረ ግን ኃጢአተኞች አልተወገዱም። ጌታ ጥሎአቸዋልና ‘የተጣለ ብር’ ብለው ይጠሩአቸዋል።” ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። “በጌታ ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል በዚያ እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ጌታን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሰዎች ሆይ! ሁላችሁ የጌታን ቃል ስሙ። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ። ‘የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ ይህ ነው’ እያላችሁ በእነዚህ የሐሰት ቃላት አትታመኑ። መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትጨቊኑ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም እንዳይሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥ ከጥንት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር፥ በዚህ ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ። “እነሆ፥ በማይረባ በሐሰት ቃላት ታምናችኋል። ትሰርቃላችሁን፥ ትገድላላችሁን፥ ታመነዝራላችሁን፥ በሐሰትም ትምላላችሁን፥ ለበዓልም ታጥናላችሁን፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁን፤ መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ፦ እነዚህን አስጸያፊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማድረግ ‘እኛ ድነናል’ አላችሁ። ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ ራሴ አይቻለሁ፥ ይላል ጌታ።” ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ምን እንዳደረግሁበት እዩ። አሁንም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ይላል ጌታ፥ በማለዳም ተነሥቼ ባለማቋረጥ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ። የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ። “እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው። እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? እኔን ለማስቆጣት፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ፥ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ፤ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቁርባን ያፈስሳሉ። እኔን ያስቈጣሉን? ይላል ጌታ፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቁጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይወርዳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።” የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሌላ መሥዋዕቶቻችሁ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ። ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። ነገር ግን፦ “ድምፄን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም እንዲሆንላችሁ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ” ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። ነገር ግን በክፉ ልባቸው ሐሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ላክሁባችሁ። ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ። “ይህን ሁሉ ቃላት ለእነርሱ ትናገራለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም።” አንተም፦ “የአምላኩን የጌታን ድምፅ ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ታጥቶአል። ጌታ የቁጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጉርሽን ቁረጪ፥ ጣዪውም፥ በተራቈቱ ኮረብቶችም ላይ ሙሾን አውጪ፥” ትላቸዋለህ። “የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል ጌታ፤ ሊያረክሱትም ስሜ በተጠራበትን ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኑረዋል። እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ለማቃጠል፥ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያሉትን የቶፌት መስገጃዎችን ሠረተዋል። ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከመታጣቱ የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም። ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ አጠፋለሁ። “በዚያን ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቿን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ። በወደዱአቸውና ባገለገሉአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፤ አይሰበሰቡም አይቀበሩምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ። እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህም ክፉ ወገን የቀሩትን ትሩፋን ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። “እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን? እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን አጥብቀው ይዘዋል፥ ለመመለስም እንቢ ብለዋል። አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ አንድም ሰው፦ ‘ምን አድርጌአለሁ?’ ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ጦርነትም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። እንዲሁም ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጫቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የጌታን ፍርድ አላወቁም። “እናንተስ፦ ‘ጥበበኞች ነን የጌታንም ሕግ ከእኛ ጋር ነው’ እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ በውኑ የጸሐፊዎች ሐሰተኛ ብዕር ሐሰት አድርጎታል። ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠዋል ተማርከዋልም፤ እነሆ፥ የጌታን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው? ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉም በግፍ ለሚገኝ ጥቅም ስስታም ነውና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ። የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ‘ስለም ሰላም’ ይላሉ። አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል ጌታ።” ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፤ የሰጠኋቸሁም ይጠፋባቸዋል። ዝም ብለን ለምን እንቀመጣለን? ጌታን ስለ በደልን አምላካችን ጌታ አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ። ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ መፈወስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። “የፈረሶቻቸው ድምፅ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርሷም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። እነሆ፥ መርዛቸውን አስማት የማያረክሰው እባቦችንና እፉኝቶችን በእናንተ መካከል እልካለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል፥” ይላል ጌታ። ኀዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል። እነሆ፦ “ጌታ በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርሷ መካከል የለምን?” የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። “በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድነው?” “መከሩ አልፎአል፥ በጋው ተፈጽሟል፥ እኛም አልዳንም።” በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠቁሬአለሁም፤ ፍርሀትም ይዞኛል። በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለምን አልሆነም? ተወግተው ስለ ሞቱት ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን እንዳለቅስ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እንድተው፥ ከእነርሱም ተለይቼ እንድሄድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና፥ እኔንም አላወቁምና፥ ይላል ጌታ። ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገሩም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ለማወቅ እንቢ ብለዋል፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸዋለሁም፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድነው? ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ፤ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል። በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀስፋቸውምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? “ለተራሮች ልቅሶንና እንጉርጉሮን ለምድረ በዳ ማሰማርያዎችም ዋይታን አነሣለሁ፥ ሰው እንዳያልፍባቸው ባድማ ሆነዋልና። ሰዎችም የከብቱን ድምፅ አይሰሙም፤ ከሰማይ ወፎች ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። ኢየሩሳሌምንም የፍርስራሽ ክምር የቀበሮም ማደሪያ አደርጋታለሁ፥ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይቀመጥባት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” ይህን የሚያስተውል ጠቢብ ሰው ማን ነው? እንዲያውጅስ የጌታ አፍ ለማን ተናገረ? ሰው እንዳያልፍባት ምድርስ ስለምን ጠፋች፥ እንደ ምድረ በዳስ ስለምን ተቃጠለች? ጌታም እንዲህ አለ፦ “የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተዋልና፥ ድምፄንም አልሰሙምና፥ በእርሱም አልተመላለሱምና፥ ነገር ግን የልባቸውን እልከኝነትና አባቶቻቸው ያስተማሩአቸውን በኣሊምን ተከትለዋልና ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህን ሕዝብ እሬትን አበላዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ። እነርሱና አባቶቻቸውም ባላወቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ በስተ ኋላቸው ሰይፍን እልክባቸዋለሁ።” የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “አስተውሉ፥ እንዲመጡም አልቃሾች ሴቶችን ጥሩ፤ እንዲመጡም ወደ ብልሃተኞች ሴቶች ላኩ፤ ዐይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ የዓይናችንም ሽፋሽፍቶች ውኃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ያነሳሱ። በጽዮን፦ ‘እንዴት ተበዘበዝን! ምድሪቱንም ትተናልና፥ ቤቶቻችንንም አፍርሰዋልና እንዴት አብዝተን አፈርን!’ የሚል የልቅሶ ድምፅ ተሰምቶአል።” እናንተ ሴቶች ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ ጆሮአችሁም የአፉን ቃል ትቀበል፥ ለሴቶች ልጆቻችሁም ልቅሶውን፥ እያንዳንዳችሁም ለባልንጀሮቻችሁ ዋይታውን አስተምሩ። ሕፃናቱን ከመንገድ ጉልማሶቹንም ከአደባባይ ለማጥፋት ሞት ወደ መስኮታችን ደርሶአል ወደ ንጉሥ ቅጥሮቻችን ውስጥ ገብቶአል። ተናገር፥ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰውም ሬሳ እንደ ጉድፍ በእርሻ ላይ፥ ማንምም እንደማይሰበስበው ከአጫጆች በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ ይወድቃል።’ ” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ ጌታ መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ ነገሮች እነዚህ ናቸውና፥ ይላል ጌታ።” “እነሆ፥ ሸለፈታቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ እንዲሁም የእስራኤል ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና፥ አሕዛብም ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና ግብጽንና ይሁዳን፥ ኤዶምያስንም፥ የአሞንንም ልጆች፥ ሞአብንም፥ በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጉራቸውን በዙሪያ የተላጩትን ሁሉ በዚያን ዘመን እቀጣለሁ።” እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ! ጌታ በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፥ ከሰማይ ምልክቶችም የተነሣ አትፍሩ፤ አሕዛብ ከእነርሱ የተነሣ ይፈራሉና። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሞያተኛውም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። በዱባ እርሻ (የአትክልት ስፍራ) ውስጥ እንዳለ እንደ ወፍ ማስፈራርያ ዓምድ ናቸው፥ እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም ስለማይችሉ ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራት አይችሉምና፥ ደግሞም መልካም መሥራት በእነርሱ ውስጥ የለምና አትፍሩአቸው።” ጌታ ሆይ! እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለ ሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? በአንድ ጊዜ ቂላ ቂሎችና ሞኞች ሆነዋል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት ከግዑዝ እንጨት የማይሻልን ነገር ብቻ ነው። የሞያተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ሐምራዊ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። ጌታ ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቁጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን መቋቋም አይችሉም። እናንተም፦ “ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ” ትሉአቸዋላችሁ። ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳርቻ ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። ሰው ሁሉ ቂላ ቂልና እውቀት የሌለው ሆኖአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። የያዕቆብ ድርሻ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ ነው። በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ! ዕቃሽን ከመሬት ሰብስቢ፤ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ በምድሪቱ የሚኖሩትን እስኪሰማቸው ድረስ በዚህ ጊዜ እወነጭፋቸዋለሁ፥ አስጨንቃቸዋለሁም።” ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቁስሌም የማይሽር ነው፥ እኔ ግን፦ “በእውነት የመከራ ቁስሌ ነው እርሱንም መሸከም ይገባኛል” አልሁ። ድንኳኔ ተበዘበዘ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፤ ልጆቼም ከእኔ ወጥተው አይገኙም፤ ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም። እረኞች ቂላ ቂል ሆነዋልና፥ ጌታንም አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል። የወሬን ድምፅ ስሙ፤ እነሆም፥ የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ሊያደርጋቸው ከሰሜን ምድር ጽኑ ሽብር መጥቷል። አቤቱ! የሰው መንገድ ከራሱ እንዳልሆነ አውቃለሁ፥ ሰውም አካሄዱን ለመምራት የሚራመድ አይደለም። አቤቱ! ገሥጸኝ፤ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን። ያዕቆብን በልተውታልና፥ ውጠውታልምና፥ አጥፍተውታልምና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አውርድ። ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። “የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ስማ፥ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገር፥ እንደዚህም በላቸው፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፥ ይህንንም ከግብጽ አገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝኩት ቃላት ነው፤ አልሁም፦ ድምፄን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ይህ ዛሬ እንደሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ እንድሰጣቸው የማልሁትን መሐላ እንዳጸና ነው።” እኔም፦ “አቤቱ! አሜን” ብዬ መለስሁለት። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህን ቃላት ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፥ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ስሙ አድርጉትም። አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ በመነሳት ደጋግሜ እያስጠነቀቅሁ፦ ድምፄን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር። እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ሁሉ አመጣሁባቸው።” ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ መካከል አድማ ተገኝቶአል። ቃሌንም ለመስማት እንቢ ወዳሉ ወደ ቀድሞው አባቶቻቸው ኃጢአት ተመለሱ፥ ሊያገለግሉአቸውም እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም። በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ይጮኻሉ፤ ነገር ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ አያድኑአቸውም። ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለአሳፋሪ ነገር መሠዊያዎችን ሠርታችኋል፥ እነርሱም ለበዓል የምታጥኑባቸው መሠዊያዎች ናቸው። አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ከመከራቸው የተነሣ ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱም ጩኸትና ልመና አታድርግ። “ክፋትን አብዝታ በመሥራትዋ ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ምን አላት? የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ከዚያም ደስተኛ ትሆኛለሽን?” ጌታ ስምሽን፦ “በመልካም ፍሬ የተዋበች የለመለመች የወይራ ዛፍ” ብሎ ጠራው፤ በጽኑ ዐውሎ ነፋስ ጩኸት እሳትን አነደደባት፥ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል። ለበዓልም በማጠናቸው አስቈጡኝ፥ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ ክፉን ነገር ተናግሮብሻል። ጌታም አስታወቀኝ እኔም አወቅሁ፤ ሥራቸውንም ገለጥህልኝ። እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ፤ እነርሱም፦ “ዛፉን ከነፍሬው እናጥፋ፥ ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታወስ ከሕያዋን ምድር እናስወግደው” ብለው ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር። ነገር ግን ኩላሊትንና ልብን የምትመረምር በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ! ሙግቴን ገልጬልሃለሁና በእነርሱ ላይ የሚሆነውን በቀልህን ልይ። ስለዚህም፦ “በእጃችን እንዳትሞት በጌታ ስም ትንቢት አትናገር” ብለው ነፍስህን ስለሚሹ ስለ ዓናቶት ሰዎች የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እቀጣቸዋለሁ፤ ጉልማሶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚተርፍ የለም። አቤቱ! ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚበድሉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል? ተክለሃቸዋል፤ ሥርም ሰድደዋል፤ አድገዋል ፍሬም አፍርተዋል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። አቤቱ! አንተ ግን፥ አውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፥ ልቤንም ወደ አንተ መሆኑን ፈትነሃል፤ እንደ ሚታረድ በግ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ እጽዋት ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች፦ “ፍጻሜያችንን አያይም” ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ተጠራርገው ጠፍተዋል። “ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ተሰናክለህ ከወደቅህ፥ በዮርዳኖስ ዱር እንዴት ታደርጋለህ? ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፤ በመልካምም ቢናገሩህም አትመናቸው።” “ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋን በእኔ ላይ አንሥታለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። ርስቴ እንደ ዝንጉርጉር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ እንዲበሉም አምጡአቸው። ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል። ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፤ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት ማንም የለም። በምድረ በዳ ባሉ በተራቈቱ ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የጌታ ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፤ እራሳቸውን አደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፤ ስለ ጌታ ጽኑ ቁጣ በፍሬያችሁ ታፍራላችሁ።” ጌታ ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጎረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ። በበዓል እንዲምል ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ፦ ‘በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለው እንዲምሉ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋዋለሁም፥ ይላል ጌታ።” ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራን መታጠቂያ ለእራስህ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቀው፤ በውኃም ውስጥ አትንከረው።” እንደ ጌታም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁት። የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እኔ መጣ እንዲህም አለኝ፦ “የገዛኸውን በወገብህ ያለውን መታጠቂያ ወስድ፥ ተነሣም፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።” ጌታም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግሁት። ከብዙ ቀንም በኋላ ጌታ፦ “ተነሣ፥ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም እንድትሸሽገው ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከዚያ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያውን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያው ተበላሽቶ ነበር፥ ለምንም አይረባም። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አጠፋለሁ። ቃሌን ለመስማት እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ሊያገለግሉአቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፥ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማይረባ እንደዚህ መታጠቂያ ይሆናሉ። መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደሚጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም፥ ምስጋናና ክብር እንዲሆኑልኝ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን አልሰሙም።” ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ይህን ቃል ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንደሚሞላ በእርግጥ እኛ አናውቅምን?” ይሉሃል። አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። ሰውንም ከሰው ጋር፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ አላትማቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም።” ስሙ፥ አድምጡም፤ ጌታ ተናግሮአልና አትታበዩ። ሳትጨልም እግራችሁም በጨለሙት ተራሮች ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨልማ ሳይለውጠው፥ ለአምላካችሁ ለጌታ ክብርን ስጡ። ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የጌታም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ እጅግ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች። ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ ፦ “የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ” በል። የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል። “ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? በልብሽም፦ ‘እነዚህ ነገሮች ስለምን ደረሱብኝ?’ ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንተ ክፋትን የለመዳችሁ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ፥ የለካሁልሽም ድርሻሽ ይህ ነው፥ ይላል ጌታ። ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የአመንዝራነትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?” ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። “ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ ስለ ምድሪቱም አለቀሱ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሏል። ታላላቆቻቸውም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ላኩ፤ ወደ ጉድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ። በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ። ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች። የሜዳ አህዮችም በተራቈቱ ኮረብቶች ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዐይኖቻቸው ጠወለጉ። “ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአትን ሠርተናል፤ ምንም እንኳ ኃጢአታችን ቢመሰክርብንም ስለ ስምህ ብለህ አቤቱ! አድርግ። አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ! በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድሪቱ እንደ እንግዳ፥ ሌሊቱን ለማሳለፍ ወደ ማደርያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ለምን ትሆናለህ? ግራ እንደ ተጋባ ሰው፥ ለማዳንም እንደማይችል ኃያል ለምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ! በመካከላችን ነህ፥ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።” ጌታ ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “በእውነት መቅበዝበዝን ወድደዋል፥ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ ጌታ በእነርሱ ደስ አይሰኝም፥ በደላቸውንም አሁን ያስታውሳል ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።” ጌታም፦ “ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው። በጾሙ ጊዜ ልመናቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ ይልቁንም በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ” አለኝ። እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት፦ ‘ዘላቂ ሰላም በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም’ ይሉአቸዋል” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ነቢያቱ በስሜ የውሸትን ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸትን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። ስለዚህ ጌታ በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት፦ ‘በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም’ ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል፦ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይጣላሉ፤እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም፤ ክፋታቸውንም በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ። ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና ፈጽሞ በማይሽር ቁስል ቆስላለችና ዐይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፍስሱ። ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ ደዌ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቁት አገር ሄደዋልና።’” በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለምን መታኸን? ፈውስስ ስለምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። አቤቱ! በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን። ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስታውስ እንጂ አታፍርስ። በውኑ በአሕዛብ ከንቱ ጣዖታት መካከል ዝናብን ሊያዘንብ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ካፊያን መስጠት ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ! አንተ አይደለህምን? አንተ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን። ጌታም እንደዚህ አለኝ፦ “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም እንኳ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አያዘነብልም፤ ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ። እነርሱም፦ ‘ወዴት እንውጣ?’ ቢሉህ፥ አንተ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ’ ትላቸዋለህ። ሰይፍን ለመግደል፥ ውሾችንም ለመጐተት፥ የሰማያትንም ወፎች የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ ዐራቱን ዓይነት ጥፋት ልኬባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። የይሁዳም ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስላደረገው ሁሉ፥ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። “ኢየሩሳሌም ሆይ! የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ቆም ብሎ የሚጠይቅ ማነ ነው? አንቺ እኔን ትተሺኛል፥ ይላል ጌታ፥ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጥፍቼሻለሁ፤ ይቅርታን ከማድረግ ደክሜአለሁ። በምድሪቱም ደጆች ውስጥ በመንሽ አበጥሬአቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፥ ሕዝቤንም አጥፍቼአለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም። መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተውብኛል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጣርንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ። ሰባት የወለደች ደክማለች፥ ነፍስዋንም አውጥታለች፤ ቀን ገና ሳለ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች ተዋርዳለችም፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ ይላል ጌታ።” እናቴ ሆይ፥ ወዮልኝ! ለምድር ሁሉ የሙግትና የጥል ሰው የሆንሁትን ወለድሽኝ፤ ለማንም አላበደርሁም፥ ማንም ለእኔ አላበደረም፥ ነገር ግን ሁሉ ይረግመኛል። ጌታ እንዲህ አለ፦ በእውነት ለመልካም ነገር አጸናሃለሁ፤ በእውነት በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላትህ እንዲለምንህ አደርገዋለሁ። በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን? “በመላ ግዛቶችህ ውስጥ ስላለ ኃጢአትህ ሁሉ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለብዝበዛ በከንቱ አሳልፌ እሰጣለሁ። የምታቃጥላችሁ እሳት ከቁጣዬ ትነድዳለችና ከጠላቶችህ ጋር ወደማታውቀው ምድር አሻግርሃለሁስ።” አቤቱ! አንተ ታውቃለህ፤ አስታውሰኝ ጐብኘኝም፥ የሚያሳድዱኝንም ተበቀልልኝ፤ ቁጣህንም ከማዘግየትህ የተነሣ እንዳታጠፋኝ፤ ስለ አንተ ስድብን እንደ ታገሥሁ እወቅ። ቃላትህ ተገኝተዋል እኔም በልቼአቸዋለሁ፤ አቤቱ! የሠራዊት አምላክ ጌታ ሆይ! በስምህ ተጠርቻለሁና ቃላትህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆኑኝ። በዋዘኞች ጉባኤ አልተቀመጥኩም አልተደሰትኩምም፤ ቁጣን ሞልተህብኛልና እጅህ በእኔ ላይ ስለ ሆነ ለብቻዬ ተቀመጥሁ። ለምን ሕመሜ የማያቋርጥ ሆነ? ቁስሌስ የማይፈወስ ለምን ሆነ? ለምንስ፦ አልሽርም አለ? በውኑ እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃ ትሆንብኛለህን? ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ላድንህና ልታደግህ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም፥ ይላል ጌታ። ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፥ ከጨካኞችም እጅ እቤዥሃለሁ።” የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ። ጌታ በዚህ ስፍራ በተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ በወለዱአቸውም እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር በወለዱአቸው አባቶቻቸው ላይ እንዲህ ይላልና፦ በክፉ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰላሜን፥ ቸርነትንና ጽኑ ፍቅርን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ለማልቀስም ሆነ ለማዘን አትሂድ። ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፥ ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፥ ስለ እነርሱም ማንም ገላውን አይነጭም ራሱንም አይላጭም፤ ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የኀዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። ለመብላትና ለመጠጣት፥ ከእነርሱም ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም፥ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራቱይን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ። “ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃላት ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፦ ‘ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገርን ለምን ጌታ ተናገረብን? በደላችንስ ምንድነው? በአምላካችንስ በጌታ ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድነው?’ ቢሉህ፥ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፥ ይላል ጌታ፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አገለገሉአቸውም ሰገዱላቸውም፥ እነርሱም ትተውኛል፥ ሕጌንም አልጠበቁም፤ እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም፥ ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ እልከኝነት ሄዳችኋል እኔንም አልሰማችሁም። ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።’ “ስለዚህ፥ እነሆ፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ተብሎ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ። “እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ፥ ይላል ጌታ፥ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እልካለሁ፥ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድኑአቸዋል። ዓይኔ በመንገዶቻቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፥ ኃጢአታቸውም ከዓይኔ አልተሸሸገም። ምድሬንም በተጠሉ ጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።” አቤቱ! ኃይሌ፥ አምባዬ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ፥ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፦ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር የማይረባቸውንም ወርሰዋል፤ በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክት አድርጎ ይሠራልን?” “ስለዚህ፥ እነሆ፥ አስታውቃቸዋለሁ፥ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ ጌታ እንደሆነ ያውቃሉ።” “የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብዕር ተጽፎአል፤ በተሾለም ዕብነ አልማዝ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያዎቻችሁ ቀንዶች ተቀርጾአል። ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያዎቻቸውንና የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውን ያስታውሳሉ። በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ! ባለጠግነትህንና መዝገቦችህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣለሁ። አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ፥ በማታውቃትም ምድር ለጠላቶችህ ባርያ እንድትሆን አደርግሃለሁ፤ ለዘለዓለም የሚነድደውን እሳት በቁጣዬ አንድዳችኋልና።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፥ ልቡም ከጌታ የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። እርሱ በምድረ በዳ እንዳለ ቁጥቋጦ ነው፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በማይቀመጥበት፥ ጨው ባለበት ምድር፥ በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። በጌታ የታመነ ጌታም መተማመኛው የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሮቹን እንደሚዘረጋ፥ ሙቀትም በመጣ ጊዜ እንደማይፈራ፥ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም ከማፍራት እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።” የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? “እኔ ጌታ ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ።” ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ ባለጠግነትንም በቅን ባልሆነ መንገድ የሚሰበስብ ሰው እንዲሁ ነውና፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል። የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። የእስራኤል ተስፋ አቤቱ! የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ ጌታን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ። አቤቱ! ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና። እነሆ፦ “የጌታ ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ!” ይሉኛል። እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ። ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ። አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው። ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር፥ በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ! ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የጌታን ቃል ስሙ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታስገቡ፥ ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ። እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ። “ ‘እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፥ ይላል ጌታ፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታስገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘለዓለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን፥ የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም፥ የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ፥ ከብንያምም አገር፥ ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ ጌታ ቤት ይመጣሉ። ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፥ አትጠፋምም።’ ” ከጌታ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ “ተነሣ፥ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፥ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁ።” ወደ ሸክላ ሠሪው ቤትም ወረድሁ፥ እነሆም፥ ሥራውን በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፥ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። “የእስራኤል ቤት ሆይ! ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ላይ መሥራት አልችልምን? ይላል ጌታ፤ እነሆ፥ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ! እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ። በሕዝብና በመንግሥት ላይ እንደምነቅል እንደማፈርስም እንደማጠፋም በተናገርሁ ጊዜ፥ ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ ላደርግበት ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። በሕዝብና በመንግሥት ላይ እንደምሠራና እንደምተክል በተናገርሁ ጊዜ፥ በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ድምፄንም ባይሰማ፥ እኔ ላደርግለት ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፥ አሳብንም አስብባችኋለሁ፤ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አስተካክሉ’ ብለህ ተናገራቸው። “እነርሱ ግን፦ ‘ተስፋ የለውም! አሳባችንን ተከትለን እንሄዳለን፥ ሁላችንም እንደ ክፉው ልባችን እልከኝነት እናደርጋለን’ አሉ። “ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል፦ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? ብላችሁ ጠይቁ። የእስራኤል ድንግል በጣም የሚያስደነግጠውን ነገር አድርጋለች። በውኑ የሊባኖስ በረዶ የድጋያማውን ምድር ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን? ሕዝቤ ግን ረስተውኛል ለከንቱ ነገርም ዐጥነዋል፤ ከመንገዳቸውም አሰናክለዋቸዋል ከቀድሞውም ጐዳና ርቀው ወዳልተሠራው ወደ ጠማማው መንገድ ሄደዋል። ምድራቸውን ለመሣቀቂያና ለዘለዓለም ማፍዋጫ አድርገዋል፤ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፥ ራሱንም ይነቀንቃል። በጠላት ፊት እንደ ምሥራቅ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።” እነርሱም፦ “ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፥ በኤርምያስ ላይ ሤራን እናሢር። ኑ፥ በአንደበት እንምታው፥ ቃላቱንም ሁሉ አናድምጥ” አሉ። አቤቱ! አድምጠኝ፥ ጠላቶቼ ምን እደሚሉ ስማ። ለነፍሴ ጉድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም ለመናገር ቁጣህንም ከእነርሱ ለመመለስ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስታውስ። ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፥ ለሰይፍም እጅ አሳልፈህ ስጣቸው፥ ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፥ ወንዶቻቸውም በሞት ይጥፉ፥ ጉልማሶቻቸውም በጦርነት ጊዜ በሰይፍ ይመቱ። ሊይዙኝ ጉድጓድ ቆፍረዋልና፥ ለእግሮቼም ወጥመድ ሸሽገዋልና ድንገት በላያቸው ጭፍራ ባመጣህ ጊዜ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ። አንተ ግን፥ አቤቱ! እኔን ለመግደል በላዬ የመከሩትን ምክር ሁሉ ታውቃለህ፤ በደላቸውን ይቅር አትበል፥ ኃጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፤ በፊትህም ይውደቁ፥ በቁጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ሂድ፥ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፥ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ በካርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃላት ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉን ነገር በዚህ ስፍራ ማምጣቴን የሚሰማ ጆሮ ሁሉ ጭው ይልበታል። ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም የይሁዳም ነገሥታት ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነውበታልና፤ እነርሱም ይህን ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታልና፥ እኔም ያላዘዝሁትን ያልተናገርሁትንም ወደ ልቤም ያልገባውን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አድርገው ለበዓል ልጆቻቸውን በእሳት ለማቃጠል የበዓልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፥ በጠላቶቻቸውም ፊት በሰይፍና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፥ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ። ይህችንም ከተማ ለመሣቀቂና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፤ የሚያልፍባትም ሁሉ ይሣቀቃል፥ ስለ ተደረገባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፥ ጠላቶቻቸውንና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና ከበባ ሁሉም የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።’ “ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የሸክላ ሠሪው ዕቃ እንደሚሰባበር ዳግመኛም ሊጠገን እንደማይችል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀብሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ። እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩባት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ፥ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ። የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፥ እነዚያ በሰገነቶቻቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቁርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ፥ እንደ ቶፌት ስፍራ የረከሱ ይሆናሉ።’ ” ኤርምያስም ጌታ ትንቢት እንዲናገር ልኮት ከነበረበት ስፍራ ከቶፌት መጣ፥ በጌታም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ፥ በዚህች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።” በጌታም ቤት የተሾመው አለቃ፥ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ። ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን መታው፥ በጌታም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው በመንቈር ውስጥ አሠረው። በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከመንቈር ውስጥ ፈታው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ “ጌታ ስምህን፦ ማጎርሚሳቢብ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ ዐይኖችህም ያያሉ፤ ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል በሰይፍም ይገድላቸዋል። የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያመጡአቸዋል። አንተም፥ ጳስኮር ሆይ! በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰት ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ፥ በዚያም ትቀበራላችሁ።” አቤቱ! አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል። በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ “ግፍና ጥፋት” ብዬ እጮኻለሁ፤ የጌታ ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና መዘበቻ ሆኖብኛልና። እኔም፦ “የጌታን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም። የብዙ ሰዎችን የክፋት ሹክሹክታ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ፦ “ምናልባት ይታለል እንደሆነ፥ እናሸንፈውም እንደሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን” ይላሉ። ጌታ ግን እንደ አስፈሪ ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘለዓለምም በማይረሳ ውርደት ይዋረዳሉ። የሠራዊት ጌታ ሆይ! ጻድቅን የምትመረምር ኩላሊትንና ልብን የምትመለከት፥ ሙግቴን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ልይ። ለጌታ ዘምሩ ጌታንም አመስግኑ፤ የችግርተኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና። የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን! እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን! “ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል” ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ እጅግ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። ያም ሰው ጌታ ሳይጸጸት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤ እናቴ መቃብር እንድትሆነኝ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ እንዲቆይ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና። ድካምንና ጣርን እንዳይ፥ ዘመኔም በእፍረት እንድታልቅ ለምን ከማኅፀን ወጣሁ? ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል በላከበት ጊዜ ነው፦ “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ ጌታን ጠይቅ፤ ምናልባትም ጌታ ለእኛ እንደ ተአምራቱ ሁሉ አድርጐ ከእኛ እንዲመለስ ያደርገዋልና።” ኤርምያስም እንዲህ አላቸው፦ “ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን የጦር መሣርያ እመልሳለሁ፥ እነርሱንም ወደዚህች ከተማ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ። እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቁጣና በመዓት በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ። በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፥ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ። ከዚህ በኋላ፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህችም ከተማ የቀሩትን፥ አገልጋዮቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም።’ “ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አኑሬአለሁ። በዚህች ከተማ ውስጥ የሚቀር በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፥ እርሱም በምርኮ ነፍሱን ያድናል። ለመልካም ሳይሆን ለክፉ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፥ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፥ ይላል ጌታ።’ “የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ። የዳዊት ቤት ሆይ! ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣና ማንም ሳያጠፋው እንዳይነድድ፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ፥ የተበዘበዘውንም ከጨቋኙ እጅ አድኑ።’ እነሆ፥ በሸለቆው ውስጥ በሜዳ ላይም ባለው አምባ የምትቀመጪ ሆይ! እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተም፦ ‘በእኛ ላይ የሚወርድ ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው?’ የምትሉ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤ እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በጫካዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፥ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።” ጌታ እንዲህ አለ፦ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥ እንዲህም በል፦ በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! አንተና ባርያዎችህ፥ በእነዚህም በሮች የሚገባው ሕዝብህ፥ የጌታን ቃል ስሙ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። ይህንንም ነገር በጥንቃቄ ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባርያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ። ነገር ግን እነዚህን ቃላት ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ባድማ እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ። ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፦ አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ። የጦር መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል። ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፦ ጌታ በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደርገ?” ይላሉ። እነርሱም፦ “የአምላካቸውን የጌታን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላገለገሉአቸውም ነዋ ብለው ይመልሳሉ።” የተወለደባትንም አገር ለማየት ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና ለሚሄደው እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተው አታልቅሱ አትዘኑለትም። በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “ዳግመኛ ወደዚህ አይመለስም፥ በተማረከባት አገር በዚያ ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።” “ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤ ‘ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ’ ለሚል፥ መስኮቶችንም ለሚያወጣለት፥ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጠው፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት! በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ ይበላና ይጠጣ ፍርድንና ጽድቅን ያደርግ አልነበረምን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። የድሀውንና የችግረተኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል ጌታ። ዓይንህና ልብህ ግን ለተጭበረበረ ትርፍ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።” ስለዚህ ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ “ ‘ወንድሜ ሆይ! ወዮ! እህቴ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም፦ ‘ጌታ ሆይ! ወዮ! ግርማዊነቱ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም። አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።” “ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን ከፍ አድርጊ፤ ከዓባሪምም ሆነሽ ጩኺ። በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም፦ ‘አልሰማም’ አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ድምፄን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው። እረኞችሽን ሁሉ ንፋስ ያሰማራቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ኃጢአትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትዋረጃለሽም። አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕመም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታቃስቻለሽ!” “እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ የማኅተም ቀለበት ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ አውልቄ እጥልህ ነበር፥ ይላል ጌታ፤ ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ። ለመመለስም ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።” በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ማንም የማይፈልገው የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለምን ተወርውረው ተጣሉ? ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! የጌታን ቃል ስሚ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወንለት የለም፥ በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመጥ በይሁዳም የሚነግሥ ከእንግዲህ ወዲህ አይገኝምና፦ መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።” “የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል ጌታ። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ጌታ ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸዋልም አልጐበኛችኋቸውምም፤ እነሆ፥ ስለ ክፉ ሥራችሁ እጐበኛችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። የመንጋዬንም ትሩፍ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ ወደ በረታቸው ራሴ ሰብሰቤ እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ያፈራሉ፥ ይበዛሉም። የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፥ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፥ ከእነርሱም አንድም አይጐድልም፥ ይላል ጌታ። “እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቁጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ እርሱም ንጉሥ ሆኖ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል። በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም በደኅንነት ይቀመጣል፥ እርሱም፦ ‘ጌታ ጽድቃችን ነው’ በሚለው በዚህ ስም የሚጠራ ይሆናል። “ስለዚህ፥ እነሆ፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለው ዳግመኛ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን፦ የእስራኤልን ቤት ዘር ከሰሜን አገርና ካሰደድኋቸውም አገሮች ሁሉ ያወጣና የመራ በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ይላሉ፤ ከዚያም በምድራቸው ይቀመጣሉ። ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከጌታ የተነሣ፥ ከቅዱስ ቃላቱም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። ምድር በአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳውም ማሰማርዎች ደርቀዋል፤ አካሄዳቸውም ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም። ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ ሌላው ቀርቶ በቤቴ ውስጥ እንኳ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ምታዳልጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ወደ እርሷ ይገፈተራሉ ተፍገምግመውም ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል ጌታ። በሰማርያ ነቢያት መካከል አጸያፊን ነገር አይቻለሁ፤ በበዓል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤልን ያስቱ ነበር። በኢየሩሳሌምም ነቢያት መካከል አስደንጋጭ ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁላቸውም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። ስለዚህ ስለ ነብያት የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኩሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና፥ እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።” የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃላት አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከጌታ አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ ጌታ፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። ቃሉን ለማየትና ለመስማት በጌታ ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው? እነሆ፥ የጌታ ዐውሎ ነፋስ! ቁጣው ወጥቶአል፥ ጥቅል ዐውሎ ነፍስ፤ እርሱም በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። የጌታ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ። እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሎቼን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር። እኔ የቅርብ አምላክ ነኝን? ይላል ጌታ፥ የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ይላል ጌታ። ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል ጌታ። “አለምሁ አለምሁ” እያሉ በስሜ ትንቢትን በሐሰት የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? አባቶቻቸው ስለ በዓል ስሜን እንደ ረሱ፥ እንዲሁ አንዱ ከሌላው ጋር በሚነጋገሩት ሕልሞቻቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? ይላል ጌታ። በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል ጌታ። ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንዱ ከሌላው ዘንድ ቃሎቼን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው፦ “እርሱ ይላል” በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ሐሰትን ትንቢት በሚያልሙ በሚናገሩም፥ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም፥ ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም ነገር አይጠቅሙአቸውም፥ ይላል ጌታ። “ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ ‘የጌታ ሸክም ምንድነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችኋለሁም፥ ይላል ጌታ’ ትላቸዋለህ። ነቢይና ካህን ሕዝቡም ‘የጌታ ሸክም’ ብሎ ቢናገር፥ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። እያንዳንዱም ለባልንጀራው፥ እያንዳንዱም ለወንድሙ እንዲህ ይበልስ፦ ‘ጌታ የመለሰው ምንድነው? ጌታስ ምን ነገር ተናገረ?’ ለሰው ሁሉ ቃሉ ሸክም ይሆንበታልና ‘የጌታ ሸክም’ ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የሕያው እግዚአብሔርን ቃላት ለውጣችኋልና። ለነቢዩ እንዲህ ትለዋለህ፦ ‘ጌታ ምን መለሰልህ?’ ‘ጌታስ የተናገረው ምንድነው?’ ነገር ግን፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብትሉ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ፦ ‘የጌታ ሸክም’ አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብላችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ፥ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። የዘለዓለምንም ስድብ፥ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘለዓለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።” የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፥ የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ ጌታ አሳየኝ፥ እነሆም፥ በጌታ መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። በአንደኛው ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፤ በሁለተኛውም ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ በለስ ነበረበት። ጌታም፦ “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው” አልሁ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የላክሁትን የይሁዳን ምርኮ በበጐነት እመለከተዋለሁ። ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፥ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። እኔም ጌታ እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና፥ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። “ነገር ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ እንደማይችል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም፥ በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌምን ትሩፍ፥ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን ክፉውን አደርግባቸዋለሁ። በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆናሉ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤና ለክፉ ነገር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እልክባቸዋለሁ።” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሀያ ሦስቱ ዓመታት፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁም። ጌታም ማልዶ ተነሥቶ ባርያዎቹን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ ላከ፤ ልኮም ግን እናንተ አላደመጣችሁም፥ ለመስማትም ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም። እርሱም፦ ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ ጌታም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ። ልታገለግሉአቸውና ልትሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ አለ። ለእናንተ ጉዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ አስቆጣችሁኝ እንጂ አልሰማችሁኝም፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቃሎቼን አልሰማችሁምና እነሆ፥ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እልካለሁ ይላል ጌታ፥ ባርያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመሣቀቂያና ለማፍዋጫም ለዘለዓለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ያገለግላሉ። ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ አደርጋታለሁ። በእርሷም ላይ የተናገርሁትን ቃሎቼን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ደግሞ እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ። የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ አለኝ፦ “የዚህን ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምልክባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። በመካከላቸውም ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዳሉም ያብዳሉም።” ከጌታም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፥ ጌታም እኔን የላከባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ማፍዋጫም እርግማንም ላደርጋቸው፥ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። የግብጽንም ንጉሥ ፈርዖንን ባርያዎቹንም አለቆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ፥ የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዑፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ አስቀሎናንም ጋዛንም አቃሮንንም የአዛጦንንም ትሩፍ፥ ኤዶምያስንም፥ ሞአብንም፥ የአሞንም ልጆች፥ የጤሮስን ነገሥታትም ሁሉ፥ የሲዶናን ነገሥታትም ሁሉ፥ በባሕር ማዶ ያለች የደሴት ነገሥታትንም፥ ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ቡዝንም፥ የጠጉራቸውንም ማዕዘን የሚቈርጡትን ሁሉ፥ የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፥ አንዱን ከሌላው በመቀጠል፥ ቅርብና ሩቅ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፤ የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል። አንተም፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፥ ስከሩም፥ አስታውኩም፥ ውደቁም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። ጽዋውንም ከእጅህ ተቀብለው ለመጠጣት እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ። እነሆ፥ ስሜ የተጠራባት ከተማ ላይ ክፉን ነገር ማምጣት እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ ፈጽሞ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ በላቸው። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ቃላት በእነርሱ ላይ ትንቢት ትናገራለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ጌታ በላይ ሆኖ ይጮኻል፥ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፥ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። ጌታ ከአሕዛብ ጋር ሙግት አለውና ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፥ ኃጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል ጌታ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፥ ጽኑም ዐውሎ ነፍስ ከምድር ዳርቻዎች ይነሣል። በዚያም ቀን ጌታ የገደላቸው ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይሰበሰቡም አይቀበሩምም። “ልትታረዱና ልትበተኑ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች፥ አልቅሱ ጩኹም፤ እናንተ የመንጋ አውራዎች፥ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። ከእረኞችም የመሸሻ ስፍራ ከመንጋ አውራዎችም ማምለጫ ይጠፋል። ጌታ ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። ከጌታ ጽኑ ቁጣ የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። እንደ ደቦል አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቁጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ መጣ። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በጌታ ቤት አደባባይ ቁም፥ በጌታም ቤት ውስጥ ለመስገድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ እንድትናገራቸው ያዘዝሁህን ቃላት ሁሉ ተናገር፤ አንዲትም ቃል አትጉድል። ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ላደርግባቸው ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ። እንዲህም በላቸው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ለመሄድ እኔን ባትሰሙ፥ ያልሰማችሁትን በማለዳ ተነሥቼ ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባርያዎቼን የነቢያትን ቃላት ባትሰሙ፥ ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፥ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።’ ” ካህናቱም ነቢያቱም ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በጌታ ቤት እነዚህን ቃላት ሲናገር ሰሙ። ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ፥ ካህናትና ነቢያት ሕዝቡም ሁሉ፦ “ፈጽሞ ትሞታለህ። በጌታ ስም፦ ‘ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፥ ይህችም ከተማ ባድማና ሰው የማይኖርባ ትሆናለች’ ብለህ ስለምን ትንቢት ተናገርህ?” ብለው ያዙት። ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰበሰቡ። የይሁዳም አለቆች እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ቤት ወደ ጌታ ቤት ወጡ፥ በአዲሱም በጌታ ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። ካህናቱና ነቢያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ፦ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁት በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሯልና ይህ ሰው ሞት ይገባዋል” ብለው ተናገሩ። ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “የሰማችሁትን ቃላት ሁሉ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር ጌታ ልኮኛል። አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ስሙ፤ ጌታም በእናንተ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። እኔ ግን፥ እነሆ፥ በእጃችሁ ነኝ፤ በዓይናችሁ መልካምና ቅን የመሰላችሁን አድርጉብኝ። ነገር ግን እነዚህን ቃላት ሁሉ በጆሮአችሁ እድናገር በእውነት ጌታ ወደ እናንተ ልኮኛልና፥ ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንደምታመጡ በእርግጥ እወቁ።” አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፦ “በአምላካችን በጌታ ስም ስለ ተናገረን ይህ ሰው ሞት አይገባውም” አሉ። ከአገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ እርሱም ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል’ ብሎ ተናገረ። በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ ንጉሡ ጌታን አልፈራን? ወደ ጌታስ አልተማጠነምን? ጌታስ በእነርሱ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር አልተወምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።” ደግሞም በጌታ ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የቂርያት-ይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፥ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃላት ሁሉ ትንቢት ተናገረ። ንጉሡም ኢዮአቄም ኃያላኑም ሁሉ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ። ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፤ ኦርዮንንም ከግብጽ አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው ሬሳውንም ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር ጣለው። ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። ጌታ እንዲህ አለኝ፦ ጠፍርንና ቀንበርን ሥራ በአንገትህም ላይ አድርግ፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ፥ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ፥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ፥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ትልካቸዋለህ። ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ፦ ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባርያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ እንዲያገለግሉትም የምድረ በዳን አራዊት ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። በራሱ ምድር ላይ መውደቅያው እስከሚመጣ ጊዜ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁም ለልጅ ልጁም ያገለግላሉ፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን አገልጋይ ያደርጉታል። ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማያገለግለውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ያን ሕዝብ እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ። እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አታገለግሉም የሚሉአችሁን ነብዮቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ ከምድራቸሁ እንድትርቁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይነግሩአችኋልና። ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እነርሱም ያርሱአታል ይቀመጡባታልም፥ ይላል ጌታ። ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በእነዚህ ቃላት ሁሉ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፦ “ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ ለእርሱና ለሕዝቡም አገልግሉአቸው በሕይወትም ኑሩ። ለባቢሎን ንጉሥ ማገልገልን እንቢ ስለሚል ሕዝብ ጌታ እንደ ተናገረው፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? ሐሰተኛን ትንቢት ለእናንተ በመናገር፦ ‘ለባቢሎን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃላት አትስሙ። እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚነግሩአችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ፥ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል ጌታ።” ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሐሰተኛን ትንቢት ለእናንተ በመናገር፦ ‘እነሆ፥ የጌታ ቤት ዕቃዎች በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳሉ’ ብለው ትንቢት የሚነግሩአችሁን የነብዮቻችሁን ቃላት አትስሙ። እነርሱን አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ አገልግሉ በሕይወትም ኑሩ። ይህችስ ከተማ ለምን ባድማ ትሆናለች? እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የጌታም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በጌታ ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይሄዱ እስቲ ወደ ሠራዊት ጌታ ይማለሉ። በዚህች ከተማ ቀርተው ስለ ተተዉት ዕቃዎች፥ ስለ ዓምዶቹ፥ ስለ ኩሬውም፥ ስለ መቀመጫዎቹም፥ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ እነዚህም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን መሳፍንት ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ያልወሰዳቸው ዕቃዎች ነበሩ፤ በጌታ ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፥ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቆያሉ፥ ይላል ጌታ፤ ከዚያም በኋላ አውጥቼአቸው ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ።” በዚያም ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ፥ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፥ ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በጌታ ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የጌታን ቤት ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳለሁ፤ ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና፥ የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና፥ ይላል ጌታ።” ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በጌታ ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ። ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፦ “አሜን፥ ጌታ እንዲህ ያድርግ፤ የጌታን ቤት ዕቃዎችና ምርኮውን ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ ጌታ የተናገርኸውን የትንቢት ቃላት ይፈጽም። ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፤ ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነትና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ ጌታ በእውነት የላከው ነቢይ እንደሆነ ይታወቃል።” ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲሁ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ።” ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ። ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ ነገር ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር ተክተሀል። የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እንዲያገለግሉት የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ያገለግሉታል፥ ሌላው ቀርቶ የምድረ በዳ አራዊትን ሰጥቼዋለሁ።’ ” ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን፦ “ሐናንያ ሆይ! ስማ፤ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ ጌታ አልላከህም። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፥ ከምድር ላይ አስወግድሃለሁ፤ በጌታ ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ’ ” አለው። ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ። ነቢዩ ኤርምያስ ተማርከው ወደ ተረፉት ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃላት ይህ ነው። ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እናቱም እቴጌይቱና ጃንደረቦቹም፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወጡ በኋላ ነው። ኤርምያስ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን ላከው፤ እንዲህም የሚል ነበር፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፦ ቤቶችን ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ትከሉ፤ ፍሬዋንም ብሉ፤ ተጋቡ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አጋቡ፥ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ይውለዱ፤ በዚያም ተባዙ ጥቂቶችም አትሁኑ። በእርሷ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና እናንትን አስማርኬ ያፈለስኩባትን ከተማ ሰላም ፈልጉ፥ ስለ እርሷም ወደ ጌታ ጸልዩ። የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ በመካከላችሁ ያሉት ነብዮቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ለእናንተ ይናገራሉ፤ እኔም አላክኋቸውም፥ ይላል ጌታ። “ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህችም ስፍራ እናንተን በመመለስ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ የማስበውን አሳብ እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ለወደፊት የሠመረ ጊዜና ተስፋ ልሰጣችሁ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ ታገኙኛላችሁ፥ ይላል ጌታ፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተንም ለምርኮ ካፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ። “እናንተም፦ ‘ጌታ በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል’ ብላችኋልና፤ በዳዊት ዙፋን ላይ ስለ ተቀመጠው ንጉሥ፥ ከእናንተም ጋር ተማርከው ስላልሄዱት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም በመካከላቸው እልክባቸዋለሁ፥ ከክፋቱም የተነሣ ሊበላ እንደማይችል እንደ ተበላሸ በለስ አደርጋቸዋለሁ። በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድኋቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል ለመረገሚያና ለመሣቀቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም ይሆናሉ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ይህም የሆነው ቃሎቼን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል ጌታ፤ በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ በተደጋጋሚ ላኩኝ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፥ ይላል ጌታ።’ ስለዚህ እናንተ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ያፈለስኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፦ ‘በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚነግሩአችሁ፥ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ በዐይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ ይህን እርግማን ይጠቀማሉ፥ እንዲህም ይላሉ፦ “የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ጌታ ያድርግህ፥” በእስራኤል ዘንድ አሳፋሪ ነገር አድርገዋልና፤ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፤ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና፤ እኔም አውቀዋለሁ ምስክርም ነኝ፥ ይላል ጌታ።’ ” ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ በል፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ወዳለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ መዕሤያ ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስምህ እንዲህ ስትል ልከሃል፦ ‘በጌታ ቤት አለቃ ሆነህ እያበደ ትንቢት የሚናገርን ሰው ሁሉ በመንቈርና በዛንጅር አስረህ እንድታኖረው ጌታ በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል። አሁንስ ትንቢት የሚነግራችሁን የዓናቶቱን ሰው ኤርምያስን ለምን አልገሠጽከውም? እርሱ፦ “ለረጅም ጊዜ በምርኮ ስለምትቆዩ ቤቶችን ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትንም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ” ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና።’ ” ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው። የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ወደ ተማረኩት ሁሉ እንዲህ ብለህ ላክ፦ ‘ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጎአችኋልና፥ ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ በጌታ ላይ ዓመፅን ተነናግሯአልና ከእርሱ ዘር በዚህ ሕዝብ መካከል ተቀምጦ፥ እኔ ለሕዝቤ የማደርገውን መልካም ነገር የሚያይ ማንም አይኖርም፥ ይላል ጌታ።’ ” ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የነገርሁህን ቃላት ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል ጌታ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱአታል፥ ይላል ጌታ።” ጌታ ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ የሽብር ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም። ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደሆነ ተመልከቱ፤ ስለምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ ሴት እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ገርጥቶ አየሁ? ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል። “በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ባዕዳን አገልጋይ አያደርጉህም፤ ነገር ግን ጌታ አምላካቸውንና የማስነሣላቸውን ንጉሣቸውን ዳዊትን ያገለግላሉ። “አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ ይላል ጌታ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረኩበት አገር አድናለሁና፤ ያዕቆብም ይመለሳል ያርፋልም በደኅንነትም ይቀመጣል፤ እርሱንም ማንም አያስፈራራውም። አንተን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል ጌታ፤ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ እንደጥፋትህ መጠን እቀጣሃለሁ እንጂ ያለ ቅጣት ከቶ አልተውህም። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስብራትህ የማይፈወስ ቁስልህም የማይሽር ነው። ሙግትህን የሚፈርድልህ የለም፥ ለቁስልህም መድኃኒት የለውም፥ ለአንተም ፈውስ የለህም። ውሽሞችህ ሁሉ ረስተውሃል አይፈልጉህምም፤ በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ ጨካኝ ሰው እንደሚቀጣው ጠላትም እንደሚያቆስለው አቁስዬሃለሁና። ሕመምህ የማይፈወስ ነውና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ እነዚህን ነገሮች አድርጌብሃለሁ። ስለዚህ የሚውጡህ ሁሉ ይዋጣሉ፥ ጠላቶችህም ሁሉ አንድም ሳይቀሩ ይማረካሉ፤ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፥ የበዘበዙህንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ። ‘ማንም የማይሻት ጽዮን!’ ‘የተጣለች’ ብለው ጠርተውሻልና እኔ ጤናሽን እመልስልሻለሁ ቁስልሽንም እፈውሳለሁ፥ ይላል ጌታ። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ዳግም ትሠራለች፥ የንጉሡ ቅጥርም ዱሮ በነበረበት ቦታ ላይ ይታነጻል። ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች የሐሤት ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አስከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም። ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፥ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ። አለቃቸው ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ይሆናል፥ ገዥአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፤ እኔ አቀርበዋለሁ እርሱም ይቀርበኛል፤ ይህስ ባይሆን ለነፍሱ ዋስትና ሰጥቶ ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል ጌታ። እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።” እነሆ፥ የጌታ ዐውሎ ነፋስ! ቁጣው ወጥቶአል፥ ጥቅል ዐውሎ ነፍስ፤ እርሱም በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። የጌታ ጽኑ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ ይህን በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ። በዚያን ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። ጌታም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በጽኑ ፍቅር ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ! እንደገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ሐሤት በሚያደርጉ ዘፋኞች ሽብሸባ እያሸበሸብሽ ትወጫለሽ። እንደገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ ወይንን በወይን እርሻዎች ትተክዪአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ እነርሱም በፍሬው ይደሰታሉ። በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቂዎች፦ ‘ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ ጌታ እንውጣ’ ብለው የሚጣሩበት ቀን ይመጣልና።” ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፤ አውጁ፥ አመስግኑ፦ ጌታ ሆይ! ሕዝብህን የእስራኤልን ትሩፍ አድን በሉ። እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዓይነ ስውርና አንካሳው ያረገዘችና ምጥ የያዛትም በአንድነት ይሆናሉ፤ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። በልቅሶ ይወጣሉ፤ እኔንም በመማፀናቸው እየመራሁ እመልሳቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኩሬ ነውና። አሕዛብ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውጁ፦ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል” በሉ። ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረታበትም እጅ አድኖታል። ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ ላይ ሆነው እልል ይላሉ፤ ስለ ጌታም በጎነቱ፥ ስለ እህሉና ስለ ወይን ጠጁ፥ ስለ ዘይቱም፥ ስለ በጎቹና ስለ ከብቶቹ በሐሤት ይሞላሉ፤ ነፍሳቸውም ውኃ ጠጥታ እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በሽብሸባ ትደሰታለች፥ ጉልማሶቹና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እለውጣለሁ፥ አጽናናቸዋለሁም፥ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል፥ ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ የሚከፈልሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ፥ ይላል ጌታ። ለወደፊት ላለሽ ጊዜ ተስፋ አለሽ፥ ይላል ጌታ፥ ልጆችሽም ወደ ግዛታቸው ይመለሳሉ። በእውነት ኤፍሬም ሲያለቅስ ሰማሁ፦ ‘ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ ጌታ አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ በኀዘን ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ ተዋረድሁም።’ በእውነት ኤፍሬም የተወደደ ልጄ ነውን? ወይስ ደስ የምሰኝበት ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አሁንም ድረስ በትክክል አስታውሰዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል ጌታ። “ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ የሄድሽበትን መንገድ ዐውራ ጐዳናውን ልብ አድርገሽ ተመልከቺ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ታመነቻለሽ? ጌታ በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።” የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ ‘የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! ጌታ ይባርክህ’ የሚልን ቃል እንደገና ይናገራሉ። የይሁዳና የከተሞችዋ ሕዝብ ሁሉ፥ ገበሬዎችና ከመንጋቸም ጋር የሚዞሩ በአንድነት በዚያ ይቀመጣሉ። የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ የዛለችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና።” ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ። “የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የማራባበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። እንዲህም ይሆናል፤ እነርሱን ልነቅላቸውና ልሰባብራቸው፥ ላፈርሳቸውና ላጠፋቸው፥ ክፉም ላደርግባቸው እንደ ተጋሁ፥ እንዲሁ ልሠራቸውና ልተክላቸው እተጋለሁ፥ ይላል ጌታ። በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ እንዲህ አይሉም፦ ‘አባቶች የሚጎመዝዝ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤’ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ የተጠረሱ ይሆናሉ።” “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የማደርግበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ እጃቸውን ይዤ ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ አደረግሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እኔ ገዢአቸው ብሆንም እንኳ ያን ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፥ ይላል ጌታ። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የማደርገው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ ‘ጌታን እወቅ’ ብሎ ከእንግዲህ ወዲህ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል ጌታ። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስምና።” ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን የማይዛነፍ ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ጽኑ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ትውልድ በፊቴ ሕዝብ የመሆኑ ነገር ለዘለዓለም ያበቃለታል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ በላይ ያለው ሰማይ ቢለካ፥ በታችም ያለው የምድር መሠረት ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ትውልድ በሙሉ እጥላለሁ፥ ይላል ጌታ።” “ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ለጌታ ከተማ የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። የመለኪያውም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ከዚያም ወደ ጎዓም ይዞራል። የሬሳና የአመድ ሸለቆ ሁሉ፥ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ ያለው የትልም እርሻ ሁሉ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድርስ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም አይፈርስምም።” በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በአሥረኛው ዓመት፥ በናቡከደነፆር በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በእስር ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አሳስሮት ነበርና፦ “ስለምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ እርሱም ይይዛታል፤ የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፥ ዓይኑም ዓይኑን ያያል እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ እርሱም ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ያፈልሰዋል፥ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል ጌታ፤ ከከላዳውያን ጋር ብትዋጉ ምንም አይቀናችሁም’?” ኤርምያስም እንዲህ አለ፦ “የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ እነሆ፥ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘በመግዛት የመቤዠት መብት የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ’ ይልሃል። እንደ ጌታም ቃል የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ፦ ‘በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፥ እባክህ፥ ግዛ፤ የርስቱና የመቤዠቱ መብት የአንተ ነውና፤ ለአንተ ግዛው’ አለኝ። ይህም የጌታ ቃል እንደሆነ አወቅሁ። በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፥ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፥ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። የተገዛበትን የውሉን ዝርዝር ሁኔታና ደንብ የያዘውን የታተመውን የውል ሰነድ እንዲሁም ካልታተመው ግልባጭ ጋር ወሰድሁ፤ የአጐቴም ልጅ አናምኤል፥ የተገዛበትን የውሉን ሰነድ የፈረሙት ምስክሮች፥ በእስርም ቤት አደባባይ የተቀመጡት አይሁድ ሁሉ እያዩ የተገዛበትን የውሉን ሰነድ ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ብዙ ቀን ተጠብቀው እንዲቆዩ የታተመውን ይህን የተገዛበትን የውል ሰነድና ካልታተመው የውል ሰነድ ጋር በአንድ ላይ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህች ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደገና ይገዛሉ።’” “ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የተገዛበትን የውሉን ሰነድ ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ ጌታ ጸለይሁ፦ ‘አቤቱ ጌታ ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ በእውነት አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ለአንተም ከቶ የሚሳንህ ምንም ነገር የለም። ለብዙ ሺህ ትውልድ ጽኑ ፍቅርን ታሳያለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፤ ታላቅና ኃያል አምላክ ሆይ! ስምህ የሠራዊት ጌታ ነው። በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት ዐይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ በዚህም እስከ ዛሬዋ ቀን ስምህን አጽንተሃል። በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ። ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማልህላቸውን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ይህችን ምድር፥ ሰጠሃቸው፤ እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ድምፅህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ እንዲያደርጉም ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። እነሆ፥ አፈር ደልድለው የመሸጉ፥ ከተማይቱን ሊይዙአት ቀርበዋል፤ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፤ የተናገርኸውም ሆኖአል፥ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ። ምንም እንኳ ከተማይቱ ለከለዳውያን እጅ ተላልፋ ብትሰጥም፤ አቤቱ ጌታ ሆይ! አንተ ግን፦ “እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ” አልኸኝ።’ ” የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ የሆንሁ ጌታ ነኝ፤ በውኑ ለእኔ የሚሳነኝ ነገር አለን? ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ይይዛታል። ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፥ እኔንም ለማስቈጣት በሰገነታቸው ላይ ለበዓል ካጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቁርባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል። የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና፥ ይላል ጌታ። ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቁጣዬንና መዓቴን አነሣሥታለችና ከፊቴ አስወግዳታለሁ፤ ይህንንም የማደርገው እኔን ለማስቈጣት፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው፥ አለቆቻቸውና ካህናቶቻቸው፥ ነብዮቻቸውና የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ፥ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ባለማቋረጥ ባስተምራቸውም እንኳ ተግሣጽን ለመቀበል አልሰሙም። ሊያረክሱትም ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኖሩ። ይሁዳን ኃጢአት ለማሠራት፥ ይህን ርኩሰት እንዲያደርጉ ባላዛቸውም በልቤም ባላስበውም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሌክ በእሳት ለመሠዋት፥ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበዓልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ። “ስለዚህ አሁን ግን የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ አንተ ስለ እርሷ፦ ‘በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች’ ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በቁጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ በደኅንነትም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። እኔን ለዘለዓለም በመፍራት ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ። ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል፥ በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ ለእነርሱ የተናገርሁትን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። እናንተም፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት፥ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ። ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም አገር፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች፥ በደጋውም ባሉ ከተሞች፥ በቈላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ፥ ምስክሮችንም ጠርተው በውሉ ሰነድ ላይ ፈርመው ያትሙታል፥ ይላል ጌታ።” ኤርምያስ ገና በእስር ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የጌታ ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ስሙ ጌታ የሆነ፥ ምድርንም የፈጠረ ጌታ፥ ሊያጸናውም የሠራው ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ተጣራ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቃቸውን ታላላቅና ስውር የሆኑ ነገሮችን እነግርሃለሁ። ከሰይፍ ፊትና ከከበባት የአፈር ድልድል ለመከላከል ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፥ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ከለዳውያን ጋር ለመዋጋት ወጥተዋል፤ ነገር ግን በቁጣዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሉአቸው ነው፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ሰውሬአለሁና። እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸዋለሁም፤ እጅግም የበዛ ሰላምንና እውነትን እገልጥላቸዋለሁ። የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ። በእኔም ላይ ከሠሩት ከበደላቸው ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ፤ በእኔም ላይ ያመፁትንና የሠሩትን የበደላቸውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር እላለሁ። የምሠራላቸውንም በጎነት ሁሉ በሚሰሙ የምድር አሕዛብ ሁሉ ፊት ይህች ከተማ ለእኔ የምስጋናና የክብር የደስታም ስም ትሆናለች፤ እኔም ስላደረግሁላት በጎነትና ሰላም ሁሉ ይፈራሉ ይንቀጠቀጣሉም። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንተ፦ ‘ያለ ሰውና ያለ እንስሳ የሆነች ባድማ ናት’ በምትሉአት በዚህች ስፍራ፥ ሰውም በማይቀመጥባቸው፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ ዳግመኛ ይህ ይሰማል እርሱም፦ የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የሙሽራው ድምፅና የሙሽራይቱ ድምፅ፥ ወደ ጌታም ቤት፦ ‘ጌታ ቸር ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታን አመስግኑ!’ እያሉ የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ ነው። የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል ጌታ። “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ባድማ ሆና፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ በሆነችው በዚህች ስፍራ፥ በከተሞችዋም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉ የእረኞች መኖሪያ ስፍራ ዳግመኛ ይኖራል። በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች፥ በቈላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም አገር፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በጎቹ መንጋውን በሚቆጥረው ሰው እጅ ሥር እንደገና ያልፋሉ፥ ይላል ጌታ። “እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቁጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም በደኅንነት ትቀመጣለች፤ እርሷም፦ ‘ጌታ ጽድቃችን ነው’ በሚለው ስም ትጠራለች። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ዳዊት በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አያጣም፤ እንዲሁም ሌዋውያን ካህናት በእኔ ፊት የሚቃጠለውን መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቁርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ፈጽሞ አያጡም።” የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በተመደበላቸው ጊዜ እንዳይሆኑ የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቁጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባርያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።” የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ይህ ሕዝብ፦ ‘ጌታ የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል’ ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ ባለመሆኑ ሕዝቤን አቃልለዋል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች እንዲሆኑ ከዘሩ ላለመውሰድ፥ የያዕቆብንና የባርያዬን የዳዊትን ዘር እኔ ደግሞ እጥላለሁ። እኔ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸዋለሁምና።” የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ፥ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና ከተሞችዋን ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሂድ ለይሁዳም ንጉሥ ለሴዴቅያስ ተናገር እንዲህም በለው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ በእሳትም ያቃጥላታል፤ አንተም በእርግጥ ትያዛለህ ለእጁም ተላልፈህ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም፤ ዓይንህም የባቢሎንን ንጉሥ ዐይን ታያለች፥ እርሱም ከአንተ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገራል፥ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።’ ነገር ግን፥ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ! የጌታን ቃል ስማ፤ ጌታ ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ ‘በሰይፍ አትሞትም፤ በሰላም ትሞታለህ። ከአንተ በፊት እንደ ነበሩ እንደ ዱሮ ነገሥታት እንደ አባቶችህ ዕጣን እንደታጠነላቸው፥ እንዲሁ ለአንተም ዕጣንን ያጥኑልሃል፦ “ወየው! ጌታ ሆይ!” እያሉ ያለቅሱልሃል፤’ እኔ ቃልን ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ።” ነቢዩ ኤርምያስ እነዚህን ቃላት ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤ እንዲህም የተናገረው የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ የቀሩትን ለኪሶንና ዓዜቃንን በወጋ ጊዜ ነበር፤ ከተመሸጉት ከይሁዳ ከተሞች መካከል የተረፉት እነዚህ ብቻ ነበሩና። ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። ይህም ቃል የመጣው ለባርያዎች ስለ አርነታቸው አዋጅ እንዲነገር ንጉሡ ሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ ነው፤ አዋጁም፦ ሰው ሁሉ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባርያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባርያውን አርነት እንዲያወጣ፥ አይሁዳዊ ወንድሙንም ማንም እንዳይገዛ የሚል ነው። ወደ ቃል ኪዳኑ የገቡ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሰምተው ማንም ሰው ወንድ ባርያውንና ሴት ባርያውን አርነት እንዲያወጣ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ማንም እንዳይገዛቸው አደረጉ፤ እነርሱም ሰምተው አርነት አወጡአቸው። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ተመልሰው አርነት ያወጡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ባርያዎቻቸውን አስመለሱ፥ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችም አድርገው ገዙአቸው። ስለዚህ የጌታ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁን ከባርነት ቤት ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፦ ‘ሰባት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ የተሸጠላችሁን ስድስትም ዓመት ያገለገላችሁን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ አርነት ታወጡታላችሁ፥ ለእናንተም ከሚሰጠው አገልግሎት ነጻ ታደርጉታላችሁ፤’ ነገር ግን አባቶቻችሁ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም። እናንተም ዛሬ ተመልሳችሁ፥ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን አርነት ለማውጣት አዋጅ በመንገር ለዓይኔ ደስ የሚያሰኝን ነገር አድርጋችሁ ነበር፥ ስሜም በተጠራበት ቤት ውስጥ በፊቴ ቃል ኪዳን አድርጋችሁ ነበር። ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አስነቀፋችሁ፥ እያንዳንዳችሁም በፈቃዳቸው እንዲሄዱ አርነት ያወጣችኋቸውን ወንድና ሴት ባርያዎቻችሁን አስመለሳችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችም እንዲሆኑላችሁ ገዛችኋቸው። “ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፤ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። ቃል ኪዳኔንም የተላለፉትን ሰዎች፥ እንቦሳውንም ቈርጠው በቁራጩ መካከል ባለፉ ጊዜ በፊቴ ያደረጉትን የቃል ኪዳኑን ሕግጋት ያልፈጸሙትን፥ የይሁዳን አለቆችና የኢየሩሳሌምን አለቆች እንዲሁም ጃንደረቦችንና ካህናትን በእንቦሳም ቁራጭ መካከል ያለፉትን የአገሩን ሕዝብ ሁሉ፥ ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። የይሁዳንም ንጉሥ ሴዴቅያስንና አለቆቹን፥ ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ ከእናንተም ለተመለሱት ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ ይላል ጌታ፥ ወደዚህችም ከተማ እመልሳቸዋለሁ፤ እርሷንም ይወጋሉ ይይዙአታልም በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የሌለበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ “ወደ ሬካባውያን ቤት ሂድና አነጋግራቸው፥ ወደ ጌታም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዱ አስገባቸው የወይን ጠጅም እንዲጠጡ ስጣቸው።” የከባስን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን፥ ወንድሞቹንም፥ ልጆቹንም ሁሉ፥ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኩ፤ ወደ ጌታም ቤት የደጁ ጠባቂ በሆነው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወደሚገኘው፥ ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አስገባኋቸው። ከዚያም በሬካባውያን ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አስቀምጬ፦ “የወይኑን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው። እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና፦ ‘እናንተና ልጆቻችሁ ለዘለዓለም የወይን ጠጅ አትጠጡ፤ በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንን አትትከሉ ወይም የወይን ቦታ አይኑራችሁ።’ እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ሰምተን፥ ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤ የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፤ ሆኖም ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጠናል፥ እኛም በመታዘዝ አባታችን ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል። ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ፦ ‘የከለዳውያንን ሠራዊትና የሶርያውያንን ሠራዊት በመፍራት ኑ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ’ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።” የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ቃሎቼን ለመስማት ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል ጌታ። የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹን የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃላት ተፈጸሙ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናገርኋቸው፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁኝም። እንዲሁም፦ ‘እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ልታገለግሉአቸውም ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ’ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ላክሁባችሁ፤ ላክሁ፥ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም። የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝም። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሆነ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና በእነርሱ ላይ የተናገርኩትን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በተቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።” ኤርምያስም ለሬካባውያን ቤት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዛቱንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም በሙሉ ፈጽማችኋልና፤ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘለዓለም ፈጽሞ አይታጣም።” እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። “አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን፥ ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ ለአንተ የተናገርሁትን ቃላት ሁሉ ጻፍበት። ምናልባት የይሁዳ ቤት እኔ ላደርግባቸው ያሰብኩትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከዚህም የተነሣ ሁላቸውም ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ይሆናል።” ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራ፥ ባሮክም ኤርምያስ እየነገረው ጌታ ለእርሱ የተናገረውን ቃላት ሁሉ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “እኔ ተከልክያለሁ፤ ወደ ጌታ ቤት ለመግባት አልችልም። አንተ ግን ሂድ፥ እየነገርሁህም የጻፍኸውን የጌታን ቃላት በጾም ቀን በጌታ ቤት በሕዝቡ ጆሮ ከክርታሱ አንብብ፤ እንዲሁም ደግሞ ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። ጌታ በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቁጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በጌታ ፊት ይቀርብ ይሆናል፥ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል።” የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ በጌታ ቤት የጌታን ቃላት ከመጽሐፉ እንዲያነብ ያዘዘውን ትእዛዝ ሁሉ አደረገ። እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር፥ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት ሕዝብ ሁሉ በጌታ ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ። ባሮክም የኤርምያስን ቃላት በላይኛው አደባባይ በጌታ ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ፥ በገማርያ ጓዳ በጌታ ቤት ውስጥ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ ከመጽሐፉ አነበበ። የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የጌታን ቃላት ሁሉ ከመጽሐፉ በሰማ ጊዜ፥ ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ጓዳ ወረደ፤ እነሆም፥ አለቆች ሁሉ፥ ጸሐፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። ሚክያስም ባሮክ መጽሐፉን በሕዝቡ ጆሮ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃላት ሁሉ ነገራቸው። አለቆቹም ሁሉ፦ “በሕዝቡ ጆሮ ያነበብከውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና” የሚል መልእክት በኲሲ ልጅ በሰሌምያ ልጅ በናታንያ ልጅ በይሁዲ እጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ መጣ። እነርሱም፦ “እስኪ ተቀመጥ፥ እየሰማንህም አንብብ” አሉት። ባሮክም እየሰሙት አነበበው። ቃሎቹንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተያዩ፥ ባሮክንም፦ “እነዚህን ቃላት ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን” አሉት። ባሮክንም፦ “እነዚህን ሁሉ ቃላት እንዴት እንደ ጻፍከው እስኪ ንገረን፤ እርሱ እየነገረህ ነውን?” ብለው ጠየቁት። ባሮክም፦ “እነዚህን ቃላት ከአፉ ይነግረኝ ነበር፥ እኔም በመጽሐፉ ላይ በቀለም እጽፍ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። አለቆቹም ባሮክን፦ “አንተና ኤርምያስ ሂዱ፥ ተሸሸጉ፥ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም ሰው አይወቅ” አሉት። ክርታሱንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ጓዳ አስቀምጠው ወደ ንጉሡ አደባባይ ገቡ፤ ቃሎቹንም ሁሉ በንጉሡ ጆሮ ተናገሩ። ንጉሡም ክርታሱን እንዲያመጣ ይሁዲን ላከ፥ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ጓዳ አመጣው፤ ይሁዲም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ እፊቱም ባለው ምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር። ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያኽል ባነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ ጸሐፊ በሚጠቀምበት ሰንጢ የተነበበለትን እየቀደደ ክርታሱ በሙሉ ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ይጥለው ነበር። ንጉሡም ሆነ እነዚህን ቃላት ሁሉ የሰሙ ባርያዎቹ በጠቅላላ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም። ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ቢለምኑትም እንኳ፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም። ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን እንዲይዙ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፥ ጌታ ግን ሰወራቸው። ንጉሡም ኤርምያስ ለባሮክ እየነገረው የጻፈውን ቃላት የያዘውን ክርታስ ካቃጠለ በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃላት ሁሉ ጻፍበት። ስለ ይሁዳም ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ በል፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ አንተ፦ “የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል፥ ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል በማለት ለምን ጻፍህበት?” ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከእርሱም በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይኖረውም፥ ሬሳውም በቀን ለፀሐይ ሐሩርና በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን ባርያዎቹንም እቀጣለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና በእነርሱ ላይ የተናገርሁትን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱና በኢየሩሳሌም በተቀመጡ፥ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።’ ” ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ፥ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃላት ሁሉ ኤርምያስ እየነገረው ጻፈበት፥ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ተመሳሳይ ብዙ ቃላት ተጨመረበት። የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር ላይ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ። በነቢዩ በኤርምያስም በኩል የተናገረውን የጌታን ቃላት እርሱም ሆነ ባርያዎቹ የአገሩም ሕዝብ አልሰሙም። ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “እባክህ፥ ወደ አምላካችን ወደ ጌታ ስለ እኛ ጸልይ” ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። እርሱንም ወደ እስር ቤት ገና አላስገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር። የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ። የጌታም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔን እንድትጠይቁኝ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ ‘እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል። ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዟታልም በእሳትም ያቃጥሉአታል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ አይሄዱምና፦ “ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ” ብላችሁ ራሳችሁን አታታሉ። እናንተንም የሚወጉዋችሁን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ድል ብታደርጉ እንኳ ከእነርሱም መካከል የቆሰሉ ሰዎች ብቻ ቢቀሩ፥ እነርሱም ሁሉ ከየድንኳኖቻቸው ይነሣሉ ይህችንም ከተማ በእሳት ያቃጥላታል።’ ” የፈርዖንም ሠራዊት ከመቃረቡ የተነሣ የከለዳውያን ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ተመልሶ በነበረ ጊዜ፥ ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን ድርሻ ከዚያ ለመቀበል ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፤ እርሱም ነቢዩን ኤርምያስን፦ “ወደ ከለዳውያን ልትኰበልል ነው” ብሎ ያዘው። ኤርምያስም፦ “ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም” አለ፤ የሪያም ግን አልሰማውም፥ ኤርምያስንም ይዞ ወደ አለቆች አመጣው። አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የእስር ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ ቤት አስረው አኖሩት። ኤርምያስም በጉድጓድ ውስጥ ለውኃ ማከማቻ ወደሚሆን ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ እርሱም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥ ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ፦ “በውኑ ከጌታ ዘንድ የሆነ ቃል አለን?” ብሎ በድብቅ ጠየቀው። ኤርምያስም፦ “አዎን አለ” ብሎ መለሰ። ከዚያም በኋላ፦ “በባቢሎን ንጉሥ እጅ ተላልፈህ ትሰጣለህ” አለ። ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “በእስር ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባርያዎችህን ወይስ ይህን ሕዝብ ምን በድያችሁ ነው? ‘የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር ላይ አይመጣም’ ብለው ትንቢት ለእናንተ ይናገሩ የነበሩ ነብዮቻችሁ ወዴት አሉ? ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፤ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።” ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በእስር ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማይቱ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር። ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃላት የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። ኤርምያስ እንዲህ ብሏልና፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ እርሱም በምርኮ ነፍሱን ያድናል፥ በሕይወትም ይኖራል። ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል።” አለቆቹም ንጉሡን፦ “ይህን የመሰለውን ቃላት እየነገራቸው የሕዝቡን ሁሉ እጅ በዚህችም ከተማ የቀሩትን የወታደሮቹን እጅ እያደከመ ነውና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና” አሉት። ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው” አለ። ኤርምያስንም ወሰዱት፤ በእስር ቤቱም አደባባይ ወደነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጉድጓድ ውስጥ ኤርምያስን በገመድ አውርደው ጣሉት። በጉድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ። በንጉሡም ቤት የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አቤሜሌክ ኤርምያስን በጉድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጉድጓድ ውስጥ ጥለው ባደረጉበት ነገር ሁሉ ክፉ ነገርን ፈጽመዋል፤ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለ ሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።” ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፦ “ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጉድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው። አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው። ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፦ “ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት፤ ከጉድጓድም አወጡት፤ ኤርምያስም በእስር ቤት አደባባይ ተቀመጠ። ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በጌታ ቤት ወደነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን፦ “እኔ አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው። ኤርምያስም ሴዴቅያስን፦ “ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ደግሞም ብመክርህ እንኳ አትሰማኝም” አለው። ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “ይህችን ነፍስ በፈጠረልን በሕያው ጌታ እምላለሁ! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም” ብሎ በድብቅ ለኤርምያስ ማለ። ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች በእርግጥ ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም።” ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፦ “ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ “አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የነገርሁህን የጌታን ድምፅ እባክህ፥ ስማ ለአንተም የቀና ይሆንልሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። ለመውጣት እንቢ ብትል ግን፥ ጌታ ያሳየኝ ነገር ይህ ነው። እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች፦ ‘ባለምዋሎችህ አሳስተውሃል አሸንፈውሃልም፤ አሁን ግን እግሮችህ በጭቃ ውስጥ ገብተዋል እነርሱም ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል’ ይላሉ። ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።” ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፦ “እነዚህንም ቃላት ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው፦ ‘ለንጉሡ ያልኸው ምንድነው? ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፤ ንጉሡስ ለአንተ ምን አለህ?’ ንገረን ቢሉህ፥ አንተም፦ ‘በዚያ እንዳልሞት ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ልመናዬን አቀረብሁ’ ” በላቸው። አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፥ እርሱም ንጉሡ እንዳዘዘው እነዚህን ሁሉ ቃላት ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማም ነበርና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ። ኤርምያስም ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀመጠ። በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በሴዴቅያስም በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማይቱ ቅጥር ተጣሰ። ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ሳምጋር ናቦ፥ የራፌሱ ሠርሰኪም፥ የራብማጉ ኤርጌል ሳራስር፥ ከተረፉት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ። የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወታደሮቹም ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ ኰበለሉ፥ በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በነበረው በር በኩል ከከተማይቱ ወጡ፤ መንገዳቸውንም ወደ ዓረባ አድርገው ተጓዙ። የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ደረሱበት፤ እርሱንም ይዘው በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች ዓይኑ እያየ በሪብላ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደለ። የሴዴቅያስንም ዐይን አወጣ፥ ወደ ባቢሎንም ለመውሰድ በሰንሰለት አሰረው። ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ፥ ወደ እርሱም ኮብልለው የነበሩትን ሰዎች፥ የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማርኮ አፈለሳቸው። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ምንም የሌላቸውን አንዳንድ ድሆች በይሁዳ አገር ተዋቸው፥ በዚያው ጊዜም የወይኑን ቦታዎችና እርሻዎችን ሰጣቸው። የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ በዘበኞቹ አለቃ በናቡዘረዳን በኩል እንዲህ ሲል ትእዛዝን ሰጠ፦ “ውሰደው፥ በበጎ ተመልከተው፥ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር አታድርግበት።” የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን፥ የራፋስቂሱ ናቡሽዝባንም የራብማጉ ኤርጌል ሳራስርም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ ልከው ኤርምያስን ከእስር ቤት አደባባይ አወጡት፤ ወደ ቤቱም እንዲወስደው ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እርሱም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ። በእስር ቤትም አደባባይ ታስሮ ሳለ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ “ሂድ፥ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሎቼን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምትፈራቸውም ሰዎች እጅ ተላልፈህ አትሰጥም። ፈጽሜ አድንሃለሁ፥ ነፍስህም ለአንተ በምርኮ ትድናለች እንጂ በሰይፍ አንተ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል ጌታ።’ ” ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ መካከል የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን እርሱን በሰንሰለት አስሮ በመውሰድ ከራማ ከለቀቀው በኋላ፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። የዘበኞቹም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው እንዲህም አለው፦ “ጌታ አምላክህ ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ፤ ጌታም አመጣው፥ እንደ ተናገረውም አደረገ፤ በጌታም ላይ ኃጢአት ሠርታችኋልና፥ ድምፁንም አልሰማችሁምና ይህ ነገር በእናንተ ላይ ሆነ። አሁን ደግሞ፥ እነሆ፥ በእጅህ ካለው ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ቢታይህ፥ ና፥ እኔም በበጎ ዐይን እመለከትሀለው፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፥ ቅር፤ እነሆ ተመልከት፥ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ለመሄድ መልካም መስሎ ወደሚታይህ ትክክልም ነው ብለህ ወደምታስበው ስፍራ ወደዚያ ሂድ። እርሱም ገና ሳይመለስ፦ የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፥ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ለመሄድ ትክክል መስሎ ወደሚታይህ ስፍራ ሁሉ ሂድ።” የዘበኞቹም አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶት አሰናበተው። ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፥ በአገሩም ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ከእርሱ ጋር ተቀመጠ። በየሜዳውም የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድሪቱ ላይ እንደ ሾመ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም፥ ወደ ባቢሎን ያልተማረኩትን በምድሪቱ ያሉትን ድሆች፥ እንዲገዛ ኀላፊነት እንደሰጠው በሰሙ ጊዜ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፥ የተንሑሜትም ልጅ ሠራያ፥ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ ከሰዎቻቸው ጋር ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ለከለዳውያን ለማገልገል አትፍሩ፤ በምድሪቱ ተቀመጡ ለባቢሎንም ንጉሥ አገልግሉ፥ መልካምም ይሆንላችኋል። እኔም፥ እነሆ፥ ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት ለእናንተ ዋስትና ለመቆም በምጽጳ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይንንና የበጋ ፍሬ ዘይትንም አከማቹ፥ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፥ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ።” እንዲሁም ደግሞ በሞዓብም፥ በአሞንም ልጆች መካከል፥ በኤዶምያስም በምድሪቱም ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ፥ የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ትሩፍ እንዳስቀረ፥ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ፥ አይሁድ ሁሉ ከተሰደዱበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ፤ ወደ ይሁዳም አገር ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ ወይንና የበጋንም ፍሬ እጅግ ብዙ አከማቹ። የቃሬያም ልጅ ዮሐናን በየሜዳውም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው፦ “የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ አንተን ለመግደል የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ላከ ፈጽሞ አታውቅምን?” አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም። የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፦ “እባክህ፥ ልሂድ፤ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ፥ የይሁዳም ትሩፍ እንዲጠፋ አንተን ለምን ይገድላል?” ብሎ በምጽጳ በድብቅ ለጎዶልያስ ተናገረ። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን፦ “በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ” አለው። በሰባተኛውም ወር ከመንግሥት ወገንና ከንጉሡ ዋና ዋና ሹማምንት አንዱ የሆነው የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በምጽጳ በአንድ ላይ እንጀራ እየበሉ ሳሉ፥ የናታንያም ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩት አሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ፥ የባቢሎንም ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን ገደሉ። እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፥ በዚያም የተገኙትን የከለዳውያንን ወታደሮች ሁሉ ገደላቸው። ከጎዶልያስ መገደል በኋላ ማንም ሳያውቅ በሁለተኛው ቀን ጢማቸውን ላጭተው ልብሳቸውንም ቀድደው ገላቸውንም ተልትለው፥ በጌታ ቤት ለማቅረብ የእህል ቁርባንና ዕጣን በእጃቸው ይዘው፥ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬምና ከሴሎ ከሰማርያም መጡ። የናታንያም ልጅ እስማኤል ከምጽጳ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ፤ በተገናኛቸውም ጊዜ፦ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። ወደ ከተማይቱም መካከል በመጡ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ገደሉአቸው፥ በጉድጓድም መካከል ጣሉአቸው። በመካከላቸውም እስማኤልን፦ “በእርሻ ውስጥ የተሸሸገ ስንዴና ገብስ ዘይትና ማርም አለንና አትግደለን” የሚሉት ዐሥር ሰዎች ተገኙ። እርሱም ተዋቸው፥ ከወንድሞቻቸውም ጋር አልገደላቸውም። እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን የሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጉድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ለመመከት የሠራው ምሽግ ነበረ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት። እስማኤልም በምጽጳ የነበረውን የሕዝቡን ትሩፍ ሁሉ፥ የንጉሡን ሴቶች ልጆች የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በምጽጳ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ ማረከ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል ማርኮ ወደ አሞን ልጆች ለመሄድ ተነሣ። የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ከእርሱም ጋር የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ ሰዎቻቸውንም ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ለመዋጋት ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው ታላቅ ኲሬ አጠገብ አገኙት። ከእስማኤልም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። እስማኤልም ከምጽጳ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ዘወር ብለው ተመለሱ፥ ወደ ቃሬያም ልጅ ወደ ዮሐናን ሄዱ። የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ ወደ አሞንም ልጆች ሄደ። የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ እርሱና ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ከምጽጳ ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ትሩፍ ሁሉ፥ እንዲሁም ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ወታደሮች፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ ጃንደረቦችንም፥ ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብጽ ለመሄድ በማቀድ በቤተልሔም አጠገብ ባለው በጌሮት ከመዓም ተቀመጡ፤ ምክንያቱም የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለ ገደለው ከለዳውያንን በመፍራታቸው ነው። የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “በዐይኖችህ እንደምታየን ከብዙ ጥቂት ተርፈናልና ልመናችን እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፥ ስለ እኛና ስለዚህ ትሩፍ ሁሉ ለጌታ ለአምላክህ ጸልይ፥ ጌታ አምላክህም የምንሄድበትን መንገድና ማድረግ የሚገባንን ነገር ያሳውቀን ይሆናል።” ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እጸልያለሁ፤ ጌታም የሚመልስላችሁን ቃል ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም።” እነርሱም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ጌታ አምላክህ በአንተ አማካይነት ወደ እኛ የላከውን ቃል ሁሉ ባናደርግ፥ ጌታ በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁንብን። የአምላካችንን የጌታን ድምፅ በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ እኛ ወደ እርሱ የምንልክህን የአምላካችንን የጌታን ድምፅ እንሰማለን።” ከዐሥር ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። ኤርምያስም የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥ እንዲህም አላቸው፦ ጸሎታችሁን በፊቱ እንዳቀርብ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ አንጻችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። የምትፈሩትን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩት፤ እናንተን ለማዳን ከእጁም ለመታደግ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና እርሱን አትፍሩ፥ ይላል ጌታ። እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ። እናንተ ግን፦ በዚህች ምድር አንቀመጥም ብትሉ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ባትሰሙ፥ እናንተም፦ አይደለም፤ ጦርነት ወደማናይባት የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት ወደማንራብባትም ወደ ግብጽ ምድር እንሄዳለን በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥ እናንተ የይሁዳ ትሩፍ ሆይ! እንግዲህ አሁን የጌታን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ግብጽ ለመግባት በዚያም ሄዳችሁ ለመቀመጥ በእርግጥ ፊታችሁን ብታቀኑ፥ የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብጽ ምድር ይደርስባችኋል፥ የሚያስደነግጣችሁም ራብ በዚያ በግብጽ ይከተላችኋል፥ በዚያም ትሞታላችሁ። ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑ ሰዎች ሁሉ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ከእነርሱ አንድም ሰው በሕይወት አይተርፍም፥ አንድም ሰው አያመልጥም። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፦ ቁጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ወረደ፥ እንዲሁ ወደ ግብጽ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይወርድባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም። እናንተ የይሁዳ ትሩፍ ሆይ! ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአችኋል፦ ወደ ግብጽ አትግቡ፤ ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ፤ እናንተ፦ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ ጌታ ጸልይ፥ ጌታ አምላካችንም የሚናገረውን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እናንተው ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል። እኔም ዛሬ ነገርኋችሁ፥ እናንተ ግን ወደ እናንተ በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የጌታን ድምፅ አልሰማችሁም። ስለዚህም አሁን ሄዳችሁ ለመቀመጥ በወደዳችሁበት በዚያ ስፍራ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንደምትሞቱ በእርግጥ እወቁ። ለእነርሱ አምላካቸው እግዚአብሔር የላከውን ይህን የአምላካቸውን የጌታን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ መናገርን በፈጸመ ጊዜ፥ የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ትዕቢተኞችም ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ሐሰት ተናግረሃል፤ ጌታ አምላካችን፦ ‘በዚያ ለመቀመጥ ወደ ግብጽ አትግቡ’ ብሎ እንድትናገር አልላከህም፤ ነገር ግን ከለዳውያን እንዲገድሉን ወደ ባቢሎንም ማርከው እንዲወስዱን በእጃቸው አሳልፈህ ልትሰጠን የኔርያ ልጅ ባሮክ በላያችን ላይ አነሣሥቶሃል።” የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ የጌታን ድምፅ አልሰሙም። የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተሰደዱባቸው ከአሕዛብ ስፍራዎች ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳን ትሩፍ ሁሉ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም ሕፃናትንም የንጉሡንም ሴቶች ልጆች፥ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከሳፋን ልጅ ከአኪቃም ልጅ ከጎዶልያስ ጋር የተዋቸውን ሰዎች ሁሉ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን የኔርያንም ልጅ ባሮክን ወሰዱ፤ የጌታንም ድምፅ አልሰሙምና ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፥ እስከ ጣፍናስ ድረስ መጡ። በጣፍናስም የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ትላልቅ ድንጋዮች በእጅህ ውሰድ፥ የይሁዳም ሰዎች እያዩ በጣፍናስ በፈርዖን ቤት መግቢያ ባለው በቅጥራኑና በጡቡ ደጃፍ ሸሽጋቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ልኬ ባርያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም የዙፋኑን ድንኳን በላያቸው ይዘረጋል። መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል።’ ” በግብጽ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም። ይህም የሆነው ስለ ሠሩት ክፋት እኔን ስላስቈጡኝ፥ በዚህም እናንተም አባቶቻችሁም እነርሱም ለማያውቁአቸው ለሌሎች አማልክት ለማጠንና ለማገልገል ስለ ሄዱ ነው። ሆኖም በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ እንዲህ ብዬ ላክሁባችሁ፦ ‘እባካችሁ፥ እንደዚህ ያለ የጠላሁትን ርኩስ ነገር አታድርጉ።’ ነገር ግን አልሰሙም ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት ላለማጠን ጆሮአቸውን አላዘነበሉም። ስለዚህ መዓቴና ቁጣዬ ወረዱ፥ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደዱ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ ባድማም ሆኑ። አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ትሩፍ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ልጅንና ሕፃንን ከእናንተ ለማጥፋት ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? እናንተም እንድትጠፉ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ እንድትሆኑ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት አጥናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ? በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት፥ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን? እስከ ዛሬ ድረስ አልተዋረዱም አልፈሩምም፥ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዓቴ አልሄዱም። “ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይሁዳን ሁሉ ለማጥፋት ፊቴን ለክፋት በእናንተ ላይ አደርጋለሁ። ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ትሩፍ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብጽም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ። ኢየሩሳሌምን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንደ ቀጣሁ፥ እንዲሁ በግብጽ ምድር የሚኖሩትን እቀጣለሁ። ስለዚህም በግብጽ ምድር በዚያ ለመቀመጥ ከገቡት ከይሁዳ ትሩፍ ማናቸውም ተመልሰው ለመቀመጠጥ ወደ ሚመኙበት ወደ ይሁዳ ምድር አያመልጡም በሕይወትም አይተርፉም አይመለሱምም፤ ከአንዳንድ ከሚያመልጡ በቀር አይመለሱም።” ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ በዚያም ቆመው የነበሩ ሴቶች ሁሉ፥ በግብጽ ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት እንዲህም አሉ፦ “አንተ በጌታ ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም። ነገር ግን እኛና አባቶቻችን ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ እንዳደረግነው፥ ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያን ጊዜም እንጀራ እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ክፉም አናይም ነበር። ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርሷም የመጠጥን ቁርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ ሁሉ ነገር ጐድሎብናል፥ በሰይፍና በራብ አልቀናል። እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት የመጠጥንም ቁርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ፈቃድ ምስልዋ ያለበት እንጐቻ አድርገንላታልን? የመጠጥንስ ቁርባን አፍስሰንላታልን?” ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፥ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ለሕዝቡም ሁሉ፥ መለሰላቸው እንዲህም አለ፦ “እናንተና አባቶቻችሁ ነገሥታቶቻችሁም አለቆቻችሁም የምድሪቱም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን ጌታ አያስታውሰውምን? በልቡስ አያኖረውምን? ጌታም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኩሰት መታገሥ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መሣቀቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደሆነ የሚኖርባት የለም። ስላጠናችሁ፥ በጌታም ላይ ኃጢአትን ስለ ሠራችሁ፥ የጌታንም ድምፅ ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዓቱም በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደሆነ ይህ ክፉ ነገር ደርሶባችኋል።” ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፦ “በግብጽ ምድር የምትገኙ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፦ ‘ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን’ ብላችሁ ተናገራችሁ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። ስለዚህ እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ፤ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ‘ሕያው በሆነ ጌታ እግዚአብሔር እምላለሁ!’ ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በእነርሱ ላይ እመለከታለሁ፤ በግብጽም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ። ከሰይፍም ያመለጡት ጥቂት ሰዎች ከግብጽ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ በዚያም ለመቀመጥ ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የይሁዳ ትሩፍ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንደሚጸና በውኑ ያውቃሉ! ቃሎቼም በእናንተ ላይ ለክፋት በእርግጥ እንደሚጸኑ እንድታውቁ በዚህች ስፍራ እቀጣችኋለሁ፤ ይህም ለእናንተ ምልክት ይሆናል፥ ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው ነፍሱንም ለሚሻው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፥ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚሽዋት እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የኔርያ ልጅ ባሮክ ኤርምያስ በቃል እየነገረው እነዚህን ቃሎች በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። “ባሮክ ሆይ! የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይልሃል፦ አንተ፦ ‘ጌታ በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፥ ዕረፍትንም አላገኘሁም’ ብለሃል። እንዲህ በለው፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም ምድሪቱን በሞላ ነው። አንተም ለራስህ ታላቅን ነገር ትሻለህን? አትሻ፥ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፥ እነሆ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።” ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። ስለ ግብጽ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት። ጋሻንና አላባሽን አዘጋጁ ወደ ጦርነትም ቅረቡ። ፈረሰኞች ሆይ! ፈረሶችን ለጉሙና ውጡ፥ ራስ ቁርንም ደፍታችሁ በቦታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ። ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል ጌታ። ፈጣኑ መሸሽ አይችልም ኃያሉም አያመልጥም፤ በሰሜን በኩል ባለው በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ እነርሱ ተሰናክለው ወደቁ። እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዞች የሚናወጥ ይህ ማን ነው? ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዞች ይናወጣል፤ እርሱም፦ እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እሸፍናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሏል። ፈረሶች ሆይ! ውጡ፤ ሰረገሎችም ሆይ! ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፉጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ። ያ ቀን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ እርሱም ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን ነው፤ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና። ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ! ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፤ ብዙ መድኃኒቶችን የተጠቀምሺው በከንቱ ነው፤ ለአንቺ መዳኛ የለሽም። ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ውርደትሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደሚመጣና የግብጽን ምድር እንደሚመታ ጌታ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። በግብጽ አውጁ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ እናንተም፦ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና ተነሥ ራስህንም አዘጋጅ በሉ። ኃይለኞችህ ስለምን ተወገዱ? ጌታ ገፍቶአቸዋልና አልቆሙም። እርሱም ብዙዎችን አሰነካከለ፥ እርሱም ደግሞ ወደቀ፤ እርስ በርሳቸውም፦ ተነሡ፥ የአስጨናቂው ሰው ከሆነው ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባትም ምድር እንመለስ ተባባሉ። በዚያም የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን፦ ሰዓቱን የሚያሳልፍ ለፍላፊ ብለው ጠሩት። እኔ ሕያው በመሆኔ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለው ንጉሥ፥ በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል። አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ሴት ልጅ ሆይ! ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠላለችምና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና በምርኮ ስለምትሄጂ ዕቃዎችሽን አሰናጂ። ግብጽ እጅግ የተዋበች ጊደር ናት፤ ነገር ግን የቆላ ዝንብ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል። በእርሷም መካከል ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮችዋ እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም። “ጠላቶችዋ በኃይል ዘምተው እንደ እንጨት ቈራጮች በምሳር ይመጡባታልና በደረቱ እንደሚሽሎኮሎክ እባብ ድምፅ ታሰማለች። እነርሱ ስፍር ቊጥር የላቸውምና ከአንበጣም ይልቅ ብዙ ናቸውና የማያሳልፍ ጥቅጥቅ ቢሆንም እንኳ የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል ጌታ። የግብጽ ሴት ልጅ ታፍራለች፤ ለሰሜኑ ሕዝብ ተላልፋ በእጃቸው ትሰጣለች።” የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤ ነፍሳቸውንም በሚሽዋት ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በባርያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ። “ነገር ግን አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁና፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል በደኅንነትም ይቀመጣል፥ እርሱንም ማንም አያስፈራውም። አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል ጌታ፤ አንተንም እንድትሰደድ ያደረግኹባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ እንደጥፋትህ መጠን እቀጣሃለሁ እንጂ ያለ ቅጣት ከቶ አልተውህም።” ፈርዖንም ጋዛን ከመምታቱ በፊት ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ውኃ ከሰሜን ይነሣል የሚያጥለቀልቅም ጐርፍ ይሆናል፤ በአገሪቱና በመላዋ ሁሉ፥ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ያጥለቀልቃቸዋል፤ ሰዎቹም ይጮኻሉ፥ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ። ከኃይለኞች ፈረሶቹ የኮቴያቸው ድምፅ፥ ከሰረገሎቹም መንጐድ፥ ከመንኰራኵሮቹም መትመም የተነሣ አባቶች በእጃቸው ድካም ምክንያት ወደ ልጆቻቸው ዘወር ብለው አይመለከቱም። ይህም የሚሆነው ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ለመደምሰስ የተረፉትንም ረዳቶች ሁሉ ከጢሮስና ከሲዶና ለማጥፋት ስለሚመጣው ቀን ነው፤ ጌታ ፍልስጥኤማውያንና የከፍቶርን ደሴት ትሩፍ ያጠፋልና። ቡሀነት በጋዛ ላይ መጥቷል፤ አስቀሎና በጸጥታ ተውጣለች፤ በሸለቆ ያላችሁ ትሩፋን ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ገላችሁን ትተለትላላችሁ? አንተ የጌታ ሰይፍ ሆይ! ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ። ጌታ ትእዛዝ ሰጥቶት እንዴት ዝም ይላል? በአስቀሎናና በባሕር ዳር ላይ በዚያ አዘጋጅቶታል።” ስለ ሞዓብ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ናባው ጠፍታለችና ወዮላት! ቂርያታይም አፍራለች ተይዛለችም፤ አምባይቱም አፍራለች ፈርሳለችም። ከእንግዲህ ወዲህ የሞዓብ ትምክሕት የለም፤ በሐሴቦን ሆነው፦ ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት፥ ብለው ክፉ ነገር አስበውባታል። መድሜን ሆይ! አንቺ ደግሞ በጸጥታ ትዋጫለሽ ሰይፍም ያሳድድሻል። መፍረስና ታላቅ ጥፋት፥ የሚል የጩኸት ድምፅ ከሖሮናይም ተሰማ። ሞዓብ ጠፍታለች፥ ልጆችዋም ጩኸትን አሰምተዋል። በሉሒት አቀበት መራር ልቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉና፥ በሖሮናይምም ቁልቁለት የጥፋትንና የጣርን ጩኸት ሰምተዋል። ሸሽታችሁ ራሳችሁን አድኑ፤ በምድረ በዳ እንዳለ ቁጥቋጦ ሁኑ። በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል። ጌታም እንደ ተናገረው፥ አጥፊው ወደ ከተማ ሁሉ ይመጣል አንዲትም ከተማ አትድንም፤ ሸለቆውም ይጠፋል ሜዳውም እንዳልነበረ ይሆናል። በርራ እንድትወጣ ለሞዓብ ክንፍ ስጡአት፤ ከተሞችዋም ሰው የማይኖርባቸው ባድማ ይሆናሉ። የጌታን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፥ ደም ከማፍሰስም ሰይፉን የሚከለክል ርጉም ይሁን። ሞዓብ ከብላቴንነቱ ጀምሮ ተረጋግቷል፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃም ወደ ዕቃ አልተንቈረቈረም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፤ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሚያገላብጡትን የምልክበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ እነርሱም ያገላብጡታል፤ ጋኖቹንም ባዶ ያደርጋሉ፥ መስቴዎቹንም ይሰብራሉ። የእስራኤልም ቤት መተማመኛቸው በነበረችው በቤቴል እንዳፈረ፥ እንዲሁ ሞዓብ በካሞሽ ያፍራል። እናንተ፦ እኛ ኃያላን በውጊያም ጽኑዓን ነን፥ እንዴት ትላላችሁ? ወደ ሞአብና ከተሞችዋ አጥፊው ወጥቶአል፥ የተመረጡትም ጉልማሶች ወደ መታረድ ወርደዋል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የሆነ ንጉሥ። የሞዓብ ጥፋት ለመምጣት ቀርቦአል የእርሱም መከራ እጅግ ፈጥኖአል። በዙሪያው ያላችሁ ሁሉ ስሙንም የምታውቁ ሁሉ፦ ብርቱው በትረ መንግሥት፥ የከበረው ሽመል፥ እንዴት ተሰበረ!፥ ብላችሁ አልቅሱለት። በዲቦን የምትኖሪ ሆይ! ሞዓብን የሚያጠፋ ወጥቶብሻልና፥ አምባሽንም ሰብሮአልና ከክብርሽ ውረጂ በደረቅም መሬት ላይ ተቀመጪ። በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ! በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤ የሸሸውንና ያመለጠችውን፦ ምን ሆኖአል?፥ ብለሽ ጠይቂ። ሞዓብም ፈርሶአልና አፈረ፤ አልቅሱ ጩኹም፤ ሞዓብ እንደ ጠፋ በአርኖን አጠገብ አውጁ። ፍርድም በሜዳው ላይ፥ በሖሎን፥ በያሳ፥ በሜፍዓት ላይ፥ በዲቦን፥ በናባው፥ በቤት ዲብላታይም ላይ፥ በቂርያታይም፥ በቤትጋሙል፥ በቤትምዖን ላይ፥ በቂርዮት፥ በባሶራ፥ በሞዓብም ምድር በቅርብና በሩቅ ባሉ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቷል። የሞዓብ ቀንድ ተቈረጠ ክንዱም ተሰበረ፥ ይላል ጌታ። በጌታ ላይ ኰርቶአልና አስክሩት፤ ሞዓብም በጥፋቱ ላይ ይንከባለላል፥ ደግሞም መሳቂያ ይሆናል። ለአንተ እስራኤል መሳቂያ አልነበረምን? ወይስ ስለ እርሱ በተናገርህ ቊጥር ራስህን የምትነቀንቀው በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን?። እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ! ከተሞችን ትታችሁ በዓለት ንቃቃት መካከል ተቀመጡ፥ በገደል አፋፍም ቤትዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ ሁኑ። እጅግ እንደ ታበየ ስለ ሞዓብ ትዕቢት ስለ ትምክህቱም ስለ ኩራቱም ስለ እብሪቱም ስለ ልቡም ትዕቢት ሰምተናል። እኔ እብሪቱን አውቃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ፉከራው ሐሰት ነው፥ ሥራውም ሐሰት ነው። ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ ለሞዓብም ሁሉ እጮኻለሁ፤ ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ። አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ! ከኢያዜር ልቅሶ ይልቅ ለአንቺ አለቅሳለሁ፤ ቅርንጫፎችሽ ባሕርን ተሻግረዋል፥ ወደ ኢያዜርም ባሕር ደርሰዋል፤ አጥፊው በበጋ ፍሬሽና በወይንሽ ላይ መጥቷል። ሐሤትና ደስታ ከፍሬያማው እርሻና ከሞዓብ ምድር ጠፍተዋል፤ የወይ ጠጁን ከወይን መጥመቂያው አጥፍቻለሁ፤ ጠማቂውም በእልልታ አይጠምቅም፥ እልልታቸውም እልልታ አይሆንም። ከሐሴቦን ጮኹ እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ ድረስ ድምፃቸውን አሰሙ፤ ከዞዓር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ደርሶአል፤ የኔምሬም ውኃ ደግሞ ይደርቃል። በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን ለአማልክቱም የሚያጥነውን ከሞዓብ አጠፋለሁ፥ ይላል ጌታ። ያተረፈው ትርፉ ጠፍቶበታልና፤ ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ እንቢልታ ድምፅ ይቃትታል፥ ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ድምፅ ይቃትታል። “ራስ ሁሉ መላጣ ጢምም ሁሉ የተላጨ ነውና፤ በእጅም ሁሉ ላይ መተልተል በወገብም ላይ ማቅ አለና። ሞዓብን ማንም እንደማይፈልገው ዕቃ ሰብሬዋለሁና በሞዓብ ሰገነት ሁሉ ላይ በአደባባዩም ላይ በሁሉም ቦታ ልቅሶ አለ፥ ይላል ጌታ። እንዴት ተሰበረ! እንዴትስ አለቀሱ! በእፍረትም የተነሣ ሞዓብ ጀርባውን እንዴት ሰጠ! ስለዚህ ሞዓብ በዙሪያው ላሉት ሁሉ መሳቂያና መደንገጫ ሆኖአል።” ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እንደ ንስር ይበርራል ክንፉንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል። ከተሞቹ ተይዘዋል፥ አምባዎቹም ተወስደዋል፥ በዚያም ቀን የሞዓብ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ሆኖአል። ሞዓብም በጌታ ላይ ኰርቶአልና ከእንግዲህ ወድያ ሕዝብ አይሆንም፥ እርሱም ይጠፋል። በሞዓብ የምትኖር ሆይ! ፍርሃትና ጉድጓድ ወጥመድም በአንተ ላይ አለ፥ ይላል ጌታ። በሞዓብ ላይ የመጐብኘትን ዓመት አመጣበታለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ከአስፈሪውም ነገር የሸሸ በጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፥ ከጉድጓድም ውስጥ የሚወጣ በወጥመድ ይያዛል። “የሸሹ ደክመው ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፤ እሳት ከሐሴቦን ነበልባልም ከሴዎን መካከል ወጥቶአል የሞዓብን ግንባር የሁከትንም ልጆች ዘውድ በልቶአል። ሞዓብ ሆይ! ወዮልህ! የካሞሽ ሰዎች ጠፍቶአል፤ ወንዶች ልጆችህ ተማርከዋልና፥ ሴቶች ልጆችህም ወደ ምርኮ ሄደዋልና። ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።” የሞዓብ ፍርድ እስከዚህ ድረስ ነው። ስለ አሞን ልጆች፤ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለእስራኤል ልጆች የሉትምን? ወይስ ወራሽ የለውምን? ታዲያ ሚልኮምስ ጋድን ለምን ወረሰ? ሕዝቡስ በከተሞቹ ላይ ለምን ተቀመጠ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአሞን ልጆች ከተማ በረባት ላይ የጦርነት ውካታን የማሰማበት ቀኖች ይመጣሉ፥ ይላል ጌታ፤ የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች፥ ሴቶች ልጆችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፥ እስራኤልም የወረሱትን ይወርሳል፥ ይላል ጌታ። ሐሴቦን ሆይ! ጋይ ፈርሳለችና አልቅሺ፤ እናንተም የረባት ሴቶች ልጆች ሆይ! ሚልኮም ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፥ ማቅም ታጠቁ፥ አልቅሱም፥ በቅጥሮችም መካከል ተርዋርዋጡ። ማን በእኔ ላይ ይመጣብኛል ብለሽ በመዝገብሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! በሸለቆችሽ፥ ውኃ በሚፈስስባቸው ሸለቆችሽ፥ ለምን ትመኪያለሽ? እነሆ፥ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ በአንቺ ላይ ፍርሃትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፥ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም። “ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆች ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።” ስለ ኤዶምያስ፤ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸውስ አልቆአልን? የዔሳውን ጥፋት እርሱን በምጐበኝበት ጊዜ አመጣበታለሁና፥ እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ! ሽሹ፥ ወደ ኋላ ተመለሱ፥ በጥልቅም ውስጥ ተቀመጡ። ወይን ለቃሚዎች ቢመጡብህ፥ ቃርሚያውን አይተዉልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፥ የሚዘርፉት የሚበቃቸውን ያህል አይደለምን? እኔ ግን ዔሳውን ዐራቈትሁት፥ የመሸሸጊያውንም ስፍራዎች ገለጥሁ፥ እርሱም ለመሸሸግ አይችልም፤ ዘሩም ወንድሞቹም ጎረቤቶቹም ጠፍተዋል እርሱም የለም። ድሀ አደጎችህን ተዋቸው እኔ በሕይወት አኖራቸዋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ይታመኑ።” ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ ጽዋውን መጠጣት የማይገባቸው ሰዎች ጠጥተውታል፤ አንተስ ሳትቀጣ ፈጽሞ ትቀራለህን? በእርግጥ ትጠጣለህ እንጂ ያለ ቅጣት አትቀርም። ባሶራ መሣቀቅያና መሰደቢያ፥ ባድማና መረገሚያ እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ከተሞችዋም ሁሉ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ።” ከጌታ ዘንድ መልእክት ሰምቻለሁ በአሕዛብም መካከል፦ “ተሰብሰቡ፥ በእርሷም ላይ ኑ ለጦርነትም ተነሡ” የሚል መልእክተኛ ተልኮአል። እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ታናሽ፥ በሰዎችም መካከል የተናቅህ አድርጌሃለሁ። በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ! ማሣቀቅያህና የልብህ ኩራት አታልለውሃል። ምንም እንኳ ጎጆህን እንደ ንስር ጎጆ ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ። “ኤዶምያስም መሣቀቂያ ትሆናለች፥ የሚያልፍባትም ሁሉ ይሣቀቃል፥ ስለ ተደረገባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። ሰዶምና ገሞራ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ጎረቤቶቻቸው እንደ ተገለባበጡ፥ ይላል ጌታ፥ እንዲሁ ማንም ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም። እነሆ፥ በጽኑ የበጎች በረት ላይ ከዮርዳኖስ ዱር ውስጥ እንደሚወጣ አንበሳ እንዲሁ እኔ ከእርሷ ዘንድ በድንገት አባርረዋለሁ፤ የተመረጠውንም ማንኛውንም ሰው በእርሷ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ እኔን እንድመጣ የሚጠራኝ ማን ነው? ወይስ በፊቴ የሚቆም እረኛ ማን ነው? ስለዚህ ጌታ በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋው ትንንሾች እንኳ ይጐትቷቸዋል፤ በእውነት የማደሪያቸውም በረት በእነርሱ ላይ ይሣቀቃል። ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ የጩኸትም ድምፅ በኤርትራ ባሕር ተሰማ። እነሆ፥ እንደ ንስር ወጥቶ ይበራል ክንፉንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፥ በዚያም ቀን የኤዶምያስ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል።” ስለ ደማስቆ፤ ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ ቀለጡም፤ ለማረፍም እንደማይችል ባሕር በፍርሃት ተናወጡ። ደማስቆ ደከመች ለመሸሽም ዘወር አለች መንቀጥቀጥም ያዛት፥ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት። የተመሰገነችው ከተማ፥ የደስታዬ ከተማ፥ ሳትለቀቅ እንዴት ቀረች? ስለዚህ ጐልማሶችዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ወታደሮችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ የወልደ አዴርንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስላደረጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ አሦር መንግሥታት፤ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፥ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ። ድንኳኖቻቸውንና መንጋቸውን፥ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ ይወስዳሉ፤ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው እየነዱ ይወስዳሉ፥ እነርሱም፦ በዙሪያቸው ሁሉ ሽብር አለ፥ እያሉ ለእነርሱ ይጮኻሉ። እናንተ በአሦር የምትኖሩ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፥ አሳብም አስቦባችኋልና ሽሹ ወደ ሩቅም ስፍራ ሂዱ በጥልቁም ውስጥ ተቀመጡ፥ ይላል ጌታ። “ተነሡ፥ በደኅንነት ተቀምጦ ተረጋግቶ ወዳለው፥ የቅጥር በርና መቀርቀሪያ ወደሌለው ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ውጡ፥ ይላል ጌታ። ግመሎቻቸው ይበዘበዛሉ የእንስሶቻቸውም ብዛት ይማረካል፤ ጠጉራቸውንም ዙሪያውን የተላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከሁሉም አቅጣጫ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ። አሦርም የቀበሮዎች መኖሪያና የዘለዓለም ባድማ ትሆናለች፤ በዚያም ማንም ሰው አይኖርም፥ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም።” በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ዋና የኃይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ። ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፥ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች ተሰድደው ያልደረሱበት ሕዝብ አይገኝም። በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ፤ በእነርሱም ላይ ጽኑ ቁጣዬ የሆነውን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍ እልክባቸዋለሁ፤ ዙፋኔንም በኤላም አኖራለሁ ከዚያም ንጉሡንና ሹማምንትን አጠፋለሁ፥ ይላል ጌታ። ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።” ጌታ ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውጁም፥ ዓላማውንም አንሡ፤ አውጁ፥ ሳትደብቁም እንዲህ በሉ፦ ባቢሎን ተያዘች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ተሰባበረ፤ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ተሰባበሩ። ሕዝብ ከሰሜን በእርሷ ላይ ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፥ የሚቀመጥባትም አይገኝም፤ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም ጌታን ይፈልጋሉ። ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው፦ ኑ፥ ከቶ በማይረሳ በዘለዓለም ቃል ኪዳን ከጌታ ጋር በአንድነት እንሁን፥ ብለው ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ። ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፥ ከተራሮችም ላይ እንዲያፈገፍጉ አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኮረብታ ሄደዋል፥ በረታቸውንም ረስተዋል። ያገኙአቸው ሁሉ አጠፉአቸው፥ ጠላቶቻቸውም፦ በጽድቅ ማደሪያ በጌታ ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በጌታ ላይ እነርሱ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም፥ አሉ። ከባቢሎን መካከል ሽሹ፥ ከከለዳውያንም ምድር ውጡ፥ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ። እነሆ፥ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ፤ በእርሷም ላይ ይሰለፋሉ፥ ከዚያም ትያዛለች፤ ፍላጾቻቸውም ተጨናግፎ ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ብልህ ጀግና ፍላጻ ናቸው። የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች፥ የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፥ ይላል ጌታ። ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ ሆይ! ደስ ቢላችሁ፥ ሐሤትንም ብታደርጉ፥ በማበራየት ላይም እንዳለች ጊደር ብትፈነጩ፥ እንደ ብርቱዎችም ፈረሶች ብታሽካኩ እንኳ፥ እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፥ የወለደቻችሁም ትዋረዳለች፤ እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ኋለኛይቱ ትሆናለች፤ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር በረሀም ትሆናለች። ከጌታ ቁጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይቀመጥባትም፤ በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይሣቀቃል በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል። እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ፥ ባቢሎንን ዙሪያዋን ክበቡ፤ በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጻንም አታስቀሩ። የጌታ በቀል ነውና በዙሪያዋ ሆናችሁ በእርሷ ላይ ጩኹ፤ እጅዋን ሰጠች፤ ግንቦችዋ ወደቁ ቅጥሮችዋም ፈረሱ፤ እርሷን ተበቀሉ እንደ ሠራችውም ሥሩባት። ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ፤ የአስጨናቂው ሰው ከሆነው ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል። እስራኤል የባዘነ በግ ነው፤ አንበሶች አሳደዱት፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ። እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል፥ ሆዱም በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ትጠግባለች። እንደትሩፍ የተውኳቸውን እነዚያን ይቅር እላቸዋለሁና በዚያን ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ነገር ግን በዚያ ምንም አይገኝም። በምራታይም ምድር ላይ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ውጣ፤ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፥ ይላል ጌታ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ። የጦርነት ሁካታ ታላቅም ጥፋት በምድሪቱ ላይ አለ። የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተሰበረ! ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት መሣቀቅያ ሆነች! ባቢሎን ሆይ! አጥምጄብሻለሁ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ ከጌታ ጋር ስለ ታገልሽ ተገኝተሻል ተይዘሻልም። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር የሚፈጽመው ሥራ አለውና ጌታ የጦር ግምጃ ቤቱን ከፍቶ የቁጣውን የጦር መሣርያ አወጣ። ከየአቅጣጫው በእርሷ ላይ ኑ፥ ጎተራዎችዋንም ክፈቱ፤ እንደ ተቈለለ ነዶ ከምርዋት ፈጽማችሁም አጥፉአት፥ ምንም ዓይነት ነገር አታስተርፉላት። ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ፥ ወደ መታረድም ይውረዱ፤ ቀናቸው፥ የመጐብኘታቸው ጊዜ ደርሶአልና ወዮላቸው! የአምላካችንን የጌታን በቀል ስለ መቅደሱም ሲል የሚበቀለውን በቀል በጽዮን ለመናገር ከባቢሎን ምድር የሚመጡትን የኰብላዮችና የስደተኞች ድምፅ አድምጡ። ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው፤ በዙሪያዋ ስፈሩባት አንድም ሰው አያምልጥ፤ በእስራኤል ቅዱስ በጌታ ላይ በኩራት አልታዘዝም ብላለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፥ እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት። ስለዚህ ጐልማሶችዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ወታደርዎችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ። ትዕቢተኛው ሆይ! የመጐብኘትህ ጊዜ፥ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ትዕቢተኛው ተሰናክሎ ወድቆአ የሚያነሣውም ማንም የለም፤ በከተሞቹም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፥ በዙሪያውም ያለውን ሁሉ ትበላለች። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተጨቊነዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይዘዋቸዋል፥ እነርሱንም ለመልቀቅ እንቢ ብለዋል። የሚዋጃቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ ነው፤ ምድሪቱንም ለማሳረፍ በባቢሎንም የሚኖሩትን ለማወክ ሙግታቸውን ፈጽሞ ይሟገታል። ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፥ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፥ ይላል ጌታ። ሰይፍ በምዋርተኞች ላይ አለ ሞኞችም ይሆናሉ፥ ሰይፍም በኃያላኖችዋ ላይ አለ እነርሱም ይጠፋሉ። ሰይፍ በፈረሶችዋና በሰረገሎችዋ ላይ በመካከልዋም ባሉት በባዕድ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ ሰይፍም በመዝገቦችዋ ላይ አለ እነርሱም ይበዘበዛሉ። እርሷ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናትና፥ እነርሱም በጣዖታቱ ላይ እንደ እብድ ይሆናሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። ስለዚህ በባቢሎን የምድረ በዳ አራዊት ከተኩላዎች ጋር ይቀመጡባታል፥ ሰጐኖችም ይቀመጡባታል፤ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘለዓለም አይቀመጥባትም፥ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም። ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ጎረቤቶቻቸውን እግዚአብሔር እንደ ገለባበጣቸው፥ ይላል ጌታ፥ እንዲሁ ማንም ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም። እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል፤ ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ። ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር የሚተምም ነው፤ በፈረሶች ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ! ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፥ እጆቹም ደክመዋል፥ ጣርም ይዞታል፥ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል። እነሆ፥ በጽኑ የበጎች በረት ላይ ከዮርዳኖስ ዱር ውስጥ እንደሚወጣ አንበሳ እንዲሁ እኔ ከእርሷ ዘንድ በድንገት አባርራቸዋለሁ፤ የተመረጠውንም ማንኛውንም ሰው በእርሷ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ እኔን እንድመጣ የሚጠራኝ ማን ነው? ወይስ በፊቴ የሚቆም እረኛ ማን ነው? ስለዚህ ጌታ በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፥ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋው ትንንሾች እንኳ ይጐትቷቸዋል፤ በእውነት የማደሪያውም በረት በእነርሱ ላይ ይሣቀቃል። ባቢሎን ስትያዝ ከነበረው የሁካታ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ተሰማ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በሌብ-ቃምያ በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ። በባቢሎንም ላይ የሚያዘሩትን ሰዎች እልካለሁ እነርሱም ያዘሩአታል፥ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። ቀስተኛው ቀስቱን አይገትር ጥሩሩንም ለብሶ አይነሣ፤ ለጐልማሶችዋ አትዘኑ ሠራዊትዋንም ሁሉ አጥፉ። በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፥ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉ። ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ ዘንድ አልተተዉም። ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፥ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፥ የጌታ የበቀል ጊዜ በእርሷ ላይ ነውና፥ እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። ባቢሎን በጌታ እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፥ አሕዛብም ከወይን ጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ እንደ እብድ ሆነዋል። ባቢሎን በድንገት ወደቀች ተሰበረችም፤ አልቅሱላት፥ ምናልባት ትፈወስ እንደሆነ ለቁስልዋ የሚቀባውን መድኃኒት ውሰዱላት። ባቢሎንን ልንፈውሳት ሞከርን፥ እርሷ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሏልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ አገራችን እንሂድ። ጌታ ጽድቃችንን በግልጥ አውጥቶአል፤ ኑ፥ በጽዮን የአምላካችንን የጌታን ሥራ እንናገር። ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አንሡ፤ ጌታ ሊያጠፋት አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፤ የጌታ በቀል ስለ መቅደሱ ሲል የሚበቀለው በቀል በእርሷ ላይ ነውና። በባቢሎን ቅጥሮች ላይ ዓላማውን አንሡ፥ ጥበቃን አጠናክሩ፥ የጥበቃን ሰዎች አቁሙ፥ ድብቅ ጦር አዘጋጁ፤ በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን ጌታ አስቦታልና እንዲሁም ደግሞ አድርጎታልና። አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገቦችም የበለጠግሽ ሆይ! የእንጀራሽ ገመድ ተበጥሶዋል ፍጻሜሽ ደርሶአል። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፦ በእውነት ብዛታቸው እንደ አንበጣ በሚሆኑ ሰዎች እሞላሻለሁ፥ እነርሱም የአሸናፊነትን ጩኸት የይጮኹብሻል። ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። ሰው ሁሉ ቂላ ቂልና እውቀት የሌለው ሆኖአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። የያዕቆብ ድርሻ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ ነው። አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤ በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ፤ በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሠረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ወንድንና ሴትን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ጐልማሳውንና ድንግሊቱን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ገዢዎችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ። በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለ ሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፥ ይላል ጌታ። አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊው ተራራ ሆይ! እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከዓለትም ራስ ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፥ ለዘለዓለምም ባድማ ትሆናለህ፥ ይላል ጌታ። በምድር ላይ ዓላማን አንሡ በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ፥ አሕዛብንም ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ጥሩባት አለቃንም በእርሷ ላይ ሹሙ፤ እንደ ጠጉራም ኩብኩባ ፈረሶችን በእርሷ ላይ አውጡ። አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት ገዢዎችዋንም ሹማምንቶችዋንም ሁሉ የግዛትዋንም ምድር ሁሉ በእርሷ ላይ ለጦርነት አዘጋጁ። ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ የጌታ አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጠች ተወራጨችም። የባቢሎን ኃያላን መዋጋትን ትተዋል በምሽጎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ደክሙአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል መቀርቀሪያዎችዋም ተሰብረዋል። ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር አንደኛው ሯጭ ሌላውን ሯጭ አንዱም መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ለመገናኘት ይሮጣል። የወንዙም መሻገርያዎች ተይዘዋል፥ የውኃ ማቆርያዎቹም በእሳት ተቃጥለዋል ወታደሮቹም በሽብር ውስጥ ናቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ ዐውድማ ነች፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል።” የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፥ አደቀቀኝም፥ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፥ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፥ ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም አውጥቶ ተፋኝ። በጽዮን የሚኖሩ እንዲህ ይበሉ፦ “በእኔና በሥጋ ዘመዶቼ ላይ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን” ኢየሩሳሌምም እንዲህ ትበል፦ “ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን”። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሙግትሽን እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም አደርቀዋለሁ ምንጭዋንም እንዲደርቅ አደርጋለሁ። ባቢሎንም የፍርስራሽ ክምር፥ የቀበሮ ማደሪያ ሰውም የማይቀመጥባት መሣቀቅያና ማፍዋጫ ትሆናለች። በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፥ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጉረመርማሉ። ሞቅ ባላቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ አሰክራቸዋለሁም፥ ይላል ጌታ። እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ። ሼሻክ እንዴት ተያዘች! ምድርም ሁሉ የሚያመሰግናት እንዴት ተወሰደች! ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መሣቀቅያ እንዴት ሆነች! ባሕሩ በባቢሎን ላይ ወጥቶባታል በሚናወጠውም ሞገዱ ተሸፍናለች። ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፥ ሰውም የማይቀመጥባቸው የሰውም ልጅ የማያልፍባቸው ምድር ሆኑ። በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይነጉዱም፥ የባቢሎንም ቅጥር ወድቆአል። ሕዝቤ ሆይ! ከመካከልዋ ውጡ እያንዳንዱም ሰው ከጌታ ጽኑ ቁጣ ነፍሱን ያድን። በምድሪቱም ከሚሰማው ወሬ የተነሣ ልባችሁ የዛለ አይሁን አትፍሩም፤ በአንዱም ዓመት አንድ ወሬ፥ በሚቀጥለውም ዓመት ሌላ ወሬ ይመጣል፥ በምድሪቱም ላይ ዓመጽ ይሆናል፥ ገዢም በገዢ ላይ ይነሣል። ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ምድርዋም ሁሉ ያፈረች ትሆናለች ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፥ ይላል ጌታ። ለባቢሎን በምድሪቱ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ወድቀዋል እንዲሁ ለእስራኤል ተወግተው ለሞቱት ባቢሎን መውደቅ አለባት። ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ! ሂዱ፥ አትቁሙ፤ በሩቅ ስፍራ ሆናችሁ ጌታን አስታውሱ፥ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡአት። ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም በጌታ ቤት ውስጥ ወዳሉት ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች ገብተዋልና ውርደት ፊታችንን ሸፍኖታል። ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን ምስሎችዋን የምቀጣበት በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጋው የሚያቃስትበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። ምንም እንኳ ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጠናክር፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል ጌታ። ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። ጌታ ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርሷም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፥ የድምፃቸውም ጩኸት ያስገመግማል። አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ኃያላኖችዋ ተያዙ፥ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ ጌታ ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፥ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል። አለቆችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ ገዢዎችዋንና ሹማምቶችዋን ኃያላኖችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘለዓለምም አንቀላፍተው አይነቁም፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለው ንጉሥ። “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰፋፊዎቹ የባቢሎን ቅጥሮች ፈጽመው ይፈርሳሉ ረጃጅሞችም በሮችዋ በእሳት ይቃጠላሉ፤ ሕዝቡም በከንቱ ጉልበቱን ይፈስሳል፥ አሕዛብም የደከሙበት ነገር ለእሳት ይሆናል።” የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ሠራያም የሻለቃ መጋቢ ባሻ አዛዥ ነበረ። በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው። ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፦ “ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ ልብ ብለህ ይህን ቃል ሁሉ አንብብና፥ እንዲህ በል፦ ‘አቤቱ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘለዓለምም ባድማ እንድትሆን ልታጠፋት በዚህች ስፍራ ላይ አንተ ተናግረሃል።’ ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት በኤፍራጥስም ወንዝ መካከል ጣለው፤ አንተም እንዲህ በል፦ ‘እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች አትነሣምም።’ ” የኤርምያስ ቃላት እስከዚህ ድረስ ነው። ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ይባል ነበር፥ እርሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። ኢዮአቄምም እንዳደረገው ሁሉ በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረገ። በእርግጥ ከጌታ ቁጣ የተነሣ ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆነ፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ። ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ለመክበብያ የሚሆን ምሽግ ሠሩባት። ከተማይቱም እስከ ንጉሡ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበር፥ ለአገሬውም ሰው እንጀራ ታጣ። የከተማይቱም ቅጥር ተጣሰ፥ ወታደሮችም ሁሉ ሸሹ፥ በሁለቱም ቅጥሮች መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማይቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ ወደ ዓረባም በሚወስደው መንገድ ሄዱ። የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉት፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ደረሱበት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ተበትነው ነበር። ንጉሡንም ያዙት፥ እርሱንም የባቢሎን ንጉሥ ወዳለባት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች ዓይኑ እያየ ገደላቸው፥ እንዲሁም የይሁዳን አለቆች ሁሉ በሪብላ ገደላቸው። የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሰንሰለት አሰረው ወደ ባቢሎንም ወሰደው፥ እስኪሞትም ድረስ በእስር ቤት አኖረው። በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በዓሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የሚያገለግለው የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። የጌታን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆችን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሁሉ አፈረሰ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን የሕዝቡን ድኆች፥ በከተማይቱም ውስጥ የተረፈውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የተረፉትንም የእጅ ሞያተኞች አፈለሰ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከአገሩ ድኆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። ከለዳውያንም በጌታ ቤት የነበሩትን የናስ ዓምዶች በጌታም ቤት የነበሩትን የውኃ ማመላለሻ ፉርጎዎችንና የናሱን ኩሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። የሸክላ ድስቶችንና መጫሪያዎችንም፥ መኰስተሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችንም፥ ሙዳዮችና የሚገለገሉባቸውንም የናስ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። የዘበኞቹም አለቃ ወጭቶቹንና ማንደጃዎቹን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖቹንና የሸክላ ድስቶቹን፥ መቅረዞችንና ሙዳዮችን መንቀሎችንም፥ የወርቁን ዕቃ በወርቅ፥ የብሩንም ዕቃ በብር አድርጎ፥ ወሰደ። ንጉሡ ሰሎሞንም ለጌታ ቤት ያሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኩሬ፥ ከኩሬውና ከውኃ ማመላለሻ ፉርጎዎቹም በታች የነበሩትን ዐሥራ ሁለቱን የናስ በሬዎች ወሰደ፤ ለእነዚህ ከናስ ለተሠረሩ ዕቃዎች ሁሉ መመዘኛ ሚዛን አልነበረም። እነዚህም ዓምዶች፥ የአንዱ ዓምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም ልኬት ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውፍረቱም አራት የጣት ስንዝር ያህል ነበረ፥ መሀል ለመሀልም ክፍት ነበረ። የናሱም ጉልላት በላዩ ነበረ፤ የአንዱም ጉልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ፥ በጉልላቱም ላይ በዙሪያው ሁሉ ከናስ የተሠሩ መረበብና ሮማኖች ነበሩበት፤ በሁለተኛውም ዓምድ ደግሞ እንደዚህ ያለ ነገርና ሮማኖች ነበሩበት። በስተ ውጭም በኩል ዘጠና ስድስት ሮማኖች ነበሩ። በመረበቡም ዙሪያ የነበሩ ሮማኖች ሁሉ አንድ መቶ ነበሩ። የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን በማዕረጉም ሁለተኛ የነበረውን ካህን ሶፎንያስን የደጃፉም ጠባቂዎች የነበሩትን ሦስቱን ሰዎች ወሰደ፤ ከከተማይቱም በወታደሮች ላይ ተሾሞ ከነበረው አንዱን አዛዥ፥ በከተማይቱም ውስጥ ከተገኙት የንጉሡ አማካሪዎች ሰባቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ ለጦርነት የሚመለምለውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስልሳ ሰዎች ወሰደ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ። ናቡከደነፆር ማርኮ ያፈለሰው የሕዝብ ቍጥር ብዛት ይህ ነው፤ በሰባተኛው ዓመት ሦስት ሺህ ሀያ ሦስት አይሁድ፤ በናቡከደነፆርም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰው ከኢየሩሳሌም ማርኮ አፈለሰ፤ በናቡከደነፆር በሀያ ሦስተኛው ዓመት የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ከአይሁድ ሰባት መቶ አርባ አምስት ሰው ማርኮ አፈለሰ፤ በአጠቃላይ የሰዎቹ ብዛት አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዓሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ አምስተኛው ቀን፥ የባቢሎን ንጉሥ ኤዌል ማሮዴክ በነገሠ በአንደኛው ዓመት ለይሁዳ ንጉሥ ለዮአኪን ቸርነት አደረገለት ከእስር ቤትም አወጣው፤ በመልካምም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። ዮአኪንም በእስር ቤትም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠ፥ በሕይወቱም ዘመን ሁሉ በንጉሡ ገበታ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። ስለ እርሱም ቀለብ የባቢሎን ንጉሥ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ፥ እስኪሞት ድረስ፥ በየዕለቱ የሚያስፍልገውን የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር። አሌፍ። ሕዝብ ሞልቶባት የነበረች ከተማ ብቻዋን እንዴት ተቀመጠች! በአሕዛብ መካከል ታላቅ የነበረች እንደ መበለት ሆናለች፥ በአውራጆች መካከል ልዕልት የነበረች ተገዢ ሆናለች። ቤት። በሌሊት እጅግ ታላቅሳለች፥ እንባዋም በጉንጭዋ ላይ አለ፥ ከውሽሞችዋ ሁሉ የሚያጽናናት የለም፥ ወዳጆችዋ ሁሉ ወነጀሉአት ጠላቶችም ሆኑአት። ጋሜል። ይሁዳ ስለ መጨነቅና ስለ ባርነት ብዛት ተማረከች፥ በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች ዕረፍትም አላገኘችም፥ የሚያስጨንቁአት ሁሉ ተጨንቃ አገኙአት። ዳሌጥ። ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፥ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፥ ድንግሎችዋም ተጨነቁ እርሷም በምሬት አለች። ሄ። ስለ ኃጢአትዋ ብዛት እግዚአብሔር አስጨንቆአታልና አስጨናቂዎችዋ ራስ ሆኑ ጠላቶችዋም ተከናወነላቸው፥ ሕፃናቶችዋ በአስጨናቂዎች ፊት ተማርከዋል። ዋው። ከጽዮን ሴት ልጅ ውበትዋ ሁሉ ወጥቶአል፥ አለቆችዋ ማሰማርያ እንደማያገኙ ዋላዎች ሆኑ፥ ከሚያባርሩአቸው ፊት ተዳክመው ሄዱ። ዛይ። ኢየሩሳሌም በጭንቀትዋና በመከራዋ ወራት ከጥንት ጀምሮ የነበረላትን የከበረን ነገር ሁሉ አሰበች፥ ሕዝብዋ በአስጨናቂዎች እጅ በወደቀ ጊዜ የሚረዳትም በሌላት ጊዜ፥ አስጨናቂዎች አዩአት በመፍረስዋም ሳቁ። ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፥ ስለዚህ ረክሳለች፥ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፥ እርሷም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች። ጤት። አደፍዋ በልብስዋ ዘርፍ ነበረ፥ ፍጻሜዋን አላሰበችም፥ ስለዚህ በድንቅ ተዋርዳለች፥ የሚያጽናናትም የለም፥ አቤቱ፥ ጠላት ከፍ ከፍ ብሏልና መከራዬን ተመልከት። ዮድ። አስጨናቂው በከበረ ነገርዋ ሁሉ ላይ እጁን ዘረጋ፥ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ ያዘዝሃቸው አሕዛብ ወደ መቅደስዋ ሲገቡ አይታለችና። ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እየጮኹ ያለቅሳሉ እንጀራም ይፈልጋሉ፥ ሰውነታቸውን ለማበርታት የከበረ ሀብታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፥ አቤቱ፥ ተጐሳቁያለሁና እይ፥ ተመልከትም። ላሜድ። እናንተ መንገድ አላፊዎች ሁሉ፥ በእናንተ ዘንድ ምንም የለምን? እግዚአብሔር በጽኑ ቁጣው ቀን እኔን እንዳስጨነቀበት በእኔ ላይ እንደተደረገው እንደ እኔ መከራ የሚመስል መከራ እንዳለ ተመልከቱ፥ እዩ። ሜም። ከላይ እሳትን ወደ አጥንቴ ሰደደ በረታችበትም፥ ለእግሬ ወጥመድ ዘረጋ ወደ ኋላም መለሰኝ፥ አጠፋኝም ቀኑንም ሁሉ አደከመኝ። ኖን። የኃጢአቶቼ ቀንበር በእጁ ተይዛለች፥ ታስረው በአንገቴ ላይ ወጥተዋል፥ ጉልበቴን አደከመ። ጌታ በፊታቸው እቆም ዘንድ በማልችላቸው እጅ አሳልፎ ሰጠኝ። ሳምኬት። ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፥ ጐልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፥ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት። ዔ። የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቆአልና ስለዚህ አለቅሳለሁ፥ ዓይኔ፥ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል። ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል። ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች የሚያጽናናት የለም፥ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፥ ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች። ጻዴ። በአፉ ነገር ላይ ዓመጽ አድርጌአለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ እባካችሁ፥ ስሙ መከራዬንም ተመልከቱ፥ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ ተማርከው ሄዱ። ቆፍ። ውሽሞቼን ጠራሁ እነርሱም አታለሉኝ፥ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ ሰውነታቸውን ያበረቱ ዘንድ መብል ሲፈልጉ በከተማ ውስጥ ሞቱ። ሬስ። አቤቱ፥ ተጨንቄአለሁና፥ አንጀቴም ታውኮብኛልና ተመልከት፥ ዓመፃን ፈጽሞ አድርጌአለሁና ልቤ በውስጤ ተገላበጠብኝ፥ በሜዳ ሰይፍ ልጆቼን አጠፋ በቤትም ሞት አለ። ሳን። እኔ እየጮኽሁ እንደማለቅስ ሰምተዋል፥ የሚያጽናናኝ የለም፥ ጠላቶቼ ሁሉ ስለ መከራዬ ሰምተዋል፥ አንተ አድርገኸዋልና ደስ አላቸው፥ ስለ እርሱ የተናገርኸውን ቀን ታመጣለህ እነርሱም እንደ እኔ ይሆናሉ። ታው። ልቅሶዬ እጅግ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና። ክፋታቸው ሁሉ ወደ ፊትህ ይድረስ፥ ስለ ኃጢአቴ ሁሉ እንዳደረግህብኝ አድርግባቸው። አሌፍ። ጌታ በቁጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደምን አደመናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቁጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም። ቤት። ጌታ የያዕቆብን ማደሪያዎች ሁሉ ዋጠ፥ አልራራምም፥ በመዓቱ የይሁዳን ሴት ልጅ አምቦች አፈረሰ፥ ወደ ምድርም አወረዳቸው መንግሥቱንና አለቆችዋን አረከሰ። ጋሜል። በጽኑ ቁጣው የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ቀጠቀጠ፥ ቀኝ እጁን ከጠላት ፊት ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያውም እንደሚባላ እንደ እሳት ነበልባል ያዕቆብን አቃጠለ። ዳሌጥ። ቀስቱን እንደ ጠላት ገተረ፥ እንደ አስጨናቂ ቀኝ እጁን አጸና፥ ለዓይንም የሚያምረውን ሁሉ ገደለ፥ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን መዓቱን እንደ እሳት አፈሰሰ። ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፥ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፥ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ። ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፥ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፥ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቁጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ። ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ። ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፥ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፥ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፥ በአንድነት ደከሙ። ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ፤ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፥ ነቢዮችዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፥ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፥ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ። ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፥ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ። ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን፦ እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል። ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፥ የሚፈውስሽ ማን ነው? ኖን። ነቢዮችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፥ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፥ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል። ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና፦ በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ። ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፥ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ፦ ውጠናታል፥ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፥ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ። ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፥ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፥ አፈረሰ አልራራምም፥ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ። ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፥ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፥ የዐይንሽ ብሌን አታቋርጥ። ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፥ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ። ሬስ። አቤቱ፥ እይ፥ በማን ላይ እንደዚህ እንዳደረግህ ተመልከት። በውኑ ሴቶች ፍሬያቸውን፥ ያቀማጠሉአቸውን ሕፃናት፥ ይበላሉን? በውኑ ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይገደላሉን? ሳን። ብላቴናውና ሽማግሌው በመንገዶች ላይ ተጋደሙ፥ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ በሰይፍ ወድቀዋል፥ በቁጣህ ቀን ገደልሃቸው፥ ሳትራራ አረድሃቸው። ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቁጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፥ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው። አሌፍ። በቁጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ። ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፥ ሰንሰለቴን አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ከለከለ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ። ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፥ ባድማ አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኩላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ። ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፥ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ። ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፥ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፥ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፦ እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፥ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች። ጤት። ጌታ በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ የሆነው እንደሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጉንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ። ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፥ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፥ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም። ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም። ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው? ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን? ሕያው ሰው የሚያጉረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጉረመርም ስለ ምንድነው? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ። በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም። ሳምኬት። በቁጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፥ ገደልኸን፥ አልራራህም። ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ። በአሕዛብ መካከል ጉድፍና ውዳቂ አደረግኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን። ድንጋጤና ቁጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ሕይወቴን በጉድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፥ እኔም፦ ጠፋሁ ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። ድምፄን ሰማህ፥ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ቀርበህ፦ አትፍራ አልህ። ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፥ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ። የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ። አቤቱ፥ በቁጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ። አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ! ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፥ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች። ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፥ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም። ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፥ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ። ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች። ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፥ ገላቸው ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ። ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቁሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፥ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፥ ደርቆአል፥ እንደ እንጨት ሆኖአል። ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፥ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል። ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፥ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኗቸው። ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቁጣውን አፍስሶአል፥ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች። ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም። ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢዮችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው። ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፥ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል። ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል፦ በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ። ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፥ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም። ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፥ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል። ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፥ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል። ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፥ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን። ሬስ። ስለ እርሱ፦ በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጉድጓዳቸው ተያዘ። ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፥ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም። ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፥ ኃጢአትሽን ይገልጣል። አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፥ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፥ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን። አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፥ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም። ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን። አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፥ እኛም በደላቸውን ተሸከምን። ባርያዎች ሠልጥነውብናል፥ ከእጃቸው የሚታደገን የለም። ከምድረበዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን። ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ። በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ። አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፥ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም። ጉልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጉልማሶችም ከበገናቸው ተሻሩ። የልባችን ደስታ ቀርቶአል፥ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፥ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን! ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፥ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፥ ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና። አቤቱ፥ አንተ ለዘለዓለም ትኖራለህ፥ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። ስለምን ለዘለዓለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ? አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፥ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፥ እጅግ ተቈጥተኸናል። በሠላሳኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ነበርሁ፥ ሰማያት ተከፈቱ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ። ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ የጌታ ቃል፥ በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ፥ ወደ ቡዚ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። በዚያም የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ሆነች፥ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስ መጣ፥ በዙሪያው ብርሃን ያለው መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበር፥ በእሳቱም መካከል የሚያንጸባርቅ ነገር ነበረ። ከመካከልም አራት ሕያው ፍጡራን የሚመስሉ ወጡ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። እያንዳንዳቸውም አራት ፊቶች፥ እያንዳንዳቸውም አራት ክንፎች ነበራቸው። እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግሮቻቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ያንጸባርቅ ነበር። ከክንፎቻቸውም ስር በአራቱም ጎናቸው የሰው እጆች ነበሩ፤ አራቱም ፊቶቻቸውና ክንፎቻቸው እንዲህ ነበሩ፦ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ ይነካካ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም፥ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር። የፊታቸውም ምስል የሰው ፊት፥ አራቱም በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፥ በግራ በኩል የላም ፊት ነበራቸው፥ አራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው። ፊታቸው እንዲህ ነበረ። ክንፎቻቸውም ወደ ላይ ተዘርግተው ነበር፥ የእያንዳንዳቸውም ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ በሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር። እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፥ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር። የሕያዋኑም መልክ የሚነድድ የእሳት ፍም ይመስል ነበር፥ በሕያዋኑም መካከል የሚነድድ ችቦ የሚመስል ወዲህና ወዲያ ይዘዋወር ነበር፥ እሳቱም ብርሃን ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር። ሕያዋኑም እንደ መብረቅ ብልጭታ ይሄዱና ይመለሱ ነበር። ሕያዋኑንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ ሕያዋን አጠገብ በምድር ላይ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ። የመንኰራኵሩም መልክና አሠራር የቢረሌ መልክ ይመስል ነበር፥ የአራቱም መልክ አንድ ዓይነት ነበር፥ መልካቸውና አሠራራቸው በመንኰራኵር መካከል ያለ መንኰራኵር ይመስል ነበር። ሲሄዱም በአራቱም ጎናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር። ጀርባቸውም ረዥምና የሚያስፈራ ነበር፥ የአራቱም ጀርባቸው ዙሪያው በዐይኖች ተሞልቶ ነበር። ሕያዋኑም ሲሄዱ መንኮራኩሮቹም በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር። እንስሶቹ ከምድር ሲነሱ መንኮራኩሮቹም ይነሱ ነበር። መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱም ይሄዳሉ፥ የሕያዋኑ መንፈስ በመንኮራኩሮቹ ውስጥ ስለ ነበረ መንኮራኩሮቹም በእነርሱ አጠገብ ይነሡ ነበር። የሕያዋኑ መንፈስ በመንኮራኩሮቹ ውስጥ ስለ ነበረ ሲሄዱ ይሄዳሉ፥ ሲቆሙ ይቆማሉ፥ ከምድር ሲነሡ መንኮራኩሮቹም በአጠገባቸው ይነሣሉ። ከሕያዋኑ ራስ በላይ የሚያስፈራ፥ ሰማይ የሚመስል፥ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ፥ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። ከሰማዩም በታች ክንፎቻቸው የአንዱ ወደ ሌላው ተዘርግተው ነበር፥ እያንዳንዱም ገላውን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፎች ነበሩት። ሲሄዱም የክንፎቻቸውን ድምፅ እንደ ብዙ ውኆች ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል አምላክ ድምፅ፥ እንደ ማዕበል ድምፅ፥ እንደ የታላቅ ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። ከራሳቸው በላይ ካለው ሰማይ በላይ ድምፅ መጣ፥ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ አደረጉ። ከራሳቸው በላይ ካለው ሰማይ በላይ ዙፋን የሚመስል ነበረ፥ እርሱም የሰንፔር ድንጋይ ይመስል ነበር፥ ዙፋን በሚመስለው፥ በላዩ ላይም ሰው የሚመስል ነበረ። ወገቡ ከሚመስለው ወደ ላይ የሚያንጸባርቅ ነገር የሚመስል፥ ቤቱም በእሳት የተከበበ የሚመስል አየሁ፥ ወገቡ ከሚመስለው ወደ ታች ደግሞ በዙሪያው ብርሃን ያለው እሳት የሚመስል አየሁ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንዳለ ቀስተ ደመና የሚመስል፥ በዙሪያው የከበበው ብርሃንም እንዲሁ ይመስል ነበር። ይህም የጌታ ክብር መልክ አምሳያ ነበር። ባየሁትም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገር ድምፅም ሰማሁ። እርሱም፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ ከአንተ ጋር እንድነጋገር በእግርህ ቁም” አለኝ። ሲያናግረኝም መንፈስ ገባብኝ፥ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ወደ እስራኤል ልጆች፥ ወደ ዓመፀኞች አገር፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁት እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በእኔ ላይ ዐመፁ። ፊታቸው የተኮሳተረና ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው፥ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፥ አንተም እንዲህ በላቸው፦ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤” እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ ያውቃሉ። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኩርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራ፥ ቃላቸውንም አትፍራ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቃላቸውን አትፍራ፥ ፊታቸውንም አትፍራው። እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙም ባይሰሙም ቃሌን ትነግራቸዋለህ። አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፥ አፍህን ክፈት፥ የምሰጥህንም ብላ። ተመለከትሁም፥ እነሆ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፥ እነሆ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት። በፊቴም ዘረጋው፥ በፊቱና በኋለውም ልቅሶ፥ ኃዘንና ዋይታም ተጽፎበት ነበር። እርሱም እንንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የቀረበልኽን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር። አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ንገራቸው። ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ ሕዝብ አልተላክህምና፥ ንግግራቸው ጥልቅ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም መስማት ወደማይቻልህ ታላላቅ ሕዝቦች አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ ይሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ቤት እኔን መስማት እንቢ ብለዋልና አንተንም አይሰሙህም፥ ምክንያቱም የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና። እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። ግምባርህን ከባልጩት እንደሚጠነክር አልማዝ አድርጌዋለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ያዝ፥ በጆሮህም ስማ። ተነሥተህም ወደ ተማረኩት፥ ወደ ሕዝብህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው። መንፈስም አነሣኝ፥ ከኋላዬም የጌታ ክብር ከሥፍራው ይባረክ የሚል ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ሰማሁ። ይህም የሕያዋኑ ክንፎች እርስ በእርሳቸው ሲማቱ የሚወጣው ድምፅ፥ በአጠገባቸውም የነበሩት የመንኰራኵሮች ድምፅ ነበር፥ እርሱም ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ነበር። መንፈስ አነሳኝ፥ ወሰደኝም፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቁጣ ሄድሁ፥ የጌታም እጅ በላዬ ላይ በርትታ ነበር። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ወደሚኖሩ፥ በቴልአቢብም ወዳሉ ምርኮኞች መጣሁ፥ በዚያ በሚኖሩበትም ሰባት ቀን በመካከላቸው በድንጋጤ ተቀመጥሁ። ከሰባቱም ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፥ የአፌን ቃል በሰማህ ጊዜ ታስጠነቅቅልኛለህ። እኔ ኃጢአተኛውን፦ ሞትን ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ ካላስጠነቀቅኸው፥ ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን አስጠንቅቀህ ካልነገርኸው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው፥ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ እርሱ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። ጻድቁ ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት ከሠራ፥ እኔም በፊቱ ዕንቅፋትን አደርጋለሁ፥ እርሱም ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል፥ የጽድቁም ሥራ አይታሰብለትም፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ጻድቁን ኃጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀው፥ ጻድቁም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ አንተም ነፍስህን አድነሃል። በዚያም የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተነሥ፥ ወደ ሜዳ ውጣ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ። እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳው ወጣሁ፥ እነሆ በዚያ በኮቦር ወንዝ ያየሁትን ክብር የሚመስል የጌታ ክብር ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ። መንፈስም ገባብኝ፥ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፦ ሂድ፥ በቤትህ ውስጥ ዘግተህ ተቀመጥ። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ ገመድ ያደርጉብሃል፥ ከእነሱም ጋር ያስሩሃል፥ ከመካከላቸውም አትወጣም፤ ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፥ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚገስጽ ሰው አትሆንባቸውም። ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለራስህ ጡብን ውሰድ፥ በፊትህም አኑራት፥ በላይዋ ላይም የኢየሩሳሌምን ሥዕል ሳልባት፤ ክበባት፥ ምሽግም ሥራባት፥ ቁልልም ሥራባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም ቅጥርን የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት። የብረት ምጣድም ውሰድ፥ በአንተና በከተማይቱ መካከል የብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርሷ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች፥ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል። አንተም በግራ ጐንህ ተኛ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፥ በምትተኛበትም ቀኖች ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ። እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀኖች ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ። እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ ድጋሚ በቀኝ ጐንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፥ አንድን ዓመት እንደ አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ። ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ፊትህን ታዞራለህ፥ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ትንቢትን ትናገርባታለህ። እነሆም ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ቀኖች እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጎንህ ወደ ሌላው ጎንህ አትገላበጥም። አንተም ለራስህ ስንዴና ገብስ፥ ባቄላና ምስር፥ ማሽላና አጃን ውሰድ፥ በአንድ ዕቃ ውስጥ አድርጋቸው፥ ለራስህም ምግብ አዘጋጅ፥ በጎንህ እንደ ምትተኛበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። የምትመገበውም ምግብ በሚዛን በየቀኑ ሃያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜውም ትበላለህ። ውኃም በልክ ትጠጣለህ፥ የኢን መስፈሪያ አንድ ስድስተኛ ትጠጣለህ፥ በየጊዜውም ትጠጣለህ። እንደ ገብስ እንጐቻ አድርገህም ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለህ። ጌታም እንዲህ አለ፦ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ርኩስ ምግባቸውን በምበትንባቸው አገሮች መካከል ይበላሉ። እኔም እንዲህ አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወይኔ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፥ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ፥ የሞተ ወይም እንስሳ የገደለውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተመልከት በሰው ፋንድያ ፈንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ፥ ምግብህንም በእርሱ አዘጋጅ። ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ እኔ በኢየሩሳሌም የምግብን በትር እሰብራለሁ፥ ምግብ እየፈሩ በሚዛን ይበላሉ፥ ውኃም እየደነገጡ በልክ ይጠጣሉ፤ ይህም ምግብና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲመነምኑ ነው። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለ ሰይፍ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ለራስህ ትወስደዋለህ፥ በራስህና በጢምህም አሳልፈው፥ ሚዛንንም ውሰድ ጠጉሩንም ትከፋፍለዋለህ። የመከበብም ወራት ሲፈጸም አንድ ሦስተኛውን በከተማይቱ መካከል በእሳት ታቃጥለዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወስደህ ዙሪያውን በሰይፍ ትመታዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወደ ነፋስ ትበትነዋለህ፥ እኔም ከኋላቸው ሰይፍ እመዝዛለሁ። ከዚህም ጥቂት ውሰድ፥ በመጐናጸፊያህም ቋጥራቸው። ከእነዚህም እንደገና ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላቸዋለህ፥ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፥ ከእርሱም እሳት ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ትወጣለች። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አገሮች በዙሪያዋ ሆነው፥ በመንግሥታት መካከል የተከልዃት ኢየሩሳሌም ይህች ናት። እርሷም ከሕዝቦች ይልቅ በትእዛዛቴ ላይ፥ በዙሪያዋ ካሉ አገሮችም ሁሉ ይልቅ በሕጌ ላይ በክፋቷ አምፃለች፥ እነርሱ ትእዛዛቴን አንቀበልም ብለዋልና፥ በሕጌም አልኖሩምና። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁካታችሁ በዙሪያችሁ ካሉት አገሮች ይልቅ ሆኗል፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አገሮችም እያዩ በመካከልሽ ፍርድን አመጣብሻለሁ። ስለ ርኩሰትሽ ሁሉ እስከ አሁን ያላደረግኹትን፥ ከዚህ በኋላም እርሱን የሚመስል የማላደርገውን ነገር በአንቺ ላይ አደርግብሻለሁ። ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፥ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፥ ፍርድንም አደርግብሻለሁ፥ ከአንቺም የተረፉትንም ሁሉ ወደ ሁሉም ነፋሳት እበትናለሁ። ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር በእድፍሽ ሁሉና በርኩሰትሽም ሁሉ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ እኔም አሳንስሻለሁ፥ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም። ከአንቺም አንድ ሦስተኛው በቸነፈር ይሞታሉ፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ፥ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። ንዴቴ ያልፋል፥ ቁጣዬም በእነርሱ ላይ እንዲያርፍ አደርጋለሁ፥ እጽናናለሁም፥ ቁጣዬን በእነርሱ ላይ በፈጸምሁ ጊዜ እኔ ጌታ በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ። በዙሪያሽም ባሉ አገሮች መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ። በአንቺ ላይ በንዴትና በቁጣ፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ፥ በዙሪያሽ ላሉ አገሮች መሰደቢያና መተረቻ፥ ማስጠንቀቂያና ድንጋጤ ትሆኛለሽ፥ እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ። የሚገድሉና የሚያጠፉ የራብ ፍላፃ በወረወርሁ ጊዜ፥ እንዳጠፋችሁ እወረውራቸዋለሁ፥ በእናንተ ላይ ረሃብን እጨምርባችኋለሁ፥ የምግባችሁንም በትር እሰብራለሁ። ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆችሽን ያሳጡሻል፥ ቸነፈርና ደምም በአንቺ በኩል ያልፋሉ፥ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ እንዲህም በል፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮች፥ ለኮረብቶች፥ ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ። መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሠበራሉ፥ የተገደሉ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቆረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል። የተገደሉትም በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ነገር ግን በአገሮች መካከል በተበተናችሁ ጊዜ የተወሰኑትን በአሕዛብ መካከል ከሰይፍ በሕይወት አስቀርላችኋለሁ። ያመለጡት ተማርከው በሄዱባቸው በአሕዛብ መካከል ሆነው ያስታውሱኛል፤ ምክንያቱም ከእኔ በራቀው አመንዝራ ልባቸውና፥ ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዐይኖቻቸው ተሰብሬአለሁና፥ በክፉ ስራቸውና በርኩሰታቸውም ሁሉ ራሳቸውን ይጸየፋሉ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ ይህን ክፉ ነገር እንደማመጣባቸው መናገሬ በከንቱ አይደለም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእጅህ አጨብጭብ፥ በእግርህም እየረገጥህ፥ ስለ የእስራኤል ቤት ክፉ የርኩሰት ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ! በል፤ በሰይፍ፥ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤ በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብ ያለውም በሰይፍ ይወድቃል፥ በሕይወት የተረፈውና የዳነውም በራብ ይሞታል፥ መዓቴን በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ። ሬሳዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ በረዣዥም ኮረብታ ሁሉ፥ በተራሮችም ራሶች ሁሉ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ ሥርና ቅጠሉም ከበዛ ባሉጥ ሁሉ ሥር ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ በወደቁ ጊዜ ያኔ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። እጄንም በእነሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዲብላ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ፍጻሜ! በአራቱም የምድሪቱ ማዕዘናት ላይ ፍጻሜ መጥቷል። አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ እሰድዳለሁ፥ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ሁሉ እመልስብሻለሁ። ዓይኔ አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽን በአንቺ ላይ እመልስብሻለሁ፥ ርኩሰቶችሽም በመካከልሽ ይሆናሉ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በክፋት ላይ ክፋት እነሆ፥ ይመጣል። ፍጻሜ መጥቷል፥ ፍጻሜ መጥቷል፥ በአንቺ ላይ ነቅቷል፥ እነሆ፥ መጥቷል። በምድር የምትኖር ሆይ፥ ፍጻሜህ ወደ አንተ መጥቷል፥ ጊዜው መጥቷል፥ ቀኑ ቀርቧል፥ የሽብር ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም። አሁን በቅርብ መዓቴን በአንቺ ላይ አፈስሳለሁ፥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ እፈጽማለሁ፥ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ሁሉ እመልስብሻለሁ። ዓይኔም አይራራም፥ እኔም አላዝንም፥ መንገድሽን በአንቺ ላይ እመልስብሻለሁ፥ ርኩሰቶችሽም በመካከልሽ ይሆናሉ፥ የምቀሥፍም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። እነሆ ቀኑ፥ እነሆ መጥቷል፥ ፍጻሜህ መጥቷል፥ ብትሩ አብቧል፥ ትዕቢትም አቆጥቁጦአል ። ሁከት ወደ ክፋት ብትርነት አደገ፥ ከእነርሱ፥ ከብዛታቸው፥ ከሀብታቸውም አንድም አይቀርም፥ ከመካከላቸው የሚልቅም የለም። ጊዜው መጥቷል፥ ቀኑ ቀርቧል፥ የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ፥ ቁጣ ብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና። በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጭ ወደሸጠው ነገር አይመለስ፥ ስለ ብዙዎቹ የተነገረው ራእይ አይመለስምና፥ ማንም ሰው በኃጢአቱ ሕይወቱን ማዳን አይችልም። መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም ነገር አዘጋጅተዋል፥ ነገር ግን ወደ ጦርነት የሚሄድ የለም፥ ቁጣዬ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና። ሰይፍ በውጭ፥ ቸነፈርና ራብም ከቤት አለ፥ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይበላዋል ። ከእነርሱም የሚሸሹ ያመልጣሉ፥ እንደ ሸለቆ እርግቦች በተራራ ላይ ይሆናሉ፥ ሁሉም በኃጢአታቸው ላይ ያቃስታሉ። እጆች ሁሉ ይዝላሉ፥ ጉልበቶችም ሁሉ እንደ ውኃ ይፈስሳሉ። ማቅ ይለብሳሉ፥ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፥ በሁሉም ፊቶች ላይ እፍረት ይሆናል፥ ራሳቸውም ሁሉ መላጣ ይሆናል። ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፥ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቆጠራል፥ በጌታ የመዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም። አይጠግቡም፥ ሆዳቸውንም አይሞሉም፥ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና። የጌጦቻቸውን ውበት ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኩሰታቸውን ምስሎችና አስከፊ ነገሮችን ሰሩባቸው፥ ስለዚህ እኔም ይህንን ለእነርሱ ርኩስ ነገር አደርገዋለሁ። በባዕድም እጅ ለዝርፊያ፥ በምድር ላሉ ክፉዎች እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እነርሱም ያረክሱአታል። ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፥ እነርሱም የተከበረ ቦታዬን ያረክሳሉ፥ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአታልም። ምድር በደም ፍርድ ተሞልታለች፥ ከተማም በዓመፅ ተሞልታለችና፥ ሰንሰለት ሥራ። ከአገሮች ሁሉ ክፉዎችን አመጣለሁ፥ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፥ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። ጭንቀት መጥቷል፥ ሰላምም ይሻሉ፥ አይገኝምም። በጥፋት ላይ ጥፋት ይመጣል፥ ወሬም ወሬን ይከተላል፥ ከነቢይ ራእይን ይፈልጋሉ፥ ከካህን ሕግ፥ ከሽማግሌዎችም ምክር ይጠፋል። ንጉሡ ያለቅሳል፥ ልዑሉም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድሪቱም ሕዝቦች እጆች ይንቀጠቀጣሉ፥ እንደ መንገዳቸው መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በስድስተኛውም ዓመት፥ በስድስተኛው ወር፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያም የጌታ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ወደቀች። እኔም አየሁ፥ እነሆም ሰውን የሚመስል ነበረ፥ ወገቡ ከሚመስለው በታች እሳት፥ ከወገቡም በላይ እንደ ብርሃን የሚመስል፥ የሚያንጸባርቅ ነገር የሚመስል ነበረ። እጅ የሚመስል ዘረጋና በራስ ጠጉሬ ወሰደኝ፥ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም ራእዮች ወደ ኢየሩሳሌም፥ ቅናትን የሚያነሣሣ የቅናት ጣዖት ወደሚገኝበት፥ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው፥ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ አመጣኝ። እነሆ በዚያ በሜዳው እንዳየሁት ራእይ የሚመስል የእስራኤል አምላክ ክብር ነበረ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዐይኖችህን ወደ ሰሜን መንገድ አንሣ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ፥ እነሆም በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል፥ በመግቢያው የቅናቱ ጣዖት ነበረ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ ከመቅደሴ ሊያርቁኝ፥ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚፈጽሙትን ታላቅ ርኩሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኩሰት ታያለህ። ወደ አደባባዩ መግቢያም አመጣኝ፥ አየሁም፥ እነሆ በግንቡ ላይ ቀዳዳ ነበረ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ ግንቡን ቦርቡረው አለኝ፥ ግንቡንም በቦረቦርሁት ጊዜ እነሆ አንድ መግቢያ አገኘሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ግባ፥ በዚህ የሚያደርጉትንም ክፉውን ርኩሰት ተመልከት። እኔም ገባሁና አየሁ፥ እነሆ የሁሉም ዓይነት የሚሳቡ ነገሮች፥ የርኩሳን እንስሶች ምስሎችና የእስራኤል ቤት ጣዖታት ሁሉ በግንቡ ዙሪያ ተስለው ነበር። ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎች ቆመው ነበር፥ የሻፋን ልጅ ያአዛንያ በመካከላቸው ቆሞ ነበር፥ እያንዳንዱም በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ መልካም መዓዛ ያለው የዕጣኑም ጢስ ወደ ላይ ይወጣ ነበር። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዱ በስዕሉ ቤት በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱም፦ “ጌታ አያየንም፥ ጌታ ምድሪቱን ትቶአታል፥ ብለዋልና።” ደግሞም “ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኩሰት ሲያደርጉ ታያለህ” አለኝ። ወደ ሰሜንም ወደሚመለከተው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ እነሆ፥ ሴቶች ለታሙዝ እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር። እርሱም፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ርኩሰት ታያለህ” አለኝ። ወደ ጌታ ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆ በጌታ መቅደስ መግቢያ፥ በመተላለፊያውና በመሠዊያው መካከል ሃያ አምስት ያህል ሰዎች ነበሩ፥ ጀርባቸው ወደ ጌታ መቅደስ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፥ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ ይህን አይተሃልን? በዚህ የሰሩትን ርኩሰት ሊያደርጉ ለይሁዳ ቤት ይህ ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱን በዓመፅ ሞልተዋታል፥ ሊያስቆጡኝም ተመልሰዋል፥ እነሆ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫቸው አቅርበዋል። ስለዚህ እኔ ደግሞ በቁጣ እሠራለሁ፥ ዓይኔ አይራራም፥ አላዝንምም፥ ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹም አልሰማቸውም።” በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ እያንዳንዳቸው በእጃቸው የጦር ይያዙ፤ ከተማይቱን የሚቀጡ በዚህ ይምጡ። እነሆ ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፥ እያንዳንዱም አጥፊውን መሣሪያ በእጁ ይዞ ነበር፥ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ፥ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። የእስራኤልም አምላክ ክብር በላዩ ላይ አርፎ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መግቢያ ሄዶ ነበር፥ በፍታ የለበሰውን በወገቡም የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘውን ሰው ጠራ። ጌታም እንዲህ አለው፦ በከተማይቱ መካከል፥ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኩሰት ሁሉ በሚተክዙና በሚያለቅሱ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክትን አድርግ። እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፦ እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፥ ዓይናችሁ አይራራ፥ አትዘኑም፤ ሽማግሌ፥ ወጣት ፥ ድንግል ፥ ሕፃናትንና ሴቶችን ግደሉ፥ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፥ በመቅደሴም ጀምሩ። በቤቱ ፊት ለፊት ከነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ ቤቱን አርክሱ፥ አደባባዮቹንም በተገደሉት ሰዎች ሙሉ፥ ውጡ፤ እነርሱም ወጡ በከተማይቱም ውስጥ ገደሉ። እነርሱ ሲገድሉ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ ጮኽሁ፥ እንዲህም አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ትሩፍ ሁሉ ታጠፋለህን? እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ኃጢአት እጅግ በዝቶአል፥ ምድሪቱ በደም ተሞልታለች፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፥ ጌታ ምድሪቱን ትቶአታል፥ ጌታ አያይም ብለዋልና። እኔም ደግሞ ዓይኔ አይራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ። እነሆም በፍታ የለበሰው፥ የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው፦ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ። እኔም አየሁ፥ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ፥ ዙፋን የሚመስል ነገር ታየ። በፍታም የለበሰውን ሰው እንዲህ አለው፦ በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ። ሰውዬው ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላው። የጌታ ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መግቢያ ላይ ቆመ፥ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በጌታ የክብር ብርሃን ተሞላ። ሁሉን የሚችል አምላክ ሲናገር እንደሚያሰማው ዓይነት ድምፅ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ ተሰማ። በፍታ የለበሰውን ሰው ሲያዘው፦ ከኪሩቤል መካከል ከመንኰራኵሮች መካከል እሳት ውሰድ አለው፥ እርሱም ገብቶ በአንድ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ። ከኪሩቤል መካከል አንድ ኪሩብ እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታ በለበሰው ሰው እጅም አኖረው፥ እርሱም ይዞ ወጣ። ኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅ የሚመስል ታየ። እኔም አየሁ፥ እነሆ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ የቢረሌ ድንጋይ ይመስል ነበር። የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበር። ሲሄዱም በአራቱም ጎናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር፥ ራስ ወደዞረበት ስፍራ ወደዚያ ይከተሉ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር። መላ አካላቸው ሁሉ፥ ጀርባቸው፥ እጃቸው፥ ክንፋቸው፥ መንኰራኵሮቹም፥ የአራቱም መንኰራኵሮች፥ ዙሪያቸው በሙሉ በዐይኖች ተሞልተው ነበር። መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ “የሚሽከረከሩ መንኰራኵሮች” ተብለው ተጠሩ። እያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፥ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛው ፊት የሰው ፊት፥ ሦስተኛው ፊት የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም ፊት የንስር ፊት ነበረ። ኪሩቤልም ተነሡ፥ እነዚህ በኮቦር ወንዝ ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው። ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፥ ኪሩቤል ከምድር ለመነሣት ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮቹም ከአጠገባቸው አይለዩም ነበር። የሕያዋኑ መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ስለ ነበረ እነዚህ ሲቆሙ እነዚያም ይቆሙ ነበር፥ እነዚህ ሲነሱ እነዚያም ከእነርሱ ጋር ይነሱ ነበር። የጌታ ክብር ከቤቱ መግቢያ ወጥቶ ከኪሩቤል በላይ ቆመ። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ እኔም እያየሁ ከምድር ተነሡ፥ ሲወጡም መንኰራኵሮች በአጠገባቸው ነበሩ፥ በጌታ ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤል አምላክ ክብርም በላያቸው ላይ ነበረ። እነዚህ በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው፥ እኔም ኪሩቤል እንደ ነበሩ አስተዋልሁ። እያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ እያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ ከክንፎቻቸው ሥርም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ነበረ። ፊቶቻቸውም በኮበር ወንዝ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፥ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፥ እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር። መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው ወደ ጌታ ቤት ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያአዛንያንንና የበናያ ልጅ ፈላጥያንን አየሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ክፉ ምክርን የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። እነርሱም፦ ቤቶች የሚሰሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት ናት፥ እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፥ የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር። የጌታም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ፦ ጌታ እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔ የልባችሁን ሐሳብ አውቃለሁና። በዚህች ከተማ ውስጥ የገደላችኋቸውን አብዝታችኋል፥ ጎዳናዎችዋንም በተገደሉት ሞልታችኋል። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ያኖራችኋቸው የተገደሉት እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ድስቱ ይህች ከተማ ናት፥ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። ሰይፍን ፈርታችኋል፥ እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ፥ በባዕዳንም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ላይ ፍርድ አመጣባችኋለሁ። በሰይፍ ትወድቃላችሁ፥ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፥ እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ሕጌንም አልፈጸማችሁምና፥ ነገር ግን በዙሪያችሁ እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል። ትንቢት እየተናገርሁ ሳለሁ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፥ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ እንዲህም አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ወዮ! የእስራኤልን ትሩፍ ፈጽመህ ታጠፋለህን? የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ወንድሞችህ፥ ዘመዶችህ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ፥ “ከጌታ ራቁ፥ ምድሪቱ ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች” ብለዋል። ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል አርቄ ብወስዳቸውም፥ በአገሮች መካከል ብበትናቸውም፥ በሄዱባቸው አገሮች በዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ። ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፥ ከተበተናችሁባቸው አገሮችም እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር ለእናንተ እሰጣችኋለሁ። ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉን ነገር ሁሉና ርኩሱን ነገር ሁሉ ከእርሷ ያወጣሉ። አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ አዲስ መንፈስም በውስጣቸው አኖራለሁ፥ ከሥጋቸውም የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ ይህም በትእዛዜ እንዲሄዱ፥ ፍርዴንም እንዲጠብቁና እንዲፈጽሙ ነው፤ ስለዚህ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። ልባቸው ወደ ጸያፍና ርኩስ ነገራቸው የሚከተል ግን መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። የጌታም ክብር ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ በምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ። መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ተለየ። ጌታ ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞቹ ተናገርሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፥ እንዲያዩ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፥ እንዲሰሙም ጆሮ አላቸው ነገር ግን አይሰሙም፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ ጓዝ ለራስህ አዘጋጅ፥ እያዩህም በቀን ወደ ምርኮ ሂድ፥ በፊታቸውም እንደ ምርኮኛ ከስፍራህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ፥ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ እያዩህ በቀን አውጣው፥ በማታም እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። እያዩህም ግንቡን ቦርቡረው፥ በእርሱም አውጣው ። ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና እያዩህ በትከሻህ ላይ ተሸከመው፥ በጨለማም ይዘኸው ውጣ፥ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን። እኔም እንደታዘዝኩት አደረግሁ፥ በቀንም ጓዙን እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፥ በምሽትም ጊዜ ግንቡን በእጄ ቦረቦርሁት፥ እያዩኝም በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ በጨለማ አወጣሁት። በማግስቱም የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት፥ ዓመፀኛ ቤት፦ ምን እያደረግህ ነው? አላሉህምን? እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በውስጧ ለሚኖሩ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው። እንዲህም በላቸው፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፥ እኔ እንዳደረግሁት እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም ወደ ስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ። በመካከላቸውም ያለው ልዑል በትከሻው ላይ ተሸክሞ በጨለማ ይወጣል፥ በዚያም ሊወጡ ግንቡን ይቦረቡራሉ፥ በዓይኑም ምድሪቱን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፥ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል። በዙሪያው ያሉ ረዳቶቹና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፥ ከኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። በአሕዛብ መካከል ስበትናቸው፥ በአገሮችም ስዘራቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በሚሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ርኩሰታቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ከእነርሱ ጥቂቶች ከሰይፍ፥ ከራብና ከቸነፈር አስቀራለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፥ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በስጋት ጠጣ፤ ለምድሪቱም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤልም ምድር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፦ በሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ስለምትጠፋ ምግባቸውን በስጋት ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፥ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ “ቀኖቹ ረዝመዋል፥ ራእይም ሁሉ ጠፍቶአል” የምትሉት ይህ ምሳሌ ምንድነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቧል በላቸው። ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። ነገር ግን እኔ ጌታ የምናገረውን ቃል እናገራለሁ፥ ይፈጸማልም፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የእስራኤል ቤት እንዲህ ይላሉ፦ የሚያየው ራእይ ለብዙ ዘመን ነው፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል። ስለዚህም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን እንዲህ በላቸው፦ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምንም ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን የሚከተሉ ሞኞች ነቢያት ወዮላቸው! እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው። በጌታ ቀን ጦርነቱን መቋቋም እንዲችል ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ ወይም ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልጠገናችሁም። ጌታ ሳይልካቸው፦ ጌታ ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ሟርትን አይተዋል፥ ሆኖም ቃላቸው እንዲፈጸም ይጠብቃሉ። እኔ ሳልናገር፦ ጌታ እንዲህ ብሏል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን አላያችሁምን፥ ውሸተኛንም ምዋርት አልተናገራችሁምን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ፥ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ እነሆ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እጄ ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፥ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ምክንያቱም ሰላም ሳይኖር ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፥ አንድ ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ በኖራ ይቀቡታል፤ በኖራ የሚቀቡትን እንዲህ በላቸው፦ ይወድቃል፤ ዶፍ ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋዮች ይወድቃሉ፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል። እነሆ ግንቡ በሚፈርስበት ጊዜ፦ የቀባችሁት ኖራ የት አለ? አይሉአችሁምን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ በቁጣዬም ዶፍ ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ሊያጠፋው ይወርዳል። ኖራ የቀባችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ፥ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይወድቃል፥ እናንተም በውስጧ ትጠፋላችሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ቁጣዬንም በግንቡ ላይና ኖራ በቀቡት ላይ እፈጽማለሁ፥ ቅጥሩና ቅጥሩን የቀቡት የሉም እላችኋለሁ። እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩ፥ ሰላም ሳይኖር የሰላምን ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ከልባቸው ትንቢት ወደሚናገሩት ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን? እፍኝ ገብስና ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት ብላችሁ፥ ውሸት ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ፥ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት በመግደል፥ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት በማትረፍ በሕዝቤ ፊት አርክሳችሁኛል። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ። መሸፈኛዎቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚህ ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ምክንያቱም እኔ ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ ከክፉ መንገዱ ተመልሶ በሕይወትም እንዳይኖር የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና፤ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ከንቱ ራእይን አታዩም፥ ምዋርትም አታሟርቱም፥ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አንዳንዶች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፥ ታዲያ እንዲጠይቁኝ ልፍቀድላቸው? ስለዚህ ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማንም ሰው ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ወደ ነቢዩም የሚመጣ፥ እኔ ጌታ እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። ይህም የእስራኤልን ቤት ለመያዝ ነው፤ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ምክንያት በልባቸው ከእኔ ተለይተዋልና፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመለሱ፥ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ፊታችሁን መልሱ። ማንም ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም የሚቀመጥ መጻተኛ፥ ራሱን ከእኔ የሚለይ፥ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ስለ እኔም ለመጠየቅ ወደ ነቢዩ የሚመጣ፥ እኔ ጌታ ራሴ እመልስለታለሁ፥ ፊቴን በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ፥ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ነቢዩ ቢታለል፥ ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ ጌታ ነኝ፥ በእርሱም ላይ እጄን እዘረጋለሁ፥ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ። በደላቸውን ይሸከማሉ፥ እንደ ጠያቂው በደል የነቢዩም በደል እንዲሁ ይሆናል። ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግመው ከእኔ ርቀው እንዳይጠፉ፥ በመተላለፋቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፥ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር ባለመታመን በእኔ ላይ ኃጢአት ብትሠራ፥ እጄን እዘረጋባታለሁ፥ የምግቧንም በትር እሰብራለሁ፥ ራብን እሰድድባታለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከእርሷ አጠፋለሁ፤ ኖኅ ዳንኤልና ኢዮብ እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ በውስጧ ቢኖሩ እንኳ በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ክፉ አውሬ በምድሪቱ እንዲያልፍ ባደርግ፥ ልጅ አልባ ቢያደርጋት፥ በአውሬው ምክንያት ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥ እነዚህ ሦስት ሰዎች በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች። ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ፦ በምድሪቱ ላይ ሰይፍ ይለፍ ብል፥ ሰውንና እንስሳን ከእርሷ ባጠፋ፥ እነዚህ ሦስት ሰዎች በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም። ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ ቁጣዬን በደም ባፈስስባትና ሰውንና እንስሳንም ከእርሷ ባጠፋ፥ ኖኅ፥ ዳንኤልና ኢዮብ በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን ሰይፍ፥ ራብ፥ ክፉ አውሬና ቸነፈር፥ ሰውንና እንስሳን ከእርሷ ለማጥፋት ብሰድድም፥ ነገር ግን እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን የሚያወጡ ይቀሩላታል፥ እነሆ ወደ እናንተ ይመጣሉ፥ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፥ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር፥ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፥ ያደረግሁትም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዱር ዛፎች መካከል ያለው የወይን ቅርንጫፍ፥ ከሁሉም ዛፎች ይልቅ የወይን ግንድ የሚበልጠው እንዴት ነው? ማንኛውም ሥራ ለመስራት እንጨት ከእርሱ ይወስዳል? ወይስ ሰዎች ዕቃ የሚንጠለጠልበትን ኩላብ ከእርሱ ይወስዳሉን? እነሆ ለመቃጠል ለእሳት ተስጥቷል፥ እሳቱም ሁለቱን ጫፎቹን በልቶታል፥ መካከሉም ተቃጥሏል፥ ለሥራ ይጠቅማልን? እነሆ ደህና ሳለ ለሥራ ካልጠቀመ፥ ይልቁንስ እሳት ከበላውና ከተቃጠለ በኋላ ሥራ ይሠራበታልን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን ግንድ እሳት እንዲበላው እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ እሰጣለሁ። ፊቴን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፥ ከእሳት ቢያመልጡም፥ እሳት ግን ይበላቸዋል፥ ፊቴን በእነርሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። እምነተ ቢስ ሆነዋልና ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኩሰትዋን አስታውቃት፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፦ መሠረትሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፥ አባትሽ አሞራዊ ነበረ፥ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። ስትወለጂ፥ በተወለድሽበት በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቆረጠም ነበር፥ ንጹሕም እንድትሆኚ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨው አልታሸሽም፥ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። አዝኖልሽ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ሊያደርግልሽ አንድም ዐይን አልራራልሽም፥ ነገር ግን በተወለድሽበት ቀን ሰውነትሽ የተጠላ ስለ ነበር በሜዳ ላይ ተጣልሽ። በአንቺም በኩል አለፍሁ፥ በደምሽም ውስጥ ስትንፈራገጪ አየሁሽ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፥ አዎን በደምሽ ውስጥ እያለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። በሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በጌጦች አጌጥሽ፥ ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፥ ጠጉርሽም አደገ፥ ሆኖም ዕርቃንሽንና ራቁትሽን ነበርሽ። በአንቺ በኩል አለፍሁ፥ አየሁሽም፥ እነሆ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበር፥ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ላይ ዘረጋሁና ዕርቃንሽን ሸፈንሁ፥ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም የእኔ ሆንሽ። በውኃ አጠብሁሽ፥ ደምሽን ከላይሽ ላይ አጠራሁ፥ በዘይትም ቀባሁሽ። ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ፥ ከጥሩ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፥ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ፥ ውድ መደረቢያም ደረብሁልሽ። በጌጥ አስጌጥሁሽ፥ በእጅሽ ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ሐብል አደረግሁልሽ። በአፍንጫሽ ቀለበት፥ በጆሮሽ ጉትቻ፥ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁ። በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታ፥ ሐርና ወርቀዘቦ ነበር፥ የላመ ዱቄት፥ ማርና ዘይትም በላሽ፥ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ፥ ለንግሥትነትም በቃሽ። በአንቺ ላይ ካኖርኋት ከውበቴ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ስምሽ በሕዝቦች መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን በውበትሽ ተመክተሻል፥ በስምሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከአላፊ አግዳሚው ሁሉ ጋር አበዛሽ። ከልብሶችሽ ጥቂቱን ወስደሽ የመስገጃ ስፍራዎችሽ ላይ በዝንጉርጉር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፥ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም። የሰጠሁሽን ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የሚያምር ጌጣጌጥ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ ሠራሽ፥ ከእነርሱም ጋር አመነዘርሽ። ወርቀዘቦ ልብሶችሽንም ወስደሽ አለበስሻቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አስቀመጥሽ። የሰጠሁሽን ምግቤን፥ እንድትበይው የሰጠሁሽን ምርጥ ዱቄት፥ ዘይትና ማር ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አስቀመጥሽ፥ እንዲህም ተደርጓል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ለእኔ የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወስደሽ ለእነርሱ መብል እንዲሆኑ ሠዋሻቸው። አመንዝራነትሽ አንሶ ነውን? ልጆቼን አረድሽ፥ በእነርሱም በኩል ስታልፊ ለእነርሱ ሰጠሻቸው፤ በርኩሰቶችሽ ሁሉና በአመንዝራነትሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቁተሽም በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የልጅነትሽን ጊዜ አላስታወስሺም። ከዚህ ሁሉ ክፋትሽ በኋላ ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለራስሽ ጉብታን ሠራሽ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ አዘጋጀሽ። በየመንገዱ ራስ ሁሉ ላይ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለአላፊ አግዳሚው ሁሉ እግርሽን ከፈትሽ፥ አመንዝራነትሽንም አበዛሽ። በሥጋ ከደለቡ ግብጻውያን ጐረቤቶችሽ ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ለማስቆጣት አመንዝራነትሽን አበዛሽ። እነሆ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ፥ ድርሻሽንም ቀንሻለሁ፥ ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ፥ ለጠላቶችሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። አልረካሽምና ከአሦራውያን ልጆች ጋር አመነዘርሽ፥ ከእነርሱም ጋር አመነዘርሽ አሁንም አልረካሽም። በከነዓን ምድር ከከላውዴዎን ጋር አመንዝራነትሽን አበዛሽ። በዚህም አልረካሽም። የማታፍር አመንዝራ ሴት ሥራ፥ እነዚህን ሁሉ ስትሠሪ ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም። በባሏ ፋንታ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ሴት ሆነሻል። ለአመንዝራዎች ሁሉ ሥጦታ ይሰጡአቸዋል፥ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ሥጦታሽን ትሰጫለሽ፥ ለአመንዝራነትሽ ከየአቅጣጫው ወደ አንቺ እንዲገቡ ጉቦ ትሰጫቸዋለሽ። አመንዝራነትሽ ከሌሎች ሴቶች የተለየ ነው፥ ማንም ለዝሙት የሚከተልሽ የለም፤ ማንም ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ ትሰጫለሽ፤ የተለየሽም ሆንሽ። ስለዚህ አመንዝራ ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሚ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍትወትሽ ስለ ፈሰሰ፥ ከወዳጆችሽ ጋር ባደረግሽው ዝሙት ዕርቃንሽ ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኩሰትሽም ጣዖታት ሁሉና ለእነርሱ ስለ ሰጠሻቸው ልጆች ደም፥ ስለዚህ እነሆ እኔ ደስ የተሰኘሽባቸውን ወዳጆችሽን ሁሉ፥ የወደድሻቸውን ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ ሁሉንም ከየአቅጣጫው በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፥ ራቁትነትሽን ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ዕርቃንሽን እገልጣለሁ። በአመንዝሮችና በደም አፍሳሽ ሴቶች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደም አመጣብሻለሁ። በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ ጉብታሽን ያፈርሳሉ፥ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብሶችሽንም ይገፉሻል፥ የሚያምሩ ጌጣጌጦችሽን ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽንና ዕራቁትሽን ይተዉሻል። የሚረብሽ ሕዝብ በአንቺ ላይ ያመጡብሻል፥ በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይቆራርጡሻል። ቤቶችሽን በእሳት ያቃጥላሉ፥ በብዙ ሴቶችም ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፥ አመንዝራነትሽን አስተውሻለሁ፥ ከእንግዲህም በኋላ ዋጋ አትሰጪም። በአንቺ ላይ ያለውን መዓቴን አቆማለሁ፥ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ፥ ከእንግዲህም አልቆጣም። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አስቆጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላስታወስሺም፤ ስለዚህ እነሆ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በርኩሰቶችሽ ሁሉ ላይ ሌላ ነውር አትጨምሪም። እነሆ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፦ “ሴት ልጇ እንደ እናቷ ናት” እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። አንቺ ባሏንና ልጆችዋን የጠላች የእናትሽ ልጅ ነሽ፥ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፥ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። ታላቅ እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር ከአንቺ በስተ ሰሜን የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፥ ታናሽ እኅትሽም ከሴቶች ልጆችዋ ጋር ከአንቺ በስተ ደቡብ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። አንቺ በእነርሱ መንገድ መሄድሽና ርኩሰታቸውንም መከተልሽ ብቻ ሳይሆን፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የበለጠ ምግባረ ብልሹ ነበርሽ። እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም። እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም በደል ይህ ነበር፤ በእርሷና በሴቶች ልጆቿ ትዕቢት፥ የምግብ ጥጋብ፥ የበለጸገ ምቾት ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። ትዕቢተኞች ነበሩ፥ በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፥ ስለዚህ ባየሁት ጊዜ አስወገድኋቸው። ሰማርያ የኃጢአትሽን ግማሽ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእነርሱ ይልቅ ርኩሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኩሰት ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው። አንቺም ደግሞ ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፥ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፥ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ። ምርኮአቸውን እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ በመካከላቸው ያለውን የአንቺንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለእነርሱ መጽናናት ስለሆንሻቸው እፍረትን እንድትሸከሚና በሠራሽውም ሁሉ እንድታፍሪ ነው። እኅቶችሽ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን? ክፋትሽ ሳይገለጥ በፊት፤ አሁን ለአራም ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ላሉት ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርሷ መሰደቢያ ሆነሻል። ክፋትሽንና ርኩሰነትሽን መሸከም አለብሽ፥ ይላል ጌታ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን ንቀሻልና፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። ነገር ግን በልጅነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር የመሠረትኩትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፥ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አቆማለሁ። የአንቺ ታላቅና የአንቺ ታናሽ እኅቶችሽን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪያለሽም፥ ሴቶች ልጆች እንዲሆኑሽም ለአንቺ እሰጣቸዋለሁ፥ ከቃል ኪዳንሽ የተነሣ ግን አይደለም። ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አቆማለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቂያለሽ፤ ያደረግሽውን ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ እንድታስቢውና እንድታፍሪ፥ ከውርደትሽም የተነሣ ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እንቆቅልሽ ጠይቅ፥ ለእስራኤልም ቤት ምሳሌን መስል፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትልቅ ክንፎች፥ ረጅም ማርገብገቢያ ያለው፥ ዝንጉርጉርና ብዙ ላባ ያለው ትልቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። ቀንበጡንም ቀነፈ፥ ወደ ከነዓንም ምድር አመጣው፥ በነጋዴዎችም ከተማ ተከለው። ከምድሪቱም ዘር ወሰደ፥ በመልካም መሬትም አኖረው፥ በብዙ ውኃ አጠገብም እንደ አኻያ ዛፍ ተከለው። በበቀለም ጊዜ ቁመቱ አጭር፥ ሐረጉ ወደ እርሱ የሚመለስ፥ ሥሮቹም በበታቹ የነበሩት ሰፊ ወይን ሆነ፥ ወይንም ሆነ፥ ቅርንጫፎችን አበቀለ፥ ቅጠልም አወጣ። ትልልቅ ክንፎችና ብዙ ላባ ያለው ሌላ አንድ ትልቅ ንስር ነበረ፥ እነሆም ይህ ወይን እንዲያጠጣው ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ፥ ቅርንጫፉንም ከተተከለበት ከመደብ ወደ እርሱ ሰደደ። ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፥ ፍሬ እንዲያፈራ፥ የተዋበ ወይን እንዲሆን ብዙም ውኃ ባለበት በመልካም መሬት ውስጥ ተተክሎ ነበር። እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያድግ ይሆንን? እንዲደርቅ፥ አዲስ የበቀለው ቅጠሉም እንዲጠወልግ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አያረግፈውምን? ከሥሩም ለመንቀል ብርቱ ክንድ ወይም ብዙ ሕዝብ አያስፈልገውም። እነሆ ሲተከልስ ያድግ ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ በመታው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለዓመፀኛ ቤት እንዲህ በል፦ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ አታውቁምን? በላቸው። ንገራቸው፦ እነሆ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና ልዑሎችዋን ወሰደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ባቢሎን አመጣቸው። ከንጉሣውያን ቤተሰብ አንዱን ዘር ወስዶ ከእርሱ ቃል ኪዳን ጋር አደረገ፥ አማለውም፥ የምድሪቱንም አለቆች ወሰደ፤ ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ ይህች መንግሥት እንድትዋረድና እራስዋን ከፍ እንዳታደርግ ነው። ነገር ግን በእርሱ ላይ ዐመጸ፥ ፈረሶችንና ብዙ ሕዝብም እንዲሰጡት መልእክተኞቹን ወደ ግብጽ ላከ። ይሳካለታልን? እነዚህን ነገሮች ያደረገስ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንን አፍርሶስ ያመልጣልን? እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ መሐላውን የናቀበት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውን ቃል ኪዳኑን ያፈረሰበት፥ ያነገሠው ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል። ብዙ ነፍሳትን ለማስወገድ ጉብታ በደለደሉ፥ ቅጥርንም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከኃያል ሠራዊቱና ከታላቅ ጉባኤው ጋር በጦርነት አይረዳውም። መሐላውን ስለ ናቀ፥ ቃል ኪዳኑንም ስላፈረሰ፥ እነሆም እጁን ሰጠ፥ እነዚህንም ሁሉ አደረገ፥ ስለዚህ አያመልጥም። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ፥ በዚያም በእኔ ላይ ለፈጸመው ክሕደት ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። የሚያመልጡ ወታደሮቹ ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፥ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ራሴ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አስቀምጠዋለሁ፥ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፥ በረጅምና ከፍ ያለ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል፥ ፍሬም ያፈራል፥ የተዋበ ዝግባ ይሆናል፥ በበታቹም ወፎች ሁሉ ይኖራሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርሩ ሁሉ ይቀመጣሉ። የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርጋለሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ አባቶች ጎምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች አጠረሰ፥ ብላችሁ ስለ እስራኤል ምድር የምትመስሉት ምሳሌ ምንድነው? እኔ ሕያው ነኝ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እንግዲህ ወዲህ ይህ ምሳሌ በእስራኤል ውስጥ በእናንተ አይመሰልም። እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፥ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች የልጅም ነፍስ የእኔ ናት፥ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች። ሰው ጻድቅ ቢሆን፥ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ በተራሮች ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹን ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውን ሚስት ባያረክስ፥ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፥ ማንንም ሰው ባያስጨንቅ፥ ነገር ግን ለባለ ዕዳው መያዣውን ቢመልስ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ በአራጣ ባያበድር፥ ትርፍ ባይወስድ፥ እጁንም ከበደል ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነተኛ ፍትሕ ቢያደርግ፥ በትእዛዜ ቢሄድ፥ እውነትን ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ፥ ከእነዚህም አንዱን የሚያደርግ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም እነዚህን ሁሉ ባይሠራ፥ በተራራም ላይ ቢበላ፥ የባልንጀራውን ሚስት ቢያረክስ፥ ድሀውንና ችግረኛውን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማ፥ መያዣውን ባይመልስ፥ ዐይኖቹን ወደ ጣዖታት ቢያነሣ፥ ርኩሰትን ቢያደርግ፥ በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፍንም ቢወስድ፥ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ እነዚህን ርኩሰቶች ሁሉ አድርጎአልና በእርግጥ ይሞታል፤ ደሙም በላዩ ላይ ይሆናል። እነሆም ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት ቢያይ፥ ቢፈራ፥ እነዚህንም ባይሠራ፥ በተራራ ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ ሰውን ባያስጨንቅ፥ መያዣውን ባይወስድ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ ድሀ ከመበደል እጁን ቢመልስ፥ አራጣ ወይም ትርፍ ባይወስድ፥ ፍርዴን ቢያደርግ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም። አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል። እናንተ ግን፦ የአባትን ኃጢአት ልጁ ለምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅና ቢያደርገው በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች፥ ልጅ የአባትን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጅን ኃጢአት አይሸከምም፥ የጻድቅ ሰው ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የክፉ ሰው ክፋትም በራሱ ላይ ይሆናል። ክፉ ሰው ከሠራው ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የሠራው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፥ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። በውኑ በኃጢአተኛው ሞት እደሰታለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ከመንገዱስ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለምን? ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ ክፉ ሰው እንደሚያደርገው ርኩሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራው ጽድቅ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና በሠራው ኃጢአት በእነሱ ይሞታል። እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ ስሙ፥ በውኑ መንገዴ ቀና አይደለምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን? ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ በዚያ ቢሞት፥ እርሱ በሠራው በደል ይሞታል። ክፉ ሰውም ከሠራው ክፋት ቢመለስ፥ ፍትሕንና ጽድቅንም ቢያደርግ ነፍሱን በሕይወት ያኖራል። የሠራውን በደል ሁሉ አይቶ ተመልሶአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። ሆኖም የእስራኤል ቤት የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ይላሉ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዶቼ ቀና አይደሉምን? ቀና ያልሆኑትስ የእናንተ መንገዶች አይደሉምን? ስለዚህ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እያንዳንዱን ሰው እንደ መንገዱ እፈርዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ተመለሱ፥ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፥ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ለምን ትሞታላችሁ? የሟቹ ሞት አልደሰትምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ። አንተም በእስራኤል ልዑሎች ላይ ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል፦ እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት ያለች እንስት አንበሳ ነበረች! በደቦል አንበሶች መካከል ተቀምጣ ግልገሎችዋን አሳደገች። ከግልገሎችዋም አንዱን አሳደገችው፥ እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፥ አደንም ተማረ፥ ሰዎችን በላ። ሕዝቦች ስለ እርሱ ሰሙ፤ በጉድጓዳቸው ተያዘ፤ በመንጠቆዎችም ይዘው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት። እርሷም ጠበቀች፥ ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ አንዱን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ፤ ደቦል አንበሳም ሆነ፥ አደንም ተማረ፤ ሰዎችን በላ። ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውን አፈረሰ፥ ምድሪቱና ሞላዋ ከግሣቱ ድምፅ የተነሣ ጠፋች። ሕዝቦችም በዙሪያው ካሉት አገሮች ሁሉ ተሰበሰቡበት፥ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ፤ በጉድጓዳቸው ተያዘ። በመንጠቆዎችም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት፥ ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ ዳግመኛ እንዳይሰማ ወደ እስር ቤት አመጡት። እናትህ በደምህ፥ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ነበረች፥ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና ቅርንጫፎች የሞሉባት ነበረች። ገዢዎች ለሚይዙት በትረ መንግሥት የሚሆኑ ብርቱ ቅርንጫፎች ነበሩአት፤ ቁመቱ ከቅርንጫፎች መካከል ረዥም ነበር፥ በርዝመቱና በቅርንጫፎቹ ብዛት ታየ። ነገር ግን በቁጣ ተነቀለች፥ ወደ መሬትም ተጣለች፤ የምሥራቅ ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱ ቅርንጫፎቿም ተሰበሩና ደረቁ፤ እሳትም በላቸው። አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማ መሬት ተተከለች። ከቅርንጫፍዋ እሳት ወጣች፥ ፍሬዋንም በላች፥ ለገዢዎች በትረ መንግሥት የሚሆን ብርቱ ቅርንጫፍ በእርሷ ዘንድ የለም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል። እንዲህም ሆነ በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች ጌታን ሊጠይቁ መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ እኔን ልትጠይቁ መጣችሁን? እኔ ሕያው ነኝ፥ ለእናንተ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኩሰት አስታውቃቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፥ ለያዕቆብ ቤት ዘር ማልሁላቸው፥ በግብጽም ምድር ራሴን ገለጥሁላቸው፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ ብዬ ማልሁላቸው። በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላችሁ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው። እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ፦ በግብጽ ምድር መካከል ቁጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። የምቀድሳቸውም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቁጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፥ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም። ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቁጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤ ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። እኔም ጌታ እንደሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመጽ አስቆጡኝ። እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ። እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኩሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም። እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤ ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ ትሰሙኝ ዘንድ ባትወድዱ ሁላችሁ ጣዖቶቻችሁን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቁርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም። በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድሩ ላይ ያመልኩኛል፤ በዚያም እቀበላቸዋለሁ፥ በዚያም ቁርባናችሁን በኩራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እፈልጋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ። ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። በዚያም የረክሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋታችሁ ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና ወደ ደቡብም ተናገር በደቡብም ባለው ዱር ላይ ትንቢት ተናገር፤ ለደቡብም ዱር፦ የጌታን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠል ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል። እኔ ጌታ እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም በለው። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፦ ይህ ምሳሌን የሚመስል አይደለምን? ብለዋል አልሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አድርግ፥ ስለ መቅደሶችም ስበክ፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተናገር ለእስራኤልም ምድር እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ሰይፌን ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፥ ጻድቁንና ክፉውን ከአንቺ ዘንድ አስወግዳለሁ። ጻድቁንና ክፉውን ከአንቺ ዘንድ ስለማስወግድ፥ ስለዚህ ሰይፌ ከደቡብ እስከ ሰሜን ባለ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። እኔ ጌታ ሰይፌን ከሰገባው እንደ መዘዝሁ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ደግሞ ወደ ሰገባው አይመለስም። አንተም የሰው ልጅ ሆይ አልቅስ፥ ወገብህን በማጉበጥና በምሬት በፊታቸው አልቅስ። እነርሱም ለምን ታለቅሳለህ? ሲሉህ እንዲህ በላቸው፦ ወሬ ስለሚመጣ ነው፥ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፥ እጆች ሁሉ ይዝላሉ፥ ነፍስ ሁሉ ትደክማለች፥ ጉልበት ሁሉ እንደ ውኃ ይፈስሳል፥ እነሆ ይመጣል ይፈጸማልም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፦ ትንቢት ተናገር፥ እንዲህም በል፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ! የተሳለና የተወለወለ ሰይፍ ነው። እንዲገድል ተስሎአል እንዲያብረቀርቅም ተወልውሏል፥ እኛስ ደስ ይለናልን? የልጄን በትር እንደ ማንኛውም ዛፍ ንቆታል። ሰይፉ እንዲወለወል፥ በእጅም እንዲያዝ ተሰጠ፤ በገዳዩ እጅ እንዲቀመጥ ተሳለ፥ ተወለወለም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ጩኽ ዋይም በል፥ በሕዝቤ ላይ ነውና፤ በእስራኤል አለቆች ሁሉ ላይ ነውና፤ እነርሱ ከሕዝቤ ጋር ወደ ሰይፍ ተጥለዋል፥ ስለዚህ ጭንህን ምታ። ፈተና ተደርጓል፥ ደግሞ የተናቀ በትር ባይኖርስ ምን ይሆናል? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። አንተም የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር፥ መዳፍህን በመዳፍህ ምታ፥ የተገደሉ ሰዎች ሰይፍ ሦስት ጊዜ ይደጋግም የሚከብባቸው የተገደለ የታላቅ ሰው ሰይፍ ነው። ልብ እንዲቀልጥ፥ ብዙዎች እንዲሰናከሉ ነው፤ በበሮቻቸው ሁሉ ላይ የሚገድል ሰይፍ አድርጌአለሁ፥ ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፥ እንዲገድልም ተጠቅልሎአል። ተዘጋጅተህ ፊትህ ወደ ወደደው ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሂድ። እኔም ደግሞ መዳፌን በመዳፌ እመታለሁ፥ ቁጣዬም ይበርዳል፥ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣበትን ሁለት መንገዶችን አድርግ፥ ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፥ ምልክትም አድርግ፥ በከተማይቱ መንገድ ራስ ላይ አድርገው። ሰይፍ ወደ አሞን ልጆች ወደ ረባት፥ ወደ ይሁዳ፥ ወደ ተመሸገች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ መንገድን አድርግ። የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ መንገዶች ራስ ላይ ቆሞ ነበር፤ ፍላጾችን ወዘወዘ፥ ከተራፊምም ጠየቀ፥ ጉበትም ተመለከተ። የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ። መሐላውንም በማሉ በዓይናቸው ዘንድ የሐሰት ምዋርት ይመስላል፥ ነገር ግን እነርሱ ይያዙ ዘንድ እርሱ ኃጢአትን ያሳስባል። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኃጢአታችሁን ስለ አሰባችሁ መተላለፋችሁም ስለ ተገለጠ ኃጢአታችሁም በሥራችሁ ሁሉ ስለ ታየ እናንተም ስለ ታሰባችሁ፥ በእጅ ትያዛላችሁ። አንተም ቀንህ የደረሰብህ፥ የኃጢአትህ ቀጠሮ ጊዜ የደረሰብህ፥ ርኩስ ኃጢአተኛ የእስራኤል አለቃ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መጠምጠሚያውን አውልቅ፥ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ የተዋረደውን ከፍ አድርግ፥ ከፍ ያለውንም አዋርድ። ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ፍርድ ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፥ ለእርሱም እሰጣለሁ። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፦ ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ቀናቸው በደረሰ፥ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ በደረሰ፥ በተገደሉት ኃጢአተኞች አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱን ራእይ ነገር ሲያዩልህ በሐሰትም ምዋርት ሲናገሩልህ፦ ሰይፍ፥ ሰይፍ ተመዝዞአል፥ ይገድልም ዘንድ ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል በል። ወደ ሰገባው መልሰው። በተፈጠርህበት ስፍራ በተወለድህባትም ምድር እፈርድብሃለሁ። ቁጣዬንም አፈስስብሃለሁ፥ በመዓቴም እሳት አነድብሃለሁ፥ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፥ ደምህም በምድር መካከል ይሆናል፥ ደግሞም አትታሰብም፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁና። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኩሰትዋን ሁሉ አስታውቃት። እንዲህም በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ደምን የምታፈስ ከተማ ሆይ!ጊዜዋ ደርሶአል፥ እንድትረክስም በራስዋ ላይ ጣዖታትን የምታደርግ፤ ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፥ በሠራሻቸውም ጣዖቶችሽ ረክሰሻል፥ ቀንሽን አቀረብሽ፥ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፥ ስለዚህ ለሕዝቦች መሰደቢያ፥ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። አንቺ ስምሽ የረከሰ፥ ሽብር የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል። እነሆ የእስራኤል ልዑሎች እያንዳንዱ እንደ አቅሙ ደም ሊያፈስሱ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። አባትንና እናትን አቃለሉ፥ በመካከልሽ መጻተኛውን ጨቆኑ፥ በአንቺ ውስጥ የሙት ልጅንና መበለቲቱን አስጨነቁ። ቅዱሳን ነገሮቼን ናቅሽ፥ ሰንበቶቼን አረከስሽ። ሐሜተኞች ሰዎች ደምን ሊያፈስሱ በአንቺ ውስጥ ነበሩ፥ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፥ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ። በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ዕራቁትነት ገለጡ፥ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። ሰውም ከጎረቤቱ ሚስት ጋር ርኩሰትን አደረገ፥ ሌላውም የልጁን ሚስት በዝሙት አረከሰ፥ ሌላውም በአንቺ ውስጥ የአባቱን ልጅ፥ እኅቱን አዋረደ። ደም ለማፍሰስ በአንቺ ውስጥ ጉቦን ተቀበሉ፥ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ጎረቤቶችሽንም ጨቁነሽ የማይገባ ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እነሆ ያለ አግባብ በአገኘሽው ትርፍና በመካከልሽ በፈሰሰው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ። ከአንቺ ጋር በምነጋገርበት ጊዜ ልብሽ መቋቋም ይችላልን? እጆችሽስ ይጸናሉን? እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ አደርገዋለሁም። ወደ አገሮች እበትንሻለሁ፥ በምድርም እዘራሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቂአለሽ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፥ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቆርቆሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር ዝቃጭ ናቸው። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ የብረት ዝቃጭ ሆናችኋልና፥ ስለዚህ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰብስባችኋለሁ። ሰው ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቆርቆሮንም ለማቅለጥ እሳትን ሊያነድበት በማቅለጫ እንደሚሰበስብ፥ እንዲሁ በቁጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። እሰበስባችሁአለሁ፥ የመዓቴንም እሳት አነድባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። ብርም በማቅለጫ ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፥ እኔም ጌታ መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ እንዲህ በላት፦ አንቺ ያልነጻሽ፥ በቁጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት። በውስጧ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና የገደለውን እንደሚበላ አንበሳ ናቸው፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ሀብትንና የከበሩ ነገሮችን ወስደዋል፤ በውስጧም ብዙዎችን መበለቶች አድርገዋል። ካህናቶችዋም ሕጌን ጥሰዋል፥ ቅዱሳት ነገሮቼንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነ ነገርና በረከሰ ነገር ላይ ልዩነትን አላደረጉም፥ በርኩስ ነገርና በንጹሕ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፥ ከሰንበቶቼ ዓይናቸውን ሰወሩ፥ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። በውስጧ ያሉ አለቆችዋ የገደሉትን እንደሚቦጫጭቁ ተኩላዎች ናቸው። ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሳሉ፥ ነፍሶችንም ያጠፋሉ። ነቢዮችዋ ጌታ ሳይናገር “ጌታ እንዲህ ይላል” እያሉ የሐሰት ራእይ በማየትና በውሸት ሟርት፥ በኖራ ይለቀልቋቸዋል። የምድሪቱ ሕዝብ ግፍ አደረጉ፥ ዝርፊያም ፈፀሙ፥ ድሃውንና ችግረኛውን አንገላቱ፥ መጻተኛውንም ያለ ፍትሕ በደሉ። ቅጥሩን የሚሠራ፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። ስለዚህ ቁጣዬን አፈሰስሁባቸው፤ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንድ እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። በግብጽ አመነዘሩ፤ በወጣትነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ተዳሰሱ፥ በዚያም የድንግልናቸው የጡቶች ጫፍ ተዳበሱ። ስማቸውም፦ የታላቂቱ ኦሆላ የእኅትዋም ኦሆሊባ ነበረ። የእኔም ሆኑ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም፦ ኦሆላ ሰማርያ ናት፥ ኦሆሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት። ኦሖላም የእኔ ሆና ሳለ አመነዘረች፥ ጦረኞች ከሆኑት አሦራውያን ውሽሞችዋ ጋር በፍትወት ተከተለቻቸው። እነርሱም ሰማያዊ የለበሱ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ፈረስ የሚጋልቡ ፈረሰኞች ነበሩ። ዝሙቷንም ከተመረጡ የአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍትወት ከተከተለቻቸው ከጣዖቶቻቸው ሁሉ ጋር እራስዋን አረከሰች። ከግብጽ ጀምሮ የነበረውን አመንዝራነቷን አልተወችም፤ በወጣትነትዋ ጊዜ ወንዶች ከእርሷ ጋር ተኝተው ነበርና፥ የድንግልናዋንም የጡቶቿ ጫፎች ዳብሰው ነበርና፥ ፍትወታቸውንም አፍስሰውባት ነበርና። ስለዚህ በፍትወት በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ እጅ፥ በአሦር ልጆች እጅ አሳልፌ ሰጠኋት። እነርሱም ዕራቁትነትዋን ገለጡ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ወሰዱ፤ እርሷንም በሰይፍ ገደሉ፤ በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች፥ ፍርድም ተፈጸመባት። እኅትዋ ኦሆሊባ ይህን አየች፥ ሆኖም በፍትወቷና በአመንዝራነቷ ከእርሷ ይልቅ ብልሹ ነበረች፥ ይህም ከእኅትዋ ይልቅ የበዛ ነበር። አሦራውያንን፥ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ ጦረኞች፥ በፈረሶችን የሚጋልቡ ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶችን በፍትወት ተከተለቻቸው። እራስዋን እንዳረከሰች አየሁ፤ ሁለቱም በአንድ መንገድ ሄዱ። አመንዝራነቷን ቀጠለችበት፤ በቀይ ቀለም የተሳለ የከለዳውያን ስዕል፥ በግድግዳ ላይ የተቀረጸ የወንዶች ምስል አየች። በወገባቸው ዝናር የታጠቁ፥ በራሳቸውም ላይ መጠምጠሚያ ያንጠለጠሉ፥ ሁሉም የተወለዱባት አገር የከለዳ የሆነች የባቢሎን ልጆች የሆኑትን ባለሥልጣኖችን ይመስሉ ነበር። በዓይኗም ባየቻቸው ጊዜ በፍትወት ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። የባቢሎንም ልጆች ወደ እርሷ፥ ወደ ፍቅር አልጋ ገቡ፥ በዝሙታቸውም አረከሱአት፤ እርሷም በእነርሱ ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። ዝሙቷን ገለጠች፥ ዕርቃንዋንም ገለጠች፥ ነፍሴ ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርሷም ተለየች። ሆኖም በግብጽ ምድር ያመነዘረችበትን የወጣትነትዋን ዘመን አስባ ዝሙቷን አበዛች። ሥጋቸው እንደ አህዮች ሥጋ፥ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍትወት ተከተለቻቸው። ስለ ወጣትነት ጡቶችሽን ግብጻውያን ጡቶችሽን የዳበሱበትን ጊዜ የወጣትነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ። ስለዚህ ኦሆሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየቻቸው ወዳጆችሽን አስነሣብሻለሁ፥ እነርሱንም ከየአቅጣጫው በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። እነርሱም የባቢሎን ልጆች፥ ከለዳውያን ሁሉ ፋቁድ፥ ሾዓ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር የአሦር ልጆች ሁሉ፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ገዢዎች፥ ባለ ሥልጣናት፥ መኰንኖችና የተጠሩ፥ ሁሉም ፈረስ የሚጋልቡ ናቸው። መሣሪያ፥ ሠረገላና መንኰራኵር ይዘው፥ ብዙ ሕዝብ ሆነው በአንቺ ላይ ይመጣሉ፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቁርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፥ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። በቁጣ እንዲቀርቡሽ ቅናቴን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ፥ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቆርጣሉ፤ ቀሪሽም በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረው በእሳት ይበላል። ልብስሽን ይገፍፉሻል የሚያማምሩ ጌጣጌጦችሽን ይወስዳሉ። ሴሰኝነትሽንና ከግብጽ ምድር ያመጣሽውን ዝሙትሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፥ ዓይንሽን ወደ እነርሱ አታነሺም፥ ግብጽንም ዳግም አታስቢም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽም በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም በጥል ይቀርቡሻል፥ የድካምሽን ፍሬ ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፥ የዝሙትሽ ዕራቁትነት፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽ ይገለጣል። ከአገሮች ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን አደረጉብሽ። በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ የእርሷን ጽዋ በእጅሽ እሰጥሻለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥልቅና ሰፊ የሆነውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ ብዙም ስለሚይዝ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ። የድንጋጤና የጥፋት ጽዋ በሆነው በእኅትሽ በሰማሪያ ጽዋ፥ በስካርና በኀዘን ትሞዪአለሽ። ትጠጪዋለሽ፥ ትጨልጪዋለሽም፥ ገሉን ታኝኪዋለሽ፥ ጡትሽንም ትቆራርጪአለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለረሳሽኝ፥ ወደ ኋላሽም ስለጣልሽኝ፥ አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ። ጌታ እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሆላና በኦሆሊባ ትፈርዳለህን? ርኩሰታቸውን ንገራቸው። አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፤ ከጣዖቶቻቸው ጋር አመንዝረዋል፤ ለእኔ የወለዷቸውን ልጆቻቸውን እንኳ መብል እንዲሆኑ አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፦ በዚያኑ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል፥ ሰንበቶቼንም ሽረዋል። ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ሊያረክሱት ወደ መቅደሴ ገብተዋልና፤ እነሆም በቤቴ ውስጥ ይህን አደረጉ። ደግሞም መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው፥ ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልከዋል፥ እነሆም መጡ፤ ታጠብሽላቸው ዓይንሽን ተኳልሽ፥ ጌጥም አደረግሽ፤ ክብር ባለው አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊቱም ማዕድ ተዘጋጅቶ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም በዚያ ላይ አስቀመጥሽ። የደስተኞችም ድምፅ በእርሷ ዘንድ ነበረ፥ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረበዳ መጡ፥ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ። እኔም በዝሙት ላረጀችው፦ አሁን ከእርሷ ጋር ያመነዝራሉ፥ እርሷም ታመነዝራለች አልሁ። ሰው ወደ አመንዝራ እንደሚገባ ወደ እርሷ ገቡ፤ ስለዚህ አመንዝራ ወደ ሆኑት ወደ ኦሆላና ወደ ኦሆሊባ ገቡ። ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል፤ ምክንያቱም አመንዝሮች ናቸውና፥ ደምም በእጃቸው አለና። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለፍርሃትና ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል፥ በሰይፋቸው ይቆርጡአቸዋል፤ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። ሴቶችም ሁሉ እንደ አመንዝራነታችሁ እንዳይሠሩ፥ እንዲጠነቀቁ አመንዝራነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። አመንዝራነታችሁን በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ ፥ የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፥ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዛሬዋ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ። ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣደው፥ ድስቱን ጣደው፥ ውኃም ጨምርበት። የስጋ ቁራጮች፥ መልካም የሆነው የስጋ ቁራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በውስጡ ጨምር፤ የተመረጡ አጥንቶችንም ሙላበት። የተመረጠውን መንጋ ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ ከስሩ ማገዶ ጨምር፤ በደንብ ይንተክተክ፥ አጥንቶቹም በውስጡ ይብሰሉ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርሷ ላልወጣ ድስት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቁራጭ ቁራጩን አውጣ፥ ዕጣ አልወደቀባትም። ደምዋ በመካከሏ አለና፤ በተራቆተ ድንጋይ ላይ አስቀመጠችው፤ በአፈር እንዲከደን መሬት ላይ አላፈሰሰችውም። እንድቆጣና፥ በቀልንም እንድበቀል፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቆተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶውን ብዙ አደርገዋለሁ። እንጨቶችን ጨምር፥ እሳቱን አንድድ፥ ሥጋውን ቀቅል፥ ማጣፈጫ ጨምረህ አደባልቀው፥ አጥንቶቹ ይቃጠሉ። እንድትሞቅ፥ ናስዋም እንድትግል፥ ርኩሰትዋም በውስጧ እንዲቀልጥ ዝገትዋም እንዲጠፋ ባዶዋን ፍም ላይ አስቀምጣት። ብዙ ለፍታ ደከመች፥ ሆኖም የዝገቱ ክምር በእሳት እንኳ አልለቀቀም። በርኩሰትሽ ሴሰኝነት አለ፥ መዓቴን በአንቺ ላይ እስክጨርስ ድረስ ከእንግዲህ ወዲያ ከርኩሰትሽ ንፁህ አትሆኚም ምክንያቱም አነጻሁሽ ነገር ግን ንፁህ አልሆንሺምና። እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፤ ይፈፀማል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልቆጠብም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም። እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የዐይንህን ምኞት በቅፅበት እወስድብሃለሁ፤ ቢሆንም ግን ዋይታ አታሰማ፥ አታልቅስ፥ እንባህንም አታፍስስ። በዝምታ ተክዝ፥ ለሙታን አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ ከንፈርህን አትሸፍን፥ የዕዝን እንጀራም አትብላ። እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በማግስቱም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ። ሕዝቡም፦ “እነዚህ የምታደርጋቸውው ነገሮች ለእኛ ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ። እኔም እንዲህ አልኋቸው፦ “የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የኃይላችሁ ትምክሕት፥ የዓይናችሁ ምኞት፥ የነፍሳችሁ ናፍቆት የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። እኔ እንዳደረግሁ እናንተም ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም፥ የዕዝን እንጀራም አትበሉም። መጠምጠሚያችሁ በራሳችሁ ላይ፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም ወይም አታለቅሱም፤ በኃጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፥ እርስ በእርሳችሁም ታለቅሳላችሁ። እንግዲህ ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ ያደረገውን ሁሉ እናንተም ታደርጋላችሁ። ይህ በሚመጣበት ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ምሽጋቸውን፥ የክብራቸውን ደስታ፥ የዓይናቸውን ምኞት፥ የነፍሳቸውን ናፍቆት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥ በዚያን ቀን፥ ያመለጠ ሰው ይህን ነገር ጆሮዎችህ እንዲሰሙ ወደ አንተ ይመጣል። በዚያን ቀን አፍህ ላመለጠው ሰው ይከፈታል፥ ትናገራለህም፥ ከዚያ በኋላም ድዳ አትሆንም። ስለዚህ ምልክት ትሆናቸዋለህ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አድርገህ ትንቢት ተናገርባቸው። ለአሞንም ልጆች እንዲህ በላቸው፦ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፥ የይሁዳም ቤት ተማርከው በተወሰዱ ጊዜ እሰይ ብለሻልና፤ ስለዚህ እነሆ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ እነርሱም በአንቺ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንቺ ውስጥ ይሠራሉ፤ ፍሬሽን ይበላሉ ወተትሽንም ይጠጣሉ። ራባን የግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ምድር ላይ በውስጥሽ ባለው ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሽ በእጅሽ አጨብጭበሻልና፥ በእግርሽም አሸብሽበሻልና፥ ስለዚህ እነሆ እጄን በአንተ ላይ ዘርግቻለሁ፥ እንዲበዘብዙህ ለሕዝቦች እሰጥሃለሁ፥ ከሕዝቦች እቆርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም እደመስስሃለሁ፤ አጠፋሃለሁም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃለህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሞአብና ሴይር፦ እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎች ሕዝቦች ነው ብለዋልና፥ ስለዚህ እነሆ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ የአሞን ልጆች በሕዝቦች መካከል እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ። በሞዓብም ላይ ፍርድ እሰጣለሁ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኤዶም በይሁዳ ቤት ላይ በቀል ተበቅሎአልና፥ በዚህም በደለኛ ሆኗል፥ በእነሱም ላይ ተበቅሎአልና፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኤዶምያስ ላይ እጄን እዘረጋለሁ፥ ከእርሷም ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማን ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እንደ ቁጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ላይ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቆርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር የቀሩትን አጠፋለሁ። ቁጣ ከተሞላበት ቅጣት ጋር ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፥ በቀሌን በእነሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ፦ “እሰይ የሕዝቦች በር የነበረች ተሰበረች፤ ወደ እኔም ተመለሰች፤ እርሷ ስለፈረሰች እኔ እሞላለሁ፤” ብላለችና። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፥ ባሕር ሞገድን እንደሚያስነሣ እንዲሁ ብዙ ሕዝቦችን አስነሣብሻለሁ። የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፥ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ አፈሯን ከእርሷ ላይ ጠርጌ የተራቆተ ዓለት አደርጋታለሁ። በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ለሕዝቦችም ብዝበዛ ትሆናለች። በሜዳ ያሉት ሴቶች ልጆችዋም በሰይፍ ይገደላሉ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነዖርን ከፈረሶች፥ ከሰረገሎች፥ ከፈረሰኞች፥ ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። በሜዳ ያሉትን ሴቶችን ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፤ በአንቺ ላይ ምሽግ ይሠራል፥ ደለልም በአንቺ ላይ ይደለድላል፥ በአንቺም ላይ ጋሻ ያነሣል። ግንብ ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያነጣጥራል፥ ግንብሽንም በሰይፉ ያፈርሳል። ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ አቧራቸው ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ወደ ፈረስች ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፥ ከፈረሰኞች፥ ከመንኩራኩሮች እና ከሰረገሎች ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ። በፈረሶቹ ኮቴዎች ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረጋግጣል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽ ምሰሶዎች ወደ መሬት ይወድቃሉ። ሀብትሽን ይዘርፋሉ፥ ሸቀጣ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽን ያፈርሳሉ፥ የተዋቡ ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽን፥ እንጨትሽንና አፈርሽን በውኆች መካከል ያስቀምጣሉ። የዘፈንሽን ብዛት አስቆማለሁ፤ የበገናሽ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም። የተራቆተ ዓለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ዳግምም አትሠሪም፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል፦ የቆሰሉት ባቃሰቱ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን? በዚያን ጊዜ የባሕር አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያስቀምጣሉ፥ ወርቀዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ይለብሳሉ፥ በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ፥ በአንቺም ይደነቃሉ። በአንቺ ላይ ሙሾ ያወርዳሉ፥ እንዲህም ይሉሻል፦ ከባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ ዝነኛ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ! አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕር ያሉ ደሴቶችም ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ጥልቁንም በላይሽ ላይ ባመጣሁብሽ ጊዜ፥ ብዙ ውኆችም ይከድኑሻል፥ የጥንት ሕዝብ ወዳሉበት ጉድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፥ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። ለድንጋጤ አደርግሻለሁ፥ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘለዓለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አውርድ፥ በባሕር መግቢያ ለምትኖረውና፥ በብዙ ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ለምትነግደው ጢሮስ እንዲህ በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ፦ “በውበት ፍጹም ነኝ” ብለሻል። ዳርቻሽ በባሕር ልብ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፍጹም አደረጉ። ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሴኒር በመጣ ጥድ ሠሩ፤ ደቀልንም ሊሰሩልሽ ከሊባኖስ ዝግባ ወሰዱ። በባሻን ባሉጦች መቅዘፊያሽን ሠሩ፤ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ ወለልሽን ሠርተዋል። ዓላማ ሆኖ እንዲያገለግልሽ፥ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቀ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሻ ደሴቶች የመጣ ሰማያዊና የወይን ጠጅ ነበር። የሲዶናና የአርቫድ ነዋሪዎች ቀዛፊዎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የነበሩት ባለሙያዎችሽ የመርከቦችሽ መሪዎች ነበሩ። በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው ከአንቺ ጋር ለመለዋወጥ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። ፋርስ፥ ሉድና ፉጥ በሠራዊትሽ ውስጥ ወታደሮችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቁርም በአንቺ ውስጥ ሰቀሉ፤ ውበትን ሰጡሽ። የአርቫድ ልጆችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ ዙሪያውን ነበሩ፥ ጋማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፥ ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ። ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፥ በብርና በብረት በቆርቆሮና በእርሳስ ዕቃሽን ለወጡ። ያቫን፥ ቱባልና ሜሼክ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ዕቃሽን በሰዎች ነፍስና በናስ ዕቃ ይለውጡ ነበር። የቶጋርማ ቤትም ዕቃዎችሽን በፈረሶች፥ በፈረሰኞችና በበቅሎዎች ለወጡ። የድዳን ልጆችም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ። ከምርትሽ ብዛት የተነሣ አራም ነጋዴሽ ነበረች፤ ዕቃዎችሽን በበሉር፥ በወይን ጠጅ፥ በወርቀ ዘቦ፥ በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቁም ይቀይሩ ነበር። ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ዕቃዎችሽን በሚኒት ስንዴ፥ ጣፋጭ ዳቦ፥ ማር፥ ዘይትና በለሳን ይለውጡ ነበር። በሁሉም ነገር ሀብታም ስለ ነበርሽ፥ ከንብረትሽ ብዛት የተነሣ፥ ደማስቆ በሔልቦን የወይን ጠጅ፥ ነጭ የበግ ጠጉር፥ ነጋዴሽ ነበረች። ከኡዛል ቭዳንና ያቫን ዕቃዎችሽን ይለውጡ ነበር፤ የተሠራ ብረትና ብርጉድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ። ድዳን ለግልቢያ በሚሆን ኮርቻ ነጋዴሽ ነበረች። ዓረብና የቄዳር ልዑላን ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶች፥ በአውራ በጎችና በፍየሎች በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ምርጥ በሆኑ ቅመማ ቅመሞች ሁሉ፥ በክበረ ድንጋይ ሁሉና በወርቅ ሸቀጥሽን ይለውጡ ነበር። ሐራን፥ ካኔ፥ ዔድን፥ የሳባ ነጋዴዎች፥ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ። እነዚህ በገበያሽ ውስጥ በአማረ ልብስ፥ በሰማያዊ ካባ፥ በወርቀ ዘቦ፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን ይነግዱ ነበር። የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚያጓጉዙልሽ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር፥ በባሕርም ልብ ውስጥ እጅግ ከበርሽ። ቀዛፊዎችሽ ወደ ታላቅ ውኆች አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ልብ ሰበረሽ። ሀብትሽ፥ ሸቀጥሽ፥ ንግድሽ፥ መርከበኞችሽ፥ መርከብ መሪዎችሽ፥ ሰባራሽን የሚጠግኑ፥ ሸቀጥሽን የሚነግዱ፥ በአንቺ ውስጥ ያሉ ወታደሮችሽ ሁሉ፥ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በውድቀትሽ ቀን ወደ ባሕር ልብ ይወድቃሉ። ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ መሰማሪያዎች ይንቀጠቀጣሉ። መቅዘፊያውን የያዙት ሁሉ፥ መርከበኞች፥ የባሕር መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ፤ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፥ ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለው ይጮኻሉ፤ በራሳቸውም ላይ አቧራ ይነሰንሳሉ፤ በአመድም ላይ ይንከባበላሉ፤ ስለ አንቺ ጠጉራቸውን ይላጫሉ፥ ማቅም ይታጠቃሉ፤ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። በልቅሶአቸውም ስለ አንቺ ሙሾን ያነሡልሻል፥ እንዲህም እያሉ በአንቺ ላይ ያሞሻሉ፦ በባሕር መካከል ጠፍቶ የቀረ እንደ ጢሮስ ማን ነው? ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ ሕዝቦችን አጥግበሻል፤ በተትረፈረፈ በሀብትሽና በሸቀጣ ሸቀጥሽ የምድርን ነገሥታት አበልጽገሻል። በጥልቅ ውኆች ውስጥ፥ በባሕር በተሰበርሽ ጊዜ ግን ሸቀጣ ሸቀጥሽና በመካከልሽ ያሉ ጉባኤሽ ሁሉ ወድቀዋል። በደሴቶች የሚኖሩ ሁሉ በአንቺ ደንግጠዋል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል፥ ፊታቸውም ተለውጦአል። ከሕዝቦች መካከል ያሉ ነጋዴዎች አፏጩብሽ፤ አስደንጋጭ ሆነሻል፥ ለዘለዓለምም አትገኚም። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህ ኰርቶአል አንተም እንዲህ ብለሃል፦ እኔ አምላክ ነኝ፥ በእግዚአብሔር ወንበር በባሕር ልብ ተቀምጫለሁ፤ ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። እነሆ፥ አንተ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነህ፥ ከአንተ የተሰወረ ምሥጢር የለም። በጥበብህና በማስተዋልህ ሀብትን ለራስህ አግኝተሃል፥ ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል። በጥበብህ ብዛትና በንግድህ ሀብትህን ጨምረሃል፥ በሀብትህም ልብህ ኰርቶአል። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና፥ ስለዚህ እነሆ ባዕዳንን፥ ጨካኞች መንግሥታትን አመጣብሃለሁ፤ በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ፥ ድምቀትህን ያረክሳሉ። ወደ ጉድጓድ ያወርዱሃል፤ በባሕር ልብ ተገድለው በሞቱበት ሞት ትሞታለህ። በገዳይህ ፊትም፦ “እኔ አምላክ ነኝ” ትላለህን? ቢሆንም አንተ በገዳይህ እጅ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። በባዕዳን እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ድንጋይ ሁሉ ልብስህ ነበር፥ ያቁት፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር። አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ። በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ። በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ። በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከሰህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርሷም በልታሃለች፥ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ። በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ አንተ ለድንጋጤ ሆነሃል፥ እስከ ዘለዓለምም አትገኝም። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም ባደረግሁባት ጊዜ በተቀደስሁባትም ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ቸነፈርንም በእርሷ ላይ፥ ደምንም በጎዳናዋ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያዋ በላይዋ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልዋ ይወድቃሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ከናቋቸው ሁሉ የሚያቆስል ኩርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባርያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ። በአሥረኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር ከወሩም በዓሥራ ሁለተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ተናገር፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “‘ወንዙ የእኔ ነው እኔ ራሴ ሠርቼዋለሁ’ የምትል፥ በወንዞች መካከል የምትተኛ፥ አንተ ታላቅ ድራጎን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ። በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፥ የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤ በቅርፊትህ ከተጣበቁት የወንዞችህ ዓሦች ሁሉ ጋር ከወንዞችህ መካከል አወጣሃለሁ። አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፤ በሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ አትከማችም፥ አትሰበሰብም፤ ምግብ እንድትሆን ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጥሃለሁ። ለእስራኤል ቤት የመቃ በትር ሆነዋልና በግብጽ የሚኖሩ ሁሉ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በእጅህ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ትከሻቸውን ሁሉ ቆረጥህ፤ በአንተ ላይ ሲደገፉ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።” ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሻለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንቺ አጠፋለሁ። የግብጽ ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ምክንያቱም ወንዙ የእኔ ነው፥ የሠራሁትም እኔ ነኝ ብሏልና። ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ በወንዞችህም ላይ ነኝ፥ የግብጽን ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴቬኔና እስከ ኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ። በእርሷ በኩል የሰው እግር አያልፍም፥ የእንስሳም እግር አያልፍም፥ ለአርባ ዓመትም ማንም አይኖርባትም። የግብጽን ምድር ባድማ በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ አደርጋታለሁ፥ ከተሞችዋንም በፈረሱት ከተሞች መካከል ለአርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ ሕዝቦች እበትናቸዋለሁ፥ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አርባውም ዓመት ሲያልቅ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው ሕዝቦች መካከል እሰበስባለሁ፤ የግብጽን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባት ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ። ከመንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በሕዝቦች ላይ ከፍ ከፍ አትልም፤ በሕዝቦችም መካከል እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ። ከእንግዲህ ወዲያ ለእስራኤል ቤት መታመኛ አይሆንም፥ እነርሱን በተከተሉ ጊዜ በደልን ያሳስባል፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ። እንዲህም ሆነ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በጢሮስ ላይ ሠራዊቱን ጽኑ ሥራ አሠራ፤ ራስ ሁሉ ተመልጧል፥ ትከሻም ሁሉ ተልጦአል፥ ሆኖም በእርሷ ላይ ለሰሩት ሥራ እርሱም ሆነ ሠራዊቱ ከጢሮስ ደመወዝ አልተቀበሉም። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛትዋን ያነሳል፥ ምርኮዋን ይማርካል፥ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል። ለእኔ ሠርተዋልና ለሠራው ሥራ ካሳ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለአንተ ደግሞ በመካከላቸው የተከፈተ አፍን እሰጥሃለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አልቅሱ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነውና፥ የጌታ ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የሕዝቦች ጊዜ ይሆናል። በግብጽ ላይ ሰይፍ ይመጣል፥ የተገደሉት በግብጽ ውስጥ ሲወድቁ፥ በኢትዮጵያ ጭንቀት ይሆናል፤ ብዛትዋን ይወስዳሉ፥ መሠረቶቿንም ያፈርሳሉ። ኢትዮጵያ፥ ፉጥ፥ ሉድ፥ ባዕዳን ሁሉ፥ ኩብና የቃል ኪዳኑ ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴቬኔ ድረስ በእርሷ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ባድማ በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ። እሳትን በግብጽ ሳነድድ፥ ረዳቶችዋም ሁሉ ሲሰበሩ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በዚያ ቀን ያለ ስጋት የተቀመጠችውን ኢትዮጵያን ለማስፈራራት መልእክተኞች ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ጭንቀት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ መጥቷልና። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አጠፋዋለሁ። እርሱና ከሕዝቦች ሁሉ ርህራሄ የሌላቸው ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በሬሳ ይሞላሉ። ወንዞችን አደርቃለሁ፥ ምድሪቱን በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሞላዋን በባዕዳን እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶችን አስወግዳለሁ፥ ምስሎችንም ከኖፍ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከግብጽ ምድር ገዢ አይነሳም፥ በግብጽ ምድር ላይ ፍርሃትን አኖራለሁ። ጳትሮስን ባድማ አደርጋለሁ፥ በጾዓን እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖ ላይም ፍርድን አመጣለሁ። የግብጽ ምሽግ በሆነችው በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፤ የኖን ብዛት አጠፋለሁ። በግብጽ እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲን ትጨነቃለች፥ ኖ ትሰባበራለች፥ ኖፍ በቀን ጠላቶች ያጠቁአታል። የአቬንና የፊ-ቤሴት ወጣቶች በሰይፍ ይወድቃሉ፥ እነዚህም ተማርከው ይወሰዳሉ። በዚያ የግብጽን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፥ በትሐፍንሔስ ቀኑ ይጨልማል፥ የኃይልዋ ትዕቢት በውስጧ ይጠፋል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ተማርከው ይወሰዳሉ። እንግዲህ በግብጽ ላይ ፍርድን አመጣለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በሰባተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ እነሆ እንዲድን በጨርቅ አልተጠቀለለም፥ ሰይፉን ለመያዝ እንዲጠነክር አልታሰረም። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የበረታችውንና የተሰበረችውን ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ እጥለዋለሁ። ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ። የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ አኖራለሁ፤ የፈርዖንንም ክንድ እሰብራለሁ፥ እሱም በፊቱ ክፉኛ እንደቆሰለ ሰው ያቃስታል። የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፥ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ በአኖርሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንንና ብዛቱን እንዲህ በላቸው፦ በታላቅነትህ ማንን ትመስላለህ? እነሆ አሦር ቅርጫፉ የተዋበ፥ ጥላ የሚሰጥ ጫካ፥ ቁመቱ የረዘመ፥ ጫፉም በቅርንጫፎች መካከል የነበረ የሊባኖስ ዝግባ ነበረ። ውኆች አበቀሉት፥ ጥልቅ ውኃ አሳደገው፥ ወንዞቹም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ። ስለዚህ ቁመቱ ከሜዳ ዛፍ ሁሉ በላይ በለጠ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ በለቀቀላቸውም ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ቅርንጫፎቹ ረዘሙ። የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆአቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ ሠሩ፥ የምድር አራዊት ሁሉ ከቅርጫፎቹ በታች ወለዱ፥ ታላላቅ ሕዝቦች ሁሉ ከጥላው በታች ኖሩ። ሥሩ በብዙ ውኃ አጠገብ ስለ ነበረ በታላቅነቱና በቅርጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አልሸፈኑትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አይመስሉትም አስታ የሚባለውም ዛፍ ቅርጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ በእግዚአብሔር ገነት የነበረ ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመስለውም ነበር። በቅርጫፎቹ ብዛት ውብ አደረግሁት፥ በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በቁመት ረዝመሃል፥ ጫፉን በቅርንጫፎች መካከል አድርጎአልና፥ ልቡም በቁመቱ ኰርቶአልና፥ ለሕዝቦች መሪ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እርሱም እንደ ክፉቱ መጠን ያደረግበታል እኔም አባርረዋለሁ። ባዕዳን፥ የሕዝቦች ጨካኞች የሆኑ፥ ቆርጠው ጣሉት፤ በተራሮች እና በሸለቆዎች ሁሉ ውስጥ ቅርጫፎቹ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፥ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከጥላው ወጥተው ትተውት ሄዱ። በወደቀው ግንድ ላይ የሰማይ ወፎች ሁሉ ተቀመጡ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ሆኑ። ወደ ጉድጓድ በሚወርዱ በሰው ልጆች መካከል ሁላቸው ለታችኛው ምድር ለሞት አልፈው ተሰጥተዋልና በውኃ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሁሉ በቁመታቸው እንዳይረዝሙ፥ ራሳቸውንም በደመናዎች መካከል እንዳያደርጉ፥ ውኃንም የሚጠጡ ኃያላኖቻቸው ሁሉ በቁመታቸው እንዳይቆሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶ አስለቀስሁ፥ ቀላዩን ስለ እርሱ ሸፈንሁት፥ ፈሳሾቹን ገታሁ፥ ታላላቆችም ውኆች ተከለከሉ፤ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት፥ የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ ዛሉ። ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ከመውደቁ ድምፅ የተነሣ ሕዝቦችን አንቀጠቀጥሁ፤ ውኃ የሚጠጡ ሁሉ፥ ምርጦችና መልካሞች የሊባኖስ ዛፎች፥ የዔድን ዛፎች ሁሉ በታችኛው ምድር ውስጥ ተጽናንተዋል። በሕዝቦች መካከል በጥላው የኖሩ ክንዱ ወደነበሩት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ከእርሱ ጋር ወደ ሲኦል ወረዱ። በክብርና በታላቅነት ከዔድን ዛፎች መካከል እንግዲህ ማንን ትመስላለህ? ሆኖም ከዔድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ትወርዳለህ፥ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ትጋደማለህ። ይህም ፈርዖንና ብዛቱ ሁሉ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም ሆነ በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት በዓሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አውርድ፥ እንዲህም በለው፦ በሕዝቦች መካከል አንበሳ መሰልህ፥ እንደ ባሕር አውሬ ነበርህ፤ በወንዞችህም ገንፍለህ ወጥተሃል፥ ውኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከብዙ ሕዝብ ጉባኤ ጋር ሆኜ መረቤን በላይህ ላይ እዘረጋለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። በምድር ላይ እተውሃለሁ፥ ለጥ ባለ ሜዳም እጥልሃለሁ፥ የሰማይ ወፎች ሁሉ በአንተ ላይ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፥ የምድርን አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ፥ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። የምትዋኝባትን ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖዎች ከአንተ ይሞላሉ። በማጠፋህ ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶቻቸውንም አጨልማለሁ፤ ፀሐይን በደመና እሸፍናለሁ፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም። የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በአንተ ላይ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ስብራትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። ብዙም ሕዝቦች አንተን አይተው እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ይንቀጠቀጣሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። በኃያላን ሰይፍ ብዙ ሕዝብህን እጥላለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያወድማሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። በብዙ ውኆች አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም ወይም የእንስሳም ኮቴ አያደፈርሰውም። በዚያን ጊዜ ውኆቻቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የግብጽንም ምድር ወና እና ባድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በመታሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንኩ ያውቃሉ። የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቆነጃጅት፤ በግብጽና ብዛትዋ ሁሉ ላይ ሙሾን ያወርዳሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በዓሥራ አምስተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርሷንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርሷንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ከረዳቶቹ ጋር ሆነው፤ ወደ ታች ወርደዋል በሰይፍም ከተገደሉት ካልተገረዙት ጋር ተኝተዋል፤ ይሏቸዋል። አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ወድቀው በተገደሉባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከባለች። መቃብራቸው በጥልቅ ጉድጓድ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብሯ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸበሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸበሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። በመቃብሯ ዙሪያ በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያሸብሩ ነበር ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል። ሜሼክና ቱባል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸብሩ ስለ ነበር ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ በሰይፍ ተገድለዋል። ከወደቁ ኃያላን ካልተገረዙ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው፥ ሰይፋቸውንም ከራስጌያቸው በታች አድርግው ወደ ሲኦል ከወረዱ ጋር አልተኙም፥ በሕያዋንም ምድር ያሸብሩ ስለ ነበር ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ነበር አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ። ኤዶምያስ እና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኃይል የነበራችው በሰይፍ ከተገደሉት፥ ካልተገረዙት እና ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተኝተዋል። የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድሪቱ ሕዝብ ከመካከላቸው አንድ ሰው ወስደው ለራሳቸው ዘበኛ ያደርጉታል፤ እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። ዘበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከቱን ባይነፋ፥ ሕዝቡን ባያስጠነቅቅ፥ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከዘበኛው እጅ እፈልጋለሁ። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ዘበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። ኃጢአተኛውን ሰው፦ ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ በምለው ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ባታስጠነቅቀው ያ ኃጢአተኛ ሰው በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ከመንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን ሰው ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ በእነርሱም እየመነመንን ነው፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። በሕያውነቴ እምላለሁ ኃጢአተኛው ሰው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ኃጢአተኛው እንዲሞት አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ጽድቁን ተማምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአትም ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። እኔም ኃጢአተኛውን ሰው፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ፥ የነጠቀውንም ቢመልስ፥ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። የሕዝብህም ልጆች፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ በእነርሱ ይሞታል። ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በእነርሱ በሕይወት ይኖርበታል። እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ። እንዲህም ሆነ፥ በተማረክን በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማይቱ ተመታች አለኝ። ያመለጠው ሰው ከመምጣቱ በፊት በነበረው ምሽት የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ ከዚያም በኋላ ዲዳ አልሆንሁም። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ ፍርስራሽ ስፍራዎች የሚኖሩ፦ አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ደግሞ ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ ሁሉም ወንድ የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአል፤ ታዲያ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በፍርስራሽ ስፍራዎች ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በሜዳ ያሉትን መብል እንዲሆን ለአራዊት እሰጠዋለሁ፥ በምሽጎችና በዋሻዎች ያሉት በቸነፈር ይሞታሉ። ምድሪቱን ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። በሰሩትም ርኩሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ በማደርግበት ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤቶቻቸው ደጃፍ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ አንዱ ከአንዱ ጋር፥ እያንዳንዱ ከወንድሙ ጋር እንዲህ ይላሉ፦ ኑ ከጌታ የመጣው ቃል ምን እንደሆነ እንስማ። ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ያልተገባ ጥቅማቸውን ይከተላልና። እነሆ አንተ እንደ ጥሩ ዘፈን፥ እንደ መልካም ድምፅ፥ እንደ ጎበዝ ተጫዋች ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። ይህም በመጣም ጊዜ፥ እነሆ ይመጣል! ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞቹንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለመገቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ማሰማራት አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ሱፉንም ትለብሳላችሁ፥ የሰቡትን ታርዳላችሁ፤ መንጋውን ግን አትጠብቁም። የደከሙትን አላበረታችሁም፥ የታመመውን አላከማችሁትም፥ የተሰበረውን አልጠገናችሁትም፥ የባዘነውን አልመለሳችሁትም፥ የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቆና ገዛችኋቸው። እረኛ ስለ ሌለ ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም የለም። ስለዚህ እረኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔም ሕያው ነኝና እረኛ ስለ ሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ እረኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእረኞች ላይ ነኝ፥ መንጋዎቼን ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ መንጋዎቼን ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያስማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልጋቸዋለሁም። እረኛ በተበተኑት መንጋዎቹ መካከል ሳለ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን፥ ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። ከሕዝቦች አወጣቸዋለሁ፥ ከአገሮች እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤል ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾች አጠገብ፥ በምድሪቱም መኖሪያ በሚሆኑ ስፍራዎች ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ ጋጣቸውም በእስራኤል ተራሮች ከፍታ ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጋጣ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጠፋውን እፈልጋለሁ፥ የባዘነውን እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን አጠፋለሁ፤ በፍትሕም እጠብቀዋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ። የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? መንጋዎቼ በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ እኔ በወፈረ በግና በከሳ በግ መካከል እፈርዳለሁ። ወደ ውጭ እስክትበትኑአቸው ድረስ በጎንና በትከሻ ስለምትገፉ፥ የደከሙትን ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባርያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። እኔም ጌታ፥ አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ባርያዬ ዳዊትም በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ። ከእነርሱ ጋር የሰላምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፥ ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ በሰላምም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናቦችም ይሆናሉ። የሜዳ ዛፍም ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም በሰላም ይኖራሉ፤ የቀንበራቸውንም ዘንግ ስሰብር ከሚገዙአቸውም እጅ ሳድናቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ከእንግዲህም ለሕዝቦች ብዝበዛ አይሆኑም፥ የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ የሚያስፈራቸውም አይኖርም። የታወቀ የተክል ቦታ አቆምላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ በምድሪቱ ላይ በረሃብ አይሰበሰቡም፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሕዝቦችን ስድብ አይሸከሙም። እኔ ጌታ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነዚያ የእስራኤል ቤትም ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ እንዲህም በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄን እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ። ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃለህ። የዘለዓለም ጥል ስላለህ በመጨረሻው የፍርዳቸው ጊዜ፥ በመከራቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና፥ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል። የሴይርን ተራራ ውድማና ባድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ። ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህ፥ በሸለቆዎችህና በውሃ መውረጃዎችህ ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ይወድቃሉ። ለዘለዓለም ባድማ አደርግሃለሁ፥ ከተሞችህም ሰው አይኖርባቸውም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ጌታ በዚያ ሳለ፥ አንተ ግን፦ “እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦችና እነዚህ ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን” ብለሃልና፥ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱን ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቁጣህና እንደ ቅናትህ መጠን አደርጋለሁ፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ መካከል ማንነቴን አስታውቃለሁ። በእስራኤል ተራሮች ላይ “ፈርሰዋል እንድንበላቸው ለእኛ ተሰጥተዋል” ብለህ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ ጌታ እንደ ሰማሁት ታውቃለህ። በአፋችሁ ታበያችሁብኝ፥ ንግግራችሁንም በእኔ ላይ አበዛችሁ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ስትደሰት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በመሆኑ እንደተደሰትህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተ፥ ኤዶም ሁሉና ሁለንተናዋ ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠላት በእናንተ ላይ፦ “እሰይ! የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል” ብሏልና፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰላጠፉአችሁ፥ ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችኋልምና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የሕዝብ ማላገጫ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለውሃ መውረጃዎችና ለሸለቆዎች፥ ለፈራረሱ ቦታዎችና ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት ሕዝቦች ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፤ ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለውሃ መውረጃዎችና ለሸለቆች እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ የሕዝቦችን ስድብ ተሸከማችሁአልና፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች በእርግጥ ስድባቸውን ይሸከማሉ ብዬ እጄን አንስቻለሁ ። እናንተም የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ ቅርንጫፎችን ታቆጠቁጣላችሁ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ ለመምጣት ቀርበዋልና። እነሆ እኔ ለእናንተ ነኝና፥ ወደ እናንተ እመለሳለሁ ፥ ትታረሳላችሁ ትዘራላችሁም፤ የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሙሉን በእናንተ ላይ አበዛለሁ፥ በከተሞቹም ሰዎች ይኖሩባቸዋል፥ የፈረሱት ስፍራዎችም ይሠራሉ፤ ሰውንና እንስሳም በእናንተ ላይ አበዛለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈራሉም፤ እንደ ቀድሞም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ መጀመሪያ ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ሰዎችን፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ፦ ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና ስለዚህ ዳግመኛ ሰው አትበይም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸው በፊቴ እንደ አደፍ ነበረ። በምድር ላይ ባፈሰሱት ደምና በጣዖቶቻቸውም አርክሰዋታልና መዓቴን አፈሰስሁባቸው። ወደ መንግሥታት በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፤ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። ወደ ሄዱባቸውም ወደ ሕዝቦች በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ የጌታ ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ለቅዱስ ስሜ እራራለሁ ። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ የምሠራው ስለ እናንተ ሳይሆን በሄዳችሁባቸው በመንግሥታት መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው። በመንግሥታት መካከል የረከሰውን፥ በመካከላቸው እናንተ ያረከሳችሁትን ታላቁን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ ዓይናቸው እያየ በእናንተ በተቀደስሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ መንግሥታት ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከመንግሥታት መካከል አወጣችኋለሁ፥ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። በእናንተ ላይ ንጹሕ ውኃ እረጫለሁ እናንተም ትነጻላችሁ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ። አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋያማ ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ በትእዛዜ እንድትሄዱና ፍርዴን እንድትጠብቁ አደርጋችኋለሁ ትፈጽሟቸዋላችሁም። ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራዋለሁ አበዛዋለሁም፥ ረኃብም አላመጣባችሁም። የረኃብን ስድብ ዳግም ከመንግሥታት እንዳትቀበሉ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ምርት አበዛለሁ። ክፉዎች መንገዶቻችሁንና መልካም ያልሆኑ ሥራዎቻችሁን ታስባላችሁ፥ ስለ በደሎቻችሁና ስለ ርኩሰቶቻችሁም ራሳችሁን ትጠላላችሁ። ይህንን የሠራሁት ለእናንተ እንዳልሆና በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። በአላፊ አግዳሚው ሁሉ ዐይን ባድማ የነበረች፥ ባድማዋ ምድር ትታረሳለች። “ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆነች፤ የወደሙት፥ ባድማ የሆኑት፥ የፈረሱት ከተሞች አጥር ተሰርቶላቸዋል፥ መኖሪያም ሆነዋል” ይላሉ። በዙሪያችሁም የቀሩት መንግሥታት፥ የፈረሱትን ስፍራዎች የሠራሁ፥ ባድማ የሆነውንም የተከልሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁንም የእስራኤል ቤት እንድሠራላቸው እንዲፈልጉኝ እፈቅድላቸዋለሁ፥ ሰዎችንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ። እንደ ተቀደሰ መንጋ፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም መንጋ፥ እንዲሁም የፈረሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ እጅ በላዬ ነበረ፥ ጌታም በመንፈሱ አወጣኝ፥ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ እሱም አጥንቶች ሞልተውበት ነበር። በእነርሱ ላይ በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፤ እነሆም፥ በጣም የደረቁ ነበሩ። እንዲህም አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” እኔም “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የጌታን ቃል ሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእናንተ ላይ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ። ጅማትንም አደርግላችኋለሁ፥ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ ቆዳ አለብሳችኋለሁ፥ በውስጣችሁ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢትንም ስናገር እነሆ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ነበር፥ አጥንት ከአጥንቱ ጋር እየሆነ አጥንቶች አንድ ላይ ሆኑ። እኔም አየሁ፥ እነሆ ጅማትና ሥጋ ነበረባቸው፥ ቆዳም ከላይ እስከ ታች ሸፈናቸው፥ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። እንዲህም አለኝ፦ “ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር የሰው ልጅ ሆይ፥ ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ በሕይወት እንዲኖሩ በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’” እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ እስትንፋስም በውስጣቸው ገባ፥ ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግ በጣም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እነሆ፦ “አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል፤ ፈጽመን ተቆርጠናል” ይላሉ። ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፥ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣችኋለሁ። ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን ስከፍት ከመቃብራችሁም ሳወጣችሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ፥ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ለራስህ ውሰድ፥ በላዩ “ለይሁዳና ለተባባሪዎቹ የእስራኤል ልጆች” ብለህ ጻፍበት፤ ሌላም በትር ውሰድ፦ በላዩም “የኤፍሬም በትር ለሆነው ለዮሴፍና ለተባባሪዎቹ፥ ለመላው የእስራኤል ቤት” ብለህ ጻፍበት። በእጅህ ውስጥ አንድ በትር እንዲሆኑ አንዱ ከአንዱ ጋር አጋጥመህ ያዛቸው። የሕዝብህ ልጆች፦ “እነዚህ ለአንተ ምን እንደ ሆኑ አትነግረንምን?” ሲሉህ፥ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በኤፍሬም እጅና በተባባሪዎቹ በእስራኤል ነገዶች ያለውን የዮሴፍን በትር እወስዳለሁ፥ ከይሁዳ በትር ጋር አስቀምጣቸዋለሁ፥ አንድ በትር አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም አንድ ይሆናሉ። በላያቸው የምትጽፍባቸው በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ይሆናሉ። አንተም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል እወስዳለሁ፥ ከየስፍራውም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥ ለሁሉም ንጉሥ ይሆናል፤ ዳግመኛ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይከፈሉም። በጣዖቶቻቸው፥ በአጸያፊ ነገሮቻቸውና በመተላለፋቸው ሁሉ ዳግመኛ አይረክሱም፤ ኃጢአት ከሠሩባቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው ሁሉ አድናቸዋለሁ፥ አነጻቸዋለሁም፤ እነርሱ ለእኔ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። አገልጋዬ ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ በፍርዴ ይሄዳሉ፥ ትእዛዜን ይጠብቃሉ ይፈጽሟቸዋልም። ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት፥ አባቶቻችሁም በኖሩባት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱ፥ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘለዓለም በእርሷ ይኖራሉ፤ አገልጋዬ ዳዊት ለዘለዓለም ልዑላቸው ይሆናል። የሰላም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ አጸናቸዋለሁ፥ አበዛቸዋለሁ፥ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘለዓለም አኖራለሁ። ማደሪያዬ በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፥ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። መቅደሴም ለዘለዓለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እስራኤልን የቀደስኩ እኔ ጌታ እንደሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የማጎግ ምድር፥ በሮሽ፥ በሜሼኽና በቱባል ላይ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ጎግ ፊትህን አቅና፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮሽ፥ የሜሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ እኔ በአንተ ላይ ነኝ። ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፥ መንጠቆ በመንጋጋህ አስገባሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህን ሁሉ፥ ፈረሶችን፥ ፈረሰኞችን፥ የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ሁሉም ሰይፍ የያዙ ጋሻና ራስ ቁርን ካደረጉ ታላቅ ጉባኤ ጋር አወጣሃለሁ፥ ሁሉም ጋሻና የራስ ቁር የለበሱ ፋርስ፥ ኢትዮጵያና ፉጥም ከእነርሱ ጋር። ጎሜርንና ሠራዊቱ ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻ ያለው የቶጋርማ ቤትና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝቦችም ከአንተ ጋር አወጣለሁ። ተዘጋጅ፥ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ጉባኤ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ጠባቂ ሁናቸው። ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘለዓለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርሷም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል። አንተም ወደ ላይ ትወጣለህ፥ እንደ ማዕበል ትመጣለህ፤ አንተና ሠራዊትህ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝብም ከአንተ ጋር ሆነው ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይመጣል፥ ክፉ ሐሳብንም ታስባለህ፤ እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ያለ ሥጋት በሰላም ወደሚኖሩ፥ ሁሉም ሳይፈሩ ያለ ቅጥር፥ ያለ መወርወሪያና ያለ በር ወደሚቀመጡ እሄዳለሁ፤ ምርኮን ልትማርክ፥ ብዝበዛን ልትበዘብዝ፤ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ። ሳባ፥ ድዳን፥ የተርሴስ ነጋዴዎች፥ መንገዶችዋም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ጎግንም እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በተቀመጠ ጊዜ በዚያ ቀን አንተ አታውቀውምን? በስተ ሰሜን ርቆ ከሚገኘው ስፍራህ አንተ፥ ከአንተም ጋር ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ ብዙ ሕዝብ፥ ታላቅ ጉባኤና ብርቱ ሠራዊት ጋር ሆነህ ትመጣለህ። ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፥ በአንተ በኩል ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ፥ አሕዛብ እንዲያውቁኝ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ፥ ለብዙ ዓመት በተነበዩ በአገልጋዮቼ በእስራኤል ነቢያት እጅ በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ፥ ቁጣዬ ከፊቴ ይወጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በቅንዓቴና በቁጣዬ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ የባሕር ዓሣዎች፥ የሰማይ ወፎች፥ የምድር አራዊት፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮች ይገለባበጣሉ፥ ገደሎች ይወድቃሉ፥ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። በተራሮቼ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍና የበረዶ ድንጋይ፥ እሳትና ዲን በእርሱና በወታደሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉት ብዙ ሕዝቦች ላይ አዘንባለሁ። ታላቅ እሆናለሁ፥ እቀደሳለሁም፥ በብዙ አሕዛብ ዐይን የታወቅሁ እሆናለሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ አሁንም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ እመልስሃለሁ፥ እመራሃለሁ፥ ከሰሜን ዳርቻ አወጣሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች እወስድሃለሁ። ቀስትህን ከግራ እጅህ እመታለሁ፥ ፍላጻዎችህንም ከቀኝ እጅህ አስጥልሃለሁ። አንተ፥ ወታደሮችህና ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። አንተ በሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በማጎግ እና ያለ ስጋት በደሴቶች በሚቀመጡት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ እንዲሰደብ አልፈቅድም፤ አሕዛብም በእስራኤል ያለሁ ቅዱስ ጌታ እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነሆ፥ ይመጣል ይሆናልም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው። በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ወጥተው፥ የጦር መሣሪያዎችን፥ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትና ፍላጻዎችን፥ የእጅ በትሮችንና ጦርንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከሜዳ አይሸከሙም፥ ከዱርም አይቆርጡም፤ የዘረፉአቸውን ይዘርፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በዚያም ቀን በእስራኤል፥ በባሕሩ በምሥራቅ በኩል ባለው በመንገደኞች ሸለቆ ለጎግ የመቃብር ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ስለሚቀበሩ፥ የመንገደኞች መተላለፊያ ይዘጋል፤ “የሐሞን-ጎግ ሸለቆ” ተብሎ ይጠራል። የእስራኤል ቤት ምድሪቱን ለማጽዳት ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሩአቸዋል ። የምድሪቱ ሕዝቦች ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፤ በምከበርበት ቀን፥ ለሥም ይሆንላቸዋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ምድሪቱን ለማጽዳት በምድሪቱ ላይ ዘወትር የሚመላለሱና በምድር ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ ሰዎችን ይለያሉ፤ ከሰባቱ ወር በኋላ ፍለጋ ይጀምራሉ። በምድርም የሚመላለሱት ሲያልፉ የሰው አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ በአጠገቡ ምልክት ያኖሩበታል። ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። ምድሪቱንም ያጸዳሉ። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ፥ ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕቴ፥ ወደ ታላቁ መሥዋዕት ከየስፍራው ተሰብሰቡ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ደምንም ትጠጣላችሁ። የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ፥ የምድር አለቆችን፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሻንን ፍሪዳዎች ሁሉ ደም ትጠጣላችሁ። እኔ በማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ፥ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። በማእዴ ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ክብሬን ለአሕዛብ እሰጣለሁ፥ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን እና በላያቸው ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። ከዚያች ቀን ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ። የእስራኤል ቤት በበደላቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ አሕዛብ ያውቃሉ፤ እኔን ስለ በደሉኝ፥ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። እንደ ርኩሰታቸውና እንደ መተላለፋቸው መጠን አደርግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው በሰላም በተቀመጡ ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ይሸከማሉ። ይህም የሚሆነው ከአሕዛብ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በእነሱ በተቀደስሁ ጊዜ ነው። እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ በአሕዛብ እንዲማረኩ አድርጌአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና፥ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አላስቀርም። ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሰውርም፥ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በተሰደድን በሀያ አምስተኛው ዓመት፥ በዓመቱ መጀመሪያ፥ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ በተመታች በዓሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረ፥ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፥ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም በደቡብ በኩል ከተማ የሚመስል ሕንፃ ነበረ። ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆ፥ መልኩ ናስ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ይዞ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። ሰውዬውም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓይንህ እይ፥ በጆሮህም ስማ፥ የማሳይህን ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል፥ ይህን እንዳሳይህ ወደዚህ ተመርተሃልና የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።” እነሆ፥ በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ ያለው የመለኪያው ዘንግ ርዝመት አንድ ክንድ ከስንዝር የሆነ ስድስት ክንድ ነበረ፤ ቅጥሩንም ለካ፥ ስፋቱ አንድ ዘንግ፥ ቁመቱም አንድ ዘንግ ነበር። ፊቱ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በር መጣ፥ በደረጃዎቹም ወጥቶ በበሩ በኩል ያለውን የቤቱን መግቢያ ወለል ወርዱን ለካ አንድ ዘንግ ነበር፥ የሌላኛውም የቤቱ መግቢያ ወለል ወርድ አንድ ዘንግ ነበር። ክፍሉም ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በክፍሎቹ መካከል ያለው ርቀት አምስት ክንድ ነበረ፤ ከበራፉም በውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ መተላለፊያ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ። በውስጥ ያለውን የበሩን መተላለፊያ ለካ አንድ ዘንግ ነበር። የበሩን መተላለፊያ ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም መተላለፊያ በውስጥ በኩል ነበረ። የምሥራቁ በር ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያ በኩል ደግሞ ሦስት ነበሩ፥ ሦስቱም እኩል ስፋት ነበራቸው፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል እኩል ነበረ። የበሩን መግቢያ ወርድ ዐሥር ክንድ፥ የበሩን ርዝመት ዐሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ። በጓዳዎቹም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ ጓዳውም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበረ። ከአንዱ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩ ወርድ ሀያ አምስት ክንድ ሆነ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ። መተላለፊያውን ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም መተላለፊያ ዙሪያ አደባባይ ነበረ። ከበሩ መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ መተላለፊያ መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ። ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ ትናንሽ መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ደግሞም በመተላለፊያው ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። ከዚያም ወደ ውጪው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ። በበሮቹ አጠገብ የነበረው ወለል ርዝመት እንደ በሮቹ መጠን ነበረ፤ ይህም ታችኛው ወለል ነበረ። ከታችኛው በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከተውን በር ርዝመትና ወርዱን ለካ። ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ እንደ ፊተኛው በር መጠናቸው እኩል ነበር፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበር። መስኮቶቹ፥ መተላለፊያዎቹና የዘንባባ ዛፎቹ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር ካሉት ጋር መጠናቸው እኩል ነበር። ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ። በምሥራቁ በር እንዳለው ዓይነት በሰሜኑ በር ትይዩ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ በር ነበር፤ ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ደቡብ መራኝ፥ እነሆ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መተላለፊያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። ከሌሎቹም ጋር እኩል መጠን ነበራቸው። በእርሱና በመተላለፊያዎቹም ዙሪያ ሌሎቹን መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። በውስጠኛው አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ በደቡብ በኩልም ከበር እስከ በር ድረስ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። በደቡብ በር በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የደቡብንም በር ለካ፤ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበረው። ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። በዙሪያውም መተላለፊያዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበረ። መተላለፊያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤ ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። መተላለፊያዎቹም ወደ ውጪው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እርሱንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤ ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። የግንቡ አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡ አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። በበሮቹ መተላለፊያ አጠገብ በር ያለው ዕቃ ቤት ነበረ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር። የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የበደሉን መሥዋዕት እንዲያርዱባቸው፥ በበሩ መተላለፊያ በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ። ከመተላለፊያው በስተ ውጭ በሰሜን በኩል ባለው በር መግቢያ አጠገብ፥ ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በበሩ መተላለፊያ በሌላኛው ወገን በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ። በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ። ለሚቃጠለው መሥዋዕት ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመታቸው ደግሞ አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት የሚያርዱበትን ዕቃዎች የሚያስቀምጡባቸው፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። በቤቱም ዙሪያ አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ተደርጎላቸው ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቀመጥባቸው ነበር። በውስጠኛው መግቢያ በውጭው በኩል በውስጠኛው አደባባይ ለሚዘምሩ ዕቃ ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ደቡብም ይመለከት ነበር፤ ሌላው ደግሞ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር። እንዲህም አለኝ፦ “ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ቤቱን ለሚጠብቁ ካህናት ነው፥ ወደ ሰሜን የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለሚጠብቁ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል እንዲያገለግሉት ወደ ጌታ የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው።” አደባባዩንም ለካ፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ወርዱም መቶ ክንድ አራት ማዕዘን ነበር፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ። ወደ ቤቱም መተላለፊያ አገባኝ፥ የመተላለፊያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበረ፤ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። የመተላለፊያው ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ወርዱ ደግሞ ዐሥራ አንድ ክንድ ነበረ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድ በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ። ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የድንኳኑን አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያው ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያው መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያ ወገን ደግሞ አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱን አርባ ክንድ ወርዱን ደግሞ ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገብቶ የመግቢያውን ዓምድ ወርድ ሁለት ክንድ፥ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱ ፊት ያለውን ርዝመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና፦ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። የቤቱን ግንብ ስድስት ክንድ፥ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ ሆነው የተሠሩ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ላይ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በቤቱ ግንብ ውስጥ የተደገፉ ስላልነበሩ፥ ቤቱ በዙሪያው ላሉት ጓዳዎች ያለው ግንብ ውስጥ እንዲደገፉ ግንቡ ውስጥ ገቡ። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ቤቱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በቤቱ ጓዳዎች አጠገብ የቀረ ባዶ ስፍራ ነበረ። በቤቱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ በጓዳዎቹ መካከል ባዶ ስፍራ ነበረ። የጓዳዎቹም መግቢያ በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል ነበረ፤ የባዶውም ስፍራ ወርድ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበረ። በባሕር መንገድ በኩል በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረው ሕንጻ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። የሕንጻው ግንብ ዙሪያ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነበረ። ቤቱንም ለካው፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ሆነ፥ የተለየው ስፍራ፥ ሕንጻውና ግንቡ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የቤቱና በምሥራቅ በኩል የነበረው የተለየው ስፍራ ስፋት አንድ መቶ ክንድ ሆነ። ወደ ኋላውም ባለው በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረውን የሕንጻውን ርዝመት በዚህና በዚያ የነበሩትን መተላለፊያዎች ጨምሮ ለካ፥ አንድ መቶ ክንድ ነበር። የቤተ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል፥ የአደባባዩ መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያዎች፥ ጠባቦቹ መስኮቶች፥ በዙሪያቸው የነበሩ ሦስት መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያ ዙሪያውን ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የተሸፈኑ ነበሩ፤ ከበሩ በላይ እስከ ውስጠኛው ቤት ድረስ፥ በዙሪያውም የነበረው ግንብ ሁሉ ውጭውም ውስጡም ተለካ። በኪሩቤልና በዘንባባ ዛፎች የተሠራ ነበር፤ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የዘንባባ ዛፍ ነበረ፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት። የሰው ፊት በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፥ የአንበሳ ፊት ደግሞ በሌላው ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ መግቢያው ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱም ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የተቀደሰው ሥፍራም የፊት ለፊት ገፅታው እንዲሁ ነበረ። ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ነበር፥ ማዕዘኖቹ፥ እግሩና ግድግዳው ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ እርሱም፦ “ይህ በጌታ ፊት ያለ ገበታ ነው” አለኝ። መቅደሱና የተቀደሰው ስፍራ ሁለት በሮች ነበሩአቸው። እያንዳንዱ በር ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ አንዱ በር ሁለት ሌላውም በር ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በእነርሱም ላይ፥ በመቅደሱ በሮች ላይ በግንቡ ላይ እንደተቀረጸው ዓይነት ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በውጭ ባለው መተላለፊያ ፊት ወፍራም እንጨት ነበረ። በመተላለፊያው በዚህና በዚያ ወገን ጠባብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎች ወፍራም ነበሩ። በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጪው አደባባይ አወጣኝ፥ በተለየው ስፍራ ፊት ለፊት፥ በሰሜን በኩል ባለው ህንጻ ፊት ለፊት ወዳለው ክፍል አገባኝ። በሰሜን በኩል ያለው መግቢያ ርዝመት መቶ ክንድ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ። በውስጠኛው አደባባይ በሀያው ክንድ ፊት ለፊት በውጭውም አደባባይ በወለሉ ፊት ለፊት በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ። ከክፍሎቹም ፊት ለፊት በውስጥ በኩል ወርዱ ዐሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መግቢያዎቹም በሰሜን በኩል ነበሩ። መተላለፊያው አሳጥሮአቸዋልና የላይኞቹ ክፍሎች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ። በሦስት ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩአቸውም፥ ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ። በክፍሎቹ ትይዩ በውጭ ያለው ቅጥር፥ በክፍሎቹ ፊት ለፊት ያለው የውጭው አደባባይ ርዝመት አምሳ ክንድ ነበረ። በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ክፍሎች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ሲሆን በመቅደሱ ፊት ለፊት የነበሩት ክፍሎች ግን ርዝመታቸው መቶ ክንድ ነበረ። ከእነዚህም ክፍሎች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባባት መግቢያ ነበረ። በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ግንብ ርዝመት፥ በተለየው ስፍራና በሕንጻው ፊት ለፊት ክፍሎች ነበሩ። በፊታቸው የነበረው መንገድም በሰሜን በኩል ያሉትን ክፍሎች ይመስል ነበር። ርዝመታቸውም፥ ወርዳቸውም፥ መውጫቸውም አቀማመጣቸውና መግቢያዎቻቸውም ተመሳሳይ ነበር። በደቡብም በኩል ካሉት ክፍሎች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ። እንዲህም አለኝ፦ በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ ጌታ የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቁርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ። ካህናቱም ከገቡ በኋላ የሚያገለግሉበትን ልብስ ሳያወልቁ ከመቅደሱ ወደ ውጭው አደባባይ አይወጡም፥ የተቀደሱ ናቸውና፤ ወደ ሕዝቡ ቦታ ሲቀርቡ ሌላ ልብስ መልበስ አለባቸው። ውስጠኛውን ቤት ለክቶ ሲጨርስ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ፥ ዙሪያውን ሁሉ ለካ። በምሥራቅ አቅጣጫ ያለውን በመለኪያ ዘንግ ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። በሰሜን አቅጣጫ ያለውን ለካ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። በደቡብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። በምዕራብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ። በአራቱ አቅጣጫ ለካ፤ የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ለመለየት ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ። ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በር አመጣኝ። እነሆ፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከወደ ምሥራቅ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ድምጽ ነበር፥ ከክብሩ የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። የጌታ ክብር በሩ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው ቤት ገባ። መንፈስም አነሣኝ፥ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አስገባኝ፤ እነሆ፥ የጌታ ክብር ቤቱን ሞላው። ከቤቱ ውስጥ ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘለዓለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ ማሳረፊያ ይህ ነው። የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በዝሙታቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ዳግመኛ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም። መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውን በመቃኔ አጠገብ በማድረጋቸው፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ግንብ ብቻ ቀረ፥ በሠሩት ርኩሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፥ ስለዚህ በቁጣዬ አጠፋኋቸው። አሁንም ዝሙታቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘለዓለም በመካከላቸው እኖራለሁ። አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ በኃጢአታቸው እንዲያፍሩ ለእስራኤል ቤት ስለ ቤቱ ንገራቸው፥ ንድፉንም ይለኩ። በሠሩት ሥራ ሁሉ የሚያፍሩ ከሆነ፥ የቤቱን ንድፉንና አሠራሩን፥ መውጫውንና መግቢያውን፥ አጠቃላይ ንድፉን፥ ሥርዓቱን ሁሉ፥ ንድፉን ሁሉ፥ ሕጉን ሁሉ አሳውቃቸው፤ ንድፉን ሁሉና ሥርዓቱን ሁሉ እንዲያዩትና እንዲያደርጉትም በፊታቸው ጻፈው። የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ በዙሪያው ያለው ስፍራ ሁሉ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው። የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፤ ክንዱም አንድ ክንድ ከስንዝር ነው። መሠረቱ ቁመቱ አንድ ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ ዙሪያውም አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ ይህም የመሠዊያው ከፍታ ነው። መሬት ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹ እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው። የመሠዊያው ምድጃው አራት ክንድ ነው፤ ከመሠዊያው ምድጃ በላይ አራት ቀንዶች አሉ። የመሠዊያው ምድጃ ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው። የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ጠርዝ ግማሽ ክንድ ነው፥ የመሠረቱም ዙሪያ አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹ ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መሠዊያው ተሰርቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በላዩ በሚያቀርቡበት ደምንም በላዩ በሚረጩበት ቀን የመሠዊያው ሥርዓት ይህ ነው። ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ለካህናት፥ ከሳዶቅ ዘር ለሆኑ ለሌዋውያን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከደሙ ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹ፥ በእርከኑ፥ በአራቱ ማዕዘን ላይ፥ በዙሪያውም ባለው ጠርዝ ላይ ታደርጋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታጠራዋለህም። ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ ከመቅደሱ ውጭ ባለው ቤት በተወሰነው ስፍራ ይቃጠላል። በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል። ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈንና ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ። በጌታ ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም በላያቸው ላይ ጨው ይነስንሱባቸው፥ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡአቸዋል። ሰባት ቀን በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውር የሌለባቸውን ከመንጋው አንድ ወይፈን ከመንጋው አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ። ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹታልም፥ እጃቸውን ይሞላሉ። ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀንና ከዚያም በኋላ፥ ካህናቱ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና የሰላም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል፤ አይከፈትምም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል። መስፍኑ ብቻ በጌታ ፊት ምግብ ለመብላት ይቀመጥበታል፤ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል። በሰሜኑ በር መንገድ ወደ ቤቱ ፊት ለፊት አገባኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆ የጌታ ክብር የጌታን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጌታ ቤት ሥርዓት ሁሉ እና ሕጉን ሁሉ የምናገርህን ሁሉ ልብ አድርግ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱን መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ። ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ርኩሰታችሁ ከእንግዲህ ሁሉ ያብቃ፥ ምግቤን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ ቤቴን እንዲያረክሱ በመቅደሴ ውስጥ እንዲሆኑ ያልተገረዘ ልብ፥ ያልተገረዘ ሥጋ ያላቸውን ባዕዳንን አግብታችኋል፥ በርኩሰታችሁም ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል። በመቅደሴ ውስጥ ሥርዓቴን ጠባቂዎች ለራሳችሁ አስቀመጣችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ያለ የባዕድ ልጅ ሁሉ፥ ልቡ ያልተገረዘ ሥጋው ያልተገረዘ የባዕድ ልጅ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ። እስራኤል እኔን ከመከተል ርቀው በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ የራቁት ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች፥ በቤቱም በሮች ዘበኞች ይሆናሉ፥ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መሥዋዕትን ያርዳሉ፥ ሊያገለግሉአቸውም በፊታቸው ይቆማሉ። በጣዖቶቻቸው ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በክህነት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደተቀደሰው ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አይቀርቡም፤ ስድባቸውንና የሠሩትን ርኩሰታቸውን ይሸከማሉ። ሆኖም ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ። የእስራኤል ልጆች ከእኔ በራቁ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙን ወደ እኔ ሊያቀርቡ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ወደ መቅደሴም ይገባሉ እኔን ለማገልገል ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴን ይጠብቃሉ። ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ አንዳች የበግ ጠጉር በላያቸው አይሁን። በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያልብ ነገር አይታጠቁ። ወደ ውጭው አደባባይ ወደ ሕዝቡ በሚወጡበት ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ፥ በተቀደሰው ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላ ልብስ ይልበሱ። ራሳቸውን አይላጩ፥ የተያዘ ጠጉራቸውንም አይልቀቁትም፥ ነገር ግን የራሳቸውን ጠጉር ይከርከሙ። ካህናቱ ሁሉ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጡ። መበለቲቱንና የተፈታችውን ለሚስትነት አይውሰዱ፤ነገር ግን ከእስራኤል ቤት ዘር የሆነችውን ድንግል ወይም የካህን ሚስት የነበረችውን መበለት ይውሰዱ። ሕዝቤን ቅዱስ በሆነውና በረከሰው መካከል እንዲለዩ ያስተምሩ፥ ንጹሕ በሆነውና ንጹሕ ባልሆነው መካከል እንዲለዩ ያሳዩአቸው። ክርክር በሚነሣበት ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ በፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ። እንዳይረክሱ ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላላገባች እኅት ይርከሱ። ከነጻ በኋላ ሰባት ቀን ይቁጠሩለት። በመቅደስም ውስጥ ሊያገለግል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ርስት ይሆንላቸዋል፤ ርስታቸው እኔ ነኝ፤ በእስራኤልም ግዛት አትስጡአቸው፤ ግዛታቸው እኔ ነኝ። የእህሉን ቁርባን፥ የኃጢአትን መሥዋዕትና የበደልን መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል። የበኩራቱ ሁሉ መጀመሪያ፥ ስጦታ ሁሉ፥ ስጦታዎቻችሁ ሁሉ፥ ለካህናት ይሆናል፤ በቤትህም ውስጥ በረከት እንዲያድር የሊጣችሁን በኵራት ለካህን ትሰጣላችሁ። ካህናቱ የሞተ ወይም ሌላ አውሬ የገደለውን ወፍ ወይም እንስሳ አይብሉ። ርስት አድርጋችሁ ምድሪቱን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድሪቱ የተቀደሰውን ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ ጌታ ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ በዳርቻው ዙሪያ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል። ከዚህም አምስት መቶ በአምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፤ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል። በዚያው ክልል ደግሞ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል። ከምድሪቱም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ ጌታን ሊያገለግሉ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፥ ስፍራውም ለቤቶቻቸው መስሪያና ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ሃያ ቤቶችም ለእነርሱ ርስት ይሆናሉ። ለከተማይቱ ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል። ለአለቃውም የሚሆነው የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በጎንና በጎን ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። ይህም ከምድሪቱ በእስራኤል ዘንድ ርስት ይሆንለታል፥ መሪዎቼ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም፥ ነገር ግን ምድሪቱን ለእስራኤል ቤት እንደ ነገዳቸው ይሰጡአቸዋል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል መሪዎች ሆይ፥ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ጭቆናን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አንሱ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እውነተኛ ሚዛን እውነተኛ የኢፍ መስፈሪያና እውነተኛው የባዶስ መስፈሪያ ይኑራችሁ። የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ ይሁን። መለኪያው የቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። አንድ ሰቅል ሀያ ጌራህ ይሆናል፤ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል እና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር፥ አንድ ምናን ይሁንላችሁ። የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ትሰጣላችሁ። የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አንድ አሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፤ ዐሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና። ውኃም ካለበት ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለት መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፤ ይህ እንዲያስተሰርይላችሁ እህል ቁርባን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለሰላም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል መሪ ይሰጣሉ። በየበዓላቱ፥ በየመባቻው፥ በየሰንበታቱ፥ በእስራኤል ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን፥ የመጠጡን መሥዋዕት ማቅረብ በመስፍኑ ላይ ይሆናል፤ እርሱ ለእስራኤል ቤት ሊያስተሰርይ የኃጢአቱን መሥዋዕትና ስጦታውን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቀርባል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፥ መቅደሱንም አንጻ። ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ የቤቱን መቃኖችና የመሠዊያው ጠርዝ በአራቱ ማዕዘን፥ የውስጠኛውም አደባባይ የበሩን መቃኖች ይቀባ። ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፥ ይኸውም ስለሚስተውና ስለየዋሁ ነው። እንዲሁም ስለ ቤቱም አስተስርዩ። በመጀመሪውያ ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታከብራላችሁ። እስከ ሰባት ቀን ድረስ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትበላላችሁ። በዚያም ቀን መስፍኑ ለራሱና ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቀርባል። በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች በሰባቱም ቀኖች ለጌታ ያቅርብ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። ለአንድ ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአንድ አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን፥ ለአንድ የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። በሰባተኛው ወር ከወሩም በዓሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ እንደ እነዚህ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱ መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉን ቁርባንና ዘይቱን ያቅርብ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውስጠኛው አደባባይ ፊቱ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ይዘጋ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀን ይከፈት እንዲሁም በወር መባቻ ቀን ይከፈት። መስፍኑ ከውጭ በኩል ባለው በር በመተላለፊያ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፥ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ። የምድሪቱ ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በሰንበታትና በመባቻ በጌታ ፊት ይስገዱ። መስፍኑ በሰንበት ቀን ለጌታ የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለእያንዳንዱም ጠቦት እጁ የሰጠችውን ያህል የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። በመባቻ ቀን ከመንጋው ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአውራው በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ያቅርብ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የቻለችውን ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። መስፍኑ በሚገባበት ጊዜ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይግባ በዚያው መንገድ ይውጣ። የምድሪቱ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ ጌታ ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፥ በደቡብ በር የገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ባለው ይውጣ እንጂ በገባበት በር አይመለስ። በመካከላቸው ያለው መስፍን በሚገቡበት ጊዜ ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ። በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቁርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የሰጠችውን ያህል፥ ለኢፍ መስፈሪያም አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል። መስፍኑ በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም የሰላሙን መሥዋዕት፥ በፈቃዱ ለጌታ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፥ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይውጣ፥ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ። በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ለጌታ ያቅርብ፤ ማለዳ ማለዳም ያቅርበው። ከእርሱም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄትን መለወሻም የሚሆን በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት ማለዳ ማለዳ የእህልን ቁርባን ያቅርብ፤ ይህ የእህል ቁርባን ዘወትር ለጌታ የሚቀርብ ለዘለዓለሙ ሥርዓት ይሁን። እንዲሁም ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱን፥ የእህሉን ቁርባንና ዘይቱን ማለዳ ማለዳ አቅርቡ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መስፍኑ ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ በውርስም ይዞታቸው ይሆናል። ነገር ግን ከባርያዎቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነጻነት ዓመት ድረሰ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለመስፍኑ ይመለስለት፤ ርስቱ ለልጆቹ ብቻ ይሁን። መስፍኑ ሕዝቡን ከይዞታቸው ሊጨቁናቸው ርስታቸውን አይውሰድባቸው፤ ሕዝቤ ሁሉ ከይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆቹ ርስትን ይስጥ። በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደተቀደሰው ክፍል አገባኝ፤ እነሆ በዚያ በምዕራብ በኩል በስተ ኋላ አንድ ስፍራ ነበረ። እንዲህም አለኝ፦ “ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳያወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፥ የእህሉንም ቁርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው።” ወደ ውጭው አደባባይ አወጣኝ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆ በእያንዳንዱ የአደባባይ ማዕዘን አደባባይ ነበረ። በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በአራቱም ማዕዘን ያሉት እኩል ነበሩ። በአራቱም ዙሪያ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ። እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።” ወደ ቤቱ መግቢያ መለሰኝ፤ እነሆ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። በሰሜኑ በር በኩል አወጣኝ፤ በውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በውጭ ወዳለው በር አመጣኝ፤ እነሆ ውኃው በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር። ሰውዬው ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ፥ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ቁርጫምጭሚት ድረስ ነበር። እንደገና አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ጉልበት ድረስ ነበር። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ድረስ ነበር። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? መራኝ፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ። በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። እንዲህም አለኝ፦ ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ አውራጃ ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል። ወንዙ በሚገባበት ስፍራ ያለ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ ይህ ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ የባሕሩ ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙ በሚገባበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል። ከዔንጌዲ ጀምሮ እስከ ዔንዔግላይም ድረስ አጥማጆች በዚያ ይቆማሉ፤ የመረቦች መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ። ረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን አይፈወስም፤ ጨው እንደሆነ ይኖራል። በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉ አይረግፍም ፍሬውም አያልቅም፤ ውኃው ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኩር ያፈራል፤ ፍሬው ለመብል ቅጠሉም ለፈውስ ይሆናል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ርስት አድርጋችሁ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት ድርሻ ይሆናል። እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት፤ ለአባቶቻችሁ ልሰጣቸው ምዬ ነበር፥ ይህች ምድር በርስትነት ለእናንተ ሆናለች። የምድሪቱ ድንበር ይህ ነው፤ በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጼዳድ መግቢያ፥ ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን፥ ድንበሩ ከባሕሩ ጀምሮ እስከ የደማስቆ ድንበር ሰሜን የሆነው ሐጻርዔኖን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። ይህም የሰሜኑ ድንበር ነው። የምሥራቁ ድንበር በሐውራንና በደማስቆ፤ በገለዓድና በእስራኤልም ምድር መካከል እስከ ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ፤ ይህም የምሥራቁ ድንበር ነው። የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ፥ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ይህም የደቡቡ ድንበር ነው። የምዕራቡ ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። ይህም የምዕራቡ ድንበር ነው። ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ትከፋፈላላችሁ። ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆች ለወለዱ ስደተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ። ስደተኛው በተቀመጠበት ነገድ በዚያ ርስቱን ስጡት፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የነገዶቹ ስም ይህ ነው። ከሰሜን ወሰን በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዳን ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ አሴር አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከአሴር ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ንፍታሌም አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ምናሴ አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከምናሴ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ኤፍሬም አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከኤፍሬም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ሮቤል አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከሮቤል ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሁዳ አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከይሁዳ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምታቀርቡት መባ የሚሆን ድርሻ ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል፥ ከድርሻዎቹ እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። ለጌታ የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱ ደግሞ አስር ሺህ ክንድ ይሆናል። ይህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የጌታ መቅደስም በመካከሉ ይሆናል። ሌዋውያን በሳቱ ጊዜ፥ እንደ ሳቱት እንደ እስራኤል ልጆች ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። ከምድሪቱ መባ የተቀደሰው መባ ለእነርሱ ይሆናል፥ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። ለሌዋውያኑ በካህናቱ ድንበር አጠገብ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ይሆናል፥ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ለጌታ የተቀደሰ ስለሆነ ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡም፥ የምድሪቱንም በኵራት ወደ ሌላ አይተላለፍም። በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ለፊት አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያና ለማሰማርያ ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። ከተማይቱ ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አጠገብ የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ ዐሥር ሺህ ወደ ምዕራብም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ይህም በተቀደሰው መባ አጠገብ ይሆናል። ምርቷም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ድርሻ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሃያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍሎች ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል። ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከጋድ ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የከተማይቱ መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። የከተማይቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ሦስት በሮች አሉ፥ አንዱ የሮቤል በር፥ አንዱ የይሁዳ በር፥ አንዱ ደግሞ የሌዊ በር ነው። በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር፥ አንዱ የብንያም በር፥ አንዱ ደግሞ የዳን በር ነው። በደቡብ በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር፥ አንዱ የይሳኮር በር አንዱ ደግሞ የዛብሎን በር ነው። በምዕራቡም በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱ የአሴር በር፥ አንዱ ደግሞ የንፍታሌም በር ነው። ዙሪያዋ ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ “ጌታ በዚያ አለ” ተብሎ ይጠራል። በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም፥ በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። ጌታ መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ ጌታ ሆሴዕን፦ “ምድሪቱ ከጌታ ርቃ ታላቅ ዝሙት አድርጋለችና ሂድ፤ አመንዝራን ሴት ውሰድና አግባ፤ የዝሙትም ልጆች ይኑሩህ፥” አለው። እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። ጌታም እንዲህ አለው፦ “ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።” ዳግመኛም ፀነሰች ሴት ልጅም ወለደች። ጌታም እንዲህ አለው፦ “የእስራኤልን ቤት ፈጽሞ ይቅር እንድላቸው ከእንግዲህ ወዲህ ርኅራኄ የለኝምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤ ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፤ እነርሱንም በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸው በጌታ አድናቸዋለሁ።” ሎሩሃማንም ጡት ባስጣለች ጊዜ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጌታም፦ “ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላካችሁ አይደለሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው፥” አለው። የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንዳማይቆጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲሁም እነርሱ፦ “ሕዝቤ አይደላችሁም” በተባሉበት በዚያ ስፍራ፦ “የሕያው አምላክ ልጆች” ይባላሉ። የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ እነርሱም አንድ አለቃ በራሳቸው ላይ ይሾማሉ፤ የኢይዝራኤልም ቀን ታላቅ ይሆናልና ከምድሪቱ ይወጣሉ። ወንድሞቻችሁን፦ “ዓሚ”፥ እኅቶቻችሁንም፦ “ሩሃማ” በሉአቸው። እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባሏ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ምንዝርናዋን ከፊትዋ፥ ዝሙትዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ አለበለዚያ ዕራቁትዋን እንድትሆን እገፍፋታለሁ፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር አደርጋታለሁ፥ በጥምም እገድላታለሁ። እንዲሁም የአመንዝራ ልጆች ናቸውና ለልጆችዋ አልራራም። እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም እርሷ አሳፋሪ ነገር አድርጋለች፤ ምክንያቱም፦ እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ፥ ብላለችና። ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፤ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለችም፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርሷም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና፥ ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ፥ ትላለች። እርሷም እህልንና ወይን ጠጅን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም ያደረጉትን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደሆንኩ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይን ጠጄንም በወቅቱ ፈጽሞ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም መሸፈኛ የነበረውን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። እንዲሁም አሁን ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችዋን ሁሉ አስቀራለሁ። እርሷም፦ “ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። በበኣሊም የበዓል ቀኖች ዕጣን ለእነርሱ በማጠንዋና ራስዋን በጉትቾችዋና በጌጥዋ በማስጌጥ ውሽሞችዋን ተከትላ እኔን በመርሳትዋ እቀጣታለሁ፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የወይን ቦታዎችዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆናት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ብላቴንነትዋ ወራት ትዘምራለች። “በዚያ ቀን፦ ‘ባሌ’ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ፦ ‘በኣሌ’ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል ጌታ፤ የበኣሊምን ስም ከአፏ አስወግዳለሁና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በስማቸው የሚያስታውሳቸው አይኖርም። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ጦርነትንም ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ በደኅንነትም እንዲያርፉ አደርጋቸዋለሁ። ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በምሕረትና በጽኑ ፍቅር ለእኔ አጭሻለሁ። ለእኔም እንድትሆኚ በታማኝነት አጭሻለሁ፤ አንቺም ጌታን ታውቂአለሽ። “እንዲህም ይሆናል፥ በዚያን ቀን እመልሳለሁ ይላል ጌታ፥ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ። በምድርም ላይ ለራሴ እንድትሆን እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን፦ ‘አንተ ሕዝቤ ነህ’ እለዋለሁ፤ እርሱም፦ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይለኛል።” ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳ ጌታ እንደሚወድዳቸው እንዲሁ አንተም ዳግመኛ ሂድ፥ በውሽማዋ የምትወደደውን አመንዝራይትን ሴት ውደድ።” እኔም በዓሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስ ገዛኋት። ለእርሷም፦ “የእኔ ሆነሽ ለብዙ ወራት ተቀመጪ፥ አታመንዝሪም፥ ለሌላ ሰውም አትሁኚ፤ እኔም እንዲሁ እሆንልሻለሁ” አልኋት። የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዓምድ፥ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን ጌታንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ ጌታና ወደ መልካምነቱ ይመጣሉ። እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ጽኑ ፍቅር አምላክንም ማወቅ በምድሪቱ ስለ ሌለ ጌታ በምድሪቱ ላይ ከሚኖሩ ጋር ሙግት አለውና የጌታን ቃል ስሙ። መራገምና መዋሸት፥ መግደልና መስረቅ፥ ማመንዘርም ገደባቸውን አልፈዋል፤ ደም ማፍሰስ ደም ማፍሰስን አስከትሏል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርሷም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር በድካም ይዝላሉ፤ የባሕሩም ዓሦች እንኳ ያልቃሉ። ነገር ግን ሙግቴ ከካህን ጋር ነውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። በቀንም ትሰናከላለህ፥ እንዲሁም ነቢይ ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ትተሃልና ለእኔ ካህን እንዳትሆን ትቼሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እነርሱም እጅግ በበዙ ቍጥር አብዝተው ኃጢአትን በእኔ ላይ ሠሩ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አዘንብለዋል። እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ ስለ መንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ እንደ ሥራቸውም ብድራትን እከፍላቸዋለሁ። እነርሱም ይበላሉ አይጠግቡም፥ ያመነዝራሉ አይበዙም ምክንያቱም ጌታን ትተው ዝሙት ተከትለዋልና፤ ወይንና አዲስ ወይን ጠጅ ልብን አጥፍቶአልና። የዝሙት መንፈስ አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና ሕዝቤ ግዑዝ እንጨታቸውን ይጠይቃሉ፥ በትራቸውም ይመልስላቸዋል። በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከባሉጥና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ፥ ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር አብረው ይሄዳሉና፥ በአማልክቶቻቸውም መቅደስ ከሚያመነዝሩ ሴቶች ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማዊ በሆኑ ጊዜ፥ ምራቶቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይጠፋል። አንተ ብታመነዝር እንኳ እስራኤል ሆይ! ይሁዳ በደለኛ አይሁን፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ብላችሁም አትማሉ። እስራኤል እንደ እልኸኛ ጊደር እልኸኛ ሆኖአል፤ ጌታስ በሰፊው ማሰማርያ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጣምሯል፤ እርሱንስ ተወው። ስካራቸውን ፈጽመዋል፥ ለምንዝርናም ራሳቸውን ፍጹም አስገዝተዋል፤ ከክብራቸው ይልቅ ውርደታቸውን እጅግ ወድደዋል። ነፋስ በክንፉ አስሮአቸዋል፤ ከመሥዋዕቶቻቸውም የተነሣ ያፍራሉ። ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ልብ አድርጉ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ! አድምጡ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነርሱን ሁሉ እገሥጻለሁ። እኔ ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ አሁን ግን ኤፍሬም ሆይ! አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። ሥራቸው ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ አልፈቀደላቸውም፤ የአመንዝራ መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ ጌታንም አላውቁምና። የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ተሰናክለዋል፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ተሰናክሎአል። ጌታንም ለመሻት በጎቻቸውንና በሬዎቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተመልሶአልና አያገኙትም። ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና ጌታን አታልለዋል፤ አሁን ደግሞ እነርሱን ከርስታቸው ጋር የወሩ መባቻ ይበላቸዋል። በጊብዓ ቀንደ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉ፤ “ብንያም ሆይ! ከአንተ ጋር ነን እያላችሁ በቤትአዌን ላይ የማስጠንቀቂያውን ነጋሪት ድምፅ አሰሙ።” ኤፍሬም በተግሣጽ ቀን ባድማ ይሆናል፤ በእስራኤል ነገዶች መካከል እርግጥ የሆነውን ነገር አሳውቂያለሁ። የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚያፈርሱ ሰዎች ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ። ኤፍሬም ትእዛዝን መከተል ፈጽሞ አልወደደምና የተጨቆነና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቁስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፥ ወደ ታላቁም ንጉሥ መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ሊፈውሳችሁ፥ ከቁስላችሁም ሊያድናችሁ አልቻለም። እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔ ራሴ ነጥቄ እሄዳለሁ እወስዳለሁም፥ ሊያድንም የሚችል ማንም የለም። በደላቸውንም ተቀብለው ፊቴን እስኪሹ ድረስ ወደ ስፍራዬ ተመልሼ እሄዳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ። እንዲህም ይላሉ፦ “ኑ፥ ወደ ጌታ እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ነፍስ ይዘራብናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት ያኖረናል። እኛም እንወቅ፤ ጌታን ለማወቅ እንትጋ፤ እንደ ንጋትም መገለጡ እርግጥ ነው፤ እንደ ዝናብ ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ በልግ ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።” ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? ስለዚህ በነቢያት እጅ ቆረጥኋቸው፥ በአፌም ቃላት ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ጽኑ ፍቅርን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና። እነርሱ ግን በአዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ቦታ እኔን አታለውኛል። ገለዓድ በደም የተቀባች የክፉ አድራጊዎች ከተማ ነች። በሰው ላይ እንደሚያደቡ ወንበዴዎች እንዲሁ ካህናት አብረው ተሰበሰቡ፥ ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ በእርግጥም፥ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ። በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ የኤፍሬም ዝሙት አለ፥ እስራኤልም ረክሶአል። ይሁዳ ሆይ! የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል። በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በገላጣም ስፍራ ወንበዴ ቀምቶአልና፤ እስራኤልን በፈወስሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ ልብ አላደረጉም፤ አሁንም ሥራዎቻቸው ከብበዋቸዋል፥ እነርሱም በፊቴ አሉ። ንጉሡን በክፋታቸው፥ ሹማምንቱንም በሐሰታቸው ደስ ያሰኛሉ። ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ የተለወሰውን ቡኮ እስኪቦካ ድረስ ጋጋሪ እሳቱን ሳይቆሰቁሰው እንደ ተወው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። በንጉሣችን ቀን ሹማምንቱ ከወይን ጠጅ ሞቅታ የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከፌዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። በሴራቸው ልባቸው እንደ ምድጃ ተቃጥላለችና፤ ጋጋሪያቸው ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በነጋም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ነደደ። ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም አጥፍተዋል፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወድቀዋል፤ ከእነርሱም መካከል ወደ እኔ የጮኸ የለም። ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ሆነ። ባዕዳን ጉልበቱን በዘበዙ፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ወደ አምላካቸው ወደ ጌታ ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌለው እንደ ሞኝ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። በመሄድ ላይ ሳሉ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ በጉባኤያቸው ላይ እንደተላለፈው እገሥጻቸዋለሁ። ከእኔ ሸሽተው ሄደዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ እታደጋቸው ነበር፥ እነርሱ ግን ሐሰትን ተናገሩብኝ። በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዓመፁ። ክንዳቸውን ያስተማርሁና ያጸናሁ እኔ ነበርሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን አሴሩብኝ። ከንቱ ወደ ሆነው ነገር ተመለሱ፤ እንደ ረገበ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከክፉ አንደበታቸው የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል። መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና እንደ ንስር በጌታ ቤት ላይ እያንዣበበ ነው። እነርሱም፦ “አምላክ ሆይ! እኛ እስራኤል እናውቅሃለን!” ብለው ወደ እኔ ጮሁ። እስራኤል በጎነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድደዋል። ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም ሾሙ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለመጥፊያቸው ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ። ሰማርያ ሆይ! እምቦሳህን አስወግጃለሁ፤ ቁጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ መንጻት የማይቻላቸው እስከ መቼ ድረስ ነው? የተሠራው ነገር ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ እርሱም በሞያተኛ የተሠራ ነው፤ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይሰባበራል። ነፋስን ዘሩ፥ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ የቆመውም እህል ዛላ የለውም፥ ከእርሱም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንኳ ባዕዳን ይበሉታል። እስራኤል ተውጦአል፤ አሁን በአሕዛብ መካከል እንደ ረከሰ ዕቃ ሆነዋል። ብቻውን እንደሚንከራተት የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆችን በገንዘብ ቀጥሯል። ከአሕዛብ መካከል ወዳጆችን በገንዘብ ቢቀጥሩም እንኳ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ በቶሎ ይመነምናሉ። ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያዎችን አብዝቶአልና የኃጢአት መሥርያ መሠዊያዎች ሆነውለታል። በሺዎች የሚቆጠሩትን ሕጎቼን ጽፌለት እንኳ እንደ እንግዳ ነገር ተቆጠሩ። የተመረጠውን መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ ጌታ ግን በእነርሱ ደስ አይሰኝም፤ በደላቸውን አሁን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ ቤተ መንግሥቶችን ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በእርሱ ከተሞች ላይ እሳት እልካለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ትበላለች። እስራኤል ሆይ! ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የዝሙትን ዋጋ ወድደሃል። አውድማውና ወይን ጠጅ መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ በመጥመቂያውም ውስጥ አዲስ የወይን ጠጅ ጐድሏል። በጌታ ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ። ለጌታም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ እንደ ኀዘን እንጀራም ይሆንባቸዋል፥ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ፤ እንጀራቸውም ለሆዳቸው ይሆናል እንጂ ወደ ጌታ ቤት አይገባም። በዓመት በዓል ቀንና በጌታ በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ቢሄዱ እንኳ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሰዋል፥ እሾኽም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። የበቀል ወራት መጥቷል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ይወቀው፤ ከበደልህና ከጥላቻህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሞኝ ሆኗል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። ነቢዩ ከአምላኬ ጋር በኤፍሬም ላይ ጠባቂ ነው፤ አሁን ግን በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ፥ በአምላኩም ቤት ጥላቻ አለ። በጊብዓ ዘመን እንደነበረው ርኩሰት እነርሱም እንዲሁ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ እንደ ወይን ዘለላ ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በወቅቱ መጀመሪያ ላይ እንዳለ እንደ በለስ በኵራት በበለስ ዛፍ ላይ ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ባዓል-ፌዖር መጡ፥ ለእፍረትም ነገር ራሳቸውን ለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ እንኳ አንድም ሰው ሳላስቀር ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ በለመለመ መስክ ተተክሎ አየሁት፤ አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። ጌታ ሆይ! ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ሳሉ ጠላኋቸው፤ ስለ ሥራዎቻቸውም ክፋት ከቤቴ አስወጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ እንኳ እጅግ የሚወዱአቸውን የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። እርሱን አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ። እስራኤል ፍሬውን የሚሰጥ የተትረፈረፈ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያዎችን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ብልጥግና መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። ልባቸው ሐሰተኛ ነው፤ በደላቸውን አሁን ይሸከማሉ፤ ጌታ መሠዊያዎቻቸውን ይሰባብራል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። አሁንም፦ “ጌታን አልፈራንምና ንጉሥ የለንም፤ ንጉሥስ ለእኛ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። የማይረባውን ቃላት ተናገሩ፤ በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ስለዚህ መርዛም አረም በእርሻ ትልሞች ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት በቀለባቸው። የሰማርያ ሰዎች የቤትአዌንን እምቦሳ ፈሩ፤ ክብሩ ከእርሱ ተለይቶታልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኹለታል። እርሱም ደግሞ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ እንዲሆን ወደ አሦር ተማርኮ ይወሰዳል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንደሚሳፈፍ ስንጥር ትጠፋለች። የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾኽና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ እነርሱም ተራሮችን፦ “ሸፍኑን!” ኮረብቶችንም፦ “ውደቁብን!” ይሉአቸዋል። እስራኤል ሆይ! ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በዓመፀኛ ልጆች ላይ በጊብዓ ጦርነት አይደርስባቸውምን? በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ እጥፍ ስለ ሆነው በደላቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ በእነርሱ ላይ ይሰበሰቡባቸዋል። ኤፍሬም ማበራየት የምትወድ የተገራች ጊደር ነበር፥ እኔም በውብ አንገትዋ ላይ አልጫንኩባትም ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም ለራሱ አፈሩን ያለሰልሳል። ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። በሕዝብህ መካከል ሽብር ይነሣል፤ ምሽጎችህም ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ሰልማን ቤትአርብኤልን በጦርነት ቀን እንዳፈረሰ፥ እናትም ከልጆችዋ ጋር ተዳምጣ ነበር። ቤቴል ሆይ! ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ እንዲሁ ይደረግባችኋል፤ ጎሕ ሲቀድ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል። እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከእኔ ዘንድ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠው ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ መራመድን አስተማርሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። ሰብአዊ በሆነ የርኅራኄ ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ እነርሱንም ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው። ወደ እኔ መመለስን አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ ከተሞቻቸውን ይመታል፥ ምዋርተኞቻቸውንም ይበላል ያጠፋልም። ሕዝቤም ከእኔ ወደ ኋላ መመለስን በጽኑ ወደዱ፤ በአንድነትም ወደ ልዑሉ ይጣራሉ፥ እርሱ ግን ከፍ ከፍ አያደርጋቸውም። ኤፍሬም ሆይ! እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ! እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አድማህ አደርግሃለሁ? እንዴትስ እንደ ጲቦይም እመለከትሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም ዳግመኛ አላጠፋም፤ በመዓትም አልመጣም። ጌታን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ ባገሣም ጊዜ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ። ኤፍሬም በሐሰት፥ የእስራኤልም ቤት በተንኰል ከበበኝ፤ ይሁዳ ግን እስካሁንም ከጌታ ጋር ይመላለሳል ለቅዱሱም ታማኝ ነው። ኤፍሬም ነፋስን ያሰማራል፥ ቀኑን ሙሉ የምሥራቅን ነፋስ ይከተላል፤ ሐሰትንና ዓመጻን ያበዛል፤ ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፥ ወደ ግብጽም ዘይት ይወስዳሉ። ጌታም ደግሞ ከይሁዳ ጋር ሙግት አለው፥ ያዕቆብንም እንደ መንገዱ ይቀጣል፤ እንደ ሥራውም ይመልስለታል። በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጉልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤ ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ተነጋገረ። እርሱም የሠራዊት አምላክ ጌታ ነው፤ የመታሰቢያው ስም ጌታ ነው። “ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን።” ከከነዓን ወገን ነው፤ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል። ኤፍሬምም፦ “በእውነት ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አያገኙብኝም” አለ። እኔም ጌታ፥ ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ። ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን ሰጥቻለሁ። ኃጢአት በገለዓድ አለ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፤ በሬዎችን በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልሞች ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ። ያዕቆብ ወደ አራም ምድር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም በጎችን ያሰማራ ነበረ። ጌታም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢያትም እጅ ጠበቀው። ኤፍሬም አስመርሮ አስቆጣው፤ ስለዚህ ደሙ በላዩ ላይ ነው፤ ጌታውም ስድቡን በራሱ ላይ ይመልሳል። ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም መካከል ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ። አሁንም ኃጢአትን እጅግ አብዝተው ይሠራሉ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሞያተኞች ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም የሚሠዉ ሰዎች፦ “እምቦሳውን ይሳሙ” ይላሉ። ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ። እኔ ግን ጌታ፥ ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም። በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር። ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ። ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ እሆንባቸዋለሁ፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤ ልጇ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይቦጫጭቃቸዋል። እስራኤል ሆይ! በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጠፍተሀል። በየከተማህ ሁሉ እንዲያድንህ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም፦ “ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ” ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ? በቁጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት። የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል። ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ ወደ ማኅፀን አፍ ራሱን አያቀርብምና ማስተዋል የጎደለው ልጅ ነው። ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ! ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ! አጥፊነትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች። በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆንም እንኳ የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የጌታ ነፋስ ከምድረበዳ ይመጣል፤ ፈሳሹንም ይጠፋል፥ ምንጩንም ይደርቃል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል። ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጉዞቻቸውም ይቀደዳሉ። እስራኤል ሆይ! በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ተመለስ። ከእናንተ ጋር ቃላትን ውሰዱ፥ ወደ ጌታም ተመለሱ፥ እንዲህም በሉት፦ “በደልን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በእንቦሳም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን። አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ፦ ‘አምላኮቻችን’ ናችሁ አንላቸውም።” ቁጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ከዳተኝነታቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ። ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሮቹን ይሰድዳል። ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል። ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ እንደ አትክልት ስፍራ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይንም ተክል ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል። ኤፍሬም ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ከጣዖታት ጋር እኔ ምን አደርጋለሁ? እኔ እመልስለታለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል። እነዚህን ነገሮች የሚያስተውል ጠቢብ ማን ነው? የሚያውቃቸውስ አስተዋይ ማን ነው? የጌታ መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ዓመፀኞች ግን ይወድቁበታል። ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፥ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፥ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፥ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው። አዲስ የወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፥ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ። ቍጥር ም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፥ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው። ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፥ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፥ ቅርንጫፎቹም ነጡ። እጮኛዋ ስለሞተባት ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ። የእህሉ ቁርባንና የመጠጡ ቁርባን ከጌታ ቤት ተወግዶአል፥ የጌታ አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ። እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች። መከሩ ከእርሻ ጠፍቶአልና ገበሬዎች ሆይ፥ ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ እፈሩ፥ የወይን አትክልተኞችም አልቅሱ። ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፥ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፥ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል። የእህሉ ቁርባንና የመጠጡ ቁርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፥ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፥ ዋይ በሉ፥ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ። ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ቤት ሰብስቡ፥ ወደ ጌታም ጩኹ። የጌታ ቀን ቀርቧልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል። ዓይናችን እያየ አይደለምን ከፊታችን ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋው? ዘሩ በምድር ውስጥ ተበላሸ፥ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል። እንስሶች እጅግ ጮኹ፥ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተቅበዘበዙ፥ የበግም መንጎች እየተሰቃዩ ነው። አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኹ። የጌታ ቀን መጥቷልና፥ እርሱም ቀርቧልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፥ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ። የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፥ ከዘለዓለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ ለብዙ ትውልድ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፥ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፥ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም። መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፥ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ። በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፥ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኰበኩባሉ። ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፥ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል። እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ጦር ሰዎችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፥ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፥ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም። አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፋም፥ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፥ በጦር መሣርያ መካከል ያልፋሉ፥ የሚያስቆማቸው ነገር የለም። በከተማም ያኰበኩባሉ፥ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፥ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፥ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ። ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፥ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ። ጌታም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ያሰማል፥ ሠራዊቱ እጅግ ብዙ ነውና፥ ቃሉንም የሚፈጽም እርሱ ኃያል ነውና፥ የጌታ ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል? አሁንስ፥ ይላል ጌታ፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፥ ጌታ አምላካችሁም ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። የሚመለስና የሚጸጸት እንደሆነ፥ ጌታ አምላካችሁም የእህልና የመጠጥ ቁርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደሆነ ማን ያውቃል? በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፥ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። የጌታም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ፦ “አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤” ከአሕዛብ መካከል፦ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ስለምን ይበሉ? ጌታም ስለ ምድሩ ቀና፥ ለሕዝቡም ራራለት። ጌታም መልሶ ሕዝቡን፦ እነሆ፥ እህልንና ወይንን ዘይትንም እልክላችኋለሁ፤ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፥ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም። የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ ፥ ወደ በረሃና ወደ ምድረ በዳ፥ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፥ እርሱም ብዙ ነገር አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፥ ክርፋቱም ይነሣል አለ። ምድር ሆይ፥ ጌታ ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፥ ደስም ይበልሽ፥ እልልም በዪ። እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፥ የምድረ በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ። እናንተ የጽዮን ልጆች፥ ጌታ አምላካችሁ ቀድሞ የሚደርሰውን ዝናብ ስለ ጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ በፊትም ቀዳሚውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፥ ለእርሱም እልል በሉ። አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፥ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ። የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ። ብዙ መብል ትበላላችሁ፥ ትጠግቡማላችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የጌታ የአምላካችሁን ስም ታመሰግናላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም። እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም። ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፥ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ወጣቶቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይም መንፈሴን አፈስሳለሁ ፥ በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፥ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ ይሆናል። ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። እንዲህም ይሆናል፥ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፥ ጌታም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚተርፉ ይኖራሉ። ደግሞም ጌታ የጠራቸው ይገኛሉ። እነሆም፥ በዚያ ወራትና በዚያ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፥ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን፥ ምድሬንም የተካፈሉአትን እፈርድባቸዋለሁ። በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሲሉ ሸጡ፥ ጠጡም። ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? በውኑ ልትበቀሉኝ ትፈልጋላችሁን? በቀልን በእኔ ላይ ማውረድ ብትሞክሩ፥ በቀሉን መልሼ በፍጥነት በእናንተ ላይ አወርደዋለሁ። ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም ብርቅዬ ዕቃዎቼንም ወደ መቅደሳችሁ አስግብታችኋልና፥ ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ በደሉን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። ጌታ ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል። ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ፥ ለጦርነት ተዘጋጁ፥ ኃያላንን አስነሡ፥ ጦረኖች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፥ ደካማውም፦ እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸኩላችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፥ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፥ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፥ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል። የጌታ ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቧልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። ጌታም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል ፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ያሰማል፥ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፥ ጌታ ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ተራሮች አዲስ ወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፥ ከጌታም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። ነገር ግን ይሁዳ ለዘለዓለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። እኔም ሳልበቀላቸው እቀራለሁን? መበቀሌ አይቀርም፤ ጌታም በጽዮን ያድራል። የአሞጽ ቃላት ፥ በቴቁሔ ከሚገኙ ከበግ አርቢዎች መካከል የነበረ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ይህ ነው። እንዲህም አለ፦ “ጌታ በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ድምፁን ያስተጋባል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ይጠወልጋሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ገለዓድን የብረት ጥርስ ባለው መውቅያ አበራይተውታልና ስለ ሦስት የደማስቆ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄልም ቤት ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የአዴርንም ልጅ የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። የደማስቆንም መቀርቀሪያ እሰብራለሁ፥ ነዋሪዎችዋንም ከአዌን ሸለቆ፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይሄዳሉ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ለኤዶምያስ አሳልፈው ለመስጠት መላውን ሕዝብ ማርከው ወስደዋልና ስለ ሦስት የጋዛ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። ነዋሪዎችዋን ከአዛጦን፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በምርኮ የሄዱትን ሕዝብ ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድማማቾችንም ቃል ኪዳን አላስታወሱምና ስለ ሦስት የጢሮስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄውንም ሁሉ አጥፍቷልና፥ ባለማቋረጥም ተቆጥቷልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት የኤዶምያስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በቴማን ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የባሶራንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ዳርቻቸውን ለማስፋት ሲሉ የገለዓድን እርጉዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት የአሞን ልጆች ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነዳለሁ፤ በጦርነትም ቀን በጩኸት፥ በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት የእርሷን የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የኤዶምያስን ንጉሥ ዐፅም አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎአልና ስለ ሦስት የሞዓብ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በሞዓብ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የቂርዮትንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ መካከል ይሞታል፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የጌታን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉአቸው ሐሰቶቻቸው አስተዋቸዋልና ስለ ሦስት የይሁዳ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በይሁዳ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጻድቁን ስለ ብር፥ ችግረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠዋልና ስለ ሦስት የእስራኤል ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ለማርከስ አባትና ልጅ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። “እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ባሉጥ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው ደመሰስሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። እኔም ከግብጽም ምድር አወጣኋችሁ፥ የአሞራዊውንም ምድር እንድትወርሱ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጉልማሶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ በእውነት እንደዚህ አይደለምን?” ይላል ጌታ። እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችሁ፤ ነቢያቱንም፦ ትንቢትን አትናገሩ፥ ብላችሁ አዘዛችሁ። “እነሆ፥ እህል የተሞላ ሠረገላ እንደሚያደቅቅ፥ እንዲሁም እኔ በመሬታችሁ ላይ አደቅቃችኋለሁ። ፈጣኑ ሯጭ መሸሽ ሳይችል ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤ ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም ሯጭ አያመልጥም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ በዚያ ቀን በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥” ይላል ጌታ። የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታ በእናንተ ላይ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ እንዲህም ይላል፦ “እኔ ከምድር ወገኖች ሁሉ እናንተን ብቻ አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ። “በውኑ ሁለት ሰዎች ተቀጣጥረው ሳይገናኙ በአንድነት ሊሄዱ ይችላሉን? ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ነገር ሳይዝ በማደርያው ሆኖ ይጮኻልን? ወይስ ወፍ፥ የሚያጠምደው ነገር ሳይኖር፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ነገር ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን? ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ቢነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ጌታ ካላደረገው በቀር በከተማ ላይ ክፉ ነገር ይሆናልን? በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባርያዎቹ ለነቢያት ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም። አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?” በአዛጦን የንጉሥ ቅጥሮችና በግብጽ ምድር ባሉ የንጉሥ ቅጥሮች ላይ አውጁ እንዲህም በሉ፦ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በመካከልዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በውስጧም ያለውን ግፍ ተመልከቱ።” “በንጉሥ ቅጥሮቻቸውም ግፍንና ቅሚያን የሚያከማቹ ቅን ነገር እንዴት እንደሚደረግ አያውቁም፥” ይላል ጌታ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ምድሪቱን በዙርያዋ ጠላት ይከባታል፤ ምሽግሽንም ከአንቺ ያፈርሳል፥ የንጉሥ ቅጥሮችሽም ይበዘበዛሉ።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ከድንክ አልጋና ከአልጋ የእግር ቁራጭ ጋር ይድናሉ።” “ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥” ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። “እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያውም ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቅም ቤቶች ይፈርሳሉ፥” ይላል ጌታ። “እናንተ በሰማርያ ተራራ ያላችሁ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችግረኛውንም የምትጨቁኑ፥ ጌቶቻቸውንም፦ ‘አምጡ እንጠጣ’ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር፦ እናንተን በሜንጦ፥ ትሩፋቶቻችሁንም በመንጠቆ የሚወስዱበት ቀን፥ እነሆ፥ በላያችሁ ይመጣል ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል። እያንዳንዳችሁ እፊታችሁ ባለ በተነደለ ስፍራ በኩል ትወጣላችሁ፤ ወደ ሬማንም ትጣላላችሁ፥” ይላል ጌታ። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላ ኑና ኃጢአትን አብዙ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን አሥራታችሁን አምጡ፤ እርሾም ያለበትን የምስጋናውን መሥዋዕት አቅርቡ፥ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “እኔ በከተማችሁ ሁሉ ራብን፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት አመጣባችኋለሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥” ይላል ጌታ። “እኔ ደግሞ መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ባለው መሬት ዘነበ፥ ባልዘነበበትም ወገን ያለው መሬት ደረቀ። የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች እየተንገዳገዱ ወደ አንዲት ከተማ ውኃ ለመጠጣት ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥” ይላል ጌታ። “በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፤ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በላው፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥” ይላል ጌታ። “በግብጽ እንደነበረው ቸነፈርን በመካከላችሁ ላክሁባችሁ፤ ጉልማሶቻችሁንም በሰይፍ ገደልሁ፥ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ የሰፈራችሁንም ግማት ወደ አፍንጫችሁ አወጣሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥” ይላል ጌታ። “ሰዶምንና ገሞራን እግዚአብሔር እንደ ገለባበጣቸው፥ እንዲሁ ገለባበጥኋችሁ፥ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥” ይላል ጌታ። “ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ! እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ! እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ።” “እነሆ፥ ተራሮችን የሠራ፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም ሐሳብ ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ ጌታ ነው።” የእስራኤል ቤት ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ። “የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ለብቻዋ ተተወች፥ የሚያነሳትም ማንም የለም።” ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና፦ “ሺህ ከሚወጣበት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት ዐሥር ይቀርላታል።” ጌታም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና፦ “እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ።” በዮሴፍ ቤት ላይ እንደ እሳት በድንገት እንዳይቀጣጠል፥ በቤቴልም ላይ የሚያጠፋው ሳይኖር እንዳይበላት፥ ጌታን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ! ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮበብ የፈጠረ፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጥ፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልም፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸው እርሱ፥ ስሙ ጌታ ነው። እርሱም ምሽጉ እንዲፈርስ በብርቱ ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣል። በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ። እናንተም ድሀውን ረግጣችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና፥ ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም። ጻድቁን የምታሠቃዩ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችግረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ! በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና። ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና፥ በእንደዚህ ያለ ዘመን አስተዋይ የሆነ ሰው ዝም ይላል። በሕይወት እንድትኖሩ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲሁም እናንተ እንደ ተናገራችሁት የሠራዊት አምላክ ጌታ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ ጌታ ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል። ስለዚህ ጌታ፥ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ‘ወዮ! ወዮ!’ ይላሉ፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ። በመካከልህ አልፋለሁና በወይኑ ቦታ ሁሉ ልቅሶ ይሆናል፥” ይላል ጌታ። የጌታን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የጌታን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። ከአንበሳ ፊት ሲሸሽ ድብ እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው። የጌታ ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን? “ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ፤ ተጸይፌዋለሁም፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም። የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቁርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለአንድነት መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም። የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ አርቅ፤ የበገናህንም ዜማ አላዳምጥም። ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።” “የእስራኤል ቤት ሆይ! በውኑ አርባ ዓመት በምድረ በዳ መሥዋዕትንና ቁርባንን አቅርባችሁልኛልን? ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎቻችሁን፥ የሳኩት የንጉሣችሁን እና የአምላካችሁን የኬዋን ኮከብ ታነሣላችሁ። ስለዚህ ከደማስቆ ባሻገር አስማርኬ አፈልሳችኋለሁ፥” ይላል ጌታ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ የሆነ። በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተማምነው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! ወደ ካልኔ እለፉና ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? ክፉውን ቀን ከእናንተ ታርቃላችሁን? የግፍንስ ወንበር ታቀርባላችሁን? ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ በበገናም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም ለራሳችሁ የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ቅባትም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለዚህ በመጀመሪያ ተማርከው ከሚፈልሱት ይሆናሉ፥ እንደ ፈቃዳቸው ከሚሆኑ መካከል ፈንጠዝያ ይርቃል። ጌታ እግዚአብሔር፦ “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ። እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። የሞተውን ሰው የሚያቃጥለው ዘመዱ አጥንቱን ከቤቱ አንስቶት ባወጣው ጊዜ፥ በቤቱም በውስጠኛው ክፍል ያለውን፦ “በእዚያ እስከ አሁን ድረስ ከአንተ ጋር ሰው አለን?” ይለዋል፥ እርሱም፦ “ማንም የለም” ይላል፤ ያንጊዜ፦ “የጌታን ስም ልንጠራ አይገባንምና ዝም በል” ይለዋል። እነሆም፥ ጌታ ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። በውኑ ፈረሶች በዓለታም መሬት ላይ ይጋልባሉን? ወይስ ሰው በበሬዎች በዚያ ላይ ሊያርስ ይችላልን? ነገር ግን እናንተ ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት ለወጣችሁ፤ በሎዴባር ደስ የሚላችሁ፥ እናንተም፦ “በብርታታችን ቃርናይምን ለራሳችን አልወሰድንምን?” የምትሉ ናችሁ። “የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ እኔ አሕዛብን አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ፤ “እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።” ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ መከር ካለፈ በኋላ ያለው እህል በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለ ነበረ። የምድሩንም እጽዋት በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ አይሆንም፥” ይላል ጌታ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርሷም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። ጌታም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።” የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ብሎ ላከ፦ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል አሢሮብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም። አሞጽ፦ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል’ ብሎ ተናግሮዋልና።” አሜስያስም አሞጽን እንዲህ አለው፦ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ዳግመኛ ትንቢት አትናገር።” አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ እኔ የመንጋዎች ጠባቂና የወርካ ዛፎችን ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ ጌታም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ ጌታም፦ “ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” አለኝ። “አሁን ደግሞ የጌታን ቃል ስማ፤ አንተ፦ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ አልህ፤ ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ እየተለካች ትከፋፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።’ ” ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የበጋ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት ነበረ። እርሱም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “የበጋ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት ነው” አልኩት። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቷል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም። በዚያ ቀን የመቅደሱ ዝማሬ ዋይታ ይሆናል፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በየስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።” ችግረኛውን የምትረግጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ ይህን ስሙ፤ እናንተ እንዲህ ትላላችሁ፦ “እህልን እንድንሸጥ መባቻው መቼ ያልፋል? ስንዴውንም ለሽያጭ ገበያ ለማቅረብ ሰንበት መቼ ያበቃል? የኢፍ መስፈሪያውንም እናሳንሳለን፥ ሰቅሉንም እናበዛለን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እናታልላለን፥ ድሀውን በብር ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛለን፥ የስንዴውን ገለባ እንሸጣለን።” ጌታ በያዕቆብ ሞገስ እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ “ሥራቸውን ሁሉ ለዘለዓለም በፍጹም አልረሳም። በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርሷም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ አትነሳምን? እንደ ግብጽም ወንዝ ተናውጣም ዳግመኛ አትወርድምን?” “በዚያም ቀን፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ “ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ቀኑም በብርሃን ሳለ ምድሩን አጨልማለሁ። ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ጸጉር መላጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ። “እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምልክበት ዘመን እየመጣ ነው፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም፦ የጌታን ቃላት ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የጌታን ቃል ለመሻት ይሯሯጣሉ፥ ነገር ግን አያገኙትም። “በዚያ ቀን ቆነጃጅት ድንግሎችና ጉልማሶች በጥም ይዝላሉ። አሺማ በምትባል የሰማርያ ጣኦት የሚምሉና፦ ‘ዳን ሆይ! ሕያው አምላክህን!’ ደግሞ፦ ‘ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ!’ ብለው የሚምሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ዳግመኛም አይነሡም።” ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ ጉልላቶቹን ምታ፥ በሰዎቹም ራስ ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። “ወደ ሲኦል ቢወርዱ እንኳ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ እንኳ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስም ራስ ላይ ቢሸሸጉ እንኳ አድኜ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ እንኳ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ እንኳ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።” ጌታ የሠራዊት አምላክ ምድርን ይዳስሳል እርሷም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች ፥ ዳግመኛም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች ። አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ጌታ ነው። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል ጌታ። “እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋዋለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥” ይላል ጌታ። “እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንደሚነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። ‘ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም’ የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ ይኸውም የኤዶምያስን ትሩፍ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ እንዲወርሱ ነው፥” ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። “እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚቀድምበት ወራት ይመጣል፥” ይላል ጌታ፤ “ተራሮችም ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ዳግም ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ የአትክልት ስፍራዎችንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም ላይ እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥” ይላል ጌታ አምላክህ። የአብድዩ ራእይ። ጌታ አምላክ ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከጌታ መልእክት ሰምተናል፥ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ፦ ተነሡ፥ በላይዋም በጦርነት እንነሣ ብሏል። እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፥ አንተ እጅግ ተንቀሃል። በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ። ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ብቻ ይሰርቁ የለምን? ወይንንም የሚቆርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ ያስቀሩ የለምን? አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተበረበረ! ብርቅዬ ሀብቱ ምንኛ ተፈለገ! ከአንተ ጋር ቃል የተገባቡ ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፥ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፥ በበታችህም ወጥመድ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል ጌታ። ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በግድያ እንዲጠፉ ኃያላን ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ። በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገው ግፍ እፍረትን ትከናነባለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። በዳር ቆመህ በተመለከትክበት ቀን፥ አሕዛብ ሀብቱን በማረኩበት፥ ባእዳን በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተም እንደ እነርሱ ነበርህ። ነገር ግን በወንድምህ የመከራ ቀን ልትደሰት፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች መጥፋት ደስ ሊልህ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ልትናገር አይገባም ነበር። በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ልትገባ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ልትመለከት፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ልትዘረጋ አይገባህም ነበር። የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ልትቆም፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ልትሰጥ አይገባህም ነበር። የጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቧልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ። ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይኖራሉ፥ እርሱም የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። ጌታ ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት የሚተርፍ አይኖርም። የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። ይህም የእስራኤል ልጆች የጦር ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለጌታ ይሆናል። የጌታ ቃል ወደ አሚታይ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦ “ተነሥ፥ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋታቸው በፊቴ ወጥቶአልና።” ዮናስ ግን ከጌታ ፊት ወደ ተርሴስ ለመሸሽ ተነሣ፤ ወደ ያፎም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምትሄድ መርከብ አገኘ፤ ከጌታ ፊት ሸሽቶ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ለመሄድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ ገባ። ጌታ ግን በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አስነሣ፥ በባሕሩም ላይ ታላቅ ማዕበል ተነሣ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱ እንዲቀልልላቸውም መርከቢቱ ውስጥ የነበሩትን ዕቃዎች ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ታችኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር። የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥ አምላክህን ጥራ፥ ምናልባትም እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን ይሆናል” አለው። እርስ በእርሳቸውም፦ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደመጣብን እንድናውቅ ኑ፥ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፥ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ። እንዲህም አሉት፦ “እባክህ ንገረን፥ ይህ ክፉ ነገር በምን ምክንያት መጣብን? ሥራህ ምንድነው? ከወዴት መጣህ? አገርህስ የት ነው? የየትኛው ሕዝብ ወገን ነህ?” እርሱም፦ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፥ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን፥ የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ ” አላቸው። ሰዎቹም እጅግ ፈሩ፥ እንዲህም አሉት፦ “ይህ ያደረግኸው ምንድነው?” እርሱ ስለ ነገራቸው፥ ከጌታ ፊት እንደ ኰበለለ አውቀዋልና። እንዲህም አሉት፦ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን ምን እናድርግብህ?” ባሕሩ መናወጡን ቀጥሎ ነበርና። እርሱም፦ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደመጣባችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው። ሰዎቹ ወደ የብሱ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፥ ባሕሩ በማዕበሉ ይናወጥባቸው ነበርና። ስለዚህ ወደ ጌታ ጮኹ፥ እንዲህም አሉ፦ “ጌታ ሆይ! እባክህ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ እንለምንሃለን፥ ንጹሕንም ደም በእኛ ላይ አታድርግ፤ ጌታ ሆይ ደስ የሚያሰኝህን አድርገሃልና።” ዮናስንም አንሥተው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም መናወጡን አቆመ። ሰዎቹም ጌታን እጅግ ፈሩ፥ ለጌታም መሥዋዕትን ሠዉ፥ ስእለትንም ተሳሉ። ጌታም ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ። በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ዮናስ ወደ ጌታ ወደ አምላኩ ጸለየ። እንዲህም አለ፦ “በመከራዬ ሆኜ ጌታን ጠራሁት፥ እርሱም መለሰልኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም ሰማህ። ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ልብ ጣልኸኝ፥ ወንዝም ከበበኝ፥ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ ላይ አለፉ። እኔም፦ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ አልሁ ነገር ግን ቅዱስ መቅደስህን ዳግም አያለሁ። ውኆች እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር ከበበኝ፥ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠመጠመ። ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፥ የምድር መወርወሪያዎችዋ ለዘለዓለም ተዘጉብኝ፤ ጌታ አምላኬ ሆይ አንተ ግን ሕይወቴን ከጉድጓድ አወጣሃት። ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ ጌታን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ መጣች። ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል። እኔ ግን ከምስጋና ቃል ጋር እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እፈፅማለሁ። ደኅንነት ከጌታ ነውና።” ጌታም ዓሣውን ተናገረው፥ እርሱም ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ ተፋው። የጌታም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዮናስ መጣ፥ እንዲህ አለው፦ “ተነሥ፥ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ እኔ የምነግርህን መልዕክት አውጅ።” ዮናስም ተነሣና ጌታ እንደ ተናገረው ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌም እጅግ ታላቅ ከተማ ነበረች፥ ለማቋረጥም ሦስት ቀን ይፈጅ ነበር። ዮናስ ወደ ከተማይቱ መግባት ጀመረ፥ የአንድ ቀን መንገድ ያህል እንደ ገባ “አሁንም ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ጮኸ። የነነዌም ሰዎች በእግዚአብሔር አመኑ፤ ጾምም አወጁ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ይህ ወሬ ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፥ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ፥ ማቅ ለበሶ በአመድም ላይ ተቀመጠ። በነነዌ ሁሉ ይህንን አዋጅ አስነገረ፦ በንጉሡና በመኳንንቱ ትእዛዝ መሠረት፥ ሰውም ሆነ እንስሳ፥ ከብትም ሆነ በግ አንዳች አይቅመሱ፤ አይሰማሩ፥ ውኃም አይጠጡ፥ ሰውም ሆነ እንስሳ በማቅ ይሸፈኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎች ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በመዳፋቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ፥ እግዚአብሔር ራርቶ ከሚነደው ቁጣው ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል? እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፥ እግዚአብሔርም ራርቶ አደርግባችኋለሁ ብሎ የተናገረውን ክፉ ነገር አላደረገውም። ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፥ ክፉኛም አበሳጨው። ወደ ጌታ ጸለየ፥ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ፥ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አስቀድሜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የፈለግሁትም ለዚህ ነበር፥ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ ከክፉ የምትመለስ አምላክ እንደሆንህ አውቄ ነበርና። አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ከሕይወት ሞት ይሻላልና፥ እባክህ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ።” ጌታም፦ “አንተ ልትቆጣ ተገቢ ነውን?” አለ። ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፥ ከተማይቱ የሚደርስባትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠራ፥ ከጥላዋ በታችም ተቀመጠ። ጌታ እግዚአብሔርም የጉሎ ተክል አበቀለ፥ ከጭንቀቱም እንድታድነው፥ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ራስ ላይ ከፍ ከፍ እንድትል አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ጉሎ ተክሉ እጅግ ተደሰተ። በማግስቱ ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርሷም የጉሎውን ተክል መታች፤ ደረቀም። ፀሐይም በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ፥ ዮናስ ራሱን እስኪስት ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለነፍሱም ሞትን ለመነና “ከሕይወት ሞት ይሻላል” አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን “ስለዚች የጉሎ ተክል ልትቆጣ ይገባህልን?” አለው። እርሱም፦ “እስከ ሞት ድረስ ልቆጣ ይገባኛል” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፦ “አንተ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው የጉሎ ተክል አዝነሃል። እኔስ ታዲያ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የጌታ ቃል ይህ ነው። ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙ፤ ምድርና ሞላዋ ታድምጥ፤ ጌታ በቅዱስ መቅደሱ ሆኖ፥ ጌታ አምላክ በእናንተ ላይ ይመስክርባችሁ። እነሆ፥ ጌታ ከስፍራው ይወጣልና፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል። ተራሮች በሥሩ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆዎችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ ከቁልቁለት እንደሚወርድ ውኃ፥ ይሰነጠቃሉ። ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበት ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋን ወደ ሸለቆ አፈሰዋለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ። የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖቶችዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰብስባቸዋለችና፥ ወደ ግልሙትና ዋጋ ይመለሳሉ። በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፥ ዋይ ዋይ እላለሁ፥ ባዶ እግሬንና ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፥ እንደ ሰጎን ልጆችም የዋይታ ድምፅ አሰማለሁ። ቁስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ ወደ ይሁዳ መጥቷል፥ ወደ ሕዝቤ በር ወደ ኢየሩሳሌምም ደርሶአል። በጋት አታውሩት፥ በፍጹም አታልቅሱ፤ በቤትልዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ። በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በራቁትነትና በእፍረት እለፊ፤ በጻኣናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትሐኤጼል ለቅሶ የመቆሚያ ስፍራውን ከእናንተ ይወስዳል። በማሮት የምትቀመጠው መልካም ነገርን ትጠባበቃለችና፤ ነገር ግን ክፉ ነገር ከጌታ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአል። በላኪሽ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሠረገላውን ከፈረሱ ጋር አያይዢ፤ እርሷ ለጽዮን ሴት ልጆች የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና። ስለዚህ ለሞሬሼት ጋት የመሸኛ ስጦታዎችን ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ይሆናሉ። በማሬሻ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዱላም ይመጣል። ደስ ስለምትሰኚባቸው ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ፀጉርሽንም ተቆረጪ፤ መላጣነትሽን እንደ ንስር አስፊ፤ በምርኮ ከአንቺ ተወስደዋልና። ክፋትን ለማድረግ በምስጢር ለሚያቅዱና በመኝታቸው ላይ ክፋ ነገርን ለሚሠሩ ወዮላቸው! ሲነጋ ይፈጽሙታል፥ ኃይል በእጃቸው ነውና። የእርሻ ቦታዎችን ይመኛሉ፥ ይይዟቸዋልም፤ ቤቶችንም፥ ይወስዷቸዋልም፤ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ውርሱን ይጨቁናሉ። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በዚህ ቤተሰብ ላይ ክፉ አቅጃለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን ማውጣት አትችሉም፤ በትዕቢትም አትሄዱም፥ ጊዜው ክፉ ነውና። በዚያ ቀን ምሳሌ ይመስልባችኋል፥ በኀዘን እንጉርጉሮ ያለቅስላችኋል፤ እርሱም፦ “ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን ድርሻ ቀየረ፤ ከእኔ እንዴት ወሰደው፤ እርሻችንን ለከዳተኞች ይከፋፍላል” ይላል። ስለዚህ በጌታ ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም። “አትስበኩ” ብለው ይሰብካሉ፤ “ስለ እነዚህ ነገሮች መስበክ የለባችሁም፤ ውርደት አይደርስብንም።” የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህ መባል አለበትን? በውኑ የጌታ መንፈስ ይቆጣልን? ሥራዎቹስ እነዚህ ናቸውን? ቃሎቼስ በቅን ለሚሄድ መልካም ነገር አያደርጉምን? ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፤ በሰላም ሳይፈሩ የሚያልፉትን ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፥ ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው። የሕዝቤን ሴቶች ከተዋበ ቤታቸው አስወጣችኋቸው፤ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘለዓለም ወሰዳችሁ። ተነሡና ሂዱ፥ ይህ የዕረፍት ቦታ አይደለምና፤ በርኩሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ትጠፋለች። በነፋስና በውሸት የሚሄድ፥ ሐሰትንም የሚናገር፥ “ስለ ወይን ጠጅና ስለሚያሰክር መጠጥ ስብከት እናገርልሃለሁ” የሚል ሰው ቢኖር፥ እርሱ የዚህ ሕዝብ ሰባኪ ይሆናል። ያዕቆብ ሆይ፥ ሁላችሁንም ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልን ትሩፍ በአንድ ላይ እሰበስባለሁ፤ በጋጣ ውስጥ እንዳሉ በጎች፥ በማሰማርያው ውስጥ እንዳለ መንጋ አደርገዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ። ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጡ፤ ንጉሣቸው በፊታቸው ሄዷል፥ ጌታም በራሳቸው ላይ ነው። እንዲህም አልሁ፦ የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዢዎች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ! ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን? መልካሙን የምትጠሉ፥ ክፉውን የምትወዱ፤ ቁርበታቸውን ከላያቸው ላይ ገፈፋችሁ፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያያችሁ፤ የሕዝቤን ሥጋ በሉ፥ ቁርበታቸውን ከላያቸው ላይ ገፈፉ፥ አጥንታቸውን ሰበሩ፤ በአፍላል እንዳለ በድስትም ውስጥ እንደሚከተት ሥጋ ቆራርጠዋል። የዚያን ጊዜ ወደ ጌታ ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል፥ ሥራቸው ክፉ ነውና። ጌታ ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፦ ሰው ሲያበላቸው “ሰላም አለ” ይላሉ፤ ካላበላቸው ግን ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ። ስለዚህ ለእናንተ ራእይ የሌለው ሌሊት ይሆንባችኋል፥ የማትጠነቁሉበት ጨለማ ይሆንባችኋል፤ ፀሐይ በነቢያት ላይ ትጠልቅባቸዋለች፥ ቀኑም ይጨልምባቸዋል። ትንቢተኞች ይዋረዳሉ፥ ጠንቋዮችም ያፍራሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ መልስ የለምና። እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እንድነግር በጌታ መንፈስ ኃይልን፥ ፍትህና ብርታት ተሞልቻለሁ። ፍትሕን የምትጠሉ፥ ትክክለኛውንም ነገር ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዢዎች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ፦ ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ። አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቷ በክፍያ ያስተምራሉ፥ ነቢዮችዋ በብር ያሟርታሉ፤ “ጌታ በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር በእኛ ላይ አይመጣብንም” እያሉ በጌታ ይደገፋሉ። ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ የዱር ከፍታ ይሆናል። እንዲህም ይሆናል፥ በመጨረሻው ዘመን የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶች በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፦ ኑ ወደ ጌታ ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ እኛም በፍለጋው እንሄዳለን ይላሉ፤ ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የጌታ ቃል ይወጣልና። በብዙዎች ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች መንግሥታት ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውን ወደ ማጭድ ለመለወጥ ይቀጠቅጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም። እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም፤ የሠራዊት ጌታ አፍ ተናግሮአልና። ሕዝብ ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳልና፥ እኛ ግን በጌታ አምላካችን ስም ለዘለዓለም ዓለም እንሄዳለን። በዚያ ቀን ይላል ጌታ፥ አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ የተጣለችውንና የጎዳኋትን አከማቻለሁ፤ አንካሳይቱን ትሩፍ፥ የተጣለችውን ብርቱ መንግሥት አደርጋታለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በጽዮን ተራራ ጌታ በእነርሱ ላይ ይነግሣል። አንተ የመንጋው ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ምሽግ ሆይ፥ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ወደ አንተ ትገባለች። አሁንስ ለምን ጮክ ብልሽ ታለቅሻለሽ? በአንቺ ዘንድ ንጉሥ ስለ ሌለ ነውን? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የያዘሽ፥ መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን? የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጪ፥ ተጨነቂ፤ አሁን ከከተማ ወጥተሽ በሜዳ ትቀመጫለሽና፥ ወደ ባቢሎንም ትሄጃለሽ፤ በዚያ ትድኛለሽ፥ በዚያም ጌታ ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል። አሁንም፦ “ትርከስ፥ ዓይናችን በጽዮን ላይ ይሁን” የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል። ነገር ግን የጌታን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ በአውድማ አከማችቷቸዋልና። የጽዮን ልጅ ሆይ ተነሺ አሂጂ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ኮቴሽንም ናስ አደርጋለሁና፤ ብዙ ሕዝቦችን ታደቅቂአለሽ፤ እኔም ትርፋቸውን ለጌታ፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ አውለዋለሁ። አሁንም የወታደሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ወታደሮችን ትሰበስቢያለሽ፥ በእኛ ላይ ከበባ አድርገዋል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጉንጩን በበትር ይመታሉ። አንቺ ግን ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትንሽ ነሽ፥ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ ከዚህ በኋላ የቀሩት ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ። እርሱም ይቆማል፥ በጌታ ኃይል፥ በግርማዊው በጌታ በአምላኩ ስም መንጋውን ያሰማራል፤ እነርሱም ተደላድለው ይኖራሉ፤ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና። ይህም ሰላም ይሆናል፤ አሦር ወደ ምድራችን ከመጣ፥ ምሽጎቻችንንም ከረገጠ፥ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን። የአሦርን ምድር በሰይፍ፥ የናምሩድንም ምድር በመግቢያው ይጠብቃሉ፤ ወደ ምድራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቻችንንም በረገጠ ጊዜ ከአሦር ይታደገናል። የያዕቆብ ትሩፍ በብዙ ሕዝቦች መካከል ከጌታ ዘንድ እንደሚመጣ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ፥ ሰውን እንደማይጠብቅ፥ የሰውን ልጆች በመጠበቅ እንደማይዘገይ ይሆናል። በዱር አራዊት መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋ መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ የያዕቆብ ትሩፍም በአሕዛብና በብዙ ሕዝቦች መካከል እንዲሁ ይሆናል። እጅህ በጠላቶችህ ላይ ትነሣለች፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጠፋሉ። በዚያ ቀን ይላል ጌታ፦ ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እደመስሳለሁ፤ የምድርህን ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈራርሳለሁ፤ አስማትን ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ጠንቋዮችም ለአንተ አይሆኑም፤ የተቀረጹ ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ለእጅህ ሥራ አትሰግድም፤ የተቀደሰ የምትለው አትክልትህን ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ። በማይታዘዙ አሕዛብ ላይ በቁጣና በመዓት እበቀላለሁ። ጌታ የሚለውን ስሙ፥ ተነሥ፥ በተራሮች ፊት ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ኮረብቶች ቃልህን ይስሙ። ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ የጌታን ወቀሳ ስሙ፤ ጌታ ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋቀሳልና። ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አደረግሁህ? ያደከምኩህስ እንዴት ነው? መልስልኝ። ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁና፤ በፊትህም ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ። ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያቀደውን፥ የቤዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትን፥ የጌታን ጽድቅ እንድታውቅ ከሺጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ የሆነውን እባክህን አስታውስ። ምን ይዤ ወደ ጌታ ፊት ልቅረብ፥ በልዑል አምላክ ፊት ልስገድን? የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድ ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልቅረብን? ጌታስ በእልፍ አውራ በጎች፥ በብዙ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? የበኩር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት ልስጠውን? ሰው ሆይ፥ መልካም ምን እንደሆነ ለአንተ ነግሮሃል፤ ፍትሕን እንድታደርግ፥ ምሕረትን እንድትወድና ከአምላክህም ጋር በትሕትና እንድትሄድ ካልሆነ በቀር ጌታ ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? የጌታ ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ ወገን ሆይ፥ ያዘጋጀው ማን እንደሆነ ስሙ። በክፉ ቤት የክፋት መዝገብ፥ አስጸያፊ ሐሰተኛ መስፈሪያ አሁንም አለን? የክፋት ሚዛንንና የአታላይ መመዘኛ ከረጢት አነጻለሁን? ባለ ጠጎችዋ ግፍ ተሞልተዋል፤ በውስጧ የሚኖሩትም ሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ አታላይ ነው። ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቁስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈረስሁህ። ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ባዶነትህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን ወደ ደህንነት አታመጣም፥ ወደ ደህንነት ያመጣኸውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ። ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራ ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይን ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም። የዖምሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቀሃልና፥ በምክራቸውም ሄዳችኋልና፤ ስለዚህ አንተን ለጥፋት ነዋሪዎቿን ደግሞ ለመዘባበቻ ሰጥቻችኋለሁ፥ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ። የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም። ታማኝ ሰው ከምድሪቱ ጠፍቶአል፥ በሰው መካከል ቅን የለም፤ ሁሉም ለደም ያደባሉ፥ እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል። እጆቻቸው ክፉ ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ልዑሉና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጉናሉ። ከእነርሱ የተሻለ የተባለው እንደ አሜከላ ነው፥ ቅን የተባለው እንደ ኩርንችት ነው፤ ጠባቂዎችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቷል፤ መሸበራቸውም አሁን ይሆናል። በጓደኛ አትታመኑ፥ በወዳጅም አትተማመኑ፤ የአፍህን ደጅ በጉያህ ከምትተኛው ጠብቅ። ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፥ ምራት በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፤ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸው። እኔ ግን ወደ ጌታ እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴን አምላክ እጠብቃለሁ፤ አምላኬ ይሰማኛል። ጠላቴ ሆይ በእኔ ደስ አይበልሽ፤ ብወድቅ እነሣለሁና፤ በጨለማ ብቀመጥ ጌታ ብርሃኔ ነውና። በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና፥ ጉዳዬን እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን እስኪያደርግልኝ ድረስ የጌታን ቁጣ እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቁንም አያለሁ። ጠላቴም ታያለች፥ “ጌታ አምላክህ የት ነው?” ያለችኝን ኀፍረት ይከድናታል፥ ዐይኖቼ ያዩአታል፤ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ የሚሠራበት ቀን፥ በዚያ ቀን ድንበርሽ ይስፋፋል። በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከተራራ እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንተ ይመጣሉ። ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት ከሥራቸው ፍሬ የተነሣ ባድማ ትሆናለች። በአትክልት ቦታ መካከል ባለው ጥሻ ብቻቸውን የተቀመጡት የርስትህን መንጋ፥ ሕዝብህን በበትርህ ጠብቅ፤ እንደ ቀደመው ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ። ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳየዋለሁ። አሕዛብ ያያሉ፥ በኀይላቸው ሁሉ ያፍራሉ፤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮዎቻቸውም ይደነቁራሉ። እንደ እባብ አፈር ይልሳሉ፥ በምድር እንደሚሳቡ ፍጥረታት እየተንቀጠቀጡ ከምሽጋቸው ይመጣሉ፤ በፍርሃት ወደ ጌታ አምላካችን ይመጣሉ፥ ከአንተ የተነሣ ይፈራሉ። በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱን ትሩፍ ዓመጽ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ርኅራኄ ይወድዳልና ቁጣውን ለዘለዓለም አያቆይም። እንደገና ይራራልናል፤ በደሎቻችንን ይረጋግጣል፥ ኃጢአታቸውን ሁሉ በባሕሩ ጥልቅ ትጥላለህ። ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን እንደማልህላቸው እውነትን ለያዕቆብ፥ ርኅራኄን ለአብርሃም ታደርጋለህ። የነነዌ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ። ጌታ ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ ጌታ ተበቃይና መዓት የተሞላ ነው፤ ጌታ ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፤ ቁጣን ለጠላቶቹ ያቆያል። ጌታ ለቁጣ የዘገየ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፤ ጌታ መንገዱ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። ባሕሩንም ይገሥጻል፥ ያደርቀዋልም፥ ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል፤ ባሳንና ቀርሜሎስም ጠውልጎአል፥ የሊባኖስም አበባ ጠውልጎአል። ተራሮችም ከእርሱ የተነሣ ተንቀጠቀጡ፥ ኮረብቶችም ቀለጡ፤ ምድር፥ ዓለምና በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ በፊቱ ተረበሹ። በቁጣው ፊት ማን ይቆማል? የቁጣውንስ ንዳድ ማን ይቋቋማል? መዓቱ እንደ እሳት ፈሰሰ፤ ከእርሱ የተነሣ ዓለቶች ተሰነጣጠቁ። ጌታ መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚሸሸጉትን ያውቃል። ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹን ጨለማ ያሳድዳቸዋል። በጌታ ላይ የምታስቡት ምንድነው? እርሱ ፍጻሜ ያደርጋል፥ መከራም ዳግመኛ አይነሣም። እንደ ተጠላለፈ እሾህ፥ በመጠጣቸውም እንደሰከሩ ቢሆኑ እንኳ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ። በጌታ ላይ ክፉ ነገር የሚያሤር፥ ክፋትንም የሚመክር፥ ከአንቺ ዘንድ ወጥቶአል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም ይቆረጣሉ፥ ያልፋልም። እኔም አስጨንቄሻለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅሽም። አሁንም ቀንበሩን ከአንቺ እሰብራለሁ፥ እስራትሽንም እበጥሳለሁ። ጌታ ከእንግዲህ ወዲህ በስምህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፤ ከአምላኮችህ ቤት ጣዖትንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ። አንተም የማትረባ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ። እነሆ፥ መልካም ዜና የሚያመጣ፥ ሰላምንም የሚያሰማ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ በዓሎችሽን አክብሪ፥ ስእለቶችሽን ክፈዪ፤ አጥፊው ፈጽሞ ተቆርጧልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንቺ በኩል አያልፍምና። የሚበትን ከፊት ለፊትሽ መጥቷል፤ ምሽጉን ጠብቂ፥ መንገዱን በደንብ ጠብቂ፤ ወገብሽን አጽኚ፥ ኃይልሽንም እጅግ አበርቺ። ጌታ የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል፤ አጥፊዎች አጥፍተዋቸዋልና፥ የወይናቸውን ቅርንጫፎች አጥፍተዋልና። የጦረኞቹ ጋሻ ቀልቶአል፥ ኃያላን ሰዎችም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱ በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፥ ጦሮቹም ይወዘወዛሉ። ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይከንፋሉ፥ በአደባባዮችም ወዲህና ወዲያ ይጣደፋሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይወረወራሉ። መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው ወደ ቅጥርዋ ይሮጣሉ፥ መጠለያም ተዘጋጅቷል። የወንዞቹ በሮች ተከፈቱ፥ ቤተ መንግሥቱም ቀለጠ። ቆሟል፥ ተገለጠች፥ ተማረከች፥ ሴቶች አገልጋዮቿም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ አለቀሱ። ነነዌ በዘመኗ ሁሉ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ እርሱም እየደረቀ ነው። “ቁሙ፥ ቁሙ” ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ፤ ሃብቷ ማለቂያ የለውምና፥ የከበረው የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቆጠርምና። ባዶ፥ ባድማና የጠፋች ሆናለች፥ ልብ ቀልጦአል፥ ጉልበቶች ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሁሉም ፊት ጠቁሮአል። አሁን ታድያ የአንበሶቹ ዋሻ፥ ደቦሎቻቸውን ያበሉበት፥ ወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፥ ግልገሎቹም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ወዴት ነው? አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ያህል ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም አነቀላቸው፥ ዋሻውን በነጠቀው፥ ጉድጓዱንም በተቦጫጨቀ ሥጋ ሞልቶታል። እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ሰረገሎችዋን አቃጥዬ አጨሰዋለሁ፥ የአንበሳ ደቦሎችሽን ሰይፍ ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽን ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልዕክተኞችሽ ድምፅ ዳግም አይሰማም። ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ማታለልና ዘረፋ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርሷ አይርቅም። የጅራፍ ድምፅ፥ የመንኰራኵር ድምፅ፥ የፈረስ ኮቴ፥ የሠረገላ መንጓጓት ተሰምቶአል፤ ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍ ይንቦገቦጋል፥ ጦር ይብለጨለጫል የተገደለ ብዛት፥ የበድን ክምር፥ ሬሳው ማለቂያ የለውም፤ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ። ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርሷም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች። እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ ልብስሽን እስከ ፊትሽ እገልጣለሁ፤ ኅፍረተ ሥጋሽን ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ። ርኩሰትንም በላይሽ ልይ እጥላለሁ፥ እንቅሻለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ። የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ፦ ነነዌ ወድማለች፤ ማን ያዝንላታል? አንቺን የሚያጽናኑ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል። አንቺ በዓባይ ፈሳሾች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን? ኢትዮጵያና ግብጽ ወሰን የለሽ ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ። ሆኖም ግን ተማርካ ተወሰደች፤ ሕፃናቶችዋ በመንገዶች ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፤ በከበርቴዎችዋ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ። አንቺ ደግሞ ትሰክሪአለሽ፥ ትደበቂያለሽ፤ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ። ምሽግሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፤ በሚወዛወዙ ጊዜ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃሉ። እነሆ፥ በመካከልሽ ያለው ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፤ የምድርሽ በሮች ለጠላቶችሽ በሰፊው ተከፍተዋል፥ መወርወሪያዎችሽን እሳት በልቶአቸዋል። ለከበባው ውኃ ለራስሽ ቅጂ፥ ምሽግሽን አጠናክሪ፤ ወደ ጭቃው ግቢ፥ ጭቃውንም ርገጪ፥ የጡብ መሥሪያ ያዢ። በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ይቆርጥሻል፥ እንደ አንበጣ ይበላሻል። እንደ አንበጣ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ። ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፤ አንበጣ ተዘረጋና በረረ። ጠባቂዎችሽ እንደ አንበጣ፥ መኳንንቶችሽም በብርድ ቀን በቅጥር ላይ እንደ ሰፈረ የኩብኩባ መንጋ ናቸው፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ይበራሉ፥ ስፍራቸው የት እንደሆነ አይታወቅም። የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፤ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፤ ሕዝብህ በተራሮች ላይ ተበትነዋል፥ የሚሰበስባቸውም የለም። ስብራትህን የሚያሽል የለም፥ ቁስልህ የከፋ ነው፤ ወሬህን የሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ የማያቋርጥ ክፋትህ ያላለፈበት ማን ነውና? ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም። ጌታ ሆይ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? “ግፍ” ብዬ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም። ክፉ ሥራ ለምን አሳየኸኝ? ድካምንስ ለምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍትሕ ድል ነሥቶ አይወጣም፤ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል። አሕዛብን እዩ፥ ተመልከቱም፤ እጅግ ተደነቁ፥ ተገረሙም፤ ቢነገራችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና። እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ለመውረስ በምድር ሁሉ ላይ የሚሄዱትን፥ መራሮችና ችኩሎች ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል። ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኩላ ይልቅ አስፈሪዎች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ፈረሰኞቻቸው ከሩቅ ይመጣሉ፥ ለመንጠቅ እንደሚቸኩል ንስር ይበርራሉ። ሁሉም ለዓመፅ ይመጣሉ፥ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችን እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ ገዢዎችም መሳቂያ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጎቹ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩን ከምረው ይወስዱታል። የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ ጠራርገው ይሄዳሉ፤ ኃይላቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው። ጌታ አምላኬ፥ ቅዱሴ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ ጌታ ሆይ፥ ለፍርድ ወስነሃቸዋል፥ ዓለት ሆይ ለተግሣጽም መሠረትሃቸው። ዐይኖችህ ክፉ እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፥ ክፉ ሥራም መመልከት አትችልም፤ አታላዮችን ለምን ትመለከታለህ? ክፉዎቹ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆኑትን ሲውጡ ለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ ገዢ እንደሌላቸው የሚሳቡ ፍጥረቶች አደረግሃቸው። ሁሉን በመንጠቆ ያወጣል፥ በመረቡ ይጎትታቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ ይለዋል፥ ሐሤትም ያደርጋል። ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። በእነርሱ ድርሻው ሰብቷልና፥ መብሉም በዝቶአልና። ስለዚህ መረቡን ባዶ ከማድረግና አሕዛብን ዘወትር ከመግደል አይቆጠብምን? በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ ምን እንደሚለኝና በአቤቱታዬም ምን መልስ እንደምሰጥ ለማየት እጠባበቃለሁ። ጌታም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለ፦ ራእዩን ጻፍ፤ የሚያነበው እንዲሮጥ በጽላት ላይ በግልፅ አድርገው። ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይፈጥናል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ጠብቀው፤ አይዘገይም። እነሆ፥ እርሱ ኮርቶአል፥ ነፍሱ በውስጡ ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። በእርግጥ ወይን አታላይ ነው፤ ትዕቢተኛ ሰው በስፍራው አርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል። እነዚህ ሁሉ፦ ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን? አበዳሪዎችህ ድንገት አይነሡምን? የሚያንቀጠቅጡህ አይነቁምን? ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ። አንተ ብዙ አሕዛብን በዝብዘሃልና፥ የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል። ከክፉ ለመታደግ ጐጆውን በከፍታ ላይ በማድረግ፥ ለቤቱ ክፉ ትርፍን የሚሰበስብ ወዮለት! ብዙ ሕዝቦችን ቆራርጠህ ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል። ድንጋይ ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከወራጅ ይመልስለታል። ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በበደል ለሚመሠርት ወዮለት! እነሆ፥ አሕዛብ ለእሳት እንደሚሠሩ፥ ሕዝቦችም ለከንቱነት እንደሚደክሙ ከሠራዊት ጌታ ዘንድ የሆነ አይደለምን? ውኃ ባሕርን እንደሚከድን፥ ምድር የጌታን ክብር በማወቅ ትሞላለችና። ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት! በክብር ፈንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጣ፥ እንዳልተገረዘም ተቆጠር፤ የጌታ የቀኙ ጽዋ በአንተ ላይ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። ከሰው ደም፥ በምድሪቱ፥ በከተማይቱና በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ከተደረገው ዓመጽ የተነሣ፤ በሊባኖስ ላይ የተደረገው ዓመጽ ይከድንሃል፤ የአራዊትም ጥፋት ያስፈራቸዋል። ሠሪው የቀረጸውና ቀልጦ የተሠራ ምስል የውሸት አስተማሪ ነውና፤ ዲዳ ጣዖትን በመሥራት ሠሪው በሠራው ይታመናልና፤ የተቀረጸ ምስል ምን ይጠቅማል? እንጨቱን “ንቃ” ዝም ያለውንም ድንጋይ “ተነሣ” ለሚለው ወዮለት! ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ በውስጡም ምንም እስትንፋስ የለበትም። ጌታ ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድሪቷ ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል። የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በሺግዮኖት። ጌታ ሆይ፥ ዝናህን ሰምቻለሁ፥ በሥራህም ጌታ ሆይ ፈራሁ፥ በዓመታት መካከል አድሰው፥ በዓመታት መካከል አስታውቀው፥ በቁጣ ጊዜ ምሕረትን አስብ። እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፓራን ተራራ መጣ። (ሴላ) ውበቱ ሰማያትን ሸፍኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፥ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል። ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ መቅሠፍትም ከእግሩ ይወጣል። ቆመ፥ ምድርንም አንቀጠቀጣት፥ ተመለከተ፥ ሕዝቦችንም አስደነገጠ፥ የዘለዓለም ተራሮች ተናጉ፥ የጥንት ኮረብቶች አጎነበሱ፥ የጥንት መንገዶች የእርሱ ናቸው። የኢትዮጵያ ድንኳኖች በጭንቀት ላይ ሆነው አየሁ፥ የሚድያን ምድር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ። ጌታ ሆይ ንዴትህ በወንዞች ላይ ነውን? ወይስ ቁጣህ በወንዞች ላይ ወይም መዓትህ በባሕር ላይ ነውን? በፈረሶችህ፥ በማዳን ሰረገሎች ላይ ተቀምጠሃልና። ቀስትህን ገለጥህ በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ። ተራሮች አንተን አይተው ተወራጩ፥ የውኃ ወጀብ አለፈ፥ ጥልቁም ድምፁን ሰጠ፥ እጁንም ወደ ላይ አነሳ። በቀስቶችህ ብርሃን፥ በጦርህ መብረቅ ፀዳል፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቀጥ ብለው ቆሙ። በቁጣ ምድርን ረገጥሃት፥ አሕዛብን በንዴት አሄድሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፥ ከመሠረቱ እስከ አንገቱ ድረስ አራቆትህ። ደስታቸው የተደበቁ ችግረኞችን እንደሚውጥ የሆነውን፥ እኛን ሊበትኑ እንደ ዐውሎ ነፋስ የመጡትን፤ የጦረኛውን ራስ በገዛ ጦሩ ወጋህ፤ በፈረሶችህ በባሕር ላይ ተራመድህ፥ ብዙ ውኆችንም ረገጥህ። እኔ ሰምቻለሁ፥ አንጀቴ ራደብኝ፥ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መበስበስ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፥ በውስጤም ተንቀጠቀጥሁ፥ በአስጨነቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፥ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ። የበለስ ዛፍ ባታብብም፥ በወይን ተክሎች ላይ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ምርት ቢቋረጥ፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ከብቶችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በጌታ ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎቼም ላይ ያስሄደኛል። ለመዘምራን አለቃ፥ በባለ አውታር መሣሪያዎቼ። በይሁዳ ንጉሥ በአሞን ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፥ ወደ አማርያ ልጅ፥ ወደ ገዳልያ ልጅ፥ ወደ ኩሺ ልጅ፥ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የጌታ ቃል ይህ ነው። “ሁሉን ነገር ከምድረ ገጽ ፈጽሜ አጠፋለሁ” ይላል ጌታ። ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሦች አጠፋለሁ፥ ክፉዎች እንዲደናቀፉ አደርጋለሁ፥ ሰውንም ከምድር ገጽ እቆርጣለሁ ይላል ጌታ። እጄንም በይሁዳ ላይና በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፥ ከዚህም ስፍራ የበዓልን ትሩፍና የጣዖታቱን ካህናት ስም ከካህናቱ ጋር እቆርጣለሁ፤ በሰገነትም ላይ ለሰማያት ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ ለጌታ የሚሰግዱትንና በእርሱም የሚምሉትን፥ በንጉሣቸውም ደግሞ የሚምሉትን፥ ጌታን ከመከተል የተመለሱትን፥ ጌታን ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ። በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ! የጌታ ቀን ቀርቧልና፤ ጌታ መሥዋዕትን አዘጋጅቷል የጠራቸውንም ቀድሶአል። በጌታ የመሥዋዕት ቀን ባለ ሥልጣኖችንና የንጉሡን ልጆች፥ እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እበቀላለሁ። በዚያን ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት በዓመፅና በማታለል የሚሞሉትን እቀጣለሁ። በዚያ ቀን ይላል ጌታ፥ “የዓሣ በር” የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ዋይታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል። እናንተ በመክቴሽ የምትኖሩ ሆይ አልቅሱ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ይጠፋሉና፥ ብርም የሚመዝኑ ሁሉ ይቆረጣሉና። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚረጉትን፥ በልባቸውም፦ “ጌታ መልካምም ክፉም አያደርግም” የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ። ሀብታቸው ይዘረፋል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይኖሩባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም። ታላቁ የጌታ ቀን ቀርቧል፤ የጌታ ቀን ድምፅ ቀርቧል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ ምርር ብሎ ይጮኻል። ያ ቀን የመዓት ቀን የጭንቀትና የሥቃይ ቀን፥ የጥፋትና የመፍረስ ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥ በተመሸጉ ከተሞችና በረጃጅም ግንቦች ላይ መለከትና ቀረርቶ የሚሰማበት ቀን ነው። በሰዎች ላይ ጭንቀትን አመጣለሁ፤ እንደ ዕውርም ይሄዳሉ፥ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ ደማቸው እንደ ትቢያ ይፈስሳል፥ ሥጋቸውም እንደ ጉድፍ ይጣላል። በጌታ የመዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች፥ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ አስፈሪ ፍፃሜ ያመጣባቸዋልና። እናንተ የማታፍሩ ሕዝብ ሆይ፥ በአንድነት ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም፤ ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የጌታም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፥ የጌታም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ፥ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ ጌታን ፈልጉ፤ ጽድቅን ፈልጉ፥ ትሕትናን ፈልጉ፤ ምናልባት በጌታ ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። ጋዛ ሰው የማይኖርባት ትሆናለች፥ አስቀሎናም ትፈራርሳለች፤ አሽዶድ በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዷታል፥ ዔቅሮንም ትነቀላለች። እናንተ በባሕር ዳር የምትኖሩ፥ የከሪታውያን ሕዝብ ወዮላችሁ! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የጌታ ቃል በእናንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብሽ እንዳይኖር አድርጌ አጠፋሻለሁ። የባሕሩም ዳር የግጦሽ መሬት፥ የእረኞች መስክና የበጎች በረት ይሆናል። የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ፤ ጌታ አምላካቸው ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳል። የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ፤ በሕዝቤም ላይ አላግጠዋል፥ በድንበራቸውም ላይ ኮርተዋል። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ ይሆናሉ፥ አረም እንደ ዋጠው ስፍራና እንደ ጨው ጉድጓድ ለዘለዓለምም ይጠፋሉ፤ የሕዝቤም ትሩፍ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል። ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ በሠራዊት ጌታ ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ በኩራትም ተናግረዋልና። ጌታ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርን አማልክት ሁሉ ያጠፋቸዋልና፤ የሕዝቦችም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች፥ ሁሉም በያሉበት ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ። እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ። እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፥ ነነዌንም ያፈራርሳታል፥ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል። መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጧ ይኖራሉ፥ ጉጉትና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፥ ድምፅም በመስኮት ይጮኻል፥ በመድረኩ ላይ ጥፋት ይደርሳል የዝግባ እንጨት ሥራ ይገለጣልና። ስጋት ሳይኖርባት የተቀመጠች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፥ በልብዋም፦ “እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ያለች፥ እንዴት አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ ሆነች! በእርሷ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፏጫል። ለዓመፀኛዪቱና ለረከሰች፥ ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት! ማንንም አታዳምጥም፥ እርምት አትቀበልም፥ በጌታ አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም። በውስጧ የሚኖሩ ባለ ሥልጣኖቿ የሚያገሡ አንበሶች ናቸው፥ ፈራጆችዋም ለጠዋት ምንም የማያስቀሩ የማታ ተኩላዎች ናቸው። ነቢዮችዋ ስዶችና ከሐዲ ሰዎች ናቸው፥ ካህናቶቿ መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ አምፀዋል። በውስጧ ያለው ጌታ ጻድቅ ነው፥ ስሕተት አያደርግም፥ ማለዳ ማለዳ ፍርዱን ለብርሃን ይሰጣል፥ አያቋርጥምም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም። መንግሥታትን አጥፍቻለሁ፥ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፥ መንገዶቻቸውን ማንም የማይተላለፍባቸው ባዶ ሆነዋል፥ ከተሞቻቸውም አንድም ሰው እንዳይገኝባቸው፥ ማንም የማይኖርባቸው ሆነዋል። እኔም አልኩ “በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፥ እርማትንም ትቀበያለሽ፤ መኖሪያዋ አይጠፋም፥ ያቀድኩትም አይደርስም።” እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ። ስለዚህ “ጠብቁኝ” ይላል ጌታ፤ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ፥ ፍርዴ ሕዝቦችን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነው፥ ይህም መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ ለማፍሰስ ነው፤ በቅንዓቴ እሳት ምድርም ሁሉ ትበላለችና። በዚያን ጊዜም ሁሉም የጌታን ሥም እንዲጠሩና በአንድ ትከሻ እንዲያገለግሉት፥ ለሕዝቦች ንጹሕን አንደበት እመልስላቸዋለሁ። ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚያመልኩኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቁርባኔን ያመጡልኛል። በዚያ ቀን በእኔ ላይ አምፀሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አታፍሪም፤ በኩራትሽ የተደሰቱትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ላይ ዳግመኛ አትታበዪም። በመካከልሽ ትሑትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በጌታም ስም ይታመናሉ። የእስራኤል ትሩፍ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይተኛሉ፥ የሚያስፈራቸውም የለም። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በሉ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ። ጌታ ቅጣትሽን አስወግዷል፥ ጠላትሽንም አጥፍቷል፤ የእስራኤል ንጉሥ ጌታ በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አትፈሪም። በዚያን ቀን ኢየሩሳሌም እንዲህ ይባልላታል፦ “ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። ጌታ አምላክሽ በመካከልሽ ኃያል ታዳጊ ነው፤ በአንቺም በፍጹም በደስታ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል።” ከበዓሉ ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። እነሆ በዚያ ዘመን፥ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ ወደ ይሁዳ ገዢ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤልና ወደ ታላቁ ካህን ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ፦ ዘመኑ አልደረሰም፥ የጌታ ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል።” የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በታጠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልሰከራችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ለማስቀመጥ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። በእርሱ ደስ እንዲለኝና እንድከበርበት፥ ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትን አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ። ይላል ጌታ። እናንተ ብዙ ነገርን ፈልጋችሁ፥ እነሆ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። በምን ምክንያት? ይላል የሠራዊት ጌታ። ምክንያቱም እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ስለፈረሰ ነው። ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም የምታበቅለውን ከልክላለች። እኔም በምድሪቱና በተራሮች፥ በእህልና በአዲሱ ወይን፥ በዘይትና ምድር በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በከብቶች ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ። የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የጌታን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል ሰሙ፥ አምላካቸው ጌታ ልኮታልና፤ ሕዝቡም በጌታ ፊት ፈሩ። የጌታ መልእክተኛ ሐጌ በጌታ መልእክት ሕዝቡን፦ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል ጌታ” ብሎ ተናገረ። ጌታም የይሁዳን ገዢ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁን ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፤ መጥተውም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ ቤት ሠሩ። ይህም በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት፥ በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን ነው። በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለይሁዳ ገዢ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁ ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምንም አይደለምን? አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል ጌታ፤ ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፤ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱ፥ ይላል ጌታ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ነው መንፈሴ በመካከላችሁ ይቆማልና አትፍሩ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እንደገና በቅርብ ጊዜ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ መንግሥታትን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በመንግሥታት ሁሉ ውድ የሆነ ዕቃም ይመጣል፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። በዳርዮስ ዘመን በሁለተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሕጉ ካህናቱን ጠይቅ፤ አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፥ ዕጥፋቱ እንጀራ ወይም ወጥ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ዘይት፥ ወይም ማናቸውንም መብል ቢነካ ያ የተነካው የተቀደሰ ይሆናልን? ካህናቱም፦ አይሆንም ብለው መለሱ። ሐጌም፦ በሬሳ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይረክሳልን? አለ። ካህናቱም፦ አዎን ይረክሳል ብለው መለሱ። ሐጌም መልሶ እንዲህ አለ፦ ይህ ሕዝብና ይህ ወገን በፊቴ እንዲሁ ነው፥ ይላል ጌታ፤ የእጆቻቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፤ በዚያ ያቀረቡትም ርኩስ ነው። አሁንም ከዛሬ ጀምራችሁ ወደ ፊት ልብ አድርጉ፥ በጌታ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመቀመጡ በፊት፥ በዚያን ጊዜ አንድ ሰው ሀያ መስፈሪያ ወዳለበት ምርት መጣ፥ የተገኘው ግን ዐሥር መስፈሪያ ብቻ ነው፤ አምሳ ማድጋ ለመቅዳት ወደ ወይን መጥመቂያው መጣ፥ የተገኘው ግን ሀያ ብቻ ነው። እጆቻችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፥ በአረማሞ፥ እና በበረዶ መታኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል ጌታ። ከዛሬው ከዘጠነኛው ወር ከሀያ አራተኛው ቀን ጀምራችሁ የሚመጣውን ጊዜ ልብ በሉ፤ የጌታ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ ልብ አድርጉ። ዘር በጎተራ አሁንም አለን? ወይንና የበለስ ዛፍ ሮማንና የወይራ ዛፍ አላፈሩም፤ ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ። ከወሩ በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለይሁዳ ገዢ ለዘሩባቤል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ፤ የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፥ የአሕዛብ መንግሥታትን ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና ነጂዎቻቸውን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችንና ፈረሰኞቻቸው እያንዳንዱ በወንድሙ ሰይፍ ይወድቃሉ። በዚያ ቀን ይላል የሠራዊት ጌታ፥ ባርያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፥ እወስድሃለሁ፥ ይላል ጌታ፥ እንደ ማተሚያ ቀለበት አደርግሃለሁ፥ እኔ መርጬሃለሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ በስምንተኛው ወር፥ የጌታ ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ጌታ በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር። ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።” የቀደሙት ነቢያት ለአባቶቻችሁ እንዲህ ብለው ሰብከዋል፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤’” እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፥ ይላል ጌታ። አባቶቻችሁ ወዴት ናቸው? ነቢያትስ ለዘለዓለም በሕይወት መኖር የሚችሉ ይመስላችኋልን? ነገር ግን ለአገልጋዮቼ ለነቢያት ያዘዝኳቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? ከዚያ እነርሱም ተጸጽተው፦ “የሠራዊት ጌታ በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ሊያደርግብን ያሰበውን እንዲሁ አድርጎብናል” በማለት ተቀበሉ። ዳርዮስ በነገሠ ሁለተኛው ዓመት፥ ሳባጥ በሚባል በዓሥራ አንደኛው ወር፥ በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ በራክዩ ልጅ፥ ወደ አዶ ልጅ፥ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እነሆ፥ አንድ ሰው በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፤ በስተ ኋላውም ቀይና ነጭ አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። እኔም፦ “ጌታዬ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ፦ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ። በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው፦ “እነዚህ ምድርን እንዲያስሱ ጌታ የላካቸው ናቸው” ብሎ መለሰ። እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ለነበረው ለጌታ መልአክ፥ “ምድርን አሰስናት፥ እነሆም፥ መላዋ ምድር በጸጥታ ዐርፋ ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። የጌታም መልአክ መልሶ፦ “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ፥ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ። ጌታም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፥ ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። እኔ ብዙም ሳልቆጣቸው እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ በምቾት በሚኖሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ መልሶ ይገነባባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ መለኪያ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ደግሞም እንዲህም ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ እንደገና በብልጽግና ይሞላሉ፤ ጌታም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ምርጫው ያደርጋታል። ዐይኖቼንም አንሥቼ እነሆም አራት ቀንዶች አየሁ። ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፦ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት። እርሱም፦ “እነዚህ ይሁዳን፥ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበተኑ ቀንዶች ናቸው” ብሎ መለሰልኝ። ጌታም አራት ጠራቢዎች አሳየኝ። እኔም፦ “እነዚህ የመጡት ምን ሊሠሩ ነው?” አልኩት። እርሱም፦ “አንድ ሰው ራሱን ቀና ማድረግ እስኪሳነው ድረስ እነዚህ ቀንዶች ይሁዳን የበተኑ ናቸው፤ እነዚህ ግን ሊያስፈራሯቸው፥ የይሁዳንም አገር ለመበተን ቀንዳቸውን ያነሡትን የአሕዛብን ቀንዶች ሊቆርጡ መጥተዋል” ብሎ ተናገረ። ዐይኖቼንም አነሣሁ፥ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ። እኔም፦ “አንተ ወዴት ነው የምትሄደው?” አልኩት። እርሱም፦ “ኢየሩሳሌምን ልለካትና ወርድና ርዝመቷ ስንት መሆኑን ለማየት ነው የምሄደው” አለኝ። እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ሌላ መልአክ ሊገናኘው እንደመጣ እርሱም ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ “ሩጥ፥ ይህንም ጎልማሳ እንዲህ በለው፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ትሆናለች። እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በመካከሏም ክብር እሆናለሁ፥ ይላል ጌታ።” ተነሡ! ተነሡ! ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል ጌታ፤ እንደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል ጌታ። አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ተነሽ፥ ኰብልይ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ከክብሩ በኋላ ወደ ዘረፏችሁ አሕዛብ ልኮኛል፥ የሚነካችሁ በቀጥታ እኔን የዓይኔን ብሌን ይነካል። እነሆ፥ እጄን በላያቸው ላይ አነሣለሁ፥ በምርኮ ተገዝተውላቸው ለነበሩት ራሳቸው በምርኮ ይዘረፋሉ፤ የሠራዊት ጌታም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ ስለምኖር ዘምሪ ደስም ይበልሽ! ይላል ጌታ። በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ ጌታ ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፥ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ። ጌታም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣታል። ጌታ ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና፥ ሰው ሁሉ፥ በፊቱ ዝም ይበል። ከዚያም እርሱ ታላቁን ካህን ኢያሱን በጌታ መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም እርሱን ለመክሰስ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። ጌታም ሰይጣንን፦ “ሰይጣን ሆይ፥ ጌታ ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ ጌታ ይገሥጽህ! በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው። ኢያሱም እድፋም ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። መልአኩም መልሶ በፊቱ የቆሙትን፦ “እድፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ” አላቸው። እርሱንም፦ “እነሆ፥ አበሳህን ከአንተ አርቄአለሁ፥ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ” አለው። ከዚያም፥ “ንጹሕ የራስ ላይ ጥምጣም ያድርጉለት” አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም አደረጉ፥ ልብስንም አለበሱት፤ የጌታም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር። የጌታም መልአክ በኢያሱ ላይ እንዲህ ሲል ብያኔ ሰጠ፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በመንገዴ ብትሄድ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፥ በቤቴ ላይ ትፈርዳለህ፥ አደባባዮቼንም ትጠብቃለህ፤ እኔም በዚህ ስፍራ ከቆሙት ጋር ስፍራን እሰጥሃለሁ።” ሊቀ ካህን ኢያሱ ሆይ፥ ስማ! በፊትህም የሚቀመጡት ባልንጀሮችህ ለሚመጣው ነገር ምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ! እነሆ፥ እኔ አገልጋዬን ቁጥቋጡን አወጣለሁ። በኢያሱ ፊት ያኖርሁትን ድንጋይ ተመልከት፤ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዐይኖች አሉ፤ እነሆ፥ ቅርጹን እቀርጻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የዚያችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ። በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ እያንዳንዱ በወይኑና በበለሱ ስር ሆኖ ባልንጀራውን ይጠራል። ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ መጣና ከእንቅልፌ የምነቃ ያህል ቀሰቀሰኝ። እርሱም፦ “የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነ መቅረዝ ይታየኛል፤ የዘይት ማሰሮም በላዩ ላይ ነበረ። በመቅረዙም ላይ ሰባት ቧንቧዎች ያሏቸው ሰባት መብራቶች ነበሩ። በተጨማሪም ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ነበሩ” አልኩት። ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ፦ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም” አልኩት። እርሱም መልሶ፦ “ለዘሩባቤል የተባለው የጌታ ቃል ይህ ነው፦ በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም፦ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ እርሱ የመደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል” ብሎ ነገረኝ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የዚህን የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን አይተው ይደሰታሉ። “እነዚህ ሰባቱም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የጌታ ዐይኖች ናቸው።” እኔም መልሼ፦ “በመቅረዙ በስተቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድን ናቸው?” አልኩት። ለሁለተኛ ጊዜም፦ “በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ የወርቅ ዘይት የሚያፈሱት እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድን ናቸው?” አልኩት። እርሱም መልሶ፦ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም፦ “ጌታ ሆይ፥ አላውቅም” አልኩት። እርሱም፦ “በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው” አለኝ። ተመልሼም ዐይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አንድ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ። እርሱም፦ “የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ወርዱም ዐሥር ክንድ ነው” አልኩት። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በምድር ፊት ሁሉ ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ የሚሰርቅና በሐሰት የሚምልም ሁሉ በእዚህ ላይ እንደተጻፈው ይጠፋል። እኔ እልከዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ ወደሚሰርቀውም ቤት፥ በሐሰትም በስሜ ወደሚምለው ቤት ይገባል፤ በቤታቸውም ውስጥ ይኖራል፥ እንጨቱንና ድንጋዩን፥ ይበላል።” ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጥቶ፦ “ዐይኖችህን አንሣ፥ ይህችም የምትወጣው ምን እንደ ሆነች እይ” አለኝ። እኔም፦ “ምንድን ናት?” አልኩት። እርሱም፦ “ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ ናት” አለኝ። ደግሞም፦ “ይህ ነው በምድር ሁሉ ያለ የእነርሱ በደል” አለ። ከዚያም የእርሳሱን መክሊት አነሡት፥ እነሆም፥ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። እርሱም፦ “ይህች ክፋት ናት” አለኝ፤ ከዚያም በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ ጣላት፥ የእርሳሱንም ጠገራ በመስፈሪያ አፍ ላይ ጣለ። ከዚያም ዐይኖቼን አንሥቼ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁለት ሴቶች ወጡ፥ በክንፎቻቸውም ነፋስ ነበረ፤ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ነበሩ፤ የኢፍ መስፈሪያውንም በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፦ “እነዚህ የኢፍ መስፈሪያውን ወዴት ይወስዱታል?” አልኩት። እርሱም፦ “በሰናዖር ምድር ቤት ሊሠሩለት ይወስዱታል፤ መቅደሱም በተዘጋጀ ጊዜ፥ እዚያ በስፍራው ይኖራል” አለኝ። ተመልሼም ዐይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። በፊተኛው ሠረገላ ቀይ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሠረገላ ጥቁር ፈረሶች ነበሩ፥ በሦስተኛውም ሠረገላ ነጭ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሠረገላ ዥጉርጉር ፈረሶች ነበሯቸው፤ ሁሉም ጠንካሮች ነበሩ። ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። መልአኩም መልሶ፦ “በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ እነዚህ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው። ጥቁር ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ ነጭ ፈረሶች ወደ ምዕራብ ይወጣሉ፥ ዥጉርጉር ፈረሶች ወደ ደቡብ ይወጣሉ” አለኝ። ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፥ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቁበው ነበር፤ እርሱም፥ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ። ከዚያም ጮኾ፦ “እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል” በማለት ተናገረኝ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይ፥ ከጦብያና ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ። ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በሊቀ ካህኑ በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፤ እንዲህም በለው፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ቁጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የጌታንም መቅደስ ይሠራል። እርሱ የጌታን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይጐናጸፋል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል ሰላማዊ መግባባት ይኖራል። ሌሎቹም አክሊሎች ለሔሌም፥ ለጦብያ፥ ለዮዳኤምና ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን፥ በጌታ መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ። በሩቅ ያሉትም መጥተው የጌታን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የጌታን ቃል በእውነት ብትታዘዙ ይህ ይሆናል። በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት፥ ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን፥ የጌታ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ። የቤቴልም ሰዎች በጌታ ፊት ልመና እንዲያቀርቡ ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ከሰዎቻቸው ጋር ላኩ፤ ለሠራዊት ጌታ ቤት ካህናት ለነቢያትም፦ “ለብዙ ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መጾምና ማልቀስ ይገባኛልን?” ብለው እንዲናገሩ ልኳቸው ነበር። የሠራዊትም ጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለምድሩ ሕዝብና ለካህናት ለሁሉም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር ስትጾሙና ስታለቅሱ፥ በውኑ ለእኔ ነው የጾማችሁልኝ? ስትበሉና ስትጠጡስ፥ የምትበሉትና የምትጠጡት ለራሳችሁ አይደለምን? ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች እየኖሩባቸው፥ በሰላም ተቀምጠው እያሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች እየኖሩባቸው በነበረ ጊዜ አይደለም እንዴ፥ ይህንን ቃል ጌታ በቀደሙት ነቢያት አማካኝነት የተናገረው? የጌታም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ እርስ በርሳችሁ ደግነትና ርኅራኄ ይኑራችሁ፤ መበለቲቱንና ድኻ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉ ነገር በልቡ አያስብ። እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ። የሠራዊት ጌታም በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ታላቅ ቁጣ መጣ። እኔ ስጠራቸው እነርሱ አልሰሙኝም፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩኝ ጊዜ እኔ አልሰማቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። በማያውቋቸው በባዕዳን አሕዛብ መካከል በዐውሎ ነፋስ በተንኳቸው። ስለዚህ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚዘዋወርባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት። የሠራዊትም ጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቁጣ ስለ እርሷ ቀንቻለሁ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊት ጌታም ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፥ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል። የከተማይቱም አደባባዮች በጎዳናው ላይ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በዚህ ወራት በዚህ በተረፈው ሕዝብ ዐይን ነገሩ ቢያስደንቅ፥ በውኑ ለእኔ ግን አስደናቂ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከፀምዕራብ ምድር እታደገዋለሁ፤ በኢየሩሳሌም ውስጥ እንዲኖሩ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በታማኝነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንት፥ መቅደሱ እንዲሠራ የሠራዊት ጌታ ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ፥ እጃችሁን አበርቱ። ከነዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰው ደሞዝ፥ ለእንስሳ ኪራይ አልነበረም፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ስለ ነበር፥ በጠላቶቻቸው የተነሣ ወደዚያ ለሚገቡትና ለሚወጡት ሰላም አልነበራቸውም። አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ በቀረው ሕዝብ ላይ አላደርግም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፥ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠልአቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ቀሪ ሕዝብ ይህን ነገር ርስት አድርጌ እሰጣለሁ። የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ በረከት መሆን እንድትችሉ አድናችኋለሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብኩ፥ እንዳልተጸጸትኩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ! እንግዲህ የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፦ እርስ በእርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም መግቢያዎች ሐቀኛና ትክክለኛ ፍርድ ፍረዱ። አንዱ በሌላው ላይ ክፉን ነገር በልቡ አያስብ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል የጌታ ቃል። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም፥ የአምስተኛው፥ የሰባተኛው፥ የአሥረኛው ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ፥ የሐሤትም በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ! የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ገና የብዙ ከተሞች ሕዝቦችና ነዋሪዎች ይመጣሉ፤ በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሰዎችም፦ “ጌታን ለመለመን፥ የሠራዊት ጌታንም ለመፈለግ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ” እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። ብዙ ወገኖችና ኃይለኛ አሕዛብም በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ ለመፈለግ፥ ጌታንም ለመለመን ይመጣሉ። የሠራዊት ጌታም እንዲህ ይላል፦ በዚያ ዘመን ከሁሉም የአሕዛብ ቋንቋ ዐሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው፦ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና እኛም ከእናንተ ጋር እንሂድ” ይላሉ። የጌታ ቃል ትንቢት በሴድራክ ምድር ላይ ይወርዳል፥ በደማስቆም ላይ ያርፋል፤ የእስራኤል ነገድ እንደ ሆነው ሁሉ፥ የአራም ከተሞች የጌታ ናቸው። ደግሞም በድንበሯ ላይ ባለችው በሐማት፥ ምንም ጠቢቦች ቢሆኑ በጢሮስና በሲዶና ላይ ያርፋል። ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፥ ብሩንም እንደ አፈር ወርቁንም እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች። እነሆ፥ ጌታ ሀብቷን ይገፍፋታል፥ ወደ ባሕርም ውስጥ ያሰምጠዋል፤ እርሷም በእሳት ትበላለች። አስቀሎና አይታ ትፈራለች፤ ጋዛ በሥጋት ትታመማለች፤ እንዲሁም አቃሮን፥ ተስፋዋ ይመነምናል። ንጉሡም ከጋዛ ይጠፋል፥ በአስቀሎናም የሚኖር አይገኝም። ድብልቅ ሕዝቦች በአዛጦን ያስተዳድራሉ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ። ደሙንም ከአፉ ውስጥ፥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቀሪ ሕዝብ ይሆናል፥ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፥ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል። አሁንም በዓይኔ ስቃያቸውን አይቻለሁና ከዚህ በኋላ ጨቋኝ አይመጣባቸውም፤ በቤቴ ዙሪያ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ ከዘራፊዎች የሚጠብቅ እንዲሰፍር አደርጋለሁ። አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ! እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። ሠረገላውንም ከኤፍሬም፥ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆናል። ለአንቺ ደግሞ በቃል ኪዳንሽ ደም፥ እስረኞችሽን ውኃ ከሌለበት ጉድጓድ አውጥቻለሁ። እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስረኞች ሆይ፥ ወደ ጽኑ አምባ ተመለሱ፤ ሁለት እጥፍ አድርጌ እንደምመልስልሽ ዛሬ እነግርሻለሁ። ይሁዳን እንደ ደጋኔ አጥፌዋለሁ፥ ኤፍሬምንም ቀስቱን አድርጌ አዘጋጅቻለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ። ጌታም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ የአምላኩም ቀስት እንደ መብረቅ ይወጣል፤ እግዚአብሔር ጌታም መለከትን ይነፋል፥ ከደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይመጣል። የሠራዊት ጌታ ይጠብቃቸዋል፤ እነርሱም ይውጧቸዋል፥ በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ፤ ይጠጧቸዋል፥ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይሞቃቸዋል፤ እንደ መሠዊያም ማዕዘኖች፥ እንደ ጥዋዎቹም የተሞሉ ይሆናሉ። በዚያም ቀን አምላካቸው ጌታ ሕዝቡን እንደ መንጋ ያድናቸዋል፤ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ያበራሉ። በጎነቱ በውበቱም እንዴት ታላቅ ነው! እህል ጎልማሶችን፥ አዲስ የወይን ጠጅም ቈነጃጅቱን ያሳምራል። የበልግ ዝናብ እንዲሰጣች ጌታን ለምኑ፤ መብረቁን ደመና የሚያደርግ ጌታ፥ ያደርጋል፥ እርሱም ለእያንዳንዱ የምድር ተክል የሚሆን ዝናብ ይሰጣል። ተራፊም ትርጒም አልባ ነገር ተናግረዋል፥ ሟርተኞችም ሐሰተኛ ራእይ አይተዋል፤ የሚያሳስቱ ሕልሞችን ተናግረዋል፤ ባዶ ማጽናኛም ሰጥተዋል፤ ለዚህም ነው እረኛም ስለ ሌላቸው እንደ በጎች የተቅበዘበዙትና የተጨነቁት። ቁጣዬ በእረኞች ላይ ነዷል፥ መሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የሠራዊት ጌታም የይሁዳን ቤት መንጋውን ጐብኝቶአል፥ በውጊያ ላይ ክብር እንደተቀዳጀ ፈረስ ያደርጋቸዋል። ከእነርሱም የማእዘን ድንጋይ፥ ከእርሱም የድንኳን ካስማ፥ ከእርሱም የጦር ቀስት፥ ከእርሱም ገዥም ይመጣል። በአንድ ላይም እንደ ጦረኞች ይሆናሉ፥ ጠላቶቻቸውንም በመንገድ ጭቃ ውስጥ የሚረግጡ ይሆናሉ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ስለሆነ ጦርነት ይገጥማሉ፥ ፈረሰኞችንም ያሳፍራሉ። የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፥ የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ፤ ስለምራራላቸው ወደ ቦታቸው እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም በእኔ እንዳልተተዉ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው ጌታ ነኝና፥ እኔም እሰማቸዋለሁ። የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል፤ ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በጌታ ሐሤት ያደርጋል። በፉጨት እጠራቸዋለሁ፤ እሰበስባቸዋለሁ፤ ስለምቤዣቸው እንደ ቀድሞው ብዙ እጥፍ ይሆናሉ። በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳን በሩቅ አገር ሆነውም ያስቡኛል፤ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይመለሳሉ። ከግብጽም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ። የሚበቃ ስፍራ እስኪጠባቸው ድረስ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ ምድር አመጣቸዋለሁ። እርሱም በጭንቅ ባሕር ያልፋል፥ የባሕር ሞገድም ጸጥ ያሰኛል፥ የዐባይም ወንዝ ከጥልቀት ይደርቃል። የአሦርም ትዕቢት ይዋረዳል፥ የግብጽም በትረ መንግሥት ይጠፋል። በጌታም አበረታቸዋለሁ፥ በስሙም ይመላለሳሉ፥ ይላል የጌታ ቃል። ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ! የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋልና አልቅሱ! እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና አልቅሱ! የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸውን ድምፅ ስሙ! የዮርዳኖስ ጥቅጥቅ ደን ወድሟልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ስሙ! አምላኬ ጌታ እንዲህ ብሏል፦ ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ። የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ እንደ በደለኞች አይቆጠሩም፥ የሸጧቸውም፦ “ባለ ጠጋ ሆኛለሁ፤ ጌታ ይመስገን!” ይላሉ። እረኞቻቸው እንኳን አይራሩላቸውም። ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል ጌታ፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላስጥላቸውም። እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም “ደስታ” የሁለተኛይቱንም ስም “አንድነት” ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም አሰማራሁ። በአንድ ወር ጊዜም እኔንም ስለሰለቹኝ፥ እነርሱም ስለጠሉኝ፥ ሦስቱን እረኞች አስወገድኩ። እኔም፦ “እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀሩትም እርስ በእርሳቸው ተበላልተው ይጨራረሱ።” አልሁ። እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን ለማፍረስ “ደስታ” የተባለችውን በትሬን ወስጄ ሰበርኳት። በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ እንዲሁም እኔን ሲመለከቱ የነበሩ የተጨነቁ መንጋዎች የጌታ ቃል እንደ ነበረ አወቁ። እኔም፦ “ደስ ብሎአችሁ እንደሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፥ ያለዚያ ግን ተውት” አልኩት። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። ጌታም፦ ሊከፍሉኝ የተስማሙበት ጥሩ ዋጋ በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በጌታ ቤት ባለው ግምጃ ክፍል ውስጥ አኖርኩት። ከዚያም በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት ለመለያየት “አንድነት” የተባለቸውን ሁለተኛይቱን በትሬን ሰበርኳት። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ አሁን እንደገና የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ። እነሆ፥ በአገር ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስተውልም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፥ የዳነውንም አይቀልብም፤ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል። መንጋውን ለሚተው ለማይረባ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዓይኑን ይውጋው፤ ክንዱም ፈጽማ ትሰልስል፤ ቀኝ ዓይኑም ፈጽማ ትታወር። ስለ እስራኤል የተነገረ የጌታ ቃል ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ለአሕዛብ ሁሉ የሚያንገዳግድ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ ደግሞም ይሁዳ እንደተከበበች ኢየሩሳሌም እንዲሁ ትከበባለች። በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ሊያጠቋት ቢሰበሰቡም፥ ሊያነሷት የሚሞክሩ ሁሉ ራሳቸውን እጅግ ይጎዳሉ። በዚያ ቀን፥ ይላል ጌታ፥ ፈረስን ሁሉ በድንጋጤ፥ ጋላቢውንም በእብደት እመታለሁ። የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ ሳሳውር፥ ዐይኖቼ ግን የይሁዳን ቤት ይጠብቃሉ። የይሁዳም አለቆች በልባቸው፦ “በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ብርታታቸው አምላካቸው የሠራዊት ጌታ ነው” ይላሉ። በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በቀኝና በግራ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፤ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ ትኖራለች። ጌታም፥ የዳዊትን ቤት ክብርና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር፥ በይሁዳ ክብር ላይ እንዳይታበይ የይሁዳን ድንኳኖች በቅድሚያ ያድናል። በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት እንዲሆን፥ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ ጌታ እንዲሆን፥ ጌታ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት መከታ ይሆናቸዋል። በዚያም ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚነሡትን አሕዛብ ሁሉ ለማጥፋት እፈልጋለሁ። በዳዊት ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የምሕረትንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ። እነርሱም ወደ እርሱ በሚመለከቱበት ጊዜ የወጉትን ይመለከታሉ። ሰውም ለአንድ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኩር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኅዘን ያዝኑለታል። በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል። ምድሪቱም ታለቅሳለች፥ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፥ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፥ የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፥ የሰሜኢ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፥ የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ። በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከኃጢአትና ከርኩሰት የሚያነጻ ምንጭ ይፈልቃል። በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። አሁንም ቢሆን ማንም ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ፦ “አንተ በጌታ ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም” ይሉታል። ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባትና እናቱ ይወጉታል። በዚያም ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው ትንቢት ስለ ራእዩ ያፍራል፥ ለማታለልም የማቅ ልብስ አይለብሱም። ነገር ግን እያንዳንዱ፦ “ከታናሽነቴ ጀምሮ አገልጋይ ነበርኩ፥ መሬት አራሽ ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም” ይላል። ማንም ሰው፦ “ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቁስል ምንድነው?” ብሎ ቢጠይቀው፥ እያንዳንዱም፦ “በወዳጆቼ ቤት የቈሰልኩት ቁስል ነው” ይላል። ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በጎቹም እንዲበተኑ እረኛውን ምታ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ አዞራለሁ። በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ሦስተኛው ተቈርጠው ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ፤ አንድ ሦስተኛው ክፍልም በእርሷ ይቀራል። አንድ ሦስተኛውን ክፍል ወደ እሳት አስገባለሁ፤ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፤ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም፦ “ይህ ሕዝቤ ነው” እላለሁ፥ እርሱም፦ “ጌታ አምላኬ ነው” ይላል። እነሆ፥ ከእናንት የተወሰድ ምርኮ በመካከላችሁ ለክፍፍል የሚበቃበት የጌታ ቀን ይመጣል። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ እንዲነሱ እሰበስባቸዋለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማይቱም እኩሌታ ለምርኮ ይጋዛል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዋ አይፈናቃልም። ጌታም ይወጣል፥ በጦርነትም ቀን እንደሚዋጋ ከእነዚያ አሕዛቦች ጋር ይዋጋል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር እግሮች በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም በመካከሉ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ጥልቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን፥ እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይሸሻል። የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ስለሚደርስ፥ በተራሮች መካከል ባለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ። በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከሆነው ሽሽት በበለጠ ትሸሻላችሁ። ከዚያም አምላኬ ጌታ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ አይኖርም። የማያቋርጥ አንድ የብርሃን ቀን ይሆናል፥ እርሱም በጌታ ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፥ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይወርዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት የማያቋርጥ ይሆናል። ጌታም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን ጌታ አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ፥ እንደ ዓረባ ትሆናለች፤ እርሷም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው የበሯ ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። ከተማዋም ሰዎች ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይኖርም። ኢየሩሳሌምም በሰላም ትኖራለች። ጌታም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዐይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር የመጣ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ያድራል፤ እርስ በእርሳቸውም ይያያዛሉ፥ አንዱም በሌላው ላይ ይነሣል። ይሁዳም እንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ለውጊያ ይነሣባታል። በዙሪያም ያሉትን የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፥ እጅግ ብዙ ወርቅና ብር፥ ልብስም ይሰበሰባል። በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎች፥ በአህዮች፥ እንዲሁም በዚያም ሰፈር ባሉ እንስሶች ሁሉ ላይ በሰዎች ላይ እንደ ሆነው ዓይነት ቸነፈር በእነርሱም ላይ ይሆናል። በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድ፥ የዳስ በዓልንም ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ። ከምድርም ወገኖች ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ለማይወጡ ለእነርሱ ዝናብ አይዘንብላቸውም። የግብጽም ወገን ባይወጣ ወደዚያም ባይሄድ፥ ጌታ የዳስ በዓልን ለማክበር የማይወጡትን አሕዛብ የሚቀሥፍበት ቸነፈር በእርሱ ላይ ይመጣል። ይህ የግብጽ ቅጣት ይሆናል፥ የዳስ በዓልንም ለማክበር የማይወጡት አሕዛብ ሁሉ ቅጣት እንደዚህ ይሆናል። በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኩራ ላይ፦ “ለጌታ የተቀደሰ” ተብሎ ይጻፋል። በጌታም ቤት ያሉ ምንቸቶች በመሠዊያው ፊት እንዳሉ ዳካዎች ይሆናሉ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። የሚሠውትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ፥ በእነርሱም ውስጥ ይቀቅሉባቸዋል። በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ነጋዴ አይገኝም። በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የጌታ ቃል ይህ ነው። ወድጃችኋለሁ ይላል ጌታ፤ እናንተ ግን፦ “እንዴት ወደድከን?” ትላላችሁ። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል ጌታ። ሆኖም ያዕቆብን ወደድኩት። ዔሳውን ግን ጠላሁት፤ ተራራውን አጠፋሁ፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች ሰጠኋቸው። ኤዶም፦ “እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን” ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ የክፋት አገር፥ ጌታ ለዘለዓለም የተቆጣው ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል።” ዐይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፦ “ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ጌታ ታላቅ ይሁን!” ትላላችሁ። “ስሜን የምትንቁ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባርያም ጌታውን ያከብራል፥ እኔ አባት ከሆንሁ መከበሬ የት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ?” ይላችኋል የሠራዊት ጌታ። እናንተም፦ “ስምህን የናቅነው እንዴት ነው?” ብላችኋል። “በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ ታቀርባላችሁ።” እናንተም፦ “ያረከስንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ። “የጌታ ገበታ የተናቀ ነው” በማለታችሁ ነው። “የታወረውን ለመሥዋዕት ስታቀርቡ፥ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ይህንን ለገዢህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህንስ ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ። “አሁንም እንዲራራልን የእግዚአብሔርን ፊት ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ። “በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ መካከል በሮችን የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥” ይላል የሠራዊት ጌታ። ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም። “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፤ በሁሉም ስፍራ ለስሜ ዕጣን ያመጣሉ፥ ንጹሕ ቁርባንም ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፥” ይላል የሠራዊት ጌታ። እናንተ ግን፦ “የጌታ ገበታ የረከሰ ነው፤ ፍሬውና ምግቡም የተናቀ ነው በማለታችሁ አረከሳችሁት። “እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፤ “የተሰረቀውን፥ አንካሳውንና የታመመውን አምጥታችኋል፤ እንዲሁም ቁርባንን አምጥታችኋል፤ በውኑ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላል ጌታ። “በመንጋው ውስጥ ተባዕት እያለው ለጌታ ተስሎት እያለ ነውር ያለበትን የሚሠዋ ተንኮለኛ ሰው የተረገመ ነው። እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፥ “ስሜም በሕዝቦች መካከል የተፈራ ነውና።” “ካህናት ሆይ፥ አሁንም ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው። “ባትሰሙ፥ ለስሜም ክብር ለመስጠት በልባችሁ ባታኖሩት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፥ “እርግማን እልክባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማለሁ፤ አሁንም ረግሜዋለሁ ምክንያቱም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና።” እነሆ፥ ዘራችሁን እገሥጻለሁ፥ በፊታችሁ ላይ ፈርስን እበትናለሁ፥ ይህም ፈርስ ለበዓላችሁ መሥዋዕት ካመጣችኋቸው ነው፤ እናንተንም ከእርሱ ጋር ያነሳችኋል ። ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ለማድረግ ይህን ትእዛዝ እንደ ላክሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ነበረ፤ እንዲያከብረኝ እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም አከበረኝ፥ ከስሜም በማክበር ፈራኝ ። የእውነት ትምህርት በአፉ ውስጥ ነበረ፥ በከንፈሩም ውስጥ ስሕተት አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙዎችንም ከኃጢአት መለሰ። የካህን ከንፈሮች ዕውቀትን መጠበቅ አለባቸው፤ ሰዎችም ሕግን ከአፉ መፈለግ አለባቸው፤ ምክንያቱም የሠራዊት ጌታ መልእክተኛ ነው። እናንተ ግን ከመንገዱ ተለይታችኋል፤ በሕግም ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ስለዚህ መንገዴን ስላልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ። የሁላችን አባት አንድ አይደለምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማርከስ ሁላችንም ለምን ወንድማችንን እናታልላለን? ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኩሰት ሠርቷል፤ ይሁዳ ጌታ የወደደውን መቅደስ አርክሶአል፥ የባዕድንም አምላክ ልጅ አግብቶአል። ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ቁርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል። ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቁርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኅዘንም ትከድናላችሁ። እናንተም፦ ለምን ይህ ሆነ? ትላላችሁ። ምክንያቱም ሚስትህን አታልለሃታልና ጌታ በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው፤ እርሷም ጓደኛህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ነበረች። አንድ አላደረጋቸውምን? የመንፈስም ቅሪት ለእርሱ ነው? አንዱስ ምን ፈልጎ ነው? የእግዚአብሔርን ዘር ፈልጎ ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጠላለሁና፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ፥ ልብሱንም በሁከት የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ። በቃላችሁ ጌታን አሰልችታችሁታል። እናንተም፦ እርሱን ያሰለቸነው በምንድን ነው? ትላላችሁ። “ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በጌታ ፊት መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ የት አለ?” በማለታችሁ ነው። እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትደሰቱበትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና፤ የሚመጣበትን ቀን መቋቋም የሚችል ማን ነው? እርሱስ ሲገለጥ የሚቆም ማን ነው? ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቁርባን እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት በሚምሉ፥ የሠራተኛውን ደመወዝ በሚያስቀሩ፥ መበለቲቱንና የሙት ልጅን በሚያስጨንቁ፥ ስደተኛውን በሚገፉ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እኔ ጌታ አልለወጥምና፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ አልጠፋችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዜ ርቃችኋል፥ አልጠበቃችሁትምም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው እንዴት ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ሰርቃችሁኛል። እናንተም፦ እንዴት እንሰርቅሃለን? ብላችኋል። በአሥራትና በቁርባን ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ ሰርቃችሁኛልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ፤ የሰማያቶችን መስኮቶች ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ስለ እናንተ በላተኛውን እገሥጻለሁ፥ የአፈራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ያለውንም ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ሕዝቦች ሁሉ የተባረኩ ብለው ይጠሩአችኋል፥ የደስታ ምድር ትሆናላችሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። በእኔ ላይ የድፍረት ቃላትን ተናግራችኋል፥ ይላል ጌታ። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድነው? ትላላችሁ። እናንተም እንዲህ ብላችኋል፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙን መጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ ፊት ኀዘንተኞች ሆነን መሄድ ምን ይጠቅመናል? አሁንም ትዕቢተኞችን የተባረኩ ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ታንጸዋል፥ እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም። በዚያን ጊዜ ጌታን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ ጌታም አደመጠ፥ ሰማም፥ ጌታን ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያከብሩ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ። እነርሱ የእኔ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ እኔ በምሠራበት ቀን፥ ሰው የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ። ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ። “እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ሥርንና ቅርንጫፍንም አያስቀርላቸውም። ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ ከጋጣ እንደ ወጡ ጥጃዎች ትቦርቃላችሁ። እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጧቸዋላችሁ፥ ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የአገልጋዬን የሙሴን ሕግ አስታውሱ። እነሆ፥ ታላቁና አስፈሪው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼ ምድርን በእርግማን እንዳልመታ፥ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶቻቸው ይመልሳል። የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ መጽሐፍ። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤ ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፤ ኤስሮም አራምን ወለደ፤ አራም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤ ሰልሞን ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝ ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤ እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ፤ ዳዊትም ከኦርዮ ሚስት ሰሎሞንን ወለደ። ሰሎሞን ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤ አሣፍ ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥ ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራም ዖዝያንን ወለደ፤ ዖዝያን ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታም አካዝን ወለደ፤ አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤ ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤ ምናሴ አሞፅን ወለደ፤ አሞፅም ኢዮስያስን ወለደ፤ ኢዮስያስ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ። ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያል ዘሩባቤልን ወለደ፤ ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤ አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዞርን ወለደ፤ አዞር ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤ አኪም ኤልዩድን ወለደ፤ ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛር ማታንን ወለደ፤ ማታን ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ስለ ነበረ ሊያጋልጣት አልፈለገም፥ በስውርም ሊተዋት አሰበ። እርሱ ይህን ሲያስብ ሳለ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርሷ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ይህ ሁሉ የሆነው ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው እንዲፈጸም ነው፦ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” ትርጉሙም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው። ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፥ እንዲህም አሉ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።” ንጉሡ ሄሮድስ ሰምቶ ታወከ፤ መላዋ ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር ታወከች፤ ሊቃነ ካህናትንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በይሁዳ ቤተልሔም ነው፤ በነቢዩ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “በይሁዳ ምድር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ይወጣልና።” ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ። እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፥ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ፥ ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ነው። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ወታደሮችን ልኮ ከሰብአ ሰገል በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያንጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የብዙ ዋይታ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና መጽናናትን እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። እንዲህም አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ።” በነቢዩ በኢሳይያስ “‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” ተብሎ የተነገረለት ይህ ነውና። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጉር የተሠራ ነበር፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም፥ ከይሁዳ ሁሉና በዮርዳኖስም ዙሪያ ካሉ አውራጃዎች ሁሉ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ይጠመቁ ነበር። ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ጥምቀት ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቁጣ እንድታመልጡ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ በልባችሁ ‘አብርሃም አባት አለን’ ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት ይችላል እላችኋለሁ። አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። “እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን ለመሸከም የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውንም ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራ ይከተዋል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን “እኔ በአንተ መጠመቅ ሲገባኝ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?” ብሎ ከለከለው። ኢየሱስ ግን “እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና ለአሁን ፍቀድልኝ፤” ሲል መለሰለት፥ ያንጊዜ ፈቀደለት። ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ከውኃ ወጣ፤ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየ፤ እነሆ፥ ከሰማያት ድምፅ ወጥቶ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” አለ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዲያብሎስ እንዲፈተን መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙ መጥቶ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። እርሱ ግን “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ በመቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመውና “‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ራስህን ወደ ታች ወርውር” አለው። ኢየሱስም “‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። እንደገና ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየውና፥ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “ሂድ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆ መላእክት መጥተው አገለገሉት። ኢየሱስ ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም ክልል ወደ አለችው በባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ በዮርዳኖስ ማዶ ያለ፥ የባሕር መንገድ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና በሞት ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ። በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትን ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝቡ መካከል ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። ዝናው በመላዋ ሶርያ ሁሉ ተሰማ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይ ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፥ አጋንንት ያደሩባቸውን፥ በጨረቃ የሚነሣባቸውንና ሽባዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ከገሊላ፥ ከዐሥሩ ከተሞች፥ ከኢየሩሳሌም፤ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፤ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ይጠግባሉና። ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። “ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” እናንተ የምድሪቱ ጨው ናችሁ፤ ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ግን በምን ይጣፍጣል? በሰው ለመረገጥ ወደ ውጭ ከመጣል በስተቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም። መብራትን አብርተው በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል እንጂ ከዕንቅብ በታች አያኖሩትም፤ በቤትም ላሉት ሁሉ ያበራል። መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ እንግዲህ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ። ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ከሕግ አንዲት ኢዮታ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም። ከእነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንድዋን እንኳ ችላ የሚል ሰዎችንም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ ነገር ግን የሚፈጽመው እንዲሁም የሚያስተምር ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም እላችኋለሁ። “ለቀደሙት ‘አትግደል፥ የገደለ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወንድሙን የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙን ‘የማያስብ’ የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ‘ደደብ’ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። መባህን በመሠዊያው ላይ በምታቀርብበት ጊዜ፥ በዚያ ሳለህ ቅር የተሰኘብህ ወንድም እንዳለ ብታስታውስ፥ መባህን እዚያው በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ፤ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ ከዚያ በኋላ መጥተህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለሎሌው እንዳይሰጥህ ወደ እስር ቤት እንዳትገባ፤ ከባላጋራህ ጋር በመንገድ አብረኸው ስትሄድ ሳለህ ፈጥነህ ተስማማ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት አይቶ የተመኛት ሁሉ ከወዲሁ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ከአንተ ቆርጠህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። “‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት ጽሕፈት ይስጣት’ ተብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞም ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን የማልኸውንም ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በፍጹም አትማሉ፤ በሰማይ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አትማሉ የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ስለዚህ ንግግራችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህ የተረፈ ግን ከክፉው ነው። “‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙት፤ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ሊከስህ ፈልጎ እጀ ጠባብህን ሊወስድ የፈለገ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢያስገድድህ፥ ሁለት ምዕራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚጠይቅህ ስጥ፤ ከአንተ ሊበደር ከሚፈልገው ፊትህን አታዙር። “‘ባልንጀራህን ውደድ፥ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ ይህን በማድረግ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች እንድትሆኑ ነው፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥኣንም ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ሽልማት ታገኛላችሁ? ቀራጮች እንኳ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም የምትሉ ከሆነ ምን የበለጠ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ። “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ መልካምም ሥራችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለበለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ዘንድ ሽልማት አታገኙም። “እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰዎች ዘንድ እንዲከበሩ በምኵራቦችና በመንገድ እንደሚያደርጉት በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ነው። በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል። “ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ በሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡ ና በየመንገዱ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል። “ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ የሚደጋገሙ ቃላትን አትጠቀሙ፥ እነርሱ ብዙ በመናገራቸው የሚሰሙ ይመስላቸዋልና። ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሳትጠይቁት ያውቃልና። ስለዚህ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’ የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ ሰዎችን ይቅር ባትሉ ግን፥ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም። “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ሰዎች መጾማቸውን እንዲያዩላቸው ፊታቸውን ይለውጣሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጾም፥ ራስህን ተቀባ፥ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር ላለው አባትህ እንጂ በሰዎች ዘንድ ጾመኛ ሆነህ እንዳትታይ፤ በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል። “ብልና ዝገት በሚያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁበት በምድር ላይ ሃብት አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልና ዝገት በማያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁበት በሰማይ ሃብትን ሰብስቡ፤ ሃብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ናት። ስለዚህ ዓይንህ ጤናማ ከሆነች፥ ሰውነትህ ሁሉ የበራ ይሆናል፤ ዓይንህ የታመመች ከሆነች ግን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማው እንዴት የበረታ ይሆን! “ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሌላውን ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ስለ ነፍሳችሁ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ ነፍስ ከምግብ ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም፥ ወይም አያጭዱም፥ ወደ ጎተራም አይሰበስቡም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል፤ ታዲያ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል እስቲ ማን ነው? ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። ነገር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እግዚአብሔር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ “ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?” ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብም እነዚህን ሁሉ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃል። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፥ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “ስለዚህ ስለነገ አትጨነቁ፥ ነገ ስለ ራሱ ይጨነቃልና፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ሳትመለከት በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? ወይም እነሆ በዓይንህ ምሰሶ እያለ ወንድምህን ‘ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣልህ ፍቀድልኝ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዓይንህ ያለውን ምሰሶ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። “ጠይቁ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል። የሚጠይቅ ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ የሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማነው? ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን? እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገርን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም! እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግና ነቢያትም ይህ ነውና። “በጠባብዋ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ በዚያም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ጠባብ፥ መንገዱም ቀጭን ነውና፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፥ በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው። በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ የወይን ፍሬ፥ ከኮሸሽላስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬን ያፈራል። መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬን ማፍራት አይችልም፥ መጥፎ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። ያንጊዜ ‘ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ’ እላቸዋለሁ። “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ጠቢብ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በዓለት ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” ኢየሱስ ይህንን ንግግር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው። ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ አንድ ለምጻም መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ” አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም እንዲህ ሲል መለሰ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ከባለሥልጣኖች በታች ነኝ፤ ከእኔ በታች ደግሞ ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ደግሞ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ይከተሉት የነበሩትን እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥቱ ልጆች ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም ለመቶ አለቃው “ሂድና እንደ እምነትህ ይሁንልህ፤” አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ አማቱ በትኩሳት ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋን ዳሰሳት፤ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ መናፍስቶቹን ሁሉ በቃል አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ። ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ “እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ፤” የተባለው እንዲፈጸም ነው። ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በአጠገቡ ሲሰበሰቡ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ። አንድ ጸሐፊ መጥቶ “መምህር ሆይ! ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጉድጓድ፥ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት የለውም፤” አለው። ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለው። ኢየሱስም “ተከተለኝ፤ ሙታንን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤” አለው። ወደ ጀልባ በገባ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ተከተሉት። እነሆ ማዕበሉ ጀልባይቱን እስኪሸፍናት ድረስ በባሕሩ ላይ ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ጌታ ሆይ! ልንጠፋ ነው፥ አድነን፤” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትፈራላችሁ?” አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸው፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ሰዎቹም “ነፋሳትና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፥ ይሄ ማነው?” እያሉ ተደነቁ። ወደ ማዶ ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ስፍራ ወጥተው ወደ እርሱ መጡ፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። እነሆ እንዲህ እያሉ ጮኹ “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?” ከእነርሱም ርቆ ብዙ የዓሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። አጋንንቱም “የምታስወጣን ከሆነ፥ ወደ ዓሣማው መንጋ ስደደን፤” ብለው ለመኑት። እርሱም “ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ወደ አሣማዎቹ ሄደው ገቡ፤ እነሆ የዓሣማዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር ሮጡ፥ በውኆቹ ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። እረኞቹም ሸሹ፤ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም አድረውባቸው በነበሩት ሰዎች የሆነውን አወሩ። እነሆ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድ ለመኑት። ወደ ጀልባ ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። እነሆ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ሆይ! ጽና፤ ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል፤” አለው። እነሆ ከጻፎች አንዳንዶቹ በልባቸው “ይህስ ይሳደባል፤” አሉ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ “ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ‘ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል’ ከማለትና ‘ተነሣና ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአቶችን ሊያስተሰርይ የሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው፤” በዚያን ጊዜ ሽባውን “ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህንን አይተው ፈሩ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አከበሩ። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህንን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ለምን ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ ሂዱና ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤’ የሚለው ምን እንደሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፤” በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ መጥተው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ እድምተኞች ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሆናል። በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖሩታል፤ ሁለቱም ይጠበቃሉ።” ይህንም ሲነግራቸው ሳለ እነሆ አንድ ገዢ መጥቶ እየሰገደ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፥ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እነሆ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ደም የሚፈስሳት ሴት ከኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” ብላ ታስብ ነበርና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ወደ ገዢው ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፥ “ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ዞር በሉ፤” አላቸው። እነርሱ ግን ሳቁበት። ነገር ግን ሕዝቡን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ልጅቱም ተነሣች። የዚህም ወሬ ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረን፤” ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤት በገባ ጊዜ ዓይነ ስውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት። በዚያን ጊዜ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰና “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ፤” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ሄደው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። እየወጡ እያለ እነሆ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑ ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ከቶ ታይቶ አይታወቅም” አሉ። ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሽታንና ሕማምን ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተሞችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ አዘነላቸው፥ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው ነበርና። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ የመከሩን ጌታ ለምኑት።” ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፥ በሽታንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፥ ቶማስና ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፥ ቀናኢው ስምዖንና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸውም፦ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ ወደ ጠፉት በጎች ወደ እስራኤል ቤት ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች፤’ ብላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ነሐስ በመቀነታችሁ አትያዙ፥ ለመንገዳችሁ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባት በማንኛዪቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የተገባው ሰው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤቱም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱ የተገባው ከሆነ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ይሁን፤ ያልተገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። ማንም የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ከሆነ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉችሁ ውጡ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል። “እነሆ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። ከሰዎች ተጠንቀቁ፥ ምክንያቱም ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና፤ ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ። አሳልፈው በሰጡአችሁ ጊዜ፥ እንዴት ወይም ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድም ወንድሙን፥ አባት ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። ስለ ስሜ በሁሉም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ከዚያች ከተማ ቢያሳድዱአችሁ ወደ ሌላዪቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞች አትጨርሱም። “ደቀመዝሙር ከመምህሩ፥ ባርያም ከጌታው አይበልጥም። ደቀመዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባርያም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔልዜቡል ካሉት፥ ቤተሰቦቹንማ እንዴት ከዚህ የበለጠ አይሉአቸው? “እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና። በጨለማ የነገርሁአችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን እርሱን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲትዋ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተ ግን የራስ ጠጉራችሁ ሁሉ እንኳ ተቆጥሮአል። ስለዚህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰዎች ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን በአባቱ ላይ፥ ሴት ልጅን በእናትዋ ላይ፥ ምራትን በአማትዋ ላይ ለማሥነሳት ነው፤ ለሰው ጠላቶቹ ቤተሰቦቹ ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔም ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። መስቀሉን ይዞ በኋላዬ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኛት ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይቀበላል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይቀበላል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ በደቀ መዝሙር ስም ብቻ የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋውን አያጣም።” ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ በኋላ፥ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ሄደ። ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ የተባረከ ነው።” እነርሱ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆ? ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ነውን? አዎን፥ ከነቢይም የሚበልጠውን እላችኋለሁ። “እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም በኃይል ይወስዱአታል። ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና፤ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ እርሱ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ ተቀምጠው እርስ በእርሳቸው እንዲህ እያሉ የሚጠሩ ልጆችን ይመስላሉ፤ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም፥ ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም’ ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘ጋኔን አለበት’ አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘እነሆ በላተኛና ጠጪ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ በሥራዋ ጸደቀች።” በዚያን ጊዜ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይነቅፋቸው ጀመር፤ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በቆየች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “የሰማያትና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን አባት ሆይ! ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ሁሉም ነገር በአባቴ ለእኔ ተሰጥቶአል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞችና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፥ ከእኔም ተማሩ፤ ምክንያቱም እኔ የዋህ በልብም ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜም ቀላል ነውና።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀመዛሙርቱ ተራቡና እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህንን አይተው “እይ! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ካህናት ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት በላ። በሰንበታት በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚያረክሱ ንጹሐንም እንደ ሆኑ በሕጉ አላነበባችሁምን? እላችኋለሁ፥ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ። እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው? ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ። ኢየሱስ ይህንን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው። እንዳያጋልጡትም አዘዛቸው፤ ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ የመረጥሁት አገልጋዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያውጃል። አይከራከርም አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ወደ ድል እስኪያመጣ ድረስ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” ከዚህ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ዲዳውም ተናገረ አየም። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን ሰምተው “ይህ በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። እርሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትከፋፈል መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ እርስ በርስዋ የምትከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁላ አትቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት መቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጡአቸዋል? በዚህም ምክንያት እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማስወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። ወይስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል? ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብ ደግሞ ይበትናል። በዚህም ምክንያት እላችኋለሁ፤ ሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስን የሰደበ ግን አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። “ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ፤ ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከመልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፥ ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህና።” በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁም የሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም። በዚያን ጊዜ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመጣም ባዶ ሆኖ፥ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ይሄድና ከእርሱ የከፉ ሰባት ሌሎች አጋንንትን ከእርሱ ጋር ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የሰውየው መጨረሻ ከፊተኛው ይልቅ የከፋ ይሆናል። ለዚህም ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” ለሕዝቡ ይህን እየተናገረ ሳለ፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ እንዲህ አለው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። እጁንም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም እናቴም ነውና።” በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ፥ በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ብዙ ነገርም በምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። አንዳንዱም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። አንዳንዱም በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም በቀለና አነቀው። አንዳንዱም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ለዚህ ነው በምሳሌ የምነግራቸው ምክንያቱም እያዩ አያዩም፥ እየሰሙም አይሰሙም ወይም አያስተውሉም። እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። መስማትን ትሰማላችሁ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን አትመለከቱም። በዓይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፥ ጆሮአቸው ደንቁሮአል፥ ዓይናቸውም ተጨፍኖአል፤ የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባኩ ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አልሰሙም።” እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም ሲል ነገራቸው “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርሷ ከዘሮች ሁሉ ያነሰች ናት፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም። ይህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም ንገረን፤” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ደግሞ የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራው ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋቶችን ሁሉና ዓመፃን ይሰበስባሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ አግኝቶ መልሶ የሸሸገው የተሰወረ መዝገብ ትመስላለች፤ ከደስታውም ብዛት ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛው። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁ የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላች ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሞቹን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አስቀመጡ፤ ክፉውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀመዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው። ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ በምኵራባቸው ያስተምራቸው ነበር፥ ተገርመውም እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ኃይል ከየት አገኘው? ይህ የጠራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር ያሉ አይደሉምን? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በስተቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። ባለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም። በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፤ አገልጋዮቹንም “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ ኃይል በእርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው፤” አለ። ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮትና እስር ቤት አስገብቶት ነበርና፤ ዮሐንስ “እርሷ ለአንተ ትሆን ዘንድ ተገቢ አይደለም” ይለው ነበርና። ሊገድለው ይፈልግ ነበር፥ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈራቸው። ነገር ግን ሄሮድስ የልደት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ጨፈረች፥ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ ሳሕን አሁን ስጠኝ” አለችው። ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ሲል እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በእስር ቤት አስቆረጠው። ራሱን በሳሕን መጥቶ ለልጅቱ ተሰጣት፤ እርሷም ወደ እናትዋ ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም መጥተው በድኑን ወሰደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ ብቻውን ገለል ወዳለ ቦታ በታንኳ ከዚያ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየከተማው በእግር ተከተሉት። በወረደም ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ ሰዓቱም አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስም “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “እነዚያን ወደዚህ ወደ እኔ አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡን በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር። በዚህ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር በጣም ርቃ ሳለች፥ ነፋስ በተቃራኒው አቅጣጫ ነበርና በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ። ወዲያው ኢየሱስ ተናገራቸው፥ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። እርሱም “ና” አለው። ጴጥሮስም ከጀልባዋ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውሃው ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ብርታት አይቶ ፈራ፤ መስጠም በጀመረም ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ወደ ጀልባዋ በወጡ ጊዜ ነፋሱ ፀጥ አለ። በጀልባዋ የነበሩትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት። ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፤ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ የልብሱን ጫፍ ብቻ ለመንካት ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ። በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህ ለምን የሽማግሌዎችን ልማድ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና” አሉት። እርሱም “እናንተስ ስለ ልማዳችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ሲል መለሰላቸው። እግዚአብሔር ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ ደግሞም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት’ ብሎ አዞአልና፤ እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ ‘አባቱን ወይም እናቱን “ከእኔ የምትጠቀመው ሁሉ መባ ነው የሚል ሁሉ፥ አባቱን አያከብርም”’ ስለ ልማዳችሁም ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ ትንቢት በትክክል ተናገረ፥ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤ የሰው ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።” ሕዝቡንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው “ስሙ አስተውሉም፤ ወደ አፍ የሚገባው ሰውን አያረክሰውም፤ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ታውቃለህን?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ።” ጴጥሮስም መልሶ “ይህንን ምሳሌ ተርጉምልን” አለው። እርሱም “እናንተም እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ እነዚህ ሰውን ያረክሱታል። ከልብ ክፉ ሐሳብ፥ መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፥ ባልታጠበ እጅ መብላት ግን ሰውን አያረክሰውም።” ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር መጥታ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ ማረኝ፤ ሴት ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድ ቃልም አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ከኋላችን እየጮኸች ነውና አሰናብታት” እያሉ ለመኑት። እርሱም “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ነው እንጂ ለሌላ አይደለም” ሲል መለሰ። እርሷ ግን መጥታ እየሰገደች “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” አለች። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል መልካም አይደለም።” እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ! ነገር ግን ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” ሲል መለሰላት። ሴት ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ዲዳዎችን፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፥ በኢየሱስም እግር ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲፈወሱ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ፥ ምክንያቱም ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋል የሚበሉት ግን የላቸውም፤ በመንገድ ላይ እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልፈልግም” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “በዚህ በምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ የሚያጠግብ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት። ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣዎቹን ይዞ አመሰገነ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ወደ ጀልባዋ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሊፈትኑት መጡና ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሲመሽ ‘ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ። ጠዋት ደግሞ ‘ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ መለየት ታውቃላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መለየት አትችሉም። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።” ከዚህ በኋላ ትቶአቸው ሄደ። ደቀመዛሙርቱ ወደ ማዶ በሚሻገሩበት ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም ይህንን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስላልያዛችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? አሁንም አታስተውሉምን? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ በቅቶ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ በቅቶ ስንት ቅርጫት እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ።” ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠነቀቁ እንዳልነገራቸው ተገነዘቡ። ኢየሱስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ወደሚባል አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎች ኤልያስ፥ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይነግሱባትም። የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” ከዚህ በኋላ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት ከሽማግሌዎች፥ ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ብዙ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ጀመር። ጴጥሮስም ገለል አድርጎ ወስዶ “ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይድረስብህ” ብሎ ይገሥጸው ጀመር። እርሱ ግን ዞሮ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፤ አንተ ሰይጣን! ለእኔ ዕንቅፋት ነህ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና።” አለው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣልና፤ በዚያን ጊዜ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ እዚህ ከቆሙት መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ደግሞ ለኤልያስ የሚሆን ሦስት ዳሶችን በዚህ እንሥራ” አለው። እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆ ከደመናው ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የተወደደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀመዛሙርቱ ይህንን ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም መጥቶ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፥ አትፍሩ” አላቸው። ዐይኖቻቸውን በገለጡ ጊዜ ግን ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ ጻፎች ‘ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል’ ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ኤልያስ በእርግጥ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ነገር ግን ኤልያስ ከዚህ በፊት መጥቷል እላችኋለሁ፤ ነገር ግን የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበላል” አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አወቁ። ወደ ሕዝቡም በመጡ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ልጄን ማርልኝ፥ በሚጥል በሽታ ክፉኛ ይሣቀያል፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ላይ ብዙ ጊዜ ደግሞ በውሃ ውስጥ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የማያምንና ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት” ኢየሱስም ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፤ ልጁም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት። እርሱም የእምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ “ከዚህ ወደዚያ ሂድ” ብትሉት ይሄዳል፤ የሚያቅታችሁ ምንም ነገርም የለም። እንዲህ ዓይነቱ በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም። በገሊላ ተሰባስበው ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አላቸው። እጅግም አዘኑ። ወደ ቅፍርናሆም በደረሱ ጊዜ ሁለት ዲናር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና “መምህራችሁ ሁለት ዲናር አይከፍልምን?” አሉት። “ይከፍላል” አለ። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ “ስምዖን ሆይ! ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው? ወይስ ከሌሎች?” አለው። እርሱም “ከሌሎች” አለው፤ ኢየሱስም “ስለዚህ ልጆች ነጻ ናቸው። ነገር ግን እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕር ሂድና መንጠቆ ጣል፥ በመጀመሪያ የሚወጣውን ዓሣ ውሰድ፥ አፉን ስትከፍት እስታቴር ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ የእኔንና የአንተን ክፈል።” በዚያች ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ሕፃን ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው፤ እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንደዚህ ሕፃን ትሑት የሆነ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጠው እርሱ ነው። “እንደዚህ ሕፃን ያለውን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል። “ከማሰናከያው የተነሣ ዓለም ወዮላት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ የማሰናከያ ማምጫ ምክንያት የሆነው ያ ሰው ግን ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ካሰናከለህ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፥ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ካሰናከለህ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል። “ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለማዳን ነው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፥ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። እንደዚሁም ደግሞ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። “ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ገሥጸው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ታተርፈዋለህ፤ ባይሰማህ ግን አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ቃል ነገር ሁሉ ይጸናልና፥ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ቁጠረው። እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ በሚለምኑት በማንኛውም ነገር ሁሉ ቢስማሙ፥ በሰማያት ባለው አባቴ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው አለሁና።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ስንት ጊዜ ቢበድለኝ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባርያዎቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ፥ አስር ሺህ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። መክፈልም ሲያቅተው እርሱ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ያለውም ሁሉ ተሽጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ስለዚህ ባርያው ወድቆ ተንበረከከና ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ አለው። የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። ነገር ግን ያ ባርያ ከዚያ ወጥቶ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን ከባልንጀሮቹ ባርያዎች አንዱን አገኘና ‘ዕዳህን ክፈለኝ’ ብሎ አንቆ ያዘው። ያል ባልንጀራው ባርያ ወድቆ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ ብሎ ለመነው። እርሱ ግን አልፈለገም፤ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ሄዶ በወኅኒ አሳሰረው። ባልንጀሮቹ ባርያዎችም ያደረገውን ሁሉ አይተው እጅግ አዘኑ፤ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። ከዚያ በኋላ ጌታው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባርያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ ጌታውም ተቆጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለሚያሠቃዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተም እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ የሰማዩ አባቴ ደግሞ እንዲሁ ያደርግባችኋል።” ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፥ ከገሊላ ወጥቶ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ መጣ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም እዚያ ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሊፈትኑት ፈልገው “ሰው በማንኛውም ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት እንዳደረጋቸው አላነበባችሁምን? ዓለም ‘በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” እነርሱም “ታዲያ ሙሴ ለምን የፍቺ ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት አዘዘ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው “ሙሴ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ በልባችሁ ጥንካሬ ምክንያት ነው፤ ከመጀመሪያው ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ በዝሙት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” ደቀ መዛሙርቱም “የባልና የሚስት ግንኙነት እንዲህ ከሆነስ መጋባት ጥሩ አይደለም” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ይህ ንግግር የተሰጠው ካልሆነ በስተቀር ሁሉም አይቀበለውም፤ ከእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፤ ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።” በዚያን ጊዜ እጆቹን ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው። ነገር ግን ኢየሱስ እንዲህ አለ “ሕፃናቱን ተዉአቸው፤ ወደ እኔም እንዲመጡ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ናትና።” እጆቹን ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። እነሆ አንድ ሰው ቀርቦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ” አለው። እርሱም “ስለ መልካም ነገር እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ከፈልግህ ግን ትእዛዛቱን ጠብቅ፤” አለው። እርሱም “የትኞቹን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።” ወጣቱም “ይህን ሁሉ ጠብቄአለሁ፤ አሁን የሚጐድለኝ ምንድነው?” አለው። ኢየሱስም “ፍጹም መሆን ከፈለግህ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማያት መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። ወጣቱ ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጸጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ከባድ ነው። ደግሜ እላችኋለሁ፤ ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።” ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ግን አያቸውና እንዲህ አላቸው “ይህ በሰው ዘንድ የማይቻል ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ የምናገኘው ታዲያ ምንድነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ስለተከተላችሁኝ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በዓሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፥ በዓሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይም ትፈርዳላችሁ። ማንም ስለ ስሜ ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘለዓለም ሕይወትንም ይወርሳል። ነገር ግን ብዙዎቹች ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። “መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሰደዳቸው። ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ እነርሱንም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው። በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’” ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ሳለ፥ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰዳቸው፥ በመንገድም ሳሉ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄድን ነው፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ እንዲያላግጡበት፥ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ከልጆችዋ ጋር ወደ እርሱ ቀረበች። እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” እነርሱም “እንችላለን” አሉት። እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ መስጠት የእኔ አይደለም ነገር ግን እርሱ በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ነው፤” አላቸው። ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ በሁለቱም ወንድማማቾች ተቆጡ። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች ጌትነታቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታላላቆቹም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም መካከል ፊተኛ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባርያ ይሁን፤ የሰው ልጅም ሊያገለግል፥ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት። ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ አዩ፥ ተከተሉትም። ወደ ኢየሩሳሌምም በቀረቡ ጊዜ ወደ ደብረዘይት ወደ ቤተ ፋጌ መጡ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ በዚያን ጊዜ የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ምንም ቢላችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉ፤ ወዲያውም ይልካቸዋል።” ይህም በነቢዩ እንዲህ የብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦ “ለጽዮን ልጅ “እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፥ በሉአት።” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያይቱንና ውርንጫዋን አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። እጅግ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። ከፊቱ ይሄዱ የነበሩትና ይከተሉት የነበሩት ሕዝብ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማን ነው?” ብሎ መላው ከተማ ተናወጠ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበሮች ገለበጠ፤ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን ሊቃነ ካህናትና ጻፎች ያደረገውን ድንቅ ነገርና በመቅደስም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቆጡ፤ “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት። ኢየሱስም “አዎን እሰማለሁ፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ራበው። በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን ከቅጠል በስተቀር ምንም አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስዋ ዛፍም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን አይተው በመደነቅ “የበለስዋ ዛፍ ወዲያውኑ እንዴት ደረቀች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ፥ በበለሲቱ ዛፍ እንደተደረገው ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ወደ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እኔም ደግሞ አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ነው ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ መጀመሪያውም ሄዶ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ወደ ወይኔ አትክልት ሥፍራ ሂድና ሥራ’ አለው። እርሱም ‘አልሄድም’ አለ፤ ቆይቶ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ሄዶ እንዲሁ አለው እርሱም ‘እሺ ጌታዬ’ ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ዘማውያን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበር፥ አላመናችሁትም፤ ቀራጮችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ በመጨረሻም ይህንን አይታችሁ እንኳ ልታምኑት ንስሐ አልገባችሁም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ የእርሻ ባለቤት ነበረ፤ እርሱም ቅጥር ቀጠረለት፤ መጭመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራለት፤ እርሻውንም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዲቀበሉለት ባርያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹም ባርያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበዙ ሌሎች ባርያዎችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው። በመጨረሻም ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት ሥፍራ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ሥፍራ ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ሁኔታ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ሥፍራ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሕፍት አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ያደቅቀዋል።” ሊቃነ ካህናትና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አወቁ። ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈሩ። ኢየሱስ አሁንም በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ እንዲጠሩ ባርያዎቹን ላከ፤ እነርሱ ግን ሊመጡ አልፈለጉም። ሌሎች ባርያዎችን ደግሞ ልኮ ‘የታደሙትን እነሆ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ግብዣ ኑ፤ በሉአቸው፤’ አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባርያዎቹን ይዘው ሰደቡአቸው፤ ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባርያዎቹን እንዲህ አላቸው ‘ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ የታደሙት ግን የተገቡ አልሆኑም፤ ስለዚህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ።’ እነዚያም ባርያዎች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንና በጎዎችን ሰበሰቡ፤ የሰርጉም ቤት በተጋባዦች ተሞላ። “ንጉሡም ተጋባዦቹን ለማየት በገባ ጊዜ፥ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። ‘ወዳጄ ሆይ! የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፤’ አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።” ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በንግግሩ እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ላኩበት፤ እነርሱም እንዱህ አሉት “መምህር ሆይ! እውነተኛ እንደሆንህ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ለማንምም አታደላም፤ የሰውን ፊት አታይምና፤ ምን ይመስልሃል? እስቲ ንገረን፥ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ ግብዞች፥ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ብር አሳዩኝ።” እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም “ይህ መልክና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው። ይህንንም ሰምተው ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ። በዚያን ቀን የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሏል። ሰባት ወንድማማቾች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ሞተ፤ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው፥ ሦስተኛው፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ እንዲህ ሆነ። ከሁሉም በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። ታዲያ በሙታን ትንሣኤ ቀን ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች? ሁሉም አግብተዋታልና።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ስታችኋል፥ ምክንያቱም መጻሕፍትን ወይም የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና። በሙታን ትንሣኤ ጊዜ እንደ መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም ወይም አይጋቡም። ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ እንዲህ ተብሎ የተነገረውን አላነበባችሁምን? ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ሕዝቡም ይህንን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ። ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “መምህር ሆይ! ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች?” እርሱም እንዲህ አለው “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ።’ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርሷም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግና ነቢያት ሁሉ ተንጠልጥለዋል።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማንስ ልጅ ነው?” እነርሱም “የዳዊት ልጅ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት ጌታ ብሎ ጠራው እንዲህ ሲል፦ ጌታ ጌታዬን “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፤ “ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” አንድም ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ ማንም አልነበረም፤ ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ አንድስ እንኳ አልነበረም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል፤ ስለዚህ የሚሉአችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ፤ የሚናገሩትን አያደርጉትምና። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም አስረው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው እንኳ ሊነኩት አይፈልጉም። ሥራቸውን ሁሉ የሚያደርጉት ሰው እንዲያይላቸው ነው፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ፤ በግብዣ ላይ የክብርን ስፍራ፥ በምኵራብም የክብርን ወንበር፥ በገበያ ቦታ ሰላምታና በሰዎች ደግሞ መምህር ተብለው መጠራትን ይፈልጋሉ። እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ነውና፤ እናንተ ሁላችሁ ደግሞ ወንድማማቾች ናችሁ። በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ፥ አባታችሁ አንድ እርሱም በሰማይ ያለው ነውና። መሪዎች ተብላችሁ አትጠሩ፥ መሪአችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ከእናንተ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሁን። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! መንግሥተ ሰማያትን በሰዎች ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ አንድ ሰው የእምነታችሁ ተከታይ ለማድረግ በባሕርና በደረቅ ትዞራላችሁ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ። “እናንተ ዕውራን መሪዎች ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፥ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ የምትሉ ወዮላችሁ። እናንተ ዕውሮችና ሞኞች! የትኛው ይበልጣል? ወርቁ ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግሞም ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ማንም በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ ትላላችሁ። እናንተ ዕውሮች! የትኛው ይበልጣል? መባው ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል በመሠዊያውና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለውም በቤተ መቅደሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይ የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በሚቀመጠው ይምላል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ ምክንያቱም ከአዝሙድ፥ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ታወጣላችሁ፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ፍርድን፥ ምሕረትንና እምነትን ትተዋላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ እነዚህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውራን መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ የጽዋውንና የሳሕኑን ውጭ ታጠራላችሁ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ራስን አለመግዛት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ንጹሕ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ በውጫቸው አምረው የሚታዩ በውስጣቸው ግን በሙታን አጥንትና በርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ትመስላላችሁና። እንዲሁም እናንተ በውጭ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ሕገ ወጥነት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁ የጻድቃንንም መቃብር ታስጌጣላችሁና፥ ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር’ ትላላችሁ። እንግዲህ የነቢያት ገዳዮች ልጆች መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ፈጽሙ። እናንተ እባቦች! የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ እነሆ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችና ጻፎችን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ ትሰቅላላችሁም፥ ከእነርሱም አንዳንዶቹን በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዱአቸዋላችሁ፤ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው ጻድቅ ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርሳል። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድዪ ወደ አንቺ የተላኩትንም የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።” ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀመዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የሚቀር የለም።” በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘መሢሑ እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ አስተውሉ፥ አትደንግጡ፥ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከሕገ ወጥነት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል። “ስለዚህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በጣራ ላይ ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ሊወስድ ወደ ኋላው አይመለስ። በነዚያ ቀናት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ መሢሑ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ታላላቅ ምልክትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። ስለዚህ ‘እነሆ በበረሀ አለ’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ በቤት ውስጥ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ቀናት መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይሎችም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ጋር ይልካቸዋል፤ የእርሱን ምርጦች ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ዛፍ ተማሩ፤ ቅርጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠሎችዋም ሲያቆጠቁጡ፥ ያንጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች አንዷ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “ነገር ግን ይህን እወቁ፤ ባለቤት ሌባ ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። “ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልህ ባርያ ማን ነው? ጌታው ሲመጣ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ የተባረከ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ነገር ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ክፉ ባርያ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባርያዎች መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ ለሁለት ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ደናግል ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሞኞች አምስቱ ደግሞ ብልሆች ነበሩ። ሞኞቹ መብራታቸውን ይዘው ነገር ግን ዘይት አልያዙም ነበር፤ ብልሆቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራው፤ ልትቀበሉት ውጡ’ የሚል ጩኸት ተሰማ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ብልሆቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን’ አሉአቸው። ብልሆቹ ግን ‘ለእኛና ለእናንተ ላይበቃ ይችላል፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሊገዙ በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ አሉት። እርሱ ግን ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም’ ሲል መለሰላቸው። ቀኑንና ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “እንግዲህ ወደ ሌላ አገር ሊሄድ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት እንደሰጣቸው ሰው ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄደና ምድርን ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባርያዎች ጌታ መጥቶ ከእነርሱ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አምጥቶ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። ባለ ሁለት መክሊቱም ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፤ ስለፈራሁም ሄጄ መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ የራስህ ይኸውልህ’ አለ። ጌታውም እንዲህ ሲል መለሰለት ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባርያ፥ ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንሁበትም እንደምሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች መስጠት ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ያለኝን ከነወለዱ እወስደው ነበር። በሉ እንግዲህ መክሊቱን ውሰዱበትና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይረባውን ባርያ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የአባቴ ቡሩካን! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ታምሜ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’ ጻድቃኑም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል ‘ጌታ ሆይ! መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና ወደ አንተ መጥተን ጠየቅንህ?’ ንጉሡም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።’ ከዚህ በኋላ በግራው ያሉትን ደግሞ እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የተረገማችሁ! ከእኔ ወዲያ ራቁ! ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’ እነርሱም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል ‘ጌታ ሆይ! ተርበህ ወይም ተጠምተህ ወይም እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ ወይም ታመህ ወይም ታስረህ መቼ አየንህና አላገለገልንህም?’ ያንጊዜ እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ያላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ እንዳላደረጋችሁት ነው።’ እነዚህ ወደ ዘለዓለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ።” እንዲህም ሆነ፤ ኢየሱስ እነዚህን ቃሎች ሁሉ ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” በዚያን ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህኑ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስን በተንኰል ይዘው ሊገድሉት ተማከሩ፤ ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ። ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በራሱ ላይም አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቆጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና።” ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታስጨንቁአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ይህን ሽቶ በሰውነቴ ላይ በማፍሰስ ለቀብሬ አደረገችው። እውነት እላችኋለሁ ይህ የምሥራች በሚሰበክበት በመላው ዓለም፥ ይህ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ እንዲህ አላቸው “አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ ምን ትሰጡኛላችሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና፥ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።” ይህንም ገና ሲናገር ሳለ፥ እነሆ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ዱላ ይዘው ከእርሱ ጋር መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡና እጃቸውን በኢየሱስ ላይ ጫኑ፥ ያዙትም። እነሆ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህኑን ባርያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። ወይስ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት አሁን ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነ ‘እንደዚህ መሆን አለበት’ የሚሉት መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ወጣችሁን? ዕለት በዕለት በመቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?” ጴጥሮስም ከቤት ውጪ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ። ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ ሌላዪቱ አየችውና በዚያ ለነበሩት “ይህም ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ እየማለ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያ ቆመው የነበሩት ጠጋ ብለው ጴጥሮስን “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህ ያስታውቅብሃልና” አሉት። በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ይራገምና ይምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። በነጋም ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስን ሊገድሉት ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለሊቃነ ካህናቱና ለሽማግሌዎቹ መለሰላቸው፤ እንዲህም አለ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ እኛ ምን አገባን? ጉዳዩ የራስህ ነው፤” አሉት። ብሩን በቤተ መቅደስ ጥሎ ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። ሊቀ ካህናቱም ብሩን አንሥተው “የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ። ተማክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በዚህም ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተብሎ ይጠራል። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ “ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ወሰዱ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት።” ኢየሱስ በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ” አለው። በሊቃነ ካህናትና በሽማግሌዎች ሲከሰስ ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ነገር እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም፤ በዚህም ገዢው እጅግ ተደነቀ። በዚያ በዓል፥ ገዢው ሕዝቡ የወደደውን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። ስለዚህ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ ኢየሱስ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ፥ ሚስቱ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ ጻድቅ ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። ሊቃነ ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ግን በርባን እንዲለቀቅ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፋ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም “በርባንን” አሉ። ጲላጦስም “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም “ይሰቀል!” አሉ። እርሱም “ምን ክፉ ነገር ሠራና?” አለ፤ እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስም ይህ ነገር ሁከት ከማስነሳት በስተቀር ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ፥ ውሃ ወስዶ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ጉዳዩ የእናንተ ነው፤” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት፤ ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰቡ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ካባ አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፤ በፊቱም ተንበርክከው “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ አፌዙበት፤ ተፉበት፤ መቃውንም ነጥቀው ራሱን መቱት። ከአፌዙበትም በኋላ ካባውን ገፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የሚባል የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጉሙ የራስ ቅል ስፍራ ወደሚባል ጎልጎታ ወደ ተባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልፈለገም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሶቹን ዕጣ ጥለው ተካፈሉት፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ምክንያት “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ አንዱ ደግሞ በግራው ተሰቀሉ። በዚያ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህሰ እስቲ ከመስቀል ውረድ፤” ይሉት ነበር። እንዲሁም ደግሞ ሊቃነ ካህናት፥ ከጻፎችና ከሽማግሌዎች ጋር እያፌዙ እንዲህ አሉት፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ነው፤ አሁን ከመስቀል ይውረድና እኛም በእርሱ እናምናለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሏልና የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም ደግሞ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ኢየሱስ “ኤሊ ኤሊ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆሙት ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው “ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወስዶ የወይን ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አስሮ አጠጣው። የተቀሩት ግን “ተወው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው ከነበሩት የብዙ ቅዱሳን በድን ተነሣ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስቷ ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አሉ። ኢየሱስን እያገለገሉት ከገሊላ የተከተሉት፥ በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች እዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያምና የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነበረ፤ እርሱም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፤ ከዐለት በወቀረው በአዲሱ መቃብሩ አኖረው፤ በመቃብሩ በር ላይ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። እዚያም መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር። በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ፥ ሊቃነ ካህናትና ፈሪሳውያን ከጲላጦስ ጋር ተሰበሰቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “ጌታ ሆይ! ያ አሳች በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ’ እንዳለ ትዝ አለን። ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡም ‘ከሙታን ተነሥቶአል’ እንዳይሉ፥ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ የኋለኛው ስሕተት ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል።” ጲላጦስም “ጠባቂዎች አሉላችሁ፤ ሄዳችሁ እንደምታውቁት አስጠብቁ፤” አላቸው። ሄደውም መቃብሩን ድንጋዩን በማተም ጠባቂዎች አቆሙ። በሰንበት መጨረሻ ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። እነሆ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ መጥቶም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩ እንደ መብረቅ፥ ልብሱ ደግሞ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። እርሱን ከመፍራት የተነሣ ጠባቂዎቹ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ ሞተ ሰው ሆኑ። መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁና፤ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአልና፤ ተኝቶ የነበረበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁ ሂዱና ‘ከሙታን ተነሥቶአል፤ እነሆ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።” በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ፈጥነው ከመቃብሩ ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። እነሆ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ሄዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል” አላቸው። ሲሄዱም ሳሉ እነሆ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለሊቃነ ካህናቱ አወሩ። ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩና ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸው፥ እንዲህም አሉአቸው፦ “‘እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ። ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደሆነ፥ እኛ እናሳምነዋለን፤ እናንተም ከሥጋት ነጻ እንድትሆኑ እናደርጋለን።” እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ይወራል። ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፤ ባዩትም ጊዜ ሰገዱ፤ አንዳዶቹ ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፥ በወልድና መንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” የእግዚአብሔር ልጅ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ፥ በነቢዩ በኢሳይያስ፥ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ።” ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኃጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ። የይሁዳ አገር በሞላ፥ የኢየሩሳሌም ሰዎች በጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቁ። ዮሐንስ የግመል ጠጉር ይለብስ፥ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ፥ አንበጣና የበረሓ ማር ይበላ ነበር። ስብከቱም፥ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፥ ከእኔ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፥ ሰማያት ተከፍተው፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ። መንፈስ ቅዱስም ወዲያው ወደ በረሓ መራው፤ በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በበረሓ ቆየ። ከአራዊትም ጋር ነበር፤ መላእክትም አገለገሉት። ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፥ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፥ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ እልፍ እንዳለ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፥ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር አባታቸውን በጀልባው ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሓፍት ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፥ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኃይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ። ሕዝቡ በሙሉ በመደነቅ፥ “ይህ ምንድነው? በሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ይህ አዲስ ትምህርት ምንድነው?” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ። ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። የስምዖን አማት በትኩሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኩሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር። ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፥ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ጀመር፤ ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዉ ሁሉ ይፈልግሃል” አሉት። እርሱም፥ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። ስለዚህ ወደ ምኵራባቸው እየገባ በመስበክና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር። አንድ ለምጻምም ወደ እርሱ ቀርቦ ከፊቱ በመንበርከክ፥ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ኢየሱስም ለሰውየው በመራራት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፥ “እፈቅዳለሁ፥ ንጻ” አለው። እርሱም ወዲያው ከለምጹ ነጻ፤ ከበሽታውም ተፈወሰ። ኢየሱስም ሰውየውን አጥብቆ በማስጠንቀቅ እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ “ለማንም አንድ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ምስክር እንዲሆናቸው ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ስለ መንጻትህም ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። ሰውየው ግን በሄደበት ሁሉ ነገሩን በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም አሠራጨ፤ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማንኛውም ከተማ በግልጽ መግባት አልተቻለውም፤ ከዚህም የተነሣ ከከተማ ውጭ በሚገኙ ሰዋራ ቦታዎች መኖር ጀመረ፤ ሰዎች ግን ከየአቅጣጫው እርሱ ወዳለበት ይመጡ ነበር። ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ፤ በቤት ውስጥ እንዳለም ተሰማ። ሰዎች ከበሩ ውጭ ያለው ስፍራ እንኳን እስኪጠባቸው ድረስ ተሰበሰቡ፤ እርሱም ቃሉን ይነግራቸው ነበር። አራት ሰዎችም አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው አመጡለት። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ማቅረብ ስላልቻሉ፥ እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፤ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤” አለው። በዚያም ተቀምጠው ከነበሩ አንዳንድ ጻሐፍት በልባቸውም “ይህ ሰው ስለምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል፤” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ ወዲያው አውቆ እንዲህ አላቸው “በልባችሁ ይህን ስለምን ታስባላችሁ? ሽባውን ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤’ ከማለትና ‘ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ፤’ ከማለት የቱ ይቀላል? ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ብሎ ሽባውን፦ “አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ። ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና “ተከተለኝ፤” አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ፤ ይከተሉትም ነበር። ጸሐፍት ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ “ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድነው?” አሉ። ኢየሱስም ሰምቶ “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም፤” አላቸው። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር። መጥተውም “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጾሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ስለ ምንድነው?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጾሙ አይችሉም። ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ወራትም ይጾማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል፤ የወይኑም ጠጅ ይፈሳል፤ አቁማዳውም ይጠፋል፤ አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።” በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀመዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። ፈሪሳውያንም “እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለምን ያደርጋሉ?” አሉት። እርሱም “ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ደግሞ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው፤” አላቸው። ኢየሱስ እንደገና ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ እነርሱም በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ አይተው ሊከስሱት ፈልገው ይጠባበቁት ነበር። እርሱም እጁ የሰለለችውን ሰው “ተነሥ! በመካከል ቁም” አለው። ከዚያም “በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዷልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ። ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ፥ ዙሪያውን በቁጣ ተመለከተና ሰውየውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም ዘረጋ፤ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ተማከሩበት። ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ ያደረገውን ነገር ሁሉ ሰምተው፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ፥ ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጡ። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ እንዳያስጨንቁት ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው ያጨናንቁት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” እያሉ ጮኹ። እርሱም ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው። ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲሆኑና ለመስበክም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” አላቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡት ዐሥራ ሁለቱም፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፤ ቦአኔርጌስ፥ ማለትም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሰየማቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስን፤ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርተሎሜውስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀነናዊው ስምዖን፥ እና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ከዚያም ወደ ቤት ገቡ፤ ምግብ መመገብ እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘመዶቹም “አእምሮውን ስቷል” ሲባል ሰምተው ሊይዙት መጡ። ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጸሐፍትም “በብዔልዜቡል ተይዟል! ደግሞም በዚህ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል!” ብለው ተናገሩ። እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን ሰይጣንን ሊያስወጣ እንዴት ይችላል? መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤተሰብ ሊቆም አይችልም። ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ቢነሣና ቢለያይ መጨረሻው ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። ነገር ግን ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ንብረቱን መዝረፍ የሚችል የለም፤ ያንጊዜ ግን ቤቱን ይዘርፋል። “በእውነት እላችኋለሁ፤ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ፥ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘለዓለም ጥፋት ይሆንበታል እንጂ ለዘለዓለም አይሰረይለትም።” ምክንያቱም “ርኩስ መንፈስ አለበት፤” ብለዋል። የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፤ በውጪም ቆመው ወደ እርሱ ሰው ላኩና አስጠሩት። ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና “እነሆ፥ እናትህ፥ ወንድሞችህና እኅቶችህ በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል፤” አሉት። እርሱም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቃቸው። በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም እየተመለከተ፥ “እነሆ! እናቴና ወንድሞቼ! የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም፥ እናቴም ነው” አለ። እንደገናም በባሕር ዳርቻ ያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረች ጀልባ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ነገር አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው፤ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ አደገ፤ አድጎም ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ስልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ፤” አለ። ብቻውንም በሆነ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በዙሪያው የነበሩት ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፥ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፦ ተመልሰው ይቅር እንዳይላቸው፥ ‘ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤ መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’” አላቸው። እንዲህም ሲል ጠየቃቸው፦ “ይህን ምሳሌ ያልተረዳችሁ፥ እንዴት ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ ታውቃላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የነበሩት፦ እነርሱ በሰሙት ጊዜ ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸው ናቸው። እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ለጊዜው ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፤ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፤ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።” እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” አላቸውም “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” እርሱም እንዲህ አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷአልና ወዲያው ማጨድ ይጀምራል።” እርሱም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርሷም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች፤ ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታወጣለች።” መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፤ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀመዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ “ወደ ማዶ እንሻገር፤” አላቸው። ሕዝቡንም ትተው በታንኳዪቱ ውስጥ እንዳለ ወሰዱት፤ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውሃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ቀስቅሰውትም “መምህር ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ዝም በል፤ ፀጥ በል፤” አለው። ነፋሱም ተወ፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። “እንዲህ የምትፈሩት ስለምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?” አላቸው። እጅግም ፈሩና “እንዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ። ከባሕሩ ማዶ ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደ ተባለ አገር መጡ። ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፥ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጣና ወደ እርሱ መጣ። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያረጋጋው የሚችል አልነበረም። በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኸ ሰውነቱን በድንጋይ ይቆራርጥ ነበር። ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾም፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው። ይህንንም ያለው፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው፤” አለው፤ ከሀገር ውጭ እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው። በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ይሰማራ ነበርና፤ ኢየሱስን፥ “ወደ አሣማዎቹ እንድንገባ ስደደን፤” ብለው ለመኑት። እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡ፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በርግገው ከገደሉ አፋፍ ወደ ባሕሩ ተወረወሩ፤ በባሕሩ ውስጥም ሰጠሙ። እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠርም አወሩ፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት መጡ። ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፥ የአጋንንት ሠራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፥ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ተቀምጦ አዩት፤ ፍርሃትም አደረባቸው። ይህንን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ለያዘው ሰው የሆነውንና በአሳማዎቹም የተደረገውን አወሩ። ከዚያም ሀገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። ኢየሱስም ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፥ በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር አብሮት ለመሆን ለመነው። ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ይልቁን፥ “ወደ ቤትህ ወደ ዘመዶችህም ሂድ፤ ጌታም ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ምሕረት እንዳሳየህ ንገራቸው” አለው። እርሱም ሄደ፤ ኢየሱስም ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተማ” በተባለው አገር በየስፍራው ያበስር ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ። ኢየሱስ እንደገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፥ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩም አጠገብ እንዳለ፤ ከምኲራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው፥ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፥ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም እያጨናነቀው ተከተለው። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለ መድኀኒቶችም ዘንድ ብዙ ተሠቃይታ፥ ያላትን ሁሉ ጨረሰች እንጂ አልተሻላትም ነበር፤ እንዲያውም ሕመሙ ብሶባት ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፥ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፥ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን እንኳ ብነካ ይፈውሰኛል” በማለት ነበር። የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ እንደዳነች በሰውነቷ ታወቃት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዞሮ፥ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፥ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን? አሉት።” እርሱም ይህን ያደረገችው ማን እንደ ሆነች ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም የተደረገላትን በማወቅዋ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ” አላት። ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፥ ሰዎች ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥተው የምኵራብ አለቃውን፥ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ ያሉትን ቢሰማም የምኵራቡ ን አለቃ፥ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት በደረሱ ጊዜ፥ ሲታወኩ፥ ሰዎቹም ሲያለቅሱና አምርረውም ሲጮኹ ተመለከተ። ወደ ውስጥ ገብቶም፥ “ይህን ያህል ለምን ትታወካላችሁ ለምን ታለቅሳላችሁ? ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጣ፤ የልጅቱንም አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን አስከትሎ ልጅቱ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም የልጅቱን እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም፥ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። ልጅቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ መራመድ ጀመረች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ ሰዎቹም እጅግ በመደነቅ ተደመሙ። እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፥ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፥ የያዕቆብና የዮሳ፥ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፥ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹ መካከል በቤተሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፥ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፥ “የዚህ ዓይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፥ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፥ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፥ እኔ ራሱን ያስቆረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷአል አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፥ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፥ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያዳምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምንቱ፥ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው፤ ንጉሡም ብላቴናዪቱን፥ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፥ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፥ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ አዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፥ የዮሐንስን ራስ ቆርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቆረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፥ “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷአል፤ በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” እርሱ ግን መልሶ፥ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፥ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው። አይተውም፥ “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ።” ከዚያም፥ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም መቶ መቶና አምሳ አምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈላቸው። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከተበላው እንጀራና ዓሣ፥ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ። እንጀራውንም የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ወዲያውም እርሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቤተሳይዳ ቀድመውት እንዲሻገሩ አዘዛቸው፤ ከዚያም ትቷቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፥ ደቀመዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፥ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሏቸው ጮኹ፤ ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፥ “አይዟችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሯቸው ሆነ፤ ነፋሱም ፀጥ አለ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤ የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር። በተሻገሩም ጊዜ፥ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ። ወዲያው እንደ ወረዱም፥ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳን ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር። ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለትም ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፥ በሥርዓቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ ሳሕንና ዐልጋን እንደማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፥ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ስለ ግብዞች ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልከኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዓት ብቻ ነው። ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። ደግሞም፥ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ። ሙሴ፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ፈጽሞ ይሙት ብሎ ነበርና፤ እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፥ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቁርባን ይኸውም መባ አድርጌለሁ ቢላቸው፥ እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።” ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፥ “እናንተም ነገሩ አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና። ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ። ቀጥሎም፥ እንዲህ አለ፤ ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ ከውስጥ፥ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፥ ምንዝር፥ ስርቆት፤ ሰው መግደል፥ ዝሙት፥ መስገብገብ፥ ክፋት፥ ማታለል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስም ማጥፋት፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸው። እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ይወጣሉ ሰውንም ያረክሱታል።” ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። ሴትዮዋም ግሪካዊት፥ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ርኩስ መንፈሱን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። እርሱ ግን፥ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፥ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። እርሷም መልሳ፥ “አዎን፥ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ” አለችው። እርሱም፥ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷአል” አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፥ ጋኔኑም ለቋት አገኘቻት። ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፥ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያም ሰዎች ደንቆሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፥ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፥ “ኤፋታህ” አለው፤ ይኸውም፥ “ተከፈት” ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸውም መጠን፥ ነገሩን አስፍተው አወሩት። ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፥ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳን አድርጓል” አሉ። በዚያን ጊዜ፥ እንደገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለቆዩና የሚበሉትም ስለ ሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ። ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፥ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት። እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀመዛሙርቱ የተረፈውን ቁርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱንም አሰናበታቸው። ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ። ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፥ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ። ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፥ እጁንም በላዩ ጭኖ፥ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፥ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፥ “ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ላከው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፈልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፥ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፥ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፥ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፥ እንደሚገደል፥ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፥ “አንተ ሰይጣን፥ ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፥ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፥ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፥ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።” ቀጥሎም፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” አላቸው። ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ይዟአቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፥ “ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም። ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፥ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፥ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፥ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም፥ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፥ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።” ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፥ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው፥ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፥ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለምን ጉዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ዲዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፏጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም አረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፥ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፥ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “አምናለሁ፤ አለማመኔን አይተህ እርዳኝ” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣታቸውን ባየ ጊዜ፥ “አንተ ደንቆሮና ዲዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዤሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎች “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው፥ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፥ “የዚህ ዓይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው። ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፥ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፥ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት፥ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ። ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፥ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፥ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። ትንሽ ልጅ አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም፥ “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው። ዮሐንስም፥ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፥ እኛን ስለማይከተልም ከለከልነው” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ተአምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤ የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም።” “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቁረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፥ ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና፤ እግርህ ብታሰናክልህ ቁረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፥ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ በገሃነም ትሉ አይሞትም እሳቱ አይጠፋምና። ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጉለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና፤ ሰውም ሁሉ በእሳት ይቀመማል። ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።” ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው። አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፥ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። እርሱም መልሶ፥ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷአል” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየውም።” እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። እርሱም፥ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤ እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው። ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፥ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው። ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፥ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” ሰውየውም፥ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላና፤ ተከተለኝም” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፥ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፥ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም፥ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይወርስ የለም። ነገር ግን ብዙዎች ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፥ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፥ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀመዛሙርቱ ተገረሙ፥ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፥ ይገርፉታል፥ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም፥ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፥ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት። ኢየሱስም፥ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፥ “አዎን እንችላለን” አሉት። ኢየሱስም፥ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው። ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቆጣት ጀመሩ። ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፥ የሁሉ ባርያ ይሁን፤ የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።” ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፥ “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ” እያለ ይጮኽ ጀመር። ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ። ኢየሱስም ቆም ብሎ፥ “ጥሩት” አላቸው። እነርሱም ዐይነ ስውሩን፥ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል” አሉት። እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፥ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ። ኢየሱስም፥ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዐይነ ስውሩም፥ “መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው። ኢየሱስም፥ “ሂድ፥ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ። ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፦ በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፥ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት፤ ማንም፥ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” ቢላችሁ፥ “ለጌታ ያስፈልገዋል፤ በቶሎም መልሶ ይልከዋል” ብላችሁ ንገሩት። እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ እመንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙት፤ ፈቱትም። በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፥ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው። ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሳቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት። ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቆረጡ ያነጥፉ ነበር። ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት! ሆሣዕና በአርአያም!” ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፥ “ከአሁን ጀምሮ ለዘለዓለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፥ “ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል፥ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፥ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፥ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምካት በለስ ደርቃለች” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤” እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፥ “ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር” ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል። ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል። እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፥ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፥ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፥ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ከሰማይ ነው” ብንል፥ “ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?” ይለናል፤ “ታዲያ፥ ከሰው ነው፤ እንበልን?” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ያምኑ ስለ ነበር ፈሩ። ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፥ “እንግዲያው እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጉድጓድ ቆፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። እንደገናም ሌላ አገልጋይ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት”፤ አሁንም እንደገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ። አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወደው ልጁ ነበረ፤ “ልጄንስ ያከብሩታል” በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው። ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፥ ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል፥ ተባባሉ፤ ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን፤ ጌታ ይህን አድርጓል፥ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው! ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፥ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተውት ሄዱ። ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፥ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። እነርሱም አመጡለት፥ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የቄሣር ነው” አሉት። ኢየሱስም፥ “የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ። ከዚህ በኋላ የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ይህ ሰው ሴትዮዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ፥ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሳኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፥ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማታውቁ ነው፤ ሙታን ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን ግን እንደሚነሡ እግዚአብሔር “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤” እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቁጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፥ እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኋይልህ ውደድ።” ሁለተኛውም ይህ ነው፤ “ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም። ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፥ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም አእምሮህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኋይልህ መውደድ፥ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፥ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥ ጌታ ጌታዬን፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፥ ይላል። “ታዲያ ዳዊት ራሱ ጌታ፥ ካለው፤ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?”። ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤ በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፥ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤ በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያክል የናስ ገንዘብ ጨመረች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሳጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድህነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።” ከቤተ መቅደስ ሲመጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፥ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደሆነ እይ” አለው። ኢየሱስም መልሶ፥ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፥ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድነው?” ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፥ “እኔ እርሱ ነኝ” እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራብ ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። ተይዛችሁ ለፍርድ በምትቀርቡበት ጊዜ፥ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል። የጥፋት ርኩሰት ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፥ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና። ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያን ጊዜ ማንም፥ “እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?” ቢላችሁ ወይም፥ “እነሆ፤ እዚያ ነው” ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፥ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፥ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። በዚያን ጊዜ፥ ከመከራው በኋላ ፀሓይ ትጨልማለች፥ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኋይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፥ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፥ ቅጠሏ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፥ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፥ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም አያውቅም። ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፥ ጸልዩም። ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፥ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፥ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፥ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ። የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፥ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፥ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፥ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቆጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፥ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፥ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምንም ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፥ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፥ መምህሩ፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?” ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ፥ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም አዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፥ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት፤ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፥ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው፤ ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” ከተነሣሁ በኋላ ግን፥ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ። ጴጥሮስም፥ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ። ኢየሱስም፥ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፥ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቆዩ” አላቸው። ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ፥ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፥ “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።” ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፥ ከካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም፥ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷአቸው ነበር። እንደደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ “መምህር ሆይ” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቆመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ጣል ያደረገ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፥ በፍታውን ጥሎ ዕራቁቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፥ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፥ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፥ የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፥ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፥ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና፥ የቡሩኩ ልጅ፥ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፥ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፥ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?”፤ እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፥ “እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፥ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና፥ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። እርሱ ግን፥ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፥ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፥ በእርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፥ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከጸሓፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋር ወዲያው ከተማከሩ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፥ “አንተው አልኸው፥” በማለት መለሰለት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፥ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ በብዙ ነገር ከሰውሃል” ሲል እንደገና ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ጲላጦስም፥ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደገና፥ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደገና፥ “ስቀለው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፥ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ?” አላቸው። እነርሱ ግን፥ “ስቀለው” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾክ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ እጅ ነሡት፤ ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፥ ትርጉሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፥ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍ፥ “ከዐመፀኞች ጋር ተቆጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አይ፥ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤ እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን።” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም፤ አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፥ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ ከመስቀል ይውረድ።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፥ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፥ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ከዚያም፥ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ። በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፥ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም አብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ። ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ጠየቀው፤ መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፥ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር። ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጠዋት በማለዳ፥ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፥ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፥ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ቀና ብለው ሲመለከቱ፥ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባሎ አዩ። ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፥ ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱ ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቷል፤ እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፥ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ፥ ብላችሁ ንገሯቸው።” ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፥ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት በመጀመሪያ ታየ። እርሷም ሄዳ፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት እያዘኑ ሲያለቅሱ አግኝታ እርሱ ሕያው መሆኑንና ለእርሷም መታየቱን ነገረቻቸው፤ እነርሱ ግን አላመኗትም። ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ታያቸው። እነርሱም ተመልሰው ይህንኑ ለቀሩት ነገሯቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱንም አላመኗቸውም። ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማዕድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፥ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነና የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።” ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ከዚያም ደቀመዛሙርቱ ወጥተው፥ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር። እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ብዙዎች በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ክስተቶች በጽሑፍ ለማዘጋጀት እንደሞከሩት ሁሉ፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር፥ ለአንተ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ታሪክ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። በዚህም ስለ ተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛነት በደንብ እንድታውቅ ብዬ ነው። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ። ከነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወር ተደበቀች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ እኔን በተመለከተበት ጊዜ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል አስወገደልኝ።” በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።፥ የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤” አላት። እርሷም በንግግሩ በጣም ደንግጣ፥ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርሷ ደግሞ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷም ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አንዳች ነገር የለምና።” ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ አገልጋይ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤” አለች። መልአኩም ከእርሷ ተለይቶ ሄደ። ማርያምም በእነዚያ ቀናት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር በይሁዳ ወደምትገኝ ከተማ ፈጥና ሄደች፤ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል። በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤ በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። እስራኤልን አገልጋዩን፥ ምሕረቱን በማስታወስ፥ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤ እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ። በዚያም ወራት የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲመዘገቡ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ምዝገባ ተከናወነ። ስለዚህ ሁሉም ለመመዝገብ፥ እያንዳንዱም ወደ የራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፥ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ሊመዘገብ ሄደ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት የሚጠብቅ፥ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤ እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባሉት ነገሮች ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት እንዲሆን ተሾሞአል፤ በዚህም የብዙዎችን የልባቸውን አሳብ የሚገለጥ ይሆናል፤ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።” ከአሴር ወገንም የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ በዕድሜዋም በጣም የገፋች ነበረች፤ እርሷም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርሷም እስከ ሰማኒያ አራት ዓመቷ ድረስ መበለት ነበረች፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም ነገር እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ ጠነከረም፤ ጥበብም ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። ወላጆቹም በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍና እናቱም አላወቁም ነበር። ነገር ግን ከመንገደኞች ጋር የነበረ መስሏቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፤ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም መካከል ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ እየሰማቸውና እየጠየቃቸው በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሶቹ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ እጅግ ተገረሙ፤ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ! ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር እኮ፤” አለችው። እርሱም፦ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም እነዚህን ነገሮች ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም የይሁዳ ገዥ ነበር፥ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስ ደግሞ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አገረ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሊኒ አገረ ገዢ ሳሉ፥ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ዘመን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። በዮርዳኖስም ዙርያ ወዳለው አገር ሁሉ መጥቶ ለኃጢአት ስርየት የንስሓን ጥምቀት ሰበከ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በሚገኘበት መጽሐፍ እንደተጻፈው፦ “በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ ጐድጓዳው ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም መንገድ ቀና ይሁን፤ ሸካራውም መንገድ የተስተካከለ ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤” ስለዚህ በእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚገቡ ፍሬዎች አፍሩ፤ በልባችሁም ‘አብርሃም አባት አለን፤’ አትበሉ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንደሚችል እነግራችኋለሁና። ቀድሞውንም እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም፦ “ታድያ፥ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ።” ግብር ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ “መምህር ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉት። እርሱም፦ “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ ምንም አትሰብስቡ፤” አላቸው። ወታደሮችም እንዲሁ፦ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ “ማንንም በግፍ ወይም በሐሰት ክስ አትበዝብዙ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሲጠብቁ ነበርና፥ ሁሉም በልባቸው ዮሐንስን በተመለከተ “እርሱ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አሰቡ፤ ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “እኔስ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ጠፍር መፍታት እንኳ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ አውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውን በጎተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ስለዚህ ለሕዝቡ ሌሎች ብዙ ምክሮችን እየሰጠ መልካም ዜናን ያበሥር ነበር፤ አገረ ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ወንድሙ ሚስት ስለ ሄሮድያዳና ሄሮድስ ስላደረገው ክፋት ሁሉ በዮሐንስ ስለ ተገሠጸ፥ በክፋቶቹ ሁሉ ላይ ይህን ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አስገባው። ሕዝቡም ሁሉ በተጠመቁ ጊዜ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል፤” የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ። ኢየሱስም አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር፤ ይታመን እንደነበረው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥ የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊ ልጅ፥ የናጌ ልጅ፥ የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮዳ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ (የዮሳስ ልጅ)፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥ የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ፥ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ፥ የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ የነአሶን ልጅ፥ የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ የናኮር ልጅ፥ የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥ የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ የመሀላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ። ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ። ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ። ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ከፍ ወዳለው ስፍራ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ “ለአንተ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውንም እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥተቶአልና ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” አለው። ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቆመው፥ እንዲህም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር፤ እነሆ፥ ‘አንተን ለመጠበቅ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል አንተን በእጃቸው ያነሡሃል፤’ ተብሎ ተጽፎአልና።” ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው፤’ ተብሏል፤” አለው። ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተወራ። እንዲሁም በሁሉም እየተመሰገነ በምኵራባቸው ያስተምር ነበር። ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደተለመደው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፤ ከአፉም ከሚወጡት ቃላት ጸጋ የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ያለ ምንም ጥርጥር ይህንን ምሳሌ ትጠቅሱብኛላችሁ ‘አንተ ሐኪም! እስቲ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግህ የሰማናቸውን ነገሮች ሁሉ፥ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ።’ ” እንዲህም አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ አንድም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም። ነገር ግን በእውነት እላችኋለሁ፤ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ፥ በምድር ሁሉ ላይ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ቢሆንም ግን ኤልያስ ወደ ሲዶናዊቷ መበለት ወደ ሰራፕታ እንጂ ወደ ሌሎቹ ወደ አንዳቸውም አልተላከም። በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ ማንም አልነጻም።” በምኵራብም ውስጥ የነበሩ ሁሉ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ በቁጣ ተሞሉ፤ ተነሥተውም ከከተማይቱ ውጭ አወጡት፤ ገፍትረውም ሊጥሉት ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ኮረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት፤ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። የገሊላ ከተማም ወደ ሆነችው ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ ቃሉ በሥልጣን ተሞልቶ ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኾ፦ “ተው፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንህ አውቄሃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ምንም ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። ሁሉም ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፦ “ይህ ቃል ምንድነው? በሥልጣንና በኃይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፥ እነርሱም ይወጣሉ፤” እያሉ ይነጋገረሩ ነበር። ስለ እርሱም የተነገረው በዙሪያው ባለው አገር፥ በሁሉ ስፍራ ተሰራጭቶ ነበር። ከምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ትኩሳት ታማ ነበር፤ ስለ እርሷም ለመኑት። በአጠገብዋም ቆሞ ትኩሳቱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው። ፀሐይም ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕሙማን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። አጋንንትም ደግሞ፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው እየጮኹ ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፥ ምክንያቱም ክርስቶስ እንደሆነ አውቀውት ነበርና። ሲነጋም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፤ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ይጥሩ ነበር። እርሱ ግን፦ “የተላክሁት በዚሀ ምክንያት ነውና ለሌሎቹ ከተማዎችም የእግዚአብሔርን መንግሥት መልካም ዜና ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው። እርሱም በይሁዳ በሚገኙት ምኵራቦች ይሰብክ ነበር። እርሱም በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ሳለ፥ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በዙርያው ይጋፉ ነበር፤ በባሕሩ ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደነበረችው ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር። ንግግሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን፦ “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ፤” አለው። ስምዖንም መልሶ፦ “አቤቱ! ሌሊቱን ሙሉ ብንደክምም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ፤” አለው። ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው በምልክት ጠሩአቸው፤ መጥተውም ሁለቱን ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጉልበት ፊት ወድቆ፦ “ጌታ ሆይ! እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከኔ ራቅ፤” አለው። እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ስላጠመዱት ዓሣ ተደንቀው ነበርና፤ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ወዳጆች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን፦ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎችን የምታጠምድ ትሆናለህ፤” አለው። ታንኳዎቹንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት። ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የወረሰው አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም ባየው ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ፦ “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ሲል ተማጸነው። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ፤” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው። እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፤ ነገር ግን፦ “ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ፤” አለው። ስለ እርሱ የሚባለው ግን ይበልጡን በስፋት ተሰራጨ፤ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤ እርሱ ግን ገለል ብሎ ወደ በምድረ በዳዎች እየሄደ ይጸልይ ነበር። እንዲህም ሆነ፤ አንድ ቀን ሲያስተምር ሳለ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ የሚፈውስበትም የጌታ ኃይል ከእርሱ ጋር ነበረ። እነሆም፥ አንድ መንቀሳቀስ የማይችል ሰው በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አስገብተውትም በፊቱ ሊያኖሩት ይፈልጉ ነበር። ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ እርሱን ለማስገባት ምንም ዓይነት መንገድ ባለማግኘታቸው ወደ ሰገነቱ ወጡ፤ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከላቸው ከነአልጋው በኢየሱስ ፊት አወረዱት። እምነታቸውንም አይቶ እንዲህ አለ፦ “አንተ ሰው! ኀጢአቶችህ ተሰረዩልህ።” ጻፎችና ፈሪሳውያንም፦ “ስድብን የሚሰነዝር ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ማን ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ይችላል?” እያሉ ያስቡ ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ባወቀ ጊዜ መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ ምን እያሰባችሁ ነው? ‘ኀጢአቶችህ ተሰረዩልህ፤’ ከማለትና ‘ተነሣና ሂድ፤’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ብሎ፥ መንቀሳቅስ የተሳነውን ሰው፦ “እነሆ አዝሃለሁ፤ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውኑ በፊታቸው ተነሣ፤ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። ሁሉም ተገረሙ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ በፍርሃትም ተሞልተው፦ “ዛሬስ አስደናቂ ነገሮችን አየን፤” አሉ። ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ስፍራ ተቀምጦ ተመለከተና፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱም ሁሉንም ነገር ትቶ፤ ተነሥቶ ተከተለው። ሌዊም ታላቅ ግብዣ በቤቱ አደረገለት፤ ከቀራጮችና ከሌሎችም ብዙ ሕዝብ በማዕድ ከእነርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም፦ “ስለምን ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ? ትጠጣላችሁም?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጉረመረሙ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልጠራ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።” እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አዘውትረው ይጾማሉ፤ ጸሎትም ያደርሳሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታጾሙ አትችሉም፤ ትችላላችሁን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀኖች ይመጣሉ፤ በነዚያ ቀኖች ይጾማሉ።” እንዲህ ሲልም በምሳሌ ነገራቸው፦ “የአዲስ ልብስ እራፊን ቀድዶ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር ማንም የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል፤ አዲሱም እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም። ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ እርሱም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጪ ይሆናል። አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል። ማንም አሮጌውን የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ አዲሱን የሚሻ የለም፤ ‘አሮጌው ይጣፍጣል’ ይላልና።” እነሆ፥ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ስለምን ታደርጋላችሁ?” ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ እንዲህ አለ፦ “ዳዊት በተራበ ጊዜ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን ነገር አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር ለመብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን ኅብስት ወስዶ እንዴት እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንዴት እንደሰጣቸው ይገልጥ የለምን?” እርሱም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤” አላቸው። እነሆ በሌላ ሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከስሱበትን ምክንያት ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፦ “ተነሣና በመካከል ቁም፤” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነውን ወይንስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ነውን ወይንስ ማጥፋት?” በዙርያው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ከቃኘ በኋላ ሰውዬውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ደኅና ሆነ። እነርሱ ግን በቁጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስም ላይ ምን እንደሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። በነዚህም ወራት ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥራ ሁለት መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነርሱም፦ ጴጥሮስ ብሎ እንደገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስም፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስንና ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛ የተባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ከሐዲ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳም ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሜዳማ ስፍራ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ እንዲሁም ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም እጅግ ብዙ ሰዎች እርሱን ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ የመጡ ነበሩ፤ በርኩሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ሰዎች ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፤ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን እንኳ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህንም የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። እንዲሁም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትወድዱትን ነገር እናንተ ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ያን ያደርጋሉና። ልትቀበሉአቸው ተስፋ የምታደርጉአቸውን ሰዎች ብታበድሩ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ባበደሩት ዋጋ ልክ እንዲመለስላቸው ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉ፤ ይመለስልናልም ብላችሁ ምንም ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። “አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ እንዳትኰነኑም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ፤ ስጡ ይሰጣችኋልም፤ በመልካምም መስፈሪያ የተጠቀጠቀና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና።” እርሱም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዐይነ ስውር ዐይነ ስውርን መምራት ይችላልን? ሁለቱም በጉድጓድ አይወድቁምን? ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም? አንተ ራስህ በዐይንህ ያለውን ምሰሶ ሳታይ እንዴት ወንድምህን፦ ‘ወንድሜ ሆይ! በዐይንህ ያለውን ጉድፍ እዳወጣ ፍቀድልኝ፤’ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” መልካም ዛፍ የተበላሸ ፍሬ አያፈራምና፤ እንዲሁም የተበላሸ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ከአጣጥ ቁጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። መልካም ሰው በልቡ ከሚገኘው መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሚገኘው ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና። ስለምን “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ትሉኛላችሁ? የምለውን ግን አታደርጉም? ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ፥ ቃሎቼንም ሰምቶ የሚያደርጋቸው ሰው ማንን እንደሚመስል አሳያችኋለሁ፤ እርሱም፦ ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ፥ በዐለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፤ ደኅና ተደርጎም ስለ ታነጸ ሊያናውጠው አልቻለም። ነገር ግን ሰምቶ የማያደርገው ቤቱን ያለ መሠረት በምድር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው፤ ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።” እርሱም ለአድማጩ ሕዝብ ንግግሩን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባርያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ልኮ ባርያውን መጥቶ እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ እያሉ አጥብቀው ለመኑት፦ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና፤ ምኵራብም የሠራልን እርሱ ነው።” ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ መቶ አለቃው ወዳጆቹን ወደ እርሱ ልኮ እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና ራስህን አታድክም፤ ወደ አንተም ለመምጣት እንኳ ራሴን የተገባሁ አድርጌ አልቆጠርሁትም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል። እኔ በእርግጥ ከሌሎች ሥልጣናት በታች የተሾምሁ ሰው ነኝ፤ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ!’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ብለው ይመጣል፤ ኣገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ብለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ይህንን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ኣገልጋዩን በመልካም ጤንነት ላይ ሆኖ አገኙት። በማግስቱም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ አንድ የሞተ ሰው ተሸክመው እያወጡ ነበር፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ነበረ፤ እርሷም መበለት ነበረች፤ የከተማይቱም ብዙ ሕዝብ ከእርሷ ጋር አብረው ነበሩ። ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፦ “አታልቅሽ፤” አላት። ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ቆሙ፤ እርሱም፦ “አንተ ወጣት! ተነሥ እልሃለሁ!” አለ። የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ፥ ይናገርም ጀመረ፤ ኢየሱስም ጐልማሳውን ለእናቱ ሰጣት። ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እንዲህ እያሉ አመሰገኑ፦ “ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል!” “እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቶአል!” ስለ እርሱም የተነገረው ይህ ነገር በመላው ይሁዳ በዙሪያውም ባለው አገር ሁሉ ተሰራጨ። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር ሁሉ አወሩለት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ወደ አንተ ላከን፦ ‘የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ” በዚያች ሰዓት ኢየሱስ ከደዌና ከሚያሠቃይ በሽታ፥ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፤ ለብዙ ዐይነ ስውሮችም የማየትን ጸጋ ሰጠ። እርሱም መልሶ ለተላኩት እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውሮች ያያሉ፤ የሚያነክሱ ይራመዳሉ፤ በለምጽ የተጠቁ ይነጻሉ፤ መስማት የተሳናቸውም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን። “እነሆ፥ መንገድህን አስቀድሞ የሚያዘጋጅ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። የሰማውም ሕዝብ ሁሉ፥ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ፥ በዮሐንስ ጥምቀት በመጠመቃቸው የእግዚአብሔርን ጻዲቅነት ተቀበሉ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ባለመጠመቃቸው ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ዕቅድ አልተቀበሉም። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ እንዲህ የሚሉትን እንቢልታ ነፋንላችሁ፤ አላሸበሸባችሁምም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁምም። መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበር፥ እናንተም “ጋኔን አለበት፤” አላችሁ። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እናንተም “እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፤ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ ነው፤” አላችሁ። ነገር ግን የጥበብ መጽደቅ በልጆችዋ ሁሉ ተረጋገጠ። ከፈሪሳውያንም አንዱ ኢየሱስን ከእርሱ ጋር እንዲበላ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም፥ በዚያች ከተማ ኀጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፥ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ አምጥታ ነበር። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ፥ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉርዋም ታብሰው፥ እግሩንም ትስመው፥ ሽቶም ትቀባው ነበረች። የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና፤” ሲል በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ፦ “ስምዖን ሆይ! አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ፤” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ! ተናገር፤” አለ። “አንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት፤ አንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ ሌላው ደግሞ አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ዕዳቸውን ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?” ስምዖንም ሲመልስ፦ “ብዙ የተወለትን ይመስለኛል፤” አለ። እርሱም፦ “በትክክል ፈረድህ፤” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ውሃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። ስለዚህም እጅግ ወዳለችና ብዙ ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል እልሃለሁ፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።” እርሷንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤” አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ “ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?” ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም፦ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤” አላት። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እያበሠረ በየከተማውና በየመንደሩ ያልፍ ነበር፤ ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ ከእነርሱም፦ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ የሄሮድስ መጋቢ የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ብዙዎች ሌሎችም ሆነው ከንብረታቸው በመጠቀም ያገለግሉአቸው ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበና ከየከተማውም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ “ዘሪ ዘሩን ለመዝራት ወጣ። በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ተረገጠም፤ የሰማይ ወፎችም ጨረሱት። ሌላውም በዐለት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንንም እየተናገረ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በቅን ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፥ በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትንም አብርቶ በእንቅብ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። የማይገለጥ ምንም የተሰወረ የማይታወቅም ወደ ብርሃንም የማይመጣ ምንም የተሸሸገ ነገር የለምና። ስለዚህ እንዴት እንደምትሰሙ በጥንቃቄ አጢኑ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።” እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፤ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት አልቻሉም። እንዲህም ተብሎ ተነገረው፦ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል።” እርሱም መልሶ፦ “እናቴና ወንድሞቼ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው፤” አላቸው። ከዕለታቱም በአንዱ ቀንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ “ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር፤” አላቸው፤ እነርሱም ለመሄድ ተነሡ። እየሄዱም ሳሉ ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደው። ዓውሎ ነፋስም በሐይቁ ላይ ተነሣ፤ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበር፤ እነርሱም በአደጋ ላይ ስለ ነበሩ ተጨንቀው ነበር። ቀርበውም፦ “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ! እየጠፋን ነው፤” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የሚናውጠውን የውኃ ሞገድ ገሠጻቸው፤ እነርሱም አቆሙ፤ ጸጥታም ሆነ። እርሱም፦ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። በፍርሃትና በመደነቅ ተውጠውም፤ እርስ በርሳቸው፦ “እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን ሳይቀር የሚያዝ፥ እነርሱም የሚታዘዙለት ይህ ለመሆኑ ማን ነው?” ተባባሉ። በገሊላም ማዶ ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ተሻገሩ። እርሱም ወደ ምድር እንደ ወረደ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፤ ለረጅም ጊዜ ልብስ አይለብስም ነበር፥ በመቃብሮች እንጂ በቤት ውስጥም አይኖርም ነበር። ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፦ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? እንዳታሰቃየኝ እለምንሃለሁ፤” አለ። እንዲህም የሆነው ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ አዞት ስለ ነበረ ነው። ለብዙም ጊዜ ይዞት ነበርና፤ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይወሰድ ነበር። ኢየሱስም፦ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና፦ “ሌጌዎን” አለው። ወደ ጥልቁም ሂዱ ብሎ እንዳያዛቸው ለመኑት። በዚያም በኮረብታው ዳርቻ ላይ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ወደ እነርሱም ለመግባት እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም። አጋንንቱም ከሰውዬው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ሐይቁ ተጣድፎ በመውረድ ሰጠመ። እረኞቹም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በገጠሩ አወሩት። ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ፥ ልቡም ተመልሶ፥ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ በታላቅ ፍርሃት ተይዘው ስለ ነበር ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ ተመለሰ። አጋንንትም የወጡለት ሰው ከእርሱ ጋር እንዲሆን ለመነው፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ አሰናበተው፦ “ወደ ቤትህ ተመለስ፤ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ተናገር።” እርሱም በመላው ከተማ ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት እየሰበከ ሄደ። ሕዝቡም ሁሉ እየጠበቁት ስለ ነበር ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ ተቀበሉት። እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፤ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ፤ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሚሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርሷም ለመሞት እያጣጣረች ነበር። ሲሄድም ሕዝቡ በዙርያው እየተጋፉት ያጨናንቁት ነበር። ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፤ ያላትንም ንብረት ሁሉ ተጠቅማ ለባለመድኃኒቶች ብታውልም ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም። ከበስተኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ ወዲያውም ደምዋ መፍሰሱን አቆመ። ኢየሱስም፦ “ማን ነው የነካኝ?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስ፦ “አቤቱ! ሕዝቡ በዙሪያህ ከበውህ እየተጋፉህ እኮ ነው!” አለ። ኢየሱስ ግን፦ “አንድ ሰው ዳስሶኛል፤ ከእኔ ኃይል መውጣቱን አውቄአለሁና፤” አለ። ሴቲቱም መደበቅ እንዳልቻለች ባወቀች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ በምን ምክንያት እንደ ዳሰሰችውና እንዴት ፈጥና እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች። እርሱም፦ “ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤” አላት። እርሱም ይህን እየተናገረ ሳለ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ፦ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም፤” አለ። ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ ለኢያኢሮስ መልሶ እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ እመን ብቻ፤ እርሷም ትድናለች።” ወደ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም፥ ከልጅቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር እንዲገባ አልፈቀደም። ሁሉም እያለቀሱ ደረታቸውን ይመቱላት ነበር። እርሱ ግን፦ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም፤” አለ። እንደ ሞተችም ስላወቁ በጣም ሳቁበት። እርሱ ግን እጅዋን ይዞ፦ “አንቺ ልጅ! ተነሺ፤” ብሎ ተጣራ። መንፈሷም ተመለሰች፤ ፈጥናም ተነሣች፤ የምትበላውም ነገር እንዲሰጣት አዘዘ። ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ፥ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ እንዲሁም ደዌን እንዲፈውሱ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገድ ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፤ ሁለት እጀ ጠባብም አይኑራችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ ከዚያም ካረፋችሁበት ቤት ወጥታችሁ ሂዱ። ሰዎች በማይቀበሉአችሁ ጊዜ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው በእግራችሁ ላይ ያለውን ትቢያ አራግፉ።” ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በሁሉ ስፍራ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች፦ “ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፤” ሌሎችም “ኤልያስ ተገለጠ፤” ሌሎችም “ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤” ይሉ ስለ ነበር ግራ ተጋባ። ሄሮድስም፦ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ይህ ማን ነው?” አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። እነርሱን ይዞ፥ ለብቻው ወደ ገለልተኛ ሰፈር፥ ቤተሳይዳ ወደምትባል ከተማ፥ ሄደ። ሕዝቡም ይህንን አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስም ያስፈልጋቸው የነበሩትንም ፈወሳቸው። ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ ዐሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ “በዚህ በምድረ በዳ ስላለን በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። እርሱ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም፦ “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በቀር ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም፤” አሉት፤ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ “በሃምሳ በሃምሳ እየከፈላችሁ አስቀምጡአቸው፤” አላቸው። እንዲህም አደረጉና ሁሉንም አስቀመጡአቸው። አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱም የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ለብቻውም ሲጸልይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፦ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ ‘መጥምቁ ዮሐንስ፥’ ሌሎችም ‘ኤልያስ፥’ ሌሎችም ‘ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤’ ይላሉ፤” አሉት። እርሱም፦ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ “የእግዚአብሔር መሢሕ ነህ፤” አለ። እርሱ ግን ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ እነርሱን አስጠንቅቆ በማዘዝ፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በጻፎችም ይናቃል፥ እንዲሁም ይገደላል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አለ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ፤ በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለ ሞቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ነበር፤ ነቅተውም ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሁለቱ ሰዎች በተለዩ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ “አቤቱ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ፥ አንድም ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ሳለ ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። እነርሱም ዝም አሉ፥ ያዩትንም ምንም ዓይነት ነገር በነዚያ ቀናት ለማንም አላወሩም። በማግስቱም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኘው። እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ፦ “መምህር ሆይ! ለእኔ ብቸኛ ልጄ ነውና፥ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። እነሆም፥ ርኩስ መንፈስ ይይዘዋል፤ ድንገትም ይጮኻል፤ አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ አድቅቆ በጭንቅ ይለቀዋል፤ ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፦ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው፤” አለ። ልጁም በመምጣት ላይ ሳለ ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው፤ ልጁንም ለአባቱ መልሶ ሰጠው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ ሳሉ፥ እርሱ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “የሰው ልጅ በሰው እጅ ተላልፎ የሚሰጥ ስለሆነ እናንተ እነዚህን ቃላት በጆሮዎቻችሁ አኑሩ፤” አለ። እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፤ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህም ነገር እርሱን ለመጠየቅ ፈሩ። ከእነርሱም መካከል ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ አንድ ሕፃን ወሰደና፥ በአጠገቡም አቁሞት፦ “ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ በእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና፤” አላቸው። ዮሐንስም መልሶ፦ “አቤቱ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው” አለው። ኢየሱስ ግን፦ “የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት፤” አለው። ኢየሱስ የሚያርግበት ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፤ እርሱም አስቀድሞ መልክተኞችን ላከ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን አቅንቶ ስለ ነበረ የመንደሩ ሰዎች አልተቀበሉትም። ደቀመዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው እንድናዝዝ ትወዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸው። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “አንተ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ምንም ስፍራ የለውም፤” አለው። ሌላውንም፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን፦ “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሙታኖቻቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አስተምር፤” አለው። እንዲሁም ሌላው፦ “ጌታ ሆይ! እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ በቤቴ ያሉትን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፥” አለ። ኢየሱስ ግን፦ “የሞፈሩን ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ማንም ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” አለው። ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መረጠ፤ ሁለት ሁለትም አድርጎ ራሱ ሊሄድበት ወደአሰበው ከተማና ስፍራ ሁሉ አስቀድሞ ላካቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት። እንግዲህ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ቦርሳም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድ ላይ ለማንም ሰላምታን አትስጡ። ወደምትገቡበትም ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፤’ በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ያድርበታል፤ ካልሆነ ግን ይመለስላችኋል። ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋልና እነርሱ የሚሰጡአችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያው ቤት ተቀመጡ። ከቤት ወደ ቤት አትዘዋወሩ። ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ የሚያቀርቡላችሁን ብሉ፤ በእርሷም ያሉትን ሕሙማንን ፈውሱና፦ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቦአል፤’ በሉአቸው። ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባዮቹዋ ወጥታችሁ እንዲህ በሉ፦ ‘ከከተማችሁም በእግሮቻችን ላይ የተጣበቀብንን ትቢያ ሳይቀር እናንተን በመቃወም እናራግፋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦአል፥ ይህን እወቁ።’ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል እላችኋለሁ። “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው በአመድ ላይም ተቀምጠው፥ ገና ድሮ፥ ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ የምትደረጊ ይመስልሻልን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። “የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።” ሰባዎቹም ሰዎች በደስታ ተመልሰው፦ “ጌታ ሆይ! አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም ምንም ነገር የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንም ስማችሁ በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ! መልካም ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድንም ማን እንደሆነ ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ አብንም ማን እንደሆነ ከወልድ በቀር ወልድም በፈቃዱ ከሚገልጥለት ሰው በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።” ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሳሉ ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፦ “የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው። እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙምም።” እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ተነሥቶ ሊፈትነው እንዲህ አለ፦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” እርሱም፦ “በሕግ ምን ተጽፎአል? እንዴትስ ታነበዋለህ?” አለው። እርሱም መልሶ፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “በትክክል መልሰሃል፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ፤” አለው። እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት፤ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው። በጉዞአቸውም ላይ ሳሉ እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። ለእርሷም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፤ እርሷም ደግሞ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ቃሉን ትሰማ ነበር። ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም፦ “ጌታ ሆይ! እኅቴ ብቻዬን እንዳገለግል ስትተወኝ አይገድህምን? እንግዲያውስ እንድታግዘኝ ንገራት፤” አለችው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ማርታ! ማርታ! በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪያለሽም፤ የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማርያምም መልካሙን ድርሻ መርጣለች፤ ከእርሷም አይወሰድባትም።” እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንዲሁ መጸለይን አስተምረን፤” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በማናቸውም ጊዜ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባት ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በለን፤ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለንና፤ ወደ ፈተናም አታግባን።’ ” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ማን ይሆን ወዳጅ ኖሮት፥ በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ እንዲህ የሚለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ! ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት ምንም የለኝምና’፤ ያም ከውስጥ መልሶ፦ ‘አታስቸግረኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ናቸው፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም፤’? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ ስለ ሆነ እንኳ ተነሥቶ ባይሰጠው፥ ስለ ንዝነዛው ግን ተነሥቶ የሚፈልገውን ያህል ይሰጠዋል። እኔም እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ ዓሣ ቢለምነው፥ በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንግዲያውስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው!” መናገርም የተሳነውን ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ መናገር የተሳነው ሰው ተናገረ፥ ሕዝቡም ተደነቁ፤ ከእነርሱ ዘንድ አንዳንዶች ግን፦ “በብዔልዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤” አሉ። ሌሎችም ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የተለያየ መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። ሰይጣንም ደግሞ እርስ በርሱ ቢለያይ መንግሥቱ እንዴት ይቆማል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ እናንተ ብላችኋልና፤ እኔስ በብዔልዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጣሉ? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥቷል። በማናቸውም ጊዜ ኀይለኛ ሰው በሚገባ የጦር ዕቃውን ታጥቆ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ንብረቱ በሰላም የተጠበቀ ይሆናል፤ ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ አደጋ ጥሎበት ካሸነፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን የጦር ዕውቃን ይወስድበታል፤ ምርኮውንም ያካፍላል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋርም የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን ፈልጎ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባለማግኘቱ ግን፦ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ ሲመጣም ተጠርጎና ተስተካክሎ ያገኘዋል። በዚያም ጊዜ ሄዶ ከእርሱ የባሱ ክፉ ሌሎች ሰባት መናፍስትን ከእርሱ ጋር ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው ሁኔታ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆናል።” ኢየሱስም ይህንን በመናገር ላይ ሳለ፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፦ “የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው፤” አለችው። እርሱ ግን፦ “በእርግጥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው፤” አለ። ሕዝብም በብዛት እየተሰበሰቡ በነበሩ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክትን ይፈልጋል፤ ከዮናስም ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ትነሳለች፥ በእነርሱም ላይ ትፈርዳለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ይነሳሉ፥ በእርሱም ላይ ይፈርዳሉ፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ። “መብራትንም አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው። ዐይንህ ጤናማ በሆነ ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ በብርሃን የተመላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ በሆነ ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ በጨለማ የተመላ ይሆናል። ስለዚህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳልሆነ በልብህ አስተውል። እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተመላ፥ ጨለማም የሆነ የአካል ክፍል የሌለው ከሆነ፥ መብራት በፀዳሉ ብርሃን እንደሚሰጥህ እንዲሁ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተመላ ይሆናል።” ይህንንም በመናገር ላይ በነበረ ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ኢየሱስም ወደ እርሱ ገብቶ ተቀመጠ። ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ በማየቱ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል። እናንተ ሞኞች! የውጭውን የፈጠረ እርሱ የውስጡንስ ደግሞ አለፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። “ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ታወጣላችሁ፤ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ግን ቸል ትላላችሁ፤ ይልቁንስ እነዚያን ደግሞ ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በምኵራቦች የከበሬታን ወንበርንና በገበያ ቦታዎች ሰላምታን ትወዳላችሁና። እናንተ ወዮላችሁ! ሰዎች ሳያውቋቸው በላያቸው የሚሄዱባቸው የተሰወሩ መቃብሮች ትመስላላችሁና።” ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ፦ “መምህር ሆይ! ይህን ስትል እኮ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው፤” አለው። እርሱም እንዲህ አለ፦ እናንተ ሕግ አዋቂዎች ደግሞ ወዮላችሁ! ለመሸከም ከባድ የሆነውን ሸክም ሰዎችን ታሸክማላችሁ፥ ራሳችሁ ግን በአንዲት ጣታችሁ እንኳ ሸክሙን አትነኩትምና። እናንተ ወዮላችሁ!አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብሮች ትሠራላችሁና። እንግዲህ በአባቶቻችሁ ሥራ ትስማማላችሁ፤ ስለ እርሱም ትመሰክራላችሁ፤ እነርሱ ገደሉአቸው እናንተ ደግሞ መቃብሮቻቸውን ትሠራላችሁና። ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፦ “ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፤ ከእነርሱም ይገድላሉ፤ ያሳድዳሉም፤ ስለዚህም ይህ ትውልድ ተጠያቂ የሚሆነው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በፈሰሰው በነቢያት ሁሉ ደም፥ ይህም ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ነው። አዎን እላችኋለሁ፤ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። እናንተ ሕግ አዋቂዎች ወዮላችሁ! የዕውቀትን መክፈቻ ወስዳችኋልና፤ ነገር ግን እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ የሚገቡትንም ከለከላችሁ።” እርሱም ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ ጻፎችና ፈሪሳውያን እርሱን እጅግ በመቃወም ስለ ብዙ ነገሮች የትንኮሳን ጥያቄ ይጠይቁት ጀመር፤ በዚህም እርሱ ከሚናገረው አንድ ነገርን ለማጥመድ አደቡበት። በዚያን ጊዜ፥ በሺዎች የሚቈጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ከብዛታቸው የተነሣ እየተረጋገጡ ሳለ፥ በቅድሚያ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፦ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ እርሱም ግብዝነት ነው። የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። ስለዚህ በጨለማ የተናገራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይታወጃል። ለእናንተም ለወዳጆቼ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ሥጋን የሚገድሉትን፥ ከዚያ አልፈው ግን ፈጽሞ ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ። ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ እርሱን ፍሩ። አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው፤ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። “እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም። ወደ ምኵራቦች፥ ወደ ገዢዎችና ወደ ባለ ሥልጣኖች ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ ወይም እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።” ከሕዝቡም አንድ ሰው “መምህር ሆይ! ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው፤” አለው። እርሱም “አንተ ሰው! ለዳኝነትና ለማከፋፈል ማን ነው በላያችሁ የሾመኝ?” አለው። “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፤ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ፤” አላቸው። ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል “አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያማ ሆነችለት። እርሱም ‘ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ?’ ብሎ በልቡ አሰበ። ‘እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጎተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፤ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ! ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስ ይበልሽ እላታለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?’ አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።” ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፤ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። “አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ፤ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን?” አለው። ጌታም አለ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ባርያ ግን ‘ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፤ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደሱም ፈቃድ ያላደረገ ያ ባርያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ፤ አሁን ቢቀጣጠል ምንኛ በወደድሁ? ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፤ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ? በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፤ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ። ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጇ ላይ ልጇም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።” ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ “ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው ‘ዝናብ ይመጣል፤’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ ‘ትኩሳት ይሆናል፥’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል። እናንት ግብዞች! የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? “እናንተ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ለመታረቅ ትጋ። የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።” በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በእነዚህ የገሊላ ሰዎች ላይ ይህ የደረሰው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ሆኑ ይመስላችኋልን?” “አይደለም”፤ እላችኋለሁ፥ “ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንዲሁ ትጠፋላችሁ። ወይንስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።” ይህንንም ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን አትክልቱ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፤ በእርሷም ፍሬ ፈልጎ ቢመጣ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም ‘እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ፈልጌ ለሦስት ዓመት ብመላለስ ምንም አላገኘሁም፤ ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቁላለች?’ አለው። እርሱ ግን መልሶ፥ ጌታ ሆይ! ዙሪያዋን እስክኰተኩትላትና ፍግ እስካፈስላት ድረስ ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደፊትም ብታፈራ፥ መልካም ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ” አለው። በሰንበት ቀንም ከምኵራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር። እነሆም፥ ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ በሽተኛ ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ጎባጣ ነበረች፤ ቀጥ ብላ መቆምም በፍጹም አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት! ከበሽታሽ ተፈውሰሻል፤” አላት፤ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራብ አለቃው ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን “ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይሆንም፤” አለ። ጌታም መልሶ እናንተ ግብዞች! ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህች ለዐሥራ ስምንት ዓመት ሰይጣን ያሠራት የአብርሃም ልጅ በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ይህንንም ሲናገር የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ በእርሱም በተደረጉት ድንቅ ነገሮች ሁሉ ሕዝቡ በሙሉ ደስ አለው። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምንን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ? ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤እርሷም አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ፤”። ደግሞም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች፤” አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። አንድ ሰውም “ጌታ ሆይ! የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፥ አይችሉምም እላችኋለሁ። ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም መልሶ ‘ከየት እንደ ሆናችሁ አላውቅም’ ይላችኋል። በዚያን ጊዜም ‘በፊትህ በላን፤ ጠጣንም፤ በአደባባያችንም አስተማርህ፤’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም ‘እላችኋለሁ፥ ከየት እንደ ሆናችሁ አላወቅም፤ ዐመፀኞች በሙሉ፥ ከእኔ ራቁ፤’ ይላችኋል። አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት እያያችሁ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፤ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።” በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዶች ቀርበው “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ውጣና ሂድ፤” አሉት። እንዲህም አላቸው “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ ‘እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን እፈጽማለሁ’ በሉአት። ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊጠፋ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም መሄድ ያስፈልገኛል። ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም! ነቢያትን የምትገድል፥ ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ። በሰንበትም ቀን ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። እነሆም፥ ሰውነቱ በሙሉ ያበጠበት ሰው በፊቱ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ብሎ ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን ጠየቀ። እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። “ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጉድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል “ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና፥ አንተንና እርሱን የጠራ መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ተውለት’ ይልሃል፤ በዚያን ጊዜም እያፈርህ ዝቅተኛውን ስፍራ መያዝ ትጀምራለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ! ወደ ላይ ውጣ’ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው “ምሳ ወይም እራት ባሰናዳህ ጊዜ፥ ምናልባት እነርሱም በተራቸው እንዳይጠሩህ፥ እንዳይክሱህም፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ሀብታም ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባሰናዳህ ጊዜ ድሆችንና ጉንድሾችን አንካሶችንም ዐይነ ስውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት አጸፋ የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።” በማእድ ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው፤” አለው። እርሱ ግን እንዲህ አለው “አንድ ሰው ታላቅ እራት አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎችን ጠራ፤ በእራትም ሰዓት የታደሙትን ‘አሁን ሁሉ ተዘጋጅቶአልና ኑ’ እንዲላቸው አገልጋዩን ላከ። ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የመጀመሪያው ‘መሬት ገዝቼአለሁ፤ ወጥቼም ላየው የግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፤’ አለው። ሌላውም ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቼአለሁ፤ ለመፈተንም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፤’ አለው። ሌላውም ‘ሚስት አግብቼአለሁ፤ ስለዚህም ልመጣ አልችልም’ አለው። አገልጋዩም መልሶ ይህንን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ አገልጋዩን ‘ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች መንገዶች ውጣ፤ ድሆችንና ጉንድሾችን ና ዐይነ ስውሮችንና አንካሶችንም ወደዚህ አስገባ፤’ አለው። አገልጋዩም ‘ጌታ ሆይ! እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፤ ሆኖም ገና ስፍራ አለ፤’ አለው። ጌታውም አገልጋዩን ‘ቤቴ እንዲሞላ ወደ ጎዳናዎችና ወደ ገጠር መንገዶች ውጣና እንዲገቡ ገፋፋቸው፤ ተጋብዘው ከነበሩት ከእነዚያ ሰዎች አንድ እንኳን እራቴን አይቀምስም እላችኋለሁ፤’ አለው።” ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት እንኳን ሳይቀር ካልናቀ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ እንዳለው አስቀድሞ ተቀምጦ ወጪውን የማይቈጥር ማን ነው? ያለዚያ መሠረቱን ቢያኖር፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ ‘ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ መደምደም አቃተው፤’ ብለው ሊቀልዱበት ይጀምራሉ። ወይንም በጦርነት ሌላውን ሊጋጠም የሚሄድ ንጉሥ፥ ሃያ ሺህ ሰው አስከትቶ የሚመጣበትን በዐሥር ሺህ ሰው ሊገጥም ይችል እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ማን ነው? ካልሆነም ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልእክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል። እንግዲህ እንደዚሁ ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ማንም ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። “ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ለምድርም ሆነ ለፍግ መቈለያ አይጠቅምም፤ ወደ ውጭም ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ቀራጮችና ኀጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎችም “ይህስ ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል፤” ብለው እርስ በርሳቸው አጉረመረሙ። ይህንንም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው “ከእናንተ መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፤’ ይላቸዋል። እንዲሁ ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ ምክንያት በሰማይ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ። “ወይም ዐሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፤’ ትላቸዋለች። እንዲሁ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ ምክንያት በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።” እንዲህም አለ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን ‘አባቴ ሆይ! ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ፤’ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች አንዱ ጋር ተጠጋ፤ እርሱም ዐሣማ እንዲያሰማራ ወደ ሜዳ ላከው። ዐሣማዎችም ከሚበሉት ፍልፋይ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ ‘ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ተቀጣሪዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና “አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከተቀጣሪዎችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፤”’ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም ‘አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤’ አለው። አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፤ በጣቱ ቀለበት በእግሩም ጫማ አጥልቁለት፤ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።’ ደስ ይላቸውም ጀመር። “ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የሙዚቃና የውዝዋዜ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹም አንዱን ጠርቶ ‘ይህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀ። እርሱም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደኅና ስላገኘውም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት፤’ አለው። እርሱም ተቈጣ፤ ሊገባም አልፈለገም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው። እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’።” ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “መጋቢ የሚያገለግለው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፤ ‘ይህ ሰው ያለህን ይበትናል፤’ የሚል ክስ በእርሱ ዘንድ አቀረቡ። ጠርቶም ‘ይህ የምሰማብህ ነገር ምንድነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ፤’ አለው። መጋቢውም በልቡ ‘ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፤ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ፤’ አለ። የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የመጀመሪያውን ‘ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ማድጋ ዘይት’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ፥ ፈጥነህም ተቀምጠና ኀምሳ ብለህ ጻፍ፤’ አለው። በኋላም ሌላውን ‘አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ዳውላ ስንዴ’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ፤’ አለው። ጌታውም ዐመፀኛውን መጋቢ ስለ ብልኃቱ አመሰገነው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። እኔም እላችኋለሁ፤ የዐመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘለዓለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ አማካኝነት ወዳጆችን ለራሳችሁ አብጁ። “በትንሹ የታመነ በብዙም እንዲሁ የታመነ ነው፤ በትንሹ የሚያታልል በብዙም እንዲሁ ያታልላል። እንግዲያስ በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አንድም አገልጋይ የለም፤ ወይ አንዱን ሲጠላ ሌላውን ይወዳል፤ ወይ አንዱን ሲጠጋ ሌላውን ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። እንዲህም አላቸው “ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሰት ነውና። “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርሷ ለመግባት ይታገላል። ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል። “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ባልዋም የፈታትን የሚያገባ ያመነዝራል። “በሐምራዊና በክት ልብስ የሚሽቀረቀር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ፤ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በቅንጦት ይኖር ነበር። አልዓዛር የሚባል አንድ ድኻ ሰው ደግሞ በቁስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከሀብታሙም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቁስሎቹን ይልሱ ነበር። ድኻውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ሀብታሙም ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ፥ አልዓዛርንም በእቅፉ አየ። እርሱም እየጮኸ ‘አብርሃም አባት ሆይ! ማረኝ፤ በዚህ ነበልባል እሠቃያለሁና የጣቱን ጫፍ በውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ላክልኝ፤’ አለ። አብርሃም ግን ‘ልጄ ሆይ! አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም ነገሮችህን እንደተቀበልህ አስብ፤ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል፤ አንተም ትሠቃያለህ። ከዚህም ሁሉ በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ማለፍ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል፤’ አለ። እርሱም ‘እንግዲያውስ፥ አባት ሆይ! ወደ አባቴ ቤት እንድትልከው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው’ አለ። አብርሃም ግን ‘ሙሴና ነቢያት አሉላቸው፤ እነርሱን ይስሙ፤’ አለው። እርሱም ‘አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ! ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሓ ይገባሉ፤’ አለ። ‘ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ሰው ቢነሣ አያምኑም፤’ አለው።” ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “መሰናክል የግዱን ሳይመጣ አይቀርም፤ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ፥ በቀንም ሰባት ጊዜ ‘ተጸጸትሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው።” ሐዋርያትም ጌታን “እምነት ጨምርልን” አሉት። ጌታም አለ፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል፤’ ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። “ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ አገልጋይ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ ‘ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ፤’ የሚለው ማን ነው? ‘የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ፤’ ይለው የለምን? ያዘዘውን ስላደረገ ያንን አገልጋይ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል፤’ በሉ።” ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ! መምህር ሆይ! ማረን፤” አሉ። አይቶም “ሂዱ፤ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፤” አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያወደሰ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከሌላ ወገን ሰው በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም፤” አለ። እርሱንም “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም ‘ይችትና!’ ወይም ‘ያቻትና!’ የምትባል አይደለችም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና፤” አላቸው። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች መካከል አንዱን ለማየት የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ አታዩትምም። እነርሱም ‘እነሆ በዚህ’ ወይም ‘እነሆ በዚያ’ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ አንድ ስፍራ ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅም፥ በቀኑ፥ እንዲህ ይሆናል። አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህም ትውልድ ሊናቅ ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመንም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፤ የጥፋት ውሃም መጣ፤ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፤ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱአት። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን የሚያጠፋ ሁሉ ይጠብቃታል። በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል እላችኋለሁ። ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች፤ ሁለተኛይቱም ትቀራለች። ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል።” ሲመልሱለትም “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው?” አሉት። እርሱም “ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ፤” አላቸው። ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንደሚገባቸው የሚያስተምር ምሳሌን ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፦ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ ወደ እርሱም እየመጣች ‘በባላጋራዬ ፊት ፍረድን ስጠኝ፤’ ትለው ነበር። ለአያሌ ቀናትም ሊፈርድላት አልፈለገም ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ፥ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ፤’ አለ።” ጌታም አለ፦ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔር ታዲያ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ፥ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል እላችኋለሁ። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” ጻድቃን ነን በማለት በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፦ “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሌላውም ቀራጭ ነበር። ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ ሲል በልቡ ጸለየ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፥ ቀማኛና ዐመፀኛ አመንዝራም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ፤’ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳን አልፈለገም፤ ነገር ግን ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ፤’ እያለ ደረቱን ይመታ ነበር። ከዚያኛው ይልቅ ይህ ሰው ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ እላችኋለሁ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፥ ራሱን ግን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል።” እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ተዉአቸው፤ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፤” አለ። ከአለቆችም አንዱ “ቸር መምህር! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛቱን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤” አለው። እርሱም “ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለ። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ “አንዲት ነገር ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን እጅግ ሀብታም ነበርና ይህንን ሰምቶ በጣም አዘነ። ኢየሱስም በዛም እንዳዘነ አይቶ “ሀብት ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፤” አለ። የሰሙትም “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል፤” አለ። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተለንሃል፤” አለ። እርሱም “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን፥ ሚስትን፥ ወንድሞችን፥ ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም፤” አላቸው። ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፤ ያፌዙበታልም፤ ያንገላቱትማል፤ ይተፉበትማል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፤ ይህም ንግግር ተሰውሮባቸው ነበር፤ የተናገረውንም አላወቁም። ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዐይነ ስውር በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። ብዙ ሰዎች ሲያልፉ ሰምቶ “ይህ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀ። እነርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስ እያለፈ ነው፤” ብለው አወሩለት። እርሱም “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ ጮኸ። በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ አብዝቶ ጮኸ። ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እንደገና ማየት እንድችል አድርገኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እይ! እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም እያወደሰ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ወደ ኢያሪኮም ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፤ ሀብታምም ነበረ። ኢየሱስ ማን እንደሆነም ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ አቃተው። በዚያችም መንገድ ማለፍ ነበረበትና ወደ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ፤” አለው። ፈጥኖም ወረደ፤ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው “ከኀጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ፤” ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን መጥቶ አል፤ ምክንያቱም እርሱም የአብርሃም ልጅ ነውና፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና፤” አለው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሳለ፥ ወደ ኢየሩሳሌም በመቃረቡ፥ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ እንደሚገለጥ ይገምቱ ነበርና፥ ተጨማሪ ምሳሌ ነገራቸው። እንዲህም አላቸው “አንድ መኰንን ለራሱ የመንግሥትን ሥልጣን ተቀብሎ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ዐሥር አገልጋዮችንም ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘እስክመጣ ድረስ ነግዱ፤’ አላቸው። የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና ‘ይህ በላያችን እንዲነግሥ አንፈልግም፤’ ብለው በኋላው መልእክተኞችን ላኩ። መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን አግልጋዮች እንዲጠሩለት አዘዘ። የመጀመሪያውም ደርሶ ‘ጌታ ሆይ! ምናንህ ዐሥር ምናን አተረፈ፤’ አለው። እርሱም ‘መልካም፥ አንተ በጎ አገልጋይ፥ በጥቂት ነገር የታመንህ ስለ ሆንክ በዐሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ፤’ አለው። ሁለተኛውም መጥቶ ‘ጌታ ሆይ! ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ፤’ አለው። ይህናውንም ‘አንተንም በአምስት ከተማዎች ላይ ሾሜሃለው፤’ አለው። ሌላውኛውም መጥቶ ‘ጌታ ሆይ! በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንክ፤ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፤ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ነህና፤’ አለው። እርሱም ‘አንተ ክፉ አገልጋይ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላስቀመጥኩትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ አወቅህ፤ ታዲያ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው ለምንድን ነው? እኔም መጥቼ ከነትርፉ እወስደው ነበር፤’ አለው። በዚያም ቆመው የነበሩትን ‘ምናኑን ውሰዱበት፤ ዐሥር ምናን ላለውም ስጡት፤’ አላቸው። እነርሱም ‘ጌታ ሆይ! ዐሥር ምናን አለው፤’ አሉት። ‘ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል እላችኋለሁ። ነገር ግን እነዚያን በላያቸው እንድነግሥ ያልፈለጉትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው፤ በፊቴም እረዱአቸው።’” ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ደብረዘይት በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበም ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ እርሷም ገብታችሁ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡት። ማንም ‘ስለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤’ በሉ”። የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ “ውርንጫውን ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ለጌታ ያስፈልገዋል፥” አሉ። ወደ ኢየሱስም አመጡት፤ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ወርውረው ኢየሱስን አስቀመጡት። ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። ወደ ደብረዘይት ቁልቁለትም ወዲያው በቀረበ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ በሙሉ ስላዩአቸው ተአምራት ደስ እያላቸው በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመሩ፤ እንዲህም አሉ፦ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር፥” አሉ። ከሕዝቡም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ! ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው፤” አሉት። ሲመልስም “እነዚህ እንኳ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ፤እላችኋለሁ” አላቸው። ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ እንዲህ እያለ አለቀሰላት፤ “አንቺስ ለሰላምሽ የሚሆነውን ምነው በዚህ ቀን ባወቅሽ ኖሮ! ነገር ግን አሁን ከዐይንሽ ተሰውሮአል። ጠላቶችሽም በዙርያሽ ቅጥር የሚሠሩበት፥ አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁብት ቀኖች ይመጣሉ። አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን በምድር ላይ ይጨፈልቃሉ፤ በአንቺ ውስጥም በድንጋይ ላይ የሚኖር ድንጋይ አያስቀሩም፤ የተጐብኘሽበትን ዘመን አላወቅሽምና።” ወደ መቅደስም ገብቶ የሚገበያዩትን ማስወጣት ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው፦ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት፤” አላቸው። በየዕለቱም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ በታላቅ ትኩረት ይሰሙት ነበርና። አንድ ቀንም ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና “እስኪ ንገረን፤ እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ነው የምታደርገው? ወይንስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ተናገሩት። ሲመልስም “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እስቲ ንገሩኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረች ወይስ ከሰዎች?” አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ በድንጋይ ይወግሩናል፤ ምክንያቱም ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉም ያምኑ ነበርና” አሉ። መልሰውም “ከየት እንደሆነ አናውቅም፤” አሉት። ኢየሱስም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው። ይህንንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ለወይን ጠባቂዎች አከራይቶ ለረጅም ጊዜ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ጊዜውም ሲደርስ ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ አገልጋይ ወደ ተከራዮቹ ላከ፤ ጠባቂዎቹ ግን ደበደቡትና ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት፥ አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። እንደገናም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይኸኛውን ደግሞ አቁሰለው አስወጡት። የወይኑ አትክልት ጌታም ‘ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል፤’ አለ። ተከራዮቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው፤’ አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? ይመጣል እነዚህንም ተከራዮች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።” ይህንንም በሰሙ ጊዜ “ይህስ በጭራሽ አይሁን፤” አሉ። እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ “እንግዲህ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ ነው የማዕዘን ራስ የሆነው፤’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት ነው? በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰባበራል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይጨፈልቀዋል፤” አለ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። በቅርብ እየተከታተሉትም ለገዢው ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። እነርሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “መምህር ሆይ! እውነትን እንደምትናገርና እንደምታስተምር በሰው ፊትም እንደማታደላ እናውቃለን፤ ይልቁንም በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ፤ ለቄሣር ግብር እንድንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። ሲመልሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በሕዝቡም ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ። የሙታንን ትንሣኤ የሚክዱ ሰዱቃውያን ቀርበው ጠየቁት፤ እንዲህም አሉ፤ “መምህር ሆይ! ሙሴ ‘አንድ ሰው ባለትዳር ወንድም ቢኖረውና፥ እርሱም ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ የእርሱን ሚስት አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሎ ጻፈልን። እንግዲህ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም አገባት፤ ሦስተኛውም፤ ሰባተኛውም እንዲሁ፤ ልጅም ሳይተው ሞቱ። ... ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፤ ለሚመጣው ዓለምና ለሙታን ትንሣኤ ተገቢ የሆኑት ግን አያገቡም፤ አይጋቡምም፤ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ወደ ፊት ሊሞቱም አይችሉም፤ የትንሣኤም ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሙታን እንደሚነሡ ግን ሙሴ እራሱ በቁጥቋጦው ታሪክ ጌታን ‘የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ’ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው “መምህር ሆይ! መልካም ተናገርህ፤” አሉት። ከዚያም ወዲህ ምንም ሊጠይቁት አልደፈሩም። እንዲህም አላቸው፥ “መሢሕ የዳዊት ልጅ ነው” እንዴት ይላሉ? ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ፦ “ጌታ ጌታዬን እንዲህ አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ፥ ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ” ይላልና፤ እንግዲህ ዳዊት እራሱ “ጌታ ብሎ ይጠራዋል፤ ታዲያ እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም ሁሉ እየሰሙት ደቀ መዛሙርቱን “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠንቀቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፥ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ ናቸው፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ፤” አለ። ዐይኑንም አንሥቶ በምጽዋት መቀበያ መባቸውን የሚያስቀምጡ ሀብታሞችን አየ። አንዲትም ድኻ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስታስቀምጥ አየና “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉ አብልጣ አስቀምጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ መዝገቡ አስቀምጠዋልና፤ እርሷ ግን እየጐደላት የነበራትን ንብረት ሁሉ ሰጠች፤” አለ። አንዳንዶቹም ስለ ቤተ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ “ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል፤” አለ። እነርሱም “መምህር ሆይ! እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሊሆን መቃረቡን የሚያሳየው ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እንዲህም አለ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤ ዘመኑም ቀርቦአል፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።” በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይታያል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ጭነው ይይዟችኋል፤ ያሳድዱአችኋ፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህም የመከላከያ መልስ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ። ተቃዋሚዎቻችሁ በሙሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆችና ወንድሞች፥ ዘመዶችና ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ በሁሉም ከስሜ የተነሣ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ። “ኢየሩሳሌም ግን በሠራዊት ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በመካከልዋም ያሉ ከእርሷ ይራቁ፤ በገጠር ያሉም ወደ እርሷ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የቅጣት ጊዜ ነውና። በነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቁጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይሰደዳሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ላይ ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ በመረበሽ ይጨነቃሉ፤ የሰማያት ኀይላት ይናወጣሉና፥ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጣውን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም መሆን ሲጀምር መዳናችሁ ቀርቦአልና ቁሙ፤ ቀናም በሉ።” እንዲህ ሲልም ምሳሌ ነገራቸው “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቁጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር፥ ስለ ኑሮም ማሰብ እንዳይዝል፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ሁልጊዜ ትጉ።” ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ደብረዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው ወደ መቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ፋሲካም ተብሎ የሚጠራው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎች እርሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ መካከል አንዱ በነበረውና የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ውስጥ ገባ፤ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከቤተ መቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። እሺም አለ፤ ሕዝብም ባልተገኘበት ጊዜ አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካም በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም “ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን፤” ብሎ ላካቸው። እነርሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም አላቸው “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል የት ነው?’ ይልሃል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈውን ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።” ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም “ከመከራዬ በፊት ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም እላችኋለሁና፤” አላቸው። ጽዋንም ተቀበሎ፥ አመስግኖም “እንካችሁ፤ ይህን በመካከላችሁ ተካፈሉት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም እላችኋለሁና” አለ። ኅብስትንም አንሥቶ፥ አመስግኖ፥ ቆረሰና እንዲህ ሲል ሰጣቸው፦ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። የሰው ልጅስ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን አሳልፎ ለሚሰጠው ሰው ወዮለት።” እነርሱም ከነሱ መሀል ይህንን የሚያደርገው ማን እንደሆነ ለማወቅ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ከእነሱ መሀል ማን እንደሚበልጥ ለማወቅ ክርክር ተነሣ። እንዲህም አላቸው አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው በጎ አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በእናንተ መሀል እንደ ታናሽ፥ ሥልጣን ያለውም እንደሚያገለግል ይሁን። ለመሆኑ ማነው ታላቅ? በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በእናንተ መሀል እንደሚያገለግል ነኝ። እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ ለመንግሥት እሾማችኋላሁ፤ በመንግሥቴም ከእኔ ማዕድ ትበላላአችሁ፥ እንዲሁም ትጠጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይም ለመፍረድ በዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ። ጌታም “ስምዖን ስምዖን ሆይ! እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና፤” አለ። እርሱም “ጌታ ሆይ! ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ፤” አለው። እርሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፥ ‘አላውቅህም’ እያልህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚያም፥ “ያለ ቦርሳና ያለ ከረጢት፥ ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም” አሉ። እርሱም “አሁን ግን ቦርሳ ያለው ይያዘው፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ የግድ መፈጸም አለበት እላችኋልለሁ፤ አዎን፤ ስለ እኔ የተባለው አሁን ይፈጸማልና፤” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ፤” አሉት። እርሱም “ይበቃል፤” አላቸው። እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ “አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው። ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፦ “ይህንስ ተው” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር በመቅደስ ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ሆኖም ይህ የእናንተ ጊዜና ጨለማው የሚሰፍንበት ወቅት ነው፤” አላቸው። ይዘውም ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። በግቢው መካከልም እሳት አንድደው፥ በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት አገልጋይ አየችውና ትኩር ብላ “ይህም እኮ ከእርሱ ጋር ነበረ፤” አለች። እርሱ ግን “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም፤” ሲል ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አይቶት “አንተም እኮ ከእነርሱ አንዱ ነህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም፤” አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላ ሰው “እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” ሲል አጥብቆ ተናገረ። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም፤” አለ። ያን ጊዜም፥ ገና እየተናገረ ሳለ ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይቀልዱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፊቱንም እየሸፈኑ “በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር፤” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ሲነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና “አንተ መሢሕ ነህን? እስቲ ንገረን፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም፤ አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁላቸውም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም “እኔ እንደሆንሁ እናንተ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። እነርሱም “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ። የተሰበሰቡት በሙሉ ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና “ይህ ሕዝባችንን ሲያስት ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል፥ ደግሞም ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ፤’ ሲል አገኘነው” ብለው ይከሱት ጀመር። ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ “አንተ አልህ፤” አለው። ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ “በዚህ ሰው ላይ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤” አለ። እነርሱ ግን “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ። ጲላጦስም ይህንን ሰምቶ ሰውየው የገሊላ ሰው እንደሆነ ጠየቀ፤ ከሄሮድስም ግዛት እንደመጣ ሲያውቅ፥ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ወደነበረው ወደ ሄሮድስ ላከው። ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፤ ተአምር ሲሠራ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። የካህናት አለቆችና ጻፎችም በብርቱ እየከሰሱት ቆመው ነበር። ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው፤ አፌዘበትም፤ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ላከው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን ወዳጆች ሆኑ፤ በፊት በመካከላቸው ጥል ነበረና። ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “‘ሕዝቡን ያስታል፤’ ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል እንኳ በዚህ ሰው ላይ አላገኘሁም። ሄሮድስም በበኩሉ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” (በበዓሉ አንድ እስረኛ ለሕዝቡ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና።) ሁሉም በአንድነት “ይህን አስወግደው፤ በርባንንም ፍታልን፤” እያሉ ጮኹ፤ እርሱም ሁከትን በከተማ አስነሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ፈልጎ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ ነገር ግን እነርሱ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ለሦስተኛ ጊዜም “ይህ ሰው ምን ክፉ ነገር ሠራ? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ፤” አላቸው። እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጥብቀው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ድምፅ በረታ። ጲላጦስም ልመናቸው እንዲፈጸም ፈረደበት። ሁከት በመፍጠርና ሰውን በመግደል ምክንያት ታስሮ የነበረውን በጥያቄአቸው መሠረት አስፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንደ ፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው። በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?” ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኰንኖቹም “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን፤” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም ወደ እርሱ ቀርበው፥ ሆምጣጤም አምጥተው “አንተ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን፤” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል በግሪክ፥ በሮማይስጥና በዕብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን፤” ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? እኛ ስለ አደረግነው የሚገባንን እየተቀበልን ነው፤ በእኛ ላይ የተወሰነው ትክክለኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም ክፋት አልሠራም፤” ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ፤” አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፤ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፤ ፀሐይም ጨለመ፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤” አለ። ይህንንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ፤” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ተመለሱ። እርሱን የሚያውቁት ሁሉ ግን ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ጭምር በሩቅ ቆመው ይህን እያዩ ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ እንዲሁም የሸንጎ አማካሪ የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ በበኩሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኽም ሰው ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን አስከሬን ለመነው፤ አውርዶም በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም እየጀመረ ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን እንዲሁም አስከሬኑን እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም ዕለት ሕጉ እንዲሚያዘው ዐረፉ። ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፥ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት፤ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲገረሙ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው “ሕያዉን ለምን በሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ እዚህ የለም፤ ይልቁንም ተነሥቶአል። ገና በገሊላ እያለ የነገራችሁን አስታውሱ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው።” እነርሱም ቃሎቹንም አስታወሱ፤ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና፥ የያዕቆብም እናት ማርያም፥ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሌሎች ሴቶች ነበሩበት። ነገር ግን ይህ ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ። እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም “አብራችሁ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?” አላቸው። እነርሱም አዝነው ቀጥ ብለው ቆሙ። ቀለዮጳ የሚባለውም አንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም የተከሠተውን ነገር የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” እርሱም “ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነው፤ የካህናት አለቆቻችንና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን የሚታደገው እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ይህ ነገር ከሆነ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ‘ሕያው ነው’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛ ጋር ከነበሩት አንዳንዶች ወደ መቃብር ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉ፤ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን አብራራላቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፤ እርሱም አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “እኛ ጋር እደር፤ እየመሸ ነው፥ ቀኑም እያለቀ ነውና፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት፤ እርሱም እነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፤ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዐይናቸውም ተከፈተና አወቁት፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም “በመንገድ ሳለን ሲያናግረንና መጻሕፍትንም ሲያስረዳን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትንም በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፥ ለስምዖንም ታይቷል” ይሉ ነበር። እነርሱም በመንገድ የሆነውን፥ እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም ሲነጋገሩ ሳለ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው “ስለምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ያድራል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ ዳስሱኝና እዩ፥ መንፈስ በእኔ እንደምታዩት፥ ሥጋና አጥንት የለውምና፤” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ ብዛት ገና ሳያምኑ ገና በመገረም ላይ ሳሉ “በዚህ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።” እስከ ቢታንያም ወሰዳቸው፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። እየባረካቸውም ከእነርሱ ተለየ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በመቅደስ ኖሩ። በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው። አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ “እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ‘አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይበልጣል፤’ ብዬ ስለ እርሱ የተናገርሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁት።” ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲኖር አየሁ። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ ‘መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው፤’ አለኝ። እኔም አይቻለሁ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።” በማግሥቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀመዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ ኢየሱስንም ሲራመድ ተመልክቶ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ፤” አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም መለስ ብሎ ሲከተሉትም አይቶ “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ!፥ (ሲተረጎም ‘መምህር ሆይ’ ማለት ነው) የምትኖረው የት ነው?” አሉት፤ እርሱም “መጥታችሁ እዩ፤” አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሢሕን አግኝተናል” አለው፤ ትርጓሜውም “ክርስቶስ” ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ” አለው፤ ትርጓሜውም “ጴጥሮስ” ማለት ነው። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል፤” አለው። ናትናኤልም “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስ “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ “ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው እነሆ!” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ፥ አየሁህ፤” አለው። ናትናኤልም መልሶ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ፤” ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው። በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም፤” አለችው። ኢየሱስም “አንቺ ሴት ሆይ ፦ ይህ ጉዳይ ለእኔ ምንድነው? ጊዜዬ ገና አልደረሰም ፤” አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ፤” አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው፤” አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት፤” አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል፤” አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ለጥቂት ቀን ተቀመጡ። የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በመቅደስም በሬዎችን፥ በጎችንና እርግቦችን የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ እርግብ ሻጪዎችንም “ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “የቤትህ ቅንዓት ይበላኛል፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። ስለዚህ አይሁድ መልሰው “ይህንን ስለ ማድረግህ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ፤” አላቸው። ስለዚህ አይሁድ “ይህ ቤተ መቅደስ ለአርባ ስድስት ዓመት እየተሠራ ነበር፤ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?” አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ እየተናገረ ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ። በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳሉ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤ ነገር ግን ኢየሱስ በበኩሉ አይተማመንባቸውም ነበር፤ ስለ ሰው ማንም እንዲመሰክር አያስፈልገውም ነበር፤ በሰው ውስጥ ያለውን እራሱ ያውቅ ነበርና። ከፈሪሳውያንም ወገን አንድ ሰው ነበረ፤ ስሙ ኒቆዲሞስ ሲሆን የአይሁድም አለቃ ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ “መምህር ሆይ! ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር መሆንህን እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፤” አለው። ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስ መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ የእኛንም ምስክርነት አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅም መሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ ከወዲሁ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፥ ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር መከናወኑ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፤ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን፥ በዚያ ብዙ ውሃ ነበርና፥ ያጠምቅ ነበር፤ እየመጡም ይጠመቁ ነበር፤ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልወረደም ነበርና። በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከልም ስለ ማንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። ወደ ዮሐንስም መጥተው “መምህር ሆይ! በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ፤” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው እንዳችም ነገር ሊቀበል አይችልም። እናንተ ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ፤’ እንዳልሁ እራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ እንዲልቅ እኔ ግን እንዳንስ ያስፈልጋል።” ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው፥ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፤ ምስክርነቱንም የሚቀበለው የለም። ምስክርነቱን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አረጋገጠ። እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና። አባት ልጁን ይወዳል፥ ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል። በልጁ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ለልጁ የማይታዘዝ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። እንግዲህ “ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል፤ ያጠምቅማል፤” መባሉን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ምንም እንኳን ደቀመዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ እራሱ ባያጠምቅም፤ የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ እንደገና ሄደ። በሰማርያም ማለፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኝ ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። አንዲት የሰማርያ ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ ደቀመዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! መቅጃ የለህም፤ ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውሃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል፤” አለችው። ኢየሱስም መልሶ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል እንጂ፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! እንዳልጠማ ውሃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውሃ ስጠኝ፤” አለችው። ኢየሱስም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ፤” አላት። ሴቲቱ መልሳ “ባል የለኝም፤” አለችው። ኢየሱስም “‘ባል የለኝም፤’ በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነቱን ተናገርሽ፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ‘ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው፤’ ትላላችሁ፤” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት “አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ለምናውቀው እንሰግዳለን፥ መዳን ከአይሁድ ነውና። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ ይኸውም አሁን ነው፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።” ሴቲቱ “ክርስቶስ የሚባል መሢሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል፤” አለችው። ኢየሱስ “የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ፤” አላት። በዚያም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን “ምን ፈለግህ?” ወይም “ስለምን ትናገራታለህ?” ያለ ማንም አልነበረም። ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች፤ ለሰዎቹም “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” አለች። ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ይህም ሲሆን ሳለ ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! ብላ፤” ብለው ለመኑት። እርሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ፤” አላቸው። ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ “የሚበላው አንዳች ምግብ ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ ማድረግ፥ ሥራውንም መፈጸም ነው። እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶአል፤ ከዚያም መከር ይመጣል፤’ ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ እርሻው ከወዲሁ ለአዝመራ እንዴት እንደ ደረሰ ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፤ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። ‘አንዱ ይዘራል፤ አንዱም ያጭዳል፤’ የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም እነርሱ በደከሙበት ገባችሁ።” ሴቲቱም “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ፤” ብላ በመሰከረችው ቃል መሠረት፥ ከዚያች ከተማ፥ ብዙ የሰማርያ ሰዎች በእርሱ አመኑ። የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ለሁለት ቀን ያህል ቆየ። በቃሉ ምክንያት ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ሴቲቱንም “አሁን የምናምነው በቃልሽ ምክንያት አይደለም፤ እኛ እራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱ በእውነት የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን፤” ይሉአት ነበር። ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች፥ እራሳቸውም ለበዓል መጥተው ነበርና፥ በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደመጣ ሰምቶ፥ ልጁ ሊሞት ስለ ቀረበ፥ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ “ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም፤” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ፤” አለው። ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ፤” አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ አገልጋዮቹ ተገናኙትና “ብላቴናህ በሕይወት አለ፤” ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ትናንት በሰባት ሰዓት ትኩሳቱ ለቀቀው፤” አሉት። አባቱም፥ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት አለ፤” ባለው በዚያ ሰዓት እንደሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋር አመነ። ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ምልክት ነው። ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው፥ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው ‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ አለኝ፤” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም “‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ስለ ነበርና፥ በዚያ ስፍራ ብዙ ሰዎች ሰለ ነበሩ ነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፤” አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ በሰንበት ይህን አድርጎ ነበርና። ኢየሱስ ግን “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ፤” ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤” ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከእራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። አብ ከቶ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ይልቁንም፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በእራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በእራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና። “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ለእራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልክተኞችን ልካችኋል፥ እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን የሰው ምስክር የሚያስፈልገኝ አይደለሁም፤ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ እንድፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ እርሱ የላከውንም እናንተ አታምኑምና፤ በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ በእነርሱም የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ታስባላችሁና፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። የሰው ክብር አያስፈልገኝም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌላችሁ ዐወቅሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ፤ አትቀበሉኝምም፤ ሌላው በእራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ፥ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ብቻ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴንስ ብታምኑት እኔንም ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። የእርሱን ጽሑፎች ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ በዓል ፋሲካም ቀርቦ ነበር። ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አለው። ሊፈትነው ይህን ተናገረ፤ እራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና። ፊልጶስ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም፤” ብሎ መለሰለት። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፦ “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ሰው ምን ይሆናል?” ኢየሱስም “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ፤” አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ፤ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፤ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤ እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “አንድም እንኳን እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ፤” አላቸው። ሰለዚህም አከማቹ፤ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው፤” አሉ። ኢየሱስም መጥተው በጉልበት ሊያነግሡት መሆናቸውን አውቆ በድጋሚ ወደ ተራራ ለብቻው ርቆ ሄደ። በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፤ በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። ከወዲሁ ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤ ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ። ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ። እርሱ ግን “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች። በማግሥቱም በባሕር ማዶ ቆሞ የነበረው ሕዝብ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤ ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ። ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀመዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ እራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። በባሕር ማዶም ሲያገኙት “መምህር ሆይ! ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን የለዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው መብል ሥሩ፤ ይህም የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ነው፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” እንግዲህ “የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን እናድርግ?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔር ሥራ ይህ ነው፤ ይህም እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው፤” አላቸው። እንዲህም አሉት፦ “ታዲያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ዓይነት ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ፤” አሉት። ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና፤” አላቸው። ስለዚህ “ጌታ ሆይ! ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም በፍጹም አይጠማም። ነገር ግን እንዳያችሁኝ፥ እንዳላመናችሁም ነገርኳችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላስወጣውም፤ ፈቃዴን ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድም እንኳን እንዳላጠፋ፥ ይልቁንም በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው ነው። የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” አይሁድም “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ፤” በማለቱ ማንጐራጐር ጀመሩ፤ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱን እናውቃቸው የለምን? ታዲያ ‘ከሰማይ ወርጃለሁ’ እንዴት ይላል?” አሉ። ኢየሱስም መለሰ፥ አላቸውም፦ “እርስ በእርሳችሁ አታንጐራጉሩ። የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤’ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ እንዲበላ፥ እናም እንዳይሞት ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው። እኔ ከሰማይ የወረደው ሕያው እንጀራ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” አይሁድም “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በእራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ፥ እኔም በአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚመገበኝ ደግሞ በእኔ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተው ነገር ግን እንደሞቱበት ዓይነት አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል።” በቅፍርናሆም፥ በምኵራብ ሲያስተምር ነበር ይህን ያለው። ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በሰሙ ጊዜ “ይህ ንግግር ከባድ ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ግን ደቀመዛሙርቱ በዚህ ምክንያት እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህ ያስናክላችኋልን? ታዲያ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ሊሆን ነው? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋስ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ፥ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደሆነ ከመጀመሪያው ያውቅ ነበርና። እንዲህም አለ፦ “ስለዚህ አልኋችሁ፤ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ ያልኋችሁ በዚህ ምክንያት ነው።” በዚህም ምክንያት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደፊትም ከእርሱ ጋር ወደ ፊት መሄድም አቆሙ። ኢየሱስም ለዐሥራ ሁለቱ “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁን?” አለ። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም “እኔ እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጫችሁ የለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው፤” ብሎ መለሰላቸው። ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ መናገሩ ነበር፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ሲሆን፥ አሳልፎም የሚሰጠው እርሱ ነበርና ነው። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበር። አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ወንድሞቹም “ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ በይፋ መታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ እራስህን ለዓለም ግለጥ፤” አሉት። ወንድሞቹም እንኳን አላመኑበትም ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ይጠላኛል፤ ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና ነው። እናንተ ወደ በዓሉ ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል አልወጣም።” ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ፥ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝቡም መካከል በእርሱ ምክንያት ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዶቹ “ደግ ሰው ነው፤” ሌሎች ደግሞ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ፤” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም “ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትምህርቴስ የላከኝ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር እንደሆነ ወይንም እኔ ከራሴ የምናገር እንደሆነ ያውቃል። ከገዛ እራሱ የሚናገር የገዛ እራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ በእርሱም ዐመፃ የለበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚፈጽም አንድ እንኳን የለም። ልትገድሉኝ ስለምን ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡ መለሱና “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንድ ሥራ ፈጸምኩ፥ ሁላችሁም ትደነቃላችሁ። ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዳንዶቹ እንዲህ አሉ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆ፥ በግልጥ ይናገራል፤ ነገር ግን ምንም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው ክርስቶስ እንደሆነ በእውነት አወቁን? ሆኖም ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደሆነ ማንም አያውቅም።” እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር “እኔንም ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ፤” ብሎ ጮኸ። ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና፥ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ሰው ካደረጋቸው ምልክቶች የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ። ፈሪሳውያን ሕዝቡ ስለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጉሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሊይዙት ዘቦችን ላኩ። ኢየሱስም “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤” አለ። አይሁድም እንዲህ ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ “እኛ እንዳናገኘው ይህ ሰው ወዴት ሊሄድ ነው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሄዶ የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር ነውን? ‘ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ የሚለውስ ይህ አባባል ምን ማለት ነው?” ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን፥ መጽሐፍ እንዳለው፥ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።” ይህንንም በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ “ይህ በእውነት ነቢዩ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች “ይህ ክርስቶስ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች ግን “ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? አሉ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፥ ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተልሔም እንደሚመጣ መጽሐፍ አልተናገረምን?” ስለዚህም ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። ዘቦቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነርሱም “ለምንድነው ያላመጣችሁት?” አሉአቸው። ዘቦቹም “እንደዚህ ሰው ማንም ከቶ አልተናገረም፤” ብለው መለሱ። ፈሪሳውያንም እንዲህ ብለው መለሱላቸው፤ “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው፤” ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ፥ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” እነርሱም መለሱና “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምርና እይ፤” አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ። ኢየሱስ ግን ወደ ደብረዘይት ሄደ። ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ፤ በመካከልም እርሱዋን አቁመው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ! ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርሷ ምን ትላለህ?” የሚከሱበትን ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህንን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት፤” አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ “አንቺ ሴት! ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም “ጌታ ሆይ! አንድም እንኳን፤” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ፤” አላት። ደግሞም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ስለ እራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድምሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ መንገድ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ላይ እንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነውና፥ ብቻዬንም አይደለሁምና፥ እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። ስለ እራሴ የምመሰክረው እኔ ነኝ፤ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” ስለዚህም “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔንም ሆነ አባቴንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤” አላቸው። ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህንን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም። ኢየሱስም ደግሞ “እኔ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁም፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤” አላቸው። አይሁድም “‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ ማለቱ እራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ። “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።” እንግዲህ “በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና፤” አላቸው። እንግዲህ “አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም “ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ። ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ፤” አላቸው። ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። ስለዚህም ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እንደሆንሁ፥ እንደዚህም የምናገረው አባቴ እንዳስተማረኝ እንጂ በእራሴ ምንም እንደማላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና፤ አብ ብቻዬን አይተወኝም፤” አላቸው። ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ። ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፤” እነርሱም መልሰው “የአብርሃም ዘር ነን፤ ከቶ ለማንም ባርያዎች አልሆንም፤ አንተ ‘አርነት ትወጣላችሁ፤’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘለዓለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘለዓለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ ነፃ ቢያወጣችሁ በእውነት ነፃ ትወጣላችሁ። የአብርሃም ዘር መሆናችሁንማ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።” መልሰውም “አባታችንስ አብርሃም ነው፤” አሉት። ኢየሱስም “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑማ ኖሮ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የምነገራችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። እናንተ የአባታችሁን ሥራ ትሠራላችሁ፤” አላቸው። እነርሱም “እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም፤ አንድ አባት አለን፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው፤” አሉት። ኢየሱስም አላቸው “እግዚአብሔርስ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከእራሱ አፍልቆ ነው፤ ሐሰተኛ፥ የሐሰትም አባት ነውና። እኔ ግን እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም። ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለምን አታምኑኝም? ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና አትሰሙም።” አይሁድ መልሰው “ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በመናገራችን ትክክል አይደለንምን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “እኔስ ጋኔን የለብኝም፤ ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ፤ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ። እኔ ግን የእራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም።” አይሁድ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም እንኳን ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ‘ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አይቀምስም፤’ ትላለህ። በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ እራስህን ማን ታደርጋለህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ ነገር ግን አላወቃችሁትም፤ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል ኖሮ እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ ነበር፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት በመመኘት ሐሤት አደረገ፤ አየም፤ ደስም አለው።” አይሁድም “ገና አምሳ ዓመት አልሞላህም፤ አብርሃምን አይተሃልን?” አሉት። ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ፤” አላቸው። ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸው፥ ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ። ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአትን የሠራው ማን ነው? እርሱ ነው ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህንንም ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች ቀባና “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ፤” አለው፤ ትርጓሜውም “የተላከ” ማለት ነው። ስለዚህም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም መጣ። ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን አይተውት የነበሩ “ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። ሌሎችም “እርሱ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ፥ እርሱ አይደለም፤” አሉ፤ እርሱ “እኔ ነኝ፤” አለ። ታድያ “ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱ መልሶ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ፤’ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ፤” አለ። “ያ ሰው ወዴት ነው?” አሉት። “አላውቅም” አለ። በፊት ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዐይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ ፈሪሳውያን እንዴት እንዳየ እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ጭቃ በዐይኖቼ አኖረ፤ ታጠብሁም፤ አያለሁም፤” አላቸውም። ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም፤” አሉ። ሌሎች ግን “ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶችን ሊያደርግ እንዴት ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዐይነ ሥውሩን፥ “አንተ ዐይኖችህን ስለ ከፈተ፥ ስለ እርሱ ምን ትላለህ?” ደግሞ አሉት። እርሱም “ነቢይ ነው፤” አለ። አይሁድ የዚያን ማየት የቻለውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ፥ ዐይን ሥውር እንደ ነበረና ማየትም እንደ ጀመረ አላመኑም፤ እነርሱንም “እናንተ ዐይን ሥውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልሰው “ይህ ልጃችን እንደሆነ ዐይነ ስውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት ማየት እንደቻለ አናውቅም፤ ወይም ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ እራሱ መናገር ይችላል፤” አሉ። ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህንን አሉ፤ “እርሱ ክርስቶስ ነው፤” ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። ስለዚህ ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት፤” አሉ። ስለዚህ ዐይን ሥውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን፤” አሉት። እርሱም መልሶ “ኀጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዐይን ሥውር እንደ ነበርሁ፥ አሁንም እንደማይ፥ ይህንን አንድ ነገር አውቃለሁ፤” አለ። ደግመውም “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይኖችህን ከፈተ?” አሉት። እርሱም መልሶ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አልሰማችሁምም፤ ስለምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትፈልጋላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። ተሳድበውም “አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤” አሉት። ሰውዬው መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “ከወዴት እንደሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፤ ዳሩ ግን ዐይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር፥ ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን። ዐይን ሥውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር።” መልሰው “አንተ ሙሉ በሙሉ በኃጢአት ተወልድህ፤ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ ሲያገኘውም “አንተ በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ “ጌታ ሆይ! በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው፤” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ፤” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ፤” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያንም መሀል ይህንን ሰምተው “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኀጢአታችሁም በዚያው ይኖራል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበሩ ሳይሆን የማይገባ በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በር ጠባቂው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፤ የእራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የእራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎቹን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወትን እንዲያገኙ፥ የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ከእነኚህ ቃላት የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች “ጋኔን አለበት፤ አብዶአልም፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ሥውሮችን ዐይን ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ ፤ ወቅቱም የብርድ ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በመቅደስ፥ በሰሎሞን ታዛ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጥ ንገረን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አታምኑም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤ እናንተ ግን ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።” አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ የትኛው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም “ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ እንጂ፤ ይልቁንም አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ እራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ‘አማልክት ናችሁ አልሁ፤’ ተብሎ በሕጋችሁ ተጽፎ የለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን እናንተ ‘ትሳደባለህ፤’ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆነ አትመኑኝ፤ የምሠራ ከሆነ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ፥ አብ በእኔ እንደሆነ እኔም በአብ እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” ደግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አምልጦ ሄደ። ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ፥ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ፥ እንደገና ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ አንድ ምልክት እንኳን አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ፤” አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ። አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ እርሱም እንደ ማርያምና እንደ እኅትዋ ማርታ ከቢታንያ የነበረው አልዓዛር ነው። ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጉርዋ ያበሰችው ስትሆን፤ የታመመውም አልዓዛር ወንድምዋ ነበር። ስለዚህም እኅቶቹ “ጌታ ሆይ! እነሆ የምትወደው ታሞአል፤” ብለው ወደ እርሱ ላኩበት። ኢየሱስም ሰምቶ “ይህ ሕመም ለሞት አይሰጥም፤ ይልቁንም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ነው” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያንጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፥ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንንና ወገናችንንም ይወስዳሉ፤” በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንደሚሻል አታስቡም፤” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው “ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን?” ተባባሉ። የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቅ ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዝዘው ነበር። ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። በዚያም እራት አዘጋጁለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት መካከል አንዱ ነበረ። ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቶ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግሮች ቀባች፤ በጠጉርዋም አበሰቻችው፤ ቤቱም በሽቶው መዓዛ ተሞላ። ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ፥ አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ “ይህ ሽቶ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ለምን አልተሰጠም?” አለ። ይህንንም የተናገረው ለድሆች አዝኖላቸው ሳይሆን ሌባ ስለ ነበረ ነው፤ የገንዘብ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። ኢየሱስም “ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤” አለ። ከአይሁድም ብዙ ሰዎች በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፤ የመጡትም በኢየሱስ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ሊገድሉት ተማከሩ፤ ከአይሁድ ብዙዎቹ በእርሱ ምክንያት እነርሱን እየተዉ በኢየሱስ ያምኑ ነበርና ነው። በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥቶ የነበረው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰማ ጊዜ፥ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዞ ሊቀበለው ወጣና “ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፤” እያሉ ጮኸ። ኢየሱስ የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ በእርሱ ላይ ተቀመጠ፤ ይህም፥ “አንቺ የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል፤” ተብሎ እንደ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው። አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል፤” ተባባሉ። በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው “ጌታ ሆይ! ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን፤” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ ስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፤ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። “አሁን ነፍሴ ታውካለች፤ ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ! ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ! ስምህን አክብረው።” ስለዚህም “አከበርሁት፤ ደግሞም አከብረዋለሁ፤” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ “ነጐድጓድ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች “መልአክ ተናገረው፤” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቷል እጂ ስለ እኔ አይደለም። አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። እንዲህ ሕዝቡ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ፤” አላቸው። ኢየሱስም ይህን ከተናገረ በኋላ ሄዶ ተሰወረባቸው። ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግም፤ እነርሱ ግን በእርሱ አላመኑም። ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ! ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስለዚህ ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎአልና፥ “በዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዐኖቻቸውን አሳወረ፤ ልባቸውውንም አደነደነ።” ክብሩን ስላየ ኢሳይያስ ይህን አለ፤ ስለ እርሱም ተናገረ። ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ኢየሱስም ጮኸ፤ እንዲህም አለ “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና፤ ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የማይቀበለኝ ቃሌንም የማይሰማ እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።” ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን፥ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ፥ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካስገባ በኋላ፥ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደሰጠው፥ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ አውቆ፥ ከማእድ ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ፤ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ፤ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ማጠብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ማበስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር በጭራሽ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ድርሻ የለህም፤” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን፥ እጄንና ራሴንም ጭምር” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁም አይደለም የምናገረው፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፥ በተከሠተ ጊዜ እኔ መሆኔን ታምኑ ዘንድ ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን ማንኛውንም ሰው የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ተረበሸ፤ እንዲህም ሲል መሰከረ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ደቀመዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ ግራ ገብቶአቸው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ይወደው የነበረው አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስምዖን ጴጥሮስም በምልክት “ሰለ ማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የእንጀራ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቁራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ፤” አለው። ነገር ግን ስለምን ይህን እንዳለው በማእድ ከተቀመጡት ማንም አላወቀም፤ ይሁዳ የገንዘብ ከረጢቱን ይዞ ስለ ነበር፥ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፤ ወይም ለድሆች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበርና። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ። ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሯል፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከብሯል፤ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ! ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እርሱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋድዱ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ወዴት ትሄዳለህ?” አለው። ኢየሱስም “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አሁን ልከተልህ የማልችለው በምን ምክንያት ነው? ነፍሴን እንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት “ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።” “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበርን? ሄጄም ስፍራ ሳዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትኖሩ ዳግምኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ።” ቶማስም “ጌታ ሆይ! ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁንም ጀምሮ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል፤” አለው። ፊልጶስ “ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም አለው “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነገራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ይህም ካልሆነ ስለ ሥራዎቹ ስትሉ እመኑኝ። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውንም ሥራ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤ አብ በወልድ እንዲከብር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘለዓለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ምክንያቱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ነው። ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ስለሚኖር፥ በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላችሁ። “ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ዘመን አለ፤ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና፤ እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትንም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላኛው ይሁዳ “ጌታ ሆይ! ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “በእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም። ልባችሁ አይታወክ፤ አይፍራም። እኔ እሄዳለሁ፤ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝ ቢሆን፥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ በተሰኛችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣልና። ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን ነግሬአችኋለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም ምንም ኃይል የለውም፤ ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ፥ አብ እንዳዘዘኝ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ። “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። በእኔ ያለውን ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእንናተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ ማፍራት አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፤ ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፤ ያቃጥሉአቸውማል። በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ፤ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ አባቴ ይከበራል። አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን፥ ደስታችሁም ፍጹም እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ። “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንደሚሰጣችሁ፥ እንድትሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬአችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዛችኋለሁ። “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስላልሆናችሁ ዓለም ይጠላችኋል። ‘ባርያ ከጌታው አይበልጥም፤’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን ካሳደዱኝ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌንም ከጠበቁ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ በስሜ ምክንያት ያደርጉባችኋል። እኔ መጥቼ ባልነገራቸው ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ሰበብ የላቸውም። እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል። ነገር ግን በሕጋቸው ‘በከንቱ ጠሉኝ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ፥ እርሱም ከአብ የሚወጣው የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። “እንዳትሰናከሉ ይህን ነግሬአችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያስወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። “አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ከእናንተም ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። “ገና ብዙ የምነግራችሁ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን እርሱ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋልና። በአብ ዘንድ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ‘በእኔ ዘንድ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል’ አልሁ። “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤”፥ ደግሞ “ወደ አብ እሄዳለሁና፤ የሚለን ነገር ምንድነው?” ተባባሉ። “እንግዲህ ‘ጥቂት’ ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤’ ስላልሁ፥ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳለችሁ፤ ሙሾም ታወጣላችሁ፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና በደስታዋ ምክንያት መከራዋን ከቶውን አታስበውም። እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያን ቀንም ከእኔ ምንም ነገር አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ፤ ትቀበሉማላችሁ።” ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ ለእናንተ የምናገርበት ሰዓት ይመጣል። በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምናለሁ አልላችሁም፤ ምክንያቱም አብ እራሱ ስለሚወዳችሁ ነው፤ ይህም እናንተ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደመጣሁ ስላመናችሁ ነው። ከአብ ዘንድ መጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጥቻለሁ፤ ደግሞም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ። ደቀመዛሙርቱ “እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ፤ በምሳሌም መናገር አቆምህ። ሁሉንም ነገር እንደምታውቅ፥ እንዲሁም ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናምናለን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “አሁን ታምናላችሁን? እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፤ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፤” ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዐይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ይህም በሥጋ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲሰጣቸው ነው። የዘለዓለም ሕይወትም ይህች ናት፤ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንከውን አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ነው። እኔ እንዳደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር፥ በራስህ ዘንድ አንተ አክብረኝ። “ከዓለም ወስጥ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ፤ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፤ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ ስለ ሰጠኸኝ ስለ እነርሱ እንጂ ስለ ዓለም አልለምንም፤ እነርሱ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ። ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ! እነዚህን የሰጠኸኝ እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን እኔ በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነትህ የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።” በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም ጭምር እንጂ ስለ እነርሱ ብቻ አልለምንም፤ ይህም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም፥ አባት ሆይ! በእኔ እንዳለህና እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም እንዲያምን ነው። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ፤ ይህም እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በፍጹም አንድ እንዲሆኑ፥ እንዲሁም አንተ እንደ ላክኸኝና በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ፥ የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። ጻድቅ አባት ሆይ! ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን፥ እኔም በእነርሱ እንድሆን፥ ስምህን አስታወቅኋቸው፤ አስታውቃቸውማለሁ። ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ወታደሮችን፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና፥ በጦር መሣርያም ታጅቦ ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ። ዳግመኛ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ፤ ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን እንኳን አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ይዞ ስለ ነበር መዘዘውና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ላልጠጣ ነውን?” አለው። እንግዲህ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፤ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ሲል አይሁድን የመከራቸው ነበረ። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀመዝሙር ወጣ፤ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በር ጠባቂ አገልጋይቱም ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ “አይደለሁም” አለ። ይበርድ ነበረና አገልጋዮችና ሎሌዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገር የሰሙኝን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነርሱ እኔ የተናገርሁትን ያውቃሉ፤” አለው። ይህንን ባለ ጊዜ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ “ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደሆን ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። “አንተስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም፤” ብሎ ካደ። ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች መካከል አንዱ፥ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፥ “በአትክልቱ ስፍራ ከእርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም በድጋሚ ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም እንዳይረክሱ፥ ይልቁንም የፋሲካን በግ እንዲበሉ በማለት ወደ ገዢው ግቢ አልገቡም። ስለዚህም ጲላጦስ ወደ ውጭ፥ ወደ እነርሱ ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ምን ዓይነት ክስ ነው አላቸው?” አላቸው። እነርሱም መልሰው “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። ጲላጦስም “እናንተ ወስዳችሁ በሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛስ ማንንም ለመግደል አልተፈቀደልንም፤” አሉት፤ ይህም ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነብር። ጲላጦስም እንደገና ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። ጲላጦስ መልሶ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስም “እንግዲያውስ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ “እውነት ምንድነው?” አለው። ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትም። ነገር ግን በፋሲካ አንድ ሰው እንድፈታላችሁ ልማድ ሆኖአል፤ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። ሁሉም በድጋሚ “በርባንን እንጂ ይህን ሰው አይደለም” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ። በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ ገረፈው። ወታደሮቹም ከእሾህ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ አኖሩ፤ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ እየቀረቡም “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም በድጋሚ ወደ ውጭ ወጥቶ “እነሆ፥ አንዲት በደል እንኳን እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ ቀይ ልብስም ለብሶ፥ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም “እነሆ ሰውዬው፤” አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎችም ባዩት ጊዜ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁድም መልሰው “እኛ ሕግ አለን፤ በሕጋችን መሠረት ሊሞት ይገባዋል፤ ራሱን የእግዚአብሔርን ልጅ አድርጎአልና” አሉት። ጲላጦስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ ተመልሶም ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን “አንተ ከየት ነህ?” አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። ስለዚህም ጲላጦስ “አታናግረኝምን? ልፈታህም ሆነ ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ኀጢአቱ የባሰ ነው” አለው። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ “ይህን ሰው ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው “ጠፍጣፋ ድንጋይ” በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። የፋሲካም በዓል የሚዘጋጅበት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ አይሁድንም “እነሆ ንጉሣችሁ!” አላቸው። እነርሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው። የካህናት አለቆችም “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት እንግዲህ በዚህ ጊዜ ነው እንዲሰቀል አሳልፎ የሰጣቸው። ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ የራስ ቅል ወደሚሉት ስፍራ፥ በዕብራይስጥም ጎልጎታ ወደ ተባለው ቦታ ወጣ። በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በአንድ ጎን፥ አንዱን በሌላ ጎን፥ ኢየሱስንም በመካከላቸው አድርገው ሰቀሉ። ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበረ። ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “እርሱ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ አለ ብለህ ጻፍ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ፤” አሉት። ጲላጦስም “የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ። ወታደሮቹም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ ወሰዱ። እጀ ጠባቡ ግን ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ለማን እንዲሆን ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም “ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነበር። ወታደሮቹም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም እንዲሁም መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱንና ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን “አንቺ ሴት ሆይ! እነሆ ልጅሽ” አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እናትህ እነኋት” አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከወዲሁ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ እንዲሁም ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና፥ ሥጋቸው በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። ወታደሮችም መጥተው ከተሰቀሉት ሰዎች መካከል የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ቀድሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ። ያየውም መስክሮአል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንደሚናገር ያውቃል። ይህ የሆነው “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም ሌላው የመጽሐፍ ክፍል “ያንን የወጉትን ያዩታል” ይላል። ከዚህም በኋላ፥ አይሁድን በመፍራት በስውር የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረው የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። እንዲሁም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። በተሰቀለበትም ስፍራ የአትክልት ቦታ ነበረ፤ በአትክልቱም ቦታ ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበረና የአይሁድ የዝግጅት ቀን ስለ ነበረ ኢየሱስን በዚያ አኖሩት። ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለሞ ሳለ በማለዳ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀመዝሙር መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ እንዲሁም በራሱ ላይ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀመዝሙር ገባ፤ አየም፤ አመነም፤ “ከሙታን መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት ነጭ ልብስ የለበሱ መላእክትም፥ የኢየሱስን ሥጋ አስተኝተውበት በነበረበት ስፍራ፥ አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤” አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ እንደሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርሷ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። ኢየሱስም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ፤’ ብለሽ ንገሪአቸው፤” አላት። መግደላዊት ማርያም ሄደችና ጌታን እንዳየችው፥ ይህንንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች። በዚያው ከሳምንቱ የመጀመሪያው በሆነው ቀን፥ በመሸ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤” አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” አላቸው። ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ሌሎቹም ደቀመዛሙርቱ “ጌታን አይተነዋል፤” አሉት። እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ላይ ካላየሁ፥ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ውስጥ ካላስገባሁ፥ እጄንም በጎኑ ቊስል ውስጥ ካላስገባሁ አላምንም፤” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም ደቀመዛሙርቱ ደግመው በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ ውስጥ አስገባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤” አለው። ቶማስም “ጌታዬና አምላኬ!” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌላ ብዙ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሢሕ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ፥ ከገሊላ ቃና የሆነው ናትናኤልም፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው። እነርሱም “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት ምንም አላጠመዱም። በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ የብስ በወጡ ጊዜ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንንም ያህል ብዙ ዓሣ ይዞ መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳን “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ። ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ከእነዚህ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፤” አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን አሰማራ፤” አለው። ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ፤” አለው። ለሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ለሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ሲያመለክት ይህንን ተናገረ። ከዚያም “ተከተለኝ፤” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። ጴጥሮስም እርሱን አይቶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እርሱስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ኢየሱስም “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድስ፥ ምን ግድ አለህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። ስለዚህ “ያ ደቀመዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰማ፤ ነገር ግን ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ ምን ግድ አለህ?” አለው እንጂ “አይሞትም፤” አላለውም ነበር። ስለ እነዚህም ነገሮች የመሰከረው፥ ይህንንም የጻፈው ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም እውነት እንደሆነ እናውቃለን። ኢየሱስም ያደረገው ሌላ ብዙ ነገር አለ፤ ሁሉም አንድ በአንድ ቢጻፍ፥ እንደሚመስለኝ፥ ዓለም እራሱ የሚጻፉትን መጻሕፍት ለመያዝ ቦታ አይበቃውም ነበር። ቴዎፍሎስ ሆይ! ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፤ ነገር ግን “ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤” አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “አብ በገዛ ሥልጣኑያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤” አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም “የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል፤” አሉአቸው። በዚያን ጊዜ ደብረዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፤ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር። በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሃያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ “ወንድሞች ሆይ! ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤ ከእኛ ጋር ተቆጥሮ ነበርና፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና። ይህም ሰው በዐመፅ ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው። በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይኑር፤’ ደግሞም ‘ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት፤’ ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።” ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ። ሲጸልዩም “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ! ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው፤” አሉ። ዕጣም ተጣጣሉላቸው፤ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ። በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋ ችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በመስጴጦምያም በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው “ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል፤” አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው “የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፤ “እግዚአብሔር ይላል ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁት፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዐመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።” ወንድሞች ሆይ! ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ነገር ግን እርሱ እንዳለው፦ ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ!” “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተሰበረ፤ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና፤” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ፤” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ “ወደ እኛ ተመልከት፤” አለው። እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ፤” አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጸና፤ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፤ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ “መልካም” በሚሉአትም በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ስለምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኀይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቆርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፤ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። “አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞም በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኀጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም። ... እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። ሙሴም ለአባቶች ‘ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች፤’ አለ። ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ፤’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ ላከው።” ለሕዝቡም ሲናገሩ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያንም፥ ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስ የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ እጅግም ተቆጥተው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ እጃቸውንም ጭነውባቸው አሁን መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ አኖሩአቸው። ነገር ግን ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑ፥ የወንዶችም ቍጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ። በነገውም አለቆቻቸውና ሽማግሌዎች ጻፎችም ሊቀ ካህናቱ ሐናም ቀያፋም ዮሐንስም እስክንድሮስም የሊቀ ካህናቱም ዘመዶች የነበሩት ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ እነርሱንም በመካከል አቁመው “በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?” ብለው ጠየቁአቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደ ዳነ ብንመረመር፥ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው።’ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፤ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው “በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገበኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፤ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደሆነ ቁረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም፤” አሉአቸው። እነርሱም እንደምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና። ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ውፍደ እፍዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ፤ እንዲህም አሉ “ጌታ ሆይ! አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ ‘አሕዛብ ለምን አጉረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ፤’ ብለህ የተናገር አምላክ ነህ። በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ። አሁንም፥ ጌታ ሆይ! ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባርያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።” ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ። ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፤ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደሆነ ማንም አልተናገረም። ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው። በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፤ በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር። ትውልዱም የቆጵሮስ ሰው የነበረ አንድ ዮሴፍ የሚሉት ሌዋዊ ነበረ፤ እርሱም በሐዋርያት በርናባስ ተባለ፤ ትርጓሜውም የመጽናናት ልጅ ነው፤ እርሻም ነበረውና ሽጦ ገንዘቡን አምጥቶ ከሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፤ ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። ጴጥሮስም “ሐናንያ ሆይ! መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም፤” አለው። ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ፤ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት፤ አውጥተውም ቀበሩት። ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች። ጴጥሮስም መልሶ “እስቲ ንገሪኝ፤ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን?” አላት። እርሷም “አዎን፤ ይህን ለሚያህል ነው፤” አለች። ጴጥሮስም “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፤ አንቺንም ያወጡሻል፤” አላት። ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች፤ ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት፤ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሩአት። በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፤ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኩሳን መናፍስት የተሠቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ፤ ቅንዓትም ሞላባቸው። በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ፤” አላቸው። በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፤ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። ሌሎዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም “ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፤ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም፤” አሉአቸው። የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። አንድ ሰውም መጥቶ “እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው፤” ብሎ አወራላቸው። በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፤ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና። አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። ሊቀ ካህናቱም “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ፤” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ “ከሰው ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት እንዲሰጥ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቆጡ፤ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፤ እንዲህም አላቸው “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ ‘እኔ ታላቅ ነኝ፤’ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፤ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፤ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ ‘ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።’” ሰሙትም፤ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፤ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር። በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፤ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ! በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፤ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” ይህም ቃል ሕዝቡን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፤ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ። እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና በእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል፤” የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አነሣሡ፤ ቀርበውም ያዙት፤ ወደ ሸንጎም አመጡትና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ‘ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል፤’ ሲል ሰምተነዋልና፤” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት። ሊቀ ካህናቱም “ይህ ነገር እንዲህ ነውን?” አለው፤ እርሱም እንዲህ አለ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ! ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በመስጴጦምያ ሳለ ታየና ‘ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድርና፤’ አለው። በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው። በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባርያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ‘እንደ ባርያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ፤ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል፤’ አለ። የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች። “የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብጽ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከመከራውም ሁሉ አወጣው፤ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፤ በግብጽና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። በግብጽና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም። ያዕቆብም በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤ በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፤ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ። ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ። ያዕቆብም ወደ ግብጽ ወረደ፤ እርሱም ሞተ፤ አባቶቻችንም፤ ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው። “እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብጽ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብጽ በዙ። እርሱም ወገናችንን ተተንኩሎ ሕፃናትን በሕይወት እንዳይጠብቁ ወደ ውጭ ይጥሉ ዘንድ አድርጎ አባቶቻችንን አስጨነቀ። በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው፤ ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። ሙሴም የግብጾችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ። “ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፤ የግብጽን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፤ ሊያስታርቃቸውም ወዶ ‘ሰዎች ሆይ! እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ?’ አላቸው። ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን ‘አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ወይስ ትናንትና የግብጹን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን?’ ብሎ ገፋው። ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ። “አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቁጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም። ጌታም ‘የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ። በግብጽ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፤ ወደ ግብጽ እልክሃለሁ፤’ አለው። “‘ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቁጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው። ይህ ሰው በግብጽ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው። ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት፤’ ያላቸው ሙሴ ነው። ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤ ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብጽ ተመለሱ፤ አሮንንም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና፤’ አሉት። በዚያም ወራት ጥጃ አድረጉ፤ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው። እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ፤ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በነቢያትም መጽሐፍ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት! አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን? ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ፤’ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል። “እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ። ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት። ነገር ግን ነቢዩ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ?’ ይላል ጌታ፥ ‘ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን?’ እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም። ... “እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፤ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም።” ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቆጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና “እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤” አለ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ነፍሴን ተቀበል፤” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ! ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር። በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ። በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት። ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር። የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ። ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ርኩሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን “እኔ ታላቅ ነኝ፤” ብሎ፥ እየጠነቆለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው፤” እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቆላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና “እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ፤” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፤ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዐመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ፤” አላቸው። እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ። የጌታም መልአክ ፊልጶስን “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሥልጣን የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ ኀላፊ አንድ ኢትዮጵያ ጃንደረባ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን “ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ፤” አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና “በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው። እርሱም “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?” ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ “እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ?” አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውሃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም “እነሆ ውሃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?” አለው። ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል፤” አለው። መልሶም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ፤” አለ። ሠረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሃ ወረዱ፤ አጠመቀውም። ከውሃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና። ፊልጶስ ግን በአዛጦን ተገኘ፤ ወደ ቂሣርያም እስኪመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር። ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፤ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ “ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምፅ ሰማ። “ጌታ ሆይ! ማን ነህ?” አለው። እርሱም “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤” አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ “ጌታ ሆይ! ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?” አለው። ጌታም “ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል፤” አለው። ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ዐይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም፤ አልጠጣምም። በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀመዝሙር ነበረ፤ ጌታም በራእይ “ሐናንያ ሆይ!” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆኝ፤” አለ። ጌታም “ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል፤” አለው። ሐናንያም መልሶ “ጌታ ሆይ! በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው፤” አለ። ጌታም “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና” አለው። ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፤ እጁንም ጭኖበት “ወንድሜ ሳውል ሆይ! ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፤ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ፤” አለ። ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዐይኑ ወደቀ፤ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ መብልም በልቶ በረታ። ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና “ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን?” አሉ። ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት። ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀመዝሙር እንደሆነ ስላላመኑ ፈሩት። በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረተረከላቸው። በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ። ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት፤ ወደ ጠርሴስም ሰደዱት። በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር። ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። ጴጥሮስም “ኤንያ ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ፤” አለው። ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ። በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀመዝሙር ነበረች፤ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርሷም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት፤ መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ “ጣቢታ ሆይ! ተነሺ፤” አላት። እርሷም ዐይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርሷ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቁርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ። በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ “ጌታ ሆይ! ምንድነው?” አለ። መልአኩም አለው “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ በእንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው፤ ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ሰገነት ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤” የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና፤” አለ። ደግሞም ሁለተኛ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ በእንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፤ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤” አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ፤” አሉት። እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፤ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ፤” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‘ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው’ እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቁርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ አለኝ። ስለዚህ ያንጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።” ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ። የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፤ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው፤ ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ “እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውሃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት። ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ፤” አሉት። ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ “እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ ይህንም ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። ‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ ርኩስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና፤’ አልሁ። ሁለተኛም ‘እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ እንደገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። እነሆም፥ ያንጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ፤ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል፤’ እንዳለው ነገረን። ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱም ወረደላቸው። ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤’ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ። በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር። ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ። የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቁጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፤ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤ እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤ ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ። በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ወጣ፤ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ። በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ። ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፤ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ላኩት። በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ። በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው፤ ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው። ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና “ፈጥነህ ተነሣ፤” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም “ታጠቅና ጫማህን አግባ፤” አለው። እንዲሁም አደረገ። “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ፤” አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ፤ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ፤” አለ። ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም “አብደሻል!” አሏት። እርሷ ግን እንዲሁ እንደሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም “መልአኩ ነው፤” አሉ። ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞቹ ንገሩ፤” አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በነጋም ጊዜ “ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን?” ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ። ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፤ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፤ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና። በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ፤ እነርሱንም ተናገራቸው፤ ሕዝቡም “የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤ የሰውም አይደለም፤” ብለው ጮኹ። ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያንጊዜ የጌታ መልአክ መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ። የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር። በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ። በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ፤” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኩር ብሎ ሲመለከተው “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፤ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ! ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ፤” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ! ስሙ። የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብጽ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። በበረሃም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፤ ሲመሰክርለትም ‘እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤’ አለ። ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ ‘እኔ ማን እንደሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤’ ይል ነበር።” እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ! ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ “የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ፤” ብሏል። ደግሞ በሌላ ስፍራ “ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም፤” ይላልና። ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “እናንተ የምትንቁ፥ ተመልከቱ፤ ተደነቁም፤ ጥፉም፤ ማንም ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና፤” ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘለዓለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ፤” ብሎ አዞናልና፤ አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፤ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው። በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኩሌቶቹ ከአይሁድ እኩሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር። በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኩር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ድምፅ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም፤” አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል፤” አሉ። በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ “ሄርሜን” አሉት። በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፤ እንዲህም አሉ “እናንተ ሰዎች! ይህን ስለምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፤ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ፤ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ። በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፤” እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ። በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው። በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፤ በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፤ ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ። ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ። አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና “እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም፤” ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር። በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው። ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ። ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው “ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል፤” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ። ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው “ወንድሞች ሆይ! አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለምን ትፈታተናላችሁ? ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።” ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፤ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር። እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ “ወንድሞች ሆይ! ስሙኝ። እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤ የፈረሰውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ። ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤ እንደገናም እሠራዋለሁ፤ የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን እንዲፈልጉ፥ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። ከጥንት ጀምሮ ሥራቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።’ ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ ነገር ግን ከጣዖት ርኩሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቆርጣለሁ። ሙሴስ ከቀደሙት ትውልድ ጀምሮ በሰንበት በሰንበት በምኵራቦቹ ሲያነቡ በየከተማው እርሱን የሚሰብኩ አሉት።” ያንጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ ፈቀዱ፤ እነርሱም በወንድሞች መካከል ዋናዎች ሆነው በርስያን የተባለው ይሁዳና ሲላስ ነበሩ። እንዲህም ጽፈው በእነርሱ እጅ ላኩ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ። ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ‘ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል፤’ ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን። ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።” እነርሱም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ሕዝቡንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። ባነበቡትም ጊዜ ከምክሩ የተነሣ ደስ አላቸው። ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው። አያሌ ቀንም ከተቀመጡ በኋላ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ሐዋርያት ሄዱ። ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ። ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር። ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን “ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፤ እንዴት እንዳሉም እንወቅ፤” አለው። በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፤ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፤ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ወጣ፤ አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር። ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀመዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ። ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት። ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፤ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና። በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቆረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር፤ በቍጥር ም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር። በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፤ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን፤” እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር። ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፤ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና። ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርሷም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር። በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ ያሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። እርሷም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ “በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ፤” ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን። ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርሷ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባርያዎች ናቸው፤” ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን “ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎም አቅርበው “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤” አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፤ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፤ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤” ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፤ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶች ሆይ! እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ኣላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ፤” አሉት። ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ “እነዚያን ሰዎች ፍታቸው፤” ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ። የወኅኒውም ጠባቂ “ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ፤” ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ግን “እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም፤ ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን፤” አላቸው። ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ፤ የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ። መጥተውም ማለዱአቸው፤ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው። ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፤ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ። በአንፊጶሊስና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፤ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ “ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው፤” ይል ነበር። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፤ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው “ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ ‘ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ፤’ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ፤” ብለው ጮኹ። ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፤ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፤ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን?” ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ። በዚያን ጊዜም ወንድሞች ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፤ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ። ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር። ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል?” አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው “አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል፤” አሉ። ይዘውም “ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና፤ እንግዲህ ይህ ነገር ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እንፈቅዳለን፤” ብለው አርዮስፋጎስ ወደ ተባለው ስፍራ ወሰዱት። የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና። ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ “የአቴና ሰዎች ሆይ! እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና፥ አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ ‘እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና፤’ ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን፤ እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀንቀጥሮአልና፤ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ እኩሌቶቹ ግን “ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን፤” አሉት። እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ። አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ። በወገኑም የጳንጦስ ሰው የሚሆን አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ መጥቶ ነበር፤ አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ ነበርና፤ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ ሥራቸውም አንድ ስለ ነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ፤ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበረና። በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፤ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር። ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር። ነገር ግን በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፥ ልብሱን እያራገፈ “ደማችሁ በራሳችሁ ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ፤” አላቸው። ከዚያም ወጥቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ገባ፤ ቤቱም በምኵራብ አጠገብ ነበረ። የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ። ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፤ ነገር ግን ተናገር፤ ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና፤” አለው። በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ። ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው “ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል፤” አሉ። ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን “አይሁድ ሆይ! ዐመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤ ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና፤” አላቸው። ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው። የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኵራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር። ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞችንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክንክራኦስ ተላጨ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ወደ ኤፌሶንም በደረሱ ጊዜ እነዚያን ከዚያ ተዋቸው፤ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር። እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲቀመጥላቸው ሲለምኑት እሺ አላለም፤ ነገር ግን ሲሰናበታቸው “የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ፤” አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ። ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ። ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፤ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ። በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ። እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፤ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር። እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜም ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት። እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፤ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና። አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም፤” አሉት። “እንደዚህ ከሆነስ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው። እነርሱም “በዮሐንስ ጥምቀት፤” አሉት። ጳውሎስም “ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሓ ጥምቀት አጠመቀ፤” አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በልሳኖችም ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ ዐሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፤ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮችይወስዱ ነበር፤ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን፤” እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ?” አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው፤ ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፤ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፤ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር። ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ “ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል፤” ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው “ሰዎች ሆይ! ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደሆነ ታውቃላችሁ። ይህም ጳውሎስ ‘በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም፤’ ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል፤ ሰምታችሁማል። ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፤ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፤ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ቁጣ ሞላባቸው “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉም ጮኹ። ከተማውም በሙሉው ተደበላለቀ፤ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። አይሁዳዊ ግን እንደሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ! የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመፋረጃ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። ስለ ሌላ ነገር እንደሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። ዛሬ ስለተደረገው ‘ሁከት ነው፤’ ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፤ ምክንያት የለምና።” ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው። ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፤ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ። ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ። በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሤራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ። የሸኙትም የቤርያው ሶጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤ እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፤ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ። ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፤ አቅፎም “ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ፤” አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪ ነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት፤ እጅግም ተጽናኑ። እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና። በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤ በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፤ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን። ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና፤ ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና። ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሤራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ በአደባባይም ሆነ በየቤታችሁ ሳስተምራችሁ የሚጠቅማችሁን ሁሉ ነገርኳችሁ እንጂ፥ ምንም ነገር አላስቀረሁባችሁም። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አስጠነቀቅኋቸው። አሁንም እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ‘እስራትና መከራ ይቆይሃል፤’ ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። አሁንም እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፤ ምንም አላስቀረሁባችሁም። በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ኤጲስ ቆጶሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። እኔ ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ እንደ ተኲላ ጨካኞች የሆኑ ሰዎች እንደሚገቡባችሁ ዐውቃለሁ። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው ጠማማ ትምህርት በማስተማር ብዙ አማኞችን ወደ እነርሱ ይስባሉ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ። አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ። ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው፤’ እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።” ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ። ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤ ይልቁንም “ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም፤” ስላላቸው ነገር እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት። ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት፤ ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፤ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ ተመርተው ነገሩት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንምተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፤ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፤ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፤ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ “እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ‘ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል፤ በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል፤’ ይላል፤” አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ “እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም፤” አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ “የጌታ ፈቃድ ይሁን፤” ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፤ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀመዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ አሉትም “ወንድም ሆይ! በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል።” በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ። ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን፤ ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል፤” ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፤ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ “ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች፤” የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያንጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ እኩሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ “አስወግደው!” እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን “አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን?” አለው። እርሱም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብጽ ሰው አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስ ግን “እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤” አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ። “እናንተ ወንድሞች አባቶችም! አሁን ለእናንተ ንገሬን ስገልጥ ስሙኝ።” በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ። ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቄ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። እኔም መልሼ ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ፤’ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፤ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም። ‘ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ?’ አልሁት። ጌታም ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል፤’ አለኝ። ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። “በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ! እይ፤’ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ። እርሱም አለኝ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል፤ ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኃጢአትህም ታጠብ።’ “ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፤ እርሱም ‘ፍጠን፤ ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፤ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና፤’ ሲለኝ አየሁት። እኔም ‘ጌታ ሆይ! በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤ የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር፤’ አልሁ። እርሱም ‘ሂድ፤ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና፤’ አለኝ።” እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፥ “እነደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፤ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና፤” አሉ። ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥ የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፤ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ “እየገረፋችሁ መርምሩት፤” አላቸው። በጠፈርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ “የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ “ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ፤” ብሎ ነገረው። የሻለቃውም ቀርቦ “አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ፤” አለው፤ እርሱም “አዎን” አለ። የሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት፤” አለ። ጳውሎስም “እኔ ግን በእርሷ ተወለድሁ፤” አለ። ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፤ አሳስሮት ነበርና። በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፤ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው። ጳውሎስም ሸንጎውን ትኩር ብሎ ተመልክቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ፤” አለ። ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ! እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው። በአጠገቡ የቆሙትም “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን?” አሉት። ጳውሎስም “ወንድሞች ሆይ! ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር፤’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አላቸው። ጳውሎስ ግን እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል፤” ብሎ በሸንጎው ጮኸ። ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ፤ ሸንጎውም ተለያየ። ሰዱቃውያን “ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም፤” የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። ታላቅ ጩኸትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው “በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን?” ብለው ተከራከሩ። ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ። በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ “ጳውሎስ ሆይ! በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ፤” አለው። በነጋም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ። ይህንም ሤራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤ እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው “ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል። እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን፤” አሉአቸው። የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ “ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፤ የሚያወራለት ነገር አለውና፤” አለው። እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና “ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ፤” አለው። የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ “የምታወራልኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው፤ የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ፤” አለው። የሻለቃውም “ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ፤” ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው። ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ “ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ፤” አላቸው። ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዢው ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው። እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፤ ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዢው ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፤ ሮማዊ እንደሆነ አውቄ ነበርና። የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤ በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም። በዚህም ሰው አይሁድ ሤራ እንደሚያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ አንተ ላኩት፤ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ እንዳይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤ በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ። እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዢው በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት። ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ “ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ፤” አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ። ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዢው አመለከቱት። በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከሰው ዘንድ ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፤ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ።” አይሁድም ደግሞ “ይህ ነገር እንዲሁ ነው፤” እያሉ ተስማሙ። ገዢውም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። ወይም በመካከላቸው ቆሜ ‘ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል፤’ ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዐመፃ ያገኙ እንደሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ።” ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና “የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ፤” ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው። የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ “አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ፤” ብሎ መለሰለት። ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው። ፊስጦስም ወደ አውራጃው ገብቶ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። የካህናቱ አለቆችና የአይሁድም ታላላቆች በጳውሎስ ላይ አመለከቱ፤ ጳውሎስንም ሲቃወም እንዲያደላላቸው እየለመኑ፥ በመንገድ ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ አስበው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው ማለዱት። ፊስጦስ ግን ጳውሎስ በቂሳርያ እንዲጠበቅ እርሱም ራሱ ወደዚያ ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ እንዳለው መለሰላቸው፤ “እንግዲህ በዚህ ሰው ክፋት ቢሆን ከእናንተ ዘንድ ያሉት ባለ ሥልጣኖች ከእኔ ጋር ወርደው ይክሰሱት፤” አላቸው። በእነርሱም ዘንድ ከስምንት ወይም ከዐሥር የማይበልጥ ቀን ተቀምጦ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በነገውም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ። በቀረበም ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱት አይሁድ ከበውት ቆሙ፤ ይረቱበትም ዘንድ የማይችሉትን ብዙና ከባድ ክስ አነሱበት፤ ጳውሎስም ሲምዋገት “የአይሁድን ሕግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሣርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልኩም፤” አለ። ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን?” ብሎ መለሰለት። ጳውሎስ ግን “እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሣር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልኩም። እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሣር ይግባኝ ብዬአለሁ፤” አለ። በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሣር ትሄዳለህ፤” ብሎ መለሰለት። ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ። በዚያውም ብዙ ቀን ስለ ተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ “ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤ በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ። እኔም ‘ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም፤’ ብዬ መለስሁላቸው። ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ። ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤ ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ ‘ሕያው ነው፤’ ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር። እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን?’ አልሁት። ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቆርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ።” አግሪጳም ፊስጦስን “ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር፤” አለው። እርሱም “ነገ ትሰማዋለህ፤” አለው። በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት። ፊስጦስም አለ “አግሪጳ ንጉሥ ሆይ! እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ። እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፤ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቆረጥሁ። ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ!በፊትህ አመጣሁት፤ እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።” አግሪጳም ጳውሎስን “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። “ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ ሊመሰክሩ ይወዱ እንደሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል ዐሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደሆነ ስለምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቆጠራል? “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፤ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቆጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። “ስለዚህም ነገር ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ ንጉሥ ሆይ! በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤’ የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም አለኝ ‘አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዐይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።’ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሓ ይገቡ ዘንድና ለንስሓ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ተናገርሁ። ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ሞከሩ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ “ጳውሎስ ሆይ! አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል፤” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ! የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን “በጥቂት ጊዜ ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ፤” አለው። ጳውሎስም “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራት በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ፤” አለው። ንጉሡም፥ አገረ ገዢውም፥ በርኒቄና ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፤ ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ፤” ብለው ተነጋገሩ። አግሪጳም ፈስጦስን “ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር፤” አለው። ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቆረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የፆም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ “እናንተ ሰዎች ሆይ! ይህ ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጉዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም፤” ብሎ መከራቸው። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግታት በጭንቅ ቻልን፤ ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፤ በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቆረጠ። ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያንጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ “እናንተ ሰዎች ሆይ! ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጉዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። አሁንም አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፤ እርሱም ጳውሎስ ሆይ! አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል፤” አለኝ። ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ! አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ። ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንድንወድቅ ያስፈልገናል። በዐሥራ አራተኛውም ሌሊት በአድርያ ባሕር ወዲህና ወዲያ ስንነዳ፥ መርከበኞች በእኩለ ሌሊት ወደ አንድ ምድር የቀረቡ መሰላቸው። መለኪያ ገመድም ቢጥሉ ሃያ በሰው ቁመት አገኙ ጥቂትም ቆይተው ሁለተኛ ቢጥሉ ዐሥራ አምስት በሰው ቁመት አገኙ፤ ድንጋያማም ወደ ሆነ ስፍራ እንዳይወድቁ ፈርተው፥ ከመርከቡ በስተ ኋላ አራት መልሕቅ አወረዱ፤ ቀንም እንዲሆን ተመኙ። መርከበኞቹም ከመርከቡ ይሸሹ ዘንድ ፈልገው ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ መጣል እንዳላቸው አመካኝተው ታንኳይቱን ወደ ባሕር ባወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮች “እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም፤” አላቸው። ያንጊዜ ወታደሮቹ የታንኳይቱን ገመድ ቆርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት። ቀንም ሲነጋ ጳውሎስ ምግብ ይበሉ ዘንድ ሁሉን ይለምን ነበር፤ እንዲህም አላቸው “እየጠበቃችሁ ምንም ሳትቀበሉ ጦማችሁን ከሰነበታችሁ ዛሬ ዐሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው። ስለዚህ ምግብ ትበሉ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ይህ ለደኅንነታችሁ ይሆናልና፤ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጉር እንኳ አትጠፋምና።” ይህንም ብሎ እንጀራን ይዞ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቆርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። ሁለም ተጽናንተው ራሳቸው ደግሞ ምግብ ተቀበሉ። በመርከቡም ያለን ሁላችን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበርን። በልተውም በጠገቡ ጊዜ ስንዴውን ወደ ባሕር እየጣሉ መርከቡን አቃለሉት። በነጋም ጊዜ ምድሩን አላወቁትም፤ ነገር ግን የአሸዋ ዳር ያለውን የባሕር ሰርጥ ተመለከቱ፤ ቢቻላቸውም መርከቡን ወደዚያ ይገፉ ዘንድ ቆረጡ። መልሕቆቹንም ፈትተው በባሕር ተዉአቸው፤ ያን ጊዜም የመቅዘፊያውን ማሠሪያ ፈቱት፤ ታናሹንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ዳር አቅንተው ይሄዱ ዘንድ ጀመሩ። ነገር ግን ሁለት ባሕር በተገናኙበት ስፍራ ወድቀው መርከቡን በዲብ ላይ ነዱ፤ በስተ ፊቱም ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፤ በስተ ኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ ይሰበር ነበር። ወታደሮቹም ከእስረኞች አንድ ስንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ይገድሉአቸው ዘንድ ተማከሩ። የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ፤ ዋና የሚያውቁትም ከመርከብ ራሳቸውን እየወረወሩ አስቀድመው ወደ ምድር ይወጡ ዘንድ፥ የቀሩትም እኩሌቶቹ በሳንቃዎች ላይ እኩሌቶቹም በመርከቡ ስባሪ ይወጡ ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ሁሉ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ። በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባለ አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም፤” አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት፤ አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ “ይህስ አምላክ ነው፤” ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፤ እርሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፤ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን። ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፤ በእርሱም የዲዮስቆሮስ ዓላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው “ወንድሞች ሆይ! እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።” እነርሱም “እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፤ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም፤ ወይም አልተናገረብህም። ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን፤” አሉት። ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። እኩሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አላመኑም፤ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ፦ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፥ መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤ በላቸው። ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ። ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽነትና በልበ ሙሉነት ያስተምር ነበር። የክርስቶስ ኢየሱስ ባርያ ጳውሎስ፥ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፥ ይህም ወንጌል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት የሰጠው ተስፋ ነው፤ ወንጌሉም ስለ ልጁ፥ በሥጋ ከዳዊት ዘር እንደመጣ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስና መንፈስ ከሙታን በመነሣት በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገለጡ ነው፤ ስለ ስሙ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ለእምነት መታዘዝን ለማምጣት ጸጋና ሐዋርያነትን በተቀበልንበት በእርሱ በኩል፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ በተጠራችሁ በእናንተም መካከል፥ በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁ፥ በሮሜ ላላችሁ ሁሉ፥ ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ስለ ሁላችሁም በመጀመሪያ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። ያለማቋረጥ እንዴት እንደማስባችሁ የልጁን ወንጌል በመስበክ በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ ምናልባት አሁን በመጨረሻ፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ ለመምጣት ሁልጊዜ በጸሎቴ እጠይቃለሁ። የሚያጸናችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁ፤ ይህም እርስ በእርሳችን በእናንተና በእኔ ዘንድ ባለች እምነት፥ አብረን እንድንጽናና ነው። ወንድሞች ሆይ! በሌሎቹ ሕዝቦች እንዳገኘሁት በእናንተም ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳቀድሁ እስከ አሁን ግን እንደ ተከለከልሁ እንድታውቁ እወዳለሁ። ለግሪኮችና ግሪኮች ላልሆኑት፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉትም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህ በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ እጓጓለሁ። በወንጌል አላፍርምና፤ በመጀመሪያ ለአይሁድ እንዲሁም ለግሪካውያን፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። በክፋታቸው እውነትን አፍነው በሚይዙ ሰዎች፥ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ ስለ እግዚአብሔር መታወቅ የሚገባው በእነርሱ መካከል ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም ለእነርሱ እግዚአብሔር ግልፅ አድርጎላቸዋል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታዩት ነገሮች፥ ይኸውም ዘላለማዊው ኃይሉና መለኮታዊነቱ ታውቆ፥ ግልፅም ሆኖ ስለሚታይ ሰበብ የላቸውም። ምክንያቱም እግዚአብሔርን እያወቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን አላከበሩትም ወይም አላመሰገኑትም፤ ነገር ግን ምክንያታቸው ዋጋ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ሞኞች ሆኑ፤ የማይጠፋውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋው በሰው፥ በወፎች፥ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሳት መልክ ምስል ለወጡ። ስለዚህ እግዚአብሔር እርስ በእርሳቸው ሥጋቸውን እንዲያዋርዱ፥ በልባቸው ፍትወት ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን አመለኩ አገለገሉትም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተባረከ ነው፤ አሜን። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ለሚያዋርድ ፍትወት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሮአዊውን ግንኙነት ተፈጥሮአዊ ባልሆነ ግንኙነት ለወጡ፤ እንዲሁም ደግሞ ወንዶች ተፈጥሮአዊ የሆነውን ከሴት ጋር መገናኘት ትተው እርስ በእርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በራሳቸው ላይ ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ እግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዐመፃ፥ በግፍ፥ በስስት፥ በክፋት፥ በቅናት፥ ነፍስ በመግደል፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በተንኮል የተሞሉ፥ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚዳፈሩ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚያውጠነጥኑ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ የማይታመኑ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት የሌላቸው ናቸው፤ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሞት ይገባቸዋል” የሚለውን ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፥ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ። ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሆይ! የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ ፈራጅ የሆንከው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። እንደዚህ በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን። አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ ላይ የምትፈርድ ያንንም የምታደርግ ሰው ሆይ! ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የቸርነቱን፥ የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ ሊመራህ እንደሆነ አታውቅምን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ ሰው ሁሉ ላይ፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፤ ነገር ግን መልካምን ለሚሠራ ሁሉ አስቀድሞ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ምስጋና፥ ክብርና ሰላም ይሆንለታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ማዳላት የለምና። ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚፈፅሙት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙት አይጸድቁምና። ሕግ የሌላቸው አሕዛብ፥ ሕግ የሚያዘውን ነገር በተፈጥሮአቸው ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸውም ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፥ ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ እርስ በእርሳቸው ሐሳባቸው ሲካሰስ ወይም ሲከላከል፥ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ። ይህም እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር የሰዎችን የተሰወሩ ነገሮች በሚፈርድበት ቀን ይሆናል። አንተ ግን አይሁዳዊ ነኝ ካልህ በሕግም ከተደገፍክ በእግዚአብሔርም ከተመካህ፥ ፈቃዱንም ካወቅህ፥ ሕግም ስለተማርህ የሚሻለውን ከወሰድህ፥ ለዓይነ ስውሮች መሪ፥ በጨለማ ላሉትም ብርሃን እንደሆንህ በራስህ የምትተማመን ከሆነ፥ የሞኞች አስተማሪ፥ የሕፃናት መምህር ነኝ ካልህ፥ በሕግም የእውቀትና የእውነት አርአያ ካለህ፥ ስለዚህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ እየሰበክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖቶችን የምትጠላ ቤተ መቅደሶችን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በሕዝቦች መካከል ይሰደባልና” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ሕግን የምትፈጽም ከሆነ መገረዝ ይጠቅማል፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ሆኖአል። ስለዚህ ያልተገረዘው የሕግን ሥርዓት ከጠበቀ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቆጠርለትምን? ከፍጥረቱ ያልተገረዘው፥ ሕግንም የሚጠብቀው፥ የሕግ መጽሐፍና መገረዝ እያለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ላይ ይፈርድብሃል። በስም አይሁዳዊ ሆኖ የሚታይ አይሁዳዊ አይደለምና፤ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ነገር ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሆነ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በፊደል አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም። እንግዲህ አይሁዳዊው ጥቅሙ ምንድነው? ወይም የመገረዝ ትርፉ ምንድነው? በማንኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው። አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጣቸው። አንዳንዶች ባያምኑስ? የእነሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ የሌለው ያደርገዋልን? በጭራሽ! “በቃልህ እውነተኛ እንድትሆን፥ ለፍርድ በቀረብክም ጊዜ አሸናፊ እንድትሆን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን። ነገር ግን ዐመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያጎላ ከሆነ ምን እንላለን? እግዚአብሔር በቁጣ ቢቀጣን ትክክል አይደለም ሊባል ነውን? እንደ ሰው እላለሁ። በጭራሽ! ያለበለዚያ እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት ይፈርዳል? ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነተኛነት በእኔ ውሸት ለክብሩ ከሞላ፥ ለምን እኔ እስካሁን እንደ ኃጢአተኛ ይፈረድብኛል? “መልካም ነገር እንዲመጣ ለምን ክፉ አናደርግም?” ይላሉ ብለው እንደሚያሙን አይደለም፤ የሚፈረድባቸው ፍርድ ትክክለኛ ነው። ስለዚህ ምን ይሁን? እኛ እንበልጣለንን? በጭራሽ! አይሁዳውያንንም ግሪካውያንንም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “ጻድቅ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም፤ የሚያስተውል የለም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ የለም፤ ሁሉም ከመንገድ ወጥተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ መልካም የሚሠራ አንድም የለም፤ አንድ ስንኳ የለም።” “ጉሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸውም አታለዋል፤” “የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤” “አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቷል፤” “እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፤ የሰላምንም መንገድ አያውቁም።” “በዐይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።” ነገር ግን አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሥር እንዲሆን፤ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሚናገር እናውቃለን፤ ምክንያቱም በሕግ ሥራ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት አይጸድቅም፤ በሕግ አማካኝነት ኃጢአት ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፤ ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ለሚያምኑ ሁሉ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት የሚገኝ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲሁ በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ ያቀረበው ነው፤ ይህም በእግዚአብሔር ትዕግስት በፊት የተደረገውን ኃጢአት በመተው ጽድቁን እንዲያሳይ ነው፤ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን እንዲያሳይ ነው። ስለዚህ ትምክህት ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በእምነት ሕግ ነው። ሰው ሕግ ከሚያዘው ሥራ ውጭ በእምነት እንደሚጸድቅ እናምናለንና። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን የአሕዛብም አምላክ ነው፤ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አንድ አምላክ አለና። ስለዚህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? በጭራሽ! ነገር ግን ሕግን እናጸናለን። እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፤ በእግዚአብሔር ፊት ግን መመካት አይችልም። መጽሐፉስ ምን አለና? “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።” እንግዲህ ለሚሠራ ሰው፥ ደመወዝ እንደ ክፍያ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፤ ለማይሠራ፥ ነገር ግን ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ ለሚያምን፥ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል። ደግሞም ዳዊት እንኳ፥ እግዚአብሔር ያለ ሥራ፥ ጽድቅን ስለሚቆጥርለት ሰው፥ ስለ መባረኩ ሲናገር፤ “መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፥ ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው የተባረኩ ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው የተባረከ ነው።” እንግዲህ ይህ መባረክ በመገረዝ መጣን? ወይስ ደግሞ ባለመገረዝ? አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። እንዴት ታዲያ ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ሳይገረዝ ነበር እንጂ፤ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። ሳይገረዝም በእምነቱ ባገኘው የጽድቅ ማኅተም፥ መገረዝን እንደ ምልክት ተቀበለ፤ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ፥ ለእነርሱም ጽድቅ ሆኖ እንዲቆጠርላቸው አባት ነውና፤ ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ጭምር ነው። ዓለምን እንዲወርስ ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም። ከሕግ የሆኑትስ ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኖአል፤ የተስፋውም ቃል ተሽሮአል፤ ሕጉ መቅሠፍትን ያስከትላልና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም። ስለዚህ በእምነት የሆነው፥ ተስፋው በእምነት እንዲያርፍና ለዘሩ ሁሉ እንዲሆን ነው፥ ይህም ሕግ ፈፃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የአብርሃምን እምነት የሚጋሩትንም ጭምር ነው፥ እርሱ የሁላችንም አባት ነውና፥ “የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ የሞተውን ሕያው በሚያደርግ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት አምላክ ፊት ነው። “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተነገረው፥ ተስፋ በሌለበት የብዙ ሕዝቦች አባት እንደሚሆን በተስፋ አመነ። መቶ ዓመት ሆኖት ሳለ ምውት የሆነውን የራሱን አካልና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆን አስቦ በእምነት አልደከመም፤ ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ በእምነት በረታ እንጂ፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ አልተጠራጠረም። የሰጠውንም ተስፋ እንደሚፈጽም ጽኑ እምነት ነበረው። በዚህም ምክንያት “ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።” ነገር ግን “ተቆጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው በእርሱ ምክንያት ብቻ አይደለም፤ ለእኛም ጭምር ነው፤ ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛም እንዲቆጠርልን ነው። ስለ ኃጢአታችን ለሞት ተላልፎ ተሰጠ፤ ለጽድቃችንም ተነሣ። እንግዲህ በእምነት ስለጸደቅን፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን፤ በእርሱም በኩል ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ በእግዚአብሔርም ክብር በተስፋ እንመካለን። በዚህ ብቻ ሳይሆን፥ መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ ስለምናውቅ በመከራም ጭምር እንመካለን፤ ጽናትም የተፈተነ ባሕርይን ያስገኝልናል፥ የተፈተነ ባሕርይም ተስፋን፤ ተስፋም ቅር አያሰኘንም፤ ምክንያቱም በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ነው። ገና ደካሞች ሳለን፥ በትክክለኛው ጊዜ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቷልና። ስለ ጻድቅ ሰው ሲል የሚሞት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ስለ መልካም ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን ይበልጡንም በእርሱ በኩል ከቁጣ እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ፥ ሞትም በኃጢአት በኩል እንደመጣ፥ እንዲሁም ሁሉም ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበረና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም። ነገር ግን ለሚመጣው ምሳሌ እንደነበረው እንደ አዳም ሕግን ባልተላለፉት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ከሞቱ፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ያለው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት ይበዛ። ስጦታውም አንድ ሰው ኃጢአትን በማድረጉ እንዳመጣው ውጤት አይደለም፤ በአንድ በኩል፥ ፍርዱ የአንድን ሰው በደል ተከትሎ ኩነኔን አመጣ፤ በሌላ በኩል ግን ስጦታው ብዙ በደልን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው በደል ምክንያት በዚህ ሰው በኩል ሞት ከነገሠ፥ ይልቁን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ስጦታ የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኩነኔ ለሰው ሁሉ እንደመጣ፥ እንዲሁም በአንድ ሰው የጽድቅ ሥራ ምክንያት ሕይወትን ለማጽደቅ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በደል እንዲበዛ ሕግ ገባ፤ ነገር ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ጸጋ ይበልጥ በዛ፤ ይህም የሆነው፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ሕይወት፥ በጽድቅ በኩል እንዲነግሥ ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት በመሥራት እንቀጥል? በጭራሽ! ለኃጢአት የሞትን እስካሁን እንዴት በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ ለመሆን እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ስለዚህ በአብ ክብር ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንኖር፥ በጥምቀት አማካኝነት በሞት ከእርሱ ጋር ተቀብረናል። የእርሱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር አንድ ከሆንን እንዲሁም ደግሞ በትንሣኤው ከእርሱ ጋር አንድ እንሆናለን፤ ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት ባርያዎች እንዳንሆን የኃጢአት ሰውነት እንዲሻር አሮጌው ማንነታችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን። የሞተስ ከኃጢአት ነጻ ወጥቶአልና። ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ እንደምንኖር እናምናለን። ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷል፥ ዳግመኛም እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ እርሱን አይገዛውም። በእርሱ ሞቷልና፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢአት ሞቷል፤ መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። እንዲሁም ደግሞ እናንተ በአንድ በኩል በእርግጥ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ በሌላ በኩል ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። ስለዚህ፥ ለምኞቱ ታዛዥ ሊያደርጋችሁ በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ኃጢአት አይንገሥ። የሰውነታችሁን ክፍሎች የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ ኃጢአት አይገዛችሁም። እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋ በታች ስለ ሆንን ኃጢአት መሥራት አለብንን? በጭራሽ! እራሳችሁን የመታዘዝ ባርያዎች አድርጋችሁ ለምታቀርቡለት፥ ለምትታዘዙት ለእርሱ ሞትን ለሚያመጣው ለኃጢአት ወይም ጽድቅን ለሚያመጣው ለመታዘዝ ባርያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? አስቀድማችሁ የኃጢአት ባርያዎች የነበራችሁ፥ ነገር ግን ለተሰጣችሁለት የትምህርት ዓይነት ከልባችሁ በመታዘዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ከኃጢአትም ነፃ ወጥታችሁ ለጽድቅ ባርያዎች ሆናችኋል። ከሥጋችሁ ደካማነት የተነሣ እንደ ሰው አነጋገር እናገራለሁ። የሰውነታችሁን ክፍሎች ሕገ ወጥነትን ለሚያመጣ ለርኩሰትና ለሕገ ወጥነት ባርያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ ስለዚህ አሁን የሰውነታችሁን ክፍሎች ቅድስና ለሚያመጣ ለጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ። የኃጢአት ባርያዎች በነበራችሁበት ጊዜ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁ። ታዲያ አሁን ከምታፍሩበት ነገር ሌላ ያንጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነውና። አሁን ግን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ባርያዎች ሆናችኋል፥ ፍሬያችሁም ቅድስና ነው፤ መጨረሻውም የዘለዓለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፥ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘለዓለም ሕይወት ነው። ወንድሞች ሆይ! ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና፤ ሕግ ሰውን የሚገዛው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን አታውቁምን? ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ በሕግ ታስራለችና፤ ባሏ ቢሞት ግን ከባል ሕግ ተፈትታለች። ስለዚህ ባሏ በሕይወት እያለ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ ትባላለች። ባሏ ቢሞት ግን ከሕጉ ነፃ ናት፥ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ አይደለችም። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ እንድትሆኑና ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ ነው። በሥጋ እያለን የኃጢአት ሥቃይ በሕግ በኩል ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በሰውነታችን ክፍሎች ይሠራ ነበር። አሁን ግን ለእርሱ ታስረን ከነበርንበት በመሞት ከሕግ ተፈትተናል ፤ ስለዚህም በአሮጌው በፊደል ሳይሆን በአዲስ በመንፈስ ኑሮ እናገለግላለን። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? በጭራሽ! ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ ኃጢአትን አላውቅም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ ምኞትን አላውቅም ነበር። ኃጢአት ግን በትእዛዝ አማካኝነት አጋጣሚን በመውሰድ ሁሉንም ዓይነት ምኞትን አስነሣ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ የሞተ ነውና። እኔም ድሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ። እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠው ትእዛዝ ለሞት መሆኑን ተገነዘብሁ፤ ኃጢአት በትእዛዝ በኩል አጋጣሚ አግኝቶ አታልሎኛልና፥ በእርሱም ገደለኝ። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፥ ትክክለኛና መልካም ነው። እንግዲህ መልካም የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? በጭራሽ! ነገር ግን ኃጢአት ኃጢአትነቱ እንዲታይ፥ መልካም በሆነው ነገር ሞትን ይሠራብኝ ነበር። ይኸውም ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት ያለ ልክ ኃጢአት እንዲሆን ነው። ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። ምን እየሠራሁ እንደሆነ አላውቅም፤ የምፈልገውን ነገር አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ነገር አደርጋለሁና። እንግዲህ የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ ሕግ ትክክል ነው እላለሁ። እንግዲህ አሁን ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን፥ በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። በእኔ ማለትም በሥጋዬ ምንም መልካም ነገር እንደማይኖር አውቃለሁና፤ መልካምን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም ነገር ግን ልፈፅመው አልችልም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፥ ነገር ግን ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁና። የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ፥ ያን የማደርገው እኔ ሳልሆን በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። ስለዚህ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፋት ወደ እኔ ይቀርባል፤ ይኸውም ሕግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ክፍሎች ባለ በኃጢአት ሕግ ምርኮኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባርያ ስሆን፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባርያ ነኝ። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶኛልና። ሕግ ከሥጋ ድካም የተነሣ ማድረግ ያልቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌና ስለ ኃጢአት ልኮ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ፥ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም አይችልም፥ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። ነገር ግን ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፥ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ፥ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ አማካይነት፥ ለሟች አካላቶቻችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ባለዕዳ ነን፤ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም፥ እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና የሰውነትን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ፥ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደገና የፍርሃት ባርያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፥ ነገር ግን “አባ! አባት!” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋል። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈሱ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ከእርሱ ጋር የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ከእርሱ ጋር መከራ ብንቀበል የእግዚአብሔር ወራሾችና ከክርስቶስም ጋር አብረን ወራሾች ነን። የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ወደ ፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው እቆጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ስለ እኛም በእርግጥ የሚያማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? መከራ ወይስ ሥቃይ፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሃብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ አደጋ፥ ወይስ ሰይፍ? ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህንን ተረድቼአለሁ፤ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ገዢዎችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ጥልቀትም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም። በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፥ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፥ ታላቅ ኃዘን የማያቋርጥም ሥቃይ በልቤ አለ። ስለ ሥጋ ዘመዶቼና ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ ከክርስቶስ ተለይቼ የተረገምሁ እንድሆን እመኝ ነበር። እነርሱም እስራኤላውያን ናቸው፤ ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግን መቀበል፥ የቤተ መቅደስ አገልግሎት፥ የተስፋ ቃላትም የእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ከእነርሱም ዘር ክርስቶስ በሥጋ መጣ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ተሽሮአል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤል አይደለምና፥ የአብርሃም ዘር ስለ ሆኑ ሁሉም የእርሱ ልጆች ናቸው ማለት አይደለም፤ ነገር ግን “ዘርህ በይስሐቅ ይጠራልሃል፤” ተባለ። ይህም የሥጋ ልጆች የሆኑት የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የተስፋው ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ ማለት ነው። ይህም የተስፋው ቃል “በዚህ ጊዜ እመጣለሁ ሳራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤” የሚል ነውና። ይህ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንድ ሰው ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ፥ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ መልካም ወይም ክፉ ሳያደርጉ፥ የእግዚአብሔር የምርጫው ዓላማ እንዲጸና፥ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው ስለሆነ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል፤” ተብሎ ተነግሮአት ነበር። “ያዕቆብን ወደድሁ፥ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላልን? በጭራሽ! ሙሴን “የምምረውን እምረዋለሁ፥ ለምራራለትም እራራለታለሁ” ብሎታልና። ስለዚህ ይህ ለፈለገ ወይም ለሮጠ አይደለም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። መጽሐፍ ፈርዖንን “ኃይሌ በአንተ እንዲታይ፥ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር፥ ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና። እንግዲህ የፈለገውን ይምረዋል የፈለገውንም እልከኛ ያደርገዋል። እንግዲህ “ታዲያ ለምን እስከ አሁን ስህተት ይፈልጋል? ፈቃዱን ሊቃወም ማን ይችላል?” ብለህ ትጠይቀኝ ይሆናል። ነገር ግን፥ ሰው ሆይ! ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? የተሠራ ነገር የሠራውን “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋልን? ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንድ ዓይነት ጭቃ አንዱን ዕቃ ለክብር፥ አንዱን ደግሞ ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ መብት የለውምን? ነገር ግን እግዚአብሔር ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉን ለማሳወቅ ፈልጎ፥ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎችን በብዙ ትዕግሥት ተቋቁሞ ቢሆንስ? ይህም አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለጠግነት እንዲገልጥ ቢሆንስ? ከእነርሱም ውስጥ ከአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ደግሞ እኛን ጠራን። በሆሴዕ ደግሞ እንዲህ እንደሚል፤ “ሕዝቤ ያልሆነውን ‘ሕዝቤ’ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደችው’ ብዬ እጠራለሁ፤ ደግሞም፥ ‘እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገረላቸው ስፍራ፥ በዚያ ‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።” ይላል። ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ይጮኻል፦ “የእስራኤል ልጆች ቍጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም ትሩፋን ይድናሉ፤ ጌታ ፍርዱን በምድር ላይ በፍጥነትና ለመጨረሻ ጊዜ ያደርገዋልና።” ደግሞም ኢሳይያስ “የሠራዊት ጌታ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን ነበር፥ ገሞራንም በመሰልን ነበር” ብሎ አስቀድሞ እንደ ተናገረው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? አሕዛብ ጽድቅን ሳይከተሉ ጽድቅን አገኙ፤ እርሱም በእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ ነገር ግን እስራኤል የጽድቅን ሕግ እየተከተለ ወደ ሕግ አልደረሰም። ለምን? ምክንያቱም በእምነት ሳይሆን በሥራ እንደሆነ ስለቆጠሩት ነው፤ ስለዚህ በማሰናከያ ድንጋይ ተሰናከሉ። ይህም “እነሆ፥ በጽዮን የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት አኖራለሁ፥ በእርሱም የሚያምን አያፍርም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ወንድሞች ሆይ! የልቤ መልካም ምኞትና እግዚአብሔርንም የምለምነው እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። ለእግዚአብሔር ቅንዓት እንዳላቸው እመሰክርላቸዋለሁ ነገር ግን ቅንአታቸው በእውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ባለማወቅ፥ የራሳቸውንም ጽድቅ ለመመሥረት በመፈለግ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምን ሁሉ እንዲጸድቅ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ ስለ ሆነው ጽድቅ ሲጽፍ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤” ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም “በልብህ ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤” ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማስነሣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ነው፤ የምንሰብከው የእምነት ቃል ይህ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር፥ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፥ በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ልዩነት የለምና፤ ያው ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ያልሰሙትንስ እንዴት ያምኑታል? ያለ ሰባኪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? “መልካሙን ዜና የሚያበሥሩ እግሮቻቸው እንዴት ውብ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ነገር ግን ሁሉም ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ማን አመነ?” ብሏልና። ስለዚህ እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፤ መስማትም በክርስቶስ ቃል በኩል ነው። ነገር ግን አልሰሙም ወይ? እላለሁ፥ በእርግጥም ሰምተዋል፤ “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” ነገር ግን እስራኤል አላወቀምን? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ “ሕዝብ ባልሆነው አስቀናችኋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብም አስቆጣችኋለሁ” ብሏል። ስለዚህ ኢሳይያስም በድፍረት “ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ” አለ። ስለ እስራኤል ግን “ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ይላል። እንግዲህ ምን ልበል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? በጭራሽ! እኔ ደግሞ ከብንያም ወገን፥ ከአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝና። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝቡን አልጣላቸውም። ወይስ ኤልያስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እስራኤል እንዴት እንደተከራከረ መጽሐፍ ምን እንደሚል አታውቁምን? “ጌታ ሆይ! ነቢያትህን ገደሉ፥ መሠዊያዎችህን አፈራረሱ፤ እናም እኔ ብቻ ቀረሁ ነፍሴንም ይፈልጓታል።” ነገር ግን መለኮታዊ መልስ ምን አለው? “ለበዓል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ።” እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ ተመርጠው የተረፉ አሉ። በጸጋ ከሆነ ግን በሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ያለዚያ ጸጋ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል። እንግዲህ ምንድነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ደነዘዙ፤ ይህም “ዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ፥ እግዚአብሔር ከባድ የእንቅልፍን መንፈስ እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው፤” ተብሎ ተጽፎአል። ዳዊትም፥ ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ሁልጊዜ ይጉበጥ ብሏል። ተመልሰው መዳን እስከማይችሉ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በጭራሽ! ነገር ግን እነርሱን ለማስቀናት፥ በእነርሱ በደል፥ መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ነገር ግን በደላቸው ለዓለም ባለጠግነት ውድቀታቸውም ለአሕዛብ ባለጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? አሁን አሕዛብ ለሆናችሁ ለእናንተ እናገራለሁ፤ እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ አገልግሎቴን አከብራለሁ፤ ይህም ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ ነው። የእነርሱ መጣል ለዓለም እርቅን ካስገኘ፥ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ምን መሆን ይችላል? በኩራቱም ቅዱስ ከሆነ ብኮው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። ነገር ግን ከቅርንጫፎቹ አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሃ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን አንተ አትሸከመውም። እንግዲህ “እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ፤” ትል ይሆናል። መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተ ግን ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው ለአንተም አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፤ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በተፈጥሮ የበረሃ ከነበረ የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ እንደ አፈጣጠርህ ሳትሆን በመልካም የወይራ ዛፍ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎች የሆኑት በራሳቸው የወይራ ዛፍ እንዴት አይገቡም? ወንድሞች ሆይ! አላዋቂዎች እንድትሆኑ አልፈልግም፤ ይህን ምሥጢር እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል መደንዘዝ ሆነበት፤ እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል። ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው። በወንጌልስ በኩል በእናንተ ምክንያት ጠላቶች ናቸው፤ በምርጫ በኩል ግን በአባቶች ምክንያት ተወዳጆች ናቸው፤ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና። እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን በማይታዘዙት ምክንያት ምሕረት እንዳገኛችሁ፥ እንዲሁም እናንተ ያገኛችሁትን ምሕረት፥ እነርሱ ደግሞ ምሕረትን እንዲያገኙ፥ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም። እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ምሕረቱን ለማሳየት ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።” የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይታወቅ ነው። “የጌታን ልብ የሚያውቅ ማን ነው?” “ወይስ አማካሪው የሆነ ማን ነው? ወይስ ብድሩን እንዲመልስ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?” ሁሉም ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱም ነውና፤ ክብር ለዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ሰውነታችሁን ሕያው መሥዋዕት፥ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም መንፈሳዊ አገልግሎታችሁ ነው። መልካም፥ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ እንደሰጣችሁ እምነት መጠን፥ በረጋ አእምሮ አስቡ እንጂ ማሰብ ከሚገባችሁ በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ እናገራለሁና። በአንድ አካል ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉን፥ የሰውነት ክፍሎቹም ሥራ አንድ እንዳልሆነ ሁሉ፥ እንዲሁም ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በእርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው የሰውነት ክፍሎች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ መጠን የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ትንቢት ከሆነ እንደ እምነት መጠን መናገር፤ አገልግሎት ከሆነ ማገልገል፤ ማስተማር ከሆነ ማስተማር፤ ምክር ከሆነ መምከር፤ መስጠት ከሆነ በልግስና መስጠት፤ ማስተዳደር ከሆነ በትጋት ማስተዳደር፤ ምሕረት ማድረግ ከሆነ በደስታ መማር። ፍቅር እውነተኛ ይሁን፤ ክፉውን ነገር ተጸየፉ፥ መልካም የሆነው ነገር አጥብቃችሁ ያዙ፤ እርስ በእርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ጌታን አገልግሉ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ ነገር ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፤ ነገር ግን የተናቁትን ቅረቡ። በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። ለማንም በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አስቡ። ቢቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ” ተብሎ ተጽፎአልና፥ ተወዳጆች ሆይ! ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ለቁጣው ቦታ ስጡ እንጂ። ነገር ግን ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማው አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና ። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ሁሉም ሰው ለበላይ ባለ ሥልጣናት ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ገዢዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ፤ ከእርሱም ምስጋናን ታገኛለህ፤ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ክፉ ብታደርግ ግን ፍራ፤ በከንቱ ሰይፍ አይታጠቅምና፤ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ስለዚህ ስለ ቁጣው ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ይገባል። በዚህም ምክንያት ደግሞ ግብር ትከፍላላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ለሁሉ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። እርስ በእርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሟልና። “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አትመኝ፤” የሚለው እና ሌላም ትእዛዝ ቢኖር፤ በዚህ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤” በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። እንግዲህ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት ጊዜው አሁን መሆኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ወደ እኛ ቀርቧልና። ሌሊቱ አልፎአል፤ ቀኑም ቀርቧል፤ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን የጦር መሣሪያ እንልበስ። በቀን እንደምንሆነው በጨዋነት እንመላለስ፤ በመሶልሶልና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ የሥጋም ሐሳብ ምኞቱን እንዲፈጽም አትፍቀዱለት። በእምነት የደከመውንም አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት። ሁሉን መብላት እንደሚችል የሚያምን አለ፤ በእምነት ደካማው ግን አትክልት ይበላል። የሚበላ የማይበላውን አይናቀው፤ የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን ጌታ ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንደሚሻል ያስባል፤ ሌላው ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው ለጌታ ብሎ ነው፤ የሚበላም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ እግዚአብሔርን ያመሰግናልና የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፤ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር የሙታንንና የሕያዋን ጌታ እንዲሆን ክርስቶስ ሞቷልና፥ ሕያውም ሆኖአልና። አንተም በወንድምህ ላይ ስለምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለምን ትንቃለህ? ሁላችን በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። “እኔ ሕያው ነኝ፤” ይላል ጌታ፤ “ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ልሳንም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። እንግዲህ ከዚህ በኋላ አንዳችን በአንዳችን ላይ አንፍረድ፤ ነገር ግን ከመፍረድ ይልቅ ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይወስን። በራሱ ርኩስ የሆነ ነገር እንደሌለ በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ፤ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ምንም ርኩስ እንዲሆን ለሚቆጥር ለእርሱ ርኩስ ነው። ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው። እንግዲህ በእናንተ ያለው መልካም ነገር እንዲሰደብ አታድርጉ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። እንደዚህ አድርጎ ክርስቶስን የሚያገልግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። እንግዲህ የሰላም ነገርና እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን ነገር እንከተል። በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ነገር በራሱ ንጹሕ ነው፤ በመጠራጠር የተበላ እንደሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወይም ማንኛውም ወንድምህ የሚሰናከልበትን ነገር አለማድረግ መልካም ነው። ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በቆጠረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ የተባረከ ነው። የሚጠራጠር ሰው ቢበላ ግን በእምነት ስላልሆነ ተኰንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው። እኛ ብርቱዎች የሆንን የደካሞችን ድካም መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት። በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ነገሮች ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል። የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ መሆንን ይስጣችሁ። ይኸውም በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት፥ እንድታከብሩ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ሊያጸና፤ ስለ እግዚአብሔር እውነት ክርስቶስ ለተገረዙት አገልጋይ ሆነ እላለሁ፤ አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩት፥ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። እንደገናም “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤” ይላል። እንደገናም “አሕዛብ ሁላችሁ! ጌታን አመስግኑ፤ ሕዝቦቹም ሁሉ ያመስግኑት፤” ደግሞም ኢሳይያስ “የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ፤” ይላል። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንደምትበዙ በማመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ። ወንድሞቼ ሆይ! እኔም ራሴ ስለ እናንተ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትወቃቀሱ እንደምትችሉ ተረድቼአለሁ። ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መሰረት በድፍረት ጻፍሁላችሁ። በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነ ነገር የምመካበት አለኝ። አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ በምልክትና በድንቅ ሥራ ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል፥ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ አልሠራሁም፤ የክርስቶስ ስም ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን ለመስበክ ተጋሁ፤ ነገር ግን “ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ስለዚህ ደግሞ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ። አሁን ግን በዚህ አገር ስፍራ ከእንግዲህ ወዲያ የለኝም፥ ከብዙ ዓመታት ጀምሮም ወደ እናንተ ልመጣ ናፍቆት ስላለኝ፥ ወደ ስፔን በምሄድበት ጊዜ፥ ከእናንተ ጋር ተደስቼ ጥቂት ካሳላፍሁ በኋላ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ሳልፍ ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል ያሉትን ድሆች ለመርዳት ወደዋል። ተደስተዋልና የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው፤ በእነርሱ መንፈሳዊ ነገር አሕዛብ ተካፋዮች ከሆኑ በሥጋዊ ነገር ደግሞ ሊያገለግሉአቸው ይገባቸዋል። ስለዚህ ይህን ፈጽሜ፥ ይህን ፍሬ ካተምሁላቸው በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ ስፔን እሄዳለሁ፤ ወደ እናንተም ስመጣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ አውቃለሁ። ወንድሞች ሆይ! ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ከእኔ ጋር እንድትጋደሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤ ይህም በይሁዳ ካሉት፥ ከማይታዘዙት እንድድን፥ ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ በቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር እንዳርፍ ነው። የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። በኬንክሪየስ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን የሆነችውን እኅታችንን ፊቢንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀአሉአት፤ ከእናንተም በምትፈልገው በማንኛውም ነገር እርዱአት፤ እርሷ ለብዙዎች ለእኔም ጭምር ረድታለችና። በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለፕሪስካና ለአኪላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ እኔ ነፍስ ሲሉ አንገታቸውን አደጋ ላይ ጣሉ፤ እነርሱንም እኔ ብቻ ሳልሆን የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያመሰግኗቸዋል፤ በእነርሱ ቤት ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው፥ ለምወደው ለኤፔኔቶን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ለእናንተ ብዙ ለደከመችው ለማሪያ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ዘመዶቼ የሆኑትና አብረውኝ ታስረው ለነበሩት ለአንድሮኒኮንና ለዩኒያን ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱ በሐዋርያት መካከል ስመጥሮችና ክርስቶስን በማመን እኔን የቀደሙ ናቸው። በጌታ ለምወደው ለአምፕሊያቶን ሰላምታ አቅርቡልኝ። በክርስቶስ አብሮን ለሚሠራው ለኡርባኖንና ለምወደውም ለስታኺ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰገነው ለአፕሊን ሰላምታ አቅርቡልኝ። የአሪስቶቡሉ ቤተሰብ ለሆኑት ሰላምታ አቅርቡልኝ። ለዘመዴ ለሄሮድዮና ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከንርቀሱ ቤተ ሰዎች በጌታ ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ ሆነው ለሚደክሙ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ እጅግ ለደከመች ለተወደደች ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ ሆኖ ለታወቀ ለሩፎን ለእኔና ለእርሱም እናት ሰላምታ አቅርቡልኝ። ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ ለሄሮሜንም ለጳጥሮባም ለሄርማንም ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ። ለፍሌጎንና ለዩልያ ለኔርያና ለእኅቱም ለአልንጦንም ከእነርሱ ጋር ላሉ ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ወንድሞች ሆይ! ከሚለያዩትና እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም መሰናክል ከሚያደርጉ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ፤ እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የገዛ ሆዳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉምና፤ በሚያሳምን ንግግርና በሽንገላ የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። መታዘዛችሁ በሁሉም ሰው ዘንድ ደርሶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። የሰላም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ ሥር ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉኪዮስ፥ ኢያሶንና ሶሲፓትሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ቴርትዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። እኔንና መላዋ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋዩስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው ገንዘብ ያዥ ኤራስቶስ፥ ወንድማችንም ኳርቶስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ በወንጌሌ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስብከት፥ ለዘመናት ተሰውሮ በነበረው የምሥጢር ግልፀት ሊያጸናችሁ ለሚችለው ለእርሱ፥ አሁን ግን ተገለጠ፤ በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ፥ አሕዛብ ሁሉ ለእምነት እንዲታዘዙ፥ በነቢያት መጻሕፍት እንዲያውቁት ተደርጓል፤ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። በእግዚአብሔር ጥሪና ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ጳውሎስ፥ ከወንድማችንም ሶስቴንስ፥ በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በክርስቶስ ኢየሱስ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በንግግር ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በሁሉም ነገር በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና፤ ለክርስቶስ እንደ ምስክርነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ፥ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ የጠራችሁ፥ እግዚአብሔር የታመነ ነው። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ሁላችሁ ተስማምታችሁ በአንድ ልቡና እና በአንድ አቋም በአንድነት የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ! በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ የቀሎኤ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። እኔ የምለው፥ እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤” “እኔስ የአጵሎስ ነኝ፤” “እኔ ግን የኬፋ ነኝ፤” “እኔስ የክርስቶስ ነኝ፤” ትላላችሁ። ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነበር? ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ማንም በስሜ ተጠመቃችሁ ሊል አይገባውም። የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ከነዚህ ሌላ አጥምቄ እንደሆነ አላውቅም። ወንጌልን ላስተምር እንጂ ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር፥ በቃል ጥበብም አይደለም። የመስቀሉ መልዕክት ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ፤” ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚህ ዘመን ተከራካሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በምንሰብከው ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ ግሪኮችም ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፤ ለተጠሩት ግን፥ ለአይሁዶች ሆነ ለግሪኮችም፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፤ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው መመዘኛ ብዙዎች ጥበበኞች አልነበሩም፥ ብዙዎች ኀያላን አልነበሩም፥ ብዙዎች ታላላቅ ሰዎች አልነበሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ እና የተናቀውን ነገር፥ ያልሆነውንም ነገር መረጠ፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፥ ጽድቃችንና ቅድስናችንም ቤዛችንም በተደረገልን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። ስለዚህ፥ እንደተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ “የሚመካ በጌታ ይመካ፤” ወንድሞች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ የእግዚአብሔርን ምስጢር በቃላት መራቀቅ ወይም ጥበብ ለእናንተ ለማወጅ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር፥ እርሱም እንደ ተሰቀለ፥ ሌላ ነገር ላለማወቅ ወስኜ ነበርና። እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ይህም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰዎች ጥበብ እንዳይሆን ነው። በዐዋቂዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህን ዓለም ወይም መጨረሻቸው ጥፋት የሚሆነውን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር ተሰውሮም የነበረውን እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዢዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ፥ አላወቀም፤ ዐውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን እንደተጻፈው፥ “ዐይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማው፤ በሰውም ልብ ያልታሰበው፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤” ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። መንፈስ፥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር፥ ሁሉን ይመረምራልና። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር የሰውን ነገር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን ነገር ማንም አያውቅም። እኛ ግን፥ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠንን፥ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። ይህን ደግሞ፥ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን፥ መንፈስ በሚያስተምረን ቃል እንናገራለን እንጂ ከሰው ጥበብ በሚገኝ ቃል አይደለም። ፍጥረታዊ ሰው ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር አይቀበለውም፤ ይህ ለእርሱ ሞኝነት ነው፥ ምክንያቱም በመንፈስ የሚመረመር ነውና፥ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራል፤ እሱ ግን በማንም አይመረመርም። ሊመክረውስ የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልቦና አለን። ወንድሞች ሆይ! እኔም፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጠንካራ መብል ለመብላት አልቻላችሁም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ገና አትችሉም፤ እናንተ ገና ሥጋውያን ናችሁ፤ ቅናትና ጭቅጭቅ እስከተገኘባችሁ፥ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ ነኝ፤” ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድነው? ጳውሎስስ ምንድነው? በእነርሱ በኩል ያመናችሁ፥ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው፥ አገልጋዮች ናቸው፤ እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ሆነ ወይም የሚያጠጣ ቢሆን ምንም አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ክፍያ ይቀበላል። ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ የእግዚአብሔር እርሻ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ። የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም በዚያ ላይ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በዚያ ላይ እንዴት እንደሚያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፥ በብር፥ በከበሩ ድንጋዮች፥ በእንጨት፥ በሣር፥ በገለባ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ፥ ያ ቀን በገሃድ ያሳያልና፤ የእያንዳንዱም ሥራ ምን መሆኑን እሳቱ ራሱ ይፈትነዋል። ማንም በዚያ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ሆኖም ግን በእሳት አልፎ ይሆናል። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደሚኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው፤ ይኼውም እናንተ ናችሁ። ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፥ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው። እንደተጻፈውም፥ “እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤” ደግሞም “ጌታ የጥበበኞችን ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል።” ስለዚህም፥ ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፥ ማንም በሰው አይመካ፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፤ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው። እንግዲህ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢራት መጋቢዎች ይቁጠረን። ከዚህም በላይ፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ያሻል። ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በማንም ሰው ዘንድ ቢፈረድብኝ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ከኅሊናዬ ምንም የለም፤ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። ስለዚህም፥ በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን የሚያወጣ ደግሞም የልብን ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ፥ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም እያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። ወንድሞች ሆይ! ስለ አንዱ በሌላው ላይ አንዳችሁም እንዳትታበዩ “ከተጻፈው አትለፍ፤” የሚለውን በእኛ እንድትማሩ፥ በዚህ ስለ እናንተ ስል ራሴንና አጵሎስን እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። አንተን እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? እንግዲህ የተቀበልክ ከሆንክ፥ እንዳልተቀበልክ የምትመካው ስለ ምንድነው? አሁንማ ሞልቶላችኋል! አሁንማ ሀብታሞች ሆናችኋል! ያለ እኛ ነግሣችኋል! እኛም ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ፥ በእርግጥ ብትነግሡ ኖሮ፥ መልካም በሆነ! እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም ትንግርት ሆነናል። እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለንም፤ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለንም፥ እንዲሁም እንንከራተታለን፤ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ክፉ ሲናገሩን በትሕትና እንመልስላቸዋለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዚህ ዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል። እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። በክርስቶስ አእላፍ መሪዎች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። እንግዲህ “እኔን የምትመስሉ ሁኑ፤” ብዬ እለምናችኋለሁ። በዚህ ምክንያት የተወደደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፤ በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ እንደማስተምረው በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። አንዳንዶች ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። ምን ትፈልጋላችሁ? በትር ይዤ ወደ እናንተ እንድመጣ? ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ? በእርግጥ በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል፤ የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይደረግ ነው፤ ይኸውም የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው አለ። እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ ልታዝኑ አይገባችሁም? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ከእናንተ ጋር እንደ አለሁ ሆኜ፥ ይህን ሥራ የሠራውን እፈርድበታለሁ። ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር፥ በጌታችን ኢየሱስ ስም ተሰብስባችሁ፥ መንፈሴም አብሮችሁ ነው፥ እንደዚህ ያለው ሰው፥ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን እንድትድን፥ ሥጋው ይፈርስ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፋችሁ ስጡት። መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁምን? እንግዲህ እርሾ እንደሌለበት እንደ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ፥ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ ተንኰልና ክፋት በሞላበት በአሮጌ እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት የቅንነትና የእውነት ቂጣ በዓላችንን እናክብር። በመልእክቴ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ ጻፍሁላችሁ። ይህም በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን ማለቴ አይደለም፤ እንዲህማ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉት ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት። ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ጥል ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በአሕዛብ ፊት ሊፋረድ እንዴት ይደፍራል? ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፥ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ ያቅታችኋልን? እለታዊው የሕይወት ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ለዚህ መሰል ጉዳይ ፍርድ ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ እንዴት ታስቀምጣላችሁ? እንድታፍሩ ስል ይህን እላለሁ። ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል! እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት በመካከላችሁ መፍጠር ለእናንተ ሽንፈት ነው። ይልቅስ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም ብትታለሉ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ፤ ታታልሉማላችሁ፤ ያውም ወንድሞቻችሁን። ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል። “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤” ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው፤ እግዚአብሔርም ጌታን ከሞት አስነሣ፥ እኛንም በኀይሉ ያስነሣናል። ሰውነታችሁ የክርስቶስ አካል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን የአካል ክፍሎች ወስጄ የአመንዝራ ክፍሎች አካል ላድርጋቸውን? ፈጽሞ ከቶ አይገባም። ወይስ ከአመንዝራ ጋር የሚገናኝ አንድ አካል እንዲሆን አታውቁምን? “ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤” ተብሏልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሰውነቱ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሰውነቱ ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሰውነታችሁ፥ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት፥ በውስጣችሁም የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆኑን አታውቁም? እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። የጻፋችሁልኝን ነገር በተመለከተ፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት ለራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንደዚሁም ደግሞ ሚስት ለባሏ። ሚስት በገዛ ሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባሏ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ እንዲሁም ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ አብራችሁ ሁኑ። ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፤ አንዱ እንደዚህ ሌላውም እንደዚያ ዓይነት። ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ ነገር ግን በመሻት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ። ላገቡት ግን የምሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ያገባች ሴት ከባሏ አትለይ፤ ብትለይም ሳታገባ ለብቻዋ ትኑር፤ ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ እንዲሁም ባል ሚስቱን አይፍታ። ሌሎችንም፥ ጌታም አይደለም፥ እኔ እላለሁ፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር፥ እርሷም ከእርሱ ጋር ለመኖር ብትስማማ፥ አይፍታት፤ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርሷ ጋር ለመኖር ቢስማማ፥ አትተወው። ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፤ ያላመነችም ሚስት በባሏ ተቀድሳለች፤ እንደዚህ ካልሆነ ግን፥ ልጆቻችሁ ርኩሳን ናቸው፤ እንደዚህ ከሆነ ግን የተቀደሱ ናቸው። የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። ሚስት ሆይ! ባልሽን ታድኚ እንደሆን ምን ታውቂያለሽ? ወይስ ባል ሆይ! ሚስትህን ታድን እንደሆንህ ምን ታውቃለህ? እያንዳንዱ ጌታ በሰጠውና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህ ነው። ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደሆነ፥ መገረዝን አይፈልግ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። እያንዳንዱ ሲጠራ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። ባርያ ሆነህ ተጠርተህ እንደሆነ አይገድህም፤ ነጻ ልትወጣ ቢቻልህ ግን ነጻነትን ተቀበል። ባርያ ሆኖ ሳላ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባርያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ! እያንዳንዱ በተጠራ ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። ደናግልን በተመለከተ የጌታ ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት የታመንሁ እሆን ዘንድ ምክሬን እለግሳችሀለሁ፤ እንግዲህ አሁን ላለንበት ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ሚስት አግብተህ እንደሆንህ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት አላገባህ እንደሆንህ ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይገጥማቸዋል፤ እኔም ከዚያ ባስጣልኳችሁ ነበር። ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ! ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፤ ልቡም ተከፍሎአል። ያላገባች ሴትና ድንግል በሰውነት በመንፈስም እንድትቀደስ የጌታን ነገር ታስባለች፤ ያገባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንደምታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአግባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም ለጌታ በጽናት እንድታገለግሉ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም። ዳሩ ግን አንድ ሰው በእጮኛው ላይ መልካም አለማድረጉን ቢያስብ፥ እጮኛውም ዕድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ፥ ሊያገባም ከፈቀደ፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ምንም አስገዳጅ የለበትም፤ ፍላጎቱን ለመቆጣጠር ከቻለና እጮኛውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። ስለዚህ ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ፥ ያላገባም የተሻለ አደረገ። ሚስት ባሏ በሕይወት እስካለ የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ እኔ አስተያየት ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል። ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ “ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን፤” እናውቃለን። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው፥ ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው። እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት በዓለም ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። ምንም እንኳ፥ በሰማይ ሆነ በምድርም፥ አማልክት ተብለው የሚጠሩ ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ እግዚአብሔር አብ አለን፤ እንዲሁም ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። ነገር ግን ይህ ዕውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለ ለመዱ፥ ለጣዖት የተሠዋ ነው፤ ብለው ይበላሉና፥ ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም። ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። አንተ ዕውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይደፋፈርምን? በአንተ ዕውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፤ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። እንግዲህ ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህ ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን ላለማሰናከል ፈጽሞ ሥጋ አልበላም። እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና፥ ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ። ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ አማኝ ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው? ይህን የምናገረው በሰው አስተሳሰብ ብቻ ነውን? ሕግስ እንዲህ ይል የለምን? “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአል። እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ በሬዎች በማሰብ ነውን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? በእርግጥ ስለ እኛ ተጽፎአል፥ ይኸውም የሚያርስ በተስፋ እንዲያርስ፥ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው ነው። እኛ መንፈሳዊን ነገር ከዘራንላችሁ፥ የእናንተን የሥጋዊን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን የመካፈል መብት ያላቸው ከሆነ፥ እኛማ ይልቁን አይኖረንም? በዚህ መብት ግን አልተጠቀምንም፥ ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል በምንም እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ። በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚያበስሩ ከወንጌል ቀለባቸውን እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ በአንዱም ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ ግዴታዬ ነውና የምመካበት የለኝም፤ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ! ይህን በፈቃዴ ባደርገው ዋጋ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። እንግዲህ ዋጋዬ ምንድነው? በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ ሳልጠቀምበት ወንጌልን እየሰበክሁ ወንጌልን ያለ ክፍያ ባስተምር ነው። ከሰው ሁሉ ነጻ የወጣሁ ስሆን፥ ብዙዎችን እንድጠቅም እንደ ባርያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድንም ለመጥቀም ስል ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን መጥቀም እንድችል፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንኩ። ሕግ የሌላቸውን ለመጠቅም ስል፥ የእግዚአብሔር ህግ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን በክርስቶስ ሕግ ስር ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንኩ። ደካሞችን መጥቀም እንድችል ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንኩ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ማዳን እንድችል፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ተካፋይ እንድሆን፥ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በሩጫ መወዳደሪያ ስፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንደሚሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ሽልማቱን ዋጋውን እንደሚቀበል አታውቁምን? ስለዚህ እናንተም እንድትቀበሉ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ራሱን መግዛት ይለማመዳል፤ እነርሱ ጠፊውን አክሊል፤ እኛ ግን የማይጠፋውን፥ ለማግኘት ነው። ስለዚህ እኔ በከንቱ እንደሚሮጥ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የቀረሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። ወንድሞች ሆይ! ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፤ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን እንዲተባበሩ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ የጠጡትም ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዐለት ነበር፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ። እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በአብዛኞቹ ደስ አልተሰኘም፤ እነርሱ ምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋልና። እነርሱ ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛም እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆኑልን። “ሕዝቡም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ አንሴስን፥ በአንዲት ቀን ሃያ ሦስት ሺህ ወድቀዋልና። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑትና በእባቦች እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳጉረመረሙና በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታጉረምርሙ። ይህ ሁሉ ነገር እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፤ የተጻፈው ግን በዘመናት መጨረሻ ለምንገኘው ለእኛ ተግሣጽ ነው። ስለዚህ የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰው ከሚደርሰው ፈተና በቀር ምንም አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፤ መታገሥ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገድ ደግሞ ያዘጋጅላችኋል። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ የምለውን ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ፥ የክርስቶስን ደም መካፈል አይደለምን? የምንቆርሰውስ ኀብስት፥ የክርስቶስን ሥጋ መካፈል አይደለምን? አንድ ኀብስት ስለ ሆነ፥ ሁላችን ያን አንዱን ኀብስት እንካፈላለንና፥ እኛ ብዙዎች ብንሆንም አንድ አካል ነን። በሥጋ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ የሚረባ ነገር ነው? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት፤ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ ምድር የጌታ ነውና፥ በእርሷ የሞላባት ሁሉ። ከማያምኑ ሰዎች አንዱ ቢጠራችሁ እናንተም ለመሄድ ብትፈልጉ ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፤” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ፤ ስለ ሌላው ሰው ሕሊና ማለቴ እንጂ ስለ ራሳችሁ ሕሊና አይደለም። ነጻነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ለምንድን ነው? እኔም በምስጋና ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለምን እሰደባለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ፥ ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ይሁን ለግሪክም እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ማሰናከያ አትሁኑ። እኔ ደግሞ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲጠቀሙ፥ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ ለማሰኘት የምጥረው፥ ይድኑ ዘንድ ነው። እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። ወንድሞች ሆይ! በሁሉ ስለምታስቡኝና እኔ ያስተላለፍኩላችሁን ትውፊት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል ትቆጠራለችና። ሴትም ራስዋን የማትከናነብ ከሆነ ደግሞ ጠጉርዋን ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን። ወንድ የእግዚአብሔር መልክና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና። ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። በዚህ ምክንያት፥ በመላእክትም ምክንያት ሴት በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል። ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ፥ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። ሴት ከወንድ እንደ ሆነች ሁሉ ወንድ ደግሞ ከሴት የሚገኝ ነውና፤ ነገር ግን ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው። በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትከናነብ ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን? ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር አይደለምን? ምክንያቱም ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታል። ማንም ግን ሊከራከር ቢፈልግ፥ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። ነገር ግን ይህን ትእዛዝ ስሰጥ አላመሰግናችሁም፤ ምክንያቱም በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚሻል ሳይሆን ለሚከፋ በመሆኑ ነው። በመጀመሪያ እንደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፤ በከፊል ያን አምናለሁ። ትክክል የሆኑት እነማን እንደ ሆኑ ተለይተው እንዲታወቁ በመካከላችሁ መለያየት መኖሩ ግድ ነውና። በአንድነት በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም። ስትበሉ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላል፤ አንዱም ይራባል ሌላው ደግሞ ይሰክራል። ኧረ ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትንቃላችሁን? ወይስ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም። እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ ለእናንተ ደግሞ ያስተላለፍኩላችሁ ይህ ነው፦ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት ኅብስትን አንሥቶ፤ አመሰገነ ቆርሶም “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤” አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚመሰረት አዲስ ኪዳን ነው፤ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤” አለ። ይህን ኅብስት በምትበሉበትና ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ። ስለዚህ ያልተገባ ሆኖ ሳለ ይህን ኅብስት የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይመርምር፤ እንዲሁም ከኅብስቱ ይብላ፤ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላል፤ ይጠጣልም። በዚሁ ምክንያት ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙና የታመሙ አሉ፥ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። በራሳችን ላይ ብንፈርድ ኖሮ ግን ባልተፈረደብንም ነበር። ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። ማንም የራበው ቢኖር፥ ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ፥ በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር በመጣሁ ጊዜ መመሪያ እሰጣችኋለሁ። ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ! አላዋቂ እንድትሆኑ አልፈልግም። አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ በማታውቁት ነገር ተመርታችሁ መናገር ወደማይችሉ ጣዖቶች ትወሰዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር “ኢየሱስ የተረገመ ነው፤” የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው፤” ሊል ማንም እንደማይችል አስታውቃችኋለሁ። ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም አሉ፤ አሠራሮችም ልዩ ልዩ አሉ፤ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ ግን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ የመንፈስን መገለጥ የሚሰጠው ለጥቅም ነው። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላውም ያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ በዚያው መንፈስ ለአንዱ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው የመፈወስ ስጦታን በዚያው አንድ መንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ተአምራትን የማድረግ ኃይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱ መናፍስትን መለየት፥ ለሌላው በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለሌላውም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን አንዱና ያው መንፈስ ያደርጋል፤ እንደፈቃዱም ለእያንዳንዱ ሰው ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም የአካል ክፍሎች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባርያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። አካል ብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ አንድ የአካል ክፍል አይደለምና። እግር “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም፤” ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም፤” ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ የአካል ክፍሎችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ሁሉም አንድ የአካል ክፍል ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው፤ አካል ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን “አታስፈልገኝም፤” ልትለው አትችልም፤ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን “አታስፈልጉኝም፤” ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ክፍሎች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉንን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፤ በምናፍርባቸውም የአካላችን ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካላችን ክፍሎች ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አስማምቷል። ይህም በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንድም አካል ቢሠቃይ የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ፤ አንድ አካልም ቢከበር የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ። እግዚአብሔርም አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት የሚያደርጉትን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፥ ሰዎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፥ አስተዳዳሪዎችንና በተለያዩ ልሳኖች የሚናገሩትን ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ሰይሟል። ሁሉም ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? ነገር ግን የላቀውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝ፥ ምስጢርን ሁሉ ባውቅ፥ ዕውቀትን ሁሉ ብረዳ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሳል፤ ቸርነትንም ያደርጋል። ፍቅር አይቀናም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም። ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል፤ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል። ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ትንቢት የመናገር ስጦታም ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላስል ነበር። ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ። አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ። እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፥ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለሚናገር የሚረዳው የለም። ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፥ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፥ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ፥ በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኩአችሁ ምን እጠቅማችሃለሁ? እንደዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ የሚታወቅ ቃል ካልወጣ፥ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለውም ቋንቋ የለም። እንግዲህ የሚነገረውን ቋንቋ ትርጉሙን ካላወቅሁ፥ ለተናጋሪው እንግዳ እሆንበታለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆንብኛል። እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት የምትሹ በመሆናችሁ፥ ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ። ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ፍሬ አልባ ነው። ታዲያ፥ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲህማ ካልሆነ፥ በመንፈስ በምትባርክበት ጊዜ፥ አንተ የምትለውን የማያውቅ እንግዳ ሰው ካልተረዳ፥ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፥ “አሜን” ሊል ይችላል? አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፥ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፥ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል። ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ። “ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፥ በባዕዳንም አንደበት ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፥ ይላል ጌታ” ተብሎ በኦሪትም ተጽፎአል። በዚህ ዓይነት፥ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑት አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፥ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፥ አብደዋል አይሉምን? ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፥ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፥ “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር፥ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ አንዱ ደግሞ ይተርጉም፤ የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን፥ በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፥ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ፥ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፥ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በቤተ ክርስቲያን መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን? ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ሰው ነኝ የሚል ቢኖር፥ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ ይህን አላውቅም የሚል ቢኖር እርሱም አይታወቅ። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ይሁን። ወንድሞች ሆይ! አሁን የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፥ ያመናችሁት በከንቱ ካልሆነ በስተቀር፥ የምትድኑበትን ወንጌል ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ለኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፥ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ ይልቁን ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ሆኖም ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፥ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነው። ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፥ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፥ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፥ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። በክርስቶስም ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደመጣ፥ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፥ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፥ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፥ ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፥ ያንጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የሚደመሰሰው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፥ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፥ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል። ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት አረጋግጣለሁ። እንደ ሰው አስተሳሰብ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ምን ሊፈይድልኝ ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው። ነገር ግን አንዱ፥ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚወጡትስ በምን ዓይነት አካል ነው?” ብሎ ቢጠይቅ። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዘር ቅንጣት እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዓይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንሰሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዓይነት ነው። እንዲሁም ሰማያውያን አካሎች አሉ፤ ምድራውያን አካሎች አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካሎች ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካሎች ክብር ሌላ ነው። የፀሓይ ክብር አንድ ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”። የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ድካማችሁ በጌታ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር በማወቅ፥ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ። አሁን ደግሞ ለቅዱሳን የሚደረገውን የገንዘብ መዋጮ በተመለከተ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት መመሪያ መሠረት አድርጉ። እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ፤ እኔ ስመጣ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ አብረውኝ ይሄዳሉ። በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስላቀድኩ በዚያ ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ፥ እናንተ ጋር እቆይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ፤ ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው። ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ ከመጣ፥ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና፥ አብሮአችሁ ያለ ሥጋት እንዲቀመጥ አድርጉ። ስለዚህ ማንም አይናቀው፤ በሰላም ወደ እኔ እንዲመለስ እርዱት፤ መመለሱንም ከወንድሞች ጋር እየጠበቅን ነው። ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ደግሞ፥ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እርሱ ግን አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል። ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ፤ የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ። ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች በአካይያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደሆኑና ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደሰጡ ታውቃላችሁ። እንደ እነርሱ ላሉትና ከእነርሱም ጋር በአገልግሎት ለሚደክሙ ሁሉ ታዘዙ። በእስጢፋኖስ፥ በፈርዶናጥስና በአካይቆስ መምጣት ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም እናንተ እዚህ ባለመኖራችሁ የጐደለኝን አሟልተዋል፤ የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋታልና። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እውቅና ይገባቸዋል። በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ፥ በቤታቸውም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የከበረ ሰላምታ በጌታ ያቀርቡላችኋል። ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቅርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። እኔ ጳውሎስ፥ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌላችኋለሁ። ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ! ና! የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ከወንድማችንም ከጢሞቴዎስ፥ በመላው አካይያ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይባረክ። እኛ በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል፥ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። የክርስቶስ ሥቃይ ስለ እኛ እንደ መብዛቱ፥ መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል። መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል እናንተም በትዕግሥት መታገስ በመቻላችሁ፥ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንደምትካፈሉ እናውቃለንና፥ ተስፋችን ስለ እናንተ ጽኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን ብታውቁት እንወዳለን፤ በሕይወታችን ተስፋ እስክመቁረጥ የሚያደርስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር። በእርግጥም፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ የሞት ፍርድ እንደተላለፈብን በውስጣችን ተሰምቶን ነበር። እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል። እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ ስትደግፉን፤ በብዙዎች ጸሎት ስለ ተሰጠን ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ ምስጋና ያቀርባሉ። ትምክህታችን ይህ ነው፦ በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ባልሆነ፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት እንደኖርን፥ የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን የተለየ ነገር አንጽፍላችሁም፥ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛን በከፊል እንደተረዳችሁን፥ በጌታ ቀን እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንመካለን። በዚህም እርግጠኛ ስለነበርኩ፥ በእጥፍ እንድትጠቀሙ አስቀድሜ ወደ እናንተ መምጣት ፈልጌ ነበር። ወደ መቄዶንያ ስሄድ በእናንተ በኩል አድርጌ ልጐበኛችሁና፥ ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ እንድትልኩኝ ዐቅጄ ነበር። ይህን ማድረግ በመፈለጌ የተከፈለ ሐሳብ አሳይቼ ይሆን? ወይስ በእኔ ዘንድ “አዎን፥ አዎን” እና “አይደለም፥ አይደለም” ማለት እንዲሁ በሰብአዊ መመዘኛ በልማድ ይሆን? እግዚአብሔር የታመነ የሆነውን ያህል በእርግጥ እኛ ለእናንተ የምንናገረው ቃል “አዎን” እና “አይደለም” አይሆንም። ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ፥ እኔም፥ በመካከላችሁ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ሁልጊዜ “አዎን” ሆኖአል። እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ “አዎን” ማለት የእርሱ ነው፤ ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር ክብር በእኛ ስለሚነገረው “አሜን” የምንለው እርሱ በኩል ነው። ነገር ግን በክርስቶስ ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፤ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። እኔ ግን ራርቼላችሁ እንደገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ፥ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ለምስክርነት እጠራለሁ። እምነታችሁ ምክንያት አድርገን እናንተን ገዢዎች አይደለንም፤ ይልቁን በእምነታችሁ ጸንታችሁ ቆማችኋልና ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን። ስለዚህ ዳግመኛ በጉብኝቴ እንዳላስቸግራችሁ ወደ እናንተ ላለመምጣት ቆረጥሁ። እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ስለምተማመን፥ ደስ ሊያሰኙኝ ወደሚገባቸው በመምጣቴ ማስቸገር እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍኩላችሁ። በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት፥ በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበር፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም። ነገር ግን ማንም ያሳዘነ ቢኖር፥ እኔን ብቻ ሳይሆን ያሳዘነው፥ ባላጋንነው በተወሰነ መልኩ፥ ሁላችሁንም ነው። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ በብዙሃኑ ስለተቀጣ በቂው ነው። ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቆርጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅራችሁን መልሳችሁ እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ። በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን ለማወቅ በማሰብ፥ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበር። እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፤ ይህን የምናደርገው በሰይጣን መበለጥ እንዳንችል ነው፤ ማናችንም የእርሱን አሳብ አንስተውም። የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ በጌታ በሩ ተከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንፈሴ ማረፍ አልቻለም፤ ምክንያቱም እዚያ ወንድሜን ቲቶን አላገኘሁትም። ስለዚህ ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን፥ በእኛም በሁሉም ስፍራ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፥ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚነግዱ እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን። እንደገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ለእናንተ ወይም ከእናንተ የተጻፈ የምስጋና ደብዳቤ ያስፈልገን ይሆንን? ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነብቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም ያልሆነ፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ፥ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። በክርስቶስም በኩል በእግዚአብሔር ያለን መተማመን ይህን ይመስላል። ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን የሚሆን አንዳችን ነገር ልናስብ እኛ የበቃን አይደለንም፤ እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ላልሆነ፥ ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን አበቃን፤ ፊደል ይገድላል፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው፥ ስለ ፊተኛው ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት ያን ያህል ክቡር ከሆነ፥ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ልቆ የከበረ አይሆንም? የኩነኔ አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ ይልቁን የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣል። በእርግጥ ያ ከብሮ የነበረው እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት ክብሩን አጥቶአል። ያ ይሻር የነበረው በክብር ከደረሰ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት ልቆ እጅግ አይከብርም! እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን፥ አብዝተን በድፍረት እንናገራለን፤ ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኩር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ ፊቱን እንደ ጋረደው እንደ ሙሴ አይደለም። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወገድ እስከ ዛሬ ድረስ በመኖሩና፥ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና፥ አሳባቸው ደነዘዘ። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ቍጥር ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ነገር ግን ሰው ወደ ጌታ ፊቱን ሲያዞር መጋረጃው ይወገዳል። ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። እኛም ሁላችን፥ በመጋረጃ በማይሸፈን ፊት፥ የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን፥ የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፥ ይህም መንፈስ ከሚሆን ጌታ የመጣ ነው። ስለዚህ ይህ አገልግሎት የተሰጠን በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ስለሆነ፥ መቼም አንታክትም። የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናል፤ በተንኮል አንመላለስም ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናቀርባለን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። እንደ እነርሱ ከሆነ የማያምኑ ሰዎችን ልቦና፥ የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ አሳውሯል። እኛ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፤ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባርያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት እንዲሰጥ ብርሃን በልባችን ውስጥ ያበራ፥ “በጨለማ ብርሃን ይብራ፤” ያለው እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን ይህ ልዩ ኃይል የእግዚአብሄር መሆኑንና ከእኛ አለመመጣቱን ግልጽ ለማድረግ፥ ይህ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ ከየአቅጣጫው መከራን እንቀበላለን እንጂ አንጨነቅም፤ ግራ እንጋባለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንተውም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን እንዲገለጥ፥ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን እንዲገለጥ፥ እኛ ሕያዋን የሆንን ስለ ኢየሱስ ስንል ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን። ስለዚህ ሞት በእኛ፥ ሕይወት ግን በእናንተ ይሠራል። ነገር ግን “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን። ምክንያቱም ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሣንና ከእናንተም ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ፥ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን እንዲያበዛ፥ ሁሉም ነገር ስለ እናንተ ሆኗል። ስለዚህ አንታክትም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድ እንኳን፥ ውስጣዊው ሰውነታችን በየዕለቱ ይታደሳል። ቀላል የሆነው ጊዜያዊ መከራችን ከመመዘኛዎች ሁሉ ለሚያልፈው ለዘላለማዊ ክብር ያዘጋጀናል። ስለዚህ የሚታየውን ሳይሆን የማይታየውን እንመልከት፥ ምክንያቱም የሚታየው ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው። የምንኖርበት ምድራዊ ድንኳን የሆነው ሕይወት ቢፈርስ፥ በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ በእጅ ያልተሠራ፥ በእግዚአብሔር የታነጸ መኖሪያ እንዳለን እናውቃለን። በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን፥ ከሰማይ የሆነ መኖሪያችንን ለመልበስ እንናፍቃለንና፤ ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት እንዲዋጥ፥ ጨምረን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፥ በዚህ ድንኳን ሳለን ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። ስለዚህ ሁልጊዜ እንታመናለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ ብናውቅም፥ የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም። አዎ፥ ታምነናል፤ ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በጌታ ዘንድ መኖር እንመርጣለን። ስለዚህ በማደሪያችን ሆንን ወይም ተለይተን ሄድን፥ እርሱን ደስ የምናሰኝ መሆንን ነው የምንፈልገው። መልካም ሆነ ወይም ክፉ፥ በሥጋችን እንደ ሠራነው ዋጋችንን ለመቀበል፥ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን። እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን፥ ሰዎችን ለማስረዳት እንጥራለን፤ ስለ ራሳችን ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጥን ነን፤ ለእናንተም ሕሊና የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ። በልብ ሳይሆን በውጫዊ ነገር ለሚመኩ፥ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት ልንሰጣችሁ እንጂ በእናንተ ፊት መልሰን ራሳችንን ለማመስገን ፈልገን አይደለም። አእምሮችንን የሳትን ብንሆን፥ የሳትነው ለእግዚአብሔር ነው፤ ጤነኞችም ብንሆን ለእናንተ ነው። አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናችን፥ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ ይህ በመሆኑም ሁሉ ሞተዋል። በሕይወትም ያሉት፥ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ፥ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሰብአዊ አመለካከት እንደምናየው አድርገን አንመለክትም፤ ክርስቶስንም በዚህ መልክ ተመልክተነው የነበርን ብንሆን እንኳን፥ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በዚህ መልክ አይደለም የምናውቀው። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል! ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል። ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው። እንግዲህ፥ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ እንለምናለን፤ እርሱ፥ “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፤” ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳንም ቀን አሁን ነው። አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በማናቸውም መንገድ አንዳች ዕንቅፋት አናኖርም። ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች በሁሉም መንገድ ራሳችንን እንሰጣለን፤ በታላቅ ጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በመታሰር፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመራብ፥ በንጽሕና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእውነተኛ ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝ እጅና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል። አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ! በግልጽ ነግረናችኋል፥ ልባችንንም ለእናንተ ወለል አድርገን ከፍተንላችኋል። እኛ ፍቅራችንን አልቆጠብንባችሁም፥ እናንተ ግን ቆጥባችሁብናል። ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን ይህን እላችኋለሁ፤ እናንተም ደግሞ ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን። ከማያምኑ ጋር አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ድርሻ አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን ስምምነት አለው? እኛ እኮ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናግሯል፥ በእነርሱ እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ፤ ርኩስንም አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ “ለእናንተም አባት እሆናለሁ፤ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ፤” ይላል ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እንግዲህ ወዳጆች ሆይ! ይህ ተስፋ ቃል ስላለን፥ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፥ እግዚአብሔርን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ። በልባችሁ ስፍራ አኑሩን፤ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላጭበረበርንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም። ይህን የምለው እናንተን ለመኮነን አይደለም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን ስፍራ እንዳላችሁ አስቀድሜ ተናግሬለሁ። ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፤ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ እኔም በመጽናናት ተሞልቻለሁ፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አልነበረውም፤ ከውጭ ጠብ ነበረ፤ ከውስጥ ደግሞ ፍርሃት ነበረብን። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም የነበራችሁን ቅንዓት ሲነገረን በእናንተ ስለተጽናናን ማለቴ ነው፤ ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ አለኝ። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ ተረድቻለሁ፤ አሁን ግን ሐዘናችሁ ወደ ንስሓ ስለመራችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ደስታዬ ስለ ሐዘናችሁ አይደለም፤ በማንኛውም መንገድ በእኛ በኩል እንድትጎዱ አንፈልግም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ወደ መዳን ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም፤ ዓለማዊው ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ለእንዴት ዓይነት ትጋት፥ ለእንዴት ዓይነት ራስን የማንጻት ጉጉት፥ ለእንዴት ዓይነት ቊጣ፥ ለእንዴት ዓይነት ፍርሃት፥ ለእንዴት ዓይነት ናፍቆት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅንዓት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅጣት እንዳደረሳችሁ ተመልከቱ! በዚህም ጉዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። እንግዲያስ ጽፌው እንኳን ቢሆን ኖሮ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእናንተ በኩል በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በደለኛ ወይም ስለ ተበዳይ አይደለም የጻፍኩት። ስለዚህ ተጽናንተናል፤ ክመጽናናታችንም ሌላ ስለ ቲቶ ደስታ እጅግ ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም ልቡ በሁላችሁም እረፍት አግኝቷል። በእርሱ ፊት ስለ እናንተ በተመካሁበት ነገር አላሳፈራችሁኝም፤ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ የተናገርነው እውነት እንደሆነ ሁሉ፥ እንደዚሁም ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደ ተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ለእናንተ ያለው ፍቅር እጅግ ጨምሯል። በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል። ወንድሞች ሆይ! በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንድታውቁት እንፈልጋለን፤ በብዙ መከራ እየተፈተኑም ቢሆን ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነበር፤ የድህነታቸው መጠን ቢበዛም ልግስናቸው የበዛ ነበር። እንደ ዐቅማቸው መጠን፥ ዐቅማቸውም የሚያልፍ እንኳን፥ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ። ለቅዱሳን በሚደረገው አገልግሎት እነርሱም ተሳታፊ የመሆንን ጸጋ እንዲያገኙ እኛን አጥብቀው ይለምኑ ነበር፤ አስቀድመው ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፥ ከዚያም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእኛም ሰጡ፥ እንጂ እኛ አስበንበት ያደረግነው አይደለም። ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ በእናንተ መካከል የጀመረውን ይህንን የቸርነት ከፍጻሜ እንዲያደርሰው ለምነነው ነበር። ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነት፥ በቃል፥ በእውቀት፥ በትጋት፥ እንዲሁም ለእኛ በፍቅራችሁ ልቃችሁ እንደተገኛችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ልቃችሁ ተገኙ። ይህንን የምለው ትእዛዝ እንደምሰጥ ሆኜ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለመመርመር ነው። የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ ታውቃላችሁ፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። በዚህም ጉዳይ ምክሬን እለግሳችኋለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤ አሁንም እንዳዐቅማችሁ መጠን ለማድረግ ያላችሁ ጉጉት እንደ ሐሳባችሁ እንዲሆንላችሁ የጀመራችሁትን ከፍጻሜ አድርሱት። በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ ባለው ባለው መጠን ተቀባይነት ይኖረዋል እንጂ የሌላውን አይጠበቅበትም። በናንተ ላይ ጫና ይብዛ ለሌሎች ደግሞ ዕረፍት ይሁን ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው። የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ፥ በዚህም ያላችሁን እኩል እንዲሆን፥ የአሁኑ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ። “ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፤ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።” ተብሎ እንደተጻፈው። ነገር ግን እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱ ምክራችንን ብቻ አይደለም የተቀበለው፥ ከቀድሞው የበለጠ በመትጋት፥ ወዶ ወደ እናንተ ይመጣል። ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ የቸርነት ሥራ ከእኛ ጋር አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጧል። እኛም ስለምናገለግለው ስለዚህ የቸርነት ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ ምክንያቱም በጌታ ፊት ብቻ ያልሆነ፥ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን ስለምናስብ ነው። በብዙ ነገር ተፈትኖና በብዙ ጉዳዮች ትጉህ ሆኖ ያገኘነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር ልከነዋል። አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከበፊት ይልቅ እጅግ ትጉህ ነው። ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፥ እናንተን ለማገልገል አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖር፥ የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። እንግዲህ ስለ ፍቅራችሁና ስለ እናንተ ያለን ትምክህት ማረጋገጫ እንዲሆነን በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ይህን ለእነርሱ በግልጽ አሳዩ። ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። በጎ ፈቃዳችሁን ስለማውቅ፤ በእናንተ ላይ የምመካበትን ምክንያት ለመቄዶንያ ሰዎች፥ “አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል፤” ብዬ ተናግሬለሁ፤ ቅንዐታችሁም ብዙዎችን አነሣሥቶአል። ነገር ግን ለእነርሱ እንደተናገርኩት፥ ስለ እናንተ ያለን ትምክህት እንዲሁ በባዶ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ወንድሞችን እልካለሁ፤ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡና ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፥ ያን ያህል ማለታችን እንድታፍሩ ባይሆንም፥ እንዲህ በመመካታችን ግን እንድናፍር ያደርገናል። እንግዲህ ዝግጁ እንድትሆኑ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን የልግስና ስጦታ እንደ ግዴታ ሳይሆን በበጎ ፈቃደኝነት ቀደም ብለው እንዲያዘጋጁ፥ እነርሱን መለመን አስፈላጊ መሆኑን አስቤበታለሁ። ይህን አስታውሱ፤ በጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራም ብዙ ያጭዳል። እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና፥ እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበው ይስጥ፤ በኀዘን ወይም በግድ ግን አይሁን። ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝታችሁ በበጎ ሥራ በቸርነት እንድትለግሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። ይህም፥ “በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል፤” ተብሎ ተጽፏል። ለዘሪ ዘርን፥ ለመብላትም እንጀራን የሚሰጥ፥ እርሱ የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤ ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ በእኛ በኩል እግዚአብሔርን የማመስገኛ ምክንያት የሚሆነውን ልግስናችሁ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ያደርጋችኋል። የዚህ አገልግሎት ረድኤት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ብዙ ምስጋና ምክንያትም ነው። በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና፥ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ ይናፍቁአችኋል። ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን። እኔም ጳውሎስ፥ ፊት ለፊት ሳገኛችሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ርቄ ግን ደፋር የምሆንባችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ ስመጣ ግን በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ በድፍረት ለመናገር አስባለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። ምንም እንኳ በሥጋ የምንመላለስ ብንሆን፥ ውጊያችንን ግን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ ምክንያቱም የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለም፤ ምሽግን ለመስበር መለኮታዊ ኃይል አለው። በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ክርክርና ማንኛውም የእብሪት እንቅፋት እናፈርሳለን፤ አእምሮን ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን፤ መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል። በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ከሆነ፥ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን እንዳይዘነጋ። በሥልጣናችን ከበፊቱ ይልቅ አሁን ብመካም እንኳን፥ ይህን ጌታ የሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ስላልሆነ አላፍርበትም። በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ። አንዳንዶች “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው፤” ይላሉ። እንዲህ የሚሉን፥ በርቀት ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን በአካልም ስንገኝ የምናደርገው መሆኑን፥ ይወቁት። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን መቁጠር ወይም ራሳችንን ማስተያየት አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ እርስ በራሳቸው ሲያመዛዝኑ፥ እርስ በራሳቸውም ሲተያዩ፥ አስተዋይ አይደሉም። እኛ ግን፥ እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን፥ እስከ እናንተ በሚደርስ ወሰን እንጂ፥ ያለ ልክ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፤ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ ድረስ መጥተናል፥ እናንተን በማካለል እንዳለፍናችሁ በማሰብ ወሰን አናልፍም። በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፤ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ፥ የምንሠራበት ወሰን እየሰፋ ይሄዳል፤ በሌላው ክፍል ስለ ተሠራው ነገር መመካት ሳያስፈልገን፥ ከእናንተ አልፎ ባለው አገር ወንጌልን ለማብሰር ያስችለናል። “የሚመካ በጌታ ይመካ፤” ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ፥ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለም። ሞኝነቴን በጥቂቱ ብትታገሡኝ በወደድኩ ነበር፤ ስለሆነም በእርግጥ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር ቅንዐት እቀናላችኋለሁና። ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ሊኖራችሁ ከሚገባ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትርቁ ብዬ እፈራለሁ። ምክንያቱም አንዱ መጥቶ እኛ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ሆኖ ብታገኙት፥ በመልካምነታችሁ ትታገሡታላችሁ። ራሴን ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደማንስ አድርጌ አልቆጥርም። በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል ይህንን ግልጽ አድርገንላችኋል። እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ እየተቀበልሁ ዘረፍሁ። ከእናንተም ጋር እያለሁ በሚጎድለኝ ጊዜ፥ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ስላሟሉልኝ፥ በማንም ላይ ሸክም አልሆንኩም፤ በማንኛውም መንገድ በእናንተ ላይ ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ እጠነቀቅማለሁ። የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህቴ በአካይያም አገር ዝም የሚያሰኘኝ አይደለም። ስለምን? ስለማልወዳችሁ ይመስላችኋል? እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል። ነገር ግን በሚመኩበት ሥራ ከእኛ እኩል በአቻነት ለመቆጠር የሚፈልጉ ሰዎችን ምክንያት ለማሳጣት፥ አሁን የማደርገውን ወደፊትም እገፋበታለሁ። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡም፥ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አጭበርባሪ ሠራተኞች ናቸው። ይህም አያስገርምም! ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ መስሎ ራሱን ለውጦ ይቀርባል። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች በመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። እንደገና ይህን እላለሁ፥ ማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ እንደ ሞኝ ለሚያስበኝ፥ እኔም በጥቂቱ እንድመካ እንደ ሞኝ ይቀበለኝ። እንደዚህ በመተማመን እየተመካሁ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አይደለም። ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። ልባሞች ስለ ሆናችሁ ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ! ማንም ባርያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበዘብዛችሁ፥ ማንም ቢጠቀምባችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ። ለዚህ ደካሞች መስለን መቅረባችንን በኀፍረት እናገራለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም ለመመካት በሚደፍርበት እኔ የምደፍርበት አለኝ። እነርሱ ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የእስራኤል ወገን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው? እንደ እብድ ሰው እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ በሥራ ብዙ ደክሜአለሁ፥ ብዙ ጊዜ ታስሬለሁ፥ ብዙ ግርፋት ደርሶብኛል፥ ብዙ ጊዜ እስከ መሞት ደርሻለሁ። አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል። ሦስት ጊዜ በበትር ተመትቻለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬለሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰባብሯል፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖሬለሁ። ብዙ ጊዜ በጉዞ ተንከራትቼአለሁ፤ በወንዝ አደጋ፥ በወንበዴዎች አደጋ፥ በወገኔ በኩል ከሚመጣ አደጋ፥ በአሕዛብ በኩል ያለ አደጋ፥ በከተማ አደጋ፥ በምድረ በዳ አደጋ፥ በባሕር አደጋ፥ በሐሰተኛ ወንድሞች በኩል አደጋ ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት፥ በእንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፥ በራብና በጥም፥ ብዙ ጊዜም በመራብ፥ በብርድና በመታረዝ አሳልፌለሁ። ሌላው ሳይቆጠር፥ በየዕለቱ የሚከብድብኝ ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መጨነቄ ነው። የሚደክም ማን ነው? እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልናደድምን? ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ መድከሜን በሚያሳይ ነገር እመካለሁ። ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንዳልዋሸሁ ያውቃል። በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን በከተማው አሰማርቶ ነበር፤ ነገር ግን በግንቡ ላይ በሚገኝ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ። በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፥ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ። ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት፥ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ እስከ ሦስተኛ ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው አውቃለሁ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ ወደ ገነት ተነጠቀ፤ በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችለውን፥ ሰውም ሊናገር ያልተፈቀደለትን ነገር ሰማ። እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ደካማ ከመሆኔ ሌላ የምመካበት የለኝም። ልመካ ብፈልግ አልሞኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው፤ ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው ባለፈ የበለጥኩ አድርጎ እንዳያስበኝ ይህን ከመናገር እቆጠባለሁ። የዚህን ግልጠት ልዩ ጸባይ በማየት እንዳልታበይ፥ ሥጋዬን መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ይህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱ ግን፥ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ በድካም ፍጹም ይሆናል” አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል እንዲያድርብኝ በበለጠ ደስታ በድካሜ መመካትን እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም፥ በመንገላታት፥ በችግር፥ በስደት፥ በጭንቀት፥ ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያንጊዜ እበረታለሁ። በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ! ይህ እናንተ ግድ ስላላችሁኝ የሆነ ነው። እኔ ከምንም የማልቆጠር ብሆን እንኳን፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አላንስምና፥ በእርግጥም እናንተ ስለ እኔ መናገር ይገባችሁ ነበር። በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት፥ በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በተአምራትም፥ በትዕግሥት በመጽናትም በመካከላችሁ ተከናውኗል። እኔ ራሴ ሸክም ሆኜባችሁ ካልሆነ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን በምን አንሳችሁ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ። እነሆ፥ ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሸክም አልሆንባችሁም፤ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግም። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን አወጣለሁ፤ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ፥ የናንተ ፍቅር እንዴት ያንሳል? ይሁን እንጂ እኔ አልከበድኳችሁም፤ ነገር ግን በብልጠት አታልዬ ያጠመድኳችሁ ሆኖ ተሰምቷችኋል። ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ እንኳ ለራሴ ተጠቅሜባችኋለሁን? ቲቶን ገፋፋሁት፤ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ ለራሱ ጥቅም አውሏችኋልን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? አንድ ዓይነት እርምጃስ አልወሰድንምን? ለእናንተ ስለ ራሳችን ሁልጊዜ መልስ የምንሰጥ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆቼ! እናንተን ለማነጽ ስንል ሁሉን እንናገራለን። ወደ እናንት ስመጣ፥ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባት ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኝነት፥ ሐሜት፥ ማሾክሾክ፥ ኩራት፥ ሁከትም ይኖር ይሆን ብዬ እሰጋለሁ። እንደገና ስመጣ በእናንተ ፊት አምላኬ ያዋርደኝ ይሆን እያልኩ፥ ከዚህ በፊት ስለ ሠሩት ኃጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኩሰት፥ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ ቀርተው እንዳላዝን እፈራለሁ። ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው። “ማንኛውም ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል።” ለሁለተኛ ጊዜ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እንደነገርኳችሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ እንደገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ለሠሩት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ እናገራለሁ፤ ይህንንም የምለው ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንደሆነ ማስረጃ በመፈለጋችሁ ነው፤ ክርስቶስ ስለ እናንተ አይደክምም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ኀያል ነው። በድካም ተሰቅሎአል፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር ደካሞች ብንሆን፤ እናንተ ለማገልገል በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን። በእምነት እንደምትኖሩ ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ካልሆናችሁ በቀር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ አታውቁም ኖሯል? እኛ ግን የማንበቃ እንዳልሆንን እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የበቃን ሆነን እንድንታይ አይደለም፤ ነገር ግን እኛ ምንም የማንበቃ እንኳን ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን እንድታደርጉ ነው። ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልም። እኛ ስንደክም እናንተም ኀይለኞች ስትበረቱ ደስ ብሎናልና፥ ፍጹማን እንድትሆኑ ደግሞ እንጸልያለን። ከእናንተ ርቄ ሳለሁ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ሥልጣኔን በኃይል እንዳልጠቀም ነው፤ ጌታም ይህን ሥልጣን የሰጠኝ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም። በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፤ ምክሬን ስሙ፤ በአንድ ልብ ሁኑ፤ በሰላም ኑሩ፤ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን። ከሰዎች ወይም በሰው አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤ ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንደ አምላካችንና አባታችን ፈቃድ፥ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ሊያድነን፥ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ሌላ ወንጌል እንዴት ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ። ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። አሁን ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሳምናለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? እስከ አሁን ሰውን ደስ የማሰኝ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ ባርያ አልሆንም ነበር። ወንድሞች ሆይ! በእኔ የተሰበከላችሁ ወንጌል ከሰው እንዳልሆነ አስታውቃችኋለሁ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንጂ ከሰው አልተቀበልሁትም ወይም አልተማርሁትም። የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ አሳድድና አጠፋ እንደ ነበር ሰምታችኋል፤ ለአባቶች ወግ ከመጠን በላይ ቅናት ስለ ነበረኝ፥ በአይሁዳዊነት ወገኖቼ ከነበሩት እኩዮቼ ብዙዎችን እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል ወንጌሉን እንድሰብክ፥ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤ ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ አረብ አገር ሄድሁ፤ እንደገና ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከዚያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። ከዚያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ መጣሁ። በክርስቶስ ያሉ የይሁዳ ቤተ ክርስቲያን አባላት አያውቁኝም ነበር፤ ነገር ግን “ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረው፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር። ከዚያ ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ቲቶንም ከእኔ ጋር ይዤው ሄድሁ፤ እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም ሮጬ እንዳልሆን፥ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል፥ በመሪነታቸው ለታወቁት ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ፥ ግሪካዊ ቢሆንም እንዲገረዝ አልተገደደም፤ ይህም ወደ ባርነት ሊመልሱን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን ነጻነታችንን ሊሰልሉ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። የወንጌሉ እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ አልተገዛንላቸውም። መሪዎች መስለው የሚታዩት፥ በፊት ምን እንደ ነበሩ ለእኔ ለውጥ የለውም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ መሪዎች የሚመስሉት ምንም ነገር አልጨመሩልኝም፤ በአንጻሩ ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት እንደተሰጠው፥ እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ አዩ፤ ጴጥሮስን ለተገረዙት ሐዋርያ እንዳደረገው፥ እኔንም ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎኛል። የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ ምሰሶዎች መስለው የሚታዩ ያዕቆብ፥ ኬፋና ዮሐንስ፥ እነርሱ ወደ ተገረዙት እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ የኅብረት ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እንድናስብ ብቻ ለመኑን፤ እኔም ይህን ለማድረግ እተጋበት የነበረ ነው። ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ሊፈረድበት ይገባ ስለ ነበር ነው። አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ፈርቶ ወደ ኋላ አፈገፈገ፥ ራሱንም ለየ። የቀሩት አይሁድ ግብዝነቱን ተከተሉ፥ በርናባስ ስንኳ ሳይቀር በግብዝነታቸው ተሳበ። ነገር ግን እነርሱ ከወንጌሉ እውነት ጋር በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ፥ በሁሉም ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እንደ አይሁድ ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ፥ አሕዛብ አይሁድ እንዲሆኑ ለምን ታስገድዳቸዋለህ?” እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን፤ ከኃጢአተኞች አሕዛብ አይደለንም፤ ሆኖም ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ሥራ እንዳልሆነ አውቀን፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። ሥጋ ሁሉ በሕግ ሥራ አይጸድቅም። ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ፥ እኛ ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ፥ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነውን? በጭራሽ አይደለም። ይህን ያፈረስኩትን እንደገና የማንጽ ከሆንሁ፥ እኔ ራሴ ሕግ ተላላፊ ነኝ። ለእግዚአብሔር እንድኖር በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼአለሁ፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ። ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልናቅሁም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነዋ! እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በዐይኖቻችሁ ላይ ተሥሎ ነበር፤ ከእናንተ ይህን ብቻ መማር እፈልጋለሁ፤ መንፈስን የተቀበላችሁት በሕግ ሥራ ነውን? ወይስ በእምነት በመስማት? እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን ግን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? ይህን ሁሉ መከራ የተቀበላችሁት በከንቱ ነውን? እንደዚያ ከሆነ በእርግጥ ከንቱ ነው። እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ድንቅን የሚሠራ፥ በሕግ ሥራ ነውን? ወይስ በእምነት በመስማታችሁ ነው? አብርሃም በእግዚአብሔር እንደ አመነና፥ ጽድቅም ሆኖ እንደ ተቆጠረለት፥ እንግዲህ እነዚህ የሚያምኑት፥ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” ብሎ አስቀድሞ ለአብርሃም ወንጌልን ሰበከለት። ስለዚህም የሚያምኑት ከታመነው ከአብርሃም ጋር ተባርከዋል። ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ይሁን፤” ተብሎ ተጽፎአልና። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሏልና፥ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግ ከእምነት አይደለም፤ ነገር ግን “የሚፈጽማቸው በእነርሱ ይኖራል።” ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ፥ ከሕግ እርግማን ዋጅቶናል፤ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፤” ተብሎ ተጽፎአልና ይህም የአብርሃም በረከት፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ አሕዛብ እንዲደርስና የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል ነው። ወንድሞች ሆይ! እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የጸና ኪዳን፥ የሰው ስንኳ ቢሆን፥ ማንም አያፈርሰውም ወይም አይጨምርበትም። የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር። ለብዙዎች እንደሆነ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደሆነ “ለዘርህም” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ይህንም እላለሁ፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የመጣው ሕግ፥ የተስፋውን ቃል ለማስቀረት፥ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን ሊሽር አይችልም። ውርስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፥ በተስፋ ቃል መሆኑ ይቀር ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም በተስፋ ቃል አማካይነት ሰጠው። ታዲያ ሕግ ለምንድን ነው? በተስፋ ቃል የተነገረው ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ ስለ መተላለፍ ተጨመረ፤ በመላእክት በኩል መካከለኛ እጅ ታዘዘ። መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን? በጭራሽ አይደለም። ሕይወትን ሊሰጥ የሚችል ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ በእርግጥ ጽድቅ በሕግ በኩል በሆነ ነበር፤ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ እንዲሰጥ፥ መጽሐፍ ሁሉን ነገር ከኃጢአት በታች ደምድሞታል። እምነት ከመምጣቱ በፊት እምነት እስኪገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ከሕግ በታች ሆነን እንጠበቅ ነበር። ስለዚህ በእምነት እንድንጸድቅ፥ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆነ፤ ነገር ግን እምነት ስለ መጣ ከእንግዲህ ወዲህ በሞግዚት ሥር አይደለንም። በክርስቶስ ኢየሱስ ባላችሁ እምነት ሁላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል። በክርስቶስ ኢየሱስ ሁላችሁም አንድ ናችሁና አይሁዳዊ ወይም ግሪካዊ የለም፥ ባርያ ወይም ነጻ ሰው የለም፥ ወንድ ወይም ሴት የለም። የክርስቶስ ከሆናችሁ ስለዚህ የአብርሃም ዘር ናችሁ፥ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ። ይህንን እላለሁ፤ ወራሹ በሕፃንነት ዘመኑ ሁሉ፥ ምንም እንኳ የሁሉ ጌታ ቢሆንም ከባርያ አይለይም፤ ነገር ግን አባቱ እስከወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በመጋቢዎች ሥር ነው። እኛም ደግሞ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ከዓለም የመጀመሪያ ትምህርቶች ሥር ተገዝተን ነበር፤ የዘመኑ ሙላት በመጣ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግ ሥር የተወለደውን ልጁን ላከ፤ ይህም ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት፥ እኛም ልጅነትን እንድናገኝ ነው። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባርያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በእግዚአብሔር በኩል ወራሽ ነህ። ነገር ግን ቀድሞ እግዚአብሔርን ሳታውቁ፥ በተፈጥሮአቸው አማልክት ላልሆኑት ተገዝታችሁ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን አውቃችሁ ይልቁንም በእግዚአብሔር ታውቃችሁ፥ እንደገና ወደ ደካማና ወደ ተናቀ የመጀመሪያ ትምህርቶች ዳግም ልትገዙላቸው ፈልጋችሁ እንዴት ትመለሳላችሁ? ቀኖችን፥ ወሮችን፥ ዘመናትንና ዓመታትን በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። ምናልባት ስለ እናንተ በከንቱ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። ወንድሞች ሆይ! እኔ እንደ እናንተ እንደሆንኩ “እንደ እኔ ሁኑ” ብዬ እለምናችኋለሁ። እናንተ አንዳችም አልበደላችሁኝም። ቀድሞ በሥጋ ድካም ወንጌልን እንደሰበክሁላችሁ ታውቃላችሁ፤ በሥጋዬ ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትም፥ አልተጸየፋችሁትምም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፥ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። እንግዲህ መባረካችሁ የት አለ? ቢቻል ኖሮ ዐይኖቻችሁን እንኳ አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደ ነበረ እኔ እመሰክርላችኋለሁ። ስለዚህ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላታችሁ ሆንሁን? ይቀኑባችኋል፥ ለመልካም ግን አይደለም፤ ነገር ግን እናንተ በእነርሱ ላይ እንድትቀኑ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። ሁልጊዜ መልካም ለሆነ ነገር ሁሉ ብትቀኑ መልካም ነው፤ ነገር ግን እኔ ከእናንተ ጋር ባለሁበት ጊዜ ብቻ አይደለም። ልጆቼ ሆይ! ክርስቶስ በእናንተ እስኪቀረጽ ድረስ ስለ እናንተ እንደገና ምጥ ይዞኛል። አሁን ከእናንተ ጋር ተገኝቼ አነጋገሬን ብለውጥ በወደድሁ ነበር፥ በእናንተ ምክንያት ግራ ገብቶኛልና። እናንተ ከሕግ በታች ለመኖር የምትፈልጉ፥ እስኪ ንገሩኝ፥ ሕጉን አልሰማችሁትምን? አብርሃም አንዱን ከባርያይቱ ሌላኛውንም ከነጻይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች እንደነበሩት ተጽፎአል። ነገር ግን የባርያይቱ ልጅ በሥጋ ልማድ ተወለደ፥ የነጻይቱ ልጅ ግን በተስፋው ቃል መሠረት ተወለደ። እነዚህም ምሳሌዎች ናቸው፤ እነዚህም ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና፥ አንደኛዋ ከሲና ተራራ ልጆችን ለባርነት ትወልዳለች፥ እርሷም አጋር ናት። ስለዚህ አጋር በዓረብ አገር ያለችው ሲና ተራራ ናት፤ አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን ነጻ ናት፤ እርሷም እናታችን ናት። “አንቺ የማትወልጅ መካን! ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ! እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና” ተብሎ ተጽፎአልና። ወንድሞች ሆይ! እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ናችሁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ በሥጋ የተወለደው በመንፈስ የተወለደውን እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “የባርያይቱ ልጅ ከነጻይቱ ልጅ ጋር እንዳይወርስ፥ ባርያይቱን ከልጇ ጋር አስወጣት” ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! የነጻይቱ ልጆች ነን እንጂ የባርያይቱ አይደለንም። በነጻነት እንድንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በባርነት ቀንበር እንደገና አትያዙ። እነሆ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፥ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። የተገረዘ ሰው ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት ብዬ ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፥ ከጸጋውም ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ፥ በእምነት፥ የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ በክርስቶስ ኢየሱስ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። ሌላ ነገር እንደማታስቡ ስለ እናንተ በጌታ እተማመናለሁ፤ የሚያውካችሁ፥ ማንም ቢሆን ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ! እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ ኖሮ ታዲያ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? ስለዚህ የመስቀል እንቅፋትነት ይቀር ነበር። የሚያውኩአችሁ ራሳቸውን ይስለቡ! ወንድሞች ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁ ለሥጋ ብቻ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር አንዳችሁ ለሌላችሁ ባርያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተፈጽሟል፥ እርሱም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ይህን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን ይመኛል፥ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚቀዋወሙ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፥ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም ግልጽ ነው፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኩሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ አስማት፥ ጠላትነት፥ ጠብ፥ ቅናት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ መሶልሶል ፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ፥ አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደ እነዚህ ያሉትን የሚቃረን ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተተነኳኮስንና እርስ በርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ። ወንድሞች ሆይ! ሰው ማንኛውንም ኃጢአት አድርጎ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። የእርስ በርሳችሁን ሸክም ተሸከሙ፥ በዚህም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን አንድ ነገር የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። እያንዳንዱ የገዛ ሥራውን ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፥ ስለ ሌላው ግን አይደለም። እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማልና። ቃሉን የሚማር መልካሙን ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ጋር ይካፈል። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል። መልካምን ሥራ ለመሥራት አንታክት፥ ካልዛልን ወቅቱ በደረሰ ጊዜ እናጭዳለንና። ስለዚህ ጊዜ ሳለን ለሰው ሁሉ፥ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። በሥጋ መልካም ሆነው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ እንድትገረዙ አስገደዱአችሁ፤ ይህን ያደረጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም፥ ነገር ግን በሥጋችሁ እንዲመኩ እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። ለእኔ ግን፥ ዓለም ለእኔ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት አይሁንብኝ። አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ፥ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ እና በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ምልክት በሰውነቴ ላይ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን። በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፤ በክርስቶስ ኢየሱስም ለታመኑ፥ በኤፌሶን ለሚገኙ ቅዱሳን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን፥ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በሰማያዊ ስፍራ በክርስቶስ የባረከን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር፥ በፍቅር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እድንሆን በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም በነጻ የሰጠን የከበረ ጸጋው እንዲመሰገን ይህን አደረገ። በእርሱም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን፥ በደሙ ቤዛነታችንን አገኘን፤ የበደላችንም ይቅርታ ሆነ። ጸጋውንም አበዛልን። በጥበብና በአእምሮ ሁሉ፥ በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል፤ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው፥ እንደ ፈቃዱና እንደ ምክሩ ሁሉን የሚያከናውን እንደ እርሱ ዓላማ የተወሰንን በክርስቶስ በርስትነት ተቀበልን። ይኸውም በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ደግሞ ለክብሩ ምስጋና እንድንሆን ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፥ በክርስቶስም አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም ለክብሩ ምስጋና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ የርስታችን መያዣ ነው። እኔ ደግሞ፥ በጌታ ኢየሱስ ለቅዱሳኖች ሁሉ ያላችሁን እምነትና ፍቅር ሰምቻለሁ፤ በዚህም ምክንያት፥ ስለ እናንተን በጸሎቴ ባስታወስኩ ቍጥር ምስጋናዬን አላቋረጥኩም። የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። በእርሱ የተጠራችሁበት ተስፋ ምን እንደሆን፥ ከቅዱሳንም ጋር የሚኖራችሁን የርስት ክብር ባለጠግነት ምንነት እንድታውቁ፥ የልቦናችሁ ዐይኖች እንዲበሩ፤ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን፥ የኀይሉ ታላቅ ብርታት አሠራር፥ ኀይሉን ምን እንደሆን እንድታውቁ፥ ይህን ኃይል እርሱ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየ ነው። የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፥ ከኃይልና ከጌትነት እንዲሁም በዚህ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ ነው። ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርሷም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። እናንተ በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ በዚህም የዚህን ዓለም አኗኗር በመከተል፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው፥ በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛም ሁላችን፥ የሥጋችንንና የህዋሳቶቻችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር፤ ደግሞም እንደ ሌሎቹ በባሕርያችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ እኛን ከወደደበት ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ፥ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለን ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። ደግሞም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፤ ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት መለኪያ የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ሊያሳይ ነው። ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ የመጣም አይደለም። ማንም እንዳይመካ ከሥራ የመጣም አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ በሕይወት እንድንመላለስ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፥ “ተገርዘናል” በሚሉት፥ “ያልተገረዛችሁ” የተባላችሁትን ያን አስታውሱ፤ በዚያ ዘመን በዚህም ዓለም ያለ ክርስቶስ ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ፥ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ፥ ተስፋን አጥታችሁና ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፥ ሁለቱን አንድ ያደረገ፥ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሕግን ከትእዛዛቱና ከሥርዓቱ ጋር ሻረ፤ ከሁለቱ አንድ አዲስ ሕዝብ ፈጥሮ ሰላምን አደረገ፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለቱን ሕዝቦች በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን ሰበከ፤ በእርሱም አማካኝነት ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት እንችላለን። እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ ባዕዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል። በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ። አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ ነው እኔ ጳውሎስ ለክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንኩት። በእርግጥ ስለ እናንተ ሲባል ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህ ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋሪያትና ለነቢያት በመንፈስ እንደተገለጠው ባለፉት ትውልዶች ለነበሩ አልተገለጠም ነበር። ይህ የሆነው፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም አማካኝነት በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነውን የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ ነው። ለዚህ ወንጌል በኀይሉ አሠራር እንደተሰጠኝ እንደ የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን አገልጋይ ሆንኩ። ከቅዱሳን ሁሉ ያነስኩ ብሆንም፥ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እንድሰብክ፥ ይህ ጸጋ ለኔ ተሰጠ፤ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረው የምሥጢር አሳብ ምን እንደሆነ ለሁሉ እንድገልጥ፥ በዚህም ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት እንድትታወቅ ነው። ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘለዓለም አሳብ ነበረ። በእርሱም ባለን እምነት አማካኝነት በድፍረትና በመተማመን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። ስለዚህ፥ ክብራችሁ ነውና፥ ስለ እናንተ ስለምቀበለው መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ። በዚህም ምክንያት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ስያሜ ያገኛል። እንደ ክብሩ ባለጠግነት መጠን፥ በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ እጸልያለሁ፤ ሥር ሰዳችሁ፥ በፍቅርም ታንጻችሁ ክርስቶስ በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ ስፋቱና ርዝመቱ፥ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ማስተዋል ላይ እንድትደርሱ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር፥ እጸልያለሁ፤ የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ድረስ እንድትሞሉ፥ እውቀትን የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር እንድታውቁ ነው። እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ፥ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ እንድትመላለሱ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትናና በየዋህነት ሁሉ፥ በትዕግሥትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ፤” ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም የክርስቶስ አካል ለመገንባት፥ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ነው፤ ይህም ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ መላው አካል በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፥ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። እንግዲህ አሕዛብ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ፥ በጌታም እለምናችኋለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸውና በልባቸው ደንዳንነት ምክንያት፥ ልቡናቸው ጨለመ፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ፥ በማይረካ ምኞት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ለሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፤ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ስለ ቀድሞ አኗኗሯችሁም፥ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውንና የተበላሸውን፥ አሮጌ ሰው አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን የሰውነት አካሎች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ፥ ኃጢአትን ግን አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። እንደ አስፈላጊነቱ፥ ለሚሰሙት ጸጋን እንዲሰጥ፥ ለማነጽ የሚጠቅም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም፥ ጩኸትና ስድብን ሁሉ፥ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ ክርስቶስም እንዳፈቀራችሁ፥ ስለ እናንተም ለእግዚአብሔር መልካም መዓዛ ያለው መባንና መሥዋዕት አድርጎ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ፥ በፍቅር ተመላለሱ። ለቅዱሳን የማይገባው፥ ማንኛውም የዝሙትና የርኩሰት፥ ወይም የስስት ነገር ሁሉ በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያጸይፍ ነገር፥ ተራና የእንዝህላል ንግግርም ፈጽመው በመካከላችሁ አይኑሩ፤ ይልቁን አመስጋኞች ሁኑ። ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም ስስታም ማለትም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ። ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ የብርሃን ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና፤ ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁን ግለጡት፤ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳን ያስነውራል። ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ፤ ከሙታንም ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል፤” ተብሏል። እንግዲህ ስለ አኗኗሯችሁ በጥንቃቄ ተጠበቁ፥ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው አይሁን፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ ብክነት እንደ ሆነው በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። እያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ! ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል የሚስት ራስ ነው። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ እንደሰጣት፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ከውሃ መታጠብ ጋር በቃሉ አንጽቶ እንዲቀድሳት፥ እንዲሁም ጉድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር የሌለባት አድርጎ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርባ እንደፈለገ፥ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ አካላቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የራሱን እካል የሚጠላ ከቶ የለምና፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበውማል። ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው እንዲህ ነው፤ ምክንያቱም እኛ የአካሉ ክፍሎች ነን። “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፤ ሚስትም ባልዋን ታክብር። ልጆች ሆይ! ተገቢ ነውና ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ። “አባትህንና እናትህን አክብር፤” ከተስፋ ቃል ጋር የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፤ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” እናንተም አባቶች ሆይ! ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው። አገልጋዮች ሆይ! ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፥ በልባችሁ ቅንነት በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባርያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታገለግሉ በጽኑ ፍላጎት ተገዙ፤ ባርያም ሆነ ነጻ ሰው፥ እያንዳንዱ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ ብድራቱን እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። እናንተም ጌቶች ሆይ! ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ታውቃላችሁ። በተረፈ በጌታ በኃይሉ ብርታትም ጠንክሩ። የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ። ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ የሰላም ወንጌል ለማወጅ በዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ። ቃል እንዲሰጠኝና አፌን በመክፈት የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ፥ ስለ እኔም ለምኑ። ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንኩ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጽ እድናገር ለምኑ። እናንተ ደግሞ በምን ሁኔታ እንዳለሁና እንዴት እንደምኖር እንድታውቁት የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ይነግራችኋል፤ ስለ እኛ ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው በዚህ ምክንያት ነው። ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እናንተን ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ ሁላችሁም በደስታ እጸልያለሁ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ ነው። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው በዚህ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ እንዲህም ያለው እውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ነው። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ በክብር ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፤ በጌታ ካሉት ወንድሞች የሚበዙት በእስራቴ ላይ ጽኑ መተማመን ኖሩዋቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ደፍረዋል። በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖር ማለት ለእኔ ፍሬያማ ሥራ የምሠራበት ቢሆን፥ ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህም በሁለቱ አማራጮች መካከል እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን ስለ እናንተ በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነገር ነው። ይህንንም ተረድቼ፥ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ከሁላችሁም ጋር እንደምቈይና እንደምኖር አውቃለሁ፤ በዚህም በእናንተ ዘንድ እንደገና ስለ መገኘቴ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ መመካታችሁ በእኔ እንዲበዛላችሁ ነው። ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ብቻ ኑሩ፤ በዚህም መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል እምነት አብራችሁ መጋደላችሁንና በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን እሰማለሁ። በምንም ዓይነት ነገር በተቃዋሚዎቻችሁ አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለ ሆነም በክርስቶስ የምታምኑ ብቻ ሳትሆኑ ስለ እርሱ መከራንም ደግሞ የምትቀበሉ ትሆናላችሁ፤ ይህም ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንደሆነ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና። ስለዚህ ለእናንተ በክርስቶስ አንዳች መበረታተታት ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናትም ቢሆን፥ የመንፈስም ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄም ቢሆኑ፥ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ፤ እናንተም የሕይወትን ቃል በጽኑ በመያዛችሁ ምክንያት በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር አብራችሁ ሐሤት አድርጉ። ነገር ግን ስለ እናንተ ባወቅሁ ጊዜ ደስ ተሰኝቼ እንድበረታታ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እኔ ሆኖ ስለ ደኅንነታችሁ በቅንነት የሚጨነቅ እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝምና፤ የተቀሩት ሁሉ ግን የክርስቶስ ኢየሱስን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም የሚሹ ናቸውና። ነገር ግን ጢሞቴዎስ ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል በማገልገል መፈተኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ በእኔ ዘንድ ያለውን ሁኔታ አይቼ፥ እርሱን ቶሎ እንደምልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እኔም ራሴ ደግሞ ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛና ወታደር፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን ኤጳፍሮዲጡስን ወደ እናንተ መላክ ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ሁላችሁን ይናፍቃልና፤ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያደረገው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ደግሞ ነው። እንግዲህ እንደገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ ምክንያቱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለመፈጸም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ለክርስተቶስ ሥራ ሲል ለሞት ተቃርቦ ነበርና። በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ። ለእናንተ ተመሳሳይ የሆነን ነገር መልሼ ለመጻፍ ለእኔ አይታክተኝም፤ ይህ ለእናንተ ለደኅንነት የሆነ ነውና። ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፤ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን በእውነትም ከተገረዙት ወገን የሆንን ነንና። እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት ነገር ያለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ጥቅም የሚያስገኘውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ ለማወቅ ስል ሁሉ ነገር ጉዳት እንደሆነ አድርጌ እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ነገሮች በማጣት ተጐዳሁ፤ እነርሱንም እንደ ጉድፍ አድርጌ ቈጠርኋቸው፤ በዚህም ክርስቶስን እንዳገኝ፥ በክርስቶስም በማመን በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንጂ በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴ ጽድቅ ሳይኖረኝ፥ በእርሱ እንድገኝ ነው፤ በሞቱም እርሱን በመምሰል ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል መከራውንም ተካፋይ መሆኔን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ምናልባትም ቢሆንልኝ የሙታን ትንሣኤን እቀዳጃለሁ። እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍጹም ለመሆን አልበቃሁም፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደ ፊት እሮጣለሁ። ወንድሞች ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደ ፊት እዘረጋለሁ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያለውን የመጠራት ሽልማት እንዳገኝ ወደ ግቡ እሮጣለሁ። እንግዲህ በአእምሮ የበሰልን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም ለእናንተ ምሳሌ እንደ ሆንን እንዲሁ የሚመላለሱትን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ ነገርኋችሁ፤ አሁንም እያነባሁ ስለ እነርሱ እነግራችኋለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ደግሞ ለራሱ ሁሉን ነገር በሥሩ ለማስገዛት በሚችልበት ኃይሉ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል። ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ደስታዬና አክሊሌ ናችሁ፤ የተወደዳችሁ ሆይ! በዚህ መንገድ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ። በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ! ከእኔ ጎን በመቆም ከቀለሜንጦስ ጋር አብረው በወንጌል ሥራ ተጋድለዋልና እነዚህን ሴቶችና የተቀሩትን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩትን እንድትረዱአቸው እለምንሃለሁ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፤ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ መምጫው ቀርቦአል። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በምንም ዓይነት ነገር አትጨነቁ። ከሰውም ማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ክቡር የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ምስጉን የሆነውን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም ሁሉ አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደገና ማሰብ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ተሰኝቻለሁ፤ አጋጣሚዎች አልተመቻቹላችሁም እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለሚያስፈልገኝ ነገር እያማረርሁ አይደለም፤ ያለኝ ነገር ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ጥቂትም ማግኘትን አውቃለሁ፤ ብዙም ማግኘትን አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ የመጥገብንና የመራብን ብዙ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ! ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተባበረ እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ ከአንድ ጊዜ በላይ የሚያስፈልገኝን ነገር ልካችሁልኝ ነበርና። ከጥሪታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታን ፈላጊ አይደለሁም። ነገር ግን የሚያስፈልገኝን ሁሉ ተቀብያለሁ፤ ተትረፍርፎልኛልም፤ መዓዛው ያማረ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከኤጳፍሮዲጡስ ተቀብዬ በሁሉ ተሟልቶልኛል። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ያሟላላችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ወንድማችንም ጢሞቴዎስ፥ በቈላስይስ ለሚኖሩ ቅዱሳንና በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁን። ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ስለ ሰማን ነው፤ ይህም እምነትና ፍቅር በሰማይ በተዘጋጀላችሁ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነውና፤ ስለዚህም ተስፋ የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም ወንጌል ወደ እናንተ ደርሶአል፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ መካከል እንደ ሆነው እንዲሁ በመላው ዓለም ፍሬ ያፈራል፤ ያድጋልም። ይህንንም ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባርያ ከሆነው ከኤጳፍራ ተማራችሁ፤ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም በመንፈስ ስለ ሆነው ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል። እናንተም ከእርሱ ተለይታችሁና ክፉ በመሥራት በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በእርሱ ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ቅዱሳን አድርጎ ለማቅረብ በሥጋዊው አካሉ በሞቱ አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አካሉም ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ካለፈባቸው መከራዎች መካከል የጐደሉትን በሥጋዬ እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ሊያሳውቅ ወደደ፤ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ያለው ክርስቶስ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ሁሉንም ሰው ለማቅረብ ሁሉንም ሰው እየገሠጽንና ሁሉንም ሰው በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ ውስጥ በኃይል በሚያቀጣጥለው ጉልበት ሁሉ እየተጋደልሁ እደክማለሁ። ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም አይተውት ስለማያውቁት ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል እንደምጋደል እንድታውቁ እወዳለሁና፤ እንዲህም የምጋደለው ልባቸው እንዲጽናና፥ በፍቅርም በአንድነት እንዲተሳሰሩ፥ በፍጹም ማስተዋልም የሚገኘውን ባለጠግነት ሁሉ እንዲኖራቸው፥ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው፤ የጥበብና የእውቀት ሀብት ሁሉ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ዘንድ ነውና። ይህንንም የምለው ማንም አሳማኝ በሚመስል ንግግር እንዳያታልላችሁ ብዬ ነው። በአካል ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፤ መልካሙንም ሥነ ሥርዓታችሁንና በክርስቶስም ላይ ያላችሁን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል። እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ አብዝታችሁ ምስጋናን በማቅረብ እንደ ተማራችሁት ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፤ በእምነትም ጽኑ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ መሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ በፍልስፍናና በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሞታችሁ የነበራችሁትን በደላችንን ሁሉ ይቅር ባለን ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ እርሱም ይፃረረንና ይቃወመን የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ በመስቀልም ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ወደ ፊት ለሚመጡት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸውና፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። ራስን ማዋረድና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባየውም ራእይ ላይ በጽኑ እየተመረኮዘ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ የሚያድገውን አካል ሁሉ የሚንከባከበውን በመገጣጠምያዎቹና በጅማቶቹ አብሮ የሚያስተሳስረውን ራስ በጽኑ ሳይዝ ማንም አያውግዛችሁ። ከመሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዓይነት ኑሮ ለምን ትኖራላችሁ? ለምንስ እንደነዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ? እነርሱም፦ “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ትእዛዛት በጥቅም ላይ በመዋላቸው የሚጠፉትን ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው፤ እንዲያው በቀላሉ የሰው ትእዛዛትና አስተምሮ ናቸው። እነዚህም በገዛ ፈቃድ የሚደረግ አምልኮንና ራስን ማዋረድ ሥጋንም የመጨቆን ጥበብ ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅሙም። እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ በሰማይ ስላለው አስቡ እንጂ በምድር ስላለው አታስቡ። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በተገለጠ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በእናንተ ያሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ ስግብግብነት” ናቸው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም በቀድሞው ሕይወታችሁ ስትኖሩ እነዚህን ነገሮች በመተግበር ትመላለሱ ነበር። አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ አስወግዳችሁታልና እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ማንም ሰው በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ይቅር በሉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካል ሥር ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ውስጥ ገዢ ይሁን፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩም፤ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ዝማሬ በልባችሁ በማመስገን ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ሚስቶች ሆይ! በጌታ ዘንድ ተገቢ ስለ ሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ! ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ የምታማርሯቸውም አትሁኑ። ልጆች ሆይ! ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። አባቶች ሆይ! ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው። ባርያዎች ሆይ! ሰውን ደስ ለማሰኘት ስትሉ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፤ ነገር ግን በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ታዘዙ። ሥራችሁንም ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት እንዲሁ በትጋት ፈጽሙት፤ ይህንንም ስታደርጉ ከጌታ የርስትን ሽልማት እንደምትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው። የሚበድልም እንደ በደሉ መጠን ብድራቱን ይቀበላል፤ ለሰው ፊትም አድልዎ የለምና። ጌቶች ሆይ! እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና ባርያዎቻችሁን በጽድቅና በቅንነት ተመልከቱአቸው። ከማመስገን ጋር በጸሎት ውስጥ ነቅታችሁ ያለማቋረጥ ትጉ፤ የታሰርኩበት ምክንያት የሆነውን የክርስቶስን ምሥጢር ለማወጅ እግዚአብሔር ለቃሉ በር እንዲከፍትልን ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ቃሉንም መናገር እንደሚገባኝ ያህል ለመግለጥ እንድችል ጸልዩልኝ። ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ እንድታውቁ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባርያ የሆነ ቲኪቆስ እኔ ስላለሁበት ሁኔታ ሁሉ ይነግራችኋል፤ እርሱን ወደ እናንተ የላክሁበት ዋነኛ ዓላማ እኛ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ እንዲያሳውቃችሁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ነው፤ ቲቂቆስም ከእናንተ ወገን ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከኦኔሲሞስ ጋር አብሮ ይመጣል። በእዚህም ሥፍራ ስላለው ሁኔታ ሁሉ ያስታውቋችኋል። “ወደ እናንተ ቢመጣ፥ ተቀበሉት፤” የሚል ትእዛዝ የተቀበላችሁለት የበርናባስ የወንድሙ ልጅ ማርቆስ እንዳረገው እንዲሁ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ከተገረዙትም ወገን የሆኑ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እኔንም አጽናንተውኛል። ከእናንተ ወገን የሆነ የክርስቶስ ባርያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይተጋል። ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ በሥራ እንደደከመ እመሰክርለታለሁና። የተወደደው ሐኪም ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤትዋም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ይህም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበ በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንዲነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምታገኙትን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። ለአክሪጳም፦ “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ!” በሉልኝ። ይህን ሰላምታ እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ ጽፌዋለሁ። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ፥ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። በጸሎታችን ጊዜ ያለማቋረጥ እያነሣናችሁ ስለ ሁላችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሁልጊዜ እናቀርባለን፤ በእግዚአብሔር በአባታችን ፊት የእምነታችሁን ሥራ፥ የፍቅራችሁን ድካም፥ በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን የተስፋችሁንም መጽናት እናስታውሳለን። በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! በእርሱ መመረጣችሁን አውቀናል። ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ፥ በብዙም መረዳት እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ ስለ እናንተ ስንል በእናንተ መካከል ምን ዓይነት ሰዎች እንደ ነበርን እናንተው ታውቃላችሁ። ደግሞ እናንተ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ቃሉን በብዙ መከራ ተቀበላችሁ፥ በዚህም እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁ። ከእናንተ በመቄዶንያና በአካያ የጌታ ቃል ብቻ አልነበረም የተሰማው፥ ነገር ግን በሁሉ ስፍራ የተወራው በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነትም ጭምር ነበር እንጂ፤ ስለዚህም እኛ ምንም መናገር አያስፈልገንም። እነርሱ ራሳቸው ስለ እኛ በእናንተ መካከል ምን ዓይነት አቀባበል ተደርጎልን እንደ ነበር፥ ሕያውም የሆነውን እውነተኛ አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደተመለሳችሁ፥ እንዲሁም ከሚመጣው ቁጣ ያዳነንን ኢየሱስን፥ እርሱ ከሞት ያስነሣውን ልጁን፥ ከመንግሥተ ስማይ እንዴት እንደምትጠብቁ ይናገራሉ። ወንድሞች ሆይ! እናንተን መጎብኘታችን በከንቱ አልነበረም፥ እናንተም ራሳችሁ ታውቁታላችሁ። ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራንና እንግልትን ብንቀበልም እንኳ፥ በታላቅም ተቃውሞ ፊት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን ድፍረትን አገኘን። ምክራችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ከተንኰልም የመነጨ አልነበረምና፤ ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው። ወንድሞች ሆይ! ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሱታላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እየሰበክን በአንዳችሁም ላይ እንኳ ሸክም ላለመሆን ስንል ሌሊትና ቀን እንሠራ ነበር። በእናንተ በአማኞች መካከል እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ነበርን እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ አባት ለልጁ እንደሚሆነው እኛም እንዴት ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን እናንተው ታውቁታላችሁ፥ በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ እንድትመላለሱ እየመከርናችሁ፥ እያጸናናችሁና እየመሰከርንላችሁ ነበር። ስለዚህም የመልእክትን ቃል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በአማኞች ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከወገኖቻችሁ ተቀብላችኋልና። እነዚያም ጌታን ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም ደግሞ አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ ለአሕዛብ እንዳንናገር በመከልከል እነርሱ እንዳይድኑ ያደርጋሉ፤ በዚህም ያለማቋረጥ የኃጢአታቸውን መስፈርያ ይሞላሉ፤ ነገር ግን በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቁጣው ይመጣባቸዋል። እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ብናጣችሁም፥ በብዙ ናፍቆት ግን ፊታችሁን ለማየት እጅግ ጓጓን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ፈልገን ነበርና፤ በእርግጥም እኔ ጳውሎስ አንድና ሁለት ጊዜ ሞክሬ ነበር፥ ሰይጣን ግን መሰናክል ሆነብን። ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የተስፋችን ወይም የደስታችን ወይም የመመክያችን አክሊል ምንድነው? እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና። ስለዚህ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ። ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን፥ የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናወጥ፥ ለዚህ እንደ ተሾምን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንደምንቀበል አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፤ ይህንንም ታውቃላችሁ። ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ “ፈታኙ ምናልባት ፈትኖአቸዋል፤ ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፤” ብዬ በመፍራት እምነታችሁን ለማወቅ ጢሞቴዎስን ላክሁ። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ መልካም ዜና አመጣልን፤ እኛ እናንተን ለማየት እንደምንናፍቅ እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁና ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱን ደግሞ ነገረን፤ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና። በእናንተ የተነሣ በአምላካችን ፊት ለተደሰትነው ደስታ ሁሉ ስለ እናንተ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ምስጋና ልናቀርብ እንችላለን? ፊታችሁን ለማየትና በእምነታችሁ የጎደለውንም ለማሟላት ሌሊትና ቀን እጅግ አብዝተን እንጸልይ የለምን? አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ይምራ፤ ጌታ እንድትበዙ ያድርጋችሁ፤ እኛም ለእናንተ ፍቅርን እንዳበዛንላችሁ እንዲሁም የእርስ በርሳችሁንና ለሁሉ ሰው ያላችሁን ፍቅር ያብዛ። ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በአባታችንና በአምላካችን ፊት ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ በቅድስና ልባችሁን ያጽና። እንግዲህ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መመላለስ እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ ተቀብላችኋል፤ በእርግጥም እየተመላለሳችሁ ነው፤ ከዚህም በበለጠ አብዝታችሁ እንድታደርጉት በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችኋለንም። በጌታ በኢየሱስ ስም ምን ዓይነት መመሪያዎች እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፥ እርሱም መቀደሳችሁ፥ ከዝሙትም መራቃችሁ ነው፤ እያንዳንዳችሁም የራሳችሁን አካል በቅድስናና በክብር እንዴት መቆጣጠር እንደምትችሉ እወቁ፥ ይህን ስታደርጉ ግን እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት መሆን የለበትም፤ አስቀድመን ደግሞ እንደ ነገርናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና፥ ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ፤ ወንድሙንም አያታልል። ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። ስለዚህ ይህን የማይቀበል፥ የማይቀበለው፥ ሰውን ሳይሆን፥ ቅዱስ መንፈሱን ደግሞም የሰጠንን እግዚአብሔርን ነው። እናንተ ራሳችሁ የእርስ በእርስ መዋደድን በእግዚአብሔር ተምራችኋልና፥ ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ በእርግጥ በመላ መቄዶንያ ላሉት ወንድሞች ሁሉ እንዲሁ አድርጋችኋል። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! እነዚህን አብዝታችሁ እንድታደርጉ በጸጥታ ለመኖር እንድትተጉ፥ በራሳችሁም ጉዳይ ላይ እንድታተኩሩ፥ እንዳዘዝናችሁም በራሳችሁ እጅ እንድትሰሩ እንለምናችኋለን፤ በዚህም በማንም ላይ ሸክም እንዳትሆኑና በውጭ ባሉት ዘንድ በአግባብ እንድትመላለሱ ነው። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! አንቀላፍተው ስላሉት፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ልታዝኑ እንደማይገባ ልናሳውቃችሁ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም ደግሞ በኢየሱስ በኩል ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል። በጌታ ቃል ይህን እንላችኋለን፤ እኛ ሕያዋን የሆንነው፥ ጌታም እስኪመጣ ድረስ የምንቀረው ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ ቃል በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን የሆንነው፥ የቀረነውም ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በእነዚህ ቃላት ተጽናኑ። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ የሚመጣ መሆኑን እናንተው ራሳችሁ በጥንቃቄ አውቃችኋልና። እነርሱም፦ “ሰላምና ደኅንነት ነው” በሚሉ ጊዜ ምጥ እንደ ያዛት እርጉዝ ሴት ድንገተኛ ጥፋት በእነርሱ ላይ ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም። ወንድሞች ሆይ! እናንተ ግን ቀኑ እንደ ሌባ እንዳይመጣባችሁ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤ እናንተ ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፥ የቀንም ልጆች ናችሁና፤ ሆኖም እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም። እንግዲያስ እንንቃ፥ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን በመጠን እንኑር፤ የእምነትንና የፍቅርንም ጥሩር፥ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ፤ እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳንን እንድናገኝ እንጂ ለቁጣ እንድንሆን አስቀድሞ አልመረጠንም። የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንድንኖር ስለ እኛ ሞተ። ስለዚህ እናንተ በእርግጥ እያደረጋችሁት እንዳላችሁት፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ አንዱም ሌላውን ያንጸው። ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም እንድታውቁ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ እንድታከብሩአቸው እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። ወንድሞች ሆይ! እንመክራችኋለን፤ ሰነፎችን ገሥጹ፤ ፈሪዎችን አጽኑ፤ ደካሞችን እርዱ፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ እንዲሁም ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ። ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ ነገር አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና። መንፈስን አታዳፍኑ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካሙንም አጥብቃችሁ ያዙ፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። የሚጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። ወንድሞች ሆይ! ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ። ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። ይህ መልእክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ዐደራ እላችኋለሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! እምነታችሁ እጅግ አድጎአልና፥ የእናንተም የእያንዳንዳችሁ ሁሉ ፍቅር ለእርስ በርሳችሁ በዝቶአልና፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግዴታ አለብን፤ ስለዚህ በምትታገሱት መከራችሁና በስደታችሁ ሁሉ ስለ እናንተ መጽናትና እምነት እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት በእናንተ እንመካለን። ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ እንድትቆጠሩ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። በእርግጥ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ ነውና፥ መከራን የሚያደርሱባችሁን በመከራ ብድራታቸውን ይከፍላል። እንዲሁም እርሱ ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል በሚመጣበት ጊዜ መከራን ለተቀበላችሁት ከእኛ ጋር ዕረፍትን ይሰጣችኋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘለዓለም ጥፋት ይቀጣሉ። ይህም የሚሆነው ምስክርነታችን በእናንተ በመታመኑ የተነሣ ባመኑት ሁሉ ዘንድ ሊደነቅና፥ በቅዱሳኑም ሊከብር በሚመጣበት ጊዜ በዚያ ቀን ነው። አምላካችን ለጥሪው የተገባችሁ እንዲያደርጋችሁና በእርሱ ኃይል የመልካም ፈቃድ መሻትንና የእምነትን ሥራ እንዲፈጽም፥ ስለ እናንተ በዚህ ነገር ሁልጊዜ እንጸልያለን፤ በዚህም ምክንያት እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ፥ እናንተም በእርሱ እንድትከብሩ ነው። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ ከእኛ በሚመስል መልእክት ወይም በቃል ወይም በመንፈስ፦ “የጌታ ቀን መጥቷል፤” ብላችሁ አእምሮአችሁ በቀላሉ አይናወጥ አይደንግጥም። ማንም ሰው በማናቸውም መንገድ አያታልላችሁ፤ ከሐዲው አስቀድሞ ሳይመጣ የዓመፅም ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም ሰው የሚያመልከውን ነገር ወይም አማልክት ነን ከሚሉት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግና በመቃወም፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ያውጃል፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ይቀመጣል። ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? አሁን ምን እንደከለከለው አውቃችኋልና በራሱ ጊዜ የተገለጠ ይሆናል። አስቀድሞም የዓመፅ ሚስጢር በሥራ ላይ ነው፤ አሁን ግን እርሱ ብቻ ይከለክለዋል፤ እርሱም እንዲህ የሚያደርገው ከመንገድ እስከሚወገድ ድረስ ነው። በዚያም ጊዜ ዓመፀኛው ይገለጣል፤ ጌታ ኢየሱስም በአፉ እስትንፋስ ይገድለዋል፤ በመምጣቱም መገለጥ ያጠፋዋል፤ ዓመፀኛው ከሙሉ ኃይልና ምልክቶች፥ ከሐሰትም ተአምራቶች ጋር ሆኖ በሰይጣን አሠራር ይመጣል። እንዲሁም ለመዳን እውነቱን ወድደው ባለ መቀበላቸው ለሚጠፉት በማታለል ክፋት ሁሉ ይመጣባቸዋል። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የሐሰትን ኑፋቄ በመላክ በስሕተት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል። በዚህም እውነቱን ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ የሚሰኙ ሁሉ ይፈረድባቸዋል። በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከመጀመሪያው አንሥቶ በመንፈስ በመቀደስና በእውነት በማመን እንድትድኑ መርጦአችኋልና፤ ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ። ስለዚህም ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና፥ የወደደን በጸጋም የዘለዓለምን መጽናናትና መልካሙን ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናናው፥ በቃልና በመልካም ሥራ ሁሉ ያጽናላችሁም። በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል እንደ ሆነው ሁሉ የጌታ ቃል ፈጥኖ እንዲስፋፋና እንዲከበር ስለ እኛ ጸልዩ፤ እንዲሁም እምነት የምትገኘው በሁሉም ሰው ዘንድ አይደለምና ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን። ነገር ግን ጌታ የታመነ ነው፤ እርሱም ያጸናችኋል ከክፉውም ይጠብቃችኋል። የምናዛችሁን ነገሮች አሁንም ወደፊትም ደግሞ እንደምታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ እንመካባችኋለን። ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ክርስቶስ ትዕግሥት ልባችሁን ያቅናው። ወንድሞች ሆይ! ከእኛ እንደ ተቀበሉት ትውፊት ሳይሆን ሥራን በመፍታት ከሚኖሩ ወንድሞች ሁሉ እንድትለዩ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። ስለዚህም እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤ ከእናንተ ዘንድ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆንበት ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ የማንንም ሰው እንጀራ እንዲያው በነፃ አልበላንም። ይህም እኛን እንድትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ አድርገን ሰጠናችሁ እንጂ ሥልጣን ስላልነበረን አይደለም። እንዲሁም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “ማንም ሊሠራ የማይወድ አይብላ፤” ብለን አዘናችሁ ነበር። ይህም የሆነው ሥራ ፈትተው ሥራን ከቶ የማይሰሩ ይልቁንም በሰው ነገር ጣልቃ የሚገቡ አንዳንዶች በእናንተ መካከል እንደሚኖሩ ስለ ሰማን ነው። እንደነዚህ ያሉትንም ሥራቸውን በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም። እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ! መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። በዚህ መልእክት በኩል ለተላከው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ሰው በምልክት ለዩት፤ እንዲያፍርም ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቁጠሩት። የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። እኔ ጳውሎስ በራሴ እጅ ይህን ሰላምታ ጽፌአለሁ፤ ይህ በማንኛውም መልእክቴ ውስጥ የሚገኝ ምልክት ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። በአዳኛችን በእግዚአብሔር በተስፋችንም በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በምሄድ ጊዜ በኤፌሶን ተቀምጠህ አንዳንድ ሰዎች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩ፥ ራሳቸውንም በተረት፥ መጨረሻም በሌለው የትውልዶች ታሪክ እንዳይጠመዱ እንድታዝ ለመንሁህ፤ ሆኖም ግን እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ከንቱ ምርምር ያመጣሉ እንጂ በእምነት የሚገኝውን የእግዚአብሔርን መጋቢነት አይጠቅሙም። የትእዛዙ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ኅሊና፤ ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ፈቀቅ ብለው ወደ ከንቱ ንግግር በመሄድ፥ ምን እንደሚናገሩ ወይም በምን ዓይነት ነገሮች ላይ በድፍረት ማረገጋገጫ እንደሚሰጡ ሳያስተውሉ የሕግ አስተማሪዎች መሆንን ይፈልጋሉ። ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ ማንኛውም ሰው ለተጠቀመበት ሕግ መልካም እንደሆነ እናውቃለን፤ ይህንንም በመረዳት ሕግ የተሠራው ለጻድቃን ሳይሆን ይልቁንስ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዐመጸኞችና ለኀጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮች፥ ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለሐሰተኞችም፥ በውሸትም ለሚምሉና የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው። ይህም ትምህርት ለእኔ በአደራ ከተሰጠኝ ከብሩክ እግዚአብሔር ክቡር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው። ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ብርታት የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤ ይሁንና ከዚህ ቀደም ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም የነበርኩ ብሆንም እንኳ ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ፤ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት ከእምነትና ከፍቅር ጋር እጅጉን በዛልኝ። “ኀጢአተኞችን ለማዳን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤” የሚለው ቃል የታመነና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋነኛው እኔ ነኝ፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ዋነኛ በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ በማሳየት፥ በእርሱ አምነው የዘለዓለም ሕይወትን ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን አደረገኝ፥ በእዚህም ምክንያት ምሕረትን አገኘሁ። ለዘመናትም ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ብቻውን አምላክ ለሆነው መፈራትና ክብር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ የተነገረውን ትንቢት ሁሉ መሠረት በማድረግ፥ በእነርሱ መልካም ውጊያን እንድትዋጋ ይህችን ትእዛዝ በአደራ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህን በምታደርግበት ጊዜ ግን እምነትንና በጎ ኅሊናን ይዘህ ይሁን፤ አንዳንዶች ሕሊናን ወደ ጎን በማድረግ፥ በእምነት ረገድ በማዕበል እንደተሰባበረች መርከብ ጠፍተዋል፤ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ከእነዚህ መካከል ናቸው፤ እነርሱም እንዳይሳደቡ ለማስተማር ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ። እንግዲህ ከሁሉ በፊት እንዲደረጉ የምመክረው ነገር ቢኖር ልመናና ጸሎት፥ ምልጃና ምስጋና ስለ ሰዎች ሁሉ እንዲደረግ እመክራለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን በመምሰልና በተገባ አካሄድ ሁሉ፥ ጸጥታ የሰፈነበትና ሰላማዊ የሆነ ሕይወት እንዲኖረን ስለ ነገሥታትና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ስላሉ ሁሉ ጸሎት እናቅርብ። ይህም በአዳኛችን በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፤ እርሱም ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ ፈቃዱ የሆነ አምላክ ነው። አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል አንድ አስታራቂ ደግሞ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ሰጠ፤ ይህም ምስክርነት ተገቢ በሆነው በራሱ ጊዜ የቀረበ ነበር፤ እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ሆኜ ተሾምሁ፤ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም። እንግዲህ በሁሉ ስፍራ ያሉ ወንዶች ንዴትንና ጥልን አስወግደው የተቀደሱ እጆቻቸውን እያነሡ እንዲጸልዩ ፈቃዴ ነው። እንዲሁም ደግሞ ሴቶች ከትሕትናና ራስን ከመግዛት ጋር በሚገባ ልብስ ራሳቸውን ያስጊጡ፤ ይሁንና በቄንጠኛ የጸጉር አሠራር ወይም በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሁን። ይልቁንም እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉ ሴቶች እንደሚገባ መልካም ሥራን በመሥራት ይሁን። ሴት በሁሉ ነገር እየታዘዘች በጽሞና ትማር፤ ሴት ግን በዝምታ ልትሆን ይገባታል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም። አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። የተታለለም አዳም አይደለም፤ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች፤ ነገር ግን ያለማቋረጥ በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራስን ከመግዛት ጋር ብትኖር፥ ሴት ልጅ በመውለድ ትድናለች። “ማንም ኤጲስ ቆጶስነት ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል፤” የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ ነቀፋ የሌለበት፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ በመጠን የሚኖር፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ በሥርዓት የሚሠራ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ የማይሰክር፥ የማይቆጣ ነገር ግን ታጋሽ የሆነ፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ገንዘብን የማያፈቅር፥ ልጆቹን በሚገባ አካሄድ ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ነገር ግን ማንም ሰው የራሱን ቤት ማስተዳደር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? በትዕቢት ተወጥሮ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል። እንዲሁም ዲያቆናት መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፥ ቃላቸውን የማያጥፉ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ለገንዘብ የማይስገበገቡ፥ የእምነትን ምሥጢር በንጹሕ ኅሊና የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። እነዚህም ደግሞ በመጀመሪያ ይፈተኑ፤ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። እንዲሁም ሴቶች መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፥ ሐሜተኞች ያልሆኑ፥ በመጠን የሚኖሩ፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ዲያቆናት ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመልካም እያስተዳደሩ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው የተከበረ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ትልቅ መተማመንን ያገኛሉ። ፈጥኜ ወደ አንተ ለመምጣት ተስፋ በማድረግ ይህን ጽፌልሃለሁ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ብዘገይ ግን፥ በዚህ በጻፍሁልህ ትእዛዝ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ የእውነት ዓምድና መሠረት በሆነችው በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ እንድታውቅ ነው። የሃይማኖታችን ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱም፦ በሥጋ ተገለጠ፥ በመንፈስ ጸደቀ፥ ለመላእክት ታየ፥ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፥ በመላው ዓለም ታመነ፥ በክብር ዐረገ፥ የሚል ነው። መንፈስ ግን በግልጥ እንዲህ ይላል በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት ትኩረት በመስጠት እምነትን ይክዳሉ፤ ይህም ትምህርት ኅሊናቸውን በጋለ ብረት በማቃጠል አደንዝዘው ውሸትን በሚናገሩ ግብዞች በኩል የሚሰጥ ነው፤ እነርሱም መጋባትን ይከለክላሉ፤ አምነውም እውነትን ላወቁት፥ ከምስጋና ጋር እግዚአብሔር የፈጠረውን ምግብ ከመቀበል እንዲቆጠቡ ያዝዛሉ። ዳሩ ግን እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ በምስጋናም ከተቀበሉት ምንም የሚጣል ነገር የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። ይህን ትእዛዝ ለወንድሞች ብታሳውቅ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃላት እየተመገብክ ያደግህ፥ የክርስቶስ ኢየሱስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። ነገር ግን ከረከሰው ከዚህ ዓለም አፈ ታሪክና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አለማምድ። ሰውነትን አካላዊ እንቅስቃሴ ማለማመድ መጠነኛ ጠቀሜታ ቢኖረውም እንኳ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣውን ሕይወት የተስፋ ቃል ስላለው፥ ለሁሉ ነገር ይጠቅማል። ይህ ቃል የታመነና ሁሉ ሰው ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ለዚህም እንደክማለን እንታገላለንም፤ ምክንያቱም ሰውን ሁሉ በተለይም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስላደረግን ነው። እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም፤ ማንም ወጣትነትህን አይናቀው፤ ይልቅስ በንግግር፥ በኑሮ፥ በፍቅር፥ በእምነት፥ በንጽሕና፥ ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን። እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝቡ በማንበብ፥ በመምከርና በማስተማር ትጋ። ሽማግሌዎች እጃቸውን በአንተ ላይ የጫኑ ጊዜ በትንቢት የተሰጠህን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። እድገትህ በሁሉ ሰው ፊት እንዲገለጥ እነዚህን ነገሮች በጥንቃቄ በሥራ ላይ አውል፤ ለእነርሱም ራስህን ሙሉ በሙሉ በመስጠት ትጋ። ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ነገሮች ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ። ሽማግሌን እንደ አባት አድርገህ ምከር እንጂ አትገሥጽ፤ እንዲሁም ጎልማሶችን እንደ ወንድሞች፥ አሮጊቶችን እንደ እናቶች፥ ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከት። በእርግጥ ረዳት የሌላቸውን መበለታትን ተንከባከብ። ማንም መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መፈጸምን ይማሩ፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ ነውና። በእርግጥ መበለት የሆነችና ያለረዳት ለብቻዋ የተተወች፥ ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ለዚህ ዓለም ደስታ የምትኖር መበለት ግን በሕይወትዋ ሳለች እንኳ የሞተች ናት። ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ እነዚህን ነገሮች ደግሞ እዘዝ። ማንም ቢሆን ግን ለገዛ ዘመዶቹ በተለይም ለቤተ ሰቡ አባላት የማያስብ ከሆነ፥ እምነትን የካደና ከማያምን ሰው ይልቅ የባሰ ነው። መበለቲቱ ከስልሳ ዓመት በታች ያልሆነች፤ የአንድም ባል ሚስት የነበረች በመዝገብ ትጻፍ፤ እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ፥ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት፥ በበጎም ሥራ ሁሉ በመትጋት፥ በመልካም ሥራዎችዋ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። ወጣት መበለታትን ግን በመዝገብ ላይ አታካትት፤ ሥጋዊ ምኞታቸው ከክርስቶስ ስለሚለያቸው መጋባትን ይፈልጋሉና፤ በዚህም በመጀመሪያ የገቡትን ቃል በማፍረሳቸው ምክንያት በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፤ ከዚህም ጎን ለጎን ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራ መፍታትን ይማራሉ፤ ሥራ ፈቶችም ብቻ ሳይሆኑ የማይገባቸውን እየተናገሩ ሰውን የሚያሙና በነገር ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ። እንግዲህ ወጣት መበለታት እንዲያገቡ፥ ልጆችንም እንዲወልዱ፥ እያንዳንዳቸውም ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስተዳድሩ እፈቅዳለሁ፤ በዚህም ተቃዋሚ የሚሳደብበትን ምንም ዓይነት ሰበብ እንዳይሰጡት ነው፤ ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን ለመከተል መንገድን ስተው ሄደዋልና። አማኝ የሆነች ማንም ሴት መበለታት ዘመዶች ቢኖሩአት፥ እነርሱን ትርዳቸው፤ ቤተክርስትያንም በእርግጥ እርዳታ የሚያሻቸውን መበለታትን መርዳት እንድትችል ሸክም አይሁኑባት። በመልካም የሚያስተዳድሩ፥ በተለይም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ ሽማግሌዎች፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። ቅዱስ መጽሐፍ፦ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል፤” ይላል። በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጽ። አንዱን ከሌላው በማበላለጥ ምንም ዓይነት ነገር ሳታደርግ፥ ያለ አድልዎ እነዚህን ትዛዛቶች እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ በተመረጡትም መላእክት ፊት አደራ እልሃለሁ። በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፤ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። ስለ ሆድህና በተደጋጋሚ ስለሚያጠቃህ በሽታ ስትል ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ በመሆኑ አስቀድሞ ፍርድን ያመለክታል፤ የሌሎች ግን የሚገለጠው ዘግየት ብሎ ነው፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፤ ያልተገለጠም ከሆነ እንኳ ተሰውሮ መቅረት አይችልም። የእግዚአብሔር ስምና ትምህርት እንዳይሰደብ፥ በቀንበር ሥር ያሉ ባርያዎች ሁሉ ጌቶቻቸውን ታላቅ ክብር እንደሚገባቸው አድርገው ይቁጠሩአቸው። የሚያምኑም ጌቶች ያሉአቸው፥ ወንድሞች ስለ ሆኑ አይናቋቸው፤ ይልቁንስ ከበፊት ይልቅ ያገልግሏቸው ምክንያቱም በመልካም ሥራቸው የሚጠቀሙት አማኞችና ወዳጆቻቸው ናቸውና። እነዚህን ነገርች አስተምርና ምከር። ማንም ሰው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከታመኑ ቃላት ጋራ የማይስማማና እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ መሠረት ካደረገው ትምህርት ጋር የማይጣጣም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከሆነ፥ በትዕቢት የተወጠረና ምንም የማያውቅ ነው፤ ነገር ግን የንትርክና በቃላት የመከራከር ለየት ያለ ክፉ ምኞት አለበት፤ እነዚህም ነገሮች የሚያመጡት ቅንዓትን፥ መከፋፈልን፥ ስድብን፥ ክፉ ጥርጣሬን፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ ሰዎች መካከል የማያቋርጥ ጭቅጭቅን ነው፤ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን መምሰል ሀብት ማግኛ ዘዴ መስሎ ይታያቸዋል። ነገር ግን ከሃይማኖት ጋር ያለኝ ይበቃኛል ማለት ትልቅ ጥቅም የሚያስገኘ ነው፤ ወደዚህ ዓለም ምንም ይዘን አልመጣንምና፥ ከዚህም ዓለም ይዘነው የምንሄደው ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን ምግብና ልብስ ካሉን እነዚህ ይበቁናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ለመሆን የሚፈልጉ በፈተናና በወጥመድ፥ ሰዎችንም በጉስቁልናና በጥፋት ወስጥ በሚያሰጥሙአቸው ከንቱና ጎጂ በሆኑ በብዙ ምኞቶች ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፤ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከእምነት ፈቀቅ በማለት መንገዳቸውን ስተው ሄደዋል፥ በብዙም ሥቃይ ራሳቸውን ወግተዋል። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ፤ ጽድቅን፥ እግዚአብሔርን መምሰልን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ መጽናትን፥ የዋህነትን ግን ተከተል። መልካሙን የእምነት ውጊያ ተዋጋ፤ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የመሰከርህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ። ለሁሉ ነገር ሕይወት በሚሰጠው በእግዚአብሔርና በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ይህን ትእዛዝ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ጠብቅ፤ የተባረከና ብቻውን ገዢ የሆነ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ይህን ነገር ተገቢ በሆነው በራሱ ጊዜ ይገልጠዋል። እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ እርሱን ከቶ ማንም አላየውም፤ ማንም ሊያየውም አይችልም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤ አሜን። በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ በሚያልፍም ባለጠግነት ላይ ሳይሆን እንድንደሰትበት ሁሉን አትረፍርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ እዘዛቸው። መልካምን ያድርጉ፥ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች በመሆን ለመለገስና ለማካፈል የተዘጋጁ ይሁኑ፤ በዚህ ዓይነት እውነተኛውን ሕይወት እንዲይዙ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ ያከማቻሉ። ጢሞቴዎስ ሆይ! በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት አለን በማለት የእምነትን መንገድ ስተዋል። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን። በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው የሕይወት ተስፋ መሠረት በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፤ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ያለማቋረጥ ሌሊትና ቀን በጸሎቴ አንተን በማስታወስ፥ አባቶቼ እንዳደረጉት በንጹሕ ኅሊና የማገለግለውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በደስታ እንድሞላ እንባህን እያስታወስኩ ላይህ እናፍቃለሁ። በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስታውሳለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድና በእናትህ በኤውንቄ የነበረ ነው፤ አሁን ደግሞ በአንተ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። በዚህም ምክንያት እጆቼን ስጭን የተሰጠህን በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ። እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። እንግዲህ ስለ ጌታችን ምስክርነት በመስጠት ወይም ስለ እርሱ በታሰርሁ በእኔ አትፈር ይልቁንም እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል። እንደ ሥራችን መጠን ሳይሆን እንደ ራሱ ዕቅድና እንደ ጸጋው መጠን አዳነን፥ በቅዱስም አጠራር ጠራን፤ ይህም ጸጋ ከዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤ አሁን ግን በወንጌል አማካይነት ሞትን በሻረው፥ ሕይወትንና ያለመበስበስን ወደ ብርሃን ባመጣው በአዳኛችን በክርስቶስ ኢየሱስ መገለጥ በኩል ተገለጠ። እኔም ለዚህ ወንጌል ሰባኪና ሐዋርያ አስተማሪም ሆኜ ተሾምሁ፤ በዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ እቀበላለሁ፤ ነገር ግን ያመንኩትን አውቃለሁና አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ለመጠበቅ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር ከእኔ የሰማኸውን እውነተኛ ቃላት ምሳሌ አድርገህ ያዝ፤ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ መልካሙን አደራ ጠብቅ። በእስያ ያሉት ሁሉ ከእኔ ዘወር ብለው እንደ ሄዱ ታውቃለህ፤ ከእነርሱም መካከል ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ይገኛሉ። ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተሰብ ምሕረትን ይስጥ፤ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፤ ነገር ግን ወደ ሮም በመጣ ጊዜ በትጋት ፈልጎ አገኘኝ፤ በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም ያከናወነውን አገልግሎት ሁሉ አንተ ደኅና አድርገህ ታውቃለህ። እንግዲህ ልጄ ሆይ! አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ታማኝ ለሆኑ ሌሎችንም ደግሞ ማስተማር ለሚችሉ ሰዎች አደራ ስጥ። እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ መልካም ወታደር ሆነህ መከራን ተቀበል። በማገልገል ላይ ያለ ማንም ወታደር፥ ዐላማው ለወታደርነት የመለመለውን ሰው ለማስደሰት እስከሆነ ድረስ፥ እንደ ማናቸውም ሰው በዕለት ተዕለት ጉዳዮች አይጠመድም። እንዲሁም ደግሞ ማንም ሯጭ ውድድሩን እንደ ሕጉ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። በርትቶ ለሚሠራው ገበሬ የፍሬው የመጀመሪያ ድርሻ ለእርሱ ሊሆን ይገባዋል። ጌታ በሁሉ ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና የምለውን ደኅና አድርገህ አሰላስል። በወንጌል የምሰብከውን፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ። ለዚህም ወንጌል ስል መከራን እቀበላለሁ፥ እንደ ወንጀለኛም በሰንሰለት እስከመታሰር ደርሻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሰሱስ ያለውን መዳን ከዘለዓለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስል ስለ ተመረጡት ደግሞ ሁሉን ነገር እታገሣለሁ። እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፦ “ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ እኛ ታማኝ ባንሆን፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” ይህን አሳስብ፤ እንዲሁም በቃላት እንዳይከራከሩ በእግዚአብሔር ፊት እዘዝ፤ ይህ የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ምንም ጥቅም የለውምና። የእውነትን ቃል በትክክለኛው መንገድ እየገለጥህ፥ የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ፥ ለእግዚአብሔር ብቁ ተደርገህ ራስህን ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጣር። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ምክንያቱም ሰዎችን ከፊት ይልቅ ወደ ኃጢአት ይመራልና፤ ቃላቸውም እንደ ቈላ ቊስል ይባላል፤ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ከእነርሱ መካከል ናቸው፤ እነዚህም፦ “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል፤” እያሉ በእውነት ነገር ስተው ሄደዋል፤ የአንዳንዶችንም እምነት አጥፍተዋል። ሆኖም የእግዚአብሔር ጠንካራ መሠረት የቆመው፦ “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለውን ማኅተም ታትሞ ነው። በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእንጨትና የሸክላ ዕቃዎችም ደግሞ ይኖራሉ፤ እኩሌቶቹም ለክብር፥ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ለውርደት ከሚሆነው ነገር ራሱን ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰ፥ ለጌታውም የሚጠቅም፥ ለመልካምም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ጠብንም እንደሚያመጡ ታውቃለህና ከሞኝነትና ከከንቱ ንትርክ ራቅ። የጌታም ባርያ ጠበኛ መሆን አይገባውም፤ ይልቁንስ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ ትዕግሥተኛና የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚገሥጽ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህም የተነሣ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓ ገብተው እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፥ እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ታስረው ከተያዙበት ከዲያብሎስ ወጥመድ ወጥተው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋልና። ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያስጨንቁ ጊዜያት እንደሚመጡ ይህን እወቅ። ሰዎች እንዲህ ይሆናሉና፤ ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብን ወዳጆች፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይቈጣጠሩ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተወጠሩ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፥ የሃይማኖትን መልክ የያዙ ነገር ግን ኃይሉን የካዱ ሆነው ይገኛሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። ከእነርሱም መካከል በየቤቱ እየተሽሎኮሎኩ በመግባት የኃጢአታቸው ሸክም የከበደባቸውንና በልዩ ልዩ ምኞትም ውስጥ የሚዋዠቁትን ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ይገኙባቸዋል። እንዲህ ያሉት ሴቶች ግን ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉ ናቸው። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው በእምነትም ረገድ ተፈትነው የወደቁ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን እነዚያ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑት እንዲሁ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት ለሁሉም ሰው ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን ዓላማዬንም፥ እምነቴንም፥ ትዕግሥቴንም፥ ፍቅሬንም፥ መጽናቴንም፥ ስደቴንም፥ መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የደረሰብኝን ነገርና የታገሥሁትን ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከሁሉም አዳነኝ። በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ለመኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አስመሳዮች እያታለሉና እየተታለሉ ከክፋት ወደ ባሰ ክፋት ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርህበትና በጽኑ ባመንኸበት ነገር ሳትናወጥ ኑር፤ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ እንዲሁም ከሕፃንነትህ አንሥቶ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ወደሚገኘው መዳን የሚመራህን ጥበብ ሊሰጡህ የሚያስችሉትን ቅዱስ መጻሕፍትን አውቀሃልና። ቅዱስ መጸሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ አነሣሽነት የተገለጠ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማርና ለመገሠጽ፥ ስሕተትንም ለማረም፥ ሰውንም በጽድቅ መንገድ ለማለማመድ ያገለግላል፤ በዚህም የእግዚአብሔር ሰው በችሎታው ፍጹም እንዲሆንና ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ይጠቅማል። በእግዚአብሔር ፊት፥ በሕያዋንና በሙታንም ላይ በሚፈርደው በጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም አጥብቄ አዝዝሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ተግተህ ሥራ፤ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ፤ ምከርም። ሰዎች እውነተኛውን ትምህርት የማይታገሱበት፤ ይልቁንም ጆሮዎቻቸውን የሚኮረኩራቸውን ነገር በመሻት ለራሳቸው ምኞት የሚመቹ አስተማሪዎችን የሚሰበስቡበት ጊዜ ይመጣልና። ከቶም እውነትን ከመስማት ጆሮዎቻቸውን ይመልሳሉ፤ መንገድንም ስተው ወደ ተረት ፈቀቅ ይላሉ። አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን በትዕግስት ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አከናውን፤ አገልግሎትህን ሙሉ ለሙሉ ፈጽም። እንደ መጠጥ ቁርባን በመፍሰስ እኔም መሥዋዕት የምሆንበት ጊዜ አሁን ደርሶአል፤ የምሄድበትም ጊዜ ቀርቡዋል። መልካሙን ውጊያ ተዋግቻለሁ፤ የሩጫውን ውድድር ጨርሼአለሁ፤ እምነትን ጠብቄአለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ጻድቅ ፈራጅ የሆነ ጌታ በዚያ ቀን ሊሸልመኝ የጽድቅ አክሊል አዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን መገለጡን በፍቅር ለናፈቁት ሁሉ ነው። በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ የተቻለህን ሁሉ ጣር፤ ዴማስ የአሁንዋን ይህችን ዓለም ወድዶ ትቶኛል፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል። ቀርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል። ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው፤ ማርቆስን ከአንተ ጋር ይዘኸው ና፥ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና። ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት። ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱን እንዲሁም መጻሕፍቱን በተለይም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ። የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ክፉ ነገሮችን አድርጎብኛል፤ ጌታ እንደ ሥራው ብድራቱን ይከፍለዋል። አንተም ደግሞ ከእርሱ ነቅተህ ራስህን ጠብቅ፤ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና። በመጀመሪያው ሙግቴ አንድም ሰው እንኳ ከጎኔ አልቆመም፤ ሁሉም ግን ከዱኝ፤ ይህንንም በደል በእነርሱ ላይ አይቁጠርባቸው፤ ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ከእኔ ጎን ጌታ ቆመ አበረታኝም፤ ከአንበሳም አፍ ዳንሁ። ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ እርሱም ለሰማያዊው መንግሥቱ እንድሆን ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተሰቦች ሰላምታ አቅርብልኝ። ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፤ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውኩት። ከክረምት በፊት እንድትመጣ የተቻለህን ሁሉ ጣር። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ጌታ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። የእግዚአብሔር ባርያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔርም የተመረጡት ያላቸውን እምነትና እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የተመሠረተውን የእውነት እውቀት ለማስፋፋት፥ ከቶውኑ የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ቃል በገባው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ያደረገ፤ ተገቢም በሆነው በራሱ ጊዜ፥ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት አማካይነት ቃሉን ገለጠ፤ የጋራ በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆንከው ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከአዳኛችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይሁን። የተቀረውን ሥራ እንድታቃናና በየከተማው እኔ እንዳዘዝሁህ ሽማግሌዎችን እንድትሾም፥ አንተን በዚህ ምክንያት በቀርጤስ ተውሁህ፤ ነቀፋ የሌለበትና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ በመዳራትም ወይም ባለመታዘዝ የማይከሰሱ አማኝ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስ ቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ ነቀፋ የሌለበት ሊሆን ይገባዋል፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚቈጣጠር ይሁን፤ እውነተኛውንም ትምህርት ለመምከርና ተቃዋሚዎቹን ለመገሠጽ እንዲችል፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። የማይታዘዙና ከንቱ ነገርን የሚያወሩ የሚያታልሉ በተለይም ከተገረዙት ወገን የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ እነዚህም ማስተማር የማይገባቸውን በማጭበርበር የሚገኘውን ጥቅም እያስተማሩ ቤተሰቦችን በሞላ አውከዋልና፥ እነርሱን ዝም ማሰኘት ይገባል። ከእነርሱ አንዱ የሆነው የገዛ ራሳቸው ነቢይ፦ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፥ ክፉ አውሬዎች፥ ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው፤” ብሏል። ይህ ምስክርነት እውነት ነው። በዚህም ምክንያት እነርሱን አጥብቀህ ገሥጽ፤ ይህን የምታደርገው በእምነት ረገድ እንዲጸኑና በአይሁድ ተረቶችና እውነትን በማይቀበሉ በሰዎች ትእዛዛት እንዳይጠመዱ ነው። ለንጹሖች ሁሉ ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ነገር ምንም የለም፤ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሆነ ኅሊናቸው ረክሶአል። እግዚአብሔርን እንደሚያውቁ በግልጥ ይናገራሉ ዳሩ ግን በሥራቸው ይክዱታል፤ የሚያጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ ብቁ ያልሆኑ ናቸው። አንተ ግን ከእውነተኛ አስተምሮ ጋር የሚጣጣመውን ነገር አስተምር። ሽማግሌዎች በመጠን የሚኖሩ፥ ክብራቸውን የሚጠብቁ፥ ራሳቸውን የሚቈጣጠሩ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም በእውነት የጸኑ እንዲሆኑ ምከራቸው፤ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሴቶች በመልካም ጠባያቸው የተቀደሱ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ ያልተገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ እንዲሆኑ ንገራቸው፤ እነርሱም ወጣት ሴቶችን ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወድዱ ያስተምሩአቸው፤ እንዲሁም በእነርሱ አማካይነት የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ ራሳቸውን የሚቈጣጠሩ፥ ንጹሖች፥ በቤታቸው ውስጥ ሥራቸውን በደንብ የሚያከናውኑ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው። ጐልማሶችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲቈጣጠሩ ምከራቸው። በነገር ሁሉ የመልካም ሥራ ምሳሌ በመሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ጽኑ እውነትንና ቅንነትን ግለጥ፤ የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር እውነተኛና የማይነቀፍ ቃልን ተናገር። ባርያዎች ለገዛ ጌቶቻቸው እንዲገዙና በነገር ሁሉ ደስ እንዲያሰኙአቸው ንገራቸው፤ እንዲሁም ሳይቃወሙና ሳይሰርቁ በጎ ታማኝነትን ሁሉ እያሳዩ ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር እንዲያስመሰግኑ ምከራቸው። ሰዎችን ሁሉ የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኀጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን ራሳችንን በመቈጣጠርና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ይመክረናል፤ እንዲሁም የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እንድንጠብቅ ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከኃጢአት ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ይህንንም በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር፤ ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ። ለገዢዎችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። እንዲሁም ማንንም የማይሰድቡ፥ ጠበኛ ያልሆኑ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ በጽኑ አስገንዝባቸው። እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባርያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት ጊዜያችንን የምናሳልፍ፥ የምንጠላ፥ እርስ በርሳችንም የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እኛ በጽድቅ በሠራናቸው ሥራዎች ሳይሆን እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እኛን አዳነን፤ ይህንንም መንፈስ፥ በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ በዚህም በጸጋው ጸድቀን በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች ለመሆን በቅተናል። ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲተጉ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤ ነገር ግን ሞኝነት ካለው ውዝግብና ከትውልዶች ታሪክ ከመከፋፈልም ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤ መለያየትን የሚያሥነሣ ሰው አንዴና ሁለቴ ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጠማማና ኃጢአተኛ በመሆኑ በራሱ ላይ እንደፈረደ አውቀሃልና። አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ ስልክ፥ ወደ ኒቆጵልዮን ወደ እኔ እንድትመጣ የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ እኔ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። ሕግ አዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን ምንም እንዳይጎድልባቸው በጉዞአቸው ተግተህ እርዳ። ከእኛም ወገን የሆኑ ሰዎች ደግሞ ፍሬ ቢሶች ሆነው እንዳይቀሩ፥ የግድ ስለሚያስፈልገው ነገር መልካም ሥራን ተግተው መሥራትን ይማሩ። ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። በእምነት ለሚወዱን ሰላምታ አቅርብልን። ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ከሆነው ጳውሎስና ከወንድሙ ጢሞቴዎስ፥ ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነው ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በጸሎቴ እያሰብኩህ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ። በጌታ በኢየሱስ ዘንድ፤ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለው ፍቅርህና እምነትህ እሰማለሁና። የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ ኦኔሲሞስ እለምንሃለሁ፤ በፊት አልጠቀመህም ነበር፤ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም በጣም እየጠቀመን ነው። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበለው። እኔስ ስለ ወንጌል በገጠመኝ እስራት አንተን ወክሎ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው በፈቅድኩ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም ነገር ላደርግ አልፈልግሁም። ዳግመኛ ተቀብለህ ለዘለዓለም እንድትይዘው ይሆናል ምናልባት ለጊዜው የተለየህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባርያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም ሆነ በጌታ ዘንድ ከባርያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? እንግዲህ እንደ ወንድምህ እስከ ቆጠርከኝ ድረስ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር በድሎህ እንደሆነ ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር፤ እኔ ጳውሎስ “እኔ እመልሰዋለሁ፤” ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አላስታውስህም። አዎን፥ ወንድሜ ሆይ! በጌታ ይህንን ጉዳይ ፈጽምልኝ። በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። ከምጠይቅህ ይልቅ አብልጠህ እንደምታደርግ በማወቅ እንደምትታዘዝም በመተማመን እጽፍልሃለሁ። ደግሞ ከዚህም ጋር የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ፤ በጸሎታችሁ ለእናንተ እንደምሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና። በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ አብረውኝም የሚሠሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በብዙ እና በልዩ ልዩ መንገዶች ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ግን፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን፥፥ እርሱም የክብሩ ጸዳልና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኀጢአታችንን ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የላቀ ስምን በተቀበለ መጠን፥ እንደዚሁ ከእነርሱ እጅግ ልቆ ይበልጣል። ከመላእክትስ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ደግሞም “እኔ አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤” ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም የበኲር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ፤” ይላል። ስለ መላእክትም “መላእክቱን ነፋሳት፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ” ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፥ “አምላክ ሆይ! ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የጽድቅ በትር የመንግሥትህ በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ፤” ይላል። እናም፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም፤” ነገር ግን ከመላእክት፥ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤” ከቶ ለማን ብሎአል? ታዲያ፥ መላእክት ሁሉ መዳንን ስለሚቀበሉ ሰዎች፥ ለአገልግሎት የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን? ስለዚህ ከሰማነው ነገር ተንሸራትተን እንዳንወድቅ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባል። በመላእክት የተነገረው ቃል በጽናት ከተረጋገጠ፥ እያንዳንዱም መተላለፍ ወይም አለመታዘዝ ትክክለኛውን ቅጣት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ ይህንኑ አረጋግጠውልናል። እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት። ስለ እርሱ የምንናገርለት፥ የሚመጣውን ዓለም ያስገዛው ለመላእክት አይደለምና። እንዲያውም በአንድ ስፍራ እንዲህ ተብሎ ተመስክሯል፦ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ወይስ ትጠነቀቅለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንክለት፤ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምከው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፤” ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አላየንም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሁላችን ሞትን እንዲቀምስ፥ ከመላእክት ለጥቂት ጊዜ ዝቅ ብሎ የነበረውን፥ የሞትን መከራ በመቀበሉ ምክንያት የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖ ኢየሱስን እናየዋለን። ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ፥ ሁሉ ነገር በእርሱና ለእርሱ የተፈጠረው፥ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ተገብቷልና። የሚቀድሰውና በእርሱም የተቀደሱት ሁሉ መገኛቸው ከአንድ ነውና፤ ከዚህ የተነሣ ወንድሞች ብሎ ሲጠራቸው አያፍርም፤ እንዲህም በማለት፥ “ስምህን ለወንድሞቼ አበሥራለሁ፤ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤” እንዲሁም፥ “እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤” ደግሞም “እነሆኝ እኔ፥ እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች” ይላል። እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፥ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ እርሱም ዲያብሎስ ነው። በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ታስረው የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንጂ ትኩረቱ ለመላእክት አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። ምክንያቱም እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል። ስለዚህ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ! የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ። ቤትን የሚሠራው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው ሁሉ፥ እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሮአልና። ለእያንዳንዱ ቤት ሠሪ አለው፤ ሁሉን የሠራ ግን እግዚአብሔር ነው። ሙሴም ወደ ፊት መባል ለሚገባው ነገር ለመመስከር፥ እንደ አገልጋይ በመላው በእግዚአብሔር ቤት ታማኝ ነበር፤ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፥፥ እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጽንተን ስንይዝ፥ ቤቱ ነን። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚለው፥ ዛሬ ድምፁን ስትሰሙት፥ በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማመጽ እንደ ሆነው፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። አባቶቻችሁ እኔን ፈተኑ፥ ሥራዬን አዩ፥ ለአርባ ዓመታት፤ ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ “ዘወትር በልባቸው ይስታሉ፤ መንገዴን ግን አላወቁም፤” አልኩ፤ በቍጣም እንደ ማልሁ፥ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም፥” ወንድሞች ሆይ! ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ በኃጢአት ተታሎ ልቡን እምቢተኛ እንዳያደርግ፥ “ዛሬ” ተብሎ የተጠራው ጊዜ እስካለ ድረስ፥ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ። የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤ “ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” እንደተባለው ነው። ሰምተው ያመጹት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትስ የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በስተቀር፥ ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? እንግዲህ ባለማመናቸው ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን። ስለዚህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ገና ተስፋ ቀርቶልን ከሆነ፥ ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንጠንቀቅ። የምሥራቹ ዜና ለእነርሱም እንደ ተነገረ ለእኛ ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም “እንዲህ ‘ወደ ዕረፍቴ አይገቡም፤’ ብዬ በቁጣዬ ማልሁ፤” እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ፥ “እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፤” ብሎአልና፤ በዚህ ስፍራም ደግሞ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም፤” ይላል፥፥ ቀደም ብሎ የምሥራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ምክንያት ስላልገቡ፥ እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ተጠብቆላቸዋል፥ ይህም አስቀድሞ እንደተባለው፥ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር “ዛሬ” ብሎ አንድ ቀን እንደገና ይቀጥራል። ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም አሳብና ትኩረት ይመረምራል፤ በፊቱም የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም፤ እኛ መልስ መስጠት በሚገባን ከእርሱ ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና ዕርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው። እንግዲህ በሰማያት የወጣ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። እኛ ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የሚችል ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር እንደ እኛ ተፈተነ፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ፥ ጸጋው ወደሚገኝበት በመታመን እንቅረብ። ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኅጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚሳሳቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ካልተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ “አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል። እርሱም ሥጋ ለብሶ በምድር በሚመላለስ ጊዜ፥ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል፥ ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ስለ ጻድቅ ፍርሃቱም ጸሎቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘለዓለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። በእግዚአብሔርም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ተጠራ። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ለማድመጥ በድንዛዜ ላይ ስለ ሆናችሁ፥ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። እስከ አሁን በነበረው ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ እንደገና የእግዚአብሔር ቃላት የመጀመሪያውን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም፤ ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ብስለት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የክርስቶስን የመጀመሪያ ትምህርት አልፈን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሓና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ነው። እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል!? አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸው፥ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩ፥ መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና መጪውንም የዓለም ኃይል የቀመሱ፥ ከዚህ ሁሉ በኋላ ቢክዱ፥ እነርሱ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደገና ስለሚሰቅሉትና ስለሚያዋርዱት፥ አይቻልም። ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ እሾህና ኩርንችትን ግን ብታወጣ፥ ጥቅም አይኖራትም፤ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። ስለ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ምንም እንኳ እንዲህ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንደሚሆንላችሁ እርግጠኝነት ይሰማናል። እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና። እናንተም ሁላችሁ በተስፋ የምትጠባበቁትን ነገር እስክትጨብጡ ድረስ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፤ ያም በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አይደለም። እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፥ የሚምልበት ከእርሱ የበለጠ ሌላ ማንም ስለ ሌለ በራሱ ማለ፤ እንዲህ ሲል፥ “በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፤ ማብዛትንም አበዛሃለሁ፤” እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ። ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉ፤ ንግግራቸውንም በመሐላ በማጽናት የክርክር ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ ይሄውም እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንዲሆንልን ነው። ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን፤ እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው፤ በዚያም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ። የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ይህ መልከጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ ለእርሱም አብርሃም ከሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፥፥ የስሙ ትርጓሜ በመጀመሪያ፥ የጽድቅ ንጉሥ ነው፤ ከዚያ ደግሞ፥ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ሐረግም የሉትም፤ ለዘመኑም መጀመሪያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደሆነ እስቲ ተመልከቱ! የአባቶች አለቃ የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር አሥራት አውጥቶ ሰጠው። ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነዚያ ክህነትን የሚቀበሉት የሌዊ ልጆች ከሕዝቡ ማለትም ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ አሥራትን እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል። ይህ ሰው ምንም ትውልዱ ከእነርሱ ባይቆጠርም እንኳ ከአብርሃም አሥራትን ተቀብሏል፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባርኮአል። ታናሹ በታላቁ እንደሚባረክ ምንም ጥርጥር የሌለውም። በዚህ በኩል የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ይቀበላሉ፤ በዚያ በኩል የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። በመሆኑም አሥራትን የሚቀበለው ሌዊ ራሱ እንኳን፥ በአብርሃም በኩል አሥራትን ሰጥቶአል፥ ማለት ያስችላል፤ ምክንያቱም መልከጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበር። እንግዲህ በሌዊ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ከሆነ፥ ሕዝቡ በዚያ ላይ የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና፤ ወደ ፊት እንደ አሮን ሹመት የሚቆጠር ሳይሆን፥ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ስለምን ያስፈልጋል? ምክንያቱም ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ ግድ ይላልና ነው። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የታወቀ ነው፤ ከዚያ ነገድ ጋር በተገናኘ ስለ ካህናት ሙሴ ምንም አልተናገረም። ይህ ይበልጥ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ግልጽ ይሆናል፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ አይደለም። ስለ እርሱ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት በክህነት ሥራ ላይ ለመቆየት ስላልቻሉ፥ የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ለዚህም ነው፥ እነርሱን ሊያማልድ ዘወትር ይኖራልና፥ በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። እንዲህ ያለው ቅዱስ፥ ነቀፋ የሌለበት፥ ንጹሕ፥ ከኃጢአተኞች የተለየ፥ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ ሊቀ ካህናት ሊኖረን ይገባል፤ እርሱ እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት፥ አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት፥ ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ይህን ራሱን ባቀረበ ጊዜ አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎታል። ሕጉ ሰዎችን ድካም እያላቸው ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማል፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን፥ ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾመልን። እንግዲህ ከተናገርነው ነገር ዋናው ይህ ነው፦ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህ ይህም ካህን የሚያቀርበው አንድ ነገር ሊኖረው ግድ ነው። እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ በነበረ ጊዜ፥ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ፤” ብሎት ነበርና፤ እነርሱ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። አሁን ግን በተሻለ ተስፋ ቃል ስለ ተመሠረተ፥ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን የተሻለ እንደሆነ ሁሉ፥ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፥፥ ፊተኛው ኪዳን ጉድለት ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ጉድለት አግኝቶባቸዋልና እንዲህ ይላቸዋል፦ “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምመሠርትበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ ከግብጽ ምድር ለማውጣት እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና እኔም ቸል አልኳቸው፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል። እያንዳንዱም ‘ጌታን እወቅ፥’ ብሎ ጐረቤቱን ወይም ወንድሙን አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።” “አዲስ” በሚል ጊዜ ፊተኛውን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ጊዜው ያለፈበትና አሮጌው ነገር ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል። የመጀመሪያው ኪዳን የአገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበራት። ድንኳን ተዘጋጅቶ ነበር፥ በእርስዋም ውስጥ ቅድስት በምትባለው መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበር። ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፤ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበር፤ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፥ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ። በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበር፤ ስለ እነዚህም በዝርዝር የመናገሪያው ሰዓት አሁን አይደለም። ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ እያለ ካህናት የአምልኮ አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ደጋግመው ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ በዚህ መንገድ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ እያለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ሲሆን፥ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም የማያደርጉ፥ ነገር ግን ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶች የሚውሉ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ስለ ሆኑ፥ እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ናቸው። ነገር ግን ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ ስለሚሆነው መልካም ነገር፥ በምትበልጠውና በምትሻለው፥ በእጆችም ባልተሠራች፥ እርሷም ከፍጡራን ባልሆነች ድንኳን፥ የዘለዓምን ቤዛነት አግኝቶ፥ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ፥ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም፥ በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ፥ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም እንዴት ልቆ፥ ሕያው እግዚአብሔርን ለማምለክ፥ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን! በዚህ ምክንያት የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞቱ ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘለዓምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። ኑዛዜ ካለ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፥ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናል። ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን ከቶ አይጠቅምም። ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳን ያለ ደም አልተመረቀም። እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ በሙሴ ለሕዝቡ ከተነገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፥ ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፥ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” አላቸው። በተመሳሳይ በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጭቷል። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፤ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት እነዚህ ነገሮች በዚህ ሥርዓት ሊነጹ ግድ ነበር፤ ነገር ግን ሰማያዊ ነገሮች ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ለመታየት ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት ደጋግሞ እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ ለመሞት ከዚያም ለፍርድ መቅረብ ተመድቦባቸዋል። እንዲሁም ክርስቶስ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ተሰውቷል። ለሁለተኛ ጊዜ ሲታይ ሊያድናቸው ለሚጠባበቁት ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን መዳንን ለማምጣት ነው። ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን ጥላ በመሆኑ፥ እውነተኛ አካል አይደለም። በየዓመቱም ዘወትር በሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚቀርቡትን ለፍጽምና ሊያበቃ ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን ባቆሙ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት ዓመታዊ የኃጢአት መታሰቢያ ነው ያለው፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ለማስወገድ አይችልም። በዚህ ምክንያት፥ ወደ ዓለም ሲመጣ፥ “መሥዋዕትንና መባን አልወደድክም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠልና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት፥ አንተ ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ፥ ‘እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ! ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፥’ አልኩ፤” ይላል። በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም፤” ይላል። እነዚህም እንደ ሕጉ የሚቀርቡት ናቸው። ከዚያም “እነሆ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፤” ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ በየዕለቱ እያገለገለ እነዚያን ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ደጋግሞ ለማቅረብ ይቆማል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድ መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ አሁን ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ እንዲህ በማለት፦ “ከነዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ “በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፥ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፤” እንደዚሁም፥ “ኀጢአታቸውንና ዐመጻቸውንም ደግሜ አላስብም፤” ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የለም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ ቅድስት ለመግባት በኢየሱስ ደም ድፍረት ስላለን፥ በአዲስና በሕያው መንገድ በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል ተከፍቶልን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተንና ሰውነታችንን በንጹህ ውሃ ታጥበን፥ በቅን ልብ በፍጹም እምነት እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና፥ ተስፋ የሚሰጠንን ምስክርነት ያለመናወጥ በጽናት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተሳሰብ፤ አንዳንዶችም ልምድ አድርገው እንደያዙት፥ መሰብሰባችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር፤ ይልቁንም የቀኑን መቅረብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርብልንም፤ ነገር ግን የሚያስፈራ የፍርድና ተቃዋሚዎችንም ለመብላት የሚጠብቅ የእሳት ግለት አለ። የሙሴን ሕግ የተላለፈ ሰው “በሁለት እና በሦስት ምስክሮች ምስክርነት” ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ የተቀደሰበትን ያንን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያስቆጣ፥ ቅጣቱ እጅግ የከፋ እንዴት የማይሆን ይመስላችኋል? “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤” ያለውን እናውቃለን፤ ደግሞም “ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።” በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁባቸውን እነዚያን የመከራ ቀናት አስታውሱ፤ አንዳንድ ጊዜ በግላጭ ለነቀፋና ለስደት የተዳረጋችሁ ነበራችሁ፤ አንዳንዴም እንዲህ ካሉት ጋር በሚደርስባቸው ነገር ተካፋይ ሆናችሁ ነበር፤ በሰማይ የበለጠና ፍጻሜ የሌለው ሀብት እንዳላችሁ በማወቃችሁ፥ የንብረታችሁን መነጠቅ በደስታ ተቀበላችሁ፤ በእስራት ላይ የነበሩትን የስቃያቸው ተካፋይ ሆናችሁ። ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ ጽናት ያስፈልጋችኋል። ምክንያቱም ገና “በጣም ጥቂት ጊዜ፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል፥ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ነፍሴ ወደ ኋላም በሚያፈገፍግ በእርሱ ደስ አትሰኝም።” እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ጋር ነን እንጂ፥ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ጋር አይደለንም። እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር እርግጠኛ የምንሆንበት፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። የቀደሙ አባቶቻችንም የተመሰከረላቸው በዚህ ነው። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠሩ፥ የሚታየውም ነገር ከሚታዩት እንዳልተፈጠረ በእምነት እንረዳለን። አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ እግዚአብሔር እንዳለና ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በዚህም ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴትም እንደሚሄድም ሳያውቅ ሄደ። ለባዕድ አገር እያለም በተስፋ ቃል በተሰጠው ምድር፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ወራሾች እንደሆኑት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በእምነት በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበር። ሣራም ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ስለ ቈጠረች፥ ምንም እንኳን መካን ብትሆን፥ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፥ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከርቀት አይተውት ሰላምታ አቀረቡለት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩም እንግዶችና መጻተኞች ለመሆንም ታመኑ። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያመለክታሉ። ያን ትተውት የወጡትን አገር አስበው ቢሆን ኖሮ፥ ወደዚያ የመመለስ እድል በነበራቸው ነበር። አሁን ግን የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና አምላካቸው ተብሎ ለመጠራት በእነርሱ አያፍርም። አብርሃም በተፈተነ ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱም አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ ስለ እርሱም፥ “ዘርህ በይስሐቅ ይጠራል” ተብሎለት ነበር። እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንደሚችል አስቦአልና፤ ይስሐቅን እንደ ምሳሌ መልሶ ተቀበለ። ይስሐቅ ስለ መጪው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፤ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት በቀረበ ጊዜ፥ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፤ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ላለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና፥ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ። የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፥ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር ትቶ የሄደው በእምነት ነበር። የበኩር ልጆችን የሚያጠፋው እንዳይነካቸው ፋሲካን የጠበቀውና ደምን መርጨትን ያደረገው በእምነት ነበር። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩ፤ የግብጽ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰመጡ። የኢያሪኮ ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ፈረሰ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው በእምነቷ ምክንያት ከማይታዘዙ ጋር አልጠፋችም። ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሳምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው ብርቱ ሆኑ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ወራሪዎችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም የሚታደጓቸውን ሳይሹ የሚበልጠውን ትንሣኤ ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ መሆንን፥ መገረፍን፥ ከዚህም በላይ እስራትንና ወኅኒን ቻሉ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፤ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ፥ እየተጨነቁ፥ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና፥ በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተገባውን የተስፋ ቃል አላገኙም። ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበር። እንግዲህ እነደዚህ ዓይነት ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ማንኛውንም ሸክምና የተጣበቅንበትን ኅጢአት ሁሉ አራግፈን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። የእምነታችንንም ራስና ፍጽምና የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፥ ውርደቱንም ንቆ፥ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ እንዴት እንደተቋቋመ አስቡ። ከኃጢአት ጋር በምታደርጉት ተጋድሎ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ እንደ ልጆችም እንዲህ በማለት የተነገራችሁን ምክር ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቅልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤ ጌታ የሚወደውን ይገሥጻልና፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ሁሉ ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፥ የተግሣጽን ቅጣት ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ሁሉም ተካፋይ ከሆኑበት ቅጣት ውጭ ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በተጨማሪ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ እንዴት በላቀ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር አይገባንም? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበር፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ለጊዜው ቅጣት ሁሉ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰላማዊ የጽድቅን ፍሬ ያፈራላቸዋል። ስለዚህ የላሉትን እጆቻችሁን የሰለሉትንም ጉልበቶቻችሁን አቅኑ። አንካሳውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይሰበር፥ ለእግራችሁ ቀና መንገድ አበጁ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጣሩ፤ ያለ ቅድስናም ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና ለመቀደስም ፈልጉ። ከመካከላችሁ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት መራራ ሥር በቅሎ እንዳያስጨንቃችሁ፥ ማንም ሴሰኛ እንዳይሆን ወይም ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደ ሸጠው ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላ እንኳን በረከቱን ለመውረስ ቢፈልግም እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ ቢፈልግም እንኳን ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና። ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፥ ወደ ጭጋጉና ወደ ጨለማው፥ ወደ ዐውሎ ነፋሱ ገና አልደረሳችሁም፤ ወደ መለከት ድምፅ፥ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምጽ አልመጣችሁም። ያን ነገር የሰሙት ሁሉ ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው እስኪለምኑ አደረሳቸው፤ ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት፤” የምትለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም። ሙሴም “እጅግ እፈራለሁ፤ እንቀጠቀጥማለሁ፤” እስኪል ድረስ የሚታየው ነገር እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፤ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። የሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላይ ሲያስረዳቸው እምቢ ያሉት ካላመለጡ፥ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ፈቀቅ የምንል እኛ እንዴት እናመልጣለን? ያንጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጧት ነበር፤ አሁን ግን “አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም፤” ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ዳሩ ግን “አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚል ቃል የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት ፍጡራን ነገሮች እንደሆኑና እንደሚለወጡ ያሳያል። ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና። እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ቀጥሉ። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች በዚህ ሳቢያ ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል። እስረኞችን አብራችኋቸው እንደታሰረ ሆናችሁ አስቡ፤ እናንተም በሥጋ እንዳለ እያሰባችሁ የተጨነቁትንም እንደራሳችሁ አስቡ። ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፥ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ሕይወታችሁ ከፍቅረ ንዋይ የጸዳ ይሁን፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ “አልለቅህም፤ ከቶም አልተውህም፤” ብሎአልና ያላችሁ ይብቃችሁ። ስለዚህ በመተማመን፥ “ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንላለን። የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፥ ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው። በልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ መልካም የሚሆነው ልባችሁ በጸጋ ቢጸና ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚኖሩትም እንኳን አልተጠቀሙም። መሠዊያ አለን፤ ሆኖም ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ ከእርሱ የመብላት መብት የላቸውም። ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት የእንስሶችን ደም ወደ ቅድስት ያቀርባል፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል። ስለዚህ ኢየሱስም በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከ መውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። በዚህ ነዋሪ የሆነች ከተማ የለችንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንፈልጋለን። እንግዲህ ዘወትር ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት አድርገን በእርሱ በኩል እናቅርብለት። እንዲሁም መልካም ማድረግንና ያላችሁን ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ። እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። እነርሱ እንደሚጠየቁበት አድርገው ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ፤ ይህንንም በደስታ እንጂ በኀዘን እንዳያደርጉት፥ አለበለዚያ አይጠቅማችሁም። ለእኛም ጸልዩልን። በነገር ሁሉ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ተረድተናል። ይልቁን ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን እንድታደርጉ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ትፈጽሙ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ወንድሞች ሆይ! ይህን በጥቂት ቃል የጻፍኩላችሁን የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ። ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ እወቁ፤ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ። ለመሪዎቻችሁ ሁሉ፥ ለቅዱሳንም ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ ያሉትም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ያዕቆብ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ደስታ አድርጋችሁ ቁጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን እንደሚያጸናችሁ ታውቃላችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን እንድትሆኑ ጽናትም ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚነዋወጥ የባሕርን ማዕበል ነው። ያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች አገኛለሁ ብሎ ሊያስብ አይገባውም። በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ሁለት ሐሳብ ያለው ሰው ነው። ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ፥ ሀብታምም እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በውርደቱ ይመካ። የፀሐይ ቃጠሎ በንዳዱ ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የመልኩም ውበት ይጠፋል፤ እንዲሁ ሀብታም ሰው በመንገዱ ይዝላል። ጌታ ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ተፈትኖ ይቀበላልና፥ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! መልካም ስጦታ ሁሉ፥ ፍጹምም በረከት ሁሉ፥ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ፥ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማና የማያደርግ ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ፥ “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።” ወንድሞቼ ሆይ! ክቡር በሆነው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ በመሆናችሁ፥ አድልዎን አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፥ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፥ “ለአንተ የሚሆን መልካም መቀመጫ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፥ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፥ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? እናንተ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? በመጽሐፍ፥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ንጉሣዊ ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። አድልዎ ብታደርጉ ግን ኃጢአት መሥራታችሁ ነው፤ እንደ ሕግ ተላላፊዎችም ትቈጠራላችሁ፤ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ ብትፈጽሙ ነገር ግን በአንዱ ብትሰናከሉ፥ ሁሉን እንደ ተላለፋችሁ ይቈጠራል። “አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደል” ብሏል። ባታመነዝር፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። ስለዚህ ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ በነጻነት ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች አድርጉ፤ ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታልና፤ ምሕረትም ፍርድን ያሸንፋል። ወንድሞቼ ሆይ! አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ቢያጡና፥ ከእናንተ መካከል አንዱ፥ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፥ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፥ ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ከሥራ የተለየ እምነት በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ቢል፤ እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ። አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንትም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? ስለዚህ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ እንደ ነበርና እምነትም በሥራ ፍጹም እንደሆነ ታያለህን? “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንደሆነ ታያለህን? እንዲሁም አመንዝራይቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በላከቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ፥ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናስገባለን፤ መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን። መርከቦችንም ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለች በታላላቅ ነገሮች ትኩራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች። ማናቸውም ዓይነት አውሬ፥ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፥ በእርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ! ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ! የበለስ ዛፍ የወይራን ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? ወይስ የወይን ተክል የበለስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም። ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ማን ነው? በመልካም አኗኗር ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኩራት አይሰማችሁ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ምድራዊ፥ ሥጋዊና አጋንንታዊ ናት። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይኖራሉ። ከላይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል። በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጋው ከፍትወት ምኞት አይደለምን? ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ትገድላላችሁ። በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ስለዚህ ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ። ስለማትለምኑ የምትፈልጉትን አታገኙም። የምትለምኑትም ለፍትወታችሁ በማሰብ በክፉ ምኞት ስለሆነ፥ ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም። አመንዝሮች ሆይ! ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ “እርሱ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል” በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? ስለዚህ፥ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” እንደሚል፥ የሚሰጠው ጸጋ ግን ከሁሉም ይበልጣል። እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች! እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፥ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል። ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ ተመልከቱ፤ ነገ የሚሆነውን አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድነው? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት አይደላችሁምን? ይልቁንም፥ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። እናንተ ግን በእብሪታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኃጢአት ያደርጋል። አሁንም እናንተ ሀብታሞች ኑ! ስለሚደርስባችሁ መከራ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። እነሆ፥ እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የአጫጆቹም ጩኸት የሠራዊት ጌታ ጆሮ ደርሶአል። በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል በመኖር ለዕርድ ቀን እንደሚዘጋጅ ልባችሁን አወፍራችኋል። እናንተን ያልተቃወመውን ጻድቁን ሰው ፈረዳችሁበት፤ ገደላችሁትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፥ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአልና። ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ፥ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ! በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ፥ ነገራችሁ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትም ሠርቶ ከሆነ፥ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኃይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናብ ሰጠ፤ ምድርም ፍሬን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፥ ይህን ይወቅ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድንለታል፤ ብዙ ኃጢአቱንም ይቅርታ ያስገኝለታል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ በጳንጦስ፥ በገላትያ፥ በቀጰዶቅያ፥ በእስያ፥ በቢታንያ፥ ለተበተኑ መጻተኞች፤ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ያወቃችሁ፥ በመንፈስ የተቀደሳቹ፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትታዘዙና በደሙም ትረጩ ዘንድ ለተመረጣችሁት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ ከምሕረቱ ብዛት በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይመስገን፤ እንዲሁም የማያልፍም፥ እድፈትም የሌለበት፥ የማይጠፋ ርስት በሰማይ ቀርቶላችኋል። ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ተዘጋጅቶላችኋል። አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና ብታዝኑም እንኳን፥ እጅግም ደስ ይላችኋል። በዚህም በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ ነው። እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩትም በእርሱ በማመናችሁ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል። የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ ነውና። ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው ፈለጉም መረመሩም፤ በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ እና ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሰክር፥ ምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን በነገሯችሁ ነገር፥ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፥ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ። ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች፥ ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ፤” ተብሎ ተጽፎአልና፤ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፥ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፥ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ አይደለም፤ ነገር ግን ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ ደም፥ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው፥ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፤ ነገር ግን ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሞት ባስነሣው ክብርንም በሰጠው፥ በእግዚአብሔር በእርሱ ትተማመናላችሁ። ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ ለወንድማማች እውነተኛ ፍቅር፥ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት በሕያውና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር እንጂ፤ ከሚጠፋ ዘር አይደለም። ምክንያቱም፥ “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው። እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ተንኰልን ሁሉ፥ ግብዝነትን፥ ቅንዓትን ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ፥ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ እነሆ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችኋልና። በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለማቅረብ፥ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፥ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። ምክንያቱም በመጽሐፍ “እነሆ፥ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፥ በጽዮን አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም፤” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።” ደግሞም፦ “ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ የሚጥላቸውም ዓለት ሆነ፤” የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ አስቀድመውም ለዚህ የተመደቡ ናቸው። እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ! ባዕዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር በሚጎበኝበት ቀን፥ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ እርሱን እንድያከብሩት በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። ስለ ጌታ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ እንደመሆኑ ታዘዙ። ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ለአገረ ገዢዎችም ቢሆን ታዘዙ። በዚህ መንገድ መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂነት ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። እናንተ አገልጋዮች ሆይ! ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። ስለ እግዚአብሔር ብሎ በግፍ መከራን ሲቀበል የሚታገሥ ምስጋና ይገባዋል። ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። ለዚህ ተጠርታችኋል፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። እርሱ ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። እንዲሁም እናንተ ሚስቶች ሆይ! ለባሎቻችሁ ታዘዙ፤ በዚህ ዓይነት አንዳንዶች በቃሉ የማያምኑ ቢሆኑም እንኳ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ጠባይ ብቻ ሊሳቡ ይችሉ ይሆናል። የሚሳቡትም አክብሮት የተሞላውንና ንጹሕ ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው። ለእናንተም ቢሆን ውበታችሁ ውጫዊ የሆነ፥ ሹሩባ በመሠራት፥ በወርቅ በማጌጥና የከበረ ልብስ በመልበስ አይሁን፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ በከበረና በማይጠፋው ጌጥ በገርነትና በጽሞና መንፈስ የተዋበው የተሰወረ ውስጣዊ ሰውነት ይሁን። በዚህ ዓይነት ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳት ሴቶች ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስውቡ ነበር። ሣራም አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ትታዘዘው ነበር፤ እናንተም ምንም ሳያስፈራችሁ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ። እናንተም ባሎች ሆይ! ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ ከሚስቶቻችሁ ጋር በመተሳሰብ ኑሩ፤ የሕይወትንም ጸጋ አብረዋችሁ ስለሚወርሱ እንደ ደካማነታቸው ሴቶችን አክብሯቸው። በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ እርስ በእርሳችሁ ተሳሰቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም በረከትን ልትወርሱ ተጠርታችኋል። “ሕይወትን የሚወድ መልካም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ፥ ምላሱን ከክፉ ይጠብቅ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉም ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻት፤ ይከተላትም። የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው የተከፈቱ ናቸው፤ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።” ለመልካም ነገር ቀናኢ ብትሆኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ዛቻቸውንም አትፍሩ፤ አትታወኩም። ነገር ግን ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተም ስላለች ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በገርነትና በአክብሮት አድርጉት፤ በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ በመንቀፍ የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ መልካም ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚእብሔር ፈቃድ ከሆነ፥ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል። ክርስቶስ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኃጢአት መከራን ተቀበለ፤ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባችሁ በሥጋ ሞተ፥ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ። በዚያው መንፈስ በእስር ቤት ወዳሉት ነፍሳት ሄዶ ሰበከላቸው፤ እነዚህ ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ሲጠብቃቸው አንታዘዝም ያሉ ናቸው። በውሃ የዳኑት ጥቂት ሲሆኑ እነርሱም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይህ ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ እናንተን ያድናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ ሳይሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የበጎ ሕሊና ልመና ነው። እርሱም ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ተገዝተውለታል። እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋ ስለ እኛ መከራን በመቀበሉ፥ እናንተም በዚህ ሐሳብ ራሳችሁን አስታጥቁ፤ ምክንያቱም በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአል። ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት አትኑሩ። አሕዛብ እንደሚያደርጉት በመዳራት፥ በሥጋዊ ምኞት፥ በስካር፥ በመሶልሶል፥ ያለ ልክ በመጠጣት፥ በአስነዋሪ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። ይህን በመሰለ ብክነት ከእነርሱ ጋር ባለመተባበራችሁ ይደነቃሉ፤ ይሰድቡአችኋልም። ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው ለእርሱ መልስ ይሰጡበታል። ወንጌል ለሙታን ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ሰው ሁሉ በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ። የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ እንግዲህ መጸለይ እንድትችሉ የረጋ አእምሮ ይኑራችሁ፤ በመጠንም ኑሩ። ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ያለ ማጉረምረም እርስ በርሳችሁ በእንግድነትን ተቀባበሉ። የእግዚአብሔርን ልዩ ልዩ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ኃይል ያገልግል፤ በዚህም ዓይነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብራል፤ ክብርና ሥልጣን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። ወዳጆች ሆይ! እንደ እሳት በሚፈትን መከራ ውስጥ ስትገኙ ያልተለመደ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ አድርጋችሁ አትደነቁ። ይልቅስ የእርሱ ክብር በሚገለጥበት ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎአችሁ ኀሤት እንድታደርጉ የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በሆናችሁበት መጠን ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ፥ የእግዚአብሔር የክብሩም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። ማንም ከእናንተ መካከል እንደ ነፍሰ ገዳይ፥ ወይም እንደ ሌባ፥ ወይም እንደ ክፉ አድራጊ፥ ወይም በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ሆኖ መከራ የሚቀበል አይኑር። ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአል፤ በቅድሚያም በእኛ የሚጀመር ከሆነ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? እንግዲህ “ጻድቅ እንኳ በጭንቅ የሚድን ከሆነ፥ የዐመፀኛውና የኀጢአተኛው መጨረሻ እንዴት ይሆን?” ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ። እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር አብሬ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆንኩ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር የሆንኩ፥ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፥ በመካከላችሁ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ። ኀላፊነት የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ ይህም በግድ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት በፈቃደኝነት፥ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን በጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ በእናንተ ኀላፊነት ሥር ላለው ለመንጋው መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በኃይል በመግዛት አይሁን። የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይደበዝዘውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታኑ ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ፤ ንቁም! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ዙሪያውን ይንጐራደዳል። በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ይህን ዓይነት መከራ እንደሚቀበሉ በማወቅ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ እርሱ ራሱ ያበረታችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ያቆማችኋል፤ ይመሠርታችኋልም። ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ኃይል ለእርሱ ይሁን! አሜን። እንደ ታማኝ ወንድም በምቆጥረው በስልዋኖስ በኩል፥ ልመክራችሁና ጸንታችሁ የምትቆሙበት ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልገልጽላችሁ በማለት፥ ይህን አጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ። ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፥ በባቢሎን ያለችው ቤተ ክርስቲያን፥ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር አቻ የሆነ ክቡር እምነትን ላገኙ፤ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። በመለኮቱ ኃይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጠን። በእነዚህም አማካኝነት፥ ከክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ፥ በተስፋው ቃል ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ፥ በክብርና በበጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። በዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ ሠናይነትን ጨምሩ፥ በሠናይነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችነት መዋደድ፥ በወንድማማችነትም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ቢኖሩአችሁና ቢበዙላችሁ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ በተመለከተ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ግን የሩቁን ነገር ማየት የማይችል ዕውር ነው፤ ከቀደመው ኀጢአቱም መንጻቱን ረስቷአል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁንና መመረጣችሁን እንድታጸኑ፥ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ይህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህ መልክ፥ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁና፥ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ጸንታችሁ ብትኖሩም፥ ስለ እነዚህ ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። በዚህ ሕይወት እስካለሁበት ጊዜ ድረስ እናንተን ዘወትር ማነቃቃት ትክክል መስሎ ይታየኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቴ ፈጥኖ እንደሚሆን አውቃለሁና፤ ከመለየቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች፥ በየትኛውም ጊዜ ማሰብ ትችሉ ዘንድ፥ በብርቱ እተጋለሁ። ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልና መምጣቱም በነገርናችሁ ጊዜ፥ ራሳችን ግርማውን በዐይናችን አይተን የምንመሰክር እንጂ፥ በሰው ብልጠት የታቀደውን ተረት ተከትለን አይደለም። ከግርማዊው ክብር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው!” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ገናናነትን ተቀብሏል። እኛም በተቀደሰው ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን፥ ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰምተናል። ደግሞም ይህን የበለጠ የሚያረጋግጥ የነቢያት ቃል አለ፤ ጎሕ እስኪቀድ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪገለጥ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚያስተውል ቃሉን ልብ በማለት መልካም ታደርጋላችሁ። ከሁሉ አስቀድማችሁ ይህን አስተውሉ፥ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ማንኛውም ትንቢት በሰው ፈቃድ ከቶ አልመጣም፤ ነገር ግን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ሰዎች ከእግዚአብሔር ተቀብለው ተናገሩ። ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይኖራሉ፤ እነርሱም ጥፋትን የሚያስከትሉ ትምህርቶች አስርገው በማስገባት የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው፥ በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋትን ያመጣሉ። እንዲሁም ብዙዎች ጸያፍ ምግባራቸውን ይከተሏቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ለገንዘብ ከመስገብገባቸው የተነሣ ራሳቸው ያዘጋጁትን ታሪክ እያወሩ ይበዘብዙአችኋል። ፍርዳቸውም ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ጥፋትም በእርግጥ ይጠብቃቸዋል! እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ፥ ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ፥ በኀጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውሃ ካወረደ፥ ኃጢአትንም እያደረጉ ላሉት ምሳሌ እንዲሆን፤ የሰዶምንና ገሞራን ከተማዎች አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ እንዲጠፉ ከፈረደባቸው፥ በዝሙት ሥራቸው ሲሳቀቅ የነበረውን ጻድቅ ሎጥን ካዳነ፤ ያ ጻድቅ ሰው፥ በመካከላቸው ሲኖር ዕለት ከዕለት የዐመፀኞችን ሴሰኛ ኑሮ እያየና እየሰማ በክፉ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን ቢያስጨንቅም፤ እንግዲህ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸው፥ እንዲሁም በደለኞችን እንዴት በቅጣት ስር ለፍርድ ቀንም ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል። ይልቁንም በርኩስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን፥ ጌትነትንም የሚንቁትን፤ ደፋሮችና እምቢተኞች ስለ ሆኑ ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ ዳሩ ግን መላእክት፥ በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ምንም ያህል ቢልቁ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። ይሁን እንጂ፥ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት እንደ ተወለዱ፥ በፍጥረታዊ ስሜታቸው እንደሚኖሩ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው። የማያውቁትን ነገር እየተሳደቡ፥ ከእነርሱም ጋር አብረው ይጠፋሉ፤ የበደላቸውን ዋጋም ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኩሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አላቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ ክፉ በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ ነገር ግን በለዓም ስለ መተላለፉ ተገሥጿአል፤ መናገር የማይችለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብደት አገደ። እነዚህ ሰዎች ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም ይጠብቃቸዋል። ከንቱና የትዕቢት ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት ለጥቂት ያመለጡትን ሰዎች በሥጋ ሴሰኛ ምኞት በማታለል ያስታሉ። ራሳቸው የጥፋት ባርያዎች ሆነው “ነጻ ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ የተገዛ ባርያ ነውና። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ፥ ዳግመኛ በእርሷ ተጠልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” እንዲሁም “እርያ ብትታጠብ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል። ወዳጆች ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፤ በሁለቱም መልእክት ቅን ልቡናችሁን በማሳሰብ አነቃቃለሁ። ከዚህ በፊት በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል፥ እንዲሁም በሐዋርያዎቻችሁም አማካይነት ያገኛችኋትን የጌታችንንና የመድኃኒታችንን ትእዛዝ እንድታስቡ ይገባል። ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻው ዘመን እንደራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ እወቁ፤ እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ፥ የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ፥ ሁሉ እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማያት በእግዚአብሔር ቃል መፈጠራቸውን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው አያስተውሉም። በዚህም ምክንያት ያንጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ፤ ነገር ግን አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር በዚሁ ቃል፥ እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቆያሉ። ወዳጆች ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው፥ ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል መኖር አይገባችሁም? እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ የምታፋጥኑ ሁኑ፤ ምክንያቱም ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የፍጥረት መሰረተ ነገር በእሳት ግለት ይቀልጣሉ! ነገር ግን እኛ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህን ሁሉ እየተጠባበቃችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤ የጌታችንም ትዕግሥት ለእናንተ መዳን እንደሆነ ቁጠሩ። እንደዚሁ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ በመልእክቶቹም ሁሉ እንዳደረገው ስለዚህ ነገር ተናግሯል። በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፤ ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። እንግዲህ ወዳጆች ሆይ! እናንተስ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፥ በዐመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከጽኑ አቋማችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም ለዘለዓለምም ክብር ይሁን! አሜን። ከመጀመሪያው የነበረውን፥ የሰማነውን፥ በዐይኖቻችንም ያየነውን፥ የተመለከትነውንና እጆቻችንም የዳሰሱትን፥ ስለ ሕይወት ቃል እንናገራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፥ አይተነዋል እንመሰክራለንም፥ በአብ ዘንድ የነበረውን ለእኛም የተገለጠውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን። ኅብረታችንም ከአብና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችን ሙሉ እንዲሆን ይህን እንጽፍላችኋለን። ከእርሱ የሰማነውና ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም። ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን እያልን በጨለማ ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ዘንድ የለም። ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን የታመነና ጻድቅ ነው፥ ከዓመፃም ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም። ልጆቼ ሆይ፥ ይህን የምጽፍላችሁ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ብዬ ነው። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለእኛ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። ትእዛዛቱን ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። “አውቀዋለሁ” የሚል፥ ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ እርሱ ሐሰተኛ ነው፥ እውነትም በእርሱ ዘንድ የለም። ቃሉን የሚጠብቅ ግን በእውነት የእግዚአብሔርን ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን። በእርሱ እኖራለሁ የሚል፥ ልክ እርሱ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል። ወዳጆቼ ሆይ፥ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍላችሁም፤ ነገር ግን ከመጀመሪያ የነበራችሁ አሮጌ ትእዛዝ ነው እንጂ፤ አሮጌውም ቃል የሰማችሁት ነው። በሌላ በኩል አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም በእርሱ እና በእናንተ ዘንድ እውነት ነው፤ ጨለማው አልፏል፥ እውነተኛው ብርሃን እያበራ ነው። በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን ግን የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ ውስጥ ነው። ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፥ በእርሱም ዘንድ ማሰናከያ የለም። ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ይኖራል፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ ጨለማው ዐይኖቹን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። ልጆች ሆይ፥ ስለ ስሙ ኃጢአታችሁ ይቅር ስለ ተባለላችሁ እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በውስጣችሁ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ ጽፌላችኋለሁ። ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን ነገሮች አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአብ ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፥ የሥጋ ምኞት፥ የዐይን ምኞት፥ በኑሮ ደረጃ መመካት፥ ከዓለም ነው እንጂ ከአብ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል። ልጆች ሆይ፥ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል ሲባል እንደ ሰማችሁት አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ በዚህም ይህ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እናውቃለን። ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ነገር ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ጋር በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ እንዲገለጥ ወጡ። እናንተ ግን ከቅዱሱ፥ ቅባት አላችሁ፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለምታውቁትና ውሸት ሁሉ ከእውነት ስላልሆነ ነው። ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? ይህ አብን እና ወልድን የሚክድ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ በወልድ የሚያምን አብ አለው። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ከኖረ፥ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። እርሱ የሰጠን ተስፋ ይህ ነው፥ እርሱም የዘለዓለም ሕይወት ነው። ስለሚያታልሉአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ስለሚኖር፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነትም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እርሱ እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። ልጆች ሆይ፥ እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ ድፍረት እንዲኖረን፥ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ካወቃችሁ፥ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፤ እንዲሁም ነን። ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛንም አያውቀንም። ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ቢገለጥ ግን እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን፥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና። በእርሱ ይህ ተስፋ ያለው ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደሆነ ራሱን ያነጻል። ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ያደርጋል፥ ኃጢአት ደግሞ ዓመጽ ነው። ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም፥ አላወቀውምም። ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ጀምሮ ኃጢአትን ይሠራል። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው። ዘሩ በእርሱ ስለሚኖር ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ ይገለጣሉ፤ ጽድቅን የማያደርግ ሁሉ እና ወንድሙን የማይወድ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት ይህ ነውና፥ እርሱም፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ፥ ከክፉው እንደነበረው ወንድሙንም እንደ ገደለው እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለምንስ ገደለው? የእርሱ ሥራ ክፉ፥ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። እኛ ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ። እርሱ ስለ እኛ ሕይወቱን አሳልፎ ስለ ሰጠን በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ሕይወታችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን ማንም የዚህ ዓለም ሀብት ቢኖረው፥ ወንድሙም ተቸግሮ አይቶ ባይራራለት፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ፥ በሥራ እና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። በዚህም ከእውነት መሆናችንን እናውቃለን፥ በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ ልባችን ቢወቅሰን እንኳ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። ወዳጆች ሆይ፥ ልባችን የማይወቅሰን ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፤ ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅ፥ በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ፥ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም እንድናምንና፥ እርሱም እንዳዘዘን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው። ትእዛዙን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በእኛ እንደሚኖር በዚህ እናውቃለን፥ ይኸውም በሰጠን በመንፈሱ ነው። ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መንፈሶች ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደመጣ የማያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም ይመጣል ሲባል የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው፥ አሁንም እንኳ በዓለም ውስጥ አለ። ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፥ አሸንፋችኋቸዋልም፥ በእናንተ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣልና። እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለምም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። በዚህም የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ እናውቃለን። ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚያፈቅር ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፥ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማያፈቅር እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል እንድንኖር እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅር በዚህ ነው፥ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን ነገር ግን እርሱ እንደ ወደደን እና ለኃጢአታችንም ማስተስሪያ እንዲሆን ልጁን ስለላከልን ነው። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ከወደደን፥ እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ያየው ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፥ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል። በእርሱ እንደምንኖር እሱም በእኛ እንደሚኖር በዚህ እናውቃለን፥ ምክንያቱም ከመንፈሱ ስለ ሰጠን ነው። አብ ወልድን የዓለም አዳኝ እንዲሆን እንደ ላከው አይተናል፥ እንመሰክራለንም። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚመሰክር ሁሉ፥ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነናልም። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፥ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። በፍርድ ቀን ድፍረት እንዲኖረን ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ ምክንያቱም እርሱ እንደሆነ እኛ ደግሞ በዚህ ዓለም እንዲሁ ነን። በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ነገር ግን ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሃት ቅጣት አለው፥ የሚፈራ ሰው በፍቅር ፍጹም አልሆነም። እርሱ አስቀድሞ ስለወደደን፥ እንወዳለን። ማንም፦ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” ቢል ወንድሙን ግን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወድ አይችልምና። ከእርሱ የተሰጠን ትእዛዝ ይህ ነው፥ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙን ደግሞ ይውደድ። ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስንጠብቅ የእግዚአብሔርን ልጆች እንደምንወድ በዚህ እናውቃለን። ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣው ይህ ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በውኃው ብቻ አይደለም ነገር ግን በውኃና በደም ነው። የሚመሰክረውም መንፈሱ ነው፥ መንፈሱ እውነት ነውና። ሦስት ምስክሮች አሉ፤ መንፈስ ውኃና ደም፤ ሦስቱም አንድ ናቸው። የሰውን ምስክርነት የምንቀበል ከሆነ የእግዚአብሔር ምስክርነት ይበልጣል፤ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረው ምስክርነት ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በራሱ ምስክር አለው፤ እግዚአብሔርን የማያምን ግን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። ምስክርነቱ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ሰጠን፥ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ግን ሕይወት የለውም። በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ፥ የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ እንድታውቁ ይህን ጽፌላችኋለሁ። በእርሱ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንጠይቅ ይሰማናል። የምንጠይቀውን እንደሚሰማን ካወቅን፥ የጠየቅነውን እንደ ተቀበልን እናውቃለን። ማንም ወንድሙ ለሞት የማያደርስ ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ እግዚአብሔርም ለሞት የማያደርስ ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ። ስለዚህ ይለምን አልልም። ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ለሞት የማያበቃ ኃጢአት አለ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንደማያደርግ እናውቃለን፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን ይጠብቃል፤ ክፉውም አይነካውም። እኛ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን፥ መላው ዓለምም በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነት የሆነውን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነት በሆነው በእርሱ እንኖራለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው። ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ። ሽማግሌው፥ ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆችዋ፥ በእውነት ለምወዳቸው፥ እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዱአቸው፥ በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘለዓለም ስለሚሆን እውነት፥ ከእግዚአብሔር አብና በእውነትና በፍቅር የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ ምሕረትና ሰላም ከእኛ ጋር ይሁን። ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአባት እንደተቀበልነው ትእዛዝ መሠረት በእውነት የሚመላለሱ ሆነው በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። አሁንም እመቤት ሆይ! አዲስን ትእዛዝ አልጽፍልሽም ነገር ግን ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረውን ነው፥ ይህም እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ። ፍቅር ይህ ነው፥ እርሱም በትእዛዛቱ መመላለስ ነው፤ ትእዛዙ ይህ ነው፥ ከመጀመሪያ ጀምሮ እንደ ሰማችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ። ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና፤ እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህም አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ነገር ግን ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና የሚወጣ ሰው ሁሉ አምላክ የለውም፤ በዚህ ትምህርት የሚኖር ግን አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው የክፉ ሥራው ተካፋይ ይሆናል። ብዙ የምጽፍላችሁ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልፈለግሁም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላናግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል። ሽማግሌው፥ በእውነት ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። ወዳጄ ሆይ! በመንፈስ እንዳደግህ ሁሉ፥ በነገር ሁሉ እንዲሳካልህና በመልካም ጤንነት እንድትኖር እጸልያለሁ። ወንድሞች መጥተው በአንተ ስላለው እውነትና አንተም በእውነት እንደምትመላለስ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። ልጆቼ በእውነት እንደሚመላለሱ ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም። ወዳጄ ሆይ! ምንም እንኳ እንግዶች ቢሆኑም ለወንድሞች የምታደርገውን ነገር ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ፤ እነርሱም በቤተ ክርስቲያን ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ ስለ ስሙ ብለው፥ ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ወጥተዋልና። ስለዚህ የእውነት የሥራ ተባባሪዎች እንድንሆን እንደነዚህ ያሉትን ልንቀበል ይገባናል። ለቤተ ክርስቲያን አንድ ነገር ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ ለመሆን የሚፈልገው ዲዮጥራፊስ አልተቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ፥ ስለ እኛ የተናገረውን ክፉ ቃል፥ የሠራውን ሥራ አሳስበዋለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሉአቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፥ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። ወዳጄ ሆይ! መልካሙን እንጂ ክፉን አትምሰል። መልካም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ድሜጥሮስ በሁሉም ተመስክሮለታል፤ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም እንመሰክርለታለን፤ ምስክርነታችን ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ። የምጽፈው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ነገር ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወደድሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊት እንነጋገራለን። ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላም ይሉሃል። ወዳጆችን በየስማቸው ሰላም በልልኝ። የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስም ለተጠበቁት፥ ለተጠሩት፤ ምሕረት ለእናንተ ይሁን፥ ሰላምና ፍቅርም ይብዛላችሁ። ወዳጆች ሆይ! ስለ ጋራ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ሁሉ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ እንድመክራችሁና እንድጽፍላችሁ ግድ ሆነብኝ። አስቀድሞ ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በዝሙት ይለውጣሉ፤ ብቸኛ ንጉሣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። ነገር ግን ሁሉን ነገር አንድ ጊዜ ያወቃችሁትን እናንተን፥ ጌታ ከግብጽ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። የመጀመሪያ ቦታቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘለዓለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ከጨለማ በታች ጠብቆአቸዋል። እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች፥ እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ በዘለዓለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ሕልመኞች ሥጋን ያረክሳሉ፥ ጌትነትን ይቃወማሉ፥ ክብር ያላቸውንም ይሳደባሉ። ነገር ግን የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ሲናገር “ጌታ ይገሥጽህ!” አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊያመጣበት አልደፈረም። እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች በደመ ነፍስ በሚያውቁት ነገር ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። ወዮላቸው! በቃየል መንገድ ሄደዋልና፥ ለደመወዝ ብለው ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፥ በቆሬም ዓመጽ ጠፍተዋል። እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ነውር ናቸው፥ ራሳቸውን እየመገቡ ያለ ኀፍረት ከእናንተ ጋር ይጋበዛሉ፥ በነፋስ የሚገፉ ውሃ የሌላቸው ደመናዎች፥ በበጋ ፍሬ የማያፈሩ፥ ሁለት ጊዜ የሞቱ፥ ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤ የገዛ ነውራቸውን አረፋ የሚደፍቁ እየባሰ የሚሄድ የባሕር ማዕበል ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም የተዘጋጀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው። ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ እንደነዚህ ላሉት እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፦ “እነሆ ጌታ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቷል፤ ይህም በሁሉ ላይ ለመፍረድ ነው፤ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኀጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዐመፀኞችም ኀጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኀጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ” እነዚህ የሚያጉረመርሙ፥ የሚያማርሩ፥ ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ናቸው፤ አፋቸው የትዕቢት ቃልን ይናገራል፤ለጥቅማቸው ሲሉ ሰዎችን ያደንቃሉ። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ አስቀድሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት የተነገረውን ቃል አስቡ፤ እነርሱ “በመጨረሻው ዘመን ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ተሳላቂዎች ይሆናሉ፤” ብለዋችኋልና። እነዚህ መለያየትን የሚፈጥሩ ፍጥረታውያን የሆኑ፥ መንፈስም የሌላቸው ናቸው። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን እያነጻችሁ፥ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚያደርሰውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፥ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። የሚጠራጠሩትን ምሕረት አድርጉላቸው፤ አንዳንዶቹን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑአቸው፤ አንዳንዶቹን በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ምሕረት አድርጉላቸው። አሁንም ሳትሰናከሉ ሊጠብቃችሁ፥ በክብሩ ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ ሊያቆማችሁ ለሚችለው፤ እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፥ ግርማ፥ ኃይልና ሥልጣን ከዘመናት ሁሉ በፊት፥ አሁንም እስከ ዘለዓለምም ድረስ ይሁን፤ አሜን። በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ይህ ነው፤ መልአኩንም ልኮ ራእዩን ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠ፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት፥ ላየውም ሁሉ መሰከረ። ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱንም ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው። ከዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው፥ ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንዲሁም ከታመነው ምስክር፥ ከሙታን በኩር ከሆነው፥ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ፤ ለወደደን፥ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም፥ ለአባቱም ለእግዚአብሔር ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን። እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ፤ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፤ አሜን። ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ “አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፤” ይላል። እኔ ዮሐንስ፥ ከእናንተ ጋር አብሬ በኢየሱስ መከራውንና መንግሥቱንና ጽናቱን የምካፈል ወንድማችሁ፥ በእግዚአብሔር ቃልና በኢየሱስ ምስክርነት ምክንያት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ ፤ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤ እንዲሁም “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊላደልፊያም ወደ ሎዲቅያም ላክ፤ አለኝ።” የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ፤ በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። ራሱና የራሱ ጠጉርም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ እግሮቹም በምድጃ ውስጥ የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውሃዎች ድምፅ ነበረ። በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፤ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚያበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ፤ ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ የሚሆነውን ጻፍ። በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።” “በኤፌሶን ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው እንዲህ ይላል፦ “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንደማትችል፥ እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ‘ነን’ የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ በትዕግስት መጽናትህንና ስለ ስሜ መከራ መቀበልህን አውቃለሁ። ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና። እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ አስብ፤ ንስሓም ግባ፥ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሓም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ። ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔም የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ትጠላለህ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ። “በሰምርኔስም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ሞቶ የነበረው፥ ሕያውም የሆነው፥ ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል፦ “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ የሚሉት፥ ይልቁንም የሰይጣንም ማኅበር የሆኑት፥ የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ። የሚጠብቅህን መከራ አትፍራ። እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያስገባ ነው፤ ለዐሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። “በጴርጋሞንም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፦ “የት እንደምትኖር አውቃለሁ፥ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ነው፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፤ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ በእኔ ያለህን እምነት አልካድህም። ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፤ ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር አሉና። እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ። እንግዲህ ንስሓ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፤ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፤ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፤ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም ተጽፎአል። “በትያጥሮንም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዐይኖች ያሉት በምድጃም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንደሚበዛ አውቃለሁ። ዳሩ ግን ‘ነቢይ ነኝ’ የምትለውን፥ ባርያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ስለምትላት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሓም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሓ መግባትን አልወደደችም። እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርሷም ጋር የሚያመነዝሩትንም ከሥራዋ ንስሓ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ፥ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ፥ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁት ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ። ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፤ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።” “በሰርዴስም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል፦ ሥራህን አውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል። በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፤ ለሞት የተቃረቡትንም የቀሩትን ነገሮች አጽና። እንግዲህ ቃሉን እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በማናቸውም ሰዓት እንደምመጣብህ ከቶ አታውቅም። ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፤ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።” “በፊላደልፊያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ‘ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፥ የዳዊትም መክፈቻ ያለው፥ ሲከፍትም፥ ማንም የማይዘጋው፤ ሲዘጋም ማንም የማይከፍተው፤ እርሱ እንዲህ ይላል’፦ “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ለመፈተን በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዲቅያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ የእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ “ሥራህን አውቃለሁ፥ በራድ ወይም ትኩስ አለመሆንህን። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ‘ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ነገር አያስፈልገኝም፤’ የምትል ስለ ሆንክ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዐይነ ስውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ የምትጐናጸፈውን ነጭ ልብስ፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳልበትን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ተነሣሣ፤ ንስሓም ግባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔም ድል እንደ ነሣሁ፥ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።” ከዚያ በኋላም አየሁ፤ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ! እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ “ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ መሆን ያለበትን ነገር አሳይሃለሁ፤” አለ። ወዲያው በመንፈስ ተመሰጥሁ፤ እነሆም ዙፋን በሰማይ ተዘጋጀ፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበረ፤ ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቁ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጣል፤ በዙፋኑም ፊት ሰባት ችቦዎች ይቀጣጠሉ ነበር፤ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዐይኖች የሞሉአቸው አራት ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ። ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፤ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፤ ሦስተኛውም እንስሳ የሰውን ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛውም እንስሳ የሚበር ንስር ይመስል ነበር። አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች ሞልተውባቸዋል፤ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ” ከማለት ቀንና ሌሊት አያርፉም ነበር። እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ገናናነት ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ይሰግዳሉ፤ አክሊላቸውንም በዙፋኑ ፊት አኑረው እንዲህ ይላሉ፥ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ! አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ገናናነት ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል፤” በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። ብርቱም መልአክ “መጽሐፉን መዘርጋትና ማኅተሞቹንም መፍታት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ “አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፥ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል፤” አለኝ። በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደው። መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፤ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሳሕን ያዙ። “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤” እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ። አየሁም፤ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፤ በታላቅም ድምፅ “የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ገናናነትም ክብርም ውዳሴም ሊቀበል ይገባዋል” አሉ። በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ “ውዳሴ ገናናነት ክብርም ኃይልም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን፤” ሲሉ ሰማሁ። አራቱም ሕያዋን ፍጡራን “አሜን” አሉ፤ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ። በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ከአራቱም ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ነጭ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ ድል እየነሣ፥ ድልም ለመንሣት ወጣ። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። ሌላም ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ፥ ሰላምን ከምድር ያስወግድ ዘንድ በእርሱ ላይ ለተቀመጠው ሥልጣን ተሰጠው፤ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ጥቁር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን መካከል እንደ ድምፅ ሰማሁ፦ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንን ግን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም የገረጣ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክርነት የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ! እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንደ እነርሱም መገደል የሚጠብቃቸውን የሌሎች አገልጋዮች የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪሞላ ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተነገራቸው። ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጉር ጥቁር ሆነች፤ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነች፤ በለስም በብርቱ ነፋስ ስትናውጥ ያልበሰለ ፍሬ እንደሚረግፍ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ፤ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፤ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም፥ ሀብታሞችም፥ ኃይለኞችም፥ አገልጋዮችም፥ ጌቶችም ሁሉ በዋሻዎችና በተራራዎች ዐለቶች ውስጥ ተሰወሩ፤ ተራራዎችንና ዐለቶችንም “በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ጸንቶ ሊቆም ይችላል?” አሉአቸው። ከዚህም በኋላ በአራቱ የምድር ማዕዘን የቆሙ አራት መላእክት አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ላይም ቢሆን ወይም በባሕር ላይ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ “የአምላካችንን ባርያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ፤” አላቸው። የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ “አሜን ውዳሴ፥ ክብር፥ ጥበብ፥ ምስጋና ገናናነት፥ ክብር ኃይልና ብርታት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ?” አለኝ። እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። እንዲህም አለኝም፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሶቻቸውንም አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቆማሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ውስጥ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእነርሱ ላይ ይዘረጋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ሆነ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይመታቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ለግማሽ ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ዐረገ። መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። የፊተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፤ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ፤ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶው ወደመ። ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞችና በውሃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፤ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንና የሌሊት ሲሶው እንዳያበራ ተከለከለ። አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት መለከትን በሚነፋበት ጊዜ ከሚቀረው ድምፅ የተነሣ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” አምስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፤ የጥልቁም ጉድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። የጥልቁንም ጉድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጉድጓዱ ወጣ፤ ፀሐይና አየርም በጉድጓዱ ጢስ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፤ የምድርም ጊንጦች እንዳላቸው ሥልጣን ዓይነት ሥልጣን ተሰጣቸው። የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተነገራቸው። ለአምስትም ወር እንዲያሰቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሉአቸው አልተፈቀደላቸውም፤ እነርሱም የሚያደርሱት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚያደርሰው ስቃይ ዓይነት ነው። በዚያም ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ አያገኙትምም፤ ሊሞቱም ይመኛሉ፤ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል። አንበጣዎቹም ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶችን ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ የሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበረ፤ የሴቶችን ጠጉር የሚመስል ጠጉር ነበራቸው፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፤ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሠረገላዎች ድምፅ ነበረ። እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፤ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፤ ሰዎችንም ለአምስት ወር ያህል የመጉዳት ሥልጣን አላቸው። ንጉሥም ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጉድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አባዶን በግሪክም አጶልዮን ነው። የፊተኛው “ወዮ” አልፎአል፤ እነሆ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት “ወዮ” ይመጣል። ስድስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲወጣ ሰማሁ፤ እርሱም መለከት ለያዘው ስድስተኛው መልአክ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው፤” አለው። የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። የፈረሰኞችም ጭፍራ ቍጥር ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፥ ጅራታቸው እባብን ይመስላል፤ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ጉዳትን ያደርሳሉ። በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ ለአጋንንትና ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶችም መስገድን አልተዉም። ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሓ አልገቡም። ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፤ የተከፈተችንም ትንሽ መጽሐፍ በእጁ ይዞ ነበር። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፤ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓዶች በየድምፃቸው ተናገሩ። ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም “ሰባቱ ነጐድጓዶች የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው፤ አትጻፈውም፤” የሚል ድምፅ ሰማሁ። በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሣ፤ ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርሷም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ “ወደ ፊት አይዘገይም ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ለመንፋት የተዘጋጀው መልአክ የመለከቱን ድምፁም በሚያሰማባቸው ቀኖች፥ የእግዚአብሔር ምሥጢር ለባርያዎቹ ለነቢያት የምሥራች በሰበከላቸው መሠረት ይፈጸማል፤” አለ። ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደገና ሲናገረኝና “ሂድና በባሕርና በምድር ላይ በቆመው መልአክ በእጅ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ፤” ሲል ሰማሁ። ወደ መልአኩም ሄጄ “ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ፤” አልሁት። እርሱም “ውሰድና ብላት፤ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች፤” አለኝ። ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት፤ በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ። “በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል፤” ተባልሁ። በትር የሚመስል የመለኪያ ሸንበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። ከመቅደሱ ውጭ ያለውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካውም፥ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና፤ እነርሱም ለአርባ ሁለት ወር ያህል የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ለሁለቱም ምስክሮቼ ኃይል እሰጣለሁ።” እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፤ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን የመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ውሃዎችንም ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ምድርን የመምታት ሥልጣን አላቸው። ምስክራነታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፤ ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፤ እርሷም በምሳሌያዊ አነጋገር ሰዶምና ግብጽ የተባለችው፥ ጌታቸውም የተሰቀለባት ከተማ ናት። ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኩል በድናቸውን ይመለከታሉ፤ በድናቸውም ወደ መቃብር እንዲገባ አይፈቅዱም። እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስላሠቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ዕጣ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም ይኖራሉ፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከሦስቱ ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። በሰማይም “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፦ “የዓለም መንግሥት የጌታችንና የመሢሑ ሆነች፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፦ “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ትልቁን ኃይልህን ስለ ወሰድክና ስለ ነገሥህ እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቈጡ፤ ቁጣህም መጣ፤ በሙታንም የምትፈርድበት ዘመን መጣ፤ ለባርያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን፥ ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን የምትሰጥበት ምድርንም የሚያጠፉትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።” በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ የኪዳኑም ታቦት በቤተ በመቅደሱ ታየ፤ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ። ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግሮችዋ በታች ያደረገች፥ ባለ ዐሥራ ሁለት ኮከቦች አክሊልም በራስዋ ላይ የደፋች አንዲት ሴት ነበረች። እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዟት ተጨንቃ ትጮኻለች። ሌላም ምልክት በሰማይ ተከሠተ፤ እነሆ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፤ በጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ከዚያም ዘንዶው ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ሕፃንዋን ለመዋጥ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች። በሰማይም ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ታላቁም ዘንዶ ወደ ታች ተጣለ፤ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል “አሁን የአምላካችን ማዳን፥ ኃይልም፥ መንግሥትም እንዲሁም የክርስቶስ ሥልጣን ሆነ፤ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም በበጉ ደምና በምስክራነታቸው ቃል ድል ነሡት፤ ሞትን እስኪሸሹ ድረስ ነፍሳቸውንም አልወደዱም። ስለዚህ ሰማያትና በውስጣቸው የምታድሩ ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሓ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት። እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ወንዝ የሚያህልን ውሃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ። ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅና ለኢየሱስ ምስክርነት ታማኝ በመሆን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ። ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኀይሉን፥ ዙፋኑንና ትልቅ ሥልጣንን ሰጠው። ከራሶቹም አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቁስል ነበረው፤ ለሞት የሚያደርሰውም ቁስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ በመገረም አውሬውን ተከተለ፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬውም “አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?” እያሉ ሰገዱለት። ታላቅ ነውርንና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፤ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ፥ ስሙንና ማደሪያውን፥ በሰማይ የሚያድሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም የመዋጋት፥ ድልም የማድረግ ፈቃድ ተሰጠው፤ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ይሰግዱለታል። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ለመማረክ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ መገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። በመጀመሪያው አውሬ ስም፥ በሙሉ ሥልጣን ይሠራ ነበር። ወደ ሞት የሚያደርሰው ቁስል ለተፈወሰለትም ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል። እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰዎች ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን ያደርጋል። በአውሬውም ፊት እንዲያደርግ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቁስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲሠሩ በምድር የሚኖሩትን ያዛቸዋል። የአውሬው ምስል እንዲናገርም ሆነ ለአውሬው ምስል የማይሰግዱትን እንዲያስወግዳቸው ለአውሬው ምስል እስትንፋስ እንዲሰጠው ተፈቀደ። ታናናሾችና ታላላቆች፥ ሀብታሞችና ድሆች፥ ጌታዎችና ባርያዎች ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ ያደርጋል፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሰው ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችልም ያደርጋል። ጥበብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ያስላው፤ የሰው ቍጥር ነውና፤ ቁጥሩም ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት ነው። ከዚያም አየሁ፤ እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከሰማይም እንደ ብዙ ውሃ ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ የመሰለ ድምፅን ሰማሁ፤ የሰማሁትም ድምፅ ደርዳሪዎች በበገናቸው ሲደረድሩ እንደሚሰማው ዓይነት ድምፅ ነበር። በዙፋኑም ፊት፥ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያንን ቅኔ ማንም ሊማረው አልቻለም። እነዚህ ከሴቶች ጋር ያልረከሱ ናቸው፤ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበትም የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም። በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ለማብሰር ዘላለማዊውን ወንጌል የያዘ ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውሃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት፤” አለ። ሌላም ሁለተኛ መልአክ “አሕዛብን ሁሉ ከዝሙትዋ የቁጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” እያለ ተከተለው። ሌላም ሦስተኛ መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥ እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር የቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፤ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሰቃያል። የሥቃያቸውም ጢስ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ይወጣል፤ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ እንዲሁም የስሙን ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።” የእግዚአብሔርን ትእዛዛትና የኢየሱስን እምነት የሚጠብቁት ቅዱሳን እዚህ ላይ ነው ጽናታቸው የሚፈለገው። ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ። “ይህንን ጻፍ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።” መንፈስም “አዎን! ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸው ይከተላቸዋልና፤” ይላል። ከዚያም አየሁ፤ እነሆም ነጭ ደመና በደመናውም ላይ የሰው ልጅን የሚመስል ተቀምጦአል፤ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው “የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ የምድሪቱ መከር ደርሶአልና፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ ምድርም ታጨደች። ሌላም መልአክ በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን “ዘለላዎቹ በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተጣራ። መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር የቁጣ ወይን መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፤ እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስና እስከ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ድረስ የሚርቅ ደም ከመጥመቂያው ወጣ። ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ። በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር የሚመስለውን አየሁ፤ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ። “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ! የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፤” እያሉ የእግዚአብሔርን ባርያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ። ከዚህም በኋላ አየሁ፤ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፤ ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ንጹሕ የጌጥ ልብስ ለበሱ፤ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ። ከአራቱም ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚኖረው እግዚአሔር ቁጣ የተሞሉትን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው። ቤተ መቅደሱ ከእግዚአብሔር ክብርና ከኀይሉ የተነሣ በጢስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ መቅደሱ መግባት አልቻለም። ለሰባቱም መላእክት “ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ፤” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ። የመጀመሪያውም መልአክ ሄዶ ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው። ሁለተኛውም መልአክ ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ ባሕሩም የሞተ ሰው ደም መሰለ፤ በባሕርም ውስጥ ሕይወት ያለው ነፍስ ሁሉ ሞተ። ሦስተኛውም መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። የውሃውም መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ! ቅዱስ ሆይ! እንዲህ ስለ ፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፤ የሚገባቸው ነውና፤” ከመሠዊያውም “አዎን፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት እንድታቃጥል ሥልጣን ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሓ አልገቡም። አምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፤ ከስቃይም የተነሣ ሰዎች መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፤ ከስቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ። ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ፥ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮችን የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ ምልክት እያደረጉ፥ በታላቁና ሁሉን በሚገዛው በእግዚአብሔር ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። “እነሆ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ ኀፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው። ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ። መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፤ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ነውጡ እጅግ ትልቅ ነበር። ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበት ጽዋ እንዲሰጣትም ታላቂቱ ባቢሎን በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች። ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም። በሚዛንም አንድ ታላንት የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሣ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነበርና። ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና፤ በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ሴት ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ በዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ፤” ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ባሉት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙትዋ ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር በግምባርዋም “ታላቂቱ ባቢሎን፥ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰት እናት” የሚል ምስጢራዊ የሆነ ስም ተጻፈ። ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ በእጅጉ ተደነቅሁ። መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “ለምንድን ነው የምትደነቀው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና ዐስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ሊወጣ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች አውሬው አስቀድሞ እንደ ነበረ አሁን ደግሞ እንደሌለ፥ ነገር ግን ተመልሶ እንደሚመጣ ሲያዩ ይደነቃሉ። ጥበብ ያለው አእምሮ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ ሰባትም ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፤ ከሰባቱም አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ያየሃቸውም ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ እቅድ አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉት የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ናቸው።” እንዲህም አለኝ “አመንዝራይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች፥ አሕዛብም፥ ቋንቋዎችም ናቸው። ያየሃቸውም ዐሥር ቀንዶችና አውሬው አመንዝራይቱን ይጠላሉ፤ ይበዘብዟታል፥ ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል። የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን በአንድ ልብ እንዲያደርጉና መንግሥታቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ እግዚአብሔር በልባቸው አሳድሮአልና። ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።” ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴስነዋልና፤ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋልና፤” ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ “ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርሷ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታወሰ። እርሷ በሰጠችው መጠን መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን በአከበረችበትና በተቀማጠለችበት ልክ ሥቃይንና ኀዘንን ስጡአት። በልብዋ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አልሆንም፤ ኀዘንም ከቶ አላይም፤’ ስላለች፥ ስለዚህም ሞትና ኀዘን፥ ራብም የሆኑት መቅሰፍቶችዋ በአንድ ቀን ይመጣሉ፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ከእርሷም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ እየጮሁ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ውስጥ ፍርድሽ ይፈጸማልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነቱም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ መልካም መዐዛ ያለውም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከነሐስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ የወይራ ዘይትም፥ ምርጥ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሠረገላም፥ ባርያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችለት ፍሬ ከአንቺ ተለይቶ ሄዶአል፤ የድሎትና የጌጥ ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይገኙም።” እነዚህን የነገዱ በእርሷም ሀብታም የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይላሉ። ይህን የሚያህል ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስል ሌላ ከተማ ነበረችን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከሀብቷ የተነሣ ሀብታም ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ። “ሰማይ ሆይ! ቅዱሳን፥ ሐዋርያትና ነቢያት ሆይ! ስለተፈረደባት በእርሷ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። ከእንግዲህ ወዲህ በገና የሚመቱና የሚዘምሩ ሰዎች ድምፅ፥ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ሰዎች ድምፅ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የማንኛውም ዕደ ጥበብ ብልሃተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።” በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም፥ በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት። ከዚህ በኋላ በሰማይ የብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅን የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፦ “ሃሌ ሉያ! ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው፤” ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና፤ በዝሙትዋ ምድርን ያበላሸችውን ታላቂቱን አመንዝራ ፈርዶባት፥ የባርያዎቹንም ደም ከእጅዋ ተበቀሎአልና። ደግመውም እንዲህ አሉ፦ “ሃሌ ሉያ! ጢስዋም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይወጣል፤” አሉ። ሃያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጡራን በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር “አሜን! ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱለት። ድምፅም ከዙፋኑ እንዲህ ሲል ወጣ፦ “ባርያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ! አምላካችንን አመስግኑ፤” የብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ የብዙ ውሃዎችም ድምፅ፥ የብርቱም ነጐድጓድም ድምፅ የሚመስል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና። የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፤ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትለብስ ተሰጥቶአታል።” ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነውና። መልአኩም “ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው፤” ብለህ ጻፍ፤ አለኝ። ደግሞም “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው፤” አለኝ። ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክርነት ከሚጠብቁት ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባርያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክርነት የትንቢት መንፈስ ነውና፤” አለኝ። ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም ነጭ ፈረስ፤ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፤ በጽድቅም ይፈርዳል፤ ይዋጋልም። ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱም በቀር ማንም የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሏል። በሰማይም ያሉት ሠራዊት ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በነጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል። በልብሱና በጭኑም ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” የሚል ስም ተጽፎአል። አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ “ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር እራት ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባርያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ ትበሉ ዘንድ” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በፈረሱም የተቀመጠውንና ሠራዊቱን ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ከነሠራዊታቸው ተሰብስበው አየሁ። አውሬውም ተያዘ፤ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛውም ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው አፍ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ። የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን፥ የቀደሞውን እባብ፥ ዘንዶውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፤ አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል። ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት የመፍረድ ሥልጣን ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርነትና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ እንዲሁም ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ እንደገና ሕያው ሆነው ከክርስቶስም ጋር ለሺህ ዓመት ነገሡ። የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ እንደገና በሕይወት አልኖሩም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። የመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆነ ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ለሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን ለማሳትና ለጦርነት ለማስከተት ይወጣል፤ ቁጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ። ታላቅና ነጭ ዙፋን፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንን፥ እንዲሁም ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላም መጽሐፍ ተከፈተ፤ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት በተጻፈው መሠረት፥ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድን ተቀበሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን አስረከበ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን አስረከቡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ፍርድን ተቀበለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ሁሉ በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ። አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ የፊተኛው ሰማይና የፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፤ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ ከዙፋኑ ወጥቶ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸውም ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዐይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” በዙፋንም የተቀመጠው “እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ፤” አለ። እኔንም “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ፤” አለኝ። እንዲህም አለኝ፦ “ተፈጽሞአል፤ አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ በነጻ እኔ እሰጣለሁ። ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፤ አምላክም እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። ነገር ግን የሚፈሩ፥ የማያምኑ፥ የሚረክሱ፥ ነፍሰ የሚያጠፉ፥ የሚሴሰኑ፥ አስማትን የሚያደርጉ፥ ጣዖትንም የሚያመልኩና የሚዋሹ ሁሉ ዕጣ ክፍላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ውስጥ ነው፤ ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።” ሰባቱ የመጨረሻዎቹ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ወደዚህ ና፤ የበጉን ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ፤” ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፤ ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ነበረባት፥ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ፥ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፤ ዐሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት፤ በደጆቹም ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመው ነበር፤ የዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፤ በእነርሱም ውስጥ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር። የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፤ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት፤ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው። ቅጥርዋንም ለካ፤ በመልአኩ በሚለካበት በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር፤ ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፤ ከተማይቱም የጠራ ብርጭቆ የሚመስል ንጹሕ ወርቅ ነበረች። የከተማይቱም ቅጥር መሠረቶች በከበረ ድንጋይ ሁሉ ያጌጦ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፥ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፥ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። ዐሥራ ሁለቱም ደጆች ዐሥራ ሁለት ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱም ደጅ ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም መንገድ እንደ መስታወት ብርሃን ከሚያስተላልፍ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበረ። ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ስለ ሆኑ በእርሷ ዘንድ መቅደስ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት፥ መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለ ሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፤ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርሷ ያመጣሉ። ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ሁሉ ወደ እርሷ ከቶ አይገባም። ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ። በከተማው አደባባይዋም መካከል፥ በወንዙም ወዲያና ወዲህ፥ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝቦች መፈወሻ ነበሩ። ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርሷ ውስጥ ይሆናል፤ ባርያዎቹም ያመልኩታል፤ ፊቱንም ያያሉ፤ ስሙም በግምባሮቻቸው ይኖራል። ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፤ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባርያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።” እነሆም “በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት ለመስገድ ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር፥ ከወንድሞችህም ነቢያት ጋር፥ የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤” አለኝ። እንዲሀም አለኝ፦ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዐመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፤ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ፤” አለ። “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው፥ በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች፥ ሴሰኛዎችም፥ ነፍሰ ገዳዮችም፥ ጣዖት አምላኪዎችም፥ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ ይቀራሉ። “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈሱና ሙሽራይቱም “ና!” ይላሉ። የሚሰማም “ና!” ይበል። የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር፥ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ድርሻውን ያጎድልበታል። ይህን የሚመሰክር “አዎን በቶሎ እመጣለሁ፤” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።